Author Archive

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት 2ኛ ጉባኤ አሜሪካን ውስጥ ተካሄደ (ጀርመን ራዲዮ)

Monday, February 25th, 2013

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት 2ኛ ጉባኤ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ቨርጂኒያ አሜሪካን ውስጥ ተካሄደ። ጉባኤው የምክር ቤቱን የእስካሁኑ እንቅስቃሴ መገምገሙንና የወደፊት አቅጣጫውንም ማስተዋወቁን የዋሽንግተን ዲሲው ወኪላችን ዘግቧል ። በሌላ በኩል በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ በሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን ሙስሊሞች አስተባባሪነት ባለፈው ቅዳሜ ዋይት ሃውስ ፊት ለፊት ሠላማዊ ሰልፍ ተካሄዷል። ስለ ቨርጂኒያው ጉባኤ ና ስለ ዋሽንግተን ዲሲው ሠላማዊ ሠልፍ አበበ ፈለቀ ዝርዝር ዘገባ አለው።

የዶክተር ዮናስ አድማሱ ትውስታ

Thursday, February 21st, 2013

የዛሬው የባህል ዝግጅታችን ትኩረት በስነ ፁሁፍና እና ቋንቋ መምህርትነት በሚታወቁት ዶክተር ዮናስ አድማሱ ስራዎች ላይ ይሆናል። ዶክተር ዮናስ ከሁለት ሳምንት በፊት በ69 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።

በአዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ በቋንቋ እና ስነ ፁሁፍ አስተማሪነት የሚታወቁት ዶክተር ዮናስ ዜና ዕረፍት ሲሰማ፣ በተለይ በቅርብ የሚያውቋቸው በሀዘን ተውጠዋል። ዶክተር ዮናስ ምን አይነት ሰው ነበሩ? የስራ ባልደረባቸው ፣ የቀድሞ መምህራቸው እና አብሮ የመስራት ዕድል የገጠማቸው ሶስት የፕሮግራማችን ተሳታፊዎች ስለ ዶክተር ዮናስ ማንነት እና ስራ በባህል ፕሮግራም አጫውተውናል።

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ስነ-ፁሁፍ ሲነሳ አብሮ ስማቸው ከሚነሱት ሰዎች መካከል ዶክተር ዮናስ እና ታላቅ ወንድማቸው ዶክተር ዮሀንስ አዱማሱ ይገኙባቸዋል። ወንድማቸው ዮሀንስ አድማሱ ስለ ባለቅኔው ዮፍታሄ ንጉሴ የፃፉት መፅሀፍ ለዕትም ሳይደርስ ነበር ሞት የቀደማቸው። ዶክተር ዮናስም ይህንን መፅሀፍ ሲያዘጋጁ ረጅም አመታት እንደፈጀባቸው ዶክተር ሄራን ይናገራሉ። በመጨረሻም መፅሀፉ አልቆ ግን ለምርቃት ጥቂት ቀናት ሲቀረው ዶክተር ዮናስ አረፉ። መፅሀፉ ትናንት በብሄራዊ ትያትር ቤት ለምርቃት በቅቷል። ይህን መፅሀፍ ለዕትም ማብቃት ምናልባትም የዶክተር ዮናስ የመጨረሻ ምኞት ነበር።

ዶክተር ዮናስን እንዴት ልናስታውሳቸው እንችላለች? በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነ ፁሁፍ ዘርፍስ ምን አይነት ሚና ተጫውተዋል?የዶክተር ዮናስ አድማሱን ማንነት እና ስራ የቃኘንበትን ዝግጅት ያድምጡ።

Play below

 

የአቶም ሳይንቲስቱ ዶ/ር ጌድዮን ጌታሁን

Tuesday, February 19th, 2013
ዶክተር ጌድዮን የሚሰሩት ጀርመን ቢሆንም ሃገራቸውንና ህዝባቸውን አልረሱም ለረዥም ጊዜ በሊቀመንበርነት በሊቀመንበርነት በመሩት ማህበር አማካይነትና በግላቸው የኢትዮጵያን የሳይንስ ትምሕርትና ተማሪዎች ይረዳሉ ።

አባይ፤ ኢትዮጵያ እና ግብፅ

Tuesday, February 19th, 2013
የአባይ ወንዝ ውሃን በመጠቀሙ ጉዳይ ላይ በኢትዮጵያና ግብጽ መካከል የነበረው የኃይል ሚዛን ወደ ኢትዮጵያ እያደላ መሆኑ ተነግሯ። ግብጽ ከአባይ ወንዝ የምታገኘውን ጥቅም ማጣት አትፈልግም። የኢትዮጵያና ግብጽ ፍጥጫ ምሥራቅ አፍሪቃን ይበልጡን ያልተረጋጋ አካባቢ እንዳያደርገው ያሰጋል።

ኢትዮጵያውያን በሳውዲ

Tuesday, February 19th, 2013
ኢትዮጵያውያን ለደረሰባቸው ግፍ ካሳ የሚያስጥ በአጠቃላይ መብቶቻቸውን የሚያስከብር የመንግሥት ተወካይ ባለማግኘታቸው ለልዩ ልዩ ችግሮች መጋለጣቸው መቀጠሉን ነብዩ ሲራክ ከጅዳ የላከው ዘገባ ያስረዳል

የአዲሱ የፓሪያርክ ምርጫ በኢትዮጵያ

Tuesday, February 19th, 2013
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶሱ በወሰነው መሰረት የካቲት 21 የፓትሪያርክ ምርጫ ይካሄዳል። የካቲት 24 ደግሞ በአዕለ ሲመቱ ይከበራል።

የታምራት ሞላና የዶ/ር ዮናስ አድማሱ ኅልፈት

Monday, February 11th, 2013
የታዋቂው ድምጻዊ (አርቲስት) ታምራት ሞላ የቀብር ሥነ ሥርዓት ዛሬ ከቀትር በኋላ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ወዳጅ ዘመዶቹና የጥበብ ባልደረቦቹ በተገኙበት ተፈፅሟል ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ተመክሮ

Thursday, January 31st, 2013

«ከውድድሩ ወጥተናል፣ ሆኖም ሰፋ ያለ ተመክሮ አካብተናልና ፣ ከዚህ ልምድ በመነሣት የወደፊቱን ሂደት እንቀይሳለን» ። ይህን ያሉት ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ አቶ ሰውነት ቢሻው ናቸው። ከ 31 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አፍሪቃ የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ብቅ ያለውና በመጀመሪያ ዙር ተሸንፈው መውጣት ዕጣቸው ከሆነ 8 የአፍሪቃ ሃገራት ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ በደቡብ አፍሪቃ ስላሳየው እንቅሥቃሴ፤ ስለደጋፊዎቹም አስተዋጽዖ፤ ሃይማኖት ጥሩነህ ከደቡብ አፍሪቃ ፣ የሚከተለውን ዘገባ አጠናቅራ ልካልናለች። ያዳምጡ:

ያመጹት የኤርትራ ወታደሮች እርምጃ በኤርትራ መንግሥት ውስጥ ውጥረቱ የመባባሱና የአገዛዙ የመዳከም ምልክት ነው – የፖለቲካ ተንታኞች

Tuesday, January 22nd, 2013


ለዶቼቬለ አስተያየታቸውን የሰጡ የፖለቲካ ተንታኞች፣ ያመጹት የኤርትራ ወታደሮች እርምጃ በኤርትራ መንግሥት ውስጥ ውጥረቱ የመባባሱና የአገዛዙ የመዳከም ምልክት መሆኑን ተናግረዋል

ትናንት ባመጹ ወታደሮች ተቋርጦ ነበር የተባለው የኤርትራ መንግሥት ቴሌቪዥን ስርጭት መቀጠሉ ተዘገበ ። በፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገባ መሰረት የኤርትራ መንግሥትም በዋና ከተማይቱ አስመራ ሁሉም ነገር ሠላማዊ መሆኑን አስታውቋል ። ይሁንና በጉዳዩ ላይ ለዶቼቬለ አስተያየታቸውን የሰጡ የፖለቲካ ተንታኞች ፣ ያመጹት የኤርትራ ወታደሮች እርምጃ በኤርትራ መንግሥት ውስጥ ውጥረቱ የመባባሱና የአገዛዙ የመዳከም ምልክት መሆኑን ተናግረዋል ።

የኤርትራ ፕሬዝዳንት የአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ቃል አቀባይ አቶ የማነ ገብረ መስቀል እንደ ትናንት ሁሉ ዛሬም አስመራ ሰላማዊ ናት ማለታቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል ። አንድ የተቃዋሚ ድረ ገፅን የጠቀሰው AFP ወደ 100 ይጠጋሉ ያላቸው ትናንት የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴርን የተቆጣጠሩ ያመፁ ወታደሮች አዛዥ እጃቸውን ለመስጠት መስማማታቸውን ዘግቧል።

የዘገባው እውነትነት ግን በሌላ ምንጭ አልተረጋገጠም ። አንዳንድ ምንጮችም የወታደሮቹን እርምጃ ከመፈንቅለ መንግሥት ጋር አስተካክለውታል ። በብሪታኒያው የጥናት ተቋም ቻተምሃውስ የአፍሪቃ ቀንድ ጉዳዮች አጥኚ አህመድ ሶልሜን ግን ከኤርትራ ትክክለኛ መረጃ ማግኘት በማይቻልበት ሁኔታ የተፈፀመውን ለማወቅ አዳጋች መሆኑን ነው ለዶቼቬለ የተናገሩት።

« መፈንቅለ መንግሥት ወይም በወታደሩ ውስጥ አመፅ ነበር ለማለት አስቸጋሪ ነው ። በአሁኑ ጊዜ የትናንቱ እርምጃ ውጤት ምን እንደሆነ ለማወቅ መጠበቅ አለብን ። ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ ሁኔታው ምን እንደሆነ አናውቅም ። ሆኖም የሆነ አይነት አመፅ እየተካሄደ ነው።»

በአንዳንድ ዘገባዎች እንደተጠቆመው ወታደሮቹ ህገ መንግሥቱ እንዲከበርና የፖለቲካ እሥረኞች እንዲፈቱ የሚጠይቀው መግለጫቸው ትናንት በኤርትራ ቴሌቪዥን እንዲነበብ አድርገዋል ። የአፍሪቃ የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች አማካሪና የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር ማሃሪ ታደለ ማሩ የወታደሮቹ እርምጃ ለመንግሥት የማስጠንቀቂያ ደውል ነው ይላሉ።

የኤርትራው ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ ይህን መሰሉ የአመፅ እንቅስቃሴ መካሄዱ ሲነገር የአሁኑ የመጀመሪያው ነው ። ይህ ወዴት ሊያመራ ይችላል ? ምንስ ያመለክታል ተብለው የተጠየቁት የቻተም ሃውሱ ተንታኝ አህመድ ሶልመን ሲመልሱ « ይህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ማምጣት አለማምጣቱ ወደፊት የሚታይ ይሆናል ። እኔ ግን ለውጥ ማምጣቱን እጠራጠራለሁ ። ኢሳያስ ሁኔታዎችን መቆጣጠር የሚችሉ ይመስለኛል ። ሆኖም በርግጥ ይህ እርምጃ በቅርቡ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ አሊ አብዶ ከድተው መኮብለላቸው ከተዘገበ በኋላ የተወሰደ 2 ተኛ እርምጃ ነው ። ስለዚህ በራሱ በአስመራ መንግሥት ውስጥ ውጥረቱ እየተጠናከረ የመምጣቱ ምልክቶች አሉ።»

የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር መሃሪም ተመሳሳይ አስተያየት ነው ያላቸው።

ትናንት በኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ ያመፁ ወታደሮች ወሰዱ የተባለው እርምጃ የቻተም ሃውሱ ተንታኝ አህመድ ስልሜን እንዳሉት የህዝቡ ብሶት መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ።

« የተደማመረ ነገር እንዳለ ይታያል የሰብአዊ መብት ይዞታው ወጣት ኤርትራውያን በግዳጅ ለውትድርና መመልመላቸውና በአነስተኛ ክፍያም ለረዥም ጊዜ እንዲያገለግሉ በመደረጉ በርካታ ወጣት ዜጎች ህይወታቸውን ለማትረፍ ወደ ሌሎች የአካባቢው ሃገራት እየተሰደዱ ነው። ስለዚህ ባለፉት 24 ሰአታት የተከናወኑት ድርጊቶች ለተፈፀሙት ሁኔታዎች እንደ ምሬት መግለጫ ሆነው ነው የሚታዩ ይመስለኛል ። ይህ እንደሚሆንም የሚጠበቅ ነው ። ሆኖም በኛ ግምት ይህ የአገዛዙ መዳከም ምልክት ነው። »

የኢትዮጵያ ገዳማት ይዞታ በእስራኤል

Sunday, January 20th, 2013

Play below

 

ከሰሃራ በታች ከሚገኙት አፍሪቃ ሃገራት በእስራኤል ገዳም እና ሌላም ይዞታ ያላት ብቸኛ ጥቁር አፍሪቃዊት አገር ኢትዮጵያ መሆንዋ ይታወቃል።

የዴር- ሱልጣን ገዳም ጥሪ በሚል ርዕስ፤ ባለፈዉ ሳምንት ባቀረብነዉ መሰናዶአችን ፤በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን እና በግብፅ ኮፕት ቤተክርስትያን መካከል በይዞታ ይገባናል ጥያቄ ምክንያት ገዳሙ መጠገን ባለመቻሉ በመፈራስ ላይ መሆኑን፤ ስለጉዳዩ ጥናታዊ ፊልም የሰሩ ጀርመናዊ የፊልም ስራ አዋቂ እና አካባቢዉ ላይ የሚገኙትን የሃይማኖት አባቶችን አነጋግረን ዘገባ አስደምጠናል።ይህ ለዘመናት የቆየ ችግር መፍትሄዉ ምን ይሆን? በእስራኤል የኢትዮጵያ ሌሎች ይዞታዎችስ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ? ከሰሃራ በታች ከሚገኙት አፍሪቃ ሃራት በእስራኤል ገዳም እና ሌላም ይዞታ ያላት ብቸኛ ጥቁር አፍሪቃዊት አገር ኢትዮጵያ መሆንዋ ይታወቃል። በስድስት ሀገራት አብያተ ክርስትያ የተያዘዉ የጎልጎታዉ ዴር ሱልጣን ገዳም ዉዝግብ ከጀመረ ከ240 ዓመታት በላይ ማስቆጠሩን ባለፈዉ ሳምንት በቅድስት ሀገር እየሩሳሌም የኢትዮጳያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን ገዳማት ሊቃነ-ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማትያስ መናገራቸዉ ይታወሳል።

መፍትሄዉ ምን ይሆን? በእስራኤል የኢትዮጵያ ገዳማትና ታሪካዊ ቦታዎችን ለማስጠበቅ የተቋቋመዉ ድርጅት የቦርድ ሊቀመንበር አቶ አለማየሁ ተስፋዪ፤ ድርጅታቸዉ የኢትዮጳያን ይዞታዎች ለማስጠበቅ በርካታ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ነዉ ሲሉ ገልጸዋል። በተለይ የዴር ሱልጣንን ይዞታ በተመለከተ በፍርድ ቤት ሳይሆን በሚኒስትሮች ደረጃ የተቋቋመ ኮሚቴ ጉዳዩን እየተከታተለዉ መሆኑን ገልጸዋል።
በርግጥ ይህን ችግር በተመለከተ መፍትሄ ለማፈላለግ በእስራኤል የኮፕት ቤተክርስትያንን እና በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤንባሲን ለማነጋገር ያደረግነዉ ጥረት አልተሳካም። በይፋ እንደሚታየዉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን እና በግብፅ ኮፕት ቤተ ክርስትያ መካከል ጠንካራ የሆነ ጥሩ መግባባት ያላቸዉ መሆኑ ነዉ። ለዚህ በምሳሌ ተጠቃሹ የግብፅ ኮፕት ቤተክርስትያን ፓትርያርክ ከዚህ ዓለም ሲለዪ ፍትሃቱን የመሩት የቀድሞዉ የኢትጵያዉ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ፓትርያርቅ አቡነ ጳዉሉስ ነበሩ።

እየሩሳሌም የሚታየዉ የሁለቱ አብያተ ክርስትያን ግንኙነት ግን ከዚህ ገጽታ እጅግ የራቀ ሆኖ ነዉ ፤ እና ይህን እንዴት ይጣጣማል? ለሚለዉ፤ በቅድስት ሀገር እየሩሳሌም የኢትዮጳያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን ገዳማት ተጠሪ ሊቃነ-ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ጉዳዩ መልስ የሌለዉ ነዉ ብለዉናል።

በሃይማኖት በሀገር ፍቅር ጸንተዉ በእየሩሳሌም ዴር ሱልጣን ገዳምን ይዞታ ለማስጠበቅ እና ለልጅ ልጅ ለማቆየት ትግል ላይ ያሉት መነኮሳት ህዝብ ሊደግፈን የሀገር ቅርስ በመሆኑም መንግስት መፍትሄ ሊያገኝልን ይገባል ሲሉ ጥሪአቸዉን ያሰማሉ። በእየሩሳሌም የሚገኙ የኢትዮጵያ ገዳማትን ይዞታ በተመለከተ በሁለት ተከታታይ ክፍል ቃለ ምልልስ በመስጠት የተባበሩንን ሁሉ በዝግጅት ክፍላችን ስም እናመሰግናለን። ሙሉዉን እንብር ያድምጡ!

ኢትዮጵያ እና የአፍሪቃ ዋንጫ ዝግጅት

Friday, January 18th, 2013

የአፍሪቃ አህጉር የዘንድሮው የእግር ኳስ ዋንጫ ቅድመ-ዝግጅት፣በጀርመናውያን እይታ ምን ይመስላል? ለዋንጫ ዋንኞቹ ተፎካካሪዎች እነማን ይሆኑ? አይቮሪኮስት፣ ዛምቢያ ወይስ ፣ እ ጎ አ የ 2010 የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ፣ እንዲሁም የዘንድሮው

የአፍሪቃ ዋንጫ አስተናጋጅ ሀገር ደቡብ አፍሪቃ!? ነገ ፣ ቅዳሜ ጥር 11 ቀን 2005 የሚጀመረው ውድድር ፣ የ 16 አገሮች ብሔራዊ ቡድኖች የሚሳተፉበት ነው።

ለነገሩ፤ ውድድሩ በተረኛዋ ሊቢያ ነበረ መስተናገድ የነበረበት። ይሁንና አምና በተፈጠረው የእርስ-በርስ ጦርነትና ከዚያም በቀጠለው አለመረጋጋት ሳቢያ በሌላ ቦታ ቢዘጋጅ ይሻላል ተብሎ፣ እ ጎ አ ከ 1996 ዓ ም ወዲህ ዕድሉ ዳግመኛ ለደቡብ አፍሪቃ ሊሰጥ ችሏል።

«ውድድሩን የማዘጋጀት ዕድል ለተሰጣት ለደቡብ አፍሪቃ ይህ ክብር ነው። ከ 2010 የዓለም ዋንጫ ወዲህ፤ የዘንድሮው የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር በዚያ እንዲስተናገድ ማድረጉ ብልህነት የተንጸባረቀበት ውሳኔ ነው። አገሪቱ፤ በመሠረተ ልማቱም ሆነ ፤ የተሳካ ውድድር ማዘጋጀት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ታሟላለችና!»

Max Grünewald በደቡብ አፍሪቃ አንደኛ ምድብ ከሚገኙት የአግር ኳስ ክለቦች፣ አያክስ ካፕሽታት ቡድን አሠልጣኝ ናቸው።

ጥር 11 የመክፈቻውና ፣ እሁድ የካቲት 3,2005 ዓ ም የፍጻሜው ግጥሚያ የሚካሄደው ጆሃንስበርግ ውስጥ በ «ሳከር ሲቲ ስቴዲዬም » ነው። የድርባኑ ሞሰስ -ማብሂዳ ስቴዲየማና ሌሎችም ለግጥሚያ ተመድበዋል። በ 2012 ጋቡን በተካሄደው የፍጻሜ ግጥሚያ፣ ሳይታሰብ፤ ዛምቢያ አይቮሪኮስትን አሸንፋ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የዋንጫ ባለቤት መሆኗ አይዘነጋም። Max Grünewald አሁንም 2 ቱ ቡድኖች ጥሩ ዕድል እንዳላቸው ያምናሉ።

«አይቮሪኮስት በኮከብ የፊት አጥቂ ድሮግባ እርዳታ እንዳለፈው ጊዜ፤ ቡድኑ በ ፍጹም ቅጣት ምት ሳይሸነፍ ፣ አሁን ውጤት ለማስመዝገብ መሰለፉ አይቀርም። ናይጀሪያን የመሳሰሉትንም በቀላሉ መገመት የሚቻል አይደለም። »

ደቡብ አፍሪቃ በምድብ ሀ ከሞሮኮ አንጎላና አስገራሚ ከተባለችው ካፑቨርድ ጋር ትጋጠማለች። ደሴቲዩ ካፑቨርድ፤ በማጣሪያ ግጥሚያ ካሜሩንን አሸንፋ ያስቀረች መሆኗ የሚዘነጋ አይደለም። ጋና በምድብ ለ ከማሊ ፣ ኒዠርና ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ጋር ይሆናል ውድድሯ! የዋንጫ ባለቤት ዛምቢያ፤ በ3ኛ ምድብ ከናይጀሪያ ቡርኪና ፋሶና ኢትዮጵያ ጋር ናት። በምድብ መ አልጀሪያ ቱኒሲያ፤ አይቮሪኮስትና ቶጎ ተጋጣሚዎች ናቸው።

አንዳንድ በከፍተኛ ደረጃ የታወቁ አፍሪቃውያን እግር ኳስ ተጫዋቾች፣ አገሮቻቸውን ወክለው ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ከመገኘት ይልቅ፣ አውሮፓ ውስጥ ለክለቦቻቸው መሰለፉን ቢመርጡም፤ ግሩዑነቫልድ እንደሚሉት፣ በዛ ያሉ ሌሎች ተጫዋቾች ብቅ-ብቅ ማለታቸው አይቀሬ ነው።ደቡብ አፍሪቃ፤ የዓለምን ዋንጫ በተሳካ ሁኔታ ካስተናገደች ወዲህ፤ የቀድሞው የብሔራዊ ቡድኗ ተጫዋች ዴቪድ ኒያቲ እንደሚለው፣ አሁንም መሰናዶዋ እንደገና የሠመረ እንደሚሆን አያጠራጥርም።

«ይህ ፣ ለኛ ፣ ለቱሪዝም ገበያና ለእግር ኳስ አፍቃሪው ህዝብም ትልቅ ዕድል ነው። ዓለም ፣ አንዲት አዳጊ ሀገር ምን ማከናወን እንደምትችል ዓለም አቀፉን የእስፖርት ማኅበረሰብም ማስተናገድ የምትችል መሆኗን ያይላታል፣ እኛም የኩራት ስሜት ያድርብናል። »

የ 43 ዓመቱ ኒያቲ ይህ ውድድር ፣ ለክፍለ-ዓለሙ በመላ ማለፊያ ሥም እንደሚያሰጥም ተስፋውን ገልጾአል።

«ውድድሩ፤ አፍሪቃ በአስፖርት ምን እንደሚመስል ያሳያል። የተነቃቃ ዐቢይ የእስፖርት ኃይል መሆኑንም ያሥመሰክርበታል። የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ፤ አንድ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ደረጃ ሊገኝ እንደሚችልም ያለንን ተስፋ ሊያለመልም ይችላል።»

የአፍሪቃ ዋንቻ ውድድር አሸናፊ ብራዚል ውስጥ ለሚካሄደው የ 2013 የዓለም ኮንፈዴሬሽን ዋንጫ ውድድር በቀጥታ ያልፋል። የአግር ኳስ አፍቃሪ ቤሪ ፣ በተለይ በዚያች ሀገር እግር ኳስ ካለው እጅግ ተወዳጅነት ጋር፣ ብዙ እንግዶች እንደሚገኙ ተስፋ ያደረጋል።

«ለማንም የምሰጠው ምክር፤ በደቡብ አፍሪቃ የሚካሄደውን የእግር ር ኳስ ጨዋታ እንዲመለከት ነው። አወንታዊ ኃይልና መንፈስ ነው የሚያጎናጽፈው። በደቡብ አፍሪቃ እግር ኳስ ህይወት አዳሽ መሆኑንም መገንዘብ ያስችላል።»

ኢትዮጵያ ሙስና አለቅጥ ከተንሰራፋባቸዉ ሀገራት አንዷ ናት – ጀርመን ራዲዮ

Friday, January 11th, 2013

በዚሕ ሳምንት አንድ አድማጫችን ከኢትዮጵያ በላኩልን የSMS መልዕክት «ኢትዮጵያ ዉስጥ ሙስና እንደ አንድ የሥራ-መስክ እየተሰራበት ነዉ»፥-በማለት የሙስናን ወይም የንቅዘትን መንሠራፋት ባልተወሳሰበ አማርኛ ገልፀዉት ነበር። በአድማጫችን አስተያየት የማይስማሙ በርግጥ ይኖራሉ። ትራንስፓረንሲ እንተርናሽናልን የመሳሰሉ ጉዳዩን ያጠኑ ድርጅቶችና ባለሙያዎች እንደሚሉት ግን ኢትዮጵያ ባጭር ጊዜ ዉስጥ ሙስና በተለይ የባለሥልጣናት ሙስና አለቅጥ ከተንሰራፋባቸዉ ሐገራት አንዷ ናት። ዛሬ ደግሞ አዲስ አበባ ዉስጥ በኢትዮጵያ ሥለላዉ ሙስናና ደረጃዉ የተደረገ ጥናት አዲስ አበባ ዉስጥ ይፋ ሆኗል። ጌታቸዉ ተድላ ሐይለ ጊዮርጊስ ዝርዝር ዘገባ አለዉ።

የርዕዮት ዓለሙ ክስና የጠበቃዋ ተቃዉሞ

Wednesday, January 9th, 2013

ርዕዮት ዓለሙ ከዚሕ ቀደም የበታች ፍርድ ቤት አስራ-አራት ዓመት እስራትና የገንዘብ መቀጮ በይኖባት ነበር።ይግማኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ግን ቅጣቱን ወደ አምስት-ዓመታት እስራት ዝቅ አድርጎታል።ርዕዮት ዓለሙ ለሰበር ሰሚዉ ችሎት አቤት ያለችዉ የአምስት ዓመቱ እስራትም የሕግ አተረጓገም ክፍተት አለበት በሚል ነበር

የጋዜጣ አምደኛ ርዕዮት ዓለሙ በአሸባሪነት ወንጀል የተበየነባት ቅጣት እንዲሠረዝ ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሠበር ሰሚ ችሎት ያቀረበችዉን አቤቱታ ችሎቱ ዉቅድቅ አደረገዉ።ርዕዮት ዓለሙ ከዚሕ ቀደም የበታች ፍርድ ቤት አስራ-አራት ዓመት እስራትና የገንዘብ መቀጮ በይኖባት ነበር።ይግማኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ግን ቅጣቱን ወደ አምስት-ዓመታት እስራት ዝቅ አድርጎታል።ርዕዮት ዓለሙ ለሰበር ሰሚዉ ችሎት አቤት ያለችዉ የአምስት ዓመቱ እስራትም የሕግ አተረጓገም ክፍተት አለበት በሚል ነበር።ትናንት አዲስ አበባ ያስቻለዉ ሰበር ሰሚ ፍርድ ቤት ግን አቤቱታን ዉድቅ አድርጎታል።የርዕዮት ጠበቃ የችሎቱን ዉሳኔ አልተቀበለቱም።ዩሐንስ ገብረ እግዚ አብሔር ዝር ዝር ዘገባ ልኮልናል።

የጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ የ100 ቀናት አመራር

Monday, January 7th, 2013

ከጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ህልፈተ ህይወት በኋላ ባለፈዉ መስከረም ወር አጋማሽ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ስልጣን ሲይዙ ፤ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችን ላቀፈችዉ ኢትዮጵያ የፖለቲካ አስታራቂ እና ጥሩ መፍትሄን ያስገኛሉ የሚል ተስፋን አሰንቆ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣን ከያዙ በኋላ በርካታ ኢትዮጵያዉያን ፤ የመሪ ለዉጡን ተከትሎ በአገሪቱ የሚኖረዉ ፖለቲካዊ እርምጃ በመጠኑም ቢሆን ተሻሽሎ የመናገር ነፃነት ይኖራል፤ በሲቪል ማህበራት ላይ እና በብዙሃን መገናኛዎች ላይ የሚደረገዉ ጫና ይቆማል፤ የሚል ተስፋ ነበራቸዉ። ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣን ከያዙ መቶ ቀናት አለፋቸዉ፤ በዚህ ግዜ ዉስጥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥራ የአገሪቱ ፖለቲካዊ እርምጃ ምን ይመስላል? ሉድገር ሻዶምሲኪ ያጠናቀረዉ ዘገባ እንደሚከተለዉ ተቀናብሯል።


ከመነሻዉ ተስፋ ሰጪ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃለ መሃላ ከመፈጸማቸዉ አስቀድሞ፤ በኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ ወቅት፤ መንግስት ለ2,000 እስረኞች ምህረት አድርጎ ከእስር በነፃ ለቀቀ። በተመሳሳይ ወቅት፤ መንግስት አሸባሪ ብሎ ከፈረጀዉ ቡድን፤ ከኦጋዴኑ ብሄራዊ ነፃ አዉጭ ግንባር- ኦብነግ ጋር፤ ኬንያ ዉስጥ ለድርድር ተቀምጦአል። ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ አልጃዚራ፤ በተሰኘዉ የቴሌቭዥን ጣብያ ቀርበዉ፤ ከኤርትራ ጋር ለማንኛዉም የሰላም ዉይይት ዝግጁነታቸዉን ሲናገሩ፤ ሃሳቡ ብሩህ ተስፋን ፈጥቆ፤ የብዙዎች ምኞት እንደሚሳካ እምነት አሳድሯል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ከወላይታ ብሄር ተወላጅ የሆኑት፤ የዉሃ ምህንድስና ምሁር፤ አቶ ኃይለማርያም፤ በእርግጥም የፖለቲካ እና የስልጣን ሽኩቻ፤ እንደሚፈጠር በሚገመትበት ወቅት፤ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣኑን መያዛቸዉ፤ ተምሳሌቱ ትልቅ ነዉ ያሉት፤ ከመንግስት ነፃ የሆነዉ፤ ዓለማቀፍ ፖለቲካ ጉዳዮችን የሚከታተለዉ ቢሮ በለንደን፤ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ምሁሩ ጃሰን ሞስሊ እንዲህ ይገልፃሉ፤ « እንደ ወላይታ ካለ አነስተኛ ከሆነ ጎሳ የመጣ ሰዉ ስልጣን መያዙ በመሰረቱ ተምሳሌቱ ትልቅ ትርጉም አለዉ። ሆኖም ተግራባዊነቱ መስራትም ይኖርበታል። የሶስት ሴት ልጆች አባት የሆኑት፤ የ 47 ዓመቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ከ1997 ዓመተ ምህረቱ ደም አፋሳሽ ምርጫ በኋላ፤ ከግዜ ወደ ግዜ አንባገነን እየሆኑ ከመጡት ከሟቹ ከመለስ ዜናዊ ጋር ሲነፃፀሩ በርግጥም በፖለቲካዉ ረገድ ግርማ ሞገሳቸዉ እንብዛም አይታይም። ኃይለማርያም በመለስ ዘመን፣የክፍለ ሃገር አስተዳዳሪ ፤ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ሆነዋል። ሆኖም ኃይለማርያም ደሳለኝ በትጥቅ ትግሉ ከኢህአዴግ ጋር አብረዉ ባይኖሩም በትምህርቱ በተሻለ መልኩ በመግፋታቸዉ በርካቶች የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ስልጣን እንዲይዙ ፈልገዉ ነበር። ስልጣኑን ከያዙ በኋላ ግን በአገሪቱ አንዳችም ፖለቲካዊ ለዉጥ አላደረጉም ሲሉ ብዙዎች ቅሪታቸዉን ይገልጻሉ። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዳዮች ምሁሩ ጃሰን ሞስሊም ይህንኑ ነዉ የሚናገሩት «የአሁኑን መንግስት የፖለቲካ ስራዎች ካለፈዉ አስተዳደር ጋር ስናነፃጽረዉ፤ በእዉነቱ ምንም አይነት ለዉጥ አይታይበትም። በቅርቡ በካቢኔ አንድ አነስተኛ ለዉጥ ተደርጎአል፤ ግን ይህ ለዉጥ ትልቅ የሚባል እና የፖለቲካዉን አካሄድ የሚቀይረዉ አይደለም።

ከጎረቤት ሶማልያ ጋር ያለዉ የፖለቲካ ሁኔታ፤ የዓባይን ዉሃ አያያዝ በተመለከተ ከሱዳንና ከግብፅ ጋር የነበረዉ አቋም አሁንም አልተቀየረም። በመጠኑ በጥያቄ የሚታይ ነገር ቢኖር፤ በሰሜን አጎራባች ከሆነችዉ ከኤርትራ ጋር ያለዉን ግንኙነት ለማሻሻል የሚደረግ እንቅስቃሴ የመኖር አለመኖሩ ጉዳይ ነዉ። ስለዚህ ያለዉ ሁኔታ የድሮዉን መቀጠል ነዉ።» መንግስት እንደተለወጠ የሀገሪቱ የልማት ትብብር አጋሮች ለለዉጥ የነበራቸዉ ጉጉት እየከሰመ መጣ። ምዕራባዉያን ዲፕሎማቶች፤ ጋዜጠኞችን በተመለከተ የፍርድ ቤት ችሎት ላይ፤ አንድም ቀን በታዛቢነት ሳይገኙ የዋሉበት ቀን የለም። እንደ ዓለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት፤ CPJ ገለጻ፤ በጸረ – ሽብሩ ህግ በአሸባሪነት ከተከሰሱት አስራ አንድ ጋዜጠኞች መካከል «እስከ ጎርጎረሳዉያኑ 2012 ዓ,ም መጨረሻ» ስድስቱም በእስር ላይ ሲሆኑ ከነዚህ መካከል ታዋቂዉ ተሸላሚ ዓምደኛ እስክንድር ነጋ ይገኝበታል። ይኸዉ የፀረ-ሽብር ህግን ተመልክቶ 29 ሙስሊም ጋዜጠኞች፤ ሙስሊም የሃይማኖት አባቶች፤ መብት ተቆርቋሪዎች፤ በአሸባሪነት ተፈርጀዋል። ለበርካታ ግዜያት ይህንኑ በመቃወም፤ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ቅሪታቸዉን በማሰማት ላይ ሲሆኑ፤ ዘወትር ዓርብ በአዲስ አበባዉ አንዋር መስጊድ መንግስት ላይ የተቃዉሞዉ ድምጻቸዉን ማሰማታቸዉን ቀጥለዋል። በጎርጎረሳዉያኑ 2012 መጠናቀቅያ ላይ፤ 16 የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በኢትዮጵያ ሃሳብን በነፃ የመግለጽ ነፃነት ይከበር ሲሉ በይፋ በላኩት ደብዳቤ መጠየቃቸዉ ይታወሳል። ይህን ደብዳቤ ከላኩት መካከል፤ ጀርመናዊዉ አሌክሳንደር ግራፍ ላምስዶርፍ ይገኙበታል። ላምስዶርፍ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል፤ «አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ግልፅ የፖለቲካ አካሄድ የሚከተሉ ከሆነ ሀገራቸዉን ወደፊት ለማራመድ እድሉ አላቸዉ። የማኅበረሰቡን ግልፅነት፤ ትችትና ነጻ ሃሳቦችን ለማስተናገድ ከፈቀዱ፤ ከጎረቤቶቻቸዉ ጋ ያላቸዉን ግንኙነት ካሻሻሉ፤ ለምሳሌ አሥመራን ለመጎብኘት ቢሄዱ ለሰላም ላላቸዉ ቁርጠኝነት ዋና አመላካች ነዉ። ይህም ለኢትዮጵያዉያንና ኢትዮጵያ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ላላት ሁኔታ ፍፁም አስተማማኝ እና መሰረታዉ ጉዳይ ነዉ።» በስልታዊ አቀማመጥዋ የአፍሪቃ ህብረት መቀመጫ በሆነችዉ በአፍሪቃ መዲና – ኢትዮጵያ ከባድ ተግዳሮቶች ተደቅነዋል። በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ ያለዉ የህዝቧ ቁጥር ከአፍሪቃ ሁለተኛ ደረጃን እንድትይዝ ቢያደርጋትም፤ አሁንም እድገቱ አልተገታም። በርካታ ብሄር ብሄረሰቦችን ያቀፈችዉ ሀገር፤ ብሄራዊ አንድነትን ከመገንባት አኳያ፤ ትግል ይዛለች። ምንም እንኳ የሀገሪቱ ኤኮኖሚ በሁለት አሃዝ ማደጉ ቢነገርም፤ የዚህ ተጠቃሚዉ በጣም ጥቂቱ፤ መካከለኛ ገቢ ያለዉ የከተማዉ ነዋሪ ነዉ። ከፀጥታ አኳያ፤ በዓለም ጸረ-ሽብርተኝነትን ከሚዋጉት ሀገራት መካከል፤ ኢትዮጵያ በሶማልያ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ቀዳሚዉን ስፍራ ይዛለች።

እንግዲህ እነዚህ፤ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከአዲሱ ከካቤኔያቸዉ ጋ በመሆን፤ ባፋጣኝ ምላሽ ሊሰጧቸዉ የሚገቧቸዉ ጉዳዮች መሆናቸዉ ነዉ። ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሹመታቸዉን ከተቀበሉበት ቀን ማግስት አንስተዉ በተደጋጋሚ፤ በፓለቲካዉ ከእሳቸዉ ቀድመዉ ስልጣን ላይ የነበሩትን የመለስ ዜናዊን ጅምሮች፤ ሳይበርዙ እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። ጋዜጠኞች እና ሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎችን የማሳደዱ ርምጃ መቀጠሉን፤ የፀጥታ አስከባሪዎችም ለተቃዉሞ ሰለፍ በሚወጡ ሙስሊሞች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት፤ የተመለከቱ ታዛቢዎች ስልጣን ከያዙ 100 ቀናት የሆናቸዉ አዲሱ የአፍሪቃዉ ቀንድ ጠንካራ ሀገር መሪ፤ ቃል በቃል የተናገሩትን መተግበራቸዉ ነዉ ሲሉ፤ ፍርሃታቸዉን እየገለፁ ነዉ። ከመንግስት ነፃ የሆነዉና ተቀማጭነቱን በለንደን ያደረገዉ ዓለማቀፍ ፖለቲካ ጉዳዮችን በሚከታተለዉ ቢሮ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ምሁር ጃሰን ሞስሊም ይህንኑ አስከትሉዉ እንዲህ ይላሉ « የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከዚህ አለም በሞት መለየት በኢትዮጵያ የፖለቲካዉን ሁኔታ አልቀየረዉም። ለምሳሌ ሃሳብን በነጻ መግለፅ ሆነ ምርጫን በሚመለከት፤ የተሻለ ነገር አላመጣም። ይህ ፖለቲካዊ አካሄድ ከ1997 ዓ,ም ጀምሮ ተግባራዊ እየሆነ ነዉ። አመራሩን ጠበቅ እያደረገ ተቃዉሞ ሲበዛበት ደግሞ በትንሹ ለቀቅ በማድረግ፤ ሁኔታዉን እያረጋጋ አስተዳደሩን ቀጥሎአል። ይህ ዘዴ አሁንም ሳይለወጥ እየተሰራበት ነዉ»

የጳዉሎስ ኞኞ ሥራዎች

Friday, January 4th, 2013

ጋዜጠኛ ጳዉሎስ ኞኞ በህይወት ዘመኑ ለአንባብያን ያበረከታቸዉ ሥራዎች ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ተበረከተ። የታዋቂዉን ጋዜጠኛና ደራሲ ሥራዎች ለተቋሙ ያበረከተዉ ልጁ ሐዋርያዉ ጳዉሎስ በግሉ ቤተመጻህፍት ለማቋቋም አቅሙ ባይፈቅድለት ኅብረተሰቡ ከዩኒቨርሲቲዉ እንዲያገኘዉና እንዲጠቀምበት አስቦ ለመስጠት መወሰኑን ገልጸል። በስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙ ታዳሚ ምሁራን የጳዉሎስ ኞኞን ስራዎች ሲዘረዝሩ በተለይ በጋዜጣ ላይ አንድ ጥያቄ አለኝ በሚለዉ አምዱ በወቅቱ የአዲስ ዘመን ጋዜጣን ቅጂ ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን አስታዉሰዋል።

ግጭት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ

Thursday, January 3rd, 2013

(Deutsche Welle) – ከትናንት ከሰአት በኋላ አንስቶ እስከ ዛሬ ጠዋት በቀጠለው ግጭት ተማሪዎች እንደቆሰሉና በተማሪዎች መኝታ ክፍሎች ላይም ጉዳት መድረሱን የአይን ምስክሮች መናገራቸውን የአዲስ አበባው ወኪላችን ገልጾልናል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በ4 ኪሎ ቅፅር ግቢ በተማሪዎች መካከል በተነሳ ግጭት ተማሪዎች መጎዳታቸውና በግጭቱ የተጠረጠሩም መያዛቸው ተስምቷል ። ከትናንት ከሰአት በኋላ አንስቶ እስከ ዛሬ ጠዋት በቀጠለው ግጭት ተማሪዎች እንደቆሰሉና በተማሪዎች መኝታ ክፍሎች ላይም ጉዳት መድረሱን የአይን ምስክሮች መናገራቸውን የአዲስ አበባው ወኪላችን ገልጾልናል ። አካባቢውም በፌደራል ፖሊስ ይጠበቅ እንደነበረም ተነግሯል ። ስለ ሁኔታው የአዲስ አበባውን ዘጋቢያችንን ዮሐንስ ገብረ እግዚ አብሔርን በስልክ አነጋግረናል።

የአዲሱ ጠ/ሚ ሹመት መፅደቅ

Friday, September 21st, 2012
የኢትዮጵያ ፓርላማ ዛሬ ባካሄደዉ አስቸኳይ ጉባኤ የአዲሱን ጠ/ሚኒስትር ሹመት አፀደቀ። ሹመታቸዉ በምክር ቤቱ የጸደቀላቸዉ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸዉ የምክትላቸዉን የአቶ ደመቀ መኮንን ሹመት ለምክር ቤቱ አቅርበዉ አፀድቀዋል።

ወጣት ሴቶች በሳውዲ ዓረቢያ

Friday, September 14th, 2012
በርካታ ኢትዮጵያውያን ሴቶች በየጊዜው የተሻለ ህይወት ፍለጋ ወደ አረብ ሀገር ይጓዟሉ። በርግጥ እዚያ ኢትዮጵያ ውስጥ በቤት ሰራተኝነት ከሚያገኙት የበለጠም ይከፈላቸዋል። ግን፤ ኑሮ በአረብ አገር በጣም ከባድ እንደሆነ፤ በተለይ ሄደው ያዩት በተደጋጋሚ ይናገራሉ።

የመለስ ዜናዊ ከህዝብ እይታ መሰወር

Friday, August 10th, 2012

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የጤንነት ይዞታና ያሉበት ሁኔታ አነጋጋሪ የሆነዉ በኢትዮጵያዉያን ዘንድ ብቻ አይደለም። ጉዳዩ በሀገር ዉስጥና በዉጭ በሚገኙ በርካታ የዲፕሎማሲዉ ማኅብረሰብ አባትም ጭምር መነጋገሪያ ስለመሆኑ ከየአቅጣጫዉ እየተገለፀ ነዉ።

በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የታወቁ መፅሔቶችና ጋዜጦችም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተዉ አቶ መለስ ዜናዊ የትናቸዉ በማለት እየጠየቁ፤ ስለጤንነታቸዉም ሆነ ስላሉበት ሁኔታ በመንግስት በኩል እስካሁን የተሰጠዉ መግለጫም የሚያረካ ሳይሆን ጥርጣሬዎችን የሚያጭር መሆኑን በመግለፅ ፅፈዉ አስነብበዋል። አንዳንዶቹ ዘገባዎች ሁኔታዉ በየዓመቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮችን ለመንግስታቸዉ የሚለግሱ ወገኖችንም ማሳሰቡን ነዉ ያመለከቱት።

Play below

 

የሶርያ መንግሥት ከባለሥልጣናቱ የገጠመው ችግር

Tuesday, August 7th, 2012

epa03347003 A handout photo made available by the official Syrian Arab News Agency (SANA) shows Syrian President Bashar Assad(R) meeting with Secretary of Iran_s Supreme National Security Council, Saeed Jalili (L), in Damascus, Syria, 07 August 2012. Jalili arrived in Damascus earlier in the day coming from Lebanon on an official visit to discuss the situation of the Iranians abducted outside Damascus, as well as the 17-month-old unrest in Syria. A Syrian rebel group claimed responsibility for holding some 48 hostages - 47 Iranians plus an Afghan. EPA/SANA/HANDOUT HANDOUT EDITORIAL USE ONLY/NO SALES +++(c) dpa - Bildfunk+++ የሶርያ ጠቅላይ ሚንስትር ሪዣድ ሂጃብ የፕሬዚደንት በሻር አል አሳድ መንግሥት በራሱ ሕዝብ ላይ ያካሂደዋል ያሉትን የጀምላ ጭፍጨፋ በመቃወም በትናንቱ ዕለት ከድተው የተቃዋሚውን ጎራ መቀላቀላቸው የሚታወስ ነው። የሶርያ መንግሥት ግን ሂጃብ ከሥልጣናቸው እንደተባረሩ ነው ያስታወቀው።

ውጭ የፖለቲካ ታዛቢዎች እንደሚሉት፡ የሶርያ ጠቅላይ ሚንስትር እና በሶርያ የተቃዋሚው ወገን ቃል አቀባይ ዘገባ መሠረት፡ ሁለት የመንግሥት ሚንስትሮች እና ሦስት ከፍተኛ የጦር ኃይሉ መኮንኖችም የከዱበት ድርጊት የፕሬዚደንት አሳድ መንግሥት ከውስጥ በገጠመው ተቃውሞ እየፈራረሰ መሆኑን ጠቋሚ ነው።

ይህ በዚህ እንዳለ፣ የሶርያ ፕሬዝደንት በሽር አልአሰድ ላለፉት 17 ወራት የተነሳባቸዉ ህዝባዊ ተቃዉሞ ለመጨፍለቅ ቆርጠዉ መነሳታቸዉን አመለከቱ። ከሁለት ሳምንታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ያሉት አልአሰድ፤ የሶርያ ህዝብና መንግስት የአሸባሪዎችን ሀገርና ሽብርተኝነትን ለመዋጋት መዘጋጀታቸዉን መግለፃቸዉን ሮይተርስ የሀገሪቱን የዜና ወኪል በመጥቀስ ዘግቧል። አልአሰድ ስለጤና ማጣታቸዉም ሆነ ስለመገደላቸዉ ሲናፈስ የነበረዉን ወሬ ለጉብኝት ደማስቆ ከሚገኙት የኢራን የከፍተኛ ብሄራዊ የደህነት ምክር ቤት ኃላፊ ሳኢድ ጃሊሊ ጋ በመሆን በቴሌቪዥን ብቅ በማለትም መሠረተ ቢስ እንደሆነ አሳይተዋል። ያዳምጡ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ም/ቤት ስብሰባ ዘገባ

Monday, August 6th, 2012

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ም/ቤት የተሰኘው ድርጅት፤ በትናንትናው ዕለት፤ ዋሽንግተን ዲ ሲ ውስጥ ህዝባዊ ስብሰባ አካሂዷል። በዚሁ ስብሰባ ላይ የተገኙ ታዳሚዎች በም/ቤቱ የወደፊት ዓላማና ግብ ላይ ውይይት አድርገዋል የስብሰባውን ሂደት የተከታተለው አበበ ፈለቀ የሚከተለውን ዘገባ ልኮልናል።

የመን የነበሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች

Tuesday, July 31st, 2012

በኢትዮጵያ መንግሥትና IOM በሚል ምሕፃረ-ቃል በሚጠራዉ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት አማካይነት ወደ ሐገራቸዉ የተመለሱት ስደተኞች በየመን አቋርጠዉ ወደ ተለያዩ አረብ ሐገራት ለመግባት ያለሙ ነበሩ።

በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ የመን ተሠደዉ የነበሩ በመቶ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን ሰሞኑን ወደ ሐገራቸዉ ተመልሰዋል። በኢትዮጵያ መንግሥትና IOM በሚል ምሕፃረ-ቃል በሚጠራዉ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት አማካይነት ወደ ሐገራቸዉ የተመለሱት ስደተኞች በየመን አቋርጠዉ ወደ ተለያዩ አረብ ሐገራት ለመግባት ያለሙ ነበሩ።የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ጌታቸዉ ተድላ ሐይለ ጊዮርጊስ እንደዘገበዉ ካለፈዉ ሳምንት ማብቂያ ጀምሮ ከአምስት መቶ በላይ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች አዲስ አበባ ገብተዋል።ዝር ዝሩን እነሆ።

Play below

 

በሞያሌው ግጭት የወያኔ ባለስልጣናቱ እጅ

Monday, July 30th, 2012

ደቡብ ኢትዮጵያ በኬንያ ጠረፍ አኳያ በምትገኘው ሞያሌ ውስጥ ረቡዕ (18.11.2004 ዓ.ም.) በተቀሰቀሰው ግጭት አንዳንድ የአካባቢው አስተዳደር አካላት እጃቸው እንደነበረበት ተገለፀ። ይህን የተነናገሩት የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ባለስልጣኑ አቶ አበበ ወርቄ ዛሬ ለዶቸ ቬሌ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ነው።

በግጭቱ 18 ሰዎች መገደላቸው እና በሺዎች የሚቆጠሩት ወሰን አቋርጠው ወደ ኬንያ እንደሸሹ ተዘግቧል። እንደ በርካታ የዜና አውታሮች ገለፃ ከኬንያ ድንበር 1 ነጥብ 6 ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ በምትገኘው ሞያሌ ተቀስቅሶ የነበረው ግጭት ጋሪ እና ቦረና በተሰኙት ሁለት ጎሳዎች የመሬት ባለቤትነት ውዝግብ ሳቢያ ነበር የተነሳው።

የተለያዩ የዜና አውታሮች በግጭቱ 18 ሰዎች ተገድለው 12 መቁሰላቸውን እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩት መሰደዳቸውን መዘገባቸው ይታወቃል። በሁለቱ ጎሳዎች መካከል የተነሳው የመሬት የይገባኛል ጥያቄ አዲስ ሳይሆን ቆየት ያለ እንደሆነ ነው የሚነገረው። እንዲያም ሆኖ ግን የጎሳ አባላቱ ለረዥም ጊዜያት ጥይት ሲያከማቹ እና መሳሪያ ሲሰበስቡ ያስቆማቸው ሀይል አልነበረም ይላሉ የአካባቢው ነዋሪ።

Play below

 

የጋና ፕሬዝደንት ድንገተኛ ሞት

Wednesday, July 25th, 2012

የጋናዉ ፕሬዝደንት ድንገት ከዚህ ዓለም በሞት መለያታቸዉ የተሰማዉ ትናንት ማምሻዉን ነዉ። ፕሬዝደንት ጆን አታ ሚልስን ሳይታሰብ ለህልፈት ያበቃቸዉ ምክንያት በይፋ ባይገለፅም፤ በቅርቡ የተለመደ የህክምና ምርመራ ለማድረግ ወደዩናይትድ ስቴትስ ተጉዘዉ እንደነበር ግን ተገልጿል።

Atta Millsየሀገር ዉስጥ የመገናኛ ብዙሃን ግን የጉሮሮ ካንሰር ሲያሰቃያቸዉ እንደቆየ ዘግበዋል። የእሳቸዉ ሞት በተረጋጋ የፖለቲካ ይዞታዋ የምትታወቀዉን ሀገር ወዴት ሊወስዳት እንደሚችል ከወዲሁ ማነጋገር ሲጀምር፤ ህልፈተ ህይወታቸዉ በተሰማ በሰዓታት ዉስጥ ምክትላቸዉ ሥፍራዉን መያዛቸዉ ነዉ የተሰማዉ። ጆን ኢቫንስ አታ ሚልስ ህይወታቸዉ ባለፈባት በሐምሌ ወር በጎርጎሮሳዊዉ የዘመን ቀመር በ21ኛዉ ቀን 1944ዓ,ም ነዉ በጋራ ምዕራባዊ ግዛት ታርዋካ በተባለች ስፍራ የተወለዱት። ቅዳሜ ዕለት 68ኛ ዓመታቸዉን ያከበሩት አታ ሚልስ በያዙት የፕሬዝደንትነት ስልጣን ለመቀጠል ታህሳስ ላይ በሚካሄደዉ ምርጫ ዳግም ለመወዳደር ተዘጋጅተዉ ነበር።

ብዙም ሳይሰማላቸዉ በዝምታ ሲያስታምሙት የከረሙት ህመም ግን ለዚህ ቀጠሮ አለበቃቸዉም፤ ከአምስት ወራት አስቀድሞ ነጠቃቸዉ እንጂ። ሞታቸዉ ጋናዎችን አስደንግጧል፤

«በጣም አዝኛለሁ፤ አዘዉትሬ እከታተላቸዉ ነበር፤ ሆኖም በጣም ጥሩ ሰዉ ነበሩ።»

ጋናዊቱ የፕሬዝደንቱን ሞት ሲሰሙ፤

«አሳዛኝ ዜና ነዉ፤ ታዉቃለህ ሰዉየዉ ትሁት ሰዉ ነበሩ፤ ጥሩ ሰብዕና ያላቸዉ ሰዉ ነበሩ፤ ሁሉም ያደንቃቸዋል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ደግሞ የተሻለዉን ያዉቃል፤ እኛ ልናደርግ የምንችለዉ ነገር አይኖርም።»

መልካም ሰብዕናቸዉን እኝህ ብቻም አይደሉ የገለፁላቸዉ፤ እኝህም ይህን ነዉ ያሉት፤

«በትሁት ሰብዕናቸዉ አስታዉሳቸዋለሁ፤ በህግ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ቢኖራቸዉም አይኮሩም ነበር፤ እንዲህ ያሉ አንዳንድ ሰዎች ምናልባት አለሁ አለሁ ሊሉ ይችላሉ፤ እሳቸዉ ግን ሁልጊዜ ትህትና የተላበሱ ነበሩ፤ የሚከበሩ ሰዉ ናቸዉ።»

ጋናዉያን ድንገት በሞት ስላጧቸዉ ፕሬዝደንት ጆን አታ ሚልስ የሰጡት አስተያየት ነዉ።

«በጣም ነዉ ያዘንኩት፤ በጣም ጥሩ ሰዉ ነዉ ያጣነዉ፤ በእርግጥ በጣም ጥሩ ሰዉ።»

ጋና ዛሬ ላለፉት አራት ዓመታት በፕሬዝደንትነት ለመሯት ሚልስ ስትተክዝ ስታነባ አርፍዳለች። በህገ መንግስቱ መሠረት ፕሬዝደንቱ በሞት ሲለይ ወዲያዉ ምክትሉ ኃላፊነቱን ይረከባል። ትናንት የፕሬዝደንት ጆን አታ ሚልስ ህልፈተ ህይወት በተሰማ በሰዓታት ዉስጥ ምክር ቤቱ ተሰበሰበ። ምክትላቸዉ የነበሩት ጆን ማሃማ ቃለመሃላ ፈፅሙና መንበሩን ተረከቡ። እስከ መጪዉ ምርጫ ድረስ በፕሬዝደንትነት የሚቆዩት ማሃማ በሞት የተለዩትን ፕሬዝደንት አባት፤ አርአያ አሏቸዉ፤

«ያጣሁት አባቴን ነዉ፤ ጓደኛዬን ነዉ፤ ምሳሌዬን ነዉ ያጣሁት፤ ከፍተኛ ጓድ ነዉ ያጣሁት፤ ፕሬዝደንት አታ ሚልስ ህይወታቸዉን ሙሉ ለዉድ ሀገራችን የሰጡ፤ በአሁኑ ወቅት በመጨረሻ የምናወሳዉ ለሀገራችን አንድነትና መረጋጋት ያደረጉትን አስተዋፅኦ ነዉ።»

ከተረጋጋ ፖለቲካዋ፤ ሌላ በዴሞክራሲያዊ ሂደት በምታካሂደዉ የስልጣን ሽግግር የምትታወቀዉ ጋና፤ የፕሬዝደንቷ ድንገተኛ ሞት እንደመሰል የአፍሪቃ ሀገሮች ዉጥንቅጥ ሳያሳያት እስከምርጫዉ የሚመራ ፕሬዝደንት መሰየሙ ተሳክቶላታል። የ53 ዓመቱ የታሪክ ምሁር ማሃም የሀገሪቱን ኤኮኖሚ በተረጋጋ መንገድ እንዲቀጥል ይረዳሉ የሚል ተስፋ ተጥሎባቸዋል። ዋናዉ ጥያቄ ግን ለቀጣዩ ምርጫ በአታሚልስ እግር በእጩነት ማን ይተካል የሚለዉ ነዉ።

ፓርቲያቸዉ ብሄራዊ ዴሞክራሲ ተተኪዉን ይመርጣል ቢባልም፤ ብዙዎች ከማሃም አያልፍም ባይናቸዉ። ከዚህ በመነሳትም ምናልባት የታህሳሱ ምርጫ ጋና ዉስጥ አለመረጋጋት ሊያስከትል ያደግሞ አሁን ባለበት ደረጃ እጅግ የወረደዉ የሀገሪቱ የገንዘብ አቅም ሊባባስ ይችላል የሚል ስጋት አለ። አክራ የሚገኘዉ የጀርመኑ ፍሬድሪሽ ኤበርት ተቋም ባልደረባ ዳንኤላ ኩሱ በእሳቸዉና በምክትላቸዉ መካከል ጥብቅ ትስስር ስለነበር የፕሬዝደንት አታ ሚልስ ድንገት ማረፍ የጋናን ፖለቲካዊ ሁኔታ አይቀይረዉም ባይ ናቸዉ፤

«በመሠረቱ በጣም ግሩም ጉድኝት ያላቸዉ የሥራ ባልደረቦች ነበሩ። ሚልስ አዘዉትረዉ በሚያደርጉት የስራ ጉዞ ምክንያት በቦታቸዉ ተክተዋቸዉ የሚሠሩት ማሃማ ነበሩ። እንደዉም አንዳንዶች ተጠባባቂ ፕሬዝደንት ነበር የሚሏቸዉ። በተሠማሩበትም በርካታ ጥሩ ነገሮችን ሠርተዋል፤ ስለዚህ በደንብ የታዩና የታወቁ ምክትል ፕሬዝደንት ነበሩ።»

በጄሪ ሮዉሊንግስ ዘመነ ሥልጣን ከጎርጎሮሳዉያኑ 1997 እስከ 2001ዓ,ም ድረስ በምክትል ፕሬዝደንትነት ጋናን ያገለገሉት አታ ሚልስ፤ አልቀናቸዉም እንጂ በ2000 እና በ2004ዓ,ም ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ምክር ቤት ለሚባለዉ ፓርቲ ፕሬዝደንታዊ እጩ ሆነዉ ቀርበዋል። በዚሁ የዘመን ቀመር 2008 መገባደጃ ላይ ግን ቀናቸዉ እና በ2009ዓ,ም ጥር ወር በትረ ስልጣኑን ጨበጡ። እንደእሳቸዉ ቢሆን በመጪዉ ታህሳስ ወር በሚካሄደዉ ምርጫ ለመፎካከርና ከተሳካም ስልጣን ላይ ለመቆየት አቅደዉ ነበር። ሞት ግን ቀደማቸዉ ሳይታሰብ፤ ሰኞ አመመኝ አሉ፤ አክራ የሚገኘዉ 37ኛ ወራደራዊ ሃኪም ቤት ገቡ፤ ማክሰኞ ህልፈታቸዉ ተሰማ። ጆን አታ ሚልስ ጋና ዉስጥ እስካሁን ከስልጣን መንበራቸዉ ሳይሻሩ ሞት የወሰዳቸዉ ፕሬዝደንት ናቸዉ።

Play below

 

የሙስሊሞች ተቃውሞና የፖሊስ እርምጃ

Monday, July 23rd, 2012

መንግሥት በሃይማኖት ጉዳዮች ጣልቃ አይግባ የሚል መልእክት የሚያሰሙ ሙስሊሞች አደባባይ እየወጡ፣ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄዎቻቸውን ሲያቀርቡ ወራት ማለፋቸውን የተለያዩ መገናኛ ብዙኀን የዘገቡበት ጉዳይ ነው። ከሰሞኑ፣ ግን ለየት ያለ ሁኔታ ማጋጠሙን ፤ ጌታቸው ተድላ ኃ/ጊዮርጊስ የላከልን ዘገባ ያስረዳል።

Play below

 

የመለስ ዜናዊ መሰወር (ጀርመን ራዲዮ)

Monday, July 23rd, 2012

የኢትዮጵያ ፀጥታ አስከባሪዎች፣ ቤተ እምነቶችን ለማርከሰም ሆነ የእምነት ነፃነት ጠየቅን ያሉ ሙስሊሞችን በአስለቃሽ ጢስ እያፈኑ፣ በዱላ እየቀጠቀጡ ፥ለማሰር የሐገሪቱን ጠቅላይ ሚንስትር ቀጥተኛ ትዕዛዝ መጠበቅ አላስፈለጋቸዉም።አዲስ አበባ የአፍሪቃ መሪዎችን ጉባኤያ ለማተናገድ የትልቅ መሪዋ አለመኖር አላጎላትም።ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን የነፃነት በአልና በአፍሪቃ ሕብረት ጉባኤ ላይ በአዲሰ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሯና በዉጪ ጉዳይ ሚንስትሯመወከሏ ክብሯን አልቀነሰባትም።የአንጋፋ ዋና መሪዋ ግራ-አጋቢ ጤንነት የዉር ድንብር እያዳፋት፣ እሳቸዉ በሌሉበት ባለችበት መቀጠሏን-ካለመቀጥሏ ቃርጮሽ መሸጎጡ ነዉ ፈተናዉ።እንዴት ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

በኢትዮጵያ የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ዴቪድ ሺንና የቀድሞዉ የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ ጦር አዛዥ ዶክተር አረጋዊ በርሔ በአካል መተዋወቅ አለመተዋወቃቸዉን እኛ አናዉቅም።ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዉን ግን ሥልጣን፣ ጊዜና ሥፍራዉ ይራራቅ እንጂ ሁሉቱም በቅርብ ያዉቋቸዋል።

የመለስን መታመም የሰሙት፣ ሥለ ሕመማቸዉና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ሥለሚያደርሰዉ ተፅዕኖ አስተያየት የሰጡትም ከቋንቋ፣ ቦታ፣ ሠዓታት ልዩነት ባለፍ እኩል ነዉ።«መለስ» አሉ የኢትዮጵያዉን መሪ መጀመሪያ እንደ ፕሬዝዳንት ኋላ እንደ ጠቅላይ ሚንስትር በቅርብ የሚያዉቋቸዉ የቀድሞዉ አሜሪካዊ ዲፕሎማት «መለስ አስቀድመዉ የሚያቅዱ አይነት መሪ ናቸዉ።»

ሺን መለስን በቅርብ ከማወቃቸዉ ከብዙ አመታት በፊት አረጋዊ በርሔ መለስን እንደ አለቃ እያዘዙ፣ እንደ የበላይ እየመሩ፣ እንደ ቀዳማዊ ታጋይ እየመከሩ የነፍጥ ትግልን አብረዋቸዉ ኖረዉበታል።#
ዶክተር አረጋዊ በዚሕ ሁሉ ዘመን በጣም በቅርብ የሚያዉቋቸዉ መለስ ግን ሺን ከገለጧቸዉ መለስ ተቃራኒ ናቸዉ።

የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዘንድሮ ለእረፍት የሚዘጋበት ቀን ተላልፎ ነበር።በልማዱ፣ በምክር ቤቱ ሕግም ምክር ቤቱ የሚዘጋዉ በሚዘጋበት ጊዜ የምክር ቤቱ አባላት በሥራ ዘመናቸዉ ያከናወኑትን ለየመረጣቸዉ ሕዝብ እንዲያስረዱና የሕዝቡን አስተያየት ሰብስበዉ እንዲመለሱ ነዉ።
የምክር ቤቱ የእረፍት ጊዜ ሲራዘም እንደራሴዎቹ ከየመረጣቸዉ ሕዝብ ጋር ለመወያየት የያዙት ቀጠሮ ይታጎላል።ጊዜዉም ያጥራል።

እንደራሴዉ በሕዝብ ከተመረጠ ከመራጩ ጋር የሚገናኝበት ቀጠሮ የታጎለ ወይም ጊዜዉ ያጠረበትን ምክንያት ለመረጠዉ ሕዝብ ማስረዳት ሥላለበት የእረፍት ጊዜዉ የተራዘመበትን ትክክለኛ ምክንያት ማወቅ ግድ በሆነበት ነበር።ምክር ቤቱ በተራዘመዉ የእረፍት ጊዜዉ የቴሌኮም ረቂቅ ሕግንና የመጪዉን ዘመን በጀት አፅድቋል።

የበጀቱን መጠን፣ ምንጩን፣ የሚዉልበን መስክ፣ ማቅረብና ማስረዳት የነበረባቸዉ የሐገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር መሆን ነበረባቸዉ።እንደሚባለዉ በሕዝብ የተመረጡት ጠቅላይ ሚንስትር ከሕዝብ አሰብስበዉ ለሕዝብ የሚያዉሉት በጀት በሕዝብ ተወካዮች ሲፀድቅ አልነበሩም።ጠቅላይ ሚንስትሩ ያልነበሩበት ምክንያት፥ ብቸኛዉ ተቃዋሚ የምክር ቤት አባል አቶ ግርማ ሠይፉ እንደሚሉት አልተነገረም።

የሕዝብ ተወካይ የሚባሉት እንደራሴዎችም-አልጠየቁም።አሜሪካዊዉ የቀድሞ ዲፕሎማት እንዳሉት አስቀድመዉ የሚያቅዱት ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ምክር ቤቱም ሆነ መንግሥታቸዉ የሚፈፅመዉን አስቀድመዉ ያቀዱት ኢሕአዴግን የዘጠና-ዘጠኝ.ሥድስት ከመቶ የድምፅ ድል ሲያጎናፅፉት ሊሆን ይችላል።

ለመለስና በመለስ የረጅም ጊዜ ዕቅድ ምክር ቤት የገቡት ሰዎች ከፓርቲያቸዉ ሌላ የሚያስረዱትም፣ የሚፈርቱም፣ የሚያከብሩትም፣ የሚጠይቃቸዉም ሕዝብ የለም።እነሱም አልጠየቁም።መለስም አልነበሩም።የመለስን መታመም የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ዘግበዉበት፥የሕመማቸዉን አይነት፥ ደረጃና የሚታከሙበትን ሥፍራ ሁሉም እንዳሻዉ ተናግሮት ሲያገባድድ ባለፈዉ ሳምንት ሐሙስ የመጀመሪያዉ የመንግሥት ይፋ መግለጫ ከአዲስ አበባ ተሰማ።

#አቶ በረከት ሥምኦን የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ።የመለስ መንግሥት ሥለ መለስ ጤና ለመናገር የዘገየዉ ሺን እንዳሉት መለስ አስቀድመዉ ሥላላቀዱት ይሆን።አቶ ግርማ እንደሚሉት ደግሞ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሥለ ጠቅላይ ሚንስትሩ ጤና ለመናገር መዘግየት ብቻ ሳይሆን የሰጡት መረጃም የተሳሳተ ነዉ።

ዶክተር አረጋዊ በርሔም ከመዘግየቱ መሳከሩ ይላሉ።

ዶቸ ቬለ እንደማንኛዉም መገናኛ ዘዴ ሁሉ ሥለመለስ ጤንነት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትና ጉዳዩ የሚመለከታቸዉን ሐገራት ሹማምንት ማብራሪያ እንዲሰጡት በተደጋጋሚ፥ በተለያየ መንገድ ጠይቆ ነበር።ከሚንስትር በረከት መግለጫ ካንድ ቀን በፊት ጠቅላይ ሚንስትሩ ይታከሙበታል የሚባለዉ በብራስልስ-ቤልጂግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኢሜይል የሠጠን መለስ ግን ጠቅላይ ሚንስትሩ ሕክምና ላይ ናቸዉ መባሉን «ሐሰትና ስሕተት» ብሎ ነበር።

ዛሬስ-ሐሰት-ስሕተቱ የትና የማን ነዉ? እዉነቱ ግን መለስ ያኔም-ዛሬም መደበኛ ሥራቸዉ ላይ የሉም።ይሕን በርግጥ ሺን እንደሚሉት አቅደዉት ሊሆን አይችልም።የኢትዮጵያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባለፈዉ አርብ ሐምሌ ስድስት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋንና የተቃዋሚዉን የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ከፍተኛ ባለሥልጣንን ጨምሮ ሃያ-አራት ጋዜጠኛና ፖለቲከኞችን በአሸባሪነት ወንጀል-ከሰባት እስከ እድሜ ልክ በሚደርስ እስራት ቀጥቷቸዋል።

የዚያኑ ዕለት ማታ ፖሊስ የአወሊያንና የሌሎች ቢያንስ ሰወስት የአዲስ አበባ መሳጂዶችን እየረመረመ በየመስጊዶ የነበሩ በሺ የሚቆጠሩ ምዕመናን በአስለቃሽ ጢስ እያፈነ፣ በዱላ እየቀጠቀጠ በየዕሥር ቤቱ አጉሯል።ፓሊስ ባለፈዉ ቅዳሜ ደግሞ ቤተ-እምነቶችን ደፍሮ በርካታ ሙስሊሞችን በጢስ ጋዝ አፍኗል፥ ደብድቧል፥ አስሯልም።

ይሕ ሁሉ አስቀድሞ የማቀድ የመሪነት ልምድና ችሎታ ያላቸዉ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ አስቀድሞዉ አቅደዉ አዘዉም ሊሆን ላይሆንም ይችላል።በዚሕ ሁሉ ጊዜ ግን መለስ መደበኛ ሥራቸዉ ላይ አለመኖሯቸዉ እርግጥ ነዉ።

ዶክተር አረጋዊ በርሔ እንደሚሉት ደግሞ መለስ ለኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ለታገሉለት ፓርቲም ሁሉም ናቸዉ።

መለስ የሉም ማለት ለኢትዮጵያ ሁሉም የለም ማለት ይሆን? አቶ ግርማ።

በሥልጣን ላይ ላለዉ ገዢ ፓርቲ ለኢሕአዲግ ግን መለስ ሁሉም ናቸዉ በሚለዉ ሐሳብ አቶ ግርማ ይስማማሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት የመለስን መታተመም በይፋ ካመነ-ካለፈዉ ሐሙስ ወዲሕ አንዳድ የሐገሪቱ ባለሥልጣናት የመለስ አለመኖር የመንግሥትን የዕለት ከዕለት ሥራ አያጉልም ባይ ናቸዉ።የገዢዉ ፓርቲ አሠራር-አወቀቃቀርም በነበረበት ይቀጥላል።ዶክተር አረጋዊ በርሔ ይሕን አይቀበሉትም።

ባለፉት ሃያ-አንድ አመታት ኢትዮጵያን የመሩት ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ለረጅም ጊዜ ከመደበኛ ሥራቸዉ ከተለዩ በሐገሪቱ ፖለቲካዊ ሒደት ላይ የሚያደርሰዉ ተፅዕኖ አይኖርም ማለት ያሳስታል።የኢትዮጵያ ፖለቲካ ማለት የተቃዋሚ ፓርቲዎችም እንቅስቃሴ ማለት ነዉ።

ዶክተር አረጋዊ በርሔ፥በይፋ እንደሚታወቀዉ፥ የሐገሪቱ ሕግ እንደሚያዘዉም የሐገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሐይለ ማርያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚንስትሩን ተክተዉ ይሠራሉ።እስከ መቼ-አይታወቅም።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

Play below

 

የመለስ ዜናዊ የጤና ሁኔታ ውዥንብር

Thursday, July 19th, 2012

በጥሩ የጤና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ማስታወቁን የሃገር ውስጥና የውጭ የዚና ወኪሎች ዘግበዋል ። ስለ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የጤና ሁኔታ ለማጣራት ዶቼቬለ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናትንም ሆነ የቤልጂግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ሃላፊዎችን ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ መታመማቸውና ህክምና ላይ የመሆናቸው ጭምጭምታ መሰማት ከጀመረ ጥቂት ወራት ተቆጥረዋል ። የጤናቸው ሁኔታ አነጋጋሪነት ተጠናክሮ የቀጠለው ግን መለስ ሰኔ መጨረሻ ላይ በኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስበሰባ ላይ ሳያገኙና በኃላም ባለፈው ሳምንት እሁድና ሠኞ በተካሄደው የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ሳይካፈሉ ከቀሩ በኋላ ነው ። ባላፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ደገሞ ብራስልስ ቤልጅየም ውስጥ በሚገኝ ሉክ በተባለ ሆስፒታል ታከሙ የተባሉት አቶ መለስ ሳያርፉ አልቀረም የሚሉ መላምቶችም መሰንዘር ጀምረው ነበር ። እነዚህን የመሳሰሉ የተለያዩ አስተያየቶች ከተለያዩ ምንጮች ሲሰሙ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ስለ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የጤና ሁኔታ ምንም ነገር ሳይባል መታመማቸው በአፍሪቃ ህብረት ጉባኤ ወቅት ነበር በይፋ የተነገረው። በአዲሱ የአፍሪቃ የልማት አጋርነት ወይም ኔፓድ ስበሰባ መክፈቻ ላይ የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት ማክ ሳሊ መለስ በጤና እክል ምክንያት አለመገኘታቸውን ካሳወቁ በኋላ የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ብሉምበርግ ለተባለው የመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ቃለ ምልልስ አቶ መለስ ከባድ ሳይሆን ቀላል ህመም እንዳጋጠማቸው ፣ እንደማንኛውም ስው ህክምና እንደሚያስፈልጋቸውና በቅርቡም እንደሚመለሱ ተናግረዋል ። የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ኤ.ኤፍ.ፒ ትንንት ባሰራጨው ዜና ግን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በጠና ታመው ብራሰልስ ቤልጅየም ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ህክምና እንድተደረገላቸው አንዳንድ ዲፕሎማቶች መናገራቸውን አስታውቋል። በዚሁ ዘገባ የ 57 ዓመቱ የአቶ መለስ የጤና ሁኔታ አስጊ መሆኑ ተጠቁሟል ። ሆኖም የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ አቶ በረከት ስምኦን፦ አቶ መለስ «በጠና አልታመሙም፤ ጤናቸውም በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል» ማለታቸዉን ኤ.ኤፍ.ፒ. በዘገባው ጠቅሷል።

አቶ መለስ ብራሰልስ ውስጥ ህክምና እየተደረገላቸው ስለመሆን አለመሆኑ በብራሰልስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ማብራሪያ እንዲሰጠን ከዶቼቬለ የአማርኛዉ ክፍል ከትናንት በስተያ ላቀረብነዉ ጥያቄ፦- ኤምባሲዉ በኢሜይል በላከልን መልስ፤ አቶ መለስ በህክምና ላይ ናቸው መባሉን «ሃሰትና ስህተት» በማለት ገልፆ ታመሙ የሚለዉን ዜና «የሃሰት ታሪኮችን በማሰራጨት በተጠመዱና በተወሰኑ ወገኖች የተፈጠረ» በማለት አጣጥሎታል። ኤምባሲው ይህን ቢልም የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ግን አቶ መለስ ለተወሰኑ ቀናት ብራሰልስ ከሚገኙት ዋና ዋና ሆስፒታሎች በአንዱ በግል መደበኛ ህክምና እንደተደረገላቸው ብራሰልስ የሚገኙ አንዳንድ ዲፕሎማቶች መናገራቸውን አስታውቋል።

ዶቼቬለ ስለ መለስ የጤና ሁኔታ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት መረጃ ለማግኘት ከዚህ ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ በተደጋጋሚ ያደረገው ሙከራ አልተሳካም ። አቶ መለስ ብራሰልስ መታከም አለመታከማቸውን እንዲያረጋግጥ ዶቼቬለ ለቤልጂግ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ጥያቄ ቢያቀርብም የመስሪያ ቤቱ ምክትል ቃል አቃባይ በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ዓይነት መግለጫ ሆነ ማስተባበያም እንደማይሰጡን ነው በስልክ የነገሩን ። ሆኖም ሪፖርተር ጋዜጣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጪዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ የውጭ ሕክምና ክትትላቸውን ጨርሰው ወደኢትዮጵያ እንደሚመለሱ የምንጮቹን ማንነት ሳይገልፅ ዘግቧል። በዚሁ ዘገባ እንደተጠቆመው መለስ፣ ወደአገራቸው ሲመለሱ ወዲያውኑ ሥራ እንደማይጀምሩና ለተወሰኑ ጊዜያት ካለባቸው ከባድ ኃላፊነት ርቀው ዕረፍት እንዲያደርጉ በሐኪሞቻቸው መመከራቸውን ማንነታቸውን ካልጠቀሳቸው ምንጮች መስማቱን ሪፖርተር አስታውቋል። የሕመማቸውም ምክንያትም የሥራጫና መሆኑ ነው የተመለከተው ።ይህን መረጃ ግን ከመንግሥት ባለሥልጣናት ማረጋገጥ አልቻልንም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕክምናቸውን ሲከታተሉበት የቆዩበት አገር ለደኅንነታቸው ሲባል እንዳይገለጽ ጠይቀዋል ያላቸው ምንጮቹ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት መለስን ያሉበት ድረስ ሄደው እንደጎበኙዋቸውም ዘግቧል። ላለፉት 21 ዓመታት ኢትዮጵያን በፕሬዝዳትነት እንዲሁም በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት አቶ መለስ ዜናዊ 20 ዓመት ሳይሞላቸው ነበር የህክምና ትምህርታቸውን አቋርጠው የደርግ መንግሥትን ለመውጋት የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ግንባር ህወሀትን የተቀላቀሉት። በ1981 ዓም የግንባሩን መሪነት የተረከቡት መለስ ከዓመታት በኋላ ግንባሩ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ተዋህዶ የመሰረተው፣ የአሁኑ ገዥ ፓርቲ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ኢህአዲግ ሊቀመንበርም ናቸው። በተቃዋሚዎችና በሰበዓዊ መብት ተሟጋቾች ሰብዓዊ መብትን በመጣስ የፕሬስ ነፃነትን በመጨቆንና ተቃዋሚዎችን በማዋከብ የሚወገዙት መለስ በደጋፊዎቻቸው ደግሞ ባለራዕይ መሪ ተደረገው ይወደሳሉ። ለጊዜው የመለስ ህመም ምንነትም ሆነ ለምን ያህል ጊዜ ከህዝብ እይታ ተሰውረው እንደሚቆዩ ግልፅ አይደለም። በአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ እርሳቸውን ተክተው የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ናቸው። አቶ ኃይለ ማርያም እስከ መቼ የእሳቸውን ቦታ ሸፍነው እንደሚሰሩም በግልፅ የታወቀ ነገር የለም።

Play below

 

የዋልድባ ገዳም ህልውና ያሳሰባቸው ኢትዮጵያውያን በጀርመን ሰልፍ አደረጉ

Thursday, July 19th, 2012

ካለፈዉ መጋቢት ወር አንስቶ ለስኳር ልማት ፕሮጀክት ሲባል ጥንታዊዉ የዋልድባ ገዳምን ይዞታ ይነካል በሚል የተለያዩ ወገኖች ስጋታቸዉን ሲገልፁ ተደምጠዋል። ፕሮጀክቱን የሚመራዉ የመንግስት አካል በበኩሉ የተጠቀሰዉ ፕሮጀክት የገዳሙን ዋነኛ ክፍል እንደማይነካ ነዉ የተናገሩት። ሰሞኑን  ደግሞ ይህ ፕሮጀክት የገዳሙን አካል ይነካል የሚል ስጋታቸዉን ለመገናኛ ብዙሃን ካስደመጡ  የገዳሙ መነኮሳት አንዱ ለእስር መዳረጋቸዉ፤ ገዳሙም ዉስጥ ወታደሮች መገኘታቸዉ ይነገራል። ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ከፍተኛ አካል ስጋታችንን ብንገልፅም ምላሽ አላገኘንም የሚሉት በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አባቶች እና ምዕመናን ዛሬ ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ ፍራንክፈርት ከተማ ላይ ሰልፍ አካሂደዋል። ዘገባውን ያዳምጡ

የሶሪያ መከላከያ ሚኒስትር ተገደሉ

Wednesday, July 18th, 2012

ሶሪያ መዲና ደማስቆ ውስጥ ዛሬ በአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት የሶሪያ መከላከያ ሚኒስትርና ና የሶሪያው ፕሬዝዳንት አማች ተገደሉ። በመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ዘገባ መሰረት ደማስቆ በሚገኘው የብሔራዊ ፀጥታ ምክር ቤት ስብሰባ በማካሄድ ላይ ሳሉ በደረሰው በዚሁ አደጋ የሶሪያ የመከላከያ ሚኒስትር ጀነራል ዳውድ ራጃ ና የፕሬዝዳንቱ አማች አሴፍ ሻውካት ተገድለዋል ። በቦብም ጥቃቱ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሃመድ አል ሻር ና የብሔራዊ ፀጥታ መስሪያ ቤት ሃላፊ ጀነራል ሂሻም ኢክቲያር ከቆሰሉት መካከል ይገኙበታል ። ከአደጋው በኋላ የሶሪያ መንግሥት ባወጣው መግለጫ አሸባሪነትን መዋጋቱን እንደሚቀጥል አስታወቋል ። በዛሬው አደጋ የተገደሉት ጀነራል ራጃ ከ,መከላከያ ሚኒስትር ሥልጣናቸው በተጨማሪ የጦር ኃይሎች ምክትል አዛዥ እንዲሁም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊቀመንበርም ነበሩ።

ሻውካት ደግሞ ምክትል መከላከያ ሚኒስትርና የቀድሞ የስለላ መስሪያ ቤት ሃላፊ ነበሩ ። የሶሪያ አማፅያን ትግሉ ከሶሪያ ክፍለ ግዛቶች ወደ መዲናይቱ ደማስቆ መሸጋገሩን ትናንት አስታውቀው ነበር , ይህ በእንዲህ እንዳለ የሶሪያውን የርስ በርስ ግጭት ለማስቆም የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሃፊ ባን ኪሙን ዲፕሎማሲያዊ ጥረታቸውን ቀጥለዋል ። ባን ኪሙን ዛሪ ከቻይና መንግሥት መሪዎች ጋር በጉዳዮ ላይ ለመምከር ቻይና ነበሩ ። ባን እንዳሉት ቻይና ግጭቱን በማስቆም ረገድ ወሳኝ ድርሻ አላት።

«ቻይና በጣም ጠቃሚ ሚና ልትጫወት ትችላለች ። እዚህ ከተገኘሁበት ምክንያት አንዱ ይህ ነው ። ይህን ጉዳይ ከቻይና መንግሥት መሪዎች ከቻይና ፕሬዝዳንት ከሁጅንታው ና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዩንግ ዴችና እንዲሁም ከሌሎችም ባለሥልጣናት ጋር እመክርበታለሁ ። የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት አንዳንድ እርምጃዎችን ወስዷል ። ሆኖም የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በከፍተኛ ደረጃ እንዲተባበር ይጠበቃል ። ምክር ቤቱ ደም መፋሰሱ እንዲቆም ወሳኝ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል»

የመለስ ዜናዊ ጤንነት ጉዳይ (ጀርመን ራዲዮ)

Tuesday, July 17th, 2012

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ታመው ቤልጅየም መዲና ብራስልስ በሚገኝ ሴይንት ሉክ በተባለ ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑን በኢንተርኔት የተለያዩ ምንጮች ዘግበዋል። ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ካለፉት ጥቂት ቀናት ወዲህ በአዲስ አበባ በይፋ አለመታየታቸው፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይትም ሆነ ትናንት በተጠናቀቀው የአፍሪቃ ህብረት ጉባዔ ላይ አለመገኘታቸው ብዙ እያነጋገረ ነው። ስለዚሁ ጉዳይ በአዲስ አበባ የሚመለከታቸውን የመንግሥት ባለሥልጣናት ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካልንም፤ በብራስልስ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስተያየት ለማግኘት በኢሜይል ብንጠይቅም ዜናው ውሸት እና የተሳሳተ ነው በሚል ያቀረብነውን ጥያቄ ሳይቀበለው ቀርቷል። በመሆኑም፡ ብራስልስ የሚገኘው ወኪላችን ገበያው ንጉሤን ጠቅላይ ሚንስትር መለስ በዚያ ሕክምና እያደረጉ ነው ስለመባሉ በበኩሉ የሰማው እንዳለ ጠይቄው ቀጣዩን መልስ ሰጥቶኛል። … [ያዳምጡ]

Play below

 

በሱዳን ጸረ-አልበሽር ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው

Tuesday, July 17th, 2012

ከአንድ ዓመት በፊት፤ በሰሜን አፍሪቃ የለውጥ እንቅሥቃሴ ከመቀጣጠሉ በፊት፤ በ 1964 እና በ1985 ዓ ም፤ ሱዳናውያን፤ «ወታደራዊ አገዛዞችን ያፈናቀለ፣ አኩሪ የህዝብ የተቃውሞ ታሪክ አለን!» በማለት ይኩራራሉ። በተጠቀሱት ዓመታት ፣ በተከሠቱ፣ የአገዛዝ ለውጦችም ፣ ተማሪዎች ወሳኝ ሚና መጫወታቸው ነው የሚነገርላቸው። በሱዳን ፤ በተለይም በመዲናይቱ በካርቱም፣ ሰኔ 9 ቀን 2004 ፣ በመባልእት ዋጋ መናር፣ በአጠቃላይ በኑሮ ውድነት ሳቢያ የተጀመረው የተቃውሞ ሰልፍ ፣ ሳይቋረጥ የቀጠለ ሲሆን፣የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችም ብርቱ የኃይል እርምጃ ከመውሰድ እንዳልተቆጠቡ መገናኛ ብዙኀን አትተዋል። ባለፈው ዓርብ ፤ የካርቱም ዩንቨርስቲ ባለሥልጣናት አንድ ሳምንት ቀደም አድርገው ፣ በአመዛኙ ትምህርት የመስጠት ተግባራቸውን ያቋረጡ ሲሆን፤ አንድ የዩንቨርስቲው የዜና ምንጭ አንዳስታወቀው፤ ተማሪዎቹ፣ የፊታችን ዓርብ ከሚጀመረው የረማደን የአንድ ወር ጾም ማብቂያ በኋላ፣ ለፈተና ተዘጋጅተው እንዲመለሱ ነው የተነገራቸው። አንድ ወር በሆነው ተቃውሞ፣ የዩንቨርስቲ ተማሪዎችም በትጋት መሳተፋቸው ነው የሚነገርላቸው። ባለሥልጣናቱ ምናልባት ከዚህ ውሳኔ የደረሱት፤ ተቃውሞው ከተጀመረበት ጊዜ ወዲህ ፤ ባለፈው ረቡዕ የታየውን የመሰለ እጅግ ብርቱ ተቃውሞ፣ ዩንቨርስቲው አጋጥሞት እንደማያውቅ በመገንዘቡ ሳይሆን እንዳልቀረ ተመልክቷል። ተቃውሞውን ለመበተን ፖሊስ የሚያስለቅስ ጋዝ ነበረ የረጨው። ዛሬ አንድ ወር በሆነው ተከታታይ የተቃውሞ ሰልፍ፤ ተቃዋሚዎች ያሰሙት የነበረው መፈክር በሰሜን አፍሪቃ በተቀጣጠለው የህዝብ መነሳሳት፤ ወጣቶች ያስተጋቡት የነበረውን ጥሪ የሚያስታውስ መሆኑን AFP ዘግቧል። ሌላው ተማሪዎቹን ያናደዳቸው ጉዳይ በዛ ያሉ ባልደረቦቻቸው ተይዘው መታሠራቸውና ፣ የትምህርት ጊዜአቸው የሚተጓጎልባቸው መሆኑ ነው።

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት፤ ተቃውሞው ይበልጥ እየተጠናከረ ይስተጋባ የነበረው ዓርብ – ዓርብ በየመሥጊዱ ከሚደረግ ጸሎትና ሥግደት በኋላ ነበር። በዚህ ላይ በተለይ በካርቱም መንትያ ከተማ በዖምዱርማን፣ ለተቃውሞው የዑማ ፓርቲ ደጋፊዎች ግንባር ቀደም ሆነው ነው የተገኙት። ተቃውሞው ፤እስከምን ድረስ ጠንካራ የሚባል ነው? የሱዳን መንግሥት ከፈተኛ ባለሥልጣናትንስ እስከምን ድረስ ነው ያሳሰበው?

የዶይቼ ቨለ የእንግሊዝኛው ክፍል ባልደረባ አይሳክ ሙጋቢ ያነጋገራቸው፤ የስምጥ ሸለቆው ተቋም የተሰኘው የምርምር ማዕከል አባል ማግዲ ኧል ጊዙሊ፣ እንዲህ ይላሉ።

«ተቃውሞው የቱን ያህል የከረረ እንደነበረ፤ በራሳቸው በፕሬዚዳንቱ ምላሽ መገንዘብ ይቻላል። እርሳቸውም መጠን ባለፈ ስሜትና አገላለጽ ነበረ የተቃውሞውን ሰልፍ የተቹት።

ሌሎች የገዥው NCP(ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ ) ባለሥልጣናትም በተመሳሳይ ቋንቋ ነው የተቹት። ሁኔታው ያሳሰባቸው ነው የሚመስሉት። ምንም እንኳ የተቃውሞው ሰልፍ ከሞላ ጎደል ጥቂት ሰዎችን ያሰባሰበ ቢሆንም፣ ቀጣይነት ያለው መሆኑን አሳይቷል። ተማሪዎቹም ከሞላ ጎደል በየዕለቱ ከካርቱም ዩንቨርስቲ ቅጽር ግቢ ውጭ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ከመጣር አልቦዘኑም። መንግሥት ፤ ከዚህ ቀደም ዐይቶት በማያውቀው ሁኔታ ነው በጽናት በመቃወም ላይ ያሉት። እ ጎ አ ከ 1995 ዓ/ም ወዲህ፣ መንግሥት አጋጥሞት የማያውቀውን ፤ የአገሪቱን እምብርት ፤ መዲናይቱን ካርቱምን ያናወጠ ብርቱ ተቃውሞ ነው ያሳዩት።»

ዓማር አልበሺር ፣ ተቃውሞውን አስመልክተው የሚናገሩት ድንጋጤን ለመሸፈን ጥረት የተደረገበት፤ አሁንም ተወዳጅ መሪ መሆናቸውን የሚዘበዝብ ነው። እውን ተወዳጅ ናቸው? መግዲ ኧል ጊዙሊ –

«እሁንም፤ የአንድ አካባቢ ተመራጭ ናቸው። ይህ እርግጥ ነው፤ ግን አገሪቱ ተከፋፍላለች። በአርሳቸው ላይ እየሰፋ የመጣ ተቃውሞ አለ። ይህ ተቃውሞ፣ እምነት ጥለውባቸው በነበሩ በአንዳንድ አካባቢዎች ጭምር ነው የተከሠተው። አዎ ፣ በተለይ በመዲናይቱ ተቀባይነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ነው የመጣው። በይበልጥ በወጣቱ ትውልድ!»

በገዥው NCP ፓርቲ መካከል ያለው መከፋፈል፣ እስከምን ድረስ ኦማር ሐሰን ኧል በሺርን በሥልጣናቸው ተደላድለው ሱዳንን እንዳይገዙ ሳንክ ይሆናል? መግዲ ኧል ጋዙሊ ተጨማሪ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር እርሳቸውም እንዲህ መልሰዋል።

«እርግጥ መንግሥት፤ ከማንኛውም በላይ በ NCP ውስጣዊ ክፍፍል ነው ተግሮቱ የሚያይልበት። ሁለት ጎራዎች አሉ። ህገ-መንግሥቱ በተሃድሶ እንዲሻሻል የሚጠይቁ ፣ የሚሹ ፣ አሉ። ይህም ሲሆን በተቃውሞው ጎራ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ወደራስ በማምጣት ከሞላ ጎደል በጎዳናዎች ያለውን የተቃውሞ ቁጣ ማብረድ ይቻላል የሚሉ ወገኖች አሉ።

እንደሚመስለኝ ይኸኛው ስልት ውድቅ የሚሆን ነው፤ ምክንያቱም፣ የተቃውሞ ሰልፈኞቹ፤ አሁን ጎዳና ላይ ናቸው። ለፖለቲካ ፓርቲዎች ስሞታ አሁን ጊዜ ያላቸው አይመስልም። እነዚህ ፓርቲዎች፤ ከ NCP ጋር በሰፊው ለመጣመር ቢፈልጉም እንኳ የሚሠምር አይመስልኝም። እቅዱ የሚሠራ አይደለም። ሌላቅ ምላሽ፤ እርግጥ አየል ያለ ፣ በኃይል የማረቅ እርምጃ ነው የሚሆነው! ይህን ደግሞ፣ ራሳቸው ፕሬዚዳንቱ የሚደግፉት ነው የሚመስለው።»

Play below

 

የታደሰ እንግዳው ኅልፈትና ዶይቸ ቨለ

Monday, July 16th, 2012

Tadesse Engidawጤናይስጥልኝ እንደምን አምሽታችኋል ? ዛሬ ጋዜጠኛ ታደሰ እንግዳው ፣ አዲስ ዘገባ ሊያቀርብልን በዝግጅት ላይ ነበረ ፣ ግን አልሆነም! እጅግ ያሳዝናል! ከዚህ በኋላ ድምፁ በራዲዮ ሊሰማ አይቻልም ። ወጣቱ፤ ጎልማሳው ጋዜጠኛ ታደሰ እንግዳው፤ ትናንት እሁድ፣ ከአዋሳ ወደ አዲስ አበባ ከ 2 ወንድሞቹ ጋር በመመለስ ላይ ሳለ፤ ከዜና ምንጮቻችን እንዳረጋገጥነው፣ ባጋጠመ የመኪና አደጋ ሳቢያ ፤ እርሱና፤ አንደኛው ወንድሙ ህይወታቸው አልፏል። በዚህ ዘግናኝ ህልፈተ ህይወት፣ ቤተሰብ ፤ ቤተዘመድ ፤ ጓደኞች ፣ እኛም የሥራ ባልደረቦቹ እጅግ አዝነናል። ስለሆነም የዛሬውን ሥርጭታችንን፣ ከሞላ ጎደል በአጠቃላይ፤ ለእርሱ መታሰቢያ እንዲሆን አድረገናል። በዚህ በራዲዮ ጣቢያው ማዕከል ከሚገኙ 6 ባልደረቦቹ ጋር የተካሄደው ልዩ ውይይት ፤ ቀጥሎ ይቀርባል።

የወያኔ ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነአንዱአለም ላይ ያሳለፈው ብይን

Friday, July 13th, 2012

(DW) — የኢትዮጵያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአሸባሪነት የተከሰሱትን ሃያ-አራት ጋዜጠኞችና ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን ከሰባት ዓመት እስከ እድሜ ልክ በሚደርስ እስራት ቀጣ።ዛሬ አዲስ አበባ ያስቻለዉ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተቃዋሚዉን የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ (አንድነት ባጭሩ) ከፍተኛ ባለሥልጣን አንዱ ዓለም አራጌን የእድሜ ልክ እስራት በይኖባቸዋል።ጋዜጠኛና ፀሀፊ እስክንድር ነጋ ደግሞ በአስራ-ስምንት ዓመት እስራት ተቀጥቷል።ሌሎቹ ተከሳሶች ከሰባት ዓመት እስከ እድሜ ልክ የሚደርስ የእስራት ቅጣት ተበይኖባቸዋል።የፍርድ ቤቱን ዉሳኔ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚዎችና የተለያዩ ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች አጥብቀዉ አዉግዘዉታል።

ተቃዋሚዉ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓሪቲ ቃል አቀባይ ዶክተር ሐይሉ አርአያ ፍርድ ቤቱን «አሸባሪ» ሲሉት፥ የፓርቲዉ አባልና ብቸኛዉ ተቃዋሚ የምክር ቤት አባል አቶ ግርማ ሠይፉ ደግሞ የተፈረደባቸዉ ሰዎች ያጠፉት ነገር የለም ብለዋል።

ከዉጪ ሲፒ ጄ በሚል ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት የኢትዮጵያ መንግሥት «አሸባሪነትን መዋጋትን ሰላማዊ ድምፆችን ለማፈን እየተጠቀመበት ነዉ» በማለት አዉግዞታል።የዓለም አቀፉ የሠብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የሑዩማን ራትስ ዋች የአፍሪቃ ጉዳይ አጥኚ ቤን ሮዉሌንስ በበኩላቸዉ ፍርዱን «አናዳጅ» ብለዉታል።

«አልገረመኝም።ምክንያቱም ከኢትዮጵያ ፍርድ ቤት እንዲሕ አይነት ዉጤት እንጠብቅ ነበርና። ይሁንና በርግጥ በጣም አዝኛለሁ።ምክንያቱም ፍርሐትሕ ሲረጋገጥ ሁሌም አሳዛኝ ነዉና።በተጨማሪም በጣም ተናድጃለሁ።ምክንያቱም የኢትዮጵያን የሠብአዊ መብት ይዞታ እንደሚከታተሉት እንደሌሎች ብዙ ሰዎች ሁሉ፥ይሕ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ ዉስጥ ያየነዉ፥ ሥርዓቱ የሚፈፅመዉ እመቃና የትኛዉንም አይነት የመናገር ነፃነት አለመታገሱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰ ለመምጣቱ የመጨረሻዉ ማረጋገጪያ በመሆኑ።እና ለኢትዮጵያ የፕረስ ነፃነትና ለመናገር ነፃነት አሳዛኝ ቀን ነዉ።»

ፍርድ ቤቱ ዛሬ እስራት ከፈረደባቸዉ ሃያ-አራት ተከሳሾች አስራ-ስድስቱ ሐገር ዉስጥ የሉም። ፖለቲከኛ አንዱ ዓለም አራጌና ጋዜጠኛ እስክድር ነጋን ጨምሮ ሌሎቹ ተከሳሾች ግን ካለፈዉ መስከረም ጀምሮ እስር ቤት ናቸዉ።የኢትዮጵያ መንግሥት አዲስ ባፀደቀዉ የፀረ-ሽብር ሕግ ጋዜጠኞች ሲፈረድባቸዉ በሰባት ወራት ዉስጥ የዛሬዉ ሰወስተኛዉ ነዉ። ያዳምጡ

ሠላማዊ ሠልፍና ግጭት በደቡብ ኢትዮጵያ

Tuesday, June 26th, 2012

የሲዳማ አርነት ንቅናቄ እንዳስታወቀዉ የሕዝቡ ጥያቄ ሠላማዊና የሕገ-መንግሥቱን ድንጋጌዎች የጠበቀ ነዉ።በሌላ በኩል የደቡብ ኢትዮጵያ መስተዳድርን ከኦሮሚያ መስተዳድር ጋር በሚያዋስኑ አካባቢዎች በተከሰተ ግጭት ሰዎች መሞት፥ መቁሰላቸዉ ተነግሯል።

ደቡብ ኢትዮጵያ የሚኖረዉ የሲዳማ ብሔረሰብ እራሱን የቻለ መስተዳድር እንዲሰጠዉ ሰሞኑን በተከታታይ ባደረገዉ ሠላማዊ ሠልፍ ጠየቀ።በደቡብ ኢትዮጵያ ርዕሠ-ከተማ በአዋሳና በአካባቢዉ ከተሞች አደባባይ የወጣዉን ሕዝብ ለመቆጣጠር መንግሥት በርካታ ፀጥታ አስከባሪዎች አስፍሯል።የሲዳማ አርነት ንቅናቄ እንዳስታወቀዉ የሕዝቡ ጥያቄ ሠላማዊና የሕገ-መንግሥቱን ድንጋጌዎች የጠበቀ ነዉ።በሌላ በኩል የደቡብ ኢትዮጵያ መስተዳድርን ከኦሮሚያ መስተዳድር ጋር በሚያዋስኑ አካባቢዎች በተከሰተ ግጭት ሰዎች መሞት፥ መቁሰላቸዉ ተነግሯል።ወኪላችን ታደሰ እንግዳዉ ከአዲስ አበባ ሁኔታዉን ተከታትሎታል። ያዳምጡ

Play below

 

ምስራቅ ኢትዮጵያና የHuman Rights Watch ዘገባ

Thursday, May 31st, 2012

ዓለም ዓቀፉ የሰብዓ መብቶች ተሟጋች ሂዉማን ራይትስ ዎች በምስራቃዊ የኢትዮጵያ ግዛት ሶማሌ ክልል ዉስጥ ልዩ የፖሊስ ኃይል ቢያንስ የአስር ሰዎች ህይወት የጠፋበት ጥቃት መሰንዘሩን አመለከተ። ድርጅቱ ይፋ ባደረገዉ ዘገባም በተጠቀሰዉ አካባቢ ባለፈዉ መጋቢት ወር በተለያዩ መንደሮች የሚገኙ ኗሪዎች በተጠቀሰዉ የፖሊስ ኃይል ታፍነዉ የተወሰዱ፤ ስቃይ የተፈፀመባቸዉ እንዲሁም ንብረት የተዘረፉ መኖራቸዉን ጠቅሰዉ አቤቱታ ማሰማታቸዉን ዘርዝሯል።

«ክስተቱን መርምረናል፤ ጋሻሞ ከሚባለዉ አካባቢ የሸሹ ሰዎችንም ጠይቀናል፤ ስለሁኔታዉ አንዳንድ የአካባቢዉን አዛዉንትም ጠይቀን አጣርተናል፤ ይህ ጉዳይ በማኅበረሰቡ ዘንድ የታወቀ ጉዳይ ነዉ፤ በዩቲውብም ምስሉን የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ የሚል እምነት አለኝ።»

ቤን ሮዉለንስ በሎንዶን የሂዉማን ራይትስ ዎች የፍቃ ዘርፍ ከፍተኛ ተመራማሪ በምስራቅ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ዉስጥ ልዩ ፖሊስ ፈፀመ ሲል ድርጅታቸዉ ስላቸወጣዉ መግለጫ ምንጭ የገለፁት ነዉ። ሮዉለንስ ቀጠሉ፤

«በአካባቢዉ አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር፤ ልዩ ፖሊስ አንድን ግለሰብ ያዋክብ ነበር፤ የአካባቢዉ ኗሪዎች ድርጊቱን እንዲያቆሙ ለማድረግ ሲሞክሩ ሰዉየዉን ገደሉት፤ ከዚያም ራግዳ አካባቢን ለቀዉ ሄዱ፤ ከዚያም ኗሪዎቹ መሣሪያ ይዘዉ ተከታተሏቸዉና ከመካከላቸዉ ጥቂቱን ገደሉ። በሚቀጥለዉ ቀን ፖሊስ አዳዳ እና ራግዳ ከተሞች ላይ ጥቃት ሰነዘረ። በየቤቱ እየተገቡ ተጠያቂዎችን በመፈለግ የተሰኑ ሰዎች ወሰዱ። ቢያንስ 25 አስረዋል፤ አስር ያልታጠቁ ሰዎች በእስር ላይ ሳሉ ገደሉ።»

እሳቸዉ እንደሚሉት በልዩ ፖሊስ እና በአካባቢዉ ኗሪዎች መካከል በተካሄደዉ ግጭት ሌሎች ከአስር በላይ የሚሆኑ ሰዎችም ህይወት ጠፍቷል። ሂውመን ራይትስ ዎች ይህን ጉዳይ በመከታተል የመዘገበ መሆኑን በመግለፅም የጉዳዩ አሳሳቢነት ከዚህ ይነሳል ይላሉ፤

«ይህ አሳሳቢ የሚሆነትበት ምክንያት፤ ልዩ ፖሊስ ከ1999ዓ,ም ጀምሮ በአካባቢዉ ይገኛል። ነገር ግን የሚፈፅሙትን ጥቃት ለማረጋገጥ እጅግ አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል። ምክንያቱም ወደኦጋዴን ለመግባት አይፈቀድም። እናም ይህ ልዩ ፖሊስ የሚፈፅመዉን የሚያሳይ አንድ መረጃ በተቀረዉ የአካባቢዉ ግዛቶች ሊኖራቸዉ የሚችለዉን ባህሪ በመጠቆሙ ስጋቱን ከፍ ያደርገዋል። ይህ ማለት ወደዚያ መግባት ሊፈቀድ ይገባል፤ የኢትዮጵያ መንግስትም ልዩ ፖሊስ የሚፈፅመዉን ማዋከብ ተመልክቶ ተጠያቂ ሊያደርገዉ ይገባል።»

ቤን ሮዉለንስ እንደሚሉት ሂዉማን ራይትስ ዎች ባደረገዉ ጥናት በተጠቀሰዉ አካባቢ የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃነት ግንባር እንቅስቃሴ በመንግስት ተገትቷል። ወትሮ የዚህ ግንባር አባል የነበሩ ወጣቶችም በልዩ ፖሊስነት ሳይካተቱ አልቀሩም።

«ኗሪዎች እንደሚሉት ኦብነግ በአካባቢዉ የለም። ኦብነግን በመበታተን ስኬት ሳይኖር የቀረ አይመስለኝም፤ አንዳንድ ወጣቶች በልዩ ፖሊስነት ሲመለመሉ አንዳንድ የቀድሞ የኦብነግ አባላትም ወደዚያዉ ሳይካተቱ አልቀሩም።»

እሳቸዉ አሁን በዚህ አካባቢ ሳይኖር አይቀርም ያሉት የጎሳዎች ቁርቁስ ቢሆንም የተጠቀሰዉ ልዩ ፖሊስ እዚያ መገኘቱ ኗሪዎችን ከማዋከብ የዘለለ ሚና የለዉም ባይናቸዉ። ሂዉማን ራይትስ ዎች ይህን ስጋቱን ያካተተዉን ዘገባ ለኢትዮጵያ መንግስም ሆነ ለሚመለከታቸዉ አካላት አቅርቦ ይሆን? ያገኘዉስ ምላሽ፤ ቤን ሮዉለንስ፤

«አዎ አቅርበናል፤ ከሶማሌ ክልላዊ መንግስት ባለስጣናት ጋ ለመነጋገር ሞክረናል፤ የፌደራል መንግስቱን ባለስልጣናትም ለማግኘት ሞክረናል ያገኘነዉ ምላሽ ግን የለም።» ያዳምጡ

የሃይሌ ገ/ሥላሴ የለንደን ኦሎምፒክ ምዕራፍ ተዘጋ

Tuesday, May 29th, 2012

ሃይሌ ገ/ሥላሴ በመጨው የለንደን ኦሎምፒክ ጨዋታ ለመሳተፍ የነበረው ተሥፋ ትናንት በኔዘርላንድ-ሄንገሎ ማጣሪያ ውድድር ፍሬ ሳይሰጥ ቀርቷል። ቀደም ሲል በማራቶን ለተሳትፎ ለመብቃት ያደረገው ጥረት ያልተሳካለት ሃይሌ በትናንቱ የአሥር ሺህ ሜትር ሩጫ በሰባተኝነት ተወስኖ ነው የቀረው። እርግጥ ሃይሌ ያሰበው አይሁንለት እንጂ የፈጀው ጊዜ አንድ ከ 36 ዓመት ዕድሜ በላይ የሆነ አትሌት እስካሁን ካስመዘገበው ሁሉ የፈጠነ ነበር። ይህም ክብረ-ወሰን ጥቂትም ቢሆን የክብረ-ወሰኑን ንጉስ ሊያጽናና ይገባል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሺን ይህን ታላቅ የስፖርት ሰው የውድድር ተሳትፎው ቢቀር እንኳ በይፋ ወኪልነት ወደ ለንደኑ ኦሎምፒክ ቢልከው በጣሙን የሚገባው ነው። በዓለምአቀፉ የስፖርት መድረክ በተጎናጸፋቸው በርካታ ድሎቹ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲነሣ ሲያስደርግ በበጎ አምባሳደርነት አገሩን በመወከል ያደረገው ታላቅ አስተዋጽኦው ጨርሶ መረሳት የሌለበት ነገር ነው።

ወደ ትናንቱ ውድድር መለስ እንበልና በሩጫው ታሪኩ በቀለ፣ ሊሊሣ ደሲሣና ስለሺ ስሂኔ ከአንድ እስከ ሶሥት በመከታተል ቀደምቱ ሲሆኑ በተለይም አሸናፊው ታሪኩ ደስታውን በታላቅ ስሜት ነበር የገለጸው።

በለንደኑ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን ወክለው የሚወዳደሩት ስፖርተኞች እስከ ሰኔ 30 ቀን በሙሉ የሚመረጡ ሲሆን በተለይም ወጣቶቹ አትሌቶች ለነሃይሌ ጥሩ ተተኪ እንደሚሆኑ ተሥፋ እናደርጋለን። የሄንገሎውን ሩጫ በአካባቢው ሃገራት የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውንም በቅርብ ሲከታተሉ በሃይሌ መሸነፍ ቢያዝኑም ድሉ የኢትዮጵያውን በመሆኑ መካሳቸውን ነው በደስታ የገለጹት።

ሩጫውን በተመለከተ ውድድሩን በስፍራው ተገኝታ የተከታተለችውን ወኪላችንን ሃይማኖት ጥሩነህን ዛሬ በስልክ አነጋግሬ ነበር።

በተቀረ ትናንት ራባት ላይ ተካሂዶ በነበረ ዓለምአቀፍ ውድድርም የኢትዮጵያ አትሌቶች አንዳንድ ጥሩ ውጤቶች ማስመዝገቡ ሆኖላቸው ነበር። የዘንድሮው የኢስታምቡል የአዳራሽ ውስጥ የዓለም ሻምፒዮና የ 800 ሜትር አሸናፊ መሐመድ አማን በሞሮኮም ድሉን ደግሞታል። በ 3 ሺህ ሜትር መሰናክል በወንዶች ጋሪ ሮባ ሲያሸንፍ በሴቶችም ሕይወት አያሌው ቀደምቷ ሆናለች። ዘገባውን ያዳምጡ

የተበላሹ ምግቦችና መድሃኒቶች በኢትዮጵያ

Thursday, May 10th, 2012

ኢትዮጵያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ነዎት? ለመመኘቱ አያድርስብዎት እንበል። ግን ያዉ ሰዉ ነዎትና ታመሙ እንበል። ሐኪምዎ የሰጠዎትን የመድሐኒት ማዘዢያ ይዘዉ መድሐት መደብር ሲሄዱ፥ አንድ አስተያየት ሰጪ እንደነገሩን፥ አስተናጋጅዎ የየትኛዉን ሐገር ይፈለጋሉ? የጀርመን፥ የሕንድ፣ የቻይና… እያለ ይጠቅዎታል። ለነገሩ መድሐኒት መደብር መሔድም አያስፈልግዎ — ካንዱ ሱቅ በደረቴ ኪንን መሸመትም ይችላሉ። ኪኒኑ አዳኝዎ – ይሁን ገዳይዎ የሚያዉቁት ግን ከወሰዱት በሕዋላ ነዉ። ቀደም ሲል ቅቤ ፈልጎ ልቁጥ ሙዝ ፥ በርበሬ አገኘሁ ብሎ የተፈጨ ሸክላ ገዛሁ ባይ ምሬት ነበር የሚሰማዉ። አሁን ደግሞ የድሬዳዋዉ ወኪላችን ዩሐንስ ገብረ እግዚአብሔር እንደዘገበዉ፥ የአገልግሎት ጊዜዉ ያለፈበት፥ ወይም ጊዜዉ የተሰረዘ፥ በጥንቃቄ ያልተያዘ፥ ምግብና መድሐኒት በየመደብሩ፥ በየጎዳናዉ ይቸበቸባል አሉ። ያዳምጡ

Play below

 

ወጣት እናቶችና የኑሮ ውድነት በኢትዮጵያ

Saturday, May 5th, 2012

የዛሬው የወጣቶች ዓለም መሰናዶ ርዕስ «ልጆቻቸውን ለብቻቸው የሚያሳድጉ ወጣት እናቶች እና የኑሮ ውድነት በኢትዮጵያ» የሚል ነው። ከአዲስ አበባ እና ከኢልባቡር ሁለት ወጣት እናቶችን አነጋግረናል። የስራ ውሎው፣ ልጅ የማሳደጉ፣ የኑሮ ውድነቱ እና የማኅበራዊ ህይወት መስተጋብሩ በወጣቶቹ ዘንድ ምን ይመስላል? ከራሳቸው ከወጣቶቹ አንደበት እንሰማለን።

ልጆቻቸውን በተለያየ ምክንያት ለብቻቸው የሚያሳድጉ እናቶች ቁጥር በኢትዮጵያ በውል ባይታወቅም በርካታ እንደሆኑ ግን ብዙዎች ይገመታሉ። በተለይ እናቶቹ ወጣት በሚሆኑበት ጊዜ የሚያጋጥማቸው ፈተና እና የኑሮ ውጣ ውረድ እንዲህ በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም። የሃያ ስድስት ዓመቷ ወጣት ነፃነት ታከለ ነዋሪነቷ በአዲስ አበባ ከተማ ነው። በቅርቡ አራት ዓመት የሚሞላት ልጇን ለብቻዋ ማሳደግ የጀመረችው የሃያ ሶስት ዓመት ወጣት ሳለች አንስቶ ነው።

የሃያ አራት ዓመት ወጣቷ ትዕግስት ወንድሙ ደግሞ በሙያዋ መምህርት ናት። ኢልባቡር መቱ በሚገኝ የገጠር ትምህርት ቤት ውስጥ ነው የምታስተምረው። የአንድ ልጅ እናት ስትሆን በስራ ምክንያት ከባለቤቷ ርቃ መኖር ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል። በወጣትነት ለብቻ ልጅ የማሳደጉን ከባድ ፈተና እንደምንም እየተወጣችው እንደሆነ ነው የምትገልፀው።

በእርግጥ የኑሮ ውድነቱ ተፅዕኖውን ያሳረፈው ልጆቻቸውን ለብቻቸው በሚያሳድጉ ወጣት እናቶች ላይ ብቻ ሳይሆን፤ በአብዛኛው ኅብረተሰብም እንደሆነ እየተገለፀ ነው። በተለይ በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ የመጣው የዋጋ ግሽበት ያስከተለው የኑሮ ውድነት በርካቶችን ለችግር መዳረጉ ይታወቃል። ወጣቷ መምህርት ትዕግስት ወንድሙ፥

ጉዳዩ የሚመለከተው መስሪያ ቤት ባወጣው ዘገባ የዋጋ ግሽበቱ 32.5 በመቶ እንደሆነ ገልጿል። ይህ መረጃ እንግዲህ ከመንግስት በኩል የተገኘ ሲሆን፤ አንዳንዶች ግሽበቱ ከዚያም በላይ እንደሆነ ነው የሚጠቁሙት። እንደ ገለፃው የምግብ ዋጋ ብቻውን በኢትዮጵያ የዘንድሮው ከዓምናው የመጋቢት ወር ጋር ሲነፃፀር በ40.9 ያህል ማሻቀቡ ይታወቃል። ተፅዕኖው እንደ አብዛኛው ኅብረተሰብ ወጣት ነፃነትን የሚመለከት ይሆን?

የኑሮ ውድነት ኢትዮጵያ ውስጥ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያሳደረውን ተፅዕኖ ለአብነት ያህል ለማሳየት አዲስ አበባ እና ኢልባቡር የሚኖሩ ሁለት ወጣቶችን ያቀረብንበት ዝግጅት ነበር። «ልጆቻቸውን ለብቻቸው የሚያሳድጉ ወጣት እናቶች እና የኑሮ ውድነት በኢትዮጵያ» በሚል ያጠናቀርነው ዝግጅት በዚህ ይጠናቀቃል።

Play below

 

ወያኔ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን አስጠነቀቀ

Friday, May 4th, 2012

የመለስ ዜናዊ መንግሥት በሃይማኖት ሽፋን ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓትን በኃይል ለመናድ የእየተንቀሳቀሱ ነው ያላቸውን ወገኖች ትናንት ማታ በሰጠው መግለጫ ላይ በጥብቅ ማስጠንቀቁን ታደሰ እንግዳው የላከልን ዘገባ ያስረዳል። ያዳምጡ

Play below

 

የሕገወጥ የጫት ነጋዴዎች ክስ በአሜሪካ ፍርድቤት

Thursday, April 19th, 2012

አሥራ ሶስት የሶማልያና የየመን ተወላጅ የሆኑ አሜሪካውያን ጫትን በህገወጥ መንገድ ወደ ዩኤስ አሜሪካ አስገብተዋል በሚል በሀገሪቱ ፌዴራዊ ፍርድ ቤት ክስ ተመሰረተባቸው። ተከሳሾቹ ባለፉት ስድስት ዓመታት ብዙ ሚልዮን የሚቆጠር ዶላር ያስገኘ ጫት ማዛዋወራቸውን የክሱ መዝገብ አመልክቶዋል። የህግ ባለሞያና ጠበቃዉ ዶክተር ፍፁም አቻሜለህ ፊደራሉ ህግ ላይ በወንጀልነት የተጠቀሰዉ ይላሉ « በፊደራሉ ህግ የተፃፈዉ ጫት ዉስጥ ስላሉ ንጥረ ነገሮች ነዉ። አንደኛዉ ካቲኖን የተባለ ንጥረ ነገር ሲሆን ፣ ሁለተኛዉ ደግሞ ካቲን የተባለ ንጥረ ነገር ነዉ ያለዉ ጫት። ካቲኖን የሚገኘዉ ጫት ከተቆረጠ 48 ሰዓት ያልሞላዉ እርጥብ ጫት ዉስጥ ነዉ። በአሜሪካ ዉስጥ እርጥብ ጫት ይዞ መገኘት ከአንድ ዓመት በላይ የሚያስቀጣ ከባድ ወንጀል ነዉ።»

Play below

 

የዓመቱ የመፃፍ ነፃነት ተሸላሚ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ

Monday, April 16th, 2012

ዓለም አቀፉ የፔን – አሜሪካ ተቋም በእስር ላይ የሚገኘውን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የአመቱ የመፃፍ ነፃነት ተሸላሚ አድርጎ መርጧል። ኢትዮጵያ ውስጥ በፀረ ሽብር ስም የመፃፍ ነፃነት ላይ ጫና እየተፈጠረ ነው ያለው ድርጅቱ እስክንድር የደረሰበትን ጫና ሁሉ ተቋቁሞ የመፃፍ ነፃነትን መብት ለማስከበር ባደረገው ትግል ለዚህ ሽልማት መመረጡን አውስቷል። የዋሽንግተን ዘጋቢያችን አበበ ፈለቀ ዝርዝር ዘገባ ይዟል።

Play below

 

የሱዳን እና የደቡብ ሱዳን ውዝግብ መባባስ

Saturday, April 14th, 2012

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የደቡብ ሱዳን ጦር ሂጂሊጅ የተባለውን የሰሜን ሱዳን ግዛት እና በአካባቢው የሚገኘውን የነዳጅ ዘይት ንጣፍ የተቆጣጠረበትን ርምጃ ከራስ መከላከል ያለፈ ድርጊት ነው ሲል፡ እንዲሁም፡ የሱዳን መንግሥት ደቡብ ሱዳንን በቦምብ ማጥቃትዋን በጥብቅ አወገዘ።

ዩኤስ አሜሪካ፣ የአፍሪቃ ህብረትና የተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት  የደቡብ ሱዳን ጦር ካላንዳች ቅድመ ግዴታ ለቆ እንዲወጣ አሳስበዋል። ይሁንና፡ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር ጦራቸው ከሂጂሊጅ እንዲወጣ የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አድርገውታል። በሁለቱ ሀገሮች መካከል አሁን እየተባባሰ የመጣው ውዝግብ፡ የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መሥሪያ ቤት፡ ዩኤንኤችሲአር እንደገለጸው፡ ብዙዎችን እንዲፈናቀሉና እንዲሰደዱ አድርጎዋል።

የሱዳን ጦር በዩኒቲ ክፍለሀገር አንድ ሥልታዊ የደቡብ ሱዳንን ድልድይ በቦምብ ካጠቁ በኋላ የሱዳን እና የደቡብ ሱዳን መሪዎች አንዱ ሌላውን ጦርነት ለመጀመር አቅዶዋል በሚል እርስበርስ መወቃቀስ ጀምረዋል። በዚሁ ጊዜ የደቡብ ሱዳን መንግሥት ጦር ባለፈው ማክሰኞ ገና በሚገባ ያልተከለለውን ድንበሩን ተሻግሮ በሱዳን ከያዘው ከሀገሪቱ ነዳጅ ዘይት መካከል ሀምሳ ከመቶው የሚመረትበትን የሂጂሊጅን ግዛት ለቆ የሚወጣበትን ቅድመ ግዴታ አስቀምጣለች። የደቡብ ሱዳን የማስታወቂያ ሚንስትር ባናባ ማርየል ቤንጀሚን እንዳስረዱት፡ ቅድመ ግዴታው ሱዳን ጦርዋን ከአቢየ የምታስወጣበትን እና በየብሱና በአየር የምታካሂደውን ጥቃት በጠቅላላ የምታቆምበትን ሀሳብ ያጠቃልላል።

በደቡብ ሱዳን የቀድሞው የተመድ ተልዕኮ ኃላፊ ፒተር ሹማን ደቡብ ሱዳን ይህን ርምጃ ለመውሰድ ያነሳሳት ምክንያት ምን ሊሆን እንደሚችል ሲያስረዱ፡

« ሁሉ ነገር የራሱ ታሪክ አለው። የሱዳን ጦር ከአንድ ዓመት በላይ በፊት አቢየን የያዘበትን፡ በአቢየ መካሄድ የነበረበት ሕዝበ ውሳኔ ሳይካሄድ የቀረበትን፡ እና ሌሎች ተመሳሳይ ሂደቶችን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ችላ ያለበት ድርጊት አሁን ውዝግቡ እንዲባባስ ድርሻ አበርክቶዋል። የተደረሱ ስምምነቶች ነበሩ። አንድ ልዩ ተልዕኮም ተዘጋጅቶ ነበር። ይህ ሁሉ አሁን የታየውን ሁኔታ አስከትሎዋል። እንደሚመስለኝ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የአዲሲቱን ሀገር የደቡብ ሱዳን የሰላም ፍላጎትን በሚገባ አላጤኑላትም። እኔ ከጥቂት ጊዜ በፊት ጁባ ነበርኩ። በሰሜኑ አካባቢ ወዳለው የድንበር አካባቢም ተጉዤ ነበር። ካርቱምም ሄጄ ነበር። ብዙ ሰዎችን አነጋግሬአለሁ። እና ሰው በተለይ ደቡብ ሱዳን ዜጎች መልስ ላላገኙት አወዛጋቢ ጉዳዮች ባፋጣኝ መልስ እንዲገኝላቸው ያሳዩት ጠንካራ ፍላጎት አስገርሞኛል። የዓለም አቀፉ ድርጅቶች ተወካዮች ያሳዩት ቸልተኝነትና ለውዝግቡ በአፍሪቃ ህብረት የተሰየመው በቀድሞው የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ታቦ ምቤኪ የሚመራው የሸምጋዮች ቡድን መፍትሄ ያስገኛል ብለው የጠበቁበት ድርጊትም አስገርሞኛል። »
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የአዲስ አበባው ድርድር ይቀጥል ዘንድ ወሳኝ አስተዋፅዖ ሊያበረክት ይችል እንደነበር ፒተር ሹማን በመግለጽ ትችት አሰምተዋል።

« ዓለም አቀፉ ማህበረሰብብዙ ማድረግ በተገባው ነበር። ጉዳዩን የአፍሪቃ ህብረት ከፍተኛ የሽምጋዮች ቡድን ብቻ በመተው ፈንታ ራሱም ፡ ጀርመንም ጭምር ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀስ ይኖርባቸው ነበር። ራሳቸውን የደቡብ ሱዳን ወዳጆች ብለው የሚጠሩት ወገኖች በደቡቡ ላይ ግፊት ማሳረፍ ብቻ ሳይሆን፡ ከዚችው አዲስ ሀገር ጋ ጠንከር ያለ ውይይትም መጀመርና ፍላጎትዋ በርግጥ ምን መሆኑን ለመረዳት መሞከር ነበረባቸው። »
አሁን ጦርነት አፋፍ ላይ የሚገኙት ሁለቱ ተቀናቃኝ ሀገሮች ከኃይል ተግባር እንዲታቀቡ፡ ደቡብ ሱዳንም የያዘችውን ግዛት ለቃ እንድትወጣና ወደ ድርድሩ ጠረጴዛ እንዲመለሱ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሳስቦዋል። ይሁንና ይህ ገሀድ መሆኑን ፔተር ሹማን አብዝተው ይጠራጠሩታል።

« አይመስለኝም፡ ዓለም አቀፍ አደራዳሪዎች፡ ታቦ ምቤኪ የሚመሩት የሸምጋዮች ቡድን ጭምር አቢየን ጉዳይ በተመለከተ ተዓማኒነት አጥተዋል። የሱዳን ጦር ባለፈው ዓመት አቢየን በያዘበት ጊዜ በደቡብ ሱዳን ርዕሰ ከተማ ጁባ ነበርኩ። የተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ቡድን ደግሞ ካርቱም ነበር፤ ግን የሱዳን ጦር አቢየን በያዘበት ርምጃ አንጻር ቡድኑ ያሰማው ተቃውሞ በጣም የሰጠው ደካማ ነበር። እና በደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆኑ ተራው ሕዝብም ሳይቀር ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ሊያምኑ እንደማይችሉ ነው ያስታወቁት። ምክር ቤቱ ሥራውን በሚገባ የሚያከናውን ከሆነ በሰሜን ሱዳን እና ነፃ መንግሥት የመሆን መብታችንን ሊነፍጉ በሚፈልጉ ላይ ርምጃ መውሰድ አለበት። እና አቢየን መያዝ በቸልታ በታለፈበት ጊዜ እምነታችንን አጥተናል። ከዚያ በኋላ ሌላ የተመ ሰላም አስከባሪ ሠራዊት ተቋቁሞዋል፡ ይሁንና፡ እስካሁን ሙሉ በሙሉ ተግባሩን ማካሄድ አልቻለም። እና የተገባ ቃል በተደጋጋሚ የተጣሰበት፡ ይህን ወይም ያኛውን ሁኔታ የሚቆጣጠር የሚታዘቡ ኮሚቴዎች፡ ኮሚሽኖች ሲቋቋሙ ብቻ ነው የታየው፤ እና ሕዝቡ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ላይ እምነት የለውም። »
የደቡብ ሱዳን ጦር ሰሞኑን በሱዳን የተቆጣጠረው ሂጂሊጅ ከሚገኝበት የደቡብ ኮርዶፋን ክፍለ ሀገር በርካቶች በውዝግቡ ሰበብ መሸሽ መገደዳቸውና ብዙዎችም በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ በናይሮቢ ኬንያ የሚገኙት የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መሥሪያ ቤት፡ በምህፃሩ ዩኤንኤችሲአር ተጠሪ ወይዘሮ ቪቭየን ታን ገልጸዋል።

« እስካሁን ወደ ደቡብ ሱዳን የዩኒቲ ክፍለ ሀገር የሸሹ አሥራ ስምንት ሺህ ስደተኞችን መዝግበናል። በተለይ ቀውሱ በቀጠለበት ድንበር አካባቢ አቅራቢያ በሚገኘው ኒዳል በተባለው የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ከለላ ያገኙ አሥራ ስድስት ሺህ ስደተኞች ሁኔታ እጅግ አሳስቦናል። ይህ የመጠለያ ጣቢያ ባለፈው ዓመት በተደጋጋሚ በተዋጊ አይሮፕላኖች የቦምብ ጥቃት ተደብድቦዋል። እና ጣቢያው አሁንም እንደገና ተመሳሳይ ጥቃት እንዳይጣልበት ሠግተናል። አሁን የተጎዳ አንድም ስደተኛ የለም። ወደፊት የሚካሄድ ጥቃት ግን ከድንበር ባሻገርም ሊስፋፋ እና የስደተኞቹን ህልውና ሥጋት ላይ ሊጥል ይችላል። በመሆኑም፡ እነዚህን ስደተኞች መረጋጋት ወደሚታይበትና የተሻለ አገልግሎት መስጠት ወደምንችልበት ወደደቡባዊ የደቡብ ሱዳን አካባቢ ለማዛወር እየሞከርን ነው፤ ግን፡ ስደተኞቹ በኑባ ተራሮች አካባቢ ከሚገኘው በድንበሩ አካባቢ ካለው ትውልድ ቦታቸው ብዙ መራቅ ስለማይፈልጉ የመዛወሩን ሂደት አልተቀበሉትም። በድንበሩ አካባቢ ያለው የፀጥታ ሁኔታ አስተማማኝ ባለመሆኑ እንደልብ መንቀሳቀስ አንችልም። ይህም ለስደተኞች ርዳታ በምናቀርብበት ሁኔታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፎዋል። »
ስደተኞቹ አካባቢያቸው በቦምብ መደብደቡን እና ውጊያውም መቀጠሉን የገለጹት ስደተኞች ወደመጠለያ ጣቢያው ለመድረስ ብዙ ሣምንታት በእግራቸው መጓዛቸውን አስታውቀዋል። ችግሩ እየተባባሰ ከሄደ የስደተኛው ቁጥር ሊጨምር ስለሚችል ዩኤንኤችሲአር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ቪቭየን ታን አስረድተዋል።

«በዚሁ አካባቢ ወዳሉት ብዙዎቹ ጣቢያዎች የሚያደርሱት መንገዶች ጥቂት በመሆናቸው የዝናቡ ወራት በቅርቡ ሳይጀምር እና እዚያ መድረሱ አዳጋች ከመሆኑ በፊት ብዙ የምግብ ርዳታ የርዳታ ቁሳቁስ ለማዘጋጀት እየሞከርን ነው።»
ያዳምጡ

Play below

 

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስለ አለም ደቻሳ ያቀረበዉ ጥያቄ

Friday, April 13th, 2012

የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ጉባኤ የዘመናዊ ባርነት ክፍል በሊባኖስ የኢትዮጵያዊትዋን የአለም ደቻሳን አሟሟት በተመለከተ የሊባኖስ መንግስት መርምሮ ይፋ እንዲያደርግ ጠየቀ። ተቋሙ በሊባኖስ ዉስጥ የሚኖሩ ከ 200,000 በላይ የዉጭ አገር ዜጎች በግርድና እየሰሩሩ መሆኑን ገልጾ፣ ከፍተኛ እንግልት እና ስቃይ እንደሚደርስባቸዉ አስታዉቆአል። የ33 አመትዋ ኢትዮጵያዊት አለም ደቻሳ፣ በአሰሪዎችዋ ከተደበደበች በኋላ እራስዋን ማጥፋትዋ የሚታወስ ነዉ። ይህንኑ የአለም ደቻሳን ሞት ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ እና የኢትዮጵያዉያን እና የዉጭ ተቋማት ተቋማቸዉን በተደጋጋሚ ሲያሰሙ ቆይተዋል።

Play below

 

ዝነኛው ኢትዮጵያዊ አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ አረፉ

Wednesday, April 11th, 2012

እዉቁ ኢትዮጵያዊ የስነ-ጥበብ ምሁር ከዚህ አለም በሞት ተለዩ። እጅግ የተከበሩ የአለም ሎሪት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ትንናት ከቀትር በኅላ በሰማንያ አመታቸዉ በድንገት ማረፋቸዉ ነዉ ዛሪ ይፋ የሆነዉ። አፈወርቅ ተክሌ ዘመናዊ ጥበብን ከኢትዮጵያ ቱፊታዊ ስነ-ጥበብ ጋር በማጣመር የሰሩዋቸዉ የቀለም ስራዎች በአለም ታዋቂነትን እንዲያገኙ አድርጎአቸዋል። በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የስነ-ጥበብ ትምህርት ዲፓርትመንት መምህራን እጅግ የተከበሩ የአለም ሎሪት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌን ለረጅም አመት ያቋቸዋል። አነጋግረናቸዉ ነበር!

Play below

 

በየመን የኢትዮጵያን ስደተኞች ሥቃይ

Friday, April 6th, 2012

በየመን በታየው አለመረጋጋት የተነሳ ላለፉት አሥራ አንድ ወራት ኑሮን በመከራ የገፉ በተመድ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መሥሪያ ቤት ኡ ኤን ኤች ሲ አር እውቅና ያገኙ ወደ አራት ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሀገሪቱ ከተፈጠረው ግጭት ከለላ ይደረግላቸው ዘንድ በመዲናይቱ ሰንዓ በተጠለሉበት ዩ ኤን ኤች ሲ አር በር ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት ደረሰባቸው። የጄዳ ወኪላችን ነቢዩ ሲራክ በስልክ ያነጋገራቸው እነዚሁ ስደተኞች በየመን የፀጥታ ኃይላት የተቀነባበረ ጥቃት እንደደረሰባቸውና ከተመድ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መሥሪያ ቤት UNHCR ርዳታ እንዳልተደረገላቸው ገልጸውለታል።

ይሁንና፣ የመን የሚገኙ የኢትዮጵያ ተገን ጠያቂዎች በየመን የደህንነት ኃይሎች ጥቃት እንደደረሰባቸዉና ከUNHCR ርዳታ እንዳላገኙ ቢያስታውቁም የመን የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን በምህፃሩ UNHCR ወቀሳዉን አስተባብሏል። የመን የሚገኙ የኢትዮጵያ ተገን ጠያቂዎች በየመን የደህንነት ኃይሎች ጥቃት እንደደረሰባቸዉ ቢያስታውቁም የመን የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን በምህፃሩ UNHCR ወቀሳዉን አስተባብሏል።

በየመን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን በምህፃሩ UNHCR እውቅና የሰጣቸው የኢትዮጵያ ተገን ጠያቂዎች በየመን ሰላም አስከባሪ ኃይላት ስለደረሰባቸው የድብደባ እና ሌሎች ጥቃቶች ቢገልፁም የመን UNHCR ቃል አቀባይ ዘይድ አል-አላያ ይህንን ያስተባብላሉ።

« በፍፁም በፍፁም ምንም ዓይነት የደረሰ ጥቃት የለም። የተወሰኑ ተገን ጠያቂዎች ወደ UNHCR ህንፃ በስተጀርባ መተው ነበር። ወደ ሌላ ቦታ መስፈር ይፈልጋሉ። ይህ ግን በአሁኑ ጊዜ ከባድ ነው። ምክንያቱም የመን የምትቀበለው ከጥቂት አገሮች ለሚመጡ ስደተኞች ነውና ። እነዚህ ተገን ጠያቂዎች ከየመን UNHCR ጋ ስምምነት በመፍጠር ወደ ተዘጋጀላቸው መጠለያ ተወስደዋል። መጠለያዉ በደቡብ የመን የሚገኝ ነዉ። ተገን ጠያቂዎቹ በራሳቸው ፍቃድ በአውቶቢስ ተጭነው ነዉ ወደ መጠለያው የተወሰዱት። በአጠቃላይ ስደተኞቹ ምንም አይነት ጥቃት አልደረሰባቸውም። ስለ ተገን ጠያቂዎች ወቀሳ የቀረበው በየመን እና ከየመን ውጪ በሚገኙ የመገናኛ ብዙኋን ነው።»

ቃል አቀባዩ የሚስማሙበት አንድ ነገር ቢኖር ስደተኞቹ UNHCR ወደ አዘጋጀው ካርታስ ወደተባለው ትልቅ እና ሰፊ መጠለያ መወሰዳችን ብቻ ነው። UNHCR ለተገን ጠያቂዎቹ የበኩሉንም ርዳታ እየሰጠ ይገኛል ሲሉም ይገልፃሉ።

« ከለላ እንሰጣለን። ለተገን ጠያቂዎች አስፈላጊ የሆኑ የህይወት አድን ርዳታ እናደርጋለን። መጠለያ እንሰጣለን። የአካል ጉዳተኛ ለሆኑት ርዳታ እንጣለን ሠርተዉ ራሳቸዉን መርዳት ለማይችሉት ደግሞ የገንዘብ ድጋፍ እንሰጣለን። »

ይሁንና በርካታ ስደተኞች ከዚህ ቀደም ስለተከሰቱ ችግሮች ላነሱት ጥያቄና በቂ መተዳደሪያ እንዲሰጣቸውም አመልክተዉ ምላሽ አላገኙም። የየመን UNHCR ቃል አቀባይ ዘይድ አል-አላያ እንደሚሉት አንዱ ችግር የተገን ጠያቂዎች በየመን መንግስት እውቅና ማግኘቱ ላይ ነው።

« ሶማሊያውያን ወደ የመን ሲመጡ በተገን ጠያቂነት የመን እውቅና ሰጥታቸዋለች። ይህም የሆነው የመን በ19 51 እና በ1967 ስምምነት ተፈራርማለች። ነገር ግን ሌሎች ዜጎች፤ እንደ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ያሉት ተገን ጠያቂዎች ግን ወደስደተኛ ሁኔታ መወሰኛ አካል መሄድ አለባቸው። ምክንያቱም UNHCR በአጠቃላይ ለስደተኞች እና ለተገን ጠያቂዎች ከለላ አይሰጥም።»

ያዳምጡ፣ ክፍል 1

Play below

 
ክፍል 2

Play below

 

ተቃውሞ በሊባኖስ የወያኔ ቆንስላ ላይ

Friday, April 6th, 2012

በሊባኖስ ቤይሩት ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ፣ ህይወቷን አጠፋች የተባለችው የዓለም ደቻሳ ሞት ከተነገረበት ማግስት አንስቶ ቤይሩት ወደሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ በመሄድ ቁጣቸውን ሲያሰሙ መቆየታቸውን የጂዳው ወኪላችን ነበዩ ሲራክ ዘግቧል ። ሊባኖስ ቤይሩት ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ፣ ህይወቷን አጠፋች የተባለችው የዓለም ደቻሳ ሞት ከተነገረበት ማግስት አንስቶ ቤይሩት ወደሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ በመሄድ ቁጣቸውን ሲያሰሙ መቆየታቸውን የጂዳው ወኪላችን ነበዩ ሲራክ ዘግቧል ። ዓለም ቆንስላው በር ላይ ስተሰቃይ በነበረበት ወቅት የሚደርስላት ማጣቷ ያስቆጫቸው እነዚሁ ኢትዮጵያውያን የቆንስላው ባለሥልጣናት መብታችንን ያስጠብቁ አለያም ለቀው ይውጡ በማለት በተለያዩ መንገዶች ተቃወሞአቸውን እየገለጹ ነው ። በቤይሩት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጀነራል በበኩላቸው ዜጎች ህጋዊ ከለላ እንዲያገኙ ጥረት እየተደረገ መሆኑንና ጉዳዩንም የሊባኖስ መንግሥት እየተመለከተው መሆኑን ለዶቼቬለ አስታውቀዋል።

Play below

 

ባለዲግሪው ጋዜጣ ሻጭ በኢትዮጵያ

Friday, April 6th, 2012

በኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች መብት ምን ያህል ይከበራል፣ ተግባራዊ ጥበቃውስ ምን ይመስላል? የዛሬው የወጣቶች ዓለም መሰናዶ ርዕስ ነው። የ24 ዓመቱ ወጣት ግዛቸው አዘዘው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፍልስፍና ትምህርት በዲግሪ መርሐ-ግብር እንደተመረቀ ገልጿል።ይሁንና ግን ወጣቱ በአካል ጉዳተኝነቴ የተነሳ ብቻ እስካሁን ስራ ለማግኘት አልቻልኩም ሲል ምሬቱን አሰምቷል። ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሰራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስትር መስሪያ ቤት ባለሙያዎችን አነጋግረናል። የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበር ፕሬዚደንትም መልስ አላቸው። በኢትዮጵያ ቁጥራቸው ትንሽ የማይባል የአካል ጉዳተኞች ከማህበረሰቡ ከሚደርስባቸው የተለያዩ ጫናዎች ባሻገር በጥረታቸው ከፍተኛ ደረጃ ሲደርሱ ይስተዋላል። በዛው መጠን ደግሞ ምንም ያህል ጥረት ብናደርግም መብታችን በተገቢው መንገድ አልተጠበቀልንም የሚሉ አይታጡም። ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መካከል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዲግሪ እንደተመረቀ የገለፀልን የ24 ዓመቱ ወጣት ግዛቸው አንዱ ነው።

Play below

 

በጂዳ የኢትዮጵያውያን ክርስቲያን እስረኞችና የወያኔ ቆንስላ

Wednesday, April 4th, 2012

ወደ 3 ወር ለሚጠጋ ጊዜ ጅዳ ሳውዲ ውስጥ በእስር ላይ የሚገኙት 36 ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በታሠሩበት ሀገር የሚገኙ የኢትዮጵያ መንግሥት ተወካዮች ለደረሰብን በደል ፍትህ እንድናገኝ አላደረጉም ሲሉ ያቀረቡትን ወቀሳ በጂዳ የኢትዮጵያ ቆንስላ አስተባበለ። በጂዳ የኢትዮጵያ ቆንስላ ፅህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ ኑረዲን ሙስጠፋ ቆንስላው ባለስልጣናት ታሳሪዎቹን ያሉበት ድረስ ሄደው እንዳነጋገሩዋቸውና ኢትዮጵያውያኑ በእስር ቤት ተፈፀመብን የሚሉት በደል እንዲጣራ ለእስር ቤቱ ሃላፊዎች መንገራቸውን አስታውቀዋል። ያነጋገራቸው ነብዩ ሲራክ ተከታዩን ዘገባ ልኮልናል።

Play below

 

በኢትዮጵያ የገደማት ይዞታ ያስከተለው ሥጋት

Friday, March 30th, 2012

በአሰቦትና በዝቋላ ገዳማት አካባቢ በቅርቡ ቃጠሎ ተነስቶ የነበረበት ሁኔታ፣ በአሰቦት ገዳም ይማር የነበረ አንድ ልጅ፣ መገደሉ፣ እንዲሁም፤ የበርሊኑ ዘጋቢአችን ይልማ ኃይለ ሚካኤል እንደዘገበው፤ በልማት ስም ፣ የዋልዳባ ገደም መደፈር፣ በዚህ በጀርመን አገር የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልጋዮችን እና አባቶችን፤ ጉዳዩ አሳስቦአቸዋል። «የገዳሙ አባቶች አለምክንያት ድምጻቸውን አላሰሙም! » ያሉት፣ በጀርመን የሚገኙት መንፈሳዊ አገልጋዮች፣ ለህዝበ ክርስቲያኑ፤ በየአጋጣሚውና በዕለተ እሁድ ሥጋታችንን መግለጽ ይኖርብናል። ለገዳሞቻችንም የተለየ የጸሎት መርኀ-ግብር እንዲወጣ እናድርግ» ሲሉ አሳስበዋል። ያዳምጡ

የዋልድባ ፕሮጀክትና የዋሽንግተን ሰልፍ

Wednesday, March 28th, 2012

በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ በሚገኙ ከተሞች የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ከትናንት በስተያ በዋልድባ ገዳም ላይ ጉዳት የሚያደርስ ነዉ ያሉት ፕሮጀክት እንዲቆም ጠየቁ። ኢትዮጵያዉያኑ ዋሽንግተን በሚገኘዉ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ደጃፍ ላይ ባደረጉት ሰልፍ ነዉ ጥያቄያቸዉን ያቀረቡት። ኤምባሲዉ በበኩሉ በፅሁፍ በሰጠዉ ምላሽ ፕሮጀክቱ እና ገዳሙ ጭራሽ አይገናኙም፤ ተቃዉሞዉ ሃይማኖታዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ አጀንዳ የያዘ ነዉ ማለቱን የዋሽንግተን ዲሲዉ ወኪላችን አበበ ፈለቀ በላከዉ ዘገባ አመልክቷል።

Play below