Author Archive

አንድ ዶላር በሃያ ብር ሊመነዘር ነው

Monday, October 3rd, 2011

(AddisNeger Online) — የኢትዮጰያ መገበያያ ገንዘብ እያደር እያገረሸበት የመጣውን የዋጋ ግሽበት መሸከም አልቻለም፡፡ በአገር ቤት የሚካሄዱ ግብይይቶችን ለማካሄድ ያለው አቅም እየዛለ፤ የአሜሪካ ዶላርን ከመሰሉ የዓለም አቀፍ መገበያያ ገንዘቦች ጋር ያለው የምዛሬ ዋጋ ደግሞ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ባለሞያዎቹ ልቅ-ውድቀት (Free fall) የሚሉት አይነት የውጭ ምንዛሬ ዋጋ መቀነስ እየተስተዋለ ነው፡፡ መፍትሄዎች ሁሉ የተሟጠጡበት የሚመስለው ብሔራዊ ባንክም ከብር ጋር መታገልን የመረጠ ይመስላል፡፡
አዲስ ነገር ኦንላይን ምንጮች በዚህ ሳምንት እንደገለጹት ብሔራዊ ባንክ በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት የብርን የአሜሪካ ዶላር የመግዛት አቅም በ15 በመቶ ያህል ለመቀነስ ተዘጋጅቷል፡፡ በዚህም በሰሞኑ መደበኛ የምንዛሬ ገበያ በአማካይ በብር 17.35 ሲገዛ የነበረው የአሜሪካን ዶላር በብር 20 ሊመነዘር ይችላል፡፡
የኢትዮጰያ መንግሥት በተለይ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ እየተባባሰ የመጣውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ አልተቻለውም፡፡ ስለዚህም በዓለም አቀፉ ገበያ የዋጋ ተወዳዳሪነትን ይጨምራል፤ በዚህም የውጭ ምንዛሬ ክምችት ተያይዞ ያድጋል በሚል በተደጋጋሚ የብርን የመግዛት አቅም ማሽመድመድን ብቸኛው አማራጭ አድርጓል፡፡ ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ በወሰደው እርምጃ የብርን የምንዛሬ ዋጋ በ20 በመቶ አውርዶት ነበር፡፡ ይኹንና የታሰበው የገቢ ንግድ ሳይጨምር የዋጋ ግሽበት ከነበረበት ከፍተኛ ምጣኔ እየገሰገሰ የኑሮ ውድነቱን አባብሶታል፡፡
የኢትዮጵያ ትልቁ የኢኮኖሚ አውታር (ማክሮኢኮኖሚ) በዋነኝነት በግብርና ምርቶች ዋጋ መውደቅ እና መነሳት እንዲሁም በውጭ ምንዛሬ ዋጋ መውጣት እና መውረድ የሚገለፅ በመኾኑ፣ በውጭ ምንዛሬ ለውጡ በአብዛኛው ተጎጂ የሚኾነው ከፍተኛውን ሸመታ በምግቦች ላይ ያደረገው ዝቅተኛ ገቢ ያለው የኀብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ ባለፉት ጥቂት ወራትም እንደተስተዋለው የብር የመግዛት አቅም እየወረደ መምጣት መሠረታዊ በሚባሉ ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ለውጥ እንዲከሰት በማድረግ ኑሮ የበለጠ ድኻውን እንዲጫነው አድርጓል፡፡
የአዲስ ነገር ኦንላይን ምንጮች እንደሚገልጹት ከሆነ በዚህ ወቅት በአውሮፓ የሚስተዋለው የኢኮኖሚ አለመረጋጋት በቀጣዮችም ወራት የብርን የመግዛት አቅም እንደሚገዳደረው ይጠበቃል፡፡ በተለይ ከፍተኛ ገቢ እንደሚያመጣ ይጠበቅ የነበረው አበባ ገበያው እየቀዘቀዘ መምጣቱ በቀጣይ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀውን የምንዛሬ ለውጥ ትርጉም አልባ ሊያደርገው ይችላል ፡፡

ባለፉት ጥቂት አመታት እንደተስተዋለው በምንዛሬ ለውጡ አብዛኛው ድኻ ቢጎዳም ወቅቶችን እየጠበቁና ዶላርን እያከማቹ በኢ-መደበኛው ገበያ ለሚሸጡ ነጋዴዎች ሰርግና ምላሽ ነው፡፡ ትላንት በዝቅተኛ ምንዛሬ የሰበሰቡትን የውጭ ምንዛሬ የዋጋ ለውጡን ተከትለው እስከ ኻያ በመቶ ያህል ትርፍ ሊሰሩበት ይችላሉ፡፡
የብር የመግዛት አቅም እየተመናመነ መምጣት የውጭ ምንዛሬን ዝቅ ከማድረግ በተጨማሪ መንግስት ከፍተኛ ምጣኔ ያላቸውን የብር ኖቶች ወደ ገበያው ለማስገባት እቅድ ይዟል፡፡ ለዓመታት ከፍተኛው የመገበያያ ኖት ኾኖ ሲያገለግል የቆየው የ100 ኖት የዋጋ ግሽበት የፈጠረበትን ጫና መቋቋም ባለመቻሉ በቅርቡ የ200 ብር ኖት ወደ ገበያው እንዲገባ ይኾናል፡፡

ነፃነትን የሚሻ ሠራዊት

Tuesday, May 10th, 2011

ግልጽ የኾነ ሎጂክ አለ፤ የኢትዮጵያ ሠራዊቱ ተብሎ ለሚጠራ አባል ሁሉ የሚተረክ፡፡ “ኢሕአዴግ የሕገ መንግሥቱ ጠባቂ ነው፡፡ ኢሕአዴግን መጠበቅ ደግሞ ሕገ መንግስቱን መጠበቅ ነው፡፡ ስለዚህም ሠራዊቱ ግንባሩን መጠበቅ ትልቁ ኃላፊነቱ ነው፡፡” ይህ ከአገር ጥቅም በላይ የገዢ ግንባሩን የሥልጣን ጥማት ለማርካት የሚነገር የሠራዊቱ መመርያ ከሁሉ የአገሪቱ ሕጎች በላቀ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው ነው፡፡ እያንዳንዱ አባልም የስሙን ያህል ያውቀዋል፡፡ ዘወትር እንዲያነበንበውም ይጠበቃል፡፡ እኔም በ1994 ዓ.ም የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅን በተማሪነት ከመቀላቀሌ መመሪያውን መተዳደርያዬ  እንዳደርግ ከወታደራዊ ሳይንስ ስልጠናዎች ይልቅ አብዮታዊ ዴሞክራሲን በሚሰብኩ ስብሰባዎች ተነገረኝ፡፡ ያንጊዜ ከልቤ ላገለግለው በፍቃደኝነት የተቀላቀልኩት ሠራዊት ዘለቂ በኾኑ ብሔራዊ ጥቅሞች አንጻር ተንሸራንቶ መገኘቱ ውሳኔዬ የተሳሳተ መኾኑን ለመገንዘብ ያስቻለኝ ነበር፡፡

ዛሬ በስደት በምኖርበት ባህር ማዶ ያሉ ወገኖችም ኾኑ የ20 ዓመታቱ የአቶ መለስ አገዛዝ ያንገፈገፋቸው በአገር ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ስለመንግስት ለውጥ በስፋት የሚነጋገሩበት ነው፡፡ የነጻነት እጦቱ፣ መራብና መጠማቱ እንዲሁም ያለ አግባብ በእስር መንገላታቱ በቂ ምክንያቶች ቢኾኑም፤ በሰሜን አፍሪካ እና በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት የተገኙት ሕዝባዊ ድሎች ለዛሬው የዜጎች መነቃቃት ግብዓት ናቸው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም በማንኛውም ጊዜ ሊከሰት ለሚችለው የኢትዮጰያ የሕዝብ የአደባባይ ተቃውሞ የሠራዊቱ ሚና ምን ይኾናል የሚለው ዋነኛ መነጋገርያ መኾኑ አልቀረም፡፡

በግብጽ እንዲሁም ሕዝባዊ ተቃውሞ ውጤት ባስመዘገበባቸው ሌሎች አገራት የታዩ የሠራዊቱ የገለልተኝነት ሚና ዛሬ የኢትዮጰያ ሠራዊት ከሚገኝበት ወታደራዊ ስነ ሥርዓት እና መዋቅር አንጻር መመልከቱ ተገቢ እንደሚኾን በማሰብ በሠራዊቱ ውስጥ በተማሪነት እንዲሁም በመምህርነት በቆየሁባቸው ሰባት ዓመታት ውስጥ ያገኘኋቸውን እውነታዎች መሰረት በማድረግ ጥቂት ነጥቦችን ለማካፈል ወደድኩ፡፡ አንድም የብሔራዊ ጥቅምን ዋጋ ከፍ ከማድረግ አኳያ በሌላም በኩልም ደግሞ ተገቢውን ወታደራዊ ሥነ ምግባር ከመጠበቅ አንጻር ዝርዝር አገራዊ ጉዳዮችን ከመተንተን ይልቅ አንኳር በሚመስሉኝ የሠራዊቱ ጉዳዮች ላይ ብቻ ለማተኮር እወዳለሁ፡፡

በፕሮፓጋንዳ ማደንዘዝ

ወታደራዊ ሳይንስ በዲሲፕሊን የታነጸ ጠንካራ ሠራዊት ለመፍጠር ዋነኛው ግብዓት ነው፡፡ እያንዳንዱ የሠራዊቱ አባል ዘመኑ ከደረሰበት ወታደራዊ ብልሃት የቻለውን ያህል እንዲቀስም ሳይንሱን ያለማቋረጥ መመርመር ግዴታውም ጭምር ነው፡፡ ማወቅ ወታደሩን የበለጠ ለሕዝቡ ታማኝ እንዲኾንና የሚጠበቅበትን አገራዊ ግዴታ እንዲወጣ ይረዳዋል፡፡ እውነታው ይሄ ቢኾንም እኔ ባሳለፍኩብት የኢሕአዴግ ሠራሽ ሠራዊት ውስጥ “ማወቅ” የሚለው ቃል ብያኔው ከዚህ የራቀ ነው፡፡

ማወቅ፣ መሠረታዊ የሰው ልጆችን መብት ከመካድ እና ያለማቋረጥ በኢሕአዴግ ካድሬዎች የሚነገሩትን ፕሮፓጋንዳዎች ከማነብነብ ጋር እጅጉን የተቆራኘ ነው፡፡ ሠራዊቱ ከመብቱ ይልቅ ግዴታዎቹን እንዲያብሰለስልና እንዲፈጽም ይጠበቅበታል፡፡ ግዴታ እንጂ መብት የሠራዊቱ አካል አይደለም፡፡ ዘወትር በሚነገረውም ፕሮፓጋንዳ ተገዢ በማድረግ የህሊና እስረኛ ይኾናል፡፡ ለመጥቀስ ያህል ለተራ ወታደር ቴክኒካል ስልጠናዎች ለሶስት ወር ብቻ ያህል ሲሰጡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ እና መሰል ኢሕአዴግ ፕሮፓጋንዳ ሥራዎች እሰከ ስድስት ወር ያህል ይዘልቃሉ፡፡ በየስብሰባውም በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ማጥመቅ እና መደንዘዝ ይቀጥላል፡፡ ብዙ ጊዜም እንደሚስተዋለው በስብሰባዎች የብዙሃኑ የሚመስሉ ጥያቄዎችን መጠየቅ ትልቅ ወንጀል ተደርጎ ነው የሚወሰደው፡፡ አገራዊ አጀንዳዎችም የሠራዊቱ ያልኾኑ ያህል ከከፍተኛ ባለስልጣናት እስካልፈለቁ ድረስ አባላት በስብሰባዎች መካከል እንዲያነሱ አይፈቀድም፡፡

ቀደም ሲል እንደጠቀስኩትም የፕሮፓጋንዳዎቹ ዓላማ ሰራዊቱ መብቱን እንዳይጠይቅ፣ ኢሕአዴግን መጠበቅ  ሕገ መንግስቱን መጠበቅ ነው ብሎ እንዲያምን እና የፕሮፓጋንዳቸው ተገዢ እንዲኾን ማድረግ ነው፡፡ ይህም አብዛኛው ሠራዊት መንግስት ከሚሰጠው ግዳጅ ውጪ በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ውስጥ ሚና እንዳይኖረው እንዲሁም ስለብሔራዊ ጥቅም እንዳያስብ ኾን ተብሎ የተደረገ ነው፡፡

ሠራዊቱ ራሱን ችሎ ህልውና እንዲኖረው ማድረግ በኢሕአዴግ ሰዎች ልብ ውስጥ የሚታሰብ አይደለም፡፡ ብዙ ጊዜ በተለያዩ ስብሰባዎች እንደሚደሰኩሩልን “ኢሕአዴግ ከሌለ ሠራዊቱ ህልውናውን ያጣል፡፡” ስልጠናዎች ሁሉ ከኢሕአዴግ ውጪ የትኛውም አካል የሠራዊቱ ወዳጅ እንዳልኾነ እና የመንግስት ለውጥ ቢመጣ ኣባላቱ ተጎጂ እንደሚኾኑ የሚሰብኩ ናቸው፡፡

እዚህ ላይ በ1997ቱ ምርጫ ወቅት የኾነውን ማስታወስ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ቅንጅት አዲስ አበባ ላይ ድል ማስመዝገቡ ሲነገር በሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች ዘንድ መደናገጥ ተፈጥሮ ነበር፡፡ በሠራዊቱ ውስጥ ተደጋጋሚ እና አሰልቺ ስብሰባዎች የበዙበት፤ አይን ያወጣ ወንጀልም የተስተዋለበት ጊዜ ነበር፡፡ በወቅቱም ከተደረጉት ስብሰባዎች ውስጥ እኔ በነበርኩበት መከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ውስጥ በጥቅምት 1998 ዓ.ም እንዲህ የሚል ውሳኔ ላይ ተደርሶ ነበር፡፡ “ሕዝቡ ተሳስቶ ሊመርጥ ይችላል፡፡ እነዚህ ሰዎች (ቅንጅቶች) ሕገ መንግስቱን ሊንዱ የመጡ ሰዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ መንግስት አዲስ አበባን ለቅንጅት ሰዎች ቢያስረክብም ሠራዊቱ ግን ማስረከብ የለበትም፡፡” ይህ ኣባባል መንግስትና ሠራዊቱ የተለያየ አቋም ያላቸው ለማስመሰል እንጂ የዚህ ሐሳብ ጠንሳሽ አራት ኪሎ እንደሚገኝ ማንም የሚስተው ጉዳይ አልነበረም፡፡

ባይተዋር ወታደር

ይህ በኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ውስጥ የኾነ ታሪክ ነው፡፡ በሰኔ 1997 ዓ.ም አንዲት የሠራዊቱ አባል በላይቤሪያ የሰላም አስከባሪ ግብረ ኃይል ውስጥ መካተቷ ይነገራታል፡፡ ብዙዎች ከግቢው ለመራቅም ይኹን ዳጎስ ላለው ክፍያ ላይቤሪያ መጓዝን እንደ ልዩ ዕድል ያዩት ስለነበር ወታደሯም በአጋጣሚው ደስተኛ ነበረች፡፡ ከደስታዋ ጋር ግን ብዙ አልተጓዘችም፡፡ ለአመራሮቹ ቅርብ የኾነ የሠራዊቱ አባል በላይቤሪያው ጉዞ አልተካተተ ኖሮ በብስጭት ባለዕድለኛ ጉዞውን ሰርዛ ለእርሱ እንድትሰጠው ይጠይቃታል፡፡ እርሷም ቀድሞ ትሻው የነበረው ዕድል እንደኾነ በመግለጽ እንደማትችል ትገልጥለታለች፡፡ እርሱ አልተናደደም ይልቁንም “እኔ ቀድሜ አንቺን ላማክር ብዬ እንጂ ቢሮ ብሄድ ያንቺን ዕድል ለእኔ ይሰጡኛል” ብሎ የሚፈልገውን አደረገ፡፡ የእርሷ ጉዞ ያለፍቃዷ ተሰርዞ ለሌላ ሰው ተሰጠ፡፡

እንዲህ አይነት አድሎ ስራዎች እጅግ የተለመዱ ናቸው፡፡ በአንድ ወቅትም በጥረቱ ያገኘውን የውጭ ትምህርት ዕድል የሌላ ብሔር ስለኾነ ብቻ የተከለከለ የመከለካከያ ኮሌጅ መምህር ራሱን ማጥፋቱ ብዙዎቻችን የሠራዊቱ አባላት በቁጭት የምናስታውሰው ነው፡፡

ይህ የግቢው ለአንድ ብሔር የማድላት ነገር የተለመደ ነው፡፡ ሌሎች ራሳቸውን ባይተዋር እንጂ የሠራዊቱ አካል መኾን የሚያኮራቸው ነገር የለም፡፡ የሻምበልነት ማዕረግ ያለውን ነገር ግን ከትግራይ ክልል ውጭ የመጣን የሌላ ብሔር ተወላጅ  ተራ ወታደር መመርያ ሊሰጠው ይችላል፡፡ በተለይ ከ1997 ምርጫ ወዲህ የሌሎች ብሔር ተወላጆች ሚና ጭራሹኑ እየጠፋ ነው፡፡ ከፍተኛ ስልጣን የያዙ ጥቂቶች አሁንም ቢኖሩም እምነት የሚጥልባቸው ባለመኖሩ በሠራዊቱ ውስጥ አሉ መባላቸው ለቁጥር ካልኾነ በቀር ፋይዳ የለውም፡፡

ላይ ላዩን ለተመለከተው የሠራዊቱ የብሔር ተዋጽኦ ምጥጥን የሚታይበት ይመስላል፡፡ ይሁንና የቁጥር መመጣጠን እና የስልጣን መጋነን ከፍተኛ ልዩነት አላቸው፡፡ የትግራይ ተወላጆች ቁጥር አነስተኛ ቢኾንም የያዙት የስልጣን ድርሻ ግን እጅግ ከፍተኛውን የያዘ ነው፡፡ ለይምሰል ከሌሎች ብሔረሰቦች የተውጣጡ ስልጣን ቢይዙም ቀደም ሲል እንደተገለጸው ዋናው የስልጣን ሞተሩ ያለው በሕወሃት እጅ ነው፡፡ ሠራዊቱ ይህንን በሚገባ ያውቃል፡፡ ነገር ግን ጥያቄ እንዳያነሳ በሕግና በደንቦች ቀንብበው ይዘውታል፡፡ የጋራም ኾነ የግል ጥያቄ እንዲነሳ አይፈለግምና፡፡

በዚህም ወቅት ብዙዎች አማራጭ አድርገው የወሰዱት ከሠራዊቱ ወጥቶ መኮብለልን ነው፡፡ ብዙዎች በተለያየ ምክንያት ከአገር እየወጡ መቅረትን መርጠዋል፡፡ በተለይ የትምህርት ደረጃቸው ከፍ ያሉት (የትግራይ ተወላጆችን ጨምሮ) በሠራዊቱ ውስጥ ያላቻው ቁጥር ከጊዜ ጊዜ እየመነመነ ነው፡፡ ብዙዎቹም እንደወጡ መቅረትን መርጠዋል፡፡

የሥርዓቱ ፈጣሪዎች ለሠራዊቱ ያላቸው ንቀት

በ1997 ቅንጅት አዲስ አበባን ማሸነፉ ሲገለጽ የመሬት መቀራመቱ ለሠራዊቱም ደርሶት ነበር፡፡ በወቅቱ የነበረው ሩጫ ጥቂት በማይባሉ የሠራዊቱ አባላት የተወደደ ባይኾንም ከመንግስት የመጣ መመርያ ነው በማለት ብዙሃኑ አባላት በመሬት ቅርጫው ተሳትፏል፡፡ እውነታውን በወቅቱ ለታዘበ የእናት አገር መሬት ሳይኾን የባእድ ይመስል ነበር፡፡ ነገሩ እንዲህ ታለፈ፡፡ ቅንጅት አዲስ አበባን ሳይረከብ ቀረ፤ መንግስትም እፎይ አለ፡፡

መንግስት መረጋጋቱን ሲያውቅ የመጀመረያው ርምጃ በሰበብ አስባቡ ለቅንጅት አድልቷል የተባለውን አባል መቅጣት ነበር፡፡ እኔም እንደማስታውሰው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመራ አንድ ስብሰባ አዋሽ አርባ ላይ ተደርጎ ነበር፡፡ በወቅቱም መንግስት ራሱ በመመሪያ የፈቀደውንና ያስፈጸመውን የመሬት መቀራመት ጉዳይ አንስቶ “ስግብግብ” የሚል ቅጥያ ለሠራዊቱ በመስጠት ቂሙን መወጣት ጀመረ፡፡ በምርጫው ሂደትም “ሕገ መንግስቱን አልጠበኩም” እንዲል እና ሂሱንም “እንዲውጥ” ተደርጎ ነበር፡፡

በጥቅምት 1998 ዓ.ም በተደረገው የአዋሽ አርባ ስብሰባ ኢሕአዴግ በግልጽ ለሰራዊቱ ያለውን ንቀት የገለጸበት ነበር፡፡ እዚህ ላይ ቢሰፍሩ ጸሐፊውንም ጭምር የሚያስገምቱ ንግግሮች ከአቶ መለስ ይደመጡ ነበር፡፡ ጉዳዩ በዚህ ብቻ አላበቃም ነበር፡፡ በቅንጅት ደጋፊነት የተጠረጠሩ ያለ ፍርድ እስር ቤት ተላኩ፡፡ “በፓርቲዎች ክርክር ወቅት የቅንጅትን አድምጠህ የኢሕአዴግ ሲመጣ ከቴሌቪዠን ክፍል ወጥተህ ሄደሃል” ተብሎ ግምገማ የተደረገበት ሁሉ ሳይቀር ለእስር ተዳረገ፡፡ 20 ሺህ ሠራዊት በአንድ ቅጽበት ተራገፈ፡፡ ታጠቅ መሙላቱን አስታውሳለሁ፡፡ በዚህ ወቅት አፋር በረሃ ላይ ለአራት ወር ያህል በማሰር አሰቃይተው ለቀዋቸዋል፡፡

ኢሕአዴግ ለሰራዊቱ ያለው ንቀት በብዙ መልክ የሚገለጽ ነው፡፡ መብቱን ከመግፈፍ አንስቶ ብሔር ከብሔር እያጋጨ ለሥልጣን ማራዘሚያ እየተጠቀመበት ነው፡፡ ጓደኛ ለጓደኛ እንዳይተማመኑ በማድረግ እንዲሁም የበታች አለቆች የላይኞቹን እንዲያዙ በማድረግ ሠራዊቱን የብሔራዊ ስሜት አሳጥቶታል፡፡

ይህ ከላይ በወፍ በረር የተመለከትኩት እውነታ ዛሬ ኢትዮጵያ አለኝ የምትለው ሠራዊት ማንነት ነው፡፡ ለነፃነት የቆመ የሚባለው ሠራዊት እንደሌላው የማህበረሰብ ክፍል ሁሉ ነጻነትን የሚሻ ነው፡፡ ድምጽ ማሰሚያ ቀዳዳ አጥቶ እንጂ የነጻነት ጥሪው ከሌሎች ቢልቅ እንጂ የሚያንስ አይደለም፡፡ . . .

 

አድጎ ለአባልነት፤ ተምሮ ለግዞት

Tuesday, April 26th, 2011

ኻያ አምስት ዓመት ኾኖኛል። ነገር ግን ይህ ዕድሜዬ ያለፉትን የኢትዮጵያ መንግሥታት በአካል ለመታዘብ እና ለመገንዘብ ላይኾን ይችላል። ይኹን እንጂ በዘመኔ ስለደረስኩበት የወያኔ አገዛዝ እና ትዉልድን የማበላሸት ዉጥን እንዲሁም በአገራችን እየተካሄደ ስላለዉ የትዉልድ ግዞት እኔ ከቋሚ ምስክሮች አንዱ ነኝ።

ልጅ ሳለሁ የኢትዮጵያ ካርታ ከእነሙሉ ቅርጹ በአንዲት እንስት ተመስሎ በየትኛውም የአገሪቱ ክልል፤ በተለይም በክፍለ ሀገር ተጓዥ አዉቶቡሶች ላይ ተለጥፎ መመልክት የተለመደ ነበር። ያ ሙሉ የነበረ የኢትዮጵያ ምስል ከአንገት በላይ ተቆርጦ፤ ካርታዋን በሥነ-ሥዕል ትምህርት ክፍለ ጊዜ እንኳ ለመሳል እስከሚያስቸግር ሰባራ እንስራ መስሎ መመልከት የዘመኔ ተማሪ ያለፈበት እውነታ ኾኗል። ከዚህ አለፍ ሲልም ለየትኛዋ ኢትዮጵያ ክብር እንደኾነ ያልታወቀውን “የዜግነት” መዝሙር መዘመር በዚያዉ በልጅነት ወቅት ያሳለፍኩት ነዉ።

ኋላም አዲስ አበባ ኮተቤ አካባቢ በሚገኘው በደጃዝማች ወንድይራድ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ ኢሕአዲግ/ወያኔ አጨቃጫቂው የኾነውን አንቀጽ 39 ድንጋጌን እንድናምንበት ከክፍል ጎደኞቼ ጋር በፕሮፓጋንዳ ነዢዎች ለውይይት ተጋበዝን፤ እኔም መነሻ ምክንያቱ እና ግቡ ምን እንደኾነ ሳላዉቅ ከክፍል ጓደኞቼ ጋራ ታደምኩ። ሲያልፍም በየቀበሌዉ ለወጣቶች ተብሎ በተዘጋጀዉ የዚሁ አንቀጽ መድረክ (የምርጫ 97 ዝግጅት መኾኑ ነዉ) ተካፈልኩ። በወቅቱ መምህራኖቻችን ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸዉን ማንኛዉንም መልዕክት እንዳያስተላልፉ ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸዉ ጀመር። ምርጫዉም ተደረገ፤ ግር ግር ተነሳ፤ አቶ ተስፋዬ እሸቴ የተባሉ ዩኒት ሊደርን ጨምሮ ብዙ መምህራን ለእንግልትና ለእስር ተዳረጉ።

 

በ1998 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ“ፋካልቲ ኦፍ ቢዝነስ ኤንድ ኢኮኖሚክስ” ዲፓርትመንት ተቀላቅዬ የሥራ አመራር ትምህርት ማጥናት ጀመርኩ። በትምህርቴም ጥሩ ዉጤት አስመዘገብኩን፤ በመመረቂያ ዓመት ላይ ለዩኒቨርሲቲ መምህርነት ጥሩ ዉጤት ያለዉ ተመራቂ ተማሪ ማመልከት እንደሚችል የሚያመላክተውን ማስታወቂያ ባየሁ ጊዜ አመለከትኩ። ነገር ግን የሥራ ዕድሉ ክፍት የኾነዉ ለኢሕአዴግ አባላት ብቻ ነበር። ኋላም በዩኒቨርሲቲዉ የኢሕአዴግ ተወካይ በኾነ ተማሪ አማካኝነት የድርጅቱ አባል እንድኾን ተጠየኩ። ይህ ባይኾን ተመርቆ የሥራ ዕድል ማግኘት ከንቱ ልፋት እንደሚኾን አስረግጦ ነገረኝ። ታዲያ ከጥቂት የዩኒቨርሲቲዉ ተማሪዎች በስተቀር ብዙኀኑ በዚሁ የሥራ ማግኘት ተስፋ የኢሕአዴግ  አባል ለመኾን የተገደደ ነዉ። እኔም ከእነርሱ እንደ አንዱ ኾንኩ።

ከዩኒቨርሲቲ ምረቃው ከአንድ ወር በኋላ “ከባህር ዳር የብአዴን ጽሕፈት ቤት ነዉ” የሚል የስልክ ጥሪ ደረሰኝ። በኢሕአዴግ አባልነቴ በኢትዮጵያ የገቢዎች እና ጉሙሩክ ባለሥልጣን ዉስጥ የሥራ ዕድል እንዳገኘሁ እና ለሥልጠና በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ አጥር ግቢ እንድገኝ አሳወቀኝ። በተባለዉ ወቅት እና ቦታ ተገኘሁ። ሥልጠናዉም በተጀመረበት ወቅት ወደ 450 የሚኾኑ እንደኔዉ ከተለያየ የአገሪቱ ክፍሎች የተወጣጡ አዲስ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን የኢሕአዴግ አባላት በቦታዉ ተገኝተው ነበር። ሥልጠናዉ ለሁለት ተከታታይ ሳምንታት የኢሕአዴግን ፖሊሲ እና ስትራቴጂ በሚመለክት ሲኾን የመጣዉም ሠልጣኝ በሙሉ በቡድን በቡድን ተከፋፍሎ የኢሕአዴግን ፖሊሲ በተመለከተ ዉይይት የሚያደርግበት ነው። በዉይይቱም እያንዳንዱ ሠልጣኝ ምን ብናገር ወይም ምን ስናገር ብሰማ በአወያዮቹ የግምገማ መዝገብ በጥሩ ኹኔታ እመዘገባለሁ ብሎ እንጂ ማንም የሚያምንበትን መናገር የሚችልበት መድረክ አልነበረም። ሥልጠናዉ በአስተባባሪዎቹ እንደተነገረዉ ስድስት ሚልዮን የኢትዮጵያ ብር የፈጀ ነበር። ይህም ለሁለት ወራት መኝታን ጨምሮ ሙሉ የምግብ እና የሠልጣኝ የኪስ ወጪን የሸፈነ ነዉ።

በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ የተደረገዉ ይኸዉ ሥልጠና ለሁለት ወር ያልተቋረጠ የሠርግ ድግስ ይመስል ነበር። ቁርስ፣ ምሳ እና እራት ሙሉ የቡፌ ዝግጅት እና እንዲሁም በሻይ ሰዓት በቀን ሁለት ግዜ በተለያዩ የታሸጉ ዉኃ እና ለስላሳ መጠጦች ከብስኩቶች እና ዶናቶቸ ጋራ የሚቀርብበት ነበር። ይህን ያየ የአገራችንን ድህነት ቢጠራር አይፈረድበትም።

የሥልጠናዉ ማጠናቀቂያ ቀን ደረሰ። ላምበረት አካባቢ በቻይና መንግሥት በተሠራዉ የፖሊቴክኒክ ኮሌጅ አጥር ጊቢ ዉስጥ “ድል ያለ ድግስ” ተሰናዳ። መጠጦች እነ ዉስኪን ጨምሮ በዐይነት በዐይነቱ ቀረቡ። ቀስ በቀስም ዋነኛ እና ቀንደኛ የተባሉት የኢሕአዴግ አባላት እና የተለያዩ መድረክ መሪዎች ከመሥሪያ ቤቱ እና ከዉጭ ተጋብዘዉ መጡ። ቀኑ እየመሸ ሲመጣም የተጠሩት እንግዶች ተሸኙ። ሽኙቱን ተከትሎ ሌላኛዉ ዙር የፌሽታ ድግስ በዲጄ በታጀበ ሙዚቃ ምሽቱ ተጀመረ። ቢራዉ እና ወይኑ በገቢዎች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን መኪኖች እየተጫኑ ግቢውን ሞሉት። በምሽቱ የተሰበሰብነዉ አዲስ የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ ሠልጣኝ አገርን ለማልማት ወይም በአገር እድገት ዉስጥ ተሳትፎ ለማድረግ ሳይኾን ለአምባገነኑ ገዥ ሥልጣን ላይ የመቆየት ሕልም አስተዋጽኦ የማድረግ የጥምቀት ሥነ- ሥርዐት ላይ ነበርን።

ወደ “ክንፈ ማሠልጠኛ ማእከል”

የሁለት ወሩ ሥልጠና እንዲህ በመሰለ ኹኔታ እንደተጠናቀቀ እኔን ጨምሮ 46 የምንኾን ሠልጣኞች ተመርጠን ለተጨማሪ ሥልጠና ታጨን። በመጀመርያ የሥልጠናዉ ይዘት እና ምንነት ለአብዛኞቻችን አልገባንም ነበር። ሥልጠናዉም ለሦስት ወራት እንደሚዘልቅ በአስተባባሪዉ በኩል ተብራራልን። ኋላ ላይ ግን ሥልጠናዉ በኢትዮጵያ የደኅንነት ቢሮ (በክንፈ ማሠልጠኛ ማእከል) እንደሚሰጥ በታወቀ ጊዜ ምን ሊያሠሩን ይኾን በማለት ፍርኀቱ እና ጥረርጣሬው ጨመረ። ኾኖም ግን ይህን ማዉራት ኀጢአት ወይም ወንጀል ይመስል ትንፍሽ የሚል አልነበረም። የእያንዳንዳችን የጣት አሻራ፤ ፎቶ ግራፍ እና የግል መረጃዎች ተወሰዱ። ሥልጠናዉ ጥብቅ ምሥጢር እንደኾነ እና ማንኛዉም የሥልጠና መረጃ በሌሎች መታወቅ እንደሌለበት በማስጠንቀቅ የመረጃ አሰባሰብ ሥልጠናዉ ተጀመረ። ተካልኝ፣ ሰለሞን፣ ገብረ እግዚአብሔር እና ፍትኀ ነገሥት  እንዲሁም ባልሳሳት ገብረ ማርያም በተባሉ አምስት አስተማሪዎች ሥልጠናው ተጀመረ።

የመጀመሪያው የንድፈ ሐሳብ ትምህርተ ስለ ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሲኾን በቀጣይ ስለ አጠቃላይ መሠረታዊ መረጃ አሰባሰብ ሰፋ ያለ ሥልጠና ተሰጠ። ቅድመ ተልእኮ እና ዕቅድ፣ የመረጃ ምንጮች፣ መረጃ ሠጭዎች ምልመላ፣ ስለ ስለላ እና ጸረ ስለላ በሥልጠናው ከተዳሰሱ ርእሶች የተወሰኑት ናቸው።

ከአንድ ወር የንድፈ ሐሳብ ሥልጠና በኋላ የመስክ ልምምድ ተደረገ። በዚሀ ጊዜ የባሰባቸው እና ኹኔታዉን ሊቋቋሙት ያልቻሉ ሲጠፉ እኔን የመሰሉ ጥቂት የሌላ ብሄር ተወላጆች በፍርኀት እና በጥርጣሬ፤ ጥቂት የትግራይ ተወላጅ የኾኑ ደግሞ  ሙሉ ለሙሉ በድፍረት ሥልጠናውን ተከታተልን። እኔ እና መሰሎቼ ዛሬ ነገ ምን ተከትሎ ይመጣ ይኾን ስንልና  ለመዉጣትም ምቹ ኹኔታ ስንጠባበቅ የሥልጠናው ግዜ አለቀ። የክንፈ ማሠልጠኛ ማእከል ዋና አስተዳዳሪ፤ አሠልጣኞች እና የገቢዎች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን ምክትል አስተዳዳሪ በተገኙበት የምረቃዉ ሥነ-ሥርዐት ተካሄደ።

በቀጣዩ ሳምንትም በአፋር ክልል በሚሌ የመግቢያ በር እና በአካባቢዉ በሚካሄደዉ እንቅስቃሴ፤ በተለይም የገዥዉን የኢሕአዴግን ሥልጣን ስጋት ላይ ሊጥሉ የሚችሉ በድንበር አካባቢ የጦር መሣርያ ዝዉዉርን የተመለከተ መረጃ እንድከታተል መመደቤ ተነገረኝ።

ይህ ሲኾን አንድ የተረዳኹት ነገር ቢኖር ለነጻነቴ የመታገል አቅሙ ባይኖረኝ እና መንገዶቹ ቢጠቡም፤ በወቅቱ ላደርገዉ እችል የነበረዉ የመጀመርያ ርምጃ ቢያንስ የዚሁ የጥፋቱ ተባባሪ እና አባል ከመኾን መቆጠብ ነበር። ነገሩ በዚህ ከቀጠለ መዉጫ እንደሌለኝ ስለተገነዘብኩ፤ ምንልባትም “ምንም እንኩዋን ጉዳት ሊደርስብኝ ይችላል” የሚል ስጋት ባይለቀኝም፤ በዚሁ ከገፋሁ የበሰ ችግር እንደሚገጥመኝ በማሰብ በግል እና በቤተሰብ ምክንያት ወደ ተመደብኩበት ቦታ ሄጄ ልሠራ እንማልችል ገልጬ የሥራ መልቀቂያ እስገባሁ። በጊዜዉ የነበረዉ የሥልጠናዉ አስተባባሪ ጥሩ ሐሳብ እንዳልኾነ ነገረኝ። ከዚያ በኋላ በመረጃ ቡድኑ አስተባባሪ ተጠርቼ ወደ ተመደብኩበት ስፍራ ሄጄ የመሥራት ድርጅታዊ ሐላፊነት እና ግዴታ እንዳለብኝ ተነገረኝ።

በዉሳኔዬ ፀንቼ ሳልሄድ ቀረሁ። ከቀናቶች በኋላ በገዛ መንደሬ ከምኖርበት ቤት በሦስት ሰዎች ተደበደብኩ። ለጊዜዉም ቢኾን የመኖርያ አካባቢዬን በመቀየር ለመሰወር ብሞክርም አልቻለኩም። የማደርገዉ እንቅስቃሴ ሁሉ በክትትል ሥር እንደኾነ ተገነዘብኩ። በስተመጨረሻም በየካ ክፍለ ከተማ አቧሬ አካባቢ የሥራ ዕድል አገኘሁ። በኋላም ወረዳ 06 ተቀጥሬ መሥራት ጀመርኩ። ብዙም ሳይቆይ በድጋሚ የኢሕአዴግ አባል እንድኾን በዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ አብዱል ሽኩር በተባሉ ሰዉ ተጠየኩ። ጥቂት ጊዜያቶች እንዲሰጠኝ በመጠየቅ ምላሼን ባዘገየዉም የቡድን አስተባባሪ ሊያደርጉኝ እንደፈለጉ እና በቅድሚያም የአባልነት ፎርም እንድሞላ ጠየቁኝ። በኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የሰንበት ቀኖችን ጨምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ከግቢዉ መዉጣት የማይፈቀድበት የአመራሮች ሥልጠና ስላለ አንሶላ፤ ብርድ ልብስ እና ሌሎችም የሚያስፈልጉኝን ነገሮች ይዤ እንድገባ ተነገረኝ። በድጋሚ ድርጅቱን በመቀላቀል የጥፋት ቡድኑ አባል እንድኾን ግዳጅ መሰል ትእዛዝ እየተሰጠኝ ነበር።

አሁን ከአገሬ ተሰድጄ በውጭ አገር እገኛለሁ። ይህ ሁሉ ያጫወትኩዋችሁ ምን ያህል እነዚህ ጥቂቶቹ የወያኔ አስተዳደር የቡድን አባላት የኢትዮጵያ የተማረ የሰዉ ኀይልን በገዛ አገሩ ለአባልነት አስገድደዉት አገልግሎቱንም ያለ ፈቃዱ እንደሚሰጥ እና ለኢኮኖሚ አስተዋዖኦ ከማድረግ ይልቅ የደኅንነታቸዉ ጠባቂ ዘበኛ እንዴት እየተደረገ ለማመልከት ነዉ። እነዚሁ የኢትዮጵያ አጥፊ የቡድን አባላት በድርጅታቸዉ በተነደፈዉ ዜጎችን የፓርቲዉ ባርያ የማድረግ ዘመቻ የተማረዉን የኅብረተሰብ ክፍልም ለባርነት ከመጋለጡ በላይ ለግዞቱም በየወሩ ሠርቶ ከሚያገኘዉ ደመወዝ ላይ የአባልነት ክፍያ እንዲከፈል ያስገድዳሉ። የፕሮፓጋንዳ መንዣ ጋዜጦቹን እና መጽሔቶቹን የመግዛት ግዴታ ተጥሎበት ማየት ለተገነዘበው ገዥዉ ፓርቲ እና እነዚሁ ጥቂት አመራሮቹ ቅኝ ገዥዎች እንጂ ከኢትዮጵያ ምድር የወጡ አይመስሉም። አዲስ የደኅንነት አገልጋይ ምልምሎችን ለማፍራት ትኩረቱን ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ያዞረዉ የጥቂቶቹ የወያኔ አመራር ቡድኖች ተገዥ የኾነዉ ኢሕአዴግ በእኔ ላይ ስላደረሰዉ አገልግሎትን ያለፈቃድ የመስጠት፤ በሞያዬ እና አገሬ ባስተማረችኝ የእዉቀት ደረጃ እንዳልሠራ እና በነጻነት የመደራጀት መብት ጭምር ነው የነፈገኝ። በወቅቱ የተመለመሉ ሌሎች እኔን መሰል  የዩኒቨርሲቲዉ ምሩቃን በተመሳሳይ መንገድ ለመረጃ ድርጅቱ በመሥራት ላይ ይገኛሉ።

(በአውሮፓ የሚገኙት የጽሑፉ አቅራቢ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉት ለደኅንነታቸው ሲሉ ነው)

 

 

 

መርካቶ የዘይት ወረፋው አይሏል

Monday, March 7th, 2011

(ኤፍሬም ካሳ)
በትናንትናው እለት ማልዶ የተነሳ ሰው ሲኒማ ራስ አካባቢ ረዣዥም ሰልፎችን በመመልከቱ ሊገረም ይችላል፡፡ ከመቼ ወዲህ ነው የማለዳ ቴአትር የተጀመረው ሲል ራሱን ሊጠይቅ ይዳዳው ይኾናል፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ ነጋዴዎች ዘይት ሲኒማ ራስ አካባቢ ከሚገኙ ማከፋፈያዎች ለመግዛት በሚያደርጉት ጥረት ነው የትያትር ቤት የሚመስሉት ረዣዥሞቹ ሰልፎች የሚፈጠሩት፡፡ ላለፉት ስድስት ቀናት ሰልፎቹ ከማለዳው አስራሁለት ሰአት ጀምሮ መፈጠር ይጀምራሉ፡፡ እስከ ቀትር ድረስ ከዘለቁ በኋላም ቢኾን አከፋፋዮቹ መጋዘኖቻቸውን ለምሳ ሲዘጉ ሰልፎቹ የመቀነስም ኾነ የመበተን አዝማሚያ አያሳዩም፡፡

መንግስት በተወሰኑ የፍጆታ እቃዎች ላይ ግሽበቱ የፈጠረውን የኑሮ ንረት ለመከላከል የዋጋ ተመን ካደረገ በኃላ አንዳንዶቹ እቃዎች ከገበያ እየተሰወሩ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከነዚህ መሀል ስኳርና ዘይት ይገኙበታል፡፡ ላለፉት ሁለት ቀናት ‹‹ሀያት›› የተሰኘው ባለ 20 ሊትር የምግብ ዘይት ገበያ ላይ በመጥፋቱ ብቸኛው አከፋፋይ ‹‹ጌት አስ ኢንተርናሽናል›› ለመኾን ተገዷል፡፡ ሌላኛው አከፋፋይ ‹‹አልሳም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር›› ብዙ ሰዎችን ስለመዘገብኩ እነርሱን ሳላስተናግድ ለጊዜው አገልግሎት አልሰጥም በማለት በዚህ ሳምንት ዘይት ማከፋፈል በማቆሙ ከፍተኛ ክፍተት እንደተፈጠረ ነው ነጋዴዎቹ የሚናገሩት፡፡

‹‹ጌት አስ ኢንተርናሽናል‹‹ በበኩሉ ማንኛውንም ዘይት ‹‹ቲን ነምበር›› ወይንም መለያ ቁጥር ለሌላቸው ነጋዴዎች እንዳይሸጥ በመንግስት ስለተነገረው ዘይቱን ከመሸጥ ጎን ለጎን ነጋዴዎቹ ንግድ ፍቃዳቸውንና የመለያ ቁጥሮቻቸውን በክላሰር እየያዙ እንዲያመጡ በመጠየቁ ብዙ ነጋዴዎች ዶክመንቶቻቸውን በእጆቻቸው አንጠልጥለው ወረፋ ለመጠባበቅ ተገደዋል፡፡

ዘይት ጥበቃ

ዛሬ ረፋዱ ላይ በአቶ ጌቱ ገለቴና በወንድማቸው አቶ አስራት የሚመራው ጌት-አስ ኢንተርናሽናል እንደ ‹‹አልሳም›› ሁሉ ከሳምንት በፊት የተመዘገቡ ደንበኞቼን ሳላስተናግድ አገልግሎት አልሰጥም በማለቱ ጥቂት ነጋዴዎች በብስጭት ሰልፉን ጥለው ሲሄዱ ብዙዎቹ ግን ሁኔታው ሊለወጥ ይችላል በሚል ሰልፋቸው ባለበት ቦታ ድንጋይ እያመጡ በመቀመጥ የሚኾነውን ሲጠባበቁ ነበር፡፡

ሃያት ሀያ ሊትር ዘይት ጌት አስ ኢንተርናሽናል በ417 ብር ለመሸጥ ነጋዴዎች ከሳምንት በፊት መመዝገብና ወረፋ መያዝ እንዳለባቸው ይገልፃል፡፡
ባለፉት ቀናት እንደታየው አንዳንድ ነጋዴዎች ሰልፉ ሲረዝምባቸው በአካባቢው በጉልበት ስራ ከሚተዳደሩ ወጣቶች ሰልፍ በሀምሳ ብር እየገዙ ዘይት ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ ተመልክተናል፡፡ ቸርቻሪዎቹ ነጋዴዎች ትርፋቸው የተወሰነና አነስተኛ ኾኖ እንዴት አንድ ሰልፍ በሀምሳ ብር ለመግዛት እንደሚደፍሩ ሲጠየቁ ምላሽ ለመስጠት አይደፍሩም፡፡ ኾኖም ነገሩን ለማጣራት ባደረግነው እንቅስቃሴ ዘይቱን በ417 ብር ነጋዴዎቹ በእጃቸው ካስገቡት በኋላ በጥቁር ገበያ እንደሚቸበችቡት ይነገራል፡፡
አልሳም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በአቶ ሳቢር አረጋ የሚተዳደር ሲሆን ጌት አስ ኢንተርናሽናል ደግሞ የጌቱ ኮሜርሻል ባለቤት በሆኑት በአቶ ጌቱ ገለቴና በወንድማቸው የሚተዳደር ድርጅት ነው፡፡ ሁለቱም የድርጅቱ ባለቤቶች ለገዢው መንግስት ልዩ ልዩ እርዳታዎችን በማድረግ ይታወቃሉ፡፡

የሲሚንቶ፣ የብረት፣ የቆርቆሮ ዋጋዎች በቅርብ ቀናት ጭማሪ ሊያሳዩ እንደሚችሉ በመርካቶ የሚገኙ አከፋፋይ ነጋዴዎች ግምታቸውን ይገልፃሉ፡፡ ለዚህ የሚያቀርቡት ምክንያትም ፋብሪካዎች የመንግስት ተመን አያዋጣንም በማለት መንግስት እርምጃ እንዳይወስድባቸው ብቻ በመስጋት ጥቂት ምርቶችን እየቆነጣጠበ መሸጥ በመጀመራቸው ነው፡፡ ‹‹በምንፈልገው መልኩ ፋብሪካዎች ምርታቸውን ሊሸጡልን አልቻሉም፤ በመኾኑም የዋጋ ንረት እና እጥረት የማይቀሩ ነገሮች ናቸው፡፡›› ይላሉ ያነጋገርናቸው ነጋዴዎች፡፡

በሰበታ ከተማ ከመሬት ሽያጭ ሙስና የተመዘበረው ገንዘብ ለፖለቲካ ሲባል እየተደበሰበሰ ነው

Monday, February 14th, 2011

(ሙሉ ገ.)
• አንድ ሹመኛ በከተማው ያሠሩት ሕንጻ “ሰርቆ ማሳያ” ተብሏል
• ግለሰቡ ከክልሉና ከኦሕዴድ ባለሥልጣናት ጋራ የሪልስቴቶች ባለቤት ሆነዋል
• መሐንዲሱ የ4 ሚልዮን ብር ቤት ሲገነቡ
በኦሮሚያ ክልል የሰበታ- ሐዋስ ከተማ ከመሬት ሽያጭ ሙስና ጋር በተያያዘ በአስተዳደር ሥራ ላይ የነበሩ ከፍተኛ የኦህዴድ- ኢህአዴግ አመራር አባላት ከገቢና ፋይናንስ ቢሮና ከደላሎች ጋር በመተባበር “ከ15 ሚልዮን ብር በላይ ገቢ ወደ ኪሳቸው ማስገባታቸውን አዲሱ አመራር ባደረገው ጥናት አረጋገጠጥኩ” አለ። ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ግን “ተጣራ የተባለው የገንዘብ መጠን ከትክክለኛው ጋራ ሲተያይ እዚህ ገባ የማይባል ነው” ብለዋል።

ሪፖርተራችን ያነጋገራቸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ነዋሪዎች ግን “አዲሱ አስተዳደር አረጋገጥኩት” ያለው የገንዘብ መጠን “የአንድ እና የሁለት የአስተዳደር ሰራተኞች የዝርፊያ ድርሻ ብቻ ነው” ሲሉ ተረጋገጠ የተባለውን የተመዘበረ የገንዘብ መጠን አነስተኛነት ይናገራሉ። “አዲሱ አስተዳደር ፖለቲካዊ ገጽታው እንዳይበላሽ መጠንቀቁን ትቶ የመሬት ምዝበራውን በደንብ ቢያጣራ ትክክለኛውን የዝርፊያ አሃዝ ይደርስበት ነበር” ብለዋል፡፡
ከመሬት ካርታ ሽያጭ ጋር በተያያዘ ሙስና ከወራት በፊት በድንገት በደኅንነት ሠራተኞች በቁጥጥር ስር የዋሉት ከአስራ አምስት በላይ የሰበታ፣ ዓለም ገና እና ወለቴ አካባቢዎች የአስተዳደር ሠራተኞችና መሃንዲሶች አሁንም በቁጥጥር ሥር የሚገኙ ሲሆን በመሬት ድለላ የአስተዳደር ሠራተኞችን ሲያገለግሉ የነበሩ ደላሎች ግን ሰሞኑን መለቀቃቸውን የአካባቢው እማኞች ገልጸውልናል፡፡
በወለቴ፣ ዓለምገና እና ሰበታ ከተሞች ከ1997 ምርጫ ዋዜማ ጀምሮ መሬት በዘመድ አዝማድ፣ በጎሳ፣ በፖለቲካ አጋርነትና በገንዘብ ጭምር በግልጽ ይቸበቸብ ነበር። “የክልሉ መንግሥትም ሆነ የፌዴራል መንግሥት ምንም ዓይነት እርምጃ ሳይወስዱ ፖለቲካዊ ጥቅም ብቻ ሲያተርፉበት ከርመዋል” ብለውናል፡፡
የቀድሞው የሰበታ ከተማ ማኅበራዊ ጉዳይ ሐላፊና የኦህዴድ ኢህአዴግ ከፍተኛ ካድሬ የነበሩት ግለሰብ እና የሰበታ ከተማ ምክትል ከንቲባ የነበሩት አቶ ገዛኸኝ ጎቤ ሰሞኑን በቁጥጥር ሥር ከዋሉት የመስተዳድሩ አባላት ውስጥ ይገኙበታል፡፡ እኝሁ ግለሰብ ምንም ያልነበራቸው የመንግሥት ሠራተኛ የነበሩ ሲሆን በቅርቡ ያስገነቡት በዓለም ገና ከተማ የሚገኝ ባለስድስት ፎቅ ህንፃ በከተማው ነዋሪ ”ሰርቆ ማሳያ‘ ተብሎ ይጠራል ይላሉ የአካባቢው ምንጮች።
አሁን በእስር ላይ የሚገኙት ሌላ ሰራተኛ ደግሞ በ1999ዓ.ም ከሌመን ወደ ሰበታ ተዘዋውረው ሲመጡ “ተራ መሃንዲስ የነበሩ ሲሆኑ በአሁኑ ጊዜ በሰበታ ከተማ በ400 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣበት ቪላ ቤት እና በውስጡም ዘመናዊ ጅምናዚየም፣ የካሜራ መቆጣጠሪያ እና ውድ አውሮፓ ሰራሽ እቃዎች ይገኙበታል” ይላሉ።
ነዋሪዎቹ የቀድሞው የከተማው ማኅበራዊ ጉዳይ ሐላፊ ከበርካታ የኦህዴድ እና የኦሮሚያ ባላሥልጣናት ጋራ በሽርክና በሰበታ፣ በገላን ከተማ እና በደብረዘይት ከተማ ሪል ስቴቶችን ማቋቋቸውን ይናገራሉ። በቅርቡ “በሙስና እና ብልሹ አሠራር ምክንያት” ከሐላፊነታቸው የተነሱት የሰበታ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አቶ ሽመልስ ሀሰኖ “በሕግ ከመጠየቅ ይልቅ የኦሮሚያ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ኃላፊ ተደርገው ተሹመዋል” ሲሉ የዜና ምንጮቻችን ገልጸውልናል፡፡
በጉዳዩ ላይ ለሪፖርተራችን አስተያየቱን የሰጠ አንድ የከተማው ነዋሪ እንደተናገረው “የከተማው እና የአካባቢው ባለሥልጣናት በሙሉ አብረው በፎርጅድ ካርኒ ሸጠው ብር ካካበቱ እና ለራሳቸውም በፎርጅድ ካርኒ ካርታ አሰርተው ቪላ ቤት ከሰሩ በኋላ ጉዳዩን ሕዝብ አውቆት መነጋገሪያ ሲሆን ተጠያቂነቱን ወደ መሃንዲሶቹ ብቻ ማምጣታቸው ተገቢ አይደለም፤ ይህ የሥርዓቱ አጠቃላይ ችግር ነው” ብሏል፡፡

አባይ ፍሰስ ብለው ከካይሮ አዲሳባ

Friday, February 11th, 2011

ከኦባም የምርጫ ፉክክር ወዲህ የብዙ ኢትዮጵያውያንን ትኩረት የሳበ የውጭ ክስተት ካለ የግብጹ አብዮት የመጀመሪያ ይመስለኛል። ሁለቱንም በጉጉት ከተከታተልንባቸው ብዙ የግልና የጋራ ምክንያቶች አንዱ ሁለቱም በአገራችን እንዲሆኑልን ስለምንፈልግ መሆኑ አያከራክርም። ቢቻል ሁለቱንም ባይቻል አንዱን ማግኘት ትልቅ ነገር ነው፤ ሁለቱንም አለማግኘት ደግሞ ያስቆጫል። ቢያንስ ለጊዜው የእኛ እጣ ይህ ነው፤ መቆጨት። መቆጨት የለውጥ መሠረት ሊሆን ይችላል፤ መቆጨት በራሱ ሕይወት እንዳይሆን ከማስፈራቱ በቀር።
እነሆ ሙባረክ በመጨረሻ ባልተመኙት መልኩ ሥልጣናቸውን ለቀቁ። የተመኙትም ቢቀር ከዚህ በተሻለ ክብር ከሥልጣን ለመውረድ የነበራቸውን ዕድል ቀን በቀን አንድ በአንድ ሲያበላሹት ለሚመለከት ግርምት መፍጠሩ አይቀርም። አምባገነኖች የሥነ ልቦና ብቻ ሳይሆን የጤነኛ ግምት (ኮመን ሲኔስ) ቀውስ ውስጥ እንደሚገቡ የሚያስታውስ አጋጣሚ ሆኖብኛል። የግብጽ ሕዝብ እንደ ኅብረተሰብ የደረሰበት የፖለቲካ ብስለት ደረጃ የሚፈተንበት ሁለተኛውና ዋናው ምዕራፍ ሊጀመር ነው። መስቀለኛው መንገድ ለተላላፊዎች ክፍት ሆኗል። ግብጽ ወዴት ትሔዳለች? አንድ የታህሪሪ አደባባይ ታዳሚ “ግብጻውያን አራተኛውን የነጻነት ፒራሚድ አቁመናል” ብሏል። በተስፋ እንመለከታቸዋለን፤ ከመልካም ምኞት ጋራ።

Crowds Celebrate After Mubarak Steps Down (Picture:Metro.co.uk)

ብዙዎቻችን የግብጽን አብዮት ለኢትዮጵያ እንደምንመኝ እገምታለሁ። ከምኞቱ ወጣ ብለን ጉዳዩን መመልከት ስንጀምር ግን መግባባት ቀርቶ መደማመጥ መቻላችንን እጠራጠራለሁ። በዚህ ዙሪያ የሚነሡት ክርክሮች በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው። ከጥያቄዎቹ መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል።
1. ¬የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በተለይም ወጣቱ ይህን አይነት እንቅስቃሴ ለመጀመርና ለመምራት የሚያስችለው ዝግጅት አለው? (የግብጹ አብዮት “መሪ የለውም” ቢባልም ድንገት ከሰማይ የወረደ አለመሆኑንም መዘንጋት የለብንም። ወጣቶች በተለያየ መንገድ ሲያብላሉትና ሲያቀጣጥሉት የሰነበቱት ጥያቄ ነበር።)
2. የኢትዮጵያ መንግሥት (መለስና የቅርብ ጓዶቻቸው)፣ እና በአምሳላቸው የተፈጠሩት ብሔር ተኮር ድርጅቶች ምን እርምጃ ይወስዳሉ? ከእነርሱ በተጻራሪ የቆሙት የፖለቲካ ኀይሎችስ ምን ሚና ይጫወታሉ?
3. እንቅስቃሴት ከሚፈጥረው “የማይቀር” ግጭት ባለፈ “ያልታሰበ” ደም መፋሰስ ሲያስከትል የሚችልበትን አደጋ ምን ያህል መቆጣጠር ይችላል?
4. የኢትዮጵያ ጦር ሚና ምን ሊሆን ይችላል?
5. ይህን መሰል አብዮት ቢቀሰቀስ በአገሪቱ የፖለቲካ መዋቅር፣ ኢኮኖሚ እና የጸጥታ ጉዳይ ላይ የሚያስከትለው ውጤት ምን ሊሆን ይችላል? ጎረቤት አገሮች ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?
6. ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምን አቋም ይወስዳሉ፤ በሒደቱስ የሚኖራቸው ተሳትፎ ምን ሊሆን ይችላል?
7. ከሙባረክ በኋላ የምትኖረው ግብጽ እና ከመለስ በኋላ የምትኖረው ኢትዮጵያ ይመሳሰላሉ? ለምን/እንዴት?
8. የምርጫ 97 ልምድ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊፈጠሩ ስለሚችሉ ሕዝባዊ ንቅናቄዎች የተወው ትምህርት ምንድን ነው?

እነዚህንና መሰል ጥያቄዎችን ማንሣት “የእኛ ጉዳይ ተስፋ የለውም፤ አደጋው ስለሚያል ያለው ባለበት ከመቀጠሉ ሌላ መውጫ የለም፤ ወይም ሕዝቡ ለነጻነት ያለውን ጥያቄ መግፋትና ትግሉን መቀጠሉ አያዋጣም፤ ጥያቄው ለሌላ ጊዜ ይተላለፍ” ብሎ እንደመጠየቅ መወሰድ የለበትም። ንግግሩን በየአጋጣሚው “የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነት፣ ፍትሕ፣ ዴሞክራሲ ይገባዋል አይገባውም? ይህን ታምናለህ አታምንም?” ወደሚል ደረጃ ማውረድ ከጀመርንም በተዘዋዋሪ ለዴሞክራሲ ይደረጋል የሚባለውን ትግል መጉዳታችን አይቀርም፤ ባለህበት እርገጥ።
እውነቱን ለመናገር ከጭቆናና ከአፈና በቀር ከግብጻውያን ጋራ የምንጋራው ብዙ ነገር የለም። ይህን መሰል ውጫዊ ልምዶችን የብሶት ማረሳሻ አድርጎ ከመቁጠር የበለጠና የተለየ እውነተኛ ፍላጎት ካለን እነዚህንና መሰል ጥያቄዎችን መዝለል አንችልም። ራሳቸውን የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እንደራሴዎች አድርገው የሚመለከቱት ብዙዎቹ ብድኖች/ግለሰቦች ይህን መሰል ጥያቄዎችን እያነሱ ለመተንተን (ትንተናው ምንም ይሁን) እና ነገሩን ለማብላላት የተዘጋጁ አይመስሉኝም። ቢያንስ ይህን እያደረጉ ስለመሆኑ ያሳወቁን ነገር ጥቂት ነው። አሁን በየአቅጣጫው የተያዘው ተራ ፉከራና ቀረርቶ ነው። “እኛ የነጻነትና የዴሞክራሲ ታጋዮች! ካይሮ ደርሰናል!” አይነት ፉከራ።
ኢትዮጵያ ውስጥ አንዳች አይነት ሕዝባዊ ተቃውሞ እንደሚቀሰቀስ ለመገመት የተለየ ምጡቅ እውቀት የሚጠይቅ ነገር አይደለም። ይህንን እንኳን ሌላው ሕዝብ ኢሕአዴግ ራሱም የሚክደው ሐቅ አይደለም። አቶ መለስ ይህን አደጋ አስቀድሞ ለመከላከል “ይበጀኛል” ያሉትን እየሠሩ ነው። ጥያቄው የመለስን አምባገነናዊ አገዛዝ የሚቃወመው የተደራጀም ይሁን ያልተደራጀ ኀይል ምን እያሰበና ምን እያደረገ ነው የሚል ነው። ሕዝባዊ ተቃውሞን በራሱ የዴሞክራሲ ግብና ተስፋ አድርጎ መመልከት ግን ግማሽ አደጋ ያረገዘ አመለካከት ነው። ሲብስ ደግሞ የማሰብ ስንፍና የተጠናወተው አመለካከት ነው። ለተሻለ ነጻነትና ልማት ተጀምረው የባሰ አፈናንና ውድመትን የወለዱ ሕዝባዊ ንቅናቄዎችን/አብዮቶችን ማስታወስ አስቸጋሪ አይደለም።
የግብጽን እና የቱኒዚያን ሰላማዊ አብዮች ማድነቅና መመኘት አንድ ጥሩ ነገር ነው። እነዚህ አብዮቶች በአንድ ወይም በሌላ መልኩ በኢትዮጵያ እንዲደገሙ መቀስቀስና መዘጋጀት ደግሞ ሌላ ጉዳይ ነው። የኢትዮጵያው አብዮት ሊኖረው የሚችለውን ገጽታ (ቢያንስ በግምት) ከወዲሁ መተንበይ እና ራስን ከፖለቲካዊ ድጋጤ ለማዳን የምር ማሰብ ግብጻውያን ለሁላችንም የተዉልን የቤት ሥራ ነው። ይህን ፈተና ምን ያህል እንደምንወጣ ለመገምገም ይህ ጉዳይ በየግላችን በኢትዮጵያ ሚዲያ (የአገር ቤትም የውጭም) እና የፖለቲካ ኀይሎች ዘንድ ለምን ያህል ጊዜ መነጋገሪያ ሆኖ እንደሚቆይ መመልከቱ የመጀመሪያው አመላካች ሊሆን ይችላል።

የጥንቱ አገርኛ ግጥም እንደሚለው አባይን ለመሻገር ወይ መታገስ ወይ ድልድይ መሥራት ግድ ነው።

አባይ ጉደል ብለው አልኝ በትሳስ፣
የምን ሆድ ይችላል እስከዚያው ደረስ።

ሰሞኑን ደግሞ አባይ ጥያቄው ሌላ ነው።

አባይ ፍሰስ ብለው ከካይሮ አዲሳባ፣
ሰልፍ አሳምር አለኝ ሆድህ እንድገባ፤
ሰልፍ አሳምሪ አለኝ ሆድሽ እንዳይባባ።

የዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የጡረታ አበል ወደ 1317 ብር ከ36 ሣንቲም ከፍ አለ

Friday, February 11th, 2011

አቶ አየለ ጫሚሶ በጠና ታመዋል

ከ1997 አወዛጋቢ ምርጫ በኃላ የአዲሱ ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ አየለ  ጫሚሶ የአልጋ ቁራኛ ሆነዋል፡፡ ሳምንታዊው ሰንደቅ ጋዜጣ በረቡእ እትሙ እንደዘገበው ሊቀመንበሩ በቤተዛታ ሆስፒታል ሲረዱ ቆይተው አሁን ከፍተኛ የውጭ ህክምና እንደሚያሻቸው ተነግሯቸው ከሆስፒታሉ ወጥተዋል፡፡

ህመሙ የጀመራቸው ካለፈው ታህሳስ ወር ወዲህ እንደሆነ የዘገበው ጋዜጣው ሊቀመንበሩ ከፓርቲው ስራ ገለል ካሉ ሰነባብተዋል፡፡ በደም ግፊት፣ በጨጓራ ህመም እንዲሁም  የምግብ መፈጨት ችግርና በአንጀታቸው ላይ የደም መድማት ሁኔታ እንዳጋጠማቸው ዘገባው አብራርቷል፡፡

የአምስት ልጆች አባት የሆኑት አቶ አየለ ጨሚሶ ታይላንድ ሄደው ለመታከም ህዝብ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው እየተማፀኑ ይገኛሉ፡፡

*                       *                              *

የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የጡረታ አበል ወደ 1317 ብር 36 ሣንቲም ከፍ አለ

ኢፌድሪ የቀድሞ ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የጡረታ አበላቸው ከ1197 ብር ከ60 ሣንቲም ወደ 1317 ብር ከ36 ሣንቲም አለ። በቅርቡ በኑሮ ውድነቱ የተነሳ የተሻሻለው የጡረታ አበል ክፍያ በዝቅተኛ ደረጃ ላሉት ጡረተኞች እስከ 84 በመቶ የሚደርስ ሲሆን ከአንድ ሺህ ብር በላይ የጡረታ አበል ለሚያገኙ ጡረተኞች ግን የ10 በመቶ ጭማሪ ብቻ ነው።

በዚህ መሠረት የቀድሞ የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የ10 በመቶ የጡረታ አበል ጭማሪ 119 ብር ከ76 ሣንቲም ብቻ ነው። ዶ/ር ነጋሶ በቅርቡ የተከበረላቸውን የጡረታ አበላቸውን ከጥቅምት 17 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ በየወሩ ወደ ክፍለ ከተማቸው በሚገኘው ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ በማምራት ጀምረዋል።

የጡረታ አበል ከተስተካከለ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሻሻለውን የጡረታ አበላቸውን ዕረቡ የካቲት 2 ቀን 2003 ዓ.ም የተቀበሉ ቢኾንም  በቀድሞ ፕሬዝዳንትታቸው ሊያገኙት የሚገባቸው ሕጋዊ ጥቅማ ጥቅሞች በ1997 ዓ.ም ምርጫ በትውልድ ቦታቸው ደምቢዶሎ በግል ተወዳድረው በማሸነፍ ፓርላማ ከገቡ በኋላ እንደተቋረጠባቸው  ይገኛል፡፡

እንዲደበዝዝ የተፈረደበት የይድነቃቸው ተሰማ ታሪክ

Monday, November 1st, 2010

ኤርሚያስ አማረ | AddisNegerOnline.com

“የአባቴ መልካም ታሪኮች ብዙ ናቸው፤ ቢያንስ ጥቂቶቹ ሊነገሩለት እና በትክክለኛው መንገድ ሊቀርቡለት በተገባ …” ይህን ያሉት የክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ልጅ አቶ ታደለ ይድነቃቸው ናቸው። በደቡብ አፍሪካ የተዘጋጀውን የዓለም ዋንጫ ምክንያት አድርጎ የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ጋዜጠኛው እስክንድር ፍሬው ካቀረበላቸው ጥያቄዎች መካካል ለአንዱ ከሰጡት መልስ ላይ የተወሰደ ነው።

ይድነቃቸው ተሰማ ፎቶ ምንጭ http://pitchinvasion.net

መልካም ታሪካቸው ቢያንስ ሊነገርላቸው ይገባል የሚባልላቸው ታላቅ የእግር ኳስ ሰው ይድነቃቸው ተሰማ እሸቴ በሕይወት የሉም። ከ23 ዓመት በፊት ነሐሴ 14 ቀን 1979 ዓ.ም አልፈዋል። የተከሉት ስም ግን አላለፈም፤ አልሞተም። ስለ ኢትዮጵያ ኾነ ስለ አፍሪካ እግር ኳስ በተነሳ ቁጥር ይድኔ በዚያ አሉ። አስታዋሻቸውም ኾነ ዘካሪያቸው ብዙ ነው። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በቅርቡ ባሳተሙት “አገቱኒ” በተሰኘ መጽሐፋቸው ክቡርነታቸውን ከስፖርትም ባሻገር የሽምግልና ካባ የተደረበላቸው ሲሉ ይገልጹዋቸዋል። በዚያው የፕሮፌሰሩ መጽሐፍ “እርቅ እና ሽምግልና” በተሰኘው ክፍል አቶ ይድነቃቸው ዛሬ ውሉ ለጠፋበት እና ለጎደፈው ለኢት ጵያዊው የሽምግልና ባህል በሕይወት ባይኖሩም እንደሚመጥኑ ምስክርነት ተነግሮላቸዋል፤ ተጽፎላቸዋል። እውነት ነው፤ ይድነቃቸው ታላቅ ሰው ነበሩ። የስፖርት ብቻ ሳይኾን የነጻነት፣ የአንድነት፣ የፍትሕ እና የጥቁር ሕዝቦች ኩራት መገለጫም ናቸው።

የኢትዮጵያን፣ የአፍሪቃን ከፍ ሲል ደግሞ የፕላኔቲቱን የእግር ኳስ ታሪክ ለመክተብ የሚዘጋጅ የትኛውም ብዕረኛ የይድነቃቸው ተሰማን በጎ ስም እና ሥራ ሳይጠቅስ ካለፈ ታሪኩ ግማሽ ሙሉ ይኾንበታል። እግር ኳስ በ1920ዎቹ በያኔዋ አዲስ አበባ መዘውተር ሲጀምር እነ ይድነቃቸው የተውኔቱ አንኳር ገጸ ባህርያት ነበሩ። በዝነኛው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ውስጥ በሚያስተምሩ የውጪ አገር ዜጎች አማካኝነት ከአዲስ አበባውያን ጋራ የተዋወቀው ተወዳጁ ስፖርት ቀስ በቀስ ከትምህርት ቤቱ ቅጥር ተሻግሮ በአቅራቢው ወደሚገኙ መንደሮች ዳዴ ማለት ጀመረ። በዚህ ጉዞው ላይ እያለ ከይድነቃቸው ጋር አራዳ ላይ ይገናኛል። መልካም እጅ ላይ የወደቀው እግር ኳስ ቀስ በቀስ በእነ ይድነቃቸው መሪነት ኢትዮጵያውያኑ እና ነጮቹ በአንድ መድረክ የሚፎካከሩበትን መንገድ እያበጀ መጣ። በአራዳ ልጆች ጆርጅ ዱካስ እና አየለ አትናሽ አስተባባሪነትም እንግሊዞችን፣ ግሪኮችን፣ ጣልያኖችን እና አርመኖችን ለመፎካከር የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ቡድን ታኅሣሥ 28 ቀን 1928 ዓ.ም ተመሠረተ።

ከምሥረታው ከሁለት ወራት በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስን የተቀላቀሉት ይድነቃቸው በአዲስ አበባ እግር ኳስ ዙሪያ ያላቸው ተሳትፎ እየተጠናከረ መጣ። ትኩረታቸው እንደ ልጃቸው በሚቆጥሩት ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ያነጣጠረ ቢኾንም፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከጣልያን ወረራ በኋላ በይፋ ሲመሠረት ይድኔ ትልቅ ድርሻ ነበራቸው። ቅዱስ ጊዮርጊስ በጦርነቱ ዘመን መጠሪያውን ወደ ሊቶሪዮ ውቤ ሰፈር አራዳ ለመቀየር ሲገደድ ይድነቃቸው እና ጓደኞቻቸው ለቡድኑ የነበራቸው ፍቅር አልቀነሰም፤ ጭራሽ እየጋለ መጣ እንጂ። ከድል በኋላ ቡድኑ መጠነኛ የአደረጃጀት ለውጥ ይዞ ብቅ ሲል ይድነቃቸው የማልያ ቀለም በመምረጥ እና እስከዛሬ ድረስ መዝለቅ የቻለውን የቡድኑን የ”ቪ” ዓርማ ጽንሰ ሐሳብ ከፈረንሳይ ክለቦች በመዋስ ሳን ጆርጅ በተሻሻለ ጎዳና እንዲራመድ ትልቁን በር ከፍተውለታል።

የፉክክሩ ጥንስስ

የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን በአምስቱ የጣልያን ወረራ ዓመታት በውጪ አገር የኮሚዩኒቲ ቡድኖች ላይ ባስመዘገበው ድል የተነሳ በእንጦጦ፣ ስድስት ኪሎ እና ቀበና ሰፈሮች መሰል እና አገርኛ ቃና ያላቸው ቡድኖች እንዲቋቋሙ ፋና ወጊ ኾነ። ኾኖም ጠላት ድል ከተደረገ በኋላ አብዛኞቹ የስድስት ኪሎ እና እና የእንጦጦ ወጣቶች ወደ ጦር ሠራዊት በመግባታቸው ቡድኖቹ ፈራረሱ። ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን አመራሩን ለጆርጅ ዱካስ እና ለይድነቃቸው ተሰማ በመስጠት ይበልጥ ተጠናከረ። በታኅሳስ ወር መጨረሻ 1928 ዓ.ም የተቋቋመው አንጋፋው ቡድን ከምሥረታው ጀምሮ ባሉት ዐሥራ ሁለት ዓመታት አመራር ሲቀበል የኖረው ከተጫዋቾቹ ነበር። ሥራ አስኪያጅ፣ ምክትል ሥራ አስኪያጅ እና ፀሐፊ የሚባል ነገር በጊዮርጊሶች ዘንድ አይታወቅም። በ1940 ዓ.ም ግን ሳን ጆርጅ በተጫዋቾች መተዳደሩን አቁሞ በአዳዲስ አመራሮች መመራትን አሀዱ አለ። አቶ ገብረሥላሴ ኦዳ (የአቶ ገ/መስቀል ኦዳ ወንድም እና የአቶ አብነት ገ/መስቀል አጎት ናቸው) የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ኾነው ተሾሙ። በምክትል ፕሬዚዳንትነት አቶ ተፈሪ ሻረው እና አቶ ጌታሁን አየለ ሲሰየሙ ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ የዋና ፀሐፊነቱን ቦታ ተረከቡ። ይድነቃቸው ከዋና ፀሐፊነታቸው ባሻገር በአሠልጣኝነት እና በተጫዋችነት ያገለግሉ ነበር።

አቶ ገብረሥላሴ ኦዳ በፕሬዝዳንትነት ቢሾሙም የቅዱስ ጊዮርጊስ እስትፋንስ ግን ይድነቃቸው ነበሩ ማለት ይቀላል። ተጫዋች ይመለምላሉ፤ አሠልጣኝ ያማክራሉ፤ ራሳቸውም ያሠለጥናሉ፤ ቡድኑ የፋይናንስ ድጋፍ የሚያገኝበትን መንገድ ይፈልጋሉ፤ ጠንከር ያሉ አስተዳደራዊ ውሳኔዎችንም በግላቸው ያሳልፋሉ። በዘመኑ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከይድነቃቸው፤ ይድነቃቸውን ደግሞ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥሎ ማስቀመጥ ፈጽሞ የሚከብድ ነበር። የአንጋፋውን ክለብ ውስጠ ምስጢር ጠንቅቀው የሚያውቁ ግለሰቦችም በአቶ ይድነቃቸው ተሰማ እና በአቶ ገብረሥላሴ ኦዳ ወገኖች መካከል ለዓመታት የዘለቀው የፉክክር ስሜት የተጠነሰሰው ያኔ መኾኑን አስምረው ያስረዳሉ።

የአሁኑ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ፕሬዝዳንት አቶ አብነት ገ/መስቀልም ይህን የፉክክር መሥመር በመከተል ዛሬ የይድነቃቸው ታሪክ ከአጎታቸው በላቀ መነገሩ ስለሚያማቸው በይድነቃቸው ዝና ላይ ውኃ የመቸለስ ሥራ የሚሠሩ ናቸው። አቶ አብነት ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሐላፊነት በ1993 ዓ.ም ከመጡ በኋላ በሸራተን አዲስ ከወዳጆቻቸው ጋራ በሚያከናውኗቸው ኢ-ወጋዊ የምሽት ውይይቶች ይህንኑ ስሜት የሚያንፀባርቅ እና የሚያጠናክር አስተያየት ሲሰጡ ይደመጣል። በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ የነበሩ ባለሞያ (ስማቸው እንዳይገለጽ ጠይቀዋል) ተመሳሳይ አስተያየቶች ከአቶ አብነት አንደበት ሲወጡ እንዳደመጡ መስክረዋል፤ “አቶ ይድነቃቸው የአጎቴን ታሪክ አላግባብ ተሻምቷል” ሲሉ ።

ዘመነ አብነት

በ1980ዎቹ የመጨረሻ ዓመታት የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ቡድን በአንድ ትልቅ የመወያያ አጀንዳ ተወጥሮ የሰነበተበት ጊዜ ነው። በበላይነት ከሚያስተዳድረው የቢራ ፋብሪካ ጥላ ወጥቶ ራሱን ይቻል ወይስ በፋብሪካው ሥር ቀጥሎ በኮሚቴ ይመራ በሚሉት ሁለት ጽንፎች ደጋፊው ሲያወዛግብ ከርሟል። ክለቡ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ ሥር በኮሚቴ ሲተዳደር ከፍተኛ አመራር ከነበሩት መካከል አቶ ገዛኸኝ አመጠ አንዱ ነበሩ። አቶ ገዛኸኝ በአንድ ወቅት የጊዜውን ኹኔታ ሲያስረዱ እንዲህ ብለዋል፦ “የእግር ኳስ ክለቡ የሚተዳደረው ከድራፍት በርሜል በፐርሰንት በሚሰበሰብ መጠነኛ ገንዘብ ነው። ቀደም ሲል የሚሰበሰበው ገንዘብ ለተጫዋቾች ደመወዝ እና ቦነስ፣ ለምግብ፣ ለሆቴል እና ለልዩ ልዩ አስተዳደራዊ ወጪዎች ይብቃቃ ነበር። እንደ ቡና ገበያ ያሉ ተፎካካሪ ክለቦች ለተጫዋቾች ፊርማ እየከፈሉ ሲመጡ ግን ከድራፍት የሚሰበሰበው ገንዘብ የእኛን ተጫዋቾችም ኾነ አዲስ ለማስመጣት ያሰብናቸውን የሚያማልል ሊኾን አልቻለም። ጭራሽ አዲስ ትጥቅ መቀየር ሁሉ ተሳነን። በአንድ ወቅት ሙሉጌታ ከበደ እና ገ/መድኅን ኀይሌ የተቀደደ ማልያ ሰፍተው ወደ ሜዳ መግባታቸውን ሁሉ አውቃለሁ። እነዚህ ኹኔታዎች የግዴታ ክለቡ ከፋብሪካው ሥር መውጣት እንዳለበት አሳሰቡን። በዚህም የአቶ አብነት ገ/መስቀል ወደ ክለቡ መምጣት መልካም አጋጣሚ ፈጠረልን። አደጋ ላይ የነበረው ቡድናችን አንገብጋቢ ከነበረው የፋይናንስ ቀውስ ተላቀቀ” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አቶ ገዛኸኝ ሽግግሩን በዚህ መልክ ቢያስቀምጡትም ጥቂት የማይባሉ ዕውቅ የቡድኑ ደጋፊዎች ግን “ቅዱስ ጊዮርጊስ አምባገነናዊ እና ለግል ጥቅማቸው ባደሩ ግለሰቦች እጅ ውስጥ የወደቀበት ውሳኔ” ሲሉ የአቶ አብነትን ሹመት እና  ካቢኔ በበጎ አያነሱትም። በብሔራዊ ቴአትር በ1993 ዓ.ም የተደረገው የባለቤትነት ሽግግር ቅዱስ ጊዮርጊስን “ራሱን የቻለ” የስፖርት ማኅበር ቢያስብለውም በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ግን በቢራ ፋብሪካ ሥር በኮሚቴ ሲመራ ከነበረበት ዘመን ባልተሻለ አስተዳደራዊ የዝቅጠት ዘመንን እንዳሳለፈ ያሳላፋቸው ክስተቶች እና ስንክ ሳሮች ምስክርነት ኾነው ይቀርባሉ።

ከስቴዲየም ግንባታ አንስቶ ክለቡን በሁለት እግሩ እስከሚያቆሙት የፋይናንስ እና የገበያ ማስፋፊያ ሥራዎች ድረስ ያሉት ዐበይት ክንውኖች በዐሥር ዓመታት ውስጥ “ከውዝፍ ፋይልነት” ነቅነቅ ማላት አለመቻላቸው በቀዳሚነት ለትችት ከሚያጋልጡት ውስጥ ይመደባሉ። ደብረዘይት ላይ ይገነባል ተብሎ ብዙም ያልተራመደው የሕፃናት ማሠልጠኛ አካዳሚ ጉዳይም ሌላው በአቶ አብነት አስተዳደር ላይ የሚነሳ አንድ ድክመት ነው። በይበልጥ ደግሞ ክለቡን በመውደድ እና በማፍቀር ስም ከሼሑ የሚፈሰውን ንዋይ ለግል ጥቅማቸው ማበልጸጊያ የተጠቀሙ እና የሚጠቀሙ ግለሰቦች መበራከታቸው ሌላው የአቶ አብነት እና የካቢኔያቸው ጥቁር ነጥብ ኾኗል። በወቅቱ አመራር ዙሪያ የተዘረዘሩት አሉታዊ ነጥቦች በየአቅጣጫው ቢበረክቱም ቡድኑ በሜዳ ላይ ባለው ውጤታማነት ዘመነ-አብነት ገደኛ ዘመን ነው ብለው የሚናገሩ ጥቂት አይደሉም። “ይድነቃቸው በአጎታቸው ላይ የወሰዱትን የበላይነት ለመቀናቀን አብነት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፤ በተለይ ደግሞ ከውጤት ጋራ በተያያዘ። በየትኛውም መንገድ ዋንጫ ወደ ቢጫማዎቹ ካዝና ቢመጣ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ፕሬዝዳንት ፍፁም ደስተኛ ናቸው” ይላሉ ከሁለት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ እግር ኳስ የተፈጠረውን ውዝግብ ተከትሎ ከአቶ አብነት ጋራ የቅርብ ግንኙነት ፈጠሩ አንድ ሰው።

ጣጣው ለይድኔም ተርፏል

ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደ ዕድሜው ብዙ ውጣ ውረዶችን ያሳለፈ ታሪካዊ ቡድን ነው። በኢትዮጵያ እግር ኳስ ብቻ ሳይኾን ለነጻነት በተደረገው ትግል እንደ ምልክት የሚወሰድ ክለብም ነው። በእነዚህ የከፍታ እና የዝቅታ ዓመታት ስሙን ከአንዴም ሁለቴ ለመቀየር ተገዷል። የአድሃሪያን አፍቃሪ በሚል ደርግ እንዲፈርስ ፈርዶበታል። ነፍጠኛውን የሚወክል ተብሎ በዘመነ ኢሕአዴግ ግልጽ የአስተዳደር  በደል አድርሶበታል። የቅዱስ ጊዮርጊስን ድንቅ ታሪክ ያለው ወይም የነጻነት ምልክት መኾኑን የማይቀበሉ አሊያም ለመሻር የሚሞክሩ ቡድኖች እና መንግሥታት የይድነቃቸው ተሰማንም ታሪክ እየደፈጠጡ የራሳቸውን ለመጻፍ ሞክረዋል፤ እየደፈጥጡትም ናቸው። ይድነቃቸው በሕይወት ሳሉ አጥብቀው የሚያራምዱት የኢትዮጵያ አንድነት መርኅ በጊዜው በትግል ላይ ከነበሩ ነጻ አውጪዎች ሳይቀር የቀዘቀዘ ትከሻ እንዲሰጣቸው ምክንያት ኾኗል። ዛሬ በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት አመራር ላይ ያሉ ቱባ ባለሥልጣናትም ይህን ቀዳዳ ተጠቅመው አንድም የግል ፉክክራቸውን፤ አሊያም የገዢው ቡድን አጋርነታቸውን ለማሳየት የይድኔን ድንቅ ታሪክ እንዳልነበር ወደ መቁጠር ደርሰው ገሸሽ አድርገውታል። “ነቢይ በገዛ አገሩ አይከበርም” እንዲል!!

የአዜብ መስፍን የስራ ባልደረባ በታክስ ማጭበርበር ታሰሩ

Sunday, October 17th, 2010

የቀድሞው የሕወሓት ታጋይ የኾኑት አቶ ዕቁባይ በርሄ አሁን ታክስ አልከፈለም ተብሎ ክስ የቀረበበትን የሜጋ ሥነጥበባት ማእከል በሥራ አስኪያጅነት ሲመሩ ነበር። ይኹንና እርሳቸው ይህ ድርጅት ታክስ አልከፈለም ተብሎ በተጠየቀበት በ1996 ዓ.ም በሐላፊነት ላይ አልነበሩም። የውስጥ ምንጮቻችን ዘገባ እንደሚጠቁመው በቅርቡ ከወይዘሮ አዜብ መስፍን ጋራ በፈጠሩት አለመግባባት ምክንያት “ታዛዥነት” ባለማሳየታቸው እስከ መሰዳደብ በመድረሳቸው ይህ ክስ ተደግሶላቸዋል ይላሉ የአዲስ ነገር የአዲስ አበባ ምንጮች።

እነዚሁ ምንጮች እንደገለጹት ወይዘሮ አዜብ መስፍን እና አቶ ዕቁባይ የነበራቸው የሥራ ግንኙነት “ነፋስ የማይገባበት” ነበር። ይህ በወይዘሮ አዜብ መስፍን ሥር የሚተዳደር ድርጅት ላለፉት ሰባት ዓመታት ታክስ ባለመክፈል ሲያጭበረብር ነበር በሚል የምርመራ መ፣ዝገብ ተከፍቶበታል። ለዚሁም ተጠያቂ ተደርገው በምርመራ ላይ የሚገኙት አቶ ዕቁባይ በርሄ ቀጣዩን ውጤት ለመስማት ፍርድ ቤቱ ለሚቀጥለው ሰኞ ቀጥሯቸዋል። [ሙሉ ዘገባውን ለማንብብ እዚህ ጋ ይጫኑ)

አቶ አባዱላ ገመዳ አፈጉባኤ፣ መለስ ዜናዊ ጠ/ሚኒስትር ሆነው ተመረጡ

Monday, October 4th, 2010

(AddisNegerOnline.com) — በአሁኑ ሰዓት በተወካዬች ምክር ቤት እየተካሄደ ባለው ጉባኤ በኢፌድሪ ፕሬዝዳንት አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ንግግር የተከፈተ ሲሆን የፕሬዝዳንቱን ንግግር ካደመጠ በኋላ አቶ አባዱላ ገመዳን በአፈ ጉባኤነት አቶ መለስ ዜናዊን በጠቅላይ ሚኒስትርነት መርጦ ለሻይ እረፍት ወጥቷል፡፡

የህዳሴ ሀሳብ በማቅረብ፣ ሀገራችን ባለ ድርብ አሀዝ እድገት ያመጡ ስለሆነ፣ በዓለም አደባባይ ለሀገራቸውና ለአህጉራቸው ኩራት እየሆኑ ስለመጡ ድርጅታችን ኢህአዴግ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አገሪቱን እንዲመሩ በድጋሚ መርጧቸዋል ሲሉ የኢህአዴግ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ኀይለማርያም ደሳለኝ አስታወቁ፡፡

አፈ ጉባኤ አባዱላ በበኩላቸው አንቀፅ ጠቅሰው አቶ መለስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መመረጣቸውን ካበሰሩ በኋላ ቤቱ ከፍተኛ ጭብጨባ ያሰማ ሲሆን አቶ መለስ ራሳቸውም ሲያጨበጭቡ ታይተዋል፡፡ በኋላም እያጨበጨበ ለነበረው ለምክር ቤቱ አባላት ቆም ብለው እጅ ከነሱ በኋላ ቃለ መሀላ ፈፅመዋል፡፡

በእለቱ በአፈ ጉባኤነት የተመረጡት አቶ አባዱላ ተደጋጋሚ ስህተት ሲሰሩ በመቆየታቸው በአዳራሹ የተገኘውን ሁሉ ሲያዝናኑ ነበር፡፡ እርሳቸውም በተሳሳቱ ቁጥር ሲስቁ ታይተዋል፡፡

አጀንዳ ነጠቃ ከባንዲራው ጀርባ?

Saturday, September 25th, 2010

የባንዲራው ቀን አከባበር እና ዙሪያውን የሚከተሉትን ንግግሮች ለሚተነትን ታዛቢ ኢሕአዴግ ቢያንስ በዚህ ጉዳይ “የቀኞቹን” አጀንዳ ማንሳቱ መሠረታዊ ሽግሽግ መሆኑ የሚያሻማ አይደለም። ይህ እርምጃ የኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነት አቀንቃኙን አንድ “ትልቅ” አጀንዳ የሚያሳጣው ነው። እርግጥ ቀደም ሲል እንዳልኩት የባንዲራን ጉዳይ ሁሉም ወገን የሚስማማበት ቢሆን አገረዊ ጠቀሜታው የላቀ በመሆኑ የሚደገፍ ነው። በፓርቲ ፖለቲካ ግን “የአጀንዳው አቀንቃኝ እኔ ነኝ፤ ኢሕአዴግ ደግሞ ተቃዋሚ ነው” በማለት ጉዳዩን አጀንዳ አድርጎ ለቆየው ጎራ ፖለቲካዊ ዋጋ የሚያስከፍለው ነው።
ጥያቄዬ ይህ ጎራ ምን እየተካሄደ እንደሆነ ተረድቷል ወይ የሚል ነው። ሌላው ቢቀር ኢሕአዴግ አጀንዳውን መጋራቱን ሳይነቅፍ ፖለቲካዊ ነጥብ ለማስቆጠር እንደሚችል ወይም ይችል እንደነበር ያውቃል ወይ? ወይስ ኢሕአዴግ አሁን ቢሆን “ባንዲራው ይወክለዋል ለሚባለው ነገር ተግባራዊ ታማኝነት የለውም” ብሎ የሚከራከርበት አጀንዳ አለው? በአርማው ላይ ሕዝበ ውሳኔ ይካሔድ ብሎ መጠየቅ ለዚህ የተሰጠ የታሰበበት መልስ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል?…

በነገራችን ላይ
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲት ንግግር እንዲያቀርቡ የቀረበላቸው ግብዣ እንዳሰቡት አልተሰካም። ጭራሹንም ያልታሰበ ትኩረት ስቦ አሳጣቸው እንጂ። ከንግግሩ በኋላ ወደ መኪናቸው ሲያመሩ አንድ የሚያጽናና ንግግር ለራሳቸው ማድረግ አለባቸው፤ ብቻቸውን….(ለምሳሌ እንዲህ የሚል) ….
ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ