Author Archive

ጥረህ ግረህ ብላ – በወርቁ ለገሠ

Thursday, August 18th, 2011

PDF

ጥረህ ግረህ ብላ
የቤት ሠራተኛ፣ ፓይለት ፕሮፌሰር
የፍ/ቤት ዳኛ መሃንዲስ ሚ/ር
በሥራ አደባባይ አንዱ ካንዱ ሳይበልጥ
የዋሁ ሲፈጋ ጮሌው ሳይቀመጥ፤
የበኩር ልጅ ሳይሆን የፓርቲ ደጋፊ
የዘር ሃረግ ጎታች የጎጥ ተለጣፊ
ሠው በሠውነቱ የተከበረበት
አንዱ ከፍ አንዱ ዝቅ ብሎ ያልታዬበት
ሁሉም ሰርቶ በላ፣ አምራች የሆነበት፤
ሃብት ሳያካብት ተቀማጭ ሳይተርፈው
ዕርዛት ቸነፈር ችጋር ሳይወርፈው
ሁለት ሥራ ሠርቶ
በአንድ ዓይን አንቀላፍቶ
ላብን አንጠፍጥፎ ጉልበትን ሰውቶ፤
አሜሪካ መኖር እንዲህ ከተቻለ
“ጥረህ ግረህ ብላ” ተግባር ላይ ከዋለ
አገሩን ሳይበድል ህዝቡም ሳያዝንበት
ብዙ ሰው ተሰዶ መምጣት ነበረበት።

በወርቁ ለገሠ (8/17/11)

መተተኛ ብዕር!

Friday, June 10th, 2011

 Click here to read

በ25 ደሥተኛ፣ በ45 ጨለምተኛ ይሆናሉ-ወርቁ ለገሠ

Sunday, April 24th, 2011

Click here to read

ምጽዓተ ግንቦት-በወርቁ ለገሠ

Friday, April 8th, 2011

ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

የነዳጅ ማደያ ሮቦቶች እንደሰው ያጭበረብራሉ? (በወርቁ ለገሠ)

Saturday, March 12th, 2011

እዚህ አሜሪካ ኤሌክትሮኒክስ የተገጠመላቸው የነዳጅ ማደያ ሮቦቶች የቀዳንውን ነዳጅ መጠን አሳይተው ዋጋ ይቀበሉን እንጅ ልክ እንደ ሰው ይሸውዳሉ እየተባለ ይወራል። ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

የመሬት ሽሚያ በኢትዮጵያ – በወርቁ ለገሠ

Saturday, March 5th, 2011

የቤልጅጉ ንጉሥ  ሊዎፖልድ 2ኛ  የአፍሪቃን አህጉር ለመቀራመት በ1884 ዓ.ም የበርሊን ኮንፈረንስ እንደጠሩ ይነገራል። በዚህ ኮንፈረንስ ዩናይትድ ስቴትስ ስትቀር ሌሎች ታላላቅ የአውሮፓ መንግሥታት ተወካዮቻቸውን ልከዋል። በሙሉ ለማንበብ ከፈለጉ እዚህ ይጫኑ

እንደማሙሽ እንሳቅ!

Tuesday, March 1st, 2011

ሆድዎትን በዕጅዎ ደግፈው በሁለቱም ዓይኖችዎ ጣምራ የዕንባ ዘለላዎች እስከሚወርዱ ድረስ ከትከት ብለው እንዲስቁ ምክንያት የሚሆን ጓደኛ ካለዎት እንደ ግል ሃኪምዎ ይቁጠሩት። ሳቅ ወይም ቀልድ ጤናማ ህይዎት ለመምራት ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን ምርምሮች አረጋግጠዋል። ሳቅና ጤንነት ምን አገናኛቸው የሚል ጥያቄ ማንሳትዎ አይቀርም። በሁለቱ መካከል ያለው መስተጋብር እንዲህ ነው። በምንስቅበት ጊዜ የሥነ ፍጥረትን ህግ ተከትለው ኬሚካላዊ ለውጦች በሰውነታችን ውስጥ ይካሄዳሉ። ጭንቀትና መረበሽን የሚፈጥሩብን አድሬናሊንና ኮርቲሶል የተሰኙት ኬሚካሎች በሳቅ ጊዜ መጠናቸው ሲያሽቆለቁል በአንፃሩ ፍንድቅድቅ እንዲንል የሚረዱን ኢንዶርፊንስ የተሰኙት ኬሚካሎች መጠን ወደላይ ያሻቅባል።

ታዲያ ሳቅ ሲባል ከአንገት በላይ ከንፈር ሸሽቶ ጥርስ የሚገጥበትን የአሜሪካኖቹን ዓይነት የይስሙላ ፈገግታ ሳይሆን ለማቆም እስከሚቸገሩ ድረስ እንደኮረኮሩት ልጅ ልብዎ እስኪጠፋ የሚከሰተውን ሳቅ ነው። ለአብነት ያህል ይህንን ይመልከቱ። ሌላም አለ። ከልብ በምንስቅበት ጊዜ በሽታ ለመቋቋም የሚረዳን የተፈጥሮ መከላከያ በእጅጉ ይጠናከራል። የኮሜዲ ፊልሞችን የሚያዩ ግለሰቦች ትኩረት ከሚስብ ፊልም ተመልካቾች ጋር ያነፃጸረ ጥናት እንደሚያስረዳው አዘውትረው ኮሜዲ የሚመለከቱ ሰዎች ልባቸው የተሻለ የጤና ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተረጋግጧል። የኮሜዲ አፍቃሪዎች የደም ዝውውር 25% መሻሻል ሲታይበት በአንፃሩ ትኩረት የሚስብ ፊልም ተመልካቾች በ35% ዝቅ ብሎ ተስተውሏል።

ሳቂታነት አመለ ሸጋ ያደርጋል። ቆንጆና ማሽላ ሳይስቁት ይስቃል ስለሚባል በምክሬ ይበልጥ ተጠቃሚ የሚሆኑት የኔ ቢጤ ፉንጋ ከሆኑ ነው። ይሳቁ። ጤናማ ብሎም ቀና ሰው ይሆናሉ። ቀና ሲሆኑ ጨለምተኝነት ለብሩህ ተስፋ ቦታውን ይለቃል። ውድ ወገኖቼ፡ የልባችን ባይሞላም፣ ያሰብነው ባይሳካም፣ በአገራችን ፖለቲካ ወልጋዳነት ብንንጨረጨርም አጋጣሚ ስናገኝ እንደማሙሽ ከትከት ብሎ መሳቅ እንልመድ፡)

በወርቁ ለገሠ (3/1/11)

ጃሎ መገን! (በወርቁ ለገሠ)

Thursday, February 17th, 2011

በአጼ ኃ/ሥላሴም ሆነ ከዚያ በፊት ባላገር መብቱን ያስከብር የነበረው ከመንግሥት በሚመደብለት ፖሊስ ወይም ነጭ ለባሽ አልነበረም።  በጉልበቱ ነው። Read more

ኢትዮጵያዊ ውጣ፣ የህንድ ዜጋ ግባ! (በወርቁ ለገሠ)

Wednesday, February 2nd, 2011

ሃያ አራት የህንድ ዜጎች ኢትዮጵያ በሚገኙ የቆዳና ሌጦ ፋብሪካዎች ተቀጠሩ ተባለ። ለማንበብ እዚህ ጠቆም ያድርጉ

ብኩን አፍሪካውያን ዕንስቶች (በወርቁ ለገሠ)

Sunday, January 30th, 2011

ብኩንነታቸው ላይ አፅንዖት ለመስጠት ዲስ-ግሬስ የሚል ቅፅል የተሰጣቸው የሮበርት ሙጋቢ ባለቤት- ግሬስ ሙጋቢ የባለቤታቸውን 85ኛ የልደት በዓል በ2009 አክብረዋል። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ሚስ ሙጋቢ የሚጠቀሙባቸው መጫሚያዎች ከ3000 በላይ ሲሆኑ እንደየቀለማቸው የፅዳት ቀለም ሳይኖራቸው አይቀርም። ልዕልቷ በየቀኑ አዲስ ጫማ እንዲጫሙ ቢደረግ መጀመሪያ የተደረገውን ጫማ እንደገና ለማጥለቅ ቢያንስ 8 ዓመት ይወስድባቸዋል ማለት ነው። ባለፈው ዓመት እግር ጥሏቸው ፓሪስ በሚገኙ ሱቆች ጎራ ቢሉ 2 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አንድ መቶ ሺህ ዩሮ እንዳወጡ ይነገራል።

በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀሱት ብኩን አፍሪካዊ ልዕልት ሰሞኑን ከቱኒሲያ የፈረጠጡት ለኢላ ትራቤልሲ ናቸው። እኝህ አፍሪካዊ ንግሥት ባለቤታቸውን የቱኒሲያው ዐብዮት ከሥልጣን ኮርቻ ላይ አስፈንጥሮ ሲጥላቸው የነበራቸውን ንብረት በሙሉ ለማሸሽ ጊዜ ቢከዳቸውም ለስደት ኑሯቸው የሚያገለግል 1.5 ቶን የሚገመት ወርቅ በጆሯቸው፣ በአንገታቸው፣ በብብታቸው፣ የተረፈውን ደግሞ በካርጎ አስጭነው ጠፍተዋል።

በተመሳሳይ ጋናዊቷ ልዕልት ኧርነስቲና ናዱ ሚልስ የጋናው ፕሬዚዳንት ሚስት ሲሆኑ እኝህ ንግሥት የሁዋይት ሃውስን የመጎብኘት ዕድል ከገጠማቸው ጥቂት የአፍሪካ ብኩን ዕንስቶች አንዷ ናቸው። “ካልሰጡ አይሰደቡ” የሚለውን የአማርኛ ብሂል እንዴት እንደሰሙት አላውቅም ለሚስ ሚሼል ኦባማ ያበረከቱት ስጦታ ጠቀም ያለና ጥራቱ በካራት ሲለካ ወደር የማይገኝለት ከከበሩ ድንጋዮች የተሠራ የዕጅ ሰዓት መሆኑ ጭምጭምታ ተሰምቷል። ልዕልት ሚልስ ለሚሼል ኦባማ በስጦታ ያበረከቱት የወርቅ ሰዓት ዋጋ ከ48 ሺህ የአሜሪካ ዶላር እንደማያንስ ተገምቷል። የጋና ቸኰሌት ወይም የአገሪቱን የባህል ልብስ በስጦታ ማቅረብ የተሻለ ክብር የሚይቀድጅ ነገር ግን በዋጋ አንፃር እዚህ ግባ የማይባል ሆኖ እያለ የውጭ ሰዓት ዋጋውን ለመክፈል ቀርቶ ለመጥራት የሚያስፈራ ዕጅ መንሻ መስጠት የብኩንነት መገለጫው ነው።

የኛዋም ልዕልት አዜብ መሥፍን በብኩንነት ተርታ ረድፍ ተገቢ ሥፍራቸውን ይዘዋል። እጅግ ውድ በሆኑ የፋሽን ሱቆች በመመላለስ 1ሺህ 200 ሚሊዮን ዩሮ ለባህር ማዶ ነጋዴዎች እንዳቀበሉ ተዘግቧል። አገር ውስጥ የሚጠፋውን ብር ለመተመን በቂ መረጃ ስላላገኘ ይመስላል የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ቤት ይቁጠረው በማለት በዝምታ አልፎታል። ልዕልት አዜብ ያ ሁሉ የወጣትነት ዕድሜያቸው በታጋይነት ባያልፍማ ኖሮ የኢትዮጵያ ህዝብ ካሁኑ በባሰ መልኩ የሚላስ የሚቀመስ አያገኝም ነበር። ተመስገን ማለት ደግ ነው። ይህንኑ ማን አየበት?

የደቡብ አፍሪቃዋ ኖምፑመሌሎ ንቱሊ ዙማ፣ ካሜሩናዊቷ ቻንታል ቢያ፣ የኮንጎ ብራዛቪሏ አንቶኒ ሳሱ ንጌሶ ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም የሃገር ሀብት የዘረፉ ብልሹ አፍሪካዊ ዕንስቶች ናቸው ተብሏል። የብክነት ሚዛን እንደመሥፈርት ከተወሰደ የስዋዚላንዱ ንጉሥ ምስዋቲ ሳልሳዊ ከመሰል አቻወቻቸው ሻል ብለው ተገኝተዋል። በ2009 ዓ.ም 13 ሚስቶቻቸውን በጋራ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ ዱባይና ታይዋንን እንዲጎበኙ ላኳቸውና ሲመለሱ ለንጉሡ ያቀረቡት የወጭ ደረሰኝ 5 ሚሊዮን ዩሮ ብቻ ነበር። ለ13 ልዕልቶች ይህ ብዙ ወጭ አይደለም። ብዙ ነው ከተባለም የአወጣጥ ዘዴው ይሁንታ ሊሰጠው ይገባዋል። መቼም አንዷ ብቻዋን ከምታጠፋው ለ13 ዕንስቶች ማከፋፈል ብልህነት ነው።

አይዘገንንም? እርግጠኛ ነኝ እያንዳንዱ አገር ያፀደቀው ህገ መንግሥት “የሀገርን ሀብት የሥልጣን ከለላ በመጠቀም ማባከን ወንጀል ነው” የሚል አንቀጽ ይኖረዋል። የዚህ ዓይነቱ ገደብ የለሽ ስግብግብነት በሰው ልጆች ዘንድ የሚከሰት ብልሹ ሥነ ምግባር ከመሆን አልፎ ባህርያተ እንስሳ የተላበሰ እኩይ ድርጊት በመሆኑ ውጉዝ ከመ አርዮስ ልንለው ይገባል ። ከዚያ ሁሉ ድሃ ጉሮሮ ላይ እየነጠቁ መዋዕለ ንዋይ እንደውሃ ማፍሰስ ብኩን የሚለው ቃል አይገልጸውም። በላዔ ሰብ መሆን ነው።

በወርቁ ለገሠ(1/29/11)
ምንጭ፡ ኤቢሲ ኢንተርናሲዮናል

ሁለት ክፉ ካገር ይጥፉ

Wednesday, January 26th, 2011

ሰሞኑን በኢትዮሜዲያ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን የድረሱልኝ ጥሪ ሳነብ አዘንኩኝ። የኦርቶዶክስ ሃይማኖትና የሳይንስ ተቋማት ኮሶ ከተጣባቸው ቆይቷል። አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ሆነው ሲሾሙ ማልቀስ፣ ምህላ መግባት፣ ኢትዮጵያ ታበጽህ ዕደዊሃ ሃበ እግዚአብሄር ማለት ያን ጊዜ ነበር። አቡነ ጳውሎስ የክርስትና ዕምነት ተከታያቸውን የመንግሥተ ሠማያት በር ሊያስከፍቱለት ቀርቶ ምድራዊ ህይወቱን አምሳለ ሲዖል አድርገውበት አረፉ። የሲኖዶሱን ህግ የጣሰ የፓትርያርክ ሲመት ሲሰጣቸው ኤሎሄ ኤሎሄ፣ አልሻዳይ፣ ፀባዖት አዶናይ ብሎ ወደሰባቱ ሰማያት መጮህ ያን ጊዜ ነበር።

ልክ እንደ አቡነ ጳውሎስ ሲመት ሁሉ የከፍተኛ ትምህርት መተዳደሪያ ደንብ ተጥሶ በሳያንሱ ህብረተሰብ ጫንቃ ላይ ከየት መጣ ሳይባል ፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴ የሥልጣን ርካብ ሲረግጥ ያን ጊዜ ነበር ለአልበርት አነስታይን፣ ለኒውቶን፣ ለአርኪመዲስና ለአርስቶትል አምላክ ስምዓነ አምላክነ ወመድሃኒነ ብሎ ሱባዔ መግባት ።

የአቡነ ጳውሎስ ጦስ በመዲናይቱ ኗሪ በሆኑ ምዕመናን ብቻ ተወስኖ አልቀረም። በመላ አገሪቱ የሚገኙ አድባራትን በጎሳ ወረርሽኝ እንድለከፉ በማስገደዱ ልጽደቅ ብትል እረስ፣ ልኮነን ብትል ቀድስ የተባለው ደረሰ።፡ይባስ ብሎ ድንበር ዘለል ጠባይ በመላበስ ባህር ማዶ ተሻግሮ አሜሪካንና አውሮፓን ሲንጠው ውሎ ሲንጠው ያድራል። በተመሳሳይ የፕሮፌሰር እንድርያስ እሼቴ መዘዝ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተወስኖ አልቀረም። መላው የሃገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች አርማውን አንስተው ተግባር ላይ አውለውታል። የእንድርያስ እሸቴን ፈለግ መከተል የግድ ነው። እንደንጉሡ አጎንብሱ ነዋ!
አቡነ ጳውሎስ ሃውልት ሲያቆሙ ተከታዮቻቸው የመሠረት ድንጋይ ቢጥሉ አያስኮንናቸውም። ተከተል አለቃህን ተመልከት ሰንደቅህን ነው። አዲስ አበባ ያሉ አድባራት ቁልፍ ቦታዎች ለጳጳሱ ታማኝ የሆኑ ቀሳውስትና ዲያቆናት ሲደለደሉ በተዋረድ የሚገኙ የትንንሽ ከተሞችና የገጠር የሃይማኖት ተቋማት አሠራሩን ኮርጀው መጠቀም ግደታቸው ነው። አባ ጳውሎስም ለዘመናት የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ደሴት ሆና የቆየችውን የቤተክርስቲያን የሃላፊነት ቦታዎች እርሳቸውና መንግሥትን ብቻ በሚደግፉ እፉኝቶች መዳፍ ውስጥ ጣሉት። ለሰው ሞት አነሰው የሚለውን አነጋግር መላልሰን የምናነብበት ዘመን ላይ አደረሱን። እንፀልያለን፣ ፈጣሪ ፊቱን ዞሯል። እንዘምራለን፣ ዝማሬ መላዕክትን ለመስማት አልታደልንም።

ፕሮፌሰር እንድርያስና አቡነ ጳውሎስ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የተደቀነ የምፅዓት ምልክቶች ናቸው። ፕሮፈሠሩ የሳይንስ ጠበብት ነኝ ቢሉም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን አያውቁትም፣ አያውቃቸውም። ከአሜሪካ ግዛት ተወርውረው ድንገት አራት ኪሎ ተተከሉ። በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የዘመናዊ ትምህርት ፈር የቀደደ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥራትና ይዘት ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ልምድ እንዲቀስም አስገደዱት። ልምዱንም ቀሰመ። ሹመት በትምህርት ሳይሆን በፓርቲ አባልነት የሚለውን አቋራጭ መንገድ ከፈተ። በሳይንሱ ጎራ አንቱ የተሰኙ ምሁራን ግን “እያንጓለለ” የሚለው የዛር ድቤ ተጎሰመባቸው። ሳይንስና ሶሻል ሳይንስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደራሂሎ ተሸኙ። ራሂሎ ሂጅ ቶሎ ቶሎ። ፋከልቲ ተወለደ ፣ ሳይንስ ሞተ። ዶክትሬት ተወለደ፣ ምርምር ሞተ። ተማሪ ተፈለፈለ፣ ትምህርት ሞተ። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደፀጉራም ውሻ ክሳቱ ሳይታወቅ እየሞተ መሆኑን ሰበር ዜና ሰማን።
ለማንኛውም ፀረ ሃይማኖተ አበው የሆኑትን ጳጳስና ሳይንስን ሳይገንዙ የቀበሩት ፕሮፌሰር ሁለት ክፉ ካገር ይጥፉ ብለን መፀለይ እንጅ ሞታቸውን መናፈቅ አይበጀንም። ምክንያቱም “ጌታ ሆይ ክፉ ሰው አታምጣብኝ” ብላ ግዑዟ መሬት ፈጣሪዋን ትለምናለች አሉ። ምህላዋ መልስ ካገኘ የኔ ቢጤው ገራገር በነሱ ምትክ መጥሪያ እንዳይላክለት ብናዝንለት መልካም ነው።
ቸር ይግጠመን
ወርቁ ለገሠ (01/26/11)

የዓለማችን አማካይ ሙቀት ጨመረ (ወርቁ ለገሠ)

Wednesday, January 19th, 2011

አንድ መቶ ስልሳ ዓመት (1850 ዓ.ም) አንስቶ የተመዘገበውን የዓለማችን አማካይ ሙቀት መሠረት በማድረግ ያለፈው 1998 ከፍተኛው ሙቀት የተከሰተበት ሲሆን 2010 ደግሞ ሁለተኛ ሆኗል። የብሪታኒያ ኢንስቲትዩት ሰሞኑን እንዳስታወቀው ይህ መረጃ የዓለም አየር ንብረት ቀስ በቀስ እየተዛባ መምጣቱን ይጠቁማል ብሏል። ከታች ሥዕሉ እንደተመለከተው ከዓለማችን አማካይ ሙቀት ጋር ሲነፃፀር 1998 ከ0.5 ድግሪ ሴንቲግሬድ፣ 2005 ደግሞ ከ0.47 በላይ ተመዝግቦባቸዋል።፡ፊል ጆንስ የተባሉት የብሪታኒያ የአየር ንብረት ምርምር ዳይሬክተር እንደሚሉት ከሆነ ያሳለፍነው ዓመት ከ1961-1990 የነበረውን አማካይ ሙቀት በ0.5 ብልጫ አሳይቷል።

በብሪታኒያ የአየር ንብረት የሚከታተለው ኢንስቲትዩት በዓለም ካሉት 3 ግዙፍ ማዕከላት አንዱ ነው። ሁለቱ የሚገኙት እዚህ ዩናይትድ ስቴትስ ሲሆን እነሱም በበኩላቸው 2010 እጅግ ሞቃት ከሚባሉት ውስጥ ይመደባል ብለዋል። በዚህ መረጃ መሠረት ከ2008 በስተቀር ከ2001-2010 የነበሩት ዓመታት ከፍተኛ ሙቀት ከታየባቸው ከ1-10 ባለው ደረጃ ውስጥ ይካተታሉ። ይህ የሚያሳዬው በግሪን ሀውስ ጋዝ ምክንያት ዓለማችን ከወትሮው እየሞቀች መምጣቷን ነው።

የዓለምን አማካይ ሙቀት ለመቀነስ የሚደረገው ትግል በተፈጠረው የምጣኔ ሃብት ቀውስ የተነሳ ለአማራጭ ሃይል ምንጭ ፍለጋ የሚመደበውን መዋዕለ ንዋይ ክፉኛ የጎዳው ከመሆኑም ባሻገር የዓለም መንግሥታት በ2012 ዓ.ም. የሚያበቃውን የኪዮቶ ስምምነት ሊተካው የሚችል ተቋም ሳይመሠረቱ ተበትነዋል።


ያም ሆነ ይህ አሁን የተገኘው መረጃ ሰው ሠራሽ የአየር ንብረት መዛባት መላ ምት ሳይሆን ገሃዳዊ መሆኑን ያጠናክራል ተብሏል።

የአየር ንብረት መዛባት ባስከተለው ተፅዕኖ ምክንያት ሩሲያ፣ ቻይናና አርጀንቲና በድርቅ መጎዳታቸውን ተከትሎ የምግብ ዋጋ ግሽበት ታይቷል። ባለፈው ዓመት ደግሞ ፓኪስታንና ቻይና በከባድ ጎርፍ ክፉኛ መመታታቸው የአየር ንብረት መዛባት ጦስ የት እየለሌ መህኑን ያስረዳል።

የአየር ንብረት መዛባት የሚያስከትለው ሙቀት ብቻ አይደለም። ለምሳሌ አንዳንድ የአውሮፓ፣ ራሽያና የዩናይተድ ስታተስ ግዛቶች በ2010 ከፍተኛ ቅዝቃዜ ተከስቶባቸው ነበር።

ባለፈው ወር በካንኩን ሜክሲኮ የተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ስብሰባ የአየር ንብረት መዛባት ለሚያጠቃቸው ድሃ አገራት ገንዘብ ለማሰባሰብ ስምምነት ላይ ተደርሷል። ነገር ግን የኪዮቶውን ስምምነት ተክቶ የአየር ብከላን ለመቀነስ የበለፀጉ አገሮች መውሰድ የሚገባቸው ዕርምጃ ተቀባይነት አላገኘም።


በርግጥ መንግሥታት በካንኩን ስብሰባቸው ላይ የዓለም አማካይ ሙቀት ኢንዱስትሪዎች ከመስፋፋታቸው በፊት ከነበረው ሙቀት ቢበዛ ከ2 ድግሪ በላይ መጨመር እንደማይኖርበት ተስማምተዋል። ነገር ግን ስምምነቱን በተግባር ለመተርጎም እያንዳንዱ አገር ሊወስደው የሚገባ ዕርምጃ በግልፅ ስላልተቀመጠ የተፈለገውን ለውጥ ማምጣት አስቸጋሪ ይሆናል።

ይህ በ እንዲህ እንዳለ የዓለም የሃይል ምንጭ ሥጋት ዝቅተኛ ለአየር ንብረት ተስማሚ የሆኑ አማራጭ ምንጮችን ለማፈላለግ መዋ ዕለ ንዋይ መፍሰሱ አይቀርም፣ ይህም እግረ መንገዱን የአየር ንብረት መዛባትን ሊቀንስ ይችላል የሚል ተስፋ አለ።

ምንጭ፡ ሬውተርስ የዜና ወኪል

ኢንተርኔትና ዲሞክራሲ

Sunday, January 16th, 2011

የቤላረስ ተወላጅ በሆኑት ኢቭጀኒ ሞሮዞቭ ኢንተርኔትና ተምኔታዊ ግንዛቤው፡ የኢንተርኔት ነፃነትና አሉታዊ ተፅዕኖ በሚል ርዕስ የተጻፈ 408 ገፆችን ያካተተ አዲስ መጽሓፍ ገበያ ላይ ውሏል።

በሽህ የሚቆጠሩ የኢራን ወጣቶች ሰኔ ወር 2009 በተደረገው ምርጫ ድምፃችን ተነጥቋል በማለት ሠላማዊ ሠልፍ የወጡ ተቃዋሚዎችን አስመልክቶ ምዕራባውያን የዜና አውታሮች ትዊተር የተሰኘውን ብሎግ የተጫወተው ሚና በተጋነነ መልኩ ዘግበዋል። ለምሣሌ የወል ስትሪት ጆርናል በኢራን የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ያለ ትዊተር ፈፅሞ የሚታሰብ አልነበረም ብሏል። ተቀማጭነቱ አሜሪካ የሆነ አንድሪው ሱሊቫን የተባለ የብሎግ ፀሃፊ የኢራንን ጨቋኝ ሥርዓት ለመታገል ይቻል ዘንድ ትዊተር ቁልፍ ሚና እንደተጫወተ ይጠቅሳል። የኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣም በበኩሉ ሠልፈኞች በትዊተር አማካይነት ደጋፊዎቻቸውን ለአመፅ ሲያነሳሱ የመንግሥት የፀጥታ ቡድኖች ተኩስ የከፈቱባቸው መሆኑን አስታውቋል።

እንደሌሎች የመገናኛ ቴክኖሎጅዎች ሁሉ የኢንተርኔት መረጃ ዐብዮታዊ ትግልን በማፋፋም ግፉዓንን ዲሞክራሲያዊ መብት ያላብሳል የሚለው እሳቤ ሰፍኖ የቆየ አመለካከት ሲሆን ከላይ ለማሳዬት እንደተሞከረው የኢራኑ ምርጫ በዋቢነት የሚጠቀስ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ሞሮዞቭ የጻፉት መፅሃፍ ይህን የሳይበር ተምኔታዊነት በፅኑ ይቃረናል። ደራሲው የሚሰጡት አመክንዮ ኢንተርኔት አፋኝ ሥርዓቶችን ለመገርሰስ የሚያስችለውን ያክል በአንድ አገር ላይ አፈና ተንሰራፍቶ እስከወዳኛው እንድቆይ ጠቃሚ መሣርያ ሆኖም ሊያገለግል ይችላል። አውቀውም ሆነ ሳያውቁ የምዕራቡ ዓለም ፖሊሲ አርቃቂዎች ኢንተርኔት ዲሞክራሲን ለማራመድ ፍቱን ዘዴ ነው የሚል ዕምነት ላይ ሙጭጭ በማለታቸው ድሞክራሲያዊ ሽግግርን ቀላል በማድረግ ፋንታ ከባድ እያደረጉት ይገኛሉ።

ደራሲው የኢራንን የኢንተርኔት ተመክሮ በመንተራስ ጠንካራ ትችት ያቀርባል። በቋታር የሚገኘው አል-ጄዚራ እንደዘገበው ከሆነ በቴህራን ትዊተር ብሎግ የዘወትር ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ60 አይበልጥም። በሠላማዊ ሠልፍ የተሳተፉት የዚህ ቴክኖሎጅ ታዳሚዎች የትዊተር ዐብዮት ተብሎ የተነገረለትን ክስተት ቀዝቃዛ ውሃ ቸልሰውበታል። በአንፃሩ የአሜሪካ መንግሥት የትዊተር አብዮት ይሁንታ እንዲያገኝ በማድረጉና ለጥገና ተብሎ ቴክኖሎጅው አመፁ በተፋፋመበት ሰዓት አገልግሎቱ በመቋረጡ የኢራን ባለሥልጣኖች ሁሉንም የሶሻል ኔትወርክ ተጠቃሚዎች ለማደን ዕድል ሰጣቸው። ለምሳሌ ወደኢራን የሚገቡ ትውልደ ኢራናዊያን ከተቃዋሚዎች ጋር የሚያገናኛቸው የፌስ ቡክ አካውንት ያላቸው መሆኑን ማጣራት ተያያዙት።፡ይህ ክስተት የአሜሪካ የፖሊሲ ጠበብቶች ከጠበቁት ውጤት የተገላቢጦሽ መሆኑን ልብ ይሏል። .

ደራሲ ሞሮዞቭ የችግሩ ምንጭ የምዕራቡ ዓለም የፖለቲካ አሳቢዎች ድሮ የሬዲዮ ፕሮፓጋንዳና ሌሎች የብዙሃን መገናኛዎች ሶቬትን ለማፈራረስ ወሳኝ ሚና እንደተጫወቱ ሁሉ ኢንተርኔት ለተመሳሳይ ተግባር ሊውል እንደሚችል በሚያራምዱት ተምኔታዊ አስተሳሰብ ነው። ይህ ግልብ የሆነ የታሪክ ንፅፅር
የኢንተርኔት መዘርጋትና የመጠቀም “ነፃነት” በዚህ ዘመን የሚገኙ ጨቋኝ ሥርዓቶችን ለማምበርከክ ይረዳል የሚል የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ መድረስ ስህተት ነው።
እንዲያውም ሥልጣን ላይ ሙጭጭ የሚሉ መሪዎች እንደሌሎች መገናኛ ብዙሃን ሁሉ ኢንተርኔትን ለሥልጣናቸው ማራዘሚያ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ማመን አለብን። ለምሣሌ የምሥራቅ ጀርመን ኗሪዎች የአሜሪካን ቴሌቭዥኖችን እንዲመለከቱ በመደረጉ የተፈጠረው መዘናጋት ብዙ ግለሰቦች ለፖለቲካ የነበራቸው ፍላጎት እንድቀዘቅዝ ምክንያት ሆኗል። ይህንን አስመልክቶ በተካሄደ ጥናት የምዕራባውያንን ቴሌብዥን የሚመለከቱ የምሥራቅ ጀርመን ዜጎች ከማይመለከቱት ጋር ሲነጻጸር በነበረው መንግሥት ላይ የሚያሳዩት ጥላቻ በዕጅጉ ያነሰ ሆኖ ተገኝቷል። አንድ የምሥራቅ ጀርመን የመንግሥት ተቃዋሚ “ዜጎቻችን በሙሉ ከምሽቱ ስምንት ሰዓት ላይ ልክ በአንድ ልብ ሆነው በቴሌቭዥን ተጭነው ከምዕራቡ ዓለም ገብተው ያድራሉ” ሲል ምሬቱን ገልጿል።

ሞሮዞቭ ልክ እንደ ቴሌቭዥን ሁሉ ጨቋኝ ሥርዓቶች ኢንተርኔትን የህዝባቸውን ቁጣ ማርገቢያ አድርገው እየተጠቀሙበት እንደሆነ በርካታ ምሳሌዎችን በጥንቃቄ አጠናቅረዋል። ጠቅለል ባለ መልኩ ሲገለጽ ህገወጥ ቪዲዮ፣ ፖርኖግራፊ፣ አስቂኝ የቪድዮ ክሊፖች እነሆ፣ የፖለቲካ ጥያቄ ከማንሳትም ሆነ ከማራገግ ራቁ የሚል መልዕክት በሥውር ለህዝባቸው ያስተላልፋሉ። በዚህ መልኩ የተቀፈደደ ህብረተሰብ ስለፖለቲካ ደንታ ቢስ መሆኑን ደራሲው አስምረውበታል።

በተለምዶ ከሚሠራበት የስለላ ዘዴ በኢንተርኔቱ ህብረተሰብ ታዳሚ የሆነውን ተቃዋሚ ለይቶ ለማወቅ ቀላልና ብዙ ወጭ የማይጠይቅ ነገር ነው። ከቻይና ተመክሮ እንደምንረዳው የሴንሰርሽፕ ቴክኖሎጅ ምጥቀት የፖለቲካ ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች ብቻ ነጥሎ በማወክ ኢንተኔት የኢኮኖሚ አገልግሎት ፋይዳው ሳይተጓጎል መጠቀም ተችሏል። ይባስ ብሎ ኢንተርኔት ለፕሮፓጋንዳ ተግባር የመዋል ባህርይ ስላለው አፋኝ ሥር ዓቶች የራሳቸውን አጀንዳ ማራመጃ ያደርጉታል። ለምሳሌ ቻይና ሥርዓቱን የሚደግፉ የሰላ ብዕር ያላቸው የብሎግ ፀሃፊዎች አሏት። በተለይ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ተአማኒነት ባጡበት ህብረተሰብ ኢንተርኔት የተሻለ አማራጭ ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችል እሙን ነው።

የአፋኝ ሥርዓት መሪዎች የኢንተርኔት ዕውቀታቸው ውሱን ነው የሚለውን አቋም ደራሲው አይስማሙበትም። ኢንተርኔት በፖለቲካ ህይዎት ውስጥ የሚጫወተውን ጉልህ ሚና ከምብዕራባውያን አቻወቻቸው የተሻለ ግንዛቤ አላቸው ይሉናል። ስለኢንተርኔት የተዛባ ግንዛቤን አስመልክቶ የሩሲያ መንግሥት ወጣት አማካሪዎች የሚጫወቱትን ሚና ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ቀድሞ የተፈለሰፉ የመገናኛ ብዙሃን ቴክኖሎጅዎች ማለትም ቴሌግራፍ፣ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድሞክራሲን ለማጠናከር ይረዳሉ ተብሎ ትልቅ ተስፋ ተጥሎባቸው ነበር። ተስፋችን ግን የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል። የቴሌቭዥን ቻነሎች መሥፋፋት እንደተጠበቀው የተመልካቹን ቁጥር እንዲያሻቅብ አላደረገውም፣ እንዲያውም አሽቆለቅለ። የትዊተር፣ ፌስ ቡክ እና ጉግልን አገልግሎት ልቅ በማድረግ የአሜሪካ መንግሥት ገለልተኛነቱን ከማጣቱ ባሻገር እነዚህ የብዙሃን መገናኛዎች ለግፈኛ ሥርዓቶች የውጭ ጉዳይ አስፈፃሚ ሆነው እንዲያገለግሉ አመቻችተውላቸዋል።

ደራሲ ሞሮዞቭ የኢንተርኔትን አጠቃቀም አስመልክቶ የሰነዘሩት አማራጭ ምንድነው? ቴክኖሎጅ በትክክል ሥራ ላይ ከዋለ ዲሞክራሲን ለማስፋፋት ያግዛል። ስለሆነም “cyber-realism” በአስቸኳይ “cyber-utopianism”ን ሊተካው ይገባል ነው የሚሉት። እያንዳንዱ ሥርወ-መንግሥት የራሱ ልዩ ባህርያት ስላሉት የሚወሰደው ዕርምጃ እነዚህን ክስተቶች ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት ከማለታቸው በስተቀር በዝርዝር ያስቀመጡት መፍትሄ የለም።

ውድ አንባብያን፦ ከቀረበው ፅሁፍ አንፃር ኢንተርኔት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ የተጫወተው ሚና ምን ይመስላል? ለሚለው ጥያቄ መልሱን ከናንተ እጠብቃለሁ። ዽምፅ ካጠፋችሁ ብዙ አልቀየማችሁም። ነገር ግን እየበሉ እየጠጡ ዝም የጋን ወንድም የሚለውን ባህላዊ ዘፈን እንዳንጎራጉር ይፈቀድልኝ።

ወርቁ ለገሠ (ምንጭ፡ ዘኢኮኖሚስት)

የፖለቲካ ነጻነትና የሲቪል መብት ንፅፅር

Monday, January 10th, 2011

ፍሪደም ሀውስ የተሰኘው ግብረ ሠናይ ድርጅት የ2010 ዓለማቀፋዊ የፖለቲካ ነጻነትና የሲቪል መብት መከበር አስመልክቶ በ194 አገሮች ላይ ያካሄደውን ጥናት ይፋ አድርጓል። ከፍተኛ የፖለትካ ነጻነትና የሲቪል መብቶች ጥሰት የሚታይባቸው አገሮች 7 ነጥብ ሲሰጣቸው በአንፃሩ ከፍተኛ የፖለቲካን የሲቪል ህብረተሰብ ነፃነት የተከበረባቸው ደግሞ 1 ነጥብ ያገኛሉ። በዚህ ነጥብ አሰጣጥ መሠረት ከ1-2.5 ሙሉ ነፃነት፣ ከ3-5 በከፊል ነፃ ከ5.5-7 ደግሞ ነጻነት የሌላቸው ሃገራት ምድብ ውስጥ ይካተታሉ።

ቀጥሎ በተመለከተው ሥዕላዊ መረጃ ለምሳሌ ጋና በፖለትካ ነፃነት 1 በሲቪል ደግሞ 2 በማግኘት በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የምትገኝ የነፃነት ማማ ሆናለች። በአንፃሩ የኢሳያስ አፈወርቄ ኤሪትራ 7 ነጥብ በማስቆጠር የተመልካችን ቀልብ ብትስብም አሃዙ ያዘለው መል ዕክት የተገላቢጦሽ እንዲሆን በመደረጉ በነፃነቱ ውድድር ተሳትፍዋ ሁራ ወጥታለች። ኢትዮጵያ በመለስ ዜናዊ አስተዳደር ሥር መንግሥታዊ መዋቅር እምብዛም ከሌላት የሶማሊያ ክፋይ አቻ መውጣቷ የመንግሥትን አስፈላጊነት በጥያቄ ቀለበት ውስጥ እንድወድቅ አድርጎታል።

ይህን መረጃ መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያን መፃዔ ዕድል በመጠኑም ቢሆን መተንበይ ይቻላል። በ2011 ኢትዮጵያ ሶስት አማራጮች አሏት። አሁን ያገኘችውን 5 ነጥብ ሳትነጠቅ መቀጠል፣ ወይም 2.5 ነጥብ በመቀነስ ነፃ ተብለው ከተፈረጁት አገሮች ተርታ መሰለፍ፣ ሶስተኛው ደግሞ 0.5 ነጥብ ብቻ በማግኘት ከእህቷ ኤርትራ ጋር መቀላቀል። አሁን ያለው የፖለቲካ ትኩሳት የሚለካው ቴርሞ ሜትር እንደሚያሳየው ባዙቃው ወደላይ እንጅ በፍጹም ወደታች የሚወርድበት ሁኔታ አይታይም። ስለዚህ 0.5 ጭማሪው ቀላልና ሊሳካ የሚችል በመሆኑ ኢትዮጵያ ሶማሌን በፎርፌ አሸንፋ ከ ኤርትራ ጋር አቻ ልትሆን እንደምትችል ለመተንበይ ነቢይ መሆን አይጠይቅም።

ወርቁ ለገሠ (01/06/11)

ዕንቅልፍ ያጣች ንብ ማር አትሠራም ተባለ (ወርቁ ለገሰ)

Saturday, January 8th, 2011

ንብ ብዙ ጊዜ የታታሪነት ምሳሌ ሆና ትጠቀሳለች። አበቦች ቀስማ ማር ለመፈብረክ ጥበብ የተካነችውን ንብ ወያኔ በ2005ቱ ብሔራዊ ምርጫ አርማው አድርጎ ተጠቅሞባታል። የኢትዮጵያ ህዝብና ንብ ሆድና ጀርባ የሆኑበት ጊዜ ቢኖር ያን ጊዜ ብቻ ነው። በተረፈ ግን “ይሠሯል ከልብ እንደንብ” እየተባለ ሥራ ወዳድነቷ ትውልድ የማይሽረው ምሳሌያዊ አነጋገር ሆኖ ይኖራል።

ሰሞኑን የተደረገ ምርምር እንደጠቆመው ንብ ለሥራ ትጉህ መሆኗ አዘውትሮ ይነገር እንጅ  ደከመኝ ሰለቸኝ የማትልና እንደሮቦት ስትከንፍ የምትኖር ፍጡር እንዳልሆነች አስምሮበታል። ሰው ዕለታዊ ተግባሩን በትክክል እንዲያከናውን ዕንቅልፍ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ንብም መተኛት፣ አስፈላጊ ሆኖም ሲገኝ ማንኮራፋት አለባት። ይህ በግኝትነቱ የመጀመሪያ መሆኑ የተነገረለት ጥናት የተካሄደው ንዝረት የሚፈጥር መሣሪያ በመጠቀም ንቦቹን ሌሊቱን ሙሉ እንዳያንቀላፉ ሆን ብሎ በመረበሽ ነው።  እንዲህ ዕንቅልፋቸው የተቆራረጠውን ሠራተኛ ንቦች ተመራማሪዎቹ ቀን ምግብ ፍለጋ ሲሰማሩ ተከታተሏቸው። እንደሚታወቀው ንቦች ማር የሚሰሩበትን አበባ ሲያስሱ ውለው በለስ ከቀናቸው ተመልሰው ለባልደረቦቻቸው ይነግሩና እንደገና ወደቦታው ይተማሉ። የአበባውን ቦታ መጀመሪያ ያገኘችው ንብ ያስከተለችው ሠራዊት ረጅም በረራ ካደረገ በኋላ ከቦታው የደረሰ መሆኑን የምታመላክተው በምታሳየው ዳንስ ነው። እዚህ ላይ ነው ዕንቅልፍ አሉታዊ ተፅእኖ ማሳደሩ የተገለጠው። ንቧ ያሳየችው ዳንስ ከወትሮው የተለዬ በመሆኑ አበባው ያለበትን ትክክለኛ ቦታ ለተከታዮቿ ማሳወቅ ተሳናት። ያ ማለት በንብ ዓለም ለከፍተኛ ኪሣራ ይዳርጋል። ለሠራተኛውም ሆነ ለንግስቲቷ ንብ ምግብ በወቅቱ አይቀርብም። ዕጭ አይፈለፈልም። ስለዚህ ሊዋለዱና የቀፎው ቁጥር መጨመር ቀርቶ የነበረችው አንድ ቀፎ ንብ አልባ ትሆናለች። የዕንቅልፍ ዕጦት መዘዝ ከንቡ ህብረተሰብ አልፎ ሰው የማር እሸት እንዳይቆርጥ ደንቃራ ይሆናል ።

ይህን የምርምር ውጤት ተንተርሰን ዕንቅልፍ ማጣት በአዳም ዘር ላይ ሊኖረው የሚችለውን ጉዳት በአጭሩ እንመልከት። ሰው በህይወት መኖር ይችል ዘንድ በቂ ዕንቅልፍ ማግኘት አለበት። እኛ ስንተኛ ሰውነታችን ውስጣዊ ጥገና ያካሂዳል። የዛለ የአካል ክፍል አገግሞ ለነገ ዝግጁ የሚሆነው ሌሊቱን ዕረፍት ሲያደርግ ነው። ግምታችን ወደገሃዱ ዓለም የሚጠጋው ንቁና ከዕንቅልፍ መጫጫን ነጻ ስንሆን ነው። ካልሆነ ግን እንፈዛለን። ቀይና አረንጓዴ መብራት ልዩነታቸው አይገባንም። የዕንቅልፍን አስፈላጊነት ለመረዳት የሃኪም ምክር መጠየቅ አስፈላጊ አይደለም። ሳይተኙ ካደሩ መልሱን ወዲያውኑ ያገኙታል።

ኢትዮጵያውያን አገራችን በኖርንበት ዘመን ዕንቅልፍ ማጣት ጥቃት ሰንዝሮብን አያውቅም። እኔ ሥጋቴ ጎኔ እንዳይላጥ ነበር። የአሜሪካው ህይወታችን ግን ከዕንቅልፋችን ጋር አጥፊና ጠፊ ሆነው ይታያሉ። ቤት የገዛንም ሆነ የተከራዬን በየወሩ ዕዳችንን የመክፈል ግዳጅ ውስጥ ገብተናል። ቀኑ እንደ ጄት ይወረወራል። አንዳንድ ጊዜ በአሜሪካ አገር አንድ ቀን 24 ሰዓት መያዙ የሚያጠራጥር ነው፡፡ የጥር ወር ኪራይ ተከፍሎ ሳያልቅ የየካቲት ብቅ ይላል። ታዲያ እንድህ ዓይነቱን አበሳ ለመወጣት ሁለት ሥራ መሥራት ግድ ነው። እዚህ ላይ ነው ዕንቅልፍ ደህና ሰንብች የምንለው። ንቧን ያንገላጀጀ ዕንቅልፍ ማጣት እኛን አዙሮ አይደፋንም ትላላችሁ? የናንተን አላውቅም። እኔ ካልተኛሁ የሰው ድምፅ ቀርቶ የራሴ ያስጠላኛል። መኪና መንዳት ይደብረኛል። በአገራችን የትራፊክ ደንብ ላይ በጉልህ ተጽፎ የሚነበብ አንድ ቁም ነገር አሁንም ትዝ ይለኛል፡ “ከጠጡ አይንዱ”። አሜሪካ ያለው የትራፊክ ደንብ “ካልተኙ አይንዱ” ቢል መልካም ነበር።

ወርቁ ለገሰ

ህይወትን ሰውቶ ህይወት መለገስ

Tuesday, December 21st, 2010

ንብ ቀፎው ሲነካበት ግው ብሎ ይተማል። ፉክክር የለም። አባቶቻችን ይህን ፈለግ በመከተል ዳር ድንበራቸው በተደፈረ ቁጥር ልክ እንደንብ በመቆጣት ግዳይ ጥለው አልፈዋል። እነሱ ሞተው እኛን አኖሩን ማለት ነው። እንዲህ ዓይነቱ መስዋዕትነት በተለያዩ የ እንስ ሳት ዝርያ የሚስተዋል ሲሆን በዕፅዋት ዓለም እንዲሁ ድንቅ በሆነ መንገድ ይከናወናል።ተክሎች እንደንብ ተፈጥሮ መርዝ አላደለቻቸውም። እንደሰው ደግሞ ጎራዴ፣ ጠመንጃ ወይም ተዋጊ ጄት ተጠቅመው ከጥቃት መከላከል አይችሉም።  ስለዚህ የሚጠቀሙበት የመከላከል ዘዴ አጥፍቶ መጥፋት ነው። እንመልከተው።

አብዛኞቹ ዕፅዋት እንደዝርያቸው በተለያዬ በሽታ ይጠቃሉ። ከነዚህ በሽታዎች አንዱ ባይረስ ነው። ከዐቅማቸው በላይ ሆኖ ካላገኙት በስተቀር ከመኖር ምዕራፍ ሊፍቃቸው የዘመተውን ዕልፍ የቫይረስ መንጋ ዝም ብለው አይመለከቱትም። ቫይረሱ መጀመሪያ የሚያጠቃው ያረፈባትን ቅጠል ነው። ከዚያች ቅጠል ውስጥ ተደብቆ ምሽጉን ካጠናከረ በኋላ ሌሎች ቅጠሎችን ላይ ያላሰለሰ ጥቃት ይሰነዝራል። በለስ ከቀናውና ሁኔታዎች ከተመቻቹለት በተክሉ የምግብና የውሃ ማስተላለፊያ ክፍል በመዛመት ሥሩን፣ ግንዱንና ቅጠሉን በመመረዝ ትልቁን ዋርካ ሊገነድሰው ይችላል። 

ይህ መጠነ ሠፊ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ግን መጀመሪያ ጥቃት የተሰነዘረባቸው የቅጠል ህዋሳት ለጎረቤቶቻቸው በሚገባቸው ቋንቋ ቫይረሱ ጉዳት እያደረሰባቸው መሆኑን ሹክ ይሏቸዋል። ጤናማ የሆኑት አጎራባች የቅጠል ህዋሳት በአቅራቢያቸው በሚገኙ ዜጎቻቸው ላይ የደረሰውን ጥፋት ረጋ ብለው ይገመግማሉ። ጥለው አይሸሹም። ጎኑና ርዝመቱን ቀይሰው ካጠኑ በኋላ ቫይረሱ የነሱን በር ገና ሳያንኳኳ ራሳቸውን ማጥፋት ይጀምራሉ። ይህ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ አጥፍተህ ጥፋ ፖሊሲ የቫይረሱን መንጋ በዙር ገጠም መሸጋገሪያ ድልድይ ያሳጣዋል። ቫይረስ ደግሞ በህይወት መኖር ይችል ዘንድ ህይዎት ያለው የተክል ህዋስ ይፈልጋል። መከበቡን ያልጠረጠረው የቫይረስ ሠራዊት ዕጁ የገቡለትን ህዋሳት በሙሉ ከፈጀ በኋላ ወደሌላው ለመዛመት ሲሞክር ዙሪያውን የከበበው አስከሬን ሆኖ ያገኘዋል። መግደል ምንም መስሎ የማይታዬው ቫይረስ በተራው የሞትን ፅዋ ይጎነጫል።  የበሽታው ሥርጭት በዚህ የረቀቀ ዘዴ ከተገታ በኋላ መሃሉ ላይ ጠባሳ የወጣበት ቅጠል ሳይቀር ይለመልማል። ጤነኞቹ ቅጠሎች የተሰውላቸውን ሰማዕታት ክብር በነፋስ ሃይል እየደነሱ ያስቧቸዋል። ተክሉም የተለመደ ሥራውን በሚገባ በማከናወን ከራሱ አልፎ ለእንስሳትና ለሰው ልጆች ህይዎትን ይለግሳል።

ሰው እኮ…..? ማለታችሁ አይቀርም። ሰውም ቢሆን ያው ነው። አባቶቻችን አድዋና ማይጨው ሞተውልን እኛ እንኖራለን። መሬት ላራሹ ያሉ ተማሪዎች ፊዳ ሆነውልን እኛ አርሰን እንበላለን፤ የ4 ኪሎ ተማሪዎች ሞተውልን እኛ እንማራለን።  ኢየሱስም በመስቀል የዋለው ለሰ ልጆች ሲል መሆኑን መጽሃፍ ቅዱስ ያስተምረናል። ርግጥ ነው በህይዎት መኖር መብት መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት በህግ አስቀምጦልናል። ይህ መብት ሲሸራረፍ ስናይ ግን እናስከብረው ዘንድ ትንሽ ትንሽ መሞት ግድ ይለናል።

እንደበሬ ሻኛ ከሰው በላይ ያውላችሁ። መልካም ገና፣ መልካም አዲስ ዓመት!!!

ወርቁ ለገሠ (12/21/10)

ሸፍጠኛ የመሬት ፖሊሲውና ወያኔ-በወርቁ ለገሠ

Sunday, December 19th, 2010

ቹክቺ የተባሉት ዘላኖች ሩሲያ በሚገኘው ቹኮትስኪ የባህር ሠላጤ ይኖራሉ። እነዚህ ሰዎች ከጥንት ጀምሮ እያደኑ ወይም በባህር ላይ እያሠገሩ የኖሩ ሰዎች ናቸው። የሶቬት ህብረት በ1920ዎቹ የአምራቾች የህብረት ሥራ ማህበር እንዲያቋቁሙ ያስገደዳቸው ሲሆን የሶቬትን ውድቀት ተከትሎ የህብረት እርሻው ፈርሷል። የፖሊሲው ውጤት? አብዛኞቹ የቹኩቺ ጎሣዎች አሁን በህይወት ለመኖር የምግብ ዕርዳታ ይፈልጋሉ። የዚህ ብልሹ የሶቬት ህብረት ፖሊሲ በደርግ ዘመን ተኮርጆ ኢትዮጵ ላይ ተሞክሯል። ከወሎና ትግራይ በግዴታ እየታፈሱ በጋምቤላ፣ በመተከልና በሌሎች አጎራባች ክልሎች ተፈትሾ የከሸፈ መሆኑን ብዙዎቻችን እናስታውሰዋለን። አሁን ደግሞ በወያኔ ፖሊሲ መልኩን ቀየር አድርጎ  ስህተቱ  እየተደገመ ይገኛል። መሬት ለኢንቨስተሮች እየተቸበቸበ ነው። ዘላኖች /አርብቶ አደር/የሆኑት ሰዎች የዚህ ፖሊሲ ዕንቅፋት ስለሚሆኑ በዘዴ ከመሬቱ ላይ ማንሳት ያስፈልጋል። በተጨማሪ ለተቃዋሚ ሃይሎች ምሽግ እየሆኑ አገልግለዋል የሚሉም አሉ። ስለዚህ የለመዱትን የአኗኗር ዘይቤ ለቀው እንዲከትሙ ግድ ይላል።  የዚህ ፖሊሲ ትጉህ አራማጅ የሆኑት ክቡር አበራ ደሬሳ “እኛ ዘላኖች ወደተሻለ ህይወት እንዲመጡ እንፈልጋለን። በዚህ መልክ ሲኖሩ ዝም ብሎ የሚመለከት ጨካኝ አንጀት የለንም” ይሉናል። ክቡር ሚኒስትሩ በመቀጠል “ይህን የተቀደሰ የመንግሥት ዓላማ የሚያራክሱ ሁሉ ፖሊሲውን ለመረዳት የተሳናቸው ደናቁርት ናቸው” በማለት ይዘልፋሉ።  

ፖሊሲውን በተግባር ለመፈፀም በተደረገው ዕንቅስቃሴ ህንድ በቀሉ የካሩቲሪ ካምፓኒ በጋምቤላ ትልቅ የርሻ መሬት ወስዷል። ሲፈልግ አበባ፣ ካልሆነም ሩዝ ሊያመርትበት ይችላል። በአካባቢው ከሚገኙ ወንዞች ለሚጠልፈው ውሃ ገደብ አልተጣለበትም። የጊሎም ሆነ የባሮ ወንዝ ጀልባ ሊሸከም ቀርቶ ቅጠል ይዞ መጓዝ እስከሚያቅተው ውሃውን ሊያሟጥጠው ይችላል። ወንዞችና አካባቢው በኬሚካል ሲበከል ተቆጣጣሪ አይኖርም። ከዚህ ኢንቨስትመንት የሚተርፈን ምንድነው? ወዮ ባሮ፣ ወዮ ጊሎ ብቻ ነው። የጋምቤላ ጫካም ተረት ተረት ይሆናል። በመሠረቱ የጋምቤላ መሬት አረንጓዴ እንደመልበሱ ለም አይደለም። ልማቱ ከጫካው ጋር በቅርብ የተቆራኘ ነው። ጫካው ከተቆረጠ የጨረቃ መሬት ለመሆን ጊዜ አይፈጅበትም። 

ያ ማለት ደግሞ አኟኮችን ጨምሮ ብዙ ጎሳዎች መፈናቀል አለባቸው። አርብቶ አደሩ ህብረተሰብ በኢትዮጵያ ከፍተኛውን የሥጋና የወተት ተዋጽኦ እንደሚያቀርብ እየታወቀ ልክ አሳፋሪ ዜጋ አስመስሎ ማቅረብና ለዘመናት ጸንቶ የኖረውን አኗኗር ማፍረስ ለማንም አይበጅም። በሶቬት አልሠራም። በሌሎች አፍሪካ አገሮች ተሞክሮ አልሠራም። ኢትዮጵያ ላይ የሚሠራበት ተአምር ምንድነው?  

የካሩቱሪ የጋምቤላ ኢንቨስትመንት ይጠቅማል ወይስ ይጎዳል? የሚል ጥያቄ አንስቶ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ የተወሰኑ ሰዎችን  አስተያየት  ሰብስቦ ነበር። ብዙዎቹ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ባሆኑም ከመለሱት ውስጥ 70 በመቶ የሚሆኑት አይጠቅምም፣ 20 በመቶ ይጠቅማል፣ 10 በመቶ ደግሞ አናውቀውም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።  የፕሮጀክቱ ሰለባ ከሆኑት አንደበት ደግሞ እዚህ ያዳምጡ  

በሠለጠነው ዓለም ግብይት ውስጥ ገብተው በቅጡ የሚሠራ የጺም መላጫ ለመግዛት ክህሎቱ የሌላቸው መሪዎቻችን የኢንቨስትመንት ፖሊሲያቸው የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም ሊያስጠብቅ ይችላል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። ይባስ ብሎ ዕውቀት እንደ ደም ያጠራቸው የወያኔ ሹማምንት ክፋት፣ ብቀላና ተንኮል ይጨምሩበታል። ከዚህ ዓይነት እኩይ ሥርዓት የሚመነጭ ፖሊሲ በሥራ ሲተረጎም የሚሰጠው ጥቅም ቀጥሎ የተዘረዘሩትን እንጅ ሌላ ሊሆን አይችልም፡  

  • ዳጎስ ያለ ጉቦ ለመቀበል የወጭ አርዕስት ይከፍታል። መሬት በሄክታር በዚያ ዋጋ ይሸጣል?
  • መንግሥትን የሚፋለሙ ሃይሎች ካሉ ለማዳከም ይበጃል-ኦጋዴን ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው
  • የ5 ዓመቱን ዕቅድ አስመልክቶ ጠ/ሩ ዕርዳታ፣ ብሎም ለፓርላማ የሚያቀርቡት ሪፖርት ያገኛሉ- ዋናው ሪፖርቱ ነው!
  • ድሃንና ድህነትን በአንድ ድንጋይ ለመግደል ያለጥርጥር ያስችላል-ኧረ እሪ በል ድሃ የሚለውን ግጥሜን አትርሱብኝ።

ወርቁ ለገሠ (12/19/10)

በሃይሌ ግን አትምጡብኝ

Friday, December 17th, 2010

Click here to read: ሃይሌ

አሁን ገና ገባኝ- በወርቁ ለገሠ

Tuesday, December 14th, 2010

ግጥም

አሁን ገና ገባኝ-በወርቁ ለገሠ

Tuesday, December 14th, 2010

ለሠዓሊ ገ/ክርስቶስ ደሥታ ማስታዎሻ:: Read the Amharic poem here

ልዩነቱን ያውቃሉ?

Sunday, December 12th, 2010

የተወሰኑ ሰዎች በጮርቃነቱ የተነቀለ ካሮት (Baby carrot) የተሻለ የምግብ ይዘት፣ ጣዕምና መስህብ አለው ብለው ስለሚያምኑ ከጎመራው ካሮት በላይ አዘውትረው ይመገቡታል። ይህን የተመጋቢ ምርጫ ልብ ያለው ማይክ የተባለ  የካሊፎርኒያ ገበሬ አንድ ቀን ለዬት ያለ ሃሳብ መጣለት። መጠኑ ከፍተኛ የሆነ የጎመራ ካሮት ከጫፉ ትንሽ የመበስበስ ምልክት ሲታይበትና ቅርጹ ከተለመደው ተጣሞ ሲገኝ ፈላጊ የለውም። እንዲህ ዓይነቱ ችግር ተከስቶ ለሽያጭ አመች ባልሆነበት ወቅት በሞተር ሁለት ቦታ በመቁረጥና በማለስለስ ጮርቃ ካሮትን አስመስሎ ለተጠቃሚ ማቅረብ እንደሚቻል ተገነዘበ። ይህንን ራዕይ ዕውን ለማድረግ ተፈላጊውን መሣሪያ በማሳዎቹ ጥግ ተከለና አንዱን ካሮት ከሁለት ቆርጦ ቅርጽ በማውጣት በላተኛው ሊለያቸው የማይችል ጮርቃ ካሮቶችን አስመስሎ በመሥራት “Baby-cut carrots ብሎ ሰየማቸው።

የሌላውን ሰው አስተያዬት ባላውቅም በኔ ግምት Baby-cut carrots የካሮት ብክነትን ለመቀነስ ግሩም የሆነ የፈጠራ ሥራ ነው። በ2006 ዓም  ካሊፎርኒያ 3/4ኛውን የዚህ “ሰው ሠራሽ ካሮት” ምርት ለገበያ አቅርባለች። በገበያ አዳራሽ በፕላስቲክ ታሽጎ የምታዩትና ለመግዛት የሚያማልላችሁ ካሮት በዚህ መልኩ የተሠራ ነው። ታዲያ ምንድነው ችግሩ? ብላችሁ መጠየቃችሁ አይቀርም።

ችግሩ እንዲህ ነው። በማሽን የተፈጠሩት ካሮቶች የተፈጥሮ ቅርጽ ተሰጥቷቸው ከመፈብረካቸው በፊት ቆዳቸው ይገለፈፋል። ያ ማለት ደግሞ ለመበስበስም ሆነ ለመበላሸት የተጋለጡ ናቸው ማለት ነው። ስለሆነም ብልሽትን ተከላክሎ ከበላተኛው ዘንድ ለማድረስ ዘዴ መቀዬስ ያስፈልጋል። ለጊዜው የተገኘው ዘዴ ልክ ለመዋኛ ገንዳችን እንደምናደርገው በክሎሪን ማከም ነው። ክሎሪን ደግሞ ለፊኛና ሌሎች የካንሰር በሽታዎች ያጋልጣል ተብሎ የብዙ ሳይንቲስቶች ጣት ተቀስሮበታል። ክፉን ከኛ ያርቀውና ማንም ሰው ካንሠር እንዲይዘው አይፈልግም። በተለያዬ መልኩ ወደሆዳችን የምናስገባው ኬሚካል አንሶ ደግሞ በካሮት በኩል ቀዳዳ መክፈት አላዋቂነት ነው። ከረጅሙ ባጭሩ መፍትሄው ምንድነው? ብላችሁ ከጠየቃችሁኝ መልሱ እንደሚከተለው ነው።

ልትገዙት ያነሳችሁት የታሸገ ካሮት “ Baby carrot” የሚል ጽሁፍ ከተለጠፈበት ይሄ ትክክለኛው ምርት ስለሆነ ሌሎች ሳያነሱባችሁ ግዙ።  Baby-cut carrot ካለ ግን ይህ እንደ አገሬ ዳቦ ቆሎ በሞተር ቅርጽ የወጣለትና በክሎሪን የታከመ ስለሆነ ይቅርባችሁ። ለዚህ ሁሉ ስሌት ጊዜየን አላጠፋም ካላችሁ ግን ጆሮው ላይ ቅጠል ያንጠለጠለውን ትልልቁን ካሮት ገዝታችሁ የራሳችሁን ቅርጽ አውጡና ተመገቡ። ሲልጡትና ሲሰሩት ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ነገር ግን ወደሆዳችን የምናስገባውን ነገር ሁሉ ሰውነታችን እንድንቆጣጠርለት ሃላፊነቱን ስለሰጠን መሰላቸት አይገባም።

ላሳጥረው። በክሎሪን ያልታከመ፣ በማሽን ያልተሰቃዬ ትኩስ ካሮት እመኝላችኋለሁ።

ምንጭ፡ http://www.snopes.com/food/tainted/carrots.asp

ወርቁ ለገሠ (12/11/10)

የአካባቢ ጤና (በወርቁ ለገሠ)

Saturday, December 4th, 2010

የምንበላው ምግብ የመጠጥ ውሃችን

የምንኖርበት ቤትና ቀያችን

የመዝናኛ ሥፍራ የትምህርት ቤታችን

አላቸው እንደምታ ለጤንነታችን።

ያቆሸሽነው ሠፈር የበከልንው ውሃ

አድርጎን ይኖራል የጤንነት ድሃ።

ታዳጊ ህጻናት፣ ጎልማሳው ወጣቱ

የሚለከፉብን ሴት፣ ወንድ አዛውንቱ

መርገም እኮ አይደለም ከሰማይ የመጣ

የጽዳት ጉድለት ነው የአካባቢ ቁጣ።

መች ሰማን አውሮፓን ታሞ ሲያስቀምጠው

የታል አሜሪካን ተስቦ የናጠው

የአካባቢ ጤና በመረጋገጡ

ከኛ ዓይነት ወረርሽኝ ቆዬ ካመለጡ።

እኛ ግን እዚያው ነን ያኔ እንደጥንቱ

ኮሌራና ታይፎይድ የነገሠበቱ።

ህጻናት ከሞቱ ከመወለዳቸው

ወጣቶች ካለቁ ሳይደርስ ህልማቸው

ባልባሌ በሽታ ካለቀ ወገኔ

እንዴት እንወጣለን ከድህነት ጠኔ?

በጸሎት አይገኝ ህዳርን ብናጥነው

በግል ጥረታችን ካላረጋገጥነው።

የአካባቢ ጽዳት የጤና ባህላችን

ሊለያይ አይችልም እንደየዕምነታችን።

ይስበኩ መምሬ በየአድባራቱ

ይምከሩ በመስጊድ ሸሁ በሶላቱ

የ1ኛ ደረጃ የኮሌጅ መምህሩ

በአጽንዖት ያስተምር ለደቀ መዝሙሩ

ሁሉም አዋጅ ይንገር ለምዕመናኑ

ለአካባቢ ጤና እንድያስብ ወገኑ።

ለይስሙላ ምርጫ ወጭው ይቁምና

ለድሃው ህዝብ ይቅረብ የሚበላ ምግብ፣ ውሃና ሳሙና

ዕጁን ከታጠበ፣ ቀዬውን ካፀዳ  በሽታ አይስፋፋም

ካልሆነ ድካም ነው ወረርሽኝ በወሬ በሪፖርት አይጠፋም።

በወርቁ ለገሠ

መረጃ፡ አዲስ አበባን በተመለከተ ከዚህ ያንብቡ

እኛና ሶማሊያ (በወርቁ ለገሠ)

Tuesday, November 23rd, 2010

Click here to read:እኛና ሶማሊያ

ከወያኔ ዛፍ የወይን ፍሬ አይለቀምም (ወርቁ ለገሠ)

Sunday, November 21st, 2010

ከወያኔ ዛፍ የወይን ፍሬ እንደማይለቀም ሁሉ የውሸት ምንጭ ከሆነች ነፍስ ሃቅ አይፈልቅም። የምትዋሽ ነፍስ የህሊና ክስ ስለሚመሰረትባት ሁልጊዜ ታፍራለች። ከገሃዱ ዓለም ጋር ባለው ቁርኝት የተነሳ  ዕውነትን ለማስታወስ ብዙ አንቸገርም። ውሸት ግን የራሳችን ፈጠራ በመሆኑ ማስታወስ እንችል ዘንድ ዕንቅልፍ አጥተን መሥራት አለብን። በተጨማሪ ሰዎች ዕምነት ስለማይጥሉብን በዙሪያችን ያሉትን ሁሉ መጥላት እንጀምራለን። ሌባ እናት ልጇን አታምነውም እንድሉ ተጠራጣሪ ስለምንሆን በጥላችን መደንበር እንጀምራለን። ስንዋሽ የሁለት ዓለም ሰዎችን ለማሳመን መታገል አለብን። 1ኛው ከኛ ውጭ የሚኖረውን ሰው ሲሆን 2ኛው የራሳችን የህሊና ዳኝነት ነው። ሰው ሃያል ፍጡር ነው። ውሸትን ቢግቱት አንቅሮ ይተፋዋል እንጅ አይውጠውም።  የመጀመሪያውን ነጥብ ለማጠናከር የሚቀጥለውን ምሳሌ እንመልከት።

ሰውዬው የቅርብ ጓደኛው እናት ይሞቱና ዛሬ ነገ ሲል ለቅሶ ሳይደርስ ድንገት በተፈጠረ አጋጣሚ ሁለቱ ጓደኛሞች ይገናኛሉ። “ይገርምሃል እናትህ ለቅሶ ቦሌ መድሃኔዓለም መጥቼ ሳልሰናበትህ ሄድኩ” ይለዋል፡ በጓደኛው መዋሸት የተበሳጨው ግለሰብ” እኔ እናቴን ቦሌ መድሃኔዓለም መቼ ቀበርኳት?” ብሎ መለሰለት። መዋሸቱ እንደተነቃበት ቶሎ ገባውና “አዬ የኔ ነገር አሁን ቦሌ መድሃኔዓለም ምን የመቃብር ቦታ አለ? ይቅርታ ቀራኒዮ ማለቴ ነው” ሲለው “ኧረ በፈጠረህ ለቀቅ አድርገኝ! እኔ እናቴን ቀራኒዮ አልቀበርኳትም” ብሎ በረጅሙ ተነፈሰ። መቸም ከዘፈንሽ ባላሳፈርሽ ነውና “ቀልብ ካጣሁ ቆይቻለሁ፣ ብሥራተ ገብሬል ለማለት እኮ ፈልጌ ነው” በማለት  እድሉን እንደገና ሞከረ። በነገሩ የተሰላቸው ግለሰብ “እኔ ብስራተ ገብሬልም እናቴን አልቀበርኩም፣ አስቸኳይ ጉዳይ ስላለኝ እንድሄድ ብትፈቅድልኝ” ሲለው እሱም በተራው ብስጭት ብሎ “ ታዲያ ወዴት አደረሳችኋት?” አለው ይባላል።

የህሊና ዳኝነት ዕውነት እስከተናገርን ድረስ ችሎቱን ዘግቶ ለጥ ብሎ ይተኛል። ስንዋሽ ከሰማ ግን ከመቅጽበት ይነቃና እኛን ለማሸማቀቅ ይተጋል።  የሥነ ልቡና ሊቃውንት የምንዋሽበት ዋነኛው ምክንያት ዕውነቱን ስንናገር ሊከተል የሚችለውን መዘዝ በመፍራት ነው ይላሉ። ዕውነቱን ተናግሮ የመሸበት ያድሯል እንድሉ መዋሸት ለጊዜው ጠቃሚ መስሎ ይታየን እንጅ ውሎ አድሮ ከጥቅሙ ጉዳቱ ይልቃል። ውሸት ሰውነታችንን መርዞ፣ መንፈሳችንን አንቅዞ እንደሻህላ ይበላናል። ዋሾ ሰው ህይዎቱን የሚገፋው ውሸት በፈበረከው ካቴና እጅ ከዎርች ታሥሮ ነው። የውሸት ፍርድ ከርቼሌ ሲያወርደን ይግባኝ በመጠየቅ ነጻ መውጣት የምንችለው በዕውነት የዳኝነት ችሎት ሲፈረድልን ብቻ ነው።

ተፈጥሯችን ለመዋሸት የተመቻቼ አይደለም። በ5ቱ ህዋሳቶቻችን በመታገዝ፣ ዓይኖቻችንን እንደካሜራ ተጠቅመን ገሃዱን ዓለም ፎቶ አንስተን በአዕምሮ ሰሌዳችን እንስለዋለን። ያለፈው ልምዳችንን ከአሁኑ ጋር እያመሳከርን የወደፊቱን ለመተንበይ በዋቢነት የምንጠቀመው ያንን የገሃዱን ዓልም  ሥዕል ነው፣ አካባቢያችንን በመቃኘት እንማራለን፣ ግንዛቢያችንን እናዳብራለን። ከቀሰምነው ልምድ በመነሳት ለአሁኑም ሆነ ለመጭው ትውልድ የዕውቀት ጮራ በመፈንጠቅ የተሻለ ዓለም በመፍጠሩ ሂደት ጉልህ ሚና ተጫውተን እናልፋለን ። ይህ በትውልድ ጸንቶ የሚኖር መስተጋብር የሚሠምረው  ተመክሯችን በሃቅ ላይ ሲመሠረት ብቻ ነው። የምንዋሽ ከሆነ ግን ውጤቱ ለየቅል ነው።

ስንዋሽ በሰውነታችን ውስጥ የሚካሄዱ ኬሚካላዊና ፊዚካላዊ ለውጦች ሰውነታችን የተለምደ ሥራውን በትክክል እንዳያከናውን ያውኩታል። ቁጡ፣ ብስጩና ተሳዳቢ እንሆናለን። ቃላት ስሜታችንን፣ ስሜታችን ደግሞ አስተሳሰባችን ላይ ጎጅ ተጽዕኖ በማሳደር ጤንነታችንን ያቃውሳል፣ ሥነ ምግባር ያስጥሳል። ጤና ስናጣ ደሥታም ይርቀናል፤  ዕኩይ አስተሳሰብና የብቀላ ጠኔ ያለልጓም ይጋልበናል።

 “ኢትፍርህዎ ለሞት ፍርህዋ ለኃጢዓት” ተብሎ እንደተጻፈው ሃቀኛ ሰው በዚች ዓለም ሲኖር ሠላም አለው፣ በወገኑ ላይ ሤራ አይጠነስስም።  በአንፃሩ ውሸታም ሰው ፈሪ ነው።  ከሞት አጥብቆ በመሸሽ እየሞተ ይኖራል። ጤና፣ ሠላምና ፍቅር ከሱ ደጃፍ አይረግጡም። የወገንም ሆነ የአገር ፍቅር የለውም። ዕምነት አይጣልበትም፡፡ ከሰው ቀርቶ ከራሱ ጋር ስለማይስማማ የሠላም ዕንቅልፍ አይተኛም፤ ራሱ በፈጠረው የውሸት ውቅያኖስ ላለመስጠም ያለ ዕረፍት ሲቀዝፍ ያድራል። ከወያኔ ዛፍ የወይን ፍሬ እንደማይለቀም ሁሉ ውሸት ከተጣባት ነፍስ ሃቅ አይፈልቅም።  

ወርቁ ለገሠ (11/21/10)

አመካከት ከዝንጀሮ ተመልከት (ወርቁ ለገሠ)

Wednesday, November 17th, 2010

ይህ የአገራችን ምሳሊያዊ አነጋገር በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በተለይ ቆላማው ክፍል የሚኖረው ህዝብ ኑሮውንና አካባቢውን ተንተርሶ የቀመረው ብሂል ነው። ዝንጀሮ ድንጋይ ሲወረወርበት ተሸብሮ የሚደናበር ፍጡር አይደለም። መጀመሪያ የድንጋዩን ፍጥነትና አቅጣጫ፣ የወረወረው ሰው አድራሻና ያነጣጠር ችሎታውን በጥንቃቄ ይገመግማል። ድንጋዩ እላዩ ላይ ሊያርፍበት ጥቂት ሴኮንዶች እስኪቀሩ የነበረበትን ቦታ በፍጹም አይቀይርም። መቼም ድንጋይ ድንጋይ ነውና ከሰው ጡንቻና ከመሬት የስበት ሃይል ባገኘው ጥምር ጉልበት ተኩራርቶ በማያገባው የዝንጀሮን ጭንቅላት ሊበረግድ ሲውዘገዘግ ዝንጀሮ  በቅጽበት ወዴት ማፈግፈግ እንዳለበት ወስኖ ፎቀቅ ይላል። ይህን ተፈጥሯዊ የሂሳብ ስሌት ስለሚጠቀም የሰው ዕጅ በከንቱ ይዝላል እንጅ ዝንጀሮ በፍጹም በድንጋይ አይመታም።  አመካከት ከዝንጀሮ ተመልከት የሚባለው ለዚህ ነው።

ሰሞኑን ደግሞ የአውስትራሊያው ተመራማሪ ዶ/ር ጉተር አመካከት ከዓሣ ዝርያ ተመልከት ይሉናል። በእንግሊዝኛው አጠራር ፓሮትፊሽ የተሰኘው ዓሣ ዕንቅልፍ ሊጥለው ከመቃረቡ በፊት  ከስንጥቡ ሥር የሚገኘውን ትልቅ ዕጢ በመጠቀም  አንድ ሰዓት የሚፈጅ መረብ እንደ ሸረሪት ድር አድርቶ መኝታውን ያዘጋጃል። ከዚህ ድካም በኋላ ልክ በቀለ ሞላ ሆቴል ስንተኛ የወባ አጎበር ውስጥ እንደምንገባ ሁሉ እሱም እዚህ መረብ ውስጥ ገብቶ ሰላማዊ ዕንቅልፉን ይለጥጣል።  እስካሁን ሳይፈታ የቆዬው እንቆቅልሽ ዓሣው በየቀኑ መረብ የመሥራቱን አታካች ሥራ ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይል  የሚፈጽምበት ምክንያት ምንድነው? የሚል ነበር። መቼም ውቅያኖስ ውስጥ ስለሚኖር ከቢምቢ ለመከላከል አስቦ እንዳልሆነ ለመገመት የሳይንስ ሊቅ መሆን ብሎም መመራመር አያስፈልግም። በተጨማሪ የወባ ትንኝ በፍቅር የወደቀችው ከሰው ደም ጋር እንጅ ለዓሣ ብዙም ሃጃ የላትም። ይሄን ዕንቆቅልሽ ለመፍታት ዾ/ር ጉተር  ዕንቅልፋቸውን ሰውተው በውድቅት ሌሊት የሚከተለውን ሙከራ አደረጉ።

ግናቲድ የተባሉ ጥገኛ ፍጡራን መረብ ውስጥና ከመረብ ውጭ የተኙ ዓሳዎችን በውድቅት ሌሊት ጥቃት እንዲሰነዝሩባቸው በሣይንሳዊ ዘዴ አሰማሯቸው። አብዛኞቹ ራሳቸው በፈበረኩት መረብ ውስጥ የተኙት ዓሦች የሠላም ዕንቅልፍ ሲያሳልፉ ከመረብ ውጭ የተኙት ዓሦች ግን እንደተኙ በተሰነዘረ ጥቃት ክፉኛ መጎዳታቸውን ተመለከቱ። በዕንቅልፍ ላይ እያለ ለጥገኛ ፍጡራን የጥቃት ሰለባ እንዳይሆን እንዲህ የዘየደ እንስሳ  እስካሁን በዓለም ላይ መኖሩን አልሰማሁም፣ ክስተቱም እጅግ አስገርሞኛል የሚል አስተያዬት ሰንዝረዋል።

ዶ/ር ጉተር ከዚህ ጥናታቸው በመነሳት የሚከተለው መላ ምት ላይ ደርሰዋል። እነዚህ የዓሣ ዝርዮች ይህን መሠል የመከላከያ ብቃት ሊካኑ የቻሉት ምናልባት ለብዙ ዘመናት ሳያሰልስ የተካሄደው  የከረረ የአጥፊና ጠፊ ትግል የወለደው ተፈጥሯዊ የመከላከል ሥልት ነው ይላሉ። ይህ አገላለጽ በአዝጋሚ ለውጥ  የሚያምኑ ሰዎች ጎራ የሚካተት ነው። የዕምነት ሰዎች ደግሞ “አቤት የሱ ሥራ!” ብለው መደመማቸው አይቀርም። ከሁለቱ ጎራዎች ባንደኛው ላይ መካተት፣ አለዚያም የራስን መላ ምት መተለም ይቻላል። ዋናው ነጥብ ከዚህ ጥናት የምንጨብጠው ቁም ነገር ምንድነው? የሚለው ነው። መልሳችን እንደመልካችንና አመላችን ሊለያይ ይችላል።  ሆኖም ግን ጥቃትን የመከላከል ዕርምጃ ግዕዛነ አዕምሮ ባለው ፍጡር አይወሰንም፣  በደመ ነፍስ የሚኖሩ እንስሳትም ይካተቱበታል የሚለው አስተሳሰብ ያስማማናል ብዬ እገምታለሁ። 

ቸር ይግጠመን

ወርቁ ለገሠ (11/17/10)

ምንጭ፡ BBC

በአገረ አሜሪካ የልጆቻችን ውጤት እንዴት ነው? (በወርቁ ለገሠ)

Sunday, November 14th, 2010

ዛሬ ይህን ለመጻፍ ያነሳሳኝ ብዙ አሜሪካውያን ስለትምህርት ጥራትና ስለልጆቻቸው መጻዔ ዕድል ሲጨነቁ ስሰማ ኢትዮጵያውያንም ይጨንቀቁ ይሆን? ለሚለው ጥያቄ እነሱ ሳይሰሙን  በአማርኛ ሹክ እንድትሉኝ ነው። ”እየበሉ እየጠጡ ዝም የጋን ወንድም እንዳይሆን”  ወላጆች ያላችሁን ልምድ ማካፈል  ይጠበቅባችኋል።

መቼም አገር ለቆ የተሰደደ ኢትዮጵያዊ አመጣጡ በፖሊቲካም ይሁን በዲቪ አሜሪካ ገብቶ ሊያገኘው የሚችለው ትሩፋት “ልጆቹን አስተምሮ ጥሩ ደረጃ  ላይ ማድረስ ነው። ትክክል ነው። አንድ ልጅ እንደ አሜሪካ በቴክኖሎጅ የመጠቀ ኢኮኖሚ ውስጥ የሥራ ዕድል እንድያገኝ ለማድረግ የሚወጣው የትምህርት ወጭ 400000 እንደሚደርስ ይገመታል። የታይፕ ስህተት አይደለም. አራት መቶ ሽህ ዶላር! ታዲያ  4 ልጅ አሜሪካ ያስተማረ ሰው ያገኘውን ጥቅም በልጆቹ ቁጥር አባዝቶ፣ ወደብር መንዝሮ ካሰላው ግንባሩን ሰማይ እስኪመታው ድረስ መጓዙ ተገቢ ነው።

ነገር ግን ልጆቻችን አሜሪካ እያገኙ ያሉት ትምህርት በርግጥ ለመጭው ህይወታቸው የተሻለ ዕውቀት የሚያስጨብጥ ነዎይ? የሚለውን አንስቶ መነጋገር ተገቢ ነው።በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ ተማሪዎች ከአውሮፓ ጋር ሲነጻጸሩ በሳይንስም ሆነ በሂሳብ ችሎታቸው ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

Trends in International Mathematics and Science Study ዘገባ እንደሚያስረዳው አሜሪካ የሚማሩ የ4ኛ ክፍል ተማሪዎች የሂሳብ ውጤታቸው ከሆንግኮንግ፣ ሲንጋፖር፣ ቻይና፣ ቴይፒ፣ ጃፓን ካዛኪስታን ሩሲያን ፌደሬሽን፣ ኢንግላንድ፣ ላቲቪያ፣ ኔዘርላንድስና ሊይቲያኒያ በታች ሆኗል። በተመሳሳይ የሳይንስ ፈተና ውጤታቸው ከሲንጋፖር፣ ቻይና፣ ቴይፒ፣ሆንግኮንግ፣ ጃፓን ካዛኪስታን ሩሲያን ፌደሬሽን፣ ላቲቪያ፣ኢንግላንድ በታች ሆኖ ተገኝቷል። ላለፉት 12 ዓመታት ከጃፓን በስተቀር ከላይ በተጠቀሱት አገሮች የተማሪዎች የሳይንስ ውጤት ከፍተኛ መሻሻል ሲታይ የአሜሪካ ተማሪዎች ውጤት ደግሞ እንዳሽቆለቆለ መሆኑን ስንገነዘብ ወላጅ የሚያስደነግጥ ዜና ነው። እፎይ! የኢትዮጵያ ውጤት እዚህ ለንፅፅር አልቀረበም።

አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው በኢንተርኔት (በተለይ ፌስቡክ)፣ አይፖድ፣ በቴሌቭዥንና በጌም ሱስ ስለተጠመዱ ነው በማለት እነዚህን ነገሮች እስከመከልከል ደርሰዋል። በአንድ ቴሌቭዥን ፕሮግራም እንደሰማሁት ደግሞ ወላጆች ኑሯቸውን ለማሸነፍ ሁለት ሥራ ሲሰሩ ዱርዬዎች በወላጆች ቦታ ቤት ይገቡና ታዳጊ ወጣቶችን ለተለያዬ ሱሳና መዘናጋት እንደሚዳርጓቸው መረጃዎች አሉ ይላሉ። ከናትና አባት ያጡትን ፍቅርና እንክብካቤ ከዱር ቤቴዎች ለማግኘት ይሞክራሉ ማለት ነው።

ለነገሩ የአበሻ ልጆች አሜሪካ ከተወለዱት የተሻለ ውጤት ያስመዘግባሉ የሚልም ተባራሪ ወሬ እሰማለሁ። ዕውነት ከሆነ ያድርግልን ነው የምለው። የአሜሪካ ልጆች ስፔሊንግ በትክክል የማይጽፉ ከሆነ ምናልባት ደህና ሲታጣ ይመለመላል ጎባጣ እንድሉ የኛን ልጆች “A” እየተሰጠ እንደሁ መጠርጠር ተገቢ ነው። በዚያ ላይ ደግሞ ብዙዎቹ የአሜሪካ ተማሪዎች በግል ት/ቤት ስለሚማሩ የኔ ቢጤው ልጆቹን የሚልክበት ት/ቤት ያን ያክል ተወዳዳሪ ሊኖረው እንደማችልም ግምት ውስጥ ይግባ።

ለማጠቃለለ ልጆቻችን በፍጥነት እየተለወጠ በመሄድ ላይ ባለው የአሜሪካ ህይወት ውስጥ ሠርቶ የመኖር ዕድላቸው ከፍ እንድል ከፈለግን ት/ቤት በሚያገኙት ዕውቀት ላይ ተስፋ መጣል የለብንም። እኛም ማስተማር፣ ጊዜያቸውን በአግባቡ እንድጠቀሙ መርዳት፣ ከቴሌቭዝንና ኢንተርኔት ጋር ያላቸውን ግንኙነት መወሰን፣ የቅርብ ክትትልና እገዛ ማድረግ ለአሜሪካ ት/ቤቶች የሚተው ሳይሆን የወላጆች ሃላፊነት ነው።

የትምህርት ነገር ያሳስባችኋል? እስቲ እንወያይበት።

ወርቁ ለገሠ (11/14/10)

የሸረሪት ፍቅር – ወርቁ ለገሠ

Monday, November 1st, 2010

Black widow spider

መቼም እዚህ አሜሪካ የማይሰማ ጉድ የለም። Black Widow የተባለች የሸረሪት ዝርያ ከፍቅረኛዋ ጋር ያላት ግንኙነት ፍቅር ባፍንጫዬ ይውጣ የሚያሰኝ ነው።

ተክለ ሰውነቱ እንከን ባይወጣለትም ከሴቷ ጋር ሲነጻጸር ወንዱ ሸረሪት አነስተኛ ነው። ሴቷ በፍቅር እንድትደራ ከተፈለገ  ወንዱ ሳይታክት የረቀቀና የተራዘመ ልመና ማድረግ ይጠበቅበታል። ወገብ የሚቆርጠው ልምምጥ ተደርጎም ለአፍቃሪነቱ በጎ ምላሽ  ሳይሰጠው ልቡ በሃዘን ተሰብሮ የሚሄድበት ሁኔታም አለ። ልመናው ፍሬ ሲሰጥ፣ የግሪኩ የፍቅር አምላክ ሲታደገው “እሺ ቤቴ ቤትህ ነው” ብላ በጥበብ አድርታ ከሰራችው የሸረሪት አፓርታማ እንድገባ ትፈቅድለትና የመኝታ ክፍሉን ቁልፍ ትሰጠዋለች። እሱም ጊዜ ሳያጠፋ ይገባና በቋንቋቸው “እወድሻለሁ ፍቅርዬ” ብሎ ከንፈሯን ምጥጥ አድርጎ በመሳም በ16 እግሮቻቸው ተቃቅፈው በፍቅር ባህር ይሰጥማሉ።

መቼም ፍቅር ሲያልቅ አያምርም ሁለቱ ፍቅረኛሞች ከገቡበት የፍቅር ሰመመን እንደተመለሱ ሴቷ ሸረሪት ክፉኛ ስለምትራብ “ፍቅርዬ የሚበላ ይዘሃል?” የሚል ጥያቄ ሲቀርብ ወንድ አፋጣኝ መልስ መስጠት ይጠበቅበታል። በፍቅር የታወረው ሸረሪት ከቤቱ ሲወጣ ቤሳ እንደሌለው ትዝ ሲለው ይርበተበታል። ዝም፣ ጭጭ፣ እርጭ ይላል ቤቱ። ሴት መላ አታጣም አይደል፡

 ወንድ ሲርበተበት አይገባንም እኛ

መራብ የለባትም የሴት ልጅ ፍቅረኛ

የሚለውን ስንኝ ትቋጥርና እንደጦር የሰላ መውጊያዋን ሆዱ ላይ በመትከል ከሰውነቱ ጭማቂ መምጠጥ ትጀምራለች። ዘራፍ ብሎ የመከላከል ዕርምጃ እንዳይወስድ በመጠኑ ከሴቷ አንሶ የተሰራ ፍጡር ነው። ሌላው ደግሞ የሸረሪት ድሩ እግሮቹን ተብትቦ ይይዛቸዋል።፡ በደመነፍስ ፍቅር የሠራበት የሸረሪት አፓርትመንት ውስጥ እግሮቹን በማወራጨት የተፈጸመበትን ግፍ ላለመቀበል ይሞክራል። ሴቷ ሸረሪት ግን “ምነው ፍቅሩዬ ጨለምተኛ ለምን ትሆናለህ? ያሳለፍናቸውን የፍቅር ሰዓታት አስታውስ እንጅ። ለሰጠሁህ ፍቅር የጠየኩትን ዋጋ በጸጋ ተቀበለው። አይዞህ!” እያለች እስከመጨረሻው ህቅታ ደሙን በመምጠጥ ለህልፈት ትዳርገዋለች። ምን ይሆናል ከፍቅር ሰመመን እንደነቃ ሱሪውን ታጥቆ ከጎኗ ፈትለክ ቢል ኖሮ ህይዎቱን ያተርፍና እንደገና ለማፍቀር ዕድል ያገኝ ነበር።

ውድ አንባቢያን- ሸረሪቷ በሰራችው ግፍ ከመገረማችሁ በፊት ይህ አጉል ጠባይ በታላቁ ፍጡር በሰው ይንጸባረቅ ይሆን ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት አንድ የቤልጅግ ፕሮፌሰር በግል ቤታቸው አዲስ የተጋቡ ሙሽሮችን እየጋበዙ ለረጅም ዓመታት ተከታትሏቸዋል። በጥናቱ መሠረት ሴት ሙሽሮቹ ወንዱ ላይ የሚያሳዩት የአሳሳም ዘይቤና መጠን ሸረሪቷ እንደወሰደችው ዕርምጃ ለሞት የሚዳርግ አይሁን እንጅ ሁኔታው በቅርብ እንደሚመሳሰል አስምሮበታል።  ፍቅር እስከ መቃብር ይሏል ይህ ነው።

ቸር ይግጠመን

ወርቁ ለገሠ (11/01/10)

ወዮ ዓለማያ – ወርቁ ለገሠ

Friday, October 29th, 2010

Forgive us Alemaya (Source: Brook Lema)

ዓለማያ የአወዳይ ልምላሜ

የሃረር  ጠባይ ሚስጥር የፍቅር ሁሉ ፍጻሜ

አለማያ የወዳጅነት ልክ ማሳያ የመስዋዕትነት ጣሪያ

እስከመጨረሻይቱ ጠብታ እስከ ህይዎቱ ህቅታ

ወዙ ነጥፎ እስኪረታ

ዝም ነው የሱስ ውለታ

ሃረርጌ አለቀሰ እንባውም ፈሰሰ

የክፉ ቀን ጓዱን ሰርክ እያስታወሰ

ወዮ ዓለማያ የሃረር ሲሳይ

ባህርም እንደሰው ሞት ይሞታል ወይ

ማነው የገደለው ብዬ አልጠይቅ እኔ

በማን ዕጅ አለፈ ብየ አልልም እኔ

የደሙን አባላ በሃርርጌ ወዝ ላይ እያየሁኝ ባይኔ

የየዋህነቱን የታዳጊነቱን የአፍቃሪነቱን ልክ መቁጠር ቢታክትም

ርግማን ሆኖብን ባበሻ ምድር ላይ ደግ አይበረክትም

ይናገር እያሱ ከሞት ተመላሹ

ይናገር ተፈሪ በባህር ደጋሹ

በአለማያ ነገር የማይወሻሹ

ያ ሃረሩ ልቤ ያ ሃሩሩ ልቤ የተንሰፈሰፈው

ያን ኩሩ ዓለማያ የዛን ጀግና ባህር መቃብሩን ሲያየው

ከጨው ልክ ያለፈ ከሬት የመረረ እንባውን የረጨው

የዓልማያን ነገር ማትረፍ እየቻለ ቸልታው ቢቆጨው

እስከመጨረሻይቱ ጠብታ እስከ ህይወቱ ህቅታ

ወዙ ነጥፎ እስኪረታ

ዝም ነው የሱስ ውለታ

አረሱት ይሉኛል የሚያርስ ይረሳቸው

ህይወቱን ሰውቶ ህይዎት በሰጣቸው

ደረቱን በብረት ቀረደዱት አሉ

ለእፍኝ ማሽላ ማተብ በጣሽ ሁሉ

አይ የሰው ውለታ አይ የሰው ሰውነት

ምኑን ለማረሻ ምኑንስ ለብረት

እስከመጨረሻይቱ ጠብታ

እስከህይወቱ ህቅታ

ወዙ ነጥፎ እስኪረታ

መቼ እንድህ የሱስ ውለታ

አበሻ ምን ሆኗል አበሻ ታክቶታል?

ለባህር መሞቱን ዘንድሮስ ትቶታል?

ወየውልሽ ጣና ወየው አባያታ ወየውልህ ጫሞ

ፊት ሰው ሞቶለታል ባህር ይሙት ደግሞ

ብለው ዶለቱ አሉ ብለው መከሩ አሉ

እንግዲህ ዘራፍ በል የባህር ልጅ ሁሉ

ቀረርቶን ተላመድ ሰይፎችህ ይሳሉ

በአለማያ ይብቃ ከሰው መዋዋሉ

ወየው አለማያ የሃረር ሲሳይ

ባህርም የሰውን ሞት ይሞታል ወይ

የሱን ሞት ማን ቻለው የቱ ጎበዝ ከቶ

300 ሽ ነፍሳት ከሞት አፍ አውጥቶ ደሙን አጠጥቶ

የሱን ህይዎቱን ሰውቶ

አወይ ዓለማያ አቤት ያንተስ ነገር

አሉላ ቢሰማ ዮሃንስ  ቢሰማ ቴዎድሮስ ቢሰማ

ምን ይውጠው ነበር ምን ይውጠን ነበር

ያ ለባህር ሟቹ ለውሃ ሰሳቹ

ባህር አሥራት ሲሆን ለሚያየው ልጆቹ

ምን ይሰመው ነበር የፈረሱ ጌታ ለደም ተሟጋቹ

መጥኔ ለሁላችን የአገር ልማድ ሻሪ የአባት ወግን ሻሪ

ስንት ባህር ገሎ ስንት ወንዝ አጉድሎ  ሽህ ዓመት አክባሪ

የየዋህነቱን የታዳጊነቱን የአፍቃሪነቱን ልክ መቁጠር ቢታክትም

ርግማን ሆኖብን ባበሻ ምድር ላይ ደግ አይበረክትም።

Source: Anonymous

Transcribed from audio file (ወርቁ ለገሠ)

(10/27/10)

ለካ እንዲህ ይከብዳል – በወርቁ ለገሰ

Friday, October 29th, 2010

Source: Internet

አልጋ ላይ ሞከረ ምንም አልተመቸው

ሶፋ ላይ ሞከረ ምንም አልተመቸው

መሬት ላይ ሁኝ አለኝ እሱም አልተመቸው

ውጭ እንውጣ አለኝ ወጣሁ ተቻኩዬ

በአበቦቹ መሃል ዛፉን ደገፍ ብዬ

አንዴ ተንበርክኮ አንድ ጊዜ ቆሞ

ወደ ታች ወደ ላይ ወደጎንም ዘሞ

እሱም አላረካው  ወደቤት መለሰኝ

አኳኋኑ አሳቀው እኔንም አሳቀኝ

አልጋ ላይ ውጭ አለኝ እኔም ወጣሁለት

ከፍ በይ ዝቅ በይ ሁሉንም ሆንኩለት

መስኮትጋ በሩ ሥር አንዴ ከግድግዳ

ምግብ ቤት ሳሎን ቤት መኝታ ቤት ጓዳ

እቤት ውስጥ በመብራት ውጭ በጸሐይ

ከግራ ወደ ቀኝ ወደ ታች ወደ ላይ

አኳኋኑ ሁሉ በሳቅ ያፈነዳል

ውብ ፎቶ ለማንሳት ለክ እንዲህ ይከብዳል።

Source: Anonymous

በለስ – በወርቁ ለገሠ

Monday, October 25th, 2010

 

በፀሐይ ንዳድ ቢቃጠል ውሃ ባያገኝ ጠብታ

አፈር ባይኖረው መሬቱ ሥሩ በቋጥኝ ቢገታ

ዕጽዋት ሁሉ  ሲያሸልብ እሱ በረሃ ነፍስ ዘርቶ

በጠላቶቹ ሳይበላ በሾሁ ጥቃት መክቶ

ችጋር ባዶ ቤት ሲገባ ስትሽቆጠቆጥ የሰው  ነፍስ

በጣፋጭ ፍሬው ይከላዋል ይታደጋታል በለስ

በለስ እያለ አትከፋም አይደርስባትም ሰቀቀን

ከራብ ተፋልሞ ያስጥላታል ያሻግራታል ክፉ ቀን

የድሃ ሲሳይ የራብ ዳኛ

የመንደር አጥር ዘበኛ

ውጭ ሊሰደድ እንደሰው

በለስም ዕጣ ደረሰው

ቆሽት ያሳርርራል ያጨሳል

የሆድ ነገር ሆድ ይብሳል

ልክ እንደ ሩዝ እንዳበባ

በለስ በተራው ሊዝ ገባ

ዕድሜ ሊቀጥል ህይወት ሊያድስ

ባዕዳንን  ሊፈውስ

በለስ እንደሰው ተሰዶ

መሻገሩ ነው ባህር ማዶ

እንደ ሰሊጥ እንደ ተልባ እንደ ኑግና እንደቡናው

አገር ለቆ ከወጣ በለስን በለስ አይቅናው።

በወርቁ ለገሠ (10/24/10)

የዕርዳታ/ስጦታ አሉታዊ ተጽዕኖ – በወርቁ ለገሠ

Saturday, October 23rd, 2010

ዕርዳታ ወይም ስጦታ አስፈላጊ በሆነበት ጊዜና ቦታ በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለ ነፍስ ሊያተርፍ፣ የወደቀውን መልሶ ሊያቋቁም እንደሚችል ጨርሶ መካድ ጨለምተኛ አመለካከት ይሆናል፡፡ ስጦታ የሚለው ስያሜ የተቀባዩን ልብ ያማልላል። የቅርብ ወዳጃችሁ አዲስ ሀይብሪድ ቶዮታ መኪና ገዝቶ ቁልፉን ቢያስረክባችሁ ወይ ደግሞ እዚህ አሜሪካ ስትመጡ አንድ ጓደኛችሁ ቤት ተከራይቶ፣ የኪስ ሰጥቶ ቢያስቀምጣችሁ ለጊዜው ደሥ አይላችሁም? ውሎ አድሮ ግን በቀረብኝ፣ አሜሪካ ስመጣ እግሬን በሰበረው የሚያሰኝ ክስተት ሊገጥማችሁ ይችላል። ገድሉን በማስመልከት መለኮታዊ ሃይል አላብሰው በሰላ ብዕር የሚጽፉ ብዙ ካድሬዎች አሉት። በርግጥ ስሙና ግብሩ ከተጣጣሙ መለኮታዊ ሃይል የማያገኝበት ምክንያት አልነበረም። ያ እንደተጠበቀ ሆኖ ለጊዜው ማተኮር የፈለኩት አሉታዊ ጎኑ ላይ ነውና ትዕግስታችሁን ጀባ በሉኝ።

ዕርዳታ/ስጦታ ከጥንት ጊዜ ጀመሮ አሁን እሳካለንበት ክፍለ ዘመን ቅርጹ ይለያይ እንጅ የሰው ልጆች እንደ ባህልና ወጋቸው ሲጠቀሙበት ይታያል። የዓላማውን ውስብስብነትና ረቂቅነት ተገን በማድረግ ለጋሽ ተቀባይን በቀላሉ የሚያጠቃበት መሣሪያም ሆኖ እንዳገለገለ መረጃዎች አሉ። ለምሳሌ በጥንት ጊዜ ህንዶች ባላንጣ ዘመዶቻቸውንና ጎረቤቶቻቸውን ለማጥፋት ጦር ሰብቆ ከመዋጋት ይልቅ ስጦታ ፍቱን የብቀላ መሣሪያ መሆኑን ፈትሸውታል። ነገሩ እንድህ ነው። በጣም የጠሉትን ባልንጀራ፣ ጎረቤት ወይም ቤተዘመድ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ላሞች በስጦታ ያበረክቱለታል። ይህ የፈረደበት ተቀባይ ብዙ ጊዜ በኢኮኖሚ ከለጋሹ የኮሰሰ ነው። ይህ ሰው ስጦታውን ስልቅጥ አድርጎ ቁጭ እንድል በወቅቱ የሚኖረው ባህልና ወግ አፈቅድለትም። በስጦታ መልክ መመለስ ይኖርበታል። 1000 ጥገቶች ተሰጥቶት 1000 መመለስ ደግሞ አንገት ማጣት ነው። ከፍ አድርጎ መስጠት በህብረተሰቡ ባህልና ወግ አንቱ የተሰኘ ከበሬታን ያጎናጽፋል። ስለዚህ የሚያርስበት በሬ ሳይቀር ሙጥጥ አድርጎ ይከፍልና ድህነቱ ሲጠናበት መኖር አለበትና በጣት በሚቆጠሩ ዓመታት የጎረቤቱ ወይም የቅርብ ዘመዶቹ ግብረበላ ይሆናል። ጠላቱ በስጦታ መልክ  ተበቀለው ማለት ነው። ሌላው ሊወስደው የሚችለው አማራጭ ዓይኑ በጨው እጥብ አድርጎ ስጦታውን ሳይመልስ መቅረት ነው። ይህም በጎ አማራጭ ሆኖ አይገኝም። ህብረተሰቡ የፈሳች ዝንጀሮ ያደርገዋል። በተጨማሪ ስጦታውን ባለመመለሱ የለጋሹን ፊት ቀና ብሎ ለማዬት ያፍራል። ይህ በሚያስከትለው የስነ ልቦና ቀውስና በሚፈጠረው የበታችነት ስሜት ባላንጣው አድርግ የሚለውን ሁሉ ሳያጉረመርም ይፈጽማል፤ አወዳደቁም አያምርም።

አሁን ካደጉ አገሮች የሚሰጥ ዕርዳታ ይዘት ጥንት ህንዶች ከሚጠቀሙበት በይዘቱ ይለያል ወይ? ለሚለው ጥያቄ መልሱ ቀላል ነው። አይለይም። ለምሳሌ አገራችንን። በዓለም ከፍተኛውን ዕርዳታ ከሚቀበሉ አገሮች አንዷ ስትሆን ጥርስ ያወጣ ድህነት የሰፈነባቸውን አገሮች ሃይሌ ገ/ሥላሴ ሯጮችን እንደሚያስከትለው እየመራቻቸው ትገኛለች።  ይህ በተነሳ ቁጥር ከመሪዎቿ በስተቀር የህዝቦቿ ሞራል ስብር፣ መንፈሳቸው ሽምቅቅ ይላል። ለዚህ ነው አብዛኛው ሰው አጋጣሚ ቢያገኝ አገሩን ለቆ መሰደድ ዝግጁነቱን የገለጸው። በሀ/ሥላሴ ዘመነ መንግሥትም ሆነ ከዚያ በፊት ይህ ለኢትዮጵያውያን የሚዘገንን ዕርምጃ ነበር። አሜሪካና አውሮፓ የሚሰጡን ከፍተኛ ዕርዳታ እንደ ግመል ሽንት ወደኋላ እንድንሄድ፣ እንደካሮት ቁልቁል እንድናድግ አድርጎናል። በገንዘብ ሊተመን የማይችል ትልቅ ዋጋ ተከፍሎበታል። ሌሎች ጥቃቅን ምክንያቶች እንደተጠበቁ ሆኖ በ ኤርትራና ኢትዮጵያ ላይ የደረሰው ዕልቂት፣ የሶማሊያ ጦርነት፣ በአገሪቱ የተንሰራፋው አምባገነን ሥርዓት ከዕርዳታ ጋር ባለን ንክኪ ምክንያት የከፈልናቸው ውድ ዋጋዎች ናቸው።

ታዋቂው እንግሊዛዊ ባዮሎጅስት ሪቻርድ ዳውኪንስ ሰልፊሽ ጅን በተሰኘው መጽሃፋቸው የሌሎችን ደህንነት ለመጠበቅ የራስን ህይወት እስከ መሰዋት የሚደርሱ  ሰዎች አሉ የሚለውን ፍልስፍና የጎሪጥ ይመለከቱታል። ለምሳሌ ይላሉ፡ ወፎችን የሚያጠቃው ጭልፊት በሰማይ ሲያንዣብብ የተመለከተች ወፍ መጣላችሁ የሚል ድምጽ በማሰማት ሌሎችን የመታደግ ብሎም የራሷን ህይወት አደጋ ላይ የመጣል ዕርምጃ ትወስዳለኝ የሚለው ርዕዮት ለሳቸው የዋህ አስተሳሰብ ነው። እንዲያውም ይላሉ የሞት አደጋ ሊያስከትል የሚችለው ጭልፊት ከየት አቅጣጫ እንደሚመጣ ያልተነገራቸው ወፎች በመደናገጥ ግማሾቹ በአጋጣሚ ወደሱ በመብረር ሳያስቡት መስዋዕትነት የሚከፍሉት እነሱ ናቸው። አቅጣጫው ከዬት እንደሆነ መጀመሪያ የለየችው ወፍ ግን ትክክለኛ በረራ በማድረግ ለመትረፍ ያላትን ዕድል ታሰፋለች ይላሉ።

ከፖለቲካ ነጻ ናቸው ብለን የምንገምታቸው የምግባረ ሠናይ ድርጅት ሰዎችም ሆኑ ሳይንቲስቶች ራሱ የሚያደርጉልን ስጦታ ከራሳቸው ወይም ከሃገራቸው ጥቅም አኳያ እንጅ  በዋናነት ከኛ ደህንነት አኳያ የሚመነጭ አይደለም፡፡ የዓለም ከበርቴው ቢል ጌት ሲረዳን የዜና አውታሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ የብሩ አሃዝ ከነሳንቲሙ ተጠቅሶ፣ የሱና የውድ ባለቤቱ ሥም በክብር መዝገብ ላይ እንድሰፍር ተደርጎ ነው። ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ለኢትዮጵያ ዕርዳታ ካደረገ ተመራማሪዎቹ ከሚያገኙት የኪስ ገንዘብ በተጨማሪ የሚታተመው የምርምር ውጤት ለተመራማሪዎቹ የደረጃ እድገት፣ ለዩኒቨርሲቲው ደግሞ የገቢ ምንጭ እንድሆን ታስቦ ነው። አንድ ፕሮፌሰር ትግራይ ውስጥ የሚደረገውን የውሃ ማቆርና የደን ልማት ዕንቅስቃሴ ሪፖርት አስመልክቶ ለመሆኑ የትግራይ መሬት እንደገና የሚለመልም ይመስልሃል? ብሎ ለቀረበለት ጥያቄ የሰጠው መልስ የሚገርምም የሚያስደንቅም ነበር። ትግራይ አትለመልምም ነው ያለው። ታዲያ ይህ ሁሉ ንብረትና ውድ ጊዜ ለምን እንድባክን ወሰናችሁ? ለሚለው ጥያቄ የሰጠው መልስ ከፍተኛ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሥልጣን የተያዘው በትግሬ ነው። አንድ የዕርዳታ ፕሮጀችት  ትግራይን ማዕከል አድርጎ ከተቀረጸ ለመጽደቅ ያለው ዕድል መቶ በመቶ ነው ሲል ምሬቱን ገልጿል።  እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባ ቁም ነገር አንድ ፕሮፈሠር የማይምንበትን ፕሮጀክት ቀርጾ ተግባር ላይ እንዲያውል ያስገደደው ምስጢር ምንድነው? የሚለው ሲሆን ከዕርዳታው በስተጀርባ ሌላ ተልዕኮ መኖሩን ነው።

 ቻይናና ህንድን ብንመለከት በ1960ዎቹ መገባደጃ ላይ በወቅቱ አንቱ የተሰኙ የኢኮኖሚ ጠበብቶች ከህዝባቸው ብዛትና ከድህነታቸው መጠነ ሰፊነት የተነሳ ለነዚህ አገሮች ዕርዳታ መስጠት ጣዕራቸውን ማራዘም ስለሚሆን መርዳት አያስፈልግም የሚል መደምደሚያ ላይ በመድረስ ዕርዳታ እንድቀንስ ሞክረዋል። እነዚህ አገሮች በአደጉ አገሮች ብያኔ ሳይደናገጡ ጥርሳቸውን ነክሰው በመሥራት በተለይ ቻይና ወሳኝ የዓለም ኢኮኖሚ ባለቤት ለመሆን በቅታለች። ይህን ጽሁፍ ሳዘጋጅ ያረቀቅኩበት ብዕር፣ ያደረኩት ዓይነ ርግብ፣ የለበስኩት ፒጃማና ቁርስ የበላሁበት ሹካ የተፈበረከው በቻይና አገር ነው። ዕርዳታ በገፍ የሚጎርፍላቸው የአፍሪካ አገሮች ግን አሁንም የልመና እጆቻቸውን እንደዘረጉ ናቸው።

ላሳጥረው። ዕርዳታ/ስጦታ ከበጎ ጎኑ ይልቅ አሉታዊ ተጽዕኖው ይጎላል የሚለውን አስተሳሰብ አራምዳለሁ። የዕድል ነገር ሆኖ እኔም ሆንኩ እናንተ በስጦታ አዟሪት ውስጥ ወድቀናል። ውጭ አገር አፈር ግጠን ካገኘናት ዶላር/ዩሮ ላይ ቆንጥረን ወደአገር ቤት የምንልከው ዕርዳታ/ስጦታ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳይኖረው ተግታችሁ ጸልዩ።

ቸር ይግጠመን።

 ወርቁ ለገሠ 10/23/10

አሻራ – በወርቁ ለገሠ

Thursday, October 21st, 2010

በዘመን ወይቦ ቀለሙ ባይደምቅም

አሻራ ህያው ነው ቢፍቁት አይለቅም

ዜግነት ቢቀየር ቢገቡ አሜሪካ

ከየት ነህ? መባሉ የማይቀር ነው ለካ!

ክልል ድንበር ሆኖ ቢከፈል አገሬ

ወሎዬ፣ ከፍቾ ሾዌና ጎንደሬ  

ቋንቋ መሥፈርት ሆኖ ሰውን ቢፈርጁት

አማራ፤ ኦሮሞ አኟክ ትግሬ ቢሉት

ደሙ ሲመረመር እምዬ አብሲኒያ

አሻራው ሲነሳ ሃገረ ኢትዮጵያ

መሆኑ አይሻርም ሲኖር በዚች ዓለም

በትውልድ ጸንቶ ይኖራል ዘላለም

በአንቺ ሆዬ ለኔ በባቲ ትዝታ

በአምባሰል ቅኝቶች ለዛና  ጨዋታ

ጊዜ ሳይወስነው ሳይገታው ርቀት

ይነጉዳል አበሻ ይጓዛል አገር ቤት

ቢሳካ ለመኖር ካልሆነም ለቀብሩ

እንደወጣ አይቀርም ይገባል አገሩ

 እንደናት እንዳባት የጣት አሻራችን

ሊለወጥ አይችልም አበሻነታችን

በዘመን ወይቦ ቀለሙ ባይደምቅም

አሻራ ህያው ነው ቢፍቁት አይለቅም

ዜግነት ቢቀየር ቢገቡ አሜሪካ

ከዬት ነህ? መባሉ የማይቀር ነው ለካ!

 በወርቁ ለገሠ (10/17/10)