ሶማሊያ ከእርስበርስ ውጊያ ወድ ሽብር


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


(DW) — ለሀያሉ አለም በርግጥ ኢራቅ አይደለችም። አፍቃኒስታን፥ ፓኪስታን ልትሆን አትችልምም።ሁሉም ግን ያያታል።ግን አያስተዉላትም።ሁሉም ይሻታል ሊያድናት ግን ይፈራል።ልትድንም አትሻም። ሶማሊያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 1991 እንዳደረገዉ ሁሉ የአፍሪቃ ሕብረትም ጦር ያስ-ዘምታል።ሶማሊያም ከጎሳ ግጭት ዉጊያ አልፋ በሽብር ፍጅት ማዕበል ትላጋለች።ፕሬዝዳት ጆርጅ ሔርበርት ዎከር ቡሽ በ1992 የዛቱ፣ የፎከሩትን ልጃቸዉ ፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ እንደ ዘመኑ ፈሊጥ በዘመናቸዉ ደገሙት።ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ቡሽ ትልቁ የሞከሩትን-በቡሽ ትንሹ ዘመን ደገሙት።ፕሬዝዳት ዩዌሪ ሙሳቬኒ እና ፕሬዝዳት ፔሩ ንኩሩንዚዛ እንደ ቡሾች፣ እንደ መለስ፣ ይፎክራሉ፣ ሸኽ ሸሪፍ እንደ አብዱላሒ ይዝታሉ።አሸባብ ያሸብራል።ሽብር እልቂቱ መነሻ፣ ሒደቱ ማጣቀሻ፣ የአለም አቋም መድረሻችን ነዉ።ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

አርብ ነዉ።የአል-ሸባብ አጥፍቶ ጠፊዎች ሙና ሆቴል ዉስጥ ሰላሳ አንድ ሰዎችን አጥፍተዉ ከጠፉ አራት ቀን ቢያልፈዉም-የሆቴሉ ወለል፣ ፍራሽ፣ ወንበር ጠረጴዛ በደም እንደተጨማለቀ ነዉ።የሆቴሉ ሥራ አስኪያጅ ቁጣ፣ ንዴትም አልበረደም።የሚጠይቃቸዉ ጋዜጠኛ መልስ እንደ ሌለዉ ያዉቁታል። ግን ጠየቁ።አብዱላሒ ወርሰሜ። «በረመዳን ወቅት እንዴት ሰዉ ይገድላሉ?» አረንጓዴና ቢጫ ቀለም የተቀባዉ የሆቴሉ ግርግዳ በደም ፍንጥቅጣቂ ተዥጎርጉሯል።ወይም በጥይትና በቦምብ ፍንጥር ጣሪ ተቦዳድሷል።

«እንዲሕ አይነት ነገር በጭራሽ ተደርጎ አያዉቅም።» ቀጠሉ።አብዱላሒ ወርሰሜ።ባለ ሰወስት ደርቡን ሆቴል ማስተዳደር ከጀመሩ ብዙ አመታት አስቆጥረዋል።ኢብራሒም ዑመርም መቅዲሾ ተወልዶ-መቅዲሾ ነዉ ያደገዉ።አሁን ቤተሰቡ የለም።እሱ ግን እዚያዉ ነዉ።ከተማይቱና ኑሮ ግን ተለወልጦቶበታል።

«ቤተሰቦቼ በሙሉ ሸሽተዋል።እኔ ግን ቤታችንን ለመጠበቅ እዚሁ ለመቆየት ወስኛለሁ።ከባዱ ዉጊያ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሁኔታዉ ሁሉ አስፈሪ ነዉ።ምንም ነገር መግዛት መግባት መዉጣት አይቻልም።እዚሕ (መቃዲሾ) የወትሮ ኑሮ የለም።»

የዚያድ ባሬን አንባገነናዊ መንግሥት ከሥልጣን ለማስወገድ ባንድ አብረዉ ሲዋጉ የነበሩት ሐይላት ባሬን በ1991 ባስወገዱ ማግሥት የተጣሉበትን ምክንያት «ሥልጣን» ከሚለዉ ዉጪያዊ ሰበብ ባለፍ አብዱላሒ ወርሰሜ፥ ወጣቱ ኢብራሒም ዑመርም ዝር ዝሩን ብዙ አያዉቁቱም።ዓሊ መሕዲ መሐመድ፥ ጄኔራል ፋራሕ አይዲድ፥ አብዲረሕማን አሕመድ ዓሊ ቱር እና ኮሎኔል ጆስ ይመሯቸዉ የነበሩት ሐይላት የገጠሙት ዉጊያ ያችን ዉብ የወደብ ከተማ በሚያደቅበት ዘመን የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ-መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ለሸምጋይነት የመረጠዉ ኢትዮጵን ነበር።1992።
የኢትዮጵያ መሪዎች ሽምግልና የጋራ ጉባኤ ከሚያስጠራበት ደረጃ ሲደርስ ለጉባኤዉ ከተጋበዙት የተወሰኑት ከአዲስ አበባዉ ጉባኤ በፊት ካይሮ ወይም ሸርም አል-ሼክ ላይ ሌላ ጉባኤ መሰየም አለበት አሉ።ግብፅ ጉባኤዉን ለማስተናገድ ፍቃደኛ ነበረች።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ቡትሩስ ቡትሩስ ጋሊም ለሐገራቸዉ አደሉ።የኢትዮጵያ ግብፆች የጥቅም ቅራኔ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፥ ይሕ ቢቀር የአፍሪቃዉያንና የአረቦች መልክና ባሕሪ ተላበሰ።

አረቦች እንደ አረብ አንድ የመሆናቸዉን ያክል እንደ ሐገር ብዙ ናቸዉ።እንደ ብዙ ነታቸዉ ሁሉ የበላይነትን ለመያዝ ግብፅ ከሊቢያ፥ ሊቢያ ሳዑዲ አረቢያ ሶማሊያ ላይ ይሻማሉ።ሶማሊያ በተለይም መቃዲሾ በአረብ እስራኤሎች ጠብ የሚዘወረዉን የአረብ-ምዕራቦች ወዳጅ-ጠላትነትን ፍትጊያ ማስተናገድም ግድ ነበረባት።አስተናገደች።1992።የሶማሊያ የጦር አበጋዞችን ለመሸምገል ባንድ ሰሞን እሁለት ሐገር የተጠራዉ ጉባኤ ሒደት-ዉጤቱ ሳይለይ እሕል ለማከፋፈል የዘመተዉ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር የጄኔራል መሐመድ ፋራሕ ዓይዲድን ሐይል ለማጥፋት ዉጊያ የገጠመበት ምክንያት ሌላ ትርጉም ከተሰጠዉ ከማማሐኛ ሊዘል አይችልም።

ሐያሉ ዓለም እንደ 1990 ዎቹ ሁሉ ለሶማሊያ ሕዝብ ሠላም-ደሕንነቱን ለማስከበር፣እንደ ድሕረ 2000ዉ ፈሊጥ ሁሉ አሸባሪዎችን ለማጥፋት የመቆም መቁረጡን ቃል ተስፋ ያዥጎደጉዳል።ጦር ያዘመተዉ ግን የሸቀጥ መርከቦቹን ደሕንነት እንጂ የሶማሊያ ሕዝብን ሠላም ለማስከበር አይደለም።መርከብ ዘራፊዎችን እንጂ አሸባሪዎችን የሚያጠፋ አይደለም።የሞቃዲሾዋ ስደተኛ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ብጤዎቻቸዉም ማን-ምን አረገልኝ ይበሉ።

«ይሕ ዉጊያ በጣም እያሰቃየን ነዉ።ሥንት አመቱ ያሁ እንዲሁ ነዉ።ይሻሻላል ብለን ጠበቅን፥ ጠበቅን፣ ምንም የደረሰልን የለም።»

የዩናይትድ ስቴትስ ጦር የጄኔራል አይዲድን ሐይል ለማጥፋት ጥቃት መክፉቱ፥ ከፖለቲካዊነት አልፎ ወደ ጎሳ የወረደዉን የሶማሊያን ጦርነት ለማስወገድ አይፈይድም በማለት አጥብቀዉ ይቃወሙ ከነበሩ አፍሪቃዉያን መካከል የኢትዮያ መሪዎች ግንባር ቀደሞቹ ነበሩ።2006 በርግጥ 1992 አይደለም።ቡሽ-ዳግማዊም ልጅ እንጂ ቡሽ ቀዳማዊ አልነበሩም።ለኢትዮጵያ ግን የድርዉም የቅርቡም-ያሁንም መሪዎች ያዉ ናቸዉ።

በ1992 የተቃወሙትን፥ ያለዉጤት ማብቁትን ያዩትን የአሜሪካኖችን እርምጃ፥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ዘመቻ በአስራ-አራተኛ አመቱ መደግማቸዉ ነዉ እንቆቅልሹ።ክሊንተን በ1993 እንዳደረጉት ሁሉ ጠቅላይ ሚንስትር መለስም ከመሞት-መግደሉ በስተቀር ለሶማሊያ ሠላም ምንም ያልተከረ ጦራቸዉን በ2009 አስወጡ።ቡሽ ቀዳማዊ በ1992: ያደረጉትን፥ መለስ በ2006 የደገሙትን፥ ሙሳቬኒ እና ንኩሩንዚዛ 2009 አሠለሱት።

ሙሳቬኒ-ዛቻ፥ የጦራቸዉ ዉጊያ ዉጤቱ ግን ላሁኑ አለየም።ግን ከቀሳሚዎቻቸዉ ተምረዉ ይሆን።ኢትዮጵያዊዉ የምሥራቅ አፍሪቃ የፖለቲካ ተንታኝ ዩሱፍ ያሲን ይጠራጠራሉ።

ለቡሽ ቀዳማዊ ዓሊ መሕዲ መሐመድ-ወዳጅ መሐመድ ፋራሕ አይዲድ-መጥፋት ያለባቸዉ ጠላት ነበሩ።ለቡሽ ቀዳማዊ ልጅ ለቡሽ ዳግማዊ የአይዲድ ቀዳማዊ ልጅ ሁሴይን አይዲድ እና ብጤዎቻቸዉ የጦር አበጋዞች ወዳጅ-ሼክ ሸሪፍ ሼኽ አሕመድ ጠላት ነበሩ።ለጠቅላይ ሚንስትር መለስ ፕሬዝዳት እዱላሒ ዩሱፍ አሕመድ ወዳጅ-ሼኽ ሸሪፍ፡እና የሽሪዓ ፍርድ ቤቶች ጠላት ነበሩ።ሼኽ ሽሪፍ ሼኽ አሕመድ አሁን ለመለስ፥ ለኦባማ ለሙሳቬኒ፥ለንኩሩንዚዛ ለተቀሩትም ወዳጅ ናቸዉ።ሙክታር ዓሊ ዙቤርና ድርጅታቸዉ አል-ሸባብ ጠላት። አሸባሪ።

የአል-ሽባብ አጥፍቶ ጠፊዎች ባለፈዉ ሳምንት የሙናን ሆቴል አሸብረዉ ስድስት የምክር ቤት እንደራሴዎችን ጨምሮ ሰላሳ-አንድ ሰዎችን በገደሉ ማግሥት ሼክ ሸሪፍ አል-ሸባብን ለማጥፋት ጦራቸዉ አዲስ ሥልት ቀይሷል አሉ።

«የመንግሥታችንን ፀጥታ አስከባሪዎች በተመለከተ ጠላታችን አዲስ ሥልት ገቢር ማድረጉን በተጨባጭ አይተናል።ለዚሕም ነዉ አዲስ ሥልት ለመከተል የወሰንነዉ።ፀጥታን ለማስከበር በስራ-ላይ መዋል የጀመረ አዲስ ሥልት ቀይሰናል።»

የሼክ-ሸሪፍ መንግሥት ጠላቶቹን ሊያጠፋ ቀርቶ ሕልዉናዉ ስድስት ሺሕ በሚጠጋዉ በዩጋንዳና በብሩንዲ ጦር ሐይል ብርታት ላይ የተመሠረተ ነዉ።የሕወት ገመዱ የሰለለችበት መንግሥት አዲስ እቅድ ነድፎ ጠላቶቹን ድል ሊያደርግ ቀርቶ በቅጡ መተንፈስ መቻሉም አጠራጣሪ ነዉ።የአል-ሸባብ ደፈጣ ተዋጊዎች ባለፈዉ ቅዳሜ በሰነዘሩት ጥቃት የሸሪፊን ቤተ-መንግሥት ከአዉሮፕላን ጣቢያዉ ጋር የሚያገናኘዉን መካቱል ሙከረማሕ የተሰኘዉን አዉሮ ጎዳና ላጭር ጊዜም ቢሆን ተቆጣጥረዉት ነበር።

በቅዳሜዉ ዉጊያ በትንሹ ሃያ ሰዎች ተገድለዋል።ከሃያ-አምስት በላይ ቆስለዋል።አል-ሸባብ አብዛኛዉን መቃዲሾን ተቆጣጥሮ የሽግግር መንግሥቱን የመጨረሻ መቀመጫ ለመቆጣጠር ተከታታይ ጥቃት የከፈተበት እና በብረት ለበስ ተሽከርካሪ ከሚታገዘዉ የዉጪ ሐይል ጋር መግጠም የመቻሉ ምክንያት አቶ ዩሱፍ እንደሚሉት ሁለት ነዉ። የራሱ የአል-ሸባብ ጥንካሬና እና በጣሙን ደግሞ የሽግግር መንግሥቱ ድክመት።

በ1990ዎቹ የኢትዮጵያና የግብፅ ወይም የአረቦችና የአፍሪቃ፥ የአረቦችና የምዕራቦች ወይም የአፍሪቃና የምዕራቦች ይመስል የነበረዉ ሽኩቻ-ዛሬም ኤርትራን በኢትዮጵያ አንጻር ከቆመዉ ሐይል ለጥፎ፥ የመን እና ጂቡቲን ግራ-ቀኝ እያላጋ ሶማሊያን ያነፍራን።ለሐያሉ አለም በርግጥ ኢራቅ አይደለችም። አፍቃኒስታን፥ ፓኪስታን ልትሆን አትችልምም።ሁሉም ግን ያያታል።ግን አያስተዉላትም።ሁሉም ይሻታል ሊያድናት ግን ይፈራል።ልትድንም አትሻም።ሶማሊያ።

ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።