Author Archive

ትዳርን የማሸነፍ ኣቅም ማጣት እድገትን ተከትሎ ኣይመጣም

Sunday, January 6th, 2013

ኢንፍሌሸንን ሊያመጡ ከሚችሉ መንስኤዎች መካከል ፈጣን የ ኢኮኖሚ እድገት ኣንዱ እንደሆነ የሚስማሙ ምሁራን በርግጥ ኣሉ። ኣንዳንድ ምሁራን ደሞ ኢንፍሌሽንን እድገት ሊያመጣው ኣይችልም ብለው ይናገራሉ። የ ሁለቱ ልዩነት ያረፈበት ነጥብ የሚመስለው ኢንፍሌሽን የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ባዩበት ወሰን ላይ ነው። የ መጀመሪያው ቡድን የሚያምነው ኢኮኖሚ ሲፈነዳ ኣገሮች የ ኢኮኖሚ ጥርመሳ (breakthrough) ሲያደርጉ የ ዋጋ ማሻቀብ ይመጣል። ይህንን የዋጋ ማሻቀብ ተከትሎም የገንዘቡ የመግዛት ኣቅም ይወርዳል ይላሉ። በነዚህ ወገኖች መረዳት የ ኢንፍሌሽንን ጽንሰ ሃሳብ በ ዋጋ ንረትና በ ገንዘብ የ መግዛት ኣቅም ማነስ ኣጥር ውስጥ ነው የሚያዩት። የ ሃገሪቱን ኣጠቃላይ ገቢ እድገት ያዩና ካምናው ዘንድሮ ኣጠቃላይ ኣሃዙ እድገት እያሳየ ግን ደሞ ዋጋ ካሸቀበ እድገቱ ያመጣው ጣጣ ነው ወደ ማለት ሊሄዱ ይችላሉ። ይህ ማለት እድገት ሲመጣ ዲማንድ ወይም ፍላጎት ይጨምራል ለእድገት በሚደረገው ሩጫ በ ገበያ ላይ ፍክክርን ስለሚያመጣና ገበያውን ስለሚያነቃቃው ግዢ ብዙ ስለሚፈጸም ዋጋ ያሸቅባል ለማለት ነው። ኣድገው የተረጋጋ ኢኮኖሚ እስኪገነቡ ድረስ ለዚሀ የመጋለጥ እድላቸው ሰፊ ነው ለማለት ነው፡፡

በሌላ በኩል ያለው ግንዛቤ ደሞ ኢንፍሌሽንን ሰፋ ባለ ኣጥር ውስጥ ያያል። በዚህ ትንታኔ መሰረት ኢንፍሌሽን ማለት በ ኣጠቃላይ የ ዋጋ ማሻቀብ ሆኖ በዚህ ሳቢያ የገንዘብ ጉልበት ሊደክም እንደሚችል ያሰምርና በዚህ ኣይቆምም የዚህን ተጽእኖም ያካትታል። በመሆኑም ዋጋ ሲያሻቅብ ገንዘብ ሲደክም የሚመጣው ተጽእኖ የ ሸማቹን ትዳር የ ማሸነፍ ኣቅምም ይመታል ማለት ነው። በመሆኑም ኢንፍሌሽን የሚባለው ጽንሰ ሃሳብ ከዋጋ ንረት ጀምሮ የገንዘብን ጉልበት ኣድቅቆ የዜጎችን ኑሮ የ ሚያደቅ ነው ማለት ነው። በዚህ ኣገባብ የምናወራው እጅግ ከፍተኛ፣ ከፍተኛ፣ ሲከፋም ሃይፐር ኢንፍሌሽን የሚባለውን ጽንሰ ሃሳብ የተመረኮዘ ኣስተያየት ነው። በ ኖርማል ሬንጅ ውስጥ ስላለው የገበያ መውጣት መውረድ ኣይደለም።

ታዲያ በዚህ ሰፋ ባለ መረዳት ጊዜ ኢንፍሌሽን ሲታይ እድገት ካለ የ ዋጋ መናር ሊኖር ቢችልም ገንዘብ ቢደክምም ግን የ ዜጎች የ መግዛት ኣቅም ያን ያህል ኣይደክምም። ምክንያቱም እድገት ስላለ የዜጎች የ ገቢ መጠንም ኣብሮ ከ ኢንፍሌሽኑ ጋር እየተፎካከረ ያድጋልና ነው። የነዚህ ቡድኖች እይታ የመጀመሪያዎቹን ምሁራንን ትንታኔ ግልጽነትና ተለጣጣቂ ተጠይቃዊ(logical) ጥያቄዎችን የ ማይመልስ የ ሚያደርግ ሊሆን ይችላል።ምክንያቱም ዋጋ ማሻቀቡና የገንዘብ ዋጋ መድከሙ ብቻውን ወይም በራሱ ምንም ኣይደለም። ዋናው ጉዳይ በሸማቹ ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ ነው መሆን ያለበትና።

በ ነዚህ ወገኖች እሳቤ ኢንፍሌሽን ማለት በቀላል ኣገላለጽ ለምሳሌ የ ዛሬ ኣመት ኣንድ ቅርጫት ይዞ ገበያ ሄዶ በ 500 ብር ግጥም ኣርጎ ቅርጫቱን ሞልቶ በ ወዛደር ኣሸክሞ ወደ ቤቱ የ ሄደ ሰውዬ ዛሬ ያንንው እቃ በዚያው ቅርጫት በዚያው ገንዘብ መጠን ገዝቶ ግን የገዛው እቃ ትንሽ ሆና በ ኣንድ እጁ ጠልጠል ኣርጎ ወይም ሸከም ብሎ ወደ ቤቱ እያዘነ ሲሄድ ማለት ነው። የ እቃው መጠን በርግጥ እንደ ደረጃው ይለያያል፡፡ ጥያቄው ታዲያ ግን ይሄ ነገር በማደግ ላይ ባለ ኣገር ይሆናል ወይ? እድገት ሲባል እኮ የምርት መጠን ወይም ኣቅርቦት መጨመርንና በዚህ ለውጥ ሳቢያ የ ህብረተሰብ የኑሮ ዘየ ላይ ተጽእኖ ሲያርፍ ነው።

ልክ ሁሉም እንደሚያምነው እድገት ሲመጣና ኢኮኖሚ ሲፈነዳ የዜጎች ፍላጎት ይጨምራል። ለምሳሌ በኛ ሃገር ደረጃ ስናየው ከዚህ በፊት ልሙጥ ሽሮ ይበላ የነበረው ዛሬ ኣዱኛ ወደ ቤቱ ብቅ እያለ ነውና ተነቃቅቶ በዘይት መብላት፣ ከዚያም ምሳና ራት የተለያዩ ምግቦችን መብላት ይፈልጋል። ትንሽ የተሻለ ኑሮ ሊያኖረው የሚችል ገንዘብ ስላገኘ በገበያ ላይም ለጋስ ይሆናል። ይከፍላል፤ ይገዛል። ሻጩም ገበያው ሲሞቅ እያየ የገዢውን ብዛትና ኣቅም እያየ ዋጋ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ በእንደዚህ ኣይነት ሂደት ጊዜ የዋጋ ንረት የሚከሰት ሲሆን እንዲህ ኣይነቱ ንረት ከ ፍላጎት መጨመር ከ ህዝብ ምቾት ፍለጋ ጋር የተፎካከረ የዋጋ ሽቀባ ስለሚሆን ይህ ጉዳይ የኢኮኖሚ እድገት ያመጣው ጣጣ ነው ሊባል ይችላል።በዚህ ጊዜ መንግስት የኢኦኖሚክ ስሌቱን እያሰላ የንረቱን መጠን ማደጉን ቢገልጽም በዜጎች ዘንድ ማጉረምረም እብዛም ኣይታይም። በዚህ ጊዜ ባለፈው ጊዜ በ 500 ብር በግ ገዝቶ የገባ ሰው ዛሬ ዋጋው በ 50 በመቶ ኣድጎ ያንኑ የሚያህል በግ 750 ብርም ቢሆን ገዘቶ ይገባል እንጂ ይህ ሰው ባዶ እጁን ኣይገባም። እድገት ካለ በጨመረው ዋጋ ያንኑ በግ እንደውም የተሻለ ገዝቶ ሊገባ የሚያስችል ኣቅም ይኖረዋል።በፈጣን እድገት ላይ ያለ ኣገር ማለት እኮ እያደገ መሄዱን በዜጎች ህይወት ላይ እያሳየ ነው የሚሄደው። እድገት ኣንዴ የኣምስቱ ኣመት የእድገት ፕላን ሲያበቃ በመጨረሻዋ ቀን ሰርፕራይዝ ተብሎ ፓርቲ የምናደርግበት ሂደት ኣይደለም። በየ ኣንጓው ዜጎች ለውጥን እያዩ የሚሄዱበት ሂደት ነው እድገት።

የዋጋ ንረት ሲመጣ ዜጎች በውነት መንግስትን ኣጥብቀው መጠየቅ የሚፈልጉት ለምን እቃ ተወደደ ኣይደለም። ለምን የኔ ትዳር የማሸነፍ ኣቅሜ ደከመ ነው የ ውስጠኛውና ዋናው ጥያቄ። ለዚህ ነው ሰራተኛው የደመወዝ ጭማሪ የሚያነሳው።ለምን ዋጋ ጨመረ ሳይሆን ዋጋ ጨምሮ የኔ ገቢ ለምን ኣይጨምርም ነው። እንግዲህ በኛ ሃገር ሁኔታ ኢንፍሌሽኑ የመጣው በ ፈጣን እድገት ምክንያት ነው ከተባለ ዜጎች የሚጠይቁት የነፍስ ወከፍ ገቢያቸው ከ ኢንፍሌሽኑ ጋር ታገሎ ተሸነፈኩ ትዳሬን ማሸነፍ ኣቃተኝ ያ እድገት ኣለ ያላችሁት ለምን ኣይደርስልኝም? ነው እንጂ ፍልስፍናው ምንም ኣይጠቅማቸውም። ኢንፍሌሽን ከ እድገት ጋር ተያይዞ ይመጣል ኣይመጣም እያሉ ሊከራከሩና ኣዳዲስ ኣሳቦችን እያነሱ በፍልስፍናው ሊዝናኑ(entertain ሊያደርጉ) ይችላሉ። ለተራው ዜጋ ግን እውነተኛው ምስክሩ የሱንና የቤተሰቡን የጏጓደኞቹን የ ኣካባቢውን ለውጥ ማየት ነው። እውነተኛ ምስክሮቹ እነዚህ ናቸው። ይሄውልህ በፈጣን ሁኔታ እድገት ስለጀመርን ነው ኣንተ ትናንት ትኖረው የነበረውን ኑሮ መኖር ያቃተህ ወይም ትዳርህ ያንገዳገደህ የሚል ኣንድምታ ያለው ፕሮፓጋንዳ ሲነዛ ኣፉን እያጣመመ ይታዘባል።

እንግዲህ ቅድም እንዳልነው ኢንፍለሽን የ ዋጋ ማሻቀብ እሱን ተከትሎ የገንዘቡ መሽመድመድ ከሚለው ጀርባ የ ዜጎች ትዳር የማሸነፍ ኣቅምን ያዘለ ጽንሰ ሃሳብ ነው። ለዚህ ነው እድገት ካለ ኢንፍሌሽን የለም የሚያሰኘን።ኢንፍሌሽንን በዚህ መረዳት ካየነው እድገትና ኢንፍሌሽን ሳይሆኑ ኣብረው የሚሄዱት የ ድህነት መጨመርና ኢንፍሌሽን ናቸው ኣብረው የሚሄዱት የሚል ድምዳሜ ላይ ኣረጋግቶ ያስቀምጠናል። ምን ማለት ነው እድገትን ተከትሎ የዋጋ ማሻቀብ ቢኖርም የዜጎች ገቢም በኣጭር ርቀት ከ ኢንፍሌሽኑ ጋር ስለሚሮጥ በዜጎች ህይወት ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ ቀላል ነው። ዜጎች በዋጋ ጭማሪ ጉዳይ ርሃብ ላይ ከወደቁ ወይም ሰፊው ህብረተሰብ ኑሮው ከደከመ በርግጥ ኢንፍሌሽኑ ከእድገት ጋር የተያያዘ እዳልሆነ ያሳያል። ዋናው ቀላሉ ሎጂክ ያለው እዚህ ጋር ነው። እድገት የሚባለው ነገር ልማታዊ ከሆነና ጤነኛ ከሆነ ኢንፍሌሽን የዜጎችን ቤት ኣያፈርስም። በዚህ ደረጃም ኣያስመርርም።ይህ ማለት ገበያው በ ኣስር ሳንቲም ሲጨምር እድገት ባለባቸው ኣገሮች የዜጎች ገቢም ኣስር ሳንቲም እየጨመረ መሄድ ኣለበት ማለት ኣይደለም። እንዲህ ኣይነት ነገር በተገባር ኣይሆንም ግን ታዲያ በተከታታይ ለኣመታት ኢንፍሌሽን ሲከሰት የዜጎች ገቢ ተፎካክሮ ካልቆመ ድህነት እየጨመረ መሄዱን ያሳያል እንጂ እድገት ኣለ ማለት ኣይቻልም።ኢንፍሌሽን እየጨመረ የዜጎች ትዳር የማሸነፍ ኣቅም እየወረደ ከመጣ በዚያች ሃገር ድህነት እየጨመረ እየጨመረ መምጣቱን ነው የሚያሳየው። የ ምርት እጥረት የ ኣቅርቦት እጥረት መኖሩን ነው የሚያሳብቀው።

ኢንፍሌሽን ሁለት ኣይነት ሊሆን ይችላል። ኣንዱ በተፈጥሮ ወይም ሰው ሰራሽ ኣደጋ ሳቢያ ድንገት የሚፈጠር የዋጋ ማሻቀብ ሲሆን ይህ ኣይነቱ ግሽበት ዜጎችን ለጊዜው ቢያስደነግጥም ኣገር ሲረጋጋ ወደ ነበረበት ሊመለስ ይችላል። ኢትዮጵያን የገጠማት ግን በተከታታይ ለረጅም ኣመታት የሚዋዥቅ ኢንፍሌሽን ነው። በ ዚህ ጊዜ ደሞ ዜጎች በ ከፍተኛ ሁኔታ ሲያማርሩ ይታያል፡፡ ይህ ኣይነቱ ችግር የሚመጣው እድገትን ተከትሎ ሳይሆን የ ኣቅርቦት እጥረት ሲከሰት ነው። በቂ ኣቅርቦት ከሌለ በዚያ ምክንያት በሚፈጠር ፉክክር ገበያ ያብዳል። በዚሀ ጊዜ ሰፊው ህዝብ መከራው ይበዛል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ኣሁን ያለው ኢንፍሌሽን በምን ተከሰተ ለሚለው ጥያቄ ብዙ ጥናት ላይጠይቅ ይችላል። ፋክቶች ስላሉ እነሱን ኣይቶ ኣንጻራዊ ድምዳሜ መስጠት ይቻላል። እንግዲህ ተመልከቱ የዛሬ ሃያ ሁለት ኣመት ገደማ ኣንድ እንቁላላል በኣስር ሳንቲም በሚሸጥበት ሰኣት ኣንድ የ 500 ብር ደመወዝተኛ ኣሁን ኣገሪቱ ኣድጋ 2000 ብር የሚከፈለው ሆኖ የኣንድ እንቁላል ዋጋ 1 ብር ከ 50 ከሆነ ኣሁን ይህ ሰራተኛ የ እድገቱ ተካፋይ ኣልሆነም ማለት ነው።እንዴውም ማደጉ ቀርቶበት በ ብዙ በ ብዙ ትዳር የማሸነፍ ኣቅሙ ወርዷል ማለት ነው። የ ሰራተኛውን ገቢ ስናይ እድገት የለም ብቻ ሳይሆን ወደ ሗላ ሄዶ ደክሞ ነው የሚታየው። የግብርናውን ጉዳይም ስናይ በርግጥ የ ከፋ ነው።

መንግስት እድገት ኣለ የህዝብ ብዛት ውጦት ነው እንጂ ኣይነት ይናገራል።በመሰረቱ ኣባባሉ ራሱ ት ህትና የጎደለው ይመስላል። እዚህ ጋር የምርት እድገትን በሁለት መንገድ ለ መግለጽ እንሞክር።በመጀመሪያ ደረጃ ኣሳባችንን ለማፋፋት ምርት ኣላደገም የሚባለው መቼ መቼ እንደሆነ እንግለጽ:: ምርት ኣላደገም ሲባል በሁለት መንገድ የሚገለጽ እሳቤ ነው። ኣንደኛ በ ሰው ሰራሽ ወይም በ ተፈጥሮ ችግሮች ሳቢያ ካምናው የ ዘንድሮው ምርት በመጠን ቀንሶ ሲገኝ ምርት ቀነሰ ወይም ኣላደገም የምንል ሲሆን ሁለተኛው ደሞ ምርቱ ሳይጨምር ቀርቶ ወይም ጨምሮ ግን የጨመረው ምርት ከህዝቡ ብዛት ጋር የማይጣጣም ከሆነ ምርት ኣላደገም ወይም ቀንሷል ነው መባል ያለበት። ለ ምሳሌ የ ዛሬ ስንት ኣመት ሃያ ሚሊዮን በነበርንበት ጊዜ 50 ሚሊዩን ኩንታል ነበር የምናመርተው ኣሁን ዘጠና ሚሊዩን ሆነን 100 ሚሊዮን ኩንታል ነው የምናመርተው ዛሬም ቁጥራችን ሃያ ሚሊዮን ሆኖልን ቢሆን ኖሮ ኣድገን ነበር ኣይባልም። ኣሁን ላለው ምርት ኣስተዋጽኦ ያደረገው ይሄው ዘጠና ሚሊዮኑ ህዘብ ነውና ይህንን ህዝብ የሚያረካ እድገት ካልተገኘ የድሮውን ኩንታል ቆጥሮ ካሁኑ ጋር እያወዳደሩ ኣድገን ነበር የህዝብ ብዛት ጉዳይ ጉድ ኣረገን እንጂ ኣይባልም።የዘጠና ሚሊዩን ህዝብ ቀረጥ ሰብስቦ በዚሁ ጉልበት ኣምርቶ ምርቱን ወደ ኣነስተኛ የህዝብ ቁጥር ዘርዝሮ ችግር ነው ማለት ኣግባብ ኣይደለም። በመሆኑም በኢትዮጵያ ውስጥ ከ ህዝቡ ብዛት ጋር ግብርናውም ስላላደገ እድገት በ ኢትዮጵያ ውስጥ ኣለ ማለት ኣይቻልም። በርግጥ የህዝብ ብዛትን በተመለከተ ለ ኢኮኖሚ እድገት ለሃገሪቱም ተስፋ (future) ጥላ የሚፈጥር በመሆኑ መንግስት የ ስነ ህዝብ ፖሊሲ መንደፍ ተግቶ ማስተማር ኣለበት።

በኣጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ሰዎች ያልፈጠረ የጥቂት ሰዎች እድገት ይኖር ይሆናል። እነዚህ ሰዎች ያበዱ ቤቶች ሊሰሩ ይችላሉ። ያ ማለት ግን ኣገር ኣደገ ማለት ኣይደለም። በ መጀመሪያ ደረጃ ኣገር የሚባለው ጽንሰ ሃሳብ ራሱ የ ቆመው በ ማጆሪቲ ነው። ሰፊው ህዝብ ነው የ ሃገር መገለጫው፡፡ ኣጠቃላይ በ ማክሮ ደረጃ ኣድገናል ከተባለ እድገቱ ሃገራዊ ነው ማለት ነው። ሃገራዊ ከሆነ ደሞ ሰፊውን ህዝብ ያቅፋል ማለት ነው። በ ዴሞክራት ሃገሮች የኢኮኖሚ እድገቱ ብዙና ሰፋ ያለ መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች የሚፈጥሩት ኣንዱ ልባቸው የዴሞክራሲ ጽንሰ ሃሳብ መገለጫው የዚሁ የማጆሪቲው ህይወት በመሆኑ ነው።

በ ኣጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ኢንፍሌሽን በተከታታይ ኣመታት እጅግ በጣም ከፍተኛ ና ከፍተኛ በሚባል የኢንፍሌሽን ሬንጅ ውስጥ በመሰንበቱ ዜጎች ሲሰቃዩ ይታያል። ባለፈው ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ኣቶ ሃይለ ማርያም ደሳለኝን ኣንድ የፓርላማ አባል የጠየቁ ሲሆን ጥያቄያቸው ትክክል ነው። ህዝቡ ይህ እድገት የሚባለው ነገር የዜጎችን ኑሮ የሚያሻሽል ኣይደለም ወይ? እያለ ካማረረ ኢንፍሌሽኑ የድህነት መገለጫ መሆኑን ያሳያል። ኣቶ ሃይለማርያምም ጥያቄውን ሊያዩት የሚገባው ኢንፍሌሽኑ የመጣው በ እድገታችን ነው ወይስ በ ህዝብ ብዛት የተነሳ የ ኣቅርቦት ችግር በሚል ሰሌት ኣይደለም። ኣማካሪዎቻቸው በ ያዝነው እድገት ምክንያት ነው የመጣው ቢሏቸው እድገቱን ሊያቆሙት ነው? በህዝብ ብዛት ምክንያት ምርቱ ኣላደገም ሊሉም ኣይጠበቅም።
ምን ማለትስ ነው? የተጠየቁት ጥያቄ ኢንፍሌሽኑን ባለበት ከማስቆም ኣልፎ ሄዶ ትዳር የማሸነፍ ኣቅም መዳከምን የሚያሳይ ነው። ኣሁን ያለውን ኢንፍሌሽን ቢያስቆሙም ለረጅም ጊዜ ሰፊው ህዝብ በሩጫው መስመር ላይ ወደ ሗላ ስለቀረ ከባድ ማስተካከያ ይጠይቃል።

እንግዲህ ኢንፍሌሽንን በሁለተኛው ትርጓሜ ካየነው እድገት የሚያመጣው ኣለመሆኑን እንረዳለን። ይህ ማለት ግን እድገትን ተከትሎ የገበያ ማሻቀብ ኣይታይም ማለት ኣይደለም ብለናል። ይህ ነገር ሊከሰት ቢችል ኣይገርምም። ይሁን እንጂ እድገት መጥቶ ግን በኢንፍሌሽን ምክንያት የዜጎች ኑሮ ወደ ሗላ ከሄደ እድገትን ሳይሆን ድህነትን የሚጠቁም፣ የ አቅርቦት እጦትን የሚያጋልጥ ክስተት ነው የሚሆነው። ኢትዮጵያም የገጠማት ነገር ይህን ይመስላል።

እግዚኣብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

ኣስተያየት ካለዎ እነሆ ኢሜየል ኣድራሻዬ
geletawzeleke@gmail.com

ሃይማኖት የግል ሃገር የጋራ ነው

Monday, December 17th, 2012

ይህን ኣባባል ስንቀባበል የኖርነው ያለ ምክንያት ኣልነበረም። ሃገራችን ብዙህነቷ የሚገለጸው በ ቋንቋና በ ባህል ብቻ ሳይሆን በ ሃይማኖትም በመሆኑ ነው። ብሂሉ ተቻችለን መኖር እንዳለብን ቃል የምንገባበት፣ የሃይማኖት ነጻነታችን የ ግል ሆኖ ኣገራችን ግን የሁላችን መሆኑዋን የምናጸናበት ኪዳን፣ የ ኣንድነት ጉዟችን ደሞ ስንቅ ነበር።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህን ትልቅ ኣላማ የሚያናጋ ሁኔታ ሲፈጠር ይታያል። የሚያሳዝነው በሃገራችን ከተነሱ ሃይማኖታዊ ግጭቶች መካከል እጅግ ብዙዎቹ ፖለቲካዊ ይዘቶች ያሉዋቸው መሆኑ ነዉ ።

በመሰረቱ ፖለቲካና ሃይማኖት የሚጣሉ ባይሆኑም ኣላማቸው ግን ኣይገናኝም። ሃይማኖታዊ ተቋማት ከዚህ ኣለም ባሻገር ሌላ ኣለም ኣለ ወደዚያ ሄጄ ዘላለም እኖራለሁ የሚል ዋና ግብ ያነገቡ ሲሆን ፖለቲካ የዚህ ኣለም ጣጣ በመሆኑ ለየብቻ መሄድ ኣለባቸው።

ከሁሉ በላይ ግን መንግስት ከሃይማኖት ጣልቃ ገብነት መቆጠቡ የሚጠቅመው ራሱን ነው።የ ሃይማኖት ተቋማት በ ህብረተሰብ ህይወት ውስጥ ካላቸው የጎላ ጠቀሜታ መካከል ኣንዱ የፍትህ ስርዓቱን በመደገፉ ረገድ ያላቸው የጎላ ሚና ነው። ለምሳሌ በሃገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ስናይ ኣንድ ሰው ለ ምስክርነት ወደ ፍርድ ቤት ሲሄድ በ መጀመሪያ እውነት ለ መመስከሩ ቃል የሚገባው ህገ መንግስቱ ላይ እጁን ጭኖ ሳይሆን ክርስቲያን ከሆነ መጽሃፍ ቅዱስ ላይ ሙስሊም ከሆነ በቁራን ላይ ነው። ይህ የሚያሳየው ፍርድ ቤት ወይም የፍትህ ስርዓቱ ከ ሃይማኖት ጣልቃ ገብነት ነጻ ቢሆንም ግን በነዚህ ተቋማት ላይ መደገፉን ነው።

እነዚህ የ ሃይማኖት ተቋማት ኣባሎቻቸውን የሚያስተምሯቸው እሴቶች ለምሳሌ፣ ኣትግደል፣ በሃሰት ኣትመስክር፣ ኣታዳላ፣ ግፍ ኣትስራ፣ ወዘተ. የፍትህ ስርዓቱ ምሶሶዎች ናቸው። እነዚህን እሴቶች መንግስት በሌላ መንገድ ከሚያስተምረው የበለጠ በሃይማኖት ተቋማት በኩል ፍሬ ሲያፈሩ የበለጠ ሃይል ይኖራቸዋልና መንግስት የሃይማኖትን ተቋማት በ ኣክብሮትና በ እንክብካቤ ሊይዛቸው ይገባል።

መንግስት በሃይማኖት ኣስተዳደር ኣካባቢ እጁን ሲያጠልቅ ኣባላት መንፈሳዊ ሽታ እየራቃቸው ይሄዳሉ። ይሰጋሉ። በተቋማቸው ያላቸው መተማመን እየቀነሰ ሲመጣ ደሞ ዞሮ ዞሮ የሚጎዱት ተቋማቱ ብቻ ሳይሆኑ የፍትህ ስርዓቱም ነው።

ዜጎች ምንም ሃይማኖት ባይኖራቸው የሚኖራቸው የህሊና ህግ ያን ያህል ጠንካራ ላይሆን ይችላል። ምንም ሃይማኖት ከሌለ ምን ኣልባትም ገንዘብ ካለህ ሃምሳ የ ሃሰት ምስክር ለመሰብሰብ ላይከብድ ይችላል። በማህበራዊ ግንኙነት ጊዜ ተማምሎ የጋራ ስራ ለመስራት ኣስቸጋሪ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ይህ ማለት ግን ሃይማኖት የሌለው ሁሉ ኣይታመንም ማለት ኣይደለም። ኣሉ ኣንዳንድ ዳኞች ለ ሙያቸው የሚሞቱ ኣሉ ኣንዳንድ ፖለቲከኞች ለ ኣላማቸው የሚሞቱ፣ ይሁን እንጂ በሰፊው እንዳገር እንደ ህዝብ ስናስበው ሃይማኖት ጠቃሚ ሃገርን እንደ መልህቅ የሚያቆም ትልቅ የተከበረ ተቋም ነው።

ለነገሩ በሃገራችን መንግስት በ ሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ መግባት የጀመረው በ ደርግ ጊዜ ነበር። ደርጉ የ ሶሻሊዝምን ስርዓት እንገነባለን ብሎ ባበደበት ሰኣት “ጎታች” ብሎ ከፈረጃቸው ተቋማት መካከል ኣንዱ ነበሩ። ዝግ እያለ ገብቶ ቄሱን ሁሉ የጾም እንዲበሉ በማድረግ የ ኦርቶዶክስን ቤተ ክርስቲያን እምነት ሊያስጥል ሞክሯል፤ ጎድቷታልም። የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮችን በፊት ለፊት ሲገድልና ሲያስር እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

ኢህኣዴግ ሲመጣ የተሻለ ነገር ይመጣል ተብሎ ተገምቶ ነበር። በተለይ መንገላታት ያደከመው የፕሮቴስታንቱ ኣማኝ ኣንጻራዊ ነጻነት ያገኛል ተብሎ የታሰበ ቢሆንም ራሳቸው የኢህኣዴግ ካድሬዎች በፈጠሩት ቀውስ በተለይ በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል ብዙ የፕሮቴስታንት ና የ ኦርቶዶክስ ሰዎች ተጋጭተው ብዙ ብዙ ጉዳት ደርሷል።

ኣሁን ደሞ የዜጎችን ቀልብ በመልካም ስራ መሳብ ያቃተው መንግስት ዜጎች ልባቸውን የጣሉበትን ባህላዊና ሃይማኖታዊ ተቋማት እያሸተተ ዜጎችን ሊቆጣጠር ይፈልጋል። በተለይ በቅርብ ጊዜ የሚታየው የከፋ ነገር ደሞ በ ኢትዮጵያ ሙሲሞች ዘንድ መንግስት የሚያሳየው ኣስጸያፊ ጣልቃ ገብነት ነው። ይህ ችግር ብዙ መዘዞችን ለሃገራችን ያመጣል ተብሎ የሚታሰብ ሲሆን ኣንዱና ትልቁ ችግር ኣክራሪነትን ይወልዳል የሚለው ስጋት ነው።

የሃይማኖት ሰዎች የሃይማኖት ነጻነት ጥያቄ ሲያነሱ ፖለቲከኞች ለፖለቲካ መብት ከሚታገሉት የከረረና የመረረ ነው። ከሁሉም በላይ የሃይማኖት ደጃቸው ሲደፈር፣ ኣምላካቸው ሲያዝን ስለሚታያቸው ቁጣቸው ይበዛል። መስዋእትነት ለመክፈልም ቢሆን ለ ሃይማኖታቸው ለ ኣምላካቸው ቢሞቱ በሰማይ ብድራት ስላላቸው ኣይፈሩም።በመሆኑም በሃይማኖት በኩል የሚመጣ ቁጣ እንዲህ በቀላሉ ኣይበርድም። ከሁሉ የሚከፋው ግን በሃይማኖቱ ውስጥ ካሉ ኣባላት ውስጥ በጣም ኣጥባቂ ያልሆኑትን ወደ ሌላ ጽንፍ እየወረወራቸው እልህና ቁጣ ይሞሉና ኣክራሪ ኣሸባሪ ሊያደርጋቸው ይችላል። ጥያቄያቸው እየከረረ ሲሄድ ኣመጹ ራሱ ከሚፈጥራቸው ኣንዳንድ መሪዎች መካከል የሚነሳ ኣስተምህሮም ሊፈጠር ይችላል። ከሁሉም በላይ ሃይማኖታቸው ፖለቲካዊ ይዘት እንዲኖረው ማድረግ ይጀምሩና ኣክራሪነት እየተወለደ ሊመጣ ይችላል። ዛሬ በኣለማችን ያሉ ኣክራሪዎች የተወለዱት ከ መልካም ኣስተዳደር እጦት ከመብት ገፈፋ ጋር እየተያያዙ የመጡ ናቸውና፡፡

መንግስት ሊረዳው የሚገባው ነገር የ ሃይማኖት ጥያቄ የሚፈታው በፖለቲካዊ መንገድ ኣለመሆኑን ነው። ልክ የፖለቲካ መብት እንዳነሱ ኣይነት በቴለቪዥን “ህጉንና ህገ መንግስቱን ኣክብረው መኖር ኣለባቸው” የሚባል ፈሊጥ መልስ ኣይሆንም፡፡ ኣያስፈራቸውምም። የሃይማኖትን ችግር በሸምግልናና በትህትና በሃይማኖት ሰዎች በኩል መፍታት ያስፈልጋል። ኢህኣዴግ የ ሙስሊሙን ጤያቄ ሌሎች የ ህዝብ ኣመጾችን በሚያፍንበት የዘወትር መሳሪያው ሊያበርደው ኣለመቻሉን መረዳት ኣለብት።

እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!
geletawzeleke@gmail.com

ማን ጸሎት ያሳርግ

Sunday, November 11th, 2012

በ ለምለም ፀጋው

ወይ ነውር አይገዛው

አምልኮት ዓልነካው፤

የኢትዮጵያን ሰው ሁሉ

በቃሊቲ አጎረው።

ይድነቃችሁ ብሎ

በየሱስ ስም ማለ፤

የመለስን ወንጌል

እንደ ክታብ አርጎ

በአንገቱ ሰቀለ።

        ለሁሉም ለመሆን

        አዲሱ ምንስቴር በቃሊቲ ሳይቀር፤

        አርብ ሰኞ ሳይል

        አለ ዓላህ አክብር።

ምነው የኔ ወዳጅ

ጓዴ የጴንጤ አማኝ                                    

አያቴ ኦርቶዶክስ

የሚያምኑ በየሱስ

የዓባቴ ወገኖች

አሉ ብዙ እስላሞች

በክርስትና መልክ እስኪ ልጠይቅህ

በቃሊቲ ቦታ ቁርስ ምሳ ሲቀርብ

ማን  ጸሎት ያሳርግ

ብለህ ታውጃለህ

ዳዊትን ይደገም

ወይስ ቁርሃን ያቅራ

በዱር በገደሉ ለመብቱ ሲያቅራራ።

           ዐረ ባላህ በሉ ወይንም በየሱስ

        እስከመቸ ድረስ

        እንዲህ እንታመስ

አዳምጠኝ ይልቅስ ወሪውን ልንገርህ

ብቻውን አልቅሷል ዖሮሞው አባትህ

ለአማራዋ እናትህ

ተው እንጅ ዓትቀልድ ምነው ምኑ ነካህ

ከለቅሶው ያልደረስህ

አሁን ገና ገባኝ አላህን ፈርቶ ነው

ሰላም በማወጅህ

        ዐረ ባላህ በሉ ወይንም በየሱስ

        እስከመቸ ድረስ

        እንዲህ እንታመስ

 

© ለምለም  ጸጋው በስልምና ሃይማኖትም ሆነ መብታቸውን ለማስጠበቅ በመናገራቸው በእስር ቤት ለሚማቅቁ ሁሉ

(http://www.ethiomedia.com/assert/4785.html)

(http://www.youtube.com/watch?feature=endscreen&v=t6Agm1q_YpM&NR=1)

http://www.youtube.com/watch?feature=endscreen&NR=1&v=tOFOCAtXzx8

 

 

ለ እህቶቻችን ልንደርስ የምንችልባቸው 4 መንገዶች!

Monday, October 15th, 2012

በኣረብ ኣገራት ለግርድና የሚሄዱትን እህቶቻችንን የሚደርስባቸውን ስቃይ መናገር መነሻዬ ኣይደለም። ያልፍልኛል፣ እናት ኣባቴን እጦራለሁ እያሉ ወደ ሊባኖስና ሌሎች የኣረብ ገልፍ ኣገራት የሚጎርፉት እህቶቻችን ከሰባዊነት ደረጃ ዝቅ ብለው ሲሰቃዩ ሌላው በተለያየ የኣለም ክፍል ያለው ኢትዮጵያዊ ከንፈሩን ከመምጠጥ ያለፈ ብዙ ነገር ሲያደርግ ኣይታይም። እግዚኣብሄር ይባርካቸውና የተለያዩ ሰባዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የቻሉትን ሁሉ እየታገሉ ነው። ግን ኢትዮጵያዊው የበኩሉን ለመወጣት ከማንም በላይ የሞራልም የዜግነትም የውዴታ ግዴታ ኣለበት።

የዛሬው ጽሁፌ በሌላው ኣለም ያለው ኢትዮጵያዊ ምን ሊያደርግ ይችላል? በሚል ተግባራዊ ዘዴዎችን ለመጠቆም ነው።
በመሆኑም ለእህቶቻችን በሚከተሉት መስመሮች ልንደርስላቸው እንችላላን።

1) ለወገን ለሃገር ተቆርቋሪ በሆኑ ኢትዮጵያዊያን የተቋቋመው ኢሳት ቴሌዚዥን ድርጅት በኣፋጣኝ መቀመጫውን ሊባኖስ ያደረገ የሪፖርተር ቡድን ሊልክ ያስፈልጋል። ይህ ቡድን በየጊዜው የሚደርሰውን በደልና እንግልት እየዘገበ በማጋላጥ ችግራቸውን ሊቀንስ ይችላል። ኣንዱ ትልቁ ችግራቸውም በየሜዳው እየሞቱ ወደ ሚዲያ ስለማይወጣ ነው። ይህ ቡድን በየጊዜው በሚያደርገው ኢንቬስትጌቲቭ ሪፖርት ለኣለም ኣቀፉም ሆነ ለ ኢትዮጵያዊያን ያሳውቃል። ኣንዱ ችግር የኢንፎርሜሽንም ነው። ባለፈው እህታችን ኣለም ደቻሳ የሞተች ጊዜ ነው ትንሽ የተደናገጥነው። ያ ወደ ሚዲያ ስለወጣ እንጂ ሚዲያ ሳያውቃቸው የሚገደሉ የሚሰቃዩ ብዙ ናቸው።

ባለፈው የ ሂውማን ራይት ዎች ባውጣው ዘገባ ላይ እንደሚያሳየው በየ ሳምንቱ ኣንድ የቤት ውስጥ ሰራተኛ ተፈጥሮኣዊ ባልሆነ መንገድ ይሞታል። እንግዲህ ልብ በሉ በሊባኖስ ውስጥ ወደ 200 ሺህ የሚጠጋ የቤት ውስጥ ሰራተኛ ያለ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ከ 60 እስከ 70 ሺህ የሚሆኑት ኢትዮጵያዊያን ናቸው። ይህ ማለት በየ ወሩ ሁለት የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ወይ ተገለው፣ ወይ ታመው ፣ወይ የሚያሳክማቸው ኣጥተው፣ ወይ ራሳቸውን እንዲያጠፉ ተገደው ይሞታሉ ማለት ነው። ከዚህ የከፋ ነገር የለምና ኢሳት ባስቸኩዋይ ደርሶ ወገንተኛነቱን፣ ኢትዮጵያዊነቱን ማሳየት ኣለበት።

2) በ ኣሜሪካን ኣገር ኣዲስ የተቋቋመው የሴቶች መብት ድርጅት ኣስቸኳይ የቤት ስራው ሊሆን የሚገባው የህግ ባለሙያ የያዘ ኣንድ ቡድን መላክ ነው። በርግጠኝነት ለመብታቸው ለሚሟገት በደላቸውን ወደ ብርሃን ለሚያወጣ ድርጅት ወጪውን እንደሚሸፍኑ እምነቴ ጽኑ ነው። ከሚያገኙዋት ጥቂት ገንዘብ ላይ እያዋጡ ወጪውን ሊሸፍኑ ስለሚችሉ ድርጅቱ በባጀት በኩል ስጋት የሚገጥመው ኣይሆንም። የተጨነቁ እህቶች ኣለን የሚላቸው ካገኙ የሚከፈለውን መስዋእትነት ይከፍላሉ። እነዚህ እህቶች ከ ኤምባሲ ያጡትን የምክር ኣገልግሎትና ፍቅር ይህ ለመብታቸው የቆመ ድርጅት ይክስላቸዋል።

3) ለሲቪክ ማህበራትና ለ ፓለቲካ ድርጅቶች።
ለግርድና የሄደችው እህታችን ስትሰቃይ ዛሬ ስትገደል ከንፈራችንን እየመጠጥን ችግሩ የሚፈታው የችግሩ ምንጭ የሆነው ኣምባገነን መንግስት ሲወገድ ነው ማለት ኣግባባ ኣይደለም። እሱን ማን ኣጣው? ኣሁን በመሃል ግን ድምጻቸው ታፍኖ ተዘልለው የሚያነቡትን እህቶች ኣይዙዋችሁ ማለት ግፋቸውን ማጋለጥ በርግጥ የህዝብ ፍቅር ያለው ድርጅርት ተግባር ነው ። የነሱን መከራና ግፍ ለፓለቲካ ፍጆታ መጠቀም ፈጽሞ ሊሆን ኣይገባም። በመሆኑም ሁለቱም ኣይነት ድርጅቶች በመገናኛ ብዙሃኖቻቸው ይህን በደል ማውጣት ማሳየት ሰላማዊ ሰልፍ ማቀድ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ሌላው ደሞ ለዚህ የዳረጋቸውን ኣስከፊ ስርኣት ለመለወጥ እንዲችሉ ሊያደራጁዋቸውም ይገባል።

4) ሌላው ከፖለቲካው ተገልሎ ያለው ኢትዮጵያዊ በሙሉ በያለበት ድምጹን በተለያየ መንገድ ማሰማት ኣለበት። በፌስ ቡክ በሰልፍ ወዘተ. ተቃውሞውን ማሰማት ኣለብት። ኣንዲት ኣረብ ኣገር የምትኖር እህታችን በስሜት ስትናገር እህቶቻቸውንና ሴቶቻቸውን ኣውጥተው ለግርድና የሰጡ ወንድሞች እንደ ኢትዮጵያዊያን ኣላየሁም ብላለች። ድሃ ኣገር እኛ ብቻ ኣይደለንም ግን እንደኛ ሴቶች ለግርድና ሄዶ የሚሰቃይ የለም ብላለች። በመሆኑም ኣለማቀፋዊ ተቃውሞ በማድረግ እህታችንን ልንደገፍ ይገባናል።
እነዚህ ከፍ ሲል ያነሳሁዋቸው ነጥቦች በውነት በጣም ቀላል ልንሰራቸው የምንችላቸው ናቸው።

እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!
ገለታው ዘለቀ

ህወሃት በምን ተጠምዶ ይሆን?

Wednesday, July 25th, 2012

ይህ ጽሁፍ ኣቶ መለስ ታመዋል፤ ህመማቸው ለሞት ይሰጣል ወይም ቢድኑም ወደ መደበኛ ስራቸው ለመመለስ ኣይችሉም የሚሉትን መላምት የተመረኮዘ ኣስተያየት ነው። ታዲያ ይህ ዜና እውነት ከሆነ በዚህ ጊዜ ህወሃት በምን ሁኔታ ላይ ይገኝ ይሆን? ብለን እንድናስብ ማድረጉ ኣይቀርም።

ባለፈው ጊዜ “ኣቶ መለስ ሲሄዱ ምን ይፈጠር ይሆን?” በሚል ርእስ ስር ባነሳነው ግምት ላይ የ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሄድ ለለውጥ ትልቅ በር መሆኑን ጠቁመናል።ኣውሸልሽሎ የሚጀመር ኣስተዳደር ሩቅ እንደማይሄድም ጠቁመናል:: ብዙ ሰውም እንዲሁ ገምቱዋል። ታዲያ በኣቶ መለስ መሄድ የተፈጠረውን ክፍተት ለመድፈንና ስርዓቱ ሳይቀየር ኣውሸልሽሎም ቢሆን እንዲሄድ የሚሹ ኣንዳንድ ጽንፈኛ የህወሃት ኣባላትም ላይተኙ ይችላሉ።

ካለፉት ጊዚያት የህወሃት ባህርያት ተነስተን ስንገምት ባሁኑ ሰኣት ህወሃት በከባድ ሽምጥ ስብሰባ ላይ መሆኑ ይሸተናል ። ነባር የህወሃት ታጋዮችን ሳይቀር ካራቱም ማእዘናት ሰብስበው የተጣሉ ሁሉ ታርቀው በውይይት ላይ መሆናቸው ኣይቀርም። ታዲያ እንዴው ለህዝብ በተሰወረ ሁኔታ የሚያደርጉት ስብሰባ ላይ ምን ምን ጉዳዮችን ሊያነሱ ይችሉ ይሆን? ብለን ደሞ ማሰባችን ኣይቀርም። ክቻልን በዚህች ኣጭር ጽሁፍ የምናነሳው በዚህ ስበሰባ ላይ ሊነሱ ይችላሉ ብለን የገመትነውን ሲሆን መለወጥ እየፈለጉ ዋስትና ለሚፈልጉ ቡድኖች ደሞ ጥቂት የዋስትና ፍንጭ ለማሳየት እንሞክራለን።

በመጀመሪያ በኣጠቃላይ የህወሃት ስብሰባ ብዙ ሰው እንደሚገምተው ሁለት የተለያዩ ኣሳቦች የሚንሸራሸሩበት ሊሆን ይችላል። ኣንዱ ቡድን የተወሰነ ለውጥ ካላደረግን በዚህ መቀጠል ኣንችልም የሚል ሊሆን ሲችል ሌላው ደሞ በዚሁ መቀጠል ኣለበት የሚል ይሆናል። በኣጠቃላይ ያለፈውን ሀያ ኣመት ስራቸውን ሲገመግሙ ግን መቸም ጥሩ ሰርተናል የሚሉ ኣይመስልም። ምክንያቱም ጥሩ እንዳልሰሩ ያውቃሉ ህዝቡም ያውቃል። በሚዲያ ጥሩ ሰራን ቢሉም ለብቻቸው ሲሰበሰቡ ግን የሆድ የሆድ ሲያወሩ ግን ጥሩ እንዳልሰሩ መስማማታቸው ኣይቀርም። ታዲያ በዚህ ላይ ይስማሙ እንጂ በቀጣይ ጉዳይ ላይ ለሁለት መከፈላቸው ኣይቀርም። ከፍ ሲል እንዳልነው ኣንዱ እንለወጥ የተወሰነ እንራመድ የሚል ሲሆን ሌላው ቡድን ደሞ ለመለወጥ የሚያሰፈሩትን ጉዳዮች ኣንስቶ መከራከሩ ኣይቀርም። ለዛሬ ይሄ ቡድን ሊያነሳቸው ይችላል ብለን የገመትነውን ለውይይት ኣቅርበን ዋስትናዎቹን በጣም ውሱን በሆነ መልኩ እንጠቁማለን።

እነዚህ ወገኖች ከሚያነሱዋቸው ሃሳቦች መካከል
1) የሃብት ጉዳይ
እንደሚታወቀው በባለፉት ሃያ ኣመታት ጊዜ ውስጥ የህወሃትን የበላይነት ለማቆየት ከተመረጡት ዘዴዎች ኣንዱ የኢኮኖሚ የበላይነት ነው። ታዲያ በዚህ ጊዜ ኣንዳንዱ በደንብ እየታሰበበት ኣንዳንዱ ደሞ ድንገት ሰርኣቱ በፈቀደለት ክፍተት እየታገዘ ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ ከፍተኛ ሃብት ኣካብቱዋል። የኣገሪቱ ሃብትም በተለያዬ ዘዴ ወደ ኅወሃት ድርጅቶችና ደጋፊ ግለሰቦች የዞረበት ሁኔታ ጎልቶ ይታያል። በመሆኑም እነዚህ በያዘነው እንቀጥል የሚሉ ወገኖች እነዚህን ሃብት የተከማቸባቸውን ድርጅቶችና ግለሰቦች እናስጠቃለን ለውጥ ከመጣና ተቃዋሚዎች ስልጣን ከያዙ እነዚህን ሃብት የተጠራቀመባቸውን ድርጅቶች ያፈርሳሉ ማፍረስ ብቻ ኣይደለም ያላግባብ የበለጸግህ ነህ በማለት ሊያሰቃዩዋቸው ሊቀጡዋቸው ይችላሉ የሚል የስጋት ኣሳብ ሊነያነሱ ይችላሉ።
ዋስትናው
ለነዚህ ወገኖች ስጋት ዋስትና ኣለ። ይህ ዋስትና በቃ ያለፈው ኣልፉዋል የያዝከውን ይዘህ በየቤትህ እደር ከሚል ጀምሮ እነሱ እንደሚያስቡት ልክ ለውጥ እንደመጣ ባለፉት ሃያ ኣመታት ውስጥ ከመንግስት ጋ ንክኪ ኖሮት ያላግባብ የበለጸገውን ሁሉ ማንቁርቱን እየተያዘ ሃብቱን የሚያስረክብበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ኣይደለም። እነዚህ ሁለቱም ኣስተሳሰቦች ትንሽ ኣርቆ የማሰብ ችግር ያለባቸው ሳይሆኑ ኣይቀሩም።

ዋስትናው ይሄ ኣይደለም። ለነዚህ ወገኖች ትልቁ ዋስትና ኣዲስ የሚፈጠረው ስርዓት ሃብትን በችኮላ የሚበጣጥስና የሚያፈርስ ኣይሆንም። እነዚህ ያላግባብ በለጸጉ የተባሉ ቡድኖችም ሆኑ ግለሰቦች ችግር ችግሩ የግለሰቦቹ ወይም የቡድኖቹ ሳይሆን የስርዓቱ በመሆኑ ይህ ነገር የሚስተካከለው በሌላ ሰርዓት ነው።

በደርግ ጊዜ ኣንድ ታሪካዊ ስህተት ተፈጽሟል። ይሄውም የነበረውን የሃገሪቱን ሃብት ሲያዛውር በስርነቀል መልክ ስለ ነበረ ጥበብ በጎደለው መልክ ተከናውኗል። ያላግባብ በጭቁኑ ደምና ላብ በልጽጋችሁዋል የተባሉ ሁሉ እስር ቤት ገቡ ተገደሉ ሃብታቸውን ቀበሌ ወሰደው። እንዲህ ኣይነት የሃብት ዝውውር ካሁን በሁዋላ በሚመጣ ለውጥ ጊዜ ኣስፈላጊ ኣይደለም። እንዳልነው ብልጽግናው ከስርዓት ችግር ጋር ተያይዞ የመጣ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው። በዚህ ወቅት ያላግባብ የበለጸጉ ብቻ ሳይሆን ያላግባብ ባድሎ የትምህርት እድል እያገኙ የተማሩም ይኖራሉ። ኣዲሱ ስርዓት ያላግባብ ተምረሃልና መልስ ወይም ወንድምህ ኣይማርም ኣይልም። ይልቅ ኣዲሱ ስርዓት ሊያደርግ የሚገባው ምንድነው በኣንድ ኣካባቢ የተከማቸውን ሃብት በተለያዩ የሃብት ስርጭት ዘዴዎች (distribution of wealth mechanisms ) በመጠቀም ተመጣጣኝ እድገትን ማምጣት ነው። ይህ የሃብት ስርጭት ፖሊሲ ያለውን ሰፊ የሃብት ልዩነት እያጠበበ ደሞ የተከማቸውን ገንዘብ ወደ ልማት እንዲዞር ሁኔታዎችን እያመቻቸ የሚሄድ ስርዓት ነው። በመሆኑም በውስጣቸው ለውጥ እየተሰማቸው ነገር ግን ይህን ስጋት ያዳበሩ ሁሉ የሚመጣው ለውጥ በግብታዊነት የሃገሪቱን ሃብት የሚያፈራርስ እንደማይሆን መገመትና ለዚህም መታገል ነው ዋስትናው። ይህ ስጋት ያለባቸው የህወሃት ደጋፊዎችና ኣባላት የሚመጣው ለውጥ በዚህ መንገድ ተሳልጦ እንዲሄድ ቢያደርጉና ለዚህ ቢሰለፉ ስጋቱን ቀንሰው የረጋ እንቅልፍ ይተኛሉ።በኣዲሱ ስርዓት የሃብት ዝውውሩ የኣሁኑን ትውልድ ብቻ ሳይሆን የሚመጡትን ትውልዶች ሁሉ ያገናዘበ መሆን ኣለበት። ሃገር ከገንዘብ በላይ ነው። ገንዘበ ኣላፊ ጠፊ ነው፡፡ በሃቀኛ ካፒታሊሰት ስርኣት ውስጥ ኣንድ ሰው ሃበታም ሰለሆነ ባንድ ጊዘ ዘጠኝ ልብስ ለብሶ ኣይሄድም፡፡ ሃብታም ሆነ ማለት ሃላፊነት ተሸከመ ማለት ነው፡፡ ደሞ ከሁሉም በላይ ይህቺ ኣገር የኛ ብቻ ኣይደለችም ገና ሊመጡ ያሉ እልፍ ትውልዶች ሁሉ የሚኖሩባት ናት። በመሆኑም ባለፈው ሃያ ኣመት በተነጣጠቅነው ገንዘብ ኣስረክብ ኣላስረክብም ኣገር ኣይፈርስም። ከዚህ ይልቅ ከፍ ሲል እንዳልነው የተለያዩ ፍትሃዊ የሃብት ስርጭት ዘዴ በመጠቀምና የተጠራቀመውን ገንዘብ በልማታዊ ስራ ላይ እንዲውል በማበረታታት ስጋቱን መቀነስ ይቻላል፡፡

2) የብሄሮች ማንነት ጉዳይ

ይሄም መልኩን ለውጦም ይሁን በቀጥታ ሊነሳ የሚችል ሃሳብ ሊሆን ይችላል። በኣንዳንድ ቅን ኣባላት ዘንድ ህወሃት ለ ብሄሮች ማንነት የሞተ ሲሆን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስልጣን ከያዙ በኣንድነት ስም የብሄሮች ማንነት ሊጨፈለቅ ይችላል ይህም የሞትንለትን ኣላማ ያፍርሳል የሚል ይሆናል። እንደነዚህ ወገኖች እምነት የባህላዊ ቡድን ኣስተዳደር(Ethnic federalism) የተሻለ ሲሆን የሚመጡት ተቃዋሚዎች ግን ይህን ኣይቀበሉም የሚል ስጋት ይኖራል ።

ዋስትና
ለዚህ ዋስትናው ሃገሪቱ በሁለቱም ኣቅጣጫ የምታድግበትን ስርዓት መዘርጋት ነው። ወደላይ የተለያዩ ብሄሮች ባህላቸውን ቋንቋቸውን ጠብቀው የሚያድጉበትን የትምህርትና የባህል ፖሊሲ መንደፍ ወደጎን ከሌሎች የሃገሪቱ ብሄሮች ጋር እሴት የሚካፈሉበትን ፖሊሲ መዘርጋት ነው። ዋናው መረዳት መሆን ያለበት ለውጥ ሁል ጊዜ በህብረተሰብ ላይ ይሰራል። ለውጥ በባህል በቋንቋ ይሰራል። ይህን ታሳቢ ያላደረገ የፖለቲካ ቅንዓት ሳይንሳዊነትና ተፈጥሮዓዊነት ስለሚጎለው ለውጥን መቀበል ያስፈልጋል።

3) ለውጡን ተከትሎ የስነ ልቡና ችግር ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት

ህወሃት ሁልጊዜ ራሱንም ሆነ ሌላውን ህዝብ የሚያየው ከውስጥ ወደ ውጭ ብቻ ነው። ይህ ተፈጥሮው ህዝብ ያላሳበውን እንዲያስብ በህዝብ ልብ ውስጥ የሌለውን ኣለ ተቀብሮ ነው ብሎ እንዲሰጋ ያደርገዋል። ባለፉት ኣመታት ኣብዛኛው ድል የኣንድ ኣካባቢ እንደሆነ ኣድርጎ የማቅረብ ኣዝማሚያ ታይቱዋል። ይህ ስነ ልቦና በርግጥ በተወሰነ ደረጃ ወደ ተራው ህዝብም ሳይሄድ ኣልቀረም። ካጠቃላዩ የፖለቲካ ድባብ ኣንጻር ዜጎች ራሳቸውን የሚገልጹት በብሄራቸው ሲሆን ይህ ስነ ልቡና ወደ ምን ኣመራ የኣመራር ችግሮች ሲከሰቱ የባለስልጣናቱ ኣካባቢ ሰዎች በግድ እንዲደግፍ ወይም ነቀፌታዎቹን እንዲደብቁ እንዲያፍሩ ያደርግ ጀመር። ከዚህ የተነሳ በኣስተዳደር ጉድለት ዙሪያ የሚነሱ ውይይቶች ሁሉ ወደ ብሄር እየሮጡ እየተጣበቁ ስለሚያስቸግሩ ኣምክህኖታዊ ውይይት ጠፋ። ኣሁንም ለውጥ ቢመጣ የህወሃት ደጋፊዎች በሌላው ዘንድ ከዘር ጋር በተያያዘ መሳለቂያ እንሆናለን። ተቃዋሚዎች ስልጣን ሲይዙም በተለይ በኛ ባህላዊ ቡድን ላይ ከፍተኛ የስሜት ስብራት ይደርስበታል ብለው የሚከራከሩ ይኖራሉ።

ዋስትናቸው
በመጀመሪያ ደረጃ ይህ ችግር ህወሃት በራሱ መነጽር ሲያየው የተጋነነ ያደርገዋል እንጂ የሚፈራውን ያህል በህዝቡ ልብ ውስጥ ኣይኖርም። የኢትዮጵያውያን ጥያቄ ወልደ ኪዳን መጣ ኣየለ ወይም ድሪባ ኣይደለም። ህዝቡ የሚሻው ከድህነት የሚያላቅቀው በቀን ሶስቴ የሚበላበትን መንገድ የሚያሳየውን መሪ ነው። ይህ ልቡ በተለያዩ ጊዚያት ታይትዋል። ከህወሃት ሰዎች የተሻሉ የሚላቸውን የሚደግፍበት ኣንዱ መነሻ ህወሃት የሚያየውን ያህል ህዝቡ በዘር ፖለቲካ መነጽር የሚያይ ኣለመሆኑን ነው። ሌላው ዋስትና ህወሃት ራሱ ኣዲስ ለሚመጣው ለውጥ ሲሰለፍና ለለውጥ ሃዋርያ ሲሆን ይሄ ከለውጥ በሁዋላ ሊከሰት ይችላል ተብሎ የሚፈራው የስነ ልቦና መጎዳዳት ይጠፋል። ድሉ የሁሉም የጋራ በመሆኑ ማንም በማንም ላይ ለመሳለቅ የሚስችል ከባቢ ኣይኖረም፡፡

4) የባንዲራ ጉዳይ
ይሄም የሚነሳ ሊሆን ይችላል። ኣንዳንድ ወገኖች መለወጡን የመንግስት ሽግሽጉን ኣምነው ነገር ግን ባንዲራው እንዲቀጥል የሚፈልጉ ይኖራሉ። ይህ ባንዲራ ቀድሞ በነበረው ላይ ሌላ ምስል ተልጥፎበት ይገኛልና በህይወት እያለን ሊለወጥ ኣይችልም የሚል ስሜት ይኖራል። የትግላቸው ተምሳሌት ኣመጣን ለሚሉት ለውጥ ታሪክ ኣድርገው የሚያዩ ሁሉ የሚመጣው ተቃዋሚ ይህን የመለወጥ ፍላጎት ሊኖረው ይችላል የሚል ነገርም ሊነሳ ይችላል።
ዋስትና
በመሰረቱ ደርግም ሲመጣ የሃይለ ስላሴን ባንዲራ ቀይሯል። ሁሉም በታሪክ መዝገብ ይመዘገባል። ዋናው በታሪክ መዝገብ መቀመጡ ሲሆን ትውልድ እያለፈ ትውልድ ሲተካ የሚሆነውን ኣናውቅም። ዋናው ግን ህዝብ በዚሀ ላይ ልቤ ያርፋል ካለ ማስገደድ ኣይቻልም። በመሆኑም የባንዲራ ጉዳይ ሲናገሩ ጎሮሮኣቸው ላይ ሳግ የሚተናነቃቸው ካሉ ሃላፊነቱ የህዝብ መሆኑን ማወቅ ነው ልባቸውን ሊያሳርፍ የሚገባው።

5) እልህ
ሌላው ኣገራችንን የጎዳው ትልቁ ችግር መንግስት እንደ መንግስት ያለማሰቡ ነው። ኣንዳንድ ግለሰቦችም ይሁኑ ቡድኖች በመንግስት ላይ ነቀፌታ ሲሰነዝሩ መንግስት መንግስትነቱን ወዲያ ይወረውርና በግለሰቦች ብሽሽቅ ውስጥ ገብቶ ይታያል። ለዚህም የመንግስትን ተቋማት ሳይቀር መሳሪያ እያደረገ ሲጠቀም መቆየቱ ያሳዝናል። መንግስት ልበ ሰፊ ሆኖ እንደ መንግስት ካላሰበ በዚህ ቀላል በሚመስል ብሽሽቅ ኣገር ሊፈርስ ይችላል። ኣሁንም በዚህ በህወሃት ስብሰባ ላይ ኣንዱ በግለት ሊነሳ የሚችለው ነገር የባህል ቡድንን ካባ ለብሶ ረግጠንም ቢሆን መግዛት ኣለብን የሚጮኸው የከሌ ብሄር ነው፣ እኛን ትግሬዎችን ንቆ ነው ወይ? የሚሉ ፉከራዎች ስብሰባውን ኣምክህኖታዊነት እንዳይኖረው መፈታተኑ ኣይቀርም። ለዚህ ነገር ምንምን ኣይባልም። ኣባካችሁ ይህቺ ኣገር የኛ ብቻ ኣይደለችም ኣገር በ እልህና በቁጣ ኣይፍረስ የሚሉ ሽማግሌዎችን እንዲሰጠን መጸለይ ነው። ሃገር ሲመሩ ከነዚህ ስሜቶች መራቅ ነው ትልቁ የሃላፊነት ስሜት መለኪያው።

እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!
ገለታው ዘለቀ
geletawzeleke@gmail.com

አቶ መልስ ሲሄዱ ምን ይፈጠር ይሆን?

Wednesday, July 18th, 2012

የ ኣቶ መለስን መሄድ ተክትሎ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ባሉ ባለስልጣናት ዘንድ ምን ሊፈጠር ይችል ይሆን? ወታደሩስ ምን ያስብ ይሆን? መቼም ህዝቡ ለውጥ በሃይል ፈልጓልና ከሳቸው መሄድ በሁዋላ ሊነሱ በሚችሉ ትርምሶች ጊዜ ብዙዎች የሚሰጉበት የብሄር ግጭት ይፈጠርስ ይሆን? በሚሉ ሃሳቦች ዙሪያ ጥቂት ግምቶች እንስጥ።ለነዚህ ከባድ ጥያቄዎች መልስ ባይኖረንም እንገምት።

የኣቶ መለስ መሄድ በፓርቲዎቻቸው ውስጥ ምን ኣንድምታ ይኖረው ይሆን?
በእንበል ገበያ ሆነን ኣሁን ኣቶ መለስ ቢሞቱ የሳቸው ሞት በኢህኣዴጎች ዘንድ የኣንድ ሰው ሞት ተደርጎ ሊወሰድ ኣይችልም። ተጽእኖኣቸው እጅግ ጉልህ ነው።ሁሉ በሁሉ የሆኑ ስልጣን ሁሉ ያለ ልክ የተማከለበትን ስርዓት የፈጠሩ ናቸው። ባለፉት ሃያ ኣመታት ከህወሃትና ኢህኣዴግ ትንሽ ሻል ይላሉ ኣገር ይወዳሉ የሚባሉትን በሙሉ ኣጭደው በልተው ጨርሰዋል። ሃይል ቀስ እያለ በጃቸው የገባ ሲሆን ድርጅቶቹ ያለሳቸው ባዶ ናቸው። በመሆኑም ኣቶ መለስ ቢሞቱ ድርጅቶቹ ኣንድ ታጋይ ነው የሞተብን ማለት ኣይችሉም። ኣዋቂ ናቸው እንዲባሉ የተሻለ እውቀት ያላቸውን ኣባረው መተማመን የሌላቸውን በእውቀት የደከሙትን ወደ ላይ ሰብስበው የኖሩ ሰው ናቸው።ብዙዎቹ ባለስልጣናት የሚሰራውን እንኳን የማያውቁ ኣሻንጉሊቶች ናቸው። በሳቸውና በቅርብ ርቀት ባሉ ባለስልጣናት መካከል ሰፊ የስልጣን ልዩነት የነበረ ስለሆነ ይህ ክፍተት ኣቶ መለስ ድንገት ቢያርፉ ተናቦ የሚመጣውን ህዝባዊ ኣመጽ ተቋቁሞ የሚቀጥል መንግስት መመስረት ኣያስችላቸውም። ኣውሸልሽለው ሊጀምሩት ቢሞክሩም ሩቅ የሚያስኬድ ከባቢ የላቸውም። የኢትዮጵያ ህዝብም ይህን ተንኮል በጅጉ የሚቃወመው የሚያሳምጸው ሲሆን በልመናና በሰባዊ መብት ጥሰት ጆሮውን የያዘው ኣለማቀፍ ማህበረሰብም ቢሆን በዚህ የጉልቻ ልውውጥ የሚረካ ወይም የሚደለል ኣይሆንላቸውም። ኣንዱ ይሄ ነው። ሌላው ደሞ በመካከለኛ ስልጣን ላይ ያሉን የኢህኣዴግ ሰዎች ስናይ ኣሁን ኣቶ መለስ ቢሞቱ ወደ ተለያየ ጥግ የሚበተኑ ይመስላል። ኣንዳንዶቹ የነበራቸውን ሚናና መጋላጥ(exposure) እያዩ የነብር ጅራት ጨብጠናልና ያበጠው ይፈንዳ ኣንዱን ተክተን እንቀጥል ከሚሉት ተስፋ ከቆረጡት የላይኛው ባለስልጣናት ዘንድ ወስዶ የሚጥላቸው ሲሆን ኣንዱ ደሞ ለውጥ ቢመጣ ነጻ ፍርድ ቤት ቢቆም ኣይበላኝም የሚል ኣንጻራዊ የሆነ የተሻለ መተማመን ያላቸው ደሞ ከሚመጣው ለውጥ ጋር ይሰለፋሉ። ኣንዳንዶች ደሞ በግል የሰሩትን እየቆጠሩ ኣገር ጥሎ መጥፋትን ኣማራጭ ያደርጋሉ። ሌሎች ደሞ በመሃል እየሰፈሩ ለውጡን ለመደገፍ ዋስትና የሚሰጣቸውን ፍለጋ ኣይናቸው መንከራተቱ ኣይቀርም።

ከፍተኛ ባለስልጣናት የሚባሉት ድንገት መሪያቸው ቢሄዱ ያንን በደህና ቀን የሰበሰቡላቸውን ፓርላማ ሰብሰብ ኣርገው ታጋይ ቢሞት ታጋይ ይተካል ብለው ቀለል ኣርገው እንቀጥል የነብር ጅራት ጨብጠናል ሲሉ እስካሁን ሲሞኙ የነበሩ የብኣዴንና ኦህዴድ ሌሎች የዘውግ ፖለቲከኞችም ምናልባት የፍርሃትን ሼል ሰብረው የሚወጡበትን ሁኔታ ሊፈጥርም ይችላል።

ወደታች የኢህኣዴግን መሰረት ስናይ ደሞ ባዶነው። በምርጫ 97 ጊዜ ኢህኣዴግ በኣዲስ ኣበባ ያገኘው ኣጠቃላይ ድምጽ በከተማዋ ውስጥ ካሉ የድርጅቱ ኣባሎቹ ቁጥር በጅጉ ኣንሶ ታይቷል ይህ የሚያሳየው ራሳቸው ኣባላቱ ኣልመረጡትም ነበር ማለት ነው። እነዚህ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ኣመራሮች የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘው ጊዜ የሚጠብቁ ኣይነት በመሆናቸው ከኣቶ መለስ በሁዋላ ለሚነሱ የህዝብ የለውጥ ጥያቄዎች ተባባሪ እንደሚሆኑ መገመት ይቻላል።
ያም ኣለ ይህ ኢህኣዴግ የተባለው ድርጅት ጥርስ የሌለው ኣንበሳ ኣርገው ስለፈጠሩት ከሳቸው መሄድ በሁዋላ በነበረበት ሊቀጥል ኣመጻዎችን ሊቋቋም ኣይችልም። በመሃከለኛ ና ባንዳንድ ለውጥ ሲፈልጉ ነገር ግን ፈርተው በቆዩ ባለስልጣናት ዘንድ የሚነሱ የ እንለወጥ ጥያቄዎችን ለማስተናገድም ካልሞከሩ ህዝባዊ ማእበል ይጠርጋቸዋል።

ወታደሩ ምን ያስብ ይሆን?
ለግምታችን መነሻ የኢትዮጵያን ወታደር ተፍጥሮ በሁለት ከፍለን እንየው። ይህ ተቋም ገና ሲመሰረት ቀድሞ የነበረውን ወታደራዊ ተቋም ሙሉ በሙሉ ኣፍርሶ በሲቪል ታጋዮች (guerilla fighters) የተገነባ በመሆኑ ከወታደራዊ ስሜቱ (Military sentiments) ይልቅ የታጋይነት ስሜት የዋጠው ተቋም ነው። ይህ ተቋም ሲቋቋም ከሌሎች ተቋሞች ባልተለየ ሁኔታ ነበር። ሲቪል ታጋይ የኢሃዴግ ሰራዊት ኣሸንፎ ኣዲስ ኣበባ ሲገባ ገሚሶቹ ታጋዮች ኮትና ሱሪ እየለበሱ በየተቋሙ የሃላፊነት ቦታ ሲይዙ ገሚሶቹ ደሞ የወታደር ልብስ ለበሱና የወታደር ማእረግ እየተጫነላቸው ወታደር ተባሉ። ሁለቱም ቡድኖች በልብስና በስያሜ ይለያዩ እንጂ ህወሃት ኢህኣዴግ የተባለው ድርጅት ኣባሎች ኣብረው የተዋጉ የትግል ጓዶች ናቸው። እንዴውም ኣገሪቱን ሲመሩ ኣብረው እየተደባለቁ የሲቪሉንም የወታደሩንም ስራ ይሰሩ ነበር።

ኣንዳንዶቹ ሲቪል ተብለው የተመደቡ ታጋዮች ጠንከር ያለ ጦርነት ሲመጣ ኣዛዥ የሆኑበት ሁኔታም ታይቷል። የመቶ ኣለቃ ግርማ ወልደጌዎርጊስ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ በቃ መቶ ኣለቅነቱን ትቼዋለሁ እንዳሉት ማለት ነው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ስነ ልቦናው ከዚሁ ከሲቪል ነጻ ኣውጭነቱ ጋር የተደባለቀ ተቋም በመሆኑ ገለልተኛነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንኳን ለማሰብ የማያስችል ተፈጥሮ እንዲኖረው ተደርጓል። ተዋግቶ የመጣለትን ድርጅት የሚጠብቅ የዘብ ስራ ያለበት የሚመስል ኣይነት ተቋም ያስመስለዋል።

ነጻ የሆነ ሃገራዊ ተቋም እንዳይሆን ተፈጥሮው ራሱ ይከለክለዋል ማለት ነው። ውስጣዊ ማንነቱ የህወሃት ክፋይ ኣካል መስሎ ተፍጥሯል። ከሃያ ኣመት በፊት ህወሃት ኢህኣዴግ ይባል የነበረው ሰራዊት ኣሁን የኢትዮጵያ መከላከያ ይባል እንጂ ታእታይ ቅርጹ ያው የድሮው መልኩ ነው። ከተፈጠረም በሗላ የነበሩት የበፊቶቹ ታጋዮች እረፍት ሲሹ ኣዲስ የሚገቡትን ኣመራሮች ባምሳላቸው እየቀረጹ ነው የሄዱት። የግምገማቸው ኣካሄድ፣ ስብእናቸው፣ የኣስተሳሰባቸው ቅኝት ስነ ልቦናቸው ኣጠቃላይ ኣሰራራቸው በዚያው መንፈስ እንዲቀጥል ጥረዋል። ይህ ጉዳይ ሃገራዊ ራእይ ያለው ተቋም እንዳይሆን የኣንድ ቡድን ጠባቂነት ስሜት እንዲያዳብር ሊያደርገው ይችላል።

ሌላው ሁለተኛው የዚህ ተቋም ተፈጥሮ ዘውጌነት ከሌሎቹ ሃገራዊ ተቋማት ሁሉ ጎልቶ የሚታይበት መሆኑ ነው። በተለይ በመካከለኛና በላይኛው ርከን ያሉ ባለስልጣናት በከፍተኛ ሁኔታ የኣንድ ባህላዊ ቡድን ሰዎች በመሆናቸው ተቋሙን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ኣስይዞታል። ይህ ተፈጥሮው በብሄር ላይ ለተቃኘው ፖለቲካ በጣም ስስ ስሜት እንዲኖረውና ገርጋራ እንዲሆን ያደርገዋል።
ከዚህ ተፈጥሮው የተነሳ ለውጥ ሲመጣ የስርወ ኣገዛዝ (statues quo) ጠባቂነት ስሜት እንዲያይልባቸው ያደርጋል።

ታዲያ ይህ ተቋም ዘውጌነት ይታይበት እንጂ በኣቶ መለስ በጥንቃቄ ሲታይና ሲመታ የነበረ ተቋም ም ነው። ኣቶ መለስ ስጋታቸውን ለመቀነስ ጥበቃቸውን ለማጠናከር ሲሉ ኣንዳንድ ደፋርና ተቋሙን ወደ ንጹህ ወታደራዊ ተቋምነት የመቀየር ኣገራዊ ራእይ ያላቸውን በየጊዜው መተው ጨርሰዋል። ኣሁን ያለው በሳቸው ጭንቅላት የሚንቀሳቀስ ነው። ይህም በመሆኑ እሳቸው ድንገት ቢለዩ ባዶነት የሚሰማው ከባድ ክፍተትም የሚፈጥር ነው።

ታዲያ ጦሩ በመዋቅር ደረጃ እንዲህ ኣይነት ተፍጥሮ ቢኖረውም ወደታች በሄድን ቁጥር በተለይ በዝቅተኛና ተራው ወታደር ኣካባቢ ጊዜ ጠብቆ ሊፈነዳ የሚችል እምቅ ብሶት እንዳለ ይሸታል። ይህ እምቅ ብሶት በህቡእ መናበብ ቆይቶ ምናልባትም ህዝባዊ ኣመጽ ሲነሳ ተቃውሞው ሊፈነዳም ይችላል። እንደ ሲሪያ ያለ ተከታታይነት ያለው ህዝባዊ ኣመጽ ቢነሳ እንደ ሲሪያ ወታደር የማይሆንባቸው ጉዳዮች ኣሉ። ታጋዮች ይህን የዘውግ ነገር ወደሰራዊቱ ሲዘረጉ መገንዘብ የነበረባቸው ነገር እነሱ የሚቆረቁራቸው የዘውግ ጉዳይ ተራውን ወታደርም እንደሚቆረቁረው ቀስ ብሎም የከፋ ሁኔታ ሊያመጣ እንደሚችል ማየት ነበር ።

የግብጹን ወታደር ስናይ በሃብት የበለጸገ ባንጻራዊ መልኩም ነጻ የነበረ ተቋም በመሆኑ ለውጡን ለመቆጣጠር ኣስችሎታል። የኢትዮጵያ ወታደር ድንበር ዘለል ለሆኑ ውጊያዎች ጠንካራ መሆኑ ሃቅ ነው። ይህ ጀግንነት በደሙም ስላለ ነው። በሃገር ውስጥ ለሚነሱ ብጥብጦች ግን ምን ሚና እንደሚኖረው በሚገባ በተግባር ኣልተፈተሸም። በ1997 ጊዜ የነበረው ኣጠቃላይ ነገር ያፈዘዘው ቢመስልም ካሁን በሁዋላ ለሚነሱ ህዝባዊ ኣመጻዎች ዝም ብሎ የሚያይ ይሆናል ማለት ያስቸግራል። ራሱ መንግስት የጫረው የዘር እሳት እዚያም ሊቀጣጠል ይችላል።

በኣጠቃላይ ጦሩ እንደ ተቋም ሲታይ በጥብቅ የተያዘ ቢመስልም የታችኛውን የበሸቀውን ክፍል መናበብ ያጠፋዋል ማለት ዘበት ነው። ልዩ ጦር በማዘጋጀት ህዝባዊ ኣመጾችን ለመቋቋም የሚፈልጉ ቡድኖች ቢነሱ ዋናው ጦር ዝም ብሎ የሚያይበት ሁኔታ መንምኗል።

ህወሃት የዘራው የዘር ፖለቲካ በህዝቡ ውስጥ ምን ያህል ሰርጾ ይሆን?
የእውነትኛ ሃገር ወዳድ የቅን ኢትዮጵያዊያን ስጋት ይሄ ነው። ኣሁን ይሄ መንግስት ድንገት ድርምስ ቢል ተከፋፍለን እንጫረስ ይሆን? የሚል ስጋት ኣለ። ይህን ሃሳብ ለመመለስ ሰፊ ጥናት ያስፈልጋል።የሆነ ሆኖ ዝም ብለን ኣንዳንድ ሃቆችን እያነሳን ብንጥል ምንም ኣይደል። በ ሁለት ምክንያቶች የዚህ የዘር ፖለቲካ ጉዳይ በህዝቡ ዘንድ የሚፈራውን ያህል ሰርጾ የግባ ኣይመስልም።

1) ህዝቡ በሃይል የዘር ፖለቲካውን ጠልቱዋል
መቼም እንደዚህ መንግስት በኣብዛኛው ህዝብ የተጠላ ያለ ኣይመስልም። ለዚህ ጥላቻ ትልቁ መሰረት የኢኮኖሚ እድገት ያለመኖሩ ድህነቱ ወዘተ. ኣይደሉም። ዋናው ከህዝቡ መንፈስ ጋር የተጋጨው የዚህ የዘር ፖለቲካ ጉዳይ ነው። ይህ ተቃውሞ እየከረረ ቀጥሎ መታየቱ ኢትዮጵያ የሆነ የፖለቲካ መተረማመስ ቢገጥማት ህዝቡ በዘር ልዩነት ተንስቶ የሚጨፋጨፍ ኣይሆንም ብሎ ለመናገር ዋቢ ይሆናል።

2) ከፍተኛ የኣንድነት ስሜት በትውልዶች ውስጥ ዘልቆ ገብቱዋል
ኣሁን በህይወት ያለውን ኢትዮጵያዊ እስቲ በ ሶስት ከፍለን እንይ። ኣንደኛው በተለምዶ ያ ትውልድ እያልን የምንጠራው ሲሆን ምናልባትም እድሜው ካምሳዎቹ ጀምሮ ወደ ላይ ያለውን ማለት ነው። ይህ ትውልድ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ሳይንሳዊ ለማድረግ የጣረ ግን ደሞ ብዙ መሰናክሎች የገጠሙት ትውልድ ነው። ያ ትውልድ ሲፈጠር ከጎኑ ኣብሮ ያደገ በጥባጭ ቢኖርበትም በ ዴሞክራሲና በ እኩልነት በኣንድነት ስሜት የተቃጠለ ነው። ይዞት ያደገው የኣንድነት ስሜቱ ለፍትህ ያለው ጥማት ለሃገሪቱ የዴሞክራሲ ትግል የመንፈስ ልዕልና ሰጥቶታል። ይሁን እንጂ በስትራተጂ ጉድለትና በሚገባ ካለመደራጀቱ የተነሳ እስካሁን የልቡን ኣላገኘም። ያ ትውልድ ከሱ ዝቅ ባሉት ከሃያ ኣምስት ኣመት ኣካባቢ በላይ ከ ሃምሳ በታች ባሉት ዘንድ እስካሁን የፖለቲካውን የዴሞክራሲውን ትግል በሚመለከት ተሰሚነት ያለውና ተጽእኖ ያለው ትውልድ ነው።

የዴሞክራሲ ትግሉንም በዋናነት በዚሁ ትውልድ መንፈስ የተቃኘ ይመስላል። ታዲያ ያ ትውልድ ኣጥብቆ የያዘውን የኣገር ኣንድነት ጥያቄ በህይወት እያለ የሚይስክደው ኣይኖርም። ከጎኑ ብቅ ያሉት የዘር ፖለቲካ ኣቀንቃኞችን በ እልህና በቁጣ እያየ የኣንድነት ስሜቱን ሲስብክ ይታያል። ያ ትውልድ በቀጣዩ ትውልድ ዘንድ የዚህችን ምድር የፖለቲካ ሩጫውን ይፈጽም ዘንድ በ ኣክብሮት የሚታይና ራእዩን ይፈጽም ዘንድ የተለቀቀ ይመስላል።

ዋናው ነገር ጠንካራ የሆነው የኣንድነት መንፈሱ ወደቀጣዩ ትውልድ በመተላለፉ በህይወት እያለ የዘር ፖለቲካ የሚፈለገውን ያህል እንዲሰርጽ (internalize) ኣላስቻለውም። ከመካከለኛው ትውልድ ዝቅ ያለው ለጋው ትልድም ያባቶቹንና የታላላቅ ወንድሞቹን ምክርና ፈለግ ስለሚከተል የህወሃት የዘር ፖለቲከ ባለፉት ሃያ ኣመታት የተደከመለትን ያህል የህዝቡን የኣንድነት መንፈስ የሰበረ ኣይመስልም።

ሌላው ቀርቶ በዚህ በዘር ፖለቲካ በቀላሉ እንይዘዋለን የተባለው ያልተማረው ገበሬ እንኳን የተማረ ይግደለኝ እያለ ልጆቹን የሚሰማ ሆኖ ተግኝትዋል። እነዚህ እንደ ኣረም ከዚያ ትውልድ ጋር የበቀሉትን ቡድኖች የሚቀበል ሳይሆን ያኔ የተነሳውን የመሬት ላራሹን ጥያቄ ያነሳውን ልጁን ዛሬም መፍትሄ ሊያመጣ ይችላል ብሎ ይጠብቃል። በዚህ መሰረት በሃገራችን የሆነ ፖለቲካዊ ትርምስ ቢፈጠር በዘር ተለያይቶ የሚነሳ ችግር ዝቅተኛ ሊሆን እንደሚችል ልንገምት ያስችለናል።ይህ ማለት ግን ላለፉት ሃያ ኣመታት የተዘራው ዘር ምንም ተጽእኖ የለውም ለማለት ኣይደለም። በደንብ ኣለው። ይሁን እንጂ የሆነ ክፍተት ቢፈጠር የሚፈራውን ያህል ችግር እንዳይፈጠር የሚያስችል ዋስትና ኣለን ለማለት እንጂ። ላልታቀደ ህዝባዊ ኣመጽ መነሳት ይህ የዘር ፖለቲካ መሰናክል ቢመስልም ሃገሪቱ ያልሆነ የፖለቲካ ትርምስ ውስጥ ብትገባ ከባድ የዘር መተላለቅ እንዳይከሰት የሚያደርጉ መሰረቶች ኣሉ ለማለት ነው።

በለውጥ ጊዜ ሊከሰቱ የምችሉትን ችግሮች ለመቀነስ የኢትዮጵያ የዴሞካሲ ሃይሎች ምን ያድርጉ?
ኢትዮጵያ የለውጥ ባቡር መንዳት ከጀመረች ውላ ኣድራለች። በርግጥ ባቡሩን የሚያሰጉ ችግሮች ኣሉ። እነዚህን ችግሮች ለመቀነስ የሃላፊነት ስሜት ካላቸው ሃይሎች የሚጠበቅ ዋና ነገር ኣለ ይሄውም ዋስትና ነው። በዘውግ ፖለቲካ በታመሰ ስርዓት ውስጥ የታቀፉ ሰራተኞች ወይም የተነካኩ ሃይሎች የሚመጣው ለውጥ በስነ ልቦና ወይም በኣካል የሚቀጣን ይሆናል ብለው የሚሰጉ ኣሉ። እነዚህ ሃይሎች ኣያሌ ሊሆኑ ይችላሉ። ታዲያ ከተቃዋሚው ጎራ ቆይ ግዴለም ዴሞክራሲ ይምጣ ፍርድ ቤት ይቁም ዋጋህን ታገኛለህ በማለት ማስበርገጉ ላሃገሪቱ የመጀመሪያ የዴሞካሲ ስርዓት ለማቆም ጠቃሚ ኣይመስልም። ይልቁን ኣዲስ የሚመጣው ለውጥ ምህረትን ይቅርታን መሰረት ኣድርጎ የሚቆም መሆኑን መስበክ ይሻላል። ርግጥ ነው ይቅርታና ምህረት ዋጋ ያስከፍላል ይሁን እንጂ የመጀመሪያውን መሰርት ስንጥል በዚህ ላይ ካልተመሰረተ ኣስቸጋሪ ይሆናል። ይህ ዋስትና የማሳየቱ ጉዳይ የሰጋውን ኣካል ስነ ልቦና ወደ ኣንድ ጥግ ሊሰበስበው ይችላል። ከሁሉም በላይ ደሞ የሚመጣውን ለውጥ የሚደግፉ ሰራዊቶች ይሆናሉ።

እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ
ቸር ያሰማን
ገለታው ዘለቀ
geletawzeleke@gmail.com

ስለ ሰላማዊ ዐመጽ7ነጥቦች!

Thursday, June 21st, 2012

1. የሰላማዊ ኣመጽ ብያኔ
በቀላል ኣገላልጽ ሰላማዊ ኣመጽ ማለት ከ ኣክብሮት ጋር ኣንስማማም ማለት ነው። ይህም በመሆኑ ሰላማዊ ኣመጽ በኢትዮጵያ በምንም መለኪያ ከሽብርተኝነት ጋር ሊያያዝ ኣይችልም። ሰላማዊ ኣመጽ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልገውንና የማይፈልገውን በግልጽ የሚያሳይበት ኣውድ ነው።
2. እውን ሰላማዊ ኣመጽ በኢትዮጵያ ሊሰራ ይችላልን?
የሰላማዊ ኣመጽን ታሪካዊ ኣመጣጥ ስናይ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ490 ኣካባቢ በ ሮም እንደተጀመረ ኣዋቂዎች ይናገራሉ። ይህ የትግል ስልት ዘዴው እያደገ መጥቶ የቅርብ ጊዜ የኣለማችንን ታሪክ እኳን ስናይ ከ 1996 ጀምሮ እስከ 1999 የተለያዩ ሃገራት ህዝቦች በዚህ የትግል ስልት ተጠቅመው ከኣምባገነን ስርኣቶች ለመላቀቅ ባደረጉት ትግል ከስልሳ ሰባቱ ሃምሳ የሚሆኑት ኣመርቂ ውጤት እዳስመዘገቡ እናነባለን።

ኣንዳንድ ወገኖች ሰላማዊ ኣመጽን ለማካሄድ ከመነሻው ትንሽም ቢሆን የፖለቲካ ክፍተት (political space) ሊኖር ይገባል፣ ትንሽም ቢሆን ህጋዊ ከለላ ያስፈልጋል ብለው ያምናሉ። ይህ መረዳት ከሰላማዊ ትግል ጋር ተደባልቆ የመጣ ሳይሆን ኣይቀርም።እውነት ነው ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ትንሽ የፖለቲካ ምህዳር ያስፈልጋል። ሰላማዊ ኣመጽ ግን ከሰላማዊ ትግል የሚለይ ሲሆን በየትኛውም መንግስታት ይሰራል። በ ኦቶክራቶች፣ በኮሚኒስቶች፣ በዴሞክራቶች፣ በነገስታት በሁሉም ሁኔታ ይሰራል።

የኣጭር ጊዜ የኣለማችንን ታሪክ ስናይ በሰርቢያ በ 1998 (Otpor!) (ተቃውሞ) የተሰኘው የወጣቶች ሰላማዊ ኣመጽ ኣምባገነኑንና በቦስኒያ፣ ክሮሺያ እና ኮሶቮ በፈጸመው የጦር ወንጀልና በሰው ልጆች ላይ በፈጸመው (Crime against humanity) ወንጀል ተጠያቂ የሆነውን ስሎቮዳን ሚሎሶቪክን ከስልጣን ለማውረድ የቻለ የትግል ስልት ነው። በሶቪየት ህብረት ጊዜ የተነሱ የነጻነት ጥያቄዎች ውስጥ ይህ የትግል ስልት ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል። በፖላንድ፣ በፊሊፒንስ፣ በሃንጋሪ፣ በቼኮዝሎቫኪያ፣ በቡልጋሪያ፣ በቺሊ ወዘተ. ተፈትኖ የወጣለት የትግል ስልት ነው።
ይህ የትግል ስልት በኢትዮጵያ የማይሰራበት ምንም ምክንያት የለም። ሰላምዊ ትግል በኢትዮጵያ ኣስቸጋሪ ወይም የማይቻል ብለው የሚያምኑ ወገኖች ሁሉ በሰላማዊ ኣመጽ በኢትዮጵያ ለውጥ ኣይመጣም ማለታቸው ኣይደለም።

የኢትዮጵያ መንግስት ተፈጥሮና የፖለቲካው ኣጠቃላይ ከባቢም ቢሆን ይህን የትግል ስልት እንዳይነሳ የሚያደርገው ኣይደለም።

3. ኢትዮጵያ ለሰላማዊ ኣመጽ የተዘጋጀች ኣገር ናት ወይ?
በኣጠቃላይ ህብረተሰብን ወደ ኣብዩትና ወደ ለውጥ ከሚገፉት ጉዳዮች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፣
1. የድህነት መጨመር
2. ኢፍትሃዊነት ፣ ሰፊ የ ኦፖርቹኒቲ እጦት፣ ስራ ኣጥነት፣ ኣድልዎ ወዘተ.
3. ከፍተኛ የገቢ ኣለመመጣጠን (Large socio-economic disparities)
4. የህዝቦች ሉኣላዊነት መደፈር
5. የኣንድነት መደፈርና
6. የብሄራዊ ማንነት መነካት
7. የነጻነት እጦት
እነዚህ ከፍ ሲል የዘረዘርናቸውን ጉዳዮች ስናይ ኢትዮጵያ በነዚህ በሁሉም ጎኗ ቆስሏል። ኣልፎ ተርፎ የነዚህ ችግሮች ጡዘትም በዜጎች ልብ ውስጥ ተፈጥሮኣዊ የለውጥ ጥያቄን ኣብስሏል። ይሁን እንጂ ለሁሉም ጊዜ ኣለው ታዲያ። በለስ ኣብቦ ያፈራና ሲበስል መቆረጥ ኣለበት። ጊዜው ሲያልፍ ጥቅም ኣይሰጥም። የህዝቦች የለውጥ ፍላጎት በከረረበት ሰኣት የሚነሳ ሰላማዊ ኣመጽ ውጤታማ ሲሆን እንዲሁ በየግለሰቡ ቤት እየተብሰለሰለ የሚያደራጀው ኣጥቶ ጊዜ ሲወስድ መጠውለግ፣ መደንዘዝ ያመጣል። ወይም ቁጣው ባልታቀደ መልኩ ይፈነዳና ሊባክን ይችላል። ለዚህ ታዲያ ሃላፊነት የወሰዱ ሃይሎች ወቅቱንና የህዝቡን ብሶት ደረጃ እያዩ ማደራጀት ለሰላማዊ ኣመጽ ማነሳሳትና መምራት ይጠበቃል።

4. በሰላማዊ ኣመጽ የሚመጣ ለውጥ ለኢትዮጵያ ያለው ጠቀሜታ
1. ድሉ የራሱ የህዝቡ ስለሚሆን ውጤቱንም በንቃት ይከታተላል፣ይጠብቃል
ህዝቡ በንቃት የተሳተፈበት ለውጥ ሁልጊዜም የሚኮራበት የሚደሰትበት ስለሚሆን በዚህ መንገድ የሚመጣ ለውጥ ጠቀሜታው የጎላ ነው።
2. ከሁሉም በላይ ለውጡን ከጥላቻ የጸዳ ስለሚያደርገው ከምንፈራው የ ክብ (vicious) በጥላቻ የተሞላ ትግል ወይም ጦርነት እንድንወጣ ኣዎንታዊ ሚና ይኖረዋል።
3. ጸጋ ለመግለጥ
የተለያየ ጸጋ ኣለን። ኣንዳንዱ ጥሩ ኣስተባባሪ ነው። ኣንዳንዱ ጥሩ መሪ ነው እነዚህ ጸጋዎች የሚገለጹበት ኣንዱ ኣውድ ይህ ህዝባዊ ኣመጽ ነው። ኣመጹ ሲነሳ ውስጣቸው ያለው ጸጋ እየገፋፋቸው ሃላፊነት እየወሰዱ የሚያስተባብሩ፣ የሚመሩ ሰዎች በዚያው ኣጋጣሚ ተስበው ቀጣዩን ለውጥ የሚመሩ ሊሆኑ ይችላሉ። ብዙ ታላላቅ መሪዎች በዚህ መንገድ ተፈጥረዋል። እውቁ የፍትህና የነጻነት ታጋይ ማርቲን ሉተር ኪንግ ኣመጽ የወለደው ነው።
4. ህብረትን ለማደስ
ሌላው ከህዝባዊ ኣመጹ ጋር ኣብሮ የሚገለጠው ነገር። ህብረትን ማደስ ኣንድነትን ማጠናከር ነው። የዜጎች ብሄራዊ ስሜት የሚበረታታበት፣ ፍቅርና መተሳሰብ የሚገለጥበት ኣውድ ነው።
5. ሰላማዊ ኣመጽ በኢትዮጵያ ምን መልክ ሊኖረው ይገባል? ማንስ ይምራው? ህዝብ ወይስ የፖለቲካ መሪዎች?
በኢትዮጵያ ውስጥ ህዝባዊ ኣመጽ በሁለት መንገድ የመነሳት እድል ኣለው ብለን እናስብ። ኣንደኛው የታቀደ በድርጅት የሚመራ ሲሆን ሁለተኛው ያልታቀደ በራሱ በህዝቡ የሚመራ። ከኢትዮጵያ ኣጠቃላይ የፖለቲካ ከባቢና ከተፈጠረው ስነ-ልቦናዊና መልካምድራዊ ክፍተት የተነሳ የታቀደው ቢሆን ሳይሻል ኣይቀርም። ያልታቀደ በህዝቡ የሚመራ ህዝባዊ ኣመጽ በኢትዮጵያ ሁኔታ ሲታይ በዛ ያሉ እክሎች ያሉበት ይመስላል። ከነዚህም መሃል፣

1. ኣመጹ በራሱ ከተቀሰቀሰ በሁዋላ የግድ የሆነ ቦታ ላይ ኣመራር መፈለጉ ኣይቀርም ታዲያ በዚህ ጊዜ ተዘልለው ያሉም ይሁን ኣገር ቤት ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ምን ያህል ህብረት ኣላቸው? ምን ያህል በኣመጹ ጊዜም ቢሆን ህብረት ፈጥሮ ኣመራር ለመስጠት ፈቃደኛ ናቸው? የሚለውን ጥያቄ ያመጣል። ድንገት የሚፈነዳው የህዝብ ኣመጽ ኣመራር ሲፈልግ ከተለያዩ ኣካላት የተለያየ ኣመራር እየመጣ ግራ ማጋባት ያመጣስ ይሆን? ኣንዳንዶች ህዝቡ ኣብዩቱን ሲያቀጣጥለው ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ወደ ኣንድነት ይሳባሉ የሚል ኣሳብ ይኖራቸው ይሆናል። በርግጥ ይህ ኣይነቱ ተግባር በሰሜን ኣፍሪካው ኣብዮት ታይቷል። ነገር ግን የኢትዮጵያን የፖለቲካ ኣሰላለፍ ስናይ ከሰሜን ኣፍሪካው ስለሚለይ ይህ ኣሳብ ላያዋጣ ይችላል። ቀድሞ ህብረት መፍጠር በኢትዮጵያ ሁኔታ ኣዋጭ ነው።

2. ከፍ ሲል እንዳልነው ባለፉት ኣመታት ከተፈጠረው የስነ ልቦና ክፍተት የተነሳ ኣንድ ቦታ ሳይታቀድ ቦግ ያለ ሰላማዊ ኣመጽ ሌላው የሃገሪቱ ክፍል ለመዛመት ምን ያህል እድል ኣለው? ጎጃም የተነሳ ኣመጽ ናዝሬት ሊያስተጋባ ይገባዋል። ቡታጅራ የተነሳ ኣመጽ ጋምቤላ ኣሶሳ ሊያስተጋባ ሊቀበለው ይገባል። ይህ ካልሆነ በየጊዜው ኣንድ ኣካባቢ ቦግ የሚለው ኣመጽ መንግስት እንዲቆጣጠረው ፋታ ይሰጠዋል። ችግሩንም በቀላሉ ለመቋቋም ያስችለዋል።
እንግዲህ ከነዚህ ጉዳዩች ኣንጻር ስናይ ነው በእቅድ የሚመራ ህዝባዊ ኣመጽ በኢትዮጵያ ማካሄድ ሳይሻል ኣይቀርም የሚያሰኘን ።

6. የታቀደ ህዝባዊ ኣመጽ ለመፍጠር ምን ያሻል?
የታቀደ ህዝባዊ ኣመጽ ለማነሳሳት የመጀመሪያው ተግባር የሃገሪቱን መልክና ተፈጥሮ የያዘ ህብረትና ኣመራር ነው መሰረቱ። ታዲያ ይህ ኣመራር በነሲብ በህብረት ስም በሩን ቡርቅቅ ኣርጎ መክፈት የለበትም። የኢትዮጵያን የፖለቲካ ትግል የጎዳው ኣፍጠው የመጡ የመንግስት ደጋፊዎች ትግል ኣይደለም። በራሱ በመንግስት እጅ እየተደራጁ ትግሉን የሚያዳሙ (hijack) የሚያደርጉ ሃይሎች ናቸው። እውነተኛዎቹ ተቃዋሚዎች ደጋፊ እናጣለን በሚል ስጋት ሆዳቸው እያወቀ ዝም ማለት የለባቸውም። ከ እውነት ጋር ሲቆሙ የሚገርመው ህዝብ ኣሽትቶ ያውቀዋል።
በሃገራችን የገና ጨዋታ ጊዜ “ሚናህን ለይ” የሚባል ነገር ኣለ። ሚና ያለዩበት የገና ጨዋታ እሩሯ የትም ኣትሄድም። እንዲሁ ሚናቸው ባለየላቸው ተጨዋቾች ተከባ ትቆያለች።

በቅንጅት ጊዜ በሚያዝያ ወር የታየው ታላቅ ትእይንት ተፈጥሮው ወደ ህዝባዊ ኣመጽ ያደላ ነበር። መንግስት ላፉ ፈቅጃለሁ ቢልም ትራንስፖርት በማሳጣት፣ በካድሬዎቹ ኣማካኝነት በማዋከብ ሰራተኛውን በማስፈራራት ሰልፉን መበተን ፈልጎ ነበር። ህዝቡ ግን ከኮልፌ ቀራንዩ ድረስ በእግሩ መጥቶ ሰልፉን ኣካሂዷል። በቅንጀት ህብረት ላይ ልቡ ስላረፈ፣ በመሪዎቹ ላይ እምነት ስላደረበት ኣውርድ የሚባለውን ለማውረድ ስቀል የሚባለውን ለመስቀል ዝግጁ ነበር። ይህ የሚያሳየው ህብረትና የሚያምነው ድርጀት ካገኘ ህዝቡ በእቅድ ለሚመራ ህዝባዊ ኣመጽ ወደሗላ የሚል ኣለመሆኑን ነው።

7. የሰላማዊ ኣመጹ ሲታቀድ ከግንዛቤ ሊገቡ የሚገባቸው ጉዳዮች

1. ህዝቡን በኣቅሙ የማታግል ስልት
በኢትዮጵያ ሰላማዊ ኣመጽ ቀጣይነት ኖሮት ፣ ለውጥ ለማምጣት እንዲችል የህዝቡን ኣጠቃላይ ኣቅም ያገናዘበ መሆን ኣለበት። በመሆኑም ኣመጹ ሲታቀድ የህዝቡን ንቃተ ህሊና፣ ኢኮኖሚ ሃይማኖትና ባህል ማገናዘብ መልካም ነው። ኣንድ ጊዜ የኣመጽ ኣይነቶችን ሁሉ ቢያሸክሙት የተሰጠውን የቤት ስራ እስከ መጨረሻ ላይወጣ ይችላል። ከሁሉም በላይ ቦግ እልም እያለ ሩቅ ኣይሄድም። በየቀኑ ሰኳር የሚገዛን ህዝብ፣ በየቀኑ ጨው የሚገዛን ህዝብ፣ በየቀኑ ዘይት እየገዛ የየቀን ኑሮውን ለመግፋት የሚታገልን ህዝብ ያየ የትግል ስልት ብዙ ብዙ ኣለ።

2. መቼት (setting)
የታቀደ ሰላማዊ ኣመጽ ሚስጥር ኣይደለም። ለሚሊዩን ህዝብ ተነግሮ ከመንግስት የሚደበቅ ነገር የለም። መቼና የት? ለሚለው ጥያቄ ግልጽ ምላሽ ሊኖረው ይገባል። ለኣብነት የምስራቅ ጀርመኖችን ታሪክ እናንሳ። በ1989 ምስራቅ ጀርመናዊያን ኣምባገነንነትን ለመቃወም ሲያቅዱ
“የሰኞ ኣብዮት” ብለው ተነሱ። በየሳምንቱ ምሽት ላይ በከተማይቱ መስቀል ኣደኣባይ እየተገናኙ ለኣንድ ኣመት ያህል የዘለቀ ተቃውሞኣቸውን ኣድርገዋል። በዚያን ጊዜ ጀርመናዊያን ሰኞን በናፍቆት እየጠበቁ ምን ላድርግ እያሉ እያሰቡ ይቃወሙ ነበር። እያደር ደጋፊያቸው እየበዛ ትግላቸው እያበበ ሄዶ በመጨረሻ የበርሊንን ግንብ ሳይቀር ለማፍረስ እና ለሁለቱ ጀርመኖች ውህደት በር ከፈተ። እቅዳቸው ኣቅማቸውን ጊዚያቸውን ያገናዘበ በመሆኑ ርቀት ተጉዘው ኣሸነፉ።
በኢትዮጵያ የሚነሳ ህዝባዊ ኣመጽም እንዲህ መቼት ሊበጅለት ይገባል። መቼቱ ክርጀርመናውያን የተለየ ሊሆን ይችላል ግን ኣሁንም ቢሆን በኢትዮጵያ ሁኔታ መቼት መፍጠር ይቻላል።

3. ስያሜ
ህዝባዊ ሰላማዊ ኣመጽ መሪ ቃል ወይም ስያሜ ያሻዋል። በ1986 የኣለምን ቀንደና ሙሰኛ የሆነውን ፈርዲናንድ ማርቆስን የፊኒፒንስ ህዝብ የጣለው የህዝብ ሃይል ኣብዮት “people power revolution” የሚል የትግል ስም ሰይመው ነው። ፊሊፒኖዎች መሪቃላቸውን ይዘው በየጎዳናው በጸሎትና በመዝመር ተቃውመው ማርቆስን ጥለዋል። በባልቲክ ግዛት በላቲቪያ ኤስቶኒያ የመዝሙር ኣብዮት “singing revolution” በሚል ስያሜ በዝማሬ ያለ ምንም ደም መፍሰስ የፈለጉትን ለውጥ ተቀዳጅተዋ።
በዚሁ በክፍለ ኣህጉራችን በ 2003 የላይቤሪያ ሴቶች በጸሎትና በመዝሙር ያደረጉት ተከታታይ ተቃውሞ የላይቤሪያውያንን የርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም ችሏል። በሊባኖስ “የዝግባ ኣብዩት”፣ በዩክሬን “የ ብርቱካን ኣብዮት” በጆርጂያ “የጽጌረዳ ኣብዮት” ይጠቀሳሉ። በኢትዮጵያም ቀስቃሽና ነሻጭ የሆነ ስያሜ ቢሰጠው ለትግሉ ሃይል ይሆናል።

4. ትግሉ ሲጦዝ (Climax) ሊመጣ የሚችለውን ለውጥ ከግንዛቤ ኣስገብቶ የታክቲክ ኣማራጮችን ቀድሞ ማስቀመጥ

በኣንድ በተመረጠ መቼትና መሪ ቃል የሚጀመር ህዝባዊ ኣመጽ በኢትዮጵያ ውስጥ መልኩን ሳይቀይር እስከመጨረሻ ላይጓዝ ይችላል።ኣመጹ እየበረታ ሲሄድ ደጋፊዎች ሲበዙ በመንግስት በኩል ሪኣክሽን መፈጠሩ ኣይቀርም። በዚህ ጊዜም ትግሉ ኣቅጣጫውን ሊቀይር ስለሚችል ሊሆኑ የሚችሉትን ውጤቶች በመተመን ኣማራጭ ታክቲክ ቀድሞ ማሰብ የእቅዱ ኣካል ነው። በኣጠቃላይ እቅዱ ያሉትን ፍራቻዎች (threats) ና መውጫቸውን ማስቀመጥ ኣለበት።

5. መረጃ መቀባበያ ዘዴዎችን መፍጠር
መንግስት ህዝባዊ ኣመጽ ብቅ ሲል የመጀመሪያው ሩጫው የመረጃ መቀባበያ ዘዴዎችን መምታት ነው። ይህ እንደሚሆን ስለሚታወቅም መንግስት ሊቆጣጠራቸው የማይችሉ የመረጃ መቀባበያ መንገዶችን መፍጠር ያስፈልጋል። በተለይ በገጠሩ ኣካባቢ ያለው ህዝብ ኣሰፋፈሩ የተራራቀ ስለሆነ ለመረጃ የራሱን ባህል የተከተለ ዘዴ መፍጠር ተገቢ ነው። ለኣብነት ያህል በደቡቡ ያገራችን ክፍል ኣንድ ቀበሌ ህዝብ ሲያምጽ ወይም ችግር ሲደርስበት ከፍታ ቦታ ላይ ጭስ ያጨሳል ሌላው ቀበሌ ደሞ ተቀብሎ ለቀጣዩ ቀበሌ የሚታይ ቦታ ላይ ያጨሳል እንዲህ እያለ ደቡብን ሊያደርስ ይችላል። እንዲህ ኣይነት ዘዴዎች በህዝቡ ባህል ውስጥ ስላሉ በቀላሉ ዓመጹን ማዳራስ ይቻላል። በከተማው ደሞ የተለየ መልክ ያለው ዘዴ መፍጠር ያሻል።
እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!
geletawzeleke@gmail.com
ገለታው ዘለቀ

http://www.ethiopianreview.com/research/5539

http://en.wikipedia.org/wiki/Nonviolent_resistance

ዴሞክራሲ በኢኮኖሚ ልማት ላይ ተጽእኖ ኣለው!

Saturday, June 16th, 2012

ኣንዳንዶች ዴሞክራሲ ከኢኮኖሚ ልማት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም ብለው ያምናሉ። ሌሎች ደግሞ ዴሞክራሲና የኢኮኖሚ ልማት ተፈጥሮኣዊ ግንኙነት ኣላቸው ወይም ዴሞክራሲ በኢኮኖሚ እድገት ላይ ኣዎንታዊ ሚና ኣለው ብለው ኣጥብቀው ያምናሉ። ታዲያ በዚህች ኣጭር ጽሁፍ የነዚህን ወገኖች ሃሳብ በጥቂት በጥቂቱ ገረፍ ገረፍ ኣርገን ወደ መጨረሻ ላይ በግል ኣስተያየት ለመቋጨት ተነስተናል።

በመጀመሪያ ዴሞክራሲ ከልማት ጋር ግንኙነት የለውም የሚሉ ወገኖች በዴሞክራሲ ስለማያምኑ ኣይደለም። ዴሞክራሲ ለህዝቦች ኣስፈላጊ ነው ብለው የሚያምኑ ናቸው። ይሁን እንጂ ዴሞክራሲና የኢኮኖሚ እድገት በተራ በተራ ወይም ለየብቻ እንደየ ተፈጥሮኣቸው ሊያድጉ የሚገባቸው ናቸው የሚል ኣንድምታ ኣላቸው። የነዚህ ሰዎች የልብ ግፊት የሚመስለው ዴሞክራሲን የኢኮኖሚ እድገት ሊያመጣው ይችላል፤ የሰው ልጅ ኢኮኖሚክ ህይወቱ ሲሻሻል ፍላጎቱ እየጨመረ ይሄዳል የዴሞክራሲ ጥያቄውም እየጨመረ ይመጣል ስለዚህ የኢኮኖሚ እድገቱ ላይ ማተኮር የህብረተሰብን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት ኣይነተኛ መንገድ ነው የሚል ይመስላል።

እነዚህ ቡድኖች ኣልፈው ሄደውም ዴሞክራሲ በታሪክም ቢሆን ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ግንኙነት የለውም እስከማለት ይደርሳሉ። በነዚህ ሰዎች መረዳት የዛሬ መቶ ሁለት መቶ ኣመት በፊት ገና ዴሞክራሲ ሳይወለድ የኢኮኖሚ እድገት ነበር ሊሉ ይችላሉ። ምሳሌ ጥቀሱ ሲባል በፈጣን እድገቱዋ የምትታወቀው ደቡብ ኮርያም ብትሆን በ 1970ዎቹ ኢኮኖሚዋ መፈንዳት ሲጀምር ትተዳደር የነበረው በ ኣምባገነኑ ፕሬዚደንት ፓርክ ነበር። በዚያን ጊዜ የኮርያ ኢኮኖሚ ከመሬት የተነሳው ኢኮኖሚውን ዴሞክራሲ ስለደገፈው ኣይደለም ይላሉ።

የሲንጋፖሩ ሊኩዋን የው እና የድህረ ማኦ ቻይና መሪዎች ዴሞክራት ሳይሆኑ ለኢኮኖሚ እድገት ግን ከዴሞክራት መሪዎች በላይ ሰርተዋልሞ ይላሉ። የኣሁኑዋን ቻይናን ደሞ ኣጥብቀው ለመከራከሪያ የሚያቀርቡዋት ይመስላል። ቻይና በፖለቲካዊ ነጻነቱዋ ከኣለም መጨረሻ ከሚሰለፉ ኣገሮች ኣንዱዋ ስትሆን ድህነትን ለመቀነስ በምታደርገው ጥረት ደሞ በኣለም ከፍተኛ ደረጃ ካላቸው ኣስር ኣገሮች መካከል ኣንዱዋ ናት። ይህ ተቃራኒ ሁኔታ የሚያሳየው የኢኮኖሚ እድገትና ዴሞክራሲ ባጣጥ በቀረጥ የማይገናኙ መሆናቸውን ነው እስከማለት ይደርሳሉ።

በሌለኛው ጎራ ያለው ኣመለካከት ደሞ የራቀ ነው። ሌሎች ደሞ ዴሞክራሲ ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ኣለው ብለው ኣጥብቀው ያምናሉ። ከነዚህ ቡድኖች ውስጥ ኣንዳንዶቹ “በጎ ነገሮች ሁሉ ኣብረው ይሄዳሉ” ከሚል ቅን ስነ-ልቦና የመነጨ ነው። ሌሎች ደሞ በመረጃ የተደገፈ በቁጥር የተገለጸ ጥናት እያቀረቡ ዴሞክራሲ በኢኮኖሚ እድገት ላይ ኣዎንታዊ ተጽእኖ ኣለው ይላሉ።

ብዙ በኢኮኖሚ የበለጸጉ ሃገራትን ስም እየጠሩ ዴሞክራቶች ናቸው ይላሉ። በኣንጻሩ ዲክተተርስ ያሉባቸውን ኣገራት ሲያዩ እጅግ ብዙዎቹ በኢኮኖሚያቸው የደከሙ ድሃዎች ናቸው። ይሄ የሚያሳየው ዴሞክራሲ በኢኮኖሚ እድገት ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ ስላለው ነው ይላሉ።በኣጠቃላይ እነዚህ ቡድኖች ዙሪያ መለስ ነጻነት ከሌለ ልማት ኣይፈጥንም። ልማት ያለ ዴሞክራሲም ጤነኛ እድገትን ኣያመጣም ብለው ይናገራሉ።ዴሞክራሲ ማለት ለዜጎች ስራ ፈጠራ ለተነሳሽነትና ለእምነት(trust)ጥሩ ከባቢ የሚፈጥር በመሆኑ ኢኮኖሚን በቀጥታም በተዘዋዋሪም ተጽእኖ ያሳድርበታል ይላሉ።

የግል ኣስተያየት
ዴሞክራሲ በኢኮኖሚ እድገት ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ ኣለው የለውም የሚለውን ክርክር ከመጀመር በፊት ዴሞክራሲን መጀመሪያ መበየን ተገቢ ሳይሆን ኣይቀርም። የክርክሩ ጥራት የሚለካው ዴሞክራሲን በምናይበት መነጽር ነው። ዴሞክራሲ ስንል ወደ ኣይምሮኣችን ቀድሞና ኣይሎ የሚመጣው ነጻ ምርጫ ከሆነ ይህንን ግንዛቤ ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ስናያይዘው የጠነከረ መረጃ ላይኖረን ይችላል። በየ ኣራት ኣምስት ኣመቱ ኣወዛጋቢ ያልሆነ ምናልባትም ኣስተማማኝ ምርጫ እያደረጉ ኣምባገነን ኣገር መሆን ይቻላል። ዴሞክራሲ ተቋማዊ ካልሆነና በህብረተሰቡ ዘንድ ባህል ካልሆነ ምርጫ ብቻውን ከኢክኖሚ እድገት ጋር ያለው ግንኙነት ግልጽ ሆኖ ላይታይ ይችላል።

ዋናው ነገር ዴሞክራሲ ስንል የህዝቦች የልእልና (sovereignty of the people) ጥያቄ ነው። በተግባር ሲዘረዘር ደሞ ዜጎች እንደዜጋም እንደሰው ልጅነታቸውም ክብርና ምርጫቸው ሊጠበቅ ይገባዋል የሚል ዶክትሪን ነው።

ግለሰቦች ብዙ ሆነው ተሰባስበው መንግስት ሲያቆሙ ተቋማት ሲመሰርቱ የየግል ዝንባሌ(interest) ስላላቸው ነው። እነዚህ ተቁዋማት ደሞ የዜጎችን ቁሳዊ ህይወትም እንዲያሽሽሉ ዘዴ ወይም መንገድ ይሆናሉ ተብለው ነው። ዴሞክራሲ ስንል የነዚህን ተቋማት ንጽህና እና ፍታዊነት ማንሳታችን ነው። ታዲያ እንዴት ነው ነጻ ፍርድ ቤት መኖር ያለ መኖሩ ከኢኮኖሚው እድገት ጋር በቀጥታ የማይያያዘው? በህጋዊ መንገድ ለመበልጸግ የፍትሁ ኣካል ገለልተኛነትና ታማኝነት በቀጥታ የኢኮኖሞውን እድገት ተጽእኖ ይፈጥርበታል። ከመቼውም በላይ ዛሬ መረጃና ገበያ በተቀላቀሉበት ዘመን እንዴት ነው ነጻ መረጃ ያለመኖሩ ኢኮኖሚውን በቀጥታ የማያገኘው?

ዴሞክራሲ በታሪክም ቢሆን ከሰው ልጆች ሁለንተናዊ እድገት ጋር ኣብሮ እያደገ የመጣ ነው። ዛሬ ኣድጎ የሚታየውን መልኩን ሳይዝ ዴሞክራሲ ኣልነበረም ማለት ኣይቻልም። ዴሞክራሲ በህዝቦች ልብና ባህል ውስጥ ነበር። ዴሞክራት ሳይሆኑ የኢኮኖሚ እድገት ኣመጡ የሚባሉት የድህረ ኮሚኒዝም ኦቶክራቶች ዴሞክራሲ የሚባል ነገር ምንም በልቦናቸው ኣልፈጠረባቸውም ማለት ኣይቻልም። ፍትህ እንዲመጣ፣ እኩልነት እንዲሰፍን፣የህዝቦች ልእልና እንዲከበር የኢኮኖሚው ክፍፍል እንዲሻሻል ሞክረዋል። ችግሩ በስልጣን የመቆየት ኣባዜ ነበር ግን ደሞ በህዝቦች ውስጥ የቀደመው የባለ ሙሉ ዴሞክራሲያዊ መብት ጥያቄ እየጠረገ ጣላቸው።

ዛሬ ህዝቦች ኣድገው ዴሞክራሲን ሰባዊ መብትን ኣጥብቀው በሚሹበት ሰኣት እነ ዲክተተር እንትና ዲክቴተር ሆነው ኢኮኖሚያቸው ኣድጉዋልና እኛም በዚህ መንገድ እንለፍ ማለት ካለማቀፉ ሁኔታም ሆነ ጊዜን ተከትሎ ካደገው የሰው ልጆች የኣስተሳሰብ እድገት ጋር ይጋጫል።

ዴሞክራሲ ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የለውም የሚሉ ሰዎች ኣሁን የሚጠቅሱዋትን የቻይናን ጉዳይ ጥቂት ብናይ መልካም ሳይሆን ኣይቀርም። በርግጥ የቻይና ኢኮኖሚ ያለ ዴሞክራሲ ነው ወይ ያደገው?

ለቻይና እድገት ሶስት ጉዳዩች ጉሉህ ኣስተዋጾ ሳያደርጉ ኣልቀሩም
1) የቀረጸችው ለእድገት ኣመቺ የሆነ የኢኦኖሚ ፖሊሲ

ይህ ፖሊሲዋ ቻይናን ባንድ በኩል የዴሞክራቲክ መልክ እንዳላት ያሳያል። ዛሬ ሶስት ኣራተኛ የሚሆነው የቻይና ህዝብ በፍትሁ በፍርድ ቤቶቻቸው መተማመን(trust) ኣላቸው። በዚህም ጣሊያንን ጨምሮ ከኣንዳንድ ዴሞክራት ኣገሮችም በላይ ቻይና በዚህ በኩል ተሽላ ተግኝታለች ማለት ነው። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ኣስር ከሚሆኑት ቻይናውያን ሰባቱ ኣመቺ የሆነ ኢንተርፕሩነር ኣካባቢ(environment) ተፈጥሩዋል ብለው ያምናሉ።

ቻይና የግል ተቁዋማቱን በለቀቀች ቁጥር ኣጠቃላይ እድገቱዋ እየጨመረ ሲመጣ ይታያል። የገበያ ነጻነት በሰጠች ቁጥር እድገትን ታያላች። ዛሬ የግሉ ሴክተር ከሃገሪቱ GDP ከፍተኛውን ድርሻ ይዙዋል። ይህ የኢኮኖሚ ፖሊሲዋ የዲክተተሮች መልክ የለውም ።

2) ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ ሃብት (Social Capital) ኣላት

በሌጋተም 2011 ጥናት መሰረት በሚገርም መልኩ 60 በመቶ የሚሆኑት ቻይናውያን ሌሎችን የሚያምኑ ናቸው። ይህ መተማመን ትልቅ ሃብታቸው ሲሆን ይህም በኣንስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ኢንቨስት ለማደርግ ስንቅ ሊሆናቸው ይችላል። ተዋረዳዊ መተማመን(trust) ላጋራ እድገትና ልማት ግብዓት ነው።

3) ሌላው በርግጥ ከውጭው ኣለምም ጋር ከፍተኛ ፍክክር ውስጥም የገባች ትመስላለች። ይሄ ኤነርጂዋ ምናልባትም ግፊት ፈጥሮላት ሊሆንም ይችላል።

ዋናው ግን ከፍ ሲል ያነሳናቸው ሁልቱ ጉዳዩች የዲክቴተርስ ሳይሆን የዴሞክራት መልክ ይሰጣታል። ይህ ደባል ስብእናዋም ነው ኣንዴ ቅይጥ ሌላ ጊዜ ድብልቅ ኣገር እያልን እንድንጠራት ያደረገን። ታዲያ ቻይና ዴሞክራሲን ሙሉ በሙሉ ባለማስተነገዱዋ በኢኮኖሚ ያላደጉ ኣገሮች በምሳሌነት ሊጠቅሱዋት የሚገባ ኣይመስልም። ዴሞክራሲን ለኢኮኖሚ እድገት ሃይል ኣድርገው ያደጉ ብዙ ኣገሮች ኣሉና።

geletawzeleke@gmail.com

Reference

http://www.prosperity.com/

የብሄር ትርጉሙ

Monday, April 30th, 2012

የብሄር ትርጉሙ ባልፉት ሃያ ኣመታት ውሰጥ በውነት ከቸኩ ቃሎቸ መካከል አንዱ “ብሄር “ የሚባለው ቃል ነው። በመሰረቱ ብሄር የሚለው ቃል መነሻው ኣማርኛ ነው። ይታወቅበት የነበረውም ትርጉም የትውልድ ኣካባቢ ነው። ለዚህም ነው ተስፋ ስላሴ ዘ ብሄረ ቡልጋ፣ አፈወርቅ ገብረየሱስ ዘ ብሄረ ዘጌ፣ ምናምን የሚባለው መሰለኝ። በዚሁ ሂሳብ ከሄድን ባሁኑ ሰኣት ማለት የምንችለው ኣቶ ሃጎስ በላይ ኣዲስ ኣበባ ከተወለዱ ዘ ብሄረ ኣዲስ ኣበባ ፣ ክቡር ዶክቶር ብርሃኑ ነጋ ዘ ብሄረ ደብረዘይት፣ እምሻው ለጥ ይበሉ ዘብሄረ ሃረር፣ ቶላ ድሪባ ዘ ብሄረ መንዝ፣ ክቡር ኣቶ ኣንዳርጋቸው ጽጌ ዘ ብሄረ ኣዲስ ኣበባ፣ እያለ ይቀጥላል ማለት ነው። ታዲያ ወያኔዎች ለምን ይህን የ ቦታ ወይም የግዛት ስም ወስደው ከ ጎሳ ፖለቲካ ላይ እንደለጠፉት ኣይታወቅም። ምን ኣልባት የጎሳ ፖለቲካ ኣሳፋሪ በመሆኑ ጎሰኛ የሚለውን ስም ለመሸፈን ይሆናል። የጎሳ ፖለቲካ ቅድስና ያለው ስላልሆነ በፊት ለፊት ለመጥራት ያፍሩበታል። ዋናው ደሞ የቃላቱ ጨዋታ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ መንግስት የሚያራምደው ፖለቲካ ታእታይ ቅርጹ (deep structure) ባህላዊ ቡድኖችን ሚና እንዲለዩ በማድረግ ግጭት ማራገብ በዚያም ሾልኮ በስልጣን መሰነባበት ነው። በመሆኑም የወያኔዎች ፖለቲካ የ ብሄር ምናምን ሳይሆን የ ባህላዊ ቡድነኝነት ፖለቲካ ኣራማጆች ናቸው ። ይህ ኣይነቱ ፖለቲካ የሳተው ትልቅ መሰረታዊ ነገር የ ቡድኖችን ገስጋሽ እና ለውጥ ናፋቂ ተፈጥሮ ነው። በተለይ በዚህ ክፍለ ዘመን ሳይንስ ራሱ የኣለምን ቁሳዊ ባህል እያዋሃደው በመጣበት ጊዜ እንዲህ ኣይነቱ በባህል ቡድን ላይ የሚሰራ ፖለቲካ ማደሪያ የለውም። በሃጋራችን ይህ ፖለቲካ ከባህል እና ቋንቋ ልዩነት ጋር ተጣብቆ ሲመጣ መጀመሪያ የተጋጨው ከየ ባህላዊ ቡድኑ እየቀደሙ በኣለም ኣቀፉ የባህል ልውውጥ እና በርስበርሱ የባህል ውህደት ጎዳና ላይ ካሉ ገስጋሽ ዜጎች ጋር ነው። ርግጥ ነው የባህልና የቋንቋ ልዩነት በኢትዮጵያ ውስጥ ኣለ። ታዲያ የኣስተዳደር ጥበብ ሲታሰብ 90 የፖለቲካ ድርጅት ኣቋቁሞ እኔ እቀድም እኔ መጀመሪያ በሚል ጨዋታ ኣይደለም የምንተዳደረው። የቡድን ፖለቲካ ውስጠኛ ስሜት እኮ ቋንቋን የወሰን መከለያ ድንጋይ ኣድርጎ በኣንድ ልል በሆነ ማእከላዊ መንግስት ስር መኖር ነው። ይህ ደሞ ኣንድ ቀን ፖለቲካው ሲፈርስ ብትንትናችን እንዲወጣ ያደርጋል። የኔን ባህል ኣትንካ እኔም ያንተን ኣልነካም ኣይባልም። የኔን ቋንቋ ኣትንካ እኔም ያንተን ኣልነካም ኣይባልም። እንዲህ ኣይነቱ ነገር ብንፈልገውም እንኩዋን ኣለማቀፋዊው ነባራዊ ሁኔታ ኣይፈቅድልንም። ይሄም ባህል መጠበቅ ማለት ኣይደለም። ኣንዳንዴ ደሞ ለውዽዽር ወይም ለክርክር መቅረብ የሌለባቸውን ማተላያ (false goods) እያመጡ ህዝብን ያደናግራሉ። የቡድን መብት ይቅደም ወይስ የግለሰብ መብት ይቅደም፧ በመሰረቱ የመቀዳደም ጉዳይ ኣይደለም ዋናው ነገር ዴሞክራሲ ራሱ ይቅደም። እሱ ሲቀድም ቤቱን በሰው ልጆች የመጨረሻ የልዩነት ቅንጣት ላይ ይሰራና ቡድኖችን ይንከባከባል። ይህ ማለት መጀመሪያ ግለሰብ ከዘያ ቀስ ብሎ ቡድን ማለት ኣይደለም። እንዲህ ኣይነቱ በተግባር ኣይገጥምም ከገጠመም ጤነኛ ዴሞክራሲ ኣይሆንም። የሰው ልጅ ለብቻውም ከሰው ጋርም ነው የሚኖረውና። የቡድንም የግልም ህይወቱ እሽቅድምድም ውስጥ ሳይገቡ ሊንከባከባቸው ይፈልጋል። ዶሮዋ ናት የምትቀድመው ወይስ እንቁላሉ የሚል የጊዜ ማጥፊያ ክርክር እዚህ ጋር ኣይሰራም። መሽቀዳደማቸው ሳይሆን ኣንዱ ያላንዱ ያለመኖራቸውን ማሳቡ የበለጠ ይጠቅመናል። እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ geletawzeleke@gmail.com