Author Archive

አቶ ጁነዲን ሳዶ ከኦሕዴድ ሥራ አስፈጻሚነት ተወገዱ

Saturday, October 6th, 2012

(Reporter) — የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሩ አቶ ጁነዲን ሳዶ ከኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ሥራ አስፈጻሚነት ተነስተው በተራ አባልነት እንዲቀጥሉ ድርጅቱ መወሰኑን ምንጮች ለሪፖርተር አስታወቁ፡፡

የኦሕዴድ ሥራ አስፈጻሚ ከመስከረም 21 ቀን እስከ መስከረም 24 ቀን 2005 ዓ.ም. ባካሄደው ዓመታዊ ጉባዔው ላይ፣ በሟች እናታቸው መኖሪያ ላይ እያሠሩት ካለው መስጅድ ጋር በተያያዘ የተገመገሙት ሚኒስትር ጁነዲን፣ ከፍተኛ የዲሲፕሊን ጉድለት መፈጸማቸውንና ካሉበት ኃላፊነትና ሥልጣን አኳያ ተገቢ ያልሆነ ሥራ መሥራታቸው በዋናነት እንደተገመገሙበት ምንጮቹ አረጋግጠዋል፡፡

አቶ ጁነዲን በእናታቸው የኑዛዜ ቃል መሠረት በመኖሪያ ቤታቸው ላይ መስጅድ ለማስገንባት፣ በሚኒስትርነታቸው ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ ለመስጅዱ ማስጨረሻ ከሳዑዲ ዓረቢያ ኤምባሲ ዕርዳታ በመጠየቃቸው፣ የመስጅዱ የመጀመሪያ ደረጃ ምርቃት ሲደረግ በኢትዮጵያ የሳዑዲ ዓረቢያ አምባሳደር ተገኝተው 500 ቅዱስ ቁርአንና 50 ሺሕ ብር ዕርዳታ መስጠታቸውን ራሳቸው አቶ ጁነዲን በጻፉት ደብዳቤ አረጋግጠዋል፡፡

ባለቤታቸው አምባሳደሩ የሰጡትን 50 ሺሕ ብር ለመቀበል ኤምባሲ ሄደው ተቀብለው ሲወጡ፣ ለሽብር ተግባር የሚውል ገንዘብ ተቀብለዋል በሚል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡ አቶ ጁነዲን በጻፉት ደብዳቤ ግን ባለቤታቸው የተከበሩ የቤት እመቤት መሆናቸውን ገልጸው ነበር፡፡

በዚህም ምክንያት በኦሕዴድ ሥራ አስፈጻሚ ስበሰባ ላይ በተደረገው ግምገማ፣ ከሥራ አስፈጻሚነት ተነስተው በተራ አባልነት እንዲቀጥሉ መወሰኑን ምንጮቹ አረጋግጠዋል፡፡

ድርጅቱ የ2004 ዓ.ም. በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸምን አንድ በአንድ የገመገመ መሆኑን የገለጹት ምንጮች፣ በፀጥታው ዘርፍ በተለይ ቦረና አካባቢ ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ላይ ድክመት መታየቱንና ወደፊት ሊታሰብበት እንደሚገባ ሰፊ ውይይት እንደተደረገበት ተናግረዋል፡፡

በሪፖርቱ ላይ የታዩትንና ድክመት ያለባቸውን አንዳንድ የሥራ ዘርፎች በቀጣይ እንዲስተካከሉ ሐሳብ ተሰጥቶ ጉባዔው መጠናቀቁ ታወቋል፡፡ በድርጅቱ ውስጥ ያሉ አመራሮች እንዳሉ እንዲቀጥሉ ከማድረግ ውጭ ከኃላፊነቱ የተነሳም ሆነ የተሾመ አመራር እንደሌለ ታውቋል፡፡

በሑመራና በሱዳን ግዛት በእርሻ ሠራተኞች መካከል በተፈጠረ ግጭት በርካታ ሰዎች ሞቱ

Saturday, August 18th, 2012

(The Reporter) — በትግራይ ክልል በሑመራ ጠረፍና በሱዳን ግዛት ውስጥ በአረም ሥራ ላይ በተሰማሩ ሠራተኞች መካከል በተቀሰቀሰ አካባቢን መሠረት ያደረገ ግጭት ምክንያት በርካታ ሰዎች መሞታቸው ታወቀ፡፡ በአካባቢው የሚገኙ የሪፖርተር ምንጮች እንደጠቆሙት፣ ከሐምሌ አጋማሽ ጀምሮ ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በመጡ ሠራተኞች መካካል በተከሰተው ግጭት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ጉዳትም ደርሷል፡፡ ምንጮች እንደሚሉት፣ ከዚህ በፊትም እንዲህ ዓይነት ግጭት አልፎ አልፎ የሚከሰት ሲሆን፣ አሁን በተለይ በጎንደርና በወሎ ተወላጆች መካከል የተፈጠረው ግጭት አካባቢያዊ ስሜትን እየያዘ መጥቷል፡፡

ግጭቱ የሚከሰተው በመቧደን መሆኑን፣ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ያለው ችግር በፀጥታ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት መረጋጋት ቢችልም፣ በሱዳን ግዛት ውስጥ ባሉት ሠራተኞች መካከል የተፈጠረው ግጭት ግን እየቀጠለ መሆኑ ተስምቷል፡፡

እንደ ምንጮች ጥቆማ፣ ከሐምሌ 18 ቀን 2004 ዓ.ም. ሃያ አራት ሰዎች በግጭቱ ሕይወታቸው ሲያልፍ፣ ነሐሴ 7 ቀን 2004 ዓ.ም. ላይ በተፈጠረው ተመሳሳይ ግጭት ደግሞ ቁጥራቸው ወደ አሥራ አንድ የሚጠጋ ሰዎቸ ሞተዋል፡፡ በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ሁኔታውን በመጣራት ላይ ነው፡፡ የማይካራ ቀበሌ (ሑመራ ወረዳ) የፀጥታ ኃላፊ የሆኑት አቶ ሳሙኤል ተፈሪ ለሪፖርተር በስልክ በሰጡት ማብራሪያ፣ እንዲህ ዓይነት ግጭት የተለመደ ቢሆንም ባለፈው ዓመት በሽማግሌዎች አማካይነት ለማስታረቅ በተደረገው ጥረት ችግሩ ተወግዶ ነበር፡፡ አቶ ሳሙኤል የሟቾቹን ቁጥር ምንጮች ከተናገሩት በታች መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ ነሐሴ 7 ቀን በተፈጠረው ግጭት የስምንት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፣ ከዚያ በፊት ከአሥራ አንድ በላይ ሰዎች መሞታቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ግጭቱ የሚከሰተው በአብዛኛው በሠራተኞች መካከል መሆኑን፣ በወሎና በጎንደር ተወላጆች መካከል አካባቢን መሠረት ያደረገ እየሆነ መምጣቱ አምነዋል፡፡ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ያለው ችግር በመከላከያ፣ በፖሊስና በሚሊሽያ ኃይሎች አማካይነት በቁጥጥር መዋሉን የሚገልጹት ኃላፊው፣ አስቸጋሪ የሆነባቸው ሱዳን ግዛት ተሻግረው በመሥራት ላይ በሚገኙ ዜጎች መካከል ያለው ግጭት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ሱዳን ግዛት ውስጥ ገብተን ማረጋጋት ተቸግረናል፤›› ብለዋል፡፡

ኃላፊው ግጭቱን በማስነሳት ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሠራተኞችን ቁጥር ባይገልጹም፣ 400 ያህል ሰዎች በማይካራ ቀበሌ በሚገኘው ዋልታ አዳራሽ ውስጥ ታሰሩ መባሉን ስህተት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ምንጮች እንደሚሉት ግን በዋልታ አዳራሽ ከ400 በላይ ሠራተኞች ለሳምንታት የታሰሩ ሲሆን፣ በአማራ ክልል በተጠርጣሪዎች የትውልድ አካባቢ ኃላፊዎች ጋር በተደረ ምክክር ወደ ትውልድ ስፍራቸው ተወስደው ጉዳያቸው እንዲጣራ እየተደረገ ነው፡፡

በሑመራ አካባቢ የጥጥ፣ የሰሊጥና የማሽላ ሰፊ ኢንቨስትመንት ሲኖር፣ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ሠራተኞች በአረምና በተጓዳኝ በሌላ የእርሻ ሥራዎች ተሰማርተው እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በገርጂ የኃይል ማስተላለፊያ የሚገኝ ትራንስፎርመር በድንገት ፈነዳ

Saturday, August 11th, 2012

(The Reporter) — ባለፈው ዓርብ ከምሽቱ አራት ሰዓት ገደማ ገርጂ መብራት ኃይል አካባቢ የሚገኘው ወረገኑ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ጣቢያ ውስጥ ከሚገኙት ትራንስፎርመሮች አንዱ፣ ባልታወቀ ምክንያት ፈንድቶ መቃጠሉንና የፍንዳታው መንስዔ በመጣራት ላይ መሆኑ ተገለጸ፡፡ ፍንዳታው በደረሰበት ሰዓት የኦሊምፒክ የሴቶች 5,000 ሜትር የሩጫ ውድድርን ለማየት በጉጉት በመጠበቅ ላይ በነበሩት የአካባቢ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ድንጋጤ የፈጠረ ሲሆን፣ ፍንዳታውን ተከትሎም በጣቢያው የነበሩ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ሠራተኞች በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች ከቤታቸው ወጥተው እንዲቆዩ ማስጠንቀቂያ መስጠታቸው ታውቋል፡፡

የፍንዳታው መንስዔ በመጣራት ላይ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ምስክር ነጋሽ ገልጸዋል፡፡ ትራንስፎርመሩ ያረጀ በመሆኑ ከኃይል ጭነት ብዛት፣ ከማርጀት ጋር ወይም ከተፈጥሮ ጋር የተያያዘ መሆኑን ለማጣራት የኮርፖሬሽኑ ባለሙያዎች በምርመራ ላይ እንደሚገኙና ውጤቱም በዛሬው ዕለት እንደሚታወቅ አብራርተዋል፡፡

በጣቢያው ውስጥ ያሉት የተቀሩት ትራንስፎርመሮች ያረጁ በመሆናቸው የኃይል ማስተላለፊያ ጣቢያውንና በአካባቢው የሚገኙትን ነዋሪዎች ከተመሳሳይ አደጋ ለመጠበቅ ምን ዋስትና አለ? በሚል ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ኮርፖሬሽኑ በአገር አቀፍ ደረጃ የተለያየ ቮልቴጅ መጠን ያላቸው ትራንስፎርመሮችን የቅድመ ጥገና ክትትል እያደረገላቸው መሆኑን ምላሽ የሰጡት ኃላፊው፣ አቅማቸውንም የማሳደግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አደጋው ከተከሰተ በኋላ ቅድሚያ የሚሰጠው በተቃጠለው ትራንስፎርመር ምክንያት ኃይል የተቋረጠባቸው አካባቢዎች ኃይል የሚያገኙበትን አማራጭ ማፈላለግ እንደሆነ የገለጹት አቶ ምስክር፣ ከዚህ ትራንስፎርመር ኃይል የሚተላለፍላቸው አካባቢዎች ግማሾቹ ከሌላ ትራንስፎርመር ኃይል ማግኘት መቻላቸውንና ቀሪዎቹም እስከ ትናንት ምሽት ድረስ እንደሚያገኙ አስታውቀዋል፡፡

በትራንስፎርመሩ መቃጠል ምክንያት የኤሌክትሪክ ኃይል ያጡት አካባቢዎች ሲኤምሲ፣ ገርጂ፣ የረር፣ መሪ፣ መገናኛ በከፊል፣ ቦሌና ባምቢስ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ ይሁንና ከፍንዳታው በፊትም ቢሆን በተለይ በየረር፣ በመብራት ኃይል፣ በገርጂና በሌሎች አካባቢዎች ካለፉት ሳምንታት ጀምሮ ኃይል በተከታታይ በመጥፋት ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የደረሰውን አደጋ ለማየት የውኃና የኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑና የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ምሕረት ደበበ በሥፍራው በትናንትናው ዕለት መገኘታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች እንዲሁም ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ ከተሞች ባለፉት ሳምንታት በተለያዩ ቀናት የኃይል መቋረጥ እየተከሰተ ሲሆን፣ የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች በያዝነው ሳምንት ለተከታታይ ቀናት የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎትን በዘመናዊ፣ በቀልጣፋና በአስተማማኝ መንገድ ለማቅረብ የሚቻልበትን መንገድ በመምከር ላይ መቆየታቸውን አቶ ምስክር አያይዘው ገልጸዋል፡፡

ሆኖም የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙትን አሮጌ ትራንስፎርመሮች ለመተካት የሚገዙ አዲስ ትራንስፎርማሮች በብዛት ጥራታቸውን ያልጠበቁ ናቸው፡፡ በመሆኑም ከዕቃ ግዥ ጋር በተያያዘ ብልሹ አሠራሮች በግልጽ እየታዩ እንደሆነና ሠራተኞችም ይህን እንዲያጋልጡ ስብሰባው በተካሄደባቸው ቀናት የጦፈ ክርክር መነሳቱን አስረድተዋል፡፡

የስልጣን ሽግግር በተመለከተ የወያኔ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ክፍተት አለበት ተባለ

Saturday, July 21st, 2012

አቶ ዮሐንስ ወልደ ገብርኤል፣ የሕግ ባለሙያ

አቶ ዮሐንስ ወልደ ገብርኤል አዲስ አበባ በቅሎ ቤት አካባቢ ነው የተወለዱት፡፡  የመጀመርያ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የጨረሱት እዚህ አዲስ አበባ ነው፡፡

በ1978 ዓ.ም. አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ገብተው በ1980 ዓ.ም. በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ በሥራው ዓለም በመጀመሪያ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሥር በሲዳሞና በዝዋይ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ዓቃቤ ሕግነት ሠርተዋል፡፡ በመቀጠል ከ1985 ዓ.ም. በኋላ በልዩ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት በልዩ ዓቃቤ ሕግና በረዳት የልዩ ዓቃቤ ሕግ ሹምነት ሠርተዋል፡፡ በሥነ ምግባርና በፀረ ሙስና ኮሚሽን በዓቃቤ ሕግነትና በኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለሥልጣን የሕግ መምርያ ኃላፊና የጉምሩክ ዓቃቤ ሕግ ሆነው የሠሩ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ለ15 ዓመታት ያህል በመንግሥት ተቋማት ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች አገልግለዋል፡፡ ሰለሞን ጐሹ የአስቸኳይ ጊዜ የፖለቲካ ሥልጣን የአመራር ክፍተትን በተመለከተ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የአስቸኳይ ጊዜ የፖለቲካ ሥልጣን የአመራር ክፍተቶችን በተመለከተ በኢትዮጵያ ታሪክ የምናገኛቸው እውነታዎች ምን ያሳያሉ?

አቶ ዮሐንስ፡- የአገር መሪዎች ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ እነሱ ለተወሰኑ ጊዜያትም ቢሆን ከቢሮአቸው ሲለዩ የሚያስተዳድሩት ሕዝብ፣ የሚመሩት መንግሥት፣ ሠራዊት፣ አገር ዕጣ ፈንታው ምንድን ነው? የሚለው ሊያስጨንቀን ይገባል፡፡ በአገራችን ታሪክ የሥልጣን አወራረስ ሁልጊዜ የተረጋጋ አይደለም፡፡ ከጥንት ጀምሮ ነገሥታት በሚሞቱበት ጊዜ ሁሌም የሚከሰቱ ኹከቶች ይኖራሉ፡፡ እንደ ጥንቱ አሠራር ከሆነ ብዙ ጊዜ የሥልጣን ሽኩቻ ስለሚኖር የሥልጣን ሽኩቻውን ለማስወገድ የነገሥታት ልጆችና ልዑላን በሙሉ ይሰበሰቡና ወህኒ አምባ ወይም እስር ቤት እንዲገቡ ይደረግ ነበር፡፡ የደርግ መንግሥት ሊመጣ ሲል የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ከሥልጣን እንደተገረሰሰ በርካታ ልዑላንና የንጉሡ ቤተሰቦች ሕፃናቱ ሳይቀሩ ወደ እስር ቤት እንዲገቡ ተደርጎ ነበር፡፡ የአገሪቱ ታሪክ በዚህ ጉዳይ ላይ ትልቅ አሻራ ጥሎ ማለፉ አይካድም፡፡ ደርግ ይህን ነገር ያደረገው የሥልጣን ሽኩቻው እንዳይመጣ ለማድረግ ነው ወይ? ለሚለው ጥያቄ መልስ መስጠት አስቸጋሪ ነው፡፡ ደርግ ዕርምጃውን ለመውሰድ የአገሪቱን ተሞክሮ እንደ ምሳሌ ወስዶ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለ፡፡ በ1999 ዓ.ም. እስር ቤት እያለሁኝ የቀጠሮ እስረኞች ወደ ፍርድ ቤት ልንሄድ አውቶቡስ ላይ በምንሳፈርበት ወቅት አንድ በወንጀል ተከሶ የታሰረ ነጋዴ ከደርግ ሦስት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ሲቀላለድ እሰማው ነበር፡፡ ለመሆኑ የደርግ ወራሽ ማነው? የሚል ጥያቄ ያነሳላቸዋል፡፡ ከአንዱ የደርግ አባል የተሰጠው ምላሽ “አይ ደርግ የወላድ መካን ነው፤ ወራሽ የለውም፤” የሚል ነበር፡፡ ይኼ ምልልስ ትልቅ የሕገ መንግሥት ጉዳይን ነው የሚያነሳው፡፡ ደርግ የራሱ የሆነ ሕገ መንግሥት ነበረው፡፡ ሥልጣኑ የተወረሰው ግን በሕገ መንግሥቱ መሠረት አልነበረም፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ የፖለቲካ ሥልጣን አመራርን በተመለከተ ያስቀመጠው ድንጋጌ የለም የሚል ክርክር አለ፡፡

አቶ ዮሐንስ፡- አሁን ያለው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የፕሬዚዳንቱንም ሆነ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሥልጣንን በተመለከተ አንድ አጋጣሚ ቢፈጠርና ሥልጣናቸውንና ኃላፊነታቸውን በሙሉ ጤንነትና በሙሉ ብቃት መፈጸም የማያስችላቸው ሁኔታ ቢከሰት፣ ማን ተክቷቸው ይሠራል ለሚለው ጥያቄ ግልጽ ምላሽ የሚሰጥ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ፖለቲካውን ወደ ጎን ትተነው ሕጋዊ የሆነ በቂ መልስ የለም፡፡ በነጠረና በተስተካከለ ሁኔታ ሕገ መንግሥቱ ላይ ተቀምጧል ብዬ አላምንም፡፡

ሪፖርተር፡- ክፍተቱ ለፕሬዚዳንቱም የሚሠራ ቢሆንም ሕገ መንግሥቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰጠው ሠፊ ስልጣን አኳያ ክፍተቱ አደገኛ ነው የሚል ስጋት ያላቸው አሉ፡፡

አቶ ዮሐንስ፡- አደገኛነቱ ምንም የሚያጠራጥርና የሚያከራክር አይደለም፡፡ የውጭዎቹን አገሮች ሕገ መንግሥቶች ትተን እዚሁ አገራችን በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የነበሩ ሁለት ሕገ መንግሥቶችን ብንመለከት፣ በ1923 ዓ.ም. እና በ1948 ዓ.ም. የወጡት ሕገ መንግሥቶች እንዲህ አይነት ክፍተቶችን ሊፈጠሩ እንደሚችሉ፣ በተለይ በከፍተኛ አስፈጻሚነት ያሉ ሰዎች ከሥራም ብዛትና እረፍት ከማጣት አኳያ፣ ሥራው በተፈጥሮው አድካሚ በመሆኑ የመታመም፣ አቅም የማነስና አቅም የማጣት ችግሮች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ከግምት ውስጥ በማስገባት ምን ዓይነት መፍትሔ መወሰድ እንዳለበት በግልጽ አስቀምጠዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግሮች ባደጉና ከፍተኛ የሕገ መንግሥት ታሪክና ደረጃ አላቸው ብለን በምንወስዳቸው እንደ አሜሪካ ባሉ አገሮች ለብዙ ጊዜ ሲፈታተኑዋቸው ነበር፡፡

ለምሳሌ አሜሪካኖች በጣም ቆይተው ነው እ.ኤ.አ. በ1967 ለዚህ ችግር መፍትሔ የሰጡት፡፡ ይህም የተደረገው በሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ አማካይነት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች በተለያዩ አገሮች የተቀረፁት ችግሮቹ በሰው ልጅ ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ መሆናቸውን በማመን ብቻ አይደለም፡፡ ጉዳቱ የአገር ስለሆነ ነው፡፡ ሕገ መንግሥት የመንግሥት አወቃቀርን፣ የሥልጣን ሽግግርን፣ የሥልጣን አወራረስን፣ ወዘተ. የሚደነግግ የበላይ ሕግ እንደመሆኑ መጠን፣ እነዚህ ጉዳዮች ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ሊደነገጉ የሚገባውም በሕገ መንግሥት ብቻ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በብዙ አገሮች ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ወይም ምክትል ፕሬዚዳንት አደጋዎች ሲከሰቱ ወይም ዋናው አስፈጻሚ ሥራውን ለመሥራት በማይችልበት ጊዜ ተክተው እንዲሠሩ የሚያስችሉ ድንጋጌዎች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ሚና ለመጫወት የሚያስችለው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ አለ?

አቶ ዮሐንስ፡- በፖርላሜንታሪያዊ ሥርዓት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት ደግሞ ፕሬዚዳንቱ ዋና አስፈጻሚ ነው፡፡ ዋና አስፈጻሚው ሊታመም፣ አቅም ሊያጣ ወይም ሥራ መሥራት የማይችልበት ሁኔታ ሊያጋጥመው፣ እንዲሁም በሞት ሊለይ ይችላል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲከሰቱ ማን ነው ተክቶ ዋነኛውን ኃላፊነት የሚወስደው? አሜሪካ ለምሳሌ ለምክትል ፕሬዚዳንቱ ሥልጣኑን ሰጥታለች፡፡ በሌሎች አገሮች ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ለፓርላማው አፈ ጉባዔ ሥልጣን የሚሰጡ አገሮችም አሉ፡፡

በኢትዮጵያ ይህን ዓይነቱን ክስተት የሚያስተናግድ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ የለንም፡፡ ዋናው አስፈጻሚ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚያግዝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አለ፡፡ በሕገ መንግሥቱ ተዘርዝሮ የተቀመጠ ሥልጣን ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አልተቀመጠም፡፡ ይልቁንም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተለይቶ የተሰጠውን ሥራ እንደሚያከናውን ነው ሕገ መንግሥቱ የሚገልጸው፡፡ በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማይኖርበት ጊዜ እሱን ተክቶ እንደሚሠራም ተደንግጓል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተለይቶ የተሰጠው ሥራ ካለ እሱን ይሠራል፡፡ ተጠሪነቱም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣኑን በውክልና ለይቶ ባልሰጠበትና  ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሌለበት ሁኔታ እንዴት ተክቶ ሊሠራ እንደሚችል ግልጽ አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጊዜያዊ ወይም ቋሚ ሕመም ቢያጋጥመው ማን ተክቶት ይሠራል ለሚለው ጥያቄ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 75 ክፍተት አለው፡፡

በተጨማሪም የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሻሿም ልክ እንደ ሌሎቹ ሚኒስትሮች ነው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት ነው የሚሾመው፡፡ እንዲያውም የሌሎች ሚኒስትሮች ቢሮዎች ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍ ያለ ኃላፊነት ይሰጣቸዋል፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሙሉ ጊዜ ሥራ እንዲኖረው በማሰብ ሌሎች ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶችን እንዲመራ የሚደረገው፡፡ የመጀመርያው መከላከያ ሚኒስትር፣ ሁለተኛው የግብርናና የገጠር ልማት ሚኒስትር፣ ሦስተኛውና የአሁኑ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደግሞ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን እንዲመሩ የተደረገውም ለዚህ ይመስላል፡፡

ሪፖርተር፡- የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ የሚዋቀረውም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ የፖለቲካ ሥልጣን አመራር ክፍተት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢፈጠር የምክር ቤቱ ሚና ምንድን ነው? ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ህልውና ውጭ ምክር ቤቱ ሥራውን መቀጠል ይችላል?

አቶ ዮሐንስ፡- የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ሥልጣን ተክቶ ሊሠራ የሚችልበት የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታዎች ይኖራሉ፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ምን ዓይነት እንደሆነ በሕገ መንግሥቱ ተካቷል፡፡ አሁን የምንነጋገርበት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም የፕሬዚዳንቱ መታመም፣ አቅም ማጣት፣ መደበኛ ሥራን ለመሥራት አለመቻል፣ በሞት መለየት፣ ወዘተ. በዚያ ውስጥ የሚካተቱ አይደሉም፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደ አንድ አካል የጠቅላይ ሚኒስትሩን ኃላፊነት ተክቶ መሥራት ስለመቻሉ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ እንደዚያ አይታየኝም፡፡ ሊሆን የሚችለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ ላይ ካለው አብዛኛውን መቀመጫ ከያዘው ፓርቲ በጊዜያዊነት አሊያም በቋሚነት ለመተካት፣ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመምረጥ፣ ኃላፊነቱን ለማሸከምና ሥልጣን ለመስጠት መሥራት ይኖርበታል፡፡

ሆኖም የተሻለው አማራጭ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ማድረግ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ማሻሻያ ሲደረግለት ፋታ የማይሰጡ አጣዳፊ ጉዳዮችንም ማስተናገድ ይቻላል፡፡ በመሀል ላይ የሚኖሩ ክፍተቶች ሁልጊዜም ኢ-ሕገ መንግሥታዊ የሥልጣን ሽግግርን ሊጋብዙ ይችላሉ፡፡ በአንቀጽ 9(3) ላይ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ የሥልጣን ሽግግር በከፍተኛ ሁኔታ ተከልክሏል፡፡ ነገር ግን ሕገ መንግሥቱ ሊሸፍናቸው በማይችሉ ክፍተቶች ላይ የሚከሰቱ የሥልጣን ሽግግሮች መፍቻ ቁልፍ የለውም፡፡ ብዙ አገሮች እንደዚህ ዓይነት ችግር ገጥሟቸዋል፡፡ መፍትሔ የሚሆኑ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችንም እንዲቀርፁ አስገድዷቸዋል፡፡ አሜሪካ እ.ኤ.አ. በ1967 ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ከማድረጓ በፊት የዚህ ዓይነት ድርጊቶችን በተደጋጋሚ አስተናግዳለች፡፡ ለምሳሌ በአንድ ወቅት ለአንድ ወር ብቻ የሠራ ፕሬዚዳንቷ በአጋጣሚ በሞት ተለይቷል፡፡ ምክትል ፕሬዚዳንቱ የቀረውን ጊዜ በፕሬዚዳንትነት ቢጨርሰውም የሥልጣን ሽግግሩ ሕገ መንግሥታዊ አልነበረም፡፡ ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ከሞቱ በኋላ ነው ችግሩ መፍትሔ እንዲሰጠው ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያው የተደረገው፡፡ በፖላንድ ባለፈው ዓመት በተከሰተው የአውሮፕላን አደጋ 96 ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ ሲያልቁ፣ አገሪቷ በፍጥነት ሌላ መንግሥት በመመሥረት ሥራው የቀጠለው የፖላንድ ሕገ መንግሥት ችግሩን የሚቀርፍ ድንጋጌ ስለነበረው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ፓርላሜንታሪያዊ ሥርዓት የምትከተል አገር በመሆኗ ፓርላማው የሚፈጠሩ ክፍተቶችን ለመሸፈን ይችላል የሚል አስተያየትም ይሰነዘራል፡፡

አቶ ዮሐንስ፡- ፓርላማው እንኳን በግልጽ ያልተሰጠውን ሥልጣን ቀርቶ ዋነኛ  የሆነውን አስፈጻሚውን የመቆጣጠር ሥልጣኑን እኮ በውክልና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አሳልፎ የሰጠ የመንግሥት አካል ነው፡፡ አዋጅ ቁጥር 691/2002 በአንቀጽ 34 ላይ የአስፈጻሚ አካላትን ተቋማት ማቀላቀል፣ ማፍረስ፣ ለሁለት መክፈል፣ ተጠሪነታቸውን መቀያየር ሥራ ከፓርላማው ወደ አስፈጻሚ አካልም ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት በውክልና እንዲዘዋወር አድርጓል፡፡ አቅሙ ቢኖረው ለምን አሳልፎ ይሰጣል? ለምክር ቤቱ ከተሰጠ ያው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሰጠ ማለት ነው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሌላ ጠቅላይ ሚኒስትር የመምረጥ ሥልጣን ሊኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን ሥራውን በአግባቡ እየሠራ ያለና ክፍተቶችን በሚገባ የሚሸፍን ተቋም ስለመሆኑ ግን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡

ሪፖርተር፡- ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ሳይደረግ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ችግር ቢፈጠርና ምርጫ ሳይደረግ ጊዜ ቢቆጠር ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውጭ እንደ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔና የመሳሰሉ አካላት በጊዜያዊነት ሥልጣን ሊይዙ ይችላሉ የሚል አስተያየት አለ፡፡

አቶ ዮሐንስ፡- የትኛው ባለሥልጣን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተክቶ የመሥራት ብቃት አለው የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል መረጃ የለኝም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ግን በግልጽ ለአንዳቸውም ሥልጣን አይሰጥም፡፡

ሪፖርተር፡- ኢሕአዴግ ከአራት ዘውግ ተኮር ፓርቲዎች የተውጣጣ ግንባር ነው፡፡ ክፍተቱ የተለያዩ ዘውግ ተኮር የሥልጣን ፉክክርን አይጋብዝም ወይ? ለዚህስ በብሔር ላይ የተመረኮዘው የፌዴራል ሥርዓት ክልሎችን ወደ ፉክክሩ እንዲገቡ አያደርግም ወይ?

አቶ ዮሐንስ፡- በብሔር ላይ የተመረኮዘውን የፌዴራል ሥርዓት እንደ ችግር አላየውም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በቋንቋው፣ በሃይማኖቱ፣ በጦርነቱ፣ በሰላሙ፣ በደስታው፣ በፍቅሩ፣ ወዘተ. በጣም የተሳሳረና የተገመደ ሕዝብ ነው፡፡ ይኼ የአመለካከት ጉዳይ ነው፡፡ በደቡብም፣ በምሥራቅም፣ በምዕራብም፣ በሰሜንም ያለው ሕዝብ ለበርካታ ሺሕ ዓመታት መስተጋብር የፈጠረ ስለሆነ፣ ያለውና የነበረው ፖለቲካዊ አሰላለፍ በሕዝቡ ውህደትና አንድነት ላይ ችግር ያመጣል ብዬ አላስብም፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገልግሎት ዘመናቸውን ለመጨረስ ባይችሉና ሌላ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመምረጥ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቢገደድ፣ ሁለተኛው ምርጫ ከመጀመርያው የተለየ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ አለ?

አቶ ዮሐንስ፡- ገዥው ፓርቲ በሕገ መንግሥቱ በተገለጸው መሠረት ከፍተኛ መቀመጫ አለው፡፡ ፓርላማው የሚወስነው ውሳኔ የፓርቲውን አቋም የሚያንፀባርቅ ነው የሚሆነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሕገ መንግሥቱ ኢሕአዴግ ካለው ፍፁም የበላይነት አኳያ አልተፈተነም የሚሉ ኃይሎች አሉ፡፡ ውሳኔዎች በድርድር እንዲያልቁ የሚያደርጉ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢኖሩ አንቀጽ 75ን ጨምሮ በርካታ የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች ይፈተኑ ነበር በሚለው አስተያየት ይስማማሉ?

አቶ ዮሐንስ፡- የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ላለፉት 17 ዓመታት የቆየ ነው፡፡ በአንፃራዊነት አስቀድሞ ከነበረው የደርግ ሕገ መንግሥት በተሻለ የተረጋጋ ሥርዓት ፈጥሯል፡፡ የተቋቋሙት  ተቋማት ሥር እንዲይዙ ለማድረግ በቂ ጊዜ ነበረው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ተፈትኗል አልተፈተነም ለማለት ያሉትን ድንጋጌዎች መመርመር ይጠይቃል፡፡ ከሥልጣን ሽግግርና አወራረስ ጋር በተያያዘ ግን በእኔ እምነት የሌሎች ፖርቲዎች ተሳትፎ ይብዛም ይነስም በፓርላማ ደረጃ ነበር፡፡ ገዥውን ፓርቲ መገዳደር የሚችል ቁጥር ይዘው ግን አያውቁም፡፡ ሕገ መንግሥቱ አልተፈተነም ለማለት በጣም ይከብዳል፡፡ አሁን እየተነጋገርን ያለው ጉዳይ ግን እስካሁን እንደ ችግር ታይቶ ውይይት አልተደረገበትም፡፡ እናም አንቀጽ 75 አልተፈተነም ሊባል ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ሁሉም የቀደሙት የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥቶች እንዲረቀቁ ካስቻሉዋቸው መንግሥታት የተሻለ ዕድሜ አልነበራቸውም፡፡ የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ከኢሕአዴግ ዘመን የመሻገርና በሌሎች መንግሥታት ሥራ ላይ የመዋል ዕድል አለው?

አቶ ዮሐንስ፡- ሁሉም ሕገ መንግሥት የመንግሥትን አደረጃጀትንና የሥልጣን አወራረስን ማዕከል ተደርጎ ነው የሚወጣው በዋናነት፡፡ በ1948 ዓ.ም የወጣው የተሻሻለው የአፄ ኃይለ ሥላሴ ሕገ መንግሥት አንድ የሆነ አደጋ ቢፈጠር ወራሾቹ እነማን እንደሆኑ በዝርዝር የሚተነትን ድንጋጌ ነበረው፡፡ ደርግ ይህን ድንጋጌ አግዶት ነበር፡፡ በሕገ መንግሥቱ ወራሽ ተደርገው የተቀመጡት ልዑል አልጋ ወራሽ ሥልጣኑን እስሚይዙ ድረስ (በወቅቱ ታመው ስለነበር ሥልጣን መያዝ የሚችሉበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ በተጨማሪም ውጭ አገር ነበር የነበሩት) ሥልጣን መያዙን በመጀመሪያ  ደንግጎ ነበር፡፡ በኋላ ላይ ያው ይህንንም ድንጋጌ ሽሮታል፡፡ ሕገ መንግሥት የአገርን ተጨባጭ ሁኔታ፣ የሕዝቡን ሁኔታ፣ ትስስር፣ አኗኗር፣ ወግ፣ ባህል፣ ልማድ፣ ታሪክ፣ ወዘተ. አገናዝቦ መውጣት ይኖርበታል፡፡  ይኼንን ያገናዘበ ሕገ መንግሥት ከሕዝቡና ከአገሪቱ ጋር ዘላቂ ነው የሚሆነው፡፡ ከዚህ ጋር ተገናዝቦ ያልውጣ ሕገ መንግሥት ዘላቂነት ላይኖረው ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ይፋ በሆነው የመንግሥት አቋም የኢፌድሪ ሕገ መንግሥት እስካሁን ምንም ዓይነት ማሻሻያ አልተደረገበትም፡፡ ምሁራን በእርግጥ በሕገ መንግሥት ማሻሻያነት የሚጠቅሷቸው ምሳሌዎች አሉ፡፡ ለምሳሌም ከብሔራዊ ሕዝብ ቆጠራ፣ ከግብር ሕግ፣ ከሕገ  መንግሥት ቀን ጋር የተያያዙትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ገዢው ፓርቲ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይን ለምንድን ነው የሚፈራው?

አቶ ዮሐንስ፡- ሕገ መንግሥት አገርና ሕዝብን ለማስተዳደር የሚቀረፅ ሰነድ ነው፡፡ ትልቅ ሰነድ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰነዶች የሕዝቡን ታሪክ፣ ወግ፣ ባህል፣ እምነትና ልማድ በሙሉ አካተው አገሪቱ  የምትመራበት ዋነኛ ትልቁ ሰነድ ነው፡፡ ይኼን የሕግ ሰነድ በየጊዜው የሕዝቡንና የአካባቢውን ተጨባጭ ሁኔታ በማገናዘብ መለወጥና ማስተካከል የማይቻል ከሆነ ዕጣ ፈንታው አደገኛ ነው የሚሆነው፡፡ ሕገ መንግሥት ማሻሻል እጅግ አስቸጋሪና ከበድ ያለ ዕርምጃ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም እንደ ሌሎች ሕጎች ለማሻሻል ቀላል አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል የሚያስፈልጉ ዕርምጃዎች፣ ድምጾች፣ ውሳኔዎች እንደ ሌሎች የበታች ሕጎች አይደሉም፡፡ በዚህም ምክንያት በጣም አስጨናቂ ሊሆን ይችላል፡፡ ቢሆንም ግን መሻሻል በሚያስፈልግበት ሁኔታ፣ ጊዜና ወቅት መሻሻል ደግሞ ይኖርበታል፡፡ ይኼ ጥያቄ የሕግ የበላይነት ጥያቄ ነው፡፡ አስፈላጊዎቹን ማስተካከያዎች ማድረግና ዝግጁ ሆኖ ማቅረብ ካልቻለ ውጤቱ አስቸጋሪ ነው  የሚሆነው፡፡

የኢፌድሪ ሕገ መንግሥት ከወጣ በኋላ እንዳልከው ሙከራዎች ተደርገዋል እንጂ በተጨባጭ የተከናወነ  የሕገ መንግሥት ማሻሻያ አልነበረም፡፡ ውሳኔ ለመስጠት የሚወስደው ጊዜ ውስብስብነትና አስቸጋሪነት ሊሆን ይችላል የሕገ መንግሥት  ማሻሻያ እንዳይደረግ የሚያደርገው፡፡ ዞሮ ዞሮ ሌላ አማራጭ ዘዴ የለም፡፡ ሕገ መንግሥት ሳይሻሻል በአማራጭ የሚከናውን ተግባር በሕገ መንግሥቱ መስተካካል፣ መደንገግና መከናወን ያለበት ትልቅ የአገር ጉዳይ ከሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ውጪ በሌሎች ሕግጋት ማስተካከል የሚቻል አይደለም የሚሆነው፡፡ ይኼ የሕጎችንና የሥልጣንን እርከን የሚያፋልስ ነው የሚሆነው፡፡ በሌሎችም አገሮች የዚህ ዓይነት አስጨናቂ ሁኔታዎች ቢፈጠሩም ዞሮ ዞሮ ግን ማሻሻል በሚገባው ጊዜ ተገቢው ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ እንዲሻሻል  የተደረጉባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ በዚህ ሕገ መንግሥት ላይ የጨመረ ወይም የቀነሰ ተብሎ ልክ እንደ ወንጌል ወይም እንደ ቁርዓን የሚነገር ሰነድ አይደለም፡፡ የሕግ ሰነድ ነው፡፡ ሕዝብና አገር የሚተዳደርበት ነው፡፡ የሃይማኖት ድርሳን አይደለም፡፡ ተግባራዊ የሚሆን፣ የሚፈጸምና ሌሎችንም ሕጎች የሚገዛ ሕግ ስለሆነ መስተካከል ባለበት ጊዜ መስተካከል አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- አንቀጽ 75 አሁን ያለውን ይዘት ከመያዙ በፊት የሕገ መንግሥት አርቃቂው ቡድን ያቀረበው ሌላ አማራጭ አልነበረም?

አቶ ዮሐንስ፡- አንድ የተለየ ቡድን በዚህ መንገድ እንዲቀረጽ አድርጓል ብዬ አላምንም፡፡ ከአንዳንድ ሰዎች  ጋር የሐሳብ ልውውጥ ሳደርግ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማይኖሩበት ጊዜ›› የሚለው የአንቀጽ 75 ክፍል በሰፊው ሊተረጎም እንደሚገባ ይከራከራሉ፡፡ በመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን  ጨምሮ አንድ አደጋ ቢከሰት ሥራን በአግባቡ የማከናወን ሁኔታ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ አለው ብለው ያስረዳሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ወዲያው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተክቶ ይሠራል ሲሉም ይገልጻሉ፡፡ ለእኔ ይኼ አያሳምነኝም፡፡ ‹‹አለመኖር›› ጊዜያዊ አልያም ቋሚ ሊሆን ይችላል፡፡ ‹‹አለመኖር›› ያለውን ሕጋዊ ትርጉም ካየን ግን ቋሚ ወይም ዘላቂ ሥራ ማከናወን አለመቻልን የሚጨምር አይደለም፡፡ በአንድ ቦታና አካባቢ ከመኖርና ካለመኖር ጋር የተያያዘ ትርጉም ነው ያለው፡፡ ለአጭር ጊዜ ወይም ለረዥም ጊዜ በአንድ አካባቢ አለመኖርን የሚያሳይ ነው፡፡ በሕመም ሥራን መሥራት አለመቻል በዚህ ውስጥ የሚካተት አይደለም፡፡  በቦታው ባይኖርም ካለበት ቦታ  ከወከለው አካል ሪፖርት የሚቀበልና ውሳኔ የሚወስንን አካል ነው የሚመለከተው፡፡

ሪፖርተር፡- ከአስቸኳይ ጊዜ የፖለቲካ ሥልጣን አመራር ክፍተት ጋር በተያዘ ትልቁ ስጋት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሲቪል ተቋማት ብቻ ሳይሆን የወታደራዊ ኃይሉም አዛዥ የበላይ ናቸው፡፡ ጦር ኃይሉ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ  ከሥልጣን ሽግግር ጋር በተያያዘ ትልቅ ሚና ያለው ነው፡፡ ይህ ክፍተት ቀዳዳ ሊከፍት አይችልም?

አቶ ዮሐንስ፡- በፖለቲካው ማን አቅምና ጥንካሬ አለው? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ለጉዳዩ ቅርብ አይደለሁም፡፡ ያለ ጥርጥር ሠራዊትን የሚመራው ዋና አዛዥ  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ የመከላከያው ሠራዊት ሚኒስትር ሲቪል መሆን  እንዳለበት ሕገ መንግሥቱ አስቀምጧል፡፡ የዚህ ዓይነት ተፅዕኖዎችን ለመከላከል ይመስላል፡፡ ባልተለመደ ሁኔታ አንቀጽ 9(3) ላይ በሕገ መንግሥቱ ካለው የሥልጣን አወራረስ ውጭ የሚያዝ ሥልጣን ኢ-ሕገ መንግሥታዊ መሆኑን የደነገገው እነዚህን ስጋቶች ለማስወገድ ይመስለኛል፡፡ ቢያንስ በሕግ ደረጃ ይኼን እንደ ስጋት አላየውም፡፡

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹን ሲያስመርቅ ጋዜጠኞች ፎቶግራፍ እንዳያነሡ ከለከለ

Wednesday, July 4th, 2012

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊታችን ሰኔ 30 እና ሐምሌ 1 ቀን 2004 ዓ.ም. በሚያካሂደው የተማሪዎች የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የሕትመት ፎቶ ጋዜጠኞች አዳራሽ ተገኝተው ፎቶ ማንሣት እንደማይችሉ አስታወቀ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለሪፖርተር በላከው ደብዳቤ ‹‹የሕትመት ሚዲያ ጋዜጠኞች የፎቶግራፍ ካሜራ ማስገባት አይችሉም፡፡ አስፈላጊውን ፎቶግራፍ ከቢሮአችን መውሰድ የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን፤›› በማለት አዳራሽ ገብተው ፎቶ እንዳያነሱ ከልክሏል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ራሱ አስተምሮ ዕውቀት ያስጨበጣቸውን ፎቶ ጋዜጠኞች ወደ አዳራሽ እንዳይገቡ የከለከለበትን ምክንያት እንዲያብራሩልን የጠየቅናቸው የዩኒቨርሲቲው የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ነፃነት ይልማ እንደገለጹት፣ ከፀጥታ (ሴኩሪቲ) አንፃር ከምረቃው አዳራሽ ተማሪም፣ ወላጅም ሆነ የሕትመት ጋዜጠኛ የፎቶግራፍ ካሜራ ይዘው እንዳይገቡ ተወስኗል፡፡ ሁለተኛው ምክንያትም ሥነ ሥርዓቱን በፎቶግራፍ እንዲያስቀሩ ከተስማማቸው ድርጅቶች ጋር ሌላ ካሜራ እንዳይገባ ስምምነት ላይ በመድረሱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ያስተላለፈውን ውሳኔ በሚመለከት ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ ፎቶ ጋዜጠኞች ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል በሰጡት አስተያየት፣ ውሳኔው የተሳሳተና አግባብነት የሌለው መሆኑን ተናግረው፣ ‹‹ፎቶ ጋዜጠኛ ከሌሎቹ ታዳሚዎች ተለይቶ የፀጥታ ችግር ያስከትላል የሚለው እሳቤ እንዴት ሊመጣ እንደቻለ የሚያጠያይቅ ከመሆኑም በላይ፣ ራሱ አሠልጥኖ ለሙያው ብቁ ያደረጋቸውን ጋዜጠኞች መከልከሉ ተቋሙን የሚያስተች ነው፤›› ብለዋል፡፡

ብቁ ጋዜጠኞችን ለማፍራት ከሚሰጣቸው ኮርሶች አንዱ ፎቶ ጆርናሊዝም መሆኑ እየታወቀ፣ ለዓመታት አስተምሮ ያስመረቃቸውንና ብቃት ያላቸውን ፎቶ ጋዜጠኞች ‹‹አዳራሽ ገብታችሁ ታዳሚዎችን ፎቶ አታነሡም፤›› ብሎ መከልከሉ አስቂኝም አስገራሚም መሆኑን አባሉ ተናግረዋል፡፡ ማንነታቸውን ካልገለጻቸው ፎቶግራፍ አንሺዎች ጋር ውል ፈጽሞ፣ ‹‹እነሱ ያነሡትን ፎቶ ውሰዱ›› ማለቱ በተቋሙና በፎቶ አንሺዎቹ መካከል ያለው ግንኙነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት መሆኑንም አክለዋል፡፡

በሙያው ሲያሠለጥናቸው ከነበሩት ፎቶ ጋዜጠኞችን የሚያሳዝንና የዩኒቨርሲቲውን አስተዳደር የሚያስተች መሆኑንም በአስተያየታቸው ገልጸዋል፡፡

‹‹ፎቶ ጋዜጠኝነት ማለት በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ በመገኘት ፎቶ አንሥቶ ለታሪክ የሚያስተላልፍና በሰነድ የሚያስቀምጥ እንጂ፣ በችርቻሮ ሥራ ላይ የሚሰለፍ ባለሙያ ማለት አይደለም፤›› ያሉት አስተያየት ሰጪው፣ የሕትመት ፎቶ ጋዜጠኞች ለተቋማቸው ለሚያሳትሙት የሕትመት ውጤት ያላቸውን ጥበብ ተጠቅመው የሚወስዱትን ፎቶግራፍ፣ ከሚጽፉት ዜና ሐተታ ጋር በማዋሐድ ብቃታቸውን ለአንባብያን ማድረስ ሲገባቸው፣ ‹‹እኔ ያነሣሁትን ፎቶ ግዙኝ›› መባሉ ከ60 ዓመታት በላይ ካስቆጠረ ተቋም የማይጠበቅና ዕውቀት የማስገብየት አቅሙ ወዴት እያመራ መሆኑን እንደሚያሳይ አብራርተዋል፡፡

የቡና ኤክስፖርት ገቢ ከታሰበው በግማሽ ቀነሰ

Saturday, June 2nd, 2012

(ሪፖርተር) — የቡና ኤክስፖርት ገቢ በግማሽ ያህል በመቀነሱ ከኤክስፖርት ይገኛል ተብሎ የታቀደው አጠቃላይ ገቢ በአንድ ቢሊዮን ብር እንዲወርድ አደረገ፡፡ በ2004 ዓ.ም ይገኛል ተብሎ የታቀደው የኤክስፖርት ገቢ አራት ቢሊዮን ዶላር ቢሆንም፣ የበጀት ዓመቱ ሊጠናቀቅ አንድ ወር እየቀረው የተገኘው ገቢ ሦስት ቢሊዮን ዶላር አልሞላም፡፡

ነባር የቡና ነጋዴዎች የቡና ንግድ ዘንድሮ ከገባበት ችግር በሚቀጥለው ዓመት የማይወጣ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከምትታወቅበት የቡና ገበያ ውጭ ልትሆን ትችላለች ሲሉ ስጋታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ነጋዴዎች ምክንያታቸውን ሲያስረዱ፣ በዚህ ዓመት ለውጭ ገበያ የቀረቡት የቡና ዓይነቶች አንደ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጣቸውና እንደ ጥራት ደረጃቸው ሳይሆን በዘፈቀደ ነው ይላሉ፡፡ “የሐረር ቡና እየተባለ የሌላ አካባቢ ቡና ይላካል” ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የቡና ነጋዴ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በዚህ ምክንያትም በርካታ የውጭ ደንበኞች ቡና መግዛታቸውን አቁመዋል፡፡ በርካታ ነጋዴዎችም መንግሥት በሚያወጣቸው ተደጋጋሚ የማያሠሩ መመርያዎች ምክንያት ከገዥዎቻቸው ጋር የገቡትን ቃል ሊጠብቁ ስላልቻሉ ከገበያ መውጣታቸው እየተነገረ ነው፡፡

በዚህ ሁኔታ በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ከቡና ኤክስፖርት አገሪቱ ታገኛለች ተብሎ ከታቀደው 1.1 ቢሊዮን ዶላር የ2004 በጀት ዓመት ሊጠናቀቅ አንድ ወር እየቀረው ከቡና የወጭ ንግድ የተገኘው 505.6 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡

መንግሥት ከ32 ዓይነት የኤክስፖርት ምርቶች በዚህ የበጀት ዓመት አገኛለሁ ብሎ ያቀደው አራት ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ከንግድ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የበጀት ዓመቱ ሊጠናቀቅ አንድ ወር ብቻ እየቀረው ከኤክስፖርት የተገኘው ገቢ ሦስት ቢሊዮን ዶላር አልሞላም፡፡

መንግሥት ከበጀት ዓመቱ መጀመሪያ አንስቶ የቡና የኤክስፖርት ገቢን ለማሳደግ በርካታ መመርያዎችን ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ ከእነዚህም መካከል ቡናን እንደተለመደው በጆንያ ማሸግ ሳያስፈልግ በጥቅሉ በኮንቴይነር ታሽጎ እንዲላክና ገዥዎችም ይህንን ቡና በጎተራ (ሳይሎ) እንዲቀበሉ የወጣው መመርያ ይገኝበታል፡፡ ይህ መመርያ አስገዳጅ በመሆኑ በወቅቱ ነጋዴዎች ጠንከር ያለ ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ በወቅቱም መላክ የነበረባቸውን ቡና መላክ አልቻሉም፡፡ ከውጭ ተቀባዮቻቸው ጋር የፈጸሙት ውልም ችግር እንዳጋጠመው ሪፖርተር በወቅቱ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

እነዚህ ችግሮች ተደማምረው የቡና የኤክስፖርት ገበያ ችግሮች የተፈጠሩበት ሲሆን፣ መንግሥት ያቀደውን ያህል ገቢ አለማግኘቱ ደግሞ ንግድ ሚኒስቴርን እንዳበሳጨው ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ንግድ ሚኒስቴር በዚህ ጉዳይ ላይ የቡና ነጋዴዎችን ጠርቶ ጠንከር ያለ ተግሳጽ ለመስጠት እየተዘጋጀ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የቡና ነጋዴዎች እንደገለጹት፣ የንግድ ሚኒስቴርን የስብሰባ ጥሪ በጉጉት እየጠበቁ ነው፡፡ ነገር ግን ውይይቱ ጠንከር ያለና በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ቢያተኩር እንደሚመርጡ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ምክንያታቸውን ሲያስረዱ ቡናን በሚመለከት በዓለም ላይ ያለው የገበያ ሁኔታ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከሚያስቡት የተለየ ነው፡፡ መንግሥት የዘረጋው የቡና ሽያጭ መዋቅር ሊታሰብበት እንደሚገባም እነዚሁ ነጋዴዎች አበክረው አስገንዝበዋል፡፡

አል አሙዲ ከ1.3 ቢሊዮን ብር በላይ ለገዛቸው ካምፓኒዎች ክፍያ አልፈጸመም

Saturday, May 26th, 2012

(ሪፖርተር) — በሼክ መሐመድ አሊ አላሙዲና በሸሪኮቻቸው የተመዘገቡ ኩባንያዎች የአምስት የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ከ1.3 ቢሊዮን ብር በላይ ለመግዛት ያሸነፉት ጨረታ ከፀደቀላቸው በኋላ፣ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ቅድሚያ ክፍያ ስላልከፈሉና ርክክብ መፈጸም ባለመቻሉ፣ የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ የመጨረሻ ጥሪ ሊያደርግላቸው ነው፡፡

በሼክ መሐመድ አሊ አላሙዲና በሸሪኮቻቸው የተመዘገቡ ኩባንያዎች የአምስት የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ከ1.3 ቢሊዮን ብር በላይ ለመግዛት ያሸነፉት ጨረታ ከፀደቀላቸው በኋላ፣ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ቅድሚያ ክፍያ ስላልከፈሉና ርክክብ መፈጸም ባለመቻሉ፣ የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ የመጨረሻ ጥሪ ሊያደርግላቸው ነው፡፡ የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ለሽያጭ አቅርቧቸው ከነበሩ ስምንት ድርጅቶች፣ አምስቱን ለመግዛት ጨረታን ማሸነፋቸው የተገለጸላቸው የሼክ አላሙዲና የሸሪኮቻቸው ኩባንያዎች ድርጅቶቹን ለመረከብ ቅድሚያ ክፍያውን በአሥር ቀናት ውስጥ እንዲከፍሉ ተጠይቀው ነበር፡፡

የኤጀንሲው ቦርድ አምስቱን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከ1.3 ቢሊዮን ብር በላይ ለመግዛት ያቀረቡትን መጫረቻ ዋጋ ካፀደቀ በኋላ፣ አሸናፊ በሆኑበት መስፈርት መሠረት ቅድሚያ መክፈል የሚገባቸው ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ እንደነበር ታውቋል፡፡ ኩባንያዎቹ የመጀመሪያ ጥሪው ከደረሳቸው ከአንድ ወር ተኩል በላይ በመሆኑ፣ ቀጣዩ ዕርምጃ የአምስት ቀናት የጊዜ ገደብ የሚሰጥ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አምስቱን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ለመግዛት አሸናፊ መሆናቸው የተገለጻላቸው ሆራይዞን ፕላንቴሽን፣ ሳዑዲ ስታር፣ ናሽናል ማይኒግ ኮርፖሬሽንና ሚድሮክ ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ የግዥው ጨረታም ፀድቆላቸው የነበረው መጋቢት 12 ቀን 2004 ዓ.ም. ነው፡፡

በሼክ አል አሙዲና በሸሪኮቻቸው ባለቤትነት የተመዘገቡት እነዚህ ኩባንያዎች አሸናፊ ባደረጋቸው የጨረታ ሰነድ መሠረት በቅድሚያ ከ35 እስከ 100 በመቶ ክፍያ መፈጸም እንደነበረባቸው ታውቋል፡፡ ኩባንያዎቹ አሸናፊ በሆኑበት ጨረታ ሜድሮክ ኢትዮጵያ የላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪን ለመግዛት ከፀደቀለት 860 ሚሊዮን ብር ውስጥ 50 በመቶውን በተጠቀሰው ጊዜ መክፈል ነበረበት፡፡ ሆራይዘን ፕላንቴሽን የተባለው ሌላው ኩባንያም የጐጀብ እርሻንና የቡና ማዘጋጃ ማከማቻን በድምሩ በ263.8 ሚሊዮን ብር ለመግዛት ያቀረበው ዋጋ ቢፀድቅለትም፣ በተመሳሳይ መክፈል የሚገባውን ቅድሚያ ክፍያ እንዳልከፈለ ታውቋል፡፡

አቦቦ እርሻ ልማትን በ90 ሚሊዮን ብር መግዛት እንደሚችልና ቅድሚያ ክፍያውን 35 በመቶ በመክፈል ዕድል የተሰጠውም ሌላው የሼክ አል አሙዲና የሸሪካቸው ኩባንያ የሆነው ሳውዲ ስታር የቅድሚያ ክፍያ እንዲፈጽም ከኤጀንሲው ለቀረበለት ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም ተብሏል፡፡

የካቲት 15 ቀን 2004 ዓ.ም. ለጨረታ ከቀረቡት ስምንት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውስጥ አንዱ የሆነው ኢትዮ ማርብል ኢንተርፕራይዝ፣ በ110 ሚሊዮን ብር ለመግዛት የቀረበው ናሽናል ማይኒንግ ኮርፖሬሽን በጨረታው አሸናፊ ከሆነበት መስፈርት አንዱ ኩባንያውን ለመግዛት ያቀረበውን ዋጋ ሙሉ በሙሉ በአንድ ጊዜ ለመክፈል ቢሆንም፣ እንደሌሎቹ ኩባንያዎች ይህም ኩባንያ የሚፈለግበትን አለመክፈሉ ታውቋል፡፡

ሼክ አል አሙዲና ሸሪኮቻቸው አሸናፊ በሆኑበት ጨረታ ላይ ተሳታፊ በመሆን ቢልቱ ሲራሮ እርሻን በስድስት ሚሊዮን ዶላር ለመግዛት ተስማምቶ የነበረው ሞሬል አግሮ ኢንዱስትሪ የተባለው የአሜሪካ ኩባንያ፣ በተመሳሳይ ቅድመ ክፍያውን አለመክፈሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሞሬል አግሮ ኢንዱስትሪ አሸናፊ የሆነው ከስድስት ሚሊዮን ዶላር ውስጥ ሦስት ሚሊዮን ዶላሩን በቅድሚያ፣ ቀሪውን በአምስት ዓመት ለመክፈል ነበር፡፡ ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃም አሸናፊነታቸው ከተረጋገጠ በኋላ ቅድመ ክፍያውን መክፈል የነበረባቸው እነዚህ ኩባንያዎች ክፍያውን አለመፈጸማቸውን አረጋግጧል፡፡

ከዚህ በኋላ ኤጀንሲው ምን ዓይነት ዕርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ለቀረበው ጥያቄ፣ ከዚህ በኋላ የተወሰኑ ጊዜያት ተጠብቀው ክፍያውን ካልፈጸሙ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንደሚጻፍላቸው ከኤጀንሲው የተገኘ መረጃ ያስረዳል፡፡ በማስጠንቀቂያ ጥሪውም ክፍያውን ካልፈጸሙ ጨረታው እንደሚሰረዝባቸው ተገልጿል፡፡ ወደዚህ ዕርምጃ ከመገባቱ በፊት ግን በድጋሚ ጥያቄው የሚቀርብላቸው መሆኑን የሚያመለክተው ኤጀንሲው፣ ጨረታውን መሰረዝ ብቻ ሳይሆን ለጨረታ ማስከበሪያ ያስያዙት ሁለት በመቶ ቢድ ቦንድም ለመንግሥት ገቢ ይደረጋል፡፡ ሆኖም አንዳንዴ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ አሸናፊው ድርጅት ያቀረበው ዋጋ ከፍተኛ መሆኑ ከታመነበትና ክፍያውን ያልፈጸመበትን በቂ ምክንያት ካቀረበ የተወሰነ ጊዜ ሊሰጠው ይችላል ተብሏል፡፡ አራቱ ድርጅቶች ለጨረታ ማስከበሪያ ያስያዙት ገንዘብ በጥቅሉ ከስምንት ሚሊዮን ብር በላይ ይሆናል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከስምንቱ የልማት ድርጅቶች አንዱ የሆነው ቃሊቲ ብረታ ብረት ፋብሪካን ከ550 ሚሊዮን ብር በላይ ለመግዛት ብቸኛ ተወዳዳሪ የነበረው ፀሐይ ኢንዱስትሪስ ግን በቀረበው የመወዳደሪያ መስፈርት መሠረት የሚፈልግበትን ክፍያ በማጠናቀቅ ላይ ነው ተብሏል፡፡ ይህ ኩባንያ በወቅቱ አሸናፊ ሊሆን ቢችልም ሽያጩ የሚፈቀድለት ኩባንያው ክፍያውን የመፈጸም አቅሙ ይጣራ የሚል ውሳኔ ተላልፎበት እንደነበር ይታወሳል፡፡ በዚሁ የኤጀንሲው ውሳኔ መሠረት የድርጅቱ አቅም ተፈትሾ መክፈል እንደሚችል ማረጋገጫ በመገኘቱ፣ ክፍያውን በማጠናቀቅ ቃሊቲ ብረታ ብረትን ለመረከብ በዝግጅት ላይ መሆኑም ታውቋል፡፡ አቅም ላይኖረው ይችላል በሚል አሸናፊ የሆነበት ውጤት ሳይፀድቅለት የቀረው ፀሐይ ኢንዱስትሪ አቅም አላቸው ከሚባሉት ከሼክ አል አሙዲናና ሸሪኮቻቸው ኩባንያዎች በፊት ቃሊቲ ብረታ ብረትን ይረከባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ፀሐይ ኢንዱስትሪስ አሸናፊ ከሆነበት ዋጋ ውስጥ በቅድሚያ ለመክፈል የተስማማው 35 በመቶውን ወይም 157.3 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ቀሪውን 65 በመቶ በአምስት ዓመት ለመክፈል እንደሆነ ታውቋል፡፡ ፀሐይ ኢንዱስትሪስ አዲስ ኩባንያ ሲሆን የኩባንያው መሥራቾች ፀሐይ ባንክ በሚል መጠሪያ ባንክ ለማቋቋም አክሲዮን በማሰባሰብ ላይ እንዳሉ ባንክ ለማቋቋም የተከፈለ ካፒታል 500 ሚሊዮን ብር መሆን እንዳለበት ብሔራዊ ባንክ ያወጣው መመርያ አቅጣጫቸውን እንዲቀይሩ ያደረጋቸው ባለአክሲዮኖች ናቸው፡፡

አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ታስሮ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ትዕዛዝ ተላለፈ

Wednesday, May 23rd, 2012

አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 436(ሐ)ን በመተላለፍ ፈጽሟል የተባለውን በሕገወጥ መንገድ መብትን የማስከበር ወንጀል፣ ለግንቦት 10 ቀን 2004 ዓ.ም. ቀርቦ እንዲያስረዳ በተላለፈለት ጥሪ መሠረት ባለመቅረቡ ታስሮ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ትዕዛዝ ተላለፈ፡፡

ትዕዛዙን ያስተላለፈው የፌዴራል መጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት የየካ ምድብ ወንጀል ችሎት ሲሆን፣ ኃይሌ ታስሮ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ያስተላለፈው የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ሚያዝያ 18 ቀን 2004 ዓ.ም. ላቀረበው የወንጀል ክስ ግንቦት 10 ቀን 2004 ዓ.ም. መልስ ይዞ እንዲቀርብ በተላለፈለት ጥሪ መሠረት ፍርድ ቤት ሳይቀርብ በመቅረቱ ነው፡፡

አትሌት ኃይሌን ለክስ ያበቃው ክስተት ህዳር 24 ቀን 2004 ዓ.ም. ከቀኑ 7፡00 ሰዓት አካባቢ በየካ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 11/12 ክልል ልዩ ቦታው ሃያ ሁለት እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ በተፈጸመ ድርጊት ነው፡፡

በተጠቀሰው አካባቢ በሚገኘው የአትሌት ኃይሌ ሕንፃ ውስጥ ተከራይተው ከሚሠሩትና ተበዳይ ከሆኑት አቶ አዲስ ደገፋ ጋር በኪራይ ውል ምክንያት በተፈጠረ አለመግባባት ጉዳዩ ፍርድ ቤት ደርሶ በክርክር ላይ እንደነበር ክሱ ያስረዳል፡፡ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ውሳኔ ሳያገኝ አቶ አዲስ ይሠሩበት የነበረውን ቢሮ ቁልፍ በሌላ ቁልፍ በመቀየር እንዳይገለገሉበት ማድረጉን ክሱ ያብራራል፡፡ ድርጊቱም በሕገወጥ መንገድ መብትን ማስከበር ወንጀል መሆኑን ጠቅሷል፡፡

አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ የፍርድ ቤቱን ጥሪ አክብሮ ፍርድ ቤት ባለመገኘቱ በ48 ሰዓታት ውስጥ ታስሮ ለግንቦት 29 ቀን 2004 ዓ.ም. ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡

በእነ አንዱዓለም አራጌ ላይ ውሳኔ ሳይሰጥ ቀረ

Saturday, May 12th, 2012

በሽብርተኝነት ተጠርጥረው በፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ክስ የተመሠረተባቸው አቶ አንዱዓለም አራጌን ጨምሮ በስምንት ተጠርጣሪዎች ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለግንቦት 3 ቀን 2004 ዓ.ም. ተሰጥቶ የነበረው ቀጠሮ ለሰኔ 14 ቀን 2004 ዓ.ም. ተቀጠረ፡፡ ክሱን እየመረመረው የሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት፣ መጋቢት 18 እና 19 ቀን 2004 ዓ.ም. የተሰሙ የተጠርጣሪዎቹ የመከላከያ ምስክሮች ቃል ከመቅረጸ ድምፅ ተገልብጦ ከመዝገቡ ጋር አለመያያዙንና ቀደም ብሎ የተሰማውም የመከላከያ ምስክሮች ቃል ከመዝገቡ ጋር የተያያዘው በቅርቡ በመሆኑ ሊደርስ እንዳልቻለ ለተጠርጣሪዎቹ አስረድቷል፡፡

አቶ አንዱዓለም አራጌ ችሎቱ እንደተሰየመ ባቀረቡት አቤቱታ፣ ‹‹ቤተሰቦቻችን፣ ጋዜጠኞችና የውጭ አገር ዜጐች ገብተው የመጨረሻውን ውሳኔያችንን እንዲሰሙ እንፈልጋለን፤ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ሰፋ ያለ አዳራሽ ይፍቀድልን፤›› በማለት ቢያመለክቱም፣ ለማመልከቻቸው ብይን ሳይሰጥ ውሳኔው አለመድረሱ ተነግሮ ጥያቄው ታልፏል፡፡

አቶ አንዱዓለም አያሌው የተባሉ ሌላ ተጠርጣሪ፣ ‹‹በማረያ ቤት ውስጥ እየረደሰብኝ ያለ በደል አለ፤ ፍርድ ቤቱ ሰምቶኝ ብይኑን በችሎት ይስጥልኝ፤›› በማለት ቢያመለክቱም፣ አቤቱታቸውን በጽሑፍ አድርገው በጽሕፈት ቤት በኩል እንዲያመለክቱ ፍርድ ቤቱ በመግለጽ፣ ችሎቱ አብቅቷል፡፡ ውሳኔውን ለመከታተል በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር፣ የእንግሊዝና የጀርመንን ዲፕሎማቶች፣ የተጠርጣሪዎቹ ቤተሰቦች፣ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ጋዜጠኞች ተገኝተዋል፡፡

በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ክስ ከተመሠረተባቸው ተጠርጣሪዎች መካከል አንዱዓለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን፣ ዮሐንስ ተረፈ፣ የሸዋስ ይሁንዓለም፣ ክንፈሚካኤል ደበበ፣ ምትኩ ዳምጤ፣ እስክንድር ነጋና አንዱዓለም አያሌው በማረሚያ ቤት ሆነው ውሳኔያቸውን እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡

ወደ ደቡብ ወሎ የተጓዙ 17 ሰዎች በመኪና አደጋ ሕይወታቸው አለፈ

Wednesday, May 9th, 2012

በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን አማራ ሳይንት ወረዳ በምትገኘውና ዛሬ በምትነግሠው ርእሰ አድባራት ተድባበ ማርያም ገዳም ለንግሥ በመጓዝ ላይ የነበሩ 17 ሰዎች፣ በደረሰባቸው የመኪና መገልበጥ አደጋ ከትናንትና በስቲያ ሕይወታቸው ማለፉን በስፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ ከትናንት በስቲያ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን በደረሰው የመኪና መገልበጥ አደጋ 17 ሰዎች ወዲያውኑ ሕይወታቸው ማለፉን፣ ሁለት ሰዎች ወደ ደሴ ሆስፒታል መላካቸውን፣ ሁለት ደግሞ ሳይንት አጅባር ህዳር 11 ሆስፒታል መግባታቸውንና አንድ ተጐጂ ደግሞ ሳይንት አጅባር ጤና ጣቢያ ዕርዳታ እየተደረገላቸው እንደሚገኙ እማኞቹ ተናግረዋል፡፡

ሕይወታቸው ካለፉት 17 ሰዎች መካከል አሥሩ እዚያው ተድባበ ማርያም ገዳም የቀብር ሥርዓታቸው በትናንትናው ዕለት ከምሽቱ 11 ሰዓት መፈጸሙን፣ የቀሪዎቹ አስከሬን ወደ አዲስ አበባና ወደየመጡበት አካባቢ እየተሸኘ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ከአዲስ አበባ በ600 ኪሎ ሜትርና ከሳይንት አጅባር በ40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የተድባበ ማርያም ገዳም ለመድረስ ጥቂት ርቀት ሲቀር ባለው ገደላማ ቦታ ላይ ሲደርስ፣ አንድ መነኩሴና ሁለት ወጣቶች ወርደው በእግራቸው መጓዝ በመጀመራቸው ከአደጋው መትረፋቸውን እማኞቹ ገልጸዋል፡፡ በመኪና አደጋው ሕይወታቸው ላለፈውና የቀብር ሥርዓታቸው በዚያው በገዳሙ ለተፈጸመው ምዕመናን ብፁዕ አቡነ ገብርኤል በተገኙበት በፈረንሳይ አቦ ቤተ ክርስቲያን ትናንት ምሽት ላይ ፀሎተ ፍትሐት መደረጉን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በጉራፋርዳ ወረዳ ሁለት ቀበሌዎች 22 የአማራ ተወላጆች ቤቶች ተቃጠሉ

Thursday, April 12th, 2012

የደቡብ ክልል መስተዳድር ማንም ሕጋዊ ሰው ከክልሉ አልተፈናቀለም በሚል ሰሞኑን መግለጫ ቢሰጥም መጋቢት 29 ለ30 አጥቢያ በጉራፋርዳ ሁለት ቀበሌዎች 22 ቤቶች መቃጠላቸውን፣ ስምንት ወፍጮዎችም ተነቃቅለው መወሰዳቸው የመኢአድ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት አማካሪ አቶ አሚሳ ሚልኮ በበኩላቸው፣ የተፈናቃዮችን ጉዳይ የሚያጣራ ኮሚቴ ስለመቋቋሙ የሚያውቁት ነገር አለመኖሩን ለሪፖርተር ገልጸዋው፣ “እውነታው ምንድነው ለሚለው በቂ መረጃ አለን” የሚሉት አቶ አሚሳ፣ ክልሉን ለቀው እንዲወጡ የተደረጉት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ አካባቢው መጥተው ደን በመጨፍጨፍ በሕገወጥ መንገድ የሰፈሩ ሰዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

“ዝም ተብሎ የሰው ጓሮ አይገባም፤ መሬት ጠቧቸው የሚመጡበት ሁኔታ ካለ ሁለቱ ክልሎች [አማራና ደቡብ ክልሎች] ሊወያዩ ይገባል፤” በማለት ሰፈራ በሕጋዊ መንገድ መካሄድ እንዳለበት ይናገራሉ፡፡

እርሳቸው እንደሚሉት፣ በጉራፋርዳ ወረዳ በሕጋዊ መንገድ መሬት ተረክቦ በአካባቢው ሲኖር የነበረ አንድም ሰው እንዲፈናቀል አልተደረገም፡፡ “አካባቢውን እንዲለቁ የተደረጉት ከየካቲት ወር በኋላ [በያዝነው ዓመት] በኋላ የመጡ ናቸው፡፡ ነባር ሰዎች ተፈናቀሉ የሚባለው ስህተት ነው፤” ብለዋል፡፡

የአላሙዲ ሸራተን ሠራተኞች ብሶት

Wednesday, April 11th, 2012

በ2002 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ በሸራተን አዲስ ማኔጅመንትና ሠራተኞች መካከል ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረው ውዝግብ፣ አሁንም መቀጠሉን ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ የሠራተኛ ማኅበር ከተቋቋመ በኋላ ሠራተኞች ቀደም ሲል ያገኙት የነበረውን ጥቅማ ጥቅም በመቀነስና አንዳንዱንም በማቆም የሆቴሉ ማኔጅመንት በደል እንዳደረሰባቸው በመግለጻቸው፣ በከፍተኛ ሁኔታ የነበረውን አለመግባባት አቶ አብነት ገብረ መስቀልና የሕግ ባለሙያው አቶ ተካ አስፋው ጣልቃ በመግባት ነገሩን ማርገባቸው ይታወሳል፡፡

በመሆኑም ማኔጅመንቱና መሠረታዊ የሠራተኛ ማኅበሩ ባደረጉት ድርድር ስምምነት ላይ በመድረሳቸው፣ እ.ኤ.አ ማርች 21 ቀን 2011 የኅብረት ስምምነት በመፈራረም፣ የተስማሙባቸውን ዝርዝር ጉዳዮች አንቀጽ በአንቀጽ በመጥቀስ ለሠራተኛው መደረግና መከበር የሚገባቸውን መብቶች፣ በአጭር ጊዜ ተግባራዊ እንዲሆኑ ተስማምተው እንደነበር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ሠራተኞችና ማኔጅመንቱ የኅብረት ስምምነቱን ከተፈራረሙ በኋላ፣ በሁለቱ መካከል ያለው ግንኙነት ጥሩ እንዲሆን በሚል የሠራተኛ ማኅበሩ አንድ ዝግጅት በማድረግ ለማኔጅመንቱ ኃላፊዎች፣ ለሆቴሉ ቅርብ ሰዎችና ለውጤታማ ሠራተኞች ሽልማት በማዘጋጀት መሸለሙን፣ በመቀጠልም የማኅበሩ ተወካዮችና የማኔጅመንት አባላት ተከታታይ ውይይቶችን ማድረጋቸውን፣ የማኅበሩ ተወካዮች ለሠራተኞቹ ሥራቸውን እንዴት መሥራት እንዳለባቸው፣ የሆቴል ሥነ ሥርዓትና ሌሎች ሥልጠናዎችን ከ50 ሰዓታት በላይ መስጠታቸውን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

ነገር ግን የሆቴሉ የማኔጅመንት ኃላፊዎች ከሠራተኞች ጋር ስምምነት ፈጥረውና በስምምነታቸው መሠረት የሠራተኞችን መብት ማክበር ሲገባቸው፣ በተቃራኒው በትንሽ በትልቁ ማስጠንቀቂያ መስጠት፣ ደመወዝ መቀነስ፣ ከሆቴሉ ባለቤት ይሰጥ የነበረውን ጉርሻ ማስቆም፣ ተቆጣጣሪዎች ላለፉት 14 ዓመታት ይሰጣቸው የነበረውን የትራንስፖርት አበል አለመክፈል፣ የደመወዝ እርከን መከልከልና ሌሎች በደሎችንም መፈጸም ተግባራቸው ማድረጋቸውን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡

መሠረታዊ የሠራተኛ ማኅበሩ በሠራተኞች ላይ እየደረሰ ያለውን አግባብ ያልሆነ የመብት ረገጣ በመቃወም የማኅበሩ ተወካዮች እ.ኤ.አ ዲሴምበር 26 እና 27 ቀን 2011 ከድርጅቱ የሰው ኃይል አስተዳደርና ረዳት አስተዳደር ጋር ተወያይተው እንደነበር፣ የሆቴሉን ምክትል ሥራ አስኪያጅ ጨምሮ ከሆቴሉ ማኔጅመንት ጋር ጃንዋሪ 3 ቀን 2012 በድጋሚ ውይይት በማድረግ ማኅበሩ ያቀረባቸውን ነጥቦች ትክክለኛነት ተረጋግጦ፣ በአንድ ወር ውስጥ ለመፈጸም ቢስማሙም ተፈጻሚ ሊሆን አለመቻሉን ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም መሠረታዊ ሠራተኛ ማኅበሩ ከዓመት በፊት ማኔጅመንቱ ለመፈጸም የተስማማባቸውን ዘጠኝ አንቀጾችን በመጥቀስና ተፈጻሚ ያልሆኑ አምስት አንቀጾችን በማስታወስ፣ በፍትሐ ብሔር ሕግ አንቀጽ 1771 እና 1776 መሠረት የሕግ ማስጠንቀቂያ መጻጻፉን፣ ተግባራዊ ካልተደረገለትም በሕግ የሠራተኛውን መብት ለማስከበር የሚገደድ መሆኑን እንዳስታወቀ ምንጮቹ አብራርተዋል፡፡

የሸራተን አዲስ የሰው ሀብት ዳይሬክተር ወ/ሮ ኤድና ታሞንዶንግ መጋቢት 18 ቀን 2004 ዓ.ም. ለሠራተኛ ማኅበሩ በጻፉት ደብዳቤ፣ ምንም የተጣሰ የኅብረት ስምምነት አንቀጽ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ ከሰባት የማያንሱ አንቀጾች ተግባራዊ መደረጋቸውንና የደመወዝ ጭማሪ ጥናትን ጨምሮ ቀሪዎቹንም ተግባራዊ ለማድረግ በሒደት ላይ መሆናቸውን ማስታወቃቸውን፣ ከሆቴሉ ማኔጅመንት ኃላፊዎች አካባቢ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

ወ/ሮ ኤድናን በስልክ ለማግኘት በተደረገው ሙከራ “እኔ ለሚዲያ መግለጫ ለመስጠት ኃላፊነቴ አይፈቅድም፤” የሚል ምላሽ በጸሐፊያቸው በኩል ሰጥተዋል፡፡ የሸራተን አዲስ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ዦንፔር ማኒጎፍን ለማግኘት ተሞክሮ “ስብሰባ ላይ ናቸው፤ ሲጨርሱ እደውላለሁ፤” የሚል ምላሽ ከጸሐፊያቸው ቢገኝም፣ ለሕትመት እስከተገባበት ሰዓት ድረስ ምላሻቸው ሊገኝ አልተቻለም፡፡ እንደገና ቢደወልላቸውም “ወጥተዋል” በመባሉ ሳይገኙ ቀርተዋል፡፡

ከቤንች-ማጂ የተፈናቀሉ አማራዎች ወደ ደብረብርሃን ተጓጓዙ

Monday, April 2nd, 2012

ሕገወጥ ሰፋሪዎች ናችሁ በሚል በደቡብ ክልላዊ መንግሥት ውሳኔ ይኖሩበት ከነበረው ጉራፋርዳ ወረዳ የተባረሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ክልል ተወላጆች ያለፍላጐታቸው ወደ ደብረ ብርሃን መጓጓዛቸውን አስታወቁ፡፡ ተፈናቃዮቹ ፍትሕ ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ ቢመጡም የባሰ በደል እየደረሰባቸው መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የደቡብ ክልል ፕሬዚደንት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ሰኔ 2003 ዓ.ም. ለቤንቺ ማጂ ዞን አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በላኩት ደብዳቤ እስከ ነሐሴ 30 ቀን 1999 ዓ.ም. ድረስ ወደ ክልሉ የመጡና በወረዳና በቀበሌ አመራሮችም ሆነ በራሳቸው መንገድ መሬት የያዙ ዜጐች እስከ ሁለት ሔክታር የእርሻ መሬትና 1,000 ካሬ ሜትር የቤት መሥሪያ እንዲሰጣቸው፣ ባሉባቸው ቀበሌዎች እንደ ሕጋዊ ሰፋሪ ተመዝግበው የክልሉ ነዋሪ መሆናቸውን አውቀው በክልሉ ሕጐች መሠረት እንዲተዳደሩ እንዲደረግ፣ ከ1999 ዓ.ም. ነሐሴ 30 ቀን በኋላ የመጡ ማናቸውም ዜጐች ወደመጡባቸው አካባቢዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲሸኙና ይህም ከቀሪዎቹና ከሚሄዱት ዜጐች ጋር በሚደረግ ውይይትና መደበኛ የሕግ አፈጻጸም ተከትሎ ተግባራዊ እንዲደረግ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ይህንን የፕሬዚዳንቱት ትዕዛዝ ተከትሎም በጉራፋርዳ ወረዳ በግብርና ሥራ ላይ ተሰማርተው የቆዩ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ የአማራ ክልል ተወላጆች ሀብትና ንብረታቸውን ጥለው በአጭር ጊዜ ውስጥ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ተወስኖባቸዋል፡፡ ተፈናቃዮቹ የሰፈሩበትን ቦታ በወረዳና በቀበሌ አመራሮች ውሳኔ በሕጋዊ መንገድ ተረክበው ግብር ሲከፍሉ መቆየታቸውን በመግለጽ ውሳኔው እንዲሻሻልላቸው ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ የትኛውም አካል ችግራቸውን ተረድቶ ምላሽ ሊሰጣቸው እንዳልቻለ ይናገራሉ፡፡ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ፌስታል ያንጠለጠሉ በርካታ ተፈናቃዮች ሀብትና ንብረት አፍርተው ይኖሩበት የነበሩበትን አካባቢ ጥለው ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት መገደዳቸውን፣ መፍትሔ ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ ቢመጡም የፈለጉትን አለማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ሐሙስ ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አቤቱታ ለማቅረብ ወደ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት የተጓዙት ተፈናቃዮች በፌዴራል ፖሊሶች ተይዘው ፓርላማ ፊት ለፊት በሚገኘውና ለመልሶ ግንባታ በታጠረው ቦታ ለተወሰኑ ደቂቃዎች እንዲቆዩ ከተደረጉ በኋላ በተሽከርካሪ ተጭነው ተወስደዋል፡፡

ከምንጮቻችን ለመረዳት እንደቻልነው ይኖሩበት ወደነበረው ጉራፋርዳ ወረዳ እንዲመለሱ ወይም ደግሞ ወደ አማራ ክልል ተመልሰው ተለዋጭ ቦታ ተሰጥቷቸው በግብርና ሥራ የሚሰማሩበት ሁኔታ ይመቻችላቸው ዘንድ አቤቱታ ለማቅረብ ወደ አዲስ አበባ ከመጡት 600 ገደማ ከሚደርሱት ተፈናቃዮች መካከል፣ አብዛኛዎቹ ባለፈው ዓርብ ከሰዓት በኋላ በፖሊሶች በኃይል እየተገፈተሩ በአራት የሕዝብ ማመላለሻና በአንድ ታክሲ ተጭነው ወደ ደብረ ብርሃን ተወስደዋል፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ወጣቶች ክበብ ውስጥ ከቀሩት ጥቂት ተፈናቃዮች መካከል አንዱ ዓርብ ምሽት ለሪፖርተር በስልክ እንደገለጹት፣ ተፈናቃዮቹ ከክበቡ ወጥተው እራት ለመብላት ሲሞክሩ በአካባቢው የነበሩ ፖሊሶች አትወጡም ብለው ከልክለዋቸዋል፡፡ ‹‹ሕፃናት ምግብ ስጡን እያሉ ነው ወደ ደብረ ብርሃን የተወሰዱት፣ መፍትሔ ፍለጋ መጥተን ግፍና በደል ደርሶብናል፡፡ የ22 ቀበሌ ሕዝብ ሲፈናቀል መንግሥት እንዴት ዝም ይላል?›› ሲሉ የሚጠይቁት እኝሁ ግለሰብ፣ መንግሥት ተፈናቃዮችን ሰብስቦ ወደ ደብረ ብርሃን የሚወስድበት ምክንያት ሊገባቸው እንዳልቻለ ይናገራሉ፡፡

ከተፈናቃዮቹ መካከል አንዱ የሆነው ወጣት በዕለቱ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ (ፖሊስ መሀል ገብቶ ቃለ ምልልሱን እስካቋረጠበት ጊዜ ድረስ) እሱና ሌሎች መሰሎቹ በ1998 ዓ.ም. ወደ ጉራፋርዳ ወረዳ በመሄድ የቀበሌውና የወረዳው አመራሮች በሰጧቸው ፈቃድ መሠረት በሕጋዊ መንገድ መሬት ተረክበው ሀብትና ንብረት አፍርተው ሕይወታቸውን ሲመሩ ቢቆዩም፣ አሁን ሕገወጥ ሰፋሪ ናችሁ ተብለው ተባረዋል፡፡

ከሦስት ሳምንት በፊት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የቤንች ማጂ ዞን አስተዳዳሪ ከአማራ ክልል መጥተው በሕገወጥ መንገድ የሰፈሩ ሰዎች በሕጋዊ መንገድ እንዲመለሱ ይደረጋል እንጂ፣ ሕገወጥ ስለሆኑ ብቻ ሰብዓዊ መብታቸው የሚጣስበት ሁኔታ እንደማይኖር ገልጸው ነበር፡፡ ይህንን ሐሳባቸውን ሲያጠናክሩም የደቡብ ክልልና የአማራ ክልል ኃላፊዎች ከሁለት ዓመት በፊት ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ ከ800 በላይ የሚሆኑ በደቡብ ክልል ሰፍረው የነበሩ የአማራ ክልል ተወላጆች ወደ ባህር ዳር እንዲጓጓዙ መደረጉን በማስረጃነት ጠቅሰው ነበር፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ተፈናቃዮች ግን በወረዳው ኃላፊ ሐሳብ አይስማሙም፡፡ እነሱ እንደሚሉት በቆዩባቸው ጊዜያት ላፈሯቸው ንብረቶች ካሳ ሳይሰጣቸው፣ ንብረታቸውን የሚሸጡበትም በቂ ጊዜ ሳይሰጣቸው ነው በግዴታ አካባቢውን ጥለው እንዲወጡ የተደረጉት፡፡

ከደቡብ ጐንደር ፎገራ ወረዳ በ1986 ዓ.ም. ለቡና ለቀማ ወደ ደቡብ ክልል ሄደው ከ1993 ዓ.ም. ጀምሮ በሕጋዊ መንገድ ባገኙት አራት ሔክታር መሬት ላይ በግብርና ሥራ ላይ ተሰማርተው መቆየታቸውን ለሪፖርተር የገለጹት አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ተፈናቃይ በበኩላቸው፣ በአካባቢው የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች እስከ 48 ሔክታር የሚደርስ መሬት ይዘው እያሉ፣ እርሳቸውን ጨምሮ ከ1999 ዓ.ም. በፊት በአካባቢው የሰፈሩ ሌሎች ዜጐች ሁለት ሔክታር መሬት ይበቃችኋል ተብለው ይዘውት የቆዩትን መሬት መነጠቃቸውን ይናገራሉ፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) መጋቢት 19 ቀን 2004 ዓ.ም. ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በጻፈው ግልጽ ደብዳቤ፣ በደቡብ ክልል ቤንቺ ማጂ ዞን ጉራፋርዳ ወረዳ ውስጥ ነዋሪ በሆኑ ዜጐች ላይ የደረሰውን ከቀየ የማፈናቀልና፣ ሀብትና ንብረትን አላግባብ የመውረስ እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያይዘው የተፈጠሩ ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

‹‹መኢአድ በጉራፋርዳ ወረዳ እየተካሄደ ያለው ሕዝብን ከቀየው የማፈናቀልና የማሳደድ ተግባር በቀጥታ በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የተሰጠ መመርያ በመሆኑ ምክንያት፣ ጉዳዩ በቀጥታ ይመለከታቸዋል ብሎ በማሰብ ለክልሉ ፕሬዚዳንት ለአቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ እንዲሁም በግልባጭ ለእርስዎና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በተጻፈ ደብዳቤ የጉዳዩን አሳሳቢነት ገልጾ መፍትሔ እንዲበጅለት ቢጠይቅም፣ ጉዳዩ እስከዛሬ ድረስ ምንም መፍትሔ ሊያገኝ አልቻለም፤›› ሲል በደብዳቤው ያመለከተው መኢአድ፣ ጉዳዩ የሃያ ሁለት ሺሕ አባወራዎችን ኑሮ እንዲሁም የብዙ ሺሕ ሴቶችንና ሕፃናትን ሕይወት አደጋ ላይ የጣለ በመሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን አስገንዝቧል፡፡

በሕጋዊ መንገድ ከመንግሥት መሬት ተሰጥቷቸው፣ ይህንንም የሚያረጋግጥ ሕጋዊ ሰነድ በእጃቸው ላይ ባለበት ሁኔታ፣ ከዚህም ባለፈ ቋሚ ተክሎችን ተክለው ሀብት ባፈሩበት ሁኔታ ላይ የሚገኙ ዜጐችን፣ በሕገወጥነት ፈርጃ ለረጅም ዓመት ከኖሩበትና ቤተሰብ ካፈሩበት ቀየ ማፈናቀልና ማሳደድ፣ እንዲሁም ያለ ምንም ካሳ ሀብትና ንብረታቸው በካድሬዎች ያለአግባብ እንዲወረስ ማድረግ፣ ለሕዝብ ቆሜያለሁ ከሚል መንግሥት በፍፁም የማይጠበቅ በመሆኑ፣ መንግሥት እንደ መንግሥት ለአገሩ ዜጐች እንዲያስብና ለመብቶቻቸውም መከበር እንዲቆም መኢአድ አክሎ ጠይቋል፡፡

የክልሉን ውሳኔ ተከትሎ በተፈናቃዮቹ ላይ የደረሰውን በደልም መኢአድ እንዲህ ሲል ይገልጻል፡፡ ‹‹ነፍሰ ጡር እናት ሌሊት ወልዳ ሲነጋ የሰዓታት ዕድሜ ካለው ልጇ ጋር ከነፍራሿ ደጅ ተጥላለች፤ ነፍሰ ጡሮች ተሰደዋል፤ የስምንት ወር ዕድሜ ካላቸው ጨቅላ ሕፃናት ጀምሮ በርካታ ሕፃናት ከሚያጠቡ እናቶቻቸው ጋር አብረው ታስረዋል፤ የሚላስ የሚቀመስ አጥተው በረሃብ ተጠብሰዋል፤ በነፍስ ወከፍ እስከ 3 ሺሕ እግር ቡና ዛፍ፣ አቡካዶ፣ ማንጐ፣ ፓፓያና ሙዝ የተከለ እንዲሁም በርካታ የንብ ቀፎ የሰቀለው፣ በከብትና በዶሮ እርባታ ላይ የተሰማራው ገበሬ ያመረተውንና ያፈራውን ሀብትና ንብረት ጥሎ ጨርቁን በፌስታል አንጠልጥሎ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ ‘ምንም ይዛችሁ ስላልመጣችሁ ምንም ይዛችሁ አትሄዱም’ እየተባሉ ንብረታቸውን ሜዳ በትነው እንዲሄዱ ተደብድበዋል፤›› ብሏል በደብዳቤው፡፡

ሕዝቡን ያስተባበሩ የነበሩና ከዚህ በፊት ከጉራፋርዳ ወረዳ ታፍሰው በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ ላይ ታግተው የነበሩ አሥራ ሦስት ያህል አባወራዎች እስካሁን የደረሱበት አለመታወቁን የጠቆመው መኢአድ፣ ይህ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ዲሞክራሲያዊ ድርጊት የተፈጠረው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በሚያስተዳድሩት አገርና በሚመሩት ሕዝብ ላይ በመሆኑ ምክንያት፣ ‹‹በአስቸኳይ የእርስዎን [የአቶ መለስን] ጣልቃ ገብነት የሚሻ ጉዳይ ሆኖ አግኝተነዋል፤›› ብሏል፡፡

መኢአድ ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በላከው በዚሁ ደብዳቤ በጉራፋርዳ ይኖሩ የነበሩ የአገሪቱ ዜጐች እየተፈጸመባቸው ያለው ግፍና በደል እንዲቆም፣ ሕፃናትና ሴቶች በከፍተኛ የምግብ እጥረትና በጤና መታወክ እየተሰቃዩ በመሆኑ የምግብና የመድኃኒት አቅርቦት በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲደረግ፣ በእስር ላይ የሚገኙ አባወራዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ፣ በዞኑ በማጐሪያ ጣቢያዎች ውስጥ የተቀመጡ አባወራዎች፣ ሕፃናትና ሴቶች እንዲሁም ወደ ጋምቤላ የተሰደዱ ዜጐች ያሉበት ሁኔታ እንዲጣራ፣ ይህም በገለልተኛ አካል እንዲረጋገጥ፣ ተፈናቃዮቹ ሕጋዊ ሰነድ ያላቸው በመሆኑና ሕጋዊ ግብር ከፋይ ዜጐች በመሆናቸው ወደ መኖሪያ ቀያቸውና ወደ ሀብት ንብረታቸው አንዲመለሱ እንዲደረግ፣ አካባቢው ለሌላ ልማት ያስፈልጋል ቢባል እንኳን ተለዋጭ ቦታ ተሰጥቷቸው ለቋሚ ተክሎቻቸው ተገቢው ካሳ ተከፍሏቸው በሕጋዊና አግባብ ባለው መንገድ እንዲፈጽም ይደረግ የሚሉና ሌሎችንም ጥያቄዎች አንስቷል፡፡

የጉራፋርዳ ተፈናቃዮች ወደ ደብረ ብርሃን ተጓጓዙ

Sunday, April 1st, 2012

ሕገወጥ ሰፋሪዎች ናችሁ በሚል በደቡብ ክልላዊ መንግሥት ውሳኔ ይኖሩበት ከነበረው ጉራፋርዳ ወረዳ የተባረሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ክልል ተወላጆች ያለፍላጐታቸው ወደ ደብረ ብርሃን መጓጓዛቸውን አስታወቁ፡፡ ተፈናቃዮቹ ፍትሕ ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ ቢመጡም የባሰ በደል እየደረሰባቸው መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የደቡብ ክልል ፕሬዚደንት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ሰኔ 2003 ዓ.ም. ለቤንቺ ማጂ ዞን አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በላኩት ደብዳቤ እስከ ነሐሴ 30 ቀን 1999 ዓ.ም. ድረስ ወደ ክልሉ የመጡና በወረዳና በቀበሌ አመራሮችም ሆነ በራሳቸው መንገድ መሬት የያዙ ዜጐች እስከ ሁለት ሔክታር የእርሻ መሬትና 1,000 ካሬ ሜትር የቤት መሥሪያ እንዲሰጣቸው፣ ባሉባቸው ቀበሌዎች እንደ ሕጋዊ ሰፋሪ ተመዝግበው የክልሉ ነዋሪ መሆናቸውን አውቀው በክልሉ ሕጐች መሠረት እንዲተዳደሩ እንዲደረግ፣ ከ1999 ዓ.ም. ነሐሴ 30 ቀን በኋላ የመጡ ማናቸውም ዜጐች ወደመጡባቸው አካባቢዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲሸኙና ይህም ከቀሪዎቹና ከሚሄዱት ዜጐች ጋር በሚደረግ ውይይትና መደበኛ የሕግ አፈጻጸም ተከትሎ ተግባራዊ እንዲደረግ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ይህንን የፕሬዚዳንቱት ትዕዛዝ ተከትሎም በጉራፋርዳ ወረዳ በግብርና ሥራ ላይ ተሰማርተው የቆዩ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ የአማራ ክልል ተወላጆች ሀብትና ንብረታቸውን ጥለው በአጭር ጊዜ ውስጥ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ተወስኖባቸዋል፡፡ ተፈናቃዮቹ የሰፈሩበትን ቦታ በወረዳና በቀበሌ አመራሮች ውሳኔ በሕጋዊ መንገድ ተረክበው ግብር ሲከፍሉ መቆየታቸውን በመግለጽ ውሳኔው እንዲሻሻልላቸው ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ የትኛውም አካል ችግራቸውን ተረድቶ ምላሽ ሊሰጣቸው እንዳልቻለ ይናገራሉ፡፡ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ፌስታል ያንጠለጠሉ በርካታ ተፈናቃዮች ሀብትና ንብረት አፍርተው ይኖሩበት የነበሩበትን አካባቢ ጥለው ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት መገደዳቸውን፣ መፍትሔ ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ ቢመጡም የፈለጉትን አለማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ሐሙስ ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አቤቱታ ለማቅረብ ወደ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት የተጓዙት ተፈናቃዮች በፌዴራል ፖሊሶች ተይዘው ፓርላማ ፊት ለፊት በሚገኘውና ለመልሶ ግንባታ በታጠረው ቦታ ለተወሰኑ ደቂቃዎች እንዲቆዩ ከተደረጉ በኋላ በተሽከርካሪ ተጭነው ተወስደዋል፡፡

ከምንጮቻችን ለመረዳት እንደቻልነው ይኖሩበት ወደነበረው ጉራፋርዳ ወረዳ እንዲመለሱ ወይም ደግሞ ወደ አማራ ክልል ተመልሰው ተለዋጭ ቦታ ተሰጥቷቸው በግብርና ሥራ የሚሰማሩበት ሁኔታ ይመቻችላቸው ዘንድ አቤቱታ ለማቅረብ ወደ አዲስ አበባ ከመጡት 600 ገደማ ከሚደርሱት ተፈናቃዮች መካከል፣ አብዛኛዎቹ ባለፈው ዓርብ ከሰዓት በኋላ በፖሊሶች በኃይል እየተገፈተሩ በአራት የሕዝብ ማመላለሻና በአንድ ታክሲ ተጭነው ወደ ደብረ ብርሃን ተወስደዋል፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ወጣቶች ክበብ ውስጥ ከቀሩት ጥቂት ተፈናቃዮች መካከል አንዱ ዓርብ ምሽት ለሪፖርተር በስልክ እንደገለጹት፣ ተፈናቃዮቹ ከክበቡ ወጥተው እራት ለመብላት ሲሞክሩ በአካባቢው የነበሩ ፖሊሶች አትወጡም ብለው ከልክለዋቸዋል፡፡ ‹‹ሕፃናት ምግብ ስጡን እያሉ ነው ወደ ደብረ ብርሃን የተወሰዱት፣ መፍትሔ ፍለጋ መጥተን ግፍና በደል ደርሶብናል፡፡ የ22 ቀበሌ ሕዝብ ሲፈናቀል መንግሥት እንዴት ዝም ይላል?›› ሲሉ የሚጠይቁት እኝሁ ግለሰብ፣ መንግሥት ተፈናቃዮችን ሰብስቦ ወደ ደብረ ብርሃን የሚወስድበት ምክንያት ሊገባቸው እንዳልቻለ ይናገራሉ፡፡

ከተፈናቃዮቹ መካከል አንዱ የሆነው ወጣት በዕለቱ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ (ፖሊስ መሀል ገብቶ ቃለ ምልልሱን እስካቋረጠበት ጊዜ ድረስ) እሱና ሌሎች መሰሎቹ በ1998 ዓ.ም. ወደ ጉራፋርዳ ወረዳ በመሄድ የቀበሌውና የወረዳው አመራሮች በሰጧቸው ፈቃድ መሠረት በሕጋዊ መንገድ መሬት ተረክበው ሀብትና ንብረት አፍርተው ሕይወታቸውን ሲመሩ ቢቆዩም፣ አሁን ሕገወጥ ሰፋሪ ናችሁ ተብለው ተባረዋል፡፡

ከሦስት ሳምንት በፊት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የቤንች ማጂ ዞን አስተዳዳሪ ከአማራ ክልል መጥተው በሕገወጥ መንገድ የሰፈሩ ሰዎች በሕጋዊ መንገድ እንዲመለሱ ይደረጋል እንጂ፣ ሕገወጥ ስለሆኑ ብቻ ሰብዓዊ መብታቸው የሚጣስበት ሁኔታ እንደማይኖር ገልጸው ነበር፡፡ ይህንን ሐሳባቸውን ሲያጠናክሩም የደቡብ ክልልና የአማራ ክልል ኃላፊዎች ከሁለት ዓመት በፊት ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ ከ800 በላይ የሚሆኑ በደቡብ ክልል ሰፍረው የነበሩ የአማራ ክልል ተወላጆች ወደ ባህር ዳር እንዲጓጓዙ መደረጉን በማስረጃነት ጠቅሰው ነበር፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ተፈናቃዮች ግን በወረዳው ኃላፊ ሐሳብ አይስማሙም፡፡ እነሱ እንደሚሉት በቆዩባቸው ጊዜያት ላፈሯቸው ንብረቶች ካሳ ሳይሰጣቸው፣ ንብረታቸውን የሚሸጡበትም በቂ ጊዜ ሳይሰጣቸው ነው በግዴታ አካባቢውን ጥለው እንዲወጡ የተደረጉት፡፡

ከደቡብ ጐንደር ፎገራ ወረዳ በ1986 ዓ.ም. ለቡና ለቀማ ወደ ደቡብ ክልል ሄደው ከ1993 ዓ.ም. ጀምሮ በሕጋዊ መንገድ ባገኙት አራት ሔክታር መሬት ላይ በግብርና ሥራ ላይ ተሰማርተው መቆየታቸውን ለሪፖርተር የገለጹት አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ተፈናቃይ በበኩላቸው፣ በአካባቢው የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች እስከ 48 ሔክታር የሚደርስ መሬት ይዘው እያሉ፣ እርሳቸውን ጨምሮ ከ1999 ዓ.ም. በፊት በአካባቢው የሰፈሩ ሌሎች ዜጐች ሁለት ሔክታር መሬት ይበቃችኋል ተብለው ይዘውት የቆዩትን መሬት መነጠቃቸውን ይናገራሉ፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) መጋቢት 19 ቀን 2004 ዓ.ም. ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በጻፈው ግልጽ ደብዳቤ፣ በደቡብ ክልል ቤንቺ ማጂ ዞን ጉራፋርዳ ወረዳ ውስጥ ነዋሪ በሆኑ ዜጐች ላይ የደረሰውን ከቀየ የማፈናቀልና፣ ሀብትና ንብረትን አላግባብ የመውረስ እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያይዘው የተፈጠሩ ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

‹‹መኢአድ በጉራፋርዳ ወረዳ እየተካሄደ ያለው ሕዝብን ከቀየው የማፈናቀልና የማሳደድ ተግባር በቀጥታ በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የተሰጠ መመርያ በመሆኑ ምክንያት፣ ጉዳዩ በቀጥታ ይመለከታቸዋል ብሎ በማሰብ ለክልሉ ፕሬዚዳንት ለአቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ እንዲሁም በግልባጭ ለእርስዎና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በተጻፈ ደብዳቤ የጉዳዩን አሳሳቢነት ገልጾ መፍትሔ እንዲበጅለት ቢጠይቅም፣ ጉዳዩ እስከዛሬ ድረስ ምንም መፍትሔ ሊያገኝ አልቻለም፤›› ሲል በደብዳቤው ያመለከተው መኢአድ፣ ጉዳዩ የሃያ ሁለት ሺሕ አባወራዎችን ኑሮ እንዲሁም የብዙ ሺሕ ሴቶችንና ሕፃናትን ሕይወት አደጋ ላይ የጣለ በመሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን አስገንዝቧል፡፡

በሕጋዊ መንገድ ከመንግሥት መሬት ተሰጥቷቸው፣ ይህንንም የሚያረጋግጥ ሕጋዊ ሰነድ በእጃቸው ላይ ባለበት ሁኔታ፣ ከዚህም ባለፈ ቋሚ ተክሎችን ተክለው ሀብት ባፈሩበት ሁኔታ ላይ የሚገኙ ዜጐችን፣ በሕገወጥነት ፈርጃ ለረጅም ዓመት ከኖሩበትና ቤተሰብ ካፈሩበት ቀየ ማፈናቀልና ማሳደድ፣ እንዲሁም ያለ ምንም ካሳ ሀብትና ንብረታቸው በካድሬዎች ያለአግባብ እንዲወረስ ማድረግ፣ ለሕዝብ ቆሜያለሁ ከሚል መንግሥት በፍፁም የማይጠበቅ በመሆኑ፣ መንግሥት እንደ መንግሥት ለአገሩ ዜጐች እንዲያስብና ለመብቶቻቸውም መከበር እንዲቆም መኢአድ አክሎ ጠይቋል፡፡

የክልሉን ውሳኔ ተከትሎ በተፈናቃዮቹ ላይ የደረሰውን በደልም መኢአድ እንዲህ ሲል ይገልጻል፡፡ ‹‹ነፍሰ ጡር እናት ሌሊት ወልዳ ሲነጋ የሰዓታት ዕድሜ ካለው ልጇ ጋር ከነፍራሿ ደጅ ተጥላለች፤ ነፍሰ ጡሮች ተሰደዋል፤ የስምንት ወር ዕድሜ ካላቸው ጨቅላ ሕፃናት ጀምሮ በርካታ ሕፃናት ከሚያጠቡ እናቶቻቸው ጋር አብረው ታስረዋል፤ የሚላስ የሚቀመስ አጥተው በረሃብ ተጠብሰዋል፤ በነፍስ ወከፍ እስከ 3 ሺሕ እግር ቡና ዛፍ፣ አቡካዶ፣ ማንጐ፣ ፓፓያና ሙዝ የተከለ እንዲሁም በርካታ የንብ ቀፎ የሰቀለው፣ በከብትና በዶሮ እርባታ ላይ የተሰማራው ገበሬ ያመረተውንና ያፈራውን ሀብትና ንብረት ጥሎ ጨርቁን በፌስታል አንጠልጥሎ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ ‘ምንም ይዛችሁ ስላልመጣችሁ ምንም ይዛችሁ አትሄዱም’ እየተባሉ ንብረታቸውን ሜዳ በትነው እንዲሄዱ ተደብድበዋል፤›› ብሏል በደብዳቤው፡፡

ሕዝቡን ያስተባበሩ የነበሩና ከዚህ በፊት ከጉራፋርዳ ወረዳ ታፍሰው በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ ላይ ታግተው የነበሩ አሥራ ሦስት ያህል አባወራዎች እስካሁን የደረሱበት አለመታወቁን የጠቆመው መኢአድ፣ ይህ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ዲሞክራሲያዊ ድርጊት የተፈጠረው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በሚያስተዳድሩት አገርና በሚመሩት ሕዝብ ላይ በመሆኑ ምክንያት፣ ‹‹በአስቸኳይ የእርስዎን [የአቶ መለስን] ጣልቃ ገብነት የሚሻ ጉዳይ ሆኖ አግኝተነዋል፤›› ብሏል፡፡

መኢአድ ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በላከው በዚሁ ደብዳቤ በጉራፋርዳ ይኖሩ የነበሩ የአገሪቱ ዜጐች እየተፈጸመባቸው ያለው ግፍና በደል እንዲቆም፣ ሕፃናትና ሴቶች በከፍተኛ የምግብ እጥረትና በጤና መታወክ እየተሰቃዩ በመሆኑ የምግብና የመድኃኒት አቅርቦት በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲደረግ፣ በእስር ላይ የሚገኙ አባወራዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ፣ በዞኑ በማጐሪያ ጣቢያዎች ውስጥ የተቀመጡ አባወራዎች፣ ሕፃናትና ሴቶች እንዲሁም ወደ ጋምቤላ የተሰደዱ ዜጐች ያሉበት ሁኔታ እንዲጣራ፣ ይህም በገለልተኛ አካል እንዲረጋገጥ፣ ተፈናቃዮቹ ሕጋዊ ሰነድ ያላቸው በመሆኑና ሕጋዊ ግብር ከፋይ ዜጐች በመሆናቸው ወደ መኖሪያ ቀያቸውና ወደ ሀብት ንብረታቸው አንዲመለሱ እንዲደረግ፣ አካባቢው ለሌላ ልማት ያስፈልጋል ቢባል እንኳን ተለዋጭ ቦታ ተሰጥቷቸው ለቋሚ ተክሎቻቸው ተገቢው ካሳ ተከፍሏቸው በሕጋዊና አግባብ ባለው መንገድ እንዲፈጽም ይደረግ የሚሉና ሌሎችንም ጥያቄዎች አንስቷል፡፡

 

6 የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ኃላፊዎች ታሰሩ

Wednesday, March 21st, 2012

የመንግሥትንና የማኅበሩን የግዢ መመርያ ያልተከተለ የ107 ሚሊዮን ብር የእህል ግዢ በመፈጸም ወንጀል የተጠረጠሩ ስድስት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ኃላፊዎች መጋቢት 6 ቀን 2004 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡ ኃላፊዎቹ ድርጊቱን ፈጽመዋል በሚል በቁጥጥር ሥር አውሎ ያሰራቸው የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ፖሊስ ነው፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የማኅበሩ የፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ፣ የኦዲት አገልግሎት ኃላፊ፣ የአስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት ኃላፊ፣ የደም ባንክ መምሪያ ኃላፊ፣ የጤና እንክብካቤ መምሪያ ኃላፊና የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት መምሪያ ኃላፊ መሆናቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያረጋግጣል፡፡

ኃላፊዎቹ በ2003 ዓ.ም. በቦረና ሞያሌ አካባቢ ለደረሰው ድርቅ፣ ከውጭ በዕርዳታ በተገኘ ገንዘብ ለተረጂዎች በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በኩል በውስን ጨረታ እህል ተገዝቶ እንዲከፋፈል የግብርና ሚኒስቴር ይጠይቃል፡፡ ኃላፊዎቹ የተጠየቀውን የእህል ግዢ መሠረት በማድረግ የመንግሥትንና የማኅበሩን የግዢ መመርያን በመጣስ፣ በእህል አቅራቢነት ያልተመዘገቡና ሕጋዊ ፈቃድ የሌላቸውን ሁለት ድርጅቶች የጨረታው አሸናፊ ማድረጋቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በተጠረጠሩበት ወንጀል ዙሪያ ምርመራ እየተደረገባቸው ሲሆን፣ ፍርድ ቤት ቀርበው ጊዜ ቀጠሮ እንደተጠየቀባቸውም ታውቋል፡፡ የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ ምክንያት ይሁን ወይም በግላቸው ባልታወቀ ሁኔታ አገር ውስጥ እንደሌሉ ተሰምቷል፡፡

ዓረና ትግራይ ፓርቲ የአመራር አባላት ጥቃት ተፈጸመባቸው

Wednesday, March 21st, 2012

ዓረና ትግራይ ለሉዓላዊነትና ለዲሞክራሲ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ፣ በ13 አመራር አባላቱ ላይ አካላዊ ጥቃትን ጨምሮ እስራት፣ ግርፋት፣ ከሥራ መባረርና ሁለንተናዊ እንግልትና ድብደባ እንደተፈጸመባቸው አሳወቀ፡፡ ዓረና ትግራይ፣ ፓርቲው ከምድር እንዲጠፋ ሁለንተናዊ ጥቃት እየተፈጸመበት መሆኑን ገልጾ፣ በተለይ በ13 አመራር አባላቱ ላይ እየተፈጸመባቸው የሚገኘው ጥቃት ግን እጅግ አሳሳቢ ሆኖ እንዳገኘው በመግለጫው አመላክቷል፡፡ ጥቃቱ በአስቸኳይ እንዲቆም ያሳሰቡት የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ገብሩ አስራት፣ በአባላቱ ላይ በሚፈጸመው እንዲህ ዓይነት ዘመቻ ምክንያት ፓርቲው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴውን መቼም እንደማያቆም ለሪፖርተር ነግረዋል፡፡

የፓርቲው መግለጫ እንደሚያመለክተው፣ አምስት አባላት ማለትም፣ ወጣት አያሌው በየነ (በ2002 ምርጫ በውቅሮ ማራይ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ)፣ ወጣት አምዛ ደሪ (በኢሮብ ልዩ ወረዳ የዓረና ተወካይ)፣ አቶ ተሾመ ገብረ መድህን (በሽሬ አካባቢ የፓርቲው ተጠሪ)፣ መምህር ይልማ ይኹኖ (በማይጨው ከተማ ተጠሪ)፣ ኢንጂነር አብዱልውሃብ ቡሽራ (የዓረና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል)፤ በቀንና በሌሊት በተለያዩ የሕወሓት አባላት አካላዊ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል፡፡ እንዲሁም ደግሞ፣ አቶ አስገደ ገብረ ሥላሴ (የሥራ አስፈጻሚ አባል) አቶ ተሾመ ገብረ መድህንና ቄስ ጉዕሽ አረጋይ (የተምቤን ነዋሪዎች)፣ አቶ አማረ ተወልደ (የሁመራ ነዋሪ)፣ አቶ ዜናዊ አስመላሽ በፖለቲካ የተቀነባበረ ክስ፣ እስራትና ድብደባ ከደረሰባቸው መካከል በመግለጫው ተጠቅሰዋል፡፡

በሦስተኛ ደረጃ የዓረና ትግራይ ፓርቲ አባል በመሆናቸው ምክንያት በተለያዩ ሰበቦች ከሥራ ተባረሩ ያላቸው መምህር ኃፍቶም ፀጋይ፣ ጋዜጠኛ ስልጣኑ ሕሽ፣ ጋዜጠኛ አንዶም ገብረ ሥላሴ፣ መምህር ጐሽ ገብረ ፃድቅ (የሥራ አስፈጻሚ አባል) ይገኙባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ በትግራይ ክልል ገዢው ፓርቲ ሕወሓት የመንግሥትን መዋቅር ተጠቅሞ፣ ዓረና በክልሉ አንድም አባል እንዳይኖረውና ምንም ዓይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዳያደርግ ከፍተኛ የፖለቲካ ጫና እየተደረገበት መሆኑን፣ “የመንግሥት አካላትና የደኅንነት ሰዎች በቤተሰብ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ በመግባት በፓርቲው አባላት ላይ ከፍተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እየፈጠሩባቸው ይገኛሉ፤” ብሏል፡፡ “ሌላው ቀርቶ ባለትዳር የሆኑ አብዛኞቹ የዓረና አባላት በፖለቲካው ጫናና ጣልቃ ገብነት ምክንያት ትዳራቸው ፈርሷል፤ ቤተሰባቸው ተበትኗል፤” ይላል መግለጫው፡፡

ዓረና ትግራይ አገር ወዳድ የሆኑ ዜጎች በፓርቲው አባላት ላይ የሚደርሰውን ጫና ለማስቆም ከፓርቲው ጎን እንዲቆሙ የጠየቀ ሲሆን፣ “አሁንም ቢሆን በሰላማዊ ትግሉ እስከመጨረሻ መታገላችንን እንቀጥላለን፤” ብሏል፡፡ ዓረና ትግራይ የመድረክ ፓርቲ አባል ሆኖ በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀስ ተቃዋሚ ፓርቲ ሲሆን፣ በምርጫ 2002 የፓርቲው የፓርላማ ተወዳዳሪ የነበሩት የአቶ አረጋዊ ገብረ ዮሐንስ ግድያን ጨምሮ በተለያዩ አባላቱ ላይ እስራት፣ ድብደባ፣ ከሥራ ማባረርና ግርፋት እንደሚፈጸምባቸው ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ የሚመለከታቸው የክልሉ ባለሥልጣናት የዓረና ፓርቲ መግለጫን በተመለከተ ለማናገር የተደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡

በቤንች ማጂ ዞን የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች አካባቢውን ልቀቁ መባላቸውን ገለጹ

Tuesday, March 20th, 2012

በደቡብ ክልል ቤንች ማጂ ዞን ጉራፋርዳ ወረዳ የሚኖሩ በርካታ የአማራ ክልል ተወላጆች ሕገወጥ ሰፋሪዎች ናችሁ በሚል እስከ የካቲት 30 ቀን 2004 ዓ.ም. ድረስ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ የተላለፈላቸው መሆኑን ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ የጉራፋርዳ ወረዳ አመራሮችና የቀበሌ ኃላፊዎች በሰጧቸው ፈቃድ መሠረት በሕጋዊ መንገድ መሬት ተረክበው በአካባቢው መኖር መጀመራቸውን የገለጹት የአማራ ክልል ተወላጆች፣ ባልጠበቁትና ባላሰቡት ሁኔታ ሀብትና ንብረታቸውን ጥለው አካባቢውን እንዲለቁ ትዕዛዝ መተላለፉ አስደንጋጭ መርዶ እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡

ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚሉት፣ በጉራፋርዳ ወረዳ በሚገኙ ቀበሌዎች የሚኖሩ በርካታ የአማራ ክልል ተወላጆች በሕጋዊ መንገድ ለተረከቡት መሬት ግብር ሲከፍሉ መቆየታቸውን የሚያረጋግጥ የግብር ካርድ እንዲሁም የወረዳና የቀበሌ አመራሮች ‹‹መሬት ይሰጣቸው›› ብለው ትዕዛዝ ያስተላለፉበት ደብዳቤ በማስረጃነት ቢኖራቸውም፣ ‹‹ሕገወጥ ናችሁ›› በሚል አካባቢውን በአስቸኳይ ለቅቀው እንዲወጡ ተወስኖባቸዋል፡፡
በክልሉ ከሰፈሩበት ጊዜ ጀምሮ ቡና፣ ፓፓያና የመሳሰሉ ተክሎችን በማምረት ሕይወታቸውን መቀየር ችለው እንደነበር የሚናገሩት እነኝሁ ሰፋሪዎች፣ ለሠሩት ቤትና ለተከሉት ተክል ግምት እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ የወረዳው ኃላፊዎች ‹‹ቆርቆሮውን ነቅላችሁ መሄድ ትችላላችሁ›› የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ገልጸዋል፡፡

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የጉራፋርዳ ነዋሪ፣ ‹‹ጉዳያችን እስከ እንባ ጠባቂ ተቋም ድረስ ብንወስድም ምንም በጐ ምላሽ ልናገኝ አልቻልንም፡፡ በሕጋዊ መንገድ ያፈራነውን ሀብትና ንብረት ጥላችሁ ሂዱ ማለት ትልቅ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ነው፤›› በማለት በሰፋሪዎች ላይ እየደረሰ ያለውን በደል ተናግረዋል፡፡

የቤንች ማጂ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዓለማየሁ አይበራ በበኩላቸው፣ በሕጋዊ መንገድ የሰፈሩ የአማራ ክልል ተወላጆች አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ ስለመደረጉ የሚያውቁት ነገር አለመኖሩን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ሕገወጥ ሰፋሪዎች መውጣት ካለባቸው የደቡብና የአማራ ክልል እንዲሁም የፌዴራል መንግሥታት አውቀውት በታቀደ መልኩ መከናወን እንዳለበት የገለጹት አቶ ዓለማየሁ፣ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ከአማራ ክልል የመጡ ሰፋሪዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ክልሉን ለቅቀው እንዲወጡ የተደረገበት አሠራር ይኖራል የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹የክልሉ መንግሥት ሰብዓዊነት የጐደለው ሥራ የሚሠራ አይደለም፡፡ ማንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በሕገወጥ መንገድ ስለመጣ በሕገወጥ መንገድ ውጣ ብለን እናባርረውም፤›› ያሉት አቶ ዓለማየሁ፣ ከአንድ ዓመት በፊት በደቡብ ክልል የሚኖሩ ሕገወጥ ሰፋሪዎችን በሚመለከት የአማራ ክልልና የደቡብ ክልል ኃላፊዎች ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ የአማራ ክልል የራሱን ዝግጅት በማድረግ ከ800 በላይ የሚሆኑ በደቡብ ክልል ይኖሩ የነበሩ ሰፋሪዎች ወደ ባህር ዳር እንዲመለሱ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡ አያይዘውም፣ ‹‹ከአማራ ክልል ወደ ደቡብ ክልል የሚደረግ ሰፈራ የለም፤ ወረዳዎች ላይ የምትፈርደው ነገር ይኖራል ብዬ አላስብም፣ መመለስ ያለበት ሰው ካለ መመለስ አለበት፡፡ ይሄ የእኛም የክልሉም አቋም ነው፡፡ ነዋሪ ያልሆነን ሰው ሥርዓት በሌለው ሁኔታ ተቀብለን ልናሰፍር አንችልም፤›› ብለዋል፡፡

ከክልሉ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በደቡብ ክልል ጉራፋርዳ ወረዳ በሚገኙ 22 ቀበሌዎች ውስጥ በተለያየ ጊዜ ከሰሜኑ የአማራ ክልል መጥተው ለረጅም ዓመታት ኑሮአቸውን በዚያው የመሠረቱ ከ78 ሺሕ በላይ ዜጐች የሚገኙ ሲሆን፣ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳደር በተላለፈ ቀጥተኛ መመርያ ከ1999 ዓ.ም. በኋላ ከሰሜን አካባቢ የመጡ ሰፋሪዎች ወደመጡበት እንዲመለሱ ታዟል፡፡ ይህን ውሳኔ ተከትሎም በአለንጋ ቀበሌ ማርያም ሰፈር በሚኖሩ ሰዎች ላይ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆን የወረዳው የገጠር ልማት ምክትል ኃላፊ አዘዋል፡፡

የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽፈራው ሸጉጤ ከሦስት ዓመት በፊት ለቤንቺ ማጂ ዞን አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በጻፉት ደብዳቤ እስከ 1999 ዓ.ም. ነሐሴ 30 ድረስ የመጡ በወረዳ፣ በቀበሌ አመራርም ይሁን በራሳቸው መንገድ መሬት የያዙ ዜጐች እስከ 2 ሔክታር የእርሻ መሬትና 1000 ካሬ ሜትር የቤት መሥሪያ እንዲሰጣቸውና ባሉባቸው ቀበሌያት እንደሕጋዊ ሰፋሪ ተመዝግበው የክልሉ ነዋሪ መሆናቸውን አውቀው በክልሉ ሕጐች መሠረት እንዲተዳደሩ እንዲደረግ፣ ከ1999 ዓ.ም. ነሐሴ 30 ቀን 2003 ዓ.ም. በኋላ የመጡ ማናቸውም ዜጐች ወደመጡባቸው አካባቢዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲሸኙ እንዲደረግና ይህም ከቀሪዎቹና ከሚሄዱት ዜጐች ጋር በሚደረግ ውይይት መደበኛ የሕግ አፈጻጸም ተከትሎ ተግባራዊ እንዲደረግ ትዕዛዝ አስተላልፈው ነበር፡፡

ፕሬዚዳንቱ በዚሁ ደብዳቤያቸው እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ሰፋሪን በሚመለከት ያለው አሠራር ከክልል ክልል የሚፈጸም ሳይሆን በክልሎች በውስጣቸው ብቻ እንዲፈጽም የጋራ አገራዊ ስምምነት ላይ የተደረሰ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ በርካታ ሕገወጥ ሰፋሪዎች የያዙት መሬት በክልሉም ሆነ በአገሪቱ በሰፈራ ለሚደራጁ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በመንግሥት ዕውቅናና ባለቤትነት ከሚሰፍሩ ሰፋሪዎች በእጅጉ የተለየና የሰፋ በመሆኑ፣ የሕገወጥ የመሬት ይዞታ መጠንን ማስተካከል እንደሚገባ ስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቀው ነበር፡፡

የክልል መስተዳደሩን ትዕዛዝ ተከትሎም የጉራፈርዳ ወረዳ የተ/ሀ/አ/ጥበቃ ኃላፊና የግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ለአለንጋ ቀበሌ አስተዳደር ጥቅምት 29 ቀን 2004 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ፣ የቀበሌው አመራሮችና ባለሙያዎች በሕገወጥ መንገድ መሬት የያዙ አርሶ አደሮችን ተከታትለው እንዲያስረክቡ፣ ይህንን የማያደርጉ የቀበሌ አመራሮችና ባለሙያዎች ካሉ ግን በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ አስጠንቅቀዋል፡፡

‹‹በ2003 ዓ.ም. መጨረሻ በወረዳችን በተደረገው የመሬት ልክዮሽ ሕጋዊና ሕገወጥ አርሶ አደሮች በልኬቱ ጊዜ ተለይቶ በሕገወጥ መንገድ /በሕገወጥ ምርትና በግዥ/ መሬት የያዙ አርሶ አደሮች መሬቱ ለመንግሥት ሙሉ በሙሉ ገቢ መደረጉ ይታወቃል፡፡ ምክንያቱም በመሬት አስተዳደር አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 110/99/ በደንብ ቁጥር 66/2000 አንድ አርሶ አደር መሬት ተለክቶ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር የሚሰጠው መሬቱን በሕጋዊ መንገድ ሲያገኝ ብቻ መሆኑ ተቀምጧል፡፡ ስለሆነም እስካሁን ያመረቱትን አንስተው ለቀበሌ አስተዳደር መሬቱን እንዲያስረክቡና መሬቱ የሕዝብና የመንግሥት መሆኑን አውቆ፣ ቀበሌው በደረሰው ስም ዝርዝር መሠረት ተከታትሎ መሬቱን እንዲረከብና ያልተለዩትን አሁንም በየጐጡ በመለየት ሪፖርት እንዲያደርጉ እያሳሰብን ክትትል በማያደርጉ የቀበሌ አመራርና ባለሙያ በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ጭምር በጥብቅ እናሳስባለን፤›› ይላል የወረዳው የግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊው ደብዳቤ፡፡

የመኢአድ ምክትል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አበበ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የመንግሥት ኃላፊዎች ነዋሪውን ሕዝብ ‹‹የያዝኩትን መሬት በፍቃዴ መልቀቄን በፊርማዬ አረጋግጣለሁ›› የሚል ወረቀት ላይ እንዲፈርሙ እያስገደዱ ነው፡፡ የሚሰፍሩበት ተለዋጭ ቦታ ሳይሰጣቸው በመሬት ላይ የተከሉት ተክል፣ ያፈሩት ሀብትና ንብረት ግምት ሳያገኝና ካሳ ሳይከፈላቸው ከክልሉ እንዲወጡ እየተደረጉ ነው፡፡

መንግሥት ለሕዝብ ከማሰብና ከመቆርቆር ይልቅ፣ ሕዝብን በማማረርና በመበደል ሥራ ላይ መጠመዱን የገለጸው መኢአድ፣ ይህ የመንግሥት ድርጊት ኃላፊነት ከጐደለው መንግሥት የሚጠበቅ እንጂ ለሕዝብ ቆሜያለሁ ከሚል መንግሥት የማይጠበቅ ተግባር በመሆኑ፣ መንግሥት እያካሄደ ካለው ዜጐችን በማፈናቀል እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንዲያቆም ጥሪ አቅርቧል፡፡

ከክልሉ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የጉራፋርዳ ወረዳ ያዘጋጀው የመሬት ማስመለሻ ቅጽ እንዲህ ይላል፡፡

‹‹እኔ አቶ/ወ/ሮ ______ የመጣሁበት አገር ______ ዞን ______ ወረዳ ______ ቀበሌ ______ ጎጥ ሲሆን፣ በ______ ዓ.ም. ከነበርኩበት አገር መጥቼ ከነ______ ቤተሰቦቼ ጋር በተለያየ መንገድ መሬት ይዤ ሳርስ የነበርኩ ሲሆን፣ አሁን የክልሉ መንግሥት ባወጣው ደንብና መመርያ እንዲሁም የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የተሻሻለው ሕገ መንግሥት አንቀጽ 40 ንዑስ አንቀጽ 3 በሚደነግገው መሠረት፣ መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የክልሉ ሕዝቦች የጋራ ንብረት በመሆኑ በሕገወጥ መንገድ በያዝኩት መሬት ላይ ያለኝ ______ እንደደረሰ በማንሳት ለቀበሌው መሬት አስተዳደር በቀን ______ ለማስረከብ ይህንን መተማመኛ ሰጥቼ የፈረምኩ ሲሆን፣ በተባለው ቀንና ሰዓት ባልለቅ /ባላስረክብ/ እንዲሁም ሌላ ተጨማሪ አዝዕርት ብዘራ በሕግ እንድጠየቅ ተስማምቻለሁ፡፡››

አንድ ኩንታል ጤፍ 1,800 ብር ደረሰ

Monday, March 19th, 2012

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጤፍ ዋጋ በሚያስገርም ሁኔታ ሲያሻቅብ ሰንብቶ በየወፍጮ ቤቶችና በየችርቻሮ መሸጫዎች ለአንድ ኩንታል እስከ 1700 ብር እየተጠየቀበት በመሆኑ፣ ሸማቾችን ከማስደንገጡም በላይ የኑሮ ውድነቱን ይበልጥ እያጦዘው ነው፡፡ የዋጋው ንረት እጅግ ከሚያሳስባቸው መካከል የቀን ሠራተኞች፣ የወር ደመወዝተኞች እንዲሁም ጡረተኞች በዋነኝነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የጤፍ ዋጋ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ጭማሪ ማድረጉ በተለይ የምግብ ቤት ቋሚ ተጠቃሚ ለሆኑ ግለሰቦችና ለላጤዎች አስቸጋሪ እንደሆነባቸው እየገለጹ ነው፡፡ ከአንድ ወር በፊት በአንድ ሺሕ ብር ይሸጥ ነበረው ማኛ ጤፍ አሁን እስከ 1700 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡

በርካታ የቤተሰብ አባላትን የሚያስተዳደሩ የወር ደመወዝተኛ ሠራተኞች ጤፍን ከበቆሎ፣ ከማሽላና ከሩዝ ጋር እየቀላቀሉ መጋገገር የተለመደ ተግባር እየሆነ መምጣቱን ይናገራሉ፡፡ ለእነዚህ ሰዎች ንፁህ የጤፍ እንጀራ ድሮ ቀረ የሚባልበት ደረጃ ላይ መድረሱ በስፋት እየተነገረ ነው፡፡

ምግብ ቤቶች የጤፍ ዋጋ መናርን ተንተርሰው የዋጋ ጭማሪ ማድረግ የጀመሩ ሲሆን፣ እንጀራ ጋግረው የሚሸጡትም በሁለት ብር ከሃያ አምስት ሳንቲም ሲያቀርቡ የነበረውን እንጀራ አሁን ወደ ሦስት ብር ከፍ አድርገው መሸጥ ጀምረዋል፡፡

በአቅርቦቱ ላይ ካልሆነ በቀር የጤፍ ምርት ችግር እንደሌለ ያስታወቀው መንግሥት፣ ወደፊት የዋጋ ሁኔታ እንደሚስተካከል በመግለጽ ችግሩን አስተባብሏል፡፡ ከአቅርቦት መስተጓጎል በተጨማሪ በዚህ የምርት ወቅት የጤፍ እጥረት አለ እየተባለ ነው፡፡

በገበያው ውስጥ እጅግ ተፈላጊው የአዳኣ ጤፍ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ዋጋ የሚጠየቅበት ሲሆን፣ የአካባቢው ገበሬዎች ከጤፍ ይልቅ ምስር አምርተው መሸጥ የሚፈልጉ በመሆናቸው፣ ከዚያ አካባቢ የሚመጣው ጤፍ መጠን እየቀነሰ መሆኑን ነጋዴዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት አንድ ኩንታል ምስር እስከ 1,800 ብር ድረስ እንደሚያወጣ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ይህ በመሆኑም በማዳበርያ ውድነት፣ ጤፍ ለማምረት ያለው ድካምና ሌሎች አማራጮች ታክለውበት፣ ገበሬው ወደ ጥራጥሬ ምርት እያመራ እንደሚገኝ እየተገለጸ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በገበያው ውስጥ ያለውን የምርት እጥረት በማሰብ የተሻለ ዋጋ ለማግኘት በማሰብ ምርቱን ከማውጣት እየተቆጠበ እንደሚገኝ፣ በመሳለሚያ እህል በረንዳ ሪፖርተር ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ነጋዴዎች ገልጸዋል፡፡ የሰሞኑን የበልግ ዝናብ አለመኖር ታሳቢ በማድረግም ከማሳቸው ላይ ምርት ያላነሱ ገበሬዎች እንዳሉም እየተነገረ ይገኛል፡፡

ከዚህ ባሻገር ደግሞ በዱከም ከማዕከላዊ ገበያ ውጪ ወደተለያዩ ቦታዎች የጤፍ ምርት እየተጫነ መሆኑን ነጋዴዎቹ ይናገራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከእህል በረንዳው ዋጋ በላይ የእህል ግብይት እየተካሄደበት በመሆኑ ለነጋዴዎች ዋጋ መጨመር ሰበብ እየሆነ እንደሚገኝ ይነገራል፡፡

የጤፍ ዋጋ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ከደብረ ብርሃን እስከ አርባ ምንጭ ድረስ ለሚገኙ ነዋሪዎች ራስ ምታት መሆን ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ በደብረ ብርሃን ማኛ ጤፍ 1500 ብር ሲያወጣ በአርባ ምንጭ ከ1300 ብር በላይ እየተሸጠ ነው፡፡

በአዲስ አበባው የእህል በረንዳ ገበያ ልዩ ማኛ ጤፍ እስከ 1750 ብር እንደሚሸጥ ሸማቾች ቢናገሩም፣ ነጋዴዎቹ ግን ይህን ዋጋ በሃምሳ ብር ይቀንሱታል፡፡

በአዲስ አበባ የጥራጥሬና የእህል ዋጋና አቅርቦት የሚወሰንበት የመሳለሚያው እህል በረንዳ ገበያ ከመስከረም ወር ጀምሮ ጭማሪ ሳያሳይ የመጣው የጤፍ ዋጋ፣ በመስከረም ወር በኩንታል ይሸጥበት ከነበረው በአንፃራዊነት ከተረጋጋበት ዋጋ ተነስቶ መጋቢት ላይ ዋጋው ንሮ እየተሸጠ ነው፡፡

መንግሥት የጤፍ ዋጋ ተወዷል ብሎ ለማረጋጋት እጁን ካስገባ ከዚህ የበለጠ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ሊከሰት እንደሚችልም ነጋዴዎቹ ያስጠነቅቃሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ጣልቃ መግባቱ ለሸማቹ ያተረፈለት ነገር እንደሌለ በማስታወስ ገበያው እንዳይነካካ መንግሥትን የመከሩት የመሳለሚያ ነጋዴዎች፣ የደላላዎች ተፅዕኖ እንዲቀንስ ባይደረግ ኖሮ አሁን ከተፈጠረው የከፋ የዋጋ ንረት ሊፈጠር ይችል እንደነበር የሚገልጹም አልጠፉም፡፡

ከጤፍ ዓይነቶች ሁሉ በዝቅተኛ በዋጋ የሚሸጠው ጥቁር ጤፍ በኩንታል 920 ብር ሲያወጣ፣ በታህሳስ ወር ግን 746 ብር ይሸጥ እንደነበር ለመረዳት ተችሏል፡፡

በየጊዜው እንዲህ ዋጋው እየተሰቀለ የመጣው የጤፍ ዋጋ ከድሃው ባሻገር የአንዳንድ ባለሥልጣናትንም ጓዳ እንደነካካው ገበያው አካባቢ የሚወራ ሲሆን፣ ከከተማው በተለየ ሁኔታ በእህል በረንዳ የታየው የዋጋ ቅናሽ የማይታመን እንደሆነባቸው መናገራቸውን የሪፖርተር ምንጮች ተናግረዋል፡፡

ነጋዴዎች የጤፍ ገበያው ጣልቃ ካልተገባበት በራሱ ጊዜ ዋጋው ይቀንሳል የሚል እምነት ቢኖራቸውም፣ የጤፍ ዋጋ ግን ወደ ምግብ ቤቶችና ወደ ሌሎች አገልግሎት መስጫዎች እየተሻገረ በመሆኑ የምግብ ዋጋውን እንደሚያንረው ነው የሚጠበቀው፡፡

በሌላ በኩል የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ ባለፈው ወር የአገሪቱ የዋጋ ግሽበት 36.3 መድረሱንና በአንድ ወር ብቻ የአራት በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ሲያመለክት፣ የምግብ ዋጋ ግሽበት ከአምናው የየካቲት ወር ዋጋ ሲነፃፀር የ47.4 በመቶ ጭማሪ እንዳስመዘገበ ያሳያል፡፡

በአዋሳ ከተማ በፖሊሶችና በነጋዴዎች መካከል በተደረገ የተኩስ ልውውጥ 6 ሰዎች ቆሰሉ

Saturday, March 17th, 2012

በአስፋው ብርሃኑ

(ሪፖርተር) — መጋቢት 5 ቀን 2004 ዓ.ም ከምሽቱ 3፡30 አካባቢ በሐዋሳ ከተማ ዓረብ ሰፈር አካባቢ ለአራት ተከታታይ ሰዓታት በጉምሩክ ፖሊሶችና በኮንትሮባንዲስቶች መካከል በነበረው የተኩስ ልውውጥ ስድስት ሰዎች ቆሰሉ፡፡ የተኩሱ መንስዔ የሆነው በልባሽ ጨርቅ የተሞሉ በርካታ የኮንትሮባንድ ቦንዳዎች በሐዋሳ ከተማ አሮጌው ገበያ ውስጥ ባለው አንድ መጋዘን ተደብቀው በመገኘታቸው ነው፡፡ የፌደራል ፖሊስ ዕቃዎቹን ለማውጣት ሲሞክር በአካባቢው በነበሩ ሰዎች የድንጋይ እሩምታ በመለቀቁ እንደሆነ በወቅቱ በስፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ያልጠበቁት ነገር የገጠማቸው ፖሊሶች ተጨማሪ ኃይል ጠይቀው ለመከላከል ቢሞክሩም፣ የኮንትሮባንዲስቶቹ ደጋፊ የሆኑ ግለሰቦች ያለማቋረጥ የድንጋይ ውርወራ በማድረጋቸውና መሣሪያ የታጠቁም ተኩስ በመጀመራቸው እንደሆነ አስተየየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡

በገበያው አካባቢ የሻይ ቤት ባለቤት የሆኑት አቶ መሐመድ ነስረዲን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከምሽቱ 3፡30 አካባቢ የተጀመረው ተኩስ ያለማቋረጥ እስከ ሌሊቱ 7፡00 ሰዓት ድረስ ቀጥሏል፡፡ ‹‹መሰል የተኩስ እሩምታ በሕይወቴ ያየሁት በ1983 ዓ.ም ደርግ የወደቀ ጊዜ ነው፡፡ ቢሆንም የዚያን ቀን የምሽቱ ተኩስ የተለየ ነው፡፡ በአንዴ አካባቢው ሩዋንዳ መሰለ እኮ፤›› በማለት አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ነዋሪ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ፖሊሶቹ በአካባቢው በብዛት የወጣውን ሕዝብና ኮንትሮባንዲስቶቹን መለየት ተስኖዋቸው የተቃውሞ ሠልፍ በመምሰሉ አስለቃሽ ጭስ መጠቀማቸውን የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡ ከቆሰሉት ስድስት ሰዎች መካከል አንድ ሕፃን እንደሚገኝበት፣ በወቅቱ የነበረው አዝማሚያ ከተማውን ለኹከት ያጋለጠ እንደነበረ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በሐዋሳ ከተማ ሰልባጅ ገበያ መሀል በጠራራ ፀሐይ በፖሊሶችና በኮንትሮባንዲስቶች መካከል ለ1፡00 ሰዓት የቆየ ግርግር ተከስቶ እንደነበረ የሚያስታውሱት የዓረብ ሰፈር ነዋሪዎች፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ኬላዎችን መቆጣጠር ተስኖታል ወይም ፈታሾች አካባቢ ችግር አለ በማለት ባለሥልጣኑ ራሱን ቢያጠራ ይሻለዋል የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በሐዋሳ ገበያ ማናቸውም ሸቀጦችና ዕቃዎች በየመደብሩ ጥበቃ ተመድቦላቸው እንደሚያድሩና በተፈጠረው ግርግር ገበያውን የመዝረፍ አዝማሚያ ስለነበር፣ ፖሊሶቹ ያንን ድርጊት ለመከላከል ጥረት እንዳደረጉ ትዕግሥቱ ረድኤት የተባለ የአካባቢው ባለቡቲክ ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡

በምሽቱ ስለተፈጠረው ሁኔታ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሐዋሳ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ያሬድ ፈቃደን ተጠይቀው፣ ‹‹በሐዋሳ ከተማ ገበያ ውስጥ የተከማቸ የኮንትሮባንድ ዕቃ መኖሩን ባለን መረጃ ከክልሉ፣ ከፌደራልና ከከተማው አስተዳደር ፖሊስ ኃይል በማቀናጀት ወደተባለው ክምችት ልንገባ ስንል፣ ኮንትሮባንዲስቶቹ ያዘጋጇቸው ምንም የማያውቁ ወጣቶች ድንጋይ በመወርወርና ኹከት በመፍጠር የመከላከል እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የተኩስ ልውውጥ ተደርጓል፤›› ሲሉ ሁኔታውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹የታጠቁ ኮንትሮባንዲስቶችም ስለነበሩ ወደ ላይ እየተኮሱ ከተማዋን ለመረበሽ ፈልገው ነበር፡፡ እኛ የማንለቃቸው መሆኑን ሲያውቁ ወደ ሌሎች የከተማ አካባቢዎች እየሄዱ በተኩስ ሕዝቡን ለማነሳሳት ጥረት አድርገው ነበር፤›› በማለት በምሽቱ የነበረው የተኩስ ልውውጥ ለማንኛውም ነዋሪ አስደንጋጭ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ልባሽ ጨርቆችና 10 ኩንታል ቡና ተይዞ ጉዳዩ እየተጣራ መሆኑን ታውቋል፡፡ ኬላዎች አካባቢ ልል የሆነ ፍተሻ አለ ስለመባሉ እንደማይስማሙበት ሲገልጹ፣ ‹‹በመሰል ተግባር የተሰማሩ ሰዎች በጠራራ ፀሐይ እንደማይፈጽሙና በገጠር ጋሪና አህያ ተጠቅመው እንደሚያሻግሩ በርካታ ጊዜ ደርሰንባቸዋል፡፡ የዚያን ምሽት ዕርምጃ የዚህ እንቅስቃሴ አካል ነው፤›› ብለዋል፡፡ በወቅቱ የደረሰ አደጋ ስለመኖሩ የተጠየቁት አቶ ፈቃደ፣ በሰውም ሆነ በንብረት ላይ አደጋ እንዳይደርስ የፖሊስ ኃይሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረጉ ምንም ዓይነት አደጋ አልተፈጠረም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ድንገተኛ ጦርነት የተፈጠረ የመሰላቸው የሐዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ተኩሱ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ሳይተኙ ለሊቱን እንዳጋመሱ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ መብራት መጥፋት አውሮፕላኖች በጨለማ ሲያርፉ አመሹ

Wednesday, March 14th, 2012

በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከትናንት በስቲያ ከቀኑ 11 ሰዓት እስከ ምሽቱ 2፡34 ሰዓት ድረስ የአውሮፕላን መንደርደርያዎች መብራቶች በመጥፋታቸው አውሮፕላኖች በጨለማ ሲያሳርፉ ማምሸታቸውን ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ችግሩ መፈታቱን ገልጾ፣ የጉዳዩ ባለቤት ኤርፖርቶች ድርጅት መሆኑን ተናግሯል፡፡

ለመንደርደሪያዎች መብራት መጥፋት ምክንያቱ ኤርፖርቶች ድርጅት በማሠራት ላይ የሚገኘው የአውሮፕላን ማቆሚያ፣ ማረፊያና ማኮብኮቢያ ማስፋፊያ ፕሮጀክትን የሚሠራው የቻይናው የመንገድና ድልድይ ግንባታ ኮርፖሬሽን (CRBC)፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሩን ሳይበጥሰው እንዳልቀረ ምንጮች ተናግረዋል፡፡

አውሮፕላን ለማረፍ ትክክለኛ አቅጣጫ በመያዝ ዝቅ ሲል ቀይ፣ ከፍ ሲል ሰማያዊና ትክክለኛ አቅጣጫውን ሲይዝ ደግሞ ነጭ መብራት የሚያሳየው ፓፒ (PAPI) የሚባለው ብርሃን ሰጪ መሣርያ ጠፍቶ እንደነበር ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡

አውሮፕላኑ ከማረፊያ ሜዳው ያለውን ርቀት በማንበብ የሚያሳውቀው መሣሪያ (Distance Measuring Equipment) ጠፍቶ እንደነበር የገለጹት ምንጮቹ፣ አውሮፕላኖቹ በጨለማ ያርፉ የነበሩት ካርጐ ተርሚናል ውስጥ በነበረ አውሮፕላን ፓይለቱ ብርሃን እያበራላቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

አንድ አውሮፕላን ከአንድ አገር ተነስቶ ወደሚያርፍበት አገር እስከሚደርስ ድረስ የሚበቃውን ነዳጅ ከሞላ በኋላ፣ በሚያርፍበት አገር የተለያዩ አጋጣሚዎች ተፈጥረው ለማረፍ ባይችል፣ ለማረፍ በሚችልባቸው ቅርብ አገሮች ወይም ማረፊያዎች ድረስ የሚያደርሰውን ወይም በአየር ላይ የሚያቆየውን ተጨማሪ ነዳጅ መያዝ እንዳለበት የገለጹት ምንጮቹ፣ ምናልባት አውሮፕላኖቹ በጨለማ እንዲያርፉ የተደረገው፣ መጠባበቂያ ነዳጅ ስላልነበራቸው ሳይሆን እንደማይቀር ግምታቸውን ገልጸዋል፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ በቅርቡ ወደምትገኘው ጂቡቲ በመሄድ ማረፍ ይችሉ እንደነበርም አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያውያን ፓይለቶች በአየር መንገዱ ረጅም ዓመታት የሠሩና ለአውሮፕላን ማረፊያው እንግዳ ባለመሆናቸው፣ ባካበቱት ልምድ በጨለማ ለማሳረፍ መቻላቸውን የገለጹት ምንጮቹ፣ አውሮፕላኑ የማረፊያ ሜዳውን ስቶ ቢያርፍ ችግር ይከተል እንደነበር ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን መጠባበቂያ የኤሌክትሪክ ኃይል (ከፍተኛ ጄኔሬተር) ማዘጋጀት እንደነበረበት የተናገሩት ምንጮቹ፣ ባለሥልጣኑ መጠባበቂያ እንዳለውና እንደሌለው ካረጋገጠ በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በራሱ ማዘጋጀት እንደነበረበት አስገንዝበዋል፡፡ ዩፒኤስ (UPS) እንኳን ቢኖር ኖሮ ከሁለት ሰዓታት በላይ ብርሃን ማግኘት ይቻል እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡

ሌላ ጊዜ በአውሮፕላን ማረፊያው ተመሳሳይ የመብራት መጥፋት ችግር ያጋጥም እንደነበር የጠቆሙት ምንጮቹ፣ ወዲያውኑ መብራት ይመጣ ስለነበር መዘናጋት የተፈጠረው ምናልባት ተመሳሳይ ክስተት ነው በሚል ሳይሆን እንደማይቀር ተናግረዋል፡፡

በ25 ሺሕ ጫማ ከፍታ ላይ ጂቡቲን ጨምሮ በአገሪቱ ያሉትን አየር መንገዶችን የሚቆጣጠረው የአካባቢ መቆጣጠሪያ ማዕከልም ጠፍቶ ማምሸቱን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡

ከትናንት በስቲያ ከቀኑ 11 ሰዓት እስከ ምሽቱ 2፡34 ሰዓት ድረስ ጠፍቶ ስለነበረው የአውሮፕላን መንደርደሪያ ሜዳ መብራት ጉዳይ ማብራሪያ እንዲሰጡን ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽንና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ ‹‹በሕጉ መሠረት ወይም በዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ሕግ፣ መብራት ለ24 ሰዓታት መሥራት አለበት፡፡ ግዴታም ነው፡፡ ለማንኛውም አሁን ችግሩ ተፈትቷል፤›› ካሉ በኋላ፣ በዋናነት የሚመለከተው የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የኤርፖርቶች ድርጅትን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ሊሳካልን ባለመቻሉ ምላሻቸውን ማካተት አልቻልንም፡፡

ኤርፖርቶች ድርጅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ማረፊያን ለማስፋፋት ለቻይናው የመንገድና ድልድይ ግንባታ ኮርፖሬሽን በ66 ሚሊዮን ዶላር ኮንትራት ሰጥቶ እያሠራ ይገኛል፡፡ ፕሮጄክቱ ሲጠናቀቅ ቦይንግ 747 እና 777 ግዙፍ አውሮፕላኖችን ጨምሮ 44 አውሮፕላኖችን በአንድ ጊዜ ለማቆም እንደሚችል ታውቋል፡፡ እስካሁን ግን 19 አውሮፕላኖችን ብቻ ነበር ማቆም የሚቻለው፡፡

ቴዲ አፍሮ ከሞት ቅጣት ያዳነው ኢትዮጵያዊ ሀገሩ ገባ

Friday, March 9th, 2012

የሰው ሕይወት አጥፍቷል በሚል በአሥር ቀናት ውስጥ በሞት እንዲቀጣ ወይም የነፍስ ዋጋ 700 ሺሕ ብር እንዲከፍል የፍርድ ውሳኔ ተላልፎበት፣ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) ሙሉ ክፍያውን (700 ሺሕ ብር) ከፍሎ ያተረፈው ኢትዮጵያዊው አስመሮም ኃይለ ሥላሴ ገብረ ኢየሱስ፣ የካቲት 14 ቀን 2004 ዓ.ም ከእስር ተፈታ፡፡ የካቲት 15 ቀን 2004 ዓ.ም አዲስ አበባ ገብቷል፡፡

አስመሮም የቀድሞ የሶማሊያ ግዛት በነበረችው ፑንትላንድ ቦሳሶ ወደብ አካባቢ ከሦስት ዓመታት በፊት በሚኖርበት ቤት ውስጥ ከሌሊቱ 7፡30 ሰዓት ሲሆን በር ሰብረው አደጋ ሊያደርሱበት በሞከሩ ሶማሊያውያን ላይ በወሰደው የመከላከል ዕርምጃ፣ አንድ ሰው ሞቶ ሌላኛው በመቁሰሉ ለእስር መዳረጉንና በመጨረሻም በሞት እንዲቀጣ ወይም ገንዘብ እንዲከፍል ተወስኖበት ነበር፡፡ ለነፍስ ዋጋ ክፈል የተባለውን 700 ሺሕ ብር በአሥር ቀናት ውስጥ ካልከፈለም በዕለተ ዓርብ ጥቅምት 17 ቀን 2004 ዓ.ም ግድያው ይፈጸምበት ነበር፡፡ ጥቅምት 14 ቀን 2004 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ የምትኖረው እህቱ ልዋም ኃይለ ሥላሴ ወደ ሪፖርተር ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል መጥታ ባቀረበችው ጥቆማ መሠረት ሁኔታው በመዘገቡ፣ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) በጋዜጣው የወጣውን ዜና በማንበብ አስመሮምን ሊታደገው ችሏል፡፡ ሕይወቱ መትረፉንም በወቅቱ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በፑንትላንድ ግዛት ታስሮ ሦስት ዓመታት ከአንድ ወር የቆየው አስመሮም፣ ስደት የጀመረው በኢትዮጵያ ኤርትራ ጦርነት ወቅት በ1990 ዓ.ም መሆኑን ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ ተወልዶ ያደገው አስመራ ከተማ ውስጥ መሆኑን የገለጸው አስመሮም፣ እናትና አባቱ ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው በወቅቱ የኤርትራ መንግሥት ያለምንም ሀብትና ንብረት ስላባረራቸው እሱና ጓደኞቹ ወደ ምፅዋ መሰደዳቸውንና ከቤተሰቡ ጋር መለያየቱን ተናግሯል፡፡

ከምፅዋ 2000 ናቅፋ በመክፈል ወደ የመን፣ ከየመን ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ገብቶ የተወሰነ ጊዜ እንደሠራ ተጠርዞ ወደ ኢትዮጵያ መመለሱን የሚናገረው አስመሮም፣ ከቤተሰቦቹ ሲለያይ አድራሻ ባለመቀበሉና ኢትዮጵያንም ሆነ ኢትዮጵያዊ ዘመዶቹን ስለማያውቃቸው፣ አዲስ አበባ መጥቶ በያዛት ገንዘብ ከመዝናናት በስተቀር ምንም ማድረግ አለመቻሉን ገልጿል፡፡

ለአሥር ጊዜያት ስደትን ሞክሮ ከተወሰነ ጊዜ የሥራ ቆይታ በስተቀር ተረጋግቶ መሥራት አለመቻሉን፣ እዚያ ሆኖ ሲሠራ ለቤተሰቡ ገንዘብ የሚልክበት አድራሻ ስለሌለው ሌሎች ለቤተሰብ ሲልኩ ያዝን እንደነበር ገልጾ፣ በስምንተኛው የስደት ጉዞው ወንድሙን ጅዳ እስር ቤት ውስጥ እንዳገኘውና አብረው ተጠርዘው ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላ ቤተሰቦቹን ማግኘቱን አውስቷል፡፡

ቤተሰቦቹን (አባቱን፣ እህትና ወንድሞቹን) መቀሌ ሄዶ ካገኘና አብሯቸው የተወሰነ ጊዜ ከተቀመጠ በኋላ ምንም የሚሠራው በማጣቱና አባቱ ሲቸገሩ (እናቱ በሕይወት የሉም) ማየት ያልቻለው አስመሮም፣ ተመልሶ ወደ ስደት መጓዙን ገልጿል፡፡ የተወሰነ ጊዜ ቤተሰቡን ከረዳ በኋላም ተጠርዞ እንደገና መመለሱንና ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ስደት ሲሄድ ከሐረር ወደ የመን የተጓዘች ፈሪሀ አብዲ የተባለችን ልጅ ማግኘቱንና በፍቅር አብረው መኖር መጀመራቸውን ተናግሯል፡፡

ከፈሪሀ ጋር በፑንትላንድ ግዛት ቦሳሶ ወደብ ላይ ሻይ ቤት መክፈታቸውንና ሦስት ልጆች መውለዳቸውን የገለጸው አስመሮም፣ ሁለቱን ልጆቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ ልከው የመጨረሻዋን ልጅ ይዘው በጋራ እየሠሩ እያሉ ከሦስት ዓመት በፊት ያልጠበቁት ችግር እንደገጠማቸው ገልጿል፡፡

አምስት ሶማሊያውያን ከሌሊቱ 7፡30 ሰዓት ሲሆን የመኖሪያ ቤታቸውን ሰብረው በመግባት ሊያደርሱባቸው የነበረውን አደጋ ለመከላከል ባደረገው ትግል አንድ ሰው በመሞቱና አንዱ በመቁሰሉ ለእስር መዳረጉንም ተናግሯል፡፡ የአንድ ወር ሕፃን ይዘው ይኼ አደጋ በመፈጠሩ የልጆቹ እናትና እህቷ የደረሱበትን ሳያውቅ የታሰረው አስመሮም፣ በወቅቱ ለማምለጥ ቢሞክርም በቁጥጥር ሥር መዋሉን ገልጿል፡፡ ከ20 ቀናት ቆይታ በኋላ ፍርድ ቤት ቢቀርብም የተፈረደበት ሞት መሆኑን የገለጸው አስመሮም፣ የነበረውን ሁኔታ ያውቁ የነበሩ የቦሳሶ ወደብ ነዋሪዎች ፍርዱን መቃወማቸውንና የኢትዮጵያ ቆንስላዎችም ጣልቃ በመግባታቸው የሞት ፍርዱ ወዲያው ተግባራዊ መሆን እንዳልቻለ ገልጿል፡፡

ፀቡ እንደተፈጠረ ለጊዜው በመጥፋቱ 250 ኢትዮጵያውያን ታስረው እንደነበርና እሱ ተይዞ ሲቀርብ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ መደረጉን ማወቁንም ተናግሯል፡፡ የገደለው ሶማሊያዊ ‹‹ዑስማን መሀመድ›› የሚባል ጎሣ ዝርያ አባል በመሆኑ ከፍተኛ ክብር እንዳላቸውና እነሱን መንካት ከፍተኛ ቅጣት የሚያስቀጣ መሆኑን፣ ፖሊሱም፣ ዳኛውም የአገሪቱም መንግሥትም የሚያደላው ለእነሱ መሆኑን አስመሮም ፍርድ ቤት ሲመላለስ ማወቁን ተናግሯል፡፡

በአካባቢ ነዋሪዎችና በኢትዮጵያም ቆንስላ ተፅዕኖ በድጋሚ ወህኒ ቤት ውስጥ ባለች አንድ ክፍል ውስጥ ዳኞች ተሰይመው ለፍርድ ቢቀርብም፣ እንደገና በሞት እንዲቀጣ እንደተወሰነበት ገልጿል፡፡ በሶማሊያ ሞት የተፈረደበት የሚገደለው ከጠዋቱ 11 ሰዓት ላይ ሲሆን፣ ከሦስት ወራት በፊት አንድ ቀን እሱንም ከእስር ቤት አስወጥተውት ሊገድሉት ይመጣሉ፡፡ የማረሚያ ቤቱ ኃላፊ ‹‹አስመሮም ልትገደል ነውና የምትናዘዘው ካለህ እዚህ ላይ ጻፍና ፈርም፤ ይኼው መኪናና ሽማግሌዎች ቀርበዋል፤ በቀብር ቦታም ሌሎች ሽማግሌዎች እየጠበቁ ነው ፍጠን፤›› እንዳለው ይናገራል፡፡

‹‹ትንሽ አሰብኩ፤ ተስፋ የለኝም፤ ቆም ብዬ ሳስብ ሶማሌ የገንዘብ ነገር እንደማይሆንለት ተገነዘብኩ፤ ከዚያም አዛዡን አንድ ነገር ተባበረኝ አልኩት፤ ከአንድ ሐበሻ ዘንድ ከ15 እስከ 20 ሺሕ ዶላር ስላለኝ ተቀበልና ለቤተሰቦቼ ላክልኝ አልኩት፡፡ እሽ ምን ልርዳህ አለኝ፡፡ ሞባይል ስጠኝ አልኩት፤ ቦሳሶ ወደሚኖርና የእኔን ጉዳይ ለሚከታተል ጓደኛዬ ደውዬ የሆነውን ሁሉ ነገርኩት፤›› የሚለው አስመሮም፣ ጓደኛው ተሯሩጦ በፑንትላንድ ለኢትዮጵያ ተወካዮች በመናገሩ፣ የአገሩ መንግሥት ግድያው እንዲቆም በማዘዙ መትረፉን አብራርቷል፡፡

የፈጣሪ ኃይል ስላለበት በሚስጥር ሊገድሉት የነበረውን ሴራ ሁሉ አልፎ እስሩ የፑንትላንድ ኃላፊዎች ወደሚኖሩበት አካባቢ መቀየሩን፣ ኃላፊዎችና ሀብታሞች ከሚበሉበት ዋሚ ከሚባል ሆቴል በቀን ለቁርስ፣ ለምሳና ለእራት የ30 ዶላር ምግብ እየታዘዘለት ሲመገብ ቆይቶ፣ መጨረሻ ላይ የካቲት 14 ቀን 2004 ዓ.ም መለቀቁንና ለአገሩ መብቃቱን በደስታ ገልጾልናል፡፡

‹‹ስለ ቴዲ አፍሮ የምናገርበት አንደበት የለኝም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያመስግንልኝ፤ እኔ ደሃና አቅም የሌለኝ ወንድሙን ስላዳነ፣ እግዚአብሔር ደግሞ ለእሱ የሚያደርግለትን ሁሉ አብዝቶ ያድርግለት፤ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ልዑካንን፣ በፑንትላንድ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄነራል ኮሎኔል አስመላሽ ወልደ ምህረትና ባልደረቦቻቸው፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሕዝብ ላደረገልኝ ነገር በሙሉ እግዚአብሔር ያክብራችሁ፤›› በማለት አስመሮም ያለውን አክብሮት ገልጿል፡፡

6 የአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከስራቸው ተባረሩ

Wednesday, March 7th, 2012

(Reporter) — የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለአምስት ቀናት ባካሄደው ግምገማ፣ ዋና ሥራ አስኪያጁን ጨምሮ ስድስት ከፍተኛ የአስተዳደሩ ኃላፊዎች ከቦታቸው እንዲነሱ ወስኗል፡፡

ለኃላፊዎቹ መነሳት ምክንያት በተለይ ከመሬት ጋር በተያያዘ ሙስና ቢሆንም፣ ‹‹በሥራ አፈጻጸም ብቃት ማነስ›› በሚል ከቦታው መነሳታቸውን ታማኝ የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ የተመራው ይኸው ግምገማ የኢሕአዴግ ከፍተኛ ኃላፊዎች በተገኙበት የተካሄደ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይሌ ፍስሐና ምክትላቸው አቶ አበበ ዘልኡል፣ የአዲስ አበባ መሬት አስተዳደርና ግንባታ ፈቃድ ባለሥልጣን ኃላፊ አቶ ቃሲም ፊጤ፣ ምክትል ኃላፊው አቶ ይርጋለም ብርሃኑ፣ የመሬት ልማት ባንክና ከተማ ማደስ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ዓለማየሁ ዓለሙ፣ የከተማ ፕላንና መረጃ ኢንስቲትዩት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳህሌ ሰርሻ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ዲዛይንና ግንባታ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አበበ ከበደ ጃለታ በግምገማው ከኃላፊነታቸው ከተነሱት መካከል ናቸው፡፡ አቶ አባተ ስጦታው ከአቅም ግንባታ ቢሮ ኃላፊነታቸው የተነሱ ሲሆን፣ ምክትል ከንቲባነታቸው በማስጠንቀቂያ መታለፉን ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ ከሚገኙ ቢሮዎችና የተለያዩ ጽሕፈት ቤቶች ኃላፊዎች መነሳታቸውን የጠቆሙት ምንጮች፣ በተለያዩ ክፍላተ ከተሞችም በርካታ ኃላፊዎች መነሳታቸውን አስታውቀዋል፡፡ ብዙዎቹ የተነሱት ከሙስናና ከማስፈጸም ብቃት ማነስ ጋር በተያያዘ መሆኑን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በዝግ ስብሰባ እየተካሄደ በነበረው ግምገማ ከኃላፊነታቸው የሚነሱ ግለሰቦች ቁጥር በርካታ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡

ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ በቅርቡ የ2004 የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት፣ አስተዳደሩ የፈለገውንና ያቀደውን ያህል የልማት ሥራውን እንዳያከናውን ሦስት ማነቆዎች እንደነበሩበት መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ እንደሳቸው አገላለጽ፣ ‹‹የልማት ዕድገት ማነቆ የሆነው አንደኛው ያልተገባ ጥቅም የመስጠትና የማግኘት አመለካከት ተግባር አለመወገድ ማለትም ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ሁለተኛው የልማት ማነቆ ደግሞ በማስፈጸም ዙሪያ ያለው የአቅም ውስንነትና ሦስተኛ ማነቆ የግንባታ ግብዓቶች በወቅቱ አለመቅረብ መሆናቸውን፤›› በሪፖርታቸው ማካተታቸውን በዝርዝር መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በተመሳሳይ ከኃላፊነታቸው የተነሱት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኃላፊዎች በአብዛኛው ከመሬት ጋር በተያያዘ በፈጸሙት ሙስናና ኔትወርክ ሲሆን፣ ለመባረራቸው ምክንያት ‹‹የሥራ አፈጻጸም ብቃት ማነስ›› በሚል መገለጹን የሪፖርተር ምንጮች ያስረዳሉ፡፡

አንዱዓለም አራጌ የግድያ ሙከራ እንደተደረገባቸው ለፍርድ ቤት አሳወቁ

Wednesday, March 7th, 2012

(Reporter) — የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ አንዱዓለም አራጌ በተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል በታሰሩበት ማረሚያ ቤት፣ የካቲት 7 ቀን 2004 ዓ.ም በአንድ ዕድሜ ልክ በተፈረደበት ግለሰብ የግድያ ሙከራ እንደተደረገባቸው፣ ጉዳያቸውን በመመርመርና በማየት ላይ ለሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት የካቲት 26 ቀን 2004 ዓ.ም ተናገሩ፡፡ ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎቹን ለየካቲት 26 ቀን 2004 ዓ.ም ቀጥሮ የነበረው፣ ቀደም ባሉት ችሎቶች በሽብር ወንጀል ክስ የመሠረተባቸውን የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ፣ የሰዎችና የሰነድ ማስረጃዎች ካዳመጠና ከመረመረመ በኋላ ‹‹ተከላከሉ›› በማለቱ፣ የተጠርጣሪዎቹን የመከላከያ ምስክሮች ለመስማት ነበር፡፡

በዕለቱ ተጠርጣሪዎቹ ከማረሚያ ቤት ወደ ፍርድ ቤት የቀረቡ ቢሆንም፣ ዓቃቤ ሕግ ያሰማቸው የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ተገልብጠው ስላልደረሷቸው፣ ጠበቆቻቸውና ተጠርጣሪዎቹ በመቃወማቸው መከላከያ ምስክሮቹ ሳይሰሙ ቀርተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ብይኑ ተገልብጦ ባይሰጣቸውም መዘጋጀት እንደነበረባቸው ቢገልጽም፣ ጠበቆቹ ‹‹ፍርድ ቤቱ ተገልብጦ እንዲሰጥ አዞ ስለነበር ስንጠብቅ ጊዜው አለፈብን፤› በማለታቸው ሌላ ቀጠሮ ከተሰጠ በኋላ አቶ አንዱዓለም ማስረዳታቸውን ቀጠሉ፡፡

አቶ አንዱዓለም ለፍርድ ቤቱ ጨምረው እንዳስረዱት፣ ድብደባው በተፈጸመባቸው ጊዜ ለፍርድ ቤት ሲያዘጋጁት የነበረ ሰነድ ተወስዶባቸዋል፤ ጤናቸውም እንደተዛባ ገልጸው፣ ከማረሚያ ቤት ውጭ ባለ የሕክምና ቦታ እንዲታከሙ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡

በአቶ አንዱዓለም ላይ የደረሰውን ድብደባ በሚመለከት በሕግ አግባብ መጠየቅ እንደሚቻል ፍርድ ቤቱ አስረድቶ፣ ‹‹ሰነድ ተወስዶብኛል፣ ሕክምና ያስፈልገኛል፣ በማረሚያ ቤት በአግባቡ አልተያዝኩም፤›› የሚሉትን ጥያቄዎች በሚመለከት የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲያስረዱ አዟል፡፡

ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ ካቀረቡት ውስጥ የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ናትናኤል መኮንና አቶ ክንፈ ሚካኤል አበበ (አበበ ቀስቶ) ሲሆኑ፣ አቶ አንዱዓለምን የድብደባ ጉዳት ያደረሰባቸው ታራሚ እነሱ ዘንድ ተዛውሮ መታሰሩን ጠቁመው፣ ለሕይወታቸው እንደሚያሰጋቸው አመልክተዋል፡፡

በማንኛውም ወቅት ችግር ሊያደርስባቸው እንደሚችል በመስጋት የሚተኙት በየተራ (ናትናኤል ሲተኛ፣ ክንፈ ሚካኤል ይጠብቃል) መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ያስረዱት ተጠርጣሪዎቹ፣ በምግባቸውም ላይ መርዝ ጨምሮ ያጠፋናል የሚል ስጋት ስላላቸው እሱን ወይም እነሱን ማረሚያ ቤቱ ለብቻቸው እንዲያስራቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

ታራሚው (አቶ አንዱዓለምን ደበደበ የተባለው) በታሰሩበት ክፍል ውስጥ የተናገራቸውን ለፍርድ ቤቱ ክብር ስለማይመጥን መናገር እንደማይፈልጉ የገለጹት ተጠርጣሪዎቹ፣ ታራሚዎቹ ኢትዮጵያውያን ባይሆኑ ኖሮ ሊያስገድላቸው እንደነበር ለፍርድ ቤቱ መግለጻቸውን ጠበቃቸው ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ ታራሚዎቹ የተናገሩትንና ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ምላሽ ለጋዜጠኞች የገለጹት የአቶ አንዱዓለም አራጌ፣ የአቶ ናትናኤል መኮንን፣ የአቶ እስክንድር ነጋና የአቶ ክንፈ ሚካኤል አበበ ጠበቃ፣ ጠበቃ ደርበው ተመስገን ናቸው፡፡

በዕለቱ የነበረውን ችሎት ለመታደም በልደታ ፍርድ ቤት የተገኙት የተጠርጣሪዎች ቤተሰቦች፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር፣ የአገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞችና ሌሎች የችሎት ታዳሚዎች ቢሆኑም፣ የፍርድ ቤቱ ችሎት አስቻይ ፖሊሶች አምባሳደሩን፣ የውጭ አገር ጋዜጠኞችን፣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳንና ጥቂት ሌሎች ታዳሚዎችን አስገብተው የአገር ውስጥ ጋዜጠኞችን በመከልከላቸው በችሎቱ ውስጥ ገብተው መዘገብ አልቻሉም፡፡ ችሎት አስቻይ ፖሊሶቹ እንደ ምክንያት የገለጹት፣ ‹‹ችሎቱ ጠባብ ስለሆነ ነው›› የሚል ቢሆንም፣ ሌላ ጊዜ እንደሚደረገው ሒደቱን በሰፊ የማስቻያ ቦታ እንዲሆን ማድረግ ወይም በታራሚዎች ከመሙላት ተጠርጣሪዎችን በየተራ ማስገባት ይቻል እንደነበር ጋዜጠኞቹ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የዕለቱ ችሎት ከዝግ ችሎት ተለይቶ እንደማይታይም ጋዜጠኞቹ ተናግረዋል፡፡

በፀረ ሽብርተኝነት ተጠርጥረው ጥቅምት 30 ቀን 2004 ዓ.ም ክስ ከተመሠረተባቸው 24 ተጠርጣሪዎች መካከል፣ በአገር ውስጥ ሆነውና በማረሚያ ቤት ጉዳያቸውን በመከታተል ላይ ያሉት አንዱዓለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን፣ ዮሐንስ ተረፈ፣ የሸዋስ ይሁንዓለም፣ ክንፈሚካኤል ደበበ፣ ምትኩ ዳምጤ፣ እስክንድር ነጋና አንዱዓለም አያሌው ናቸው፡፡

ደራሲ ማሞ ውድነህ በጠና ታመዋል

Wednesday, February 22nd, 2012

(ሪፖርተር) — ታዋቂውና አንጋፋው ደራሲ አቶ ማሞ ውድነህ ጤንነታቸው ታውኮ አልጋ ከያዙ አንድ ወር ሆኗቸዋል፡፡ በቅድሚያ ዳግማዊ ምኒልክ ቀጥሎም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታሎች ሕክምና ቢከታተሉም ለተጨማሪ ሕክምና ወደ ኢንተርናሽል የልብና ልብ ነክ ደዌዎች ሆስፒታል ከገቡ ሦስት ቀኖች አስቆጥረዋል፡፡

ሔኖክ ያሬድ በተኙበት ሆስፒታል ትናትና አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ሕመምዎ ምንድን ነው?

አቶ ማሞ፡- ሕመሜ ከልብ ጋራ የተያያዘ ነው፡፡ ቀደም ብዬ በውጭም ታክሜያለሁ፡፡ እግሬ እብጠት አሳይቷል፤ ሰውነቴ ውኃ ቋጥሯል፤ ሐኪሞች እርሱን ለማስወጣት ትንሽ ጊዜ ይጠይቀናል ብለዋል፡፡ ስኳሩም ሳስታምመው 24 ዓመት ሆኗል፡፡ የደም ዙረቱም ችግር አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- የሕክምናዎ ሒደት ምን ይመስላል?

አቶ ማሞ፡- መጀመርያ የታከምሁት ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ነው፡፡ የእግሬን ቁስል አዩና የሚችሉትን አደረጉና ወደ ጥቁር አንበሳ በሪፈራል ሄድኩ፡፡ ጥቁር አንበሳ በስንት መከራ ነው አልጋ ያገኘሁት፡፡ የመጀመርያው ቀን ድንገተኛ ክፍል ወደቅሁ፤ መከራዬን አየሁ፤ ያን ቀን ለመሞት ተመኝቼ ነበር፤ ሲዖል ነበር፡፡ በማግሥቱ ሁለተኛ ማዕረግ አልጋ ተገኝቶ ሜዲካል ገባሁ፤ የተወሰነ ጊዜ ቆየሁ፤ ከ5ኛ ፎቅ ወደ 8ኛ ፎቅ ወሰዱኝ፤ ብዙ ምርመራ በያይነቱ ተካሔዶ ውጤቱ ደህና ነው፤ ያለው ችግር ቀስ በቀስ ይወጣል አሉኝ፤ ይሁን እንጂ አራት ቀን ተሰቃየሁና ትናንት ዲስቻርጅ አድርጉኝ አልኩኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ምክንያትዎ ምንድን ነው?

አቶ ማሞ፡- ሐኪሞቹ ራሳቸው ጉድለቱ ከእኛ ነው ወይ ብለው ጠይቀውኛል፡፡ በእኛ ደንብ መሠረት ከሆስፒታሉ የሚወጡበትን ምክንያት ጻፍ አሉኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ጻፉ?

አቶ ማሞ፡- ያ ክፍል ለእኔ እስር ቤት ነበር፡፡ አልጋው ላይ እንደዚህ መተኛት አይቻልም፡፡ የረገበ ሽቦ ነው፤ ከሆስፒታሉ ጋራ አብሮ የተሠራ ይመስላል፡፡ ለመነሣትም፣ ለመተኛትም ሰው ያስፈልጋል፡፡ ክፍሉ 1ኛ ማዕረግ ተባለ እንጂ ውኃም መብራትም የለውም፡፡ ጭልጭል የምትል የራስጌ መብራት አለው፡፡ በረሮ ስገል ነው የምውለው፡፡ ምግብ ሲሸታቸው ይወጣሉ፡፡ ረጨን ብለውን ነበር፤ ተላምደውታል መሰለኝ፡፡ ውኃ በባልዲ እየተቀዳ ወደ በሽተኛ የሚገባበት ነውና ወጣሁ፡፡ እዚህ ሰው የሚተኛበት አልጋ አገኘሁ፡፡ ጥቁር አንበሳ ምርመራቸውን ፈልጌ ነበር ውጤቱን አልሰጡኝም፤ እዚህ እንደገና ልመረመር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ነፃ ሕክምና ጤና ጥበቃ አልሰጠዎትም?

አቶ ማሞ፡- ለማን? ለእኔ? የት ያውቀኛል? ሚኒስትሩ አያውቁኝ፡፡ ልጆቼን ውሎ ያግባ እስከዛሬ ያለው ደህና ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ያለውን አላውቀውም፤ ከበድ እያለ ይሄዳል፡፡

የደራስያን ማኅበር ተጠርተው ሥራ አስፈጻሚዎቹ መጥተው ችግርህ ምንድን ነው? አሉኝ፡፡ ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሕክምና በነፃ እንድታገኝ እንጽፋለን ብለው ሔዱ፡፡ ይጻፉ አይጻፉ አላውቅም፡፡

አቶ ጌታቸው በለጠ ባህል ሚኒስትሮችን ጠይቋቸው ነበር፡፡ ‹‹እኛ ለእርሳቸው ዕርዳታ እናደርጋለን›› ብለዋል የሚል ነገር ሰምቼ ነበር፡፡ እስካሁን ባለው ሒደት ዕርዳታ አልፈልግም፤ ከእንግዲህ ባለው ይከብደኝ እንደሆነ አላውቅም፡፡

ለባህል ነገር አስተዋጽዖ ላደረጉ ሰዎች ባህል ሚኒስቴር ምንድን ነው ሥራው? የማይገባኝ ይኸ ነው፡፡ ስፖርት ብቻ ነው ወይ የሚሯሯጠው፣ የሰውና የአገር ትልቅ ንብረት ዕውቀት ነው፡፡ ደራሲዎችና ሠዓሊዎች ዕውቀት አመንጪዎችና ፈንጣቂዎች ናቸው፡፡ እዚህ አገር እነርሱን የሚንከባከበው ማን ነው? እስኪ ንገረኝ? በሥራዎቻችን ተጠቃሚው ሕዝብ ነው እኮ፡፡ ሕዝብ በዕውቀት እንዲበለጽግ ማድረግ ያለበት ማነው? ያንን ዕውቀት የሚያመነጩ ሰዎችን መጠበቅ፣ የት ገቡ? ምን ሆኑ? ብሎ ማለት ያለበት ማነው? የማይገባኝ ደግሞ ይኼ ነው፡፡ ዱሮ እንደምናውቀው አፄ ኃይለ ሥላሴ ለዚህ ነገር በራቸው ክፍት ነበር፡፡ ሠዓሊዎችን፣ ደራሲዎችን፣ አዝማሪዎችንም ይወዳሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ምንም የለም? በአንድ ሰው የግል ጥረት ብቻ አገር ይገነባል ወይ? የሚያበረታታቸው ማነው? ያደረግነው አስተዋጽኦ ግምት ውስጥ ካልገባ እንዴት ሆኖ ነው ዕውቀት የሚስፋው እስቲ ሰልቁልን፣ ንገሩልን፡፡

ከአዘጋጁ፡- የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው በለጠን ማኅበሩ ለአቶ ማሞ ውድነህ ምን እያደረገላቸው እንደሚገኝ ከትናንት በስቲያ ጠይቀናቸው የሚከተለውን መልሰዋል፡፡ ‹‹መታከም የሚችሉበትን ሁኔታ ለመጠየቅ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩን ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም እኔ ራሴ በአካል ሔጄ ደብዳቤውን በጸሐፊያቸው በኩል አድርሻለሁ፡፡

ጉዳዩ ግፊት እንዲደረግበትም ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስትርና ሚኒስትር ዴኤታው ጽፈናል፡፡ ያለምንም ማጋነን በየቀኑ ቢያንስ ሦስቴ አራቴ እንደውላለን፡፡ ክቡር ሚኒስትር አይተዋል ወይ? በአገራቸው ውስጥ የነፃ ሕክምና እንዲፈቀድላቸው ብለን ጠይቀናል፡፡ ምላሽ አላገኘንም፡፡ ዛሬ እንኳን በሕዝብ ግንኙነቱ በኩል ግፊት ለማድረግ በተደጋጋሚ ሞክረን፤ ስልክ ጠብቁ ተብለናል፡፡

ማኅበራችን እጅግ አዝኗል፤ ይቻላል አይቻልም አንድ ጉዳይ ነው፡፡ ሌላ አማራጭ እንዳንፈልግ ወደ ሚረዷቸው ሰዎች እንዳንሄድ አድርገውናል፡፡ በመሠረቱ አቶ ማሞ ውድነህ በምንም ሆነ ምን አገራቸውን አገልግለዋል፤ በሙያቸው፣ በአገር ሽማግሌነታቸው አገራቸውን አገልግለዋል፡፡ ለአገር የሚገባውን ሁሉ አድርገዋል፡፡

እስከመቼ ድረስ ነው የኢትዮጵያ ደራስያን፣ የኪነ ጥበብ ሰዎች ሲሞቱ የምንለምነው? እስኪ የአገር ውስጥ ሙከራ እናድርግ ክቡር ሚኒስትሩ ሊወስኑ ይችላሉ ብንልም ለሁለት ሳምንት በሞትና በሕይወት ላይ ያለን ሰው ውሳኔ ለመስጠት ስለመቸገራቸው ማኅበራችን እጅግ ማዘኑን በይፋ እንዲገለጽልን እንፈልጋለን፤›› ብለዋል፡፡

በባሏ ጥቃት ዓይኖቿ የተጎዱት ነፍሰ ጡር በከፍተኛ ስቃይ ላይ ትገኛለች

Monday, February 20th, 2012

(REPORTER) — ነፍሰ ጡሯ በባለቤቷ በደረሰባት ድብደባ በዓይኖቿ፣ በአፍንጫዋና በመላ ሰውነቷ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባት በከፍተኛ ስቃይ ላይ እንደምትገኝ ቤተሰቦቿ አስታወቁ፡፡

በሁለት ዓይኖቿ ላይ የተፈጸመው ጥቃት የጉዳት መጠኑ ምን ያህል እንደሆነ የሕክምና ውጤት እየተጠባበቁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ወ/ሮ ፀዳለች አስረስ ጥር 29 ቀን 2004 ዓ.ም. ከምትሠራበት ዳሸን ባንክ ውላ ወደ ቤቷ ስትገባ፣ “እኔ የምልሽን የማትፈጽሚው ሆን ብለሽ ነው” በማለት ሠራተኛቸውንና የሁለት ዓመት ሕፃን ልጃቸውን ወደ ሱቅ በመላክ በፈጸመባት ጥቃት ጉዳት እንዳደረሰባት የሚናገሩት ቤተሰቦቿ፣ በሁለቱም ዓይኖቿ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱንና ዓይኖቿ ማየት አለማየታቸውን ለማረጋገጥ ከዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ውጤት እተየጠባበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አፍንጫዋ መሰበሩንና ሕክምና ብታገኝም ከፍተኛ ደም እየፈሰሳት መሆኑን የምትናገረው የተጐጂዋ እህት፣ የሁለት ወር ነፍሰ ጡር መሆኗንም ገልጻላች፡፡

ድርጊቱ ከተፈጸመባት ዕለት ጀምሮ ለንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መረጃው እንደደረሰ፣ ነገር ግን ጥቃቱን አድርሷል የተባለው ተጠርጣሪው ባለቤቷ መሰለ ግርማ እስካሁን በቁጥጥር ሥር አለመዋሉን የተጐጂዋ እህት ገልጻለች፡፡ በቤተሰቦቹና በጓደኞቹ አማካይነት እርቅ እንዲፈጸም በተለያየ መንገድ ጥያቄ እያቀረበ መሆኑን የተጎጂዋ እህት አስረድታ፣ ፖሊስ ግለሰቡን እንዴት በቁጥጥር ሥር ማዋል እንዳልቻለ ግራ እንደገባት አስረድታለች፡፡ ፖሊሶች በተደጋጋሚ ሲጠየቁ የመያዥያ ትዕዛዝ ከፍርድ ቤት አውጥተው እየተከታተሉት መሆኑን እንደገለጹላቸው ተናግራለች፡፡

ባልና ሚስቶቹ ትዳር መሥርተው ልጅ ከወለዱ ሁለት ዓመታት እንዳለፋቸው የገለጸችው የተጐጂዋ እህት፣ ግንኙነታቸው ግን ከልጅነታቸው ከስድስተኛ ክፍል ጀምሮ ሁለቱም ከተወለዱበት ደቡብ ክልል ጀምጀም አውራጃ ቦሬ ከተማ ውስጥ መሆኑን ትናገራለች፡፡ ሁለቱም ውጤት አግኝተው ዩኒቨርስቲ ሲገቡ እሷ አምቦ እሱ ደግሞ ጅማ ቢደርሳቸውም፣ እሷ ወደ ጅማ ዩኒቨርሲቲ በፈቃዷ ተቀይራ ሁለቱም ከጅማ ዩኒቨርሲቲ መመረቃቸውንና በተለያዩ የዳሸን ባንክ ቅርንጫፎች እንደሚሠሩ አስታውቃለች፡፡

ትዳር መሥረተው አብረው መኖር ከጀመሩ ጊዜ አንስቶ ስምምነት እንደሌላቸው የገለጸችው የተጐጂዋ እህት፣ ተጐጂዋ እንደነገረቻት ባለቤቷ አደጋውን ያደረሰባት ምክንያት፣ እሷ ቀድሞ ከምትሠራበት የደንበኞች አገልግሎት የሥራ መደብ ተቀይራ ቢሮ ውስጥ ገብታ እንድትሠራ አለቃዋ እንደነገራት ትነግረዋለች፡፡ “አይ አይሆንም፤ ሂጅና መሥራት የምፈልገው ፊት ለፊት በሚሠራው የደንበኞች አገልግሎት ክፍል ነው በይውና በቀድሞ ቦታሽ እንድትሠሪ ጠይቂ፤” ይላታል፡፡ አለቃዋ ከእንግዶች ጋር ስለነበር ማናገር ባለመቻሏ የሥራ ሰዓት አብቅቶ ወደ ቤታቸው እንደሄደችና አለቃዋን እንዳላናገረች ትነግረዋለች፡፡ በዚህ ጊዜ “ይኼንን ያደረግሺው አውቀሽ ነው፤ ከዚያ ቦታ ለመቀየር ፍላጐት ስለሌለሽ ነው፤” በማለት ሕፃኑንና ሠራተኛቸውን ወደ ሱቅ በመላክ ጉዳቱን እንዳደረሰባት እንደነገረቻት እህትየው ገልጻለች፡፡

ድርጊቱን በማድረስ ወንጀል የተጠረጠረው የተጐጂዋ ባለቤት ለምን ሊያዝ እንዳልቻለ፣ ክትትሉስ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያን ለማነጋገር ቢሞከርም፣ ጉዳዩ በምርመራ ላይ መሆኑን ከመግለጽ ያለፈ ተጨማሪ መረጃ ማግኘት አልተቻለም፡፡

በአዳማ 45 ክሊኒኮችና የመድኃኒት መደብሮች ታሸጉ

Saturday, February 11th, 2012

የአዳማ (ናዝሬት) ከተማ አስተዳደር የተለያዩ ጉድለቶች አሉባቸው ያላቸውን 21 ክሊኒኮችና 24 የመድኃኒት መደብሮችን አሸገ፡፡ ከከተማው የጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ባለፈው ሐሙስ እንዲታሸጉ ከተወሰነባቸው መድኃኒት ቤቶች መካከል ስድስቱ ምንም ዓይነት ፈቃድ ያልነበራቸው ናቸው፡፡

ለእሸጋው ምክንያት ናቸው ከተባሉት ምክንያቶች ውስጥ በዋናነት የተጠቀሱት በትክክለኛ ባለሙያዎች ማሠራት አለመቻል፣ ፈቃድ ያለማደስ፣ በሌሎች ሰዎች ሥራውን ማሠራት፣ ከተፈቀደላቸው የአገልግሎት መጠን በላይ ሲሠሩ መገኘትና የመሳሰሉት እንደሚገኙበት የጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አበራ ፈይሳ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ዕርምጃው አስተዳደራዊ እንደሆነ ያመለከቱት አቶ አበራ፣ እሸጋ የተደረገባቸው ክሊኒኮችና የመድኃኒት መደብሮች የታየባቸውን ጉድለት እንዲያስተካክሉ የጊዜ ገደብ ተሰጥቷቸዋል፡፡

የተወሰደባቸው አስተዳደራዊ ዕርምጃም ከአንድ እስከ ሁለት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ማሟላት የሚገባቸውን አሟልተው የሚቀርቡ ከሆነ አገልግሎታቸውን መልሰው የሚጀምሩበት ዕድል ያለ ሲሆን፣ ይህንን ካላደረጉ ግን ሥራውን መጀመር እንደማይችሉ ከአቶ አበራ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ ማሟላት የሚገባቸውን በተደረገው ጥናት መሠረት በዝርዝር የተነገራቸው ሲሆን፣ ለምሳሌ በቂ ባለሙያ የሌላቸው ከሆነ ይህንን ማሟላት አለባቸው፡፡ የሕክምና መሣሪያ ጉድለት ከሆነም የጎደለውን መሣሪያ አሟልቶ መቅረብ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

ይህ ውሳኔ ፈቃድ ሳይኖራቸው ሲሠሩ የቆዩትን ክሊኒኮችና መድኃኒት ቤቶች እንደማይመለከት ገልጸዋል፡፡

ጽሕፈት ቤታቸው ይህንን ዕርምጃ ቀደም ብሎ በተወሰነ ደረጃ የወሰደ መሆኑን የገለጹት አቶ አበራ፣ አሁን ግን በተጠናከረ ሁኔታ እንዲቀጥል የተደረገው ተጠቃሚዎችን ጉዳት ላይ የሚጥሉ ሕገወጥ ተግባራት እንዳይስፋፉና የተሻለ የጤና አጠባበቅ ሥርዓትን ለመዘርጋት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የታሸጉትን ጨምሮ በአጠቃላይ ወደ 128 የሚሆኑ ክሊኒኮችና መድኃኒት መደብሮች በአዳማ ውስጥ ይገኛሉ፡፡

የቀድሞው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዋና ጸሐፊ አረፉ

Wednesday, February 8th, 2012

(ሪፖርተር) — የቀድሞው የሕፃናት ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዋና ጸሐፊ የነበሩት ኮሚሽነር ተሠራ ወርቅ ሽመልስና የኢትዮጵያ መንገዶች ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር መስፍን ኃይሌ ሥርዓተ ቀብር ከትናንት በስቲያ ተፈጸመ፡፡ ላለፉት አምስት አሠርት በተለያዩ ሰብዓዊና አገራዊ ጉዳዮች ከመንግሥት ከፍተኛ ሹምነት እስከ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መሪነት ያገለገሉት ኮሚሽነር ተሠራ ወርቅ፣ በተለይ በ1960ዎቹና 70ዎቹ በአገሪቱ ተከሥቶ የነበረውን የተፈጥሮ አደጋ ለመቋቋም ከተሰማሩት ግንባር ቀደምት መካከል አንዱ እንደነበሩ ከሕይወት ታሪካቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡

በቀይ መስቀል ማኅበር ዋና ጸሐፊነት ዘመናቸው የደም ባንክን ያቋቋሙት አቶ ተሠራ ወርቅ፣ ከነበሩባቸው ኃላፊነቶች መካከል የልጆች፣ ወጣቶችና ቤተሰብ ደኅንነት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የቴርዴስ ሆምስ የምሥራቅና የሰሜን አፍሪካ ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ፣ የዓባይ (ናይል) ተፋሰስ አገሮች የዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ሰብሳቢ ሆነው ያገለገሉበት ይገኙባቸዋል፡፡

ከአባታቸው አቶ ሽመልስ ዘነበወርቅና ከእናታቸው ወ/ሮ አፀደማርያም ቸርነት ጥቅምት 30 ቀን 1939 ዓ.ም. በሐረር ከተማ የተወለዱት ኮሚሽነር ተሠራ ወርቅ፣ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን በሐረር ስዊድን ሚሽን፣ ሁለተኛ ደረጃን በአዲስ አበባ ኮከበ ጽባሕ ትምህርት ቤት ሲከታተሉ፣ ከንግድ ሥራ ኮሌጅ በ1957 ዓ.ም. ተመርቀዋል፡፡

ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በአገር ውስጥና በውጭ አገር ሕክምና ሲከታተሉ የነበሩት ኮሚሽነር ተሠራ ቀብራቸው ጥር 28 ቀን 2004 ዓ.ም. በሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡ ኮሚሽነር ተሠራ ወርቅ የአንዲት ሴትና አንድ ወንድ ልጆች አባት ነበሩ፡፡

በተያያዘ ዜና በሐምሌ ወር 2003 ዓ.ም የተቋቋመው የኢትዮጵያ መንገዶች ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ኢንጂነር መስፍን ኃይሌ፣ ጥር 27 ቀን 2004 ዓ.ም አርፈው ጥር 28 ቀን 2004 ዓ.ም የቀብር ሥርዓታቸው በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡

ኢንጂነር መስፍን ከ1981 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሐምሌ ወር 2003 ዓ.ም ድረስ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በተለያዩ ከፍተኛ ኃላፊነቶች የሠሩ መሆናቸውን ከሕይወት ታሪካቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡ በቀብራቸው ሥነ ሥርዓት ላይ አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳን ጨምሮ በርካታ የመንግሥት ባለሥልጣናት ተገኝተዋል፡፡

የላንቻ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ ተፈረደባቸው

Saturday, February 4th, 2012

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የላንቻ አካባቢ ማዛዥ ጣቢያ አዛዥ ምክትል ኮማንደር ግርማ ሰንበቶን ጨምሮ አራት ግለሰቦች በተመሠረተባቸው የሙስና ወንጀል በእስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ ተወሰነባቸው፡፡ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ በምክትል ኮማንደር ግርማ ሰንበቶ፣ ፍቃዱ ኦልጅራ፣ አብዱራዛቅ ዑመርና ዓለም ገብሬ በተባሉ ግለሰቦች ላይ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ፣ በሰዎችና በሰነድ ማስረጃዎች በመረጋገጡ የቅጣት ውሳኔው መተላለፉን የኮሚሽኑ ማስረጃ ያብራራል፡፡

ምክትል ኮማንደር ግርማ ሰንበቶ በሁለት ዓመታት ከሦስት ወራት ፅኑ እስራትና በ1500 ብር፣ ፍቃዱ ኦልጅራ በሦስት ዓመታት ፅኑ እስራትና በ1000 ብር፣ አብዱራዛቅ ዑመር በአምስት ዓመታት ፅኑ እስራትና በ5500 ብርና ዓለም ገብሬ በአንድ ዓመት ከስድስት ወራት ፅኑ እስራትና በ500 ብር እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል፡፡

የፖሊስ አዛዡን ጨምሮ ግለሰቦቹ የፈጸሙትን የሙስና ወንጀል የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ በክሱ እንዳብራራው፣ ፍቃዱ ኦልጀራ ታህሳስ 9 ቀን 2001 ዓ.ም የግል ተበዳይ የሆኑትን ዓለማየሁ እሸቱ የተባሉትን ግለሰብ፣ ‹‹የሰጠሁህን ቼክ መልስልኝና በምትኩ ገንዘብ እሰጥሀለሁ፤›› በማለት በአዲስ ከተማ ከፍለ ከተማ ቀበሌ 12 ልዩ ቦታው አዲስ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ፊት ለፊት በቀጠሮ ለመገናኘት ይስማማሉ፡፡

በቀጠሮው ቦታ ፍቃዱ ኦልጅራ፣ አብዱራዛቅ ዑመርና ዓለም ገብሬ ካልተያዙ ሁለት የመከላከያ ሠራዊት ልብስ ከለበሱ ግብረ አበሮቻቸውና ማንነቱ ካልታወቀ ሾፌር ጋር በመሆን ተበዳዩን ግለሰብ ‹‹ትፈለጋለህ›› በማለት በካቴና አስረው፣ በአብዱራዛቅ ኮብራ መኪና ውስጥ አስገድደው ካስገቧቸው በኋላ፣ ወደ ቦሌ መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ጀርባ ይወስዷቸዋል፡፡ ተበዳዩን ይዘውት የመጡት ቼክ ‹‹አምጣ ወይም 400,000 ብር ወስጃለሁ ብለህ ፈርም›› በማለትም ይደበድቡዋቸዋል፡፡ ተበዳዩ ግን ‹‹አልፈርምም›› ይላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ግለሰቦቹ ተበዳዩን በካቴና አስረው ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ላንቻ ፖሊስ ጣቢያ ይወስዷቸዋል፡፡ የጣቢያው አዛዥ ምክትል ኮማንደር ግርማ ሰንበቶ ሕግን የማስከበር ግዴታቸውን ሳይወጡ፣ ሥልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀም ተበዳዩ ታስረው እንዲያድሩ ለተረኛ ፖሊስ ትዕዛዝ ይሰጣሉ፡፡

የግል ተበዳይ አቶ ዓለማየሁ እሸቱ ከሕግ አግባብ ውጭ በካቴና ታስረው በፖሊስ ጣቢያው ወንበር ላይ እንዲያድሩ ይደረጋል፡፡ በመሆኑም ፍርደኞቹ ግለሰቡን አፍነው በመውሰድና ነፃነታቸውን በማሳጣት በመብታቸው ላይ ከፍተኛ በደል በማድረሳቸውና ሥልጣንን አላግባብ በመጠቀም በፈጸሙበት ሰውን የመጥለፍና ታስቦ በሚፈጸም ከባድ የአካል ጉዳት የማድረስ ወንጀል ተከሰው፣ ውሳኔው እንደተላለፈባቸው የኮሚሽኑ ማብራሪያ ያስረዳል፡፡

በሽብር ወንጀል የተከሰሱት እነ ኤልያስ ክፍሌ ተፈረደባቸው

Thursday, January 26th, 2012

(ሪፖርተር) — የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ጥር 17 ቀን 2004 ዓ.ም. በዋለው ችሎት በአምስት የሽብር ወንጀል ተከሳሾች ላይ ከዕድሜ ልክ እስከ 19 ዓመትና የገንዘብ ቅጣት ወሰነ፡፡ በዚህ መሠረት ኤልያስ ክፍሌ የዕድሜ ልክ እስራት የተወሰነበት ሲሆን፣ ዘሪሁን ገብረ እግዚአብሔር የ17 ዓመት እስራትና የ50 ሺሕ ብር ቅጣት፣ ውብሸት ታዬ የ14 ዓመት እስራትና የ33 ሺሕ ብር ቅጣት፣ ሒሩት ክፍሌ የ19 ዓመት እስራት፣ ርዕዮት ዓለሙ የ14 ዓመት እስራትና የ36 ሺሕ ብር ቅጣት ተወስኖባቸዋል፡፡

አምስቱም ተከሳሾች እያንዳንዳቸው ለአምስት ዓመታት ከሕዝባዊ መብቶቻቸው እንዲታገዱ ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡

በሽብር ወንጀል የተከሰሱት ኤልያስ ክፍሌና ጋዜጠኞች ጥፋተኛ ተባሉ

Saturday, January 21st, 2012

ሪፖርተር — ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በተደራጀ የሽብር ድርጊት ለማፈራረስ ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል በሚል በሽብር ወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው ኤልያስ ክፍሌ፣ ዘሪሁን ገብረ እግዚአብሔር፣ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ ሂሩት ክፍሌና ጋዜጠኛና መምህርት ርዕዮት ዓለሙ ጥር 11 ቀን 2004 ዓ.ም. ጥፋተኛ ተባሉ፡፡ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የመሠረተባቸውን አራት ክሶች፣ ያቀረባቸውን የሰዎችና የሰነድ ማስረጃዎች ተከሳሾቹ ካቀረቧቸው የሰውና የሰነድ መከላከያ ማስረጃዎች ከሕጉ ድንጋጌ ጋር በመመርመር የጥፋተኝነት ውሳኔውን ያስተላለፈው፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ነው፡፡

ዓቃቤ ሕግ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረውና በአገር ውስጥ ሆነው ጉዳያቸውን በመከታተል ላይ ባሉት የመኢዴአፓ ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ገብረ እግዚአብሔር፣ በአውራምባ ታይምስ ምክትል አዘጋጅ ውብሸት ታዬ፣ ሂሩት ክፍሌ፣ ጋዜጠኛና መምህርት ርዕዮት ዓለሙ ላይ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች የሰጡትን የምስክርነት ቃል ፍርድ ቤቱ በንባብ አስታውሷል፡፡

በሌለበት ክስ በተመሠረተበትና ጥፋተኛ በተባለው ኤልያስ ክፍሌ የፋይናንስ ድጋፍ ሰጪነት፣ አስተባባሪነት፣ በህቡዕ ተደራጅተው ጥቃት ለማድረስ የሽብር ቅስቀሳ ለማድረግ ‹‹በቃ፣ መለስ በቃ›› የሚል ጽሑፍ በቀይ ቀለም በአዲስ አበባ በተለያዩ ሥፍራዎች በተለይ አቶ ዘሪሁን በመረጣቸው ቦታዎች መጻፋቸውንና መመስከራቸውን ገልጿል፡፡

ጋዜጠኛ ውብሸትና ርዕዮት ዓለሙ ፎቶግራፍ በማንሳት ለኤልያስ ክፍሌ መላካቸውን፣ በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ለመጻፍ ጸሐፊዎችን በመመልመልና ከኤልያስ ክፍሌ ጋር በመገናኘት የተለያዩ ትዕዛዞችን እንደተቀበሉ ምስክሮቹ መመስከራቸውን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

አቶ ዘሪሁን ባቀረቧቸው የመከላከያ ምስክሮች በሕጋዊ መንገድ የተቋቋመ ፖለቲካ ፓርቲ መሪ መሆናቸውን፣ ገንዘብ ከውጭ የተላከላቸው ከዘመድ መሆኑን፣ ገንዘቡንም ለፓርቲ ሥራና ለግል መጠቀሚያ ማዋላቸውን፣ በሰላማዊ መንገድ ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ ፈቃድ ጠይቀው መከልከላቸውን በሰውና በሰነድ ለፍርድ ቤቱ ማስረዳታቸውን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬም ገንዘብ ተልኮለት ለአባቱ የሕክምና ወጪ ማዋሉን፣ ጋዜጠኛ መሆኑንና የብተና ፖለቲካ በሚል በሚሠራበት ጋዜጣ ላይ ትችት ማቅረቡን ማስረዳቱን ፍርድ ቤቱ ተናግሯል፡፡

ፍርድ ቤቱ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችንና የመከላከያ ምስክሮችን የምስክርነት ቃልና የሰነድ ማስረጃዎች ከሕጉ አግባብ ጋር በመመርመር ‹‹በቃ መለስ፣ በቃ›› የሚል ጽሑፍ ለመጻፍ መስማማታቸውን፣ ፎቶ አስነስተው መላካቸውን፣ በኢንተርኔት የተለያዩ ጽሑፎችን መጻጻፋቸውን፣ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ያስረዱ መሆኑንና ተከሳሾች ያቀረቡት መከላከያ ምስክርና ማስረጃ የሽብር ወንጀሉን ለመፈጸም የሚያስችላቸው አለመሆኑን ባለማስረዳታቸው፣ የዓቃቤ ሕግ ማስረጃ የሽብር ወንጀሉን ለመፈጸም ማሴራቸውንና ማቀዳቸውን የሚያስረዳ በመሆኑ፣ በሽብርተኛ ሕጉ 652/2001 አንቀጽ 4 መሠረት ጥፋተኛ መሆናቸውን በንባብ አሰምቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ በሰጠው ፍርድ በአንደኛው፣ በሁለተኛውና በሦስተኛው ክስ ሁሉም ተከሳሾች ጥፋተኛ ሲባሉ፣ ኤልያስ ክፍሌ በአራተኛ ክስ ማለትም የኢትዮጵያ ጠላት ከሆነው ከኤርትራ መንግሥት ጋር በማበር የኢትዮጵያን መንግሥት በኃይል ለመጣል ከሚንቀሳቀሰው የሽብር ቡድን የሰበሰበውን ገንዘብ የሽብርተኝነት ድርጊት እንዲፈጸም ለማድረግ በስውር በመላኩ በድጋሚ ጥፋተኛ ተብሏል፡፡

ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ፍርዱን ከሰጠ በኋላ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው የቅጣት ማክበጃ ሐሳብ፣ ሁሉም ተከሳሾች በሠሩት ተደራራቢ ወንጀል ቅጣቱ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ2002 ዓ.ም. በወጣው የቅጣት ማንዋልና በወንጀል ሕጉ እጅግ ከብዶ እንዲቀጡ ጠይቋል፡፡

የአቶ ዘሪሁን፣ የጋዜጠኛ ውብሸትና የሂሩት ክፍሌ ተከላካይ ጠበቃ፣ ጠበቃ ደርበው ተመስገን ባቀረቡት የቅጣት ማቅለያ ሐሳብ፣ ወንጀሉ የተፈጸመው በሕግ የተፈቀዱ ተግባራትን ማለትም የፖለቲካ ፓርቲ ሲመሩ፣ ጋዜጠኛ ሆነው ማኅበራዊ ለውጥን ሲፈልጉ ወሰን ስላለፉ እንጂ፣ በአፍቅሮተ ነዋይ ተጠምደው ወራዳነትን ያልፈጸሙ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪ ድርጊቱ ፍጻሜ ሳያገኝ በሙከራ የቀረ በመሆኑ፣ በተለይ ዘሪሁንና ውብሸት ከዚህ በፊት በሌላ ወንጀል ተከሰው የማያውቁ በመሆናቸውና ሪከርድም ስላልቀረበባቸው፣ ሂሩት ክፍሌ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበባት ተደራራቢ የወንጀል ድርጊት ከወንጀል ሕጉ አንቀጽ 67 አንፃር እንዲመዘንላት አቶ ደርበው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

ሁሉም ተከሳሾች የቤተሰብ ኃላፊ መሆናቸውን፣ በእስራት ቢቀጡ ቤተሰቦቻቸው የማኅበረሰቡ ሸክም እንደሚሆኑ በመጥቀስ ቅጣቱ በቅጣት ማንዋሉ የተቀመጠው በዝቅተኛ ደረጃ እንዲሆንላቸው፣ ከባድ ሆኖ የሚወሰነው ከባድ ጥፋት ላደረሱ ወንጀለኞች መሆኑን፣ የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ከቅጣት ማኑዋሉ ጋር በተቀራረበ ጊዜ ስለወጣ በወንጀል ሕጉ መሠረት እንዲወሰንላቸው ጠይቀዋል፡፡ እስራት ከተወሰነባቸው ደግሞ በገደብ እንዲያዝላቸው ወይም በገንዘብ እንዲለወጥላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀው የቅጣት አስተያየታቸውን አጠቃለዋል፡፡

የጋዜጠኛና መምህርት ርዕዮት ጠበቃ፣ ጠበቃ ሞላ ዘገዬ ባቀረቡት የቅጣት ማቅለያ፣ ርዕዮት አስተማሪና ጋዜጠኛ መሆኗን ገልጸው፣ ተፈጸመ በተባለው ድርጊት ውስጥ የገባችው አስቀድማ አስባ ወይም በከባድ ቸልተኝነት ሳይሆን፣ በጋዜጠኛነቷ የተፈጸመ መሆኑንና ከእሷ ሐሳብ ውጭ በሆነ በእግረ መንገድ የተፈጸመ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

ተከሳና ተወቅሳ የማታውቅ፣ በአካባቢዋም ሆነ በመሥሪያ ቤቷ በፀባይዋ የተመሰገነች መሆኗን፣ ፍርድ ቤቱ ወጣትነቷን ከግምት ውስጥ አስገብቶ በእስር ከምትቆይ ለኅብረተሰቡ የምትሰጠውን አስተዋጽኦ ከግምት ውስጥ አስገብቶ፣ ቅጣቱ እጅግ በጣም ቀሎና በቅጣት ማንዋሉ ዝቅተኛው ተብሎ እንዲወሰንላቸውና ቢቻል በገንዘብ እንዲቀየርላት በመጠየቅ አስተያየታቸውን አቅርበዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የቤተሰብ ኃላፊ ናቸው የተባሉትን ጥፋተኞች ከቅጣት ውሳኔ በፊት ማስረጃ እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ለጥር 17 ቀን 2004 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ዓባይ በረሃ ገደል ውስጥ በገባው አውቶቡስ 43 ሰዎች ሞቱ

Wednesday, January 18th, 2012

(ሪፖርተር) — በትናንትናው ዕለት ከአዲስ አበባ 46 ተሳፋሪዎችን ይዞ ወደ ጐንደር በመጓዝ ላይ በነበረው የሰሌዳ ቁጥር 40411 በሆነው ስካይ ባስ፣ ዓባይ በረሃ ሕዳሴ ድልድይ መዳረሻ ሲደርስ መስመሩን ስቶ ገደል በመግባቱ፣ 43 ሰዎች መሞታቸውን በስፍራው የተገኘው የሪፖርተር ዘጋቢ ለማወቅ ችሏል፡፡
buss accident in northern Ethiopia, January 17, 2012
አውቶቡሱ ከሾፌሩ፣ ከረዳቱና ከአንዲት አስተናጋጅ ውጭ 46 ተሳፋሪዎች ይዞ በመጓዝ ላይ እያለ ምክንያቱ ባልታወቀበት ሁኔታ ወደ ሕዳሴ ድልድይ መቃረቡን የሚያመለክቱ አንፀባራቂ ምልክቶችን ጥሶ በግምት ከ80 ሜትር በላይ ጥልቀት ያለው ገደል ውስጥ ገብቷል፡፡

አውቶቡሱ ገደል መግባቱን ተከትሎ በተሰማው የፍንዳታ ድምፅ ምክንያት የሕዳሴውን ድልድይ የሚጠብቁ ታጣቂዎች ፈጥነው ቢደርሱም፣ ተሽከርካሪው በእሳት በመያያዙ በሕይወት የተረፉትን ለመርዳት መቸገራቸውን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

አደጋው ከደረሰ በኋላ በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎችና ከጐንደርና ከባህርዳር ወደ አዲስ አበባ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ወደ ጐንደርና ባህር ዳር በመጓዝ ላይ ያሉ መንገደኞች ሁሉ ባደረጉት መረባረብ፣ በእሳት የተቃጠሉና በአደጋው ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰባት ሰዎች ለማውጣት መቻላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከአደጋው ከተረፉት ስድስት ተጓዦች መካከል አንደኛው ከአውስትራሊያ መጥቶ የጥምቀትን በዓል ለማክበር ወደ ጐንደር እየተጓዘ እንደነበር፣ “ወንድሜን ጥሩልኝ ስልክ ደውሉልኝ” ብሎ በመናገር ላይ እያለ ሕይወቱ ማለፉን ዘጋቢው ማየቱን ተናግሯል፡፡ አውቶቡሱ ውስጡ ሙሉ በሙሉ በእሳት በመያያዙ አደጋው የደረሰባቸውና ሕይወታቸው ያለፈው ተጓዦች አስከሬንም ሳይቃጠል እንዳልቀረ ተገምቷል፡፡

ከባድ አደጋ የደረሰባቸውና በሕይወት የተረፉት አንዲት ሴትና አምስት ወንዶች፣ በአካባቢው በተገኙ የቀይ መስቀል ሠራተኞች የመጀመርያ ዕርዳታ ከተደረገላቸው በኋላ ወደ ሕክምና ቦታ መወሰዳቸው ታውቋል፡፡ በግምት ከጠዋቱ አራት ሰዓት አካባቢ የተከሰተው አደጋ እስከ ቀኑ ስድስት ሰዓት ድረስ እንደቆየ ታውቋል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኘውን የስካይ ባስ አክሲዮን ማኅበር ኃላፊዎችን አነጋግረናቸው፣ በደረሰው አደጋ እጅግ በጣም መደንገጣቸውንና ስለ አደጋው የሚያጣራ የቴክኒክ ቡድን ወደ ስፍራው መላካቸውን ተናግረዋል፡፡

አውቶቡሱ አንድ ጊዜ ተጉዞ ሲመለስ ሙሉ ምርመራ እንደሚደረግለት፣ መስተዋቶቹ አደጋ እንኳን ቢከሰት በቀላሉ የሚሰበሩ፣ አላስፈላጊ የሆነ ነገር ቢገጥም በሚል ደግሞ በእያንዳንዱ ተሳፋሪ መስታወት አቅራቢያ መስተዋት መስበሪያ መዶሻ እንደሚሰቀል ኃላፊዎቹ ተናግረው፣ አደጋው በምን ሁኔታና ምክንያት እንደደረሰ መናገር የሚችሉት የቴክኒክ ቡድኑ ለሚመለከተው አካል ካሳወቀ በኋላ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ስካይ ባስ ከሦስት ዓመታት በፊት ከሦስት ሺሕ በላይ በሆኑ ባለአክሲዮኖች የተቋቋመ የግል ማኅበር ነው፡፡ አሁን ከተገለበጠው አውቶቡስ ጋር 14 አውቶቡሶች ሲኖሩት ከሁለቱ በስተቀር 12ቱ መፀዳጃ ቤት፣ የአየር መቅዘፊያ ባግና የተለያዩ መስተንግዶዎች አሏቸው፡፡ ሁለቱ አውቶቡሶችም መኝታ ክፍሎች አሏቸው፡፡ እያንዳንዳቸው አውቶቡሶች በ3.5 ሚሊዮን ብር የተገዙ ሲሆን፣ በቀጥታ ከፋብሪካው ተገዝተው የመጡ መሆናቸውን ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያዊው ዶክተር ጁባ ውስጥ ተገደሉ

Wednesday, January 18th, 2012

(ሪፖርተር) — በደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ የአፍሪካ ሕክምናና ምርምር ፋውንዴሽን (አመሬፍ) ዳይሬክተር የነበሩት ኢትዮጵያዊው ዶክተር ዓለማየሁ ሰይፉ ባልታወቁ ታጣቂዎች ጥር 5 ቀን 2004 ዓ.ም. ተገደሉ፡፡ በጁባ ከተማ ዳርቻ በሆነችው የማላካል አካባቢ በሚገኘው ቤታቸው በር ላይ በታጣቂዎች ባለፈው ቅዳሜ ምሽት ላይ የተገደሉት የ46 ዓመቱ ዶክተር ዓለማየሁ፣ መኪናቸውንና ሌሎች ንብረቶቻቸውን መዘረፋቸው ታውቋል፡፡

Dr Alemayehu Seifu

የደቡብ ሱዳን መንግሥት ግድያውን ለማጣራት ምርመራ እያካሄደ ሲሆን፣ የዶክተሩን መኪናም እሑድ ከሰዓት በኋላ ላይ ያምቢዮ ጁባ መንገድ ላይ ተገኝቷል፡፡ ፖሊስም መኪናውን ሲያሽከረክረው የነበረውን ግለሰብ በቁጥጥር ሥር እንዳዋለው ታውቋል፡፡

የዶክተር ዓለማየሁ አስከሬን ባለፈው እሑድ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ ባለፈው ሰኞ ሲኤምሲ መንገድ ላይ በምትገኘው የሳህሊተ ምህረት ቤተ ክርስቲያን የቀብር ሥነ ሥርዓት ተደርጐላቸዋል፡፡ ዶክተር ዓለማየሁ የ15 ዓመት ወንድ ልጅና የ12 ዓመት ሴት ልጅ አባት ነበሩ፡፡

የአመሬፍ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ትዕግሥት ግርማ በዶክተር ዓለማየሁ ሞት የተሰማቸውን ሐዘን የገለጹ ሲሆን፣ ‹‹ይህ ለመላው የአመሬፍ ቤተሰብ አሳዛኝ ክስተት ነው፡፡ አመሬፍም በዚህ አሳዛኝ ወቅት ከዶክተር ዓለማየሁ ቤተሰብና በደቡብ ሱዳን ከሚገኙ የአመሬፍ ሠራተኞች ጐን ይቆማል፤›› ብለዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም፣ ‹‹አመሬፍ ጉዳዩን አስመልክቶ ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ጋር በቅርበት እየሠራ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ዶክተር ዓለማየሁ በጁባ የሚገኘው አመሬፍ ዳይሬክተር የሆኑት ባለፈው ዓመት ጥር ወር ሲሆን፣ ከዚያ በፊት እ.ኤ.አ. ከመስከረም 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ የአመሬፍ ምክትል ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል፡፡ ዶክተር ዓለማየሁ አመሬፍ ከመግባታቸው በፊት በዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት፣ በኬር ኢንተርናሽናልና በአማራ ክልል ጤና ቢሮ ይሠሩ ነበር፡፡

ዶክተር ዓለማየሁ በሕክምና የዶክትሬት ዲግሪ ሲኖራቸው፣ በሕዝብ ጤና የማስትሬት ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡

አመሬፍም በዶክተሩ ምትክ የፕሮግራም ማኔጀር የነበሩትን ዶክተር ጆሴፍ ሊፑዋን ዳይሬክተር አድርጐ ሾሟቸዋል፡፡

ዘጠኝ የመድረክ አመራር አባላት በሽብር ወንጀል ተከሰሱ

Wednesday, January 11th, 2012

(ሪፖርተር) — የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ሥራ አስፈጻሚ አባልና የኦሮሞ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) ምክትል ሊቀመንበር፣ አቶ በቀለ ገርባና የመድረክ አባል ድርጅት የሆነው የኦሮሞ ሕዝብ ኮንግረስ (ኦሕኮ) የፓርቲ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ኦልባና ለሊሳን ጨምሮ ዘጠኝ ግለሰቦች፣ በሽብር ወንጀል ተሳትፎ ተጠርጥረው ታህሳስ 30 ቀን 2004 ዓ.ም ክስ ተመሠረተባቸው፡፡ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ጥቅምት 1 ቀን 2004 ዓ.ም በተጻፈ የክስ ማመልከቻ ከትናንት በስቲያ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ክስ የመሠረተባቸው ተጠርጣሪዎች፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ቋንቋ መምህር፣ የኦፌዴን ምክትል ሊቀመንበርና የመድረክ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ በቀለ ገርባ፣ የኦሮሞ ሕዝብ ኮንግረስ የፓርቲ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ኦልባና ሌሊሳ፣ አቶ ወልቤካ ለሚ (ኩማ ቀቢ)፣ አደም ቡሳ፣ ሀዋ ዋቆ፣ መሐመድ መሉ፣ ደረጀ ከተማ፣ አዲሱ ሞክሪና ገልገሎ ጉፋ ይባላሉ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1) (ሀ) (ለ)፣ 38 እና 241ን በመተላለፍ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት በተፈረጀው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ውስጥ ታጣቂ አባል መሆናቸውን የክስ ቻርዱ ይገልጻል፡፡ ኬንያ ሶለሎ ጎልቦ በሚባል ቦታ ሥልጠና ወስደዋል፤ ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲን ሽፋን በማድረግ የኦነግን የሽብር ተልዕኮ ለማስፈጸም መንቀሳቀሳቸውን ክሱ በዝርዝር አስቀምጧል፡፡

ዓቃቤ ሕግ አቶ በቀለ ገርባ የኦፌዴን ፓርቲን ሽፋን በማድረግ ወጣቶችን በማደራጀትና በመመልመል፣ ለኦነግ በህቡዕ እንዲሠሩ በማድረግ፣ በጥር ወር 2002 ዓ.ም በአምቦ ከተማ ኦነግ በቅርቡ አሸንፎ ወደ አገር ውስጥ እንደሚገባ በመግለጽና ‹‹ከኦነግ ጎን ቆመን በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት መጣል አለብን›› በማለት መመርያ በመስጠት፣ በሐምሌ ወር 2003 ዓ.ም ተማሪዎችንና ሕዝቡን ለአመፅና ለብጥብጥ እንዲነሱ ቅስቀሳ እንዲደረግ መመርያ በመስጠትና መምህርነታቸውን ሽፋን በማድረግ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመመረቂያ ጽሑፍ ሊሰጧቸው የሚመጡትን ተማሪዎች ‹‹በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት በሰላማዊ ትግል ማውረድ አዋጭ አይደለም፤ በኃይል ከሥልጣን ማውረድ አለብን፤›› በማለት መመርያ መስጠታቸውን በክስ ቻርጁ አመልክቷል፡፡

አቶ ኦልባና ሌሊሳ ደግሞ ሕጋዊ ፓርቲን (ኦሕኮ) ሽፋን በማድረግ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ በአምቦ ከተማ ወጣቶችን በመሰብሰብ ‹‹ምርጫው ስላልተሳካልን›› በማለት በመንግሥት ላይ ረብሻ እንዲያነሳ ትዕዛዝ በመስጠት፣ በህቡዕ ለኦነግ አባልነት በመመልመል፣ በአምቦ ከተማ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ንብረቶች እንዲወድሙ ማድረጋቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ አቶ ኦልባና ቀኑ ባልታወቀበት ሰኔ 2003 ዓ.ም ምርጫ 2002 ስላልተሳካ በ2004 ዓ.ም በመላው ኦሮሚያ አመፅና ብጥብጥ እንዲነሳ ለማድረግ አባላትን በማደራጀት፣ በማሳተፍ፣ አባላትን በኦሕኮ ከለላ አዲስ አበባ በመጥራት፣ ‹‹ይኼንን መንግሥት በኃይልና በትጥቅ ትግል መናድ አለብን፤›› በማለትና በኦሕኮ ስም የኦነግን ተልዕኮ ለማሳካት ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ክሱ ያብራራል፡፡

ቀሪዎቹም ሰባት ተከሳሾች የኦነግ አባል በመሆን በምዕራብ አርሲ ኮፈሌ ወረዳ በህቡዕ በመንቀሳቀስ ተማሪዎች እንዲረብሹ በማስተባበር፣ በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ እንደነበርና ኬንያ ሰላሎ በመሄድ በኦነግ ካድሬዎች መሠልጠናቸውን ክሱ በዝርዝር አስፍሯል፡፡

ከዘጠኙ ተጠርጣሪ ተከሳሾች መካከል አምስተኛ ተከሳሽ ሀዋ ዋቆ ሴት ስትሆን፣ እ.ኤ.አ በ2006 ኬንያ ማንዴራ የተባለ ቦታ በመሄድ የኦነግ የፖለቲካና ወታደራዊ ሥልጠና መውሰዷን፣ የኦነግ አባል መሆኗን፣ ኬንያ ሞያሌ ቡትዬ በተባለ ቦታ ሆና የኦነግ አባላትን ስትመለምልና ወደ ኬንያ ስትልክና እስከ 2003 ዓ.ም ድረስ የሽብር ተልዕኮውን ለማሳካት ስትንቀሳቀስ እንደነበር፣ በኦሮሚያ ክልል አዳማ ውስጥ የተሀድሶ ሥልጠና በመውሰድ ላይ እያለች የኬንያ ስልክ መስመር አውጥታ ለሚሠለጥኑት አባላት በመስጠት ኦነግን በአዲስ ሁኔታ ለማደራጀት ስትንቀሳቀስ እንደነበረች የዓቃቤ ሕግ የክስ ዝርዝር ይገልጻል፡፡ ደረጀ ከተማ የተባለውም ተጠርጣሪ የኦሕኮ አባልነቱን ከለላ በማድረግ በህቡዕ ለኦነግ አባላትን ሲመለምል እንደነበር፣ በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ጊኒር እንዲሄዱ በማድረግና የሽብር ተልዕኮውን ለማሳካት ከኦነግ ታጣቂ ቡድን ጋር በድብቅ በመገናኘት ሲሳተፍ እንደነበር በክሱ ተጠቅሷል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በኦልባና፣ በደረጃና በገልገሎ ላይ ሁለት ሁለት ክሶችን የመሠረተ ሲሆን፣ መሣሪያዎችን ደብቆ በመገኘት፣ ‹‹የኦሮሞ ነፃነት ግንባር የጋራ ጠላትን አብሮ መፋለም የወቅቱ ጥያቄና የታሪክ ግዴታ ነው፤ በጠመንጃ እናስወግደዋለን፤›› ብለው በመቀስቀስ፣ የሥራ ዕቅድና የወጣቶች ስምሪት ተግባራትን በማስቀመጥና በሦስት ደረጃ በመከፋፈል፣ በማዘጋጀትና ከኦነግ ኃላፊዎች ጋር በመወያየት ውሳኔ በመስጠት መሳተፋቸውን ክሶቹ ያብራራሉ፡፡

ሁሉም ተጠርጣሪ ተከሳሾች የኦነግን የሽብር ተልዕኮ ለማሳካት የቅስቀሳ ጽሑፎችን በማስተላለፍ የተንቀሳቀሱ በመሆኑ፣ በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈጸሙት የመገፋፋትና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ወንጀል መከሰሳቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ ሁሉም ተከሳሾች ለፍርድ ቤቱ በሰጡት የእምነት ክህደት ቃላቸው ክሱን እንደማይቃወሙ፣ ድርጊቱን ግን እንዳልፈጸሙ አስረድተዋል፡፡ ሦስተኛና ስድስተኛ ተከሳሾች ግን ክሱንም ድርጊቱንም ተቃውመዋል፡፡

አቶ በቀለ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ የኦሮሞ ሕዝብ እየተበደለና እየተገፋ ያለ ሕዝብ ነው ብለው ስለሚያምኑ ለውጥ እንዲመጣለት በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ ፖለቲከኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ አቶ ኦልባና በበኩላቸው ለፍርድ ቤቱ እንደገለጹት፣ እሳቸው የታሰሩት ለአምኒስቲ ኢንተርናሽናል ልዑክ መረጃ ሰጥተዋል በሚል መሆኑንና ሌላ ምንም የፈጸሙት ወንጀል እንደሌለ ገልጸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ከትናንት በስቲያና በትናንትናው ዕለት ዘጠኝ፣ ዘጠኝ በድምሩ 18 የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችን የሰማ ሲሆን፣ ምስክርነታቸውን የሰጡት መስካሪዎች ተጠርጣሪዎቹ ለኦነግ አባልነት እንደመለመሏቸው፣ ሥልጠና መውሰዳቸውንና ከኦነግ ጋር ስለነበራቸው ግንኙነት አስረድተው፣ በመጨረሻም የኦነግ ዓላማ የኦሮሞ ሕዝቦችን የሚያስጨርስ መሆኑ ስለገባቸው ከአባልነት ትተው የወጡ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ከፊሎቹ ምስክሮች የተጠርጣሪዎቹ ቤት ሲበረበር በታዛቢነት የተገኙ መሆናቸውን መስክረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ቀሪ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማትና በኤግዚቢትነት የተያዙና ከክሱ ጋር ያልተያያዙ ሰነዶች ካሉ ተያይዘው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ በመስጠት፣ ለጥር 8 ቀን 2004 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የአበራሽ ኃይላይን ዓይኖች ያጠፋው ተከሳሽ በሞት እንዲቀጣ ተጠየቀ

Wednesday, December 28th, 2011

(ሪፖርተር) — የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና አስተናጋጅ የነበረችውን አበራሽ ኃይላይን ሁለት ዓይኖች ማጥፋቱ የተረጋገጠበት የቀድሞ ባለቤቷ አቶ ፍስሐ ታደሰ፣ በሞት እንዲቀጣ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በቅጣት ማክበጃ አስተያየቱ ከትናንት በስቲያ ጠየቀ፡፡ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ጥያቄውን ያቀረበው ክሱን ሲመረምር ቆይቶ ታኅሣሥ 16 ቀን 2004 ዓ.ም በተከሰሰበት ሁለት የወንጀል ክሶች ጥፋተኛ መሆኑን በሰጠው ፍርድ ላረጋገጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ሲሆን፣ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግና የተከሳሽ ጠበቆች የቅጣት ማክበጃና የቅጣት ማቅለያ ሐሳባቸውን እንዲያቀርቡ ፍርድ ቤቱ በጠየቀበት ወቅት ነው፡፡

ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው የቅጣት ማክበጃ ሐሳብ እንደገለጸው፣ ‹‹በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር 117 በተደነገገው መሠረት ወንጀሉ ፍፃሜ አግኝቷል፡፡ በመሆኑም ተከሳሽ ከፈጸመው የወንጀል ድርጊት አንፃር በሞት መቀጣት አለበት፡፡ ዓቃቤ ሕግ ለጠየቀው የሞት ቅጣት ሰባት የቅጣት ማክበጃዎችን ከወንጀል ሕጉ አንቀጾች እየጠቀሰ አቅርቧል፡፡ ተከሳሹ ድርጊቱን ከፈጸመ በኋላ ራሱ ሄዶ ፖሊስ የጠራ ቢሆንም፣ ተከሳሽ ፍርድ ቤት ሲቀርብ ክዶ ተከራክሯል፡፡ ድርጊቱንም የፈጸመው ወራዳነቱን በሚያሳይ ሁኔታ በቀድሞ ባለቤቱ ላይ በመሆኑ፣ ድርጊቱን የፈጸመው ከምሽቱ አራት ሰዓት በኋላ ጨለማን ተገን በማድረግ በዕድሜ ታናሹ በሆነች ሴት ልጅ ላይ በመሆኑ፣ ጥቃቱን ሲፈጽምባት ሆን ብሎ ደም ወደ አዕምሮዋ እንዲፈስና ጉዳት እንዲደርስባት በማድረጉ፣ ሆስተስ ሆና እየሠራች ቤተሰቦቿን እንዳትረዳና እስከ መጨረሻው ሥራ እንዳይኖራት በማድረጉ፣ የቀድሞ ፍቅረኛዋ ስለነበር ቢፋቱም በእሷ ላይ ወንጀል ይፈጽማል የሚል እምነት የሌላት በመሆኑ፣ ከፍቺ በኋላ ሳትጠራጠር በመቅረቧ ከባድ የመግደል ሙከራ ፈጽሞባታል፤›› በማለት ሌሎችንም ዝርዝር ጉዳዮች በማቅረብ ቅጣቱ ከብዶ በሞት ወይም በእድሜ ልክ እንዲቀጣ ጠይቋል፡፡

የተከሳሹ ጠበቆች የቅጣት ማቅለያ ሐሳብ እንዲያቀርቡ ሲጠየቁ፣ ‹‹ባለፈው ቀጠሮ አቤቱታችንን በጽሕፈት ቤት በኩል አስገብተን ስለነበር ዛሬ የመጣነው መልስ ለመስማት በመሆኑ አልተዘጋጀንም፤›› ብለዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የጠበቆቹን አስተያየት ካደመጠ በኋላ፣ አቤቱታ የተባለው ከማስረጃ ጋር ግንኙነት የሌለው ከሆነ ነው፡፡ ከማስረጃ ጋር ግንኙነት ያለው አቤቱታ አልተባለም፤ ቢሮ የቀረበው አቤቱታ የችሎቱን ሒደት ሊያቋርጥ የሚችል አይሆንም፡፡ እናንተም ስትሠሩበት የቆያችሁበት ነው እንጂ አዲስ አሠራር አይደለም፡፡ ጥፋተኛ ከተባለ በኋላ ቀጠሮ የሚሰጠው ለቅጣት ውሳኔ እንጂ አስተያት ለመቀበል አይደለም፡፡ ተመካከሩና የቅጣት ማቅለያ አስተያየታችሁን ስጡ ብሏል፡፡

ጠበቆቹ፣ ‹‹የእኛ ስህተት ነው ከተባለ እንቀበላለን፡፡ ግን አልተዘጋጀንም፤ ፍርድ ቤቱ አልተረዳችሁም ሊለን ይችላል፤›› ካሉ በኋላ ከተከሳሹ ጋር በመመካከር የቅጣት ማቅለያ ሐሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

የተከሳሽ ጠበቆች በሰጡት የቅጣት ማቅለያ አስተያየት እንደገለጹት፣ ደንበኛቸው ጥፋተኛ የተባለው በወንጀል ሕጉ 27(1) እና 539(1) መሠረት ነው፡፡ በግድያ ሙከራ በማንኛውም የሕግ ደረጃ በሞት ይቀጣ አይባልም፡፡ በመሆኑም የዓቃቤ ሕግን በሞት ይቀጣ ጥያቄን ተቃውመዋል፡፡ አብዛኛዎቹ የቅጣት ማክበጃ ሐሳቦች በክሱ ላይ የተጠቀሱና ክሱን ያቋቋሙ በመሆናቸው በማክበጃነት ሊቀርቡ አይገባም ብለዋል፡፡ ተጎጂዋ በተከሳሽ ላይ የነበራት እምነት መባሉ አቻ ሆነው የሚኖሩ ስለነበሩ፣ አንዱ ባንዱ ላይ የሚኖር ዓይነት ሆኖ የቀረበውንም እንቃወማለን ብለዋል፡፡ ተከሳሹ የቀደመ የወንጀል ሪከርድ የለበትም፡፡ በዚህም ፀባዩ መልካም እንደነበር ይገመታል፡፡ በሠራው ድርጊት ተፀፅቷል፡፡ ለዚህም ማስረጃ የሚሆነው በተጎጂዋ ላይ ድርጊቱን ከፈጸመ በኋላ ወደ ፖሊስ ሄዶ ባይናገር የበለጠ አደጋ ይደርስ ነበር፡፡ የኤችአይቪ/ኤድስ ታማሚ ነው፡፡ ከአሥር በላይ የሚሆኑ ረዳት የሌላቸውን ወገኖቹን እንደሚረዳ በመግለጽ (ማስረጃ ሰነድ እናስገበለን) ቅጣቱ ቀሎ እንዲወሰንለት ጠበቆቹ ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የሁለቱን ተከራካሪ ወገኖች የቅጣት ማክበጃና ማቅለያ ሐሳብ ከሰማ በኋላ፣ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ለታኅሣሥ 20 ቀን 2004 ዓ.ም. የቀጠሮ ትዕዛዝ ሲሰጥ፣ ተከሳሹ አቤቱታ አለኝ አለ፡፡

አቤቱታውን በጽሕፈት ቤት በኩል እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ቢነግረውም፣ ‹‹በጽሕፈት ቤት በኩል ተብሎ ባመለክትም ምላሽ አላገኘሁም፡፡ እኔ የምናገረው እዚህ ነው፡፡ ይህ ፍርድ ቤት ካልሰማኝ የት ልናገር? ሚዲያዎች ‹የምንፈራው ውሸትን ብቻ ነው› እያሉ ስለእኔና ተጎጂዋ በሌሎች ሰዎች የተሰጠ ዘገባ እያስተላለፉ ነው፡፡ ‹የሚዲያዎቹን ስም ጠቅሷል› ለእኔም ዕድል ይሰጠኝና ልናገር፡፡ ያልተናገርኩት ብዙ ጉድ አለ፡፡ እኔ ስለቅጣቱ ችግር የለብኝም፡፡ የሴቶች ጥቃት በእኔ መቀጣት የሚቆም ከሆነ ችግር የለም፤›› በማለት ተናገረ፡፡

ፍርድ ቤቱ ተከሳሹን በማስቆም አቤቱታውን በጽሕፈት ቤት በኩል ማቅረብ እንደሚችል፣ ከውሳኔ በኋላ በይግባኝም ቢሆን ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ማቅረብ እንደሚችልና መጠየቅ ያለበት አካል ካለ እንደሚጠየቅ በመግለጽ ችሎቱ አበቃ፡፡

ሆስተስ አበራሽ ኃይላይ በቀድሞ ባለቤቷ አቶ ፍስሐ ታደሰ መስከረም 2 ቀን 2004 ዓ.ም. ከምሽቱ 4፡30 ሰዓት ላይ ተከራይታ በምትኖርበት ገርጂ ኮንዶሚኒየም ቤት ውስጥ ጥቃት ደርሶባታል፡፡ ራሱ ባመጣቸው የአካባቢው ፖሊሶችና ግቢውን በሚጠብቁ ጥበቃዎች ዕርዳታ በራሱ ወጪ ኮሪያ ሆስፒታል፣ በሪፈራል ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል፣ ከዚያም ቤተዛታ ሆስፒታል ጊዜያዊ ዕርዳታ ተደርጎላታል፡፡ መስከረም 5 ቀን 2004 ዓ.ም. ወደ ባንኮክ ለሕክምና ሄዳ ሁለቱም ዓይኖቿ ከጥቅም ውጭ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ እስካሁንም በሕክምና ላይ ትገኛለች፡፡ ዓቃቤ ሕግ በአቶ ፍስሐ ታደሰ ላይ በከባድ የሰው መግደል ሙከራና በሕግ የተከለከለን የጦር መሣሪያ ይዞ መገኘት የወንጀል ክሶችን መሥርቷል፡፡

የሰዎች ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ ካሰማና ካሳየ በኋላ፣ ፍርድ ቤቱ አቶ ፍስሐን ተከላከል ብሎ በይኖበታል፡፡ አቶ ፍስሐም የሰዎች መከላከያ ምስክሮችና የሕክምናና የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል፡፡

ፍርድ ቤቱ ሁለቱም ወገኖች ያቀረቡትን ማስረጃዎች ከሕጉ ጋር በማመሳከር መርምሯል፡፡ ሆኖም አቶ ፍስሐ ያቀረባቸው ምስክሮች ሁለቱ ባልና ሚስት ሆነው ሲኖሩ ይከባበሩ፣ ያስቀኑና መልካም ትዳር እንደነበራቸው ከማስረዳት ውጭ ስለተፈጠረው ሁኔታ የሚያስረዱ ሆነው አለማግኘቱን፣ የሰነድ ማስረጃውም ከደረሰው የወንጀል ድርጊት ጋር እምብዛም ዝምድና ስለሌለው፣ የዓቃቤ ሕግን ማስረጃዎች ሊከላከል ባለመቻሉ ጥፋተኛ ብሎታል፡፡

27 የመኢአድ አባላት ታሰሩ

Wednesday, December 28th, 2011

(ሪፖርተር) — በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ልዩ ዞን በዘንጋ አዋንዴ ቀበሌ 27 የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) አመራርና አባላት በገዢው ፓርቲ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን መኢአድ አስታወቀ፡፡ የደምባ ጎፋ ወረዳ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ማዩ ማይጠሎ በበኩላቸው፣ የተጠቀሱት የመኢአድ አባላት የታሰሩት በአካባቢው እየተከናወነ ያለውን የልማት ሥራ ለማደናቀፍ በመንቀሳቀሳቸው መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

መኢአድ ትናንት ለሪፖርተር በላከው ጥቆማ እንዳስታወቀው፣ ታኅሣሥ 16 ቀን 2004 ዓ.ም. ከታሰሩት የመኢአድ አባላት መካከል ስድስቱ የፓርቲው አመራሮች ናቸው፡፡

በጎፋ ልዩ ዞን የዘንጋ አዋንዴ ቀበሌ የመኢአድ ሰብሳቢ አቶ ኢልካዩ ኤሮ፣ ምክትል ሰብሳቢው መምህር አየለ ታደሰ፣ ዋና ጸሐፊው አቶ ዘሪሁን እኩሌ፣ የመኢአድ ሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ ኢሳያስ ዘርቦ፣ ሃምሳ አለቃ ማናዬ ሞላልኝና አቶ መንግሥቱ ማናዬ ታኅሣሥ 16 ቀን 2004 ዓ.ም. ከቀኑ 10፡00 ሰዓት አካባቢ በመኢአድ ጽሕፈት ቤት ውስጥ በስብሰባ ላይ እያሉ በፖሊሶች የታሰሩ መሆናቸውን መኢአድ አስታውቋል፡፡

ሌሎቹ ሃያ አንድ የዘንጋ አዋንዴ ቀበሌ የመኢአድ ሥራ አስፈጻሚዎችና አባላት የታሰሩትም ከላይ በተጠቀሰው ቀን ምሽት የወረዳው የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት የመኢአድ አባላት በሚኖሩበት አካባቢ አሰሳ እንዲካሄድ ካዘዙ በኋላ መሆኑንም ገልጿል፡፡

የዳምባ ጎፋ ወረዳ የምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ማዩ ማይጠሎ በበኩላቸው፣ የመኢአድ አባላት የታሰሩት የክልሉ መንግሥት በአካባቢው እያከናወነ ያለውን የተፋሰስ ልማት ለማደናቀፍ ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

እርሳቸው እንዳሉት፣ በደምባ ጎፋ ወረዳ የተፋሰስ ሥራ ለመሥራት ለቀያሾች ሥልጠና እየተሰጠና ጐን ለጐን ሌሎች የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ባሉበት በአሁኑ ጊዜ፣ ሃያ ሰባቱ የመኢአድ አባላት ‹‹የተፋሰስ ሥራውን አንሠራም›› ብለው በመቃወማቸው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሊውሉ ችለዋል፡፡

በአካባቢው የሚኖሩት የመኢአድ አባላት በሌሎች ቀበሌዎች የሚገኙ ነዋሪዎች በተፋሰስ ሥራው እንዳይሳተፉ የሚጠይቅ ደብዳቤ አዘጋጅተው ለመበተን ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን የጠቆሙት አቶ ማዩ፣ ታኅሣሥ 16 ቀን 2004 ዓ.ም. ሃያ ሰባቱ የመኢአድ አባላት ልማቱን ለማደናቀፍ ተመሳሳይ አጀንዳ ይዘው ሲወያዩ በነበረበት ወቅት በፀጥታ ኃይሎች መታሰራቸውን አረጋግጠዋል፡፡

የመኢአድ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የደቡብ ኢትዮጵያ ቀጣና ኃላፊ አቶ እንድሪያስ ኤሮ በበኩላቸው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የመኢአድ አባላት የታሰሩት ልማት በማደናቀፋቸው ሳይሆን የግለሰቦችን ማሳ አንቆፍርም ብለው በመቃወማቸው ነው፡፡

በአካባቢው የሚገኘውን የግለሰቦች ማሳ ከመቆፈር ይልቅ ነዋሪዎች በጋራ የሚጠቀሙበትን መሬት ለተፋሰስ ሥራ ማዋል የተሻለ እንደሚሆን በመጠቆም ለቀበሌው ኃላፊዎች በጽሑፍ ጥያቄ ማቅረባቸውን የገለጹት አቶ እንድሪያስ፣ ይህ የመቃወም መብት ልማት እንደማደናቀፍ ተወስዶ የመኢአድ አባላት ለእስር መዳረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡

‹‹የዜጎች የመናገርና የመጻፍ መብት የተጠበቀ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች ማንኛውንም ነገር የመቃወም መብት አላቸው፤›› የሚሉት አቶ እንድሪያስ፣ የደምባ ጎፋ ወረዳ ባለሥልጣናት ግን ሕገ መንግሥቱ ለዜጐች የሰጠውን መብት በመጣስ ሰላማዊ ዜጐችን እያሰሩ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡

‹‹ዜጎች በመንግሥት ባለሥልጣናት የሚወሰኑ ውሳኔዎችን መቃወም አይችሉም ወይ?›› የሚል ጥያቄ ያቀረብንላቸው የወረዳው ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ማዩ ማይጠሎ ግን፣ ‹‹ይህ የልማትና የሕይወት ጉዳይ ነው፡፡ እነሱ ካልሠሩ ማን መጥቶ ሊሠራላቸው ነው? አንሠራም ማለት አይችሉም፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ወረዳውም በመኢአድ አባላት ላይ ‹‹ልማትን በማደናቀፍ›› በሚል ክስ ለመመሥረት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

መኢአድ እንደሚለው፣ ሁሉም የመኢአድ አመራርና አባላት ከሚኖሩበት አካባቢ 17 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው የሻውላ ከተማ ታስረዋል፡፡ የዘንጋ አዋንዴ ቀበሌ የመኢአድ ጽሕፈት ቤትን የቀበሌው የመኢአድ አባላት ከመኢአድ ከፍተኛ አመራር ጋር በመመካከር በ2001 ዓ.ም. በራሳቸው ወጪ እንዳቋቋሙት መኢአድ አስታውቋል፡፡

በአቧሬ ገበያ ሱቆችና መኖርያ ቤቶች ወደሙ

Wednesday, December 21st, 2011

በአዲስ አበባ ከሚገኙ ትላልቅ የገበያ ሥፍራዎች መካከል አንዱ በሆነው አቧሬ ገበያ በተነሳ ድንገተኛ የእሳት ቃጠሎ፣ 103 ሱቆችና የመኖርያ ቤቶች መውደማቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ድርጅት መረጃ ግን 70 ሱቆችና መኖሪያ ቤቶች ናቸው የተቃጠሉት ይላል፡፡ “51 ሱቆችና 52 መኖርያ ቤቶች ናቸው የወደሙት፤” ሲሉ የአካባቢው ነጋዴዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የወረዳ ስድስት የሥራ ኃላፊዎችም በእስካሁኑ ሒደት 100 የሚጠጉ ተጎጂዎችን መመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡

ሰኞ ለማክሰኞ አጥቢያ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ላይ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ ሱቆቹንና መኖርያ ቤቶችን ሙሉ በሙሉ ወደ ትቢያ ለውጧል፡፡

አደጋው በተከሰተበት ሰዓት የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ድርጅት ጥሩ በሚባል ሰዓት በአካባቢው ቢደርስም፣ ንብረቶቹን ግን ከቃጠሎ ማትረፍ እንዳልቻለ ተጎጂ ነጋዴዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የእሳት አደጋ ተከላካዮች በስፍራው ሲደርሱ አንድ ሱቅ ወድሞ እሳቱ ወደ ሁለተኛው ሱቅ እየተዛመተ ነበር የሚሉት የአካባቢው ነጋዴዎች፣ ድርጅቱ ግን ንፋስ አጠረኝ! መግቢያ አጣሁ! በሚል ጊዜ በመፍጀቱ እሳቱ ተዛምቷል ሲሉ ምሬታቸው ገልጸዋል፡፡

“አጠገባችን ወንዝ አለ፡፡ ወንዙን ተጠቅመን እሳቱን መቆጣጠር እንችል ነበር፤ ነገር ግን ተከልክለናል፤” ሲሉ የልብስ መሸጫ ሱቃቸው ዓይናቸው እያየ እንዳጡ የሚናገሩ አንድ ነጋዴ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ያስገረማቸውን ነገር ለሪፖርተር ሲገልጹ፣ ከአንድ ዓመት በፊት የእሳት አደጋ አገልግሎት ድርጅት በአቧሬ ገበያ እሳት ቢነሳ እንዴት ሊቆጠጠረው እንደሚችል ልምምድ አድርጎ ነበር፡፡ ‹‹ያ ሁሉ ልምምድ የትገባ?›› ሲሉ አግራሞታቸውን ገልጸው፣ የድርጅቱን የብቃት ደረጃ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

የድርጅቱ ኮሙዩኒኬሽን ኦፊሰር አቶ ንጋቱ ማሞ እንደገለጹት፣ ሱቆቹም ሆኑ ቤቶቹ የተሠሩት ግድግዳቸውም፣ ጣሪያቸውም በቆርቆሮ ሆኖ ነው፡፡ ቆርቆሮ ላይ ውኃ በሚለቀቅበት ጊዜ ወደ ውስጥ የሚገባ ባለመሆኑ የማጥፋቱን ሥራ አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ አቶ ንጋቱ ቀጥለውም ገበያው መኪና የሚያስገባ መተላለፊያ መንገድ የሌለውና ተቀጣጣይ የሆኑ ሸቀጦች ለምሳሌ ጋዝ የሚገኙበት በመሆኑ እሳቱን ለመቆጣጠር ሁለት ሰዓት ተኩል ፈጅቷል፡፡

የልምምዱን ሁኔታ ሲገልጹም ድርጅቱ የልምምድ ፕሮግራሞች አሉት፡፡ የሚለማመደው እንዴት በቅንጅት እንደሚሠራና የትራፊክ ሁኔታን ለመፈተሽ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ያም ሆኖ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች አገልግሎት ድርጅት የቱንም ቢል ተጎጂዎችን የሚያሳምን አልሆነም፡፡ ተጎጂዎቹ ይህ ጥፋት የደረሰባቸው በድርጅቱ ድክመት እንደሆነ እርግጠኛ ሆነው ይገልጻሉ፡፡

እሳቱን ለማጥፋት ዘጠኝ የእሳት ማጥፊያ ከባድ መኪኖች ተሰማርተዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱ መኪና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲሆን፣ በሰዓቱ የነበሩ የዓይን እማኞች ለእሳቱ መጥፋት ከፍተኛውን ድርሻ የወሰደው የአየር መንገድ የእሳት ማጥፊያ ተሽከርካሪ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ምክንያታቸው መኪናው የሚለቀው የውኃ ኃይል ብዛትና ውኃው ረጅም ርቀት መጓዝ መቻሉ ነው፡፡

በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 በሚገኘው አቧሬ ገበያ በደረሰው ቃጠሎ 500 ሺሕ ብር  መውደሙንና ሁለት ሚሊዮን ብር ከውድመት መትረፉን ድርጅቱ ገልጿል፡፡ ይህንንም ነዋሪዎቹ አይቀበሉም፡፡ ከአንድ ሱቅ ብቻ ከ150 ሺሕ ብር በላይ ንብረት ወድሟል፡፡ ምን ዓይነት ስሌት ነው ሲሉ ለድርጅቱ ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡

በዚህ አደጋ አምስት የድርጅቱ የእሳት ማጥፊያ ብርጌድ ሠራተኞችና ሁለት የአካባቢው ነዋሪዎች ለጉዳት ተዳርገዋል፡፡ አንድ ሰው የደረሰባቸው ጉዳት ከፍተኛ ሲሆን በየካቲት 12 ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው ነው፡፡

አቧሬ ገበያ ከመርካቶና ከሾላ ገበያዎች ቀጥሎ ሕዝቡ የሚገበያይበት ትልቅ ገበያ ነው፡፡ በአካባቢው የመኖርያ ቤት ኪራይ ርካሽ በመሆኑ ሸቀጦች በተነፃፃሪ በርካሽ ዋጋ የሚቀርቡበት ገበያ ነው፡፡

አደጋው የደረሰበትን ይህን ቦታ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታውና የከንቲባው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞቱማ መቃሳን ጨምሮ የተለያዩ የከተማው ባለሥልጣናት ጎብኝተውታል፡፡

አቶ አባተ በሥፍራው ለተገኙ የወረዳው ኃላፊዎች ከከተማው ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ጋር ጊዜያዊ ኮሚቴ እንዲያቋቁሙና በአስቸኳይ ጊዜያዊ መጠለያና ብርድ ልብስ ለተጎጂዎች እንዲቀርብ አዘዋል፡፡

 

የኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ከኃላፊነት ለቀቁ

Saturday, December 17th, 2011

የኢትዮጵያ ኢንቨሰትመንት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሆነው ለረዥም ዓመታት ያገለገሉት አቶ አቢ ወልደመስቀል ከኃላፊነታቸው ለቀቁ፡፡

ታማኝ የዜና ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኅዳር 26 ቀን 2004 ዓ.ም. አቶ አቢ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በፃፉት ደብዳቤ በራሳቸው ፈቃድ ሥራቸውን ከጥር 1 ቀን 2004 ዓ.ም. ጀምሮ መልቀቅ እንደሚፈልጉ ገልጸው መልቀቂያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

ጥያቄያቸው ተቀባይነት ማግኘቱን የሚገልጽ ደብዳቤ ሐሙስ ዕለት ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፊት ቤት እንደደረሳቸው ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

አቶ አቢ በውጪ አገር የሚገኝ በአንድ ዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ ሥራ ማግኘታቸውን የገለጹት ምንጮች፣ በቅርቡ ወደዚያው እንደሚያቀኑ ተናግረዋል፡፡

አቶ አቢ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲን በተለያዩ ኃላፊነቶች ለ20 ዓመታት ያህል አገልግለዋል፡፡ አቶ አቢ መሥርያ ቤቱ ሲቋቋም በመምሪያ ኃላፊነት ሥራቸውን የጀመሩ ሲሆን በመቀጠል ምክትል ዋና ሥራ አሰኪያጅ ሆነው አገልግለዋል፡፡ መሥሪያ ቤቱ ወደ ኮምሽንነት ሲቀየር ምክትል ኮምሽነር ሆነው ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡

በወቅቱ ዋና ኮምሽነር የነበሩት አቶ ታደሠ ኃይሌ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ሲሾሙ አቶ አቢ ወደ ዋና ኮምሽነርነት ተሸጋግረዋል፡፡ በመቀጠልም መሥርያ ቤቱ ወደ ኤጀንሲነት ከተቀየረ በኋላ እስከአሁን በዋና ዳይሬክተርነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ አቶ አቢ ለመሥሪያ ቤቱ ባበረከቱት የረዥም ጊዜ አገልግሎት ከመንግሥት ምስጋና እንደተቸራቸው ምንጮች አክለው ገልጸዋል፡፡

ስምንት ሕፃናት ደቡብ ክልል ማሳደጊያ ውስጥ ሞቱ

Saturday, December 10th, 2011

በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን ውስጥ በሚገኘው ቅዱስ ፍራንቼስኮ በተባለ የሕፃናት ማሳደጊያ ውስጥ፣ ስምንት ሕፃናት በኩፍኝ ሞቱ ሦስቱ ሕፃናት ለአሜሪካውያን አሳዳጊዎች በጉዲፈቻ ተሰጥተው የነበሩ መሆኑን፣ ማሳደጊያው ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ ፍትሐ ብሔር ቦሌ ምድብ ችሎት ህዳር 11 ቀን 2004 ዓ.ም. ገልጿል፡፡ ማሳደጊያው ይህን ሊያሳውቅ የቻለው ከክልሉ በአደራ የተረከባቸውን 14 የጉዲፈቻ ውሳኔ ያረፈባቸውን ሕፃናት ለጉዲፈቻ አድራጊዎቹ ወኪል እንዲያስረክብ በታዘዘው መሠረት ቀርቦ ባስረዳበት ጊዜ ነው፡፡

ማሳደጊያው ሕፃናቱ መሞታቸውን ባስረዳበት ደብዳቤ ከሞቱት ሕፃናት ውስጥ ውሳኔ ያረፈባቸው ተረፈ ኃይሉ፣ ምህረት መሐመድ፣ ተገኝ ታደሰና ተረፈች አቡኮ የተባሉ ሕፃናት እንደሚገኙበት ይግለጽ እንጂ፣ የመጨረሻዋ ሕፃን ሞት ያልተረጋገጠ መሆኑን ከፍርድ ቤቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከዚህ ቀደም ማሳደጊያው አሥራ አራቱን ሕፃናት ለጉዲፈቻ አድራጊ ቤተሰቦች ወኪሎች እንዲያስረክቡ በፍርድ ቤቱ ታዞ የነበረ ቢሆንም፣ ሕፃናቱ ከዚህ በፊት ያድጉበት የነበረው ስፔሻል ሚሽን ፎር ኮሚዩኒቲ ቤዝድ ዴቨሎፕመንት የሚባል ማሳደጊያ በክልሉ መንግሥት ከተዘጋ በኋላ፣ በአደራ የተረከባቸው በመሆኑ ማስረከብ እንደማይችል ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ፍርድ ቤቱም ማሳደጊያው ሕፃናቱ የጉዲፈቻ ውሳኔ ያረፈባቸው በመሆኑ ለህጋዊ ወላጆች ወኪል እንዲያስረክብ በድጋሚ ትዕዛዝ ሊያስተላልፍ ችሏል፡፡

ፍርድ ቤቱ ከዚህም በተጨማሪ የደቡብ ክልል ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ሕፃናቱን ተረክቦ በአደራ የሰጠ አካል በመሆኑ፣ ሕፃናቱን ቀርቦ እንዲያስረክብ ትዕዛዝ ቢያስተላልፍም በትዕዛዙ መሠረት ቀርቦ ባለመፈጸሙ፣ የቢሮው ኃላፊ በፌዴራል ፖሊስ ታስረው እንዲቀርቡና ልጆቹን እንዲያስረክቡ ጥቅምት 30 ቀን 2004 ዓ.ም. ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡

በዚህ ትዕዛዝ መሠረት የቢሮው ኃላፊ አቶ ስኳሬ ሸዳ፣ የሴቶች ዘርፍ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሕይወት ኃይሉና የሕፃናት ዘርፍ ዳይሬክተር ወ/ሮ አሸነፈች አድማሱ ከሞት የተረፉትን ሕፃናት በፌዴራል ፖሊስ አማካይነት ይዘው ህዳር 12 ቀን 2004 ዓ.ም. ፍርድ ቤቱ ቀርበዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም ሕፃናቱ ውሳኔ ካረፈባቸው ከሐምሌ ወር ጀምሮ እንዲያስረክቡ ሲጠየቁ ለምን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዳላከበሩ ሲጠይቃቸው፣ ሕፃናቱን ማሳደጊያ ከተዘጋባቸው ሌሎች ሕፃናት ጋር ወደ ሌሎች ማሳደጊያዎች በአደራ ያስገቧቸው መሆኑን ገልጸው፣ ሕይወታቸው በድጋሚ ይጣራ በሚል መነሻ እንዲቆዩ የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፍርድ ቤት በሕፃናቱ ላይ ውሳኔ አስተላልፎ እያለ የክልሉ መንግሥት የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ያልፈጸመው በክልሉ ስም የመጣ ትዕዛዝ ባለመኖሩ ነው በሚል ምክንያት ባቆየበት ወቅት፣ ልጆቹን በአደራ ባስቀመጠበት ማሳደጊያ ውስጥ በተከሰተው ኩፍኝ ውሳኔ ከተሰጠባቸው ልጆች ውስጥ አራት ሕፃናት መሞታቸውንና በተጨማሪም ሌሎት አራት ሕፃናት መሞታቸውን ኃላፊዎቹ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

ኃላፊዎቹ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሠረት ያልፈጸሙት በክልሉ ስም የመጣ ውሳኔ ባለመኖሩ ባለማወቅ መሆኑንና ወደፊት ለሚሰጡ ትዕዛዞች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን በመግለጽ ፍርድ ቤቱን ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም ቢሮው በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሠረት ያልፈጸመው በቂ ግንዛቤ ሳይኖረው መሆኑን በመግለጽ፣ በሕጉ መሠረት በማስጠንቀቂያና በተግሳጽ እንዳሰናበታቸው ህዳር 12 ቀን 2004 ዓ.ም. የሰጠው ትዕዛዝ ያስረዳል፡፡
የጉዲፈቻ ውሳኔ ተሰጥቶባቸው በኩፍኝ ምክንያት ሕይወታቸው ካለፈው ሕፃናት አንዱ ሕፃን ተገኝ ታደሰ፣ በርናርድ ፍራንክሊን ሉዊስ ጁኒየርና ኤሪን ክርስቲና ሉዊስ ለተባሉ አሜሪካውያን ጥንዶች በጉዲፈቻ ተሰጥቶ ሒደቱ እስኪያልቅ በመጣበበቅ ላይ ነበር፡፡
ሕፃን ተገኝ ለጉዲፈቻ ከመሰጠቱ በፊት የሁለት ወር ዕድሜ እያለው መጋቢት 21 ቀን 2003 ዓ.ም. ተጥሎ የተገኘ መሆኑን፣ ቀደም ሲል ያድግበት በነበረው ስፔሻል ሚሽን ፎር ኮሚዮኒቲ ቤዝድ ዴቨሎፕመንትና በጉዲፈቻ አድራጊ ቤተሰቦቹ ወኪል ወርልድ አሶስዬሽን ፎር ችልድረን ኤንድ ፓረንትስ መካከል ግንቦት 3 ቀን 2003 ዓ.ም. የጉዲፈቻ ውል ተፈጽሟል፡፡ ፍርድ ቤቱም ይህን የጉዲፈቻ ውል ሐምሌ 6 ቀን 2003 ዓ.ም. አጽፅቆታል፡፡

በኩፍኝ ምክንያት ከሞቱት ሕፃናትና የፍርድ ቤት ውሳኔ ካረፈባቸው መካከል ሁለተኛው ተረፈ ኃይሉም እንዲሁ ብሬክዌል ዳቢህ ኢንግና ታና ኤሪን ራይችትኒክ ኢንግ በተባሉ አሜሪካዊያን ጥንዶች በጉዲፈቻ ተሰጥቶ ሒደቱ እስኪያልቅ በመጠባበቅ ላይ ነበር፡፡
ሕፃኑ የ10 ቀናት ዕድሜ እያለው መጋቢት 14 ቀን 2003 ዓ.ም. ተጥሎ የተገኘ ሲሆን፣ ጉዲፈቻ አድራጊ ወላጆቹ በወኪላቸው ወርልድ አሶስዬሽን ፎር ችልድረን ኤንድ ፓረንትስ አማካይነት ከተመሳሳይ ማሳደጊያ ጋር ሚያዝያ 21 ቀን 2003 ዓ.ም. የጉዲፈቻ ውል ተፈራርመው ፍርድ ቤቱ ሰኔ 28 ቀን 2003 ዓ.ም. ውሉን አፅድቆታል፡፡

ሦስተኛዋ የኩፍኝ ሰለባ የሆነችው ሕፃን ምህረት መሐመድ ዶ/ር ኢላና ናሽ ለተባሉ አሜሪካዊት ሴት ለጉዲፈቻ ተሰጥታ የነበረ መሆኑን፣ ወላጅ እናቷ የልጅቷን አባት የማታውቅ መሆኑንና ማሳደግ እንደማትችል በመግለጽ፣ ሕፃኗ በጉዲፈቻ እንድትሰጥ ተስማምታ የነበረ መሆኑን ከውሳኔው ለመረዳት ተችሏል፡፡

ዶ/ር ናሽ የ11 ወራት ዕድሜ የነበራትን ሕፃን በጉዲፈቻ ወስዶ ለማሳደግ በተመሳሳይ ወኪል ከተመሳሳይ የሕፃናት ማሳደጊያ ድርጅት ጋር ግንቦት 10 ቀን 2003 ዓ.ም. የጉዲፈቻ ውል የተፈራረሙ ሲሆን፣ ውሉን ፍርድ ቤቱ ሰኔ 28 ቀን 2003 ዓ.ም. አፅድቆታል፡፡
የክልሉ መንግሥት ውሳኔ ካረፈባቸው ሕፃናት መካከል ሞተዋል ተብለው ለፍርድ ቤቱ ሪፖርት ከተደረገባቸው ሕፃናት ውስጥ፣ ሕፃን ተረፈች አቡኮ የተባለችውን ልጅ የእኔ ናት ብሎ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ ያቀረበ አካል ባለመኖሩ፣ ሞቷ እርግጠኛ አለመሆኑን ከፍርድ ቤቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ፍርድ ቤቱ የሕፃናቱን ሞት ከማሳደጊያው ቅዱስ ፍራንቼስኮና ከክልሉ ኃላፊዎች ከተረዳ በኋላ የፌዴራል ፖሊስ የሕፃናቱን ሞት ምክንያት በምርመራ አጣርቶ ውጤቱን ታህሳስ 20 ቀን 2004 ዓ.ም. እንዲያቀርብ አዟል፡፡

“ የአገራችን መሠረታዊ ችግሮች በፕሮፖጋንዳ ጋጋታና በባዶ መፈክር፣ እንዲሁም በአልባሌ ትወና አይፈታም” መድረክ

Saturday, December 10th, 2011

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲዊ አንድነት መድረክ በቅርቡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ድርጅት የተላለፈው ‹‹አኬልዳማ›› የተሰኘው ፕሮግራም ‹‹ድራማ›› መሆኑንና የመድረክ አባል ድርጅቶችን ድራማው በፍፁም አይከፋፍላቸውም አለ፡፡ መድረክ ትናንት ‹‹በፈጠራ የፖለቲካ ተውኔት ተቃዋሚዎችን መክሰስና ሕዝቡን ማሸበር ይቁም›› በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ፣ ኢሕአዴግ “አኬልዳማ” በሚል የፈጠረው ድራማ “የመድረክ አባላት እየተከፋፈሉ ነው” የሚል መልክት ለማስተላለፍ አቅዷል ይላል፡፡

‹‹ለመድረክና ለአባል ድርጅቶቹ ህልውና ስጋት እየሆነ ያለው ኢሕአዴግ ራሱ መሆኑን ሕዝባችን ይገነዘበዋል ብለን እናምናለን፡፡ የሩቁን እንኳ ብንተወው ላለፉት አሥር ወራት የኢሕአዴግ የፕሮፓጋንዳ ጥቃት ዒላማ ያልሆነ የመድረክ አባል የለም፤›› ሲል የመድረክ መግለጫ ያትታል፡፡

መድረክ ለዚህ ማስረጃውን ሲያቀርብ የመድረክ አባል ድርጅቶች የሆኑ የኦሮሞ አባል ድርጅቶች አባላት በግፍ ታስረዋል፣ መሪዎቻቸውም በአኬልዳማ ቴአትር ውስጥ ተካተዋል፡፡ በዓረና አባላት ላይ በተከታታይ የተፈጸሙት የእሥርና የወከባ ዘመቻዎች የሚታወቁ ናቸው፡፡ የአንድነት ፓርቲ አባላት ለአሰቃቂ እስር ተዳርገዋል፡፡ የአንድነት አባላት ያልሆኑ ሰዎች “ወንጀለኛ የአንድነት አባላት›› በማለት ሕዝቡን ለማወናበድ ጥረት ተደርጓል ይላል፡፡

“እኛ የገዛ ሕዝባችንን እልቂትና ደም መፍሰስ በጭራሽ አንመኝም” የሚለው የመድረክ መግለጫ፣ ‹‹አኬልዳማ›› የተሰኘው ድራማ የሕዝቡን ሰቆቃና ዋይታ ለመደበቅና ያልሆነ አቅጣጫ ለመፍጠር ያደረገው ሙከራ ነው ሲል የቴሌቪዥኑን ፕሮግራም ይኮንነዋል፡፡

መድረክ አያይዞ የአገሪቱ ችግሮች በአልባሌ ትወና እንደማይፈታ ታውቆ፣ በአስቸኳይ አገሪቱንና ሕዝቦቿን ወደ ብሔራዊ መግባባት መውሰድ እንደሚገባ ገልጿል፡፡

“በአኬልዳማ ድራማ የመድረክ አባል ድርጅቶች የአገሪቱን ገጽታ ለማበላሸት፣ ከሻዕቢያ ጋር በማቆራኘት አፍቃሪ ኤርትራ ናቸው የሚል ተረት ለማስነገርም ሞክሯል፡፡ በመድረክ እምነት የአገራችን ገጽታ እንዲበላሽና ሕዝቦቿ በቀጣይ ስጋትና ሽብር ውስጥ እንዲኖሩ እያደረገ ያለው ኢሕአዴግ ራሱ መሆኑን በተደጋጋሚ ገልጸናል፡፡ ይህንን ስንልም ከባዶ ነገር ተነስተን የኢሕአዴግን ስም ለማጥፋት የተወጠነ ነገር ስላይደለ፣ የአገራችንን ገጽታ እያበላሹ ያሉትንና የሕዝቡንም የስጋትና የሰቆቃ ምንጭ የሆኑትን ነገሮች አንስተን ኢሕአዴግን የተወሰኑ ጥያቄዎችን መጠየቅ እንወዳለን፤” ብሏል፡፡

መድረክ አሥር ያህል መጠይቆችን ያቀረበ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል ኢሕአዴግ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ አለማካሄዱን፣ ዜጎችን በግፍ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማሰሩን፣ የዕርዳታ እህልና ማዳበሪያን በፖለቲካ ታማኝነት መስጠቱን፣ የመንግሥት አገልግሎቶችን በእኩልነትና በፍትሐዊነት ስለማቅረቡ ማስረጃ ማቅረብ እንደማይችል፣ ወዘተ ይዘረዝራል፡፡

“የእኛ ዓላማ በኢሕአዴግ አምባገነናዊነትና ማንአለብኝነት የተነሳ በአገራችን የተከሰተው እልቂትና ቆይታ እንዲገታ መታገል ነው፤” የሚለው መድረክ፣ “በዚህ አጋጣሚ የአገራችን መሠረታዊ ችግሮች በፕሮፖጋንዳ ጋጋታና በባዶ መፈክር፣ እንዲሁም በአልባሌ ትወና እንደማይፈታ ታውቆ፣ በአስቸኳይ አገሪቷንና ሕዝቦቿን ወደ ብሔራዊ መግባባት እንድንወስዳት በቁርጠኝነት መሥራት እንደሆነ እናምናለን፤” ብሏል፡፡

የዘላቂው ሰላምና ብልጽግና መሠረት “የኢኬልዳማ” መሰል ቴአትር ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ይሁንታ የሚፈጠር ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት መሆኑን ለአፍታ እንኳ እንዳይረሳ ለማሳሰብ እንደሚፈልግ መድረክ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

በሕገወጥ መንገድ ከአገር የሚወጣው ከፍተኛ ገንዘብ የትልቅ ወንጀል ማሳያ መሆኑ ተገለጸ

Saturday, December 10th, 2011

ሕገወጥ በሆነ መንገድ ከኢትዮጵያ የሚወጣው ከፍተኛ ገንዘብ በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ዋነኛውና ትልቁ ወንጀል መሆኑን፣ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የፋይናንስ ባለሙያ ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ ባለሙያው በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት ባለፈው ሳምንት የአንድ ዓለም አቀፍ ተቋም ጥናት ከኢትዮጵያ በሕገወጥ መንገድ እ.ኤ.አ. በ2009 ብቻ 3.26 ቢሊዮን ዶላር መውጣቱን ከገለጸ በኋላ ነው፡፡

በዚህ ወር በይፋ ይወጣል የተባለውንና ግሎባል ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ በተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት የተጠናከረውን ጥናት ጠቅሶ የወጣው ሪፖርት፣ ከኢትዮጵያ በሕገወጥ መንገድ እ.ኤ.አ. ከ2000 እስከ 2009 ባሉት አሥር ዓመታት ውስጥ፣ 11.7 ቢሊዮን ዶላር በሕገወጥ መንገድ ማጣቷን ያብራራል፡፡

በሪፖርቱ እንደተመለከተው የዓመት የነፍስ ወከፍ ገቢዋ ከ365 ዶላር ያልዘለለው ኢትዮጵያ፣ በሕገወጥ መንገድ ከሚወጣ ከፍተኛ ገንዘብ ዋነኛዋ ተጎጂ ከሆኑ አገሮች መካከል አንዷ እንደሚያደርጋት ያብራራል፡፡

ወደ 166 ታዳጊ አገሮችን የሚያካትተውና በዚህ ወር ይፋ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው ጥናት፣ ለዚህ በሕገወጥ መንገድ ከታዳጊ አገሮች ለሚወጣ ገንዘብ ዋነኛው ምክንያት ከሙስና ጋር እንደሚያያዝ፣ ቀሪው ደግሞ ከአገሮች የገቢና የወጪ ንግድ ውስጥ በሚፈጸም ሕገወጥ አሠራር መሆኑን ይገልጻል፡፡

ይሁንና በተባበሩት መንግሥት የንግድና ልማት ጉባዔ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት አቶ ታፈረ ተስፋቸው፣ ከታዳጊ አገሮች ሕገወጥ በሆነ መንገድ የሚወጣው ገንዘብ ከ70 እስከ 75 በመቶ ከገቢና ወጪ ንግድ ሕገወጥ የሆነ የደረሰኝ አሠራር መሆኑን፣ ለዚህም ቀደም ሲል በአብዛኛው የሚወቀሱት ትላልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችና አንዳንድ የመንግሥት ኃላፊነት የተሰጣቸው ግለሰቦች መሆናቸውን ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡

ሪፖርቱ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2009 ብቻ በሕገወጥ መንገድ ከ3.26 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ማጣቷን ሲገልጽ፣ ይህም አገሪቱ እ.ኤ.አ. በ2009 ከወጪ ንግድ ካገኘችው ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በእጅጉ የሚልቅ ነው፡፡

“ይፋ ይሆናል ተብሎ በሚጠበቀው ሪፖርት እ.ኤ.አ. በ2009 በሕገወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ ወጥቷል የተባለው ገንዘብ እንዴት እንደተሰላ ባላውቅም፣ መጠኑ በጣም ብዙ ነው፤” ያሉት የኢኮኖሚ ባለሙያውና በተባበሩት መንግሥታት የንግድና ልማት ጉባዔ ከፍተኛ ባለሥልጣን ከሆኑት በጣት ከሚቆጠሩ አፍሪካውያን አንዱ የሆኑት አቶ ታፈረ፣ ከኢትዮጵያ ከ70 እስከ 75 በመቶ የሚሆነው በሕገወጥ መንገድ የሚመጣው ገንዘብ ከወጪና ገቢ ንግድ ጋር የተያያዘ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በገቢና በወጪ ንግድ ደረሠኞች በሕገወጥ መንገድ በማዘጋጀት አንዳንድ ላኪዎችና አስመጪዎች የማጭበርበር ተግባር እንደሚፈጽሙ አስረድተዋል፡፡

እንደዚህ ዓይነት ሪፖርት ወይም ጥናት በሚካሄድበት ጊዜ ቁጥሮችን የማስሊያው ዘዴ በግምት ላይ የተመረኮዘ በመሆኑ፣ የሚወጡት ቁጥሮች ሙሉ በሙሉ ትክክል ሊሆኑ የማይችሉበት ሁኔታ መኖሩንም ባለሙያው ጠቅሰዋል፡፡

ከኢትዮጵያ በሕገወጥ መንገድ ይወጣል የተባለው ገንዘብ ዋነኛ መስመሩ ከወጪና ገቢ ንግድ ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ከትክክለኛው ባነሰ ዋጋ የኤክስፖርት ገቢውን በደረሰኝ በመግለጽ፣ ገቢ የተደረገውን የዕቃ ዋጋ ደግሞ ከዋጋው በላይ ከፍ አድርጎ ደረሰኝ በማዘጀት ተገቢ ያልሆነ አሠራር መሆኑንም አቶ ታፈረ አብራርተዋል፡፡

ይኼው ሪፖርት በፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እጅም መግባቱ የገለጹት የኮሚሽኑ የሥራ ኃላፊዎች፣ ሪፖርቱ ለኮሚሽኑ ዓይን ገላጭ ሊሆን እንደሚችልም ገልጸዋል፡፡

ሕገወጥ በሆነ መንገድ ከታዳጊ አገሮች የሚወጣው ከፍተኛ ገንዘብ የአገሮቹን ዕድገት የሚፈታተን እንደሆነ የሚያብራራው ሪፖርቱ፣ ይህንንም ለማስወገድ ዓለም አቀፋዊና ፈጣን የሆነ የታክስ መረጃ ልውውጥ መረብ መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን መክሯል፡፡

ይህንን ሪፖርት አስመልክቶ የብሔራዊ ባንክና ሌሎች ይመላከታቸዋል የተባሉ የመንግሥት መሥርያ ቤቶች ኃላፊዎች ለማነጋገር የተደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

የግብረሰዶማውያኑ ስብሰባ የፈጠረው ትኩሳት

Sunday, December 4th, 2011

(Reporter) — ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ የሚጀመረው 16ኛው ዓለም አቀፍ የኤችአይቪ/ኤድስና የአባላዘር በሽታዎች(አይካሳ) ጉባዔን አስታክኮ፣ መሰንበቻውን የግብረሰዶማውያን ቡድን እያካሄደ ያለውን እንቅስቃሴ ከተለያዩ ወገኖች ተቃውሞ ሲቀርብበት ነበር፡፡

በተለይ የሃይማኖት መሪዎች ለትናንት በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል ለማካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት ስለነበረው ስብሰባ ምንነትና ይዘት የሚያሳይና የሚኮንን መግለጫ ሊሰጡ ካሉ በኋላ መሰረዙን በሪፖርተር ባለፈው ረቡዕ ማውጣታችን ይታወሳል፡፡ ግብረሰዶማውያኑ ስብሰባቸውን በተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ ማዕከል ማካሄዳቸውም እየተነገረ ነው፡፡

ትናንት ማለዳ ላይ በስብሰባ ማዕከሉ የግብረሰዶማውያኑ ስብሰባ እንደሚካሄድ ሰምተው ለተቃውሞ የወጡ ጥቂት ሰዎች በፖሊስ ተበትነዋል፡፡ ፖሊስ ለተቃውሞ የወጡትን የበተነው በሕጋዊ መንገድ የወጡ አይደሉም በማለት ነው፡፡ ድርጊቱን በምስል ለማስቀረት በስፍራው የተገኘው የሪፖርተር ፎቶ ጋዜጠኛም በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሎ ያነሣቸው ምስሎች ቅጂዎችም ተወስደዋል፡፡

በእንዲህ ዓይነቱ አወዛጋቢ ሁኔታ ውስጥ ለአምስት ቀናት የሚካሄደው የአይካሳ ጉባዔ ዛሬ ይጀመራል፡፡ ከጉባዔው ባሻገር፣‹‹የግብረሰዶማውያኑ ስብሰባ የፈጠረው ትኩሳት›› በሚል ርእስ በተለያዩ ወገኖች የተሰጡትን አስተያየቶችና ምልከታዎችን የሚያሳየውን ሐተታ ከዚህ በታች ይመልከቱ፡፡

ሰዶማውያን ማለት ግብረሰዶምን የሚፈጽሙ ይህም ወንድ ከወንድ ሴት ከሴት ጋር ዝሙት የሚያደርጉ ማለት እንደሆነ መዝገበ ቃላቱ ይፈታዋል፡፡ ግብረሰዶማዊነት የሚለውን ስያሜም የተገኘው በአደባባይ ለመጀመርያ ጊዜ ድርጊቱን በፈጸሙ ሰዎች አገር ስም ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን በድረ ገጹ ባወጣው ጽሑፍ እንደተገለጸው፣በዘመናት ታሪክ ውስጥ በእግዚአብሔር ዘንድ መጸጸትን፣ የቁጣ ጅራፍን፣ መዓትንና እጅግ መራራ ቅጣትን ካስከተሉ እኩያን ተግባራት መካከል ተፈጥሮ ከሚያዘው ውጪ ወንዶች ከወንዶችና ሴቶች ከሴቶች ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት አንዱ ነው፡፡

ይህ በቅዱስ መጽሐፍ የተግባሩ እኩይነት የቅጣቱ አስከፊነት በተጨባጭ የተነገረለት ግብረሰዶማዊነት ሳይቋረጥ የዘመናትን ድንበር ተሻግሮ ነውርነቱ እንደ መልካም ተግባር ተቆጥሮ በአራቱ መአዝነ ዓለም እየተፈጸመ ይገኛል፡፡ በተለይም በሥልጣኔ ወደፊት ተራምደዋል የሚባሉት ምዕራባውያን ድርጊቱን ከ1980ዎቹ አጋማሽ ጀምረው በምስጢርና በድብቅ መፈጸማቸውን ትተው ወደ አደባባይ ካወጡት ሰነባብቷል፡፡

የድርጊቱም ፈጻሚዎች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እጅግ እያሻቀበ መጥቷል፡፡ አንዳንድ ምዕራባውያን አገሮች በሕጋቸው ያጸደቁት ግብረሰዶማዊነትን እኩያን የሆኑ አንዳንድ የኪነጥበብ ሰዎች ሙያውን ለወሲብ ንግድ ማስፋፊያ በማዋል በፊልም፣ በሲኒማ እየተወኑ በእርስ በእርስ ጦርነት፣ በረሐብ፣ በኤች አይ ቪ/ኤድስ ቁምስቅላቸውን ለሚያዩ አፍሪካውያን ጭምር እንካችሁ እያሉ ነው፡፡

ግብረሰዶማዊነት ወደ ኢትዮጵያ የገባው ለተለያየ ጉዳይ ወደ አገሪቱ በሚመጡ የወጭ አገር ዜጐችና በውጩ ዓለም ኑረው በተመለሱና በሚመለሱ አንዳንድ ኢትዮጵያውን ጭምር መሆኑን ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች የዚህ አጸያፊ ድርጊት ሰለባ የሆኑትና ሰለባ የሚያደርጉት ቀደም ሲል በእነርሱ ላይ ካለፈቃዳቸው በግብረሰዶማውያን ተገደው በመደፈራቸው በመሆኑ ይነገራል፡፡ በተለያዩ ጥቅማጥቅም በመታለል በተፈጸመባቸው ወሲባዊ ጥቃት የእነርሱን የሕይወት መስመር ለመከተል እንዳበቃቸው ከግብረሰዶማውያኑ የተገኙ መረጃዎች እንደሚጠቁሙ በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡ ግብረሰዶማውያኑ ዛሬ በአዲስ አበባና በተለያዩ ከተሞች ኅቡዕ ድርጅት በማቋቋም፣ በካፌዎች እና በተለያዩ የመዝናኛ ቦታዎች ድርጊቱን እያስፋፉ ይገኛሉ፡፡

‹‹ውግዘት የሚገባው ተግባር›› በሚል ርእስ ማኅበረ ቅዱሳን ባወጣው ጥናት፣ በተለያዩ ወገኖች ታዝሎ ኢትዮጵያ የገባው ግብረሰዶማዊነት በተለይም ዕድሜያቸው ከ10-14 በሚደርሱ የጐዳና ተዳዳሪዎች፣ በአንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እገዛ በሕፃናት ማሳደጊያ ማዕከል በሚኖሩ አዳጊዎች ላይ ሳይቀር ድርጊቱ እየተፈጸመባቸው ነው፡፡ የድርጊቱ ፈጻሚዎች ሕፃናትንና ወጣቶችን ለማማለል የተለያዩ አደንዛዥ ዕፆችን፣ ከረሜላ፣ ቸኮላት መሳይ ማደንዘዣ፣ ጫት፣ አልኮል እና የሚጤስ ነገር በመጠቀም ካደነዘዙአቸው በኋላ ድርጊቱን ይፈጽሙባቸዋል፡፡ እንዲሁም ጐልማሶችን በተለያዩ መሣሪያዎች በማስፈራራት እንደሚደፍሯቸው ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

ዓለም በቴክኖሎጂ ምጥቀት ወደ አንድ መንደር እየተለወጠች በመምጣቷ በዓለም ላይ የሚከሰት ሠናይም ሆነ እኩይ ለሆነ ነገር ሁሉ አገራት ተጋላጭ ናቸው፡፡ ከአንድ አገር ወደሌላ በሚደረግ ዝውውር፣ የቴክኖሎጂ የኢንፎርሜሽን እና ከዚሁ ጋር አብሮ በተለያዩ መንገዶች በሚደረጉ የእኩይ ልማድ ልውውጥ ምክንያት የምዕራባውያንን ፈለግ ለመከተል ደፋ ቀና የሚሉ አንዳንድ ወገኖች በአገራችን ብቅ ማለታቸው እየተሰማ ነው፡፡ በመንፈሳዊ ሥነ ምግባር በፈሪሐ እግዚአብሔር እየተጓዘች በኖረችው አገራችን እንደዚህ ዓይነት ድርጊት ለመፈጸም የሚንቀሳቀሱ ሰዎች መነሳታቸው እጅግ ያሳዝናል፤ ያሳስባልም፡፡ በቅድስት አገር ኢትዮጵያ የድርጊቱ ፈጻሚዎች እንቅስቃሴ ከተሰማበት ወዲህ ድርጊቱ ያሳሰባት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታኅሣሥ 13 ቀን 2001 ዓ.ም. በአንድ ግብረ ሠናይ ድርጅት አስተባባሪነት «ግብረሰዶማዊነት መብት ወይስ የዝሙት ከፍታ ጫፍ» በሚል ርእስ ከሃይማኖት ከባህል፣ ከታሪክና ከሳይንስ አኳያ በአፍሪካ ኅብረት በመከረበት ወቅት ድርጊቱን በማውገዝ አቋሟን ገልጻለች፡፡ ከተላለፈው የአቋም መግለጫ የሚከተለው ይጠቀሳል፡፡ «በሀገራችን ሕገ መንግሥት ውስጥ እንደተመለከተው ጋብቻ ክቡር መሆኑን ለቤተሰብም ጥበቃ የሚደረግለት መሆኑንና በሀገራችን ካሉ የሃይማኖት እሴቶች ተቃራኒ የሆኑ ጉዳዮች በማንኛውም መስፈርት ግብረሰዶማዊነት መብት ተደርጎ ተቀባይነት ማግኘት የማይገባው በመሆኑ ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ይህንን አውቆ እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን፡፡»

‹‹ግብረሰዶማዊነት›› በሚል ርእስ በዩናይትድ ፎር ላይፍ የተዘጋጀ መጽሐፍ በዓለም አቀፍ የበሽታዎች መግለጫ ዝርዝር ላይ ግብረሰዶማዊነት እንደበሽታ ተቆጥሮ ለብዙ ዓመታት መስፈሩን ያትታል፡፡ ይኸው መጽሐፍ እንደሚለው፣ በአሜሪካ የአእምሮ ሕክምና ማኅበር ግብረሰዶማዊነትን ከአእምሮ መዛባት ጋር በተያያዘ የሚፈጠር በሽታ አድርጐ ይቆጥረው ስለነበር በአእምሮ በሽታዎች ዝርዝር ውስጥ ተመዝግቦ ቆይቷል፡፡

ነገር ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከሁለቱም ሥፍራዎች ከበሽታዎች ዝርዝር ውስጥ እንዲሰረዝ ተደርጓል፡፡ በርካታ ባለሙያዎች ከበሽታዎች ዝርዝር አንዳይሰረዝ ያቀረቡት ተቃውሞ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ግብረሰዶማዊነት ከበሽታዎች ዝርዝር ሲሰረዝ የቀረበው ምክንያት አንድ ሰው ግብረሰዶማዊ መሆን ወይም አለመሆን ‹‹መብት›› ነው በሚል አመለካከት ነበር፡፡

መጽሐፉ በ1996 ኢትዮጵያ ውስጥ የተካሔደውን አንድ ጥናታዊ መረጃ ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ከሆነ፣ ሰዎችን ወደዚህ ሕይወት እንዲገቡ ያደረጓቸው የውጭ አገር ዜጎች፣ በውጭ አገር የሚኖሩና ወደ ውጭ አገር ለንግድ ብዙ ጊዜ የሚመላለሱ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ በአጠቃላይ እንደ ችግር ሲታይ መነሻ ሆኖ የቀረበው የውጭ ተጽዕኖ ሲሆን በአገራችን ሕጻናት ላይ ጥቃት ፈጽመው የተያዙ፣ አሁንም በዕርዳታ ስም ወደ አገራችን በመግባት ይህን ጥቃት እያደረሱ ያሉ የውጭ ዜጎች ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በጥናቱም መሠረት እርስ በርሳቸው የሚጠራሩበት የተለያዩ ስሞች ሲኖራቸው አብዛኛው የሚጠቀሙበት ስም ‹‹ዜጋ›› የሚል ነው፡፡ አንዳንዴ ይህ ስያሜ ‹‹ኦፔራ››፣ ‹‹ወገን›› በሚባሉ ስያሜዎች እንደሚተኩም መጽሐፉ ከጥናት የተገኘውን መረጃ ጠቅሶ አስፍሯል፡፡ ‹‹ጅራሬ›› ለወሲብ ንግድ ወይም የአዳር ጓደኛ ፍለጋ አደባባይ መውጣት የሚያመለክት ቃል ሲሆን፤ ‹‹ብርታሎ›› (ቆምጬ) ከገጠር ለሚመጡ ግብረሰዶማውያን የወጡ መጠሪያዎች ናቸው፡፡ ‹‹ጀሲካ ሞናሊዛ›› የመሳሰሉትም ለከተሜ ግብረ ሰዶማውያን የተሰጡ መጠሪያና ‹‹ቆሚ›› ገንዘብ ለማግኛ እንደ ሥራ በመንገድ ላይ የሚቆሙ መሆናቸውን አመላክቷል፡፡ ‹‹መክተብ›› ማለት ደግሞ ይህን የሕይወት መንገድ የማያውቁትን ወደ ግብረ ሰዶማዊነት የሕይወት ልምምድ መመልመል ማለት ነው፡፡ እርስ በርሳቸው የሚጠራሩበት የቁልምጫ ስም ‹‹እሷ›› የሚል ነው፡፡

በዚህ ጥናታዊ ጽሑፍ መሠረት በአዲስ አበባ መሃል ከተማ በታወቁ መንገዶች፣ በቡና ቤቶች፣ ካፍቴሪያዎችና ኮሪደር ቦታዎች ላይ አንዱ ሌላውን እንደሚያገኙ ተጠቁሟል፡፡ በተለይ የሦስት ቡና ቤቶችና የሁለት ካፍቴሪያዎች ባለቤቶች እነሱ በመሆናቸውና የተቀጠሩት አስተናጋጆችም ግብረሰዶማውያን በመሆናቸው ዘና ብለው ለመገናኘት አስችሏቸዋል፡፡ ወደ እነዚህ ሥፍራዎች ሲመጡ ሁለት ወይም ሦስት ሆነው ተቃቅፈው ወይም እጅ ለእጅ ተያይዘው ይገባሉ፡፡ ተመሳሳይ የጾታ ጋብቻ ሕጋዊ እንዲሆን የሚታገሉ አንዳንድ ድርጅቶች እንዳሉም አንዳንድ ምንጮች ይገልጻሉ፡፡ የእነዚህ ድርጅቶች ታሪካዊ ዳራ /ጀርባ/ ሲጠና ግብረሰዶማዊነት በሕግ እንዲፈቀድ የሚንቀሳቀሱት የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግር /ፍላጎት/ ስለሆነ ሕዝቡን ለመርዳት ብለው ሳይሆን ኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲና በመሆንዋ ለራሳቸው ስውር ዓላማ ማስፈጸሚያ ስለምትመቻቸው ነው፡፡ ይኸውም ኢትዮጵያ ይሁን ብላ የምትፈቅደው ማናቸውም ነገሮች በሌሎች አፍሪካ አገሮች ላይ ተጽዕኖ እንደሚያመጣ በማሰብ አገራችንን እንደ መግቢያ በር አድርገው በሌሎች የአፍሪካ አገሮችም እንቅስቃሴያቸውን ለማስፋፋት ነው፡፡

• ‹‹በጤናማ የኑሮ ዘይቤ ወደ ኅብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ የበኩላችን ጥረት ማድረግ አለብን››
ዶ/ር ሥዩም አንቶንዮስ የዩናይትድ ፎር ላይፍ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር
ዓለም አቀፍ የግብረሰዶማውያን ስብሰባ እንደሚካሔድ መነገሩን ተከትሎ ተገቢ አለመሆኑን ለማመልከት ባለፈው ሐሙስ ኅዳር 21 ቀን 2004 ዓ.ም. ሳር ቤት በሚገኘው የኢንተርናሽናል ኢቫንጄሊካል ቸርች የንስሐና የምልጃ ፕሮግራም ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች ተካሒዶ ነበር፡፡

ሐኪሙ ዶ/ር ሥዩም አንቶንዮስ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ፕሮግራሙ የተዘጋጀው በግብረሰዶም ጉዳይ ቤተ ክርስቲያን ሰፊ ግንዛቤ እንድታገኝ ለማድረግ ነው፡፡ ያለው ችግር ምን ይመስላል? ግብረሰዶማዊነት ምንድን ነው? የሚያስከትላቸውስ ዘርፈ ብዙ ጠንቆች ምን ይመስላሉ? ከሳይንሱም ሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ እይታ ለማየት ተሞክሯል፡፡ በምድሪቱ ላይ ላለው ቀውስ ጸሎትና ምልጃ ነው የተካሔደው፡፡ ሰሞኑን በአዲስ አበባ በተከሠተው ሁኔታ ግብረሰዶማውያኑ እናደርጋለን ብለው ያሰቡት ስብሰባ በምድሪቱ ላይ መጥፎ ተጽዕኖ እንደሚያመጣ ስለሚታመን ያ እንዳይሆን በእግዚአብሔር ፊት የምልጃ ጸሎት ተደርጓል፡፡

የቁጥራቸው መብዛት ማነስ መሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ አፍሪካን በግብረሰዶማዊነት እንዴት መድረስ እንችላለን? ብለው የሚነጋገሩ አካላት ስብሰባ ማድረጋቸው ከፍተኛ ተጽዕኖ ይኖረዋል፡፡

ግብረሰዶማዊነት ለትውልድ ጥፋት የሆነ፣ ጥፋትን የሚያመጣ፣ ከፍተኛ ማኅበራዊ ቀውስን የሚፈጥርና ትውልድን የሚያመክን ነገር ነው፡፡ ይኼ ነገር ኅብረተሰባችን መካከል እየተስፋፋ በመጣ ቁጥር የአገርን ልማትና ዕድገት ይጎዳል፡፡

ኅብረተሰቡ ይኸን ነገር አይፈልገውም፤ በሕጋችንም ተቀምጧል፡፡ ሕገ መንግሥቱም አይደግፍም፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ እምነቶች አጥብቀው ይቃወማሉ፡፡ ስለዚህ የውጭ ድርጅቶች በዕርዳታ ስም ይኸን ተጽዕኖ ቢያደርጉም ዕርዳታው ቢቀር ይሻላል እንጂ ይኸንን ዓይነት አስተሳሰብ መቀበላችን ለኛ ሰፊ አደጋና የከፋ ቀውስ ሊያመጣ የሚችል ነው፡፡ ተጽዕኗቸው አለ፤ በግልጽ የሚናገሩት ነው፡፡

ቆም ብለን በደንብ አስበን አመዛዝነን የትኛው የተሻለ ነው? የትኛው ያዋጣናል ብሎ ማሰቡ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ መንግሥታችንም እንደዚህ ዓይነት አቋም እንዳለው እናምናለን፡፡ ከሃይማኖት መሪዎች የሚጠበቅ ሥራ አለ፡፡ እንደሚያስከትል ማስተማር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይኸ በደንብ አልተሠራም ክፍተት አለ፡፡

ግብረሰዶማውያን ሰዎች ናቸው፡፡ በሰውነታቸው ሊጠሉ አይገባቸውም፡፡ ልንጠላው ወይም ልንጸየፈው የሚገባን ግብረሰዶማዊነትን ወይም ድርጊቱንና የኑሮ ዘይቤውን ነው፡፡ ሰውየውን ከድርጊቱ መለየት መቻል አለብን፡፡ በዚህ ሕይወት ውስጥ ያሉት ሰዎች በሥነ ልቦና ቀውስ ውስጥ ያሉ ለመሆናቸው ብዙ ሳይንሳዊ ምርምሮች ያረጋግጣሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገቢውን የምክር አገልግሎትና ድጋፍ በመስጠት ጤናማ የኑሮ ዘይቤ ወደ ኅብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ባለሙያዎችም የሃይማኖት አባቶችም የበኩላችንን ጥረት ማድረግ አለብን፡፡

ይህን የምናደርግበት ዋናው ዓላማ ግብረሰዶማዊነት ኅብረተሰብን የሚያጠፋ ነገር ስለሆነ፣ የሰውን ሰብዕና የሚያበላሽ ማንነቱን የሚያጎድፍ ለብዙ የጤና ቀውሶች የሚያጋልጥ፣ ለአካላዊና ሥነ ልቦናዊ ለማኅበራዊ ቀውስም የሚዳርግ ስለሆነ ጤናማ ሥራ ፈጣሪ ዜጋ እንዳይኖረን የሚያደርግና የአገር ልማትና ዕድገት የሚያጠፋም ስለሆነ ነው፡፡ ይህንን አደጋ ለመቀነስ ሁላችን ባለን አቅም ሁሉ መረባረብ አለብን፡፡ በዚያ ሕይወት ውስጥ ያሉት ደግሞ የሚወጡበትን መንገድ የተሐድሶ ማዕከላትን በማቋቋም መርዳት አለብን፡፡ እውነቱን ለማስተማር ሰፊ ሥራ ይጠበቅብናልና የሚመለከተን ሁላችን ባለሙያውም፣ ጋዜጠኛውም፣ አስተማሪውም፣ የሃይማኖት አባቱም፣ መንግሥትም ሁላችን ተባብረን ለዚህ ነገር መፍትሔ መፈለግ ይጠበቅብናል፡፡

• ‹‹የሃይማኖት መሪዎች ሊጮሁ ይገባል››
ሼክ አደም ካሚል የእስላማዊ ጥናት ተመራማሪ
እስልምና ግብረሰዶምን በጣም ይኮንነዋል፡፡ ማንኛውም ሃይማኖት አይደግፈውም፤ የተጠላ ነው፡፡

ምዕራባውያን እንደፋሽን አድርገው የሚጠቀሙበት በእነርሱ አገር እንደ ሕገ መንግሥትም አድርገው ከመብት ጋር የተያያዘ ነው የሚሉት ከሃይማኖቱ ውጭ የሆኑ ፓርቲዎችና መሪዎች የሚሰነዝሩትና የሚቀይሱት ስልት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ኢትዮጵያ በታሪክ የታወቀች ሦስቱን ታላላቅ ሃይማኖቶች የተቀበለችና ያስተናገደች አገር ነች፡፡ ከዚህ አንጻር መሠረተ እምነቱን ይዞ የሚሔድ ሕዝብ ያለባት የረዥም ጊዜ ታሪክ ያላት አገር እንደነዚህ ያሉ አስቀያሚና ቆሻሻ ነገሮች በአገራችን ባለፈው ትውልድ ታይቶም ታስቦ ታልሞ አይታወቅም ነበር፡፡ አሁን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በረቀቀ ቁጥርና ሦስተኛው ዓለም ትውልድ አልባ፣ ዘር አልባ እንዲሆን በተለይ የተለያዩ ነገሮች ይቀይሱብናል፡፡ ለአገራችን ተስማሚ ያልሆኑ ባህሎች፣ ወጎችና ልምዶች እንዲንፀባረቁ ዕቅድ ተነድፎ ልምዳችንን፣ ክብራችንን ጠብቀን እንዳንሔድ የሚደረግ ሴራና ዳባ የተዘረጋ ይመስለኛል፡፡ መነሻ የሚያደርጉት ድህነታችንን፣ ችግራችንን ነው፡፡ እና በዕርዳታና በበጎ አድራጎት ስም የሚገቡት ድርጅቶች ሁሉ ነፃ ናቸው ማለት አንችልም፡፡ ይኼ ዴሞክራሲ ማለት አይደለም፤ የሰው መብት ነው ማለትም አይደለም፡፡ ሰውን የሚያጠፋ፣ ሰውን የሚያዳክም ነው፡፡ ችግራችን ኋላቀርነትና ድህነት ነው፡፡ ከዚያ ለመውጣት በሚጥርበትና ሕዝቡ ወደ ሥራ ገብቶ በተለያዩ እምነቶቹ ተቻችሎ የሚኖርበት አገር ስለሆነ ይኸንን ክብራችንን ጠብቀን መሔዳችን የሚያስኮርፋቸው አካሎች በውጩ በተለይ በምዕራቡ ዓለም ያሉ ይመስለኛል፡፡ በእስልምና በቅዱስ ቁርዓን በግልጽ የተቀመጠ አንቀጽ አለ፡፡

ሉጥ የተባሉ ነቢይ ነበሩ፡፡ በዚያን ጊዜ ዜጎቻቸው እንዲህ ያለ ተግባሮች በሚፈጽሙበት ጊዜ አላህ በጅብሪል አማካይነት ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ባለመቀበላቸው መሬቱን ገልብጦ እንዲቀጡና እንዲጠፉ አድርጓቸዋል፡፡ ስለዚህ እንደዚህ ያሉ ነገሮች የመጥፊያችን ዋዜማ ነው ማለት እችላለሁ፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ሊያውቀው የሚገባው የራሷ የሆነ ባህል አላት፡፡ በክርስትናም፣ በእስልምናም ተከብሮ የቆየ ለሌላው አርአያ የሆንበት ሌላው ቀርቶ በክርስትና በዓላት ከአውሮፓ እየመጡ እምነታቸውን፣ ባህላቸውንና ልምዳቸውን እየቀሰሙ እየተማሩ የረሱትን የእምነት ባህላቸውን እንኳ እያዩ ነው ያሉት፡፡

እኛን የሚያሳስበው ሌላው ነገር በከተማችን ሴተኛ አዳሪ መብዛት ነው ትዳር አልባ ከሆንን ወቅቱ አሁን የምንጮህበት ጊዜ ይመስለኛል፡፡ መቅሰፍቱ ለተወሰነ እምነት ተከታይ ብቻ የመጣ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያውያን ላይ ያንዣበበ የተከሠተ አደጋ ነውና የሃይማኖት መሪዎች ሊጮሁ ይገባል፡፡

ቤተ ክርስቲያንም፣ መስጊዶችም መጮህ አለባቸው፡፡ ለዚህ ጉዳይ ተብሎ አጀንዳ ተቀርጾ ኮንፈረንስ መካሔድ አለበት፤ በተለይ ወጣቱ የሚሳተፍበት መድረክ ተከፍቶ የሃይማኖት መሪዎች ተሳትፈውበት ከእምነት አንጻር አደጋው ምን እንደሆነ መግለጫ የሚሰጡበት መድረክ መከፈት ይኖርበታል፡፡ መንግሥትም ኋላቀርነትን እዋጋለሁ እያለ ዕቅድ በሚያወጣበትና አገራችን መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው አገሮች ትሔዳለች ሲባል እንደዚህ ያሉ መቅሰፍቶች መከሠታቸው ለምናፈራው ትውልድ አደጋና አገሪቱን የሚጎትት ስለሆነ ዕርምጃ ሊወሰድበት ይገባል፡፡ ሆቴሎችን፣ ቡና ቤቶችን፣ ምሽት ቤቶችን መቆጣጠር እንጂ ከመብት አንጻር ብቻ መታየት የለበትም፡፡

በውጭ አገር ካሉት ኢትዮጵያውያንም ለአገራችን ባዕድ የሆነ ነገርም የሚያመጡ አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብም ነገሩ ሊያሳስባቸው ሊነጋገሩበትም ይገባል፡፡ ኤምባሲዎችም እየሰበሰቡ ማነጋገር ቱሪስቶች ወደ አገር ቤት በሚመጡበት ሰዓትም የአገራችን ባህልና ክልክል የሆነውን ነገርንም ማሳወቅ ይገባቸዋል፡፡

• ‹‹ጢሱ እንዳይታይ ከመጣር ይልቅ እሳቱ እንዲጠፋ ብንሠራ የተሻለ ውጤት እናመጣለን››
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት
ኢትዮጵያ የሃይማኖት ሀገር ናት፡፡ ከ90 በመቶ በላይ የሆነው ሕዝቧ በእምነቱ ግብረ ሰዶምን ይቃወማል ብቻ ሳይሆን ይጸየፋል፡፡ የሀገሪቱ ሕጎችም ግብረ ሰዶማዊነትን በወንጀልነት ይፈርጃሉ፡፡ ከሕዝቡ እምነት ብቻ ሳይሆን ከባህሉ ጋርም የሚጣረስ ጉዳይ ነው፡፡

እንዲህ ያለውን ነገር በማኅበረሰቡ ውስጥ እንዲስፋፋ የሚሠሩ፣ ሕዝቡም ያልበላውን የሚያክኩ ተቋማት እና ግለሰቦች አጋጣሚዎቹን እንዳይጠቀሙ የሚመለከተን ሁሉ በርግጠኛነት መከላከል ይጠበቅብናል፡፡

ግብረሰዶማዊነትን ካልተቀበላችሁ፣ የግብረሰዶማውያንን መብት ካልደገፋችሁ አንረዳም እያሉ የሚያስፈራሩ ምዕራባውያን ኃያላን አሉ፡፡ ራሳችንን አጥተን የሚመጣ ርዳታ ለቀብር ማስፈጸሚያነት ብቻ የሚውል ነው፡፡ እናም እንዲቀርብን እንንገራቸው፡፡

የጉባኤው አዘጋጆችም ቢሆኑ ወደ ጉባኤው ለሚመጡ እንግዶች የኢትዮጵያን ሕግ እና የሞራል እሴቶች አስቀድመው የመግለጽ እና የማስጠንቀቅ ግዴታ አለባቸው፡፡

የሀገራችን ሰው እሳቱ ከሌለ ጢሱ አይታይም ይላል፡፡ አሁንም ቢሆን ምናልባት በጎላ መልኩ አልወጣ ይሆናል እንጂ ያለ ምክንያት የግብረ ሰዶማዊነት ጉዳይ በዚህ ወቅት አልተነሣም፡፡ ጢሱ እንዳይታይ ከመጣር ይልቅ እሳቱ እንዲጠፋ ብንሠራ የተሻለ ውጤት እናመጣለን፡፡

የኢትዮጵያ ሕግ ምን ይላል?
በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ (1996) ክፍል ሁለት ‹‹ለተፈጥሮ ባሕርይ ተቃራኒ የሆነ የግብረ ሥጋ ግንኙነቶች›› በሚል ርእስ በአንቀጽ 629፣ ግብረሰዶም እና ለንጽሕና ክብር ተቃራኒ የሆኑ ሌሎች ድርጊቶች በሚል ርእስ፣ ‹‹ማንም ሰው ከእርሱ ጋር አንድ ዓይነት ጾታ ካለው ከሌላ ሰው ጋር ግብረሰዶም ወይም ለንጽሕና ክብር ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆነውን ሌላ ድርጊት የፈጸመ ማንኛውም ሰው ከቀላል እስራት እስከ ከባድ ወንጀል ቅጣት እንደሚጠብቀው ይደነግጋል፡፡

በአንቀጽ 631 ደግሞ ‹‹ለአካለ መጠን ባልደረሱ ልጆች ላይ የሚፈጸሙ የግብረሰዶም ጥቃትና ለክብረ ንጽሕና ተቃራኒ የሆነ ሌላ ድርጊት›› በሚል ርእስ፣ ንኡስ አንቀጽ 1. ማንም ሰው ከእርሱ ጋር አንድ ዓይነት ጾታ ባለውና ለአካለ መጠን ባልደረሰ ልጅ ላይ የግብረሰዶም ጥቃት የፈጸመ እንደሆነ፤ የተበዳዩ ዕድሜ አሥራ ሦስት ዓመት ሆኖ አሥራ ስምንት ዓመት ያልሞላው ሲሆን፣ ከሦስት ዓመት እስከ አሥራ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እሥራት ይቀጣል፡፡ የተበዳዩ ዕድሜ ከአሥራ ሦስት ዓመት በታች ሲሆን፣ ከአሥራ አምስት ዓመት እስከ ሃያ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡ በተጨማሪም አንዲት ሴት ለአካለ መጠን ባልደረሰች ልጅ ላይ የግብረሰዶም ጥቃት የፈጸመች እንደሆነ፣ ከአሥር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ትቀጣለች በማለት ደንግጓል፡፡ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግም አንቀጽ 13 መሠረት ይህ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ በሕግ የተከለከለ መሆኑም ተደንግጓል፡፡

አበራሽ ኃይላይ ስለተፈጸመባት ጥቃት ፍርድ ቤት ቀርባ መሰከረች

Wednesday, November 16th, 2011

Aberash Hailay (Reporter) — ሁለት ዓይኖቿ በስለት ተወግተው በመጥፋታቸውና በተለያዩ የሰውነት ክፍሎቿ ላይ ከባድ ጉዳት ደርሶባት፣ ታይላንድ ባንኮክ ሆስፒታል በሕክምና ላይ የምትገኘው ሆስተስ አበራሽ ኃይላይ፣ ከትናንት በስቲያ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ፣ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ቀርባ የምስክርነት ቃሏን አሰማች፡፡

አበራሽ ፍርድ ቤት ተገኝታ የምስክርነት ቃሏን የሰጠችው፣ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በተጠርጣሪው የቀድሞ ባለቤቷ ላይ ጥቅምት 24 ቀን 2004 ዓ.ም. አሻሽሎ በመሠረተው ከባድ የሰው መግደል ሙከራና የተከለከለ የጦር መሣሪያ በመያዝ ወንጀሎች አምስተኛ ምስክር አድርጎ ስለቆጠራት ነው፡፡

ዓቃቤ ሕግ ምስክሯ ለፍርድ ቤቱ ስለምታስረዳለት የምስክርነት ቃል አስቀድሞ ለፍርድ ቤቱ ባስያዘው ጭብጥ እንደገለጸው፣ በተጠርጣሪው የቀድሞ ባለቤቷ ፍስሐ ታደሰ ላይ ሁለት የወንጀል ክሶችን ያቀረበው፣ በምስክሯ (አበራሽ) ላይ መስከረም 2 ቀን 2004 ዓ.ም ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት አካባቢ በምትኖርበት ኮንዶሚኒየም ቤት ውስጥ በመገኘት በክሱ ላይ የተመለከተውን ድርጊት ፈጽሟል፡፡ ድርጊቱን ስለመፈጸሙ እውን መሆኑንም አምስተኛ ምስክሩና የጥቃቱ ሰለባ የሆነችው ሆስተስ አበራሽ ኃይላይ በቃሏ እንደምታረጋግጥለት ካስመዘገበ በኋላ፣ ምስክሯ ወደ ችሎቱ እንድትገባ ፍርድ ቤቱ አዘዘ፡፡

በዕለቱ የነበረው የችሎት ታዳሚ እጅግ በርካታ ስለነበረና ምስክሯ በፊት ለፊት የችሎት በር መግባት ባለመቻሏ፣ በዳኞች መግቢያ በር በኩል እንድትገባ ተደረገ፡፡ በዳኞች መግቢያ በር ሦስት ፖሊሶች የተቀመጠችበትን ዊልቸር እየገፉ ሲያስገቧት በችሎቱ የታደመው ሕዝብ ከንፈሩን እየመጠጠ መጠነኛ ድምፅ ሲያሰማ፣ የቀድሞ ባለቤቷና ክስ የተመሠረተበት አቶ ፍስሐ ታደሰ ግን፤ ከፍተኛ ድምፅ በማሰማት፣ ‘ወይኔ፣ ወይኔ፣ ወይኔ…’ ብሎ በመጮህ ማልቀስ ጀመረ፡፡

ከወትሮው ለየት ባለ ሁኔታ በዕለቱ በርካታ ፖሊሶች ችሎቱን ታድመው ስለነበር፣ የተወሰኑት ታዳሚውን፣ የተወሰኑት ደግሞ ተጠርጣሪውን ዝም ካሰኙ በኋላ፣ ሆስተስ አበራሽ ቃለ መሀላ ፈጽማ የምስክርነት ቃሏን መስጠት ጀመረች፡፡

ዓቃቤ ሕግ ለምስክሯ መሪ ጥያቄ ለማቅረብ በመዘጋጀት ላይ እንዳለ፣ ተጠርጣሪው ‹‹ሆድዬ ስለ እግዚአብሔር ብለሽ እውነቱን ተናገሪ›› በማለት ጮኾ ሲናገር፣ ፍርድ ቤቱ እሱን በማስጠንቀቅ እንዲቀመጥ ካደረገው በኋላ በእስረኞች ማቆያ ሳጥን ውስጥ ተቀምጦ ማዳመጥ ጀመረ፡፡ አበራሽ ስለተፈጸመባት ጥቃት፣ መቼ፣ እንዴትና በማንና በምን ሁኔታ እንደተፈጸመ ለፍርድ ቤቱ እንድታስረዳለት ጠየቃት፡፡

ወ/ሮ አበራሽ በተጠየቀችው መሠረት ስለተፈጸመባት ጥቃት ለፍርድ ቤቱ እንደገለጸችው፣ መስከረም 2 ቀን 2004 ዓ.ም. ከነበረችበት ቦታ እህቷ እየሸኘቻት ሳለ፣ ተጠርጣሪው ስልክ ደወለላት፡፡ ‹‹የት ነው ያለሽው?›› ብሎም ጠየቃት፡፡ ‹‹ወደ ቤቴ እየሄድኩ ነው፤ ስደርስ እደውልልሀለሁ፤›› አለችው፡፡ እቤቷ ስትደርስ ደወለችለት፡፡ ‹‹እየመጣሁ ነው›› አላት፡፡

ከምሽቱ ከአራት እስከ አራት ተኩል በሚሆን ጊዜ ውስጥ አቶ ፍስሐ እሷ በምትኖርበት ገርጂ ቁጥር 5 ኮንዶሚኒየም ቤት ውስጥ መድረሱን የገለጸችው ወ/ሮ አበራሽ፣ አቶ ፍስሐ ገና ገብቶ ቁጭ ሲል ሲጋራ በመለኮሱ ‹‹ሳይነስ እንዳለብኝ ታውቃለህ፤ አጥፋልኝ፤›› ስትለው፣ ‹‹ዛሬ ለመጨረሻ ጊዜ ነው ሁለተኛ አላጨስም፤›› በማለት ሲጋራውን አጥፍቶ መቀመጡን ለፍርድ ቤቱ አስረድታለች፡፡

‹‹ተለያየን፣ ልጅም አልወለድንም፤›› ካላት በኋላ፣ በተቀመጡበት ፊት ለፊት በግድግዳ ላይ የተሰቀሉትን የእህቷንና የወንድሟን ፎቶግራፎችንና በቴሌቪዥን ላይ የተቀመጠውን የእናቷን ፎቶ እየተመለከተ፤ ‹‹የናትሽስ ይሁን፣ እኔ ከእህትና ከወንድምሽ በምን አንሼ ነው ፎቶዬ ያልተሰቀለው?›› በማለት ነገር ነገር ሲለው ‹‹ነገ በራሪ ስለሆንኩ ማረፍ አለብኝ፤ ሂድልኝ›› አለችው፡፡ ‹‹እሺ እሄዳለሁ›› በማለት ወደ መውጫው በር ከተራመደ በኋላ፣ ‹‹የመጨረሻ ስጦታ ይዤልሽ መጥቻለሁ›› በማለት ከኪሱ ሽጉጥ በማውጣት መጀመሪያ ወደ ግድግዳው፣ ቀጥሎ ወደ እርሷ በመደገን እንድትቀመጥ ትዕዛዝ ማስተላለፉን መስክራለች፡፡

‹‹ውይ ፊሽ እየቀለድክ ነው?›› ስትለው ‹‹ቁጭ በይ ብዬሻለሁ›› በማለት በያዘው ሽጉጥ ሰደፍ ግንባሯን ሲመታት ቁጭ ማለቷን የገለጸችው ወ/ሮ አበራሽ፣ ቀጥሎ በእግሩና በእጁ ደጋግሞ ሲመታት፣ ራሷን ለመከላከል የሞት ሞቷን ስትይዘው፣ ሁለቱም ተያይዘው መውደቃቸውንና እሷ ከላይ እሱ ከታች መደራረባቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድታለች፡፡

ሽጉጡን ለመንጠቅ በተኙበት ትግል ብትጀምርም፣ አንገቷን አንቆ ስለያዛት ራሷን መቆጣጠር አቅቷት ራሷን ስትስት እንደለቀቃት የተናገረችው ምስክሯ፤ የቆየችበትን ሰዓት ባታውቀውም ስትነቃ ከፊት ለፊቷ ቆሞ ስለነበረ ከኪሱ ስለት ነገር አውጥቶ ግራ ዓይኗን እንደወጋትና ቀኝ ዓይኗን ሊደግማት ሲል በእጇ መከላከሏን ገልጻለች፡፡

ፀጉሯን ይዞ ከመሬት ጋር እንዳጋጫት፣ ቀኝ ዓይኗንም ደጋግሞ እንደወጋትና በእጁ ጣት የግራ ዓይኗን ወደ ውጭ ጎልጉሎ እንዳወጣው የመሰከረችው ወ/ሮ አበራሽ፣ ራሷን ከሳተች በኋላ ወገቧንና የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቿን በመምታት ሽጉጡን በእጇ አስጨብጧት መሄዱን ተናግራለች፡፡

በትዳር ቆይተው ከተፋቱ በኋላ ስለነበራቸው ግንኙነት ተጠይቃ እንዳስረዳችው፣ ከተፋቱ በኋላ በሠለጠነ መንገድ እህትና ወንድም ሆነው የመኖር ሐሳብ ስለነበራት እንዳልተራራቁ ገልጻ፣ እሱ ግን ስልክ ደውሎ ሲያጣት ወይም ሲነጋገሩ አለመግባባት ሲኖር ያስፈራራት እንደነበርም አስታውቃለች፡፡

በጳጉሜን 6 ቀን 2003 ዓ.ም. ከውጭ የመጡ ጓደኞቿ ጋብዘዋት ሲዝናኑ ደውሎላት ‹‹እንገናኝ›› ሲላት፣ ከጓደኞቿ ጋር መሆኗን ገልጻለት ‹‹አንገናኝም›› ስትለው ዝቶባትና አስፈራርቷት እንደነበር የተናገረችው ምስክሯ፣ የፈራቸው እንደደረሰባት ተናግራለች፡፡

ስለደረሰባት ጉዳት ከሐኪም የተነገራትን ሁኔታም ተጠይቃ በጭንቅላቷ ውስጥ ደም መፍሰሱን፤ ሁለቱም ዓይኖቿ ሙሉ በሙሉ መጥፋታቸውን፣ የቀኝ ዓይኗ ነርቭ መጎዳቱን፣ ወገቧ ብዙ መቆም እንደማያስችላት (የፊዚዮፔራፒ ሕክምና እየተደረገላት ነው) በግራ በኩል ያለው ሰውነቷ በሙሉ መደንዘዙን፣ ሦስት የእጆቿ ጣቶች መጎዳታቸውን ከሐኪሞቿ ማወቋንና ሕክምናዋን እንዳልጨረሰች በዝርዝር አስረድታለች፡፡

የተከሳሹ ጠበቆች ለደረሰባት ጉዳት እነሱም እንደሚያዝኑ ገልጸው፣ አቶ ፍስሐ ደውሎ እንደሚመጣ መፍቀዷን ወይም መከልከሏን፣ ከመጣ በኋላ በስንት ሰዓት መደባደብ እንደጀመሩ፣ መጀመሪያ የተነጋገሩት በሰላም ነው ወይስ አይደለም ጣቱን ዓይኗ ውስጥ ሲያስገባ ታውቃለች ወይስ አታውቅም? ሲያስገባ ይታያት ወይም አይታያት እንደሆነ፣ ፖሊስ ጠርቶ ሲመጣ ‹‹ፊሽ›› ያለችው ድምፁን በምን እንደለየችው፣ የሚሉና ሌሎችንም መስቀለኛ ጥያቄዎችን አቅርበውላታል፡፡

እንዲመጣ እንደፈቀደችለት፣ የመጣውም ከአራት እስከ አራት ተኩል ባለው ሰዓት ውስጥ መሆኑን፣ ትንሽ ቆይቶ ድብደባ መጀመሩን፣ ጣቱን በዓይኗ ውስጥ ሲያስገባ ያማት ስለነበር ይታወቃት እንደነበር፣ ጣቱን ሲከት ግን አለማየቷን፣ ከፖሊስ ጋር መጥቶ ፖሊስ ሲጠራት ‹‹ፊሽ ነህ›› ያለችው ሁልጊዜ ድምፁን እየቀያየረ ያናግራት ስለነበር እሱ መስሏት መሆኑንና ለሌሎችም ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት የምስክርነት ቃሏን አጠቃላለች፡፡

ፍርድ ቤቱ ምስክርነቷን ከጨረሰች በኋላ ተከሳሹ በሁለቱም ክሶች እንዲከላከል ብይን ሰጥቷል፡፡ የመከላከያ ምስክሮቹን ለመስማት ለህዳር 12 ቀን 2004 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሲሰጥ የተከሳሽ ጠበቆች ማመልከቻ አቅርበው ፍርድ ቤቱ ሰምቷቸዋል፡፡

ጠበቆቹ ባቀረቡት አቤቱታ የግል ተበዳይዋን (ወሮ አበራሽ) በመከላከያ ማስረጃነት ስለቆጠሯት፣ ረዘም ያለ ጊዜ ተሰጥቷቸው ወይም በአዳሪ እንድትሰማላቸው ሲጠይቁ፣ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ምላሽ ምስክር ማሰማት የሚቻለው መጥሪያ ወስዶ በመጥራት በመሆኑ፣ እነሱም መጥሪያ አውጥተው ማስመስከር መብታቸው መሆኑን በመግለጽ፣ የቀጠሮው ቀን ግን እንደማይቀየር በማዘዝ ችሎቱ ተጠናቋል፡፡

ወ/ሮ አበራሽ ከፍርድ ቤት መልስ በሸራተን አዲስ የኢትዮጵያ ሴቶች ቅንጅት ማኅበር ባዘጋጀላት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተገኝታ፣ በተፈጸመባት አስከፊ ወንጀል ከጎኗ ለቆሙ ማኅበራት፣ ለመገናኛ ብዙኅን፣ እስካሁን ለወጣውና ወደፊትም ለሚቀጥለው የሕክምና ክፍያ ሙሉ ወጭ የቻሏትን ሼክ መሐመድ አሊ አል አሙዲን፣ ለኢትዮጵያ አየር መንገድና ለሌሎችም ምስጋና አቅርባ ‹‹እኔ ልቤ ተሰብሯል፤ የህሊና ስብራት እንዳይደርስብኝ ላጽናናችሁኝ ሁሉ እግዚአብሔር ከእኔ ዓይነት አስከፊ ሁኔታ ከነቤተሰቦቻችሁ ይጠብቃችሁ፤›› ብላለች፡፡

አዲስ የሊዝ መመሪያ በአትክልት ተራ ትርምስ ፈጠረ

Wednesday, November 9th, 2011

(Reporter) — የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ በሚያስተዳድራቸው የንግድ ቤቶች ላይ ተፈጸሙ የተባሉ ሕገወጥ ተግባራትን ሥርዓት ለማስያዝ በሚል ያወጣውን መመርያ ተከትሎ አዲስ አበባ መሰንበቻውን ተተራምሳለች፡፡

በተለይ በከተማው ውስጥ ከሚገኙ የንግድ ስፍራዎች መካከል ዋነኛው የአትክልት መሸጫ ማዕከል የሆነው የፒያሳ አትክልት ተራ ባለው ልዩ ባህሪ ምክንያት ብጥብጥ እያስተናገደ ነው፡፡

ኤጀንሲው ጥቅምት 17 ቀን 2004 ዓ.ም. አዲስ መመርያ አውጥቶ ‹‹ሕግ ለማስከበር›› አትክልት ተራ የተጓዘው ጥቅምት 27 ቀን 2004 ዓ.ም. ነበር፡፡ የኤጀንሲው ግብረ ኃይል በፖሊስ ጥበቃ እየተደረገለት በአካባቢው የሚገኙ የገበያ ማዕከል ተከራዮች ውላቸው ከዚያኑ ቀን ጀምሮ እንደተቋረጠ የሚገልጹ ደብዳቤዎችን በየንግድ ማዕከሉ በር ላይ ለጥፏል፡፡

በኤጀንሲው የአካባቢው ቀጣና ኃላፊ አረጋሽ ቸኮል ፊርማ ወ/ሮ ፎዝያ ከድርና ወ/ሮ ሙሉ ገብረ ኪዳን ለተባሉ ግለሰቦች የተጻፈው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፣ ኤጀንሲው ከእነዚህ ግለሰቦች ጋር የነበረውን ውል ማቋረጡንና የእነርሱን ሱቅ የተከራዩት ግን ከኤጀንሲው ጋር እንደሚቀጥሉ ይገልጻል፡፡

ይህ ሁኔታ በአካባቢው ከፍተኛ አለመግባባት ፈጥሮ በርካታ ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ አድርጓል፡፡ ጣይቱ ሆቴል ፊት ለፊት በሚገኘው የፒያሳ ፖሊስ ጣቢያ ይህንኑ ትዕይንት ከትናንት በስትያ ለማየት ተችሏል፡፡

ቤቶቹን ከኤጀንሲው እንደተከራዩ የሚናገሩና ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ግለሰቦች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ወ/ሮ ሶፊያና ወ/ሮ ሙሉን ጨምሮ አራት ሰፋፊ የንግድ ቤቶች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ተይዟል፡፡ መመርያው በፍርድ ቤት የተያዘን ጉዳይ እንደማይመለከት ቢገልጽም፣ ኤጀንሲው ውል እንደተቋረጠ መግለጹ አግባብነት የለውም ይላሉ፡፡ በእርግጥም በአዋጁ ተራ ቁጥር አሥር፣ መመርያው ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ያለ ከሆነ፣ መመርያው ተፈጻሚ እንደማይሆን ይደነግጋል፡፡

የአትክልት ተራ ከሌሎች ገበያዎች ለምሳሌ ከመርካቶና ከሾላ ገበያ የሚለየው ተከራዮቹ ለሰዓታት ብቻ በቦታው ላይ ተቀምጠው ከነገዱ በኋላ የሚነሱ፣ እነሱም ከተነሱ በኋላ ሌሎች ነጋዴዎች ቦታውን ይዘው ንግዳቸውን የሚቀጥሉ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ ሒደትም በአንድ ቦታ ብቻ አራት ነጋዴዎች ከዋናው አከራይ ውጭ ተከራይተው የሚነግዱ በመሆኑ፣ አለመግባባቱን ከፍ እንዳደረገው የአካባቢውን የንግድ እንቅስቃሴ በቅርብ የሚያውቁ ነጋዴዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹መመርያው ከወጣ በኋላ አትክልት ተራ ሰላም የለውም፡፡ ሰላሙንም በቅርብ ያገኛል ብዬ አላምንም፤›› ሲል በአካባቢው በጊዜያዊነት ቦታ እየተከራየ የሚሠራው ኡስማን መሐመድ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

የፒያሳው አትክልት ተራ ሥራ ከጀመረ ከ50 ዓመታት በላይ እንዳስቆጠረ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የቀበሌ፣ የግልና የኤጀንሲው ይዞታ በሆኑ 386 ቤቶች ሥራ የሚካሄድበት ይህ አካባቢ፣ ከ54 ዓመታት በኋላም የንግድ ማዕከላትን ሳይጨምር ወይም ማስፋፊያ ሳያካሄድበት 10 ሺሕ ነጋዴዎች በየዕለቱ ይርመሰመሱበታል፡፡
በአትክልት ተራ በእያንዳንዱ ቦታ ገንዘብ በኪራይ የሚገኝበት ሲሆን፣ በርካታ ሚሊዮን የብር ኖቶች በየዕለቱ የሚንቀሳቀሱበትና በቤተሰባዊ ግንኙነት፣ በኃይልና በገንዘብ ‹‹ኔትወርክ›› የተሳሰረ ሥራ የሚሠራበት አካባቢ እንደሆነም ይነገራል፡፡

በዚህ አካባቢ ዘመናዊ የንግድ ማዕከል ለመገንባት የተቋቋመው ቢስ አትክልትና አግሮ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር በቦታው ላይ ባካሄደው ጥናት መሠረት ‹‹በአምባገነናዊ ስሜት ተፅዕኖ ሥር የሚገኝ የገበያ ስፍራ›› ይለዋል፡፡

በፒያሳ አትክልት ተራ ሌሊት የገባ አንድ አትክልት የጫነ መኪና እስከ 1200 ብር ይከፍላል፡፡ ተከራይ ነጋዴዎችም እንዲሁ በውድ የሚከራዩ ሲሆን፣ ይህ ያንገፈገፋቸው ተከራይ ነጋዴዎች የኔትወርኩን ሰንሰለት ለመበጣጠስ ጊዜው አሁን ነው ቢሉም፣ ነባር የኤጀንሲው ተከራዮች ደግሞ ላለፉት 35 ዓመታት ሲተዳደሩበት የቆዩት ንብረት እንዲሁ እንደዘበት ሲሄድ የተዋጠላቸው አይመስሉም፡፡

ከእነዚህ ውጭም በዚሁ ቦታ ውክልና ይዘው የሚያከራዩ ወይም ጉዳይ በማስፈጸም ኮሚሽን የሚያገኙ መኖራቸው የአደባባይ ሚስጥር እንደሆነ ይነገራል፡፡ እነዚህ አካላትም የዚሁ ቦታ ጥቅም ተቋዳሽ ለመሆን የግብግቡ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ከዋናው የኤጀንሲው ተከራይ በስተቀር የንግድ ፈቃድ ያለው ባለመኖሩና ከእነዚህ ተከራዮችም በቋሚነት የመከራየት ልማድም ባለመኖሩ በአካባቢው የተነሳውን አለመግባባት አክርሮታል፡፡

የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲም ሆነ የቀበሌ ቤቶችን ተከራይተው ሸንሽነው ለሌላ ነጋዴ ባከራዩ ላይ መንግሥት የወሰደውን ዕርምጃ በሁለት መልኩ የሚመለከቱ አካላት ተፈጥረዋል፡፡ ግማሾቹ የመንግሥትን ዕርምጃ በፅንሰ ሐሳብ ደረጃ ትክክል መሆኑን ቢያምኑም፣ ትክክለኛ የተከራይ ተከራይ ወይም ቀጣይ የቤቱ ባለቤት መሆን የሚችልበት ግልጽ አሠራር ስለመኖሩ ይጠራጠራሉ፡፡

እነዚህ ግለሰቦች በአትክልት ተራ ከኤጀንሲው ጋር ውል ለመፈጸም እየተሯሯጡ የሚገኙት በእርግጥ እነማን ናቸው? ሲሉ ውስጥ አዋቂ እንደሆኑ የሚጠቁም ጥርጣሬያቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ በእጅ አዙር ንግድ ቤቶቹን ሊቆጣጠሩ የሚችሉበት መንገድ እንዳለም ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡

የወያኔ የመሬት ሊዝ አዋጅና የይዞታ ባለቤትነት

Wednesday, November 2nd, 2011

(Reporter) — የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር መስከረም 30 ቀን 2004 ዓ.ም. የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ በወጣው አዋጅ ዙርያ ትናንት ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል፡፡

መግለጫውን የሰጡት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ደሳለኝ አምባውና በሚኒስቴሩ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እስራኤል ተስፋዬ ናቸው፡፡ አዋጁን በተመለከተ በተለይ አቶ እስራኤል ለጋዜጠኞች ከሰጡት ማብራርያ የተወሰነውን ዝርዝር ከዚህ በታች ይመልከቱ፡፡

ቀደም ሲል የነበረው አዋጅ 272/94 ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ሥራ ላይ ውሏል፡፡ እንደምታውቁት መሬት የከተሞች ብቸኛ ሀብት ነው፡፡ ይህንን ብቸኛ ሀብት በአግባቡ ለማስተዳደር በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ አዋጆች ወጥተዋል፡፡ የእነዚህ አዋጆች አካል የሆነው አዋጅ ቁጥር 272 በሥራ ላይ በነበረበት ጊዜ አዋጁ ሲወጣ ያላያቸው ከፍተኛ ክፍተቶችና ችግሮች ተከስተዋል፡፡ እንዲሁም መሬትን የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲኖረው ለማስቻል የተሻለ አሠራር መፍጠር አስፈልጓል፡፡

ይህ ሥርዓት ካልተፈጠረ በተለይ በከተማ መሬት ላይ ትልቅ ችግርና የኪራይ ሰብሳቢነት አደጋ ነው የሚኖረው፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት የታየውን ችግር ለመፍታት በመጀመርያ የዳሰሳ ጥናት ተደርጓል፡፡ ጥናቱ በመሬት ላይ በተጨባጭ ያሉ ችግሮችን የለየ ነው፡፡ ከዚህ ጥናት ተነስተን ወደ ፖሊሲው ነው የገባነው፡፡ የፖሊሲው አቅጣጫ መሬት ላይ ወጥ የሆነ ልማትና ማኔጅመንት እንዲኖር የሚያስችል ነው፡፡ እነዚህን ችግሮች በፖሊሲው ምላሽ ተሰጥቶ ወደ ሕግ አግባብ መጥቷል ማለት ነው፡፡ እንደአብነት ከነበሩት ችግሮች አንዱ ክፍተት፣ መሬት ላይ ምንም ዓይነት ግንባታ ሲያካሂዱ ወይም ከደረጃ በታች የሆነ ግንባታ በማካሄድ ለሦስተኛ ወገን ማስተላለፍ ነው፡፡

ከዚህ ግብይት መንግሥት ሊያገኝ የሚገባው ጥቅም በግለሰቦች ኪስ ውስጥ እንዲገባ ሆኗል፡፡ በዚህ ዘርፍ ትልቅ የኪራይ ሰብሳቢነት አደጋ ነው የተፈጠረው፡፡ ይህ ማለት ባዶ መሬትን፣ ለልማት ሊውል የሚችል መሬትን፣ ወቅት ጠብቆና አጥሮ ይዞ ከዚያ በኋላ በጊዜ ሒደት ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨመር በማስተላለፍ ብቻ፣ አላግባብ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወደተወሰኑ ግለሰቦች ኪስ እየገባ የንብረት ልውውጡን ገበያ አናግቷል፡፡

ሌላው ትንሽ መሠረት ተጥሎና መሠረት የጣለበትን ቦታ በመሸጥ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብም ሲታፈስ ቆይቷል፡፡ ይኼ የራሱ የሆነ ትልቅ ችግር ነው፡፡ ሌላው በዚህ አዋጅ የነበረው አንዱ ከተሞች በጊዜ ሒደት ወደ ሊዝ ሥርዓት ይሸጋገራሉ ይላል፡፡ ሆኖም ግን የአዋጅን መንፈስ ተከትሎ ወደ ሊዝ የማሸጋገር ሒደቱ ከክልል ክልል፣ ከከተሞች ከተሞች ወጣ ገባ ነው የሆነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ 150 ከተሞች ብቻ ናቸው በሊዝ ሥርዓት መሬት በማስተላለፍ ላይ ያሉት፡፡ ይኼ ማለት በሊዝ ሥርዓት ቦታ ማስተላለፍ ማለትና አሁን ያለውን ነባር ይዞታን ወደ ሊዝ ማስተላለፍ የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ በሊዝ አግባብ ቦታ ማስተላለፍ ማለት መንግሥት መሬት ላይ የመሠረተ ልማት አሟልቶ ማስተላለፍ ማለት ነው፡፡ ይኼ እንግዲህ በአገር አቀፍ ደረጃ 950 ከተሞች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 150 ናቸው ይህንን የሚገለገሉበት፡፡ የሊዝ ሥርዓቱ ካለው ጠቀሜታ አንፃር ወደ ሊዝ ሥሪት ማስገባቱ ዘግይቷል፡፡ ይህንን ማስተካከል አስፈልጓል፡፡

ሌላው የመሬት አሰጣጥ ስልቱ በጣም ወጣ ገባ ነው፡፡ የቀድሞ አዋጅ ከድርድር ጀምሮ አምስት ያህል ቦታ የሚሰጥበት ስልት ነበረው፡፡ እነዚህ ስልቶች ወደታች ሲወርዱ አፈጻጸማቸውም ይለያያል፡፡ ከድርድር ጀምሮ በዕጣ፣ በሽልማት፣ በምደባና በጨረታ ቦታ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ የስልቶቹ አተገባበር የተለያየ ነበር፡፡ ይህንን ሁኔታ ወጥ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ግልጽ በሆነ መንገድ ስልቱን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በመነሳት በአዋጁ ሁሉም ክፍል ላይ ማሻሻያ ተደርጓል፡፡ አንደኛ የመሬት አስተዳደርና ልማት ሥርዓቱ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲኖር ማስቻል ነው፡፡ በጣም ግልጽ ተጠያቂነት ያለበት አሠራር ለማስፈን አዲሱን አዋጅ ቁጥር 272/2004 ማውጣት አስፈልጓል፡፡ አዋጁ አምስት ክፍሎችንና 37 አንቀጾችን ይዞ ወጥቷል፡፡ በስፋት በመሬት ላይ ትኩረት አድርጎና እንዲስተካከል በሚያደርግ መልኩ ተቀርጿል፡፡

አዋጁ ከፍተኛ ውዥንብርና ስጋት በኅብረተሰቡና በቤተሰብ ውስጥ አምጥቷል
አዋጁ መስከረም 30 ቀን 2004 ዓ.ም. ነው የፀደቀው፡፡ ከዚያ ጊዜ በኋላ በኅብረተሰቡ ውስጥ ለማስረፅ የተወሰነ ጊዜ ወስዷል፡፡ ይኼንን አዋጅ በአግባቡ ማስረዳት ይጠበቃል፡፡ በቀጣይም የምንሄድበት ጉዳይ ነው፡፡ በሊዝ አዋጁ ስጋት የሚፈጥር ምንም ነገር እንደሌለ ነው እኔ የምገነዘበው፡፡ በተለይ ሽያጭን በተመለከተ፡፡ ካነሳችሁት ጥያቄ አንፃር ለምሳሌ አንድ ሰው ይዞታውን ይሸጣል፡፡ የተሸጠውን ይዞታ ሲያስተላልፍ ወደ ሊዝ ሥሪት ይገባል፡፡ ይህ እንግዲህ በቤተሰብ መካከል የተለያየ አምባጓሮ እየፈጠረ ነው፡፡ ይህ የሚፈጸመው ነባር ሥሪት ላይ ያለ ንብረት ለመሸጥ የሚከላከል ነገር የለም፡፡ ይሸጣል፡፡ ሲሸጥ ግን እንደምታውቁት መሬት በዚህች አገር የሕዝብና የመንግሥት ሀብት ነው፡፡ ንብረቱ በሚሸጥበት ጊዜ በተገኘው ዋጋ ይሸጣል፡፡ ይኼ የመሬት ዋጋ ነው? ይኼ የቤቱ ዋጋ ነው? አይለይም፡፡ እንዲሁ ይሸጣል፡፡ ነገር ግን ለስም ዝውውር በሚመጣበት ጊዜ የስም ዝውውሩ የሚደረገው በሊዝ አግባብ ነው የሚሆነው፡፡ በሊዝ አግባብ ሲዛወር አንዱ መነሻ ዋጋውን መሠረት አድርጎ ነው፡፡ ይህ መነሻ ዋጋ እንግዲህ አዲስ አበባ በየትኛውም ቦታ ብትሄዱ መነሻ ዋጋው ከ600 ብር አይበልጥም፡፡

ለምሳሌ አንድ ሰው በ200 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያለ ንብረቱን ሲሸጥ ይህ ቦታ የሚገኝበት አካባቢ ያለው መነሻ ዋጋ በካሬ ሜትር 500 ብር ቢሆን 200 ሲባዛ በ500 ይሆናል 100 ሺሕ ብር ነው፡፡ የሊዝ ዋጋው 100 ሺሕ ብር ነው ማለት ነው፡፡ በሊዝ ውል ላይ በተቀመጠው መሠረት ከዚህ ገንዘብ ላይ 10 በመቶ ነው የሚከፍለው ወደ ስም ዝውውር ሲገባ፡፡ ይህንን ይከፍልና ቀሪውን ዘጠና በመቶ በሊዝ ውል በተቀመጠው መሠረት በ30 ወይም በ40 ዓመት አጠናቆ ይጨርሳል ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት አንደኛ ይህ መሬት ለገዢው አካል ዋጋ (ቫሊዩ) እንዲኖረው ያደርገዋል፡፡ የሊዝ ዋጋ ይኖረዋል፤ የሊዝ ዋጋ የሚሰጣቸው መብቶችና ጥቅሞች አሉ፡፡ ከነባር ይዞታ ይልቅ፡፡ አሁን ይህ ዋጋ በዋስትና ለማስያዝና በከፈለው መጠን እዚያው ላይ ባለው መጠን በዋስትና ለማስያዝና ተጠቃሚ ለመሆን ያስችላል፡፡ ሁለተኛ አንዴ ውል ሲገባ 30 ዓመትም ይሁን 40 ዓመት ውል በገባበት ወቅት ከሚከፍለው የሊዝ ክፍያ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ በነበረው ነባር የይዞታ ሥርዓት ቢሆን ሰውየው የሚከፍለው በየወቅቱ በሚከለሰው ግብር ነው፡፡ በየዓመቱ ሊጨምር ይችላል፡፡

በየወቅቱ የማይጨመር ክፍያ ነው በየጊዜው ለሊዝ ኪራይ የሚከፍለው፡፡ ሁለተኛ ለሕዝብ ጥቅም ተብሎ ከቦታው ላይ ሲነሳ ተመሳሳይ ስፋትና ደረጃ ባለው ቦታ ላይ ነው ልዋጭ የሚሰጠው፡፡ ስለዚህ ጥቅሙ ያለው ወደ ሊዝ የተሸጋገረለት ሰው ነው፡፡ ይህ ሲታይ መንግሥት ቀደም ሲል መረጃዎች ላይ ካያችሁ የመሬት ዋጋ ይህን ያህል የሚል አለው፡፡ የንብረቱ ይህንን ያህል የሚል አለው ከዚያ ያቺ የተተመነችውን ነው የሚከፍለው፡፡ ይህ ተተምኖ ነው ክፍያ የሚፈጸመው፡፡ ቀድሞ ሲከፈል የነበረው አሹራ በአዲሱ አዋጅ ወደ ሊዝ ሲዞር በሊዝ ክፍያ ይተካል፡፡ ይህ ማለት በጣም ኢምንት የሆነ ክፍያ ነው የሚከፍለው፡፡ ስለዚህ በግለሰቦች ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ የለም፡፡

በውርስ የተገኘ ይዞታ
የግል ባለይዞታ ሆነው በውርስ ከአንድ ሺሕ እስከ አንድ ሺሕ አምስት መቶ ካሬ ሜትር ወይም ሰፋ ያለ ይዞታ በውርስ ያገኙ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ በውርስ ያገኙ ሰዎች ቦታውን በውርስ ያገኙ በመሆኑ አዋጁም ከውርስ በስተቀር ስለሚል አይከፍሉም፡፡ በሌሎች ክፍለ ከተሞች ደግሞ ይከፍላሉ አሠራሩ ወጥ አይደለም የሚባል ነገር አለ፡፡ ለነገሩ አሁን ባለው ሁኔታ አዋጁ ተግባራዊ አልተደረገም፡፡ የሽግግር ጊዜ ተቀምጦለታል፡፡ ስለዚህ አሁን ባለው ሁኔታ ክፍለ ከተሞች አንተ ትከፍላለህ አንተ አትከፍልም የሚያስብል ነገር የለም፡፡ አዋጁ ሦስት ወር የሽግግር ጊዜ አስቀምጧል፡፡ በዚህ አግባብ ላይ ያለ ውርስ የቀረበበት ምክንያት ምንድን ነው? ለውርስ የማይከፈልበት ምክንያት ምንድን ነው? የሚሉ ነገሮን ማየት ተገቢ ነው፡፡ አንዱ ውርስ ሲሆን ‹‹ኖርማል ትራንዛክሽን›› አይደለም የሚፈጸመው፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕጉ ውርሱ ለሚገባቸው አካላት ነው ይዞታው የሚተላለፈው ይላል፡፡ ይህ መብት ያላቸው አካላት ደግሞ ትራንዛክሽን ውስጥ ለመግባት ያላቸው የኢኮኖሚ ሁኔታ ዝግጁ ካለመሆኑ አንፃር ትራንዛክሽን ሊፈጸም አይችልም፡፡ በመሆኑም መብታቸው መተላለፍ ካለበት ተነጣጥሎ መቅረት የለበትም ስለዚህ እንዲተላለፍላቸው ይደረጋል፡፡ ግን በቀጣይ እነዚህም ቢሆኑ በሚጠናው ጥናት መሠረት ከኅብረተሰቡ ጋር ውይይት ተደርጎ በቀጣይ ከነባር ይዞታ ሥሪት ወደ ሊዝ ሥሪት በሚሸጋገርበት ጊዜ የሚፈጸም ነው የሚሆነው፡፡ በጥናቱ ይህንን ያህል ካሬ ቦታ ያለው ሰው ምን ያህል ይከፍላል የሚል ቀጣይ አጠቃላይ ጥናት ተደርጎ መልስ የሚሰጥበት ይሆናል፡፡

የባዶ መሬት ሽያጭ
አንድ መንግሥት በሊዝ አግባብ ቦታ ሲሰጥ ቦታው ቀጥታ ለልማት ውሎ፣ የሥራ ዕድል ፈጥሮ፣ ኢኮኖሚውን አሳድጎ፣ ሌሎች ተጨማሪ ጥቅሞችን እንዲያመጣ ነው፡፡ ባዶ መሬት እንዲገላበጥ አይደለም የመንግሥት ፍላጎት፡፡ ይሁንና ግን እነዚህ መጠነኛ ግንባታ የገነቡ ሰዎች ግንባታውን ለመቀጠል አቅም ሊያጥራቸው ይችላል፡፡ በተወሰነ ደረጃ ላይ የተወሰነ የአቅም ማነስ ተፈጥሮ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ በሚሆን ጊዜ አዋጁ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ሰውየው መብቱን ማስተላለፍ ይችላል፡፡ አይደለም ግንባታ ከግማሽ በታች አከናውኖ ይቅርና የግንባታ ዘመኑ እስካላለፈ ድረስ ባዶ መሬትም ማስተላለፍ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ይህንን ይዞታ ሲያስተላልፍ ይህ ሰው በዚያ ቦታ ላይ ያለው ዋጋ፣ የመሠረተ ልማት፣ የግብይት ዋጋ ከፍ ማለት፣ ጥቅሞች የተገኙት በመንግሥት በተካሄዱ ሥራዎች እንጂ ሰውየው የሠራቸው አይደሉም፡፡ ለውጡ የመጣው ከተሞች መሠረተ ልማት ዘርግተው ሀብታቸውን አፍሰው ባመጡት ጥቅም ነው፡፡

ሻጩ ቦታውን ሲያስተላልፍ የንብረቱን ዋጋ ማለትም ለሊዝ የከፈለውን ቅድመ ክፍያ ማግኘት ይችላል፡፡ ይህ ገንዘብ በባንክ ቢቀመጥ ወለድም ያገኛል፡፡ ከተገኘው የመሬት ዋጋ ልዩነቱን አምስት በመቶ ያህሉን ይሰጠዋል፡፡ ለለፋበት ወዲህ ወዲያ ላለበት ማለት ነው፡፡ በዚህ አግባብ ክፍያው ይፈጸማል፡፡ የሚተላለፍለት ግለሰብ ግን የሊዝ ውሉን ቀደም ሲል በ18 ወር ይጠናቀቃል ተብሎ ውል ከተፈጸመ አዲሱ ውል ተቀባይም በዚህ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እርግጠኛ መሆን ይኖርበታል፡፡ ነባር ይዞታን ወደ ሊዝ ሥሪት ሲገባ ይኼ አዋጅ ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ነባር ይዞታ ወደ ሊዝ በሚሸጋገርበት ጊዜ ጥናት ተደርጎ ነው፡፡ አራት ዓመት የተሰጠው ለጥናት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ጥናት ተደርጎ ከኅብረተሰቡ ጋር በቂ ውይይት ተደርጎበት ወደ ሊዝ ሥርዓት የሚሸጋገርበት አግባብ ይኖራል፡፡ ወደ ሊዝ ሲሸጋገር በመነሻ ዋጋ ነው የሚተላለፈው፡፡ ነገር ግን ይህንን ጥናት ሳይጠብቅ የሚሸጋገሩ ነገሮች ተለይተው ተቀምጠዋል፡፡ አንዱ በትራንዛክሽን ጊዜ ይህ ጥናት ሳይጠበቅ ወደ ሊዝ እንዲገባ ይደረጋል፡፡

ሁለተኛው በሕገወጥ አግባባ የየተያዘ መሬት ሕጋዊ እንዲሆን ከተሞች ሲወስኑ ቀድሞ በዚያ መሬት የተከፈለ ነገር የለም፤ አግባብ በሆነ አካል የተሰጠ ቦታም አይደለም፡፡ ከተሞች ይህንን ቦታ ወደ ሊዝ ሥርዓት እንዲገባ ሲያደርጉ በሊዝ አግባብ ይሆናል፡፡ ሌላው ሁለት ይዞታዎች ሲቀላቀሉ ሊዝ ይሆናል፡፡ ማለትም አንድ ሰው ነባር ይዞታ አለው፡፡ እዚያ አጠገብ ቦታ በሊዝ ቢገዛና መቀላቀል ካሰበ ቦታው በሊዝ ሥሪት ይገባል፡፡ እንዲሁ እንዲቀጥል ከፈለገ ይዞታው ወደ ሊዝ ሳይገባ ይቀጥልበታል፡፡ ይቀላቀል ሲል ነው ወደ ሊዝ ሥሪት የሚገባው፡፡ ሰውየው ለነባር ይዞታው የሚከፍለው በአካባቢው የቦታ መነሻ ዋጋ ይሆናል፡፡ ካርታው አንድ ላይ ይዘጋጅለታል፡፡ ከዚያ ወደ ውል ይኬዳል፡፡ በሚወጣው ደንብ ላይ በደንብ የሚዘረዘሩ ነገሮች ይኖራሉ፡፡

የሊዝ ዘመን ዕድሳት
አዋጁ ሊዝ ሊታደስ በማይችልበት ሁኔታ ካሳ አይከፈልም ይላል፡፡ ሊዝ የማይታደስበት ሁኔታ አለ ወይ? እንግዲህ ለአንድ የሊዝ ዘመን ለመኖርያ ቤት ለምሳሌ በሊዝ ቦታ ተወስዷል፡፡ ካርታው ቢታይ ለ99 ዓመት የሊዝ ዘመን ይላል፡፡ ለንግድም ሆነ ለሁሉም የሊዝ ዘመን ተቀምጧል፡፡ ይህን ወስዶ ልማቱን እየፈጸመ ሲኖር ቆይቶ 89 ዓመት ይደርሳል፡፡ አዋጁ እንደሚለው ከ10 ዓመት በፊት ለሊዝ ዕድሳት ማመልከት ስላለበት እዚህ ዘመን ላይ ሲደርስ ይታደሳልኝ ብሎ ይቀርባል፡፡ በሚቀርብበት ጊዜ እንግዲህ በ100 ዓመት ዕድሜ የአንድ ከተማን ዕድገት ማሰብ ትችላላችሁ፡፡ በአዲስ አበባ አይደለም በመቶ ዓመት ባለፉት 10 እና 20 ዓመታት የመጣውን ለውጥ ታስተውላላችሁ፡፡

ከዚህ ለውጥ ተነስቶ ያ ቦታ በሚጠናው ማስተር ፕላን መሠረት አሥር ዓመት ለማስተር ፕላን የተሰጠው ዕድሜ ነው፡፡ በማስተር ፕላኑ መሠረት ቦታው ለሌላ ልማት እንዲውል ነው የተወሰነው እንበል፡፡ በማስተር ፕላኑ ከዚያ በኋላ ይኼ ቦታ አይታደስም፡፡ በቀጣይ ሌላ ልማት ነው የሚካሄድበት ተብሎ ተወስኗል፡፡ ስለዚህ ካሳ አያገኝም ማለት ነው፡፡ ካሳ የማያገኘው በሊዝ የተሰጠ መሬት መቶ ዓመት ካገለገለ በኋላ ካሳ አይገባውም፡፡ አይደለም አንድ መሬት አንድ አገር ለምሳሌ ታይላንድን ውሰዱ እንግሊዞች በሊዝ ወስደው ገነቡ፡፡ ከ90-100 ዓመት ኖሩ፡፡ የሊዝ ዘመኑ ሲጠናቀቅ ወጡ ማለት ነው፡፡ አንድ የተከፈለ ካሳ የለም፡፡ በተሰጣቸው የሊዝ ዘመን ተጠቅመዋል፡፡ ግለሰቡ የሚገባውን ተጠቅሟል ተብሎ ነው የሚታመነው፡፡ ስለዚህ ካሳ አይገባውም፡፡ ንብረቱን ማንሳት ብቻ ነው፡፡

በምደባ ቦታ ስለመስጠት
ተተኪ ቤት ማግኘት የማይቻል ሲሆን ለምሳሌ መልሶ ማልማት ቦታ ላይ ተከራዮች አሉ፡፡ ከቀበሌ ከመንግሥት የተከራየ አለ፡፡ የመጀመርያው የሚሆነው ኮንዶሚኒየም በሚገነባባቸው ከተሞች ኮንዶሚኒየም እንዲያገኙ ማስቻል ነው፡፡ በአዲስ አበባ እየተፈጸመ ነው፡፡ ኮንዶሚኒየም በማይገነባባቸው ከተሞች ግን እነዚህ ተነሺዎች እንዲደራጁ ተደርጎ በሚያስቀምጡት የገንዘብ መጠን፣ እዚህ ላይ ሰውየው ቁርጠኛ ሆኖ ገንዘብ ማጠራቀም አለበት፡፡ ሲያጠራቅም 60 በመቶውን መንግሥት ያበድረዋል፡፡ ቦታውን ያለማል፡፡ 40 በመቶ ገንዘብ አስቀምጦ ማልማት ካልቻለ ወይም ካልፈለገ ሦስት በመቶ ተቀጥቶ ገንዘቡን [ያስቀመጠውን] ይወሰዳል፡፡ ምንም የሌለው ከሆነስ? ምንም የሌለው ከሆነ በተለያዩ የመልሶ ማልማት ቦታዎች ላይ እንደሚደረገው ተለዋጭ የቀበሌ ቤት ይሰጠዋል፡፡

ነባር ይዞታ ወደ ሊዝ ሲገባ ሕገ መንግሥቱ ያስቀመጠውን ንብረት የማፍራት ዋስትና አይጥስም?
በሊዝ በወሰደው መሬት ላይ ንብረት ማፍራትና በነባር ይዞታ ላይ ንብረት ማፍራት የትኛው ነው ለአልሚው ጥቅም ያለው? ይህ አዋጅ ሕገ መንግሥቱ ያስቀመጠውን ነው ይዞ የሄደው፡፡ ሊዝ ሲሆን ይህ መብት ይሸረፋል ወይ ነው? ሊዝ ሲሆን እንዲያውም የተሻለ ተጠቃሚ ያደርገዋል እንጂ ጉዳት የለውም፡፡ በሊዝ ሥርዓት ያውም ገና ጥናቱ ተጠናቆ ከአራት ዓመት በኋላ የሚወሰን ውሳኔ ነው፡፡ እሱም ሆኖ ሳያበቃ አሠራሩ ንብረት የማፍራትን መብትን ያጠናክረዋል እንጂ የሚሸረሽርበት አግባብ የለውም፡፡ አንድ ሰው ንብረት ሲያፈራ በዋስትና እንዲያዝለት የማድረግም ጭምር ነው፡፡ ንብረት ማፍራት ብቻውን ምንም አይደለም፡፡ ንብረት ማፍራት ዋስትና ሲኖረው ነው ጥቅም ያለው፡፡ ይኼ አዋጅ ምንድን ነው ያደረገው? ይህ ንብረት ወደሊዝ ሲመጣ የሊዝ ዋስትናን ነው የሚያጎናጽፈው፡፡ ስለዚህ ዋስትናው በተጠናከረ ሁኔታ ከመሬቱና ከንብረቱ ጋር ባለበት ሁኔታ ይቀጥልለታል፡፡ የመያዣ ዋስትናው ይጠናከርለታል፡፡ ከዚሁ ጋር በተለይ ከማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ ጋር የሚመጡ አሠራሮች ይኖራሉ፡፡ ይህን ሁኔታ የበለጠ ያጠናክርለታል፡፡ መብቱን ሰፋ ያደርግለታል፡፡ ወደ ሊዝ ሲገባ መብቱ ከመሸርሸር ይልቅ እንዲያውም ይጠናከራል፡፡ በነባሩም ይዞታ ይህ መብት የተሸራረፈበት ሁኔታ የለም፡፡ ተጠናክሮ ነው ያለው፡፡ በሊዝ ሥሪት ደግሞ ሀብት የማፍራት ጉዳይ የበለጠ ዋስትና ይኖረዋል፡፡

በአዲሱ የሊዝ አዋጁ ሕዝብ ተደናግሯል

Wednesday, October 26th, 2011

(Reporter) — በቅርቡ የመሬት ሊዝ አዋጅ በፓርላማ ፀድቋል፡፡ የአዲስ አበባ መስተዳድርም በዋና ዋና መንገዶችና ኪስ ቦታ ውስጥ ያሉ መሬቶች ሕንፃ እንዲሠራባቸው መመርያ አውጥቷል፡፡

በየቀበሌው የሚመለከታቸውን እየሰበሰበ የሚሠሩ ወይም የማይሠሩ መሆናቸውን በፊርማ እንዲያረጋግጡ እያደረገ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ በእኛ በኩል የሊዝ አዋጅ ለምን ወጣ? ሕንፃ ሥሩ ለምን ተባለ? ብለን መቃወምም አንፈልግም፤ ግሩም መመርያና አዋጅ ነው ብለንም መደገፍ አንችልም፡፡ ከሁሉም በፊት የሚቀድመው አዋጁና መመርያው ለኅብረተሰቡ ግልጽ ስላልሆነለት እየተደናገረና እየተጨነቀ መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት አዋጁም መመርያውም ምን እያሉ እንደሆነ በግልጽ ከሕዝብ ጋር በመቀራረብ ያስረዱ! ያብራሩ! ያወያዩ! ነው የምንለው፡፡

በሊዝ አዋጁ ዙሪያ ባለይዞታው ግለሰብ ልነጠቅ ነው ማለት ነው ወይ? ማውረስ አልችልም ማለት ነው ወይ? የገዛ መሬቴን በሊዝ ግዛው እየተባልኩ ነው ወይ ያለሁት? ወዘተ እያለ በጣም እየተጨነቀና እየተረበሸ ነው፡፡

መሬት መግዛት የሚፈልገው ደግሞ ለባለይዞታው ከከፈልኩ በኋላ እንደገና በሊዝ ለመንግሥት ልከፍል ነው ወይ? ሁለት ክፍያ ከሆነ ዋጋው አይንርም ወይ? እኔ በውድ የምገዛው ከሆነና ግንባታ ካከናወንኩበት በኋላ እኔም በውድ ዋጋ መሸጥ አለበኝ ማለት ነው ወይ? እያለ እየተደናበረ ነው፡፡

ከአምስት መቶ ካሬ ሜትር በላይ ይወሰዳል ወይም በሊዝ የሚያዝ ይሆናል የሚለውም መደናገር እየፈጠረ ነው፡፡ እስካሁን የያዝኩትስ ምን ይሆናል ማለት ነው? መገንባት ብፈልግ አልችልም ማለት ነው ወይ? የሚል ጥያቄ እያስነሳ ነው፡፡

በአተገባበሩ ላይም ለመሆኑ ካሁን በኋላ ለሚደረገው ሽያጭና ግዥ ነው ወይስ ላለፉት ሃያ ዓመታት የነበሩ ይዞታዎችም ወደኋላ ተመልሰው ክፍያና የሊዝ ውል ሊፈጸምባቸው ነው? ካሁን ቀደም የገዛና የገነባ እንደገና ወደኋላ ተመልሰህ ክፈል ሊባል ነው ወይ? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው፡፡

የሊዝ አዋጅ ያስፈልጋል፡፡ በየጊዜው እየተከታተሉ ግልጽ ማድረግና አስፈላጊ ማሻሻያዎችን ማካተትም ያስፈልጋል፡፡ አዋጁ ለአገርና ለሕዝብ ይጠቅማል ወይ? አዋጁ ለልማት ዋስትና ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ይነሳ እንደሆነ እንጂ የአዋጁን አስፈላጊነትና ጠቃሚ መሆን ማረጋገጥ ነው የሚያስፈልገው፡፡

ሕዝብ አዋጁ ጠቃሚ ነው ብሎ ሊቀበለው የሚችለው ደግሞ ሲብራራለት፣ ሲወያይበትና ሲያምንበት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ታወጀ እንጂ ለሕዝቡ ግልጽ የሚያደርግና የሚያብራራ አልተገኘም፡፡ በዚህ ምክንያትም ሕዝቡ ፍርኃት፣ ጭንቀት፣ መደናበርና መደነጋገር በዝቶበታል፡፡

ውይይት ከተደረገበት ጠቃሚ ነው ወይም ጠቃሚ አይደለም ብሎ መከራከር ይቻላል፡፡ ይህ ይጨመር ይህ ይቀነስ ማለትም ይከተላል፡፡ ይህ እንዲሆን የሚመለከታችሁ የመንግሥት አካላት አስረዱ! አብራሩ! አወያዩ! እንላለን፡፡

ያለው መደናገር በሊዝ አዋጁ ላይ ብቻ አይደለም፡፡ በሕንፃ ግንባታ ዙርያም መመርያው ላይ መደናገር አለ፡፡ ሕንፃ ካልገነባሁ እነጠቃሁ ማለት ነው? መገንባት ያለብኝ በስንት ቀን፣ ወር ወይም ዓመት ውስጥ ነው? ለመሆኑ የሚገነባውስ ባለ አራት ፎቅ ነው? ባለ ሰባት ፎቅ ነው? ባለስንት ነው? የሚል ጥያቄ አለ፡፡

በተለይም መገንባት የሚፈልግ ባለይዞታ ገንዘብን በሚመለከት ከዘመድ አዝማድ ለመወያየት ጊዜ ያስፈልገዋል፡፡ ለመሐንዲሶች ሥራ መስጠትና ዲዛይን ማሠራት አለ፡፡ የግንባታ ስምምነት አለ፡፡ የግንባታ ፈቃድ አለ፡፡ ማቴሪያል ማዘጋጀት አለ፡፡ ይህ ሁሉ ከባድ ሥራ እያለ የሚሰጠው ጊዜ በቂ አይደለም፤ እያቻኮሉን ነው የሚል ስሞታ ይደመጣል፡፡

አዲስ አበባ ዘመናዊ ገጽታ፣ መልክና ይዘት አይኑራት የሚል የለም፡፡ ውበት ማለት ሕንፃ ነው የሚል ትርጓሜ ብቻ እንዲሰፍን ባንስማማም፣ ከሕንፃዎች ጐን ለጐን መናፈሻዎችና አረንጓዴ አካባቢዎችም ያስፈልጋሉ፡፡ ለሕንፃ ግንባታ የተከለለ አካባቢ ይኑር ብንልም፣ የመኖሪያ፣ የኢንዱስትሪ የመዝናኛና የሥራ አካባቢዎች ይለዩ ባዮች ብንሆንም፣ አዲስ አበባን ዘመናዊ ለማድረግ የሚደረጉ ጥረቶችንና ሙከራዎችን እንደግፋለን፡፡

ነገር ግን ምን እየተባለ እንደሆነ መደናገር አለና አሁንም የሚመለከታቸው የመንግሥት መሥርያ ቤቶችና ኃላፊዎች እንዲያብራሩ፣ እንዲያስረዱና እንዲያወያዩ እንጠይቃለን፡፡

በየቀበሌው አወያያተን የለም ወይ? የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል፡፡ አዎን ስብሰባዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን የሕዝብ ጥያቄና አቤቱታ የቀረበቡባቸው ስብሰባዎች ስለሆኑ የሕዝብን ጥያቄ ይዞ መልስ አዘጋጅቶ ማብራራትና ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡

በተለይ ጊዜው የኢኮኖሚ ችግር የሚታይበት ስለሆነ፣ ከምንም ጊዜ በላይ መገናኘት፣ መቀራረብና መወያየት ያስፈልጋል፡፡ መደማመጥ የግድ ይላል፡፡ የሕዝብን ጥያቄ ጊዜ ሰጥቶ ማዳመጥና መፍትሔ መፈለግ የግድ ይላል፡፡

ልማቱም በአንድ በኩል እንዳይደናቀፍ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝብን ከጐን አሰልፎና አሳምኖ ማልማት እየተቻለ፣ አላስፈላጊ መቃቃርና መራራቅ ፈጥሮ ልማትን ማደናቀፍ እንዳይኖር መጠንቀቅ የማይታለፍ ነው እንላለን፡፡

በተለይ በተለይ በመቀራረብ በርካታ ችግሮችን መፍታት እየተቻለ በመራራቅ ምክንያት ችግር እየተባባሰ ነውና እንጠንቀቅ፡፡

የሰሞኑን ሁኔታ ስናይ ደግሞ በሊዝ አዋጁና በሕንፃ ግንባታ መመርያ ዙሪያ ሕዝብ ተደናግሯል፤ ተደናግጧል፤ ተጨንቋልና የሚመለከታችሁ መንግሥታዊ አካላትና ኃላፊዎች አብራሩ! አስረዱ! አወያዩ!

አማርኛ በአፋር ክልል ከስራ ቋንቋነት ሊቀየረ ነው

Wednesday, October 26th, 2011

(Reporter) — ላለፉት 20 ዓመታት የአማርኛ ቋንቋን የሥራ ቋንቋው አድርጎ ሲጠቀም የቆየው የአፋር ክልል መንግሥት፣ በቅርቡ የአፋርኛን ቋንቋ የክልሉ የሥራ ቋንቋ አድርጎ ለመጠቀም ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ተጠሪ አቶ ጠሃ አህመድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በቅርቡ የክልሉ የሥራ ቋንቋን አፋርኛ ለማድረግ ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡ ኃላፊው እንዳሉት፣ በክልሉ የተማረ የሰው ኃይል ስላልነበረ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ የክልሉ የመንግሥት ሠራተኞች የሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ነበሩ፡፡ በዚህም ምክንያት ክልሉ አማርኛን የሥራ ቋንቋ አድርጎ ለመጠቀም ተገዶ ቆይቷል፡፡

በአሁኑ ወቅትም የሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ሠራተኞችን በአፋርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ሙሉ ለሙሉ ከመተካት ይልቅ፣ በየመሥርያ ቤቱ የአፋርኛ ቋንቋ አስተማሪዎቹን መድቦ አስተምሯል፡፡

አሁን በተያዘው አቅጣጫ መሠረት ሠራተኞች ሳይንሳፈፉ የክልሉ የሥራ ቋንቋን አፋርኛ ለማድረግ፣ ትምህርት ቤቶችም በአፋርኛ ቋንቋ እንዲያስተምሩ በቂ መምህራን ሲመደቡ የማስተማር ዝግጅቱም ተጠናቋል ብለዋል፡፡

እነ ኤልያስ ክፍሌ የተመሠረተባቸው የአሸባሪነት ክስ እንዲሻሻል ትዕዛዝ ተሰጠ

Saturday, October 22nd, 2011

(ሪፖርተር) — ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በተደራጀ የሸብር ድርጊት ለማፍረስ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ተደርሶባቸዋል በሚል በሽብር ወንጀል በኤልያስ ክፍሌና በአራት ተጠርጣሪዎች ላይ ከተመሠረቱት አራት ክሶች መካከል፣ ሁለተኛው እንዲሻሻል ፍርድ ቤት ጥቅምት 9 ቀን 2004 ዓ.ም. ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በሽብር ወንጀል ተጠርጣሪዎቹ ላይ ጳጉሜን 1 ቀን 2003 ዓ.ም. የመሠረተው ክስ፣ ጥቅምት 9 ቀን 2004 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ቀርቦ የተነበበ ሲሆን፣ በተከላካይ ጠበቆች በቀረበ ተቃውሞ ሁለተኛውን ክስ ዓቃቤ ሕግ አሻሽሎ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

በሽብር ወንጀል ተጠርጣሪዎቹ አቶ ኤልያስ ክፍሌ (በሌሉበት)፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ገብረ እግዚአብሔር፣ የአውራ አምባ ታይምስ ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ ውብሸት ታዬ፣ መምህርትና ዓምደኛ ርዕዮት ዓለሙና ሒሩት ክፍሌ ሲሆኑ፣ ጠበቆቻቸው እንዲሻሻል ጥያቄ ያቀረቡት ክስ ዓቃቤ ሕግ በሁለተኛነት ባቀረበውና ሁሉንም ተጠርጣሪዎችን በሚመለከተው ክስ ላይ፣ በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ ሰባትን በመተላለፍ የሚለው ነው፡፡

እንደ ጠበቆቹ ተቃውሞ በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ ሰባት ሥር ሁለት ንዑስ አንቀጾች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ የትኛውም ተከሳሽ በየትኛው ንዑስ አንቀጽ እንደሚጠየቅ ስለማይገልጽ፣ በግልጽ መቀመጥ እንዳለበት ያቀረቡት ተቃውሞ በፍርድ ቤቱ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ በመሆኑም ዓቃቤ ሕግ አንቀጾቹን ለያይቶና አስተካክሎ እንዲያቀርብ ታዟል፡፡

ጥቅምት 9 ቀን 2004 ዓ.ም. የአምስቱንም የሽብር ወንጀል ተጠርጣሪዎች ክስ ማየት የጀመረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት፣ ክሱን በንባብ ከማሰማቱ በፊት ተጠርጣሪዎቹ መኖራቸውን አረጋግጦ፣ አቶ ኤልያስ ክፍሌ በጋዜጣ ቢጠሩም ሊቀርቡ አለመቻላቸውን ዓቃቤ ሕግ በማስታወቁ በወንጀል ሕግ ቁጥር 163 መሠረት በሌሉበት እንዲታይ ወስኗል፡፡

ፍርድ ቤቱ በችሎት ለተገኙት ተጠርጣሪዎች የተከሰሱበትን የወንጀል ዝርዝር በንባብ ካሰማ በኋላ፣ በወንጀል ሕግ 130 መሠረት የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ቅሬታ ካላቸው እንዲያቀርቡ ጠይቋል፡፡

ተቃውሞ እንዳላቸው የገለጹት የአቶ ዘሪሁን፣ የጋዜጠኛ ውብሸትና የሒሩት ጠበቃ ደርበው ተመስገን፣ የወንጀል ድርጊቶቹና የሕጉ አገላለጽ አይጣጣሙም ብለዋል፡፡ “ደጋፊ መረጃዎቹ ተጠርጣሪዎቹ ክሱን በግልጽ ተረድተው ለመከላከል በሚያስችል መልኩ አልቀረቡም፡፡ ተከሳሹ የተከሰሰበትን ወንጀል ለይቶና አውቆ መልስ ለመስጠት እንዲችል፣ እያንዳንዱ ክስ ወንጀሉንና ሁኔታውን በዝርዝር መግለጽ አለበት፡፡ የወንጀል ሕግ 12ን መመልከት ያስፈልጋል፤” ያሉት ጠበቃው፣ በተጠርጣሪ ተከሳሾቹ ላይ የቀረበው ክስ ከተጠቀሱት የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ አንቀጾች ጋር የማይሄድና በጥቅሉ የቀረበ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 111/1/ሐ መሠረት ወንጀሉ የተፈጸመበት ጊዜና ቦታ መገለጽ ቢኖርበትም፣ በክሱ ላይ ቀኑና ወሩ ባልታወቀበት ከ2003 ጀምሮ መባሉ ‹‹እኔ አልነበርኩም›› ብሎ ለሚከራከር አመቺ አይደለም ብለዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በአንደኛ ክሱ ጥምረት በመፍጠር፣ የትብብር ስምምነት በመፈራረም፣ በጋራ የሽብር ስትራቴጂና ዕቅድ ላይ በመወያየት፣ የሥራ ክፍፍል በማድረግ የኤሌክትሪክ መስመሮችን ከጥቅም ውጭ ለማድረግ በመስማማት ከሚል ጥቅም አባባል በቀር እነማን የት እንደተፈራረሙ፣ የት ቦታና መቼ የጋራ ውይይት እንዳደረጉና እንደተስማሙ ስለማያመለክት በማለት ጠበቃው ተቃውመዋል፡፡

እንደ ጠበቃ ደርበው ተቃውሞ፣ ተከሳሾቹ ምን የሚባል የሽብርና የቅስቀሳ ጽሑፎች ከማን እንደተቀበሉ፣ ለማን እንዳሠራጩ፣ እነማን ያሉበትን የሽብር ቡድን እንዳደራጁ፣ ከየትኛው የሽብር ቡድን ገንዘብ እንደተቀበሉና ማን ለተባለ የሽብር ቡድን መረጃ እንደሰጡ በቦታና በጊዜ ተለይቶ አልተጠቀሰም፡፡

የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3(6) እና ወይም 4 ሥር የሚለው የዓቃቤ ሕግ ክስ በተፈጸመው ወንጀል እርግጠኛ አለመሆን ስለሚያሳይ፣ ተከሳሹ ለመከላከል በሚያስችል መልኩ በግልጽ አለመቀመጡን ጠበቃው አስታውቀዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በሦስተኛ ክሱ በሁሉም ተከሳሾች ላይ የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ ዘጠኝን፣ በአማራጭም የወንጀል ሕግ አንቀጽ 684 (1) እና (2) መጥቀሱን የገለጹት ጠበቃው፣ በአዋጁ አንቀጽ ዘጠኝ እንደተገለጸው፣ በሽብርተኝነት ድርጊት የተገኘን ንብረት ስለመያዝና መገልገል የሚገልጽ ቢሆንም፣ ገንዘቡ በምን ዓይነት የሽብር ተግባር ከእነማን እንደተገኘ አለመገለጹን ጠቁመው፣ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 684 (1) እና (2) ግን በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብን የሚመለከት ስለሆነ በሙስና በአደንዛዥ ዕፅ ወይም በመድኃኒት ዝውውር፣ በሕገወጥ የጦር መሣርያ ንግድና በሌላ ሕገወጥ ተግባር የተገኘ መሆኑን ክሱ እንደማያመላክት፣ ወይም የተጠቀሰው የወንጀል ወጤት አለመሆኑን እንደማያሳይ አብራርተዋል፡፡

የመምህርትና ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ ጠበቃ ሆነው የቀረቡት ጠበቃ፣ ጠበቃ ሞላ ዘገዬ ተቃውሞ ካላቸው እንዲያስመዘግቡ ፍርድ ቤቱ ሲጠይቃቸው፣ የሌሎች ተከሳሾች ጠበቃ ደርበው ተመስገን ያስመዘገቡት የተቃውሞ ሐሳብ ለእሳቸው እንዲመዘገብላቸው ፍርድ ቤቱን በመጠየቅ አስመዝግበዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ከጠበቆቹ የተነሳበትን የተቃውሞ ሐሳብ በሚመለከት በሰጠው ምላሽ፣ ለተጠቀሱት ክሶች ሁሉ ዝርዝር ማስረጃዎችን ማቅረቡን፣ የእያንዳንዱ ተጠርጣሪ ግንኙነትን መግለጹን፣ ተናግሮ ወቅቱና ጊዜው አልተጠቀሰም ለተባለው ተቃውሞ ‹‹ዓመተ ምህረቱ 2003 መሆኑ ተጠቅሷል፤ ወሩና ቀኑ ከመስከረም እስከ ነሐሴ ሊሆን ይችላል፤›› በማለት መልስ ሰጥቷል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ዝርዝር ነገሮችን ወደፊት በማስረጃ የሚያሳይ መሆኑንም አስታውቋል፡፡

በጧቱ የችሎት ጊዜ ሊጠናቀቅ ያልቻለው የዓቃቤ ሕግና የተከሳሽ ጠበቆች የተቃውሞ ምልልስ ከሰዓት 8፡30 ሰዓት ላይ ቀጥሎ፣ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ብይን ጠበቆች ጊዜና ቦታ አልተጠቀሰም ያሉትን፣ ከወንጀሉ ባህሪ አንፃር ፍርድ ቤቱ እንዳልተቀበለው ገልጾ፣ ተጠርጣሪዎች ያላቸውን የወንጀል ተሳትፎን በሚመለከት ዓቃቤ ሕግ በሚያቀርባቸው ማስረጃዎች የሚታይ መሆኑን ተናግሮ፣ ዓቃቤ ሕግ የሚያሻሽለውን ክስ ሰምቶ፣ የተጠርጣሪ ተከሳሾቹን የዕምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ለጥቅምት 13 ቀን 2004 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የኢሕአዴግ ከፍተኛ ሹማምንት ከኃላፊነት ተነሱ

Wednesday, October 19th, 2011

(ሪፖርተር) — የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ አመራር ቡድን ጥቅምት 2 እና 3 ቀን 2004 ዓ.ም. ባደረገው ግምገማ፣ የከተማውን ምክትል ከንቲባ፣ የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና ሌላ የአዲስ አበባ የመዋቅር አባላትና ሥልጠና ዘርፍ ኃላፊን ከኃላፊነት ማንሳቱን ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ የከተማውን ከንቲባንና ሥራ አስኪያጅን ያካተተው የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ አመራር ቡድን ግምገማ፣ ምክትል ከንቲባውና የማስታወቂያ ቢሮ ኃላፊ አቶ ከፍያለው አዘዘን፣ የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ልዑል ሰገድ ይፍሩንና የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ የአባላትና ሥልጠና ዘርፍ ኃላፊውን አቶ ካሚል መሐመድን ከኃላፊነታቸው አንስቷል፡፡

ኃላፊዎቹ የተሰማሩበትን ዓላማና እምነት ወደ ጐን በመተው ከማዕከል እስከ ወረዳ ድረስ የቡድን ትስስር (ኔትወርኪንግ) ፈጥረው መገኘታቸውን የግምገማ ቡድኑ ማረጋገጡን ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡

አላግባብ የሆነ ኔትወርክ በመዘርጋት፣ የጉራጌ ወጣት ማኅበርን ያለምንም ምክክር ብቻቸውን በማቋቋምና ከፍተኛ በሆነ የአቅም ማነስ ምክንያት አቶ ካሚል ሲገመገሙ፣ አቶ ልዑል ሰገድ ደግሞ አደራጅቶ ባለመምራት፣ ማለትም የኢሕአዴግን መዋቅር ባልተከተለ መንገድ መጓዝ፣ ብቁ ተሳታፊዎችን ማሸማቀቅና ምሁራንን አለማቅረብ በሚል መገምገማቸውን ምንጮቹ አረጋግጠዋል፡፡

ግምገማው ሁሉንም የቢሮ ኃላፊዎችና ምክትሎቻቸውን ያካተተ መሆኑን የገለጹት ምንጮቹ በርካቶቹ በማስጠንቀቂያ ሲታለፉ፣ ጥቂቶቹ የሥልጣን ሽግሽግና የመታገድ ዕጣ እንደደረሰባቸው ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ አስተዳደርና ምክትል ከንቲባና የማስታወቂያ ቢሮ ኃላፊው አቶ ከፍያለው አዘዘ ምትክም ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊና በአሁኑ ጊዜ የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ አባተ ስጦታው መሾማቸውን ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡ አቶ ከፍያለው በአዲስ አበባ አስተዳደር ውስጥ ከላይ እስከታች ድረስ ተገቢ ያልሆነ ኔትወርክ በመዘርጋታቸው መገምገማቸውና ለያዙት ቦታ ብቁ እንዳልሆኑ ተገልጿል፡፡

አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የአስተዳደሩ ከፍተኛ ሹም ለሪፖርተር እንደ ገለጹት፣ ግምገማው የተጀመረው አሁን አይደለም፡፡ ከሰኔ ወር 2003 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ጊዜያት የተደረገ ነው፡፡ አሁንም አልተጠናቀቀም፡፡ እስከ ወረዳ ድረስ ቀጥሏል፡፡ ግምገማው በአንድ ነገር ላይ ያነጣጠረና ብልሹ አሠራር ላይ ብቻ ያተኮረ አይደለም፡፡
ችግር ያለባቸው ራሳቸው አመልክተውና አስታውቀው በሚችሉት ሙያ እንዲመደቡ ጠይቀዋል፡፡ በክፍለ ከተማና በወረዳ እየሠሩ ያሉ፣ ነገር ግን ብቃት ያላቸውና ለማዕከል መመደብ የሚችሉትም እንዲመደቡ ይደረጋል፡፡ ለምሳሌ በከተማው ሥራ አስኪያጅ ጽሕፈት ቤት ሥር ያለው የውኃ፣ የፅዳትና የውበት ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ የነበሩበት አቶ ዓለሙ ዘበርጋ ሁለት ዓመት ሠርተው ‹‹በቃኝ መልሱኝ›› በማለታቸው ቀድሞ ወደነበሩበት የማስተማር ሥራ ተመልሰዋል፡፡

‹‹ምንግዜም ቢሆንም ቀልብ የሚስበው የላይኛው ክፍል ወይም ትላልቁ ሹማምንት ላይ ሲደርስ ብቻ ገኖ ይታያል፤›› ያሉት ሹሙ፣ አስተዳደሩ ተከታታይ ውይይቶችንና ግምገማዎችን በማድረግ ውሳኔዎችን አስተላልፎ በመጨረሻ ለሕዝቡ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡

በሞትና በዕድሜ ልክ እስር እንዲቀጡ የተወሰነባቸው 16 የደርግ ባለሥልጣናት ተፈቱ

Wednesday, October 5th, 2011

በዘር ማጥፋት ወንጀል ተከሰው በሞትና በዕድሜ ልክ እስር እንዲቀጡ ከተወሰነባቸው የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል 16ቱ ተፈቱ፡፡

በዘር ማጥፋት ወንጀል ከተከሰሱት 23 ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል 20 ዓመት በእስር ያሳለፉት 16 ባለሥልጣናት በአመክሮ በትናንትናው ዕለት ተፈትተዋል፡፡

ትናንትና የተፈቱት ባለሥልጣናት የቀድሞው የደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ፣ ምክትል ፕሬዚዳንት ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ፣ ሻምበል ለገሰ አስፋው፣ ኮሎኔል እንዳለ ተሰማ፣ ሜጀር ጀነራል ውብሸት ደሴ፣ ሌተና ኮሎኔል ናደው ዘካሪያስ፣ መቶ አለቃ ጴጥሮስ ገብሬ፣ መቶ አለቃ ስለሺ መንገሻ፣ ሻለቃ ደጀኔ ወንድማገኘሁ፣ አቶ እሸቱ ሸንቁጤ፣ አቶ ልሳኑ ሞላ፣ ብርጋዴር ጄነራል ለገሰ በላይነህ፣ አቶ ገስግስ ገብረ መስቀል፣ አቶ አበበ እሸቱ፣ አቶ በሪሁን ማሞና መቶ አለቃ ደሳለኝ በላይ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹም ባለሥልጣናት 20 ዓመት ሲሞላቸው ጊዜያቸውን ጠብቀው ይለቀቃሉ ተብሏል፡፡

ባለፈው ዓመት ታህሳስ ወር በወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነየሱስ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንና በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሃይማኖት መሪዎች፣ በደርግ ዘመን የተፈጸመው በደልና ጥፋት፣ በአገራዊ ይቅርታና እርቅ እንዲጨረስና ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ የእርቁና የይቅርታው ተካፋይ እንዲሆን ጥሪ አቅርበው ነበር፡፡ በወቅቱ ባለሥልጣናቱ የፈጸሙዋቸውን የተለያዩ ወንጀሎች በማመን እግዚአብሔርን፣ ሕዝብንና መንግሥትን ይቅርታ መጠየቅ እንደፈለጉ የሃይማኖት መሪዎቹ አስታውቀው ነበር፡፡ የእርቅና የሰላም ሥራ የአገሪቱ የተሀድሶ አንዱ አካል በመሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት አካላት እንዲያውቁት መደረጉን የገለጹት የሃይማኖት መሪዎቹ፣ በዘመኑ የተፈጸመው በደል ፈጣሪንም፣ ሰውንም ያሳዘነ እንደነበር በመግለጽ ምሕረትንና ይቅርታን መጠየቅ እንደሚገባ አሳስበው ነበር፡፡

ከአራቱም የሃይማኖት ተቋማት የተውጣጣ ዓብይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ለሁለት ዓመታት መሥራቱን የገለጹት የሃይማኖት መሪዎቹ፣ በዘመኑ ጥፋት ሰለባ ከነበሩ ማኅበራት ጋር በመመካከር መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸው ነበር፡፡ ሆኖም የሃይማኖት መሪዎቹ የይቅርታና የእርቅ ጥያቄ ከተለያዩ አካላት ተቃውሞ ገጥሞት ነበር፡፡ በተለይም በደርግ ሥርዓት ተጐጂ ከነበሩና ከተጐጂ ቤተሰቦች የሃይማኖት መሪዎቹ የጀመሩት የይሁንታና የይቅርታ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡

በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ የባሥልጣናቱ ከእስር የመፈታት ጉዳይ ዘጠኝ ወራትን ካሳለፈ በኋላ፣ 16ቱ ባለሥልጣናት ትናንትና ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ወጥተዋል፡፡ ከባለሥልጣናቱ መካከል በደርግ ዘመን የደኅንነት ሚኒስትር የነበሩት ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ይታወሳል፡፡

በማዕከላዊ እስር ቤት ደበበ እሸቱን ጨምሮ 78 የሽብር ተጠርጣሪዎች ታስረው ይገኛሉ

Sunday, October 2nd, 2011

(ሪፖርተር) — የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) አባል የሆኑት አቶ ኦልባና ሌሊሳና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ፣ በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ 78 ግለሰቦች በፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) መታሰራቸውን ማረጋገጡን የኢትዮጵያ ሰብዓዊነት መብት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ ኮሚሽኑ መስከረም 19 ቀን 2004 ዓ.ም ለሪፖርተር በላከው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፣ መስከረም 3 ቀን 2004 ዓ.ም በዋና ኮሚሽነሩ አምባሳደር ጥሩነህ ዜና የተመራው ቡድን የምርመራ ማዕከሉን በጎበኘበት ወቅት፣ ከሦስት እስከ 12 የሚደርሱ ተጠርጣሪዎች የሚያርፉባቸው 11 ጠበብ ያሉ ክፍሎችንም ጎብኝቷል፡፡

በቅርቡ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉትን ተጠርጣሪዎች የጎበኘው ቡድኑ፣ ተጠርጣሪዎቹ የሚያርፉባቸው ክፍሎች ጠባብ ቢሆኑም፣ መጨናነቅ እንደማይታይና በቂ ብርሃን ማስገባት የሚችሉ መሆኑን መመልከቱንና ከተጠርጣሪዎቹም መረዳቱን አስታውቋል፡፡

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል የመድረክ አባል የሆኑትን አቶ በቀለ ገርባና አቶ ኦልባና ሌሊሳን አነጋግሮ እንደተረዳው፣ በፍርድ ቤት መያዢያ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን፣ በሕገ መንግሥቱ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ፍርድ ቤት መቅረባቸውንና አካላዊ ድብደባም ሆነ የማሰቃየት ተግባር እንዳልተፈጸመባቸው እንደነገሩት አስታውቋል፡፡

የቀድሞው የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ አመራር የነበረው አርቲስት ደበበ እሸቱ ግን ቤተሰቦቹን በበቂ ሁኔታ እያገኘ እንዳልሆነ መግለጹን ቡድኑ አልደበቀም፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የተፋጠነ ፍትሕ እያገኙ እንዳልሆነ ከመግለጻቸውም በተጨማሪ፣ ኮሚሽኑም መሻሻል እንዳለበት መገንዘቡን የኮሙዩኒኬሽን ኢንፎርሜሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ ብርሃኑ አባዲ ገልጸዋል፡፡

የምርመራው ሒደት መጓተት እንደሚታይበትና መሻሻል እንዳለበት ኮሚሽኑ ገልጾ፣ ከምርመራ ክፍሉ ኃላፊ ኮማንደር ረታ ተስፋዬ ጋር በተደረገው ውይይት አርቲስት ደበበ ያነሳው ቅሬታም ሆነ ሁሉም ነገር እንደሚሻሻል ቃል መገባቱን አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ጥሩነህ ዜና የተመራው ቡድን ጉብኝት ሲያደርግ ለምን ጋዜጠኞችን መጋበዝ እንዳልፈለገ አቶ ብርሃኑ ተጠይቀው፣ ‹‹ጋዜጠኛ ይዞ መሄዱ ጥቅም የለውም አይባልም፡፡ የኮሚሽኑ ዓላማ ግን ጉብኝት አድርጎ ለየሚዲያዎቹ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት በመሆኑ አላስፈለገውም ነበር፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በዕለቱ በተደረገው ጉብኝት ያለፖሊስ ጥበቃ በነፃነት የመጎብኘትና ተጠርጣሪዎችን ማነጋገር መቻሉን፣ ተጠርጣሪዎቹ አጋጠመን ያሉትንና እየተደረገላቸው ያለውን ነገር ሁሉ በግልጽነት ለቡድኑ መንገራቸውን አቶ ብርሃኑ አክለዋል፡፡