Author Archive
#Ethiopia: የአድዋ [ዕ]ድል
Friday, March 1st, 2013መቶ ዐሥራ ሰባት ዓመት ወደኋላ፤ መጀመሪያ (ከዚህም ዓመታት በፊት) አውሮጳውያን ኃያላን በበርሊን ያደረጉት ‹‹አፍሪቃን የመቀራመት›› ስምምነት ይቀድማል፡፡ ሁሉም የየራሳቸውን ሲወስዱ፣ ጣሊያንም ኢትዮጵያ (እና ሶማሊያ…) ደርሰዋት ነበር፡፡ የመጀመሪያው የጣሊያን ጦር በባሕርምላሽ (የአሁኗ ኤርትራ) በኩል ሲመጣ የወቅቱ የባሕርምላሽ ገዢ የነበሩት የራስ አሉላ እንግዳ (አባ ነጋ) ሠራዊት የጣሊያንን ሠራዊት ዶጋሊ ላይ በተደረገ ፍልሚያ ከ500 ወታደር 100 ብቻ በሕይወት አስቀርቶ መለሰው፡፡ ያኔ የጣሊያን ፓርላማ ተሰበሰበ፤ ተሰብስቦም አላበቃ በ332 ለ40 አብላጫ ድምፅ ወደኢትዮጵያ ተጨማሪ (5000ሺ ወታደር የያዘ) ሠራዊት ለመላክ ወሰነ፡፡
ከዚያ በኋላ ነው የውጫሌ ውል የተከተለው፡፡ ለጠነከረ ወዳጅነት እና ለጋራ ተጠቃሚነት በምኒልክ እና በጣልያን መልእክተኛ መካከል የተፈረመው የውጫሌ ውል ደግሞ አማርኛውና ጣልያንኛው አንድ ዓይነት ትርጉም ይኑረው ቢልም አንቀጽ 17 ‹‹ኢትዮጵያ የጣልያን ሞግዚት›› እንድትሆን በተዘዋዋሪ የሚያታልል ነበር፡፡ ትርጉሙ ሲነቃበት ዐጤ ምኒልክ ውድቅ ከማድረግ አልተመለሱም፡፡ እንግዲህ የአድዋ ጦርነት መነሻ የሚባለው ይህ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ለኢጣሊያ የበርሊን ስምምነት ሽልማት መሆኗ ግን መሠረቱ ነው፡፡
ጦርነቱ ሲጀመር አገር ዘመተ፡፡ 80,000 ኢትዮጵያውያን ለጦርነቱ ሲወጡ ከነዚህ ውስጥ ቆመህ ጠብቀኝ ጠብመንጃ የታጠቁት ጥቂቶቹ ነበሩ፡፡ ሌላው ጦርና ጋሻውን እየሰበቀ ወጣ፡፡ በጣሊያን በኩል ደግሞ 18,000 ወታደሮች ተሰለፉ፡፡ የአገር ፍቅር፣ የጀግንነት እና የአትንኩኝ ባይነቱ ጦርነት ተጀመረ፡፡ ጀግኖች ተጋደሉ፤ በዕለቱ ጦርነት ማብቂያ ላይ የጣልያን ሠራዊት በአውሮጳውያን የቅኝ ገዢነት ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ እልቂት አስተናገደ፡፡ እስከ 7,000 የሚገመቱ የጣሊያን ወታደሮች ሞቱ፣ 3000 ያህል ተማረኩ፤ በኢትዮጵያ ወገንም 4,000 የሚጠጉ ተሰዉ፣ የቆሰሉት ደግሞ ከ10,000 በላይ ነበሩ፡፡ ድል ለኢትዮጵያ ሆነ፡፡
የድሉ ዜና እንደተሰማ የጣልያን ጋዜጦች የጣልያንን ሠራዊት ‹‹ውኃ፣ ውኃ›› ያሰኘችውን የእቴጌ ጣይቱን ፎቶ በሽፋን ገጻቸው ላይ ይዘው ሲወጡ፣ የጣልያን ሕዝብ ደግሞ ውርደቱን ለማውገዝ ‹‹ሆ…›› ብሎ አደባባይ ወጣ፡፡ የ‹‹ኃያል አገራቸው በምስኪን አገር መሸነፍ›› ያንገበገባቸው ጣልያናውያን በሮም ከፍተኛ ነውጥ ከሰቱ፤ ፖሊስ ነውጡን ለመበተን ቢተጋም ተቃውሞው ግን በአድዋ ድል ሳምንት የወቅቱን የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስፒን ከስልጣን አስለቅቋል፡፡
የአብሮነት ዕድል
የአድዋ ድልን ለመመስከር ከበቁ ሰዎች መካከል አንድ እንግሊዛዊ ኮሎኔል የአድዋ ድል ኢትዮጵያውያንን ያስተሳሰረ ‹‹መግነጢሳዊ ምስጢር›› ነው ብሎታል፡፡ የዐፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መሳፍንትን የማፈራረስ እና አንዲት ኢትዮጵያ የመመስረት ሕልም፣ በዚህም በዚያም በሚያምፁ አገረ-ገዢዎች ሳቢያ አልተሳካም ነበር፡፡ ዐፄ ዮሐንስም ያንን የዐፄ ቴዎድሮስ ሕልም በራሳቸው መንገድ ለማሟላት ተፍጨርጭረው፣ ነገር ግን ዘመናቸውን በሙሉ በጦርነት እንደዋተቱ ተሰውተው አልፈዋል፤ ዐፄ ምኒልክንም የዚሁ ዕጣፈንታ ሰለባ ከመሆን ያተረፋቸው የአድዋ ጦርነት እና ድል ነው፡፡
የአድዋ ጦርነት ሠራዊት ሁለት ሦስተኛ ያዋጡት ዐጤ ምኒልክ ናቸው፡፡ ቀሪውን ግን የሸፈነው የየአካባቢው ነገሥታት እና ገዢዎች ሠራዊት ነው፡፡ በወቅቱ ከዐፄ ምኒልክ ጋር ስምምነት ላይ ያልደረሱ (ወይም ማዕከላዊ መንግሥታቸውን ያልተቀበሉ) በርካታ አገረገዢዎች ሳይቀሩ ከጎናቸው ተሰልፈው ልዩነታቸው በአገር ውስጥ ጉዳይ እንጂ ከአገር ውጪ በሚመጣ ጉዳይ አንድነታቸውን አስመስክረዋል፡፡ ከጦርነቱ መልስም የምኒልክ ማዕከላዊ መንግሥት በመጠናከሩ ኢትዮጵያ አሁን ያላትን ቅርፅ ለመያዝ የሚያበቃ አቅም እና ጥንካሬ አፈራች፡፡
ዐጤ ምኒልክ ከአድዋ መልስ በመጠኑ የተረጋጋ፣ የተባበረ እና ሰላማዊ አገር መምራት በመቻላቸው አሁንም ድረስ የዘለቁ በርካታ ‹‹የመጀመሪያ›› ነገሮችን ለመመስረት የቻሉት ድሉ ባመጣው ዕድል ነው፡፡
የመታወቅ ዕድል
‹‹የሃይማኖት ጠላቶቿን ሽሽት በሯን ዘግታ ለአንድ ሺሕ ዓመታት ተኝታ የውጪውን ዓለም ረስታ፣ የውጪው ዓለምም ረሳት›› የተባለቸው ኢትዮጵያ ስሟ በድጋሚ እንዲታወቅ አድዋ ዕድል ሆነላት፡፡ የአድዋ ድል የአውሮጳን የዓለም መሪነት ለመጀመሪያ ጊዜ ጥያቄ ውስጥ የጣለ ገጠመኝ ነው፡፡ የዓለምን ታሪክ በሁለት ከፍለን ብንመለከተው፣ አውሮጳውያን ወደላይ እየገሰገሱ የመጡት እስከአድዋ ዘመን ሆኖ ልክ ከዚያ በኋላ ቀስ በቀስ ለአሜሪካ አስረክበው ቁጭ እንዳሉ ማስተዋል እንችላለን፡፡
የጣልያኖችን ሽንፈት የሰሙት አሜሪካኖች በኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣቸው ላይ ብቻ ያሰፈሯቸውን ዐብይ ርዕሶች እናስታውስ “Italy’s Terrible Defeat,” “Italy is Awe-Struck,” “Italy Like Pandemonium,” እና “Italy’s Wrathful Mobs.” የጣልያን ሽንፈት፣ የጣልያን ውርደት ይላሉ እንጂ ባለአገሯ ኢትዮጵያ፣ አገሯን ተከላክላ ማሸነፏ ኢትዮጵያን ርዕስ ላይ አላስቀመጣትም ነበር፡፡
ሆኖም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ነገሮች መለወጥ ጀመሩ፡፡ የዓለም መንግሥታት በሙሉ ከምኒልክ መንግሥትጋ የተለያዩ ስምነቶችን ለማድረግ ይጣደፉ ጀመር፡፡ ብዙ የአውሮጳ መንግሥታት ቆንስላቸውን በኢትዮጵያ መሠረቱ፣ ከዚሁጋ ተያይዞ ዘመናዊ ትምህርት፣ ቴክኖሎጂዎች እና ዘመናዊ አስተዳደርም ቀስ በቀስ እየተስፋፋ መጣ፡፡
የአድዋ ድል፣ ኋላ ለመጣው የማይጨው ድል እና በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ኢትዮጵያ በዓለም ዙሪያ ለነበራት ስመ ገናናነት ፈር ቀዳጅ ነው፡፡
የነጻነትና እኩልነት ዕድል
ጥቁሮች ከነጮች ያነሱ ፍጡራን አለመሆናቸውንና ራሳቸውን በራሳቸው መምራት እንደሚችሉ በዓለም ፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ያስመሰከሩት በአድዋ ድል ነው፡፡ የአድዋ ድል ዜና ፀጥ-ለጥ ብለው ይገዙ ለነበሩ አፍሪካውያን ከ‹‹እንቢተኝነት›› ጀርባ ‹‹ነጻነት›› እንዳለ እንዲገባቸው አድርጓል፡፡ አውሮጳውያን አሁንም ድረስ አፍሪካን ከተኛችበት እንደቀሰቀሷት ያምናሉ፡፡ እነርሱ ባያነቁን ኖሮ ተኝተን የ‹‹ጃንግል›› ኑሯችንን ብቻ እንደምንገፋ ይጽፋሉ፡፡ እኛም ኢትዮጵያውያን እንዲሁ ነው የምናስበው፣ አፍሪካውያንን ባናነቃቸው ኖሮ ያለምንም ቅሬታ እየተገዙ ይኖሩ ነበር፤ ምናልባት ቢነቁ እንኳን ‹‹ማንነታቸው›› አሁን ከጠፋው በላይ ሙሉ ለሙሉ ከከሰመ በኋላ ነበር፡፡
#Ethiopia, #StopCensorship: ሐሳብን በነጻ መግለጽ በኢትዮጵያ – ሕገ መንግሥት ላይ እና በተግባር
Thursday, February 21st, 2013በበፍቃዱ ኃይሉ
ሰሞኑ ‹‹የሕገ-መንግሥቱ›› ይከበር የበይነመረብ ዘመቻ 2ኛ ዙር በአንቀጽ 29 (ሐሳብንና አመለካከትን የመያዝና የመግለጽ መብት) ይከበር ዙሪያ በዞን ዘጠኝ አስተባባሪነት እየተካሄደ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ለዘመቻው ግብአት እንዲሆኑ አንዳንድ እውነታዎችን ስለሕገመንግሥቱ እና ስለቀደሙት፣ ስለአተገባበሩም ጭምር እነሆ፡-
ሐምሌ 30/1966 በንጉሡ ነገሥት መንግሥት ረቂቅ ሕገ-መንግሥት፡-
አንቀጽ 25/1
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሐሳብ ነፃነት አለው፡፡ ማናቸውንም ሐሳብ በንግግር፣ በጽሑፍ ወይም በሌላ ዘዴ የመግለጽና የማሰራጨት እንዲሁም ሌሎች የገለጹትን የማወቅ መብት አለው፡፡
አንቀጽ 25/2
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መስከረም 1/1980 ያወጣው ሕገ-መንግሥት፡-
አንቀጽ 47/1
የኢትዮጵያውያን የንግግር፣ የጽሑፍ፣ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ትዕይንተ ሕዝብ የማድረግና በማኅበር የመደራጀት ነጻነት የተረጋገጠ ነው፡፡
አንቀጽ 47/2
መንግሥት ለነዚህ ነጻነቶች ተግባራዊ መሆን አስፈላጊውን ቁሳዊና ሞራላዊ ድጋፍ ያደርጋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት (ሕዳር 29/1987)፡-
አንቀጽ 29
የአመለካከት እናሐሳብን በነጻ የመያዝናየመግለጽ መብት
1. ማንኛውምሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነትየመሰለውን አመለካከት ለመያዝይችላል፡፡
2. ማንኛውምሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነትሐሳቡን የመግለጽ ነጻነትአለው፡፡ ይህ ነጻነትበሀገር ውስጥም ሆነከሀገር ውጭ ወሰንሳይደረግበት በቃልም ሆነበጽሑፍ ወይም በሕትመት፣በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫዘዴ፣ ማንኛውንም ዓይነት መረጃናሐሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨትነጻነቶችን የካትታል፡፡
3. የኘሬስናየሌሎች መገናኛ ብዙኃን፣እንዲሁም የሥነ ጥበብፈጠራ ነጻነት ተረጋግጧል፡፡ የኘሬስነጻነት በተለይ የሚከተሉትንመብቶች ያጠኝልላል፣
ሀ/ የቅድሚያ ምርመራ በማንኛውምመልኩ የተከለከለ መሆኑን፣
ለ/ የሕዝብን ጥቅም የሚመለከትመረጃ የማግኘት ዕድልን፡፡
በተራ ቁጥር 1 እና 2 ላይ እንደተመለከተው ንጉሡም ሆኑ ደርግ ሙሉ ሐሳብን የመግለጽ መብት መውጫቸው/መውደቂያቸው ሰዓት ላይ ለመስጠት ሞክረዋል/ሰጥተዋል፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት የሽግግር መንግሥቱ ሕገ-መንግሥት ላይ የብሔሮች መብት እስከመገንጠልን ያሰፈረ ቢሆንም ስለሐሳብ ነጻነት የሚናገረው የለም፡፡ በ1987ቱ ሕገ-መንግሥት ግን የተሻለ የሚባል የሐሳብ ነጻነትን ፈቅዷል፡፡ ከሌሎቹ መንግሥታቶች እርምጃም የሚለየው የፕሬስ ሕጉ ወጥቶ በተግባር ላይ የሚውልበት መንገድ መመቻቸቱ ነው፡፡ ሆኖም ሁሉም ነገሮች ባሉበት አልቀጠለም፡፡ የተሻሻለው የፕሬስ አዋጅ፣ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅና ሌሎችም መልሰው የመብቱን ወሰን አጥብበውታል፡፡ ነገር ግን አሁን ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ገደብ የሚከናወነው በአስተዳደራዊ አፈና ነው፡፡
ከ1983 ወዲህ ያሉ እውነታዎች፡-
1. የመጀመሪያው ነጻ ጋዜጣ ‹‹ዕይታ›› ይባላል፤ የፕሬስ አዋጁ ከመውጣቱ በታኅሳስ ወር 1984 መታተም ጀምሯል፡፡ የቅጁ ብዛት ከ50,000 እስከ 70,000 ይደርስ ነበር፡፡ በወቅቱ በርካታ ‹‹የስም ማጥፋት›› ክሶችን በመንግሥት አስተናግዷል፡፡ በመጨረሻም የቅጂ ብዛቱ ወደ 5,000 ደርሶ በጥቅምት ወር 1986 ሕትመቱ ተቋርጧል፡፡ (ቅድመ ምርጫ 97 አካባቢ ይታተሙ የነበሩ ጋዜጦች እትም እስከ 1050,000 ድረስ ከፍ ብሎ የነበረ ቢሆንም ከዚያ በኋላ እያሽቆለቆለ መጥቶ በ2004 መጨረሻ ላይ ሕትመቱ የተቋረጠው እና የወቅቱን እጅግ ከፍተኛ ቅጂ ያሳትም የነበረው ነጻ ጋዜጣ ፍትሕ ነበር፡፡ ፍትሕ የታገደበትን የመጨረሻ እትሙን በ30,000 ቅጂ ነበር ለብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ያዘዘው፡፡ በጥር ወር ስርጭት ላይ ከዋሉ ጋዜጦችን ያስመዘገበው የሪፖርተር እሁድ እትም ሲሆን እሱም 11,000 ነው /የብሮድካስት መረጃ/)
2. እስከ ሐምሌ 1989 ብቻ 265 ጋዜጦች እና 120 መጽሔቶች ሕጋዊ ፈቃድ ወስደዋል፡፡ …… (በጥር ወር ለስርጭት የበቁት 12 የፖለቲካ ጋዜጦች፣ 6 የስፖርት እና 1 የጤናና ስነልቦና ጋዜጦች እና 21 መጽሔቶች ናቸው፡፡)
3. በሕግ ባይከለከልም በኢትዮጵያ ለአንድም የግል ተቋም የቴሌቪዥን አገልግሎት አልተፈቀደም፡፡ ብቸኛው የግል አገር አቀፍ ሬዲዮ ስርጭት የፋና ሬዲዮ ሲሆን ሬዲዮ ፋና ንብረትነቱ የሕወሓት/ኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ነው፡፡ ሬዲዮ ፋና በተለያዩ ከተሞች ኤፍ ኤም ስርጭቶችን በማሰራጨት፣ የራሱን ሕንፃ በማስገንባት ወደኮርፖሬትነት ለማደግ የቻለ የመጀመሪያው እና ብቸኛው ሬዲዮ ጣቢያ ነው፡፡ ሸገር እና ዛሚ ኤፍ ኤሞች ሌሎች ‹‹በገለልተኛ›› የተያዙ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ሲሆኑ፤ የሸገር ትኩረት ማኅበራዊ ጉዳዮች ሲሆኑ፣ የዛሚ ትኩረት ደግሞ የመንግሥትን ፖሊሲ ማበረታታት እና ማሞካሸት ላይ ያተኮረ ነው፡፡
የካምፓስ ተማሪዎች የጎሳ ግጭት፤ ከመነሻው እስከ መድረሻው
Monday, February 11th, 2013ይህ ጽሑፍ ባለፈው ወር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ በብሔር ሰበብ በተነሳ ፀብ ላይ ተመስርተው በተከታታይ ድረገጾች ላይ የተጻፉ ጽሑፎች መነሻነት የተጻፈ ማጠናከሪያ ሐተታ ነው፡፡ ስለሆነም እዚህ ውስጥ የተበታተኑት የሰዎቹ ውይይት አጽርኆት (summary) እና ተጨማሪ ሐሳቦች ይንፀባረቃሉ፡፡
ጃዋር መሐመድ (የፖለቲካ ተንታኝ) ነበር ውይይቱን የጀመረው፤ በጽሑፉ ‹‹ዩኒቨርሲቲዎች ነጻ መንፈስ ተኮትኩቶ የሚያድግባቸው፣ እልፍ ገጽታ ያላቸውን ችግሮቻችን ለመፍታት የሚያስችሉ አዳዲስ ሐሳቦች የሚፈልቁበት የላቀ እና ገንቢ ውይይቶች የሚካሔዱባቸው ቦታዎች መሆን ይገባቸዋል፡፡ በተቃራኒው ግን፣ የኢትዮጵያ ኮሌጆች የዘረኝነት፣ ጠባብነት እና አመጽ መፈልፈያ እየሆኑ ነው፡፡›› ይላል፡፡
እኔም በዚህ ጽሑፍ ይህንኑ ጉዳይ ከታሪክ እና ከወቅታዊ ጉዳዮች አንጻር እመላለስበታለሁ፡፡
ለመሆኑ መቼ እና በማን ተጀመረ?
የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ዕድሜ አጭር በመሆኑ ብሔር-ነክ ግጭቶች መቼ እንደተጀመሩ የሚዘረዝር መረጃ ማግኘት ቢቸግርም እንኳን ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ) እንደሆነ መገመት አይቸግርም፡፡ ሆኖም በቅርቡ በጆን ያንግ የተጻፈ፣ Peasants Revolution of Ethiopia የሚል ርዕስ ያለውን መጽሐፍ ሳገላብጥ ያገኘሁት አንቀጽ አጀማመሩን የሚገልጽ መስሎኝ ወስጄዋለሁ፡፡
“…ዊንጌት ውስጥ … በአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሚመሩ የትግራይ ተወላጅ ተማሪዎች በቅርጫት ኳስ ጨዋታ ላይ በተነሳ አለመግባባት ከኦሮሞ ተወላጆች ጋር ተጋጩ፡፡ ከዚያ ቀጥሎ መለስ በጣም አወዛጋቢ የነበረውን እና በአድዋ ጦርነት ወቅት የትግራይ ተወላጆች ከየትኛውም ብሔረሰብ የበለጠ የሕይወት እና የሰው ኃይል ከፍለዋል፣ ምኒልክንም ለድል አብቅተዋል የሚል የታሪክ ጽሑፍ አቀረቡ…” (ገጽ 82) እያለ ይቀጥላል፡፡
ይሁን እንጂ የካምፓስ ውስጥ የዩንቨርስቲ ግጭት ድምፅ አግኝቶ የቀጠለው በኢሕአዴግ ዘመን ነው፡፡ ለዚህ እንደ መንስኤ ሊቆጠር የሚችለው (1). የብሔር ፌዴራሊዝሙ፣ እና (2). ከደርግ አፈና በኋላ የተመለሰው አንጻራዊ የመነጋገር ነጻነት ነው፡፡ በደርግ ዘመን የብሔር (በጥቅሉ የፖለቲካ) ውይይት በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የመነሳት ዕድሉ ጠባብ ስለነበር ግጭቱም አይነሳም ነበር፡፡ የወቅቱን ዝምታ ራንዲ ሮኒንግ ባልስቪክ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ ባተመላቸው የዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ ጥናታዊ ጽሑፋቸው (The Quest for Expression: State and The University in Ethiopia Under Three Regimes. 1952-2005) ላይ እንዲህ ገልጸውታል፡፡
‹‹…ከአብዮቱ ፍንዳታ 10 ዓመት በኋላ (የአ.አ.) ዩኒቨርሲቲን እና በጥቅሉ ማኅበረሰቡን ከጠበቅኩት እና በንጉሡም ሆነ በክፍለዘመኑ መጨረሻ - በመለስ ዜናዊ መንግሥታዊ-ስርዓት ካየሁት በላይ በፍርሐት ተሸብቦ ነበር፡፡ ሕይወት ተስፋ በሚያስቆርጥ መልኩ የማይጠበቅ እና ደኅንነት የጎደለበት ሆኖ ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተማሪዎች ማንኛውንም አስተያየት በአገሪቱ ውስጥ እየተከናወነ ስላለ ጉዳይ ከመስጠት ይቆጠቡ ነበር፡፡ ምክንያቱም ንግግራቸው ሁሉ ፖለቲካዊ ትርጉም ይሰጠዋል፡፡…››
ጸሐፊው ወደኢሕአዴግ ዘመን ሲመልሱን፣ ‹የዩኒቨርሲቲው ዶርሚተሪዎች በጎሳ ተከፋፍለዋል፤ አማራዎቹ የጎሣ ጽንፈኝነትን ሲቃወሙ ኦሮሞዎቹ ተማሪዎች ደግሞ ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸውን እንደተነጠቁ ይሰማቸዋል፡፡ በትግሬዎቹ እና ቀሪዎቹ መካከል ደግሞ ቀዝቃዛ ጦርነት ተከፍቷል› ይላሉ፡፡ በ1993 የኦሮሞ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው ቤተ መጽሐፍት ውስጥ ተለቅመው እንዲጠፉላቸው የሚፈልጉትን ቃላት ዝርዝር በፊርማ ለወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አስገብተው ነበር፡፡ ይሄ ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ ተማሪዎቹ የማይፈልጓቸው ቃላቶች ያሉባቸውን መጽሐፍት ገጾች እየቀደዱ መውጣት ጀመሩ፡፡
ከዚያ በኋላ ብሔር ነክ ጥያቄዎችን በውስጥ ለውስጥ ሽኩቻ መመለስ፣ በየብሔሩ እየተቧደኑ ማኅበራዊ ግንኙነት መመስረት እና ከማኅበራዊ ግንኙነቱ መስመር ውጪ ያለውን ሁሉ በጠላትነት መፈረጅ፣ አለምግባባቶች ሲኖሩ መደባደብ ‹‹ብዝኃነት (plurality)›ን ዒላማ ያደረገው የዩንቨርስቲ ሕይወት ክሽፈት መለያ ሆነ፡፡
የካምፓስ ተማሪዎች ለምን በብሔር ይጋጫሉ?
ሀ. የመንግሥት ሴራ?
ጃዋር መሐመድ ‹የኢትዮጵያ ካምፓሶች ዓይናውጣ ጦርነት፤ መነሾ ግብ እና ተጽዕኖ› በዳሰሰበት ጽሑፉ መንግሥት ከመነሻ እስከመድረሻው ድረስ ተጠያቂ መሆን እንዳለበት ያትታል፡፡ ለጃዋር ዋና የካምፓስ ተማሪዎች ብሔር ነክ ግጨቶች መንስኤ የሚባሉት ሁለት ናቸው፤ (1). የአካዳሚያዊ ነጻነት አለመኖር (ነጻ ማኅበራት አለመፈቀዳቸው፣ የመወያያ የተማሪዎች ሕትመቶች አለመኖራቸው እና መታገዳቸውን ይጨምራል)፣ (2). የገዢው ፓርቲ የስለላ አባላት ተማሪዎቹ ውስጥ መሰግሰጋቸው እና የመከፋፈል ሚና መጫወታቸው፡፡
ጃዋር በትንታኔው ‹‹ማኅበራት እንዲኖሩ አለመፈቀዱ የባሕል እና ማንነት ልውውጥ እና ትውውቅ ዕድል ስለማይሰጥ፣ የካምፓስ ማኅበራዊ ክበቡ በግምት፣ በተሳሳተ መረጃ፣ እና በጥርጣሬ ስለሚሞላ ለጠባብነት እና አግላይነት መንገዱን ይጠርጋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ካምፓስ ደግሞ ለቡድን አመጽ የተጠመደ የጊዜ ቦምብ ነው፡፡›› በማለት በዩንቨርስቲዎቻችን የሚነሱት ግጭቶች በማኅበራት እና መሰል ውይይቶች ሊፈቱ የሚችሉ ጥያቄዎች በፍራቻ እና አካዳሚያዊ ነጻነት ባለማግኘት ምክንያት የሚፈጠሩ መሆናቸውን ያስረዳል፡፡ እንደጃዋር ገዢው ፓርቲ ይህንን የሚያደርገው ዘመነ ሥልጣኑን ለማስረዘም ‹ከፋፍለህ ግዛ› የተሰኘ ስልት ስለሚጠቀም እንጂ የችግሩ መንስኤ ጠፍቶት አይደለም፡፡
በተመሳሳይ መንገድ በ1990 አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ግቢ ውስጥ (ስድስት ኪሎ) በጎሳ ጉዳይ በተነሳ ግጭት ፖሊስ እርምጃ ሲወስድ “ማንኛውም ኦሮሞ ስም ያለው ሰው ወደእስር ይገባል፤ የትግራይ እና አማራ ስም ያላቸው ተማሪዎችን ግን ከሌሎቹ ለይተው ‹እነዚህ የኛ ሰዎች ናቸው›፤ ወይም ‹እነዚህ የኛ ናቸው ተዉኣቸው› ይላሉ፤” በማለት ራንዲ ጽፈዋል፡፡ ይህ ሁለት የፖሊስ ዓይን የሚያንፀባርቀው መንግሥት ጉዳዩን ከላይ የሚመለከትበትን ሁኔታ ነው፡፡
ይህ ዓይነቱ የመንግሥት/የፖሊስ ችግሩን አፈታት የኦሮሞዎቹን ተማሪዎች የመጠቃት ስሜት እንደሚያጋግለው እና ጎሳዊ ጽንፈኝነት ውስጥ ሊከታቸው እንደሚችል መገመት ከባድ አይደለም፤ ጃዋርም በዚህ ይስማማል፡፡ የኦሮሞ ተማሪዎች ተለይተው መለቀማቸው ሌላውን በጥርጣሬ እና በአጥቂነት እንዲመለከቱት እና ጥላቻ ውስጥ እንዲወድቅ ያደርገዋል ይላል፡፡
እዚህ ጽሑፍ ላይ ተመስርተው የተሰጡ ምላሾች የዚህን መንስኤ እውነታነት አስረግጠው፣ ነገር ግን ጃዋር ዘነጋቸው የሚሏቸውን ተጨማሪ የግጭት መንስኤዎች ይጠቁማሉ፡፡
ለ. የኦሮሞ ተማሪዎች የመቻቻል ባሕል ማነስ?
ዐብይ ተክለማርያም (የቀድሞዋ አዲስ ነገር ጋዜጠኛ) ለጃዋር ትንታኔ በሰጠው አጭር የምላሽ ማብራሪያ ላይ በጽሑፉ ይዘት እውነትነት ቢስማማም የጥፋተኝነቱን ድርሻ ለመንግሥት ብቻ መስጠቱ ተገቢ አይደለም ይላል፡፡ ዐብይ የምናወራውን ነገር እርግጠኝነቱን ለማወቅ ጥልቅ ጥናት ያስፈልጋል ቢልም፤ ጉዳዩ ግን አሁን እንደምንለው ‹ጥቁር እና ነጭ› ብቻ እንዳልሆነ ተናግሯል፡፡ መንግሥት ብቻ መወቀስ የለበትም የተማሪዎቹ የመቻቻል ባሕል ማነስ ለእሳቱ ነዳጅ አቀብሏል ነው አባባሉ፡፡ እሱ እንደሚለው የኦሮሞ አክቲቪስቶችየፀረ-ነፍጠኛ ትርክት ለዚህ ተጠያቂ ነው፡፡
እውነት ነው፤ የኦነግ ትግል የተጧጧፈው በ‹‹ኦሮሞ ኮሎናይዜሽን›› ትርክት ነው፤ ኦነግ እና ብዙዎቹ የኦሮሞ ፖለቲካ አራማጆች የሚያምኑት የኦሮሞ ሕዝብ በብሔሩ ብቻ ሲጨቆን (‹‹ቅኝ ሲገዛ››?) ኖሯል እና አሁን ነጻ መውጣት አለበት ብለው ነው፡፡ እርግጥ ነው፤ ነጻነትን ከመገንጠል አጀንዳ ጋር ማራመዳቸውን አሁን ብዙዎቹ ቀይረውታል፡፡ ያለመገንጠል ‹‹እኩል ነጻ ሆኖ መኖር ይቻላል›› በሚል - ሆኖም ግን አሁንም ድረስ ጭቆናው አለ ብለው ማሰባቸው ለመቧደን እና ከሌላው ጋር እንዲጋጩ፣ ሌላውን በጥርጣሬም እንዲመለከቱ አድርጓቸዋል፡፡ አሁንም በዙሪያቸው ያለው ሁሉ የ‹‹ነፍጠኛ›› የበላይነቱን ሊያራምድብን ነው በሚል የመፈረጅ ሁኔታ አለ፡፡ ይህም ለተደጋጋሚ ግጭቶች መቀስቀስ መንስኤ ይሆናል፤ ከላይ እንደተጠቀሰውም መንግሥትም ሊጠቀምበት ይችላል፡፡
በዚህ መሐል ግን የሚነሳ አንድ ጥያቄ ይኖራል፡፡
ለምን ኦሮሞ ብቻ?
ዘላለም ክብረት (የሕግ መምህር) የጃዋርን እና ዐብይን ምልልስ አስከትሎ ባሰፈረው አስተያየት አዘል ጽሑፉ እሱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበረበት ወቅት የግጭቱ ሰለባ መሆኑን ጠቅሶ፣ ነገር ግን ባያቸው ግጭቶች ውስጥ ሁሉ የኦሮሞ ተማሪዎች መኖራቸውን ጠቅሷል፡፡ ተደጋጋሚ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ግጭቶችን የተመለከትን እንደሆነ ግጭቶቹ ሁሉ የኦሮሞ ተማሪዎችን ይነካል፡፡
ራንዲም ከላይ በጠቀስነው ጽሑፍ ላይ ሦስት የካምፓስ የጎሳ ቡድኖች መኖራቸውን ይናገራሉ፡፡ ኦሮሞዎች፣ የገዢው ፓርቲ ደጋፊ ናቸው በሚል የሚፈረጀት ትግሬዎች እና አማራዎች፡፡ ራንዲ ከደቡብ የመጡት አማራዎቹ ቡድን ውስጥ እንደሚመደቡ ተናግረዋል፡፡ በእርሳቸው መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሱት ግጭቶች ሁሉ ሰለባ የሆኑት፣ የተከሰሱት እና የታሰሩት ኦሮሞዎች መሆናቸው ግጭቱ በአብዛኛው ኦሮሞዎችን በማዕከላዊነት የሚያካትት እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡
እንግዲህ በዚህ እውነታ ላይ ተመርኩዘን ስንሄድ የኦሮመ ተማሪዎችን አንድም ሆነ ብሎ የሚተነኩሳቸው አለ (የመንግሥት ሴራ እንደተባለው) አለ አሊያም እነርሱ (የመቻቻል ባሕል) ችግር አለባቸው የሚል አጣብቂኝ ጥርጣሬ ውስጥ ይጥለናል፡፡
የኦሮሞ ሕዝብ ከሌላው ጋር…?
የኦሮሞ ተማሪዎችን የመቻቻል ባሕል ለመፈተሽ በተቻለን አቅም ወደኋላ መለስ ብለን የኦሮሞ ሕዝብ ከሌላው ማኅበረሰብ ጋር እንዴት ተቻችሎ ይኖር እንደነበር መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ በዚህም የምናገኘው ተማሪዎቹን ከከሰስንበት ተቃራኒውን ነው፡፡ ዶ/ር ዶናልድ ሌቪን ስለኦሮሞ ሦስት ዓይነት ትርክቶች በሚያውሩበት ጽሑፋቸው የኦሮሞ ሕዝብን የመቻቻል፣ እና ከሌላው ጋር በፍጥነት የመዋሀድ ችሎታ እንዲህ በአድናቆት አስፍረውታል፡፡
‹‹ለመላመድ፣ ለመመሳሰል፣ እና ለእርስበርስ ጋብቻ ያላቸው ፈቃደኝነት ምስጋና ይግባውና፣ የኦሮሞ ሰፋሪዎች በሄዱበት ሁሉ ካለው ሕዝብ ጋር ተዋህደዋል፡፡ የግልጽነት እና ወዳጅነት ባሕሪያቸው አዲስ መጤዎች ማኅበረሰባቸውን እንዲቀላቀል የሚጋብዝ ነው፡፡ በየሰፈሩበት አጎራባች ቦታዎች ካሉ ሰዎች ጋር ጦርነቱ ለጊዜውም ይሁን በዘላቂነት ከመቆሙ የሚዛመዱበት ነገር አያጡም፡፡ ይህ ከሌሎች ጋር የመወዳጀት ችሎታቸው እነርሱ የሌሎችን፣ ሌሎችም የነርሱን ባሕል እንዲወራረሱ አድርጓል፡፡ ኦሮሞዎች በሰሜን ክርስትናን፣ በምስራቅ ደግሞ እስልምናን ተቀብለዋል፤ በደቡብ ምዕራብ ግዛተነገሥት ሲያቋቁሙ በሸዋ ደግሞ እርሻ ጀምረዋል፡፡ ከአማርኛ ተናጋሪዎች ጋር በቀላሉ መቀላቀል መቻላቸው ምስጋና ይግባውና ቀድሞ ሴማዊ የነበረው እና ከግዕዝ፣ ትግርኛ፣ አረቢኛ፣ እና እብራይስጥ የመጣው አማርኛ ቋንቋ አሁን የምስራቃዊ ኩሽ ሰዋሰው፣ ግስ እና ዘዬ ከኦሮምኛ ቋንቋ ወርሶ ወስዷል፡፡
‹‹በደቡብ፣ እነዚህ ቅልቅሎች ሁሉንም ቡድን ያሳትፋሉ፡፡ ስለዚህ፣ በጉራጌ ዞን አካባቢ የሰፈሩ ኦሮሞዎች የእንሰት ባሕልን በመውረሳቸው በኦሮሞዎች ሳይቀር ‹‹ግማሽ ጉራጌ›› በመባል ይቀለድባቸዋል፡፡ የጉጂ ኦሮሞ ኦቱዎች ከሲዳማ ባሕል ጋር በጣም ከመቀላቀላቸው የተነሳ አንዳንዶቹ ሲዳምኛ ብቻ ነው የሚናገሩት፡፡ በሌላ በኩል፣ የጉጂ ኦሮሞዎች የሲዳማ እና ወላይታ ሰዎችን ወደራሳቸው ባሕል ወስደው ቀላቅለዋቸዋል፡፡››
ይህን ስናነብ፤ ይህን ዓይነት የመቻቻል እና የመላመድ ባሕርይ ካለው የኦሮሞ ሕዝብ አብራክ ውስጥ የወጡት ተማሪዎችን የመቻቻል ባሕል ያንሳቸዋል ለማለት ስር የሰደደ መሰረት እናጣለን፡፡ እናም ‹‹የአሁኑ ተማሪዎች ግጭት የኦሮሞ ተማሪዎች የመቻቻል ባሕል ማነስ ከየት መጣ?›› ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን፡፡ እንግዲህ ለዚህ ጥየቄ የሚቀረን መልስ ጃዋር በጽሑፉ ጠቅሶት እንደነበረው ‹‹የመንግሥት ካድሬዎች ትንኮሳ›› አሊያም ዐብይ እንዳለው ‹‹የፀረ-ነፍጠኛ ትርክት የዘለቃቸው ተማሪዎቹ የመቻቻል ባሕል ማነስ›› ለችግሩ ተጠያቂዎች ሆነው ይቀራሉ፡፡
የግጭቶቹ መነሾዎች
ዘላለም በጽሑፉ ‹‹የሐጎስ እና ገመቹ የግል ፀብ ወደ ትግሬ እና ኦሮሞ ተማሪዎች ያድጋል›› በማለት ግለሰባዊ አስተሳሰብ በቡድን እየተተካ እንደሆነ ያለውን ስጋት ጠቁሟል፡፡
የካምፓስ ውስጥ ፀቦች በግለሰቦች ግጭት ብቻ አይደለም የሚነሱት፤ በቃላት አጠቃቀምም ጭምር ነው፡፡ አንዱ ሌላኛውን ለማብሸቅ፣ ወይም ባለማወቅ በሚጠቀመው የተነወረ ቃል (the “G…” word) ሳቢያ የተነሳ ፀብ… ምናልባትም በውቀቱ ስዩም (ማኅበራዊ ሐያሲ) አስተያየት ሲሰጥ ‹‹ይህን ያለው የምን አገር ተወላጅ ነው ከማለት በፊት ማነው ያለው?›› ለማለት ባለመቻላቸው የሚመጣ ችግር ነው፡፡
ዐብይ የ‹‹ነፍጠኛ›› መጽሐፍትን በማጣቀሳቸው ክፍል ውስጥ በካምፓስ ተማሪ ኦሮሞዎች የተደበደቡ መምህራን ስለመኖራቸው ብዙ ታሪክ መስማቱን ጽፏል፡፡ ዘላለምም የተነወሩ ቃላትን የሚጠቅሱ መጽሐፍት ገጾች በየካምፓሱ ላይብረሪ ተቀድደው አልቀዋል ብሏል፡፡ የሁለቱንም አስተያየት ያደመጠ ሰው መጀመሪያ ሊጠይቅ የሚችለው ጥያቄ ቢኖር ‹‹መጽሐፍቱን በማጥፋት [ያልተወደደውን] ታሪክ ማጥፋት ይቻላል ወይ?›› የሚል ነው፡፡
‹‹ሰዎች በቋንቋቸው መማር ይገባቸዋል›› ብሎ እንደሚያምን የጠቀሰው ዐብይ ‹‹የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተለያዩ ዓይነት አመለካከቶችን ማወቅ እንዳለባቸውም›› አክሎ ተናግሯል፡፡ ይህንኑ ሐሳብ የሚያጠናክረው ደግሞ ዘላለም ክብረት ነው፤ በሁለቱ ተንታኞች ምልልስ ላይ ተመርኩዞ በጻፈው ጽሑፍ ላይ እንዳሰፈረው ጉዳዩን ትቶ በመጽሐፍቱ መኖር/አለመኖር፣ ለመማሪያነት መጠቀስ/አለመጠቀስ ማዕከላዊ ጉዳይ ሆኖ መወሳቱ እና “መጽሐፍቶቹ ከቤተ መጽሐፍቱ እንዲወጡ መጠየቅ መሳቂያነት/ዕብደት ነው” ብሏል፡፡
ከላይ እንዳየናቸው ግጭቶቹ መነሾዋቸው አንድ ወይም ሁለት ግለሰቦች ወይም ደግሞ ቃል ቢሆንም ቅሉ ግን ተጠቂ የሚሆኑት በተለያየ ቡድን/ብሔር ውስጥ የታጠሩ ሰዎች ሁሉ ናቸው፡፡ ይህ እንግዲህ ዩኒቨርሲቲዎች ከተለያዩ ክልል የመጡ ተማሪዎችን ቀይጠው በማስተናገድ ከነልዩነት አብሮ መኖር እንዲችሉ የማድረጉ ሙከራ ምን ያህል ከስኬት እንደራቀ የሚያሳይ ውጤት መሆኑ ነው፡፡
ለመሆኑ መፍትሔ አለው?
መፍትሔ የሌለው ችግር የለም፤ ምንም እንኳን ካምፓሶች በየብሔሩ ሽምቅ የሚዋጉ ማኅበረሰቦችን ቢያፈሩም ተማሪዎቹ ከዩንቨርስቲ ሲወጡ የሚኖሩበት ማኅበረሰብ ከተማሪዎቹ እጅግ የላቀ የመቻቻል ባሕል ስላለው እንደዚያ ዓይነቱ ነገር ማኅበረሰቡን የመበጥበጥ ዕድሉ ጠባብ ሆኖ ከርሟል - ቢያንስ እስካሁን ድረስ፡፡ ምክንያቱም ተማሪዎቹ ተመርቀው ሲወጡ የሚኖሩበት ብዝኃ-ብሔሮችን አቅፎ የተቀመጠ ከተማ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ነገሮች እየተባባሱ ከሄዱ እና ካሁኑ ፈር ካልተበጀላቸው ነገሩ የተገላቢጦሽ ሊሄድ ይችላል፡፡ ተማሪዎቹ የካምፓስ ውስጥ አግላይ-አቋማቸውን በማኅበረሰቡ ውስጥ ሊያስተጋቡ እና ማኅበረሰቡም ሊቀበላቸው ይችላል የሚል ስጋት አለኝ፡፡
ለዚህ ነው ችግሩን ‹‹የካምፓስ ተማሪዎች ዛሬም እንደለመዱት በብሔር ተጋጩ›› ብቻ ብለን እንደዋዛ ማለፍ የማይኖርብን፡፡ ችግሩን እንዳያዳግም አድርጎ ለማባረር የመጀመሪያው መፍትሔ የሚሆኑትን ካሁኑ ማፈላለግ ያሻል፡-
ሀ. ማውራት፣ ማውራት፣ ማውራት
በውቀቱ ስዩም የመጨረሻው የካምፓስ ተማሪዎች ግጭት የተከሰተ ዕለት (በታኅሳስ ወር/2005) በጻፈው አንጀት አርስ ጽሑፉ መደምደሚያ ላይ ‹‹መፍትሄው ምሁራዊ አይናፋርነትን ትቶ መወያየት ነው፤›› ብሎ መክሯል፡፡ ‹‹በተደጋጋሚ እንደምናየው፣ ባንዱ ኃጢያት ሌላው ይሙት የሚል ብሉያዊ አስተሳሰብ የካምፓስ ልማድ የሆነ ይመስላል፡፡ ብዙ የተማሩ፣ የተመራመሩ ሰዎችን እንዴት አንድ ተንኳሽ ሊያተራምሳቸው ይችላል?››ብሎ አንድ በቃላት በሚነሳ ጦርነት እንዴት እንደሚከፋፍለን እና የመወያየት ባሕላችን ማነስ ‹‹ቃላት›› እንኳን መቋቋም እንዳነሰን ታዝቧል፡፡
ጎሣዊ ነውረኛ ቃላት ከመጽሐፍት ውስጥ እና ከመጽሐፍት ገጾች እንዲወገዱ ከመጣር ይልቅ አማራጭ ትርክት ፈጥሮ፣ የትኛው የተሻለ እንደሆነ ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን ባለማውራት፣ እና አፍን በመለጎም ከዕውቀት መታቀብ እንጂ ለውጥ አይመጣም፡፡ በዝምታ እና በመፈረጅ ፍርሐት ከማለቅ በጫፍ አልባ ሙግት ውስጥ እያለፉ እያደጉ መኖር ይሻላል፡፡
ለ. አራማጆችና ምሁራን በትርክቶቻቸው መቻቻልን አይርሱ
በቀለ ገርባ በ‹‹አሸባሪነት›› ፍርዱ ብያኔ ላይ ማቅለያ ሲጠየቅ ከተናገረው ውስጥ ትግሉን ‹‹…በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ግፍና መከራ እንደሚገባ ሳልገልጽ ቀርቼ ከሆነና ይህንንም ያደረኩት ለሕዝቦች አብሮ መኖር ከማሰብና ከወንድማማችነት ላነሰ ተግባር ከሆነ የኦሮሞን ሕዝብ… [በደሉን] ከሚገባው በላይ አጋንኜው ከሆነና ይህንንም ያደረኩት ለግል ጥቅምና ዝና ከሆነ እግዚአብሔርንይቅርታ እጠይቃለሁ…›› ብሎ ነበር፡፡ ያ የበቀለ ንግግር የብሔር ነጻነት ትግል አጀንዳን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡
አሁንም የብሔር ነጻነት አራማጆች የሚታገሉለትን የብሔሮች እኩልነት እና ነጻነት ዒላማ ካልዘነጉ በቀር ሁልጊዜም በግጭት እና ከሌላው ጋር በመቆራቆስ የሚመጣ ለውጥ እንደሌለ በቅጡ መረዳት ይኖርባቸዋል፡፡ ስለዚህ የተለያዩ ትርክቶች ይህንን ሐቅ ዘንግተው አንዱ ከሌላኛው ጋር ጠላትነት በማፍራት የሚመጣ ነጻነት እንደሌለ በማመን መቻቻልን ያገናዘበ ትርክት ይዞ ከአጉል ጽንፍ እና ‹‹ጽንፍ ነው አይደለም›› ሙግት መውጣት እና ለኅብረተሰቡ አብሮ፣ በነጻነት እና እኩልነት መኖር የሚበጅ የመፍትሔ ሐሳብ መቀየስ እና መታገል ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ ጉዳዩን ለግል አጀንዳ በማራገብ ችግሩን ማክፋት እንጂ ማቅለል ይከብዳል፡፡
ሐ. መንግሥት የሚበጀውን ይወቅ
ጃዋር ሕዝቦች በምንም ይሁን በምን (በተለይ በብሔር) ከተከፋፈሉ መንግሥት ላይ የማመጽ አቅምም አንድነቱም ስለማይኖራቸው፣ ዕድሜው እንዲረዝምለት ይፈልገዋል ይላል፡፡ ሆኖም፣ ይህ ዓይነቱ የከፋፍለህ ግዛ ጫወታ፣ በእሳት የመጫወት ያክል ነው ይላል የገዛ ሐሳቡን ሲያጠናክር፡፡
መንግሥት የብሔር ፌዴራሊዝም ከ‹‹መለያ-አጀንዳነት›› ይልቅ የአተገባበር እና ሌሎቹም ችግሮች እንከኖቹን ነቅሶ እንዴት ማስተካከል እንደሚቻል ተጨንቆ መሥራት ይኖርበታል፡፡ ‹‹የብሔር ጥያቄ ተመልሷል›› ብሎ በደረቅ ዓረፍተነገር ለማሳመን ከመሞከር ይልቅ በየአቅጣጫው የሚነሱ ጥያቄዎችን ማዳመጥ ይበጃል፡፡ የተለዩ የብሔር አባላት የሚመረጡበት፣ የተለዩ የብሔር አባላት የሚገለሉበትን ያልተጻፈ አሠራር የምር መታገል እና የምር የብሔረሰቦችን እኩልነት ለማስፈን ቁርጠኝነቱን ማሳየት አለበት፡፡
ስለዚህ መንግሥት ከጊዜያዊ የሥልጣን ማስቀጠያነት ተሻግሮ የረዥም ዓመት ሕልም ማፍራት አለበት፡፡ የጎሳ ግጭት ለማንም አይበጅም፤ እርስ በእርሱ የሚበጣበጥ ሕዝብ ይዞ መምራት ብሎም ብጥብጡን ሥልጣን ለማስረዘሚያነት እስከመጠቀም ማለም ደግሞ የጅል ብልሐት መሆኑን አውቆ መንግሥታችን መጠንቀቅ እና ወደቀልቡ መመለስ ይኖርበታል፡፡
መ. ከመንደረተኛነትን አስተሳሰብ መላቀቅ
‹‹ጠባብነት›› የሚለው ሐሳብ የሚመጣው ሰዎች ከራሳቸው ዙሪያ ውጪ ሌላ ዓለም እንደሌለ በማሰብ ልዩነትን መረዳት እና ከነልዩነት አብሮ መኖር ሲያቅታቸው ነው፡፡ ይህንን ነው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ‹‹መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ›› በሚለው መጽሐፋቸው ‹‹መንደረተኝነት›› ሲሉ የገለጹት፣ እኔ ልንገላገለው/ልንጠነቀቅለት ይገባል የምለውን አስተሳሰብ ከእርሳቸው በምዋሰው አንቀጽ አብራራዋለሁ፡-
‹‹…መንደረተኛነት ማለት ከመንደር በማይወጣ አስተሳሰብና ከመንደር በማይወጣ ስሜት መመራት ነው፤ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ለሚኖሩ ሰዎች ዓለማቸው መንደራቸው ነች፤ ከዚያች መንደር ውጪ ሌላ ዓለም የለም፤ ቢኖርም የሚንቁትና የሚጠሉት ነው፤ መንደረተኛነት በግድ ብዙ የአስተሳሰብ ግድፈቶችን ያስከትላል፤ የራስን መንደር የዓለም እምብርት የሆነችና ዓለምንም ኢምንት አስመስሎ በመገመት፣ መንደርዋን ወሰን-የለሽ በማድረግ አስተያየትን ያጠናግራል፤ በአስተሳሰብም ደረጃ መንደረተኛነት ቁሞ-ቀር ያደርጋል፤ የአካል፣ የአእምሮንና የመንፈስን ዕድገትና እርምጃ ያፍናል፤ መንደረተኛነት የታሪክን መሠረትና የታሪክን ትክክኛ አካሄድ ለመረዳትና የታሪክ ባለቤት ለመሆን የሰው ልጅ የአለውን ችሎታ በመቀነስ ትልቅ እንቅፋት ይሆናል፡፡…››
መደምደሚያ
ጃዋር መሐመድ እና ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ በኦነግ ርዕዮተ-ዓለም ላይ በተከራከሩበት የጽሑፍ ምልልስ ላይ ጃዋር የተጠቀመውን ሐረግ ብጠቀም ጥሩ መደምደሚያ ይሆነኛል፡-
‹‹…ኢትዮጵያ ያላለቀች ፕሮጀክት ነች፡፡ በመጨረሻዋ ቅርጹዋ ላይ ሁላችንም የየራሳችን ሚና አለን፡፡ ነገር ግን ይህ እንዲሆን የሚያስፈልገን ትንሹ የባሕሪ ለውጥ አርስበርስ መደማመጥ፣ አንዱ የሌላውን ሕመም መረዳት እና እውነታውን ሳያዛቡ እንዳለ ማቅረብ ነው፡፡ …››
“መክሸፍ” እንደ ኢትዮጵያ ሚዲያ – መጽሔቶች
Monday, February 4th, 2013ወቅቱ መጽሔቶች እንደአሸን የፈሉበት፣ ጋዜጦች ደግሞ ቁጥራቸው የተመናመነበት ነው፡፡ ብዙዎቹ [የአማርኛ] መጽሔቶች የሚወጡት በየ15ቀኑ ቅዳሜ ቀን ነው፡፡ ጥቂቶች በወር አንዴ እና አዲስጉዳይ ብቻ በየሳምንቱ ይታተማል፡፡ በመጽሔቶቹ ታሪክ አንጻራዊ ደረጃ ሊሰጠው የሚችለው እና የራሱን ስም (ብራንድ) እየገነባ ነው ሊባል የሚችለው አዲስጉዳይ ነው፡፡ በየሳምንቱ መውጣቱ፣ የመጽሔት ቅርጽ (structure) መያዙ፣ በርካታ ጸሐፊያን እና አምደኛ ያሉት መሆኑ ለዚህ አስተዋጽኦ አድርጎለታል፡፡ ሌላው ቀርቶ አዲስ ጉዳይ በየ15 ቀኑ፣ ከዚያም በየሳምንቱ መታተም መቻሉ በራሱ ሌሎቹንም ስቧቸዋል፡፡ ባለሙሉ ቀለም ለመሆንም የመጀመሪያ አርኣያቸው ሆኗል፡፡ ይሁን እንጂ አዲስጉዳይም ቢሆን በተለይ ከይዘት ጥንካሬ ትችት ማምለጥ አይችልም፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን አዲስ ጉዳይን እና ሌሎቹን መጽሔቶች በአንድ መስፈርት መመዘኑ ተገቢ ስለማይሆን እሱን ነጥለን ትተን ሌሉቹ /አብዛኛዎቹ መጽሔቶች/ ላይ ያሉትን ችግሮች እና “ከሽፈዋል”፣ በአዲስ መንገድ ትንሳኤ ያስፈልጋቸዋል ብለን እንከራከራለን፡፡
በማስተዋል አሳታሚ ከተገዛ በኋላ የተለየ ጥንካሬ ያላቸው ፖለቲካዊ ትችቶችን በበርካታ ጸሐፍት ያስተናግድ የነበረው አዲስ ታይምስ ጋዜጣም ተስፋ ሰጪ ነበር፡፡ ነገር ግን የአዲስ ታይምስ ሕትመትም ለጊዜው በመቋረጡ በዚህ ጽሑፍ አንዳስሰውም፡፡
ይዘት
ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ያገላበጥናቸው መጽሔቶች ሁሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ ከአንድ፣ ሁለት በቀር ቋሚ አምድ የላቸውም፡፡ ይህም የተዘበራረቀ ሐሳብ ያላቸውን ጽሑፎች እዚህም እዚያም በመሰደር፣ የአንባቢን ሐሳብ በአንድ ማኖር እንዲሳናቸው አስገድዷል፡፡ ይህ ጉዳይ ተጽዕኖውን የሚያሳድረው በአንባቢዎቻቸው ብቻ ሳይሆን በመጽሔቶቹም በራሳቸው ላይ ነው፡፡ መጽሔቶቹ በየጊዜው የሚያወጧቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በተመለከተ ሦስት እና አራት ነገሮችን ብቻ ማስተዋል ይችላል፡፡ እነዚህም፡- የቴዲ አፍሮ የግል እና የግል ያልሆኑ ጉዳዮች፣ የሃይማኖት ልዩነት እና መከፋፈል አጀንዳዎች፣ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ጉዳይ እና አሁን ደግሞ - ገበያው ይጠይቃልና - የአገር ውስጥ ፖለቲካ ጉዳዮች ናቸው፡፡
መጽሔቶቹ በነዚህ ጉዳዮች ላይ እንደየወቅቱ ወረት ‹‹መንደረተኛ›› ሊባል በሚችል መልኩ ጉዳዮችን ያራግባሉ፡፡ ነገር ግን በጽሑፎቻቸው አንጽሮተ-ዕይታ ለመጨመር አይሞክሩም፤ ሌላው ቀርቶ አንዱን አጀንዳ እጅግ በሚያሰለች መልኩ ለረዥም ጊዜ ይዘው ማመንዠክ ይወዳሉ፡፡ እንደምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ስለጤፍ መወደድ መንስኤ ብለው የተናገሩትን ብዙዎቹ መጽሔቶች እንደርዕስ መዝዘው ይይዙት እና ነገር ግን ምንም ፋይዳ የሌለው ትንተና ከርዕሱ የበለጠ ዋጋ በሌለው ሐተታ ያቀርባሉ፡፡ (ይህ ዜና ማመንዠክ አባዜ የቀድሞው ጠ/ሚኒስተር ሞትን እንዲሁም ተከትለው የመጡ የፓለቲካ ወሬዎችን ይጨምራል፡፡)
የጽሑፎቹ ወጥነት - “ኢቪዲኦን ወደ ወረቀት?”
መጽሔቶቹ ብዙ ቦታዎች ላይ የጽሑፎቹን ጸሐፊ ስም ሳይጠቅሱ ያልፋሉ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ሁለት ነው፡፡ የመጀመሪያው ምክንያት ጽሑፎቹ ወጥ ሥራዎች (originals) ስላልሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ጥቂት አባላት ብቻ ስለሚኖሯቸው እና እነዚያው ጸሐፍት ሁሉንም ነገር (ፖለቲካውን፣ ፋሽኑንም፣ ኢኮኖሚውንም፣ ማኅበራዊውንም፣ መዝናኛውንም) ብቻቸውን ስለሚጽፉት እንዳይታወቅ ከመፈለግም ነው፡፡
በሰው ኃይል እጥረትም ይሁን በፈጠራ ማነስ መጽሔቶቹ ወጥ ያልሆኑ ሥራዎችን ሲያትሙ ስም እንኳን ለመጥቀስ የሚዘነጉበት፣ የዋነኛውን ጸሐፊ ፈቃድ ለማግኘት እንኳን የማይገዱበት እና ኢትዮጵያዊ ካልሆነ እንዲያውም የራሳቸው የፈጠራ ጽሑፍ እንደሆነ አስመስለው የሚያቀርቡበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡
እዚህ ላይ በምሳሌ ሳይጠቀስ የማይታለፉት የዳንኤል ክብረት እና የአቤ ቶክቻው ጽሑፎች ናቸው፡፡ የዳንኤል ክብረት ጽሑፎች አዲስጉዳይ ላይ ታትመው፣ ከዚያ የግል ድረገጹ ላይ ከወጡ በኋላ ከዚያ ተገልብጠው መልሰው ሌሎች መጽሔቶች ላይ ማንበብ የተለመደ ድራማ ነው፡፡ አቤ ቶክቻውም በግል ድረገጹ ላይ የሚያትማቸው ፖለቲካዊ ወጎች ከአንድ በላይ በሆኑ መጽሔቶች ላይ በአንድ ቀን ታትመው የሚወጡበት አጋጣሚ በርካታ ነው፡፡
በዚህ እና በሌላም መንገድ መጽሔቶቹ ግፋ ቢል ከ5 እምብዛም በማይበልጡ፣ እንዲያውም ብዙ ጊዜ የማይጽፉ ነገር ግን ለመጽሔቱ ሞገስ ሲባል ስማቸው ብቻ በሰፈሩ አምደኞች ስም ከለላ በጥቂት ጸሐፊዎች ቁንጽል ሐሳብ በሚስተናገዱ በርካታ ጽሑፎች እና በይነመረብ እና ማኅበራዊ አውታሮች ላይ በሚገለበጡ ጽሑፎች ጥገኝነት ገንዘብ ብቻ በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ ይህንን የመጽሔቶቻንን ነገር ያየ ሰው ኢቪዲኦን ወደ ወረቀት የመቀየር ሥራ ላይ ብቻ መጠመዳቸው በሐፍረት አንገት ሊያስደፋው ይችላል፡፡
እውነታ ማዛባት
የመጽሔቶቻችን ሌላኛው ትልቁ ችግር እውነታ ማዛባት ነው፡፡ ለምሳሌ ቆንጆ መጽሔት በቁጥር 34 እትሙ ‹‹ብርቱኳን ስዬን በነጻ ለቃለች›› የሚል ነገር በጽሑፉ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ብርቱኳን አቶ ስዬን በዋስትና የለቀቀች መሆኑን መረጃ ለሌለው አንባቢ የተለየ እውነት ሰጥቶ ያሰናብተዋል ማለት ነው፡፡
መጽሔቶች እውነታውን የሚያዛቡት በስህተት ብቻም አይደለም፡፡ ገንዘብ የተቀበሉለትን (በተለይ የጥበብ) ሥራ አዋድዶ በመጻፍም አሳፋሪ ተግባር ውስጥም አይታጡም፡፡ በዚህ መደድ፣ ለምሳሌ ባለፈው ቅዳሜ (ጥር 19/2005) የወጡት ሎሚ እና ማራኪ መጽሔቶች በከተማዋ ምንም ሊባል በሚችል መንገድ ያልተደመጠውን የብርሀኑ ተዘራ ‹‹ተበቺሳ›› አልበም እንዴት አሞካሽተው እንዳለፉት ማንበብ ጥርጣሬውን ለማረጋገጥ መንገድ ይሆነናል፡፡ ሎሚ (ቁጥር 40) ‹‹ተበቺሳ ከሚገባው በላይ ነው ተቀባይነቱ›› ሲል፤ ማራኪ (ቁጥር 33) ደግሞ ‹‹ብርሀኑ ተዘራ ገበያውን እየመራ ነው›› ይለናል፡፡ ጽሑፉን ሲያስነብቧችሁ ግን ማስረጃቸው የቃላት ድርደራ ብቻ ሆኖ ታገኙታላችሁ፡፡
ርዕሰ አንቀጽ
የመጽሔቶቹ ድክመት ጣሪያ የሚነካው በርዕሰ አንቀጾቻቸው ነው፡፡ ብዙዎቹ መጽሔቶች ለ40 ገጽ እትማቸው ግማሽ ገጽ ርዕሰ አንቀጽ መጻፍ አይችሉም፡፡ የሚጽፏቸው አንቀጾችም ቢሆኑ ጠንካራ ጉዳዮችን ለመንካት የማይደፍሩ፣ አቋም ይዘው የማይሞግቱ ናቸው፡፡ ሎሚ መጽሔት ‹‹ማንዴላ በነጻ ወታደራዊ ስልጠና ያገኙባት አገር በመሆኗ፣ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ወደደቡብ አፍሪካ ለመሄድ ቪዛ ፍለጋ መቸገር የለባቸውም›› የሚል መከራከሪያ ርዕሰ አንቀጹ ላይ አስፍሯል፡፡ ቆንጆ መጽሔት ርዕሰ አንቀጽ የጻፈለትን ጉዳይ (የውኃ ክፍል፣ ቴሌ እና መንገድ ትራንስፖርት ተስማምተው እንዲሰሩ የሚመክር አንቀጽ) ዋና ትንታኔ ‹ሦስቱ ባዶ ወንበሮች› በሚል ጽሑፍ አስቀምጧል፡፡ ሆኖም ጽሑፉ የተወሰደው ከኤፍሬም እሸቴ (አደባባይ) የግል ድረገጽ ላይ ነው፡፡ ኤፍሬም በመጽሔቱ ላይ በአምደኝነትም ሆነ በአዘጋጅነት ስሙ አልሰፈረም፡፡
ባለፈው ቅዳሜ (ጥር 19/2005) ከወጡት መጽሔቶች ሁሉ በአንጻሩ ጥሩ ርዕሰ አንቀጽ ይዞ ወጥቷል ሊባል የሚችለው ላይፍ መጽሔት ሲሆን ‹‹ኢቲቪ የመንግሥት ሌባ?›› የሚል ጥያቄ አቅርቦ በአንጻሩ የተሻለ ለመሞገት ሞክሯል፡፡፡፡
የሽፋን ገጽ እና የገጽ ቅንብር
የዲዛይን ጉዳይ ሌላኛው የመጽሔቶቻችን አንባቢዎች የራስ ምታት ነው፡፡ የሽፋን ገጽ ዲዛይኖች ብዙውን ጊዜ በብዙ ምስሎች የታጨቁ ከመሆናቸው የተነሳ የትኛውን አይተን፣ የቱ ላይ ማተኮር እንዳለብን ራሱ ግራ ያጋባሉ፡፡ ሊያ መጽሔት (በቁጥር 20) በአንዲት የሽፋን ገጹ ላይ ብቻ የቴዲ አፍሮ፣ ኃ/ማርያም ደሳለኝ፣ ሰብለ ተፈራ፣ አማኑኤል በቀለ፣ መኣዛ መንሥቴ እና ‹ፎርቹን› ጋዜጣ EPRDF Generation በሚል ርዕስ ከረዥም ጊዜ በፊት ለጻፈው ጽሑፉ የተጠቀመበትን ጀርባቸው ብቻ የሚታዩ 9 ወጣቶች ምስሎች አትሞ ወጥቷል፡፡
ሎሚም (በቁጥር 40) እትሙ ሰባት የውስጥ ታሪኮቹን ርዕስ በምስል አስደግፎ ሽፋን ላይ አትሟቸዋል፤ ላይፍ መጽሔትም (በቁጥር 99) አምስት የውስጥ ታሪኮቹን ምስል ሽፋን ገጹ ላይ አውጥቷል፡፡ መጽሔቶቹ በተጨማሪም በውስጥ ገጾቻቸው ቋሚ የሚባል የጽሑፍ አቀማመጥ፣ የፎንት መጠን እና ዓይነት አመራረጥ፣ የምስል አደራደር የላቸውም፡፡ ይህ ሁሉ ተደማምሮ ሲታይ የአንባቢን የማንበብ ፍላጎት ጥርቅም አድርጎ ለመዝጋት ሲባል የተፈጠሩ ያስመስላቸዋል፡፡
ተስፋ ሰጪዎቹ
መጽሔቶቹ በዚህ ሁሉ የመክሸፍ አደጋ ውስጥ ሆነውም እንኳ ተስፋ ሰጪዎች ከውስጣቸው አይታጡባቸውም፡፡ እንደምሳሌ ዕንቁን እና ቁምነገርን መውሰድ ይቻላል፡፡ ዕንቁ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ የሆኑ ጽሑፎችን በበርካታ ቋሚ አምደኞች እና አዘጋጆች፣ በተወሰነላቸው ርዕሰ ጉዳዮች እና ሙያዊ ዕውቀቱ ባላቸው ሰዎች እያስተናገደ በየ15 ቀኑ የሚታተም መጽሔት ነው፡፡ (የይዘታቸው ጉዳይ ገደቡ እንዳለ ሆኖ) ቁምነገርም በተለይ በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአብዛኛዎቹ መጽሔቶች ተርታ ለመውጣት የመሻሽል እርምጃዎችን ለማድረግ እየሞከረ መሆኑ የሚደነቅ ነው
የከሸፉትን ማን አከሸፋቸው?
ጥያቄው በጥናት የተደገፈ መልስ ያስፈልገዋል፡፡ ሆኖም ከአክሻፊዎቻቸው መካከል ፈጣሪያቸው ኢሕአዴግ እንዳለበት መናገር ቀላል ነው፡፡ ኢሕአዴግ የግል መገናኛ ብዙኃንን ከፈቀደ በኋላ ቀስበቀስ፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እየገደላቸው ነው፡፡ ስስ ወይም ፋይዳ የሌላቸውን ጽሑፎች ብቻ የሚነግሡበትን ባሕል የፈጠረውም የቁጥጥር ፍቅሩ ነው፡፡ ጠንካራ እና የተሻለ ይዘት ያላቸው የሕትመት ውጤቶች በአንባቢ እጦት ሳይሆን በኢሕአዴግ በጎ ፍቃድ እጦት ከገበያ በአጭሩ ይሰናበታሉ፡። አስተዳደራዊ ተግዳሮቶችን መፍጠርና ሲብስም የሕግን ከለላነት መጠቀሚያ የሚያደርገው መንግሥት መጽሔቶችን “አደጋ ወደሌለበት ማኅበረሰባዊ ለውጥ ወደማያመጣ ጨዋታ” ገፍቷቸዋል፡፡ ነገር ግን በክሽፈቱ ውስጥ የአሳታሚዎቹ ለሥራ ጥራት ቁርጠኛ አለመሆን እና ትርፍ ተኮር መሆን ትልቅ ሚና ያለው መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡
አሁን ነጻ ጋዜጣ ማሳተም በኢትዮጵያ ‹‹የማይቻል›› ደረጃ እየደረሰ ያለበት ነው፡፡ ብዙዎቹ የግል ማተሚያ ቤቶች ማተም የሚችሉት መጽሔት በመሆኑ እና ፖለቲካዊ መረጃዎችን ለማግኘት ሕዝቡ ረሀቡን በመጽሔቶች እያሳየ በመሆኑ መጽሔቶቹ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ተገደዋል፡፡ ነገር ግን አሁን ያለው የመጽሔቶች የአቅርቦት ባሕል መቀየር አለበት፡፡ ስለዚህ ትልቁ ቁምነገር ግን መጽሔቶቹን ማን አከሸፋቸው ሳይሆን እንዴት ወደትንሳኤ ይምጡ የሚለው ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ የመጀመሪያው ጉዳይ ችግር እንዳለባቸው በማመን ችግራቸውን ለይተው ለማወቅ እና ለማረም ቁርጠኝነት ላይ እንዲደርሱ መምከር ነው፤ ከዚያ ስም ያለው መጽሔት ለመገንባት መውሰድ የሚገባውን ‹ሪስክ› ሁሉ መውሰድ፡፡ ይህንን ለሚሞክር አንባቢው እንደማያሳፍር በተደጋጋሚ አሳይቷልና፡፡
---
ማስታወሻ፡-
ይህ ጽሑፍ ‹‹መክሸፍ›› በሚል ርዕስ የምናወጣቸው ተከታታይ ጽሑፎች አካል ነው፣
ተጓዳኝ ጽሑፍ፡-
----
የዚህ ጽሑፍ ዋና ቅጂ በኢትዮጵያ እንዳይበብ በታገደው በዞን ዘጠኝ ጦማር ላይ ይገኛል፡፡የኢትዮጵያዊነት መንፈስና የደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ
Friday, February 1st, 2013በፍቅር ለይኩን
There are two things that can bring this planet closer together: love and football.
--Iran coach Afshin Ghotbi
--Iran coach Afshin Ghotbi
ይህ ለዚህ ጽሑፌ መግቢያ ይሆነኝ ዘንድ የመረጥኩትን ኃይለ ቃል በ1998ቱ የዓለም ዋንጫ ባለንጣዎቹ የዛሬዋ ልዕለ ኃያል አሜሪካና በአስር ሺህ ዘመናትን በሚያስከነዳ ግዙፍ ስልጣኔዋና ታሪኳ ምትኩራራው ኢራን በተፋጠጡበትና የእግር ኳስ መድረክ የኢራኑ አሰልጣኝ ስለዚህ አስደናቂ አጋጣሚ በአድናቆት የተናገረው ነው፡፡ የአሜሪካው የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትም the mother of all games በሚል አጭር ቃል ነበር ሁለቱን አገራት ግጥሚያ የገለፁት፡፡ እስቲ ስፖርት በፖለቲካው መድረክ ካለው አዎንታዊ ሚና በመነሳት ስለ ሰሞኑ የአፍሪካ ዋንጫ ጥቂት ነገሮችን ልበል፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ ከሦስት አሠርት ዓመታት በኋላ ተሳታፊ በሆነችበት በዘንድሮው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የፈጠረብን ደስታ፣ ሐሴትና ሞቅታ ገና ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፋችንን የምታበስረውን የመጨረሻዋን ፊሽካ ከሰማንባት ቅጽበት ጀምሮ የተፈጠረ ውብና ልዩ ስሜት ነው፡፡
ይህ ብሔራዊ ስሜታችን ከኢትዮጵያዊነት ምሉዕ ኩራት፣ ስሜትና ትኩሳቱ ጋር አብሮን ዘልቆ በእግር ኳሱ መድረክ በዓለም ኅብረተሰብ ዘንድ አብዝተን ከምንታወቅበት ‹‹የራብና የጦርነት ምድር›› ከሚለው ገጽታችን ባሻገር ኢትዮጵያ ‹‹የኳስ ጥበብን የተካኑ የውብ ሕዝቦች አገር ናት!›› የሚለውን ሌላውን ውብና ተወዳጅ ገጽታችንን ለዓለም ሕዝብ አሳይቶ አልፏል፡፡
ይህን ብሔራዊ ቡድናችን ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉን ተከትሎ በደቡብ አፍሪካ ባሉ ኢትዮጵያውያን መካከል የነበረውን የኢትዮጵያዊነት ጥልቅ ፍቅርና የአንድነት ውብ ስሜት የታዘበ አንድ ደቡብ አፍሪካዊ ወዳጄ በኢሜይል ባደረሰኝ መልእክቱ እንዲህ ሲል ነበር አድናቆቱንና ትዝብቱን ያካፈለኝ፡-
ጆሐንስበርግ እንደ ኢትዮጵያን ሀበሾች የቁልምጫ አጠራር ‹‹ጆዚ››፣ በርካታ ስደተኛ ኢትዮጵያን በሚበዙባት ከተማ ነች፡፡ በዚህች ጭንቅንቅና ትርምስምስ በሚበዛባት የደቡብ አፍሪካዊ የቢዝነስ ከተማ በሰሞኑን እያየሁት ያለው ነገር በእጅጉ የሚያስደምም ነው፡፡ ‹‹ጆዚ››/ጆሐንስበርግ በኢትዮጵያ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ሰንደቀ ዓላማ ደምቃ ተውባለች፡፡
የኢትዮጵያን ሱቆች፣ መኪናዎች፣ መኖሪያ ሕንጻዎች… ሁሉ በዚህ የአፍሪካ ነፃነት ተምሳሌት በሆነ የኢትዮጵያ ሰንደቀ ዓላማ ደምቀዋል፣ አሸብርቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሦስት አሠርተ ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ መብቃቱ የፈጠረው የደስታ ስሜት በእጅጉን ከፍተኛ ነው፡፡ ዋልያዎቹ ከዛምቢያ ጋር የመጀመሪያውን ፍልሚያ ለማድረግ ወደ ጆሐንስበርግ ከገቡበት ዕለት ጀምሮ በኢትዮጵያውያን ፊት ላይ የሚታየው ደስታና ጉጉት በእጅጉ የሚያስገርም ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዛምቢያ አቻው ጋር ባደረገው ጨዋታና ዋልያዎቹ በእኩል ውጤት ከተለያዩ በኋላም የነበረው ስሜት በእጅጉ የሚያስደንቅ ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነት ጠንካራ የሆነ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ፣ ብሔራዊ ስሜትና ፍቅር የፈጠረው ትእይንት ለእኔ፣ ለበርካታ ደቡብ አፍሪካውያንና የሌሎች አገር ዜጎች እንግዳ ነው፡፡ በአጠቃላይ ትእይንቱን በቃል ለመግለፅ በእጅጉ የሚያዳግት ነው፡፡
በአብዛኛው አፍሪካውያንና ምዕራባውያን ዘንድ ‹‹በርሃብና በጦርነት›› የምታወቀው ኢትዮጵያ በስፖርት መድረክ በእንዲህ ዓይነት የደመቀ፣ ያማረ ብሔራዊ ስሜት፣ አንድነትና አገር ፍቅር ስሜት ብቅ ማለቷ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡ ሲል በኤሜይል መልእክቱ ገልፆልኛል፡፡
እንዲሁም የቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪና በአሁን ወቅት በጆሐንስበርግ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማራው ጓደኛዬ ቴዎድሮስም የኢትዮጵያዊነት ጠንካራ መንፈስ ያስተሳሰራቸው ደጋፊዎች በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዩ ሰንደቀ ዓላማ ስር አንድ ሆነው ስሜታቸውን የገለጹበትን ሁኔታ እንዲህ ሲል ገልፆልኛል፡-
መላው ስታዲዮም በአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ሰንደቀ ዓላማችን ደምቋል፡፡ ሰንደ ዓላማችን እንዲያ በምቦምቤላ ስታዲዮም ከፍ ብሎ ሲውለበለብ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ፊት ላይ ይታይ የነበረውን የደስታ ስሜት፣ ጭንቀትና ጉጉት ሳይ የተሰማኝ ስሜት በቃላት ለመግለፅ በእጅጉ ያዳግተኛል፡፡
የአፍሪካውያንና የመላው የዓለማችን ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተጋድሎ መገለጫ የሆነው ሰንደቀ ዓላማችን እንዲያ በስታዲዮም ውስጥ ከፍ ብሎ ሳየው አባቶቻችን ለዚህች ሰንደቀ ዓላማ የከፈሉት ክቡር የሆነ መስዋዕትነት በዓይነ ህሊናዬ ገዝፎና ገኖ ታየኝ፡፡
አረንጓዴ፣ ቢጫውና ቀዩ ሰንደቀ ዓላማችን በመላ አፍሪካዊና በጥቁር ሕዝቦች መካከል ያለውን ከበሬታ ለአፍታ ሳስበው ልዩ ስሜትን ነው የፈጠረብኝ፡፡ በእውነት ነው የምልህ በዛ የነበረውን የኢትዮጵያውያኑን ስሜት በአካል ተገኝተህ ብታየው ሊፈጥርብህ የሚችለውን ስሜት ለመግለጽ ቃላት በእጅጉ ያጥርህ ነበር፡፡ በእውነት ነው የምልህ በኢትዮጵያዊነቴ በእጅጉ የኮራሁበት ቀን ነው፡፡ ሲል ገልፆልኛል ‹‹ከጆዚ›› ከደቡብ አፍሪካዊቷ የንግድ ከተማ ጆሐንስበርግ፡፡
የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት፣ የኢትዮጵያችን መለያ ሰንደቀ ዓላማ ለአፍሪካውያንና ለጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ኩራት፣ የነፃነትና የልዑላዊነት ተምሳሌት መሆኑ በብዙዎች ዘንድ የተመሰከረለት ነው፡፡ አዛውንቱ ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን የክህደት ቁልቁለት በሚለው መጽሐፋቸው እንደገለፁትም፡-
…ኢትዮጵያዊነት በቄጤማ ጉዝጓዝ ላይ የሚታየው መተሳሰብና መፈቃቀር ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የአስተዋይነት፣ የሚዛናዊነት የጨዋነት ባሕርይ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ረጅምና ተጽፎ ያላለቀ ታሪክ ነው፤ ብዙ ሰዎችም የተሰዉለት ስሜት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ስቃይና መከራ ነው፤ ኢትዮጵያዊነት ኩራትና ክብርም ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ጭቆናና ጥቃት ነው፤ ኢትዮጵያዊነት አሻፈረኝና እምቢ ባይነትም ነው፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ሊያስተምረን እንደሚችለው ኢትዮጵያዊነት እንደ ላስቲክ ነው፡፡ ሲስቡት ይሳባል፣ ሲለቁት ይሰበሰባል፡፡ ማለት ይሳብና ይሳሳል እንጂ አይበጠስም…፡፡
ይህ ታሪካዊ እውነታ ነው የደቡብ አፍሪካውን የነፃነት ታጋይ፣ የሰላም አርበኛ፣ የእርቅ አባትና የፍቅርና ወንድማማችነት ተምሳሌት የሆኑትን ማንዴላ/ማዲባ ረጅሙን የትግል ዘመናቸውን በተረኩበት Long Walk to Freedom በሚለው መጽሐፋቸው ስለ ኢትዮጵያ እንዲህ እንዲሉ ያስገደዳቸው፡-
“Ethiopia always has a special place in my imagination and the prospect of visiting Ethiopia attracted me more strongly than a trip to France, England, and America combined. I felt I would be visiting my own genesis, unearthing the roots of what made me an African.”
ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያንና ለኔልሰን ማንዴላ እናት ምድራቸው ብቻ ሳትሆን የትናንት አባቶቻቸው፣ አያቶቻቸውና ቅድመ አያቶቻው፡- ‹‹የአፍሪካዊነት፣ የጥቁር ሕዝቦች፣ በአጠቃላይ የሰው ልጆች ግዙፍ ስልጣኔ፣ ባህል፣ ታሪክ፣ ቋንቋና ቅርስ መገለጫም እንደሆነች አድርገው ነው የሚያስቧት፡፡››
ወንድማችን በፍቄም በፌሰ ቡክ ገጹ በደቡብ አፍሪካው የ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ መላው መንፈሷና ሰውነቷ በኢትዮጵያ ባንዲራ ተውቦ ዓይኖቿን ወደ አርያም አንስታ ለዋልያዎቹ ድል ማድረግ ስትጸልይና መልካም ምኞቷን ስትገልጽ የነበረችውን የፕሪቶሪያዋን ጸሐይን፡-
‹‹በእናት ምድሯ በኢትዮጵያ ውበት፣ ፍቅር፣ አንድነትና ኩራት ያበደች የዘመናችን ጣይቱ፣ የጥቁር አፈር ውብ ፈርጥ፣ የኢትዮጵያዊነት አንድነት፣ ውብ ኅብር ታላቅ ተምሳሌት ናት፡፡›› ሲል ያሞከሻት፡፡
በዚህ ኢትዮጵያዊነት ከፍ ብሎ በታየበት በደቡብ አፍሪካ የ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ያሰደመመኝና በእጅጉ ስሜትን የነካው ደግሞ በጠላትነት የተፈረጁ፣ መንግሥቶቻቸው እርስ በርሳቸው የሚካሰሱና የሚወነጃጀሉ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን፣ ለዋልያዎቹ/ለጥቋቁሮቹ አንበሶች ድጋፋቸውን ለመስጠት የተገናኙበትና ባለፈው ሳምንት በፌስ ቡክ ገፆች ‹‹አስታራቂም የለ፣ እኛው እንታረቅ›› በሚል መልእክት የብዙዎቻችንን የፌሰ ቡክ ገጽ አድምቆ የከረመው የኢትዮጵያውያኑና ኤርትራውያኑ ውብ ሴቶች ምስል ነው፡፡
እነዚህ በባህል፣ በታሪክ፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋና በደም የተሳሳሩ ሕዝቦች በመንግሥቶቻቸው መካከል ያለውን የጠላትነት መንፈስ ወደጎን ትተው በስፖርቱ መድረክ ለሰላም፣ ለፍቅር፣ ለአንድነት፣ ለወንድማማችነት… ያላቸውን አዎንታዊ ስሜትና ፍላጎት የገለጹበት ሁኔታ በእጅጉ ደስ የሚያሰኝ ነው፡፡
በተቃራኒው እስካሁን ድረስ እያሰገረመኝ ያለው ነገር ደግሞ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፡- ‹‹ከኤርትራ ጋር ለመደራደርና ሰላምን ማውረድ አስመራም ድረስ ቢሆን እንኳን እሄዳለሁ፡፡›› ባሉ ማግስት፣ ‹‹በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ሁለቱ አገራት የሚያድረጉትን ጨዋታ በሌላ ሦስተኛ አገር እንጂ በአስመራ ለማድረግ ፈቃደኛ አይደለንም፡፡›› የሚለውን መረር ያለውን መግለጫ ሳስብ ደግሞ የመንግሥታችን ለሰላም አለኝ የሚለው ናፍቆቱና አቋሙና ግራ ያጋባኛል፡፡
እናም ‹‹ሰፖርት ለሰላም፣ ለፍቅር፣ ለወንድማማችነትና ለአንድነት…!›› የሚለው መርህ በመንግሥት ባለስልጣኖቻችንና በስፖርቱ መስክ ባሉ ኃላፊዎች ዘንድ ትርጓሜው ምን እንደሆነ በግልፅ ያስረዱን ዘንድ ደግመን ደጋግመን እንድንጠይቃቸው እንገደዳለን፡፡
በመጨረሻም የኢትዮጵያዊነት ኅብር በጎላበት፣ ኢትዮጵያዊነት ውበትና አንድነት በደመቀበት በዘንድሮው ከሦስት አሠርተ ዓመታት በኋላ ተሳታፊ በሆንበት በደቡብ አፍሪካው የእግር ኳስ ዋንጫ፣ በተቃራኒው ደግሞ በዚህ ውድድር የታዘብነው፣ የሆነውና ያየናቸው ዘረኝነት፣ ጥላቻ፣ መከፋፈልና እልኸኝነት… ገና በመካከላችን ሰላምን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን፣ ብሔራዊ እርቅንና መግባባትን ለማስፈን ረጅም ጉዞ እንደሚጠብቀን ያሳየ ነው ብል ብዙም ከእውነታው የራቅኹ አይመስለኝም፡፡
ለዚህ ጉዞአችን መሳካትና ውጤት ደግሞ ሀገራዊ/ብሔራዊ ራእይ፣ ጠንካራና በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ የማይናወጽ ጽኑ መንፈስ ያላቸው፣ ከዘረኝነት፣ ከጥላቻና ከአድልዎ የጸዱ ኢትዮጵያውያን ማንዴላዎች፣ ጋንዲዎች፣ ሉተሮች… ወዘተ በእጅጉ እንደሚያስፈልጉን አስባለሁ፡፡
ሰላም! ሻሎም!
----
ጸሐፊውን ለማግኘት በኢሜይል አድራሻቸው fikirbefikir@gmail.com ይጻፉላቸው::
----
ጸሐፊውን ለማግኘት በኢሜይል አድራሻቸው fikirbefikir@gmail.com ይጻፉላቸው::
1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት እና የነጻ ማኅበራት ፋይዳ
Tuesday, January 22nd, 2013በ2004 የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ‹‹መጅሊስ ይቀየር›› ጥያቄ መቀስቀሱን ተከትሎ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ዩንቨርስቲዎች በአንዱ ውስጥ በጉዳዩ ዙሪያ ለመወያየት ስብሰባ ተጠራ፡፡ ስብሰባው ላይ የዩንቨርስቲው የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዚደንት የነበረው የእስልምና እምነት ተከታይ እጁን አውጥቶ ‹‹ትላንትና ምንም ነገር እንዳልናገር ከዩንቨርስቲው አስተዳደር ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶኝ ነበር፥ ሆኖም…›› ብሎ ሐሳቡን ተናገረ፤ ያ የዩንቨርስቲ የተማሪዎች ኅ ብረት ፕሬዚደንት በማግስቱ ከኃላፊነቱ ተነሳ፡፡
ይህ በኢሕአዴግ ዘመን ያለውን ግለሰባዊም ሆነ ቡድናዊ መብት ደረጃ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ምሳሌ ሲሆን በዚሁ ተንደርድረን፣ በ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት ጉልህ ሚና የተጫወቱትን ተመሳሳይ አካላት እንመለከታለን፤ ለመሆኑ እነዚህ ሕዝባዊ አካላት እነማን ነበሩ?
የ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት የኋላ ኋላ ገጠሬው ቢቀላቀለውም፣ በአብዛኛው የተመራው በከተማ ነዋሪዎች ነው ማለት ይቻላል፡፡ አንዳርጋቸው ጥሩነህ Ethiopian Revolution 1974-1987፡ A transformation from an aristocratic to a totalitarian autocracy (1993) በተሰኘው ጥናታቸው ላይ በአብዮቱ ዋና ተዋናይ የነበሩትን አካላት ከነ[ተቀራራቢ] ቁጥራቸው ዘርዝረዋቸዋል፡፡
“የኢትዮጵያ ንግድ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን 80,000 አባላት፤ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር (አባላቱ የመንግሥት ሠራተኞች ነበሩ፤) ብዛታቸውም 18,000 ነበር፡፡ ከመንግሥት ሠራተኞቹ በተጨማሪ 10,000 የምድር ጦር እና 30,000 የፖሊስ አባላትን ጨምሮ 55,000 የሠራዊት አባላትን የሠራተኛ ማኅበሩ ያካትታል፡፡
በወቅቱ የተመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር 70,000 ነበር፤ ከነርሱ ውስጥ 6,000ዎቹ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ናቸው፤ (በተጨማሪም በውጭ ሃገራት የዩንቨርስቲ ጥናት ላይ የነበሩ ሌሎች 2,000 ተማሪዎች ነበሩ)፡፡
“ስለዚህ ከጠቅላላው 3 ሚሊዮን የከተማና ከተማ ቀመስ ቦታዎች ነዋሪ ሕዝብ ውስጥ ፖለቲካዊ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ የነበሩት የመንግሥት ሠራተኞች፣ ወታደሮች እና ተማሪዎች ከ300,000 የማይበልጡ የከተማ ነዋሪዎች ነበሩ፡፡”
በየማኅበራቱ የታቀፉት እና ፖለቲካዊ ንቁ የነበሩት ሕዝቦች ቁጥር ከጠቅላላው የከተማ ሕዝብ አንጻር እንኳን ሲታይ ከ10 በመቶ የማይበልጡ እና በወቅቱ ከነበረው ጠቅላላ የሕዝብ ብዛት አንጻር ከ1 በመቶ የማይበልጡ ቢሆንም አብዮቱን ማስነሳት ችለዋል፡፡ አብዮቱ ከተማ እና ኮርፖሬታዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ ሳይወሰን አገር አቀፍ እንዲሆን በማድረግና ስር ሰድዶ የነበረውን ንጉሣዊውን ስርዓት በማንገጫገጭ ለማስወገድም ችሏል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው በተለያዩ ማኅበራት ጥንካሬ ነው እንጂ በተሳታፊዎቹ ቁጥር ብዛት አይደለም ብዬ አምናለሁ፡፡ በዝርዝር እንመልከተው፡-
የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ)
ኢሠማኮ የተለያዩ መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ለጥቅማቸው ለመቆም ያቋቋሟቸው ማኅበራት አቃፊ ኮንፌዴሬሽን ነበር፡፡
ኢሠማኮ በ1965፣ 167 የሠራተኞች ማኅበራትን ያቀፈ ሲሆን ከ80,000 በላይ አባላት ነበሩት፡፡ ኮንፌዴሬሽኑ በ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት ወቅት ውስጥ የነበረው ሚና ከየትኛውም አካል የጎላ ነበር፡፡ ኮንፌዴሬሽኑ በመጀመሪያ የሠራተኞቹን ጥቅም ያስጠብቃሉ ያላቸውን (የደሞዝ ጭማሪ፣ የሠራተኞች የመደራጀት መብቶች) እና ሌሎችም (5 ያክል) ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ይዘት ያላቸውን - ብዙ ምንጮች እንደሚሉት 16 (አንዳርጋቸው ጥሩነህ 17 ነው ይላሉ) ጥያቄዎች አነሳ፡፡ መንግሥት ይህንን ጥያቄያቸውን ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ ጠቅላላ አድማ ለጥር 30/1965 እንደሚጠራም አስጠነቀቀ፡፡ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳልካቸው መኮንን ከአድማው ቀነ ቀጠሮ አንድ ቀን ቀድመው ጥያቄዎቹ ከሦስት እስከ ስድስት ወር በሚደርስ ጊዜ መልስ እንደሚያገኙ ብቻ ተናገሩ፡፡ በማግስቱ (የካቲት 1/1965 /ማርች 8/) ግን እስከ መቶ ሺሕ የሚጠጉ ሰዎች የሥራ ገበታቸው ላይ ባለመገኘት የሥራ ማቆም አድማ አደረጉ፡፡ የታሪክ ጸሐፊዎች በዕለቱ ፀጥ-ረጭ የማለቱን ገጠመኝ የሚያስታውሱት በተለይ አዲስ አበባ ‹‹ሽባ ሆነች /በእንብርክኳ ሄደች/›› በማለት ነው፡፡
በወቅቱ ኮንፌዴሬሽኑ የገጠመው ችግር አብዛኛዎቹ ሠራተኞች በአድማው ከሦስት ቀን በላይ መሳተፍ አለመቻላቸው ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት አብዛኛዎቹ ሠራተኞች ኑሯቸው ከእጅ ወደአፍ ስለሆነና ሥራችንን አጥተነው እንቀራለን የሚል ፍራቻ ስለነበረባቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ለጥያቄዎቻቸው በሙሉ መልስ የሚሰጥ ስምምነት የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳልካቸው እንዲፈርሙ ማስገደድ አላቃታቸውም፡፡ እንዲያም ሆኖ የአድማው ትልቅ ግብ ተደርጎ እስከዛሬም የሚቆጠረው እንቅስቃሴው ሌሎች በርካታ አድማዎችን እና መንግሥትን ለለውጥ የሚያስገድዱ እበያዎችን ማበረታቱ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር (ኢመማ)
ኢመማ ከ60 ዓመት በላይ ያስቆጠረ አንጋፋ ማኅበር ነው፡፡ ይሁን እንጂ እንደንጉሡ ዘመን ማብቂያ ሰሞን አቅመ-ትልቅ ማኅበር ሆኖ አያውቅም፡፡ በ1965፣ 18,000 ያህል አባላት ነበሩት፡፡ ማኅበሩ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ቢያንስ ለስድስት ዓመታት ያክል በደሞዝ ጭማሪ እና የደሞዝ ስኬል ጉዳይ ሲነታረክ ከርሟል፡፡ አንዳርጋቸው ጥሩነህ እንደጻፉት የመምህራን ማኅበሩ የካቲት 11/1966 ታክሲዎች የነዳጅ ጭማሪን ተከትሎ በጠሩት አድማ ላይ ተደምሮ የትምህርቱን ሥርዓት በዝምታ ሊያውለው ወሰነ፡፡ ማኅበሩ ጥያቄዎቹን ከመምህራን (የደሞዝ እና የሴክተሩ ክለሳም) በላይ እንዲሆን፤ የሰላማዊ ሰልፍ መብት እንዲከበር፣ የደሞዝ ወለል እንዲበጅ፣ ለፋብሪካ ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ እንዲደረግ፣ ለኢንዱስትሪ ሠራተኞች የጡረታ መብት እንዲከበር፣ ሠራተኞን የማባረሪያው ሕግ እንዲስተካከል እና ሌሎችንም ጥያቄዎችን አነገበ፡፡
የመምህራን ማኅበሩ የደሞዝ ስኬት ይሻሻል ጥያቄውን ከአብዮቱ 6 ዓመት ቀድሞ ያነሳ ቢሆንም መልስ ማግኘት ባለመቻሉ ትግሉን አጠናክሮ፣ የመምህራንን ብቻ ሳይሆን የሌሎችም ሠራተኞች መብቶችን የሚያስከብሩ እና ሌሎችም ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን አንግቦ ተጠናክሮ በመንቀሳቀስ የሌሎቹን ማኅበራት ዓይን ለመግለጥ መቻሉ እንደስኬት ይቆጠርለታል፡፡
የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች ማኅበር (USUAA)
የኢትዮጵያ ዩንቨርስቲዎች ማኅበር (ከቀኃሥ - ዩንቨርስቲ በተጨማሪ የሌሎች ሁለት ራስ ገዝ አካባቢዎች ዩንቨርስቲዎችን የሚጨምር ሲሆን) የነበረው አቅም ግን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ማኅበር ያነሰ ነበር፡፡ ሆኖም የተማሪዎች ሚና ጉልህ ነው በሚል እስከዛሬም ‹‹የተማሪዎች እንቅስቃሴ›› ውጤት ሆኖ የሚታወሰው የ1966ቱ አብዮት በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ማኅበር (ESUNA) እና የኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ማኅበር በአውሮፓ (ESUE) የታገዘ ነበር፡፡
የዩንቨርስቲ ተማሪዎች እንቅስቃሴ እስካሁንም ድረስ በተቃዋሚ እና ገዢው ወገን ያሉትን አንጋፋ ፖለቲከኞች ያነሳሳ እና ለአብዮቱ ምልከታዎችን ለግሶታል፡፡ አንጋፋዎቹ የ‹‹መሬት ላራሹ›› እና የብሔሮች እኩልነት ጥያቄ ቦታ የተሰጣቸው ያኔ - በተማሪዎቹ አማካይነት ነው፡፡ USUAA (በ1966 መባቻ ላይ የታገደባቸውን) ‘ስትራግል’ የተሰኘ ጋዜጣ በማሳተም የብሔሮች መብት እስከመገንጠል ድረስ የመዝለቅ ጥያቁዎችን ሳይቀር አንስቷል፡፡ መኢሶን፣ ኢሕአፓንና ሕወሓትን የመሰሉ ለተከታዮቹ ረዘም ላሉ ዓመታት ተጽዕኖ ፈጣሪ ፓርቲዎችም የተፈጠሩትም ከተማሪዎች እንቅስቃሴ ነው፡፡
በተማሪዎቹ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ጉልህ ሚና ኖሮት ነገር ግን ብዙም ያልተወራለት ‹‹Crocodiles Society›› (የአዞዎቹ ማኅበረሰብ) የሚባለው ነው፡፡ ይህ ቡድን የዩንቨርስቲውን እንቅስቃሴ ያጋግሉ የነበሩትን ‹‹ዜና እና አስተያየቶች›› የታተሙበትን በራሪ ወረቀቶች የማዘጋጀት/የማሰራጨት ሚና የነበረው ሲሆን ‹‹መሬት ላራሹ›› የሚለው አጀንዳም የፈለቀው ከዚያ እንደሆነ የባሕሩ ዘውዴ Documenting the Ethiopian Student Movement: An Exercise in Oral History ይጠቃቅሳል፡፡
የተማሪዎች ኅብረት ለአብዮቱ መፋፋም የሐሳብ መዋጮ፣ እና የፓርቲ መመስረት የመጨረሻው ውጤት ቢሆንም የትምህርት ክፍለጊዜዎችን ክፍል ባለመግባት እና የተቃውሞ ሰልፍ በማስነሳትም ጭምር የወቅቱ ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ ተግተው ነበር፡፡
ይሁን እንጂ የተማሪዎቹ እንቅስቃሴም ፈተና ነበረበት፡፡ የወቅቱ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች ኅብረት ፕሬዚደንት ጥላሁን ግዛው ባልታወቁ ሰዎች (በዝግታ በምትነዳ መኪና ውስጥ በተተኮሰ ጥይት) ተገድሏል፡፡ ጆን ያንግ Peasants Revolution of Ethiopia በተባለ መጽሐፋቸው ጥላሁን ‹‹ከገንጣዮች እንቅስቃሴ ጋር ትተባበራለህ›› በሚል ዩንቨርስቲውን ለቅቆ እንዲወጣ ማስጠንቀቂያ እንደደረሰው ገልጾ ነበር ሲሉ ጽፈዋል፡፡
ከነዚህ በተጨማሪም የ5 ሣንቲም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን ተከትሎ የተጠራው የታክሲ ማቆም አድማም ለአብዮቱ መጧጧፍ እና ለንጉሡ ስርዐት የኢኮኖሚ ፈተና ለመሆን በቅቷል፡፡
ትላንት ይማረኝ?
ደርግ ሁሉንም ማኅበራት በራሱ መልክ ለማዋቀር ሞክሮ ነበር፡፡ የነጋዴዎች፣ የከተሜዎች፣ የገበሬዎች… እየተባለ ማኅበር በማኅበር አገሪቱን አጥለቀለቃት፡፡ አንዳርጋቸው ከላይ በጠቀስነው ጥናታዊ ጽሑፋቸው “ከሞላጎደል ሁሉም ዜጋ አንዱ፣ ወይም ሌላኛው ወይም ከአንድ በላይ የሆነ ማኅበር/ራት ውስጥ መታቀፉ የማይቀር ነበር፡፡ ዕድሜዋ ከ18 እስከ 30 የሚደርሳት ሴት ለምሳሌ የገበሬች ወይም የከተሜዎች ማኅበር (እንደምትኖርበት ቦታ ሁኔታ) እና የወጣት አብዮተኞች ማኅበር አባል ትሆናለች፡፡ እንዲሁም፣ የነጋዴዎች፣ የነርሶች፣ የዶክተሮች ብሎም የፓርቲ አባልም ልትሆን ትችላለች፤” በማለት የደርግን ዘመን ማኅበር የረከሰበት ቢሆንም ሁሉም የመንግሥታዊ ስርዐቱን ከማስፈፀም በላይ ፋይዳ እንዳልነበራቸው አመላክተዋል፡፡
በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት ደግሞ የተለየ አጨዋወት እናገኛለን፡፡ ኢሕአዴግ በጥቅሉ በመደራጀት (communalism) ያምናል፤ ሆኖም እያንዳንዱን ማኅበር የመቆጣጠር ኃላፊነቱን ግን ካድሬዎቹ እንዲወስዱት ይፈልጋል - እስካሁን ባለው ሁኔታ ተሳክቶለታልም፡፡
የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ማኅበር በ1993 የገጠመው የነጻነት ማጣት ችግር እና የዩንቨርስቲው ቀውስ እስከዛሬ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በወቅቱ የዩንቨርስቲ ተማሪዎቹ 4 ጥያቄዎችን በማንሳት ያመጹ ቢሆንም ከወቅቷ ሚኒስቴር ያገኙት የመጨረሻው መልስ ‹‹ካልፈለጋችሁ ግቢውን ጥላችሁ ውጡ›› የሚል ነው፡፡ ተማሪዎቹ በእምቢተኝነት አድማቸውን በመቀጠላቸው ደግሞ በአድማ በታኞች ብዙዎች ሲጎዱ ለሞት የተዳረጉም እንዳሉ በወቅቱ የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ጉባኤ ዝርዝር መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ የዩንቨርስቲው ማኅበር በኢሕአዴግ ዘመን ‹ሕሊና› የተሰኘ ጋዜጣ ሦስት ጊዜ ያህል ብቻ ያሳተመ እና ያሰራጨ ቢሆንም ከዚያ በኋላ ታግዷል፡፡ አሁን ሁሉም ሊባል በሚችል ሁኔታ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ማኅበራት ፕሬዚደንቶች በውስጠ ታዋቂነት ካድሬዎች ናቸው፡፡
የመምህራን ማኅበሩን የነጻነቱ ዘመኑ በ1999 ከማብቃቱ በፊት ፕሬዚደንቱ የነበሩት ታዬ ወልደሰማያት ታስረው ሲፈቱ ከአገር ተሰደዋል፡፡ የግጭቱ መንስኤ ነው የሚባለው መንግሥት የሚያምነውን ማኅበር አዲሱ ኢመማ በማለት ለመፍጠር መሞከሩ ነው፡፡ ጉዳዩ ፍርድቤት የደረሰ ቢሆንም መንግሥት ግን ዕውቅናውን ለአዲሱ ሰጥቶ የቀድሞውን አፈራርሶታል፡፡ የመምህራን ማኅበሩ የውድቀት ምልክት ነው ብዬ እዚህ ልፈርድበት የሚያስደፍረኝ በ2004 የመምህራን ደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ ለዲፕሎማ ምሩቅ 31 ብር፣ ለዲግሪ ምሩቅ ደግሞ 73 ብር እንዲሆን ሲወሰን ማኅበሩ - ውሳኔውን ማድነቁን በማጣቀስ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ማኅበራት የቆሙለትን አካል ጥቅም በማስጠበቅ ፈንታ የመንግሥትን ፊት እያዩ ማዳነቅ ወይም ማራከስ ሲይዙ ፋይዳቸው ዋጋ ያጣል፡፡
በሌላ በኩል በሕግ ባይከለከልም ሌላ የመምኅራን ማኅበር ለማቋቋም እንደቀድሞው ምቹ የፖለቲካ ሁኔታ እንደሌላ የሚናገሩም አሉ፡፡ The Status of Governance, Academic Freedom, and Teaching Personnel in Ethiopian Higher Education Institutions በሚል በFSS ርዕስ በተደረገ ጥናት ላይ ነጻ የመምህራን ማኅበር ለማቋቋም ማሰብ በጅማ ዩንቨርስቲ መምህራን ‹‹unattainable luxury›› ተብሎ ሲገለጽ የባሕር ዳር ዩንቨርስቲ ተወያዮች ደግሞ ‹‹You never think of forming teachers’ association since the political environment is complex and ambiguous›› በማለት የመምህራን ማኅበር ማቋቋምን እንደተአምር ገልፀውታል፡፡ ይህንኑ በሚያጠናክር መልኩ ያለፈውን ከመፍረሱ በፊት እና አዲሱ እየተቋቋመ ሳለ የነበራቸውን አቋም ሲተቹ፣ አሰፋ ፍስሐ የተባሉ ጸሐፊ Ethiopia's Experiment in Accommodating Diversity: 20 Years’ Balance Sheet ባሉት መጣጥፋቸው ላይ ‹‹ሁለት የመምህራን ማኅበራት አሉ፤ አንዱ ገዢውን ፓርቲ ሌላኛው ተቃዋሚዎችን ይደግፋሉ›› በማለት ከፖለቲካ አጀንዳ የፀዱ (ነጻ) እንዳልሆኑ መስክረዋል፡፡
አዲስ አበባ የወጣቶች ማኅበር አላት፤ የወጣቶቹ ማኅበር ከኢሕአዴግ ደጋፊዎች ወጣቶች ሊግ የሚለይበት አንዳችም ባሕሪ የለውም፤ የቀድሞ የወጣቶች ማኅበሩ ፕሬዚደንት የነበሩት አቶ ታጠቅ አሁን ሁነኛ ሹመት በመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ተሰጥቷቸዋል፡፡ የአሁኖቹም ‹‹ወጣትነታቸው›› ሲያልፍበት ይሾማሉ፡፡ ማኅበራቱ የመንግሥትን ሥርዐት መደገፋቸው እንደጥፋት ላይቆጠር ይችላል፤ ሆኖም በመንግሥታዊ ሥርዐቱ ውስጥ የሚወክሏቸውን የኅብረተሰብ አካላት ጥቅም በሕጉ ውስጥ በአግባቡ ካላስጠበቁ ቅቡልነት ያሳጣቸዋል፡፡ አሁን እየሆነ ያለውም ይኸው ነው፡፡
የሴቶች ማኅበርም አለ፣ ከኢሕአዴግ ደጋፊ የሴቶች ሊግ የሚለይበት የለም፤ በጥቅሉ ሁሉም ማኅበር (የንግዶቹን ጥቃቅን እና አነስተኛ ማኅበራት ጨምሮ) በኢሕአዴግ እና በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ክበብ ውስጥ የተቀነበቡ እና አሻግረው ማየት እንዳይችሉ ተደርገው የተሠሩ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ሌሎቹንም በገለልተኛ ወገኖች የሚመሠረቱ ማኅበራት ካድሬዎች በግራም በቀኝም ብለው የፕሬዚደንትነቱን ስፍራ ይቆናጠጡ እና የመንግሥትን ሕልም ማስፈፀሚያ ያደርጉታል፡፡ በካድሬዎች የማይመሩትም የባለሙያዎች ማኅበራት ሳይቀሩ ኢሕአዴግን ላለማስቀየም ወይም ለማኅበሩ ሕልውና ሲሉ እውነትን ለመናገር ከመቆጠብ ጀምሮ የሠሩትን ጥናት ውጤት ለሕዝብ ይፋ ሳያደርጉ የመደርደሪያ ማሞቂያ አድርጎ እስከማቆየት ድረስ ይዘልቃሉ፡፡ በጥቅሉ አሁንም ማኅበራት አሉ፤ ማኅበራቱ ግን እንኳን የሥርዐት መሻሻልና ለውጥ ሊጠይቁ ቀርቶ ቢሳሳትም ባይሳሳት መንግሥትን ከመደገፍ የተለየ ተግባር የላቸውም - የኔ መደምደሚያ ነው፡፡
------
ማስታወሻ፡-
ይህ ጽሑፍ ‹‹ስለለውጥ›› በሚል የሚቀርቡት ተከታታይ ጽሑፎች አካል ነው፤
-----
ተጓዳኝ ጽሑፎች፤
ዋኤል ጎኒም ኢትዮጵያዊ ቢሆን ኖሮ…?
Friday, January 11th, 2013-->ዋኤል ጎኔም የግብጽ ደኅንነት ሰዎች ደብድበው የገደሉትን ካሊድ ሰኢድ ለማሰብ ‹‹እኔም ካሌድ ሰኢድ ነኝ›› የተሰኘ የፌስቡክ ገጽ ከፍቶ ለግብጽ አብዮት ያበቃ ሰው ነው፡፡ የመጀመሪያውን የአደባባይ እንውጣ ጥሪ ያቀረበው ይኸው የፌስቡክ ገጽ ነው፡፡ ዋኤል አደባባይ የወጡበትን የመጀመሪያ ቀን (ጃንዋሪ 25) አንድ ዓመት ለማክበር (Revolution 2.0 የተባለ) መጽሐፍ አሳትሟል፡፡ የመጽሐፉ ገቢ በሙሉ በአብዮቱ ለተጎዱ ሰዎች መደጎሚያ እንደሚውልም ተነግሯል፡፡ አሁን እዚህ ልጽፍላችሁ ያሰብኩት ግን ዋኤል ገጹን እና የግል ማንነቱን አስመልክቶ ለሚቀርብለት ጥያቄ ይሰጥ የነበረውን መልስ ነው (መጽሐፉ ላይ እንዳሰፈረው)፤ ዋኤል ኢትዮጵያዊ ቢሆንና የከፈተው ገጽም ኢትዮጵያዊ ቢሆን ኖሮ… በሚል ምናባዊ ምሳሌ፡፡ ስለዚህ ጽሑፉ በዋኤል የተጻፈው በኢትዮጵያኛ ተተርጉሞ ነው ልትሉት ትችላላችሁ፡፡
ስምህ ማነው?
[1]ስሜ ሽብሬ ደሳለኝ ነው፤
[2]ስሜ ዩሱፍ አብደላ ነው፤
[3]ስሜ እስክንድር ነጋ ነው፤
[4]ስሜ ርዕዮት አለሙ ነው፤
[5]ስሜ አሕመዲን ጀበል ነው፤
[6]ስሜ አንዱአለም አራጌ ነው፤
[7]ስሜ በቀለ ገርባ ነው፤
[8]ስሜ ኦልባና ሌሊሳ ነው፤
[9]ስሜ መስፍን ነጋሽ ነው፤
[10]ስሜ አርጋው አሽኔ ነው፤
ስሜ…. ብዙ ነው፡፡
እኔ በጎዳና ላይ የተገደልኩ፣ ያለወንጀሌ የታሰርኩ፣ ያለሀጢያቴ የተገረፍኩ፣ መብቴን በፍርሐት የተነጠቅኩ፣ ከገዛ አገሬ የተሰደድኩ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡
ዕድሜህ ስንት ነው?
ዕድሜዬ ይህን ያህል ነው አልልም፤ ነገር ግን ከተወለድኩ ጀምሮ ያለው ያው አምባገነን መሪ ነው፤… ሙስናውም ያው ነው፤…. ጭቆናው ያው ነው፤… እናም በአገሬ የገነነው የፖለቲካ ፓርቲ ‹‹ተስፋ የለም›› ይባላል፡፡
ከጠቀስካቸው ሰዎች ጋር ዝምድና አለህ?
እነዚህ ሰዎች የተኛውን ውስጤን ቀስቅሰውታል… ዕድሜ ለነርሱ አሁን ለውጥ ማምጣት እንደምችል ይሰማኛል፤… ታዲያ በራዕይ አልተዛመድንም ማለት ይቻላል?... አንድም ቀን አግኝቻቸው የማላውቃቸው እነዚህ ሰዎች ወንድሞቼ/እህቶቼ ናቸው፡፡
ይህንን የምታደርገው ለምንድን ነው?
ወገኖቼ ላይ የሚደርሰውን በደል ተመልክቼ ወደጥናት ክፍሌ ስገባ እምባዬን መግታት አልችልም፤… ፍርሐት የተጫናቸው ኢትዮጵያውያን ምን ያህል ውርደትን እንደሚታገሱ አየሁ… ከራሴ በመጀመር በፍርሐት የምሠራውን ስህተት ሁሉ ማረም ጀመርኩ፤ እናም ለዛ ነው ይህንን ገጽ የፈጠርኩት፡፡ ለተበደሉ ወገኖቼ ያለቀስኩት ለሞቱ ዘመዶቼ ካለቀስኩት በላይ ነው… በየዕለቱ ፎቷቸውን ስመለከት ድብታ ውስጥ እገባለሁ፤ ኢ-ፍትሐዊነትን እስከመጨረሻው ለመዋጋትም ለራሴ ቃል እገባለሁ፡፡
ማነው በገንዘብ የሚረዳህ?
ፈጣሪ ይመስገን፣ የገንዘብ ምንጮቼ ብዙ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ንቃተ ሕሊናዬ ነው… ይህ ምንጬ በቀን አራት ሰዓተ ብቻ እንድተኛ እና ጠዋትም ፊቴን ከመታጠቤ በፊት የፌስቡክ ገጼን እንድከፍት ያስገድደኛል፡፡
ሁለተኛው ምንጬ መማሬ ነው፡፡ በመማሬ ደስተኛ ነኝ፤ ዕውቀቴን አገሬን ለማገልገል አውለዋለሁ፡፡
ሦስተኛው ምንጬ የልጆች አባት መሆኔ ነው፡፡ ሁሌም የሚጨንቀኝ ልጆቼ አንድ ቀን ‹‹አባዬ፤ ዜጎች ሲጨቆኑ እያየህ አቅምህ የሚፈቅደውን ለምን አላደረግክም?›› ብለው ይጠይቁኛል ብዬ ነው፡፡
የመጨረሻው ምንጬ የሕዝብ ፍቅር ነው፡፡ አይቶኝ የማያውቅ፤ አይቼው የማላውቀው እና በስም የማንተዋወቀው ሕዝብ ፍቅር… በየዕለቱ የአመሰግናለሁ ማስታወሻ ይደርሰኛል…. የተለያዩ ዲዛይኖች፣ ሎጎዎች፣ ቪዲዮዎች ይልኩልኛል… ገጹ ብዙ ሰዎች ጋር እንዲደርስ ያስተዋውቁልኛል፡፡
ስለዚህ ምንድን ነው የምትፈልገው?
ይህንን ገጽ የፈጠርኩት ራሴን ከአደጋ ለመጠበቅ ብቻ አይደለም.. ነገር ግን አገራችን መልሳ የኛው የሕዝቦቿ እንድትሆን ከመፈለግ በላይ ሌላ ዓላማ የለኝም… አንድ ቀን እንዲህ ይሆናል ብዬ አልማለሁ፡- እርስ በእርስ ዳግም እንዋደዳለን፤ ሁላችንም ኢ-ፍትሐዊነትን እንቃወማለን፤ ከመሐከላችን ማንኛውም ሰው ክፉ ነገር ቢያይ ራሱ ይፈታዋል… እናም የመንግሥት ቅጥረኛ አንድን ዜጋ በጥፊ ከመምታቱ በፊት አንድ ሺሕ ጊዜ ያስብበታል፡፡
አትፈራም?
በጣም እፈራለሁ እንጂ፤… ፍርሐት እኮ የሰው ልጅ ተፈጥሮ ነው… ለተጨቆኑ ዜጎች የሚቆረቆር እንደእኔ እና እናንተ ያለ ሰው ግን ካለ ፍርሐቴ ይከስማል… ዕጣፈንታችንንም የምንወስነው እኛው ራሳችን እንሆናለን… እንዲህ እያልን፡- ‹‹ማንም ያለዕድሜው አይሞትም፣ ማንም ያለወንጀሉ አይታሰርም፣ ማንም አገሩን ለቅቆ አይሰደድም…›› አንድ ዘመዴ በ25 ዓመቱ ሞተ… ቁም ነገር ካልሠራሁበት የኔ ዕድሜ መርዘሙስ ምን ዋጋ አለው?
ብዙ ሰዎች ይህንን ለማመን ይቸገራሉ፤ እውነቱን ለመናገር ቃሉ የወጣው ከልቤ ነው… አገሬን ከልቤ እወዳታለሁ እናም በተሻለ ሁኔታ የምንኖርባት አገር እንድትሆን እፈልጋለሁ፡፡ መፈንቅለ መንግሥት ወይም አብዮት የማቀጣጠል ዓላማ የለኝም… እራሴን እንደፖለቲካዊ መሪም አልቆጥርም… ዋሊያዎችን እና ሉሲዎችን የሚደግፍ፣ ካፌ ደጃፍ ላይ ቁጭ ብሎ ተቆራጭ እየበላ፣ ማኪያቶ እየጠጣ ጋዜጣ የሚያነብ ተራ ዜጋ ነኝ፡፡… የሚከፋኝ ብሔራዊ ቡድናችን በሰው አገር ሲሸነፍ ነው፡፡ … ቁምነገሩ በኢትዮጵያዊነቴ መኩራት እፈልጋለሁ፡፡… ማንም ሰው የዜግነት ክብሩን ተገፍፎ እንዲጨቆን አልፈልግም፡፡ ይኸው ነው ምኞቴ፡፡
----
[1] - ሽብሬ ደሳለኝ፤ ምርጫ 97ን ተከትሎ በተነሳው ብጥብጥ የመንግሥት ጥይት ሰለባ የሆነች ወጣት ተማሪ፤ [1] - ዩሱፍ አብደላ፤ በተመሳሳይ ወቅት የተገደለ የኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ተማሪ፤
[3] - እስክንድር ነጋ፤ በሽብርተኝነት ተከሶ የተፈረደበት ጋዜጠኛ፤
[4] - ርዕዮ ዓለሙ፤ መረጃ ለሽብርተኞች አቀብለሻል በሚል የተፈረደባት ጋዜጠኛ፤
[5] - አሕመዲን ጀበል፤ በሙስሊሞች የመጅሊስ ይቀየር ጉዳይ የታሰረ፣ ጋዜጠኛ እና ደራሲ፤
[6] - አንዱአለም አራጌ፤ ሽብር አሲረሃል በሚል የተፈረደበት የአንድነት ፓርቲ አባል፤
[7] - በቀለ ገርባ፤ ከኦነግ ጋር ግንኙነት አለህ በሚል የተፈረደበት የኦፌዴን ም/ሊቀመንበር፤
[8] - ኦልባና ሌሊሳ፤ ከኦነግ ጋር ግንኙነት አለህ በሚል 8 ዓመት የተፈረደበት የኦብኮ አባል፤
[9] - መስፍን ነጋሽ፤ በሽብርተኝነት አዋጅ/ክስ ምክንያት ከተሰደዱ የቀድሞዋ አዲስ ነገር ጋዜጠኞች አንዱ፤
[10] - አርጋው አሽኔ፤ የመረጃ ምንጩን እንዲሰጥ በመንግሥት ኃይሎች በግዴታ በመጠየቁ የተሰደደ ጋዜጠኛ፤
እነዚህን አንብባችኋቸዋል?
Saturday, January 5th, 2013በዚህ ጦማር ላይ ከጻፍኩ ሰነበትኩ:: ነገር ግን ብዙዎቻችሁ እንደምታውቁት የጠፋሁት መጻፍ እርም ብዬ ሳይሆን ዞን ዘጠኝ ላይ መጻፍ በመጀመሬ ነው:: ታዲያ ምናለ ይሄንን subscribe አድርገው ዞን ዘጠኝን ያላደረጉ ካሉ ቢያነቡኝ ብዬ ጥቂቶቹን እንዲህ ዘረዘርኳቸው:: እንዳሻችሁ አድርጓቸው::
15. የሥርዐት ለውጥ እና ሃይማኖቶች
14. ለውጥን መቋቋም እና መፍራት
13. አብዮት ወይስ አዝጋሚ-ለውጥ?
12. ግልጽ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ
11. በኢትዮጵያ የቡድን አመራር ተጀምሯል?
10. የጉዞ ማስታወሻ፤ ሥልጣኔ ወደላይ እና ወደታች
9. የጉዞ ማስታወሻ፤ መቐለን በአንድ ቀን
8. ኢሕአዴግ ሥልጣኑን በምርጫ ይለቃል?
7. “ጠንቅቆ” የመጻፍና አለመጻፍ ጉዳይ
6. የእነርሱ እና የእኛ ሕዳሴ
5. የታክሲ ሰልፍ መጀመሪያውና መጨረሻው
4. ‹‹ሕዝብ›› ምንድን ነው?
3. የትችት ባሕላችንን ብንተቸውስ?
2. ይቅርታ የሚገባው የኢትዮጵያ ሕዝብ!
1. “አራማጅነት” በኢትዮጵያ
የአዲስ አበባ ከተማ እና ምርጫዋ
Friday, November 9th, 2012አዲስ አበባ 125ኛ ዓመቷን እያከበረች ነው፡፡ በከተማይቱ ልደት ሰሞን እናትና አባቷ (በመናገሻ ከተማነት የቆረቆሯት አጤ ምኒልክ እና ስሟን ያወጡለት እቴጌ ጣይቱ) ስማቸው ሲነሳ አልሰማሁም፡፡ ይልቁንም ላለፉት 21 ዓመታት በፌዴራል መንግሥቱ ርዕሰ መሪነታቸው በእጅ አዙር የዘወሯት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ስም በተደጋጋሚ ሲነሳ እና በየመንገዱ ዳር በቆሙ ‹ቢልቦርዶች› ላይ ከከተማይቱ የመሠረተ ልማት አውታሮች ፎቶ ፊት ለፊት በጉልህ በተቀመጡ ምስሎቻቸው ታጅቦ ታይቷል፡፡
የክብረ በዓሉን ክንውን እንዲያዘጋጅ የኢሕአዴግ ሰዎች የሚመሯቸው ዋልታ እና ፋና ጥምር-ድቅል የሆነው ዋፋ የማስታወቂያ ድርጅት ሙሉ ኃላፊነቱን ወስዷል፡፡ ምናልባትም የዚሁ የፓርቲ ጥገኝነት ጉዳይ ይሆናል መለስን በግምባር ቀደምነት የከተማይቱን ቆርቋሪ አስዘንግቶ ያስጠቀሳቸው፡፡
ለነገሩ ይህን ጽሑፍ ለማሰናዳት ያነሳሳኝ የክብረ በዓሉን ዐብይ-ሰብ (figure) ለመሰየም አይደለም፡፡ ስለከተማይቱ እያነሳሁ ይህንን ያፈጠጠ ስህተት ሳልነቅስ ማለፍ ስላልሆነልኝ ነው፡፡ የጽሑፌ ርዕሰ ጉዳይ ሚያዝያ ወር ላይ የሚካሄደው ምርጫ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምርጫ ከሀገር አቀፍ ምርጫ በሁለት ዓመት እንዲዘገይ የሆነው፣ በምርጫ 97 ከአንድ ወንበር በስተቀር ሁሉንም የከተማዋን ምክር ቤት መቀመጫዎች አሸንፎ የነበረው ቅንጅት ምክር ቤቱ ለመግባት ባለመፍቀዱ ማሟያ ምርጫ እስኪካሄድ በተፈጠረው መዘግየት ሳቢያ ነው፡፡
ሀገሪቱ ከአንድ ጠቅላይ ሚኒስትር በላይ ባላየችባቸው ሁለት ዐሥርት ዓመታት ውስጥ፣ አዲስ አበባ አምስት ከንቲባዎችን ለማየት ታድላለች፡፡ አንዴ ግዜያዊ የባለአደራ ከንቲባ ስታስተናግድ ቀደም ብሎ ደግሞ ‹‹ተበለሻሸች›› ተብሎ - የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን በሚፈቅደው መሠረት - ምክር ቤቷ ፈርሶ በድጋሚ እንዲገነባ ተደርጎ ነበር፡፡ በነዚህ ጊዜያት ከተሠሩ ሕንፃዎች እና መንገዶች በተጨማሪ በተለይ ሕዝቡን ያማከለ ሥራ የሠሩት አርከበ ናቸው፡፡ አርከበ የኮንዶሚኒዬም ቤቶችን እና አርከበ ሱቆች ተብሎ በማኅበረሰቡ የተሰየሙላቸውን ጥቃቅን እና አነስተኛ ንግድ ቤቶች ያስጀመሩ ከንቲባ ናቸው፡፡
በዐሥር ክፍለከተሞችና ከ100 በላይ በሆኑ ቀበሌዎች (አሁን ወረዳዎች) የተከፋፈለችው አዲስ አበባ ከ5 እስከ 7 ሚሊዮን የሚደርሱ ነዋሪዎች እየዋሉ እንደሚያድሩባት ይገመታል፡፡ ከነዚህ ውስጥ የነዋሪነት መታወቂያ ያላቸው ከ3 ሚሊዮን አይበልጡም፡፡ ለምርጫ ብቁ የሆኑት ደግሞ 2.2 ሚሊዮን የሚጠጉት ብቻ ናቸው፡፡
በምርጫው ማን ይሳተፋል?
በሀገር አቀፉ ምርጫ 2002 የተሳተፉት/የመረጡት አዲስ አበቤዎች ብዛት ከ50 በመቶ እምብዛም የተሻገረ አልነበረም፡፡ በድኅረ ምርጫ 97 የተቀየመው ተቃዋሚ ሕዝብ ውስጥ ብዙኃኑ ለምርጫ ባለመመዝገብ፣ ወይም ከተመዘገበ በኋላ ባለመምረጥ እና የምርጫ ወረቀቱ ላይ ቅያሜውን ጽፎ ወረቀቱን በማበላሸት ተቃውሞውን መግለጽ መርጧል፡፡ በሌላ በኩል የነርሱ ድምፅ ለውጥ እንደማያመጣ በማመን ባለመምረጥ ዕድላቸውን የሚያባክኑትም ሰዎች ቁጥር እልፍ ነው፡፡
ከዚህ ተሞክሮ በመነሳት ስለዚህ ዓመቱ የከተማ ምክር ቤት ምርጫ መገመት የምንችለው ተቃዋሚዎችን ከሚደግፈው ኅብረተሰብ ይልቅ ገዢውን የሚደግፉት የሊግ እና የፓርቲው አባላት በምርጫ ተሳትፎ ጎልተው ይታያሉ፡፡ ለዚህ ችግር የፖለቲካ ምኅዳሩን ካጠበበው ኢሕአዴግ እኩል አባላት ምልመላ እና ማኅበራዊ የፖለቲካ ተሳትፎ (civic participation) እንዲያድግ ሲሠሩ ብዙም የማይስተዋሉት ተቃዋሚዎች ተወቃሾች ናቸው፡፡
በፓርቲዎች በኩል የገዢው ፓርቲ ተሳታፊነት ላይ ጥያቄ የማይኖር ሲሆን፣ እንዳለፈው የከተማይቱ ምክር ቤት ምርጫ ብቻውን ሮጦ ብቻውን ያሸንፋል ወይስ ተቃዋሚዎች ያጅቡታል የሚለው ጥያቄ ይከተላል፡፡
የምርጫ ቦርድ የምርጫውን 21 ክንውኖች ለማርቀቅ ከ75 ፓርቲዎች ጋር እንደተመካከረ መናገር፣ ተቃዋሚዎች በዚህ ምርጫ እንደሚሳተፉ አንድ አመላካች ነው፡፡ ትልቁ የተቃዋሚዎች ስብስብ ግንባር የሆነው መድረክን ጨምሮ 34 ፓርቲዎችም ተሰባስበው እየመከሩ መሆኑ ተቃዋሚዎች ለተሳትፎ መዘጋጀታቸውን ሌላው አመላካች ነው፡፡
ለምክር የተሰባሰቡት ተቃዋሚዎች ከኢሕአዴግ ጋር ለመደራደር በሚፈልጉባቸው ነጥቦች ዙሪያ አብረው እየሠሩ መሆኑን መናገራቸውም ኢሕአዴግ መድረክን በሚወቅስበት ቋንቋ የምርጫ ሥነ ምግባሩን ሰነድ ካልፈረሙ አልደራደርም ብሎ ድርቅ ካለ - ምርጫው የተቃዋሚ ድርቅ ይመታው ይሆናል የሚል ስጋት እየገባኝ ነው፡፡
በዚህ ስጋት ዙሪያ (በግል መገናኛ ብዙኃን) ተጠይቀው መልስ የሰጡት የመድረክና ሰማያዊ ፓርቲ ሰዎች ሲሆኑ ሁለቱም በምርጫው የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው ነገር ግን ‹‹ለአጃቢነት›› ብቻ ሳይሆን ለተወዳዳሪነት የሚያበቃ ምኅዳር መኖር እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ በግሌ ኢሕአዴግ በዚህ ወቅት ምኅዳሩን ከዚህ በላይ ሊያሰፋ ይችላል ብሎ የሚያስጠብቅ ምንም ተስፋ አይታየኝም፡፡ ስለዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ በቃላቸው ከፀኑ በመጨረሻ ሰዐትም ቢሆን ውድድሩን ረግጠው በመውጣት ኢሕአዴግ ብቻውን ተወዳድሮ ብቻውን ያሸነፈበትን ያለፈውን የከተማ ምክር ቤት ምርጫ ታሪክ እንዲደግም ያደርጉታል የሚለው ስጋቴ አይሏል፡፡
ምርጫውን ማን ያሸንፋል?
ተቃዋሚዎች ባለው ምኅዳር ተወዳድረን ዕድላችንን እንሞክራለን የሚሉ ቢሆን እንኳን የበጀት እጥረታቸው በቂ ቅስቀሳ ከማድረግ ስለሚገድባቸው - አንድ፣ የኢሕአዴግ ቤት ለቤት ቅስቀሳ /በነገራችን ላይ የቤት ለቤት ቅስቀሳው በ‹‹ገለልተኛ›› ምርጫ አስፈፃሚዎች አማካይነት ‹‹ነዋሪዎች የፈለጉትን እንዲመርጡ ብቻ›› የሚቀሰቅሱ ቢሆኑም ነዋሪዎች ሰዎቹን (ቀስቃሾቹን) በኢሕአዴግ-ዘመም እንቅስቃሴያቸው ስለሚያውቋቸው የኢሕአዴግ ቤት ለቤት ቅስቀሳ እንደሆነ ነው የሚቆጥሩት - እናም በቤት ለቤት ቅስቀሳው/ እና የአንድ ለአምስት ጠርናፊ እና አስጠርናፊ ስትራቴጂዎች ኢሕአዴግ የመራጮችን ልብ አንድም በፍርሐት አሊያም በፕሮፓጋንዳ ብዛት ስለሚሸንፍ - ሁለት ምክንያቶች የአሸናፊነቱን ነገር /ከግማሽ በላይ መቀመጫ ወንበሮችን የማግኘቱ ነገር/ ከኢሕአዴግ ውጪ ይሆናል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ሊሆን ይችላል፡፡
በሌላ በኩል ሁለት ጉዳዮች ለተቃዋሚዎች እስከመጨረሻው ድረስ እንዲታገሉ ምክንያት ይሆኗቸዋል፡፡ የመጀመሪያው ምክንያት አዲስ አበቤዎች በኢሕአዴግ ላይ ያላቸው ቅያሜ ጥልቀት ነው፡፡ የቅያሜው ምንጭ ከተለያዩ ፖለቲካዊ አፈናዎች እስከ ኑሮ ውድነት ድረስ ይዘልቃሉ፡፡ የኑሮ ውድነት በከተማዎች ውስጥ የገነነ እንደሆነ ኢሕአዴግም ሳይቀር ያምናል፡፡ የአዲስ አበባ ነዋሪ በአብዛኘው በቅጥር የሚተዳደር ደሞዝተኛ መሆኑ ደግሞ ወር ጠብቆ የሚያገኛት ምንዳ ከኑሮ ውድነት የመረረውን ገፈት እንዲቀምስ አስገድዶታል፡፡ በዚያ ላይ በስታትስቲክስ ኤጀንሲ የ2004 ሪፖርት ላይ እንደታየው ከ25 በመቶ በላይ ሥራ አጦች በመኖራቸው ሩብ ያክሉ የከተማ ሕዝብ በአየር ላይ እንዲንሳፈፍ ተገዷል፡፡ ይህ ምሬት የሚወልዳቸው ነዋሪዎች በኢሕአዴግ መማረራቸው ብቻ ተቃዋሚዎችን ባያውቋቸውም ወይም ባያምኗቸውም እንዲመርጧቸው እና ኢሕአዴግን በምርጫ ካርድ እንዲቀጡት ሊያስገድዳቸው ይችላል፡፡
ሁለተኛው ምክንያት ምሬቱ ቢኖርም ምርጫው ይጭበረበራል የሚለውን ስጋት የሚሽር ነው፡፡ በአዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር የበላይ ታዛቢነት የሚካሄድ ምርጫ መሆኑን የሚጠቅሱት ተስፈኞች ምንም እንኳን የፖለቲከኝነታቸውን ድርሻ ያገናዘበ ባይመስልም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ሃይማኖተኛ መሆናቸው በይፋ መነገሩ በማጭበርበር ድርጊቶች ላይ ሀገር አቀፍ መሻሽል እንዲጠብቁ ብዙዎችን አስገድዷል፡፡ ይሁንና የጠቅላይ ሚኒስትር መኖሩ ብቻውንም ቢሆን የተሻለ ፍትሐዊ ምርጫ እንደሚካሄድና እንደማይካሄድ ለማወቅ እስከመጨረሻው በመሳተፍ መሞከር የግድ ያስፈልጋል፡፡
ውጤቱ ምን ያመጣል?
እስካሁን ባለው አያያዝ /ተቃዋሚዎች አስማታዊ ጥበብ ተጠቅመው መነቃቃት ካልፈጠሩ በቀር/ አብዛኛዎቹ ወንበሮች ወደኢሕአዴግ እንደሚሄዱ አያጠራጥርም፡፡ ነገር ግን ምርጫው በፍትሐዊ መንገድ ተካሂዶ የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ተቃዋሚዎች የምክር ቤት ወንበር ካገኙ ብዙ የተቆረጡ ተስፋዎች መልሰው ይቀጠላሉ፡፡
ለምሳሌ፣ ለ2007ቱ ሀገር አቀፍ ምርጫ አዲስ መነቃቃት ይፈጠራል፣ በተጨማሪም አዲስ አበባ በፖለቲካዊ ሚና እና በኢኮኖሚያዊ አቅሟ የስበት ማዕከል (center of gravity) እንደመሆኗ በከተማይቱ የሚመጣው ለውጥ በሀገሪቱ ለውጥ ላይ ጉልህ ሚና የሚጫወት በመሆኑ አገሪቱ በኢሕአዴግ አፍላ የሥልጣን ዘመናት አይታ የነበረውን ዓይነት የዴሞክራሲ ጭላንጭል ዳግም ማየት ትችል ይሆናል፡፡
ነገር ግን ያልተጠበቀው ሆኖ ተቃዋሚዎች አዲስ አበባን በጥምረትም ቢሆን ቢያሸንፉ፣ ያለምንም ጥርጥር ምርጫ 2007 በተቃዋሚዎች የበላይነት ሊጠናቀቅ እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ እርግጥ ነው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመጪው የአዲስ አበባ ምክር ቤት ጋር መስማማት ካልቻሉ ስልጣናቸውን እና ደጋፊያቸው የሆነውን የተወካዮች ምክርቤት ተጠቅመው አፈራርሰውት ሌላ ምርጫ ሊያካሂዱ ይችላሉ፡፡ ይህ ግን አሳሳቢ አይደለም፣ ምክንያቱም የማይሆነው ከሆነ በኋላ የሚታሰብበት ጉዳይ ነውና!
አሁን ወደነባራዊው እውነታ እንመለስና ገዢው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚዎች ተወዳዳሪ እጩዎችን ሲያቀርቡ ሊያስቡበት የሚገባውን ትልቅ ቁም ነገር እናንሳ - አዲስ አበቤዎችን መመልመል፡፡ አዲስ አበባ ወልዳ ባሳደገቻቸው ልጆቿ መመራት አለባት ብዬ አምናለሁ፤ ከኔ ጎን የሚቆሙ ሌሎችም በርካቶች ናቸው፡፡ ስለሆነም ፓርቲዎች እጩዎቻቸው የአዲስ አበባን ነገረ ሁኔታ በቅጡ የሚረዱ፣ አዲስ አበባ ውስጥ ተወልደው ያደጉ (ወይም ለበርካታ ዓመታት የኖሩባትን) ዕጩዎች እንዲመለምሉ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፡፡
የኛ ኃይል
Monday, October 15th, 2012ከዞን ዘጠኝ የተወሰደ
“ፒያሳ፤ መሐሙድጋ ጠብቂኝ” በመሐመድ ሰልማን የተጻፈ እና ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፈ ኢ-ልቦለዳዊ መጣጥፎች ስብስብ ነው፡፡ የዛሬ ዓመት ገደማ ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ በተባለ መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት አማካይነትመጽሐፉን የመገምገሚያ ዝግጅት አምስት ኪሎ በሚገኘው ብሔራዊ ሙዚዬም ቀርቦ ነበር፡፡ በውይይቱ መሐል የመጽሐፉ ዝነኝነት ምንጮች ምን ምን ናቸው የሚል ውይይት የነበረ ሲሆን ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ‹‹ደራሲው የአዲስ ነገር ጋዜጣ ጸሐፊ የነበረ›› መሆኑን እና ‹‹ጽሑፎቹም በአዲስ ነገር ጋዜጣ እና ድረገጽ ላይ ወጥተው የነበሩ›› መሆናቸውን ጠቀሰ፡፡ ውይይቱ የአዲስ ነገር ጋዜጣ መታሰቢያ ይመስል፣ የትዝታ ጫወታው ተጧጧፈ እናም ከውይይቱ ተሳታፊዎች አንዱ የሚከተለውን ሲናገር ረዥም ጭብጨባ አዳራሹን አደመቀው ወጣቱ አስተያየት ሰጪ በንግግሩ መሃል የተጠቀመው እና ጢም ብሎ የሞላውን አዳራሽ በጭብጨባ ያናጋው ንግግር የሚከተለው ነበር፡፡
‹‹ይህ ትውልድ በአዲስ ነገር ጋዜጣ የሚደራደር ትውልድ አይደለም፡፡››
ጉዳዩን አስገራሚ የሚደርገው ወጣቱ ይህንን የተናገረው አዲስ ነገር ጋዜጣ መታተም ካቆመች ከሁለት ዓመታት በኋላ መሆኑ ሲሆን፣ አጋጣሚው የጋዜጣዋ መንፈስ በበርካቶች ልብ ውስጥ በትኩስነት መኖሩን የሚናገር ነበር፡፡
ዛሬ፣ ጥቅምት 5/2005 የዓለም የጡመራ የተግባር ቀን (Blog Action Day 2012) “የኛ ኃይል” በሚል መሪ ቃል ይከበራል፡፡ የጡመራ የተግባር ቀን በየዓመቱ የሚከበር፣ በዓለም ዙሪያ ያሉ ጦማሪዎች በሙሉ በአንድ ሐሳብ ዙሪያ የሚጽፉበት ቀን ነው፡፡ የተጀመረው እ.ኤ.አ. በ2007 ሲሆን በተመሳሳይ ዓመት ‹‹አካባቢ››፣ በ2008 ‹‹ድህነት››፣ በ2009 ‹‹አየር ለውጥ››፣ በ2010 ‹‹ውሃ››፣ በ2011 ‹‹ምግብ›› በሚል ሲካሄድ ዘንድሮ ደግሞ በ2012 ‹‹የእኛ ኃይል›› በሚል እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የዘንድሮው መሪ ቃል፣ ማኅበረሰብ፣ እኩልነት፣ ፀረ-ሙስና እና ነጻነትን በተመለከተ የኛ ኃይል ምን እንደሆነ በመስበክ እንዲከበር ታስቦ የተመረጠ ነው፡፡ አከባበሩ ቀላል ነው፤ አስተባባሪዎቹ እንዳስቀመጡት ‹‹profile someone or a group who inspires you by the way they made a positive influence… (ባመጡት አዎንታዊ ተጽዕኖ ያነቃቃችሁን የየሆነ ሰው ወይም ቡድን በመምረጥ ጻፉ…)›› የሚል ነው፡፡
እኛም ጮክ ብለን ስናስብበት እና በጭንቅላታችን ያቃጨለችው አዲስ ነገር ጋዜጣ ብቻ ሆነች፡፡ አዲስ ነገር ጋዜጣ ለሁለት ዓመታት (ከጥቅምት 2000 እስከ ታሕሳስ 2002) ብቻ በስርጭት የቆየች ነገር ግን መራኄ አዘጋጇ መስፍን ነጋሽ የጋዜጣዋን ሁለተኛ ዓመት አስመልክቶ እንደገለፀው ‹‹አጭር ግን ረዥም ዓመት›› የኖረች ያክል የማትረሳ ጋዜጣ ናት፡፡
አዲስ ነገር ጋዜጣ በሌጣ ግለሰብ ተፅዕኖ እና ባለቤትነት የማትመራ፣ በስድስት መሥራች አባላት የተቋቋመች እና በሕፀፅ አታች (critical analysis) ጽሁፎቿ ከፍተኛ ተወዳጅነትን እና ተነባቢነትን ለማትረፍ የበቃች፣ የአንባቢውን ቁጥር ያሳደገች፣ የጸሐፍትን ችሎታ የፈተነች (standard ያኖረች)፣ በየጊዜው በማደግ እና ተፅዕኖ በመፍጠር ላይ የነበረች ጋዜጣ ነበረች፡፡ ጋዜጣዋ በቅንጅት መፍረክረክ ሰሞን ተመስርታ በተለይም ኢሕአዴግን በሚነቅፈው ማኅበረሰብ ውስጥ የነበረው የስሜት ስብራት በመጠገን ከፍተኛ መነቃቃትን ለመፍጠር የቻለች እና በማንኛውም መለኪያ አማራጭ መገናኛ ብዙሐን የሚለውን ማዕረግ ለመቀበል የምትመጥን ናት ለማለት ያስደፍራል፡፡፡
ሃሌሉያ እና Terje S Skjerda የተባሉ የጥናት ባለሞያዎችበግል ጋዜጦች ብቃት ላይ እ.ኤ.አ. በ2009 ባደረጉት እና ሁሉንም የግል ጋዜጦች ሊባል በሚችል መልኩ በነቀፉበት ጥናታቸው ውስጥ አዲስ ነገር ጋዜጣን እንዲህ ሲሉ ነበር የጠቀሷት፡-
[To be fair,…] There are newspapers which have steered away from extremist reporting and instead try to give space for different voices. Late 2007 saw the launch of Addis Neger, a private newspaper which by 2009 has grown to become one of the two largest Amharic weeklies with a weekly circulation of 25,000-30,000 copies. Its profile is serious,balanced and critical journalism with emphasis on commentaries and in-depth stories. Within the professional limitations that exist, Addis Neger and other publications have produced valuable reporting which has challenged the government in the public sphere.
([ሚዛናዊ ለመሆን…] ከፅንፈኛ ሪፖርቶች አፈንግጠው ለተለያዩ ድምፆች ቦታ የሰጡም ጋዜጦች ነበሩ፡፡ በ2002 ከአገሪቱ ሁለት ከፍተኛ ስርጭት ያላቸው (ከ25,000-30,000 ቅጂ) ጋዜጦች መካከል አንዱ ለመሆን የበቃው የአዲስ ነገር ጋዜጣ መመስረት በ2000 አጥቢያ ታየ፡፡ ይዘቱ በአስተያየቶች እና ጥልቅ ታሪኮች ላይ ያተኮረ፣ ቁምነገር አዘል፣ ሚዛናዊ እና ሂስ አዘል ጋዜጠኝነትን የተከተለ ነበር፡፡ በነባራዊው የሙያተኞች እጥረት አዲስ ነገር እና ሌሎችም መንግስትን በሕዝባዊ ክበብ ውስጥ የሚገዳደር እሴት ፈጥረዋል፡፡)
አዲስ ነገር ጋዜጣ፣ መስራቾቿ እና ጋዜጠኞቿ በመሰደዳቸው አሁን መታተም ካቆመች ሦስት ዓመታት እየተጠጋት ነው፡፡ ሁለቱ ጋዜጠኞቿ ዐብይ ተክለማርያም እና መስፍን ነጋሽም በቅርቡ ሽብርተኝነትን በመተባበር የ8 ዓመት እስር ተፈርዶባቸው በስደት ላይ ይገኛሉ፡፡ አዲስ ነገር ጋዜጣ ላይ ይወጡ የነበሩት ጽሑፎች ግን እስካሁንም ተፅዕኗቸው አልበረደም፡፡ ዳንኤል ክብረት፣በእውቀቱ ስዩም እና መሐመድ ሰልማን የአዲስ ነገር ላይ ጽሑፋቸውን መጽሐፍ አድርገዋቸው እንደአዲስ በብዙ ሺህ ኮፒዎች ተሸጠዋል፡፡ እነሠርጸ ፍሬስብሓት በሙዚቃ ላይ፣ እነማስረሻ ማሞ በፊልም ላይ የሚጽፏቸው ሂሶች የአልበሙን እና የፊልሙን ገበያ ከመወሰንም በላይ፣ ባለሙያዎቹ ለሥራቸው እንዲጠነቀቁ፣ ለአድማጭ ተደራሹም እንዲመርጥ የሚያደርጉ ነበሩ፡፡ ዶ/ር ብርሃኔ ረዳኢ በአስቂኝ የአጻጻፍ ስልቱ የሚያቀርባቸው የሕክምና ነክ ጉዳዮች የብዙዎችን ቀልብ እንደገዙ እስከዛሬም ይታወሳሉ፡፡
የአዲስ ነገር በኢትዮጵያ ፕሬስ ላይ የፈጠረችው ተጽእኖ በቀላሉ የሚታይ አልነበረም፡፡ እንደ አማራጭ፣ ተወዳጅ እና ተመራጭ ሚዲያ ሆኖ ከመቆየትም፣ በተጨማሪ የንባብ ባሕልን ወደ ፋሽንነት ለማምጣት እንዲሁም የወጣቱን ትውልድ ድምጽ የማሰማትም ሚና ነበራት፡፡ አዲስ ነገር ወደ ንባብ እና ወደ ቁም ነገር ያመጣቻቸው አያሌ ወጣቶች ዛሬም ከአዲስ ነገር አለመኖር በኋላም ሐሳብን በነጻነት ስለ መግለጽ ሲጨነቁ እና ሲጠበቡ ይታያሉ፡፡ በአዲስ ነገር መነሳሳት የተነሳም ወደ ጡመራ እና ውይይት የመጡ፣ ተስፋ ማድረግ የጀመሩም ቀላል አይደሉም፡፡
ከሚዲያው የሚመነጭ ጤናማ የአደባባይ ተዋስኦ በጠፋበት በፕሬሱ የጨለማ ዘመን ማግስት አዲስ ነገርን ማግኘት ለጤናማ ሕዝባዊ ውይይቶች መከፈት አስተዋጽዖ የነበረው ከመሆኑም በላይ ጋዜጣዋ መንግስትን በጠንካራ መልኩ በመተቸት ብትታማም የገዥውን ፓርቲ አቋም የሚያንጸባርቁ ቋሚ አምደኞች ነበሯት፡፡ አሁን በሥራ ላይ የሚገኙ እና ታዋቂ የሆኑ የሚዲያ ተቋማትም ቢሆኑ ራሳቸውን ሲገልጹ አዲስ ነገርን ማነጻጸሪያ ሲያደርጓት ተስተውሏል፡፡
ከሚዲያው የሚመነጭ ጤናማ የአደባባይ ተዋስኦ በጠፋበት በፕሬሱ የጨለማ ዘመን ማግስት አዲስ ነገርን ማግኘት ለጤናማ ሕዝባዊ ውይይቶች መከፈት አስተዋጽዖ የነበረው ከመሆኑም በላይ ጋዜጣዋ መንግስትን በጠንካራ መልኩ በመተቸት ብትታማም የገዥውን ፓርቲ አቋም የሚያንጸባርቁ ቋሚ አምደኞች ነበሯት፡፡ አሁን በሥራ ላይ የሚገኙ እና ታዋቂ የሆኑ የሚዲያ ተቋማትም ቢሆኑ ራሳቸውን ሲገልጹ አዲስ ነገርን ማነጻጸሪያ ሲያደርጓት ተስተውሏል፡፡
የኃይለማርያም ፲ ተግዳሮቶች
Wednesday, October 10th, 2012የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ኅልፈት ከተሰማ 50 ቀናት ሆኑት፤ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ቃለ መሓላ ከፈፀሙ ደግሞ 18 ቀናት፡፡ እነዚህ ከሁለት ሳምንታት እምብዛም ያልበለጡ ቀናት የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምን አያያዝ ለመገምገም በቂ አይደሉም ነገር ግን ‹‹ያባት ዕዳ ለልጅ›› በሚለው ብሒል መሠረት የመለስን ፈለግ በመከተል እና ባለመከተል መካከል፣ ሊያመጧቸው በሚችሏቸው ለውጦች እና ሕዝብ/አገር ከሚጠብቅባቸው ነገሮች አንፃር የሚጠብቃቸውን ተግዳሮት ማስቀመጥ ይቻላል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በተለይ ከቪኦኤ የእንግሊዝኛው አገልግሎት ጋር ባደረጉት የ40 ደቂቃ ቃለምልልስ፥ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የተለየ አቋም እንደሌላቸው መታዘብ ይቻላል፡፡ ፓርቲውም ቢሆን የአቶ መለስን ውርስ ለማስቀጠል እንደሚተጋ በተደጋጋሚ ተናግሯል፡፡ በተቃራኒው መለስ የሚባልላቸውን ያህል ውጤታማ እና ፍፁም አልነበሩም፡፡ ለዚህም ምስክሩ ሳይዘጉ የተዉአቸው የሚከተሉት አጀንዳዎች ናቸው፡፡ የአቶ ኃይለማርያም ተግዳሮቶች ሁነው ይቀጥላሉ፡፡
፩ - የምርጫ 2007 ጉዳይ
ምርጫ 2007፣ በ20ዓመት ውስጥ መለስ በበላይነት የማይከታተሉት/የማይመሩት የመጀመሪያው ምርጫ ነው፡፡ ከምርጫ 97 ውጤት አወዛጋቢነት፣ ከምርጫ 2002 የኢሕአዴግ ጠቅላይ ገዢነት በኋላ የሚካሄድ ማንኛውም ምርጫ ቀልብ የሚስብ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ከዚያም በላይ ደግሞ ለሁለቱም ምርጫዎች እንከን ተጠያቂ የሆኑት መለስ አለመኖራቸው፥ የተለየ ነገር ይኖር ይሆን የሚለውን ጥርጣሬ በር ይከፍትለታል፡፡
ይህንን ጥርጣሬ አዎንታዊ ምላሸ ሰጥቶ ተአማኒነትን ለመጎናፀፍ አቶ ኃይለማርያም ቀላል የማይባል ተግዳሮት ይጠብቃቸዋል፡፡
ተቃዋሚ ፖለቲከኞች በ1987፣ በ1992 እና በ1997 ማግኘት ከቻሉት የፓርላማ ወንበር አንፃር በ2002 ወደ አንድ ወንበር የተመለሱት በፖለቲካው ምሕዳር መጥበብ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ኢሕአዴግ በደፈናው ይህን ቢክድም መከራከሪያ ነጥቦችን ዘርዝሮ እውነታውን ማረጋገጥ ግን ከባድ አይደለም፡፡ ስለዚህ አቶ ኃይለማርያም ባላቸው ስልጣን ሁሉ ተጠቅመው ይህን ምህዳር ማስፋት ወይም ወደነበረበት መመለስ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ፈተናው ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ሕዝባዊ ቅቡልነት የሚያገኝ ምርጫ ከማካሄድም በተጨማሪ በፓርቲው አባሎች እና ደጋፊዎች ኢሕአዴግን ለስልጣን የሚያበቃ የፓርላማ ወንበር እንዲያስገኙለት ይጠበቅባቸዋል፡፡ አለበለዚያ፣ ሕዝቡ ድምፁን ለኢሕአዴግ የነፈገው በከረመ ብሶቱ ቢሆንም እንኳን በእርሳቸው አስተዳደር መሳበቡ የማይቀር ተግዳሮታቸው ነው፡፡
፪ - የሕዳሴው ጉዳይ
የኢትዮጵያ መንግስት በተለይ ከ2000 ወዲህ ያለውን ጊዜ የሕዳሴው ዘመን ብሎ ሰይሞታል፡፡ ከምርጫ 2002 ውጤት በኋላ ደግሞ በአምስት ዓመታት የሚጠናቀቅ፣ ‹‹የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ›› የተሰኘ፣ በጣም አጓጊ፣ ድህነትን ‹ቻው፣ ቻው› ለማለት ያለመ ዕቅድ ተነድፏል፣ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ አንዱ የዚህ አካል ነው፡፡
የ‹ትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድ› ሁለት ዓመቱን የጨረሰ በመሆኑ እስካሁን የመጣበት መንገድ በአምስት ዓመት ውስጥ የተባለው ቦታ እንደማያደርስ ያሳብቃል፡፡ የሕዳሴው ግድብ መጀመሪያ በአራት፣ ቀጥሎ በሰባት ዓመታት ያልቃል የተባለ ቢሆንም አንደኛ ዓመቱን ሲያከብር 6 በመቶ ብቻ መጠናቀቁ ስለተነገረ በዚህ ስሌት 16 ዓመት ድረስ ሊፈጅ እንደሚችል ይገመታል፡፡
ከዚህ እውነታ በተቃራኒ መለስ የኢትዮጵያ መሐንዲስ ናቸው በሚል ሲሞካሹ፣ እንከን የማይወጣላቸው እንደነበሩም እየተነገረ ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ፣ ለዕቅዶቹ በታቀደላቸው ጊዜ አለመጠናቀቅ ተጠያቂ የመሆን ተግዳሮት የሚገጥማቸው አቶ ኃይለማርያም ናቸው፡፡
፫ - የኑሮ ውድነት ጉዳይ
የአቶ መለስ አስተዳደር በጣም ሲወቀስባቸው ከነበሩ ጉዳዮች መካከል የኑሮ ውድነት በግንባር ቀደምነት ይታወሳል፡፡ በተለይም የከተማ ኑሮ ውድነት በየዕለቱ እያሻቀበ እና የብር የመግዛት አቅም እየወረደ መምጣቱ ለመንግስታቸው የራስ ምታት መሆኑን የኢሕአዴግ ሰዎችም ቢሆኑ የማይክዱት ሐቅ ነው፡፡ መጀመሪያ ሰሞን መለስ የዋጋ ግዥበቱ የተከሰተው በኢኮኖሚያችን ማደግ ምክንያት የግለሰቦች ፍላጎት በማሻቀቡ መሆኑን የተናገሩ ቢሆንም፣ ቆይተው መንግስት አላግባብ ብዙ ብር ማተሙን እንደምክንያት መጥቀሳቸው ይታወሳል፡፡
የኑሮ ውድነት፣ ከፖለቲካዊ ጥያቄዎች ሁሉ በላይ ሕዝቡን አስቆጥቶ ለለውጥ ሊያነሳሳው ይችላል እየተባለ በሚፈራበት በዚህ ወቅት፣ አቶ ኃይለማርያም የአመራሩን በትር ጨብጠዋል፡፡ ስለሆነም ይህንን ለ10 ዓመታት ያህል በሚያስፈራ ፍጥነት እየገሰገሰ ያለውን የዋጋ ግዥበት መቆጣጠር አለዚያም ውጤቱን መቀበል የኃይለማርያም ሌላኛው ተግዳሮት ነው፡፡
፬ - የዳያስፖራዎች ጉዳይ
መለስ እና ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ዓይንና ናጫ ሁነው መክረማቸው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በተለይም በሰሜን አሜሪካ፣ በአንዳንድ የአውሮፓ አገራት እና በደቡብ አፍሪካ መለስ የሚገኙባቸው ስብሰባዎች ሁሉ በተቃው ሰልፍ ይጥለቀለቁ ነበር፡፡ ዳያስፖራው፣ በሚከፍታቸው የተለያዩ ድረገጾች ምርር ያለ ተቃውሞውን ሲያሰማባቸው ከርሟል፡፡ በጥቅሉ መንግስታቸው የዳያስፖራውን ድጋፍም እውቅናም አጥቷል ማለት ይቻላል፡፡
አቶ ኃይለማርያም ምንም እንኳን የመለስን ጅማሮ የማስቀጠል ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ደጋግመው ቢናገሩም፣ ጠባቸውንም ለማስቀጠል ይሻሉ ብዬ አልገምትም፡፡ ይሁን እንጂ የዳያስፖራውን ልብ መልሰው ለኢሕአዴግ የማራራቱ ጉዳይ ቀላል ተግዳሮት አይሆንላቸውም፡፡
፭ - የተአማኒ ተቋማት ጉዳይ
ወሳኝ የሚባሉት የመንግስት ተቋማት - ለምሳሌ ፍርድ ቤት፣ መገናኛ ብዙሐን (የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እና ሌሎችም…)፣ የምርጫ ቦርድ፣ የፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ዕንባ ጠባቂ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ሰብዐዊ መብት ኮሚሽን እና ሌሎችም ለመንግስት ወይም ለገዢው ፓርቲ ይወግናሉ የሚል ቅሬታ በኅብረተሰቡ ውስጥ ይንፀባረቃል፡፡ እንዲያውም፣ የመንግስት እና የገዢው ፓርቲ ሥራ ተቀላቅሎ እየተሠራ ነው፤ የመንግስት መሥሪያ ቤቶች የመንግስትን ኃብት እየተጠቀሙ ነው የሚል ተደጋጋሚ ወቀሳ ይሰማል፡፡ መንግስት ከሷቸው የተረታባቸው፣ ወይም መንግስትን ከሰው የረቱ ተቃዋሚ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች የሉም የሚል ብሶት ይሰማል፡፡
በዚህ ዐውድ ውስጥ ያሉና ተአማኒነታቸውን ያጡ ተቋማት እንዲህ ሁነው መዝለቅ እንደለሌባቸው ይታመናል፡፡ ይህንን እውነታ መረዳትና በቁርጠኝነት መፍትሄ የመፈለግ ወይም ተቋማትን ከፓርቲ ተፅዕኖ የማላቀቁ ተግዳሮትም አቶ ኃይለማርያን እየጠበቃቸው ነው፡፡
፮ - የኤርትራ ጉዳይ
የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጦርነት ምንም እንኳን በዝምታ ላይ ቢገኝም፣ አንድ ቀን ያገረሽ ይሆን የሚለው ጉዳይ የሁለቱ አገራት ብቻ ሳይሆን የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የዘወትር ስጋት ነው፡፡ እንዲያውም የአቶ መለስን ሞት ተከትሎ ሊቀሰቀሱ የሚችሉ ግጭቶች ይኖሩ ይሆናል የሚሉ ፍራቻዎችም በጥቂቶች አዕምሮ ውስጥ አለ፡፡
ይህም ብቻም አይደለም፣ ለአንዳንዶች የአሰብ ጉዳይ የተዘጋ ጉዳይ ነው፡፡ ጥቂት ለማይባሉት ደግሞ ገና ትኩስ አጀንዳ እንደሆነ ተዳፍኖ አለ፡፡ ተቃዋሚዎች ወደብ ጉዳይ ላይ ቀርተዋል እየተባሉ የሚታሙትም ለዚያው ነው - ጉዳዩ የተዘጋ የሚመስለውን ያክል ያልተዘጋ በመሆኑ፡፡ በዚህ መሓል፣ ሊመለሱ ለሚችሉ ጥያቄዎች መልስ ማፈላለግ፣ በሁለቱ አገራት መካከል ሰላምን ባለበት ማቆየት፣ ምናልባት ግጭት ቢፈጠር እንኳን ተዘጋጅቶ መጠበቅ እና አገሪቱ ላይ ቀውስ ሳያስቀጥል በፊት መቆጣጠር የአቶ ኃይለማርያም ተግዳሮት ይሆናል፡፡
፯ - የሶማሊያ ጉዳይ
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ከኃይለሥላሴ ጊዜ ጀምሮ የሚቆሰቆስ እና የሚከስም ግጭት አላቸው፡፡ አሁን ግን ዋናው ጠብ ከዋናው መንግስት ጋር ሳይሆን፣ ከአል ሻባብ ጋር ነው፡፡ አል ሻባብ በአልቃይዳ ይረዳል በሚል ከኢትዮጵያ ይልቅ ጠላትነቱ ለአሜሪካ ነው፣ ይህንን ያክል ተቀባይነት እንዲያገኝ ያደረገው የአቶ መለስ መንግስት እርሱን ለመውጋት ሶማሊያ መግባቱ ነው የሚሉ ክሶች ተደጋግመው ይሰማሉ፡፡
ኢትዮጵያ አል ሻባብን አባርሬ መጣሁ ብላ ተናግራ ሳትጨርስ አል ሻባብ ከሽግግር መንግስቱ መቋዲሾን መቀማቱ ተሰማ፡፡ አሁንም በድጋሚ የኬንያን ሠራዊት ተከትሎ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሶማሊያ ውስጥ ይገኛል፡፡ አል ሻባብ የአቶ መለስን ሞት ተከትሎ ኢትዮጵያ ላይ ዛቻ የሚመስል መግለጫ አውጥቷል፡፡ አሁን በርግጥም አል ሻባብ ጠላታችን ነው፤ ስለዚህ በሕዝብም ሆነ በአገር ላይ ሊያደርስ የሚችለውን አደጋ ቀድሞ መከላከል፣ ሶማሊያን በሠራዊትም ሆነ በሰው ኃይል እየደገፉ በተዘዋዋሪ የኢትዮጵያን ደህንነት የማስጠበቁ ጉዳይ ለኃይለማርያም ቀላል ተግዳሮት አይደለም፡፡
፰ - የፖለቲካ እስረኞች ጉዳይ
አቶ መለስ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ እስረኛ የለም ብለው ያምኑ ነበር፡፡ አቶ ኃይለማርያምም ይህንኑ ጉዳይ ለቪኦኤ ሲያስረዱ የታሰሩት ጋዜጠኞች እና ፖለቲከኞች ጉዳይ ሁለት ባርኔጣ የማድረግ ጉዳይ ነው ብለውታል፡፡ በአንደኛው ባርኔጣቸው በሕጋዊ መንገድ ጋዜጠኝነት እና ፖለቲከኝነታቸውን ይተገብራሉ፣ በሌላኛው ባርኔጣቸው በጋዜጠኝነት እና በፖለቲከኝነት ስም ያሸብራሉ ባይ ናቸው አቶ ኃይለማርያም - ተከሳሾቹ ጋዜጠኞች እና ፖለቲከኞችን፡፡
በዚህ ግን ብዙዎች አይስማሙም፤ የጋዜጠኛ ማኅበራት፣ የሰብዐዊ መብት ተቆርቋሪዎች እና ኃያላን መንግስታት ሳይቀሩ በኦፊሴላዊ መግለጫዎች ይህንን አውግዘዋል፣ እያወገዙም ነው፡፡
እንዲያውም ኢሕአዴግ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መርሑ፣ በአውራ ፓርቲ ስም ጠቅልሎ በመግዛት ሕልሙ የፈጠረው የፖለቲካ ምሕዳርን የማጥበብ እና ለስልጣኑ የሚያሰጉ ወገኖችን የማፈኛ ዘዴው ነው ብለው ይማረራሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች እውነት የላቸውም ብሎ ማስረጃ መስጠት ለገዢው ፓርቲ ይከብደዋል፡፡ አቶ ኃይለማርያም ሌሎች ጋዜጠኞችን እና ፖለቲከኞችን ያለማሰር ብቻ ሳይሆን፣ የታሰሩትን ማስፈታት እና የተሰደዱትን በማስመለስ ሰላማዊ የተቀናቃኝነት መንፈስ የማዳበር ታላቅ ኃላፊነት እና ተግዳሮት ከፊታቸው ይጠብቃቸዋል፡፡
፱ - የሰብዐዊ መብት እና ዴሞክራሲ ጉዳይ
የአቶ መለስ መንግስት ክፉኛ ሲወቀስባቸው የነበሩት ጉዳዮች በሕገ መንግስቱ የተደነገጉትን ሰብአዊ እና ፖለቲካዊ መብቶችን በመጣስ ነው፡፡ አቶ መለስም ራሳቸው፣ በተለይም በዓለም አቀፍ አደባባዮች ዴሞክራሲያቸው ገና በዕድገት ላይ መሆኑን እና ለልማት ትኩረት በመስጠታቸው የደከሙበተ የቤት ሥራ እንደሆነ ለማስረዳት ሲጥሩ ከርመዋል፡፡ ልማቱ በራሱ ተሳክቷል/አልተሳካም የሚለው ጉንጭ አልፋ ክርክር ቢሆንም፣ ልማትም ሆነ ዴሞክራሲ በሒደት የሚመጡ ነገሮች መሆናቸውን መካድ አይቻልም፡፡ ነገር ግን ለልማቱ ተተግቷል የሚባለውን ያክል ለዴሞክራሲ ያልተተጋበት ምክንያት ምን እንደሆነ አይታወቅም፡፡
ይህ የሰብዐዊ መብት እና የዴሞክራሲ ጥያቄ በተለይም በምዕራባውያን ዘንድ ኃይለማርያምን የሚገዳደር ጉዳይ እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡ ምዕራባውያን ከመለስ ጋር በነበራቸው የፀረ - ሽብር የጋራ ወዳጅነት እና በመለስ አንደበተ ርቱዕነት፣ የእርዳታ አሰጣጥ ቅድመ ሁኔታቸው የነበረውን ዴሞክራሲ ዘንግተውት ከርመዋል፡፡ በዚሁ ግን ላይቀጥሉ ይችላሉ፤ ለዚህ እና ለሕዝባቸውም ሲሉ አቶ ኃይለማርያም የዴሞክራሲ እና ሰብዐዊ መብት ጥበቃን ጉዳይ ዋጋ ለመስጠት እንዲተጉ የሚጠበቅባቸው፡፡
፲ - የኢሕአዴግ ውስጥ ጉዳይ
ኢሕአዴግ የአራት ፓርቲዎች ድምር መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመለስ አገዛዝ ስር፣ የኅወሓት ሚና ከሌሎቹ የጎላ ሆኖ የቆየ ቢሆንም አሁን ብዙዎች እንደሚገምቱት በኅወሓት የኋላ ግፊት በአቶ ኃይለማርያም አመራር የበፊቱ ሕብረታቸው ይኖራል ብሎ መጠበቅ የዋሕነት ሊሆን ይችላል፡፡ መለስ በሁሉም ፓርቲዎች፣ በተለይም በኀወሓት ተቀባይነት ስለነበራቸው፣ አንዱን ሲጫኑ እንኳን ተቀባይነት የማግኘት ዕድል ነበራቸው፡፡ አቶ ኃይለማርያም፣ በኅወሓት የበላይነት ከሚመራው ሠራዊት አንስቶ ሌሎቹንም ፓርቲዎች የማዘዙ ጉዳይ ትልቅ ተግዳሮት ይሆንባቸዋል፡፡
የኢሕአዴግ ፓርቲዎች ከመለስ ኅልፈት በፊት ወደአንድነት ይዋሃዳሉ ተብለው የነበረ ቢሆንም ባልታወቀ ምክንያት የሚዋሃዱበት ጊዜ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል፡፡ ያንን የውህደት ዕድል የመምራቱም ሆነ ሁሉንም ፓርቲዎች አቻችሎ በስምምነት የማስቀጠሉ ፈተና በፍፁም ቀላል አይሆንም፤ ካልተሳካላቸው ደግሞ ግንባሩ ሊሰነጣጠቅ እና እንደገዢ መቆም ሊያቅተው ስለሚችል በፓርቲው ውስጥ ምናልባት ሊገጥሟቸው ከሚችሉ ተግዳሮቶች ሁሉ ይህ የበረታ ነው፡፡
እንግዲህ ዋና ዋናዎቹን ብቻ ለመዘርዘር ተሞከረ እንጂ ከዚህም በላይ ተግዳሮቶች እንደሚኖሩባቸው መገመት ቀላል ነው፡፡ ኢሕአዴግ እስካሁን ድረስ ያልተላቀቀውን የጫካ መንፈስ ማጥፋት፣ የፕሬሱን ነፃነት ማጠናከር እና ሌሎችም በርካታ ተግዳሮቶች ይኖሩባቸዋል፡፡
በዚህ ጽሑፍ ተግዳሮቶቻቸውን ብቻ ለመግለፅ ሞከርን እንጂ በርካታ ዕድሎችም አሉዋቸው፡፡ ከመለስ ሞት በኋላ የተፈራውን እና የተወራውን ያህል በፓርቲው ውስጥም ሆነ በመንግስታዊ አስተዳደሩ ላይ የተከሰተ፣ የጎላ ውዥንብር አለመኖሩ ምናልባትም ፓርቲው በውስጣዊ አሠራሩ ዴሞክራሲያዊ ሊሆን ይችላል የሚል አስተሳሰብ ፈጥሯል፤ ያ እውነት ከሆነ ፓርቲው ሌሎቹን ችግሮች በውስጣዊ የአፈታት ዘዴ በመፍታት ጥንካሬውን ጠብቆ መዝለቅ ይችል ይሆናል፡፡
የ2004 ሒሳብ ሲዘጋ
Saturday, September 8th, 2012እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉ በዚህ ዓመትም ሰዎች ከፌስቡክ ውጪ እንዴት እንደሚኖሩ ለማወቅ ጉግል ውስጥ ፈልጌም፣ አስፈልጌም መልስ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ስለዚህ በፌስቡክ ውስጥ መኖሬን ቀጥያለሁ፡፡ በርግጥ ፌስቡክ ምንም አልጎደለበትም፤ እንኳን የሆነው የታሰበው ሳይቀር ይወራበታል፡፡ ለአብነትም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትርን ሞት መጥቀስ ይቻላል፡፡
ፌስቡክ ምድር ላይ ካለው ‹እቤት-እመስሪያቤት› ምልልስ የተሻለ ፋይዳ ያለው ሥራ ለመስራት የተመቸ ዕድልም ይፈጥራል፡፡ የዳቦ ጉዳይ (bread winning) ሁላችንንም በየሙያችን ቢያሰማራንም፣ የምንናፍቀው እና የሚናፍቀን ሌላ ነገር የለም ማለት መቼም አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ የምንዋደደውን ያክል የምንወደውና የሚወደንን ዓይነት መንግስት ያገኘንበት ጊዜ እምብዛም ነው፡፡ ይህንን መናፈቅ እና መማከር ደንብ ሆኖ፣ በሌላም፣ ዓመቱን ሙሉ በጻፍናቸው ነገሮች ያስደሰትነው ሰው እንዳለ ሁሉ ያስቀየምነው የለም ማለት ዘበት ነውና፣ ያው የግል ጥቅም ይዞን አለመሆኑ ታውቆ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ይቅር መባባልን የመሰለ ነገር የለም፡፡
በዚህ ዓመት በፌስቡክ ገጼ ላይ ያሰፈርኳቸውን እና ከወዳጆቼ ጋር ቅኔ የተዛረፍኩባቸውን ግጥሞች በአንድ መድብል ‹‹የፌስቡክ ትሩፋት›› በሚል ጠርዠዋለሁ፡፡ ማንም ቢፈልግ እዚያው ባለበት ማንበብ፣ ወይም ዳውንሎድ ማድረግ ይችላል፡፡ አምና ሁለት ሺህ ሦሰትን በአርባ ሁለት በሚል በ2003 የጻፍኳቸውን ጦማሮች አንድላይ ቢጠረዙ መልካም ነው በሚል ማስቀመጤ ይታወሳል፡፡ አሁንም ዘንድሮ የሞነጫጨርኳቸውን እዚህ አስቀምጫለሁ፡፡
በስህተቴ ያረማችሁኝን እና የነቀፋችሁኝን፣ በብርታቴ ላይ አበርታች የሆነ አስተያየታችሁን ለሰጣችሁኝ፣ በዝምታ ስታነቡኝ ከርማችሁ መንገድ ላይ ስታገኙኝ ለነገራችሁኝ እና ለሌሎቻችሁም ሁሉ ምስጋናዬ እንዲደርሳችሁ ከጉልበቴ ሸብረክ ማለቴን እንደምታስቡልኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
አዲሱ ዓመት ሕልማችን የሚሞላበት፣ ለፍቅራችን ዋጋ የምንሰጥበት ይሁን፤ አሜን!
በ2004 የተጻፉ
- መንግስት ያልቻለውን እኛ ብንሞክረውስ?
- ሞክሮ መሳሳት እና ከስህተት መማር
- ፍቅር፤ ከፍቅር እስከ መቃብር (ልቦለድ)
- የአፋልጉኝ ማስታወቂያ ለተቃዋሚዎች
- የትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድና አንዳንድ አካላት
- ኢትዮጵያውያን ለምን ዲቪ አይሞሉ?
- “ደረሰኝ ሳይቀበሉ፥ ሒሳብ አይክፈሉ”
- “አሰብ የማን ናት?”ን በጨረፍታ
- “ይህ - የታገልንለትን ጉዳይ አለማወቅ ነው”
- አዎንታዊ ሀቆች ስለሊቢያ እና ጋዳፊ (Positive facts about Libya and Gadaffi) (ፌስቡክ ላይ ብቻ)
- ኢትዮጵያ ከኢሕአዴግ በኋላ፤ ሰጥቶ የመንጠቅ ዘመነ መንግስት
- In T1me - ጊዜ ገንዘብ (ገንዘብ ጊዜ) ቢሆን ኖሮ!
- “Every nation deserves its government” - ኦቶ ቮን ቢስማርክ
- የኢሕአዴግ ‹‹ትርፍ›› እና ኪሳራ
- “ኢትዮጵያውያን፣ ኢትዮጵያ እያለች ሃገር የላቸውም”
- የዳዊት ከበደ እና የተመስገን ደሳለኝ ወጎች
- ጨርቆስና ቦሌ - ሕይወትን እኛ እንደኖርነው!
- እስኪ ስለዋጋ - ቆም ብለን እናውጋ!
- ገመና 2፣ ሰው ለሰው፣ ጀግንነትና ኢትዮጵያ
- ሰማንያ ሚሊዮን እስከምንደርስ እንታገላለን
- የፈረንጅ አምልኮ በኢትዮጵያ
- የኢትዮ ቴሌኮም ቁልቁለት
- አፍንጫ ሲመታ ዓይን አያለቅስም ወይ?
- የሐበሻ አምልኮ በኢትዮጵያ
- አማርኛ በመዝገብ ላይ
- የቫለንታይን ጉርሻ ለወንዶች፤ የአዲስ አበባ ሴቶችን እንደታዘብኳቸው - ልማላችሁ! (ፌስቡክ ላይ ብቻ)
- ኑሮ በአገርኛ÷ ጾም ይበዛበታል!
- የአሜሪካ ኮንግረስ እና ሌሎችም ከኢትዮጵያ ፓርላማ መማር የሚገባቸው!
- ሦስት ሰዓታትን በግዞት (ፌስቡክ ላይ ብቻ)
- እቴጌ ጣይቱ ብጡል እና እቴጌ አዜብ መስፍን
- እንደ እርሳቸው ያለ ፊትም አልነበረ፤ አሁንም የለ፤ ምናልባት፣ ምናልባት ወደፊት ሊኖር ይችላል!
- ሕዝቦች ግለሰብን ይጨቁናሉ!
- እውትም ‘ሰሚ ያጡ ድምፆች!’
- መራመድና ባሉበት መሽከርከር፤ ሁለት የኑሮ ፈሊጦች
- እስኪ እንጠያየቅ፤ አገራችን የት ነው? (መጠባበቂያ ካስፈለገ)
- የቴዲ አፍሮን አልበም ያልገዛሁባቸው 5 ምክንያቶች
- ደጉ ኢትዮጵያዊ፤ ከልብ ካለቀሱ እምባ እንደማይገድ ያስመሰከረ ስብስብ
- የኢትዮጵያ መንግስት መጠላቱን የሚያሳብቁ ምልክቶች
- ከአከሌን አሰሩት እስከ አከሌን አገዱት!
- አብዮት ወረት ነው!
- የጋንዲ፣ ኪንግ እና ማንዴላ መንፈስ
- ዴሞክራሲ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ወይስ የለም? (እርስዎ ምን ይላሉ?)
- የመፈረጅ ፍራቻ እና የመፈረጅ አደጋ
- ከ21 ዓመት በኋላ (ዴሞክራሲ ሲሰላ)
- “አሸባሪ” ፊልምም ይታገድ ጀመር (በነገራችን ላይ ከወራት በኋላ ድጋሚ ለአንድ ሳምንት እንዲታይ ተደርጓል)
- የአንድ ኪራይ ሰብሳቢ መንግስት ታሪክ
- እነአልበርት አይንስታይን ስለዘንድሮው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምን ይላሉ?
- Hookah እና አሜሪካ
- የተመቻቸ ጊዜ መጠበቅ?
- አምስት የኢትዮጵያ ጠላቶች
- የባለፀጋዋን አገር ዜጋ፤ አቶ ድህነትን እናስተዋውቅዎ
- እውነቱ እና ፍርሃቱ
- የእንቆቅልሹ እንቆቅልሾች
- ጫወታ ስለ ‘የኦሎምፒክ ጫወታዎች’
- ፋጡማ ኖረች አልኖረች፣ ጳጳሱ ኖሩ አልኖሩ…?
- የመለስ ሁለት መልክ
- ነውርን ማን ፈጠረው?
- በቁማቸው ከገደሉት በሞታቸው የገደሉት
- የ”ኢሕአዴግ ቀይ እስክሪብቶ”ን እኔ እንደወደድኩት… (ዞን ዘጠኝ ላይ)
- ፎንቱ ፎኒፍ ሪፈታ ጄናን ኢቲሌን ጂቢቻ ቲ ካቴ(ዞን ዘጠኝ ላይ)
- የመለስ ዜናዊ ‘ሀሁ’ በስልጣን ጎዳና (ዞን ዘጠኝ ላይ)
- እውነት እና እስር ቤት (እስካሁን ለሰው ያላሳየሁት/ልቦለድ)
በቁማቸው ከገደሉት በሞታቸው የገደሉት
Saturday, September 1st, 2012የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ሞት በብዙዎች ጉንጭ ለሁለት ወር ሲጉላላ ቆይቶ በኢትዮጵያ መንግስት ከተረጋገጠ ይኸው ሁለት ሳምንት ሊሆነው ጥቂት ቀናት ቀሩት፡፡ መንግስት ብሔራዊ የሐዘን ቀናት እስከዕለተ ቀብራቸው በማወጁ ባንዲራም ዝቅ ብሎ እየተውለበለበ ነው፣ መገናኛ ብዙሐንም ሙሉ ትኩረታቸውን በዚያው በሐዘኑ ጉዳይ ላይ እንዳደረጉ ናቸው፡፡ (በነገራችን ላይ የጡረተኛ ሚኒስትሮችን ጥቅማጥቅም የሚዘረዝረው የ2001 አዋጅ ላይ [አንቀጽ 11/1/ለ] ብሔራዊ የሐዘን ቀን አንድ ቀን እንደሆነ ይደነገጋል፡፡)
ኢትዮጵያውያን ወትሮም ቢሆን ሐዘን የማክረር ባሕላችን የተጋነነ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሠልስት ሳይቀር እየተሰረዘ የሦስቱ ቀን ሐዘን ወደሁለት ዝቅ እንዲል ተደርጓል፡፡ በነገራችን ላይ የሐዘን ቀናት ወደሦስት ቀናት ዝቅ እንዲሉ የተደረገው በአፄ ምኒልክ አዋጅ የዛሬ መቶ ዓመት ገደማ ነበር፡፡ እንግዲህ በሰሞኑ፣ ሁለት ሳምንታት የዘለቀ የሐዘን ግዜ መቶ ዓመት ያህል ወደኋላ ተመልሰናል ማለት ይቻላል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር የሞተበት አገር ሕዝብ ማዘኑ አስገራሚ ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን በውዴታም ይሁን በግዴታ ይህንን ያህል ቀናት ማዘኑ ወይም እንዲያዝን ማድረጉ ብዙ ጥያቄዎችን ያጭራል፡፡ በዚህ ጽሑፍ የምናውራውም ከዚህ ፈር ከለቀቀ የሐዘን ግዜ በስተጀርባ ስላሉ ጉዳዮች ነው፡፡
አንድ፤ ችግር ይኖር ይሆን?
አገሪቱ አሁን እየተመራች ያለችው በተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ነው ቢባልም፣ ያንን የሚያስመሰክር ነገር አላየንም፡፡ የመንግስት ልሳን የሆኑት እነ አዲስ ዘመን ሳይቀሩ ‹‹ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር›› እያሉ ነው የሚጠሯቸው፡፡ ከዚያም በላይ አሳሳቢው ግን በቶሎ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ማዕረግ በፓርላማ ምርጫ እንዲቀበሉ አለመደረጉ አጠያያቂ ነው፡፡ ምንም እንኳን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት በታወቀ በሦስተኛው ቀን ተመርጠው፣ ቃለመሓላ እንደሚፈጽሙ ቃል ተገብቶልን የነበረ ቢሆንም፣ መጀመሪያ ‹‹በአቡነ ጳውሎስ ቀብር›› በኋላም ደግሞ ‹‹የፓርላማ አባላት ሐዘናቸውን ይወጡ›› በሚሉ የማያሳምኑ ምክንያቶች ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል፡፡ ይሄ ቁርጥ ያለ ቀን ለማስቀመጥ ያለመወሰን ጉዳይ አሁንም በአቶ ኃይለማርያም ተተኪነት ላይ በግንባሩ ውስጥ (ከምስጢር ወዳድነቱ አንፃር) ስምምነቶች አለመኖራቸውን የሚያጠራጥር ነው፡፡
እንደሚታወሰው የጠቅላይ ሚኒስትሩን መታመም በስንት ውትወታ ያመነው የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ፣ ሕመሙን አቃልሎ ነበር የተናገረው፡፡ በሌላ በኩል በተለይ በማሕበራዊ አውታሮች ውስጥ የተናፈሱት ወሬዎች ደግሞ ‹‹የሚተኩት ሰው ላይ እስኪስማሙ እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞተዋል›› የሚል አንድምታ ነበራቸው፡፡ የዚያን ግዜውን ወሬ ውሸትነት የሚያረጋግጥ ነገር እስካልተገኘ የአሁኑንም በሐዘን የተሸፈነ የጊዜ ክፍተት በጥርጣሬ መመልከቱ ምንም ሊያስገርም አይገባም፡፡ ስለዚህ የመንግስት አካላት ጉዳዩ የሕዝብ መሆኑን በማወቅ ግልጽነት እና ኃላፊነት የተሞላበት አሠራር እንዲከተሉ እመክራለሁ፡፡
ሁለት፤ መተኪያ የላቸውም?
የመለስን ሞት ተከትሎ አቶ ኃይለማርያምን ጨምሮ አብዛኛው የቴሌቪዥን አስተያየት ሰጪ ‹‹እርሳቸውን መተካት አይቻልም›› ለማለት መድፈራቸው ለአገራችን ትልቅ ቅሌት ነው፡፡ ለዚያ ነው የ80 ሚሊዮኖች አገር ‹ከአንድ ሰው ሌላ ብቃት ያለው ዜጋ የላትም› የሚለውን መርዶ ስላሰማን የመለስ ሞት እርሳቸው በሕይወት እያሉ ካደረሱብን የሰብአዊ መብት ጥሰት ሁለ በላይ ገደለን ለማለት የደፈርኩት፡፡ ይሄ አባባል፣ ኢትዮጵያ ከመለስ እጅግ የተሻሉ እልፍ ሰዎች አላት ብለን የምናምነውን ዜጎች ብቻ ሳይሆን እራሳቸውን የኢሕአዴግ አባላት እና ደጋፊዎችንም ጭምር የሚሳደብ ነው፡፡
የኢሕአዴግ አባላት ‹አንድ መለስን መተኪያ የለንም› ብለው የሚሉ ከሆነ ስልጣኑን ለተቀናቃኝ ፓርቲዎች ማስረከብ ወይም በጥምረት ለመሥራት መወሰን አለባቸው፡፡ ምክንያቱም እራሳቸው እንደነገሩን እና ‹‹መለስ የጀመሩትን ልማት እናስቀጥላለን›› መፈክር ውስጥ ውስጡን እንደምንረዳው ሁሉ ነገር እርሳቸው ነበሩና ሌሎቹ በሙሉ በእርሳቸው ሽፋን የነበሩ ናቸው ማለት ነው፡፡
በሌላ በኩል ከሕዝቡ መካከል የወጡ እና በእኔ አመለካከት ኢሕአዴግን እና ፕሮፓጋንዳውን በቅጡ ያልተረዱ ሰዎችም ይህንኑ ‹መለስ መተኪያ የላቸውም› የተሰኘ ነጠላ ዜማ እያስተጋቡ የመንግስት መገናኛ ብዙሐን ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ሆነዋል፡፡ እነዚህ ዜጎች በመለስ 21 ዓመት የዘለቀ የስልጣን ዘመን ምን ዓይነት ስርዓት እንደተፈጠረ ሕያው ምስክሮች ናቸው፡፡ በየትኛውም ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ የቱንም ያህል የሚከበር ታላቅ ሰው ቢሞት ይታዘንለት እንደሆን እንጂ፣ መተኪያ የለውም ምን ይውጠናል የሚል ስጋት አይፈጠርም፡፡
የመለስን ሞት ተከትሎ የተስተዋለው ነገር የአምባገነን ስርዓት ፍሬዎችን ያሳያል፡፡ በአምባገነን ስርዓቶች ውስጥ የማኅበረሰቡ አባላት ከአምባገነኑ መሪ በቀር ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው እንዲሰማቸው ተደርገው ይቀረፃሉ፡፡ እንግዲህ ሁላችንም እንደምናውቀው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከስልጣን ይውረዱ ሲባል በፓርቲ ውስጥ ስብሰባ እዬዬ ሲባል የተከረመው ለዚያ ነው፡፡
አቶ መለስ በየትኛውም የምርጫ ክርክሮች ወቅት ከተቃዋሚዎች ጋር ፊትለፊት እንዲገጥሙ ተደርጎ አያውቅም፣ ከየትኛውም ኢትዮጵያዊ የግል ጋዜጠኛ ጋር በፖለቲካ ጉዳይ የብቻ ለብቻ የቃለ ምልልስ እንዲሰጡ ተደርጎ አያውቅም፤ ገፅታ ለመገንባት በሚያስችሉ መድረኮች ላይ ብቻ እንዲገኙ እና በጥንቃቄ የተመረጡ ንግግሮችን ብቻ እንዲያደርጉ ሲመቻችላቸው ከመክረሙ አንፃር የማኅበረሰቡ አካላት ላይ ‹ከሳቸው ሌላ የለን ይሆን?› የሚል ውዥንብር መፍጠሩ አያስገርምም፤ የሚያስገርመው ሊተኳቸው ዕጩ ሆነው የቀረቡት ግለሰብም ይህንኑ ማስተጋባታቸው ነው፡፡
ሦስት፤ ሐዘን ወይስ …?
የመለስን አስተዳደር ተመዝግበው እየተንቀሳቀሱ ባሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በየሳምንቱ በሚታተሙ ጥቂት ጋዜጦች እና በየአምስት ዓመቱ (ለይስሙላ) በሚካሄደው ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ነበር እያሉ የሚከራከሩ አሉ፡፡ በመሰረቱ እነዚህ ሰዎች የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸውን እንጂ በጠበበ ምህዳር እንዳይፈናፈኑ መታሰራቸውን፣ ጋዜጠኞች በጻፉት ነገር መከሰስና መታሰራቸውን፣ ምርጫዎች ከጊዜ ወደጊዜ በአንድ ፓርቲ የበላይነት ብቻ የሚጠናቀቁ መሆናቸውን ሳይጠቅሱ ያልፋሉ፡፡ እነዚህ ቁምነገሮች ደግሞ የስርዓቱን ዋነኛ ባሕርያት ገላጭ ናቸው፡፡
የመለስ አስተዳደር ‹‹ሕገመንግስታዊ አምባገነን (constitutional dictatorship)›› የሚባለው ዓይነት ነው፡፡ ይህ የአምባገነን ዓይነት መሪዎች ለአደጋ ጊዜ እንዲጠቀሙበት በሕገመንግስቱ ላይ የሚሰጣቸው ስልጣንን ተጠቅመው ለጭቆና ሲያውሉት የሚፈጠር ነው፡፡ የአሜሪካው የቀድሞ ፕሬዚደንት ፍራንክሊን ሩዝቬልት ‹‹ታላቁ ድብታ (Great Depression)›› በመባል በሚታወቀው የኢኮኖሚ ውድቀት እና የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አገራቸውን ከውድቀት ለማዳን ይህንን ስልጣናቸውን በመጠቀም ኮንግረሱን ሳያማክሩ እርምጃዎች ወስደዋል፡፡
አቶ መለስ ዜናዊ ግን ምንም ዓይነት ተጨባጭ ችግሮች ባልተመዘገቡበት ጊዜ ፓርላማውን ሳያማክሩ ሶማልያ ገብተዋል፣ ምርጫ 97 የተካሄደ ዕለት የሰራዊቱን ተጠሪነት ወደራሳቸው አዙረዋል፣ የፌዴራል ከተማዋ አዲስ አበባን እና የደቡብ ክልልን ምክርቤቶች በትነዋል፡፡ ከዚያም በላይ ጨቋኝና ከሕገመንግስቱጋ የሚጋጩ አዋጆችን አውጥተው የተፎካካሪዎቻቸውን አቅም አዳክመዋል፣ የተፎካካሪዎቻቸውን ደጋፊዎች ወኔና ተስፋ ቀምተዋል፡፡
እናም ይህንን ሁሉ በውጤታማነት ካከናወኑ በኋላ የሞታቸው ዜና ሲሰማ (በእርግጥ ከብዙሐኑ አንፃር ሲታዩ ብዙ ናቸው ለማለት ቢቸግርም) ለቁጥር የሚያታክቱ ሰዎች አስከሬናቸውን ለመቀበል መውጣታቸው፣ ቤተመንግስት ድረስ ለቅሶ ለመድረስ መሰለፋቸው እና አሁንም በመጪው የቀብራቸው ስርዓት ላይ መገኘታቸው የሚሰጠው ትርጉም አለ፡፡ አንደኛ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም ቢጨቁኑት ምህረት የማይቸግረው መሆኑ፣ ሁለተኛ፤ በአስተዳደራቸው የተፈጠረው የፍራቻ ድባብ አሁንም ለእርሳቸው አላዘንክም በሚል ቅጣት ያስከትልብኛል ብሎ በመፍራቱ፣ ሦስተኛ አጋጣሚውን በመጠቀም ቤተመንግስቱን ለመጎብኘት ወይም የገቢ ምንጭ ለመፍጠር (ፎቶ፣ ፖስተር እና ቲሸርት ሽያጮችን ልብ ይሏል) ነው፡፡
አራት፤ ኪሳራው በማን ነው?
መለስ መሞታቸው በመንግስት መገናኛ ብዙሐን ከታወጀ በኋላ የአገሪቱ ኢኮኖሚም በሐዘን እንዲቆዝም የተፈረደበት ይመስላል፡፡ የመንግስት መሥሪያ ቤቶች በሥራ ሰዓት ሐዘን ነው በሚል እንዲሰበሰቡ ይታዘዛሉ፣ በክልሎች የለቅሶ ስነስርዓቶች ይዘጋጁ እና ሰዎች እንዲገኙ ሲባል መሥሪያ ቤቶችም እየተዘጉ ነው፡፡ ከዚህም በላይ በቁመታቸው ከዚህ በፊት አይተናቸው የማናውቃቸው ‹ቢልቦርዶች› እየታተሙ ይለጠፋሉ (በአራዳ ሕንፃ ቁመት የተዘረጋውን ልብ ይሏል)፡፡ ሌላው ቀርቶ መስቀል አደባባይ የተተከለውን ድንኳን ለመገንባት የተንቀሳቀሰው ክሬን እና የወጣበት ወጪ አመታዊ በጀቷን በብድር ከምትሞላ አገር የሚጠበቅ አይደለም፡፡
የአሁኖቹ መሪዎች ሕዝቡ ያሳየውን ሰብአዊ ርህራሔ እና ሐዘን እንዳያቆም ይፈልጉ እንጂ ሕዝቦች ሐዘኑ ይቀጥል እስካላሉ ድረስ ለብክነቱ ተጠያቂ መሆን አይችሉም፡፡ በዚህ የኑሮ ውድነት ዜጎች ከአፋቸው እየነጠሉ የሚከፍሉት ታክስ ለፖስተር ማሳተሚያ፣ ለመፈክር እና ለፕሮፓጋንዳ ብሎም የፓርቲ አባሎችና የደጋፊዎች ሊግ አባላት እና ሌሎችንም ማመላለሻ ትራንስፖርት ፍጆታ መዋሉ የመንግስትን ማን አለብኝነት (ተጠያቂነት ማጣት) ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡
መንግስት በዚህ ግዜ የሚያስፈልገው፣ ይህችን አጋጣሚ ተጠቅሞ እውነተኛ ለውጥ ለማምጣት እና መፍጨርጨር የነበረ ቢሆንም፣ ‹እንኳን ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ› የሆነውን ኢኮኖሚያችንን በአልባሌ ብክነት ማባከኑ ጉዟችንን እያደር እንቦጭ ያሰኘዋልና ሊታሰብበት ይገባል፡፡
በመጨረሻም
በዓለማችን ለአንድ ሰው ቀብር ብዙ ሰው አደባባይ በማስወጣት ግብጾችን የሚፎካከራቸው የለም፡፡ 5 ሚሊየን የሚገመቱ ግብጻውያን እ.ኤ.አ በጥቅምት ወር 1970 ለፕሬዘንዳንታቸው ጋሜል አብደል ናስር ቀብር አደባባይ ወጥተዋል፡፡ የኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራሮችም እሁድ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ለአቶ መለስ ቀብር እንዲወጡ ይፈልጋሉ፡፡ እርግጥ ለቀብሩ ሊወጡ የሚችሉት የግብጻውያኑን ያክል ባይሆኑም ብዙ እንደሚሆኑ መገመት ከባድ አይደለም፡፡
ነገር ግን ይህ የጎሳ ልዩነት ተደረገብኝ፣ የኢኮኖሚ በደል ደረሰብኝ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት ደረሰብኝ፣ ዴሞክራሲያዊ መብቴን ተነፈግኩ ሳይል ሐዘኔታውን በክብር እየገለፀ ያለ ሕዝብ ብዙ የሚገባው መሆኑን መዘንጋት ታሪካዊ ስህተት ነው፡፡ ይህ ሕዝብ በሐዘን ሰበብ ከድንኳኑ ጀርባ ሌላ ደባ የሚሰራበት ዓይነት ሕዝብ አይደለም፡፡ ይህ ሕዝብ የስርዓት ለውጥ እንጂ የንጉሥ ለውጥ ምንም አይፈይድለትም፡፡
---
ይህ ጽሑፍ የተዘጋጀው ለፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ቢሆንም፣ ጋዜጣው እንዳይታተም በብርሃንና ሠላም ማተሚያ ቤት በመታገዱ እዚህ አስፍሬዋለሁ፡፡
ነውርን ማን ፈጠረው?
Monday, August 27th, 2012ሰሞኑን በሞት ስልጣናቸውን ስለለቀቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ያለኝን ትዝታ ‹የመለስ ሁለት መልክ› በሚል ጽፌው ነበር፡፡ ጽሑፉ ውስጥ የመለስ አስተዳደር በተለይ የተመቻቸው የብሔር አባላት እንዳሉ በስም በመጥቀሴ ‹‹ዘረኛ ነህ›› የሚል ብዙ አስተያየት ተሰንዝሮብኛል፡፡ እነሆ ይህ አስተያየትም ይህን ጽሑፍ ወልዷል፡፡ ነውርን ማን ፈጠረው? በመጀመሪያም፡-
ነፃነት እና ልቅነት
ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ለድርድር የማይቀመጡለት አጀንዳ ነው፡፡ ሆኖም ሁሉም ሰው ሐሳቤን በነፃነት የመግለፅ መብቴ በሕግ ተደንግጓል ወይም ተፈጥሮ ያጎናፀፈኝ ነው በማለት እንዳሻው አይናገርም፡፡ በተለይም ሐሳቡ የሚቀርብበት ሚዲየም ሰፊ ሲሆንና ብዙ ተደራሲዎች ሲኖሩት ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ጥንቃቄ የሚያስፈልግበት በርካታ ምክንያቶች አሉ፤ ከነዚህም ውስጥ የሕዝብን አቅጣጫ ላለማሳት፣ መረንነትን ወይም ልቅነትን ላለማስፋፋት እና አሁን ስለሆነው ሳይሆን ነገ እንዲሆን ስለምንፈልገው በመሳሳት (ሳ ላልቶ ይነበብ) ነው፡፡ ሁሉንም በሒደት ወደታች አብራራቸዋለሁ፡፡
‹የሕዝብን አቅጣጫ ላለማሳት› ያልኩት ሐሳባችንን የምንገልጽበት አገባብ (context) ተደራሲያኑ ጋር ሲደርስ ሌላ አንድምታ እንዳይኖረው የሚለውን ነው፡፡ ምናልባትም ያለፈው ጽሑፍ ውስጥ ‹ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት አዲስ አበባ ውስጥ ከተሰሩ ሕንፃዎች መካከል አብዛኛዎቹ የትግራይ ልጆች ንብረት ናቸው› ማለቴ በአንባቢው ዘንድ የትግራይ ልጆች ሁሉ በኢሕአዴግ ስርዓት ተጠቅሟል የሚል ትርጉም ከሰጠ አቅጣጫ አስቷል ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን እኔ በፃፍኩበት መንፈስ የትግራይ ተወላጆች ከኢትዮጵያ ሕዝብ አንፃር ካላቸው ድርሻ (proportion) ጋር ሲወዳደር በስልጣን እና በከተማ ሃብት ይዞታ ላይ ያላቸው ድርሻ ከፍ ያለ ነው የሚል ነው፡፡
ይሄንን እውነታ እንዳላነሳ የሚያስገድደኝ አካል ሊኖር አይችልም፤ የአገላለፁ አቀራረብ ላይ ውይይት ሊደረግ ግን እንደሚችል አልደራደርም፡፡ ይልቁንም ይህንን ጉዳይ የማይወራ ‹‹ነውር›› ነው የሚሉት (የሚያነውሩት) የስርዓቱ ፈጣሪዎች ወይም ተጠቃሚዎች ራሳቸው እንደሆኑም ይሰማኛል፡፡
‹መረንነትን ወይም ልቅነትን ላለማስፋፋት› ያልኩትን በወሲብ እና ወሲብ ነክ ጉዳዮች ብገልፀው ይበልጥ ይብራራልኛል ብዬ አስባለሁ፡፡ በባሕላችን፣ መወሻሸምም ሆነ ወሲባዊ ውስልትናዎችዝነኛ ናቸው፡፡ ነገር ግን በጥቅሉ ስለወሲብ ነክ ጉዳዮች በአደባባይ ማውራት ነውር ነው፤ ስለዚህ ስለመፍትሄዎቹ እንኳን ማውራት አልተቻለም፡፡ በመሰረቱ በኔ ሐሳብ፣ ከድርጊቱ የከፋ ወሬ ሊኖር አይችልም፡፡ ነገር ግን የድርጊቱ ፈፃሚዎች እንዲነውር አድርገው ስር አሰድደውታል ስለዚህ አይወራም፡፡ ለምን የሚል ጥያቄ ሲነሳ የሚሰጠው ዘመናዊ ተብዬ መልስ በዚህ ጉዳይ የሚወሩ ጉዳዮች ልቅነትን ወይም መረንነትን ያስከትላሉ ነው፡፡ እንዲህ አድርጉ ሌሎችም እንዲህ እያደረጉ ነው ካላሉ ወይም አደራረጉን የሚያስተዋውቅ ማስታወቂያ ካላወጡ ነውሩ ምኑ ላይ ነው፡፡ ይህ አጀንዳ ባደባባይ ላይ እንዳይውል የሚታገሉት የድርጊቱ ባለቤቶች እና ለውጡ እንዳይመጣ የሚፈልጉት ነውረኞች ራሳቸው ናቸው፡፡
ስለዚህ አስተሳሰቡ ራሱ የተሳሳተ ከሆነ (ከሕዝቦች ሕሊና ውስጥ መኖሩ እሙን ስለሆነ) በትክክለኛው ለማረም፣ አልያም ካልተሳሳተ መፍትሔ ሐሳቦችን ለማፍለቅ ሐሳብን በአግባቡ መግለፅ ሊያስፈርጅ ፈፅሞ አይገባም፡፡
እያስመሰሉ መኖር
ዛሬ የሆነውን እንዳልሆነ እያስመሰሉ መኖር ሕይወታችን ነው - ስለነገ ሲባል፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ የሕግ ስርዓቱ በፓርቲ ቁጥጥር ስር እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ገዢው ፓርቲ ያይናችንን ቀለም ካልወደደው፣ አንዱን የሽብር፣ ወይም የወንጀለኛ አንቀፅ መዝዞ፣ በራሱ ትርጓሜ ተርጉሞ አሊያም ካስፈለገ አዲስ አዋጅ አውጥቶ መቀመቅ ሊያወርደን ይችላል፣ እያደረገውም ነው፡፡ ነገር ግን ነገ ኢትዮጵያ እንዲህ ሆና ትቀጥላለች ብለን አናስብም፡፡ የሕግ የበላይነት ስለሚሰፍንባት የነገዋ ኢትዮጵያ ብለን ሕግ አክብረን እንንቀሳቀሳለን፣ አዋጅ ወይም መመሪያ ሲወጣ እንደማይቀየር እያወቅን ይህ መስተካከል አለበት እያልን እንፅፋለን፣ ምርጫዎች እንደሚጭበረበሩ እያወቅን እንመርጣለን… ሁሉም ዛሬ ስላለው ውሸት ሳይሆን ነገ እውን ትሆናለች ብለን ስለምናስባት ኢትዮጵያ ተብሎ የሚደረግ ማስመሰል ነው፡፡
በጎሳ ጉዳይም ቢሆን እንደዚያው ነው፡፡ እኔ በግሌ በቅጡ የማውቀው ብሔር እንኳን የለኝም፡፡ ነገር ግን በዚህ ስርዓት ውስጥ ግን የየትኛው ብሔር ተወላጆች ፈላጭ ቆራጮች እንደሆኑ አውቃለሁ፣ ማንም ያውቃል፡፡ ይህ ፍትሐዊ ያልሆነ የኃይል እና የሀብት ክፍፍል አገሪቱን እየጎዳት እንደሆነ እያወቅኩ እንኳን ብዙ ጊዜ ዝም ብያለሁ፣ ነገ የማስባት ኢትዮጵያ ሁሉም እኩል እንጂ ‹‹አንዳንዶች የበለጠ እኩል የሚሆኑባት›› አይደለችም፣ ስለዚህ ስለነገዋ ኢትዮጵያዬ ስል የዛሬውን ባልፈው ነገ ይረሳል በሚል ነው፡፡
ይህ ማስመሰል በጎ ቢሆንም፣ እውነቱ መነገሩ ግን ክፉ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ አልደረስኩም፡፡ መወራት አለበት፤ ካላወራነውማ የዛሬው ሲቀየር የነገ ባለተራ ደግሞ የራሱን ዓይነት ‹‹ዛሬ›› ሊደግም የማይችለው እንዴት ነው?
የመለስ ሁለት መልክ
Friday, August 24th, 2012የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሞት ‹‹ድንገተኝነት›› ብዙ ድራማዎችን አስከትሏል፡፡ መጀመሪያ ላይ ብዙዎች ተደሰቱ፣ ማታ ላይ ኢቴቪ ያነጋገራቸው ‹‹አንዳንድ ሰዎች›› የሰውየውን ታላቅ መሪነት ሲዘክሩ ያድናቂዎቻቸው ቁጥር ጨመረ፣ በጣም ማታ ላይ ወ/ሮ አዜብ ‹‹ተቀጣሁ፤ ምን አጥፍቼ ነው?›› በማለት ሙሾ ሲያወርዱ ‹‹የመለስ ታላቅነት›› የተገለፀላቸው ሰዎች ቁጥር በእጥፍ አደገ፡፡ ልብ በሉ በሞታቸው የመጀመሪያ ዕለት ብቻ ሁለት የተለያየ ገጽታ ለመያዝ የበቁት መለስ ዜናዊ ብቻ ናቸው፡፡ ነገርዬው ግን አብሯቸው የኖረ ነው፡፡
ዴሞክራሲያዊ-አምባገነን
መለስ ዴሞክራሲያዊ መንግስት የሚመስል ነገር መስርተዋል፡፡ ‹‹ዴሞክራሲ›› የሚለው ቃል በሚዲያ ተደጋግሞ እንዲነገርም ይፈልጋሉ፤ ያለ እንዲመስል፡፡ በምርጫ ማሸነፍ ያለበት የእርሳቸው ፓርቲ ብቻ እንደሆነ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የገዢው ፓርቲ ደጋፊ እንዲሆኑ፣ ጋዜጦችና ጋዜጠኞ ስኬታቸውን ብቻ እንዲያወሩ ይፈልጋሉ፡፡ ነገሩ የተገላቢጦሽ ሲሄድም የሚወስዱትን እርምጃ በ21 ዓመታት አመራራቸው አሳይተውናል፡፡
መለስ ሳያነቡት እንደማያመልጣቸው የነገሩን The Economist ከሞታቸው በኋላ በጻፈው ጽሑፍ ‹‹መለስ አምባገነንነት ተቀባይነት እንዲያገኝ ሰርተዋል›› በማለት አስታውሷቸዋል፡፡
ኢትዮ-ኤርትራዊነት
መለስ ኦነግ፣ ኦብነግንና ምንም ሪፖርት የተደረገ ጥፋት ሰርቶ የማያውቀውን ግንቦት ሰባትን በአሸባሪነት ሲፈርጁ ለስንት እልቂት ሰበብ የሆነውን ‹‹ሻዕቢያ››ን አሸባሪ ያላሉት በእርሳቸው መስፈርት ስላልሆነ ከመሰላችሁ አትሸወዱ፡፡ ቤተሰባቸው ስለሆነ ነው፡፡ መለስ ለኤርትራ እና ለኢሳይያስ ጥልቅ ፍቅር ነበራቸው፡፡ የ‹‹ትሮይ ፈረስ›› የሚለውን መጽሐፍ ካነበባችሁ ‹‹ኅወሓት››ን ማን ጠፍጥፎ እንደሰራው ይገባችኋል፡፡ በእናታቸው ኤርትራዊ የሆኑት መለስ ኅወሓት ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረ በኋላ ለኢሳይያስ ኤርትራን የመገንጠል እና የአሰብ ወደብን የመቀማት ሕልም ተባባሪ ሆነዋል፡፡ በትግል ወቅት የሚሰነዘሩ ሐሳቦችን ‹‹የኤርትራ ሕዝብ ትግል ባፍጢሙ አይደፋም›› የሚል መጽሐፍ በመጻፍ በጠብመንጃም በጽሑፍም ታግለዋል፡፡
አገር ወዳድ - የአገር ጠላት
መለስ - በተለይ በስልጣናቸው መጨረሻ ሰሞን አገር ወዳድ ለመምሰል ይጥሩ ነበር፡፡ በተቃራኒው ታሪካችንን በመቶ ዓመት ሲቀጩት፣ ባንዲራችንን ከተራ ጨርቅ በላይ ፋይዳ እንደሌለው ሲነግሩን ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ‹‹አገር ማለት ሕዝቡ ነው›› ባሉበት አፋቸው ‹ለልማቱ (ለሕንፃና መንገዱ) ሲባል ሕዝቡ ይጎሳቆል› ብለውበታል፡፡ ልዩነቱ የሚጎሳቆለው ሕዝብ እና የሚጣሰው ሰብአዊነት የእርሳቸውን እና የቤተሰባቸውን በር አያንኳኳም፡፡ ኤርትራን ያህል ሃገር እና አሰብን የሚያህል ወደብ አሳልፈው ሰጥተው፣ መልሰው ደግሞ ባድሜን ለምታክል ቁራጭ መሬት 120 ሺ ሰው ይገብሩብናል፡፡
ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና ድህነት
የመለስ ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ዓመታት ‹‹በሁለት ዲጂት›› አድጋለች፡፡ ሕዝቡ ግን ከመቼውም የበለጠ ድህነት ውስጥ ገብቷል፡፡ የገንዘብ ግዥበቱ ዕድገት በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ አይታወቅም፡፡ እርግጥ ነው በርካታ መንገዶች ተሰርተዋል፣ ብዙ ሕንፃዎች ቆመዋል ነገር ግን ኢሕአዴግ በገባ በ10 ዓመቱ በቀን ሦስቴ አበላዋለሁ ብለው ቃል ገብተውለት የነበረውን ሕዝብ በ20 ዓመታቸውም አላበሉትም፡፡
እውነቱን እየተነጋገርን ስለሆነ የተሰሩት ሕንፃዎች የማን ናቸው የሚለውን ጥያቄም መልሰን እንለፍ፡፡ በፊት በታታሪ ሰራተኝነታቸው የኢዲስ አበባን ግማሽ ሃብት ተቆጣጥረው የነበሩት ነጋዴዎችና ባለሃብቶች ጉራጌዎች ነበሩ፡፡ ዛሬስ? ኢሕአዴግ ከገባ ወዲህ የተሰሩትን ሕንፃዎች ብትቆጥሩ ከግማሽ በላይ ለሚሆኑት ባለቤት የትግራይ ልጆች ናቸው፡፡ በ20 ዓመት ይህን ሁሉ ሀብት ያፈሩት በምን ጥበብ ነው?
ንግግር አዋቂው ተሳዳቢ
ንግግር አዋቂ (አንደበተ ርቱዕ) ሰዎች አይሳደቡም፤ ምክንያቱም በንግግራቸው ማሳመን ይችላሉ፡፡ ስድብ በንግግር ማሳመን ያልቻለ ሰው ውጤት ነው፡፡ መለስ ዜናዊ ንግግር ሆነ እንዲሁም በጥቅሉ አዋቂነታቸው በሰፊው ይወራላቸዋል፡፡ ይህንን ግን በቅጡ ላጤነው የቱ’ጋ እንደሆነ ለማወቅ ይቸግራል፡፡ አንደበተ ርቱዕነት በንግግር ለዛ ማሳመን እንጂ ቃላትን በመሰንጠቅ፣ አዳዲስ የስያሜ ባጅ በመለጠፍና በማደናገር የሚፈጠር አይደለም፡፡ ስለፖሊሲያቸው ሲጠየቁ ‹ፊዚካል ፖሊሲ› የሚባል የለም ‹ፊስካል ፖሊሲ› ነው የሚባለው የሚል ዋና መስመሩን የሳተ ‹‹የፉጨት›› ሌክቸር መስጠት ያምራቸዋል፡፡ ከአንደበተ ርቱዕ ሰዎች በማይጠበቅ መልኩ ‹‹የገማ፣ የበከተ፣ የበሰበሰ፣ ደደብ…›› የሚሉ ስድቦችን በሕዝብ ፊት ደጋግመው ተሳድበዋል፡፡
አሁን መለስ ሞተዋል፡፡ ቀብራቸው በእልፍ ሺህ (እውነት እየተነጋገርን አይደል፤ ከነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በትግራይ ተወላጆች፣ ወደሩብ በሚጠጉ አባሎቻቸውና የስርዓቱ ተጠቃሚዎች እና ወደሩብ በሚጠጉ ግራ የገባቸው ሰዎች) አጀባ፣ በኢቴቪ እና ሬዲዮዎች ፕሮፓጋንዳ ይካሄዳል፡፡ የፕሮፓጋንዳው መዓት ‹‹ሳያዩ የሚያምኑትን›› ብዙሐን ኢትዮጵያውያንን ለኢሕአዴግ እንደሚመለምል አልጠራጠርም፡፡ ቢሆንም ግን መለስ ሲሞቱ (የመሪ ሳይሆን የስርዓት ለውጥ ነው በማለት) ንቄው የነበረውን የሕልፈታቸውን ብስራት ዛሬ አግኝቸዋለሁ፡፡
ፋጡማ ኖረች አልኖረች፣ ጳጳሱ ኖሩ አልኖሩ…?
Monday, August 20th, 2012አቡነ ጳውሎስን እጅግ በጣም አወዛጋቢ ከሆኑ ኢትዮጵያውያን ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ተርታ እመድባቸዋለሁ፡፡ ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት ለክብራቸው የቆመላቸው ሐውልት ሲገነባ አገር ምድሩ ሌላ አጀንዳ አጥቶ ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ‹ሰው በቁሙ ለምን ሐውልት ያሰራል?› የተሰኘ ጽሑፍ በአንባቢ ቁጥር ተወዳዳሪ የተገኘለት ባለፈው ሳምንት የታወጀው የሞታቸው ዜና ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ የተቀረጸበት የስነ ምግባር ወግ ሰው ከሞተ በኋላ ማክበር ላይ ስለተመሰረተ፣ ሙት ወቃሽነት ከነውሮች ሁሉ የከፋ ነውር ነው፡፡ ስለዚህ ሰሞኑን የማይወዷቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ ምዕመናን ሳይቀሩ ‹‹ነፍስ ይማር›› መባባልን እንደትልቅ ቁምነገር፣ በተቃራኒው ደግሞ ‹‹ሞታቸውን እንደመልካም አጋጣሚ›› የሚቆጥሩትን እንደ አጥፊ በመታዘብ ላይ ናቸው፡፡ እኔም በበኩሌ ስለአቡኑ አወዛጋቢ ዐበይት የታሪክ ትውስታዎች ከአወራሁ በኋላ፣ ሃይማኖተኛ ባልሆንም ስለ‹በሰላም ይረፉ ማለት ማንን ገደለ?› ለሚለው ጥያቄ የራሴን እምቢታ ለመስጠት በዚህ ጽሑፍ መጥቻለሁ፡፡
ማዕረጋቸው አንድ አንቀጽ የሚደርስላቸው አቡነ ጳውሎስ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት ውጪ ላሉት ሁሉ የተመቹ ነበሩ፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ አማኞች ዘንድ ግን መልካም ስም የላቸውም፡፡ የስማቸው መበላሸት የሚጀምረው ደግሞ ወደ መንበረ ጵጵስናው የመጡበት መንገድ ላይ ይጀምራል፡፡
ጳጳሱ እንደአብዛኛዎቹ የፖለቲካ መሪዎቻችን ሁሉ፣ ከትግራይ ክልል ያውም ከአድዋ ነው የፈለቁት፡፡ ኢሕአዴግ አዲስ አበባን በተቆጣጠረ በዓመቱ፣ አቡነ መርቆርዮስ ተሰድደው እርሳቸው ጳጳስ ለመሆን በቁ፡፡ ከዚያ በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ከየትኛውም ቤተ ሃይማኖት የበለጠ መስዋእትነት ስትከፍል ነበር፡፡ Haustein & Østebø የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ቁጥር በኢትዮጵያ ከ54 በመቶ ወደ 43.5 በመቶ የወረደው በኢሕአዴግ ወይም በአቡነ ጳውሎስ ዘመን እንደሆነ ይነግሩናል፡፡
አቡነ ጳውሎስ በ1993 ተነስቶ በነበረው የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች አመጽ ወቅት የፌዴራል ፖሊሶችን ቆመጥ ሸሽተው ወደ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በመግባት ለመሸሸግ የሞከሩ ምዕመኖቻቸውን እንደወንጀለኛ አሳልፈው በመስጠት አሳፍረዋቸዋል፡፡ በመሰረቱ፣ በአንደበተ ርቱዕነታቸው እና በሰበካ ችሎታቸው የማይታሙት አቡን ምዕመኖቹ ወንጀለኞች ቢሆኑ እንኳን በሚሰብኩት ትምህርት መሰረት ለንስሐ ማብቃት እንጂ ለሌላ ‹ደብዳቢ› ወንጀለኛ አሳልፈው መስጠት አልነበረባቸውም፡፡ እንዲሰብኩ በተሾሙበት እምነት ውስጥ በቅጽበታዊ ንስሐ ብቻ ‹‹እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከኔ ጋር በገነት ትሆናለህ›› (ሉቃስ 23፡43) እንደሚባል ዘንግተውታል የሚል እምነት የለኝም - የሚበልጥባቸውን መርጠው እንጂ፡፡
በአቡነ ጳውሎስ አስተዳደር ቤተክህነት ከመቼውም ጊዜ በላይ በሙስና እንደተርመጠመጠች እሙን ነው፡፡ አቡኑም ቢሆኑ በፎር ዊል ድራይቮቻቸው፣ በኩርፍቱ አባልነታቸው እና ከእርሳቸው በፊት ተደርጎ በማይታወቅ ሁኔታ በጠብደል ቦዲጋርዶች ጥበቃ አዝማሚያ የሚነግሩን የሃብታቸውን ብዛትም ጭምር ነው፡፡ ‹‹ቤተ መንግስታቸውም›› ቢሆን የቢሊዬነሮችን ቪላ ይፎካከራል፡፡ ይሄ ብዙም አይከፋም፣ ነገር ግን (እንደ ‹እጅጋየሁ› ባሉ) አገልጋዮቻቸው ስም እራሳቸውን (ልክ እንደጠቅላይ ሚኒስትሩ) ወደተመላኪ ፍጡርነት በመቀየር ሒደት ላይ ሳሉ ነው ሞት የቀደማቸው፡፡
በየቤተ ክርስቲያናቱ ደጃፍ ለመሳለም ማማተብ ስትጀምሩ የርሳቸውን ትልልቅ ፎቶዎች ፊለፊት ማየታችሁ አይቀርም፣ የዛሬ ሁለት ዓመትም በዓለ ሲመታቸወን ለማክበር ቦሌ መድሀኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፊትለፊት የቆመላቸው ሐውልት በ‹‹ዴሞክራሲያዊው›› ሲኖዶስ በ20 ቀን ውስጥ እንዲፈርስ ተፈርዶበት በአስተዳደራቸው ለገምተኝነት እንደቆመ ቀርቷል፡፡ ከጥቂት ቀናት በፊት በሸራተን አዲስ ሆቴል ያከበሩትም የ20ኛ ዓመት በዓለ ሲመታቸው እንዲሁ አወዛጋቢ ነበር፡፡ ጣሪያቸው የሚያፈስ ቤተመቅደሶች በሞሉባት አገር የጳጳሱን ‹‹ሹመት ያዳብር›› ለመብላት ያንን ሁሉ ገንዘብ ማባከን ከ‹‹ሃይማኖተኛ›› ቀርቶ ከተራ ነጋዴም አይጠበቅም፡፡
የሆነ ሆኖ፣ በድንገት ዜና ሕልፈታቸው ባለፈው ሳምንት ተሰማ፡፡ እሱን ተከትሎ የተዘባረቀ ስሜት በተለይ በማሕበራዊ አውታሮች ዙሪያ ይደመጥ ጀመር፡፡ ብዙዎች ደስታቸውን መደበቅ አልቻሉም፣ ይህም ሃጢያት ሆነ/እንደ ሃጢያት ተቆጠረ፡፡ በመሰረቱ በአቡኑ ሞት መደሰትን እንደስህተት የቆጠሩት ወገኖች መሳሳታቸውን የሚናገሩ ምክንያቶች እንዳሉ ከበርካታ ውይይቶች ውስጥ ነቅሼ አውጥቻለሁ፡፡ እነርሱም፡-
- በቤተ ክርስቲያን እምነት ሁሉም እርምጃ (ሞትን ጨምሮ)፣ የሚወሰደው በእግዚአብሔር ነውና በእግዚአብሔር ውሳኔ መደሰት ነውር የለውም፤ አለዚያ ደግሞ ፀጉሬን ካልነጨሁ (ፀጉርክን ካልነጨህ) ብሎ ማለት የእዜአብሔርን ውሳኔ ከመገዳደር የማይተናነስ እንደሆነ በአማኞች ስለሚቆጠር፣
- ቀናኢ-ቤተክርስቲያን የሆኑ ሰዎች በጳጳሱ ፈቃድ በቤተክርስቲያኒቱ እና ምዕመኑ ላይ እየደረሰ ያለው በደል ማብቂያ ነው ብለው አስበዋል እና የደስታቸው ምንጭ የጳጳሱ ሞት ሳይሆን የመጻኢው ዕድል ተስፋ ስለሆነ፣
- ሐዘንም ሆነ ደስታ ልቦና ፈቅዶ የሚከሰቱ እንጂ ለሰው ይምሰል የሚገለፁ ባለመሆናቸው፤ ያዘነው ‹‹አዘንኩ›› የተደሰተውም ‹‹ተደሰትኩ›› የማለት የማይገሰሰ ሰብአዊ መብት ስለሆነ እና… ወዘተ ናቸው፡፡
ቀጣዩ ጉዳይ
ለኔ አሳሳቢው አጀንዳ፣ ቀጣዩ ጳጳስ ማን ይሆኑ ይሆን የሚለው ነው፡፡ በሕገ ቤተክርስቲያን አንቀጽ 13 መሰረት (ይለናል ዕንቁ መጽሔት) ጳጳሳት የሚመረጡት በየቤተክርስቲያናቱ ቀሳውስት እና ሰንበት ተማሪዎች በየቤተክርስትያናቱ እና ገዳማቱ (በቀበሌ ይሁን ካልተባለ) ነው፡፡ ስለሆነም በቅርቡ ምርጫ እንደሚካሄድ እና አንድ ጳጳስ አቡኑን እንደሚተኳቸው ይታመናል፡፡ የጳጳሱ ሞት እና የምትካቸው ጉዳይ ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮችን ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ የሚመለከት ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ ነው እኔም እዚህ መጻፌ!
ጫወታ ስለ ‘የኦሎምፒክ ጫወታዎች’
Friday, August 10th, 2012እንደመታደል ሆኖ ከ200 በላይ አገሮች ጋር ተፎካክረን እስከ 20ኛ የሚደርስ ደረጃ የምናገኝበት ብቸኛው መድረክ የኦሎምፒክ ጫወታዎች ነው፡፡ (ማን ነበር ‹የምንወዳደረውም ሆነ የምናሸነፈው በአትሌቲክስ ብቻ፣ ከአትሌቲክስም በሩጫ ብቻ፣ ከሩጫም በረዥም ርቀት ብቻ› ብሎ ከዓመታት በፊት ‹ጭብጨባ አታብዙ› ያለን የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ? እርግጥ ነው፣ ዘንድሮስ አልተሳካም እንጂ አጭር ርቀትም፣ ዋናም ሞካክረናል በሉልኝ!!!)
ጫወታ አንድ፤ የኦሎምፒክ ፉክክር ፖለቲካ
የዓለምአቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴው በኦሎምፒክ ቻርተሩ ምዕራፍ አንድ ክፍል ስድስት ላይ ‹‹የኦሎምፒክ ጫወታ ፉክክሮች በግለሰቦች ወይም በቡድኖች ብቻ እንጂ በአገራት መካከል አይደለም…›› ይላል፤ ድንቄም! እና ታዲያ ለምንድን ነው ግለሰቦቹ በአገራት ተከፋፍለው የሚጫወቱት፣ ለምንድን ነው ሲያሸነፉ የአገራቸው ብሔራዊ መዝሙር የሚዘመረው፣ ለምንድን አገራት ባገኙት የወርቅ ቁጥር ደረጃ የሚሰጣቸው? እኛ እንደሆንን የምንደሰተውም ሆነ የምናዝነው ነገሩን ያገር ጉዳይ አርገነው ነው፡፡
ጫወታ ሁለት፤ ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ
ኢትዮጵያ የለንደኑን ጨምሮ በ13 የበጋ ኦሎምፒክ ጫወታዎች ላይ ተሳታፊ ሆናለች፡፡ ከነዚህ ውስጥ ከሦስቱ በስተቀር በሁሉም ሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ ገብታለች፡፡ ሜዳልያ ሰንጠረዥ ውስጥ ከገባችባቸው 10 ጫወታዎች ውስጥ አንድም ወርቅ ያላገኘችው በሙኒክ ኦሎምፒክ ነው፡፡
በኦሎምፒክ መድረክ የለንደን ኦሎምፒክን ሳይጨምር 38 ሜዳሊያዎችን ስታገኝ፣ ሲተነተኑ 18 ወርቅ፣ 6 ብር እና 14 ነሐሶች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ (እና በአፍሪካ) የኦሎምፒክ ታሪክ የመጀመሪያውን ወርቅ ያስገኘው አበበ ቢቂላ ሲሆን፣ በሴቶች ደግሞ ደራርቱ ቱሉ ናት፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ ሜዳልያዎች (8) ያገኘችው በሲድኒ ኦሎምፒክ ሲሆን፣ በአቴንስ እና ቤጂንግ ኦሎምፒኮች በያንዳንዳቸው ሰባት አግኝታለች፡፡
የለንደን ኦሎምፒክን ሳይጨምር፣ በተገኙት ሜዳሊያዎች ድምር ኢትዮጵያ ከዓለም የኦሎምፒክ አገራት አንፃር 40ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡
![]() |
| የለንደን ኦሎምፒክ ፓርክ |
ጫወታ ሦስት፤ ኢትዮጵያዊ ኦሎምፒክ በጾታ
ከለንደን ኦሎምፒክ በፊት በተደረጉ ጫወታዎች …. ሜዳሊያ በወንዶች እና … ሜዳሊያ በሴቶች ለኢትዮጵያ ገቢ ተደርገዋል፡፡ ከባርሴሎና ኦሎምፒክ ወዲህ እስከ ቤጂንግ በሴቶች 14 ሜዳሊያ በወንዶች ደግሞ 13 ሜዳሊያዎች ተገኝተዋል፡፡ በዘንድሮው የለንደን ኦሎምፒክም እስካሁን በተገኙት አራት ሜዳሊያዎች ውስጥ ከአንዱ ነሐስ በስተቀር ሦስቱ በሴቶች የተገኙ ናቸው፡፡
ጫወታ አራት፤ የኦሎምፒክ ድል ኢኮኖሚ
በኦሎምፒክ ድል ብዙ ገንዘብ አይገኝም፤ ክብር እና ስም እንጂ፡፡ በኦሎምፒክ ድል ግን የአገራት ኢኮኖሚ ይገለጣል፡፡ ኢኮኖሚያቸው ትልልቅ የሆኑ አገራት ብዙ ሜዳሊያዎችን የማግኘት ዕድላቸው የሰፋ ነው፡፡ ለምሳሌ የተባበሩት የአሜሪካ አገራት (United States of America) 3ተኛ ከወጣችበት የሞንትሪያል ኦሎምፒክ በቀር በሁሉም አንደኛ ወይም ሁለተኛ ስትወጣ ኖራለች፡፡ በምጣኔ ሐብት ደረጃ መጤ የምትባለው ቻይና ደግሞ ከአትላንታ ኦሎምፒክ ጀምሮ በአገሯ እስካሰናዳችው ያለፈው የቤጂንግ ኦሎምፒክ ድረስ ከአራተኛ ጀምራ፣ ሦስተኛ፣ ሁለተኛ፣ እያለች አንደኛ ለመሆን በቅታለች - ልክ እንደGDPዋ ዕድገት ማለት ነው!
ጫወታ አምስት፤ ኢትዮጵያ በለንደን ኦሎምፒክ
ኢትዮጵያ ለለንደን የበጋ ኦሎምፒክ የላከቻቸው ስፖርተኞች ቁጥር 34 ነው፡፡ ሁለቱ ዋናተኞች ሲሆኑ ቀሪዎቹ አትሌቶች ናቸው፡፡ እስካሁን በኦሎምፒክ ታሪካችን በ10,000 ሜትር ሴቶች አራት የወርቅ ሜዳሊያ ስናገኝ አራቱም አንድ ቤተሰብ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ሁለቱን ጥሩነሽ ዲባባ በቤጂንግ እና ለንደን ኦሎምፒክ ስትወስድ፣ አክስቷ ደራርቱ ቱሉ ደግሞ የባርሴሎናውን እና የሲድኒውን ወስዳለች፡፡ ሜዳሊያዎችን አንድ ቤተሰብ ውስጥ በማስቀረት ታሪኩ በቀለም የራሱ ድርሻ አለው፤ የ10,000 ሜትር ነሐስ አጥልቋል - ለንደን ላይ፡፡
የእንቆቅልሹ እንቆቅልሾች
Sunday, July 22nd, 2012ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ ሲሞቱ፣ መኳንንቱ ለሕዝቡ የ‹እምዬ›ን ሞት ለማርዳት ፈርተው ዓመታት ቆይተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊስ ዳግማዊው ‹ዳግማዊ-ምኒልክ› ለመሆን በቅተው ይሆን እንዴ? ይህቺን ጽሁፍ እስካሰናዳሁባት ሰዓት ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልካም ጤንነት ላይ ናቸው፣ በጠና ታመዋል እና ሞተዋል የሚሉ ‹‹ታማኝ ምንጮች›› ከየአቅጣጫው እየፈለቁ ነው፡፡ እውነታውን ምሎ የሚናገር ሕዝብ ወይም የሕዝብ አባል ግን የለንም፤ ጉዳዩ በእንቆቅልሽ የተሞላ ነው፡፡
አሁን፣ አሁን ገዢው ፓርቲ የራሱ ዋሾነት ሳያንሰው የአማራጭ መረጃ ምንጮችን ታማኝነት እስከወዲያኛው ለማድረቅ ሆነ ብሎ የሚጫወተው ‹ጌም› ያለ እየመሰለኝ መጥቷል፡፡ በ‹‹ታማኝ ምንጮች›› በኩል የሐሰት መረጃዎችን ማፍሰስ፣ በጣም እስኪናፈሱ መጠበቅ፣ ወሬዎቹን በከፊል የሚያረጋግጡ መግለጫዎችን መስጠት፣ መጨረሻ ላይ ግን ወሬዎቹ በሙሉ ‹‹ከአሉባልታ›› ያልበለጡ መሆናቸውን አረጋግጦ የዜና ምንጮቹን ተአማኒነት መግደል፡፡ ለኔ፣ መለስ ቢያንስ በቅርቡ ወደቢሯቸው መመለስ ከቻሉ ተናፋሽ ወሬዎችን ለማመን ይሄ የመጨረሻዬ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ከዚያ በፊት የዚህ እንቆቅልሽ እነቆቅልሾች ስለሆኑት ነገሮች ትንሽ ልበል፡፡
እንቆቅልሽ አንድ፡- የግልጽነት ነገር
የገዢው ፓርቲ አባላት እና የመንግስት ባለስልጣናት ከረፈደ በኋላም ቢሆን መለስ መታመማቸውን አምነዋል፡፡ በርግጥ እነሱ በማሕበራዊ አውታሮች እንደሚወራው ሕመማቸውን አላካበዱትም፡፡ ሆኖም መታመማቸውን ለማመን ሁለት ሳምንታት ስለፈጀባቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋፊዎችም ሆኑ ነቃፊዎች እውነታውን ለማወቅ ሲወዘወዙ ከርመዋል፡፡ መንግስት አትናዱት እያለ በሚመክረን ሕገመንግስቱ አንቀጽ 12 ላይ እንዳስቀመጠው ‹‹የመንግስት ጉዳዮች ለሕዝብ ግልጽ መሆን አለባቸው›› ይላል፡፡ ሆኖም ማንም ከቁብ የቆጠረው ያለ አይመስልም፤ አንደኛ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምን የሥራ ገበታቸው ላይ እንዳልተገኙ አልተነገረንም ነበር፣ ሁለተኛ ማን እንደተካቸው ሊነገረን አልተፈቀደም፤ ምክንያቱ እንቆቅልሽ ነው!
እንቆቅልሽ ሁለት፡- የአመኔታ ነገር
የመንግስት ባለስልጣናት ስለመለስ የጤና ሁኔታ መግለጫ ከሰጡ በኋላም ቢሆን የመለስ የጤና ችግር በጣም ከባድ እንደሆነና እንዲያውም ሳይሞቱ እንዳልቀረ መወራቱ ቀጥሏል፡፡ መንግስት ይፋዊ መግለጫ አለመስጠቱ ኅብረተሰቡን ሲያምሰው መክረሙ አንሶ መግለጫ መስጠቱም መፍትሄ ያወረደ አይመስልም፡፡ የመንግስት መግለጫ ፋይዳ የሌለው በምን ምክንያት ነው ብንል ምናልባት ካስለመደን ውሸት የመነጨ ነው ሊባል ይችላል - ታዲያ ለምን ነበር የመንግስት ሰዎች መግለጫውን እንዲነግሩን የፈለግነው፣ የምንፈልገውን ለመስማት? እንቆቅልሽ ነው!
እንቆቅልሽ ሦስት፡- የስርዓት ነገር
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሞቱ ማነው ስልጣናቸውን የሚወስደው ለሚለው ጥያቄ የመጀመሪያው መልስ የሚሆነው፣ ‹‹ምክትል ጠ/ሚኒስትሩ ወክለዋቸው እየሰሩ ይቆዩና ፓርላማው በምትካቸው ይመርጣል›› የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ማንም ይሄ መልስ የሚዋጥለት ሰው (ቢያንስ ከተቃዋሚው እና ‹መሃል ሰፋሪ› ነን ከሚሉት ወገን) ማግኘት አይቻልም፡፡ ኢሕአዴግ ሕገመንግስቱን ካፀደቀ ከ17 ዓመታት በኋላም እንኳን ቢሆን ዘርግቼዋለሁ በሚለው ስርዓት ላይ እምነት ያለው ሕዝብ አላፈራም ማለት ነው፡፡ ታዲያ ምን ሲሰራ ከረመ? እንቆቅልሽ ነው!
እንቆቅልሽ አራት፡- የአብዮቱ ነገር
በመንግስት እርምጃዎች የመንግስት ሠራተኛው፣ ነጋዴው፣ ባለንብረቱ፣ ሙስሊሙ፣ ክርስቲያኑ፣…ሥራ ያጣው ወይም ደሞዙ የማያኖረው ከተሜ፣ ማዳበሪያ መግዣ ያጣው ወይም የማዳበሪያ እዳውን መክፈያ የቸገረው ገበሬ፣… ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በሆነ መንገድ ተቀይሟል፡፡ ይሄ ቅያሜው ደግሞ ከየአቅጣጫው ቀስበቀስ እንደፍም እየጋለ ነበር፣ ይሄ ግለት አንድ ቀን ሲፈነዳ ‹አብዮት› ይባላል፡፡ መለስ ከሞቱ (ወይም ቢሞቱ) የተጀመረው አብዮት ይቀለበሳል ማለት ነው? የአንድ ሰው መሞት የችግሮችን ሁሉ ቁልፍ ይፈታል ማለት ነው? የተበሳጩ ዜጎች አብዮቱን ለመቆስቆስ የሚጠቀሙበትን ወናፍ አስቀምጠው አገር አማን ነው ይሉ ይሆን? እንቆቅልሽ ነው!
እንቆቅልሽ አምስት፡- የኢሕአዴግ ነገር
ላለፉት 21 ዓመታት በመለስ አመራር ስር ያለው ኅወሓት/ኢሕአዴግ ሲያጠፋ በመለስ ሲሳበብ ቆይቷል፡፡ ኅወሓት/ኢሕአዴግን ለቅቀው የወጡት ቡድኖች እና ግለሰቦች ሳይቀሩ የሚወቅሱት መለስን ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ መለስ ባይኖሩበት ኖሮ ወደኢሕአዴግ ተመልሰው መግባት የሚፈልጉ እስኪመስለን ድረስ በጥርጣሬ እየተመለከትናቸው ነው፡፡ እሺ ‹መለስ› ኢሕአዴግን እንዲህ ጨቁነውትና በራሳቸው መስመር እየጎተቱ አስቸግረውት ከነበር፣ ለኢ-ዴሞክራሲያዊነት ብቻቸውን ዳርገውት ከነበር፣ የኢሕአዴግ ስህተቶች የግለሰቡ ችግሮች እንጂ የፓርቲው ካልነበር፣ አሁን ከሞቱ (ወይም ቢሞቱ) ኢሕአዴግ ነፃ ይወጣ ይሆን? እንቆቅልሽ ነው!
እውነቱ እና ፍርሃቱ
Tuesday, July 10th, 2012
የፍራቻ ፖለቲካ እና የፖለቲካ ፍራቻ - ጥንድ በኢትዮጵያ መሪዎችና ሕዝቦች መሀል የተጋረጡ የጦር መሳሪያዎች ናቸው፡፡ ሕዝቡ ካልፈራ ፖለቲከኞቹ የፍራቻ ፖለቲካ ይጫወታሉ፣ ፖለቲከኞቹ የፍራቻ ፖለቲካ ካልተጫወቱ ሕዝቡ ፖለቲካን ይፈራል፡፡ የሁለቱም ውጤት አንድ ነው፤ ውጤቱም ሕዝቡ መሪዎቹን የሚያስከፋ ነገር መናገርም ሆነ መተግበር ይፈራል፡፡የፍራቻ ፖለቲካ፤ በገዢው እና ተቃዋሚዎቹ
ጥንት፣ ወትሮም ንጉሥ የማይከሰስ በመሆኑ መንግስታት ሕዝቦቻቸውን ማስፈራራታቸው የደንብ ያህል ነበር፡፡ ‹‹የተማረ ይምራን›› መባል ከተጀመረበት እና ደርግ የንጉሡን መንበር ከተረከበበት ጊዜ ወዲህም ግን ‹‹ደንቡ›› አልቆመም፡፡ ደርግ ‹‹አብዮቱን›› ሊቀለብሱ የሚንቀሳቀሱትን በሙሉ እንደማይምራቸው በሕዝብ ፊት ምሎ ዘመተባቸው፡፡ አብዮቱን ከሚቀለብሱት እንዳንዱ ላለመሆን የፈራ በሙሉ የኢሠፓ አባል ሆኖ በወንድሙ ላይ ዘመተ፡፡ ቀሪው ‹‹መሀል መስፈር›› የፈለገውም፣ ከፍራቻው’ጋ እንደተሟገተ 17 ዓመታት ኖረ፡፡
ኢሕአዴግ ቀርቶ የፍራቻ ፖለቲካ የቀረ ከመሰለ በኋላ ግን መልኩን ቀይሮ መጣ፡፡ አብዮቱን መቀልበስ፣ ሕገመንግስቱን መቀልበስ በሚል ተተካ፡፡ መንግስት የተቃወመውን ሁሉ በሆነ ስም በመፈረጅ ስለሚወነጅል፣ ላለመፈረጅ የሚሰጋው ሁሉ ወደወጣበት ምሽግ ተመልሶ ገባ፡፡ ‹‹ፖለቲካ እና ኮረንቲ›› የሚለው አባባል የተፈጠረው ያኔ ነው፡፡
የፍራቻ ፖለቲካን፣ ኢሕአዴግ በሌላም አካሔድ ይጫወትበታል፡፡ እንደገዢው ፓርቲ ዲስኩር ከሆነ፣ ኢሕአዴግ ከወረደ ወይም ተቃዋሚዎች ወደስልጣን ከወጡ የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ/ነፃነት ተዳፍኖ ይቀራል፣ የሃይማኖቶች እኩልነት አደጋ ላይ ይወድቃል፣ ልማቱ ይደናቀፋል… ወዘተ፣ ወዘተ፡፡
የዚህኑ ግልባጭ ተቃዋሚዎችም ይጠቀሙበታል፡፡ ኢሕአዴግ ካልወረደ ብሔር ብሔረሰቦች እርስ በእርሳቸው ይባላሉ፣ የኢትዮጵያ አንድነት እመቃብር ይወርዳል፣ ሃይማኖተኞች ጽንፈኛ ይሆናሉ፣ ኢኮኖሚው ተጣምሞ ይቀራል… ወዘተ፣ ወዘተ፡፡ ሙግቶቹ እውነትነት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን የፖለቲካዊ ጫወታም ሆነ የምጣኔ ሃብታዊ ትንታኔ እና ትንቢት ለማይገባው ምስኪን ግን ያኛው ከመጣ፣ ይሄኛው ከወረደ ወይም ያኛው ካልመጣ ይሄኛው ከሰነበተ ነገሩ ሁሉ ምስቅልቅሉ ወጥቶ፣ ሕዝቦች ሁሉ አደጋ ላይ ወድቀው…በሚል ፍርሃት ሙሉ ራዕይ ታቅፎ ይቀራል፡፡ ለሁሉም እንደመፍትሄ የሚቆጥረው ደግሞ ሽሽት /ስደትን/ ነው፡፡
የፖለቲካ ፍራቻ፤ በተመልካቹ ሕዝብ
የ2011 Legatum Prosperity Index፤ ኢትዮጵያን ከ110 አገሮች ጋር አወዳድሮ በብልፅግናዋ 108ኛ ባስቀመጠበት ሪፖርቱ Safety & Security ንዑስ ዘርፍም 106ተኛ ይበቃሻል ለማለት ያበቃውን ምክንያት ሲዘረዝር፣ “The Ethiopian government has been known to engage in political violence and, globally, Ethiopia is the country where expression of political views is perceived by the population to be most restricted. This may be contributing to the rate of flight of professionals, intellectuals, and political dissidents, which is among the 20 highest rates in the world.” (‹‹የኢትዮጵያ መንግስት በፖለቲካዊ አመጾች ላይ እጁን በማስገባት ይታወቃል፣ በዓለምአቀፍ ደረጃም ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ አመለካከትን ማንፀባረቅ በጣም የተገደበባት አገር ተደርጋ በዜጎቿ ትታሰባለች፤ ይህ ምናልባትም፣ ከዓለማችን ችግሩ የከፋባቸው 20 አገራት መካከል ኢትዮጵያን ላሰለፋት፥ የባለሙያዎች፣ ምሁራን እና ፖለቲከኞች ስደት መንስኤ ሳይሆን አይቀርም፡፡››) ብሏል፡፡
Personal Freedom ብሎ በሰየመው ንዑስ ዘርፍም ኢትዮጵያ ውራ (110ኛ) ሆናለች፡፡ ሲዘረዝረውም እንዲህ ብሎ ነው፤ “Ethiopia ranks among the bottom 10 countries for citizens’ freedoms in expression, belief, association, and personal autonomy.” (‹‹ኢትዮጵያ ለዜጎቿ ሐሳብን፣ እምነትን፣ ማሕበርን፣ እና የመግለፅ ነፃነት፣ እና የግል አቋምን ለማንፀባረቅ ከማይመቹ የዓለማችን 10 አገሮች ተርታ ትሰለፋለች፡፡››)
ሐሳብን ለመግለፅ ካለመቻል ጀርባ ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን የማይገልፁት/ለመግለጽ የሚፈሩት ፖለቲካዊ አመለካከታቸውን ብቻ አይደለም ሃይማኖታዊ፣ ፆታዊ ጉዳዮቻቸውንም ጭምር ነው፡፡ ለዚህ አንዱ አስተዋፅዖ አዋጪ ‹‹የመቻቻል ምሳሌ›› የሚባለው ነገር ግን ‹‹መቻቻልን›› በጥያቄ ምልክት ውስጥ ያስቀመጠው ባሕላችን ነው፡፡ ‹‹መቻቻል›› በአገራችን አናሳው ብዙሐኑን ሲችል በሚል እሳቤ ተውጦ መክረሙ አጨቃጫቂ አይደለም፡፡ ስለዚህ አፈንጋጭ አመለካከቶች እውነታ ቢኖራቸውም እንኳን ተቀባይነት አይኖራቸውም፣ ሌላው ቀርቶ አፈንጋጭ አሳቢው ከሐሳቡ’ጋ ተግባብቶ እንዳይኖር ዱላ ይበዛበታል፡፡ ይህ ባሕል የወለደው ፍራቻ ፖለቲካዊ አስተሳሰብን የማንፀባረቅ፣ አንፀባርቆ ተቀባይነት የማጣት ፍራቻን ይወልዳል፡፡
ሕዝባችን ይፈራል፣ እንዲፈራም ታሪኩ ያስገድደዋል፤ ነገር ግን የሚፈራው በብትር የሚቀጣውን መንግስት ብቻ ሳይሆን በቃላት እና በማግለል የሚቀጣውን የራሱን ማኅበረሰብም ጭምር ነው፡፡ በዚህም የራሱን ሐሳብ ለራሱ አፍኖ በማለፍ ለአገሪቱ ለውጥ የሚበጁ በርካታ አማራጭ ሐሳቦችን አፍኖ ገድሏል፡፡ ይህንን ዓይነቱን ሕዝባዊ ፍራቻ አምባገነን መንግስታት ይፈልጉታል፣ እንዲለመልም እንጂ እንዲኮሰምን አያደርጉም፡፡ ለአምባገነን መንግስታት፣ ፍርሃት ከሰራዊቱ ይልቅ ሕዝቡን ከተቃውሞ ያቅብላቸዋል፡፡
በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ደፋር ጋዜጠኞች፣ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እና አፈንጋጭ ሃይማኖተኞች ሲገደሉ ነበር፣ እየታሰሩ እና እየተሳደዱ ነው፡፡ ይህ እውነታ ግን ከሕዝባዊው የፍራቻ አድማስ የበለጠ አይደለም፡፡ በግሌ የኢሕአዴግ መንግስትን ካጠነከሩት ጉዳዮች መካከል የሕዝቡ ፍራቻውን ከእውነተኛው ስጋት (risk) በላይ ማግነን እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ለዚህም ነው ይህንን መጻፌ!
የባለፀጋዋን አገር ዜጋ፤ አቶ ድህነትን እናስተዋውቅዎ
Wednesday, July 4th, 2012ከዕለታት አንድ ቀን ከምሣ መልስ ቡና የምጠጣበት ካፌ ተሰይሜያለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የአዲስ አበባ መስተዳደር ፕሮግራም ይተላለፋል፡፡ ፕሮግራም አቅራቢያዋ በእኛ ቲቪ ያልተለመደ ዓይነት ፕሮግራም እያቀረበች ነው፡፡ አንዷ መምህርት ትናገራለች ‹‹ልጆቹ ራሳቸውን ይስታሉ›› አለች፡፡ ልጆቹ ያለቻቸው እሷ የምታስተምርበት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያሉ ተማሪዎችን ነው፡፡
‹‹እናነሳቸውና ካፌ ወስደን ውሃ አጠጥተን፣ ዳቦ አብልተን ስንለቃቸው ደህና ይሆናሉ፤›› አለች መምህርቷ፡፡ ‹‹በኋላ ላይ ሲደጋገምብን ጠይቀናቸው- ለካስ የሚወድቁት ምግብ ከበሉ ሁለት ሦስት ቀን እየሆናቸው ነው፡፡››
ያንን ፕሮግራም ተመልክተው ከእንባቸው ጋር ያልታገሉ ሰዎች አልነበሩም፡፡ ሕፃናቱ በተለያዩ ምክንያቶች ከወላጆቸቸው የተነጠሉ ሲሆኑ፣ ያልተነጠሉትም ቢሆኑ ቤተሰቦቻቸው በየቀኑ የመመገብ አቅም የሌላቸው ነበሩ፡፡ የኋላ ኋላ በደረሰኝ መረጃ ያንን ፕሮግራም ያቀረበችው ጋዜጠኛ ‹‹በመርዶ ነጋሪነት›› ከአለቆቿ ተግሳፅ ደርሶባታል፡፡
- - -
ኢቴቪ ጫወታ አማረልኝ ብሎ ያቀረባቸው ወጣቶች ናቸው፡፡ ኮሌጅ ዘልቀው ዲግሪ እንደጨበጡ ተናግረዋል፡፡ አሁን ግን በኮብል ስቶን ጠረባ ሥራ ላይ ተሰማርተዋል፡፡ ኢቴቪ ይሄንን ‹‹ሥራ ፈጠራ›› ብሎታል፡፡ በሥራ ፈጠራና በሥራ አለመናቅ በኩል መስመር አለ፡፡ እነዚህ የተማሩ ኃይሎች፣ የፈለገ ሥራ ባይንቁ እንኳን የተማረ ኃይል እጥረት አለባት የምትባለው አገር ውስጥ ምናልባትም ከዚያ ውጪ ሌላ የሥራ አማራጭ የሌላቸውን ሥራ እየተሻሙ ነው፣ በልተው ለማደር፡፡
- - -
ሰማያዊ ፓርቲ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ፕሮፌሰር መስፍን መወያያ ንግግር አቅርበው ነበር፡፡ ከታዳሚዎቹ አንዱ ‹‹ማስተርስ አለኝ፤›› አለ፡፡ ‹‹ነገር ግን ሥራ አጥቼ በስንት መከራ አሁን አንድ ሺህ ከምናምን ደሞዝ እየበላሁ ነው፡፡ ነገር ግን የክፍለሃገር ልጅ በመሆኔና የቤት ኪራዩን ስለማልችለው ዛሬ አንዱ፣ ነገ አንዱ ጓደኛዬ ቤት እያደርኩ ነው፡፡ ለዚህ ኑሮ ያበቃኝን ኢሕአዴግ እግዚአብሔር ይስጠው›› አለ፡፡ ሪፖርተርም ይህ አይግረማችሁ ሲለን እንዲያውም ‹‹ዲግሪ ያላቸው ዜጎች የጎዳና ተዳዳሪዎች ሆነዋል›› የሚል ዜና አስነብቦናል፡፡
- - -
አንድ መምህር ጓደኛዬን አገኘሁት፡፡ በተለይም እዚህ ከተማ ውስጥ ቤተሰብ ስለሌላቸው መምህራን ባልደረቦቹ ሕይወት ይነግረኝ ገባ፡፡ መምህራኑ ርካሽ ከሚባለው ከት/ቤቱ ካፍቴሪያ ይመገባሉ፡፡ ነገር ግን ተቆራርጣ የምትደርሳቸው ደሞዛቸው በዕዳ ‹‹ኔጌቲቨ›› ትገባለች፡፡ አንዳንዴ ምህረት ይደረግላቸዋል፣ ባብዛኛው ግን ለሚቀጥለው ወር ይሸጋገርባቸዋል፡፡
ጓደኛዬ ሲነግረኝ ‹‹አንዱ፣ የደሞዝ ቀን ዕዳውን ሲያወራርድ 35 ሳንቲም ቀረው፡፡ እሷኑ ሲጃራ ገዝቶ አጨሰባት፡፡›› ይህንን የነገርኩት ሌላ ሰው ‹‹ሲጃራ በ35 ሳንቲም ማግኘቱም ጥሩ ነው፡፡›› አለኝ፡፡
- - -
አምስት የኢትዮጵያ ጠላቶች
Friday, June 29th, 2012‹‹ኢትዮጵያ አገሬ›› ከሚለው ሐረግ በቀር በዚህ ዘመን አንገት የሚያስቀና ነገር ማግኘት እየከበደ ነው፡፡ እሴቶቻችን እየተሸረሸሩ፣ ፍቅራችን እየጠወለገ፣ ተስፋችን እየመነመነ.. መጥቷል፡፡ መንስኤው እንደውጤቱ እልፍ ነው፡፡ እኔም እንደወትሮዬ አምስት አጀንዳዎችን አንስቼ አንድነታቸውን የማስደመድምበት ምክረ መጣጥፍ ይዤ ቀርቤያለሁ - እነሆ!
1ኛ
‹‹ገበታ ንጉሥ ነው››
ገበታ እንደንጉሥ የሚቆጠርባት ኢትዮጵያ ገበታን ለማግነን ምክንያት አላት፡፡ የዓለም ስልጣኔ እምብርት የሆነችው ግብጽ ጥንታዊና ዘመናዊ ከተሞቿ የተቆረቆሩት በአባይ ወንዝ ዳርቻ ነው፡፡ ግብጽ ምድሯ ውሃ ባያፈልቅም ከደጇ በሚያልፈው ውሃ ሕዝቦቿን ከረሃብ ለመታደግ ችላለች፡፡ ‹‹ከሞኝ ደጃፍ ምሳር ይቆረጣል›› ነውና ተረቱ ኢትዮጵያ ግን የረሃብ ምሳሌ ነች፡፡ ከሰማይ ዝናብ ዘነበ/አልዘነበ በሚል የምግብ ዋስትናዋን በሚትዮሮሎጂ ዕድል ላይ የጣለችው ኢትዮጵያ የረሃብን ነገር ታውቀዋለች እና ‹‹ገበታ ንጉሥ ነው›› እያለች ብትተርት አይፈረድባትም - ረሃብ አንደኛ ጠላቷ ነውና፡፡
2ኛ
‹‹ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም››
ኢትዮጵያውያን አማኞች ናቸው፡፡ ክርስትና ከመፈጠሩ በፊት አክሱም ሃውልትን ያስቆማቸው እምነታቸው ነው፡፡ ነገሮች ሁሉ በፈጣሪ ፈቃድ እንጂ በሰው ጉልበት ይሆናል ብለው አያምኑም፡፡ ይህንን በርካታ ምሳሌና የኑሮ ዘይቤያቸው ይመሰክራል፡፡ እርግጥ በዘመናዊዋ እና በቀድሞዋ ኢትዮጵያ መካከል ልዩነት ይኖራል ብሎ መጠርጠር መልካም ነው፡፡ እንደምሳሌም ጥንታዊዎቹ የአክሱም ሐውልትን ያቆሙት በትግል እንጂ በዕድል አይደለም፤ ሌላ ምሳሌ፣ ቀደምት የላሊበላ ታሪክ ጸሃፊዎች ላሊበላ የታነፀው እነዚህ ታሪክ ጸሃፊዎች የኢትዮጵያውያንን የእጅ ሥራ ‹‹ታድለው›› እንጂ ‹‹ታግለው›› ያገኙት ስላልመሰላቸው ከነዚያኞቹ እነዚህኞቹ ያንሳሉ - እምነትን በመምረጣቸው ብቻ ሳይሆን መታደልን ቁጭ ብለው በመጠበቃቸው፡፡
‹‹ጠንቋይ መቀለብ›› የተሰኘች አባባል አለች፤ ‹‹ማወቅን›› ትወክላለች፡፡ በአገራችን ‹አዋቂ› የሚለው ቃል ‹ጠንቋይ› ከሚለው እኩል ያገለግላል፡፡ የእጅ ሥራ ባለሙያዎች ጥሩ ስም የላቸውም - ‹‹ቡዳ›› ናቸው፡፡ አሁንም ድረስ በሥራው ግን በቶሎ የተሳካለት ሰው/ነጋዴ ‹‹ምን የተለየ ሥራ ሰርቶ ነው?›› ብሎ ሊማርበት ከሚፈልገው ይልቅ ‹‹አስጠንቁሎ/አስደግሞ ነው›› እያለ የሚያማው ተመልካች ይበዛል፡፡ ከሥራ ይልቅ ምትሃት ዋጋ አለው፡፡ ድህነቱንም ሮጦ ያመለጠ ሰው ግፋ ቢል ‹‹ፈጣሪ ረዳው›› ይባል እንደሆን እንጂ ‹‹ለፍቶ አገኘ›› የሚባልበት ጊዜ እምብዛም ነው፡፡ ኢትዮጵያ ችግር ላይ ነች - ዜጎቿ ለስኬት አቋራጭ መንገድ ያስሳሉ - አምልኮን ወይም እምነትን የሙጢኝ ብለው ‹‹የቆጡን ሲጠብቁ፣ የብብታቸው››ን ያጣሉ፡፡
3ኛ
‹‹ሰማይ አይታረስ ንጉሥ አይከሰስ››ኢትዮጵያውያን ንግሥና እና ሰማይን የምናነፃፅር ብቸኛ ዓለመኞች ነን፡፡ ንጉሥ ካ’ሉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፈረዱ በቃ - አበቃ ብለን እጅና እግራችንን አጣጥፈን የምንቀመጥ ሰዎች ነን፣ ጭቆና ከንጉሥ ከመጣ አሜን ብሎ የሚሸከም ጫንቃ ያለን ፍጡሮች ነን - በልምድ፡፡ ይሄ ልምድ ከንጉሥ ጀምሮ እስከታችኛው እርከን ይወርዳል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን የሥራ ቦታ አለቆቻችን ሲሳሳቱ ደፍረን አናርማቸውም፣ ሲጨቁኑን አንታገላቸውም፣ መስመር ሲስቱ አንመልሳቸውም - ምክንያቱም ንጉሥ አይከሰስም፡፡ በዚህ መንገድ ብዙ አምባገነኖችን ፈጥረናል፣ ገና እንፈጥራለን - ንጉሥ ባለመክሰስ፡፡
4ኛ
‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል››
የጉበኝነት፣ ሙሰኝነት፣ በስልጣን መባለግ ወይም መበልፀግ በአገራችን ዕድሜው ስንት እንደሆነ ለማወቅ ይሄ ተረት መተረት የጀመረበትን ጊዜ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ሹመኞች ሊያገለግሉት የተሾሙለትን ሕዝብ መበዝበዝ እንደመብት ይቆጥሩታል፡፡ ጥንት ጀምሮ እስከዛሬ የዘለቀው የሹመኛ የመብላት ‹‹መብት›› ተሹሞ የማይበላውን፣ በተሾመበት መስክ ባይተዋር የሚያደርግ ነው፡፡ ተሹሞ ባለመብላቱ እንደሚቆጭ እየተነገረው አለመብላትን የሚመርጥ ምናልባትም ለሌሎች ሹመኞች ስለማይመች የሚወገድበት መንገድ ይመቻችለታል፤ ባልሰራው ወንጀል ይከሰሳል፣ የበይዎቹን ገፈት ይቀምሳል፡፡ ሹመኞች ሲበሉ የሚመለከቱ ሰዎች ‹‹ባለጊዜ›› ብለው ያልፏቸው እንደሆን እንጂ እንደወንጀለኛ አይሷቸውም፣ አይወቅሷቸውም፣ አያጋልጧቸውም፡፡ እንዲያውም ብዙዎቹን ሹመኞች የሚያባልጓቸው ሕዝቦች ናቸው፡፡ ለዚያ ነው ዛሬ፣ ዛሬ ብዙዎች ሹመትን የሚመኙት ለመብላት የሆነው - ሌላው ጠላታችን፡፡
5ኛ
‹‹እል’ፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል››
የተማረው፣ ያልተማረው፣ ድሃው፣ ሃብታሙ፣ ከተሜው፣ ገጠሬው - ሁሉም አንድ ሕልም አለው፡፡ ከኢትዮጵያ ውጪ ወደ አንዱ አገር መኮብለል፡፡ እርግጥ ከላይ ተረቱ ‹‹ዛሬን ሲያልፉ ነገ እልፍ ይገኛል›› የሚል ትርጉም ሊሰጥ ይችላል፡፡ ይህም ቢሆን ችሎ ማሳለፍ፣ ‹ታግሎ› ሳይሆን ቅድም እንደታዘብነው ‹ታግሶ› ማሳለፍ ላይ ነው ዓላማው፡፡ ከዚያም በከፋ ግን ኢትዮጵያውያን አልፎ መሄድ እየተማርን ነው፡፡ ከ5 ዓሥርት ዓመታት በፊት ከኢትዮጵያ የወጡ ሰዎች ስም ዝርዝር በጋዜጣ ይታተምባት የነበረችው አገር ዛሬ በፈላሾቿ (diasporas) ቁጥር አንድ አገር መመስረት የምትችል ሆናለች፡፡ ምክንያቱም ዜጎቿ ‹እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል› ብለው ያምናሉ፡፡ በዚህም አገራችን እልፍ የሚሰሩ ክንዶች፣ እልፍ የሚፈጥሩ ጭንቅላቶችን አጥታለች - ስደት ጠላቷን እየተከተለች፡፡
ድምር ውጤቱ?
ለጠላቶቻችን ማጣቀሻነት ተረትና ምሳሌዎቻችን የተጠቀምኩት ያለምክንያት አይደለም፡፡ ተረትና ምሳሌ የብዙዎች አስተሳሰብ ብዙዎችን በሚያግባባ መንገድ የሚገለፅበት ቋንቋዊ ዘይቤ ነው፡፡ እነዚህ ተረትና ምሳሌ ስር የሰደዱ ባሕልና አስተሳሰባችንን (mentality) ይነግሩናል፡፡ ሁሉም ታዲያ የምስራች የላቸውም - እዚህ እንደጠቀስኳቸው ያሉቱ መርዶ ናቸው፡፡ መርዶዎቻችንን ደምረን ስንመለከታቸው ድምራቸው አንድ ነው፡፡ ሁሉም የተዘረዘሩት የዕውቀት ማነስ ውጤቶች ናቸው፡፡ ይህንን መቅረፍ ደግሞ የሚቻለው በትምህርት ነው፡፡ ጥራት ያለው ትምህርትን ለሁሉም በማዳረስ፡፡የተመቻቸ ጊዜ መጠበቅ?
Thursday, June 28th, 2012ኅወሓትን ለ10 ዓመታት የመሩት አቦይ ስብሃት፣ የመሪነቱን ሥልጣን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በፈቃዳቸው ካስረከቡ 23 ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ ለአዲስጉዳይ በሰጡት ቃለምልልስ ላይ፣ አቦይ ስብሃት ‹‹የኅወሓትም ሆነ የኢሕአዴግ ሕገ-ደንብ አንድ ኃላፊ በስልጣን ላይ የሚቆይበትን ዓመት አይገድብም፡፡…›› ብለው ተናግረዋል፡፡ እውነት ነው፤ እንኳን የፓርቲው የአገሪቱ ሕገ-መንግስትም ለ‹‹ትዕምርትነት›› የሚቀመጠውን ፕሬዚደንት የስልጣን ዘመን ሲገድብ፣ የክልል ፓርላማን እስከመበተን ስልጣን የተቸረውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዘመነ መንግስት አይወስነውም፡፡
‹‹የተመቻቸ ጊዜ ልጠብቅ ካልኩ፥ 50 ዓመትም አይበቃኝ፤›› ዶ/ር እሌኒ - ለሪፖርተር ጋዜጣ፡፡
ኢሕአዴግ እንዲህ ዓይነት ነገር ይወዳል፡፡ ለምሳሌ በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 39 ላይ ‹የራስን እድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል› ብሎ ይጽፍና ‹መገንጠል›ን ምን አመጣው ተብሎ ሲጠየቅ ‹‹ብሔር ብሔረሰቦች በመፈቃቀር እና በመፈቃቀድ አብረው የሚኖሩት የመለያየት መብት እንዳላቸው ስንነግራቸው ነው›› ብሎ ይከራከራል፡፡ በዚህ ‹‹ሕገ-መንግስታዊ አተረጓጎም›› ነው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘመነ መንግስት አለመገደብን የምመለከተው፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ (ወይም የኢሕአዴግ) የስልጣን ዘመን አለመገደቡ፣ አንድ፤ አቦይ ስብሃት እንዳሉት ‹‹…ፕሮግራሙን ማዕከል አድርጎ የጋራ አመራርን እስካረጋገጠ ድረስ…›› ችግር የለውም ለማለት ይመስላል፣ ሁለት፤ የስልጣን ዘመኑ ሳይገደብ በገዛ ፍቃዱ ይለቃል የሚል ተስፋ ይዞ ይሆናል - ልክ እንደመገንጠል/አለመገንጠሉ፡፡ ሦስት፤ የፓርቲው ሊቀመንበር ቁጭ ባሉበት የሊቀመንበሩ የሥልጣን ዘመን ይወሰን የሚል ጥያቄ ማንሳት ለአባላቱ አስፈርቷቸው ይሆናል፡፡
አንድ ሰው ለረዥም ጊዜ አንድ ቦታ ላይ ሲቀመጥ የቦታውን ኃላፊነቶች በአግባቡ እያወቀ እና የካበተ ልምድ እያፈራ ይመጣል፤ ታዲያ ለምን የለመደውን ሰው አስነስቶ አዲስ መተካት ያስፈልጋል?
ስልጣን በተለይም ትላልቅ ተቋማትን እና ሃገርን የመምራት ስልጣን በአንድ ሰው ወሳኝነት ላይ (በተለይም እንደኛ አገር ባለው ተሞክሮ በፍፁማዊ ሁኔታ በአንድ ሰው ወሳኝነት ላይ) ጥገኛ ሊሆን ቢችልም የቡድን ሥራ ውጤት ነው፡፡ በአመራር ቦታ ላይ የሚቀመጡ ሰዎች ኃላፊነት ነገሮች መስመራቸውን ጠብቀው እንዲሄዱ ማድረግ ብቻ ነው እንጂ ሌላው ሌላው የብዙዎች ድምር ፍሬ ነው፡፡
ይህንን በቀላል ምሳሌ ብናየው እንዲህ ይሆናል፡-
አንድ ሹፌር መኪና ሲነዳ (መሪ፤ ሃገር ሲመራ) እንደማለት ነው፡፡ ሹፌሩ (መሪው) መኪናውን (አገሪቱን) የሚፈለግበት ቦታ ለማድረስ መጀመሪያ በአግባቡ የተጠረገ ጥርጊያ መንገድ (ፖሊሲ፣ ስርዓት) ያስፈልገዋል፣ ረዳት (አማካሪ) ያስፈልገዋል፡፡ መኪናው ጥሩ ኢንጂን (ተቋማት) እና ነዳጅ (ምሁራን) ያስፈልጉታል፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ከተሟሉ፤ አንደኛ ሹፌሩ ከተጠረገለት መንገድ ውጪ አይሄድም፣ ሁለተኛ ተሳፋሪዎቹን (ሕዝቦችን) የሚፈለገው ቦታ ለማድረስ ብዙ ጥበብ አይጠበቅበትም፡፡ ነገር ግን ያለ እረፍት ለረዥም ሰዓታት ከነዳ (ለረዥም ዓመታት ከመራ) መሃል ላይ በድካም መዛሉና መስመር መሳቱ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ ሹፌሩ ተቀያሪ ያስፈልገዋል፣ ኢንጂኑ ሲያረጅ ‹ሰርቪስ› ይደረጋል፣ ነዳጁ ሲያልቅ ይሞላል/ይተካል፣ ረዳቱም ሲደክም ይቀየራል፡፡ በዚህ አካሄድ ተቀያሪው ያንኑ ጥርጊያ ይዞ በአዲስ ጉልበት፣ በአልተሞከረ ዘዴ፣ በመስቀለኛ መንገዶች ሳይደናገር ወደመዳረሻው ተከታዮቹን ይዞ፣ መኪናውን ለአደጋ ሳያጋልጥ ይዘልቃል፡፡
እንግዲህ መሪዎች መተካት ያለባቸው ከስትራፖ (fatigue) እንዲተርፉ እና ሌሎች የሚታያቸውን አዲስ መንገድ ወይም አካሄድ እንዲከተሉ ነው፡፡ በእኛ አገር ‹‹…የተጀመረው ልማት እንዳይደናቀፍ…›› የሚለው ምክንያት ስልጣንን ላለመልቀቅ እንደምክንያት ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ የተስተካከለ ስርዓቱ አለ ከተባለ በተተኪው አካል የተጀመረው ልማት የማይጨረስበት ምክንያት ምንድን ነው? ተቋማት በአንድ ባለ ሙሉ ስልጣን መሪዎች (እነ መብራት (ወይም ‹‹መጥፋት››) ኃይልን ምሳሌ መውሰድ ይቻላል) ብቻ ዘላለም ከተመሩ፣ አገር በአንድ ጠቅላይ ሚኒስቴር፣ በአንድ ፓርቲ ብቻ ከተመራች ለረዥም ጊዜ (ለምሳሌ ለ21 ዓመታት) እየተፈጠሩ መፍትሄ ያጡ ችግሮችን በአዲስ መልኩ ተመልክቶ፣ በአዲስ መፍትሄ እንዴት መፍታት ይቻላል?
ከሰሞኑ በኢሕአዴግ ቤት እና ጎረቤት ባልተሞከረ መልኩ ዶ/ር እሌኒ ገ/መድህን ከምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚነታቸው በገዛ ፈቃዳቸው ለቀዋል፡፡ መልቀቃቸው በጣም አነጋጋሪ የሆነው ከኢሕአዴግ በወዳጅነት የሚሠራ ወይም አባላቱ ስልጣን በመልቀቅ ስለማይታወቁ ነው፡፡ ኢሕአዴጎቹ ምናልባትም ‹‹…የተመቻቸ ጊዜ…›› እየጠበቁ ይሆን የሚል ጥያቄ ሁልጊዜ ያቃጭልብኝ ነበር፡፡
‹‹…ምናልባት የጀመሩት ‹ልማት› የሚያልቅበትን - የተመቻቸ ጊዜ? ምናልባት የተዘጋጀ ተተኪ የተፈጠረ የሚመስላቸው - የተመቻቸ ጊዜ? ምናልባት የሆነ የማናውቀው የተመቻቸ ጊዜ ይመጣ ይሆን?...›› እያሉ እየጠበቁ ይሆናል ብዬ አስብ ነበር፡፡ ‹ያ የተመቻቸ ጊዜ› መቼም እንደማይመጣ እያወቅኩት፡፡ ታዲያ ዶ/ር እሌኒ ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት መልስ ለአለቆቻቸው ለነ አቶ መለስ ዜናዊም ትምህርት ይሆናል ብዬ አሰብኩ፡፡
Hookah እና አሜሪካ
Saturday, June 23rd, 2012ይህንን ጽሁፍ ለመጻፍ ስነሳ ‹‹የኛ ሰው በአሜሪካ›› የሚል ርዕስ ልሰጠው ፈልጌ ነበር፡፡ ችግሩ ይሄ ርዕስ አሜሪካንን ረግጠው በተመለሱ ሰዎች ስለተለመደ ባይተዋርነት ተስማምቶኝ ተውኩት፤ በሌላ በኩል የየኛ ሰው በአሜሪካ ኑሮ በሁካ ብቻ አይገለፅም የሚል ርህራሄም ተሰምቶኛል፡፡
ሁካ - የሺሻ አሜሪካዊ ስሟ ነው፡፡ አዲስ ጋይድ የምትባል፣ በቀለም የተንቆጠቆጠች፣ ዲዛይኗ እና ጠረኗ ያማረ፣ ጽሁፎቿ ዋዘኛ፣ ዳያስፖራውን ኢላማ ያደረገች መጽሄት በአጋጣሚ እጄ ገብታ ሳገለባብጣት ማስታወቂያ እንደሚበዛባት አስተውያለሁ፡፡
ካየሁዋቸው ማስታወቂያዎች ውስጥ - በተለይም የአበሻ ካፌና ሬስቶራንቶቹ ማስታወቂያዎች ከዘጠኙ ስምንቱ ሁካን በስዕል ወይም በጽሁፍ አስተዋውቀዋል፡፡
የሁካ ማጨሻዋ እቃ በወርቃማ ቀለም የተንቆጠቆጠ፣ ዙሪያው በአረቢያል መጅሪስ የደመቀ፣ አፋቸው ላይ ጡሩምባ መሳይ የሁካውን ጫፍ የሰኩ ወይም እንደፈላ ጀበና ከአፋቸው ጢስ ቡልቅ፣ ቡልቅ የሚያደርጉ ሴቶች፣ ወዘተ፣ ወዘተ ለቁርስ ቤቶቹ ማስታወቂያ ሳይቀር ፍጆታ ሁነዋል፡፡
‹‹የኛ ሰዎች በአሜሪካ›› ታሰቡኝ!
ዘመድ ጥየቃ፣ ወይም ሚስት/ባል ፍለጋ፣ ወይም የቆጠቡትን አጥፍተው ለመመለስ የሚሄዱ ዳያስፖራዎች ‹‹የለመለመ ጫት ናፍቆኛል!›› የሚሏት ነገር ትዝ አለችኝ፡፡ የአገራችን ሰው ጫት መቃምን ዘመነኝነት ካደረገው ሰነባብቷል፡፡ ለጫት ግድ የለውም የሚባለው ሰው እንኳን ቅዳሜ እና እሁድን ማሳለፊያው ጫት ነው፡፡ እንዲያውም ‹‹ትልልቆቹ››፣ በየሳምነቱ የሥራ ቀናት ‹‹ቢዚ›› የሆኑት ሰዎች እሁድ እሁድ ‹‹ዛፍ ላይ እንውጣ›› እየተባባሉ ነው የሚጠራሩት፡፡ (ባለፈው ሰሞን የኛ ፕሬስ የተባለ ጋዜጣ ‹‹አርቲስቱ ከጓደኞቹ ጋር ጫት ለመቃም በየቀኑ አንድሺህ ብር ያወጣል›› ብሎ ያወራት ወሬ ስንት ፍልስምና አፈላስማኛለች መሰላችሁ? ስንት ሰው በአንድ ሺህ ብር በወር ስንት ቤተሰብ ለማስተዳደር አስማት በሚሰራባት አገር ውስጥ ‹‹አርቲስቱ›› በቀን አንድ ሺህ ብር ለጫት - ‹አጀብ!› አያሰኝም?)
የእንጦጦ ጎዳናዎች ዳርቻ ላይ ተኮልኩለው የሚቆሙ መኪኖች - ውስጣቸው ዙርባ ጫት ዙሪያ የሰፈሩ ባለጠጎች አሉባቸው፡፡ ፒያሣ ከማሕሙድ ሙዚቃ ቤት ወደ ሰይጣን ቤት ቁልቁል ባንኮ ዲሮማ ተደግፈው ሲወርዱ የሚያገኟቸው መኪኖችም የሚቆሙት ይህንኑ ጉዳይ ለማስፈጸም ነው፡፡ ሌላም፣ ሌላም ቦታ! በጫት ምርቃና የተጻፉ ፖለቲካዊ ትንታኔዎች በየጋዜጦቹ፣ በጫት ምርቃና የሚቀርቡ ፕሮግራሞች በየኤፍ ኤም ሬዲዮዎቹ፣ በጫት ምርቃና የሚወጡ ፖለሲዎች በየቤተመንግስቱ (ይቅርታ በቤተ መንግስቱ)፣ በጫት ምርቃና….?
ቢሆንም ግን ይሄ የአገርቤት አመል ውቅያኖስ ያቋርጣል የሚል ግምት አልነበረኝም፡፡ ነገር ግን እውነታው የእኛ ሰው - አገር አቋርጦ ሲሄድ ለሱሳሱስ ዕውቅና ከመስጠት የተሻገረ ስልጣኔ እንደማያገባው - ሬስቶራንቶችን በምግብ ምስል ከማስተዋወቅ ይልቅ - በሁካ ማጨሻ ጋን ማስተዋወቅ - እንደማሕበረሰብ ዋጋ የምንሰጠውን ነገር ግን እያስታወሰ የሚያስተዛዝበን ነገር ነው፡፡
እኔ እዚህ ቁጭ ብዬ ሳስበው በቅድሚያ የሚያቃጭልብኝ የዳያስፖራ ፖለቲካ ነው፡፡ በአገርቤት ያሉ አርቲስቶች በምርቃ የሚጽፉት ድርሰት እና ፊልም - መጀመሪያ ላይ ዋና ገጸ ባሕሪው የሚጠራበት ስም ተረስቶ መጨረሻ ላይ ሌላ ሲሆን ገጥሞኝ ያውቃል፡፡ አሁንም በሁካ ቤት ምክር የተመሰረቱ የዳያስፖራ ፓርቲዎች አገራችንን…… (እናንተ ጨርሱልኝ!)
---
ይሄ ጽሁፍ ከደሙ ነፃ የሆኑ ዳያስፖራዎችን አይመለከትም፡፡እነአልበርት አይንስታይን ስለዘንድሮው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምን ይላሉ?
Sunday, June 17th, 2012ስም ያለው ነገር ሁሉ ‹‹ያለ›› ነገር ነው እያለ ከልጆቹ’ጋ ሲሟገት የነበረ አንድ ጦማሪ ወዳጄ፥ ስማቸው ከመቃብር በላይ የዋለላቸው ሰዎችም ስማቸውን የሚጠሩ ሰዎች እስካሉ ድረስ ‹‹የሉም›› ማለት አይቻልም - ምክንያቱም ‹‹አሉ›› ብሏል፡፡ መከራከሪያው ለዚህ ጽሁፍ መንደርደሪያ ግብአትነት ብቁ ስለሆነ ያለምንም ክርክር ተቀብዬዋለሁ፡፡ የጨዋታዬ ርዕሰ ጉዳይ ግን ‹‹ያለ›› እና ‹‹የሌለ›› ነገር አይደለም፡፡ ይልቁንም አንዳንድ ሕያዋን ሰዎች ከተናገሯቸው ሕያው ንግግሮች መካከል እያጣቀሱ የዛሬውን የአገራችንን ፖለቲካ መሄየስ ነው፡፡ በምናባዊ ሳይንስ ሊቁ አልበርት አይንስታይን ብንጀምርስ?
1. አልበርት አይንስታይን
“The world will not be destroyed by those who do evil, but by those who watch them without doing anything.” (ዓለማችን የምትጠፋው ክፉ በሚያደርጉ ሰዎች ሳይሆን ክፉ ሲያደርጉ እያዩ ዝም በሚሏቸው ሰዎች ነው፡፡)
በኢትዮጵያ የፖለቲካ እውነታ በየጓዳው ከመንሾካሾክ እና ከመብሸቅ ባሻገር ይሄ መንግስት (ይሄ ገዢ) ያለእኛ ተገዢነት እና ፈቃደኝነት ሊጨቁነን እንደማይችል ገብቶን የተነጠቅነውን ነፃነት ለማስመለስ የምንሞክር እጅግ ጥቂቶች ነን፡፡ በተለይም ‹‹ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ ብዙሐኑን ስላላማከለ አንድ ቀን አገሪቱ ወደማትወጣው ችግር ውስጥ ትገባለች፣ ወዘተ. ወዘተ...›› እያሉ የጋን ውስጥ ትንታኔያቸውን የሚሰጡት ነገር ግን ለጋዜጣ እንኳን ማብራሪያ ለመስጠት ‹‹ስሜ ከተጠቀሰ አይሆንም›› የሚሉ ምሁራን ከአጥፊው ገዢው ፓርቲ ይልቅ - ለጥፋቱ ተጠያቂ መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡
2. ማሕተመ ጋንዲ
“You assist an evil system most effectively by obeying its orders and decrees. An evil system never deserves such allegiance. Allegiance to it means partaking of the evil. A good person will resist an evil system with his or her whole soul.” (መጥፎ ስርዓትን በጣም ጥሩ አድርገህ የምታጠናክረው ትዕዛዛቱን እና አገዛዙን እሺ ብለህ ስትቀበል ነው፡፡ መጥፎ ስርዓት እንዲህ ዓይነት ታዛዥነት አይገባውም፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ስርዓት መታዘዝ ማለት ለጥፋቱ ተባባሪ መሆን ማለት ነው፡፡ ማንኛውም መልካም ሰው የተበላሸ ስርዓትን በሙሉ እስትንፋሱ ይቃወማል፡፡)
በዘመነ ኢሕአዴግ አምባገነን በአምባገነን እግር ተተክቷል፣ ዘረኝነት ከመቼውም በበለጠ ነግሷል፣ ሐሳብን በነፃ የመግለጽ መብትና በምርጫ መንግስት የመቀየር እድል ብቅ ብሎ ወደ ሰንኮፉ ተመልሶ ገብቷል… ሁሉንም ክፉ ድርጊቶች እናውቃለን፣ እንታዘባለን፡፡ ሆኖም ምንም ማድረግ እንደማይችል ሰው እጅና እግራችንን አጣጥፈን ተቀምጠናል፡፡ የሰላማዊ ትግል ምሳሌ የሆነው ማሕተመ ጋንዲ ግን ለእንዲህ ዓይነቱ ብልሹ ስርዓት ከመታዘዝ የበለጠ ውርደት እንደሌለ ይነግረናል፡፡ ሰዎች በማያምኑበት ሥርዓት ተገዢ በሆኑ ቁጥር የስርዓቱን ስር መስደድ እያጎለበቱ እንደሆነ ነው የላይኛው አባባሉ የሚያስረዳው፡፡ ስለዚህ በጋንዲ ዓይን ትዝብት ውስጥ ገብተናል፤ ለማንፈልገው አገዛዝ ‹‹እምቢታ›› የሌለን የክፉ ስርዓት ሰለባ ሆነናል፡፡
3. ዴዝሞንድ ቱቱ
“If you are neutral in situations of injustice, you have chosen the side of the oppressor. If an elephant has its foot in the tail of a mouse and you say that you are neutral, the mouse will not appreciate your neutrality.” (ኢ-ፍትሐዊ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ከማንም ለመወገን ካልፈለግክ፣ ያኔ የጨቋኙን ተግባር መደገፍ መርጠሃል ማለት ነው፡፡ ዝሆን የአይጧን ጭራ ረግጦ እያየህ፣ ገለልተኛ ነኝ ብትል ያንተ ገለልተኝነት ለአይጧ አይዋጥላትም፡፡)
በአገራችን ምን እየተከሰተ ነው? የኃይል ሚዛኑ ወዴት አጋድሏል? ብረቱን የታጠቀው ማነው? የፍርድ ቤቶች ዳኛ ማነው? የዚህን መልስ እውነታ በልቡ እያጉላላ ‹‹የለም፤ ዛሬ የተረገጥኩት እኔ ስላልሆንኩ አይመለከተኝምና ለማንም የማልወግን ገለልተኛ መሆን አለብኝ›› ብሎ ዝም ማለት ሁሉን ኃይል ተቆጣጥሮ ሌላውን ኃይል ለሚረግጠው አካል መወገን ማለት ነው፡፡ ገለልተኝነት ወይም ዝምተኝነት በሚዛናዊ ተቀናቃኞች መሃል እንጂ በጨቋኝ ተጨቋኞች መሃከል ለጨቋኙ መወገን ማለት ነው - ይህንንም ዴዝሞንድ ቱቱ ቁልጭ አርገው ከላይ ተናግረውታል፡፡
የዓለማችን ታላላቅ ሰዎች ስለወቅታዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ይህንን አሉ፤ እርስዎስ ምን ይላሉ?
የአንድ ኪራይ ሰብሳቢ መንግስት ታሪክ
Monday, June 11th, 2012የመንግስት መሥሪያ ቤቶች እጣ ክፍሎቼ እንዳልሆኑ እየተረጋገጠ ነው፡፡ ባለፈው ሰሞን እርሜን ‹ኢሚግሬሽን› ብሄድ ለሦስት ሰዓታት በግዞት እንደቆየሁ አጫውቻችሁ ነበር፡፡ ዛሬ ጠዋት ደግሞ የጓደኛዬን ጉዳይ ላስፈጽም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰነድ ማረጋገጫ ቢሮ ተገኘሁ፡፡ እዚህ እንደከዚህ ቀደሙ አካላዊ ጥቃት ባይደርስብኝም - መንግስታችንን በኪራይ ሰብሳቢነት እንድታዘበው የሚያደርገኝ ነገር ተከስቷል፡፡
ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ የሰነድ ማረጋገጫ ሥራ የሚባለው ሰነዱን ባለቢሮዎቹ ተኮር ብለው ካዩት በኋላ ማሕተም ይመቱበታል - አለቀ፡፡ ይህ ሥራ የ30 ሰከንድ ሥራ ቢሆንም ብዙ ያስከፍላል - በጊዜም፣ በገንዘብም፡፡
እኔ የሄድኩት አንድ የትምህርት ማስረጃ ሰነድ ላይ የእውነተኛነት ማረጋገጫ ማሕተም ለማስመታት ነው፡፡ ይህንን ሰነድ ሌላ ቦታም ቀደም ብሎ ማረጋገጫ ማሕተም ማስመታት በቅድመ ሁኔታነት ተከናውኗል፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የሰነዶች ማረጋገጫ ቢሮ ደግሞ ከግቢ ውጪ ጥቂት፣ ጊቢ ውስጥ ደግሞ በአግዳሚ ወንበር እና ከዚያ የተረፈው ግድግዳ ተደግፎ ቆሞ የተሰለፈ ብዙ ሰው አለ፡፡ ያንን መጠበቅ - በተለይ እንደኔ ላለውና በስጋ ሳይሆን ባጥንት ብቻ ለቆመ ሰው - ወገብን ይፈታተናል፡፡
በግምት ለሁለት ሰዓታት ያህል በሰልፍ ጠብቄያለሁ፡፡ ተሰልፌ ግን ስሰጋ የነበረው ስለወገቤ፣ ስለጥበቃው ወይም ከምሳ ሰዓት በፊት ወረፋው ባይደርሰኝስ ስለሚለው አልነበረም፡፡ እነዚህኞቹ እዳቸው ገብስ ነው፡፡ እኔን የጨነቀኝ ይህን ሁሉ ሰዓት ጠብቄ ያላሟላኸው አንድ ነገር አለ ተብዬ ሰልፉን እንደገና እንድጀምር ብደረግስ?
ኪራይ ሰብሳቢነት - አንድ
ይሄን የሚያህል ሰልፍ ያለበት ቢሮ ምን፣ ምን እንደሚያስፈልግ መረጃ የሚጠየቅበት በቂ መንገድ የለም፡፡ የጊቢ ውስጥ መረጃ ሰጪ ሴት ብትኖርም የውጪውን ሰልፍ ከጨረሱ በኋላ እንደገና ወደኋላ መመለስ የሚባል ጣጣ አለ፡፡ ይህንኑ ፍራቻ አሰስ ገሰሱን ሁሉ ኮፒ ከማድረግ አንስቶ የተቻለኝን ሁሉ (መጨረሻ ላይ ግን አስፈላጊ እንዳልነበር የተረዳሁትን) ጥንቃቄ አደረግኩ፡፡ ምን አለ ይሄ ቢሮ ሁሉንም መረጃዎች የሚያቀርብበት ኤሌክትሮኒክ የመረጃ ምንጭ (ምናልባት ስልክ፣ ምናልባት ድረገጽ) ቢኖረውና ከጭንቀት ቢገላግለን፡፡ ይህንን ለማድረግ ገንዘብ የሚያጥረው ከመሰላችሁ - ኪራይ ሰብሳቢነት ሁለትን አንብቡ፡፡
ኪራይ ሰብሳቢነት - ሁለት
ለዚህ ለጠቀስኩላች የ30 ሰከንድ አገልግሎት ጽ/ቤቱ 150 ብር ጠይቆኛል፡፡ ወቸ ጉድ! ቢቻል ይሄ ለታክስ ከፋይነቴ በነፃ የሚሰጠኝ አገልግሎት መሆን ነበረበት፡፡ አሊያም ዋጋው ባይበዛ! ለየትኛው ሥራ? የሆነ ነገር የሚሰጡኝ ነገር ቢኖር? - እሺ! የሆነ የሰነዱን እውነተኛነት የሚያረጋግጡበት ውጣ ውረድ ቢኖር? - እሺ! የሆነ ነገር ቢኖር ክፍያው አሳማኝ ይሆን ነበር፡፡ ያሳዝናል፤ ከኔ የበለጠ ብር - እንደየሰነዳቸው ዓይነት - የሚከፍሉ ሰዎችም አይቻለሁ፡፡ ነገር ግን ለዚህ ከኪራይ ሰብሳቢነት ውጪ ስም አላገኘሁለትም፡፡ በየ30 ሰከንዱ በ7 መስኮቶች የሚሰበሰበው ገንዘብ ምን ይደረግ ይሆን?
ኪራይ ሰብሳቢነት - ሦስት
ከፊት ለፊቴ ተሰልፋ የነበረች አንዲት ሴት ስልክ ስታወራ የነበረች ልጅ ‹‹ወደአዲስ አበባ ሄጄ እኮ ነው የዘጋኋችሁ…›› ስትል ሰማኋት፡፡ መጀመሪያ አሃ! ለካስ ከክፍለሃገርም የሚመጡ አሉ ብዬ ተጽናናሁ፣ ቀጥሎ እንዴ! ለካ እኔም ራሴ ክፍለሃገር ላለው ጓደኛዬ ተወክዬ ነው አልኩ እና አሰብኩ፣ ሰልሼ ስለአሰራሩ ማሰብ ቀጠልኩ፡፡
ቆይ ይሄ ፌዴራሊዝም የሚባለው ነገር እኒህ እኒህ ሥራዎችን እንኳን በየክልሉ፣ በየወረዳው ማከፋፈል ካልቻለ - ግዴታ ለትንሹም ለትልቁም ከየክፍለሃገሩ እየተመሙ ወደአዲስ አበባ መምጣት አለባቸው ማለት ነው? አንዲት ማሕተም ለማስመታት ከሥራ የቀናት ፈቃድ መውሰድ፣ የሆቴል እና የትራንስፖርት ወጪ ማድረግ - ፈጽሞ ፍትሐዊ አሰራር አይደለም፡፡ እዚህ ብቻ አይደለም፣ ‹ኢሚግሬሽንም›፣ ሌሎቹም መሰል ቢሮዎች ውስጥ ይህ ነገር መታረም አለበት፡፡ የፌዴራል መንግስቱ ሥራ ቢሆንም እንኳን ግዴታ አንድ ቦታ ተማክሎ መሰራት አለበት የሚል ሕግ የለም፣ ሊኖርም አይችልም፡፡ ስለዚህ ይሄ የመንግስታዊ ኪራይ ሰብሳቢነት ውጤት ነው ብዬ ደመደምኩ፡፡
“አሸባሪ” ፊልምም ይታገድ ጀመር
Saturday, June 9th, 2012ከዚህ ቀደም ‹የባሕር በር› በሚል ርዕስ በጥላሁን ጉግሳ የተሰራው የአማርኛ ፊልም በኢቴቪ ማስታወቂያው እንዳይታይ ታግዶ የአንድ ሰሞን አወዛጋቢ አጀንዳ ለመሆን በቅቶ ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የፊልሙ ዋና ገጸ ባሕሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ‹‹በእኔ እምነት፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ አንድ ቀን መልሰው አንድ ይሆናሉ፡፡›› ብለው መናገራቸው ነው፡፡ ያለምንም ማጋነን መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ አንድ ሆነው ከሚያዩ ከሚና ሕንጻ ላይ ዓይናቸው እያየ ቁልቁል ቢወረወሩ ይመርጣሉ፡፡ የሻዕቢያን የጫካ ውለታን ኤርትራን እንደተገነጠለች በማስቀረት ነው የሚያረጋግጡት፡፡ እንዴያውም አንዳንዴ ሳስበው መለስ ከስልጣን መውረድ የማይፈልጉት ለሻዕቢያ እንደርሳቸው ታማኝ የሚሆን ኢትዮጵያዊ መተካት ስለሚከብዳቸው ይመስለኛል፡፡
ወደቀደመው ነገራችን ስንመለስ ትላንት አርብ፣ በኤድናሞል ማቲ መልቲፕሌክስ ሲኒማ መታየት የጀመረው ‘The Dictator’ የተሰኘ ፊልም እንዳይታይ ታገደየሚል ዜና አነበብኩ፡፡ መውጣቱን ከሰማሁ ጀምሮ በጉጉት ስጠብቀው የነበረው ይህ እምባና ሳቅ ያዘለ (comedy satire) ፊልም ሦስት ቀን እንኳን እንዳይታይ በመደረጉ ለእሁዴ ሳይደርስልኝ ቀርቷል፡፡ ግን ለምን የሚለው ጥያቄ አጭር ግምቴን እንደሚከተለው አስቀምጣለሁ፡፡
በባሮን ኮኸን በገዛ ፊልሙ መሪ ተዋናይ የሆነበት ይህ ስላቃዊ ፊልም የጋዳፊ እና የሳዳም ሁሴን ድቅያ የሆነ አምባገነነዋ ገዢ ሆኖ የሚጫወት ገጸ ባሕሪ ፈጥሯል፡፡ ከፊልሙ ቅኝቶች ላይ ለማንበብ እንደሞከርኩት በርካታ የአምባገነኖች ባሕርያት የተሰገሰጉበት ይህ ፊልም፣ ከአንድ ወዳጄ እንደሰማሁት ደግሞ የኛውን ‹መለስ› ዜናዊን ቁልጭ የሚመስሉ በርካታ ትዕይንቶች አሉት፡፡ እናም የፊልሙ መታገድ ዋነኛ ምክንያት ከዚህ ውጪ ምን ሊሆን ይችላል?
በርካታ ጋዜጦች ታገዱ፣ ሰላማዊ ሰልፍ ታገደ፣ በመንግስት ያልተወደዱ ዘፈኖች በመንግስት ይዞታ ስር ባሉ ሬዲዮ ጣቢያዎች እንዳይተላለፉ ታገዱ፣ አንዳንድ መጽሃፍቶች ሜጋ መጽሃፍት ማከፋፈያ ውስጥ እንዳይገቡ ታገዱ፣ የተቃዋሚ ድረገጾችና ጦማሮች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይነበቡ ታገዱ፣ የጀርመንና የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮዎች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይሰሙ ታገዱ፣ …. ታገዱ፣ ታገዱ፡፡
10ሩ የድህረ-ግንቦት 20 ኪሳራዎች
Wednesday, May 30th, 2012አቶ መለስና ጓደኞቻቸው አምባገነን ስርአትን ለመቀየር ነፍጥ አንስተው፣ በጭቆና ላለመኖር ሲሉ በህይወታቸው ተወራርደዋል፤ አላማቸውን ለማሳካት ገድለዋል ሞተዋል፡፡ ድል ቀንቷቸው የዛሬ 21 አመት አምባገነኑን የደርግ ስርአት አስወግደው ምኒሊክ ቤተመንግስት ሲገቡ ኢትዮጵያን በለውጥ ጎዳና ሊመሩ፣ ዴሞክራሲን በማስፈን በሀገሪቱ አዲስ ታሪክ እንዲያኖሩ የሚያስችል ዕድል ነበራቸው ፡፡ አምባገነኑን የኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያምን ደርግ ካስወገዱ በኋላ ግን አምባገነኑን የአቶ መለስ ዜናዊን ስርአት ከማስቀመጥ ባለፈ በግንቦት 20 ድል ታሪክ ሊሰሩ አልቻሉም፡፡
ያ ሁሉ መስዋዕትነት የተከፈለበት፣ በተለያዩ ጎራዎች የተሰለፉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት ዶጋ አመድ አድርጎ ግንቦት 20, 1983 ዓ.ም የተቋጨው ጦርነት አንድን ወታደራዊ አምባገነን መሪ በኃይል በማስወገድ የይምሰል ዴሞክራሲያዊ ስርአትን(pseudo democracy) የገነባ ሲቪል አምባገነን መተካት የተወሰነ ቡድንን ወይም ግለሰቦችን ፖለቲካዊ የበላይነት(hegemony) ለማረጋገጥ ያለመ እንዳልነበር በትጥቅ ትግሉ ተሳታፊ የነበሩ ግለሰቦች ያረጋግጣሉ፡፡ የህወሓት ነባር ታጋይና የቀድሞው የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገብሩ አስራት ሰኔ 19,2002 ለወጣችው አዲስ ፕሬስ ጋዜጣ አሞራው ስለተባለ የህወሓት ጀግና ታጋይ ሲያስረዱ ‹‹አሞራው ቀና ብሎ እየተደረገና እየሆነ ያለውን ነገር ቢያይ ይገርመው ነበር›› ካሉ በኋላ የአቶ መለስ መንግስት በአሞራውና በሌሎች ታጋይ ሰማእታት መስዋዕትነት ስልጣን እየነገደ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ህወሓት/ኢህአዴግ ስልጣን የያዘበት ተመሳሳይ ወቅት አምባገነናዊ ኮሚኒስት ስርአቶችን በማስወገድ ዴሞክራሲያዊ ግንባታ የጀመሩት የምስራቅ አውሮፓ ሀገራት በአጭር ጊዜ ውስጥ አመርቂ ለውጥ ማምጣታቸውን Carleton University፡ Institute of European and Russian Studies አጥኚ የሆኑት ድራጎስ ፖፓ (DRAGOS POPA) ሮሜኒያንና ቡልጋሪያን ነቅሰው ያመላክታሉ፡፡ የባልካን ሀገራትም ሁለት አስርት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ እምርታ ማምጣታቸውን The democratic transformation of the Balkans በሚል ርዕስ የቀረበው የሮዛ ባልፈር እና ኮሪና ስትራቱላት (Rosa Balfour and Corina Stratulat) ጥናት ያመላክታል፡፡ ጥናቱ የባልካን ሀገራት በአጭር ጊዜያት ውስጥ ሶስት መሰረታዊ ለውጦችን ማስመዝገባቸውን ያስረዳል‹‹ከጦርነት ወደ ሰላም፣ ከኮሚኒዝም የእዝ ኢኮኖሚ ወደ ነፃ ገበያ እንዲሁም ከአንድ ፓርቲ አገዛዝ ወደ መድብለ ዴሞክራሲ ተለውጠዋል›› ይላል፡፡ በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ ባለፉት 21 አመታት የታየውና አሁንም ያለው ነባራዊ ሁኔታ ለግንቦት 20 ድል የወጣውን የህይወት ግብር እና በድሉ ማግስት የተገኘውን የግንቦት 20 ፍሬ ስናወራርድ ውጤቱ ኪሳራን የሚያመላክት ነው፡፡
ይህ ጽሁፍ በህወሓት በስተመጨረሻም በህወሓት/ኢህአዴግ መሪነት ለ17 አመታት በተደረገው ፅኑ ትግል የተገኘው የግንቦት 20 ድል ሊያመጣ ያልቻላቸውን አስር አንኳር ነጥቦች ይፈትሻል፡፡
፩
ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን መገንባት ያለመቻሉ
ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ በሂደት ውጤት የሚያስገኝ ጥረት ነው፡፡ ጤናማ ሂደት እስከኖረ ድረስም የግንባታው እድገት አይቀሬ ውጤት ነው፡፡ ዛሬ በዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታቸው ምሳሌ የሚሆኑት ሀገራት በቅፅበታዊ ለውጥ/ክስተት ካሉበት ደረጃ ላይ አልደረሱም፡፡ ከ1983 ግንቦት 20 ወዲህ ኢትዮጵያ በዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ሂደት ውስጥ መግባቷን የአቶ መለስ መንግስት ሲናገር ይደመጣል፡፡ ሆኖም ሂደቱ አንዴ ወደ ፊት ሌላ ጊዜ ደግሞ ወደኋላ ሲንሸራተት ቆይቶ በአሁኑ ጊዜ ተኮላሽቷል፡፡ ምርጫ ቦርድም ሆነ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ወይም የእንባ ጠባቂ ተቋም በኢህአዴግ ‹‹ሞተር›› የሚንቀሳቀሱ፣ በመንግስት ሳምባ የሚተነፍሱ በህዝብ አመኔታ የሌላቸው የስም ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ናቸው፡፡ የአቶ መለስ መንግስት በ21 አመት የስልጣን ዘመኑ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ለመገንባት አለመድፈሩ/አለመፈለጉ የድህረ ግንቦት 20 ኪሳራ ማሳያነው፡፡
፪
ከተፅዕኖ ነፃ የሆኑ የፍትህ አካላትን መገንባት አለመቻሉ
በኢትዮጵያ ለህግ የሚሰጠው ቦታ ከፍ ያለ ነው፡፡ ህግን የማክበር እና ለፍትህ አካላት አመቴታና ክብር የሚሰጥ ባህላዊ መሠረትም አለ፡፡ ይህ ባህላዊና ሞራላዊ መሠረት በተለይ ከደርግ መንግስት ስልጣን መያዝ በኋላ የመሸርሸር ምልክት ማሳየት ጀመረ፡፡ “የደርግ ሹማምንት በፍትህ አካላት ላይ የተለያዩ ጫናዎችን በማሳደር ፍርድን ለማጣመም ጥረት ያደርጉ ነበር” የሚሉት አቶ አለማየሁ አዱኛ በህግ አማካሪና ጠበቃነት ይሰራሉ፡፡ አቶ አለማየሁ እንደሚሉት ከመንግስት አካላት ጫና ቢኖርም የፍትህ አካላቱ ከነበራቸው ጠንካራ መሠረት አንፃር ነፃነታቸውን ያስደፈሩ አልነበሩም፡፡ ይህ ሁኔታ የደርግ ባለስልጣናት ለሚወስዷቸው እርምጃዎች ህጋዊ ከለላ ከመስጠት ይልቅ ግልጽ ፖለቲካዊ እርምጃ ይወስዱ ነበር፡፡ የደርግ አምባገነንነትና ጨፍጫፊነት አጠያያቂ ባይሆንም እነዚህ ህገወጥ እርምጃዎች የሚወስዱት በማናለብኝነት በተወጠሩ ባለስልጣናት “የጐበዝ አለቆች” እንጂ በፍትህ አካላት አልነበረም፡፡ ህወሓት /ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ግን ሁሉንም ተቋማት በአንድ የፖለቲካ አስተሳሰብ የማጥመድ አባዜ የፍትህ አካላትንም አልተወም፡፡ ፖሊስ፣ አቃቤ ህግ እና ፍርድ ቤቶች ከመጋረጃ ጀርባ በኢህአዴግ ባለስልጣናት የሚሰጡ ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን “በህግ” ስም ያስተላልፋሉ፡፡ ኢህአዴግ እራሱ ያፀደቀውን ህገ መንግስት በመጣሱ የፍትህ አካላትን ነፃነት ከመጋፋት ባለፈም፣ ፖለቲካዊ ተፅዕኖ የሚያደርሱ አፋኝና ኢፍትሀዊ ‹‹ህጐችንም›› በማፅደቅ ፍትህንና ህጋዊ ስርዓትን የሚያዋርዱ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ ግንቦት 20 ነፃ የፍትህ አካላት እንዲለመልሙ አለማድረጉ ሌላው የድህረ-ግንቦት 20 ኪሳራ ነው፡፡
፫
ብሔራዊ ስሜትን መናዱ (ኢትዮጵያዊነትን ማኮሰሱ)
ብሔራዊ ስሜት መናድ ለአንድ ሀገርና በውስጧ ለሚኖሩ ዜጎች ደህንነት አደጋን ይደቅናል፡፡ የኢህአዴግ መንግስት ኢትዮጵያዊነት የሚንዱና ጎጣዊ ማንነት ላይ የሚያተኩሩ ፖለቲካዊ እሳቤዎችን በህዝቡ ውስጥ እንዲዘሩና እንዲስፋፉ ያላሰለሰ ጥረት አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያን ጥንተ ታሪክ በመካድ ህዝቦች በግድ የተጠፈሩባት ‹‹የአጤ ምኒሊክ ፍጡር›› አድርገው ያስቀምጧታል፡፡ ይህ አስተሳሰብ ህወሓት ስልጣን ላይ ሳይወጣ ያራምደው እንደ ነበር ግልፅ ነው፤(የኤርትራ ህዝብ ትግል ከየት ወዴት 1979ን ልብ ይሏል) የአስተሳሰቡ መነሻ የኢትዮጵያን ጥንተ ታሪክ በመካድ ቢነሳም መጨረሻው የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል የሚል ክፉ ድምዳሜ ላይ የሚያደርስ ነው፡፡ ይህ የፀረ ኢትዮጵያዊነት ውጤት በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን መጀመሪያ ኤርትራን በማስገንጠል ተጀምሮ በ1987ቱ ህገ-መንግስት አንቀፅ 39ን በማካተት መሰረቱን አጠናከረ፡፡ ከኤርትራ መገንጠል በኋላ በተነሳው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጦስ ከሁለቱም ሀገራት ‹‹ወደ ሀገራቸው› የተሸኙ ዜጎችን ሰቆቃ ለተመለከተ፣ የተሳሰረን ህዝብ ‹‹የራስን እድል በራስ በመወሰን›› ሰበብ መነጠል የሚያመጣውን ስነልቦናዊ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጦስ ለማገናዘብ አይቸግረውም፡፡ ሆኖም ኢህአዴግ አደገኛ አስተሳሰቡን ለማረቅ የሚፈልግ አይመስልም፡፡
የአቶ መለስ መንግስት አራምዳለሁ ለሚለው ‹‹የልማታዊ መንግስት›› ፍልስፍና ብሔራዊ ስሜት የጎላ ሚና እንዳለው ምሁራን የተለያዩ ሀገራትን ልምድ በመጥቀስ ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ተፋልሶ ውስጥ የሚዋትተው የአቶ መለስ ኢህአዴግ ከኢትዮጵያዊነት ጋር መላተሙ ሌላው የድህረ-ግንቦት 20 ክስረት አመላካች ነው፡፡
፬
የብሔር ጥያቄ ምላሽ አለማግኘቱ
በ1960ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ ይስተጋቡ ከነበሩ የፖለቲካ ጥያቄዎች ውስጥ የብሔር ጥያቄ አንደኛው ነው፡፡ ኢህአዴግ ይህን ጥያቄ እንደ ሰንደቅ አንስቶ የብሔረሰቦችን እኩልነት እንዳረጋገጠ ይናገራል፡፡ የብሔር እኩልነት የግንቦት 20 ፍሬ እንደሆነም ደግሞ ደጋግሞ ለማሳመን ጥሯል፡፡ ሆኖም ከግንቦት 20 በኋላም ተገፋን ተጨቆንን የሚሉ የብሔር ቡድኖች በየምክንያቱ ብቅ ብቅ ማለት ቀጥለዋል፡፡ ኢህአዴግ በቋንቋ ከመማርና ከመዳኘት ባለፈ ብሄረሰቦች ራሳቸውን የምር እንዲያስተዳድሩ የሚፈልግ አይመስልም፡፡ አቶ ገብሩ አስራትም በኢትዮጵያ የብሔረሰቦች መብት እንዳልተከበረ ያምናሉ፡፡ አቶ ገብሩ ‹‹ህወሓት ከጋርዮሽ አመራር ወደ አንድ ሰው ብቸኛ መሪነት›› በሚለው ፅሁፋቸው ብሔሮች በአካባቢያቸው ጉዳይ ፖለቲካዊ ስልጣን ኖሯቸው እንደማይወስኑና በአካባቢያቸው ኢኮኖሚያዊ ልማት ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ያስረዳሉ፡፡ ለዚህም ይመስላል ከህወሓትና ከፌደራል መንግስት የሚወከሉ አካላት በክልል አስተዳደሮች ውስጥ ጣልቃ ገብ ተሳትፎ ያላቸው፡፡ በፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ በቁጥር 39 የተሰራጨው መረጃ እንዳመለከተው ‹‹ኦሮሚያ የምትተዳደረው በክልሉ ም/ቤት በተመረጡት አቶ አለማየሁ አቶምሳ ሳይሆን ከህወሓት በተመደቡት አቶ ገ/ተንሳይ ወ/ትንሳይ ነው፡፡›› ይኸው መረጃ አያይዞም ቀደም ሲልም ሰለሞን ጢሞ የተባሉ የህወሓት ሰው ኦሮሚያን ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው ያስተዳድሯት እንደ ነበር አስታውሷል፡፡ የሌሎች ክልሎች ብሄረሰቦችም ራስን በራስ የማስተዳደር ዕድል እንደሌላቸው ይነገራል፡፡
በብሄር ብሄረሰቦች ቀን ብቻ በጭፈራ የሚታየውና በስርአቱ ተቺዎች ዘንድ ‹‹የብሔር ብሄረሰቦች መብት እስከ መጨፈር›› የሚል ስላቅ የሚገለፀው ‹‹እኩልነት›› በፖለቲካው መድረክ አይታይም፡፡ ይህ ሁኔታ ተጨማሪ የድህረ-ግንቦት 20 ኪሳራ ሆኗል፡፡
፭
ፍትሀዊ ያልሆነ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት መስፈን (corny capitalism)
የአቶ መለስ መንግስት በ21 አመት የስልጣን ቆይታው ሊያሳካ ካልቻላቸው መሰረታዊ የህዝብ ጥቅሞች መካከል ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አለማረጋገጡ ዋንኛው ነው፡፡ መንግስት በኢኮኖሚ ውስጥ የሚያደርገው የበዛ ጣልቃ ገብነት፣ ኢትዮጵያውያን በኢኮኖሚው ውስጥ ፍትሀዊ ጥቅም እንዲያገኙ የሚያግዝ እንደሆነ ሹማምንቱ በተለያዩ መድረኮች ከመግለፅ አይታክቱም፡፡ መንግስትም የሚያንቀሳቅሳቸውን ግዙፍ ድርጅቶችም ከእጁ ለማውጣት አይፈልግም፡፡ የበታፈነ ደረጃ የተፈቀደው ‹‹የነፃ ገበያ ስርአት›› ሁሉንም የንግድ ህብረተሰብ ክፍል እኩል ተጠቃሚ አላደረገም፡፡
ኢህአዴግ ራሱ ያወጣውን ህግ ተላልፎ የፈለፈላቸው፣ በቢሊየን የሚቆጠር ካፒታል የሚያንቀሳቅሱትን የገዢው ፓርቲ ንብረት የሆኑ ኩባንያዎችን በማጠናከር እንዲሁም ከመንግስቱ ጋር ቅርበት ያላቸው ግለሰቦች የተለየ ጥቅም የሚያገኙበት ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች ይህንን ስርአት ኮርኒ ካፒታሊዝም (crony capitalism) በሚል ይጠሩታል፡፡ ኮርኒ ካፒታሊዝም የሀገሪቱ ሀብት ከስርአቱ ጋር ስምም ወደ ሆኑ ጥቂት ባለፀጋ ግለሰቦች እንዲፈስ የሚያደርግ ስርአት ነው፡፡ ኢትዮጵያ እየገነባች ያለችው ኢኮኖሚም ሆነ ቁሳዊ ልማት ጥቂቶችን ብቻ ተጠቃሚ ማድረጉ የድህረ-ግንቦት 20 ኪሳራዎች መሀከል የሚጠቀስ ከመሆኑም በላይ አስተዳደሩ ለተዘፈቀበት ሙስና ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ነው፡፡
፮
የሙስና መስፋፋት
ፕሮፌሰር ሰይድ ሐሰን በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ትንታኔዎችን በማቅረብ ይታወቃሉ፡፡ እኚህ ምሁር ሙስና ኢትዮጵያ ውስጥ ስር የሰደደ ስርአት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ በቅርቡ ‹‹ሙስና ኡ! ኡ! እሪ! እሪ!›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሁፍ ዓለም ባንክ ባደረገው ጥናት ኢትዮጵያ ውስጥ ሙስና አደገኛ ስርአነት ወደ መሆን መሸጋገሩን ያብራራሉ፡፡ ፍርድ ቤት፣ ፖሊስ፣ ጉምሩክና የገቢዎች ባለስልጣን፣ የወረዳ አስተዳደርና ማዘጋጃ ቤቶች ሙስና በእጅጉ የተንሰራፋባቸው ናቸው፡፡
የህወሓት አንጋፋ መሪ የነበሩት አቶ ስብሀት ነጋም ሙስና በሀገሪቱ አደገኛ ደረጃ ላይ መገኘቱ እንዳሳሰባቸው በይፋ መግለፃቸውና አቶ መለስም የመንግስት አካላትም በአደገኛ ሙስና መዘፈቃቸውን ማመናቸው ሙስና ከድህረ-ግንቦት 20 ኪሳራዎች መሀከል የሚጠቀስ ሆኗል፡፡
፯
ስርአቱን የሚተቹ አካላትን ማፈን
የህወሓት/ኢህአዴግ ታጋዮች ደርግን ከተዋጉበት ምክንያት አንዱ የደርግ ተቃውሞን የማፈን እርማጃ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ታጋዮቹ ደርግን አስወግደው ሌላ ‹‹ደርግ›› መተካታቸውን የሚያስረዱ በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ ስርአቱን የሚተቹ አካላትን የአቶ መለስ መንግስት ማሰር የጀመረው በቅርቡ ባይሆንም፣ በአረብ ሀገራት የተከሰተውን መነሳሳት ተከትሎ የተቃውሞ ፖለቲካ አመራሮችንና ጋዜጠኞችን ‹‹በሽብር›› ሰበብ ቃሊቲ አውርዷል፡፡ በይፋም ሆነ በኢመደበኛ ወጎች መንግስትን መተቸት የሚያስጠይቅበት ደረጃ በመድረስ ላይ ይገኛል፡፡
መንግስት ስርአቱን የሚተቹ አካላትን ለማሸማቀቅ የሚጠቀምባቸው መንገዶች ሰላማዊ ትግልን የሚያደናቅፉ ከመሆናቸውም በላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ብሶትና ተቃውሞ ወደ ግብታዊ አብዮት የመምራት ውጤትም ሊያስከትል ይችላል፡፡ በሰላማዊ ትግል ተስፋ ቆርጠው መሳሪያ ያነሱ ቡድኖችን ያበራከተው ይህ አካሄድ፣ ከኢህአዴግ ጋር ልዩነት ያላቸው የፖለቲካ ቡድኖች በሰላማዊ ትግል እንዲሳተፉ አለማበረታታቱ የአቶ መለስ ስርአት የድህረ-ግንቦት 20 ክስረት አንድ አካል ነው፡፡
፰
ነፃ የሲቪክ ማህበራት አለመጠናከራቸው
ነፃ ማህበራት በአንድ ሀገር ላይ ዴሞክራሲ እንዲያብብ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ፡፡ሚካኤል ባራቶን (Michael Bratton) ‹‹CIVIL SOCIETY AND POLITICAL TRANSITION IN AFRICA›› በሚል ፅሁፋቸው ከቀዝቃዛው ጦርነት መጠናቀቅ በኋላ ነፃ ማህበራት በዴሞክራሲ ግንባታ ያላቸው ሚና እየተጠናከረ እንደመጣ ያስረዳሉ፡፡ አያይዘውም ነፃ ማህበራት ይህን አበርክቷቸውን እንዲወጡ የመንግስትን ኃይል የሚዘውሩ አካላት ፈቃደኝነት አስፈላጊ መሆኑን አበክረው ይገልፃሉ፡፡ የነፃ ማህበራት አበርክቶ በኢትዮጵያ ከመዳከም አልፎ የተዳፈነ ይመስላል፡፡
ኢህአዴግ ከ1997 በፊት በአንፃራዊ መለኪያ ንቁ ተሳትፎ የነበራቸውን ማህበራት፣ ከድህረ 97 በኋላ ነፃነታቸውን የሚጋፋና ህልውናቸውን የሚፈታተን ህግ በማፅደቅ አልፈስፍሷቸዋል፡፡ የማህበራቱን ነፃነት በመጋፋት የፓርቲውን ፖለቲካ የሚያራምዱ ግለሰቦችን በአመራር ደረጃ በማስረግ ጭምር ተሳትፏቸውን አዳፍኗል፡፡
መንግስት ነፃ ማህበራት የህዝቡን ዴሞክራሲያዊ ባህልና ግንዛቤ በማዳበር የሚያበረከረቱትን አስተዋፅኦ ከማበረታታት ይልቅ፣ ከዚምባቡዌ፣ ሲንጋፖርና ሩሲያ የተወሰዱ አደገኛ ልምዶችን የቃረመ አደገኛ የበጎ አድራጎትና የሲቪክ ድርጅቶች አዋጅ አፅድቋል፡፡ በዚህ ህግ ምክንያት የመስራት አቅማቸው የተሸመደመደ እና ወደ ሌላ ዘርፍ ስራቸውን የቀየሩ ማህበራት ቁጥር በርካታ ነው፡፡
ይህ ማህበራትን የማዳከምና ነፃነታቸውን የማሳጣት ስትራቴጂ በቀጥታ የህዝቡን የነፃነት የመደራጀት መብት የሚጋፋ ከመሆኑም በላይ ዴሞክራሲ የማይዋጥላቸው አምባገነን መንግስታት ተግባር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር 21 አመታትን በምኒሊክ ቤተመንግስት ያሳለፈው የአቶ መለስ መንግስት ነፃ ማህበራትን በስልት ማዳከሙ የድህረ-ግንቦት 20 ኪሳራዎች መካከል ይጠቀሳል፡፡
፱
የነፃ ፕሬስስ ሀሳብን የመግለፅ መብት አለመከበሩ
ኢህአዴግ ወደ ስልጣን እንደወጣ ከወሰዳቸው አበረታች እርምጃዎች ውስጥ የፕሬስና ሀሳብን የመግለፅ መብትን “መፍቀዱ” ነው፡፡ መንግስት ይህ መብት ህገመንግስታዊ እንዲሆን ቢያደርግም በተግባር ግን አፋኝ እርምጃዎችን ከጅምሩ መውሰዱ ነፃ ፕሬስ እንዳይዳብር እንቅፋት ሆኗል፡፡
የአንድ ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ መገለጫ የሆነው የፕሬስና ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት በኢትዮጵያ አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ መንግስት ላይ ትችት የሚያቀርቡ ጋዜጠኞች እና ሀሳባቸውን በይፋ የሚገልፁ ፖለቲከኞች መታሰር፤ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የአደባባይ ምሁራንን አርቋል፡፡
ሀሳባቸው የሚገልፁ ጋዜጠኞችና ተቺዎች ከእስር ጋር ተፋጠው ለመስራት ተገደዋል፡፡ ኢህአዴግ ያወጣቸው የፕሬስና የፀረ ሽብር አዋጆች ኢትዮጵያውያን ሀሳባቸውን በፕሬስ ውጤቶች እንዳይገልፁ የሚጠፍር ከመሆኑም በላይ በአንዳንድ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ መረጃዎችን እንዳያገኙ አግዷል፡፡ በተለይም ኢህአዴግ በቅርቡ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት በኩል ቅድመ ምርመራን ለመጀመር እንቅስቃሴ መጀመሩ ከላይ ያየናቸው የድህረ ግንቦት 20 ኪሳራዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሀገሪቱ የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ እንዲከስም አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲያብብ በሚረዱት የፕሬስ ውጤቶች አለማደግ ብሎም መመናመን የድህረ ግንቦት 20 ኪሳራ ሌላው ማሳያ ነው፡፡
፲
ሀገሪቱ በአንድ ጠቅላይ አምባገነን መሪ ስር መውደቋ
ጠቅላይ አምባገነንነት በአጭር ጊዜ የሚገነባ ሳይሆን ዴሞክራሲያዊ ስርአትን ከመገንባት የበለጠ ጊዜና ወጪ ይጠይቃል፡፡ ይህን አምባገነናዊ ስርአት ለመገንባት መንግስት በህዝቡ ሁሉን አቀፍ የህይወት ፈርጅ ውስጥ ቁጥጥር ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ በትምህርት ፣ በኢኮኖሚ ፣ ማህበራዊ፣ በባህልና ኪነጥበብ ውስጥ ፖለቲካዊ ቁጥጥር በማድረግ እንዲሁም ፖለቲካዊ እንነታቸውን በማጥመቅ አቶ መለስ ጠቅላይ አምባገነን መሆንን መርጠዋል፡፡
በ2002 ምርጫ 99.6 በመቶ በሆነ ውጤት ፓርላማውን የተቆጣጠረው የአቶ መለስ መንግስት አውራ ፓርቲ መሆኑን በመግለጽ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ተንኮታኩቶ ጠቅላይ አምባገነን ስርዓት መደላደሉን አብስሯል፡፡ ግንቦት 20 አቶ መለስን በኢትዮጵያ አንግሷል፡፡ በሀገሪቱ ላይ ብቸኛው አድራጊና ፈጣሪ አቶ መለስ ናቸው፡፡ ሙገሳቸውም ሆነ ወቀሳቸው ድጋፋቸውም ሆነ ተቃውሟቸው እንደ እግዜር ቃል ይታያል፡፡ ለግንቦት ሃያ የተከፈለው መስዋዕትነት አቶ መለስን የሀገሪቱን ቁንጮ ከማድረግ ያለፈ ውጤት ያመጣ አይመስልም፡፡ የድህረ ግንቦት 20 ኪሳራዎች የኢትዮጵያ ህዝብ ከህወሓት/ኢህአዴግ ነፃ የሚወጣውን የድል ቀን እንዲጠብቅ ሳያስገድዱት የሚቀር አይመስልም፡፡















