Author Archive

የመለስ አልጋ ወራሾች (ከተስፋዬ ገብረአብ)

Thursday, July 19th, 2012

“መለስ ታመመ” የሚለውን ወሬ ተከትሎ፣ ኮማ ውስጥ መግባቱና መሞቱ እየተነገረ ሰንብቶአል። የወያኔ መንግስት ግን ወሬውን አፍኖ ለመቆየት ተጨናነቀ። መለስ ጀርመን ሃገር ላይ ቀዶ ጥገና ህክምና ማድረጉ በአንድ ወገን ሲገለፅ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ቤልጅየም 10 ቀናት አልጋ ይዞ መሰንበቱ ተሰምቶአል።

“አዲሳባ ገባ” የሚለው ተሰምቶ ሳያበቃ፣ “ብራስልስ ላይ መሆኑ ተረጋገጠ” ተባለ። ወሬዎቹ መልከ ብዙና ውል አልባ ነበሩ። ዞረም ቀረ መለስ ታሞአል። ከመለስ መታመም ጋር በተያያዘ እንዲሞትም ሆነ እንዲፈወስ የሚፀልዩ ተደምጠዋል። ከህይወት ልምድ እንደተረዳሁት ከሆነ፣ አምላክ የፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ እጁን ስለማያስገባ የሁለቱንም ወገን ፀሎት የሚሰማ አይመስለኝም። መፍትሄው አበበ ገላው እንዳደረገው፣ እያንዳንዱ ለአላማው መሳካት አንድ ነገር ማድረግ ብቻ ነው።
እርግጥ ነው፣ መለስ በደም ካንሰር እና በአንጎል እጢ ህመም በመሰቃየት ላይ መሆኑ ተረጋግጦአል። በግልፅ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ ከዚህ በሁዋላ እንደቀድሞው ወደ ቢሮው ገብቶ ስራውን መስራት ይቸገር ይሆናል። እንደሚሰማው ከማንበብና ከመፃፍ እንዲገለል በሃኪም የተመከረው ከስድስት ወራት በፊት ነበር። ዞሮ ዞሮ መለስ በህይወት አለ። እንዲህ በአጭር ጊዜ ለህይወቱ የሚያሰጋው አለመሆኑም ይሰማል። እንደተነገረው ቀዶ ህክምናም አላደረገም። የአንጎል እጢውን በጨረር ሊያክሙት ሲሞክሩ ነበር የከረሙት። ቀዶ ህክምና ለመሞከር ጊዜው ገና መሆኑን ዶክተሮቹ ለመለስ ነግረውታል። ይህን መረጃ እንደ ጥሬ እውነታ በመያዝ ግን ስለ አጠቃላዩ የአካባቢያችን ፖለቲካ አንዳንድ ነጥቦችን
ማንሳት ይቻል ይሆናል።

የመለስን መታመም ተከትሎ በኢህአዴግ የአመራር አባላትና በጄኔራል መኮንኖች መካከል የተፈጠረው መቧደን በጣም አሳሳቢና ለውይይት የሚጋብዝ ሆኖ ሰንብቶአል። አመራር አባላቱ የመለስ እድሜ አጭር መሆኑን በመገመታቸው ለህልውናቸው ሲሉ አይኖቻቸውን ወደ ምኒልክ ቤተመንግስት ልከው ከረሙ። አሁንም በሰራዊትና በሲቪል ባለስልጣናት መካከል የስልጣን ሽኩቻ ስለመኖሩ እየተፃፈ ነው። ኢህአዴግ ቀድሞውንም አንድነት አልነበረውምና ከመለስ መታመም ጋር ድርጅቱ በየአቅጣጫው ሲፈነዳዳ ታይቶአል። የመለስ አልጋ ወራሽ ሊሆኑ ይችላሉ የሚባሉ ስሞችም በየሚዲያው እየተገለፀ ቆይቷል። ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ አዜብ መስፍን እና ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ ቀዳሚ እጩዎች ሆነዋል።

የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ የፃፈውን አይቻለሁ። የግምት ወይም የመረጃ ስህተት አለባቸው። ለአብነት በረከት ስምኦንና አዜብ መስፍን በአንድ ቡድን ውስጥ ሊሰሩ አይችሉም። በሁለቱ መካከል ባለፉት 30 ቀናት ውስጥ ከፍተኛ ጦርነት ተነስቶ ሰንብቶአል። አዜብ በሚዲያ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ ገብታ በረከትን ለማዘዝ ሞክራ ነበር። በረከት በጣም በመበሳጨቱ፣ “አንቺን በዚህ ጉዳይ ውስጥ ምን ያገባሻል? ሚስት ብቻ መሆንሽን ለምን ትረሽዋለሽ?” ይላታል።

በበረከት ልቅ ንግግር እብደት ውስጥ የገባችው አዜብ በሃይለማርያም ደሳለኝ በኩል በረከት ላይ ተፅእኖ ለማድረግ ሞከረች። እዚህ ላይ ግን በረከት ችግር ውስጥ ገባ። ወደደም ጠላ ሃይለማርያም የበላይ አለቃው ነው። መንበርከክ ግን አልቻለም። የብአዴን ምንጮች እንደሚገልፁት፣ በረከት ስምኦን አኩርፎ ወደ እናት ክልሉ ዋና ከተማ ወደ ባህርዳር ኮበለለ። ስራውን ትቶ ባህርዳር አንድ ሳምንት እንደቆየ በአዲሱ ለገሰ ልመና እና ማግባባት ወደ አዲስአበባ ሊመለስ ችሎአል። የመለስን መታመም ተከትሎ በረከት ወላጅ አልባ ልጅ መስሎ ታየ። መለስ ከስራው ገለል ከማለቱ የተፈጠረ ቁጥር አንድ ሽኩቻ ነበር። አዜብ ሃይለማርያም ደሳለኝን መጋለብ መጀመሯ እውነት ነው። እዚህ ላይ ሃይለማርያም ወደ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሳበበትን ዋና አላማም ለመረዳት ያሰችላል። ነባር ሚኒስትሮችና ትግሬ ያልሆኑ ታጋዮችን በዚህ መንገድ ከቤተመንግስቱ ለማራቅ ሃይለማርያም መልካም መንገድ ሆኖ ሊያገለግል ይቻለዋል።

የህወሃት ነባር የአመራር አባላት በዚህ ወቅት ይከፋፈላሉ ማለት ግን ለእውነት የቀረበ አይደለም። ከተከፋፈሉ ቤተመንግስት ውስጥ ማን እንደሚገባ ያውቃሉ። የምኒልክን ቤተመንግስት አንድ ጊዜ ከለቀቁ፣ ዳግም እንደማይመለሱባትም ይረዳሉ። ስለዚህ ህወሃት ለአራት ወይም ለሶስት ተከፋፍሎ ትርምስ ውስጥ እንደሚገባ መጠበቅ የዋህነት ነው። ከተመስገን ትንታኔ የምስማማበት የብአዴን ተፎካካሪነት ጉዳይ ነው። በዚህ ወቅት አዲሱ ለገሰ እንደሚገመተው በጡረታ የተገለለ አይደለም። እንደ ጆርጅ ኦርዌል ውሾች ሸሽጎ ያኖራቸው ከፍተኛ መኮንኖች ካሉት ብልህነቱን ማድነቅ ይቻላል። ብአዴን ተሸፋፍኖና ተጠጋግኖ ያደፈጠ ድርጅት ነው። አብዛኞቹ የብአዴን ካድሬዎች ቁጭት ይሰማቸዋል። ህወሃትን የሚገለብጡበት አጋጣሚ ከተገኘ፣ ከመጠቀም አይመለሱም ተብሎ ይታሰባል። በርግጥ ከህወሃት የተሻለ ስርአት መገንባት ይችላሉ ተብሎ ተስፋ አይደረግም። ህላዌና ካሳ ሸሪፎ ከኢህአፓ መንፈስ ጋር አብረው ያሉ እንደመሆናቸው፣ ኢህአፓን
ወደ ጓዳቸው ለመጋበዝ ይሞክሩ ይሆናል። መለስ ዜናዊ ዘግይቶም ሆነ ፈጥኖ በሞት የሚሰናበት ከሆነ የብአዴን አመራር አባላት ከባድ ፈተና ውስጥ ይገባሉ። ምክንያቱም የመለስ ዜናዊ መንግስታዊ ወንበር በሌላ የህወሃት ሰው የሚወረስ ከሆነ፣ ለብአዴን ታሪካዊ ውርደት ይሆንበታል። ብአዴን ለ23 አመታት የኢህአዴግ ምክትልነትን ወንበር ይዞ ቆይቶአል። ከ23 አመታት በሁዋላ ሊቀመንበሩ “በሞት” ቦታውን ሲለቅ፣ ብአዴን ሊቀመንበርነቱን መተካት ካልቻለ ለዘመናት የሚወነጀሉበትን አሽከርነት በማፅደቅ እነርሱም ወደ መቃብራቸው ያመራሉ። በግብፅ የቀበሌ አስተዳደር ውስጥ ኦርቶዶክስ ክርስትያኖች ምንጊዜም ምክትልነት ቋሚ ቦታቸው እንደሆነው ሁሉ፣ ብአዴንም ምክትልነትን አምኖ ሳይቀበል
አልቀረም። ከዚህ ውርደት ለመዳን ብአዴን ሁለት አማራጮች አሉት። የመጀመሪያው መለስ እንዳይሞት መፀለይ ሲሆን፣ ሁለተኛው የመለስን ወንበር ለመያዝ ሽምጥ መጋለብ ናቸው።

መለስ የሰራዊቱን ትግርኛ ተናጋሪ አመራር ለሁለት ከፍሎ ሲያስተዳድረው ነበር። በቀጥታ ሳሞራ የኑስ የሰራዊቱ አዛዥ ቢሆንም፣ በጎን ደግሞ ሌላ መዋቅር ዘርግቶ ቆይቶአል። ታደሰ ወረደ እና ወዲ አሸብር የሚባሉት ጄኔራሎች ከሳሞራ እዝ ውጭ ከመለስ ጋር ግንኙነት ነበራቸው። ታደሰ ወረደ መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ ድፍረቱም ብቃቱም ሊኖረው ይችላል። ወዲ አሸብር እብድ ነው። ምን ሊያደርግ እንደሚችል ከወዲሁ መገመት አይቻልም። የመለስን ልጅ ክርስትና ያነሳው ጄኔራል ወዲ መድህን፣ አቅሙ ባይኖረውም የታዘዘውን የመፈፀም ችግር የለበትም። እነዚህ ሶስት ጄኔራሎች አዜብና ቴዎድሮስ ላይ ሊደርስ የሚችል አደጋ ካለ ለመመከት ተወርዋሪ ሃይል ይዘው የሚጠብቁ ሊሆኑ ይችላሉ። በተቀረ
የህወሃት ጥቅምና ስልጣን እስካልተነካ ድረስ ሰራዊቱ ወደ ቤተመንግስት ታንክ ለማንቀሳቀስ አይገደድም።

ከመለስ መታመም ጋር ተያይዞ በኢህአዴግ ውስጥ ከብአዴንና ከህወሃት ነባር አመራር አባላት በቀር ለሽኩቻው ብቃት ያለው ሃይል ማየት አይቻልም።

ለመሆኑ በዚህ ወቅት የተቃዋሚ ሃይላት ቦታ የት ነው?

አንዳንድ ተቃዋሚዎች እራሳቸውን ከምርጫ ውጭ በማድረግ፣ “አዜብ ትተካለች፣ የለም ሃይለማርያም ነው” ሲባባሉ ስሰማ ጠጉሬን ማከኬ አልቀረም። በትግርኛ ተናጋሪዎች ቁጥጥር ስር የወደቀው መድረክ ራሱን እንደ አማራጭ በማየት ፈንታ፣ “የሚተካ የተዘጋጀ ሃይል የለም። መጥፎም ቢሆን መንግስት ያስፈልጋል” አይነት ህወሃትን የማዳን አዝማሚያ ያላቸው ይመስላል። “የአንድነት” መሪ ዶክተር ነጋሶ የሚሰማቸው ጠፋ እንጂ እሳቸውም እንደ መለስ ታመዋል። እግዜር ይማራቸው።

“ኢህአፓ ምን እያሉ ይሆን?” በሚል ወደ ድረገፃቸው ገብቼ ነበር። “ኢህአፓ በአዲስ አበባ ወረቀት በተነ” የሚል ዜና ለጥፈዋል። ከ30 አመታት በሁዋላም የትግል ስልት አልቀየሩም። ፌስቡክ እና ኢሜይል በተስፋፋበት
ዘመን ወረቀት መበተን ለምን ያስፈልጋል? በጥንት ዘመን ወረቀት መበተን ያስፈለገው ሌላ አማራጭ ስላልነበረ ነው።

የዶክተር ፍስሃ እሸቱ የሽግግር ምክርቤት፣ “መለስ ሞቶአል፣ አረጋግጠናል” ብለው አውጀዋል። ፊሽ መቼም ችኩል ነው። አዲስ ናቸውና ከልምድ እየተማሩ ይሄዱ ይሆናል። የፖለቲካ ድርጅቶች ለዜና መሽቀዳደም የለባቸውም። ዜና መቅደም የጋዜጠኞች ስራ ነው። እንደ ሽግግር ምክርቤት አቅጣጫ ማሳየት ነው የሚጠበቅባቸው። በመሰረቱ የመለስ መሞት የችግሮች መፍትሄ አይሆንም። ከመለስ መወገድ በሁዋላ ስልጣኑን ህዝብ እንዲቆጣጠር ታክቲክና ስትራቴጂ መንደፍ ያስፈልጋል።

በመጨረሻ የተስፋ አይኖች የሚያርፉት በታጠቁት ሃይሎች ላይ ነው። ኦነግ፣ ግንቦት 7 እና ሌሎችም ሃይሎች ተቀናጅተው አንድ የታጠቀ የጋራ ሃይል ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል። አለመረጋጋት ቢፈጠር የሚያረጋጋ ሃይል ያስፈልጋልና ይህ ለነገ ሊባል የማይገባ ተግባር ይመስለኛል። አንዲህም ሆኖ የሃይል ሚዛኑን ስመረምረው በአስፈሪ ጭጋግ ውስጥ ያለን መስሎ ይሰማኛል። ህወሃት ደክሞታል። የሚገፈትረው ግን አጣ። ተቃዋሚዎችም አልተደራጁም። መንገዱ ወዴት ያደርስ ይሆን? እንደ ፕሮፌሰር መስፍን፣ “እግዜር ያውቃል” ማለት ብቻ ይሆን የቀረን?

በጥንት ዘመን አንድ ጋዜጣ፣ “ማርክ ትዌይን ሞተ” የሚል ዜና አትሞ ነበር። ማርክ ትዌይን ለጋዜጣው በላከው የማስተባበያ ደብዳቤ፣ “ስለኔ መሞት የፃፋችሁትን ዜና አንብቤዋለሁ። ተጋንኖአል።” ብሎ ነበር። ምናልባት መለስ በቴሌቭዥን ብቅ ብሎ፣ ተመሳሳይ ነገር ይነግረን ይሆናል። የሚበጀው ህወሃት እንደ ስርአት ይሞት ዘንድ፣ ታክቲክና ስትራቴጂ ነድፎ መትጋት ብቻ ይመስለኛል።

አለማየሁ እንደ አራፋት… (ከተስፋዬ ገ/አብ)

Tuesday, July 3rd, 2012

ይህን ከመፃፌ በፊት አልጀዚራ እያየሁ ነበር። ያሲር አረፋት የተገደለው (…he might have been poisoned with polonium, a rare radioactive isotope. ) ተመርዞ ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁም ወሬ አወጁ። ልብሱና የጥርስ ብሩሹን ስዊዘርላንድ ላይ በመመርመር የተገኘውን ውጤት ዋቢ በማድረግ፣ አራፋት 2004 ላይ ተመርዞ ተገድሎ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል። ሞቶ ከተቀበረ ከስምንት አመታት በሁዋላ ይህ ምስጢር ተገኘ። በጎ ነው። እውነት ከተቀበረችበት ብቅ ማለቷ በርግጥም በጎ ነው። ጊዜው ሲደርስ ጆንጋራንግ እንዴት እንደተገደለም እንሰማ ይሆናል።

ቴሌቪዥኑን አጥፍቼ ወደ መኝታዬ ሳመራ ስለ አለማየሁ አቶምሳ አስታወስኩ። በተመሳሳይ ተመርዞ መታመሙና ከዛሬ ነገ ህይወቱ ታልፋለች እየተባለ ባንኮክ ህክምና ላይ እንደሚገኝ አውቃለሁ። ለመሆኑ አለማየሁን ማን መረዘው? ለምን አላማ?

የዚህን ምስጢር ከእለታት አንድ ቀን እንሰማዋለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። በዚህ ባለንበት ዘመን አስቸጋሪ ሰዎችን የማስወገጃው ቀዳሚ ዘዴ ምረዛ እየሆነ በመሄዱ፣ በጣም አሳሳቢ ሆኖአል። በተለይም እስርቤት ያሉ የነፃነት ታጋዮች፣ ራሳቸውን የሚከላከሉበት እድል በጣም ጠባብ በመሆኑ ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል።

አለማየሁን በቅርብ አውቀው ነበር። ከኦህዴድ አመራር አባላት የተለየ ነበር። ዋናው ተወዳጅ ባህርይው የአንጎሉን መናገር መቻሉ ነበር። ታዛዥ እና እጁ በደም የተጨማለቀ አለመሆኑም ይታወቃል። ወደ ኦሮሚያ ፕሬዚዳንትነት ከመሳቡ በፊት ከአመራር አነባላቱ ጋር እየተጋጨ፣ ገለል ተደርጎ ቆይቶአል። የግጭቱ ምክንያት ሙስናን መቃወሙና ማህበራዊ ፍትህ መጠየቁ ነበር። በዚህ ምክንያት በኦነግነት ተፈርጆ በአይነቁራኛ ሲጠበቅ ኖሮአል። በኦነግነት የሚጠረጠር የነበረን ግለሰብ ወደ ስልጣን እንዲመጣ ለምን እንዳደረጉ ገርሞን ሳንጨርስ፣ መመረዙ ተነገረን።

“ማን መረዘው? ለምን?” ለሚሉት ጥያቄዎች ያልተረጋገጠ ሹክሹክታ እንጂ ምንም መረጃ የለም። በምረዛው በሰፊው የሚታሙት ግለሰቦችም ተጠርተው አልተጠየቁም፣ ስራቸው ላይ ናቸው። አባዱላ እና ሙክታር የድርጊቱ ፈፃሚዎች ስለመሆናቸው ተብሎ ተብሎ ያለቀለት ነው። የወያኔ መንግስትም በጉዳዩ ላይ ትንፍሽ ብሎ አያውቅም። አባዱላ ስልጣኑን በመነጠቁ፣ ሙክታር ደግሞ የአለማየሁን ቦታ በመመኘቱ በርግጥ ይህን ሊፈፅሙ ይችላሉ? ወይስ በእነርሱ ሰም ድርጊቱን የፈፀመ ሌላ ጥልማሞት አለ? አለማየሁ ማገገም ከቻለ ፍንጭ ይሰጠን ይሆናል። እግዚሃር ይማረው!

ከህወሓት መውደቅ በኋላ

Monday, June 25th, 2012

ከተስፋዬ ገብረአብ

“አበበ ባልቻ – እንደ ሕወሓት” በሚል ርእስ ‘ሰውለሰው’ በሚለው ድራማ ላይ የፃፍኩትን ተከትሎ አንዳንድ አስተያየቶችን ሳነብ ቆይቻለሁ። አበበ ባልቻ ሕወሓትን ወክሎ ሲተውን እንደነበር በብዙዎች ዘንድ ታምኖበታል። የአስናቀ አወዳደቅ የሕወሓት (አዜብ / መለስ)ን ፍፃሜ የሚያመለክት ስለመሆኑም ሰፊ ግንዛቤ አለ።

በድራማው ውስጥ፣ “የኢትዮጵያ ወኪልማናት?” የሚለው ጥያቄ ላይ ግን ልዩነት አለ። አንድ ሰው በብእር ስም cyberethiopia.com ላይ እንዳሰፈረው ከሆነ የኢትዮጵያ ወኪል ከማህሌት ይልቅ የአስናቀ ሚስት ናት። እንዲህ ሲል አብራርቶታል፣

“…የመስፍን ሚስት ኢትዮጵያን ትወክላለች ተብሏል’ ሲል (መባል አለመባሉ አንድ ነገር ሆኖ)፣ ይሄ ምን ማለት ነው? በድራማው ውስጥ ማህሌት ቤተሰቧን የምትወድና “ስኬታማ” እናት ብትሆንም ለባሏ ግልጽነት ይጎድላታል። ሚስጥሯን ከባሏ ይልቅ ለአስናቀ መንገር የሚቀላት እናት ናት። ከአንድም ሁለት ሶስት ጊዜ ቃሏን ስታጥፍ ትታያለች። ማህሌት ለባሏ ግልጽ ልትሆን አልቻለችም። ከባሏ ይልቅ ለአስናቀ ግልጽ መሆንን ስለመረጠች፣ ይህ ስህተቷ ሊያስከትል የነበረውን አደጋ፣ እንደ አጋጣሚ በፊልሙ ድንገተኛ መቋረጥና በአስናቀ መሞት ከአደጋ ያመለጠች ይመስላል። ይህን ታሪክ በምን መልኩ ነው ከኢትዮጵያ ጋር የምናያይዘው? ይልቁን የአስናቀ ሚስት ኢትዮጵያን እንደምትወክል አድርጎ ማየት ይቻላል። አስናቀ ቤቱን ማስተዳደር እንዳልቻለ ባል፣ እንደ በዝባዥ መሪ ማየት ይቻላል። የአስናቀ ሚስት ቻይነትና ርህሩህነት በአንፃሩ ይስተዋላል። ለልጆቿ ያላት ፍቅር፣ ለአስናቀም ቢሆን ይቅር ባይነቷ፣ መልካም ሰው መሆንን እስከመረጠ ድረስ ለሱ ያላትን ፍቅር በማንም እንደማትተካ ማሳየቷ፣ አገርን መወከል የሚያስችል፣ ትክክለኛ የእናትነትና “የሚስትነት” ባህሪ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የአስናቀ ወሮበላነት፣ እንደ አባት ልጆቹን በወጉ ማስተዳደርና ማሳደግ አለማቻሉ፣ ሴት ልጁን ለህልፈት መዳረጉ፣ ወንድ ልጁ ከእናቱ ጋር የቁምስቅል ኑሮ እንዲኖር መፍረዱ ወዘተ… በትክክልም የአስናቀ ሚስት አገርን እንድትወክል ያደርጋታል….” (የዚህን ፅሁፍ የቋንቋ አጠቃቀም አርቄዋለሁ)

ከላይ ባለው ፅሁፍ አስተያየት የማይስማሙ አሉ። ይልቁን የአስናቀ ሚስት የትግራይ ክልል ወኪል ስለመሆኗ ይገምታሉ። እኔም ይበልጥ ወደዚህኛው አስተያየት አደላለሁ። በህወሃት አገዛዝ ይበልጥ እየተሰቃየ ያለው ክልል ትግራይ መሆኑን ብዙዎች አያምኑም። እንግዲህ ተደራስያን የጥበብ ስራዎችን በተለያየ መንገድ መገንዘብ መብታቸው ነውና በዚህ ጉዳይ መከራከር ተገቢ አይሆንም።

“ሰውለሰው” ድራማ አለመቋረጡና ከሶስት ሳምንታት በሁዋላ እንደሚቀጥል እየተነገረ ነው። በርግጥ ድራማው ከቀጠለ አጓጊ ይሆናል። ምክንያቱም በድራማው ውስጥ ከህወሃት መውደቅ በሁዋላ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት ሊቀጥል እንደሚችል በምናብ ልናይበት እንችላለን። “በድራማው ውስጥ ኢትዮጵያ ማናት?” ለሚለው አከራካሪ ጥያቄም በትክክል ምላሽ ማግኘት ይቻላል።

“ሰውለሰው” የተባለው ድራማ ሲቀጥል ቁልፍ ለሆኑ አንዳንድ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ምላሽ እያገኘን እንደምንሄድ ግልፅ ነው። እንደ ባለፈው የድራማው ፍፃሜ ከሆነ ህወሃት ወድቋል። በአንፃሩ የመስፍን ወልደማርያም የህጋዊነት የአስተሳሰብ መንፈስ የበላይነቱን ጨብጧል። ማህሌት መንታ መንገድ ላይ ቆማ፣ ያልፈፀመችውን ወንጀል ለመደበቅ እየጣረች ነው። ህወሃት በህገወጥ መንገድ ያከማቸው ገንዘብ ወደ ሼክ መሃመድ አላሙዲ የባንክ አካውንት ተዘዋውሮአል። በዚህ መሃል የትግራይ ክልል (የአስናቀ ሚስት) የምታገኘው ፖለቲካዊ ትርፍ ከቶ ምን ሊሆን ይችላል? የአስናቀ ሚስት በወንጀለኛው ባሏ ሞትና ውድቀት የሚሰማት ምን ይሆን? ከሁለት ሳምንታት በሁዋላ ድራማው ከቀጠለ የዚህን ምስጢር ፍንጭ ለማግኘት እንሞክራለን። ይህ ብቻ አይደለም። በመጪው ዘመን የኦህዴድና የብአዴን አመራር አባላት እጣ ፈንታ ምን ይሆናል? ይህም ትንቢታዊ ታሪክ ይኖረው ይሆናል። የመድሃኒት እናት ከአንድ ልክስክስ የህክምና ባለሙያ ጋር ሆና በልጇ እና በልጅ ልጇ ላይ በፈፀመችው ወንጀል የሚደርስባትን ችግር በቀጣዩ የድራማው ተከታታይ ክፍል እናየው ይሆናል። የመዲ እናት ስትተውን ኦህዴድና ብአዴንን እያሰብን ሊሆን ይገባል።

“ሶስና” ሆና የምትጫወተውን ገፀባህርይ በጣም ነው የምወዳት። ከልጅቱ ጋር ፍቅር ይዞኛል ለማለት እደፍራለሁ። በንግግሯ ወንዶችን ቆሌያቸውን ስትገፋቸው በተለይ ከልቤ እዝናናለሁ። የአበሻ ሴቶች ጥያቄ ወኪል ሆኖ ትታየኛለች። ሳቋ፣ እንባዋ፣ ስድቧ ሁሉም ያምርባታል። የምትሞቅ የምሽት የሻማ ብርሃን ናት። ከወያኔ መውደቅ በሁዋላ አዲሳባ ሄጄ ይህችን ሴት ማግኘቴ አይቀርም። እኔ ወዳለሁበት አካባቢ በድንገት ብቅ ካለችም እንግዳዬ አድርጌ ልጋብዛት እፈልጋለሁ።

“ሰውለሰው” ድራማ ላይ ኢትዮጵያ ተስፋ፣ የሃገር ምሰሶ ሆኖ የሚተውነው ገፀባህርይ መስፍን የሚናገራቸውን በጥንቃቄ መረዳት ይገባል። የምንመኘውን ስርአት የሚያንፀባርቅ ነው።

በመጨረሻ “ሰውለሰው” ድራማ ፖለቲካዊ ይዘት እንዳለው ብዙዎች ሳይገነዘቡ መቆየታቸውን ከተፃፉ አስተያየቶች መረዳት ችያለሁ። ወደፊት በድራማው ላይ ተከታታይ አስተያየት የመስጠት አሳብ አለኝ። እስከዚያው የቃጂማው ጊዮርጊስ በቸር ያሰንብተን።

አበበ ባልቻ እንደ ሕወሐት? – ከተስፋዬ ገብረአብ

Monday, June 18th, 2012

ከተስፋዬ ገብረአብ

“ሰው ለሰው” የተባለው ድራማ በድንገት ከመጠናቀቁ ጋር በተያያዘ በርካታ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው። ትኩረቴን የሳበው ግን ስለ ተዋንያኑ ውክልና ፌስ ቡክ ላይ የተሰራጨው ወግ ነው። ይችን ቁራጭ መታጥፍ ለመክተብ መነሻ ሆኖኛል።

አበበ ባልቻ ሲተውነው የቆየው ገፀባህርይ (አስናቀ አሸብር) እንደ ህወሃት ወኪል ተሰይሞአል። አስናቀ በጠባዩ ለሃገሪቱ ደንታ የለውም። ገንዘብ በጣም ይወዳል። አብሮአደጉን መስፍን ሊበቀለው ይፈልጋል። ተሳዳቢ ሲሆን፣ በጉልበቱ ይመካል። በቅጥረኞቹ በኩል ሰዎችን ያስደበድባል፣ ያስገድላል። ሃብታም ካገኘ ሊዘርፈው በማሰብ ያንዣብባል። ያም ሆኖ ግን አስናቀ መጨረሻው አላማረም። ንብረት ያከማቸበትን አዳራሽ ሲከፍተው፣ በህገወጥ መንገድ ያከማቸው ንብረት ብን ብሎ ጠፍቶአል። የነበረውን ጥሬ ገንዘብ በሙሉ ወዳልታወቀ ሃብታም፣ (አላሙዲ?) በማዛወሩ በድንገት ባዶውን ቀረ። እና የደም ግፊት? አንቀጥቅጦ ገደለው። የቅርብ ረዳቱ እያሳቀበት ህይወቱ አለፈች።

መስፍን የተባለው ገፀባህርይ በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ተመስሎአል። ማህሌት ደግሞ የኢትዮጵያ ምሳሌ ነበረች። የመስፍንና የማህሌት ሁለት ልጆች የኢትዮጵያ ህዝብ ወኪሎች ኖረዋል። ሴቷ ልጅ ውጭ ሃገር በስደት ላይ፣ ወንዱ ደግሞ (ብሩክ) በአገር ቤት ይኖራሉ። ውጭ ሃገር ያለችው ሴት ልጅ በዚያው ቀልጣ ቀርታለች። ብሩክ የፍቅረኛውንና የልጁን ህይወት ለማዳን መከራውን ያያል። መስፍን በባህርይው ህገወጥ ነገር አይወድም። ለሃገሩ በጎ ነገር ይመኛል። ሚዛናዊ ነው። እልኸኛ ሲሆን፣ ፈሪ አይደለም። ቤተሰቡን ይወዳል። የፕሮፌሰር መስፍንን ሰብእና ለመቅረፅ የታሰበ ይመስላል።

የወያኔ ድርጅታዊ አሰራሮች በድራማው በብዙ ቦታ ተጋልጠዋል። ለአብነት ማህሌት ህገወጥ ተግባር እንድትፈፅም ያደረጋት ራሱ አስናቀ ነበር። መልሶ ግን ማስረጃውን ለግል ጥቅሙ በማዋል ማህሌት እንድትንበረከክለት ለማድረግ ሲሞክር ይታያል። ወያኔ እነ አባዱላን ወንጀል እንዲሰሩ ካደረገ በሁዋላ መልሶ እንደፈለገ የሚጠቀምባቸው በዚሁ መንገድ ነበር። እንደ ማህሌት በየዋህነት የፈፀሙት ወንጀል እንዳይጋለጥባቸው ሲሉ፣ ለህወሃት እየሰገዱ ለመኖር የተገደዱ በርካታ ባለስልጣናትን አውቃለሁ።

ልኡል (የአስናቀ ወንድ ልጅ) ከህወሃት የተወገዱት የህወሃት አመራር አባላት ወኪል ነው ተብሏል። ልኡል የህወሃት ወኪል ልጅ ቢሆንም፣ የስርአቱን ህገወጥ ድርጊት በመቃወም ወደ ሰፊው ህዝብ ጎራ ተቀላቅሎአል። የልኡልና የመስፍን ውይይቶች በጠቅላላ የህወሃትን አካሄድ በሚቃወሙ የህወሃት አባላትና በተቃዋሚ ሃይላት መካከል ያለውን ግንኙነት እንዲጠቁም ተደርጎ ተቀርፆአል። በርግጥ ደራስያኑ ይህን ስለማሰባቸው የሚታወቅ ነገር የለም። የተደራስያን መብት የሚባል ነገር ግን አለ። በተለይ አፈና ባለበት ስርአት ውስጥ የሚኖር ተደራሲ ማንኛውንም የጥበብ ስራ ከወቅታዊ አስተሳሰቦች ጋር ለማመሳሰል ጥረት ማድረጉ የተለመደ ነው።

የገፀባህርያቱ ዝርዝር ውክልና ሳያስገርመኝ አልቀረም። መለስ ብዬ ታሪኩን አንድ ባንድ ሳሰላስለው በትክክልም አሁን ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ ፍንትው አድርጎ ሲገልፅ የሰነበተ ድራማ ይመስላል። ድራማው በፍጥነት እንዲቋጭ የተደረገው ፖለቲካዊ ይዘት እንዳለው በመታወቁ ይሆን?

በኔ የግል አስተያየት ድራማው በጥሩ አጨራረስ ተደምድሞአል። ያልተስማማኝ ጉዳይ ቢኖር መዲ ከነልጇ መሞቷ ነው። ፅንስ ሁልጊዜ፣ ከትውልድ መቀጠልና ከተስፋ ጋር የሚዛመድ እንደመሆኑ፣ ክስተቱ ተስፋን የሚገድል ሆኖብኛል። ማህሌት እንደ ኢትዮጵያ ወኪልነቷ የልጅ ልጇን ማየት ነበረባት። በእርግጥ ድራማው ያለቀው ብሩክ ከመሰደዱ በፊት መሆኑ የድራማው ጠንካራ ጎን ነው። ድራማው ከማለቁ በፊት ብሩክ በቁጣ ወደ ፍቅረኛው እናት ሲራመድ አይተናል። ይህ የብሩክ እንቅስቃሴ ህዝብ ሲቆጣ ሊፈፅም የሚችለውን የመጨረሻ አደገኛ ሁኔታ የሚጠቁም ሆኖ ታይቶአል። የመድሃኒት እናት ልጇን የገደለችው ባለማወቅ ነው። ይህች ሴት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ወኪል ትመስላለች። ባለማወቅ የራስ ጥቅም ላይ ጥይት መተኮስ።

ድራማው ያላለቀ ቢመስልም በጥሩ ሁኔታ ተደምድሞአል። ርግጥ ነው ሟቾች በዝተዋል። በለውጥ ወቅት መስዋእትነት የሚጠበቅ ነው። ተወዳጁ ገፀባህርይ መስፍን በመጨረሻ ድል ማድረጉ ተስፋ ነው። የኢትዮጵያ ተምሳሌት ሆና የሰነበተችው ማህሌት በጭንቀትና በፍርሃት እንደተዋጠች ድራማው ማለቁ በትክክልም አሁን ኢትዮጵያ ያለችበትን አስጨናቂ ሁኔታ ይጠቁማል። የአስናቀ አወዳደቅ የህወሃትን የመጪው ዘመን እጣ ፈንታ ያመላክታል።

በረከትና መለስ ድራማው ገብቶአቸው ከሆነ ብዙ ሊማሩበት ይችላሉ። ኢህአዴግ 99.6 % በመቶ የኢትዮጵያ ህዝብ ደጋፊዬ ነው እያለ የራሱን ድምፅ ይሰማል። ከእለታት አንድ ቀን አዳራሹን ሲከፍቱት ግን ባዶ ሆኖ ያገኘዋል። በመጨረሻ ደራስያኑን አድንቄያለሁ። በመቀጠል መሪ ተዋንያኑ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። ዳይሬክተሩና የድምፅ ባለሞያው፣ ወደር የላቸውም። የጥበብ አምላክ ሌላ ብዙ ያፈልቁ ዘንድ ያግዛቸው።

የመነን 4ኛ ባል! – ከተስፋዬ ገ/አብ

Wednesday, June 6th, 2012

ከብዙ አመታት በፊት ተፈሪ መኮንን የሚባል አንድ ወጣት ደጃዝማች በሃረር አካባቢ ይኖር ነበር። እና ኑሮውን በሰላም በመኖር ላይ ሳለ አንድ ቀን ያልጠበቀው ነገር ገጠመው። ተፈሪ እንደወትሮው ጸሎት ላይ ሳለ ስልክ እንደሚፈልገው ተነገረው። የደወለለት የአጤ ምኒልክ ዙፋን ወራሽ ልጅ እያሱ ነበር። ሰላምታ ከተለዋወጡ በሁዋላ ልጅ እያሱ በቀጥታ ተፈሪን እንዲህ አለው፣

“ስማ ተፈሪ! የእህቴን ልጅ መነን አስፋውን ልድርልህ ወስኛለሁ። የአንተ አሳብ ምንድነው?”

ተፈሪ በጣም ደነገጠ። ምክንያቱም መነን ከሶስተኛ ባሏ ጋር ከተጋባች ገና አንድ አመት እንኳ አልሞላትም ነበር። ከዚያ በፊት ካገባቻቸው ሁለት ባሎች በድምሩ አራት ልጆች መውለዷንም ያውቃል። አራት ልጆች ከወለደች በሁዋላ ሶስተኛ ባል አግብታ በመኖር ላይ ያለችን ሴት፣ “ልዳርልህ” የሚል አሳብ ሲቀርብለት ተፈሪ መደንገጡ የሚጠበቅ ነበር። እና ድንጋጤውን ዋጥ አድርጎ ጥያቄ አቀረበ፣

“ጌታዬ! ለኔ የምታስብልኝን ሁሉ በደስታ መቀበል ፍላጎቴ ነው። ዳሩ ግን መነን የራስ ልኡልሰገድ ሚስት ናት። እንዴት ሆኖ ነው ለኔ የምትዳረው?”

ልጅ እያሱ በቁጣ ቃል ምላሽ ሰጠ፣

“እሱን ለኔ ተወው። አንተ እዚህ ውስጥ መግባት የለብህም። የጠየቅሁህ ‘መነንን ታገባታለህ ወይስ አታገባትም?’ የሚለውን ነው…”

በዚህ ጊዜ ተፈሪ መኮንን ምላሹን ሰጠ፣

“እሺ አገባታለሁ”

“እንግዲያው በ15 ቀናት ውስጥ ሽማግሌ ወደአዲሳባ ላክልን። አንተ አዲሳባ መምጣት አያስፈልግህም። ሽማግሌዎቹ ሚስትህን ይዘውልህ ይመጣሉ።”

ሁለቱ የባላባት ልጆች በዚህ መልኩ ስለመነን በሚነጋገሩበት ወቅት መነን ከሶስተኛ ባሏ እና ከአራት ልጆቿ ጋር በሰላም በመኖር ላይ ነበረች። ለአራተኛ ጊዜ ለሌላ ባል እዳራለሁ ብላ በህልምዋ እንኳ አሳቡ አልነበራትም። ከሶስተኛ ባሏ ጋር በፍቅርና በደስታ መኖር ጀምራ ነበር።

ተፈሪ መኮንን ከልጅ እያሱ ጋር የስልክ ንግግሩን ካበቃ በሁዋላ በቀጥታ ወደ ፀሎቱ ነበር የተመለሰው። ፀሎቱን እንዳበቃም ከአባቱ ወዳጆችና ነባር መኳንንቶች ጋር በጉዳዩ ላይ መከሩበት። ጋብቻውን ከመቀበል ውጭ ምርጫ አልነበራቸውም። መነንን እንደ ሙሽራ በማጀብ ወደ አራተኛ ባሏ የሚያመጧትም አራት ሲህ ወታደሮች ወደ አዲስአበባ ተላኩ። ከሞቀ ትዳሯ እና ከሶስተኛ ባሏ ነጥለውም ወደ ሃረር ወስደው ለተፈሪ መኮንን ዳሯት። ወይዘሮ መነን ወደ ተዘጋጀላቸው አራተኛ ባል እንድትሄድ ስትጠየቅ፣ “አምላክ በዚሁ በቃሽ ይበለኝ” ከማለት ሌላ አንዳችም ቃል እንዳልተነፈሰች ይነገራል። በርግጥም አምላክ ፀሎቷን ሰምቶላታል።

አጤ ሃይለስላሴ ተገደው እቴጌ መነንን ካገቡ በሁዋላ እስከ ህይወታቸው ፍፃሜ በጋብቻ ኖረዋል። እቴጌ መነንም ከአራተኛ ባላቸው በርካታ ልጆችን ለማፍራት በቅተዋል።

(የትረካ ምንጭ፣ ዘውዴ ረታ – ተፈሪ መኮንን)

የጎጃም ልዕልት

Friday, April 20th, 2012

ከተስፋዬ ገ/አብ

“የእናቷን ውበት ወርሳለች” ይሏታል። ርግጥ ነው፣ ወይዘሮ ላቀች ይህ ቀረሽ የማይባሉ ደርባባ ወይዘሮ ነበሩ። የቀድሞ የወጣትነት ወዘናቸው ወደ ልጃቸው ተሻግሮ ማየት ችለዋል። በዚህም ተባለ በዚያ ልጅቱ የንጉስ ተክለሃይማኖት ሴት ልጅ ናት። ስምን መልአክ ያወጣዋልና ስሟ ንግስት ይባላል። ስለዚህ ቆንጆ ናት። ከቁንጅናዋ በላይ ግን ሊጠቀስላት የሚችል ቁምነገር ነበራት። ከደብረ ኤልያስ ገዳም በመጡ ሊቃውንት ፅህፈትና ቅኔ ተምራ ነበር። አባቷ እያሉ አጊጣለች። ርግጥ አሁን ፀሃይ ጠልቃባት ነበር…

ንጉስ ተክለሃይማኖት የልጃቸውን ወግ ማእረግ ሳያዩ አርፈው ነበርና ልእልቷን ለማጨት በክብር የሚጠየቅ ባለቤት፣ ወይም የሚከበርና የሚፈራ ወገን አልነበራትም። ስለዚህ ዘመኑ ያፈረጠማቸው ደጃዝማቾች የንጉሱን ሴት ልጅ ሚስት ለማድረግ ጦር ወደ መስበቅ ተቃርበው ነበር። ወይዘሮ ላቀች ውሉ ጠፍቶአቸዋል። በግራና በቀኝ የሚጎነታተሉትን ጉልበታም ባላባቶች ማስቀየም ተቸግረው፣ አንዱን መወሰን ሳይችሉ ብዙ ወራት አሳለፉ። የደጃዝማቾቹ የሽኩቻ ወሬም በእረኛው በኩል በየመንደሩና በየመልካው ይናኝ ይዞአል፣

(“ስማኝማ! ልጅ መርእድ … ደፈጫ ሲበላ የከረመ ወይፈን አምሃ ብሎ ለንግስት ላከላት ይባላል”

“መርእድ ንግስትን ሊያገባ? ይሄ ጎሮጎሞ አጋሚዶ! ንጉሱ ቢኖሩ መች ይደፍር ነበር?”

“ደጃች ገሰሰ ‘ንግስት የኔ ካልሆነች ህይወቴ ታልፋለች’ ብሏል አሉ”

“አዬየ! ማርያም ትሁነን እንግዲይህ….ለከርሞ ጦር መስበቅ አይቀርም…”)

በየቤተክስያኑ ወሬው ይሄ ብቻ ነበር። ወይዘሮ ላቀች ለደጃች መርእድ “ቃል ሰጥተዋል” የሚለውን ወሬ ተከትሎ ደግሞ፣ ልእልቲቱ አኩርፋለች የሚል ወሬ ሹክሹክታ ብቅ አለ። ይሄም ቢሆን አነጋግሮአል፣

“እናቷ ተፈቀደች እሷ ምናገባት?”

“አውሬ ድመት ናት ይላሉ”

“ጠበል መውሰድ ነው እንግዲይህ…”

ወይዘሮ ላቀች በልጃቸው ጉዳይ ክፉኛ ተቸግረው እንደነበር መፃህፍት ያወጋሉ። በርግጥ የመኳንንቱ ግፊት ቢበረታ፣ እናትየው “መርእድ ያንሳት” ሲሉ መስማማታቸው እውነት ነበር። ሆኖም የጎጃሟ ልእልት፣ “መርእድን አላገባም” በማለቷ በሁለቱ ደጃዝማቾች መካከል ውጥረቱ ከረረ። በልጅ መርእድና በደጃች ገሰሰ ወገኖች መካከል ግጭት የማይቀር መሆኑ ሲታወቅ፣ ጉዳዩ ወደ አጤ ምኒልክ እንዲደርስ ተደረገ። ለአንድ አመት ያህልም አጤ ምኒልክ ጣልቃ ገብተው ሲሸመግሉ ቆዩ። በመጨረሻ ግን ጉዳዩ እልባት አገኘ። ደጃች ገሰሰ የንጉሱን ልጅ እንዲያነሳ ከተወሰነ በሁዋላ፣ አጤ ምኒልክ ልጅ መርእድን ወደ አዲስአበባ አስጠሩት።

* * *

ልጅ መርእድ አዲሳባ ደርሶ ደጅ እየጠና መሆኑ ሲነገራቸው አጤ ምኒልክ በፍጥነት ወደ እልፍኝ እንዲቀርብ አዘዙ። ልጅ መርእድ ከንጉሰ ነገስቱ ዙፋን ፊት ቀርቦ በደንቡ መሰረት ለጥ ብሎ እጅ ነሳ።

“አረፍ በል” አሉት።

እየተርበተበተ ወንበር ያዘ።

“…ያልወደደችህን ልጅ ወዳኛለች ብለህ ጦርነት ልታነሳ ነበር” አሉት ቆጣ ብለው።

“ጃንሆይ! እንደሱ አይደለም…”

“እንደሱ ነው’ንጂ! ምን እንደሱ አይደለም ትለኛለህ?”

“እናቷ ወይዘሮ ላቀች ፈቅደውልኝ ነበር…”

“እናቷን ነው የምታገባ ልጅቷን?”

ልጅ መርእድ የሙግት ስልቱን ቀየረ፣

“ጃንሆይ! ደጃች ገሰሰ አስፈራርቶ ነው የወሰዳት…”

“አትቀላምድ!” ብለው ተቆጡ ንጉሱ፣ “….ዳኛ ሆነው እንዲፈርዱ ግራዝማች ወልደዮሃንስን ሾሜ ነበር። ግራዝማች ግን ዳኝነቱን ትተው ለአንተና ለአባትህ ወገን ሆኑ። እሷን፣ ‘ከጃንሆይ እናጣላሻለን’ ብላችሁ አስፈራርታችሁ አሳቧን ልትገለብጡ ፈለጋችሁ…”

“ጃንሆይ! እኔ ይሄን አላውቅም።”

“አንተ ይሄን አታውቅም? እንግዲያው አባትህ አልነገረህም ይሆናል። ንግስት ራሷ ወረቀት ጥፋ የሰደደችልኝ እጄ ላይ አለ። ‘መርእድን አልፈልግም፤ ገሰሰ ይሻለኛል’ ብላለች። ምን ትላለህ እንግዲህ?”

ልጅ መርእድ ተስፋ ባለመቁረጥ ይሟገት ቀጠለ…

“ጃንሆይ! ንግስት ሚስቴ እንድትሆን ተመኝቼ ነበር…”

“ልጅ መርእድ! በግድ ይሆናል እንዴ ታዲያ? እሷ እንደወደደችህ ነው’ንጂ፣ እገሌን ታግባ፣ እገሌን አታግባ የምለው እኔ ምን አግብቶኝ ነው? አንተስ ቀድሞውኑ የሷን ልብ ሳትይዝ እንዴት እጇን ለመያዝ ትቃጣለህ?”

“ጃንሆይ! አምሃ ብዬ ደፈጫ እየበላ ያደገ ወይፈን ልኬላት ነበር!”

“ወይፈን ሰጥተህ ልቧን ለማግኘት ተመኘህ? እንዴት ይሆናል? አባቷ ሞተባት እንጂ የንጉስ ልጅ ናት እኮ! ወይፈን ብቻ ሳይሆን፣ ጊደርና በቅሎ ጨምረህ ልትሰጣት ይገባ ነበር። እዚያው አባቷ አገር ጉልት ሰጥታችሁ መለማመጥ በተገባ። ሲሆን ሁለት ጉልት፣ ካልሆነ አንድ ጉልት ሰጥተህ አቆላምጠህ ባታለልካት ነበር እንጂ፣ እሷ ‘አይሆንልኝም፣ የወደድሁትን አገባለሁ’ ስትል እኔ ምን አደርግልሃለሁ? የንጉስ ተክለሃይማኖትን ልጅ እንደ ገረድ አንቄ ልሰጥህ ነው? ምን ይሁን ማለትህ ነው?”

“ጃንሆይ! መጀመሪያ ላይ እሺ ብላኝ ነበር እኮ…”

“አትቀላምድ! እሺ አላለችህም”

“ቆርቦ ያንሳኝ ብላ ነበር…”

“ጅላጅሎ! ቆርቦ ያንሳኝ ማለቷ ምን ማለት ነው? አንተ ባንድ እንደማትረጋ አውቃለች። ቆርበህ እንደማታነሳት አውቃ እምቢ ማለቷ ነው። ይሄ አይገባህም?”

በመጨረሻ ልጅ መርእድ ተሸነፈ።

“ተሳስቻለሁ ጃንሆይ! ይቅር ይበሉኝ” አለ።

ጃንሆይ ግን ተቆጥተውበት ስለነበር፣ “ተነስ ተከተለኝ” አሉትና ከዙፋናቸው ተነሱ።

በጃንሆይ ዙሪያ ነበሩት ሁሉ የሳቅ ድምፅ አሰሙ። ቀጥሎ የሚሆነው የገባው ልጅ መርእድ (ምናልባት እድሉን እያማረረ) ጃንሆይን ተከትሎ ወደ ጓዳ ገባ። በግራና በቀኝ ጠባባብ መስኮቶች ያሉት ሰፊ ክፍል ነበር። መካከሉ ላይ ካለው ጠረጴዛና አንድ ወንበር በቀር በክፍሉ ውስጥ አንዳችም እቃ አልነበረም። ግድግዳው ላይ የተለያዩ ዱላዎች ተንጠልጥለዋል። አጤ ምንሊክ ከሽመሎቹ አንዱን እየመረጡ እንዲህ አሉት፣

“ቀላምደህ ጦርነት ልታነሳ ነበር። ላጠፋኸው ጥፋት ጥሩ ፍትፍት መቅመስ አለብህ?”

“ጃንሆይ! አጥፍቻለሁ ብያለሁኮ!”

“ቢሆንም፣ ጠጅ ሳትቀምስማ አትወጣም…”

እንደ ራቻ እያገላበጡ ይገርፉት ጀመር። አጥንቱንና ክፉ ቦታ እንዳይመቱት እየተጠነቀቁ፣ ልክ አባት ልጁን እንደሚቀጣው አስጎንብሰው ጀርባ ጀርባውን በዱላ ዠለጡት። ይህችን የጃንሆይ የዱላ ፍትፍት ብዙዎች ፊታውራሪዎችና ራሶች ጭምር እንደቀመሷት ስለሚያውቅ፣ ልጅ መርእድም ድምፅ ሳያሰማ ቀጨሞውን በፀጥታ ጠጣ። አጤ ምኒልክ ዝቅተኛውን ቅጣት 12 ዱላ ካቀመሱት በሁዋላ ዱላውን እነበረበት ቦታ ሰቀሉ። እናም እንደገና ልጅ መርእድን አስከትለው ወደ እልፍኛቸው ተመለሱ። በቤተመንግስቱ ደንብና ስርአት መሰረትም ምኒልክ በዙፋናቸው፣ ልጅ መርእድም በቦታው ተቀመጡ።

በመጨረሻ እንዲህ ሲሉ አሰናበቱት፣

“…እስቲ ለማን እንደምንድርህ እናያለን። እዚሁ አካባቢ ቆይ!”

(የትረካ ምንጭ፡ ጳውሎስ ኞኞ፣ (አጤ ምኒልክ)፣ Count Gleichen – With the Mission to Menilik, ደጃዝማች ከበደ ተሰማ)

ጎሹም ሄደላችሁ!

Tuesday, April 17th, 2012

ከተስፋዬ ገ/አብ

የኮሎኔል መንግስቱን መፅሃፍ ሳነብ ከገረሙኝ ነገሮች አንዱ የኮሎኔል ጎሹ ወልዴን ስም አለመጥቀሱ ነበር። ቢያንስ፣ “የታጠቅ ጦር ሰፈር አመሰራረት” በሚለው ምእራፍ ስር እንኳ ስሙን ሊያነሳው በተገባ።

በቂ ምክንያት ማቅረብ ባልችልም ስለ ኮሎኔል ጎሹ በጎ ስሜት አለኝ። ምናልባት የመንግስቱን ስርአት ተቃውሞ ስለኮበለለ እንደ ውለታ ቆጥሬለት ሊሆን ይችላል። ጊዜው አይረሳኝም። ጎሹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ለቆ ሲኮበልል እኔ ደብረዘይት ነበርኩ።
በአየር ሃይልና በአየር ወለዶች የብረት ጫማ ቁጥጥር ስር የነበረችው ደብረዘይት በጎሹ ወልዴ የመኮብለል ወሬ ታምሳ እንደነበር አስታውሳለሁ። “የቡርቃ ዝምታ” ላይ እንደጠቀስኩት፣ ደብረዘይት ላይ የፖለቲካ ወሬ የሚከካው ከአየርሃይል ሆቴል ባንኮኒ ላይ ነበር። እዚያ የማይመጣ የለም። በተለይም ሁሉን አዋቂና አስፈፃሚ የሆኑት መስመራዊ መኮንኖች የሆቴሉ ቋሚ ደንበኞች ናቸው። ለሃሜቱና ለብልግናው ደብረዘይት ምቹ ናት። ዋዝጂፕ እያንኳኩ፣ ከጠመንጃና ከጥይት ፋብሪካ፣ ከአየር መቃወሚያና ከታንክ መገጣጠሚያው ወደ አየር ሃይል ሆቴል ይጎርፋሉ።
ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ አገር ለቆ በኮበለለ ሰሞን ከሆቴሉ ባንኮኒ አካባቢ የሰማሁዋት ግጥም ዛሬም ድረስ ትታወሰኛለች፣
አትመንጥሩ፣ አትመንጥሩ – ደኑን ስንላችሁ፣
ነብሩም አንበሳውም – ጎሹም ሄደላችሁ…

ፖለቲካና ስነጥበብ ሲቀላቀሉ ያሳብዳል። እነዚህ ሁለት ስንኞች ለጎሹ ወልዴ ወገናዊነት እንዲሰማኝ ሳያደርጉኝ አልቀሩም። በዚያው ሰሞን ደግሞ ሌላ ወሬ ወደ አየር ሃይል ሆቴል ብቅ አለ። “ደቡብ ከሚገኘው እዝ 10 ሺህ ወታደሮች ከነትጥቃቸው ከድተው ኬንያ ገቡ” የሚል ነበር። ጎሹ ወልዴ ከአሜሪካ ወደ ናይሮቢ ተመልሶ፣ እነዚያን የከዱ የጦርሰራዊት አባላት እየመራ፣ በሞያሌ በኩል ወደ አዲስአበባ እየገሰገሰ ነው” ተባለ። በወቅቱ በጎረምሳነት መንፈስ፣ “እየገሰገሰ ነው!”፣ “በከበባ”፣ “በማጥለቅለቅ” የሚሉ ቃላት ይስቡኝ ነበር። ምናልባት፣ በ18ኛው ክፍለዘመን ገበሬ አደራጅቶ፣ ፒተርስቡርግን ከብቦ ንግስቲቷን ስላንቀጠቀጣት አመፀኛ ያነበብኩት በዚያው ሰሞን ስለነበር ሊሆንም ይችላል።
ምን ያደርጋል?
የጎሹ ወልዴ ሰራዊት “ከዛሬ ነገ አዋሳ ደረሰ” እያልን ብንጠብቅም ወሬው “የቆሪጥ ፉገራ” ሆኖ ቀረ። በግልባጩ እንዴት እንደሆነ እስከዛሬ ምስጢሩ ባልተነገረ ፍጥነት፣ እኔ ወያኔ ሆኜ፣ እኔ ባቀረብኩት ሃሳብ መሰረት፣ ወያኔ 25 አመታት መንገስ እንዲችል፣ ለቢሾፍቱ ቆሪጥ ነጭ ላም አርደንለት፣ ቆሪጥ “ለ25 አመት ንገሱ! አዲሳባ ግቡ!” ብሎ ስለፈቀደ እንደ ፓሎኒ ኳስ እየነጠርን አዲሳባ ገባን።
ከዚያም እንደገና የጎሹ ወልዴ ስም ተነሳ።
“መድህን የተባለ ፓርቲ መስርቶአል። ጎሹና ቢል ክሊንተን የትምህርት ቤት ጓደኛሞች ነበሩ። ወያኔ አለቀላት!” የሚል የወሬ ምላጭ ጆሮአችንን ሸረካከተው።
በዚህች አለም የህይወት መንገድ ላይ ህይወት ተገላቢጦሽ ስትሆን ብዙ ጊዜ አይቻታለሁ። ዛሬ ጎሹም ክሊንተንም የሉም። የነበረው ሁሉ እንዳልነበር ሟች ሆኖአል። ሟች መሆን ደባሪ ነው። ጎሹ “መድህን” የተባለ ድርጅቱን ለልደቱ በነፃ ሸጦለት ሲያበቃ፣ “ጴንጤ ሆኛለሁ ተውኝ!” ማለቱን ሰማሁ።
“ያ! ቆፍጣና ወታደር ምን ቢገጥመው ይሆን እንዲህ ባንዴ ፊቱ የጨለመ?” ብዬ ጠየቅሁ።
እምነት ላይ ጠበቅ ያሉ ጓደኞቼ፣
“…ተሳስተሃል! ጎሹ ዘላለማዊ የህይወት መንገድ አጊኝቷል። ለራስህ እወቅበት።” አሉኝ።
ፖለቲከኞቹ ጓደኞቼ ደግሞ፣
“…ጎሹን በነገር አሳብደው ከፖለቲካ የጨዋታ ሜዳ ያባረሩት ኢህአፓዎች ናቸው” ሲሉ ‘ምስጢር’ ነገሩኝ። ሁለቱም ምክንያቶች አልተዋጡልኝም። “ጎሹ ከራሱ እየሸሸ ነው” አልኩ።
ርግጥ ነው፣ ጎሹ ከተሰናበተ በሁዋላ ሌሎች ነብርና አንበሳዎች ተተክተው ነበር። ብዙዎች እየመጡ ሄደዋል። ያልቻሉ ተሰናብተዋል። የቻሉ ቀጥለዋል። ስድቡንም፣ ውግዘቱንም፣ ሃሜቱንም ችለው የነፃነትን ብርሃን በሩቅ እያዩ የሚጓዙ አሉ። ህዝብ ምንጊዜም ተስፋ አይቆርጥም። የደከሙትን እየሸኘ አዳዲሶችን ይወልዳል። ቢሆንም ግን …ቢሆንም ግን…እንዲህ ባለው ጊዜ ቢያንስ አሳብን መሰንዘር በጎ በሆነ ነበር…

አባቶችና ልጆች (ከተስፋዬ ገ/አብ)

Saturday, April 7th, 2012

ወደ ጎንደር የህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ለማስተማር የመጣ አንድ ጀርመናዊ ሃኪም አንዲት የገበሬ ሚስት እያከመ ነበር። እንዴት ሾልኮ እንደገባ ባይታወቅም የሴትየዋ ባል ከሚስቱ ራስጌ ላይ ቆሟል። ገበሬው የታመመች ሚስቱን በስስት አይን፣ ፈረንጁን ሃኪም ደግሞ በተስፋ ይመለከታል። ጀርመናዊው ሃኪም ቆጣ ብሎ ከሚስቱ ራስጌ ተጠግቶ የቆመውን ገበሬ እንዲያስወጡት አዘዘ። ረዳቶቹ ገበሬውን እየገፈታተሩ አስወጡት። ፈረንጁም ህክምናውን ጀመረ…

* * *

በግምት ከሶስት ሰአታት በሁዋላ የሰላ ጎራዴ የያዘ አንድ ገበሬ የጎንደር ሆስፒታልን ቀውጢ አደረገው። የሆስፒታሉ ሪሴፕሽን ላይ ጎራዴውን እያወናጨፈ፣ እንደ ጥይት በሚተኮስ ድምፅ ይጮህ ጀመር፣

“አምጡልኝ፣ ያንን ነጫጭባ ጣልያን! እንደ ገበሎ ወገቡን ሁለት ቦታ ላይ ካልቀነጠስኩት እኔ የአባቴ ልጅ አይደለሁም!”

ሆስፒታሉ በዚያው ቅፅበት ተተራመሰ!

ሁኔታው ወዴት እንደሚያመራ የገባቸው ነባር ሃኪሞችና ነርሶች ጀርመናዊውን ሃኪም ቢሮ ውስጥ ቆልፈውበት በውጭና በውስጥ ፈረንጁን ከበውት ለጥበቃ ቆሙ። አንዲት ነርስ ወደ ጎንደር ፖሊስ በመደወል አስቸኳይ የእርዳታ ጥሪ አደረገች። የሆስፒታሉ የጥበቃ ዘቦች አእምሮውን የሳተ የሚመስለውን ባለጎራዴ በርቀት ከብበው ይማፀኑት ጀመር፣

“እባክህ ረጋ በል!”

ገበሬው ግን ሊረጋጋ አልቻለም።

“ገለል በሉ ከፊቴ! ሁዋላ ሰበብ ትሆናላችሁ! ከእናንተ ጠብ የለኝም! ገለል በሉ ብያለሁ…”
“እባክህ ረጋ በል ጌታው! ጎራዴውን አስቀምጥና እንነጋገር!?”
“በህግ አምላክ ሰበብ አትሁኑብኝ!”
ገበሬው ጎራዴውን ልክ እንደ ገብስ አጨዳ አይነት፣ አየሩ ላይ እየሰነዘረ፣ አየሩን በሰላ ጎራዴው ያጭደዋል። እንደሚገነፍል የጀበና ቡና ያለ የእልህ ቁጣ ከልቡ ብልቃጥ እየተተኮሰ፣ እንደ ማቅራራት ያደርገዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጀርመናዊው ሃኪም እጅና እግሩ እየተንቀጠቀጠ ወደ ጀርመን ኤምባሲ ለመደወል ቢጠይቅም፣ እጁን ይዘው እንደምንም አረጋጉት። ባለ ጎራዴው ገበሬ ዘቦቹን ጥሶ ቢመጣ እንኳ፣ የሆስፒታሉን ሃኪሞችና ነርሶች ገድሎ ሳይጨርስ እሱ ዘንድ ሊደርስ እንደማይችል በእርግጠኛነት ቃላቸውን ሰጡት።

በዚህ መካከል ፖሊሶች ደረሱ። እነርሱም እንደ ዘቦቹ፣ ጠመንጃቸውን አቀባብለው ገበሬው ላይ በመደገን ጎራዴውን እንዲያስቀምጥ መማፀን ጀመሩ። ግማሽ ሰአት እንኳ ባልወሰደው በዚህ ቅፅበታዊ ግርግር ውስጥ፣ በሆስፒታሉ ውስጥ ነባር የሆነ አንድ የአስተዳደር ሰራተኛ መፍትሄ አበጀ። በሆስፒታሉ ውስጥ ለህክምና ከተኙ ከበድ ያሉ አዛውንቶች መካከል ሁለቱን መርጦ በማምጣት፣ ወደ ባለጎራዴው ተጠግተው እንዲያነጋግሩት ፖለሶቹም ገለል እንዲሉ አደረገ።

ከአስር ደቂቃ በሁዋላ ባለጎራዴው ረገብ አለ። ጎራዴውን ማወዛወዙንም ቀነሰ። በመቀጠል ስለተፈጠረው ችግር ለጀርመናዊው ሃኪም ገለፃ ተደረገለት። ገበሬው ለምን ሊገድለው እንደመጣ ለጀርመናዊው ማብራሪያ ሲደረግለት፣ በድንጋጤ ደሙ ከፊቱ ላይ ጥርግርግ ብሎ ጠፍቶ፣ ያልተፃፈበት ነጭ ወረቀት መስሎ እንደነበር አጠገቡ የነበሩት መስክረዋል። ሆኖም ችግሩ ሊወገድ እንደሚችል በእርግጠኛነት ነገሩት። በርግጥ ገበሬውን በቁጥጥር ስር ማድረግ እንደሚቻል ነግረውታል። መፍትሄ እንደማይሆን ግን አስረዱት። የገበሬው ዘመዶች ሊበቀሉት እንደሚችሉ በመጠቆም፣ የሚሻለው እርቅ መሆኑን ጠቆሙት። ጀርመናዊው ሃኪም ምን ጥፋት እንደፈፀመ በትክክል ሊገባው ባይችልም የተፈጠረውን ከፍተኛ ግርገር በመመልከት አንድ አደገኛ ነገር መከሰቱን ተገንዝቦ ስለነበር፣ ምንም ሳያመነታ ገበሬውን ይቅርታ ለመጠየቅ ተስማማ፣

* * *

እነሆ! ገበሬውና ሃኪሙ በሰዎች እንደታጀቡ በየተራ የገበሬው ሚስት ወደተኛችበት የበሽተኛ ክፍል እንዲገቡ ተደረገ። ገበሬው ጎራዴውን እንደጨበጠ ከሚስቱ ራስጌ አጠገብ ቆመ። ጀርመናዊው ሃኪም ከበሽተኛዋ አልጋ ግርጌ በኩል እንዲቆም አደረጉት። አሸማጋዮቹና የሆስፒታሉ ጥቂት ዶክተሮች በመካከል ላይ ቆሙ። በአገሩ ባህል መሰረትም አሸማጋዮቹ የተፈጠረውን ችግር በዝርዝር አብራሩ። ከዚያም በአስተርጓሚ በኩል ፈረንጁን እንዲህ አሉት፣

“የህመምተኛዋን የተከበሩ ባል በማመናጨቅ መልኩ እጅህን አወዛውዘህ፣ ‘አስወጡት!’ ማለትህ ልክ አይደለም። እሳቸው ባለቤታቸው እንደመሆናቸው ከዚህ መውጣት ካለባቸውም በጨዋ ደንብ ለብቻቸው ገለል በማድረግ ሊነገራቸው ይገባል እንጂ፣ ሚስታቸው ፊት በዚህ መንገድ ማመናጨቁ ክብር የሚነካ ነው። እሳቸውም እንዲህ ሚስታቸው ፊት ክብራቸው ተነክቶ፣ አባወራ ሆነው መኖር ስለማይችሉ ጎራዴያቸውን ይዘው መጥተዋል። ርግጥ ነው፣ እርስዎም እንግዳችን እንደመሆንዎ መከበር አለቦት። እንዲህ ያለ ነገር በመፈጠሩም አዝነናል። የእግዚአብሄር ፀጋ አልተለየንምና ግን በመካከላችሁ ደም አልፈሰሰም። አሁን እርስዎም በደል እንደፈፀሙባቸው አውቀው፣ በሚስታቸው ፊት ይቅርታ ይጠይቋቸው!”
ጀርመናዊው ሃኪም በሽማግሌዎቹ በተመከረው መሰረት በአስተርጓሚ ምላሽ ሰጠ፣

“በእውነቱ እሳቸው የህመምተኛዋ ባል መሆናቸውን አላወቅሁም ነበር። የአነጋገር ጠባይና ልማድ ሆኖብኝ እንጂ ማመናጨቄም አልነበረም። ከሃገሬ ድረስ ሌሊትና ቀን ተጉዤ እዚህ መምጣቴ የታመሙትን ለመርዳት እንጂ ክብር ለመንካት አይደለም። መቼም አጥፍቼ ከሆነ እሳቸውንም ባለቤታቸውንም ይቅርታ እጠይቃለሁ!”

ሃኪሙ የተናገረው ለገበሬውና ለሚስቱ ተተርጉሞ ሲነገራቸው፣ ሁለቱም ስሜታዊ ሆነው በነጠላቸው ጫፍ አይኖቻቸውን አባብሰዋል። ገበሬውም በዚያችው ቅፅበት ጎራዴውን ከሽማግሎቹ ለአንዱ ካስረከበ በሁዋላ፣ የሚከተለውን ተናገረ፣

“እኔም ብሆን ሚስቴን ከህመሟ ይፈውሱልኛል ብዬ ተስፋ ያደረግሁት በርስዎ ላይ ነው። የክብር ነገር ሆነብኝና ግን አስቀየምሁዎ! ጣሊያን መስለውኝ ያለ ስምዎ ስም በመስጠቴና በመዝለፌ እኔም ብሆን ይቅርታ እጠይቃለሁ። ሊያጠቃኝ ጎራዴ መዘዘብኝ ብለው በልብዎ ቂም ይዘው ሚስቴን ችላ እንዳይሉብኝም ርስዎም ቃሎን ይስጡኝ።”

ይህ የገበሬው ንግግር ለፈረንጁ ሃኪም ሲተረጎምለት ፊቱ የማረቆ ድልህ መምሰሉ ታይቶአል። ሚስትየዋ አንዳችም ያልተናገረች ሲሆን፣ ፈረንጁ ይቅርታ ሲጠይቅ ግን ከወገቧ እንደመነሳት ብላ፣ “አይገባም” እንደማለት አክብሮቷን ገልፃለታለች። በዚህ መልኩ እርቁ ከተፈፀመ በሁዋላ ሁለቱ በእድሜ የሚቀራረቡ ባላንጣዎች ትከሻ ለትከሻ እንዲሳሳሙ አደረጓቸው።

* * *
ይህን ታሪክ ያጫወተኝ በወቅቱ ከኮሌጁ የህክምና ተማሪዎች አንዱ የነበረ ጓደኛዬ ሲሆን፣ ታሪኩ ከተፈፀመም 19 አመታት ሆኖታል። ሆኖም ይህ ታሪክ አእምሮዬ ላይ ነግሶ እንደመኖሩ፣ የክብር ጉዳይ በተነሳ ቁጥር በጨዋታ መሃል ስጠቅሰው ኖሬያለሁ። ርግጥ ነው፣ ያ የበጌምድር ገበሬ ከኛ ዘመን ትውልድ ጋር የመንፈስ ዝምድና ይኖረዋል ለማለት ቃጥቶኝ አያውቅም። የ18ኛው ክፍለዘመን አበሾች ወደመቃብራቸው ሲጓዙ፣ “እኛ እንዲህ ነበርን” ለማለት ለምልክት ትተውት የሄዱት መስሎ ይሰማኛል።

መለስ ዜናዊ በማን ይተካል?

Sunday, April 1st, 2012

ከተስፋዬ ገ/አብ

ወቅታዊውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ የሃይል አሰላለፍ በመገምገም፣ “መለስ ዜናዊ! – በማን ይተካል?” ለሚለው ጥያቄ ምላሽ መስጠት በርግጥ ቀላል አይደለም። በቅድሚያ ግን “በርግጥ መለስ ዜናዊ ስልጣኑን ይለቃል?” ብሎ መጠየቅ ይገባል። መለስ ዜናዊ፣ “ከሁዋላ ሆኜ ማገዜ ባይቀርም፣ እለቃለሁ” ብሎ ደጋግሞ ነግሮናል። ተቃዋሚዎች በበኩላቸው፣ “መለስ እለቃለሁ ቢልም ባይልም አፍንጫውን ተይዞ ይለቃል” ሲሉ ቁጣ ባዘለ ድምፅ እየገለፁ ነው። የሆነው ሆኖ በራሱ ፍላጎትም ሆነ ተገዶ መለስ ስልጣኑን መልቀቁ የማይቀር ከሆነ ቀጣዩ የኢትዮጵያ መሪ ማን ይሆናል? በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ ተንትኖ የፃፈ አላጋጠመኝም…

ስዬ እና ብርቱካን…?

ሁለቱ የፖለቲካ ሰዎች (አይን ካረፈባቸው) የቀጣዩ ዘመንየኢትዮጵያ መሪዎች መካከል መሆናቸው ይወሳል። መቼም አሜሪካኖች ለኛ ካላቸው የተቃጠለ ፍቅር የተነሳ፣ የአፍሪቃ ቀንድችግር ያሳስባቸዋል። በፖለቲካውም በረሃቡም መሃንዲስና በጎአድራጊናቸው። “የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ተጣምረው አንድ ሃይል መሆንአቃታቸው እንጂ ባገዝናቸው ነበር” ሲሉ ማማረራቸው ብዙ ጊዜ ይሰማል። ያሬድ ጥበቡ የበረከትን መፅሃፍ በተቸበት መጣጥፉ፣ “የስዬና የአሜሪካኖችን መቀራረብ” በጨረፍታ አጫውቶናል። በይስሃቅ ኤፍሬምና በብርቱካን ሚደቅሳ መካከል “የቀጠለው”ግንኙነትም እንዲሁ ርእሰወግ ሆኖ ሰነባብቶአል። የስዬ አብርሃ አስፈላጊነት በአሜሪካኖቹ ከታመነበት ቆየ። ስዬ በህወሃትና በተቃዋሚዎች መካከል ድልድይ እንዲሆንላቸው ይፈልጋሉ። ሰራዊቱንም እንደነበረ ያቆይላቸዋል። ጄኔራል ሳሞራን ከላይ ነጥሎ በማንሳትብቻ የሰራዊቱን መዋቅር እንደነበረ ለማስቀጠል፣ ስዬ ሁነኛ ምርጫቸው ነው። የከፋ ነገር ከመጣ መለስም ቢሆን በዚህ ይስማማል።  ስዬን በቀጥታበመለስ ቦታ ማስቀመጡ ግን አስቸጋሪ ነው። ብርቱካን ከላይ ብትሆን ሚዛኑ ሊጠበቅ ይችላል። ሴት መሆኗ እና የገነባችው ስም፣ የወጣች በትማህበረሰብ ሁሉ ሚዛናዊ ያደርጋታል” ይላሉ። ማሰብ ችግር የለውም። ምን ችግር አለው?

ሃይሌና መሃመድ….?

ሃይሌ ገብረስላሴና መሃመድ አላሙዲ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን ያስቡይሆን? ሁለቱም ከጀርባ ግፊት አለባቸው። የኛ ሰው መቼም ክፉና ተንኮለኛ ነው። ከፈገግታ ጋር ወደ ጆሮ ጠጋ ብሎ ማሳሳት ይችልበታል። “ሼክ መሃመድ… ህዝቡ እኮ ‘እሳቸው ቢመሩን ይሻል ነበር’ እያለ ነው። ቢያስቡበት ጥሩ ነው…” “ሃይሊሻ! ለምን አትወዳደርም? የላይቤሪያው ጆርጅ ዊሃ እንኳ ተወዳድሮአል። ህዝቡ ግልብጥ ብሎ ነው የሚመርጥህ…” ታምራት ላይኔ ጠቅላይ ሚኒስትር በነበረ ጊዜ  ይህንኑ  የአላሙዲ ፍላጎት አጫውቶኝ ነበር። ቃለመጠይቅ አድርጌው ካበቃን በሁዋላ ስናወጋ፣ “የሼኩ የረጅም ጊዜ እቅዱ ወደ ፖለቲካው መግባት ነው። ከሆነለት አገሪቱን መምራት ይፈልጋል” ብሎ እንደነገረኝ አስታውሳለሁ። አሁን እንኳ አሳቡን ሳይለውጥ አልቀረም። በወርቅ ቁፋሮ ተጠምዶአል። ከእለታት አንድ ቀን የኢትዮጵያ ህዝብ ከእንቅልፉ ሲነቃ፣ ትልልቅ ባዶ ጉድጓዶችን ያገኛል። የሃይሌ ገብረስላሴን ጠቅላይ ሚኒስትር የመሆን ጉዳይ ለመለስ በጥያቄ መልክ አቅርበውለት ነበር። “…ይህን በተመለከተ ከሃይሌ ጋር አላወራንም” ሲል መልስ ሰጠ። አያያዘናም የማስጠንቀቂያ ወንድማዊ ቃል አከለበት፣ “….ሃይሌ ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ ውጤታማ ይሆናል ወይስ አይሆንም የሚለውን ለመፍረድአልችልም። ሆኖም ወደ ፖለቲካ የመግባት ሙሉ መብት አለው…” በውነቱ መለስ ሃይሌን ደግ መክሮታል። ሁለቱ ታዋቂ ሰዎች ከቀጣዩ ዘመን የጠቅላይ ሚኒስትርነት የስም ዝርዝር ላይ እጃቸውንም ሆነ ስማቸውን ባያስገቡ ይጠቅማቸዋል። ይልቁንመለስን በመምከርና ታሪካዊ ምርጫ አካሂዶ፣ ታሪክ እንዲሰራ ቢያግባቡት እነርሱንም ታሪክ ሲያስታውሳቸው ይኖራል።

እነ ተወልደ…?

“እነ ተወልደ” በሚል ተውላጠ ስም ከሚታወቁት መካከል እንደገና አንሰራርቶ ወደ ስልጣን የሚመለስ ሊኖር ይችላል? አይመስለኝም። እነ ተወልደ ከፖለቲካው ርቀዋል። ለነገሩ ባመለካከትም ተለያይተዋል። ልዩነታቸው በፈረደባት ኤርትራ ዙሪያ ነው። ተወልደ ከመለስ ጋር የከረረ እልህና ፀብ ቢኖረውም፣ በአሰብና በኤርትራ ሉአላዊነት አጀንዳ ላይ አሁንም በአቋሙ ላይ እንደፀና መሆኑ ይሰማል። የስዬ፣ የገብሩና የጆቤን ቅስቀሳ፣ እንደ ደጋፊ መፈለጊያ ብቻ የያዋል። አለምሰገድ ገብረአምላክና ሰለሞን ጢሞም በተመሳሳይ በተወልደ መንገድ በመጓዝ ላይ ናቸው። ቀሪዎቹ የህወሃት አንጋፋዎች ወደ ቢዝነሱ አለም ገብተዋል። ፃድቃንና ጃማይካ፣ “ራያ” የተባለውን ቢራ ለመገንባት እንቅልፍ አጥተዋል። ፃድቃን ከደቡብ ሱዳን ያገኘውን ገንዘብ ወደ ማሌዢያ ባለማሸሸቱ ሊመሰገን ይገባዋል። ሃይለኛ እና ተሳዳቢ የነበረው ቢተው በላይ እንኳ፣ እንዲህ ረግቦ በቢዝነሱ ላይ መወሰኑ ያስደንቃል። ታስሮ ከተፈታ ወዲህ ፀጥተኛ ሆኖአል። አሁን አሁን፣ እስርቤት ገብተው የሚወጡ ፖለቲከኞች ጠባያቸው ለምን እንደሚለወጥ ሊገባኝ አልቻለም። የሚወጓቸው መርፌ ይኖር ይሆን? በጥቅሉ እነ ተወልደ ከወደፊቷ ኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን ያነሱ ይመስላሉ። መልካም የጡረታ ዘመን እንመኝላቸዋለን።

ፍሰሃ እሸቱ….? 

ፍሰሃ በግልፅ ቋንቋ፣ “ስልጣን አልፈልግም” ብሎ ተናግሮአል። አያይዞም፣ “እንደ ማርቲን ሉተር ኪንግ ነፃነት የሚገኝበትን አቋራጭ መንገድ ላሳያችሁ ነው የመጣሁት” ብሎናል። እንደ ፍሰሃ እቅድ በውጭ አገር የተበተኑትን እና በነገር ካራ ርስበርስ የሚወጋጉትን ተቃዋሚዎች በማስታረቅ በመጪው ሰኔ ወር ላይ አንድ ካውንስል ያቋቁማል። ከፖለቲካ ርቆ የተቀመጠውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ማንቀሳቀስ እንደሚችልም በርግጠኛነት አብራርቶአል። ያን ጊዜ፣ እንደ ፍስሃ ህልም 50 ሺህ ኢትዮጵያዊ ተቃዋሚ “እንደ ቆላ ወፍ – እንደ ግሪሳ” ዋሽንግተን ዲሲ ነጩ ቤተመንግስት ደጃፍ ላይ ይጥለቀለቃል። ይህ ሲፈፀም፣ አሜሪካና መላው አለም የኢትዮጵያን ህዝብ የነፃነትና የዴሞክራሲ ጥያቄ ማዳመጥ ይጀምራል። 50 ሺህ ተቃዋሚ እንደ ግሪሳ ዋሽንግተንን ሲያንቀጠቅጣት በኢትዮጵያም በተመሳሳይ አመፁ ይፈነዳል። እናም አፋኙ የመለስ ስርአት በመጪዎቹ ስድስት ወራት፣ (ከመስከረም 2012 ወዲህ) የስልጣን እድሜው ያበቃለታል። ካውንስሉም የሽግግር ሂደቱን ተረክቦ ቀጣዩን የምርጫ ስርአት ይዘረጋል።

መቸም ፍሰሃ እሸቱ በቃል እንዲህ ቀለል አድርጎ እንደተነተነው በተግባር መፈፀም ከቻለ፣ እሱ “ስልጣን አልፈልግም” ቢልም የኢትዮጵያ ህዝብ፣ አስገድዶ የጠቅላይ ሚኒስትርነቷን ወንበር ያስረክበዋል።  እንግዲህ በቅርቡ ደግሞ “ከፍሰሃ ጀርባ እነ አጅሬዎቹ አሉ”  የሚል ሹክሹክታ ያነበብኩ ይመስለኛል። ከሆነ በርግጥ ሊሳካለት ይችል ይሆናል። የሆነው ሆኖ ፍሰሃ ራሱን ከወደፊት እጩ መሪዎች አንዱ አድርጎ ፈጥሮአል…

ብርሃኑና አንዳርጋቸው…?

ብርሃኑ ነጋ እና ግንቦት 7 የስልጣን ፍላጎት እንደሌላቸው ገና ከመነሻው ግልፅ አድርገዋል። ይህን አባባል ግን ተቀብዬው አላውቅም። በፕሮግራማቸው መሰረት ትግሉን መርተው ድል ማድረጉ ከተሳካላቸው በወደፊቱ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሳይወዳደሩ ዳር ላይ ይቆማሉ ተብሎ አይታሰብም። እንደምናየው የተከተሉት የትግል አቅጣጫ ፈተና የበዛበት ሳይሆን አልቀረም። እንደ ድመት 9 ነፍስ ያላቸው ይመስል፣ የሞት ፍርድ ሜዳሊያ ተሸክመዋል። ከወያኔ እስርቤት የተከተቱ ብዙ አባላት አላቸው። በተግባርም ሆነ በፕሮፓጋንዳው ወያኔን በብርቱ እየተፈታተኑት ነው። የትጥቅ ትግል የሚከተሉ እንደመሆናቸው፣ ምን እየሰሩ እንዳሉ ማወቅ አይቻልም። ብዙውን ጊዜ ምን እየሰሩ እንዳሉ የሚነግረን ወያኔ ነው። “ሊገሉኝ ነበር – ያዝኳቸው! ሊያፈነዱ ነበር – አከሸፍኩት!” ይለናል። ከከማል – ኦነግ፣ ከአፋርና ከህብረብሄራዊ ድርጅቶች ጋር የጋራ ግብ ነድፈው በመጓዝ ላይ ናቸው። በመሆኑም ብርሃኑ እና አንዳርጋቸውም መጪዋን ኢትዮጵያ ለመረከብ አማራጭ ሆነው ይታያሉ…

አረጋዊና ግደይ…?

አረጋዊና ግደይ ህወሃትን መስርተው ሲያበቁ ከህወሃት ተባረሩ የፖለቲካ ሰዎች ናቸው። ስለሁለቱ ሰዎች ሳስብ በሚዲያ ብቻ ከሚያደርጉት አስተዋፅኦ ባሻገር፣ ለምን ወደ መሬት ወርደው እንደማይንቀሳቀሱ አላውቅም። “ደሚት” በሚል ስም የሚጠሩትን የትግራይ አማፅያን ለምን ማግኘት እንደማይፈልጉም አይገባኝም። በተጧጧፈው ትግል ውስጥ ሙሉ ተሳታፊ ሆነው አይሰሙኝም። ምርጫ ሲደርስ ብቅ ይላሉ። መልሰው ደግሞ እልም ይላሉ። አረጋዊ በርሄ መለስ እና ስብሃትን የሚተችበት እድል ካገኘ ብቅ ይላል። በተረፈ ብዙም የለም። ስርአቱን የሚያውቁት እንደመሆኑ ብዙ ማገዝ በቻሉ ነበር። ምናልባት አቻችለው መጓዝ ይፈልጉ ይሆናል። ግንባር መስመሩ ላይ አሉ ማለት ግን አይቻልም። ስለዚህ የትም የሉም…

ነጋሶ – በየነ- መረራ….?

በየነና መረራ ሸክማቸውን ስዬ አብርሃ ላይ ጭነው እረፍት የፈለጉ መስለው ታይተዋል። በየነ ጴጥሮስ ፕሬዚዳንት ግርማን ለመተካት ሞክሮ ከከሸፈበት ወዲህ ተስፋ ቆርጦአል። መረራ በንግግሩ ለወያኔ ጩቤ ቢሆንባቸውም፣ አሁን አሁን የአፍእላፊ ክሱን በመስጋት ቃላት በመምረጥ ሲጨናነቅ ይታያል። በፍርሃት ማሰሮ ውስጥ ተጨረማምቶ መቀመጥ ግዴታው የሆነ ፖለቲከኛ ምን አይነት ትግል ማድረግ ይቻለዋል? በርግጥ ጊዮርጊስ ከፈቀደ ሁለቱ አንጋፋዎች ወደፊት ሚኒስትር የመሆን እድል ይኖራቸው ይሆናል። መለስን ይተካሉ ብሎ የሚጠብቅ ግን ያለ አይመስልም።

ነጋሶ የዋህ ናቸው። የቅርብ የትግል ጓዳቸው አንዷለም አራጌ ታስሮ በጡጫና በእርግጫ ሲደበደብ እሳቸው፣ “በአንቀፅ 22 መሰረት..” የሚል አረፍተ ነገር ያለበት መግለጫ ሰጡ። ኢትዮጵያ ላይ ምን አንቀፅ አለ? ሌላው ቀርቶ አንቀፅ 39 እንኳ፣ ለህወሃት ስትራቴጂአዊ ፍላጎት ብቻ ተብሎ የገባ ነው። ዶክተር ነጋሶ አንቀፅ 22ን ከሚጠቅሱ፣ የብሉይ ኪዳን ህግን ቢጠቅሱ በተሻለ ነበር። ማለትም፣ “ለእርግጫ – እርግጫ! ለጡጫ – ጡጫ!” የሚለውን። ነጋሶ የወያኔን ህገመንግስት ያረቀቁት ከልባቸው ስለነበር፣ አሁንም ህጉ በስራ ላይ ያለ ይመስላቸዋል። ነጋሶ ይህን ያህል ዘመን ከህወሃት ጋር አብረው ሰርተው፣ የህወሃትን አንጎልና ልብ አለማወቃቸውን ሳስበው ግርም ይለኛል። የሆነው ሆኖ ነጋሶ ጊዳዳ ኢትዮጵያን ከመምራት አንፃር አማራጭ ናቸው ብዬ አላስብም።  ታሪክ ግን፣ “ሰላምተኛ እና ጥሩ ሰው ነበሩ” በሚል ያስታውሳቸው ይሆናል።

ታማኝ በየነ…?

ታማኝ ኮሜዲያን በነበረበት ጊዜ በጣም ያስቀን ነበር። ከመነሻውም ግን ቀልዶቹ ፖለቲካ የተርከፈከፈባቸው ነበሩ። በተፈጥሮው በነፃነት የመናገር ተሰጥኦ ስላለው በዘመነ ደርግም ቢሆን፣ ከሌሎች ይልቅ ልቆ ደፍሮ ፖለቲካውን ይነካካ ነበር። ፖለቲካ በቀልድ ሲቀርብ አጥንት ይሰብራል። እንደ ታማኝ ፖለቲካዊ ኩመካ ቢሆን የወያኔ አጥንቶች ከመሰባበር አልፈው ዱቄት መሆን ነበረባቸው። ታማኝ ኩመካውን በመተው ወደ ፖለቲካው ከገባ ወዲህ ብዙ ፈተናዎች ገጥመውታል። አንዳንድ ወዳጆቹ ጠጋ ብለው፣ “ታማኝ! ፖለቲካውን ትተህ ወደ ሙያህ ብትመለስ ይሻልሃል። የሚያምርብህ ኩምክናው ነው” ብለውታል። አንድ ዘመዱ ደግሞ፣ “…ስትናገር አዝማሪ ነኝ ትላለህ። እኛ በዘራችን አዝማሪነት የለብንም። ለምን ስማችንን ታጠፋለህ?” ሲል ጠይቆታል። ቀልድ ሊሆን ይችላል። “ፕሮፌሰርና ዶክተር መውቀስ ታበዛለህ” እያሉ የሚተቹት የመኖራቸውን ያህል፣ “ፕሮፌሰርና ዶክተር ከሚባሉት አንተ ትሻላለህ።” እስከማለት የሚሄዱም አሉ። ደግነቱ ታማኝ በትችቱም ሆነ በሙገሳው የሚሞቀውም ሆነ የሚበርደው አይነት አይመስልም። ባለ አዞ ቆዳ ነው። እንደልቡ ይናገራል። ጠላቶቹም ወዳጆቹም ጓጉተው ያዳምጡታል። “የኔ እውነቶች” የሚለው አባባል አለው። በርግጥ አስቦ ከሚናገረው ይልቅ፣ በስሜት ከልቡ የሚያፈልቀው ይበልጥ ሳቢ ነው። የታማኝ ፈተና የወያኔ ውግዘትና የጥራዝ ነጠቆች ትችት ብቻ አይደለም። ቱባ የሚባሉ ሰዎችን በፖለቲካው ለማነሳሳት በሚያደርገው ጥረት ብዙ ፈተና ይገጥመዋል። ታማኝ ቀረብ እያለ ወደ ስብሰባ ወይም ወደ ተቃውሞ ሰልፍ እንዲወጡ ሲጠይቃቸው እንዲህ የሚል ምላሽ የሚሰጡት አሉ፣ “አዲሳባ ላይ ቤት መስራት ጀምሬያለሁ። በቪዲዮ የምታይ ከሆነ አስቸጋሪ ነው። ሊተናኮሉኝ ይችላሉ። በአሳብ ግን አብሬያችሁ ነኝ። ለማንኛውም ሞት ለወያኔ!” ሌሎች ደግሞ፣  “ምን መሰለህ ታማኝ!? በዚህ ገፈርሳ አካባቢ መሬት ወስጃለሁ። ለዶሮ እርባታ ነው ያሰብኳት። አጥሯን አጥሬ እስክጨርስ ገለል ማለት ይሻላል። የምትሰሩትን ግን እደግፋለሁ። በርቱ! ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!” በርግማን ወያኔ የሞሞት ቢሆን ኖሮ ቀብሩ ገና ድሮ በተፈፀመ። በምርቃት ኢትዮጵያ ለዘልአለም መኖር ብትችልም ይህ ሁሉ ድካም ባላስፈለገ። መቼም እንዲህ ካሉ ፎጋሪዎች ጋር ተባብሮ ወያኔን ማስወገድ ህልም ነው። ታማኝ እንዲህ ባሉ ሰዎች ተከቦ፣ መንፈሱ ባለመርገቡ አደንቀዋለሁ፣ አዝንለታለሁም። በርግጥ ታማኝ ‘ፖለቲከኛ ነኝ’ ብሎ አያውቅም። ርግማን ሆኖብን እንጂ ታማኝ ጊዜውን በፖለቲካ ጉዳይ ማባከን አልነበረበትም። ይቺ “የተረገመች” አገር ተሳክቶላት የሰው ልጅ እንደ ሰው የሚከበርባት አገር ለመሆን ከበቃች ግን፣ መጪው ትውልድ ታማኝን ወደ ነፃነት በሚያመራው መንገድ ላይ እንደ መንገድ ጠራጊ ያስታውሰው ይሆናል…

ዳውድ እና ዱጋሳ…?

የዳውድ ኢብሳና የዱጋሳ በከኮን ኦነግ በሩቅ አጣምሮም ሆነ ለያይቶ ማየት ይቻል ይሆናል። ልዩነታቸውን አቻችለው የቀድሞውን ጠንካራ ኦነግ ወደ ነበረበት ለመመለስ እየሰሩ መሆኑ ይሰማል። የሽማግሎዎችና የወጣት ኦሮሞዎች ግፊት አለበት። “የአንድነት ሃይሎች” ዳውድ ኢብሳን አክራሪ ይሉታል። ለረጅም ጊዜ የኦነግ ሰራዊት ኮማንደር የነበረውን ዱጋሳ በከኮን ቢያውቁት ኖሮ ግን ዳውድን ያመሰግኑት ነበር። ዞሮ ዞሮ ይህ ነባሩ የኦነግ ሃይል እንደገና ተሰብስቦ፣ አንድ ሃይል መፍጠር ከቻለ በቀጣይዋ ኢትዮጵያ ላይ ተፅእኖ የማሳደር አቅሙ ቀላል አይሆንም። ባለፉት 20 አመታት ከቋንቋ እና ኦሮሚያን ክልል ከመመስረት አንፃር የተሰሩ በጎ ስራዎች በኦነግ ግፊት የተፈፀሙ ናቸው። በመሆኑም የኦሮሞ ህዝብ ስነልቦና ከኦነግ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። ከመለስ ስልጣን መልቀቅ ጋር ተያይዞ የኦሮሞ ህዝብ በኦነግ ዙሪያ ሊሰለፍ መቻሉን ማስቀረት የሚቻል አይመስልም። እናም ዳውድና ዱጋሳን በአእምሮ ውስጥ መያዙ የግድ ይላል።

ሃይለማርያም ደሳለኝ….?

 

ሌላው አማራጭ ራሱ ወያኔ ነው። ኢትዮጵያ የተባለችው አገር በመለስ ዜናዊ እጅ ላይ ያለች አገር እንደመሆኗ ወያኔ፣ “ጥፋ ከዚህ” የሚባልና በቀላሉ የሚገፈተር ሃይል አይደለም። ስልጣን፣ ጠመንጃ፣ ገንዘብና ተንኮል የታጠቀ አደገኛ ሃይል ነው። መለስ እስከ 2015 የአባይ ግድብን በማጠናቀቅ፣ የአዲስአበባን የከተማ ባቡር በማስመረቅ፣ የኑሮ ውድነቱን መቀነስና ኢኮኖሚውን ማረጋጋት ከቻልን እስከ 2030 ስልጣን በእጃችን ይሆናል” እያለ አባላቱን እየሰበከ ይገኛል። በግልባጩ ህወሃት ውስጥ ውስጡን ያልተረጋጋና በቋፍ ላይ ያለ ቡድን መሆኑን ማመን አይፈልግም። የኢኮኖሚ እድገት ቢኖር እንኳ፣ የመብትና የነፃነትን መገፈፍን ሊተካ አይችልም። የሰው ልጅ ለክብሩ እንጂ ለሆዱ አይኖርም። መለስ የመብትና ዴሞክራሲ ጥያቄውን ዘግቶ ሃይለማርያምን በሞግዚትነት ለማንገስ ተዘጋጅቶአል። “ይህን ከማድረግ ሊያስቆመን የሚችል ሃይል የለም” ብሎም ያምናል። በርትተው ሊቃወሙ የሚችሉትን ግለሰቦች ሁሉ በካሮትና ዱላ ስልት ለመቆጣጠር ሙከራውን ቀጥሎአል። እንግዲህ የመለስ የመጀመሪያ ምርጫ ሃይለማርያም ሊሆን ቢችልም፣ ሃይሌ በእግሩ መቆም አቅቶት እንዳይንገዳገድ እነ ደብረፅዮንና ቴዎድሮስ አድሃኖም ታኮ ሆነው ያገለግሉታል። እስከ 2030? ምን ችግር አለው? ህልም ማለም አይከለከልም…

ያልታወቁ ወጣቶች….?

የመለስ ዜናዊን ስልጣን ሊረከቡ የሚችሉ ወጣቶች ወደፊት እየመጡ ይሆን? በቅንጅት የብርቱካን አብዮት ወቅት፣ ትንታግ የነበሩ ወጣቶች አበባማው አብዮቱ ከከሸፈ በሁዋላ አብዛኞቹ ተሰደዋል። የኦነግ ወጣት አባላትም እንዲሁ መሪዎቻቸውን ተከትለው ኮብልለዋል። ህዝብ ግን በርግጥ ተስፋ አይቆርጥም። እንደገና አምጦ ታጋዮችን ይወልዳል። ማን ያውቃል? ገና ያላወቅናቸው የአገር ተስፋዎች ይኖሩ ይሆናል። ምናልባት በኢህአዴግ መዋቅር ውስጥ ያደፈጡ ሊሆኑ ይችላሉ። ምናልባት ደግሞ በሰራዊቱ ውስጥ ያሉ መስመራዊ መኮንኖች! ምናልባት በአንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ ሶስት ሆነው የሚመካከሩ ሻለቆችና ሻምበሎች ይኖሩ ይሆን? እነዚህ ያልታወቁ ወጣቶች ከቶ እነማናቸው? ምናልባት ከትግራይ ይነሱ ይሆን?

በመጨረሻ….?

በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሰላማዊ ፖለቲከኞች ምንም ማድረግ እንደማይችሉ በተደጋጋሚ የታየ ቢሆንም፣ ዞሮ ዞሮ ትግሉ መካሄድ ያለበት ከውስጥ መሆኑ ይታመናል። ርግጥ ነው፣ ልክ እኔ እንደማደርገው እንዲህ ደጅ ሆኖ መለፍለፍ ቀላል ነው። በቀለ ገርባ፣ እስክንድርና አንዷለም ጫማ ውስጥ መግባት ግን እጅግ ከባድ ሊሆን ይችላል። እየወደቁ ወደፊት ከመግፋት በቀር ግን ምርጫ የለም። ያም ሆኖ የእርቅ መንፈስ አስፈላጊነት መቼም ቢሆን ጊዜው አያልፍበትም። ከ50 አመታት በሁዋላ አሁን ስለፖለቲካ የምናወጋው አንዳችንም በህይወት አንኖርም። ተጠራርተንና ተጠራርገን እንወገዳለን። ምን ይሆን ለቀጣዩ ትውልድ ትተንለት የምናልፈው? ቂምና ጥላቻ? የማያባራ ጦርነት? ቅጥፈትና ሌብነት? ሃሜትና ቡጨቃ? ከቶ ምን ይሆን? በመጨረሻ ከተጠቀሱትና ካልተጠቀሱት መካከል “በቀጣይ ኢትዮጵያን የሚመራት ማነው?” የሚለው ጥያቄ በርግጥ አሁንም አልተመለሰም። ሆኖም “የነገው ቀን” በፍጥነት ወደ እኛ እየገሰገሰ ስለሆነ፣ መለስን ማን እንደሚተካ በቅርቡ እናውቀው ይሆናል…

ወያኔ ተጨናንቆአል?

Friday, March 30th, 2012

ርግጥ ነው ሰሞኑን ወያኔ በጣም ተጨናንቆአል።

ለአመፅ እርሾ ሊሆኑ በሚችሉ ቁጣዎች ተከበዋል። የሶማሊያ ተልእኮ እየከሸፈ ነው። አልሸባብ እያሸመቀ ደጋግሞ አደጋ መጣሉን በመቀጠሉ፣ ከዚህ በላይ ሶማሊያ መቆየት እንደማይችሉ ተረድተው ጓዛቸውን መሸከፍ ይዘዋል። ከኤርትራ ጋር የጀመሩት የጦርነት ድራማ፣ ላይ ላዩን ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ እንደሚያውሉት አለመሆኑ ተባኖበታል። የውስጥ ቀውሱ ተባብሶአል። የመምህራን አመፅ ወዴት እንደሚያመራ አልታወቀም። ቢታፈንም መልኩን ቀይሮ መከሰቱ የማይቀር ነው። የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንን ነባር ቅርሶች የማውደሙ ሴራ አማኙን ህዝብ ያሸማቀቀና ያስደነገጠ ሆኖአል። ገና አልተቋጨም። ከደቡብ ክልል የተፈናቀሉት አማሮች ጉዳይ፣ ሊታፈን ባለመቻሉ ፈንድቶ ወጥቶአል። የኑሮ ውድነቱና የዋጋ ግሽበቱንም ሊቆጣጠሩት አልቻሉም። ሙስናው ጣራ ነክቶአል። ስርቆቱ፣ “ተከተል አለቃህን” የሚል ስያሜ አጊኝቷል። የህወሃት ወገኖች የቅንጦት ህይወት ይሉኝታ አጥቶአል። እና በዙሪያቸው ያለውን የተቆጣ የህዝብ አይን ለማፈን መጨነቃቸውን ማስተዋል ይቻላል። አፈና ግን መፍትሄ ሊሆን አይችልም።

ምርጫው አንድ ብቻ ነው። ከራስ ጋር እና ከእውነታው ጋር መታረቅ!

(“የቅዳሜ ማስታወሻ” እስከ ትናንት ኢትዮጵያ ላይ ይጎበኝ ነበር። ዛሬ ማለዳ ስመለከት ግን “ኢትዮጵያ” በሚለው ስር ምንም አያሳይም። በፌስቡክ በኩል የኢትዮጵያ አንባቢዎቼን ጠይቄ፣ ከዛሬ ማለዳ ጀምሮ የእኔና የአቤ ቶክቻው ብሎጎች መዘጋታቸውን አረጋግጠውልኛል። በርግጥ ደብረፅዮን ብሎግ እያሳደደ መዝጋት ከጀመረ ስራ በዝቶበታል ማለት ነው።)

መለስ ዜናዊ ከሞት እንዴት እንዳመለጠ … ተስፋዬ ገብረአብ

Monday, March 5th, 2012

ከተስፋዬ ገብረአብ

ትረካውን ጥቂት አሰማምሬው ይሆናል እንጂ ይህ የምገልፅላችሁ ታሪክ በትክክል የተፈፀመ ነው። ታሪኩን ካጫወተኝ ሰው ጋር ስናወራ፣
“ልፃፈው?” ስል ጠየቅሁት።
ሳቀ! በጣም ሳቀ! እና ፈቀደልኝ።
“ፃፈው! ድክመታችንን ያሳያል …” አለ።

* * *

ባጭር ጊዜ ውስጥ የታቀደ ነበር። በረቀቀ ጥበብም ሁኔታዎች ተስተካክለዋል። የቀረ ነገር ቢኖር በእቅዱ መሰረት መለስ ዜናዊ ላይ አደጋውን የሚጥል ደፋር ሰው ማግኘት ብቻ ነበር። የማጥቃት እቅዱን ለመፈፀም የታሰበው በጦር መሳሪያ አልነበረም። በቡጢ ነበር። አንድ ሃይለኛ ቡጢ! በቃ!

ቦታው ብራስልስ ነው። የአውሮፓ ህብረት ስብሰባ ላይ መለስ እንደሚገኝ ተረጋግጦአል። መረጃው አስተማማኝ ነበር። ለማስተማመኑ ማረጋገጫው መለስ ዜናዊ የሚቀመጥባት መቀመጫ ጭምር መታወቋ ነበር። የሆነው ሆኖ መለስ ላይ አደጋውን የሚጥል ሰው ለማግኘት ጥቂት ሰአታት ወስዶአል። ደግነቱ ከእቅዱ አዘጋጆች አንዱ፣

“እኔ እፈፅመዋለሁ! ደህና ቡጢ አቀምሰዋለሁ፣ ወይም አሰንብተዋለሁ!” አለ።

የዚህን ሰው እውነተኛ ስም መግለፅ አልፈልግም። ለትረካው እንዲያመቸኝ ግን ሙላቱ ብዬዋለሁ። ባጭሩ ደግሞ “ሙሌ!” እንለዋለን። እና ይህን ተግባር ለመፈፀም ሙሌ ሃላፊነቱን ወሰደ።

እነሆ! ዝግጅቱ ተጠናቆአል። ሙሌ ወደ ስብሰባ አዳራሹ ጋዜጠኛ ሆኖ ይገባ ዘንድ የመግቢያ ወረቀት አጊኝቶአል። ካሜራ አንገቱ ላይ አንጠለጠለ። ግንባሩን ቋጠረ። ሙሌ ረጅም ሲሆን፣ እጁ ረጅምና እንደ ወይራ ጥምዝዝ ያለ ነበር። ከአዘጋጆቹ አንዱ መከረው፣

“ሙሉ ሃይልህን አታሳርፍበት። ዋናው መልእክታችንን ማስተላለፍ ነው” አለው።

ሙሌ በዚህ አልተስማማም።

“ከሰነዝርኩማ እጠረምሰዋለሁ። ነካክቶ መተው አላውቅበትም”

ርግጥ ነው፣ መለስን አንድ ጥሩ ቡጢ ማቅመስ አለምን የሚያዳርስ ዜና ይሆናል። በተለይ ደግሞ መለስ ዜናዊ በየእስርቤቱ የሚያስደበድባቸው የዴሞክራሲ ታጋዮች፣ የሚደርስባቸውን ህመም እሱም እንዲቀምሰው ከተደረገ ሊሰማው ይችላል። ካልቀመሰው እንዴት ሊሰማው ይችላል?

የስብሰባው ሰአት እየተቃረበ በሄደ መጠን የሙላቱ ቁጣ እየጨመረ ሄደ። መለስ ይቀመጣል ተብሎ የተገመተበትን ቦታ በካርታ ጭምር ሲያጠና ቡጢውን እንደጨበጠ ነበር። እንባው ኮለል ብሎ ሳይወርድም አልቀረም። እንዲህ ያሉ እንባዎች ከቁጭት ኩሬ የሚፈልቁ ናቸው።

የመጨረሻዋ ሰአት እንደተቃረበች ሙሌ፣

“ይህን ታሪካዊ ድርጊት የምፈፅመው እንደ ልደቱ አያሌው ባንዴራ ለብሼ መሆን አለበት” የሚል አሳብ አቀረበ። ይህ ግን ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ። ስሜታዊ መሆን እንደማይገባ ተነገረው። ተራ ጋዜጠኛ ሆኖ፣ በስልት ወደ መለስ ዜናዊ መጠጋት እንዳለበትም ተመከረ። ለማንኛውም በሚል ሙሌ በተደጋጋሚና በልዩ ልዩ ቅርፅ ፎቶ እንደዲነሳ ተደረገ….

የስብሰባው ሰአት ደረሰ። መሪዎች ገቡ። ጋዜጠኞችም ወደ ውስጥ ጎረፉ። ሙሌም እንደማንኛው ተራ ጋዜጠኛ ተቀላቅሎ ወደ ውስጥ ዘለቀ። ከስብሰባው ውጭ ያሉ ጋዜጠኞች ጊዜ ለመቆጠብ ለዜናው የሚሆኑ አንዳንድ ነጥቦችን በቁራጭ ወረቀት ላይ መያዝ ጀማመሩ፣

“… በመለስ ዜናዊ አገዛዝ የተበሳጨ አንድ ጋዜጠኛ የመለስ ዜናዊን ሁለት ከንፈሮች በቡጢ አነደደ!”

“… መለስ ዜናዊ የቡጢን ህመም ቀመሰ! በሆስፒታል እርዳታ እየተደረገለት ሲሆን ለህይወቱ ሳያሰጋው አይቀርም።”

“… የአይን ምስክሮች እንደገለፁት የሙላቱ ቀኝ እጅ የመለስ ከንፈሮች ላይ ባረፉባት ደቂቃ፣ ‘ጧ!’ የሚል የፍንዳታ ድምፅ ተሰምቷል።”

“… ከሃኪሞች የሾለከ ዜና እንደሚገልፀው የመለስ ከንፈር ከባድ የመተርተር አደጋ ደርሶበታል።”

“… የቤልጂየም ሃኪሞች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እርዳታ እያደረጉለት ነው”

“… የመለስ ጥርሶች አለመጎዳታቸው ታወቀ! ዝርዝሩን እንደደደረሰን እንገልፃለን…”

እደጅ የነበሩት የእቅዱ አዘጋጆች ውጤቱን ለመስማት በጥፍራቸው ቆመው እየጠበቁ ነበር። ትንፋሽ አጥሯቸው በመጠባበቅ ላይ ሳሉም ሙሌ ካሜራውን እንዳንጠለጠለ ተመልሶ ብቅ አለ፣

“ምነው?” ሲሉ ጠየቁት።
በረጅሙ ተነፈሰ።
“አጣኸው እንዴ?”
“ማየትማ አይቼዋለሁ።”
“እና ታዲያ ለምን አልመታኸውም?”

“ፎቶ የማነሳው በመምሰል ስጠጋው፣ እሱም ልመታው እንዳሰብኩ ገባው መሰለኝ ፍርሃቱን አይኖቹ ውስጥ አየሁ። ልመታው እችል ነበር። አጠገቡ ነበርኩ…”

በከበቡት ሰዎች ዙሪያ ጥልቅ ዝምታ ወደቀ። ቃል የሚተነፍስ ጠፋ። በዚህ ጊዜ ሙሌ እንዲህ ሲል ፀጥታውን ሰበረው፣

“ፎቶግራፍ ግን አንስቼዋለሁ። ካላመናችሁኝ ላሳያችሁ እችላለሁ!”

የሃውልት ጉዳይ (ከተስፋዬ ገብረአብ)

Monday, June 27th, 2011

ሰሞኑን “አዲስ ነገር – ድረገፅ” የለጠፋቸውን የዜና ጭማቂዎች ሳነብ ትኩረት የሚስብ ርእስ ገጠመኝ። ይህም ካርል ሄንዝ ለተባሉ ጀርመናዊ አዲሳባ ላይ ሃውልት ሊቆምላቸው የመወሰኑ ዜና ነበር።

ለመሆኑ እኒህ ሰው ማናቸው? ማነው የወሰነላቸው? በምን መለኪያ? ከማን ጋር ተወዳድረው? ለኢትዮጵያ ምን በጎ ቢሰሩ ይሆን፣ ለሃውልት የበቁት? የሚታወቅ ዝርዝር ነገር የለም።

ታሪካቸውን ለማንበብ ስሞክር፣ “ሰዎች ለሰዎች” የተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅት መስርተው ብዙ ሰዎችን ህይወት ለውጠዋል ተባለ። የሰሩት መልካም ነው። ግን በመንግስት ደረጃ “እግዚአብሄር ይስጥልን” ቢባሉ አይበቃም?

በርግጥ መለስ ዜናዊ በጣም ያደንቃቸዋል። በመሆኑም ከሳር ቤት ወደ መካኒሳ በሚወስደው መንገድ ላይ አንድ አደባባይ ሸለማቸው። አደባባዩ ላይ የሚቆምላቸውን ሃውልት የመሰረት ድንጋይ ለማኖር ኩማ ደመቅሳ መታዘዙም ተዘግቦአል።

እንግዲህ ሌላ ያመለጠኝ ዜና ከሌለ በቀር፣ ኢህአዴግ በ20 አመታት ውስጥ እንዲገነቡ ካፀደቃቸው ሃውልቶች ውስጥ የካርል ሄንዝ 5ኛ መሆኑ ነው። ቀደም ሲል፣ የጄኔራል ሃየሎም፣ የአቡነ ጳውሎስና የአሉላ አባነጋ የተገነቡ ሲሆን፣ የአፄ ዮሃንስ በግንባታ ላይ መሆኑ ተሰምቶአል። ከቀዳሚዎቹ አራት ሃውልቶች አከራካሪው የአቡነ ጳውሎስ ብቻ ነው። 5ኛው ካርል ሄንዝ የሚያከራክር ሳይሆን የሚያስተዛዝብ ነው።

ሃውልቶች የአካባቢውን ህዝብ ስነልቦና ግምት ውስጥ ማስገባት አለባቸው። ለምሳሌ መለስ ዜናዊ የራሱን ሃውልት አዲሳባ ላይ ሊተክል አይችልም። ለመትከል ከወሰነ 24 ሰአት በታንክና በመትረየስ ማስጠበቅ አለበት። በመሰረቱ ግን በሃገር ደረጃ ሃውልት የሚተከልለት ሰው ማን መሆን እንዳለበት ጥናት ማድረግ ጠቃሚ ይመስለኛል። መለስ ስለፈቀደ ብቻ የተተከለ ሃውልት፣ የአካባቢው ህዝብ ድጋፍ ከሌለው ውሃ እንዳጣ ችግኝ መድረቁ አይቀርም።

በቅን ልቦና እናስብ ከተባለ ካርል ሄንዝ ከበአሉ ግርማ እና ከአፄ ቴዎድሮስ በፊት ሃውልት እንዲሰራለት መወሰኑ ለኢትዮጵያ ህዝብ ስድብ ነው። ለነገሩ የጥበብ ሰዎቻችን የተረሱ ናቸው። ከበደ ሚካኤል ከፑሽኪንና ከቦድሌር የሚያንሱ አልነበሩም። ጥላሁን ገሰሰና ፀጋዬ ገብረመድህን ሃውልቱ ቢቀር የመንገድ እና የሙዝየም ስም እንኳ ቢሰጣቸው መልካም ነበር።

ወያኔ በነበርኩበት ዘመን፣ “መቱ” የተባለችው ከተማ በበአሉ ግርማ ስም እንድትሰየምና ከሞጆ እስከ ዱከም ያለው መሬት “መዳወላቡ” የተባለ ስም ተሰጥቶት የኦሮሚያ ዋና ከተማ ሆኖ እንዲታወጅ የሚጠቁም አሳብ እፎይታ ጋዜጣ ላይ ፅፌ ነበር። ስለበአሉ ግርማ ሃውልት ማንሳቴ፣ ኩማን በጣም እንዳበሳጨው ትዝ ይለኛል። በስልክ “መነሻህ ምንድነው?” ብሎ ሲጠይቀኝ፣ በአሉ ግርማ ለእውነት ሲል ህይወቱን ስለከፈለ ይገባዋል። መቱን የመረጥኩለት ስለተወለደባት ነው። በአናቱ ደግሞ በአሉ ግርማ ኦሮሞ ነው” አልኩት። የመጨረሻዋ ነጥብ የኩማን ቀልብ ከሳብኩ በሚል የጨመርኳት ነበረች። አልተሳካልኝም። ምክንያቱም የኩማ ጆሮ ከበላይ አካል የሚመጣን አሳብ ብቻ ነው የሚያዳምጠው። ይኸው አሁን ኩማ ለካርል ሄንዝ ሃውልት እንዲተክል ሲታዘዝ በደስታ መቀበሉን ሰማን። ርግጥ ነው፣ህዝቡ ተባብሮ ለበአሉ ግርማ ሃውልት ለመስራት ቢጠይቅ እንኳ፣ አዲሳባ ላይ አደባባይ እንደማይፈቀድ ግልፅ ነው። በአሉ ግርማ ለኤርትራ ህዝብም ውለታ የሰራ እንደመሆኑ፣ አስመራ – ፓራዲዞ የተባለው ሰፈር ላይ ሃውልት እንዲያቆምለት ሻእቢያን በደብዳቤ የመጠየቅ አሳብ አለኝ። ምክንያቱም መቃብሩ ያልታወቀው በአሉ ሃውልት ሊኖረው የግድ ይላል። ወጣቶች የበአሉ ግርማን ሃውልት ሲመለከቱ፣ የመንፈስ ብርታት እንደሚያገኙ ምንም ጥያቄ የለውም። በርግጥም በዚያ በጨለማው ዘመን በአሉ ግርማ ጭል ጭል የምትል የሻማ ብርሃን ነበር። የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ጉዳይ ወዴት እያመራ እንደሆነ ማየትና ያየውን መናገር የቻለው፣ ሻእቢያ ገና ናቅፋ ተራራ ላይ ሳለ መሆኑ ሲታሰብ በአሉ ነቢይ ነበር ያሰኛል።

ከ15 አመታት በፊት “እፍታ” በተባሉ የመፃህፍት ቅፆች ላይ ይህንኑ የሃውልት ጉዳይ አንስቼ በጠነከሩ ቃላት መተቸቴን አስታውሳለሁ። ለመጪው ትውልድ አርአያ ሊሆኑ ለሚችሉ ሰዎች ሃውልት ለማቆም የሚወሰነው በምን መለኪያ ነው?

የግጭት ሰበብ መፍጠሪያ ፈንጂ ለመቅበር ካልሆነ በቀር፣ የአቡነ ጳውሎስ ሃውልት አስፈላጊ አልነበረም። ሃውልት የሚተከልለት ሰው አበባ ሲቀመጥለት ነው የምናውቀው። በዚህ ዘመን “በሽብርተኞች” እንዳይመታ ጥበቃ የሚደረግለት ሃውልት ቢኖር የአቡነ ጳውሎስ ሳይሆን አይቀርም። ወደፊት የአቡነ ጳውሎስ ሃውልት መፍረሱ እንደማይቀር ወያኔ ያውቃል። ያን ጊዜ ግን፣ “አቡነ ጳውሎስ ትግሬ ስለሆኑ አማራዎች ሃውልቱን አፈረሱት” በሚል ሊቀሰቅስበት ይሞክር ይሆናል።

እየቆየ የሚፈነዳ ፈንጂ የሚባለው እንግዲህ እንዲህ ያለው ነው። ነገር ፍለጋ ካልሆነ፣ ሰውየው እንዲህ በህዝብ እንደተጠሉ እየታወቀ ሃውልታቸውን አዲሳባ መሃል መትከል ምን አመጣው? የልዩነት ሰበብ እንዲሆን?

በሺህ ዘመን ትውልድ ህያው የሚሆን ታሪክ ሰርተው ያለፉ፣ ሃውልታቸውን የተከሉት በሰው ልጅ መንፈስ ውስጥ ነው። በጎ ተግባር እንጂ ሃውልት ህያው አያደርግም። መለስም ቢሆን፣ በባከነ ሰአት ተጠቅሞ፣ ከእልህ ፖለቲካ ወጥቶ፣ አንድ ጎል ቢያስቆጥር በመትረየስ የማይጠበቅ ሃውልት መገንባት በቻለ ነበር። ለዚህ ግን የታደለ አይመስልም። ከህዝቡ ፍላጎት በተቃራኒው ጎዳና መጓዙን ቀጥሎበታል።

በመጨረሻ በአለም ፀሃይ ወዳጆ አንዲት የምወዳት ግጥም ልሰናበት፣

አክሱም ላሊበላን – የቀየሰ አእምሮ፣
ያነፀው አዋቂ – ዛሬ ቢኖር ኖሮ፣
ይወቀስ ይሰደብ – ይወገዝ ነበረ፣
እንኳን እሱ ሞቶ – ስራው ብቻ ቀረ።

ፀሃፊውን ለማግኘት፡ tgebreab@gmail.com———————————————————————

የመለስ “ጠንካራ” ጐን! (ከተስፋዬ ገብረአብ)

Wednesday, April 27th, 2011

ከተስፋዬ ገብረአብ

(pdf)

ከጥቂት ቀናት በፊት ‘ብዙ ወንድምአገኝ’ ከካናዳ ስልክ ደውላ እንዲህ ስትል ጠየቀችኝ፣
“ምነው ጠፋህ ታዲያ?”
መልስ ከመስጠቴ በፊት በግሳፄ እንዲህ ቀጠለች፣
“በአመት አንድ መፅሃፍ መፃፍ በቂ ይመስልሃል? ከሃገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ስለ ቀድሞ አለቆችህ አንድ ነገር ማለት አለብህ።”

ከአንጋፋዋ ጋዜጠኛ ጋር የስልክ ቆይታዬን ካበቃሁ በሁዋላ ኮምፕዩተሬ ላይ አዲስ ገፅ ገለጥሁና፣ “የመለስ ደካማ ጎን!” የሚል ርእስ አሰፈርኩ።
የለም! የለም!

ስለ መለስ ደካማ ጎኖች ብዙ ተብሎአል። አል – ማርያምን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የፖለቲካ ጉዳይ ተንታኞች የመለስንም ሆነ የቡድኑን ደካማ ጎኖች በበቂ ተንትነዋል። ኦባንግ ሜቶ፣ ገላሳ ድልቦ፣ ብርሃኑ ነጋ፣ አረጋዊ በርሄ፣ ጌታቸው ጂጂ፣ ፈቃደ ሸዋቀና፣ መስፍን ወልደማርያም፣ ግደይ ዘርአፅዮን፣ ሌንጮ ለታ፣ አንዳርጋቸው ፅጌ፣ አሰፋ ጫቦ፣ እስክንድር ነጋ፣ ወንድሙ መኮንን እና ሌሎችም በመፅሃፍና በመጣጥፍ መለስን ገለባብጠው አሳይተውናል። ገና ወደፊትም ብዙ እናነባለን። በዚህ መጣጥፍ መለስ ላለፉት 20 አመታት ስልጣን ላይ ለመቆየት የተጠቀመበትን የአመራር ጥበብ ምስጢር እና ጠንካራ ጎኑን በጨረፍታ ለመነካካት እሻለሁ። እና ርእሱን ለወጥኩት።

* * *

የአንድን ግለሰብ ወይም ቡድን፣ “ጠንካራ ጐን” ወይም “ደካማ ጐን” ስንገልፅ እንደየአመለካከታችን ሊለያይ ስለሚችል ላንግባባ እንችላለን።

ለአብነት በኢህአዴግ ውስጥ አማራና ኦሮሞን የወከሉት አባዱላና አዲሱ በሕወሓት አለቆቻቸው ዘንድ እንዴት እንደሚታዩ ማየት ይቻላል።

በኢህአዴግ የፖሊት ቢሮ ግምገማ ላይ፣ የአባዱላ ገመዳ ጠንካራ ጐን፣ “ታማኝነቱ!” ደካማ ጎኑ ደግሞ፣ “የአቅም እጥረቱ!” እየተባለ ላለፉት 15 አመታት ሙሉ ሲነገር ነበር። በተገላቢጦሽ ሰፊው የኦህዴድ አባል አባዱላ ታማኝነቱን ቅድሚያ ለመለስ በማድረጉ ሲነቅፉት ቆይተዋል። በዚህ መካከል ‘አባዱላ ራሱን እንዴት ማየት እንዳለበት ተቸግሮአል’ የሚል ወግ እየሰማን ነው። በመለስ ቡድን የግምገማ መለኪያ፣ ‘ለህዝብ ታማኝ መሆን’ ደካማ ጎን ተብሎ እንደሚያስፈርጅ አባዱላ ከራሱ ልምድ ለመገንዘብ እድል አጊኝቷል። ከህዝብ በፊት ለድርጅትህ ታማኝ መሆን የኢህአዴግ ቀዳሚ መርህ ነው።

አዲሱ ለገሰ ከልቡም ሆነ ከጨጓራው ሕወሓትን ያፈቅራል። ለዚህ አፍቅሮቱ የተሰጠው ስያሜ፣ “ከትምክህተኛነት የፀዳ” የሚል ሲሆን፣ ይህም “የአዲሱ ለገሰ ጠንካራ ጎን” እየተባለ ለዘመናት እምቢልታ ሲነፋለት ኖሮአል። ጠንካራ የተባለው የአዲሱ ባህርይ እውነተኛ ስም፣ “አድርባይነት” እንደሚባል ግን መለስ በልቡ ያውቃል። ጮሌው መለስ መልስ በኪሱ ብቻ ሳይሆን፣ ሙያውን በልቡ የመያዝ ጠንካራ ጎንም አለው።

ለመነሻ ያህል የመለስን ሰብእና በጨረፍታ እንገምግም ከተባለ መለስ፣ “ለእውነት ሟች” ከሚባሉ ሰዎች ተርታ ሊመደብ አይችልም። በአንፃሩ አስመሳይ ነው። ኢህአዴግንም በተመሳሳይ በአስመሳዮች ሞልቶታል። ገና ደርግ ሳይወድቅ በማሌሊት ዘመን የተጣባውን ልማድ ዛሬም ድረስ ይዞት ዘልቆአል። ማሌሊት የተባለው ፓርቲ ድንገት ከምድረገፅ ከመሰወሩ በፊት እንዲሁ በአፈ ጮማዎች ተሞልቶ፣ “ክብሩ ይስፋ መድሃኔአለም! ማሌሊት ተወለደልን!” እያሉ የሚያመሰግኑ የዋህ ቄሶች ሳይቀሩ በአባልነት ተመልምለው ነበር።

መለስ ዜናዊ፣ “መጥፎም ይሁን ጥሩ አላማ ያለውን ሰው አከብራለሁ” ብሎ ሲናገር ሰምቼዋለሁ። ይሄ እውነት አይደለም። በድርጅቱ ውስጥ የሰበሰባቸው ካድሬዎች አብዛኞቹ አድርባዮች ናቸው። የአሁኖቹማ ብሶባቸው መለስ ሲናገር በማያስቀው ጭምር ህብረ – ማስካካቱን ተላምደውታል። ቀደም ያሉት የድል ማግስት ዋነኛ አማካሪዎችም ቢሆኑ፣ የጭንቅላታቸውን መናገር የማይችሉ ታዛዦች ነበሩ። ተቀዳ አለሙ ሊጠቀስ የሚችል ማሳያ ነው።

ተቀዳ ለ19 አመታት የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ሆኖ ሲሰራ የኢህአዴግ (ብአዴን) አባል ሆኖ አልተመዘገበም። በቅርቡ ስለዚሁ ጉዳይ ተጠይቆ ምላሽ ሲሰጥ በኢህአዴግ ስርአት ውስጥ የፓርቲው አባል ሳይኮንም ሃገርን ማገልገል እንደሚቻል ምስክርነት ሲሰጥ ሰምቼ በጣም ገርሞኛል። ይሄ ውሸት ነው። ኢህአዴግ አዲስአበባን ሲቆጣጠር የኢህአዴግ አባል ለመሆን ፈቃደኛ ከነበሩ ቀዳሚ ሰዎች ተቀዳ አንዱ ነበር። በወቅቱ ግን ‘የኢሰፓ አባላት ለኢህአዴግ አባልነት አይመለመሉም’ የሚል መመሪያ ወጥቶ ስለነበር፣ ተቀዳ በአባልነት ሳይመዘገብ እንዲቆይ ተወሰነ። መለስ እንደ ተቀዳ ያሉ ተጣጣፊ ሰብእና ያላቸውን ግለሰቦች በዙሪያው በማሰባሰቡ እሱ የሚያምንበትን ብቻ ማስፈፀም እንዲችል አድርጎታል። የተቀዳ መመፃደቅ ግን ከማስገመት ያለፈ ጥቅም አያስገኝም።

ሌላ ጊዜ ደግሞ መለስ “ጉረኛ ሰው አልወድም” ብሎ ሲናገር ሰማሁት። ይሄም ውሸት ነው። መለስ እራሱ የለየለት ቡፋ ነው። ቡፋነቱን የሚያሳዩ 101 አብነቶችን መደርደር ይቻላል።

ሩቅ ሳንሄድ በቅርቡ “የወር ደሞዜ 6400 ብር ነው” ብሎ ተናገረ። አያያዘናም እሱም እንደ ፋብሪካ ወዛደሮች የደሞዝ ጭማሪ እየጠበቀ መሆኑን አከለበት። የልብ ድካም ያለባቸው ሰዎች ይህን ቢሰሙ በብስጭት በዚያው ሊያመልጡ ይችላሉ። መለስ በ57 አመት እድሜው እንዲህ ያለ ጉራ አያምርበትም። ቢያንስ በአመት አንድ ሚሊዮን ብር የማይወራረድ ገንዘብ እንደሚበላ እናውቃለን። ይሄ ለ12 ወራት ተካፍሎ የወር ደሞዙ በአናቱ ሲታከልበት የመለስ የወር ደሞዝ 89 733 ብር ይመጣል። ይህ እንግዲህ በጥሬው የሚወስደው ነው። ለፕሮቶኮል መጠበቂያ ተብሎ የሚወጣው ሚሊዮናት ዶላር አይታሰብም። ለእሱና ለቤተሰቡ ህክምና፣ መዝናኛ እና የልጆች ትምህርት ቤት ክፍያ ሁሉ የሚፈፀመው ከደሞዙ ውጭ ከሃገሪቱ ጉሮሮ ነው። እንዲያው ሁሉም ነገር ይቅርና ባለፈው አመት ባለቤቱ አዜብ መስፍን ለመላ ቤተሰቧ የልብስ ወጪ 1.2 ሚሊዮን ዩሮ የከፈለችው ከየት አምጥታ ነው? ቤተመንግስት ውስጥ ዶላር የሚተፋ ዘንዶ ይኖራት ይሆን? ከዚህ ባሻገር የአዲሳባ ህዝብ ለአዜብ መስፍን፣ “የሙስና እናት” የሚል ቅፅል ስም እንደሰጣት መለስ ያውቃል ብዬ እገምታለሁ። “ህዝቡ ምናባቱ ያመጣል?” የሚል ንቀት አባይን ቀርቶ ተከዜን አያሻግርም። ስልጣን ሲበዛ ጭቆናና ዘረፋው እየበረታ እንደሚሄድ ከታሪክ የተማርነው እውነት ነው። ያም ሆኖ ዞሮ ዞሮ ግለሰቦች እንደ ጥላ አላፊ ናቸው። የሰው ልጅን አእምሮ እንዲደክም የሚያደርገው ፍርሃት ነውና፣ መሪዎችም ማለፋቸው ካልቀረ ከፍርሃት ነፃ የሆነ ትውልድ አፍርተው ቢያልፉ ይመረጣል።

* * *
ኢትዮጵያ በሶስት ሺህ አመታት ታሪኳ ከአድዋ መሪ ስታገኝ መለስ ዜናዊ ሁለተኛው መሆኑ ነው። የመጀመሪያው ከአድዋ የተገኘው መሪያችን ራስ ስሁል ሚካኤል ይባላል። ራስ ስሁል አፄ ኢዮአስን በሻሽ አንቆ ገድሎ የጎንደርን ስልጣን በእጁ ካስገባ በሁዋላ አቢሲንያን 40 አመታት እየረገጠ ገዝቶአል። እንደ አዲሱ ለገሰ እና አባዱላ ገመዳ ስሁል ሚካኤልም የጎንደርን አሻንጉሊት ባላባት ይሾምና ይሽር ነበር። ስሁል ሚካኤል በእጅጉ ጨካኝ ልብ ነበረው። ገድለ ታሪኩ እንደሚያወጋው ከሆነ፣ ስሁል በስተእርጅናው ዘመን አንድ ጊዜ ባላባቶችን ሰብስቦ እያናገረ ሳለ በመካከሉ እንቅልፍ ወሰደው። የጎንደር ባላባቶች እጅግ በጣም ይፈሩት ስለነበር ደፍሮ ከእንቅልፉ የሚቀሰቅሰው አልተገኘም። ስሁል ሚካኤል ጠረጴዛው ላይ እንቅልፉን ጠግቦ ሲነቃ ሚኒስትሮቹ በተቀመጡበት ሲቁለጨለጩ አገኛቸው። እናም እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፣ “ክቡራን! እስካሁን ስልጣን ላይ ነን እንዴ?”

የመጀመሪያው የህወሃት መሪ ገሰሰው አየለ፣ የበረሃ ስሙን “ስሁል” ሲል የመረጠው የቀዳማዊው ስሁል አድናቂ ስለነበር ነው ይባላል። መለስ ዜናዊም ይኸው በቀዳማዊው ስሁል የአገዛዝ ስልት የዘመናችንን ሰው እየረገጠ መግዛት ከጀመረ ሃያ አመት ደፈነ። የስልጣን ዘመኑን ከቀዳማዊው ስሁል ወይም ከቆንጆይቱ ዮዲት ጉዲት ጋር ለማስተካከል ሃያ አመታት ብቻ ይቀሩታል። በርግጥ በመጪው ምርጫ እንደማይወዳደር ነግሮናል። በየአመቱ መታለል ስለሰለቸን ግን አናምነውም። መለስ ስልጣኑን ቢለቅ እንኳ፣ ጥርሰ ፍንጭቱን ሃይለማርያምን ከላይ ቁጭ አድርጎ፣ እሱ እንደ ፑቲን ከጀርባ ሆኖ፣ ሃይሌን እንደ ሜድቬዴቭ አስቀምጦ በእጅ አዙር መምራቱ አይቀርም። ከ2010 በሁዋላ ተመልሶ እንደማይመጣም ቢሆን ዋስትና የለንም።

በ16ኛው ክፍለዘመን ጥጋበኛው አፄ ልብነድንግል፣ “ጦርነት ናፈቀኝ፣ ጦር አውርድ!” እያለ መሬቱን በጅራፍ ሲገርፍ እግዚአብሄር ተቆጥቶ ይማም አህመድ ግራኝን እንደላከለት ታሪካዊ ተረት ሰምተን ነበር። የዚህ ዘመን ሰዎች ግን ነቄ! ስለሆንን እንዲህ ያሉ ተረቶችን ማመን ትተናል።

እግዚአብሄር እጅ፣ እግር እና አእምሮ ሰጥቶን ሲያበቃ፣ የምድርን ሃላፊነት ለኛው እንደተወልን ተመራምረን ደርሰንበታል። በመሆኑም የምንፈልገውን ማድረግ የኛ ፈንታ ነው። የማንፈልገውን ከተቀበልንም የኛ ድክመት ነው። በተቀረ መለስ ዜናዊን እግዚአብሄር አላመጣብንም። ስለዚህ እግዚአብሄር ከስልጣኑ አያነሳውም። በግድም ሆነ በውድ መለስን የማስወገዱ ተግባር እኛው ላይ የተጣለ ሃላፊነት ነው። እኛ ገፍተን ካልወረወርነው መለስ ዜናዊ እንደ ስሁል ሚካኤል ገና በእንቅልፍ ልቡ ሳይቀር ይገዛናል።

መለስም ቢሆን ስልጣኑን እግዚአብሄር እንዳልሰጠው አሳምሮ ያውቃል። ለስልጣን የበቃው በጭንቅላቱ ተጠቅሞ እንደሆነ ስለሚያምን፣ ስልጣኑን ሳያስነካ ለማስጠበቅ የቤት ስራውን ተግቶ ከመስራት ቦዝኖ አያውቅም። በመሰረቱ መለስ በእግዚአብሄር መኖር አያምንም። ስለዚህ ‘ሰው መግደል ሃጢአት ነው’ ብሎ ሊያስብ አይችልም። ‘የሰው ልጅ ከሞተ በሁዋላ ለዘልአለሙ በዚያው ሞቶ ይቀራል እንጂ፣ ከሞት ተነስቶ ለፍርድ አይቀርብም’ ብሎ የሚያምን ሰው ደግሞ ከህሊና ጥያቄ ነፃ መሆኑን መዘንጋት አይገባም።

እንደ ቡልቻ ደመቅሳ ያሉ ፈሪሃ እግዚአብሄር ያላቸው የፖለቲካ ሰዎች ከመለስ ጋር የፖለቲካ ቁማር መጫወቱን የተቸገሩት በዚህ የአመለካከት መራራቅ ምክንያት ነው። ከበደ ብዙነሽ በተመሳሳይ ጃንሆይ ላይ በሸፈቱ ጊዜ የሚያምኗትን ታቦት አሳይተው ነበር የማረኳቸው። ቡልቻ በባህርይ ትሁትና ይሉኝታ ያላቸው የተማሩ ጨዋ ሰው ናቸው። መለስ በአንፃሩ የገዛ ሚኒስትሮቹን፣ “ወዲ ሸርሙጣ!” እያለ የሚሳደብ ስድ፣ ባለጌ እና በትግርኛ ‘ወዲሹቕ’ የሚባል አይነት ኡላ ነው። ቡልቻ ሰላማዊ ሰው መግደል ይቅርና የሰው ሬሳ በአይናቸው አይተው የሚያውቁ አይደሉም። የኛ ዘመን ሰላማዊ ትግል ታሪካዊ ተረትና ታሪካዊ ፉገራ ሆኖ የዘለቀው፣ የገዢው ፓርቲና የሰላማዊ ትግል ታጋዮች መንፈስ እንደ ገፈርሳ እና እንደ ጨፌዶንሳ በመራራቁ ነው።

ከሰላማዊ ትግል ባሻገር የመለስን የአገዛዝ ስርአት የሚታገሉ ሃይሎች ጠንቅቀው መገንዘብ ያለባቸው እውነትም መለስ ከቲማቲምና ከእንቁላል ውርወራዎች ባሻገር፣ እሳት የሚተፉ አይኖችን ማየት እንደሚሻ ነው። እራሱ እንደተናገረውም ጀርባውን በእሳት አስገርፎ ያገኘውን ስልጣን፣ ከቲማቲም ለተሰራ ፈንጂ ደንግጦ የማስረከብ ዝንባሌ የለውም። ስልጣኑን ከማስረከቡ በፊት ጀርባውን በጋለ ሰንሰለት የሚገሸልጠውን ተቃዋሚ ማየት ይፈልጋል። ካልሆነ ግን በ2020 ላይ ከእንቅልፉ ባንኖ ሲያበቃ፣ ባለቤቱን ጠርቶ፣

“አዜብ! እስኪ ጅራፍ አምጪልኝና መሬቱን እንግረፈው?” ማለቱ አይቀሬ ይሆናል።

* * *
መለስ ዜናዊ ሃያ አመታት በስልጣን መቆየት የቻለበት አንድ የማይካድ ጠንካራ ጎን አለው። ይህም የተቃዋሚዎችን ደካማ ጎን በትክክል ማወቁ እና ያንን ደካማ ጎናቸውን በአግባቡ ሊጠቀምበት መቻሉ ነው። መለስ የተቃዋሚዎችን ደካማ ጎን በትክክል ማወቅ በመቻሉ የማጥቃት ርምጃዎቹን እያነጣጠረ በመተኮስ ቤተመንግስታዊ ግቢውን እስካሁን ሳያስደፍር መቆየት ችሎአል። እሱ የሚመራውን ቡድን ስስ ብልት ሳያስነካ ለመጠበቅም ከፍተኛ እድል አጊኝቷል።

መንግስቱ ሃይለማርያምን ከመለስ ጋር ስናነፃፅረው መንግስቱ ስሜታዊ ብቻ ነበር። “የባህር በር” እና “የሃገር አንድነት” የተባሉ ግዙፍ አጀንዳዎችን ይዞ እንኳ ስልጣኑን መጠበቅ ሳይቻለው ቀረ። መንግስቱን ለውድቀት ካበቁ በርካታ ምክንያቶች አንዱ፣ በጠላቶቹ ላይ ያሳደረው ንቀት ነበር።

የተቃዋሚዎቹን እና የራሱን ልክ በትክክል የማያውቅ መሪ በመሳሪያ ሃይልም ሆነ በአላማው ቀናነት ብቻ ቆሞ ሊቆይ ከቶውንም አይቻለውም። ቅን አላማ ብቻውን የትም አያደርስም። የነፃነት ትግል ውጤት እንዲያመጣ ከተፈለገ፣ ታክቲክና ስትራቴጂ ከመንደፍ ባሻገር ድርጊትና መስዋእትነትን ይጠይቃል።

መለስ የህዝብ ድጋፍ የለውም። ይህ የተረጋገጠ እውነት ነው። የህዝብ ድጋፍ ከሌለው እንዴት እስካሁን ስልጣን ላይ ሊቆይ ቻለ? “በጠመንጃ ሃይል” የሚሉ አሉ። አምባገነን መንግስታት የታጠቁት ጠመንጃ በሁለተኛ ደረጃ ሊታይ የሚችል መሆኑን ግን የአረቡ አለም አብዮት አሳይቶናል። መለስ ለ20 አመታት ስልጣን ላይ መቆየት የቻለው ለቢሾፍቱ ቆሪጥ ነጭ ላም ስላረደለትም አይደለም። ምላሹ አንድ ነው። የተቃዋሚዎችን ደካማ ጎን በትክክል ስለተጠቀመበት ብቻ ነው።

አንዳንድ ሰዎች፣
“አናሳው ቡድን እንዴት ሰፊውን ህዝብ ተቆጣጥሮ መዝለቅ ቻለ?” ሲሉ ደጋግመው ይጠይቃሉ።

ሌሎች ደግሞ፣
“እንጦጦ ላይ ቆመን ሽንታችንን ብንሸና ወያኔ ተጠራርጎ ይጠፋል” ብለው ፅፈው አንብቤያለሁ።

የዘመናችን ችግር “አንድ ነገር መናገር” ሳይሆን “አንድ ነገር ማድረግ አለመቻል” ሆኖአል። “እንጦጦ ላይ ቆመህ መሽናት” የሚባለው ምሳሌያዊ ንግግር እንደ አባባል ሲመዘን በእውነቱ ወርቅ ነው። ከአባባል ካላለፈ ግን አመድ ነው። አመድ ሆነው የቀሩ በርካታ አባባሎች ሞልተውናል። “በቃ!!” የሚለው አዲስ መሪ ቃል አመድ ሆኖ እንዳይቀር የመለስን የአመራር ጥበብ ማወቅ ግድ ይላል። “የመለስ የአመራር ጥበብ የተቃዋሚዎችን ደካማ ጎን ማወቅ መቻሉ ነው” የሚለውን አባባል መደጋገሜ አለምክንያት አይደለም። ይህ ነጥብ በቅጡ ሊብራራ ይገባዋል ብዬ ስለማምን ነው።

ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ሲባል፣ “ወያኔ አልቆለታል” ብሎ መፃፍና መቀስቀስ ተገቢ ሊሆን ይችላል። ፖለቲከኛው ራሱ፣ እራሱ የፃፈውን ፕሮፓጋንዳ አምኖ፣ “እውነትም ወያኔ አልቆለታል” ብሎ ካመነ ግን “ታጥቦ ተተኩሶ – ለጭቃ!” እንደማለት ይሆናል። የራስን ፕሮፓጋንዳዊ አባባል ከማመን ባሻገር፣ የወያኔ የፕሮፓጋንዳ ሰለባ የመሆን ጉድለትም በስፋት ይታያል።

“መለስ ዜናዊ አዲስ ቤተመንግስት ማስገንባት ጀመረ” የሚለው ዜና በወርሃ መጋቢት ላይ ግንባር ቀደም ዜና ነበር።

ይህንን ዜና ቀድሞ በዝርዝር ያቀረበው የአማረ አረጋዊ ሪፖርተር ጋዜጣ ነበር። “አማረ እና ጌታቸው አሰፋ ይህን ዜና ተመካክረው ነው ያወጡት” ለማለት የሚያበቃ መረጃ የለኝም። ይሄ ዜና ድብቅ አላማ እንደነበረው ግን መረጃ አለኝ። ዜናው የተለቀቀበት ወቅት የአረብ ሃገራት መሪዎች ቤተመንግስታቸውን እየለቀቁ የሚሸሹበት ጊዜ ነበር። “ተረኛው ኮብላይ መለስ ዜናዊ ነው” የሚለው ትንበያም ተስፋፍቶአል። የመለስ የካቢኔ አባላትም ጭንቀት ውስጥ መግባታቸው ተሰምቶአል። በዚህ መካከል መለስ በአረብ ሃገራቱ አብዮት አለመደናገጡን የሚጠቁምለት አንድ ዜና መፈልሰፍ ነበረበት። “መለስ የኩብለላው ተረኛ ነው” የሚለው ወሬ፣ “መለስ አዲስ ባለመዋኛ ቤተመንግስት እየገነባ ነው” በሚለው እንዲተካ ሞከሩ። በነመለስ አስተሳሰብ ይሄ ዜና፣ ለተደናገጡት ደጋፊዎቹ ማረጋጊያ፣ የአመፅ ቅስቀሳ ለጀመሩ ተቃዋሚዎች ወሽመጥ መበጠሻ ሆኖ የታለመ ነበር። ይህ ዜና ለመለስ ጊዜያዊ ጭንቀት ማስተንፈሻ አገልግሎ ሊሆን ቢችልም፣ ሙከራቸው ግን አልሰመረም። ያም ሆኖ የተቃዋሚ ሜድያዎች ሳያውቁት ዜናውን በማሰራጨት የመለስ ተባባሪ ሆነዋል። ዜናዎች በዚህ መንገድ እንደሚፈበረኩ ሁሉ፣ እንደ አባይ ግድብ ያለ የመወያያ አጀንዳዎችም እየተዘጋጁ ይላኩልናል። እነዚህን ለይቶ ማወቅና ህዝቡን ማንቃት የፖለቲካ ሰዎች የስራ ድርሻ ነው።

“የመለስ ጠንካራ ጎን የተቃዋሚዎችን ደካማ ጎን በትክክል ማወቅ መቻሉ ነው” ብያለሁ። በአንፃሩ ተቃዋሚዎች የመለስን ቡድን ደካማ ጎን በትክክል ካወቁ በቀላሉ ሊያጠቁት ይቻላቸዋል። የመለስን ቡድን ደካማ ጎን በትክክል አለማወቅ ማለት፣ ለማጅራት ገትር በሽታ የወባ ኪኒን እንደ መስጠት ይቆጠራል። መለስ የሻእቢያን ስም ከአፉ የማይለየው፣ በዋነኛነት በጦር ሃይል ያጠቁኛል ብሎ ሰግቶ ሳይሆን፣ “ደካማ ጎኔን በትክክል ያውቁብኛል” ብሎ ስለሚያምን ነው። “ከአብሮ አደግህ – አብረህ አትሰደድ” ይላል ኦሮሞ ሲተርት።

ወደተነሳሁበት ዋና ነጥብ እየዘለቅሁ ነው።

ከአንድ አመት በፊት አንድ የኦነግ ሰው ቤቱ ራት ጋብዞኝ ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮችን አንስተን ስንጨዋወት እንዲህ አለኝ፣
“…ደርግ የመሬት ላራሹን አዋጅ በማወጅ የኦሮሞን ህዝብ የመሬቱ ባለቤት አደረገው። ወያኔ ለኛ ብሎ ባይሆንም ለራሱ ሲል በቋንቋችን እንድንጠቀም ፈቀደ። መሬት እና ቋንቋ መሰረታዊ ጥያቄዎቻችን ነበሩ። ያልተመለሱ ቀሪ ጥያቄዎች ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ፣ አለያም የፍትህና የዴሞክራሲ ጥያቄ ናቸው። መሰረታዊ መብቶቻችንን ለማስጠበቅ የምናደርገውን ትግል ስለሚጠራጠሩት፣ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ህብረት ለመፍጠር ተቸግረናል። ይህቺ ሃገር እኩል የምትደርሰን ከሆነ፣ ለደህንነቷም እኩል የሃላፊነት ስሜት ሊኖረን እንደሚችል መቀበል ይገባል። ዞሮ ዞሮ በቀጣዩ ጉዞ ከተግባባን ዴሞክራሲያዊ ስርአት አብሮ ያኖረናል።ካልተስማማን ግን ነፃነትን በግድ እናገኛለን”

መለስ ዜናዊ ላለፉት 20 አመታት አጤ ምኒልክ ቤተመንግስት መቆየት የቻለው እዚህ አካባቢ ያለውን ክፍተት እንደየሁኔታው ሊጠቀምበት በመቻሉ ነበር።

የሰሞኑ ግርግር መነሻውም ሆነ መቋጠሪያው ከዚህ አያልፍም። “ሻእቢያ አዲሳባን ባግዳድ ሊያደርጋት ነው” የሚለው ከበሮ ወዲያውኑ በመበሳቱ ከጥቅም ውጭ ሆኖአል። በመቀጠል “የአባይ ግድብ” ታላቅ ፈረሰኛ ዜና ሆኖ ብቅ አለ። መለስ ፓርላማ ላይ ቀርቦ፣ “ትንቢተ ዜናዊ” የተባለውን ምእራፍ በምርቃና ሲያምበለብለው በጥሞና አዳምጬዋለሁ። ነጥቦቹ ሲጨመቁ እንደሚከተለው ናቸው፣

• ግብፅ በራሷ የጦር ሃይል ታጠቃናለች ብለን አንሰጋም። በነጭ ለባሾች በኩል እንዳታጠቃን ግን እንሰጋለን።

• በአመለካከት ሊግባቡ የማይችሉ ሃይሎች ኦነግ፣ ኦብነግ፣ የደርግ ቅሪቶች እና የትምክህት ሃይሎች እኛን ለማጥቃት በሻእቢያ ካምፕ ውስጥ ተሰባስበዋል።

• አዲሱ እቅዳቸው አዲስአበባን ባግዳድ ማድረግ ሲሆን፣ ህዝብ በሚሰበሰብበት ቦታ ፈንጂ ለማፈንዳት እየሰሩ ነው። በዚህ ድርጊት ሻእቢያ ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ኦነግ፣ ኦብነግ እና የትምክህት ሃይሎች ግን ምን ጥቅም እንደሚያገኙ አላውቅም።

• አዲሳባን ባግዳድ ለማድረግ የሽብሩን ተግባር ከአመፅ ተግባር ጋር አንድ ላይ ለማቀናጀት ዝግጅት እየተደረገ ነው።

የመለስ የፓርላማ ንግግር ዋና ነጥብ የመጨረሻዋ ብቻ ነበረች። ሌላው ሁሉ ማጀቢያ ነው። ህዝቡ ለአመፅ እንዳይነሳሳ፣ “ተጠንቀቅ! ፈንጂ ተደግሶልሃል።” ብሎ ሊያስፈራራ እየሞከረ ነበር። ይህች የመጨረሻዋ ነጥብም መለስ ምን አይነት ጭንቀትና ስጋት ውስጥ እንዳለ ልቡን ግልጥልጥ አድርጋ የምታሳይ ናት።

ኤርትራና ግብፅን እንተዋቸው።

‘ግብፃውያንና ኤርትራውያን አዲሳባ ላይ ፈንጂ ያፈነዳሉ’ ስላልተባለም አጀንዳችን ሊሆኑ አይችሉም። የግብፅና የኤርትራ ሚና ከጀርባ መሆኑን መለስ ስለተነተነ በግንባር ስላሉት እንነጋገር።

እንደ መለስ ትንተና ህዝብ በተሰበሰበበት ቦታ ‘ፈንጂ ያፈነዳሉ’ ተብለው የሚጠበቁት የኢትዮጵያውያን ተቃዋሚ ድርጅት አባላት እንማን ናቸው? በተለይም መለስ በዘዴ ጣልቃ ያስገባቸው “የትምክህት ሃይሎች” መሪዎች በግለሰብ ደረጃ ሲዘረዘሩ ማን ማን ይባላሉ? የጥቂቶችን ስም መጥራት ካስፈለገ፣ ወያኔ በጥቁር መዝገቡ ላይ ካሰፈራቸው መካከል፣ መስፍን ወልደማርያም፣ ነገደ ጎበዜ፣ ብርሃኑ ነጋ፣ ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ፣ አንዳርጋቸው ፅጌ፣ ነአምን ዘለቀ ሊጠቀሱ ይችላሉ። መሃመድ እስማኤል ኦማር እና የቤልጅየሙ መሃመድ ሃሰን፣ ዳውድ ኢብሳ እና ሃሰን ሁሴን፣ ቡልቱም ቢዮና በያን አሶባ የመሳሰሉት የኦጋዴን እና የኦሮሞ የፖለቲካ ሰዎችም አሸባሪ ተብለው ተመዝግበዋል። እነዚህ ናቸው መርካቶ ላይ ፈንጂ አፈንድተው ህዝብ ለመጨረስ በአንድ ካምፕ የተሰባሰቡት? ወይስ ሌሎች የማናውቃቸው ባለውቃቢና መናፍስት ይኖሩ ይሆን?

መለስ በፓርላማ ዲስኩሩ፣
‘እነዚህ ሰዎች ህዝቡ ላይ ፈንጂ በማፈንዳት ምን እንደሚጠቀሙ አላውቅም’ ማለቱ በጣም አስቂኝ ነበር። ከመነሻው የተጠቀሱት ሰዎች የሚደግፋቸውን ህዝብ በፈንጂ ለመጨርስ መቼ አቀዱና! ሃገሪቱን ለጅምላና ለችርቻሮ ገበያ ሲያቀርባት የነበረው ማን እንደሆነ ህዝቡ ያውቃል። የተሰመረበት የመለስ አባባል መለስ የቀድሞ ጮሌነቱን እንኳ አጥቶ ጭንቀት ውስጥ መግባቱን የሚጠቁም ነበር። የእውር ድንብሩንም የተቃዋሚዎችን የትብብር አስኳል ለማፍረስ በሙሉ አቅሙ እየተፍጨረጨረ ይገኛል።

በቅርቡ በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ የኦነግ፣ የኦብነግ እና የግንቦት ሰባት ደጋፊዎችና ሌሎችም የአገዛዙ ስርአት ተቃዋሚ ዜጎች፣ እንደ አንድ ሰውና እንደ አንድ ቡድን አፋኙን ስርአት በመቃወም ያሳዩት አስደናቂ ህብረት የመለስ ብቸኛ ጠንካራ ጎን ላይ የተተኮሰ የመድፍ ቁምቡላ ነበር ማለት ይቻላል። ተቃዋሚዎች ነባር ሆኖ የዘለቀ ዋነኛ ድክመታቸውን ማስወገድ ከቻሉ መለስ ብቸኛ የማጥቂያ ካርዱን ተነጥቆ ባዶ እጁን ይቀራል።

“ተቃዋሚ ሃይላትም ሆኑ ህዝቡ ‘በዘር የማትከፋፈል አንድ ኢትዮጵያ’ በሚለው ጃንጥላ ስር ቁጭ ብለው ሊነጋገሩ አይችሉም” ብሎ መለስ ዜናዊ በጥብቅ ያምናል።

ስለዚህ ተቃዋሚ ሃይላት የመሰባሰብ ሙከራ ሲያሳዩ ሙሉ ሃይሉን ያን ህብረት ከመበተን ላይ ያውላል። በዘር የመከፋፈያ አጀንዳዎች ቀላል እንደመሆናቸው ብዙውን ጊዜ ወያኔ አላማውን ለማሳካት ብዙ ችግር አይገጥመውም። ወያኔ ከቅንጅት ማእበል ይልቅ እጅግ አስደንግጦት የነበረው ኡትሬክት ላይ የተመሰረተው AFD እንደነበር ይታወሳል። ቅንጅት በበረታ ጊዜ ወያኔ ኦነግን እንደማስፈራሪያ ጭራቅ ስሙን እየጠራ ሊያስፈራራ መሞከሩ አይዘነጋም። ከማስፈራራትም በላይ በአዲሳባ ዙሪያ የሚኖሩ ኦሮሞ አርሶአደሮችን በኦነግ ስም በፈረሰኛነት አደራጅተው “አማራ ከመሬታችን ይውጣ!” በሚል መሪ ቃል አዲስአበባ ላይ ግድያና ዝርፊያ እንዲጀምሩ አዘጋጅቶአቸው ነበር። በወቅቱ ይህን ፕሮጀክት ለማስፈፀም ሲያስተባብር የነበረው አባዱላ ከህሊናው ታርቆ፣ የዚህን ያልተፈፀመ ፕሮጀክት ዝርዝር ሊያጋልጥ ከቻለ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ከውለታ ሊቆጠርለት እንደሚችል አያጠራጥርም።

በወያኔ የመከላከያ ሰራዊት ውስጥ በተደረጉ በርካታ ግምገማዎች፣ አማራ እና ኦሮሞ ወታደሮች ላይ በተመሳሳይ ጊዜ የጠረጋ ዘመቻ የተፈፀመበት አንድም ጊዜ የለም። እንደየወቅቱ ትኩሳት እየታየ የፈረቃ ምንጠራ ሲካሄድባቸው ቆይቷል።

አማራዎች ሲመነጠሩ ለኦሮሞው፣
“…ነፍጠኛና ትምክህተኞችን እናፅዳ” የሚል ግብዣ ይቀርብለታል።

ኦሮሞችን ለመምታት ሲታቀድ ደግሞ፣
“የኦነግ አሸባሪዎችን እናስወግድ” በሚል መሪ ቃል አማራው ይቀሰቀሳል።

በዚህ መሃል የህወሃት ካድሬዎች መካከሉ ላይ እንደ ጆከር ሁሉም ዘንድ ይገባሉ። በዚህ መንገድ ከፋፍሎ ማስተዳደር የወያኔ የማይቀየር ስትራቴጂ መሆኑ ባለፉት ሃያ አመታት የታየና የተረጋገጠ ሆኖአል። ዜጎች ከክልል ወደ ክልል ተዘዋውረው እንዳይሰሩ ማድረግ ከተቀበሩት ፈንጂዎች ዋነኛው ነው።ተፈራ ዋልዋ፣ “ቆንጥር እየቧጠጣቸው ያገኙት ስልጣን ነውና ይገባቸዋል” እንዳለው በተመሳሳይ ጠበል የተጠመቁ ግለሰቦችን በዙሪያቸው ኮልኩለው፣ ሃገሪቱ ራሷን ችላ በእግራ እንዳትቆም የሚያደርጉ ምሰሶዎችን በትጋት እየተከሉ ይገኛሉ። የትግራይ ሰው እንዳያፈነግጥ የያዙበት ዘዴም፣ “አማራና ኦሮሞ ስልጣን ከያዘ ይፈጅሃል፣ ከቤትህ አፈናቀሎ ያባርርሃል!” የሚል የማያቋርጥ ሽብር በመንዛት ሲሆን፣ በዩኒቬርሲቲ፣ በውጭ ሃገራትና በክልል ከተሞች የተደራጁት የትግራይ ኮሚኒቲ ቋሚ አጀንዳዎችም፣ ህወሃት ከሌለ ኢትዮጵያዊነት አብሮ እንደሚያከትም የሚሰብኩ ናቸው።

“ወያኔ በሰራዊቱና በሲቪል ውስጥ ይህን ዘዴ በተደጋጋሚና በቀላሉ እንዴት ሊጠቀምበት ቻለ?” ለሚለው ጥያቄ መልሱ አሁንም ቀላል ነው። የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች የወያኔን ከፋፍሎ የመምታት ዘዴ ለማክሸፍ የሚያስችል ራእይ ያለው፣ የድርጊት ህብረት መፍጠር ባለመቻላቸው ነበር።

ከዚህ ከሰሞኑ ግርግር ጀርባ ያለው ታላቁ አጀንዳም ጽንፈኛ ሆነው የቆዩት ፖለቲከኞች ውስጥ ውስጡን በመግባባት ጎዳና ላይ መራመድ መጀመራቸውን በመረዳታቸው መሆኑ ግልፅ ነው። መለስን እስከዛሬ ስልጣን ላይ ይቆይ ዘንድ ያገዘችው የቁማር ካርድ አደጋ ላይ ወድቃለች። በመሆኑም መመኪያ አስማቱን ከሞት ለማትረፍ አዳዲስ የማደናቀፊያ እቅዶችን ነድፎ ብቅ አለ። የአባይ ግድብ አንዱ ነው።

መለስ ይሳካለት ይሆን?
ለዚህ ጥያቄ ከወዲሁ ምላሽ መስጠት አይቻልም። በዘር መከፋፈሉ በኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ የበለጠ እንዲቀጥል ጥረቱ ቀጥሎአል። በተለይ የሁለቱ አበይት ብሄሮች ህብረት አስጊ እየሆነ ስለመጣ፣ ያን ለመበተን በሙሉ ሃይላቸው ዘመቻ ጀምረዋል። በአሜሪካና በአውሮፓ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ ኦሮሞዎች የኦነግን ባንዴራ መያዛቸውን እሳት ለመለኮሻ ሊጠቀሙበት ሲሞክሩ ተደምጠዋል። ትግሬዎችን በዘራቸውና በቋንቋቸው የሚያሽሟጥጡም ተሰምተዋል። መለስ የላካቸው የወያኔ ካድሬዎች፣ “አህያ! አህያ! ገና ትረገጣለህ! ገና ትገዛለህ!” እያሉ በአደባባይ ቁሻሻቸውን ሲያስታውኩ ታይተዋል። ፈቃደ ሸዋቀና የተባለ ግለሰብ በጨዋ ደንብ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ስብሰባ ከተጠራ በሁዋላ፣ የአዳራሹ በር ላይ ሲደርስ “አንተማ የትግሬ ጠላት ነህ አትገባም” ተብሎ ሲከለከል፣ ጋዜጠኛው አዲሱ አበበ በጆሮው ሰምቶአል። “አህያ! ገና ትገዛለህ!” እያሉ የተሳደቡት የህወሃት ካድሬዎች ግን “ዘረኞች ናችሁና አትገቡም” ተብለው አልተከለከሉም። በዚህ ድርጊት ስሜታቸውን መያዝ ያልቻሉም፤ ተመሳሳይ ዘረኛ አባባሎችን ቢጠቀሙ ሊፈረድባቸው አይችልም። አንድ ዜጋ በሰው ሃገር ባይተዋር መሆኑ ሳይበቃው፣ በገዛ ሃገሩ ጉዳይ ላይ፣ “አይመለከትህም” ሲባል ከዚያ የከፋ መራራ ሁኔታ ሊገጥመው ከቶውንም አይችልም። ታማኝ በየነ እንባ እየተናነቀው፣ እንደ እሳት ሲንተከተክ ስሜቱን የማይገነዘብለት ሊኖር አይችልም። ይህን አይነት የዘር ግጭት አዝማሚያዎችን መለስ አጥብቆ ይፈልጋቸዋል።

ከእለታት አንድ ቀን አማራ እና ኦሮሞ የተባሉት ሁለቱ ግዙፍ ብሄሮች ህብረት ፈጥረው አንድ ሃይል ይሆኑ ይሆናል ብሎ መለስ መጠርጠሩ ወይም መስጋቱ አልቀረም። ይህ ስጋት እውን ከሆነ ትግራይን እንደ መጨረሻ መሸሻ ምሽግ ይዞ ለመቆየት ከወዲሁ ትግሬዎችን ከገዛ ወንድሞቻቸው ጋር ማናከሱን በተከታታይ ሲሰራበት ቆይቷል። ይህም አሁን የጀመረው አዲስ ስትራቴጂ አይደለም።

መለስ እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ማድረግ የሚችለውን ሁሉ መሞከሩ እንደማይቀር ከወዲሁ መረዳት ይገባል። መለስ የሃገሪቱን መሬት የሚቸበችብበት ሰይጣናዊ ምክንያቶች ይኖሩታል። ሙጋቤ የገበሬውን መሬት ለማስመለስ በመሞከሩ የሃገሪቱ ህዝብ የከፈለውን መራር ዋጋ የምናውቀው ነው። ተመሳሳይ ፈንጂ እየተቀበረልን ነው። ይሄ ግን እዳው ገብስ ነው። መለስ ኢትዮጵያ የተባለችውን ሃገር ህልውናዋን በጅምላ ከመሸጠም አይመለስም።

በተቃዋሚ የፖለቲካ መሪዎች በኩል እንደ ጀመሩት ልዩነታቸውን አቻችለው፣ ወደ መጨረሻው ግባቸው በትጋት ይጓዙ ይሆን?

በልበ ሙሉነት “ይቻላቸዋል!” ማለቱ ቢቸግርም ከበረቱና አሻግረው ማየት ከቻሉ ግን አያቅታቸውም። የውስጥ ትግሉ ፈታኝ ቢሆንም፣ ባላጋራቸው የዋዛ ባይሆንም፣ ሊፈፅሙት ይችላሉ። የኢትዮጵያ ህዝብ ለመስዋእትነት ዝግጁ እንደሆነ በተደጋጋሚ አስመስክሮአል። የመቻቻል ባህል ከመሪዎች ይጠበቃል። የእርስ በርስ ሽኩቻዎች ይቆሙ ዘንድ ይጠበቃል። ጉዞው ወደ ዴሞክራሲ ከሆነ፣ “የኔ ፖሊሲ ካንተ ፖሊስ ይሻላል!” የሚል ሙግት ጊዜውና ወቅቱ ሊሆን አይችልም። በዚህ ዘመን በፖሊሲ ልዩነት መናከስ ለመለስ ጠንካራ ጎን እገዛ ከማድረግ የዘለለ ውጤት አይኖረውም።

(ፀሃፊውን ለማግኘት፡ ttgebreab@yahoo.com)

መለስ ሰጠ! መለስ ነሳ! (ከተስፋዬ ገብረአብ)

Tuesday, January 25th, 2011

በዚህ ሰሞን “የዋህ አዛውንት” በሚል ርእስ ያሰፈርኩትን አጭር መጣጥፍ አስመልክቶ አንዳንድ አሉታዊ አስተያየቶችን አንብቤያለሁ። እናም “ዶክተር ነጋሶ ተርበዋል፣ ተጠምተዋል” በሚል ርእስ ታትሞ ያነበብኩት ቃለመጠይቅ እጅግ እንዳስገረመኝ ተጨማሪ አስተያየት ማከሉን ወደድኩ።
ዶክተር ነጋሶ የቤታቸው ጣሪያ ውሃ እንደሚያፈስና ቀዳዳውን በላስቲክ እየሸፈኑ ክረምቱን እንዳሳለፉ ተናግረዋል። እስኪ በድጋሚ እናጢነው? በርግጥ ለጣራ ቆርቆሮ መበሳት ችግር የነጋሶ አቅም ላስቲክ መሸፈን ብቻ ነበር? እኔ እስከማውቀው ለቆርቆሮ መቀደድ ችግር መፍትሄው ሌላ ቆርቆሮ መተካት ነው። ያን ማድረግ ደግሞ ከነጋሶ አቅም በላይ አልነበረም። ነጋሶን ከሚያክል የተቃዋሚ ድርጅት መሪ በዚህ ደረጃ ስለ ግል ችግር መስማትም የሚጠበቅ አልነበረም። ምክንያቱም የዚህ ዘመን አንገብጋቢ ጉዳይ የሃገሪቱ የህልውና ጣሪያ መቀደድ እንጂ የነጋሶ ጣሪያ ጉዳይ አይደለም።
“ነጋሶ ጊዳዳ የተሰናባች ፕሬዚዳንት ጥቅማ ጥቅማቸውን በመተዋቸው መስዋእትነት ከፍለዋል” በሚል ጀግንነታቸውን ማጉላት የሚፈልጉም አሳባቸውን ሰንዝረዋል። የ80 አመቱ አዛውንት አቶ ፅጌ ሃብተማርያም ጥረው ግረው ያፈሩትን ንብረት ሰውተው እስርቤት ተቀምጠው የለም እንዴ? ጄኔራል ተፈራ ማሞ አይነስቡ ላይ በቡጢ እየተደበደበ ማጎሪያ ቤት ተጥሎ የለም እንዴ? የጄኔራሉ ንብረት በመወረሱ ልጆቹ የሚጠለሉበትና የሚበሉት ተቸግረው ወድቀው የለም እንዴ? ለመሰረታዊ መብቶች መከበር ሲታገሉ ከባድ ስቃዮችን የሚቀበሉ ዜጎች ባሉበት ሃገር፣ እንዴት ነው ስለነጋሶ ጣሪያ መቀደድ መቆርቆርና ማዘን የሚቻለው? ይሄ ምፀት እና ፌዝ ነው።
ዶክተር ነጋሶ በቃለመጠይቁ ላይ፣ “ስለመለስ ዜናዊ የፖለቲካ ሰብእና” እንዲገልፁ ተጠይቀው ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። የግል ችግራቸውን ለመተንተን ግን ሙሉ ገፅ አልበቃቸውም። “የዶክተር ነጋሶ መስዋእትነት” የሚባለው በኔ በኩል ተቀባይነት የለውም። የመስዋእትነትን ክብር ማዋረድም ይሆናል። ነጋሶ ሂሳባቸውን ያሰሉት፣ በየአምስት አመቱ እየተመረጡ የፓርላማ ወንበር ማሞቁን ነበር። በ1997 ፓርላማ ገብተው የፈየዱት አንድም ሊጠቀስ የሚችል ጠቃሚ ነገር አልነበረም። አምስቱንም አመት ሲሟገቱ የነበረው የተሰናባች ፕሬዚዳንት ጥቅማጥቅማቸውን ለማስከበር ነበር። በ2001 ምርጫ መለስ ሳይፈቅድላቸው ቀረ። በመሰረቱ ከስራ መባረር በነጋሶ የተጀመረ አይደለም። ዩኒቨርሲቲ መምህራን የነበሩ ከ40 በላይ ምሁራን ሲሰናበቱ ነጋሶ ስልጣን ላይ ነበሩ። እነዚያ የተባረሩ ምሁራን በመባረራቸው ችግር እንደደረሰባቸው ሲናገሩ አልሰማንም። ያልተናገሩት ችግር ስላልደረሰባቸው አይመስለኝም። ጉዳዩ በሃገር ደረጃ የመጣ ችግር ስለነበር፣ አጠቃላይ መፍትሄን የሚጠይቅ መሆኑን በመረዳት ይመስለኛል። በርግጥም አብዛኞቹ ወደ ትግሉ ነው የገቡት።
በተቀረ መለስ ዜናዊ የነጋሶ ጊዳዳን ጥቅማጥቅም በማስቀረቱ ጥፋተኛ ነው ብዬ አላምንም። ነጋሶ ጊዳዳ ፕሬዚዳንት የሆኑት በህዝብ ተመርጠው ሳይሆን፣ አንቀፅ 39 እንዲፀድቅ የህገመንግስቱን ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ስለመሩ መለስ ያበረከተላቸው ስጦታ ነው። ስልጣኑን ራሱ ሰጣቸው፣ ጥቅማጥቅሙንም ራሱ ነፈጋቸው። ዶክተር ነጋሶ የተነጠቁት ህዝብ የሰጣቸውን መብት ሳይሆን፣ መለስ የፈቀደላቸውን ነው። እናም “መለስ ሰጠ – መለስ ነሳ”።
(ፀሃፊውን ለማግኘት፣ ttgebreab@gmail.com)

የዋህ አዛውንት (ከተስፋዬ ገብረአብ)

Monday, January 24th, 2011

በስደት በከተምኩባት የስደት ጎጆዬ በፀጥታ ተቀምጬ፣ “የስደተኛው ማስታወሻ”ን የአርትኦት ስራ እየሰራሁ ሳለ አንድ ጓደኛዬ የኢሜይል መልእክት ላከልኝ።
“ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ስላንተ ተናግረዋልና አንብበው” የሚል ነበር መልእክቱ።
በተጠቆምኩት ሊንክ ገብቼ ቃለመጠይቁን አነበብኩት። እናም በእውነቱ የነጋሶ ቃለመጠይቅ ልቤን ክፉኛ ስለነካው፣ የአርትኦት ስራዬን አቋርጬ ይችን ወግ ጫርኩ።
* * *
የእንባ ከረጢቴ ባይደርቅ ኖሮ በነጋሶ ቃለመጠይቅ ስቅስቅ ብዬ አለቅስ ነበር። ዳሩ ምን ያደርጋል? ማልቀስ ካቆምሁ ቆየሁ። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ እንዲህ ችግር ላይ ይወድቃሉ ብሎ ከቶ ማን ያስባል? በቃለመጠይቁ ከገለፁልን ጥቂቱን ልቀንጭብላችሁ፣
• ዶክተሩ ጣራው የሚያፈስ ቤት ውስጥ ነው የሚኖሩት? ጣራቸው ላይ ላስቲክ ሸፍነው ነው ክረምቱን ያሳለፉት? አንድ ቀን ጣራው ተንዶ ሊገድላቸው እንደሚችልም ገልፀዋል።

• ሩዋንዳዊቷ የማደጎ ልጃቸውም በችግር ምክንያት የፅዳት ሰራተኛ ሆና ተቀጥራ ትሰራ ነበር?

• ዶክተሩ መኪናም የላቸውም። በታክሲ ነው የሚጓዙት። ባለታክሲዎችም እየተሳቀቁ ሂሳብ አይቀበሏቸውም። ተሳፋሪዎችም ይከፍሉላቸዋል።

• መለስ ዜናዊ የጡረታ መብታቸውን አዘግይቶባቸው ቤት ውስጥ ምግብ የሚገዛውም በሚስታቸው ደሞዝና ልጃቸው የፅዳት ስራ ስትሰራ ውላ፣ ወገቧ ጎብጦ በምታመጣው ገንዘብ ነው።

እንግዲህ ከላይ የተገለፀው ሁሉ በነጋሶ ቃለመጠይቅ ላይ የተነገረ ነው። እና ይሄ አያስለቅስም?
ለዚህ ሁሉ አስለቃሽ ግፍ ደግሞ ተጠያቂው መለስ ዜናዊ ነው’ ብለውናል። ነጋሶ ቃል በቃል “አስር አመት ሙሉ ምግብ ለስራ ስሰራ ነበር” ሲሉ ነው ብሶታቸውን ለጋዜጠኛው የተነፈሱት። እኔ በበኩሌ ይሄን አላውቅም ነበር። ዶክተር ነጋሶ ላለፉት አስር አመታት “ምግብ ለስራ” ላይ እንደነበሩ ጋዜጦች እንዴት ሳይፅፉት እንደቀሩም አይገባኝም። ነጋሶ፣ እንደ ቤተመንግስቱ አንበሳ፣ “መለስ ዜናዊ እስር ቤት ሳይከተኝ፣ በጥይት ሳይመታኝ ‘በረሃብ’ ሊገለኝ ነው!!” ሲሉም እሪታቸውን ለኢትዮጵያ ህዝብ አሰምተዋል።

ዳሩ ግን ያልገባኝ ነገር አለ።
ልጃቸው አልተማረችም እንዴ? በእናቷ ጀርመናዊት፣ በአባቷ ዶክተር የሆነች የቤተሰቡ ብቸኛ ልጅ፣ ተምራ አንድ ደህና ቦታ መድረስ እንዴት አቃታት? ደግሞስ በእናቷ በኩል ስኮላርሺፕ ሊፈለግላት አልተቻለም ይሆን? ጀርመኖች ለዜጋቸው ቀርቶ ለኛ ለስደተኛውም ተርፈዋል። ለነገሩ የፅዳት ስራውን የምትሰራው የት ይሆን? ጀርመን ኤምባሲ ውስጥ ከሆነ መቼም ደሞዙ ከአንድ ሚኒስትር ደሞዝ እኩል ስለሆነ ዶክተር ነጋሶ ማለቃቀስ የለባቸውም። ይህም ሆኖ ነጋሶ ስለልጃቸው የፅዳት ስራ መስራት ሚዲያ ላይ ማወጅ አስፈላጊ ነበር? ምን ጥቅም ይገኝበታል? የማስተዛዘኛ የፖለቲካ ንግድ? በልጅህ መነገድ ግን ያልተለመደ ነው። ሰውም እኮ ይታዘባል መቼም። ስንቱ በ1000 ብር ደሞዝ ስድስት ልጆቹን አሳድጎ፣ አስተምሮ ደህና ቦታ ያድርስ የለም እንዴ? ነጋሶ ረጅም ጊዜ ታስረው የነበረ ቢሆን እንኳ፣ ምክንያቱ ይገባናል። ታስረው አያውቁም፣ ፕሬዚዳንት እያሉ ደግሞ የጠገበ ደሞዝ ነበራቸው። ለኑሮ ድምቡሎ አያወጡም ነበር። ስድስት አመታት ሙሉ ደሞዛቸው ዝም ብሎ ባንክ ነበር የሚገባላቸው። እና ምን አድርገው ጨረሱት?

እሺ ደህና እሱ ይቅር።
አንድ የታሪክ ምሁር እንዲህ ስለ ኑሮ ችግር አንስቶ ሲያለቅስ አያሳፍርም? ሚስቱ ጥሩ ደሞዝ ያላት፣ አንድ ልጅ ብቻ ያለው፣ የዶክተርነትን ማእረግ የለበሰ ሰው እንዲህ ምርር ብሎ ካለቀሰ፣ ሌላው ህዝብ እንዴት እየኖረ ነው ሊባል ይሆን? ለመሆኑ እነ ገብሩ አስራትና ስዬ አብርሃ በምንድነው የሚኖሩት? “ተቸገርን” ሲሉ ሰምተን አናውቅም። የግል ጉዳያቸውን ባደባባይ ማውጣት ስለማይሹ ይሆን ወይስ አልተቸገሩም? የነጋሶ መቸገር እንዴት የተለየ ሆነ?

እስከዛሬ በወያኔ የተፈናቀለው ባለሙያ እንዲህ እንደ ነጋሶ ተማርሮ ሲያለቅስ ሰምተነው አናውቅም። ነጋሶ ገንዘብ ያጠፋሉ እንዳይባል፣ ቀምቃሚ የሚባሉ አይደሉም። የሲጋራ ወጪ በርግጥ ሊጫናቸው ይችላል። ቢሆንም ግን ራሳቸውን ለመቻል መስነፍ አልነበረባቸውም። የታሪክ ምሁር እንደመሆናቸው መፅሃፍ ቢጤ ጫር ጫር ቢያደርጉ፣ መፃፍ ካልቻሉ ደግሞ የአስመሮም ለገሰን “ገዳ” ወደ ኦሮምኛ ቢተረጉሙ ለቀሪ ህይወታቸው፣ ስምና ገንዘብ ባተረፉበት ነበር። “በሚስቴ ደሞዝ ነው የምተዳደረው” የሚለው ማስተዛዘኛ ብዙም አልተመቸኝም። ወንድ ልጅ የፈለገ ቢቸግረው በሚስቱና በልጆቹ ፊት አያለቅስም። ባህላችን አይፈቅድም። አባት መከታና መመኪያ በሆነበት ህብረተሰብ ውስጥ ነው ያለነው። ከማልቀስ መሸፈት ይሻላል። እርግጠኛ ነኝ የነጋሶ ልጅ ቃለመጠይቁን ስታነብ በአባቷ ሁኔታ ትሸማቀቃለች። የኢትዮጵያ ህዝብ በመሰረቱ አልቃሻ አይወድም። “ከባልንጀራው ማታ የተለየ – እንደ አጥቢያ ኮከብ ሲነጋ ታየ!” እያለ በኩራት የሚዘምር ህዝብ መሃል አልቃሻነት ያስንቃል። ሌላው ሁሉ ቢቀር ለኑሮ አንዳንድ ዘዴ አይጠፋም። ለአብነት ቡልቻ ደመቅሳ ሃብታም ናቸው። የነጋሶም ጓደኛ ናቸው። ከእሳቸው ተበድረው ከሙያቸው ጋር የሚሄድ አንድ የአማካሪ ቢሮ ከፍተው መንቀሳቀስ ይችላሉ። የፓርላማውን ደሞዝ ተማምነው ቆይተው፣ እሱ ሲቀር እንደ ህፃን ልጅ “ራበኝ!!” ማለት ግን ያስተዛዝባል።

በተቀረ ነጋሶ በቃለመጠይቃቸው ላይ ቀደም ሲል ስለኔ ተጠይቀው ለአውራምባ ጋዜጣ የሰጡትን ምላሽ፣ “አላልኩም” ብለው ክደዋል። ይሄ አያከራክረንም። ጋዜጣውን በማየት ብቻ ማን እንደዋሸ ማረጋገጥ ይቻላል።

የመጨረሻው የነጋሶ አባባል ግን ልብ የሚነካ ሆኖ አጊንቼዋለሁ።
“ሰዎች መንገድ ላይ ሲያገኙኝ፣ ‘እንወድሃለን’ እያሉ ግንባሬና መላጣዬ ላይ ይስሙኛል” ነበር ያሉት።
ይሄ ትልቅ ሃብት ነው። ነፃነትን የመሰለ አርኪ ነገር የለም – በዚህች ምድር ላይ። መለስ ዜናዊ አዲሳባ ላይ በእግሩ ለመጓዝ ቢሞክር መላጣውን የሚስምለት አያገኝም። ይልቁን ቅንድቡን ለመላጨት በሚቸኩሉ ሰዎች ይከበባል። ቸር ያቆየን!!

የመለስ ቀልዶች (ከተስፋዬ ገብረአብ)

Thursday, September 30th, 2010

ወያኔ ጉባኤውን አዳማ ላይ አካሄደ።

እናም ጉባኤው በአትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ ንግግር ተቋጨ። መለስ ዜናዊም በሃይሌ ንግግር ሲስቅ በቴሌቪዥን ተመለከትነው። መለስ ዜናዊ፣ “በአምስት አመታት አጠናቅቀዋለሁ” ያለውን ትንግርታዊ፣ አስማታዊና ሰማያዊ የልማት እቅድ ዶክተር ሃይሌ ከመለስ ብሶ፣ “በሁለት አመታት እንጨርሰዋለን” ሲል ቃል ገባ። አያይዞም አትሌት ሃይሌ፣ “ስለ ሰከንድ ማሰብ አለብን” ሲል ተናገረ።

ሃይሌ ሃብቱንም ሆነ ክብሩን ያገኘው ባቋራጭ ሳይሆን፣ ላቡን ጠብ! አድርጎ በመሆኑ አከብረዋለሁ። የሃይሌ ክብር የግሉ ሳይሆን የሃገሪቱ ጭምር በመሆኑ ደግሞ ለሃይሌ ያለኝ አክብሮት ድርብ ነው።

ሻለቃ ሃይሌ ወደ ወያኔ ጉባኤ ሄዶ ያደረገውን የተሳከረ ዲስኩር ግን አልወደድኩለትም። በዚህ ድርጊቱ ሃይሌን የመኮነን ፍላጎት የለኝም። ጉባኤው ላይ ያድረገውን ንግግር አምኖበት ነው ብዬም አላስብም። ሃይሌ ከወያኔ ሰዎች የሚደርስበትን ጫና በቅርብ ከሚያውቁት አንዱ ስሆን፣ ገንዘብ በጥሬው እንዲያመጣ ጭምር እንደሚያስገድዱት መረጃዎች አሉ።

ሃይሌ ገንዘብ ለባለስልጣናቱ የሚሰጠው በምትኩ ሌላ ጥቅም ለማግኘት ሳይሆን፣ የችግር ወሬ እያወሩ ገንዘብ እንዲሰጣቸው ስለሚጫኑት ነው። በዚህ በወያኔ ዘመን ባለገንዘብ ከሆንክ የግዴታ አጠገብህ ለሚገኝ ባለስልጣን ግብር መክፈል አለብህ። ይህ በስውር የፀደቀ የስርአቱ ህግ ነው።

ሆኖም ሃይሌ አዳማ በተካሄደው የኢህአዴግ ጉባኤ ላይ ተገኝቶ ያንን ግራ የተጋባ ንግግር ያደርግ ዘንድ ያስገደደው አልነበረም።
“ጉባኤያችሁን በማጠናቀቃችሁ፣ እንኳን ደስ ያላችሁ” ብሎ ብቻ አመስግኖ በዘዴ ሹልክ ብሎ ማምለጥ ይችል ነበር።
ባለቅኔ መንግስቱ ለማ “ለአረንጓዴው አብዮት አረንጓዴ እንቁላል ውለዱ” በሚል መርህ፣ የኢሰፓን ምስረታ በግጥም እንዲያሞግሱ ሲጠየቁ እንዴት ሸውደው እንዳለፉ የምንረሳው አይደለም። ጳውሎስ ኞኞም፣ “ሰርቶአደር ጋዜጣን ትወደዋለህ ወይ?” ተብሎ ሲጠየቅ ምን እንደመለሰ አንረሳውም።
ምን ነበር ያለው?
“ማርያምን ትወዳታለህ ወይ?” ተብሎ የሚጠየቅ ሰው ምን ብሎ መለሰ?
“ከግንድ የሚያላጋ ልጅ እያላት እንዴት ነው የማልወዳት?”
በርግጥ እየሱስ ክርስቶስ የፍቅር አምላክ ነው። ጳውሎስ ኞኞ አባባሉን ለማጣፈጥ ያለው ይሆናል።
ሃይሌ ግን በየዋህነት ለመለስ ቀልድ ተመቸ። ጉባኤው ላይ ቀርቦ፣ በደቂቃ ልዩነት አንድ ሚሊዮን ዶላር ስለማግኘትና ስለማጣት መፈላሰፍ ባላስፈለገው ነበር። የአትሌቲክስን የማሸነፍና የመሸነፍ ልምዱን ቀመር እንደ ወረደ አምጥቶ የሃገሪቱ የኢኮኖሚ አጀንዳ ላይ አለበሰው።

በሃይሌ ንግግር መለስ ከአንጀቱ ሲስቅ አይተነዋል። መለስ የሳቀው በሃይሌ ንግግር ተደስቶ ሳይሆን፣ በሃይሌ የዋህነት ተገርሞ መሆን አለበት። ምክንያቱም እዚያ ጉባኤ ላይ የሚበተነው የልማት ተስፋና አበባ በመጪው አምስት አመታት እንደማይፈፀም መለስ ዜናዊ አሳምሮ ያውቅ ነበር።

ይህን ካሰብኩ በሁዋላ ጥቂት ተከዝኩ። እናም አንድ የካህሊል ጊብራን ወግ ትዝ አለችኝ። መጽሃፉ አጠገቤ ስለሌለ በራሴው መንገድ ላውጋችሁ፣

በጥንት ዘመን አንድ አማኝ ቄስና ኢአማኒ ፈላስፋ የአንድ ከተማ ነዋሪዎችን ሰብስበው በእግዚአብሄር ጉዳይ ላይ ክርክር ያካሂዱ ነበር።
አማኙ ቄስ “እግዚአብሄር ፈጣሪ አምላካችን ነው” ሲል መፅሃፍ ቅዱስን እየጠቀሰ ረጅም ሰአት ሰበከ።
ኢአማኒው ፈላስፋ በበኩሉ “እግዚአብሄር የሚባል ነገር የለም። የሰው ፈጠራ ነው” ብሎ ህዝቡን ለማሳመን ሲፈላሰፍ ዋለ።
ሙግቱ እንዳበቃ ተሟጋቾችም፣ ህዝቡም ወደየቤቱ ተበተነ።
አማኙ ቄስ ታዲያ ቤቱ እንደገባ መፅሃፍ ቅዱሱን አቃጠለና ከዚያች እለት ጀምሮ “እግዚአብሄር የለም” ሲል ደመደመ።
ኢአማኒው ፈላስፋ በበኩሉ ቤቱ እንደደረሰ መሬት ላይ ተንበርክኮ እንዲህ ሲል ፀለየ፣
“አምላኬ ሆይ! በዛሬው እለት አንተ ፈጣሪዬ እንደሆንክ አመንኩ! እስከዛሬ ስለካድኩህ ይቅር በለኝ!!”

ሶስተኛው መድፍ (ከተስፋዬ ገብረአብ)

Friday, September 24th, 2010

እነሆ! “የስደተኛው ማስታወሻ” የተባለው መድፍ ተሰርቶ ተገባዶአል…
በዚህ አያያዜ ቶሎ የምጨርሰው ይመስለኛል። “ስደት” ርእሰ ጉዳዩ ሰፊ ነው። ይፃፍ ከተባለ 20 ጥራዝም አይበቃው። ሆኖም አጀንዳዬ ከሃገራችን ፖለቲካ ሊያፈነግጥ እንደማይችል ግልፅ ነው። የአብዛኛው የስደት ምክንያቱ ፖለቲካውም አይደል? በመሆኑም ስደትና ፖለቲካውን ከወቅታዊ ጉዳዮቻችን ጋር እያዋሃድኩ እተርካለሁ።

* * *

“የስደተኛው ማስታወሻ”ን የተሟላ ለማድረግ አውሮፓን እየዞርኳት ነው።
ስዊድን፣ ጀርመን፣ ፊንላንድ፣ ሆላንድና ቤልጅየምን ያዳረስኩ ሲሆን፣ ራሺያ እና ፈረንሳይ በቅርቡ የምፈፅማቸው ጉዞዎች ይሆናሉ። “የስደተኛው ማስታወሻ” የትረካ ማእከል ኔዘርላንድስ ናት። ሆላንድ ላይ እንደ ልብ ያገኘሁት የአበሻ ሰው ታሪክ የኛን ዘመን አመፀኛ ስደተኛ መወከል ይቻለዋል። የአመስተርዳም “እሳቶች”ም ታሪክ መስራት ጀምረዋል። ከበረቱ ጅማሬው ለትውልድ የሚያልፍ ይሆናል።

ሆላንድ ላይ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ስደተኛ ሆኜ ገብቼ ነበር።
ዳሩ ምን ያደርጋል? በአንድ ወር ውስጥ የመኖሪያ ፈቃድ ሰጥተው አሰናበቱኝ። በርግጥ ቁርጥራጭ ወረቀቶቼን ለመያዝ አንድ ወር በቂ ነበር። እና በቀጣዩ ማስታወሻ እውነተኛውን የአውሮፓ የስደት ህይወት ስለማወጋችሁ ከወዲሁ ለመራር ሳቆች ተዘጋጁ።
በተመሳሳይ ወደ ጀርመንም ሄጄ ነበር። ኑረንበርግ፣ ፍራንክፈርትና ሙኒክ ከተሞችን ጎብኝቻለሁ ወይም ሰነባብቻለሁ። ከደብረዘይት ልጆች ጋርም መልካም ጊዜዎች ነበሩኝ።
“ሳታስፈቅደን ታሪካችንን መሸጥ ጀመርክ?” ሲሉም ቀልደውብኛል።

* * *
አውሮፓ ላይ ከጥቂት አንቱ የተባሉ የኛ ሰዎች ጋርም ተገናኝቼያለሁ።
ከነዚህ አንዱ ሌንጮ ለታ ነው። ኡትሬክት የተባለች ከተማ ላይ ተገናኘንና ከግማሽ ቀን በላይ አብረን ቆየን። ሌንጮን እንደጠበቅሁት አገኘሁት። ከሌንጮ ጋር ማውራት ምቾት የሚሰጥ መሆኑ አያጠያይቅም። ባነሳናቸው የኢትዮጵያ ታሪክ ነክ አጀንዳዎች ላይ በአብዛኛው መስማማት ችለን ነበር። መቸም ነጋሶ ጊዳዳና ሌንጮን ማወዳደር አይቻልም። ዶክተር ነጋሶ በህይወቱ ውስጥ የወሰነው ትልቁ ውሳኔ፣ ከመለስ ወደ ስዬ ያደረገው ሽግግር ነው ማለት ይቻላል። እራሳቸውን መሆን የማይችሉ ሰዎች የሚያስከትሉት ጉዳት ለህብረተሰብ ይተርፋል። እና ሌንጮ የጠበቅሁት አይነት ሰው ሆኖ አገኘሁት። በመሆኑም በቀጣይ መፅሃፌ ላይ፣ “ከሌንጮ ጋር ቡና ጠጣሁ” የሚል አንድ ምእራፍ ይኖረኝ ይሆናል። በርግጥ ከሌንጮ ጋር ቆይታዬን ገና አላበቃሁም። እሱ ወደ ሚኖርባት ወደ ኦስሎ ከተማ ሄጄ በድጋሚ ላገኘው ቀጠሮ ይዘናል።

ከዶክተር ነገደ ጎበዜ ጋር በስልክ መገናኘት ከጀመርኩም ቆየሁ።
እኒህ አንጋፋ የፖለቲካ ሰው ያልታተመና ተፅፎ ያላለቀ ማስታወሻ እንዳላቸው ሰምቼ ስለነበር፣ ይህንኑ አንስቼላቸው ነበር። ማስታወሻው መኖሩንና በፈረንሳይኛ የተፃፈ መሆኑን ነግረውኛል። እንግዲህ በቅርቡ በድጋሚ ወደ ብራስልስ ሄጄ ያንን ማስታወሻ በእጄ ለማስገባት እጥራለሁ። በ66 አብዮት ዘመን ከነበሩ ወጣቶች፣ በህይወት የቀሩና ብዙ ምስጢር የሚያውቁት እኒህ ሰው ናቸውና ከጊዜ ጋር መሽቀዳደም ያስፈልጋል።

እርግጥ ነው በርካታ ሰዎችን ለማግኘት የስም ዝርዝር አውጥቼያለሁ።
ፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ ሌላው ናቸው። እሳቸውም በአንድ መጣጥፋቸው እንደገለፁት ከእኒህ አንጋፋ መምህር ጋር የቃጅማው ጊዮርጊስን ጠበል በመቋደሱ እንዛመዳለን። ከዚያ ባሻገር የእኒህ መምህር መፃህፍት ከሻንጣዬ አይለዩም። “The Time Machine” የተባለውን የሳይንስ ፊልም አይታችሁታል? ጌታቸው ሃይሌ ለኛ እንዲያ ሆነውልናል። አሜሪካኖቹ ቪዛ ከሰጡኝ ሚኒሶታ ሄጄ አገኛቸዋለሁ። የመጪው መፅሃፌ አካልም አደርጋቸዋለሁ።

* * *

ከሳምንታት በፊት ብራስልስ ሄጄ ነበር።
ስለ መለስ እና ብርሃነ ገብረክርስቶስ አንዳንድ ነገሮችን አጊንቼያለሁ። መቼም ብራስልስ መለስ በሚስጥር የሚመላለስባት ከተማ መሆኗን ታውቁ ይሆናል። አንዳንድ ሃገር ወዳዶች ብዙ ተባብረውኛል። ቀጣዩ መፅሃፍ ላይ የሚወጣ ስለሆነ ግን ያገኘሁትን የእሳት ዳር ወግ እዚህ አልናገርም። እስከዚያው ሁለቱ ቱጃሮች ሆዳቸውን ይቁረጣቸው።
ለነገሩ መለስ ሆዱን የሚቆርጠው አይነት ሰው አይደለም።
ቅንድቡን በጨው አጥቦ አዜብ መስፍንን የፖሊት ቢሮ አባል አድርጓት አረፈው። በርግጥ የመለስ ያፈጠጠ ድርቅና ገርሞኝ እንጂ ይህች ነገረኛ ሴትዮ መጣች ቀረች ለውጥ የለውም። ከጀመርኩ ላይቀር ግን አምባሳደር ብርሃነን ትንሽ በሃሜት ብንቦጭቀው ምን ይመስላችሁዋል? ሃሜት የማትወዱ በItalics የተፃፈውን አንቀፅ የመዝለል መብታችሁ የተጠበቀ ነው።

….እንደሚታወቀው አምባሳደር ብርሃኔ እንትን ይወዳሉ።
በ2002 ማብቂያ ላይ በተደረገው የህወሃት ጉባኤ አምባሳደሩን የህወሃት ፖሊት ቢሮ አባል ከመሆን ያደናቀፋቸውም እንትን የመወደድ ጠባያቸው ውጤት ተኮር በመሆኑ ነው የሚል ሃሜት አለ። ያ ባይሆን ኖሮ አምባሳደሩ ከአዜብ መስፍን ያነሰ ችሎታ አልነበራቸውም። በርግጥ የግል ፋይላቸው የሚያመለክተው “ዩኒቬርሲቲ ገቡ” የሚል እንጂ “ጨርሰው ወጡ” የሚል የለበትም። በዊንጌት ተማሪነታቸው ግን የመለስ ሲንየር ነበሩ። አዜብ ደግሞ መለስን ከማግባቷ በፊት ወጥቤት ሰራተኛ የነበረች ሲሆን፣ ከዚያ ቀደም ብሎ ደግሞ የበጎች እረኛ ነበረች። እረኛ መሆን መልካም ነው። ከእረኛነት ወደ ቤተመንግስት የሚደረግ ቀጥተኛ በረራ ግን ብዙውን ጊዜ አደጋ አለው። ይህቺ ሴትዮ፣ በሚዲያ ስትቀርብ እንዲህ “ስድአፍ” የሆነችው፣ ፀሃይ እንዳላገኘ ዘንጋዳ ፈጣን እድገት ስላጋጠማት ሳይሆን አይቀርም።
ወደ ዋናው ሃሜት ልመለስና አምባሳደር ብርሃነ ፖሊት ቢሮነቱን ያጣው እንትን በመውደዱ ነው።
ይሄ ሃሜት አይደለም! በርግጥ ሃሜት ነው። “እውነት አዘል ሃሜት” እንለዋለን። አምባሳደሩ እንደሚወራባቸው ከሆነ ብራስልስ ላይ በቢሮአቸው የሚሰሩ ቆንጆ እንትኖችን ፈጅተው ጨርሰው፣ ያንዳንዶቹን ወደ እህቶቻቸው ጭምር ተሻግረዋል። ይህን ስል መቼም ማንን ማለቴ እንደሆነ ሰራተኞቹ ስለሚያውቁ ሳቅ በሳቅ ይሆናሉ።
ሳልነግራችሁ ረስቼ!
አምባሳደሩ ከሚስታቸው ጋር ታረቁ እኮ!!
“አራት ሚሊዮን ዶላር ይበቃሻል፣ ሌላውን መልሺ። አምባሳደሩም ይቅርታ ይጠይቅሽ እና ታረቁ።” የሚሉ ሽማግሌዎች ተላኩባት። (ሽማግሌዎቹ እነማን እንደሆኑ አላውቅም። ያው መቼም ፕሮፌሰር ይስሃቅ ኤፍሬም ይሆናሉ። ሌላ ታዲያ ማን ሽማግሌ አለ?) የሆነው ሆኖ፣ ሽማግሌዎቹም በእግረመንገድ፣
“ሶሎሜ ታደሰም ብትሆን ወንደላጤ አጊኝታ አግብታለች። የሚያሰጋሽ ነገር የለም” ስላሉዋት ተስማማችና አራት ሚሊዮን ዶላር ብቻ አስቀርታ፣ ሌላውን ለህወሃት ተመላሽ አድርጋ ወደ ብራስልስ ገባች አሉ።
ድንቅ ነው!!
የህወሃት አባላት እውነት መስሎአቸው የሞቱለት ትግል፣ የትግራይ ህዝብ በስሙ የሚነገድበት አብዮት፣ እንዲህ የሚሊዮናት ዶላር መቀለጃ ሆኖ አርፎታል። ለነገሩ የህወሃት አባላትም ሆኑ የትግራይ ህዝብ ይህን አያውቁም ማለቴ አይደለም። “እንኳን ይቺን የዝንብ ወያኔ እናውቃለን” ያለው ማን ነበር?…..

የሆነው ሆኖ ብራስልስ ቆንጆ ከተማ ሆና አገኘሁዋት። እንደ ጨርቆስ አይነት ኪስ አውላቂዎች ግን ሞልተውባታል። ብራስልስ ላይ ደስ ካሉኝ ነገሮች አንዱ ካርል ማርክስና ቪክቶር ሁጎ ቡና ይጠጡበት የነበረውን ቦታ መጎብኘቴ ነው። ሁለቱም ሰዎች ንጉሶቻቸው ሲያስቸግሯቸው ብራስልስ እየመጡ ይጠለሉ ነበር አሉ። እነሱ ቁጭ ይሉባት የነበረው ቦታ ላይ ቁጭ ብዬ ማኪያቶ ጠጣሁ። በርካታ ጎብኚዎችም ይህንኑ ያደርጋሉ።

* * *
ስዊድን የሄድኩ ጊዜም ማርክስን አስታውሼዋለሁ።
እዚያ የሄድኩበት እለት የሰራተኞች ቀን እየተከበረ ነበር። ሰልፈኛ ወዛደሮች “Marx Was Right!!” የሚል መፈክር ይዘው አገር ምድሩን በጩኸት ሲበጠብጡ፣ እኔ ግንቡን ተደግፌ በትካዜ እየተመለከትኳቸው ዋልኩ። ከየሃገሩ የመጡ ስደተኞች የአመፅ መዝሙርና ኢንተርናሲዮናልን እየዘመሩ የየሃገራቸውን መንግስት ሲያወግዙ ዋሉ። አላየሁዋቸውም እንጂ በሌላ አቅጣጫ የብርቱካን ሚደቅሳን ምስል የያዙ የኛ ሰዎችም፣ “አትነሳም ወይ!?” እያሉ ነበር። ይህንን ያጫወተኝ ማቴዎስ ከተማ የተባለው ገጣሚ ነው። በነገራችን ላይ “ተነሳ ተራመድ!” የተባለውን የአየር ሃይል መዝሙር የገጠመው ማቴዎስ ነው የሚባለው እውነት ነው?

ለነገሩ ምኑን ተነስተን ተራመድነው?
ተሽመድምደን ቁጭ ብለን፣ እጃችንን ለእግዚአብሄር እንደዘረጋን ቀርተነዋል። አሁንማ ይቺ እጅ መዘርጋቷም ምቀኛ ተነስቶባት፣ አዲስ የሚታተሙት መፅሃፍ ቅዱሶች ላይ፣ “ኢትዮጵያ” የሚለው “ሱዳን” በሚል መተካት ከጀመረ ስንት ጊዜው? መቼም ኢትዮጵያ የሚሏት ሃገር ጠላቷ መብዛቱ? ግን ከምድረ ገፅ አልጠፋ ብላቸው ተቸግረዋል። እንደ ድመት ዘጠኝ ነፍስ ያላት ሃገር!

* * *
የስቶክሆልም ቆይታዬ መልካም ነበር።
ፅጌረዳ ከተባለች የደብረዘይት ጓደኛዬ ቤት ሁለት ሌሊት አደርኩ። ጣት የሚያስቆረጥም የጉራጌ ክትፎ ሰርታ አበላችን። ፅጌረዳ ሽበቷ ከመብዛቱ በቀር፣ ውበቷ እያንፀባረቀ ጠበቀኝ። ትክ ብዬ ሳስተውላት ፅጌረዳ “ኢትዮጵያ”ን ራሷን መስላ ታየችኝ። እድሜ ውበቷን ያልነካው፣ ትካዜና የወገኖቿ ናፍቆት የተጫጫናት!
….እና ፅጌረዳ ገና ስታየኝ እንባዋ ገንፍሎ ፊቷን አለበሰው።
የልጅነት ጓደኛን በድንገት ማግኘት እንዴት ደስ ይላል? ፅጌረዳን ረሳችሁዋት እንዴ? “የጋዜጠኛው ማስታወሻ” ላይ ስለሷ ተርኬ ነበር እኮ? ባለቤቷም ታዲያ መልካም ሰው ሆኖ አገኘሁት። ሌሊት እንዲያውም እስከ አውሮፕላን ማረፊያው የሸኘኝ እሱ ራሱ ነበር። ስለዚያች የቢሾፍቱ ቀጤማ በመግባባት ማውራት በመቻላችን በጣም ደነቀኝ! ስልጣኔ ማለት እንዲህ ነው። የፅጌረዳ ነገር ለዘልአለሙ ያከተመ ነው። ስሜቱ ግን አብሮኝ ዝንተአለም ይኖራል። ለመሆኑ የሚስታችንን የቀድሞ የከንፈር ወዳጅ ቤታችን የመጋበዝ ችሎታ ያለን ሃበሾች ስንት እንሆን? እኔ በበኩሌ የማደርገው አይመስለኝም። እንኳን ቤቴ ልጋብዘው ገና ሳየው እንደ ፊጋ በሬ የማገነግን ይመስለኛል። ይህን ካላደረግሁማ ምኑን አበሻ ሆንኩት?

* * *

ወደ ሩሲያ የማደርገው ጉዞ ከአሁኑ ናፍቆኛል።
ራሺያ እንደገባሁ በቅድሚያ የማደርገው ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ባቡር ወይም አውቶብስ ይዤ ኒዥኒይ ኖቭጎሮድ እሄዳለሁ። ይቺ ከተማ ከቅዱስ ፒተርስበርግ ቀጥሎ ሶስተኛዋ የራሺያ ትልቋ ከተማ ናት። ማክሲም ጎርኪይ የተወለደባትና የህይወትን መራራ እሬት የጨለጠባት ከተማ። ኒዥኒይ ኖቭጎሮድ የቢሾፍቱ ያህል ትታየኛለች። ጎርኪይ እንዴት አድርጎ ነው በቃላት የሳላት? የጎርኪይን ትረካዎች አንብባችሁ ከሆነ፣ ጎርኪይ ኒዥኒይ ኖቭጎሮድ ላይ ቆሻሻ ለቃሚ ነበር። በሚለቅመው ቆሻሻና የወዳደቀ አጥንት ምክንያት ታዲያ እጁ ጠቆረበት። በሳሙና ፈግፍጎ ቢታጠበውም ሊለቅለት አልቻለም። ጎርኪይ ምንም እንኳ የነጣ ድሃ ቢሆንም፣ የከንፈር ወዳጅ ለማበጀት መሞከሩ ግን አልቀረም።
ኮረዶቹ ከተዋወቁት በሁዋላ እየተጠየፉት እንዲህ ሲሉ ይጠይቁታል፣
“እጅህን ለምን አትታጠበውም?”
“ታጥቤዋለሁ። ግን አይለቅም!” ሲል ይመልሳል።
ከዚያም ኮረዶቹ ሰበብ ፈጥረው ጥለውት ዘወር ይላሉ።
ጎርኪይ እንዲህ ያሉ ታሪኮችን በውብ ብእሩ ያጫውተናል። እና ጎርኪይ ያቺ የናቀችውን ኮረዳ ደግሞ ከ20 አመታት በሁዋላ የአንድ የፖሊስ ሚስት ሆና ተጎሳቅላ እንዳገኛት እንደዋዛ ያወጋናል። የጎርኪይን የህይወት ታሪክ ማንበብ ማለት ቀኑን ሙሉ መሳቅ ማለት ነው። ጎርኪይ በ1936 በ68 አመት እድሜው ሞስኮ አጠገብ ከሚገኝ መኖሪያ ቤቱ አረፈ። እንግሊዛዊው ደራሲ ጆርጅ በርናንድ ሾው የማክሲም ጎርኪይን የእረፍት ዜና መጥተው ሲነግሩት እንዲህ ሲል መናገሩ ተመዝግቦለታል፣
“ጎርኪይ ሞተ? በሉ የኔንም የመቀበሪያ ሳጥን አዘጋጁልኝ። የ19ኛው ክፍለ ዘመን ፀሃፍት የመሰናበቻችን ጊዜ እንደደረሰ ለመናገር እድፍራለሁ።”
እነሆ! ኒዥኒይ ኖቭጎሮድን ለማየት መጓዜ ነው።
ቮልጋ ወንዝን እስካየውም ቸኩያለሁ። ኦካ ዳርቻም ቁጭ እላለሁ። የበረዶው ወቅት ሳይገባ እንድፈጥንም ጓደኞቼ መክረውኛል። በረዶው መውረድ ከጀመረ ቮልጋ እንደ አለት በረዶ ይሆናል አሉ። ጉድ ነው። ወንዝ ደንዝዞ፣ እንደ አስፓልት መኪና ሲሄድበት እግዜር ያሳያችሁ። የኛው ጀግናው አዋሽ ግን መደንዘዙን አያውቅበትም። ከአመት አመት እያቅራራ የሚጓዘው አዋሽ!! ሃገር ወዳዱ አዋሽ!! ስደትን የተጠየፈው አዋሽ!! በሃገሩ ላይ ዘምሮ፣ በሃገሩ መሬት ላይ የሚቀበረው አዋሽ! ፀጋዬ ገብረመድህን ትዝ አላችሁ? እንዲህ ሲል…

“…እስከመቼ ይሆን አዋሽ፣
አዋሽ ቡርቃው፣ መጫ ምንጩ፣ ዳዳ ፅንሱ፣ ሸዋ ፍንጩ፣
ውጠህ ተውጠህ እርጩ፣
ንግርትህ ምንድነው አዋሽ? አባ ብቻ፣ አባ እንቅጩ፣
ዘልአለምህን ፈሰህ ላታልቅ፣
ምነው ተስፋ መቁረጥን አታውቅ?
እስከ መቼ ይሆን አዋሽ?
አዋሽ ቡቡ፣ ሮሮ ብርቁ፣
የዘልአለም ንዳድ ስንቁ፣
እነ ዋቢሸበሌማ ሰብረው ውቅያኖስ ሲዘልቁ፣
እነ ግዮን አልፈው ወርደው፣ ሱዳንን ምስርን ሲያጠምቁ፣
ምነው ያንተ ጉዞ ብቻ በረሃ ላይ መታነቁ?…”

“አዋሽ” የብዙ ነገር ምሳሌ ነው። “ሃገር ወዳድ” የሚሉት አሉ። ፀጋዬ ገብረመድህን በ“አዋሽ” የመሰለው ግን የኢትዮጵያን ህዝብ ሳይሆን አይቀርም። ጉዞው በረሃ ላይ የታነቀበት ህዝብ! ግን ደግሞ ተስፋ መቁረጥን የማያውቅ ህዝብ! ለነገሩ የጀግኖች መፍለቂያ የነበረ፣ የአዋሽ አባት ሃገር እንዲህ በአረም ተውጦ እንደሚቀር፣ ሎሬት ፀጋዬ ታይቶት ነበርን? ማን ያውቃል? ለማንኛውም ቮልጋን ልጎበኝ ወደ ሩሲያ መሄዴ ነው። እዚያ ሄጄ የሚያጋጥመኝንም “የስደተኛው ማስታወሻ” ላይ አወጋችሁዋለሁ።

(….በነገራችን ላይ ሳልረሳው…
በምፅፋቸው መፃህፍት ምክንያት የሚናደዱ የወያኔ ደጋፊዎች አስተያየታቸውን ለምን በስማቸው እንደማይፅፉ ሳላስብ አልቀረሁም። የብእር ስም መጠቀም ነውር አይደለም። አብዛኞቹ ግን ከኔ ጋር እንደሚተዋወቁ ሆነው ይፅፋሉ። እኔ ግን አላውቃቸውም። ለምን ይሆን የሚሸሸጉት? ማንን ይሆን የሚፈሩት? ያው መቼም አስተናጋጃቸው የኢትዮሚዲያው አብርሃ በላይ ነው። ቀንዱንም ሸኮናውንም እየሰበሰበ ይለጥፈዋል።
ሰሞኑን ደግሞ፣ “የጋዜጠኛው ማስታወሻን የፃፈው የማነ ገብረአብ ነው” የሚል ፅሁፍ ለጥፎ ነበር።
ይሄ ሰውዬ ጤና የለውም እንዴ? “ገብረአብ” የሚል ስም እየፈለገ አስቸገረ እኮ! ባለፈው “ንዋይ ገብረአብ ታላቅ ወንድሙ ነው” ብሎ ፃፈና አጋለጥኩት። አሁን ደግሞ የማነ ገብረአብ ሆነ የኔ መፅህፍ ደራሲ!? ይሄ ሰውዬ “ገብረአብ” የሚባል ሰይጣን ለክፎታል እንዴ? “የታገሰ ከሚስቱ ይወልዳል” ይባላል። ትንሽ ከጠበቃችሁ የኔ ግጥሞች ሁሉ የይልማ ገብረአብ ይሆናሉ።
ዶክተር ሼክስፒር ፈይሳ! በቅድሚያ እንደምን ከርመሃል? ደህና ነህ ወይ? ጤናህስ? ወደ ዋናው ጉዳይ ልግባና….አብርሃ በላይ ጓደኛህ ነው አይደለም? እባክህ ቀስ ብለህ ምከረው። “ገብረአብ” የሚል ስም እየፈለገ ከኔ ጋር የሚያያይዘውን ነገር ይተወኝ ብያለሁ ይተወኝ! እንቢ የሚል ከሆነ ግን፣ ምን አደርጋለሁ? ያው መተው ነው። ገብረአቦች ሲያልቁበት ምን እንደሚውጠው አየዋለሁ። ለነገሩ አሁን አሁን አብርሃ ቆዳው ስስ መሆኑን ስላየሁ፣ እሱን ማብሸቅ ደስ ይለኝ ጀምሮአል። አብርሃን ለማብሸቅ ስዬን በጨረፍታ ነካ ማድረግ በቂ ነው። ስዬን ከምትነካበት ሚስቱን ብትነካበት ይመርጣል።)

ወደ ቁምነገሩ ልመለስና…
በመሰረቱ በፖለቲካ ጉዳይ ግለሰቦች ላይ መንጠልጠል በጣም አደገኛ ነው። ግለሰቦች ሰዎች ናቸው። ነገ ከአቋማቸው ሊንሸራተቱ ይችላሉ። ያን ጊዜ ደብቁኝ ይመጣል። ለዚህ መፍትሄው በአላማ ዙሪያ መሰባሰብ ነው። የግንቦት 7 አባል ባልሆንም፣ በሩቅ እንደማያቸው ከሆነ አካሄዳቸው ተስፋ እና እምነት ያሳድራል። አመራሩ ሲተማማ ሰምቼ አላውቅም። የፖለቲካ ፕሮግራም ነድፈው፣ ባስቀመጡት መርህ መንገድ ላይ ሲጓዙ ይታያሉ። በወሬ የተጠመዱ አለመሆናቸው ይታያል። ወደ ተግባር በመግባታቸው ወያኔም ተደናግጦአል። መለስ ዜናዊ የግንቦት7ን ስም መጥራት መጀመሩ፣ በደካማ ጎኑ ገብተው ስጋት እንደፈጠሩበት ይጠቁመኛል።

ወያኔ የሚንቅህ ከሆነ ስምህን አያነሳም።
የነገደ ጎበዜን ስም ከአፋቸው የማይለዩት፣ ዶክተር ነገደ ከካስትሮ ጋር ተሻርከው፣ የሙስሊም ጀለቢያ ለብሰው አዲሳባ በመግባት፣ መንግስቱ ሃይለማርያም ላይ መፈንቅለ መንግስት እንደሞከሩት ሁሉ፣ ከዛሬ ነገ አንድ ተንኮል ሰርተው ዙፋኔን ጉድ ያደርጉኛል ብሎ ስለሚጨነቅ ይመስለኛል። በርግጥም ወያኔን ለማስወገድ ፍላጎቱ ካለ ጊዜው አሁን ነው። ከወያኔ ወደ ወያኔ የሚደረገው ሽግግር ስር ከመስደዱ በፊት መንቃት ብልህነት ነው። ፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ የጠሩትን “የክተት አዋጅ” ከግንቦት7 የሰሞኑ “ወያኔን የማግለል” ጥሪ ጋር ማዋሃድ ግድ ይላል። ጥምረትም በጥንቃቄ ከተሰራበት ወጤት ያስገኛል…

* * *

“የስደተኛው”ን ለመፃፍ ወደ ለንደን የመሄድ እቅድም ይዤያለሁ።
ለንደን ላይ ፍራሹ ተፈርሾ፣ ከርቤና ቀበሪቾ የተባሉ እጣኖች ጢሳቸው እየተንበለበለ፣ የአየርባየር ትግሉና ፖለቲካው የጦፈበት፣ ወያኔ እንደ ሽንኩርት ድቅቅ ተደርጎ የሚከተፍበት በርጫ ቤት መኖሩን ነግረውኛል። እዚያ በርጫ ቤት ተሰይሜ አንድ የዘመናችንን የትግል ታሪክ እፅፋለሁ። የነዚያ በርጫ ቤቶች አስቂኝ ጠባይ አብዛኞቹ ጫት ቃሚዎች የወያኔ ተቃዋሚዎች መሆናቸው ሲሆን፣ የጫቱ ገቢ ደግሞ በተዘዋዋሪ ለአዜብ መስፍን መሆኑ ነው። እዚህ ላይ አንድ የዘመነ ደርግ ጄኔራል ትዝ አለኝ። ሰራዊቱ እየሸሸ ሲያስቸግረው ምን ነበር ያለው?

“ታሪክ ዋሽቶአል፣ አሊያም ትውልድ ተኮላሽቶአል!”

ታሪክ እንኳ አልዋሸም። ትውልድ ሳይኮላሽ ግን አልቀረም። ገና ሳይወለድ የሚሰደድ ትውልድ። በልመና የሚኮራ ዜጋ የተፈለፈለበት ዘመን። ዳሩ! ልጆቻቸውን አሜሪካዊ ለማድረግ የሚሻሙ መሪዎች ከነገሱበት ዘመን ምን ይጠበቃል? ሰድቦ ለሰዳቢ የሚሰጥ መሪ! ቃል የእምነት እስትንፋስ መሆኑን ያማያውቅ ንጉስ! …

* * *

በተቀረ “ስደተኛው ማስታወሻ” ላይ በርካታ ተነባቢ ታሪኮች ሳይኖሩ አይቀሩም።
33 ምእራፋትን ያቀፈ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ፣ “መለስና ብርሃኑ”፣ “የመንገዴ ላይ አበቦች”፣ “የአመስተርዳም እሳቶች”፣ “በጭጋጋማ ጉም ውስጥ”፣ “አስቀያሚ ገፅታችን”፣ “የሳጥናኤል ጉዳይ”፣ “የሻምቡ ንጉስ”፣ “የጁገል በርጫ ላይ”፣ “የታማኝ ሸክም” (ታማኝ በየነን ይመለከታል)፣ “አረጋዊ እና ግደይ”፣ “በቃሊቲ ጣራ ስር”፣ እና “የስለላ ስራ” ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው።

“የስለላ ስራ” የሚለው ርእስ በጣም ተነባቢ ሊሆን ይችላል።

በጋዜጠኛነት ሙያ ብዙ የሰራሁ እንደመሆኔ ስለ ስለላ ስራ ጠለቅ ያለ ልምድና እውቀት አለኝ። በመሰረቱ “የስለላ ስራ” ማለት “ጆሮጠቢነት” ማለት አይደለም። ባጭሩ “የተደበቀ መረጃ ፈልጎ ማግኘት” ማለት ነው። ከዚያ ዝቅ ያለ ሌላ ትርጉም የለውም። የስለላ ባለሙያዎችን በሁለት ከፍሎ ማየትም ይቻላል። የመጀመሪያዎቹ የፖለቲካ አላማ ሰላዮች ናቸው። ሌሎቹ ጋዜጠኞች እና ደራስያን ናቸው። ጋዜጠኞችና ደራስያን የስለላ ስራ የሚሰሩት አንድ የተደበቀን እውነት ፈልፍለው በማውጣት ለህዝብ ይፋ ለማድረግ ነው። የፖለቲካ አላማ ያላቸው ሰላዮች ደግሞ፣ መንግስታቸውን አለያም የሚያምኑበትን አላማ ከጥቃት ለማዳን ስለላ የሚያካሂዱ ናቸው። በሁለቱም ጎራዎች ዘንድ የተደበቀ መረጃ ለማግኘት የረቀቀ ሙያዊ ስራ ይሰራል። ለአብነት ህወሃት መሃል አገር ከሚገኙ አባላቱ የሚያገኘውን የኢትዮጵያን ሰራዊት የሚመለከት መረጃ በመለስ ዜናዊ በኩል ለዚያድባሬ ያቀብል እንደነበር መረጃ አለ። ዛሬ ግን መለስ የኢትዮጵያ መሪ ነው። በርግጥ ይህ ርእሰ ጉዳይ ሰፊ ነው። በቀጣይ መፅሃፌ በሰፊው ተንትኜዋለሁ። በጋዜጠኛነት የስራ ዘመኔ መረጃ ለማግኘት የምጠቀምባቸውን ዘዴዎችና የፖለቲካ አላማ ሰላዮችን አስደማሚ ፖለቲካዊ የቁማር ጨዋታ አወጋችሁዋለሁ።

በመጨረሻ ….
መፃፍ እንደምቀጥል ማረጋገጥ እሻለሁ። እንደ አባኮዳ የሚያክላሉና ስማቸውን መግለፅ የሚሰጉ ጥልማሞቶች፣ ምን ያህል በፍርሃት ጉድጓድ ውስጥ እንደሰመጡ ይታዩኛል። የቢሾፍቱ ቆሪጥ ምህረቱን ያውርድላቸው። በኔ በኩል ከሞት በቀር የሚያቆመኝ ሃይል የለም! አያ ሞት ደግሞ ካንዴም ስንቴ ስለሳተችኝ፣ አሁን ተላምደን ቤተሰብ ሆነናል። ተራ ግለሰብ ብሆንም መንፈሴ ብርቱ ነው። ስለዚህ በህይወት ዘመኔ የማምንበትን እንደልቤ ተናግሬ ለማለፍ የወሰንኩ ሰው ነኝ። የኔን እምነት የሚጋሩ በሚሊዮናት ወገኖች እንዳሉኝ ማወቄ ደግሞ ብርታት ሆኖኛል። ወጣቶች በኔ ስልት መፃፍ ጀምረዋል…

“ብሾፍቱን ዳግም አታያትም!” እያሉ የሚዝቱብኝ እንዴት የዋህ ናቸው?

መፃህፍቶቼ ገና ድሮ መላ ኢትዮጵያን አጥለቅልቀውት የለም እንዴ? ለመሆኑ ከዚህ በላይ በሃገር መገኘት አለ? የስንቱን ወጣት ኢትዮጵያዊ አይን እንደገለጥሁ እነዚህ ጥቋቁር ሰዎች ቢገነዘቡ ቆመውም መሄድ ባልቻሉ። “የደራሲው ማስታወሻ” አዲስ አበባ ላይ በድብቅ እየታተመ 150 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል። ማን እያተመ እንደሚሸጠው ግን እንኳን እኔ የወያኔ የፀጥታ ክፍልም ሊደርስበት አልቻለም።

(…አዲስአበባ ከወያኔ ቁጥጥር ውጭ ስለመሆኗ የሚጠራጠር ካለ፣ እሱ የትም የለም። ሳሞራ የኑስና ጌታቸው አሰፋ ነቅተው መጠበቅ የቻሉት ቤተመንግስቱን ብቻ ነው። በተቀረ ወያኔ እንደ ጉም ተንሳፎአል። አንዲት የትግራይ ልጅ የሆነች ጓደኛዬ እንዳጫወተችኝ፣ እናቷ የትግሬ ሹሩባ ተሰርተው መርካቶ መሄድ አልቻሉም። የህዝቡን አይን ፈርተውና ተሳቀው ትተውታል። የትእዝብት አይን ከጦር በላይ ይዋጋል። ይሄ የማይፈለግ እውነታ የወያኔ ሰዎችን ፍርሃት ለቆባቸዋል። እንደምንሰማው ከሆነ፣ በግድ ተይዘው እንጂ፣ የመልቀቂያ ማመልከቻ የሚያስገቡና ዲፕሎማት ሆነው ውጭ ሃገር ለመሄድ የሚጠይቁ የወያኔ የአመራር አባላት እየበረከቱ ሄደዋል። ጎርፉ ሳይውጣቸው ባገኙት ቀዳዳ ሁሉ፣ ከነጫጩቶቻቸው ለማምለጥ መላ ጎርጓሪዎች ሆነዋል። እውነታቸውን ነው። መንግስቱ ሃይለማርያም እነ ለገሰ አስፋው ላይ ያደረሰውን ቅሌት መቅመስ አይሹም…)

የወያኔ ካድሬዎች ራሳቸውም “የደራሲው ማስታወሻ”ን በድብቅ ከአዟሪ ላይ እየገዙ፣ የገዛ ሃጢአታቸውን በማንበብ ላይ እንዳሉ ሰምቼያለሁ። ካነበቡት መካከል ጄኔራል ባጫ ደበሌ (ደስተኛው ጄኔራል) አንዱ ነው። ካነበበ በሁዋላ ሰዎች ሲጠይቁት የተናገረውን ፅፈው ልከውልኛል። እንዲህ አለ አሉ፣

“ስለኔ የተፃፈው ሚዛኑን ያልጠበቀ ነው። እኔ ጄኔራል የሆንኩት ከአስር አለቃነት ተነስቼ ነው። ከእረኛነት ተነስተው ጄኔራል የሆኑ የህወሃት አባላት አሉ አይደለም ወይ?”

በባጫ ደበሌ አባባል በጣም ተስማምቻለሁ። ባጫ 100 % ልክ ነው። ስለዚህም አንድ አሳብ ማቅረብ እፈልጋለሁ። ወያኔ ሲወድቅ ጄኔራል ባጫ በወንጀል መጠየቅ የለበትም። እስካሁን ለፈፀመው ጥፋት አንድ ነገር እንዲያደርግ ግን እንጠይቀዋለን። ይህም የሜጄር ጄኔራልነት ማእረጉን እንደለበሰ፣ መስቀል አደባባይ ላይ ህዝብ በተሰበሰበበት የማይክል ጃክሰንን Moon Walking ይደንስልናል። ከዚያም ከነገንዘቡ ከነንብረቱ በነፃነት ወደቤቱ ይሄዳል! ባጫ የስርአቱ ሰለባ እንጂ ወንጀለኛ አይደለም። መጪው መንግስት ይህን በማስታወሻው እንዲይዘው እፈልጋለሁ።

እኔን በተመለከተ የትውልድ ሃገሬን ዳግም አየሁ አላየሁ አሳሳቢ አይደለም።
ርግጥ ነው፣ በህይወት ወደ ቢሾፍቱ የመመለስ እድል አላገኝም ይሆናል። ገብረክርስቶስ ደስታም ወደሚወዳት ሃገሩ ሳይመለስ ነው ህይወቱን ያጣው። ሙሴም 40 አመታት ከተጓዘ በሁዋላም እንኳ እስራኤል የተባለች ሃገሩን መሬት ሳይረግጥ ነው የሞተው። እና ሊያጋጥም ይችላል። የነፃነት ትግል ጠባይ እንዲያ ነው። እስከ እለተ ሞቴ ግን እግዚአብሄር የሰጠኝን የነፃነት መድፍ “ግማሽ ነጋዴ! ግማሽ መደዴ!” ከሆኑ ሰዎች አናት ላይ አምበለብለዋለሁ…

(ደራሲውን ለማግኘት በሚከተለው ኢሜይል አድራሻ ይላኩ፡ ttgebreab@gmail.com)
መስከረም፣ 22 2010

የዶክተር ብርሃኑ ጥሪ! (ከተ.ገ.)

Wednesday, September 22nd, 2010

የነሱን ቢራ ከምትጠጣ ለነፃነትህ ውሃ ጠጣ!!

እንግዲህ ይሄ ዳሸን ቢራና ፔፕሲኮላን የሚመለከት ሊሆን ይችላል።

እነሱ ያመረቱትን ከምትለብስ የተቀደደ ልብስ ልበስ!

የአልመዳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ Made in USA የሚል ታግ እየለጠፈ የአዲስአበባን ገበያዎች ማጥለቅለቁን ያውቃሉ? ከዱባይ ኮንቴይነር እያስጫኑ፣ ያለቀረጥ እያስገቡ ትርፍ ስለሚዝቁ የወያኔ ሰዎችስ ሰምተዋል?

በነሱ ሲሚንቶ ከምትገነባ ሆን ብለህ ሌላ መንገድ ፈልግ! ወይም ግንባታውን ለጊዜው አዘግይ!

የወያኔው የመሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ አትራፊ እንዲሆን የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ከአቅም በታች እንዲያመርት ተደርጓል። የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ የቦርድ ሊቀመንበር ደግሞ ስዩም መስፍን ነው። የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ኢንጂንየር የወያኔን ሸር በመቃወሙ 5 አመት መታሰሩንስ ያውቃሉ? ሌላም ልጨምርሎት። ባንድ ወቅት የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካን ለመጠገንና ለማስፋፋት ኮንትራት ፈርሞ ሊመጣ የነበረውን ጀርመናዊ ኢንጂንየር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ቪዛ ስለከለከለው የማስፋፋትና የጥገና ፕሮጀክቱ ተቋርጦአል። ሙገር ይህን መስዋእትነት የሚከፍለው፣ መሶቦ ሲሚንቶ አትራፊ አንዲሆን ነበር።

የመንግስት ሰራተኛ የሆንሽ በስራሽ ላይ ለግሚ! በቀን ሰርተሽ የምትጨርሺውን ስራ ሳምንት አቆይው።

ይሄ ጥሪ ተግባራዊ መሆን ሲጀምር ወያኔ ተሽመድምዶ እጁን ይሰጣል። ማህተማ ጋንዲ በዚህ የትግል ዘዴ ህንድ የተባለች ሃገሩን ነፃ ማውጣቱ የሚታወስ ነው።

በመስሪያ ቤትሽ የሚደረገውን የዘረፋ ምስጢር፣ ወይም ማናቸውንም ይጠቅማል ብለሽ የምታስቢውን መረጃ፣ ለነፃነት ታጋዮች አሳልፈሽ ስጪ፣

እያንዳንዱ ዜጋ ለሃገሩ ሰላይ ከሆነ ድል ቅርብ ይሆናል። በመጨረሻ የሚያሸንፈው ጥሩ የተመገበው ሳይሆን፣ በቂ መረጃ ያለው ሃይል ብቻ ነው።

(የዶክተር ብርሃኑን ጥሪ ሙሉውን ለማዳመጥ www.ginbot7.com ይጎብኙ!)

የስዬ “ምስጢሮች” (ከተስፋዬ ገብረአብ)

Thursday, September 16th, 2010

ስዬ አብርሃ የፃፈውን መፅሃፍ አነበብኩት።

የተደጋገመውን ዝባዝንኬ እየዘለልኩ እንደምንም ጨረስኩት። የስዬ ወንድሞች የገዟቸው መኪኖች የሻንሲ ቁጥር ምንም ስለማያደርግልኝ እየነጠርኩ አልፌዋለሁ።

ስዬ ላይ አልፈረድኩበትም።

ከነበረበት የስልጣን ደረጃ ጋር የሚመጣጠን የማንበብ ልምድ እንደሌለው ይታወቃል። በአናቱ የተፈጥሮ እብሪቱ ሲታከልበት ማንኛውም የተጠረዘ ነገር ሁሉ መፅሃፍ ሊሆን የሚችል ቢመስለው አያስደንቅም። ጥሩ አንባቢ ያልሆነ ሰው ለመፃፍ ባይሞክር ይመረጣል። የመፅሃፍ ጥብቅ ወዳጅ ያልሆነ ሰው በድፍረትና በወኔ ወደ መፃፍ ከገባ እንደ ስዬ አብርሃና ካሳዬ አራጋው አይነት ችግር ላይ ይወድቃሉ። ጥሩ አንባቢ ሆነህ ሳለም ታሪክህን የግድ ራስህ መፃፍ ላይኖርብህ ይችላል። ከፃፍክም ደግሞ ጥሩ አማካሪና አርታኢ መፈለግ ይገባ ይሆናል። ሂላሪ ክሊንተን ወይም ኔልሰን ማንዴላ ታሪካቸውን ራሳቸው አልፃፉትም። “ድብቅ ብእረኞች” (ghost writers) ተብለው የሚታወቁ ባለሙያዎች ከጀርባ አሉ። የጄኔራል ጃጋማ ኬሎ ትረካ ጥሩ የተዋጣለት የፍቅረማርቆስን ብእር ስለተዋሱ ነው። ጃንሆይ እነዚያን ትላልቅ ጥራዞች ራሳቸው አልፃፉዋቸውም። መንግስቱ ሃይለማርያምም በስልጣን ዘመኑ ብእር ሲይዝ ዘባራቂ ነበር። ጋዜጠኛ ከበደ አኒሳ መንግስቱ የሚቸከችከውን ዝባዝንኬ በማቃናት መከራቸውን ያዩ ነበር። አንድ ጊዜ መንጌ ቴክሱ ለአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ጉባኤ የሚቀርብ ንግግሩ ላይ፣ “መሃመድ ጋዳፊ ህዝብ ያስታወከው መሪ ነው” የሚል አረፍተነገር ጨምሮ፣ በመከራ ተለምኖ ነው ያቺ አረፍተነገር የተሰረዘችው።

ስዬ አብርሃ በጎ መካሪ ካጠገቡ ሳያስቀምጥ እንደ ኪም ኢል ሱንግ የህይወት ታሪክ አንድ ትልቅ ጥራዝ ጀባ ሊለን በቃ። ገንዘብ ካለ ምን ችግር አለ? ችግሩ ግን ተነባቢነትን በገንዘብ መግዛት አይቻልም። ስዬ አብርሃ ወንድሞቹ የገዟቸውን የጭነት መኪኖች የሻንሲ ቁጥር በመጽሃፉ ሲደረድር አማካሪዎቹ ዝም ብለው ማየታቸው ለምን ይሆን? የሆነው ሆኖ የስዬ አብርሃ መፅሃፍ ላይ ሂስ የማቅረብ ፍላጎት የለኝም። ጊዜም የለኝም። አንዳንድ ያስገረሙኝን ነጥቦች ብቻ በጨረፍታ ላነሳ ወደድኩ።

ለአብነት ስዬ አብርሃ እንዲህ ይለናል፣

ታምራት ላይኔ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆኑ አለቃዬ ነበር። እኔ ሚኒስትር ነኝ። በመሰረቱ አንድ ሚኒስትር ጠቅላይ ሚኒስትርን ሊያዝዝ አይችልም።”

ቃል በቃል ባይሆንም ስዬ ይህን ይለናል። ይህችን ያነበበ ፈገግ ብሎ ከማለፍ ውጭ ምን ሊል ይችላል?

ገፅ 155 ላይ ታዲያ የራሱን አባባል እንዲህ ሲል ያፈርሰዋል።

“የብአዴን አመራር የራሱን የቤት ስራ ለመስራት የሚቸገር መሆኑን ከድሮ ጀምሮ አሳምሬ አውቃለሁ።”

እና ታዲያ የራሱን የቤት ስራ መስራት የማይችል ሰው ነው ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው የሾሙት?

እንዲህ ይለናል ደግሞ፣

“ትምኒት የቤታችን የመጨረሻ ልጅ ናት። እሷ ብቻ ናት ሴት ልጅ።”

ትምኒት እድሜዋ 34 መሆኑም ተጠቅሷል። በመቀጠል ደግሞ ስዬ ሌሎች ሁለት ወንድሞቹ እድሜያቸው ሁለቱም 33 መሆኑን ይገልፃል። ወንድሞቹ መንታ አይደሉም። እንዴት ሁለቱም 33 ሊሆኑ ቻሉ? ትምኒትስ እድሜዋ 34 ሆኖ ሳለ እንዴት የመጨረሻ ልጅ ሆነች?

ምላሽ የለውም። ፈገግ ብለህ ማለፍ ብቻ ነው።

ገፅ 231 ላይ ደግሞ እንዲህ ይለናል፣

እኔ ከእስር ቤት ስወጣ እናቴ እልልልልል አለች። እናቴን ከ6 አመታት በፊት ተምቤን ላይ ያየሁዋት ነበር። ተጎሳቁላ ጠበቀችኝ። ወዘተ…”

ስዬ አብርሃ ይህንን ማለቱን ረስቶት ገፅ 118 ላይ ደግሞ እንዲህ ይለናል፣

ፍርድ ቤት ስቀርብ እናቴ በትምኒት ተደግፋ መጥታ ነበር…”

በዚህ አያበቃም። ከመታሰሩ በፊት እናቱን ከወንድሙ ከምህረተአብ ቤት (ምህረተአብ የታሰረ ቀን) አግኝቷት እንደነበርና ሶፋ ላይ ቁጭ ብላ እንደነበር ጭምር ይነግረናል።

ስዬ የሚዋሸው ነገር ለማሳመር ብሎ ይሆን፣ ወይ የውሸት ልማድ ስላለበት አላውቅም። እናቱን በተመለከተ ሶስት የተለያየ ነገር መናገሩ ግን ያስገርማል።
አማካሪዎቹንም ትዝብት ላይ ይጥላል።

ከአንባቢ ርህራሄ ለማግኘት ሲል የሚያሰፍራቸው ማስተዛዘኛ ነገሮችም አሉት።

ለአብነት ስለ ትምኒት ሲገልፅ፣ በ500 ብር ደሞዝ ተቀጥራ የምትሰራ፣ ከደሞዟ ሌላ ገቢ የሌላት ምስኪን ሴት ስለመሆኗ ሊነግረን ሞክሯል። ሱሬ እና ሸሚዝ ብቻ የነበረው የእህቱ ባል ባንድ አዳር እንዴት የሚሊዮን ብር ቼክ ለመፈረም እንደበቃ ግን አይነግረንም።

ገፅ 83 ላይ ደግሞ ስለ ባለቤቱ መኪና መነጠቅ አንስቶ ሲያወጋ፣ የትምኒትን በድህነት መኖር እንደነገረን ረስቶት፣ “እኔ ከታሰርኩ በሁዋላ ባለቤቴ የትምኒትን መኪና መጠቀም ጀመረች” ይላል።

የ500 ብር ደሞዝተኛዋ ትምኒት እንዴት አይነት የቁጠባ ዘዴ ተጠቅማ የ120 ሺህ ብር መኪና መግዛት እንደቻለች ግን አልነገረንም።

የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት ሲገልፅም እንዲሁ በርካታ አስቂኝ ወጎችን አግኝቻለሁ። ገፅ 19 ላይ ከኤርትራ ጋር ለተደረገው ጦርነት የኮማንድ ፖስት አባላት ተብለው የተመረጡ ሰዎችን ስም ይዘረዝራል። እነሱም፣ “ተወልደን ጨምሮ የማእከላዊ ኮማንድ ፖስቱ አባላት መለስ፣ ተፈራ፣ ፃድቃን፣ አባዱላ፣ አበበ (ጆቤ)፣ እና እኔ ነበርን” ይላል።

ስዬ ሳያውቀው ሕወሃት ለሚታማበት ዋና ጉዳይ ማረጋገጫ እየሰጠ ነበር። እዚያው በዚያው ገፅ 49 ላይ፣ “የአባዱላ ፓርቲ በመለስ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ ነው” ሲል ያረጋግጣል። ብአዴንንም “የቤት ስራቸውን የማይሰሩ” ይላቸዋል። ደቡቦችን ደግሞ፣ “አባተ ኪሾን እውነቱን ካወጣህ ስልጣንህን እንድትቀጥል እናደርግሃለን አሉት” እያለ የሃገሪቱ አጀንዳ ሁሉ በህወሃት ፍላጎት የሚሰራ መሆኑን እያረጋገጠ፣ ያረጋገጠውን ደግሞ መልሶ ለማፍረስ ይሞክራል።

ከመነሻው ኮማንድ ፖስቱ ውስጥ አባዱላና ተፈራ እንዲገቡ የተደረገው አማራና ኦሮሞ በሃገር ደረጃ ተወክሎአል እንዲባል ለተመልካች ለማስመሰል መሆኑን ስዬ አያምንም። እውነቱ ግን ያ ነው። በኮማንድ ፖስቱ በሙሉ ትግሬዎች እንዲሆኑ የተደረገው በመላ ሃገሪቱ ዋና ጉዳዮች ላይ ብቸኛው ወሳኝ አካል ህወሃት ብቻ ስለሆነ መሆኑን ማስረጃ ማቅረብ አያሻውም። ስዬ ግን በተዘዋዋሪ ራሱን ያጋልጣል እንጂ ይህን ማመን አይፈልግም። በኤርትራ ጦርነት አመራር ሌላው ኢትዮጵያዊ ለመሞት ብቻ እንጂ አጀንዳው ላይ ለመወያየትና አሳብ ለመስጠት እንዳልተፈቀደለት ስዬ በተዘዋዋሪ አረጋግጦታል። ከዚያም ባሻገር ስዬና ተወልደ የመንግስት መዋቅር ውስጥ አልነበሩበትም። በምን ህግ? በየትኛው አሰራርና ደንብ? በየትኛው የህገመንግስቱ አንቀፅ መሰረት ይሆን ያ ማእከል የተዋቀረው?

የሃገሪቱ ቁልፍ ቦታዎች ሁሉ በትግሬዎች መያዛቸውን ስዬ ብዙ ቦታ በተዘዋዋሪ ገልፆልናል። አምቼ በተባለው ኩባንያ፣ የህግ አማካሪው፣ ኮንሰልታንቱ፣ የመንግስት ወኪሉ፣ ሶስቱም ትግሬዎች ናቸው። ኢዮብ ሃጎስ፣ ፀሃዬ ነጋሽ፣ እና ፍጡርዘአብ ይባላሉ። እነዚህ ሰዎች የያዙት ቦታ ደግሞ ግዢ ለመፈፀም ቁልፍ ቦታ ነው። ሁሉም እዚያው በዚያው በስልክ ያልቃል። በተለይም በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ዝርፊያው በተሳካ መንገድ መቀጠል ችሎ ነበር። ገፅ 365 ላይ በተመሳሳይ በተዘዋዋሪ ራሱን ያጋልጣል። ስለ 600 መኪኖች ግዢ ለማንሳት ተገዶ ነበር። በዚያ ሰበብ ከባንክ ብድር ተፈቅዶላቸው በአንድ አዳር ባለሃብት ስለሆኑ ትግሬዎች ጉዳይ ግን ሳይጠቅስ ሸፋፍኖ አልፎታል።

ገፅ 22 ላይ ደግሞ፣ “ሰራዊታችን ወደ ኤርትራ የሚያደርገው ግስጋሴ ቆሞ ሻእቢያ ከመደምሰስ የተረፈበትን ስንክሳር ወደፊት ታሪክ ያወጣዋል” ሲል ገልፆአል። ሌላ ቦታም እንዲሁ፣ ሰንአፌን አልፎ የሄደው ጦር እንዴት እንደተገታ “እንቆቅልሽ ነው።”

ምን ይሆን ይሄ እንቆቅልሽ? ምን ይሆን ይሄ ስንክሳር?

ስዬ ለምን እዚያው ፍርጥርጥ አድርጎ ሳይነግረን ቀረ? እንቆቅልሹስ ከማን ነው? ስዬ የላይኛው ኮማንድ ቀለበት ውስጥ በአመራር ደረጃ ላይ ነበረ። እንዲያውም መለስ በድምፅ ተሸንፎ፣ ‘የመለስ ደጋፊ ካሱ ይላላ ብቻ ነበር’ ብሎ ራሱ ስዬ ይነግረናል። እና ይሄ እንቆቅልሽ እና ስንክሳር ምን ይሆን? ለምን ስዬ ሳይነግረን ዘለለው? ለመቼ ነው የሚያቆየው? ‘አላውቅም’ ሊል አይችልም። እሱ ነው የላይኛው ከፍተኛ አካል። “መለስን ወይም ኢሳይያስን አሊያም ሲአይኤን ፈርቶ ነው የማይናገረው” ልንል አንችልም። ታዲያ አስመራን ከመቆጣጠር ያገዳቸው እንቆቅልሽና ስንክሳር ምን ይሆን? ስዬ ይህን ሳይነግረን መፅሃፉን ዘጋ። ወደፊትም አይነግረንም። ‘ለምን?’ ቢባል ምንም ስንክሳርና እንቆቅልሽ አልነበረም።

ይህን ጉዳይ፣ “የደራሲው ማስታወሻ” ላይም ገልጬዋለሁ።

በቀጥታ ለመናገር ስዬ እየዋሸና እያጨበረበረ ነው። በጦርነቱ የተቻላቸውን ሁሉ ሞከረዋል! ስላልተቻለም ተመልሰዋል! ሌላ ሰበብ ማብዛት ለምን አስፈለገ? ወያኔ ሰራዊት ባረንቱ ከገባ በሁዋላ ሰራዊቱን አስከትለው 5000 የትግራይን ገበሬ ለዘረፋ አሰማርተዋል። በዚህ ዘረፋም ጀበናና ማርገብገቢያ ብቻ ሳይሆን ማሳ ላይ የነበረ ጥቅል ጎመን ሳይቀር በአህያ እየጫኑ ወስደዋል። ከዘረፋው በሁዋላ ሰራዊቱ ተመልሶ ወጣ። ስለዘረፋው ባረንቱ ሄጄ ከገበሬዎች የሰማሁ ሲሆን፣ “ከእነዚህ ጋር ሲወዳደር የደርግ ሰራዊት ጨዋ ነበር።” ብለው ነግረውኛል።

ውጊያውን በተመለከተ ወደፊት ይፋ የሚሆን ምንም እንቆቅልሽ የለም። ቢኖር እስካሁን እናውቀው ነበር። ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ስዬ የማያውቀው ምንም መረጃ የለም። የሻእቢያ የውጊያ ስልት በወያኔም ሆነ በደርግ በግልፅ ይታወቃል። ሻእቢያ ሃይል ሲበረታበት አንድ እግር በመሬት እያደረገ ማፈግፈጉ አዲስ ስልት አይደለም። ስለዚሁ ጉዳይ መንግስቱ ሃይለማርያም ደጋግሞ ሲናገር ተሰምቶአል። “በየቀኑ በሚደረግ ውጊያ ተራራ እየተነጣጠቅን ስንዋጋ ነው የኖርነው።” ብሏል። ደርግ ከመውደቁ በፊት ሻእቢያ ምፅዋና ከረንን በጦነት ይዞአቸው መልሶ ለቆአቸዋል። የሰው ሃይል እጥረት ያለባቸው ተዋጊዎች የሚጠቀሙበት ዘዴ ነው። ስዬ በመፅሃፉ ይህን በግልፅ ከመናገር ይልቅ አንድ ትልቅ የሚያውቀው ምስጢር ያለ ለማስመሰል ሞክሯል።

“ይህን ምስጢር፣ ይህን ስንክሳር፣ ይህን እንቆቅልሽ ወደፊት ታሪክ ያወጣዋል” ሲል ፃፈ።

ምንድነው ያ ምስጢር?

“መለስ ዜናዊ የተባለው ሰው ለሻእቢያ ምስጢር ያቀብል ነበር!? ኢሳይያስና መለስ በምስጢር ይገናኛሉ? የኢትዮጵያን ሰራዊት ያስጨረሰው ሆን ብሎ መለስ ዜናዊ ነው? የሲአይኤ እጅ አለበት? ወይስ ሌላ ወሬ አለ?”

ስዬ አብርሃ ያልነገረን ምስጢር የት ይሆን ተፈልጎ የሚገኝ? በርግጥ ምስጢር ካለ መለስን ለማጋለጥና እድሜውን ለማሳጠር ጊዜው አሁን ነው። የነፃነት ትግሉን ያጣድፍልናል። ስዬ ያልነገረን፣ “ጊዜ ይመልሰው” የተባለው መረጃ ከተጋለጠ፣ ለመለስ ድጋፍ እየሰጡ ስቃያችንን ያራዘሙ አጎብዳጆችም ወደ ሰፊው ህዝብ ጎራ እንዲመጡ ባገዘ ነበር። በተቀረ ስለ እንቆቅልሽ ማውራት መብት ያለው ከአዛዥነቱ ቀለበት ውጭ ያለ ብቻ ነው።

መቼም የስዬ መፅሃፍ ሳይታወቀው አንዳንድ ምስጢር ማሾለኩ አልቀረም።

አንድ ቦታ ላይ ስዬ፣ “ሾፌሬ ታሰረ። መኪናዬንም ተነጠቅሁ” ሲል ይገልፃል።

ሾፌሩ ስሙ ተከስተ እንደሚባልና የመከላከያ ሰራዊት አባል መሆኑንም ይጠቅሳል። እንዴት ነው ነገሩ? ስዬ የመንግስት መዋቅር ውስጥ የለበትም። የመከላከያ አባልም አይደለም። ሰራዊቱም የፓርቲ አባል አይደለም። እንዴት ነው ታዲያ ስዬ በመከላከያ በጀትና የሰው ሃይል የሚጠቀመው? የወያኔ ህገመንግስት መቼም በየቦታው እርቃኑን እንደቀረ ነው። እና ስዬ ልቡን ሞልቶ የመፅሃፉን ስም፣ “ፍትህና ዳኝነት” ሲል ሰይሞታል።

ሌላ ቦታ ደግሞ ሌላ ታሪክ ያመጣል።

በታሰረበት እለት ፖሊስ ጣቢያ ሄዶ ግርማይ ማንጁስ የተባለውን የፖሊስ አዛዥ፣ እንዴት እንዳስፈራራውና እንዳንቀጠቀጠው ሊነግረን ይሞክራል።

ስዬ ማን ስለሆነ ይሆን ያን ማድረግ መቻሉ? ምን እንድናስብ ይሆንን ይሄን የሚነግረን? “ቤተኛ ነኝ” ለማለት ነው? ምን ለማለት ነው?

ሌሎች ኢትዮጵያውያን ፖሊስ ጣቢያ ሄደው ፖሊሱን በሃይለቃል አይናገሩም። እሱ ያን በማድረጉ፣ “እንዴት ያለ ጀግና ነው!?” ብለን እንድናደንቀው ይሆን የፈለገው?

“ፖሊስ ጣቢያው በር ላይ ቆምኩና ‘ስዬ በር ላይ ቆሞአል።’ ብለህ ንገረው አልኩት። ወዲያው ግርማይ ማንጁስ ወደ ውስጥ እንድገባ ፈቀደ” ሲል ይነግረናል። ታምራት ላይኔን ግን ትግሬ ፖሊሶች በጥፊ ይመቱት ነበር። ይህ ልዩነት እንዳይኖር የሚደረገውን ትግል ስዬ የተረዳው አይመስልም። ሱፐርማን እና ስፓይደርማን ለመሆን ይሞክራል። እንደ ሸዋዚንገርም ጡንቻውን ያሳየናል። የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠይቀው ማንም ማንንም የማያስፈራራበት፣ የህግ የበላይነት የሚከበርበት ስርአት እንዲመጣ አይደለምን?

ሌላ ቦታ ደግሞ EFFORT ከአምቼ 173 መኪኖች መግዛቱን ይገልፅልናል። ገንዘቡ ከየት መጣ? ይህንን አይናገርም።

እንደ EFFORT ስማቸው የደበዘዘና ከመቃብር በላይ ያሉ ለስሙ የአማራውና የኦሮሞውም የንግድ ድርጅቶችም ነበሩ። እነሱ በቅናሽ ከአምቼ መኪና ሊገዙ ጠይቀው እንዳልተፈቀደ ግን ትንፍሽ ሳይል አልፎአል። የዲንሾ ሊቀመንበር የነበረው ዱባለ ጃሌ በራሱ ስልጣን ለዲንሾ መኪኖች በመግዛቱ፣ በስዬ አብርሃ የውርደት ስድብ ደርሶበት ለአእምሮ መቃወስ መብቃቱን “የጋዜጠኛው ማስታወሻ” ላይ መተረኬ ይታወሳል። በግልባጩ ስዬ ወንድሞቹ በቅናሽ መኪና መግዛታቸው ህጋዊ መሆኑን ሊያሳምነን 500 ገጽ ፃፈ።

ለEFFORT የተገዙት 173 መኪኖች የመገጣጠሙ ስራ ለመስፍን ኢንጂነሪነግ ስራው መሰጠቱንም ስዬ ፅፎአል። መቀሌ ላይ የተተከለው የመስፍን ኢንጂነሪንግ ፋብሪካ ስራውን የጀመረባቸውን ግዙፍና ውድ ማሺኖች ከየት እንዳመጣ ግን ስዬ አልገለፀም። ወደፊትም አይገልፅም። የፋብሪካው ከፊል ማሽኖች መንግስቱ ሃይለማርያም ለመከላከያ ኢንጂነሪነግ ደብረዘይት መኮድ ላይ ያከማቻቸው ማሽኖች መሆናቸውን የምናውቅ ከጥቂት በላይ ነን። እነዚህን ማሽኖች በሌሊት እየጫኑ የመውሰዱን የዝርፊያ ስራ ያስፈፀመውና የመራው ስዬ ራሱ ነው።

“ለከፈልነው ደም የሚገባን ድርሻችን ነው” ሲል አልነበረም እንዴ?

መስፍን ኢንጂነሪንግ ሲመረቅ፣ “ይህ ብረታ ብረት ለከሰከስነው አጥንት ምትክ ነው” ብሎ የተናገረው ማነው?

መንግስቱ ሃይለማርያም በብድር ያመጣቸውን ማሽኖች እዳ የኢትዮጵያ ህዝብ ከፍሎታል። ንብረቱ ግን ወደ EFFORT ነው የተላለፈው። EFFORT የመንግስት ተቋም አይደለም።

እዚህ ላይ ታዲያ ፍትህ የታለ? ስዬ ይህን መሰል ነገሮችን በመፅሃፉ ሳይነካ ዘሎታል። ይህን ስለ መሰለ ራሱ ስላስፈፀመው የወያኔ ዘረኛ ቅሌት አንድ ገፅ እንኳ የይቅርታ ቃል ሳይተነፍስ ስለ ወንድሞቹ ንብረት ጉዳይ 500 ገፆች መከመሩ ሳያስደምመኝ አልቀረም።

ሌላ ቦታ ደግሞ ስለ ወንድሙ ስለ አሰፋ አብርሃ ታስሮ መቆየት ሲፅፍ፣

“አሰፋ አብርሃ እስር ቤት እያለ እናታችን ብትሞት መዘዘ አለው?’ ብዬ ለመለስ ዜናዊ መልእክት ላክሁበት” ይለናል።

እና ብዙም ሳይቆይ አሰፋ አብርሃ ተፈታ። የሚደንቅ ነው። እስኪ ይሄን ገልበጥ አድርገን እንመልከተው? ብርቱካን ሚደቅሳ እስር ቤት እያለች እናቷ ቢሞቱስ? መዘዝ የለውም?

“ስዬ ማን ስለሆነ ነው መለስን እንዲህ ማስፈራራት የቻለው?” ተብሎ ቢጠየቅ ምላሹ “ስዬ አሁንም ህወሃት ነው” የሚል ይሆናል። ለመሆኑ ስዬ ለ“ትግል ጓዱ” ለብርቱካን ያን አይነት የማስፈራሪያ መልእክት ለመለስ ለምን ሳይልክ ቀረ?

ምክንያቱ ግልፅ ነው። የብርቱካን መታሰሯ ሳይሆን መፈታቷ ሆነ መዘዙ። የብርትኳን መፈታት የዘገየው መለስን የሚያስፈራራ እንደ ስዬ ያለ “ጀግና” ስለጠፋ ይሆን? “መዘዝ አለው!” ብሎ መለስን በሃይለቃል የሚናገረው ሰው ጠፋ? ስዬ እንዲያ እያለን ነው። የቤተሰብ ጥል እና የባዳ ጥል መሆኑ ነው እንግዲህ…

በህወሃት ዙሪያ በሃብት የተተኮሱ ቤተሰቦችና የኢትዮጵያ ህዝብ የሁለት አለም ሰዎች ለመሆን መብቃታቸውን ማስተዋል ይቻላል። አጀንዳዎቻችን ተለያይተዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ “ፍትህ” ሲልና እነ ስዬ “ፍትህ” ሲሉ ለየቅል ቢሆኑም ተመሳስለው ለመምጣት እየጣሩ ይመስላሉ።

ስዬ 6 አመታት ቢታሰርም ከህወሃት የአስተሳሰብ ቀለበት አለመውጣቱን በዝባዝንኬ ከታጨቀው መፅሃፉ ማጤን አይገድም። አሁንም ወደዚያው ጀምሮት ወደ ተቋረጠበት የአገዛዝና የቅንጦት ህይወት ለመመለስ የቤት ስራውን እየሰራ ነው። ሰይጣን ካገዘው ይሳካለት ይሆናል።

ርግጥ ነው፣ ስልጣን ያባልጋል።
ካልተሳሳትኩ ለገሰ አስፋው ላይ አንድ ቀልድ ተቀልዶበት ነበር መሰለኝ፣
“ጮማውን እንዴት ለመዳችሁት?” ሲባል፣
“በመከራ” አለ አሉ።

የወያኔ የላይኛው ቀለበት ከባዶ ወደ ቢሊዮን ተተኩሰዋል። ይህ ሃብት አስደንግጧቸዋል። ሰው በጠባዩ ሃብት ሲበዛበት ስግብግብና ጨካኝ እየሆነ ይሄዳል። ሞቡቱ ሴሴሴኮ የጭካኔና የስግብግበነት ምሳሌ ነበር። ጁሌስ ኔሬሬ ባዶ እጁን ወደ ምድር መጣ፤ ባዶ እጁንም ወደ መቃብሩ ሄደ። ስሙም የተከበረ ሆነ። እግዚአብሄር ለእኛም እያለቀስን የምንቀብረውን መሪ ይስጠን።

(ጸሀፊውን በዚህ ኢሜይል አድራሻ ማግኘት ይቻላል ttgebreab@gmail.com)