Author Archive
ዶክተር ዮናስ አድማሱ ዐረፈ
Friday, February 8th, 2013አቡነ ሺኖዳ ሞታቸው ለግብጽ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን መላውን ዓለም የጎዳ ነው
Monday, March 26th, 2012ነፍስ ኄር ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ 3ኛን ቀርቤ የማየት ዕድል ያገኘሁት የዛሬ ዓመት ነበር፡፡ ግብጽ ካይሮ በሚገኘው አባስያ መንበረ ፓትርያርክ ግቢ ውስጥ፡፡ በመንበረ ፓትርያርኩ ግቢ አራት አብያተ ክርስቲያናት ሲገኙ ትልቁ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል ነው፡፡ ያሠሩት ከአቡነ ሺኖዳ በፊት የግብጽ ፓትርያርክ የነበሩት አቡነ ቄርሎስ 6ኛ ሲሆኑ ቅዳሴ ቤቱ የተከበረውም በ1968 ዓም ነው፡፡ እኛም ኢትዮጵያውያን በንጉሥ ኃይለ ሥላሴ በኩል አስተዋጽዖ ያደረግንበት ካቴድራል ነው፡፡
እኔ ግብጽ ስገባ በሀገሪቱ የተቀሰቀሰው አብዮት ሙባረክን አውርዶ ከፍተኛውን ወታደራዊ ምክር ቤት ተክቶ ነበር፡፡ ያም ቢሆን ግን የታሕሪር አደባባይ አሁንም ከአብዮቱ ውጥረት ነጻ አልነበረም፡፡ በተለየም ከዓርብ የጁምዐ ስግደት በኋላ ወደ ታሕሪር ማምራት የወቅቱ ልማድ ነበር፡፡
በየአካባቢው ከፍተኛ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ ታላላቅ መሥሪያ ቤቶች በወታደሮች ጥበቃ ይደረግባቸዋል፡፡ አብያተ ክርስቲያናትም እንዲሁ፡፡ የገናን በዓል ለማክበር በተሰበሰቡ ክርስቲያኖች ላይ ፈንጅ ተጠምዶ ብዙዎቹን ከገደለ በኋላ በየአብያተ ክርስቲያናቱ የሚደረገው ጥበቃ እና ፍተሻ ጠበቅ ብሏል፡፡
በጠዋቱ ቁርስም አልቀመስን፡፡ በግብጽ ቤተ ክርስቲያን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወኪል የሆኑት አባ ገብረ ሕይወት ወይንም ግብጻውያን እንደሚጠሯቸው አቡነ ሐያት ከፖፕ ሺኖዳ ጋር የተያዘው ቀጠሮ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት መሆኑን ትናንት ማታ ነግረውናል፡፡
እኛ ያረፍነው መዲናት ናስር ከሚገኘው የቅድስት ድንግል ማርያም እና የቅዱስ አትናቴዎስ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ ነው፡፡ ከቤተ ክርስቲያኑ አጠገብ የእንግዶች ማረፊያ ባለ አራት ፎቅ ሕንፃ አለ፡፡ እኛ ሁለተኛው ፎቅ ላይ ነው ያረፍነው፡፡
ከመዲናት ናስር ወደ መንበረ ፓትርያርኩ ወደ አባስያ ለመጓዝ የተጨናነቀውን የካይሮ ትራፊክ ማለፍ ይጠይቃል፡፡ እዚህ ሀገር መኪናው ከሰው ቁጥር ይበዛል፡፡ እስካሁን የትራፊክ መብራት ሲበራ እንጂ በመብራት መኪና ሲቆም አላየሁም፡፡ ጡሩንባ እየነፉ መጓዝ ብቻ ነው፡፡ መኪኖቹ ጡሩንባ እንጂ ፍሬን ያላቸው አይመስሉም፡፡
የመንበረ ፓትርያርኩ አካባቢ በወታደሮች እየተጠበቀ ነው፡፡ ወደ ግቢው የምትገቡት በደኅንነት መፈተሻ ሳጥኑ በኩል አልፋችሁ ነው፡፡ ከግቢው ሰፊውን ክፍል የያዘው ቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል ሲሆን የፓትርያርኩ መኖርያ በካቴድራሉ ፊት ለፊት፣ ከዋናው መግቢያ ጀርባ ይገኛል፡፡
ይህ መንበረ ፕትርክና የተገነባበት ቦታ ጥንት የግብጻውያን ክርስቲያኖች መቃብር የነበረበት ቦታ ነው፡፡ ቦታው ለቤተ ክርስቲያኒቱ የተሰጠው በ969 ዓም ለቤተ መንግሥቱ መሥሪያ ተብሎ በተወሰደባት ቦታ ምትክ ነው፡፡ በቦታው ላይ ጥንታዊው የአባ ሮዩስ ቤተ ክርስቲያን ነበረበት፡፡
በ12ኛው መክዘ በአካባቢው 12 አብያተ ክርስቲያናት ነበሩ፡፡ በ1280 ዓም አብያተ ክርስቲያናቱ ተቃጠሉ፡፡ ከዚያም በቦታው ሁለት አብያተ ክርስቲያናት ተሠሩ፡፡
ወደ መንበረ ፕትርክናው ልትደርሱ ስትሉ ከግራ እና ከቀኝ ተራራ የሚያህሉ ሁለት ውሾች አሉ፡፡ በቅርብ ጊዜያት በግብፃውያን ክርስቲያኖች ላይ አደጋዎች እየበዙ ሲመጡ ለጥበቃ የገቡ የመንግሥት ፈታሾች ናቸው አሉን፡፡
ወደ ውስጥ ስንዘልቅ አያሌ እንግዶች ተኮልኩለዋል፡፡ ወደ እንግዶች መጠበቂያ ቤት ወሰዱንና አንድ ሠላሳ ደቂቃ ተቀመጥን፡፡ ከዚያም ወደ ልዩ ጸሐፊያቸው ወደ አቡነ ኤርምያስ ቢሮ ገባን፡፡
ፖፕ ሺኖዳ ሦስት ልዩ ጸሐፊዎች አሏቸው፡፡ ሦስቱም ኤጲስ ቆጶሳት ናቸው፡፡ ሃያ ደቂቃ ያህል በልዩ ጽሕፈት ቤቱ ካረፍን በኋላ ተራችን ደርሶ ገባን፡፡
አቡነ ሺኖዳ አጭር ናቸው፡፡ መንበራቸውም እንደ እርሳቸው አጭር ነው፡፡ ጥቁሩን የጳጳሳት ልብስ ለብሰዋል፡፡ በእድሜ እና በአገልግሎት ብዛት መዳከማቸውን የፊታቸው ገጽታ ይመሰክራል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ረቡዕ እና ዓርብ በካይሮ እና በእስክንድርያ ምእመናኑን ማስተማራቸውን አልተውም፡፡ እኤአ ኦገስት 3 1923 ዓም በላዕላይ ግብጽ አስዩት አብኑብ በተባለ ቦታ የተወለዱት ሺኖዳ ዛሬ በሰማንያ ስምንተኛው እድሜ ላይ ይገኛሉ፡፡ የጻፏቸው ከአንድ መቶ በላይ መጻሕፍት በመንበረ ፓትርያኩ ቤተ መጻሕፍት ልዩ ቦታ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ወላጆቻቸው የሰጧቸው ስም ናዚር ጋዪድ የሚል ነበር፡፡ ገና በተወለዱ በጥቂት ቀናት ውስጥ እናታቸውን ያጡት ሺኖዳ ከአምስት እኅቶቻቸው እና ከሁለት ወንድሞቻቸው ጋር ብቻቸውን ቀሩ፡፡ የመጀመርያውን ትምህርት በዳማንሁር ባንሐ ካይሮ የተከታተሉ ሲሆን ከካይሮ ዩኒቨርሲቲ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በታሪክ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋ ወሰዱ፡፡
ከዚያም ከኮፕቲክ ሴሚናሪ በነገረ መለኮት የመጀመረያ ዲግሪ አግኝተው በዚያው ሴሚናሪ የብሉይ እና የሐዲስ ኪዳን መምህር ሆኑ፡፡ የግብጽ ቤተ ክርስቲያንን ከድካም ያበረታት ሐቢብ ጊዮርጊስ የሰንበት ት/ቤቶችን እንቅስቃሴ ሲጀምር ዋናው የተልዕኮው አንቀሳቃሽ ሺኖዳ ነበሩ፡፡ እርሳቸው በዚያ ወቅት የኮፕቲክ ወጣቶች ኅብረትን መሠረቱ፡፡ ለሰንበት ት/ቤቶች መጽሔቶች የተለያዩ ጽሑፎችን በማበርከት ወጣቱን ያበረቱት ነበር፡፡ በኋላ ዘመን የመንፈስ አርነት (The release of the Sprit) ተብሎ የታተመው መጽሐፋቸው የእነዚህ መጣጥፎች ስብስብ ነው፡፡
በሐምሌ 18 ቀን 1954 ዓም እኤአ በዋዲ ኤል ናትሩን ወደሚገኘው የሶርያውያን ገዳም ገብተው ምንኩስናን ተቀበሉ፡፡ የገዳሙ አበ ምኔት እንጦንስ የሚል ስም ሰጧቸው፡፡ በዚያ ገዳም ሺኖዳ አያሌ ቀደምት የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትን ማንበባቸው ይነገራል፡፡ በመነኮሱ በዓመታቸው ክህነት ተቀብለው ቄስ ሆኑ፡፡
ሺኖዳ ከምንም በላይ ለምንኩስና እና ለምናኔ ሕይወት ልዩ ትኩረት አላቸው፡፡ በእርሳቸው ዘመን በግብጽ የነበሩት እና ለግብጻውያን ገዳማዊ ሕይወት እንደገና ማንሠራራት ታላቅ አስተዋጽዖ ያደረጉት የኢትዮጵያዊው አብዱል መሲሕ (ገብረ ክርስቶስ) ደቀ መዝሙር ነበሩ፡፡ የገብረ ክርስቶስን ፍጹማዊ መንገድም ለመከተል ይጥሩ ነበር፡፡ በዚህም የተነሣ ለብዙ ዓመታት የኖሩትም በተባሕትዎ ነበር፡፡ መጀመርያ ከገዳሙ ሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ አንድ ዋሻ ውስጥ ተቀመጡ፤ በመቀጠልም ከገዳሙ ዐሥር ኪሎ ሜትር ወደ ሚርቅ እና በባሕር አል ፋሪግ ወደሚገኝ ዋሻ ገብተው ተጋድሎዋቸውን ቀጠሉ፡፡
ባሕታዊው (The Hermit) የተሰኘውንና በኋላ እኤአ በ1954 የታተመውን ቅኔያቸውን የጻፉት በዚህ ጊዜ ነበር፡፡
በ1959 እኤአ ቄርሎስ ስድስተኛ ልዩ ጸሐፊያቸው አድርገው ሾሟቸው፡፡ ሺኖዳ ግን ደስተኛ አልነበሩም፡፡ ከገዳማቸው መውጣት እና በኣታቸውን መልቀቅ አያስደስታቸውም ነበር፡፡ ብዙ ጊዜያቸውንም የሚያሳልፉት በዋሻቸው ውስጥ በጸሎት እና ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ ነበር፡፡ ለብዙ ጊዜያትም ወደ ኤጲስ ቆጶስነት እንዳይጠሩ ሲከላከሉ ኖረዋል፡፡
በ1962 እኤአ ሺኖዳ በነበሩበት ገዳም ውስጥ አንድ አስተዳደራዊ ችግር ተፈጠረ፡፡ ጉዳዩም ወደ ፓትርያርክ ቄርሎስ ስድስተኛ ዘንድ ቀረበ፡፡ በዚያ ጊዜ ሺኖዳ በገዳሙ አስተዳደር ውስጥ ነበሩበት፡፡ ገዳማውያኑ እንደ ጥንቱ አበው ሆነው እንዲኖሩ፣ ገዳማት የችግር ቦታዎች ሳይሆኑ የጸሎት ቦታዎች እንዲሆኑ፤ የግብጽ ገዳማት አዲሱን ትውልድ ለመቀበል በሚችሉበት መንገድ እንዲደራጁ፤ ገዳማውያኑ ሥራ፣ ጸሎት እና ትምህርትን አጣምረው እንዲይዙ ይታገሉ ነበር፡፡ ይህ የሺኖዳ ሃሳብ ያልተስማማቸው አንዳንድ ገዳማውያንም ሺኖዳን ከስሰው ወደ ቄርሎስ ዘንድ አቀረቧቸው፡፡
አቡነ ቄርሎስ ስድስተኛ ሺኖዳን አስጠሯቸው፡፡ ሺኖዳ በቄርሎስ እግር ሥር ተደፍተው «አጥፍቻለሁ፣ ድሮም ኃላፊነቱን የተቀበልኩት ያለ ዐቅሜ ነው፡፡ እባክዎ ከኃላፊነት ያንሱኝና በዋሻዬ ብቻ ተወስኜ ልኑር፡፡ እኔ ደካማ ሰው ነኝ» ሲሉ ለመኗቸው፡፡
ቄርሎስም «ዛሬ እንደርና ነገ ውሳኔዬን አሳውቃለሁ» አሉ፡፡
በማግሥቱ መስከረም 30 ቀን 1962 ዓም እኤአ ፓትርያርክ ቄርሎስ እና ሌሎች ጳጳሳት የሺኖዳን ጉዳይ ለማየት በመንበረ ፓትርያርኩ ተሰባሰቡ፡፡ ሺኖዳ ውሳኔውን በጉጉት ነበር የጠበቁት፡፡ ኃላፊነት ከሚባለው ነገር ተገላግለው የምናኔ ሕይወታቸውን ብቻ ለመያዝ ፈልገዋል፡፡
ሺኖዳ ተጠሩ፡፡ ጳጳሳቱ ቆሙ፡፡ ሁሉም ቄርሎስን ያይ ነበር፡፡ ሺኖዳ እንዲንበረከኩ ተነገራቸው፡፡ ተንበረከኩ፡፡ ቄርሎስ እጃቸውን በሺኖዳ ላይ ጫኑ፡፡ ሌሎች ጳጳሳትም ወደ እርሳቸው መጡ፡፡
ሳይታሰብ አቡነ ሺኖዳ ተብለው የግብጽ የመንፈሳውያን ኮሌጆች እና የትምህርት ተቋማት ጳጳስ ሆነው ተሾሙ፡፡ ሺኖዳ ደነገጡ፡፡ አለቀሱም፡፡
በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ላይ ጥናት በማድረግ የታወቀው የካይሮ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሩ ጀርመናዊው ኦቶአ ሜናድረስ የአቡነ ሺኖዳን መሾም ሲሰማ እንኳን ደስ ያለዎት የሚል ደብዳቤ ላከላቸው፡፡ ሺኖዳ ግን የመለሱለት የሚከተለውን ነበር:
«የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እና ሰላም ካንተ ጋር ይሁን፡፡ እንኳን ደስ ያለዎት ብለህ በቅንነት ስለላክህልኝ መልእክት አመሰግንሃለሁ፡፡ ያንተን ወዳጅነት እና ፍቅር መቼም አልዘነጋውም፡፡ እውነቱን ለመናገር ግን ለእኔ መላክ ያለበት የኀዘን ደብዳቤ እንጂ የደስታ ደብዳቤ አይደለም፡፡ አንድ መነኩሴ ጸጥታ የተሞላበትን የጸሎት በረሃ ለቅቆ ጫጫታ እና ሁካታ በተሞላበት ከተማ እንዲኖር ሲደረግ እንዴት እንኳድ ደስ ያለህ ይባላል? ማርያምን ከክርስቶስ እግር ሥር ተነሥታ ማርታን ልታግዝ ወደ ጓዳ ስትገባ ማነው እንኳን ደስ ያለሽ የሚላት? ለእኔ ይህ ደስታ ሳይሆን ሀፍረት ነው፡፡ እኔ ኤጲስ ቆጶስ ሆኜ የተሾምኩበትን ቀን በደስታ ሳይሆን በኀዘን እና በለቅሶ ነው የማስታውሰው፡፡ ብሕትውና እና የተጋድሎ ጸሎት ከምንም በላይ የሚበልጥ ነገር ነው፡፡ ብሕትውና እና ምናኔ ከኤጲስ ቆጶስነት ቀርቶ ከፓትርያርክነት ጋር እንኳን የሚወዳደር አይደለም፡፡
«ወዳጄ ሆይ እውነተኛው ቅድስና ሲመት ሳይሆን ልብን ቤተ መቅደስ አድርጎ ለክርስቶስ መቀደስ ነው፡፡ ክርስቶስ በመጨረሻው ቀን የልባችንን ንጽሕና እንጂ የክህነታችንን መዓርግ አይጠይቀንም፡፡ ይህንን ደብዳቤ የምጽፍልህ በምወድዳት ዋሻዬ፣ በባሕር አል ፋሬግ፣ በዋዲ ኤል ናትሩን ውስጥ ሆኜ ነው፡፡ እዚህም እስከ ጥምቀት ድረስ ለመቆየት አስባለሁ፡፡ ከዚያም ወደ ካይሮ እመለሳለሁ፡፡»
አቡነ ሺኖዳ እያለቀሱ ያቺን የዋዲ ኤል ናትሩን ዋሻ ትተው ካይሮ ቢመጡም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ወደ ዋሻቸው መሄድ ያዘወትሩ እንደ ነበር ታሪካቸውን የጻፈላቸው የቅርብ ወዳጃቸው እና በእምነቱ ፕሮቴስታንት የነበረው ኦቶአ ሜናድረስ ይናገራል፡፡
እስከ 1969 እኤአ ድረስ የቤተ ክርስቲያኒቱን የትምህርት ተቋማት በዘመናዊ መልኩ አደራጇቸው፡፡ በዚህ የተነሣም በሙሉ ጊዜያቸው የሚማሩ ተማሪዎች ቁጥር ከአንድ መቶ ወደ 207 አደገ፡፡ ሺኖዳም በየሳምንቱ ዓርብ ዓርብ ሕዝቡን የሚያስተምሩበት እና የሕዝቡን ጥያቄዎች የሚመልሱበት የትምህርት መርሐ ግብር ከፈቱ፡፡ እስከ አሥር ሺ የሚጠጋ ሕዝብም መርሐ ግብሩን ይከታተለው ነበር፡፡ ለሰንበት ትምህርት ቤቶች የሚሆኑ መጻሕፍትን፣ መዝሙሮችን እና ትምህርቶችን ያዘጋጁ ነበር፡፡ የሰንበት ትምህርት ቤት መምህራንንም ያሠለጥኑ ነበር፡፡ በዚህ የሥራ ብዛት ውስጥ እያሉ እንኳን የሳምንቱን ግማሽ በካይሮ ቀሪውን ደግሞ በገዳማቸው ዋሻ ውስጥ ያሳልፉ ነበር፡፡
በዚሁ ዓመት ሺኖዳ የመካከለኛው ምሥራቅ የነገረ መለኮት ተቋማት ማኅበር ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ፡፡ቤተ ክርስቲያኒቱን ከሌሎቹ ጋር የማቀራረቡን ሥራ የጀመሩት ገና በጳጳስነታቸው ዘመን ነው፡፡ በእርሳቸው መሪነት ቤተ ክርስቲያኒቱ በአያሌ የነገረ መለኮት ውይይቶች ላይ ተሳትፋለች፡፡
ፓርትያርክ ቄርሎስ በመጋቢት 9 ቀን 1971 ዓም ዐረፉ፡፡ በመጋቢት 22 የተሰበሰበው የግብጽ ሲኖዶስም ተተኪውን ለመምረጥ ዝግጅት ጀመረ፡፡ አምስት እጩዎችንም መረጠ፡፡ ነገር ግን በመካከሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ አያሌ ፈተናዎች ገጠሟት፡፡ በዚህም ምክንያት ፓትርያርክ ሳይመረጠ ረዥም ጊዜ ቆየ፡፡ በጥቅምት 29 ቀን የተሰበሰበው ቅዱስ ሲኖዶስ የእጩዎችን ቁጥር ወደ ሦስት ዝቅ አደረገው፡፡ የሦስቱም እጩዎች ስም በመንበረ ማርቆስ ካቴድራል መንበር ላይ ተቀመጠ፡፡ ሕዝቡ እና ገዳማውያኑም ለሦስት ቀን ሱባኤ ያዙ፡፡
ጥቅምት 31 ቀን 1971 እኤአ በሰንበት ዕለት ሕዝቡ፣ ካህናቱ፣ ገዳማውያኑ እና ጳጳሳቱ በተገኙበት ጸሎት ከተደረሰ በኋላ አንድ ዓይኑን በሻሽ ለተሸፈነ አይማን ሙኒር ካሊል የተባለ ሕፃን በመንበሩ ላይ የተጸለየባቸው ስሞች ቀረቡለት፡፡ እጁን ዘርግቶ አንዱን ዕጣ አወጣው፡፡ በወቅቱ ቤተ ክርስቲያኒቱን በጊዜያዊነት ይመራ የነበረው ኮሚቴ ሊቀ መንበር ለሆኑት ለሜትሮጶሊጣን አንቶኒዮስም ሰጣቸው፡፡
ወረቀቱን ዘረጉት፡፡ «እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያናችን አባት ይሆኑ ዘንድ አቡነ ሺኖዳን መርጧል» ሲሉ አካባቢው በጭብጨባ እና በእልልታ ተናጋ፡፡ ከሁለት ሳምንት በኋላ የዛሬ ዐርባ ዓመት ኅዳር 14 ቀን 1971 እኤአ በቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል፣ ሺኖዳ 3ኛ 117ኛው የግብጽ ፓትርያርክ ተብለው ተሾሙ፡፡
በእራሳቸው ዘመን ቤተ ክርስቲያኒቱ እንደገና ኃይል አገኘች፡፡ አሁንም በነገረ መለኮት ኮሌጅ ያስተምራሉ፡፡ የኮሌጁ ዲንም ነበሩ፡፡ የኤልኬራዛ መጽሔት አዘጋጅ ናቸው፡፡ ዓርብ ዓርብ ያስተምራሉ፡፡ ገዳማትን እና ትምህርት ቤቶችን አስፋፉ፡፡ ወጣቱን ወደ አገልግሎት ጠሩ፡፡
አሁንም በፓትርያርክነታቸው ዘመን በአባ ቢሾይ ገዳም የሳምንቱን ግማሽ በገዳማዊ ሕይወት ማሳለፋቸውን አልተውም፡፡ መጻሕፍትን ይጽፋሉ፡፡ በውጭ እና በሀገር ውስጥ ያለውን ሕዝብ ይጎበኛሉ፡፡ እርሳቸው ሲሾሙ በውጭ ያሉት አጥቢያዎች ሰባት ብቻ ነበሩ፡፡ አሁን ግን በአሜሪካ እና ካናዳ የሚገኙትን አብያተ ክርስቲያናት እንኳ ከሰማንያ በላይ አድርሰዋቸዋል፡፡ በአውስትራልያ 26፣ በአውሮፓ 30 አጥቢያዎች ይገኛሉ፡፡
ሺኖዳ ለአቋማቸው እና ለእምነታቸው ሲሉ ስደትን የቀመሱ ፓትርያርክ ነበሩ፡፡ አንዋር ሳዳት የግብጽ መሪ በነበረ ጊዜ በቤተ ክርስቲያኒቱ እና በምእመናኗ ላይ የሚደርሰውን መከራ በመቃወም ሺኖዳ ደጋግመው ይናገሩ ነበር፡፡ በዚህ ያልተደሰተው ሳዳት መስከረም 3 ቀን 1981 እኤአ ባወጣው ዐዋጅ ሲኖዳን ከመንበራቸው አሳደዳቸው፡፡ በግዞትም ወደ አባ ብሶይ ገዳም ተላኩ፡፡
ሕዝቡ ሌላ አባት አንመርጥም ብሎ ተከትሏቸው አባ ብሶይ ገዳም ገባ፡፡ እዚያም በሚወዱት ገዳም ተጋድሏቸውን እና ትምህርታቸውን ቀጠሉ፡፡ በገዳሙ በግዞት ለአራት ዓመት ተኩል ከቆዩ በኋላ ሳዳት ሞቶ ሙባረክ ሲተካ በጥር 2 ቀን 1985 እኤአ ወደ መንበራቸው ተመለሱ፡፡
ሺኖዳ ቀልድ ዐዋቂ ናቸው፡፡ በተለይ ሕፃናትን ማስተማር ይችሉበታል፡፡ ሕዝቡን ሲያስተምሩም ቀልድ እና ታሪክ ጣል ማድረግ ይወዳሉ፡፡ ሴቶች በቤተ ክርስቲያን የነበራቸውን የአገልግሎት ተሳትፎ በማሳደግም ሺኖዳ ከፍተኛ ለውጥ አምጥተዋል፡፡ ሺኖዳ ለሀገራቸው ያላቸው ፍቅር ልክ የለውም፡፡ «በልባችን ውስጥ ያለችው ግብጽ ከምናያት ግብጽ ትበልጣለች» የሚለው አባባላቸው በግብጻውያን ልብ ለዘለዓለም ታትሞ ቀርቷል፡፡ ክርስቲያን እና ሙስሊሙ ሕዝብ ተከባብሮ እና ተባብሮ እንዲኖር በብርቱ ጥረዋል፡፡
በዐርባ ዓመት አገልግሎታቸው ከአንድ መቶ በላይ መጻሕፍትን ጽፈዋል፡፡ ንግግር ዐዋቂ፣ ባለ ቅኔ፣ ሰባኪ እና ደራሲ ናቸው ሲኖዳ፡፡ እንደዚህ ያለ ታላቅ ሰው በሀገራችን ሲሞት «አራት ሰው ሞተ ይባላል፡፡ እኔም
አራት ሰው ሞተ ደረሰና ጥሪ
ደራሲ፣ ሰባኪ፣ ጳጳስ እና መሪ
ያልኩት ለዚህ ነበር፡፡
በሙስሊሞች፣ በፕሮቴስታንቶች እና በካቶሊኮች ዘንድ የሚወደዱ እና የሚከበሩ አባት ሆነዋል፡፡ የታላቁ የአልአዝሐር መስጊድ ኢማም የፖፕ ሺኖዳን ሞት ተከትሎ «ግብጽ እኒህን ጥበበኛ ሰው በምትፈልግበት ወሳኝ ጊዜ እርሳቸውን ማጣታችን የሚያንገበግብ ነው» ነበር ያሉት፡፡
ሞታቸው ለግብጽ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን መላውን ዓለም የጎዳ ነው፡፡ ተወዶ የሚኖርና ተለቅሶለት የሚቀበር የሃይማኖት መሪ በዓለም ላይ እየጠፋ ባለበት በዚህ ጊዜ ሺኖዳ በሕይወታቸውም በሞታቸውም ያስተማሩ አባት ሆነዋል፡፡
እነሆ ፊት ለፊታቸው ቆሜ ዝም ብዬ አያቸዋለሁ፡፡ የተቀመጡበት መንበር ይህንን ያህል የተብለጨለጨ አይደለም፡፡ አንዳች የሚስብ ነገር ግን አለው፡፡ የርሳቸውም ልብስ ከመደበኛው የመነኮሳት ልብስ የዘለለ ልዩ ጌጥ የለውም፡፡ አንዳች ነገር ግን ረቦበታል፡፡
ከእርሳቸው ጋር ፎቶ ለመነሣት አስፈቅጄ ስቀርብ የወጣቱን እንቅስቃሴ በተመለከተ ጠየቁኝ፡፡ እኔም በአጭሩ ነገርኳቸው፡፡ «እንደ አባቶቻችሁ ለእግዚአብሔር ብቻ ስትሉ አገልግሉ፡፡ የናንተ አባቶች ለእግዚአብሔር ብቻ ሲሉ የሚያገለግሉ ነበሩ» አሉ፡፡
ስንለያቸው ለእያንዳንዳችን ፊርማቸው ያረፈበት ስጦታ ሰጡን፤ ከዚያም
«አሁን ለሕክምና ወደ አሜሪካ በቅርብ እጓዛለሁ፡፡ እግዚአብሔር ጤና እንዲሰጠኝ እና በሚገባ እንዳገለግል ጸልዩልኝ» አሉ ሺኖዳ፡፡
ወይ አልጸለይንላቸውም፣ ወይም ጸሎታችን አልረዳቸውም መሰል ባገኘናቸው በዓመቱ መጋቢት 8 ቀን 2004 ዓም ዐረፉ፡፡ በሚወዱት በአባ ብሾይ ገዳምም ተቀበሩ፡፡
በዝቋላ ገዳም የእሳት አደጋ መከላከል ጥረት ፖሊሶች እንቅፋት እየፈጠሩ ናቸው
Wednesday, March 21st, 2012የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በዝቋላ ገዳም ተገኝተው የአደጋ መከላከሉን ሥራ እያስተባበሩ ይገኛሉ፡፡ አሁን በስልክ እንደገለጡልኝ እሳቱን የመከላከሉ ተግባር በወጣቶቹ በሚገባ እየተሠራ ነው፡፡ በፈቃዳቸው እና በራሳቸው ቁሳቁስ በኢትዮጵያዊ እና ኦርቶዶክሳዊ ወኔ ወጣቱ ትውልድ ያደረገውን ሃይማኖታዊ ተግባር አድንቀዋል፡፡
የአካባቢው ፖሊሶች ተጨማሪ የሰው ኃይል አያስፈልግም፣ ያለው በቂ ነው በሚል ሌሎችን ተጓዦች ያገዱ ሲሆን፣ ተጓዦቹ እንደገለጡት የያዙት ምግብ ማለፍ ባለመቻሉ እየተበላሸ ነው፡፡ ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ከሚመለከታቸው ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመቅረፍ እየሞከሩ ነው፡፡ ቢያንስ ውኃው እና ምግቡ እንዲያልፍ ለማድረግ፡
ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በገዳሙ ተገኝተው ቅዳሴ በመቀደስ፣ በወጣቶቹ እና በፖሊስ መካከል ችግር በተፈጠረ ጊዜ በማረጋጋት፣ እንደ ወጣቱ እኩል እሳቱን ተጋፍጠው ያሳዩት አባትነት በቦታው በተገኙት ወጣቶች ዘንድ አድናቆት እና አክብሮት አትርፎላቸዋል፡፡
ዝቋላ ካለፉት ቀናት በተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ አልፎ አልፎ ገደሉ ሥር ከሚታየው ጭስ በስተቀር ይህ ነው የተባለ የጎላ እሳት አሁን የለም፡፡ ከየአካባቢው የሄዱት ወጣቶች ከገዳማውያኑ እና ከአደጋ መከላከል ባለሞያዎች ጋር በቅንጅት ባደረጉት ተጋድሎ ገዳሙን ከአደጋ ታድገውታል፡፡ ምንም እንኳን በአካባቢው ያለው ሙቀት ቀትር ላይ ሲጨምር የሚሆነው ባይታወቅም በአሁኑ ደረጃ ግን እሳቱ ከገደሉ በላይ እንዳይወጣ አካባቢውን የማጽዳት እና የእሳት መከላከያ የመሥራቱ ሥራ ተጠናክሯል፡፡
ዝቋላ እየነደደ ነው
Monday, March 19th, 2012ይህንን ጽሑፍ ስጽፍ እሳቱ ከተከላካዮች ዐቅም በላይ ሆኖ ወደ ገዳሙ በመዝለቅ ላይ ይገኛል፡፡ እሳቱ ገዳሙን ከወደ ሐይቁ በኩል እያጠቃው ነው፡፡ ከአዲስ አበባ እና ከደብረ ዘይት ተጉዘው በመከላከል ላይ የተሠማሩት ወገኖች ከዐቅማቸው በላይ እየሆነ ነው፡፡ እግዚአብሔር ካልረዳን ከሰዓታት በኋላ ታላቁን ገዳም እናጣዋለን፡፡
ውኃውን ከወንበር ማርያም ወደ ተራራው ለማውጣት መንግሥት የኡራል መኪኖችን እንዲተባበር የገዳሙ አበ ምኔት እየጠየቁ ነው፡፡ በስልክ ያገኘሁት እና በመከላከል ተግባሩ ላይ የተሠማራው ወንድም «አሁን ልንሸነፍ ነው፤ ታላቁንም ገዳም ልናጣው ነው፣ እሳቱ ፊት ለፊቴ እየመጣ ነው፡፡ እኛ መሸሽ እንችላለን፣ ገዳሙን ግን ምን እናደርገዋለን» ብሎኛል፡፡
(ኢሜይል dkibret@gmail.com)
የዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ደን በመንደድ ላይ ነው
Monday, March 19th, 2012ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት የሚገኘው የዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ደን በመንደድ ላይ መሆኑን የገዳሙ አባቶች እየተናገሩ ነው፡፡ እሳቱ መንደድ ከጀመረ ወደ ሃያ አራት ሰዓት ሊጠጋ ነው፡፡ መንግሥት ከአካባቢው የውኃ ቦቴዎችን እና ወታደሮችን በማንቀሳቀስ ውኃውን ለማጥፋት ጥረት እያደረገ ቢሆንም እሳቱ ግን ወደ ገዳሙ በመጠጋት ላይ ነው፡፡
አሁን አማራጫችን አንድ ብቻ ነው፡፡ የዝቋላን ገዳም ከማጣታችን በፊት ያለንን ነገር ሁሉ ይዘን በተገኘው ትራንስፖርት ወደ ዝቋላ መትመም ብቻ፡፡ ወንበር ማርያም ድረስ የውኃ ቦቴዎቹ ሊደርሱ ይችላሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ያለውን ባገኘነው ዕቃ ሁሉ ውኃውን ይዘን በመውጣት መረባረብ፡፡ ያለበለዚያ ግን የዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ወደ ታሪክነት ይቀየራል፡፡
እነሆ ክርስትናችን የሚፈተንበት፣ ኢትዮጵያዊነታችንም የሚለካበት ጊዜ መጣ፣ በእሳት ተቃጥለው ያቆዩትን ገዳም ከእሳት ማዳን ካልቻልን እንግዲህ የኛ መኖር ትርጉሙ ምንድን ነው?
መኪኖች ያሏችሁ አንቀሳቅሱ፣ ጉልበት ያላችሁ ተንቀሳቀሱ፣ ሌላም አማራጭ ያላችሁ በፍጥነት ተጓዙ፣እሳቱን በእምነት እንቅደመው፡፡
ዋልድባን መተሐራ፣ ስኳሩንም መራራ
Sunday, March 18th, 2012ዳንኤል ክብረት
[PDF]
ኢትዮጵያ ካሏት ጥንታዊ፣ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ቦታዎች ዋልድባ አንዱ ብቻ ሳይሆን ዋነኛው ነው፡፡ በሰሜን ጎንደር እና በምዕራብ ትግራይ ተንጣልሎ፣ ከሰሜን ተራራዎች ሠንሠለት ግርጌ ተዘርግቶ የሚገኘው ይህ ገዳም፣ በብዙ ወጣ ገባ መልክዐ ምድሮች እና ኮረብታዎች የተሞላ፣ አብዛኛውም በደን የተሸፈነ ነው፡፡ እንደ ኤዶም ገነት አራት ጅረቶች የሚያጠጡት ሲሆን ሴሞ በሰሜን፣ ተከዜ በምሥራቅ፣ ዘወረግ በምዕራብ፣ ዜዋ ደግሞ በደቡብ ያረሰርሱታል፡፡
የዋልድባ ገዳም ታሪክ ሳብ ብሎ ወደ መጀመርያው የክርስትና ዘመናት ይጓዛል፡፡ በ5ኛው መክዘ በአካባቢው በተባሕትዎ ይኖሩ የነበሩ መናንያን እንደነበሩበት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በ485 ዓም ከሰሜን ሸዋ የተነሡ ምእመናን ወደ አካባቢው ተጉዘው መጋቢት 27 ቀን ዋልድባ መግባታቸውን የቦታው ታሪክ ያሳያል፡፡ በ574 ደግሞ ሌሎች ከቡልጋ መጥተው ተቀላቅለዋቸዋል፡፡
በዘመነ ዮዲት ቦታው ከጠፋ በኋላ እንዲሁ ሲኖር አሁንም ለሦስተኛ ጊዜ ከሰሜን ሸዋ ቡልጋ የመጡ ክርስቲያኖች አንሥተውት ነበር፡፡ በኋላ ግን በንጉሥ አግብዐ ጽዮን ዘመን (1278 – 1286 ዓም) ለጊዜው ባልታወቀ በምክንያት ገዳሙ ጠፍ ሆነ፡፡ ዋልድባ እንደገና የቀናው እና በኢትዮጵያ ቤተ ክርስ ቲያን ታሪክ ውስጥ ልዩ ቦታ የያዘው በንጉሥ ዓምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥት በተነሡት በአባ ሳሙኤል ዘዋልድባ ነው፡፡
በ1319 አካባቢ ከደብረ ሊባኖስ የተንቀሳቀሰ አንድ የመነኮሳት ቡድን (አባ ሙሴ፣ አባ እስጢፋኖስ፣ አባ ገብረ መስቀል እና አባ ገብረ ክርስቶስ) ዋልድባ በመግባት ሥርዓተ ገዳሙን አጽንተውታል፡፡ በገዳሙ እህል መመገብ የቀረው ከእነርሱ መምጣት በኋላ መሆኑ ይነገራል፡፡ የዚህ ሃሳብ አመንጭም አባ ሙሴ መሆናቸውን የገዳሙ ታሪክ ያትታል፡፡ እነዚህ መነኮሳትም የእርሳቸውን ሃሳብ በመቀበል የገዳሙ ምግብ ቋርፍ እንዲሆን ወሰኑ፡፡ በገዳሙ እህል የሚበላው ለልደት፣ ለትንሣኤ እና ለካህናተ ሰማይ በዓል ብቻ እንዲሆንም ደነገጉ፡፡
በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት (1426-1440 ዓም) የዋልድባ ገዳም ክልል በአራቱ ወንዞች መካከል እንዲሆን ዐዋጅ ተደንግጎ ነበር፡፡ ዐዋጁ ማንኛውም የሀገር ገዥ እና አራሽ ወደ ክልሉ ገብቶ ምንም ዓይነት ሥራ እንዳይሠራ የሚከለክል ነበር፡፡
የዋልድባ ገዳም እስከ ግራኝ ወረራ ጊዜ ቆይቶ በመከራው ሰዓት ጠፍ ለመሆን ደርሶ ነበር፡፡ በኋላ ግን ከወረራው የተረፉ መነኮሳት ተሰባስበው እንደገና አቀኑት፡፡ በመካከልም እየጠፋ እየቀና ለብዙ ዘመናት ኖረ፡፡ በተለይም በዘመነ መሳፍንት በነበረው የእምነት ክርክር የዋልድባ መነኮሳት ዋነኛ ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡
የዋልድባ ገዳም ቦታ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ
የዋልድባ ገዳም በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ልዩ ቦታ ካላቸው ገዳማት አንዱ ነው፡፡
በረዥም ታሪኩ፡- የዋልድባ ገዳም ከአንድ ሺ ዘመን በላይ የተሻገረ ታሪክ ያለው ገዳም ነው፡፡ በዚህም ከተሰዓቱ ቅዱሳን እና ከደብረ ሊባኖስ ታሪክ ጋር የሚተካከል ታሪክ አለው፡፡ የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን የረዥም ዘመን ታሪክ ለማጥናት ሕያው ከሆኑት ምስክሮች መካከል የዋልድባ ገዳም አንዱ ነው፡፡ በጥንታዊው የክርስትና ዘመን፣ በመካከለኛው ዘመን፣ በዘመነ መሳፍንት እና በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ የታሪክ ምዕራፎች ውስጥ የተሻገረ በመሆኑ ማን ይናገር የሚለውን የሚያሟላ ነው፡፡
እመቤታችን በኪደተ እግሯ ከባረከቻቸው ቦታዎች አንዱ መሆኑ፡ የዋልድባ ገዳም እመቤታችን ወደኢትዮጵያ በስደቷ ጊዜ መጥታ በኪደተ እግሯ ከባረከቻቸው እና ጌታችን በሕፃንነቱ ትንቢት ከተናገረላቸው ቦታዎች አንዱ ነው፡፡
ከሌሎች ቦታዎች አያሌ ቅዱሳን የሚጎበኙት ቦታ ነው፡ የዋልድባ ገዳምን ለመሳለም አያሌ ቅዱሳን ወደ ቦታው ይመጣሉ፡፡ በታሪክ እንኳን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘደብረ ሊባኖስ ሦስት ጊዜ ወደ ቦታው መጥተው ተሳልመውታል፡፡ ገድለ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም አባ ጊዮርጊስ ወደ ገዳሙ መምጣቱን ይተርካል፡፡ ኢየሩሳሌምን ለመሳለም የተጓዙ ኢትዮጵያውያን መናንያን እና ቅዱሳን ሁሉ በዋልድባ ገዳም አልፈው፣ ተሳልመው እና ተባርከው፣ በሱዳን በኩል ያልፉ ነበር፡፡
በጥንታዊ ቅርሶቹ፡- የዋልድባ ገዳም ከሺ ዓመታት በላይ ያጠራቀማቸው የሀገሪቱን እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ቅርሶች ጠብቆ እና አቅፎ የያዘ ገዳም ነው፡፡ በተለያዩ ዘመናት ገዳሙ ሲፈታ እንኳን በአካባቢው በሚገኙ የተፈጥሮ መከለያዎች ውስጥ ቅርሶቹን እያስቀመጡ በማትረፍ አቆይተውልናል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከሚገኙ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ገድላት መካከል አንዱ የዋልድባው ገድለ ተክለ ሃይማኖት ነው፡፡
በልዩ የምናኔ አኗኗሩ፡- የዋልዳባ ገዳም ጥንታዊውን የነእንጦንስን የምናኔ ሕይወት ጠብቆ የኖረ፣ከቋርፍ በቀር የላመ የጣመ የማይበላበት፣ መናንያን ከአራዊት ጋር የሚኖሩበት፣ የጽሞና ቦታ ነው፡፡ አንዳንድ መናንያንም ከብቃት ሲደርሱ ማኅበሩን አስፈቅደው የተባሕትዎ ሕይወትን በመያዝ በዱር በገደሉ እንደወደቁ ይቀራሉ፡፡ በገዳሙ ጫካዎች የተዘዋወሩ እንደሚገልጡት በቁም ጸሎት ላይ እንዳሉ ያረፉ አበው ባረፉበት ቦታ ቆመው ለብዙ ዘመናት በመቆየታቸው፣ በአካባቢው ለሚዘዋወሩ ሌሎች መናንያን ያሉ መስለው ይታያሉ፡፡
በቦታው አቀማመጥ፡- የዋልድባ ገዳም በሁለት ክልሎች ውስጥ የሚገኝ ሰፊ ገዳም ነው፡፡ በአራት ወንዞች ተከልሎ በአያሌ አጥቢያዎች የተዋቀረ አንድ አውራጃ የሚያህል ገዳም፡፡
በትምህርት ቤቱ፡- የዋልድባ ገዳም አያሌ ሊቃውንትን ያፈሩ የአብነት ት/ቤቶች ቦታ ነው፡፡ መናንያኑ ከምናኔያዊ ሕይወት በተጨማሪ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርቶች በገዳሙ ይማራሉ፡፡
ብዙ አበውን ያፈራ ነው፡- የዋልድባ ገዳም ለቤተ ክርስቲያን ታላላቅ አስተዋጽዖ ያደረጉ ብዙ አባቶችን ያፈራ ገዳም ነው፡፡ በየአጥቢያው ከሚገኙ መነኮሳት መካከል ቢያንስ አንድ የዋልድባ መነኩሴ አይጠፋም ይባላል፡፡ የዋልድባ መነኮሳት በግብጽ፣ በኢየሩሳሌም፣ በአውሮፓ እና በአሜሪካ ለአገልግሎት ተሠማርተዋል፡፡ ይህም የገዳሙን ሁለገብ አስተዋጽዖ ያመለክታል፡፡
ዋልድባ በኢትዮጵያ ውስጥ ነባር ደኖች ከሚገኙበት የምናኔ ቦታዎች አንዱ ነው፡፡ የዋልድባ ደን አንድ አውራጃ የሚያክል እና በሀገር በቀል ዛፎች የተሞላ፣ የአራዊት እና የአዕዋፍ ማደርያ የሆነ ቦታ ነው፡፡ ዛሬ ለአካባቢ ጥበቃ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ገበሬውን ሁሉ በአካባቢ ጥበቃ ተግባር በማሳተፍ ላይ ባለበት ጊዜ የዋልድባን ጥብቅ የግዝት ደን ክልል ማረስ የሚጋጭ ተግባር ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም ዐቀፍ መድረኮች ድምጽዋን ከፍ አድርጋ እየተከራ ከረችባቸው ከሚገኙ ጉዳዮች አንዱ የአረንጓዴ ልማት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ እንኳንስ ነባር ደኖችን መንካት ሊፈቅድ አዳዲስ የዛፍ ቦታዎችንም ጥበቃ እንዲደረግላቸው የሚሟገት ነው፡፡
የዋልድባ ይዞታ ከሥነ ምሕዳር አንፃር ሲታይ የሀገሪቱ አንዱ የመተንፈሻ ሳንባዋ ነው ያሰኛል፡፡
የዋልድባ ሰሞነኛ ነገር
ዋልድባ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰሞነኛ ጉዳይ እንዲሆን ያደረገው በአካባቢው የስኳር እርሻ እና ፋብሪካ ይከፈታል መባሉ ነው፡፡ ይህንን ተከትሎ የገዳሙ መነኮሳት እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደረሰ አቤቱታ ያሰሙ ሲሆን ሕዝቡም ሁኔታውን መወያያ አድርጎታል፡፡ አካባቢውን በቅርብ ከጎበኙ አካላት እንደ ተገኘው መረጃ ከሆነ በአካባቢው የስኳር ኢንዱስትሪ ለማቋቋም መንግሥት እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ በዚህ እንቅስቃሴውም እህል አይግባብሽ፣ ዘር አይዘራብሽ ተብሎ ከተከለለው የገዳሙ ክልል 2.5 ኪሎ ሜትር ዘልቆ ለመንገድ የሚሆን ቦታ አርሷል፡፡ ገዳማውያኑ እና የአካባቢው ምእመናን በጋራ የሚጠቀሙባቸው አራት አብያተ ክርስቲያናት ማለትም
· ማየ ሕርገጽ ቅዱስ ጊዮርጊስ (የሴቶች ገዳም)
· ዕጣኖ ቅድስት ማርያም (የገዳሙ እህል ቤት)
· ደላስ ቆቃ አቡነ አረጋዊ እና
· ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ናቸው
መንግሥት እንደሚለው እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት መነሣታቸው የማይቀር ሲሆን ለዚህም ካሣ እንደ ሚከፍል ገልጧል፡፡
የአካባቢው ምእመናን የዋልድባን ቅዱስ አፈር በመሻት ቀብራቸውን በገዳሙ ማድረጋቸው የተለመደ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜም ወደ ክልሉ ሳይደርሱ የዛሬማን እና የአንሽያን ወንዞች ተሻግረው የሚቀብሩ አሉ፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች አካባቢው ሲታረስ 27 ዐጽሞች ተገኝተዋል፡፡ በገዳሙ ክልልም ተቀብረዋል፡፡ ወደፊትም በቀጣይ ሥራ ሌሎች ሊገኙ እንደሚችሉ ይገመታል፡፡
በአካባቢው የሚገኘው ነዋሪ ሲገለገልባቸው የነበሩ 14 የገጠር አብያተ ክርስቲያናት ይነሣሉ፡፡ የአካባቢው ሕዝብ ወደ ሌላ ቦታ ሄዶ የሚሠፍርበት አሥራ አንድ መንደሮች ተመቻችተዋል፡፡ እነዚህን የተነሡትን የገጠር አብያተ ክርስቲያናት በአዲሶቹ የሠፈራ ቦታዎች እንደሚገነባ መንግሥት ተናግሯል፡፡
እጅግ አከራካሪ የሆነው አባ ነጻ የሚባለው እና በገዳሙ የግዝት ክልል የሚገኘው ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ አቡነ ተስፋ ሐዋርያትን ጨምሮ አያሌ ቅዱሳን ዐጽም ያረፈበት ይህ ቤተ ክርስቲያን በግዝት ክልሉ ውስጥ በመሆኑ አይነሣም፡፡ ነገር ግን የግድቡ ውኃ ወደ አካባቢው ስለሚደርስ የገዳሙን ሕልውና ሊያሠጋው እንደሚችል ገዳማውያኑ ተናግረዋል፡፡ የመንግሥት አካላት የግድቡ ግንባታ ገዳሙን እንዳ ይነካው ተደርጎ ሊሠራ እንደሚችል ቢገልጡም ገዳማውያኑ ግን ሥጋታቸውን የሚቀርፍ ነገር ባለ ማግኘታቸው አልተቀበሉትም፡፡
በአደርቃይ በኩል ያለውን የገዳሙን ክልል በርክነት ለመከለል የቀረበው ዕቅድ በገዳማውያኑ ተቀባይነት ባለማግኘቱ መሠረዙን ምንጮች ገልጠውልናል፡፡
የዋልድባ ጉዳይ ለምን ይህንን ያህል መነጋገርያ ሆነ?
ዋልድባ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዓይነተኛ ገዳም ነው፡፡ የዋልድባ ገዳም እንኳን በቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች ቀርቶ በምእመናንም ዘንድ የሚታወቅ እና የሚጠበቅ ገዳም ነው፡፡ «አልፎ አልፎ በዋልድባም ይዘፈናል»፣«ላወቀባት ገረገራም ዋልድባ ናት» የሚባለው አባባል ዋልድባ ገዳም ለሥነ ቃል የበቃ የሕዝብ ገዳም መሆኑን ያሳያል፡፡ የዋልድባ መነጋገርያ መሆን ገዳሙ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ያለውን ታላቅ ቦታ አመላካች ነው፡፡
የሰሞኑ ትኩሳት መመርያን እንጂ መረጃን መሠረት የማያደርገው አሠራራችን ያመጣውም ችግር ነው፡፡ መቼም አንድ የስኳር ኢንዱስትሪ እንደ ታዴዎስ እርሻ በአንድ ቀን ታስቦ በአንድ ቀን አይጀመርም፡፡ የብዙ ጊዜ ዕቅድ እና ፕሮጀክት ውጤት ነው፡፡ በዚህ ጥናት ውስጥ ሊካተቱ ከሚገባቸው ጉዳዮች አንዱ የፕሮጀክቱ አካባቢያዊ ተቀባይነት ነው፡፡ በዚያ አካባቢ የሚኖሩ ነባር ነዋሪዎች ፕሮጀክቱ በእነርሱ ላይ ስለሚያመጣው ጉዳትም ይሁን ስለሚሰጠው ጥቅም ማወቅ፣መወያየት፣ሃሳብ ማቅረብ እና መሰማትም አለባቸው፡፡
እንኳንና የአካባቢው ሰዎች ሌላውም ግብር ከፋይ ዜጋ ቢሆን በእርሱ ግብር ስለሚሠራው ሥራ በዝርዝር ማወቅ ያስፈልገዋል፡፡
ዋልድባ አካባቢ በሚሠራው ሥራ ይህ የሆነ አይመስለኝም፡፡ መመርያው ተግባራዊ መሆኑን እንጂ መረጃው ሕዝቡ ዘንድ ደርሶ በጎ ምላሽ መግኘት አለማግኘቱን ያየው አካል የለም፡፡ ዋልድባ ገዳም ነው፣ በሀገሪቱ ታሪክ የማይተካ ሚና የነበረው ገዳም ነው፣ አያሌ አባቶችን አፍርቶ ያሠማራ ገዳም ነው፡፡ አብ ሲነካ ወልድ ይነካ እንደሚባለው ዋልድባ ሲነካ አብረው የሚነኩ ብዙ አካላት አሉ፡፡ ይህ እየታወቀ እንዲሁ በድፍረት ወደ ሥራው መገባቱ እስከመቼውም የማያባራ ችግር ለገዳሙም ለሚጀመረው ኢንዱስ ትሪም መፍጠር ነው፡፡
ስኳሩን እንደሚፈልጉት፣ በስኳሩ ኢንዱስትሪ ተቀጥረው እንደሚሠሩት የሀገሪቱ ዜጎች ሁሉ የገዳሙ መናንያንም የዚህች ሀገር ዜጎች ናቸው፡፡ በሀገሪቱ ሂደት የመጠቀም እንጂ ያለ መጎዳት መብት ያላቸው ዜጎች፡፡ የሚጎዱት ጉዳት እንኳን ቢኖር አምነውበት፣ ተቀብለውት፣ መሥዋዕትነት ለመክፈል ወስነውበት፣ ከዚያም በላይ ደግሞ ያሥምረው ብለው አቡነ ዘበሰማያት ደግመውበት መደረግ አለበት፡፡ ይህ አለ መሆኑን በቀላሉ ከሚያሳዩን ነገሮች አንዱ ወደ ግዝቱ የገዳሙ ክልል ሁለት ኪሎ ሜትር ተኩል ከራ ከመንግሥት ዕቅድ እንኳን በተቃራኒው ተገብቶ መታረሱ ነው፡፡
የዋልድባ ገዳም መነጋገርያ ከሆነ በኋላ እንኳን የሚመለከታቸው አካላት (ቤተ ክህነት እና መንግሥት) ለሕዝብ መረጃ ሲሰጡ አልታዩም፡፡ ሁሉም ነገር የሚሰማው በሹክሹክታ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሐሜት እንደ ባህል ለተያዘበት ማኅበረሰብ ያልተገባ ሥጋት እና ጭንቀት መፍጠሩ የማይቀር ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ መንግሥታት ማኅበራዊ የመረጃ መረቦችን እየተጠቀሙ የዕለት ተዕለት ጉዳዮችን ለሕዝባቸው መንገር በጀመሩበት ዘመን ብሔራዊ የሚዲያ ተቋማት እንኳን ነገሩን ዝም ማለት አልነበረባቸውም፡፡
ሌላው ችግር ደግሞ ነገሮችን አጣጥሞ ያለ መጓዝ ችግር ነው፡፡ ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ እና የግብርና ልማት ያስፈልጋታል፡፡ ሌላም ልማት ያስፈልጋታል፡፡ ነገር ግን ዕድገታችን አንዱን ገድሎ በሌላው መቃብር ላይ የሚቆም መሆን የለበትም፡፡ ከ90 በመቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ በላይ ሃይማኖተኛ መሆኑን በሕዝብ ቆጠራዎች ላይ አሳይቷል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የሃይማኖት ጉዳይ የሀገሪቱ ዋና ጉዳይ ነው ማለት ነው፡፡ የምንጓዘው ጉዞም ይህንን የሀገሪቱን ዋና ጉዳይ ከግምት ያስገባ መሆን አለበት፡፡
የኢትዮጵያ ዕድገት ከታሪኳ፣ ባህልዋ፣ ሃይማኖቷ እና ቅርሷ ጋር የተጣጣመ መሆን አለበት፡፡ አዲስ ሕንፃ ለመሥራት ብለን ላሊበላን ማፍረስ ወይንም አኩስምን መጣል የለብንም፡፡ አዲስ ደን የምንተክለው የዐፄ ዘርዐ ያዕቆብን የሱጳ ደን ነቅለን በምናገኘው ሜዳ ላይ መሆን የለበትም፡፡ ነባር እሴቶቻችን ከአዳዲስ እሴቶቻችን ጋር የሚጣጣሙበትን ወይንም አብረው የሚጓዙበትን መንገድ መፈለግ ነው ዋናው ሥራችን፡፡
በዋልድባ አካባቢ የልማት ሥራ ለመሥራት መነሣቱ አይደለም ችግሩ፡፡ ከልማት ሥራው በፊት የዋልድባ ገዳም ይቀድማል፡፡ ቢያንስ በ1000 ዓመት ይቀድማል፡፡ የልማቱ ሥራ ከዋልድባ ገዳም ጋር መጣጣም አለበት እንጂ፣ የዋልድባ ገዳም ከልማት ሥራው ጋር እንዲጣጣም መጠየቅ የለበትም፡፡ እንዲህ ባለ አካባቢ ምን ዓይነት ልማት መደረግ አለበት? ይህ ሲከናወንስ የገዳሙ እሴቶች፣ መብቶች እና ሀብቶች እንዴት መጠበቅ ይችላሉ? ከሚሠራው ሥራ ገዳሙ የሚጠቀምበት እንጂ የማይጎዳበት መንገድም ቀድሞ መፈለግ አለበት፡፡
እዚህ ላይ ከግምት ውስጥ መግባት የነበረባቸው ቢያንስ ሦስት ጉዳዮች አሉ፡፡
አካባቢያዊ መስተጋብር፡- ይህ አካባቢ የገዳም አካባቢ ነው፡፡ ይህ ገዳምም በዚያ ቦታ ከሺ ዓመታት በላይ ኖሯል፡፡ እናም በአካባቢው የሚደረጉ ሥራዎች የገዳሙን ገዳማዊ እሴቶች የማያጠፉ መሆን አለባቸው፡፡ ገዳሙ ከዓለም ሰዎች እንቅስቃሴ የራቀ፣ ጸጥታ የነገሠበት እና ጥብቅ ክልል ያለው ነው፡፡ በዚህ አካባቢ የገዳሙን ክልል መንካቱ ብቻ አይደለም ነገሩ፡፡ ከገዳሙ ክልል ውጭ የሚሠራ ሥራም ቢሆን እነዚህን የገዳሙን እሴቶች የጠበቁ መሆን አለባቸው፡፡ ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ በገዳሙ አካባቢ ይሠራል የተባለው የስኳር ኢንዱስትሪ ነው፡፡ የስኳር ኢንዱስትሪ ከፍተኛ የሰው ኃይል የሚጠይቅ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ በዚህ ከፍተኛ የሰው ኃይል የተነሣም በሀገራችን የስኳር እርሻ እና ፋብሪካ ባሉባቸው አካባቢዎች ሁሉ ከተሞች ተመሥርተዋል፡፡ ወንጂ እና መተሐራን ይጠቅሷል፡፡ ይህ ማለት አካባቢው ከፍተኛ የሰው ኃይል እንቅስቃሴ ይኖርበታል ማለት ነው፡፡
ይህንን ዓይነት እንቅስቃሴ የማይጠይቅ ተግባር በአካባቢው ማከናወን አንዱ አማራጭ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ የአካባቢው የሰው እንቅስቃሴ ገዳማዊ ሕይወቱን እንዳይረብሸው በሚያስችል መንገድ የሚከናወንበትን ሥራ መሥራት ነው፡፡ አሁን እንደሚታየው በዚህ ጉዳይ የታሰበ ነገር ስለመኖሩ ምንም ዓይነት ግልጽ መረጃ የለም፡፡
በአንዳንድ ሀገሮች በአንድ ቦታ ላይ የአካባቢውን ነባራዊ መልክዐ ምድር፣ መልክዐ ጠባይ እና መልክዐ እሴት የሚቀይሩ ተግባሮች ከመከናወናቸው በፊት ነባር ነዋሪዎች አስተያየት እንዲሰጡባቸው ይደረጋል፡፡ የነዋሪዎቹን ስምምነት ማግኘትም መሠረታዊ ነገር ይሆናል፡፡ በአሜሪካን ሀገር በአንድ መንደር አካባቢ ቤተ ክርስቲያን ለማቋቋም የአካባቢው ነዋሪ ፈቃድ መገኘቱ ወሳኝ ተግባር ነው፡፡
ከአካላዊ ጉዳት ነጻ መሆን፡- ገዳሙ የሀገሪቱ መንፈሳዊ ሀብትም ቅርስም ነው፡፡ የአኩስም ሐውልትን ወደ አኩስም የመለስነው በሮም አደባባይ መቀመጡ ክብካቤ ስላሳጣው አይደለም፡፡ የአኩስም ሐውልት መንበሩ፣ ክብሩም አኩስም ስለሆነች እንጂ፡፡ ከአኩስም መነቀሉን ስለ ተቃወምን ነው ያስመለስነው፡፡ የዋልድባም እንደዚሁ ነው፡፡ ዋልድባ በሀገሩ ከነ ሙሉ ክብሩ የመኖር ኢትዮጵያዊም ሕጋዊም መብት አለው፡፡ በአካባቢው የሚሠሩ ሥራዎች በገዳሙ ላይ አካላዊ ጉዳት የማያስከትሉ መሆን አለባቸው፡፡ አሁን እንደምናየው ግን የገዳሙ የግዝት ክልል ታርሷል፡፡ የገዳሙ የእህል ቤት ወይንም ሞፈር ቤት የሚባለው ቤተ ክርስቲያን ሊነሣ ነው፡፡ የሴቶቹ ገዳም ሊነሣ ነው፡፡ በአንደኛው የገዳሙ ቤተ ክርስቲያንም ግድቡ አደጋ ሊያደርስ ይችላል የሚል ሥጋት ተፈጥሯል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ እነዚህን ሁሉ አደጋዎች በሚቀንስ እና የገዳሙን ህልውና በማይነካ መልኩ ፕሮጀክቱን መቅረጽ የገዳማውያኑ ጭንቀት ሳይሆን የአጥኚው እና የአስጠኚው ጭንቀቶች መሆን ነበረባቸው፡፡ ልማቱ ከአካባቢው እሴት ጋር ተጣጥሞ በሚሄድበት መንገድ ላይ ገዳማውያኑ በነጻ መክረው፣ የሃሳቡ ባለቤቶች እና ተሳታፊዎች መደረግም ነበረባቸው፡፡ ወይ በሥጋታቸው መሠረት መሠራት፣ ያለበለዚያም ደግሞ ሥጋቱን በሚያስቀር መንገድ መሠራት ነበረበት፡፡
መንፈሳዊ ጉዳት እንዳይደርስ ማድረግ፡- አስቀድሞ የገዳሙን ማኅበረሰብ ባሳተፈ፣ ችግሮችን በሚፈታ እና ሁለቱም አካላት ሳይጣረሱ በተዐቅቦ ሊኖሩ በሚችሉበት መንገድ ባለመካሄዱ ገዳማውያኑ ምን ሊመጣ ይችላል? በሚለው መንፈስ ተረብሸዋል፡፡ አሁን ክርክሩ የተነሣበት ወቅት በዋልድባ ገዳም ዋናው የሱባኤ ጊዜ ነው፡፡ መነኮሳቱ እና መናንያኑ ከገዳማቸው አይወጡም፡፡ በዚህ ወቅት የነገሩ መነሣት በገዳሙ እና በምእመናኑ ዘንድ መንፈሳዊ ረብሻን ፈጥሯል፡፡ ነገሩ በመገባ ቢታብበት ኖሮ ይህንን ወቅት ማስቀደም ወይንም ማሳለፍ በተገባ ነበር፡፡
ለምሳሌ አሁን እርሻው በሚታረስበት አካባቢ ከጥንት ጀምሮ ቀብር እንደነበረ ይታወቃል፡፡ ዐጽሙ ይፍለስ ከተባለ እንኳን ይህንን ጉዳይ ከገዳሙ ጋር ተነጋግሮ ገዳማዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ ማከናወን ይገባ ነበረ፡፡
አዙረህ አዙረህ ካገሬ መልሰኝ
በሹም የታዘዘ አፈር አታልብሰኝ
እያለ በሚያንጎራጉር የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ የመቃብር ቦታ ያለውን ዋጋ ዘአስቀድሞ መተንበይ አስቸጋሪ አይመስልም፡፡ ዐጽሞቹ የት የት ይገኛሉ? መፍለስ ካለባቸው በምን ዓይነት ሃይማኖታዊ እና ሰብአዊ ሥርዓት? ማን ያፍልሳቸው? የት ይረፉ? የሚሉት እንደ አንድ ተግባር ሊታሰብባቸው ይገባ ነበር፡፡ ለነገሩ የአዲስ አበባ አጥቢያዎች በግዴለሽነት ያለ በቂ ሃይማኖታዊ፣ ሰብአዊ ሥርዓት እና ክብር ነባር ዐጽሞችን በሚያነሡበት በዚህ ዘመን መንግሥትን በዚህ ረገድ መውቀስ ከባድ ይሆናል፡፡ እነዚህ አበው እና እማት ለሀገር እና ለሕዝብ የሚጸልዩ ናቸው፡፡ ጸሎታቸው እንጂ ኀዘናቸው ማንንም አይጠቅምም፡፡ ይህ የዋልድባ ገዳም ጉዳይ በተገቢው መንገድ ባለመያዙ ከዋልድባ አልፎ ሌሎችን ገዳማውያንም የሚያሳስብ ነገር እየሆነ ነው፡፡
ጉዳዩ እና ቤተ ክህነት
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ነባር ይዞታዎች በውል ለይቶ ማወቅ፣መብታቸውን ማስጠበቅ፣ በሀገሪቱ ውስጥ በሚከናወኑ ተግባራት ተጠቃሚዎች እንጂ ተጎጅዎች እናይሆኑ መጠበቅ፣ ችግሮች ሲፈጠሩ የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥቅም በሚያስከብር፣ የሀገርንም ዕድገት በሚራዳ መልኩ እንዲፈቱ ማድረግ የቤተ ክህነቱ ሥራ ነው፡፡
አሁን በታየው ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ቤተ ክህነቱ ሕዝቡ ተገቢውን መረጃ እንዲያገኝ፣ ችግሮች ቀድመው እንዳይከሰቱ፣ ከተከሰቱም እንዲታረሙ፣ ወሬዎች እንዳይጋነኑ፣ ማድረግ ይገባው ነበር፡፡ ለቅዱስ ሲኖዶስም ከዚህ የሚበልጥ ጉዳይ አልነበረውም፡፡
በመጀመርያ ደረጃ ልዑካንን ልኮ ተገቢውን መረጃ መሰብሰብ፣ በተሰበሰበው መረጃ ላይ የተመሠረተ መግለጫ መስጠት፣ ከሚመለከታቸው ጋር መነጋገር እና የደረሰበትን ማስታወቅ ይገባው ነበር፡፡ ባለቤት ካልጮኸ ጎረቤት አይረዳም እንዲሉ፡፡ አስቀድሞም እንዲህ ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በንቃት በመሳተፍ አሁን የተከሰተውን ችግር በማያ ስከስቱበት መንገድ እንዲከናወኑ የበኩሉን ማድረግ ነበረበት፡፡
ገዳማውያኑ ለአቤቱታ አዲስ አበባ ሲመጡ ተቀብሎ ማስተናገድ፣ ችግራቸውን መስማት፣ ከሚመለከ ታቸው አካላት ጋር ማገናኘት፣ ጉዳያቸውን መከታተል እና የነገሩ ባለ ቤት ሆኖ መሥራት ይገባው ነበር፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮች ግን ችግሮችን የመፍታት ዐቅማችንን ሳይሆን ቤተ ክህነታችን ያለበትን ደረጃ የሚያሳዩን እየሆኑ ነው፡፡
«ኢውልድብና»
አንድን ሃይማኖታዊ፣ ታካሪዊ፣ ባህላዊ እና ጥንታዊ እሴትን ከግምት ውስጥ ሳያስገቡ፣ መብቱን እና ክብሩን ብሎም እሴቶቹን ከግምት ውስጥ ሳያስገቡ ሌላ ጠቃሚ ነው የተባለን ነገር ማከናወን «ኢውል ድብና» ተብሏል፡፡ ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ፣ ባህላዊ እና ትውፊታዊ እሴቶችን ጠብቆ ለሀገራዊ ተግባራትን ማከናወን ደግሞ «ማወልደብ፣ ውልድብና»፡፡ ዋልድባ ላይ የደረሰውን መሠረት በማድረግ ነው ስሙን የወሰድኩት፡፡
ይኼ ጉዳይ ነገም የሀገሪቱ እና የቤተ ክርስቲያኒቱ መነጋገርያ መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ ኢውልድብና መንግሥት እና ሕዝብን የሚቀያይም፣ የሕዝብን ተሳታፊነት የሚቀንስ፣ የሚሠሩ ተግባራት ቅቡል እና ዘላቂ እንዳይሆኑ የሚያደርግ፣ ነገሮችን በአንድ ዓይን ብቻ የሚያሳይ አሠራር ነው፡፡ ባለፈው መንግሥት ጊዜ የገበሬውን ቅቡልነት ሳያገኙ የተሠሩ ተግባራት የደረሰባቸውን ማየቱ ብቻ ትምህርት በሆነን ነበር፡፡ አያሌ ቦታዎች በደን ተሸፈኑ፡፡ ደን አስፈላጊ ነገር ነበር፡፡ ይሁንታ ስላላገኘ ግን ደርግ ሲወድቅ ደኑ ሊቀጥል አልቻለም፡፡ አንድ ነገር ጥሩ እና ጠቃሚ ስለሆነ ብቻ እድሜ አይኖረውም ሕዝባዊ ተቀባይነት ሲኖረውም ጭምር እንጂ፡፡
ኢውልድብና መልካሙ ነገር በመስተጋብር ችግር ምክንያት እንዲጠላ የሚያደርገ አሠራር ነው፡፡ ኢውልድብና አንድ ነገር በሚያስገኘው ቁሳዊ ውጤት ብቻ ከዐውዱ ውጭ እንዲታይ አድርጎ አካባቢያዊ ስሙምነት እንዳይፈጠር የሚያደርግ ነው፡፡
እናም አሁንም አልረፈደምና አሉ የሚባሉ ችግሮችን በቀና መንፈስ እንፍታቸው፡፡ ልማቱም ታሪኩም፣ እምነቱም፣ ቅርሱም ተጣጥመው የሚሄዱበትን መንገድ እንፈልግ፡፡ እንደ ሜዶን እና ፋርስ ሕግ የተቆረጠ የማይቀጠል ከምናደርገው፣ ነገሩን እንደገና ብናየው፡፡ እነዚህ መናንያን በኢንዱስትሪው ላይ ከሚያዝኑበት ቢባርኩት ይሻለናል፡፡
የሀገሬ ሰው «ገብስ እና ፈረስ የሚያጣላ» እንደሚለው የማይጣሉትን ጉዳዮች በኛ ችግር ምክንያት አናጣላቸው፡፡ ያለበለዚያ ግን አካሄዳችን ዋልድባን መተሐራ፣ ስኳሩንም መራራ የሚያደርገው ይሆናል፡፡
ገበያ ሲያመች
Friday, March 16th, 2012ከዳንኤል ክብረት
በድሮ ዘመን ነው አሉ፡፡ ልጂቱ ምጣድ ልትገዛ ገበያ ትወጣለች፡፡ ጥሩ ምጣድ መርጠው እንዲገዙላት እናቷን አስከትላለች፡፡ ገበያ ስትገባ እንዴው ሁሉም ነገር ቀልጧል፡፡ የማይሸጥ የማይለወጥ ነገር የለም፡፡ «ምነው?» «ስትል ጦር ሊመጣ ነው ተብሎ ሁሉም ነገር ተወዷል» ይሏታል፡፡ «ምን ምን ይሸጣል?» ብላ ትጠይቃለች፡፡ «ምን የማይሸጥ ነገር አለ፡፡ ከብት ይሸጣል፣ ወርቅ ይሸጣል፣ እህል ይሸጣል፣ ልብስ ይሸጣል፣ ሰውም ይሸጣል» ይሏታል፡፡
«ደግሞ ሰው ለምን ይሸጣል?» ብላ ትጠይቃለች፡፡ «ባርያ መሸጥ መለወጥ ሊቀር ስለሆነ ሁሉም አሁን እየገዛ ነው» ትባላለች፡፡ እናቷን አንድ ጥላ ሥር አሳርፋ ሄዳ ስታይ እውነትም ልጅ ዐዋቂው፣ ባልቴት ሽማግሌው ሁሉ በባርያ ፈንጋይ እየተያዘ ይሸጣል፡፡ ስትሮጥ ሄደችና እናቷን ይዛ መጥታ በአራት ከብት ለወጠቻት፡፡ ነገሩን የሰማው የሀገሬ ሰው ጉድ ጉድ ብሎ ሲያበቃ «ገበያ ቢያመቻት እናቷን ሸጠቻት» የሚል ተረት አወጣላት፡፡
የሁኔታዎች መመቻቸት የሚያመጡትን ኢሞራላዊነት ከገለጥንባቸው ነባር አባባሎቻችን አንዱ ነው ይኼ፡፡ «የአንዳንዱ ሰው ትክክለኛነት፣ ቆራጥነት፣ ሞራላዊነት፣ ጥንካሬ፣ የዓላማ ጽናት፣ እምነት፣ ገበያው እስኪ ያመቸው ድረስ ነው፤ ገበያ ካመቸው ሁሉንም ሽጦ ለማትረፍ ዝግጁ ነው» ነው የሚሉን ቀደምቶቻችን፡፡
ገበያ ሲመች የማይሠራ ኢሞራላዊ ሥራ የለም፡፡ ገበያ ሲመች ሀገር ይሸጣል፣ ኅሊና ይሸጣል፣ መሬት ይሸጣል፣ ቅርስ ይሸጣል፣ ስም ይሸጣል፣ ባህል ይሸጣል፣ ፍትሕ ይሸጣል፣ እናት ይሸጣል፣ አባት ይሸጣል፣ ልጅ ይሸጣል፣ አካል ይሸጣል፣ ሞያ ይሸጣል፣ ሰርተፊኬት ይሸጣል፣ ክህነት ይሸጣል፣ እምነት ይሸጣል፡፡ ምን የማይሸጥ ነገር አለ፡፡
አንዳንዶች ለመኖር ኅሊናን መሸጥ የሚያዋጣ ከመሰላቸው ከመሸጥ ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ገበያ ካመቸ ኅሊናን ይሸጡታል፡፡ መመዘኛቸው ትክክል ነው አይደለም፣ ሞራላዊ ነው አይደለም፣ እውነት ነው አይደለም፣ ሕጋዊ ነው አይደለም የሚለው ሳይሆን ያዋጣል ወይስ አያዋጣም የሚለው ብቻ ነው፡፡ እየሠሩ ያለው ነገር ከሚያምኑበት ነገር ጋር ቢጋጭም ባይጋጭም፣ ትናንት ሲያስቡት ከነበረው ነገር ጋር ቢለያይም ቢስማማም፣ ቀድሞ ከተናገሩት ነገር ጋር ቢሠመርም ባይሠምርም ዋናው ነገር አሁን ያዋጣል ወይስ አያዋጣም ብቻ ነው፡፡
እንደዚህ ዓይነት ሰዎች የሚሞቱለት አቋም፣ ሃሳብ፣ ርእዮተ ዓለም፣ መሥመር፣ እምነት፣ ማንነት፣ ራእይ የላቸውም፡፡ እንኳንስ ሃሳባቸውን እና አቋማቸውን የሚያዋጣ ሆኖ ካገኙት የትውልድ ቦታቸውን፣ ብሔረሰባቸውን እና ወላጆቻቸውን ጭምር ለመቀየር ዝግጁ ናቸው፡፡ ትናንት አዋጥቷቸው ጎጃም ተወልደው እንደሆነ የዛሬውን ገበያ አይተው ጎንደር ሊወለዱ ይችላሉ፡፡ ጎንደር መወለዳቸው የረከሰ ከመሰላቸውም ትግራይ ወይንም ወለጋ ከመወለድ ወደ ኋላ አይሉም፡፡
እነዚህ ሰዎች አማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ ወላይታ፣ ሶማሌ ወይንም ጉራጌ የሚሆኑት ከዚያ ማኅበረሰብ ስለተወለዱ ወይንም እዚያ ስላደጉ፣ ያለበለዚያም ቋንቋውን ስለሚናገሩ አይደለም፡፡ ያዋጣል ወይስ አያዋጣም? ነው መመዘኛው፡፡ ገበያው ካመቼ ማንነትም ይቸበቸባል፡፡
ሰው አመለካከቱን፣ አቋሙን ወይንም ርእየቱን ሊቀይር ይችላል፡፡ ነገር ግን ተአምራዊ በሆነ ድንገቴ መንገድ ሰው እነዚህን ነገሮች ሊቀይር አይችልም፡፡ የሰው ኅሊና እንደ ኮምፒውተር በፈለጉት ጊዜ የፈለጉትን ሶፍትዌር በፍጥነት የሚጭኑበት አይደለምና፡፡ ማሰብ፣ ማብሰልሰል፣ ከራሱ ጋር መሟገት፣ መረዳት፣ ማስረዳት፣ መመዘን፣ ማመዛዘን ይፈልጋል፡፡ ሲያምንም በምክንያት ነው፣ ሲለወጥም በምክንያት ነው፡፡
የገበያ ሰዎች ግን እንደዚህ አይደሉም፡፡ አንድን አቋም ወይንም አስተሳሰብ፣ አመለካከት ወይንም ርእዮተ ዓለም የሚመዝኑት ከአቋማቸው እና ከአስተሳሰባቸው አንፃር አይደለም፡፡ ትክክል ነው ወይንስ ስሕተት፣ ያስኬዳል ወይስ አያስኬድም፣ ያሳምናል ወይስ አያሳምንም፣ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም፣ ሕጋዊ ነው ወይስ አይደለም፣ የሚል መመዘኛ የላቸውም፡፡ ይሸጣል ወይስ አይሸጥም ነው ጥያቄአቸው፡፡
ያለ ምንም አሳማኝ ምክንያት ሰው ይዞት ከነበረው አቋም በድንገት በተቃራኒው ከተገኘ አንዳች የሚያዋጣ ገበያ አግኝቷል ማለት ነው፡፡ ሰው እንዴት በድንገት ከተቃዋሚነት ወደ ደጋፊነት ከደጋፊነትም ወደ ተቃዋሚነት ሊቀየር ይችላል፡፡ አስተሳሰብ ሂደት እንጂ ተአምር አይደለማ፡፡
በሀገራችን የየከተማውን መሬት ቸብችበው ቸብችበው የጨረሱት እነማን ናቸው? ለገበያ እንጂ ለኅሊናቸው የማይሠሩ ናቸዋ፡፡ መሬት ውድ ነው? አዎ፡፡ ሚሊየን ብር ያስገኛል? አዎ፡፡ የተቀመጡበት ቦታ ሊያስቸበችብ የሚያስችል ነው? አዎ፡፡ እነ እገሌ የከበሩት መሬት ሽጠው አይደለም? አዎ፡፡ ታድያ እኔስ የምችለውን ያህል ሽጬ የድርሻዬን ብወስድ ምናለ? እንዴ ኅሊና የለም እንዴ፡፡ ገበያው ያመች ይሆናል፡፡ ግን ገበያ ስላመቸኮ እናት አትሸጥም፡፡
የሀገር ሕግ ሊላላ ይችላል፡፡ ሁኔታዎች ሊያመቹ ይችላሉ፡፡ ገበያው ደርቶ ይሆናል፡፡ ዕድል እንደ ትኩስ ኬክ ፊት ለፊት ቀርቦ ይሆናል፡፡ እድሜ ልክ ተሠርቶ የማይገኝ ገንዘብ በካሬ ሜትር ይገኝ ይሆናል፡፡ ግን ኅሊናስ፡፡ አእምሮስ፡፡ ኢትዮጵያ የኛስ ሀገር አይደለችም እንዴ፡፡ ትውልድስ? ነገስ? አይታሰብም እንዴ፡፡
ሰውኮ ከእንስሳ ከሚለይባቸው ነገሮች አንዱ እርሱ ህልው ሆኖ ከሚኖርባቸው ዘመናት በኋላ ላለው ህልውናውም ስለሚያስብ ነው፡፡ በዐጸደ ሥጋ እያለ በአካል ህልው ይሆናል፡፡ በአካልም ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ከዐጸደ ሥጋነት ሲያልፍ ደግሞ በታሪክ ውስጥ ህልው ይሆናል፡፡ ወይንም በዐጸደ ነፍስ ህልው ይሆናል፡፡ ሰውኮ ስለ ሁለተኛ ህላዌውም መጨነቅ አለበት፡፡ እኔ ከሞትኩ ያለችውኮ ማን እንደሆነች እናውቃታለን፡፡
ከጣልያን ጋር አምስት ዓመታት የተዋጉት አርበኞች በዘመናቸው ለመጠቀም አልነበረም መሥዋዕትነት የከፈሉት፡፡ እንዲያውም በዘመናቸው ለመጠቀም ከጣልያን ጋር መሞዳሞዱ የተሻለ ይሆንላቸው ነበር፡፡ ሀገራቸውን እና ክብራቸውን ሽጠው የዕለት ክብር የዓመት ግብር ማግኘት ይችሉ ነበር፡፡ ግን ሌላም ነገር አለ፡፡ ታሪክ አለ፡፡ ማንነት አለ፡፡ ሀገራዊ ክብር እና ኩራት አለ፡፡ የዜግነት ግዴታ አለ፡፡ ይህ ነው አስገድዶ ጫካ ያስገባቸው እንጂ ሀገር ለመሸጥማ እንደዚያ ጊዜ አመቺ ገበያ አልነበረም፡፡ እነርሱ ግን ገበያ አመቸ ብለው እናታቸውን አልሸጡም፡፡
ሰው ጉቦ ለመቀበል መሟገት ያለበት ከኅሊናው ጋር ነው፡፡ ሁኔታዎቹ ጉቦ ለመቀበል ያመቻሉ ወይስ አያመቹም አይደለም መመዘኛው፡፡ ሰው በዘመድ አዝማድ ለመሥራት መመዘኛው የነገሩ ትክክል መሆን እና አለመሆን እንጂ ጊዜው ለዘመድ አሠራር ያመቻል ወይስ አያመችም መሆን አልነበረበትም፡፡
አሁን አሁንኮ ገበያ ኅሊናን እና ልቡናን እየተካ ነው፡፡ የሞራልን እና የእምነትን ቦታ እየወሰደ ነው፡፡ ሁሉ ገበያ መር ከሆነ ለዚህ ሕዝብ የሚያዝንለት ታድያ ማነው? ነጋዴውም ለገበያው፣ ባለ ሥልጣኑም ለገበያው፣ የሃይማኖት መሪውም ለገበያው፣ ገበሬውም ለገበያው ብቻ ከታዘዘ ለኅሊናው የሚታዘዝ ማን ሊሆን ነው፡፡ ይህ እኛ የምናገለግለው፣ የምንሸጥለት፣ የምንወስንለት እና የምንወስንበት ሕዝብ የኛ አይደለም እንዴ፡፡
ገበያው አመቼ ተብሎ የአንድ ብር ጨው አሥር ብር፣ የሁለት መቶ ብር በግ ሦስት ሺ ብር፣ የአሥር ብር ዘይት መቶ ብር፣ የሰባት ብር ስኳር ሃምሳ ብር፣ የሦስት መቶ ብር ጤፍ ሁለት ሺ ብር፣ የሁለት ብር ሽንኩርት ስድሳ ብር መሸጥ አለበት እንዴ፡፡ ይህኮ ዕቃ መሸጥ አይደለም የገዛ ሕዝብን መሸጥ እንጂ፡፡ እንዴት ባህል አንድ ያደረገንን፣ እንዴት ታሪክ አንድ ያደረገንን፣ ገበያ ይለያየናል፡፡ እንዴት እምነት ያፋቀረንን፣ ኢትዮጵያዊነት ያስተዛዘነንን ገበያ ያጨካክነናል፡፡
እንዴው ለመሆኑ እኛ ሰባኪ፣ ዘማሪ፣ ፓስተር፣ ቄስ፣ ሼክ፣ አስመላኪ፣ አስዘማሪ፣ አስ ሰጋጅ፣ ነቢይ፣አጥማቂ፣ መጋቢ፣ አለቃ፣ መልአከ እገሌ፣ ጳጳስ፣ የተባልነው ሰዎች እውነት እንነጋገርና ለቦታው ተገቢ ስለሆንን፣ ዕውቀቱ ስላለን፣ ቦታውን የሚመጥን ጸጋ እና ቅድስና ስላለን ነው ወይስ ገበያው ስላመቼ ነው የተቀመጥነው፡፡ ለመሆኑ የያዝነው ቦታ ክብር፣ ዝና፣ ገንዘብ እና ጥቅም፣ የማያስገኝ ቢሆን ኖሮ አሁን ባለንበት ቦታ ተለምነን እንኳን እንቀመጥ ነበር? ገበያ ስለሚያመች ግን ለቦታው የተሠራውን ሥርዓት ሸጥነው፤ መመዘኛውን ቸበቸብነው፡፡ የፈጣሪን ጸጋ በገንዘብ ለወጥነው፡፡ እኛ ወደ ቦታው መሄድ ሲገባን ቦታውን ወደ እኛ አመጣነው፡፡
ይኼ በየቤተ እምነቱ የምንሰማው ትርምስ፣ ግርግር፣ ውጣ ውረድ፣ ትግትግ፣ ጭቅጭቅ፣ ሙግት በዋናነት የገበያ ግርግር ነው፡፡ ዛሬ ገበያው ከሚገባቸው ሰዎች ይልቅ ለጮሌዎች ያመቻል፡፡ ዛሬ ገበያው ኅሊናቸውን በጥሩ ዋጋ መሸጥ ለሚችሉ ሰዎች ያመቻል፡፡ የሚገባቸው ሰዎች በየጓዳው እና በየፍርክታው ቀሩና የማይገባን ሰዎች ቦታውን ያዝነው፡፡ እነዚያ ለምን ቀሩ? ኅሊናቸውን መሸጥ ባለመቻላቸው፡፡
«በከንቱ የተቀበላችሁትን በከንቱ ስጡ» ያለውን የፈጸሙትማ ኩርማን እንጀራ በልተው፣ አጎዛ ላይ ተቀምጠው፣ መደብ ላይ ተኝተው ለፈጣሪ ሲያገለግሉ ኖሩ፡፡ እነዚያማ እውነትን ለገበያ ከማቅረብ ይልቅ ለያዙት እውነት መሞትን መረጡ፡፡ እነዚያማ በአቋማቸው ላይ ከመደራደር ይልቅ ከነ አቋማቸው መሰቃየትን መረጡ፡፡ እነዚያማ ጥያቄያቸው ስንት? የሚል ሳይሆን ለምን? የሚል ሆነ፡፡ እውነተኞች እንጂ ገበያተኞች መሆን ስላቃታቸው ከገበያ ውጭ ሆኑ፡፡
ገበያ ካመቸ ልጅም ትዳርም እንደሚሸጥ በዘመናችን አየንኮ፡፡ እዚህ አሜሪካ ብቻቸውን ለሆኑ እናቶች መንግሥት የሚሰጠው የተለየ ክብካቤ እና የገንዘብ ርዳታ አለ፡፡ ታድያ አንዳንዱ ባለ ትዳር የሀገሬ ሰው ተስማምቶ በፍርድ ቤት ይለያያል፡፡ ከዚያም ባልም ለብቻ ሚስትም ለብቻ በመኖር ይህንን ርዳታ ይቀበላሉ፡፡ ባህል ደኅና ሰንበት፣ ይሉኝታ ደኅና ሰንብት፣ ሃይማኖት ደኅና ሰንብት ማለት ይኼኔ ነው፡፡
አንዳንድ ቦታማ ይኼ ተለያይቶ መኖር ይለምድባቸውና በዚያው ተፋትተው የሚቀሩ ብዙ ናቸው፡፡ የአሜሪካ ገበያ ትዳርን ሽጦ ገንዘብ ያስገኛል፡፡ ገበያ ካመቸ ምን የማይሸጥ ነገር አለ፡፡
በአሜሪካ ምድር የቅንጦት መኪኖችን ከሚነዱ የሀገሬ ልጆች መካከል ጥቂቶቹ ልጆቻቸውን በመሸጥ የገዙት መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡ ልጅ ለማሳደግ አልቻልኩም ብለው ለአሳዳጊ ሰዎች ያስረክባሉ፡፡ ከዚያም በአንድ በኩል ለልጆቻው ያወጡት የነበረውን ቆጥበው፣ በሌላ በኩል ደግሞ በልጆቻቸው ቁጥር የታክስ ተመላሽ አሠርተው በሚያገኙት ገንዘብ ደልቀቅ ያለ መኪና ገዝተው ደልቀቅ ብለው ያሽከረክራሉ፡፡ አይቆ ረቁራቸውም፣ አይሰማቸውም፣ አያንገበግባቸውም፣ አያሳፍራቸውም፡፡ ገበያ አመችቷቸው ኅሊናቸውንም ልጆቻቸውንም ሽጠዋልና፡፡
ባህላችን ካቆየልን በጎ ነገሮች አንዱ ለኅሊና መሞት ነው፡፡ በልማዳችን የጠፋ ከብት ያገኘ ሰው እንኳን እስከ ሰባት ዓመት ባለቤቱን ይጠብቅ ነበር፡፡ ሞራላዊነት ከማየሉ የተነሣ ተገፍቶ እና ተጨቁኖ ያደረገው ኢ ሞራላዊ ነገር እየቆረቆረው
ልጅ አሳድግ ብዬ
ካገር እኖር ብዬ
ላባሻ ዳርኩለት ሚስቴን እቴ ብዬ
እያለ ያንጎራጉር ነበር፡፡ አንድ ባላባት ተከትሎ የመጣ ጦረኛ በየገበሬው ቤት ይሠማራና ይቀመጣል፡፡ የገበሬው ሚስት ቆንጆ ከሆነች «ይህቺ እኅትህ ናት አይደል» ይለዋል፡፡ አይደለችም ካለ ይገድለዋል፡፡ ወይንም ያሳሥረዋል፡፡ እናም «አዎን» ይላል፡፡ በግድ አዎ አሰኝቶ ሚስቱን ይዞበት ያድራል፡፡ ይህንን ነው በእንጉርጉሮ የገለጠው፡፡
ዛሬኮ ተሰምቶት የሚያንጎራጉር የለም፡፡ እንዲያውም በኩራት ይነገራል፡፡ አራዳነት፣ ቀልጣፋነት፣ ብልጥነት፣ ሆኗል፡፡ ገበያ መር ኢኮኖሚ እንጂ ገበያ መር ማኅበረሰብ በሰላም እና በአንድነት መዝለቅ አይችልም፡፡ የማኅበረሰቡ እሴቶች በሙሉ ለገበያ እየቀረቡ እንዳመቺነቱ ከተቸበቸቡ ያን ሕዝብ አንድ አድርጎ የሚያስተሳስር ምን ነገር ይተርፈዋል?
አንጀቴ ተቆርጦ ከሆዴ ከወጣ
እንግዲህ ሐኪሙ ምን ሊቀጥል መጣ
አይደል ያለቺው ዘፋኟ፡፡
ሕይወት ለሰጠ ሞት?
Wednesday, March 14th, 2012ዳንኤል ክብረት
እናት ታምጣለች፡፡ ያለ የሌለ ኃይሏን ሁሉ እያሟጠጠች፡፡
የመንደሯ አዋላጅ እሜቴ ድንበሯ «አይዞሽ ግፊ» ይላሉ እየደጋገሙ፡፡ የመንደሯ ታላላቅ ሴቶችም ዙርያዋን ከብበው «ማርያም ማርያም» እያሉ ይለምናሉ፡፡
አንዳንዶቹ «የመጀመርያዋ ስለሆነ ነው» ይላሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ «ምናልባት ጭንቅላቱ ትልቅ ሆኖ ይሆናል» ይላሉ፡፡ ብቻ ሁሉም በሁላገርሽ ላይ ምጡ የጠናበትን ምክንያት እንደ መሰላቸውን ይተነትናሉ፡፡
ሁላገርሽ መንፈሷም ዐቅሟም እየደከመ መጣ፡፡ ሰውነቷን ላብ አጠመቀው፡፡ ድንገት እንደ ብራቅ እሪ ብላ ስትጮኽ ልጁ ፈትለክ ብሎ ወጣ፡፡ በዚያውም የሁላገርሽ ነፍስም አብራ ወጣች፡፡
እሜቴ ድንበሯ «ኧረ ቀዘቀዘችብኝ፤ ኧረ አንድ በሉኝ» እየተርበተበቱ ጮኹ፡፡ የሚያደርጉት ነገር ግራ ገባቸው፡፡ ሁላገርሽ ቀዝቅዛባቸዋለች፣ ሕፃኑ ደግሞ ብቅ ብሏል፡፡
ይህን ጊዜ ወደዚህች ምድር አዲስ ሆኖ የመጣው ሕፃን አንዳች ፍጡር ከፊት ለፊቱ ቆሞ አየ፡፡ ጥልማሞት የመሰለ አስፈሪ ፍጡር፡፡ ርዝመቱ በመልአክ እንጂ በሰው ክንድ የማይደረስበት፡፡ በዓለም ላይ ያሉ አስቀያሚ ገጽታዎችን ሁሉ ሰብስቦ የያዘ፡፡ በእጁ ደግሞ የሁላገ ርሽን ነፍስ ይዟታል፡፡
ከሁላገርሽ ማኅፀን የወጣው አዲስ ሕፃን ገና የፍርሃት ስሜት አልተፈጠረበትም፡፡ ስለ ጭራቅ እና ስለ ሰይጣን የሚነገሩ እውነቶችንም ተረቶችንም ገና አልሰማም፡፡ ደግነት እና ክፋት፣ መልካም እና ክፉ ገና በማኅበረሰቡ ደንብ ተለይተው አልተሳሉበትም፡፡ እናም ያንን ጥልምያኮስ የመሰለ ፍጡር አልፈራውም፡፡
«አንተ ማነህ? ደግሞስ የእናቴን ነፍስ የትነው የምትወስዳት?» ሲል ጠየቀው፡፡
«እኔማ ሞት ነኝ፡፡ እናትህ አንተን እወልዳለሁ ብላ ሞተች፡፡ ያንተ ሕይወት ሲጀመር የእርሷ አለቀ፤» ሲል አሰቃቂ ጥርሶቹን ብልጭ አደረገበት፡፡
«እንዴት ሕይወት የሚሰጥ ሕይወት ያጣል፡፡ እንዴት ላለው ይጨመርለታል እንጂ ይወሰድበታል፤ እንዴት የሚሰጥ ይራባል፤ እንዴትስ የሚያበራ ይጨልምበታል» ሲል ጠየቀው፡፡
«እርሱን እኔ አልመልስልህም፤ የኔ ድርሻ ነፍሷን መውሰድ ብቻ ነው» አለው ሞት፡፡
«ይህ ከሆነማ እኔም እከተልሃለሁ፡፡ ምንጩን የሚያደርቅ ውኃ፣ ፋኖሱን የሚያጠፋ መብራት፣ ማሳውን የሚገደል እሸት፣ ዛፉን የሚገነድስ ፍሬ፣ ምጣዱን የሚሰብር እንጀራ መሆን የምፈልግ ይመስልሃል?» አለው ሕፃኑ፡፡
«እርሷን እንጂ አንተን ለመውሰድ አልመጣሁም» አለው ሞት ከፊቱ እንደ መራቅ እያለ፡፡
«ነገርኩህኮ እኛ ሰዎች እንጂ እፉኝቶች አይደለንም፡፡ የእፉኝት ልጆች ሲፀነሱ አባታቸው፣ ሲወለዱ እናታቸውን ይገድላሉ ይባላል፡፡ እኛ ግን ሰዎች ነን፡፡»
«አንተ ለፈጣሪ የሚጠየቀውን ጥያቄ ነው እኔን የምትጠይቀኝ» አለው ሞት፡፡
«አሁን ገና እውነት ተናገርክ» አለና ሕፃኑ አንገቱን ወደ ሰማይ ቀና አደረገ፡፡ ከዚያም እንዲህ ሲል አሰምቶ ጮኸ፡፡
«ፈጣሪ ሞቷል»
ያን ጊዜ እልፍ አእላፍ መላእክት እንደ እሳት ላንቃ የሚንበለበል ሰይፋቸውን መዝዘው፣ የእሳት ዝናር ታጥቀው በሕፃኑ ዙርያ ቆሙ፡፡
«ምን አልክ?» ሲል አንደኛው መልአክ ጠየቀው፡፡
«ፈጣሪ ሞቷል» አለና ሕፃኑ ላንቃው እስከሚሰነጠቅ ጮኸ፡፡
«ይህ የድፍረት ኃጢአት ነው፤ ከባድ ወንጀልም ነው፡፡ አንተ ገና ዓለምን አላየህም፤ መጻሕፍትን አላነበብክም፣ ከሰዎች ሕይወት አልተማርክም፤ ከራስህም ሕይወት ልምድ አልቀሰምክም፡፡ እንዴት ከጥቂት ሰዓታት በፊት ተወልደህ እንዲህ ያለ ድፍረት ይወጣሃል» ሲል ተናገረው መልአኩ በቁጣ፡፡
«ልክ ነው» አለ ሕፃኑ፡፡ «ልክ ነው የተናገርኩት ድፍረት እንደሆነ፤ እመቀ እመቃት የሚከት ኃጢአት እንደሆነም ዐውቃለሁ» አለ ሕፃኑ በዙርያው የከበቡትን መላእክት በለጋ ዓይኑ እያየ፡፡ «ግን እስኪ ልጠይቃችሁ? ሕይወት የሰጠችኝ እናቴ ከሞተች፣ ለዓለም ሕይወት የሰጠ ፈጣሪ ሞቷል ማለት ነውኮ፡፡ እናቴኮ የፈጣሪን አደራ ተረክባ የፈጣሪን ሥራ ነበር የሠራችው፡፡ ሕይወትን ለሰጠ ዋጋው ሞት ከሆነ ለዓለም ሕይወትን ለሰጠ ፈጣሪ ምን ዋጋ ተከፈለው ታድያ?» ሲል ጠየቃቸው፡፡
በዚህ ጊዜ የብዙዎቹ መላእክት ሰይፎች ቀዘቀዙ፡፡ የአንዳንዶቹም ወደ ሰገባቸው ተመለሱ፡፡ ሌሎች ደግሞ ያንን የሰዓታት ሕፃን በአንክሮ ተመለከቱት፡፡ እንዲህ ያለ ነገር አጋጥሞት የማያውቀው ሞት ግራ ተጋባ፡፡ ጉዳዩ በዚህ እንደማያቆም ገባው መሰል እፍን አድርጎ ይዟት የነበረውን የሁላገርሽን ነፍስ ለቀቅ አደረጋት፡፡
ወዲያው ምድርን ከአፅናፍ እስከ አጽናፍ ያነጋነገ ክስተት ተፈጠረ፡፡
ፀሐይ ጨለመች፡፡ ከዋክብት ረገፉ፡፡ ወንዞች እና ምንጮች ደረቁ፡፡ አየራት ጸጥ አሉ፡፡ ምድር መዞሯን አቋርጣ ቆመች፡፡ በሕፃኑ ዙርያ የቆሙት መላእክት የምጽአት ቀን የመጣ መሰላቸውና ሰይፋቸውን መዘዙ፡፡
ከሰማያት የመጣ ድምጽ ግን ፍጡራንን እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፡፡ «ለምን እንዲህ አደረጋችሁ?»
ፀሐይም ተነሣች፡፡ እንዲህም አለች «እኔ ለዚህ ዓለም ሌት ተቀን ብርሃንን እሰጣለሁ፡፡ እኔ የምሰጠውን ብርሃን የሚቀበል፣ ነገር ግን ብርሃኑን የምሰጠውን እኔን የማይፈልግ ሕግ ካለ ለምን እኖራለሁ?»
ከዋክብቱ «የኛም ጥያቄ ነው» አሉና ብልጭ፣ብልጭ፣ ብልጭልጭ ብለው አጨበጨቡ፡፡
ወንዞችም እንዲህ አሉ፡ «ውኃ የሚሰጥ ወንዝ እንዲደርቅ ከተደረገ የኛ መኖርስ ለምንድን ነው?»
ምንጮችም «ይህ የኛም ጥያቄ ነው» አሉና ፏፏቴ አሰሙ፡፡
አየራትም አሉ «የኛን አየር እየተነፈሱ እኛን የሚበክሉን ከሆነ ከዚህ ሰዓት ጀምሮ መኖር አንፈ ልግም»ከአራቱ መዓዝናት የተነሡ ነፋሳትም ዊይይይይው፣ዊይይይይው ብለው አጨበጨቡ፡፡
ምድርም ተናገረች፣ እንዲህም አለች «እኔ እዞራለሁ፣ ቀንና ሌሊትን አፈራርቃለሁ፣ ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑትን ሁሉ እሰጣለሁ፤ አገልግሎቴን እንጂ እኔን ካልፈለጉኝ፤ ጥቅሜን ወስደው እኔን በኬሚካል እና በበካይ ጋዝ ከገደሉኝ ለምን እዞራለሁ፤ ዛፎቼን ቆርጠው ሳንባ ከነሱኝ ለምን እንከራተታለሁ?»
የፍጡራን አቤቱታ ሲያበቃ ሕፃኑ ቀጠለ
«እኔ ለፈጣሪ አንድ ጥያቄ አለኝ»
ከሰማይ የመጣውም ድምጽ «ተናገር» አለው፡፡
«አንተ የሕይወት መገኛ ነህ፤ ግን አንተ ትሞታለህ?» አለና ጠየቀ፡፡
በዚህ ጊዜ ሞት ደነገጠ፤ ነገሩ በእርሱ ላይ የተጠመጠመ መሰለውና የሁላገርሽን ነፍስ በሁለት እጁ እንደ ማቀፍ አደረጋት፡፡ ምንም እንኳን የሞት እቅፍ ባይሞቅ፡፡
«ደግሞስ» አለ ሕፃኑ «አባት እና እናታችሁን አክብሩ ብለሃል፤እኔ ስወለድ እናቴ ከሞተች ሕግህ እንዴት አድርጎ ይፈጸማል? እናትነትስ እንዴት ክብር ይሆናል? መውለድኮ በዓለም ላይ ትልቁ ኃላፊነት ነው፡፡ ሰዎች ገንዘብ፣ ወርቅ፣ አልማዝ በኃላፊነት ሊቀበሉ ይችላሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ ግን ሰው ይበልጣቸዋል፡፡ ሰውን ያህል ፍጡር በኃላፊነት ተቀብሎ፤ ተሸክሞ፤ አሳድጎ፤ ከሚበሉት አካፍሎ፤ ተጠንቅቆ፤ የራስን ሕይወት አካፍሎ፤ መከራን ተቀብሎ ሰው ማድረግ የፈጣሪን ሥራ መሳተፍ ነው፡፡ ይህንን ኃላፊነት የተወጣች እናት መሸለም ሲገባት እንዴት ሞት ይታዘዝባት?
«እንዲያውም አንድ ሕይወት ለሰጠች ሁለት ይገባት ነበር፡፡ እርሷኮ ሠላሳ፣ ስድሳ፣ መቶ ያፈራች ዛፍ ናት፤ እንዴት ትቆረጣለች? የፍትሕ ሀገሯ የት ነው? የርትዕስ ማደርያዋ ወዴት አለ?
«ከዚህ በላይስ ፍቅር ወዴት ይገኛል? ሕይወት ለመስጠት ሲሉ ከመሞት፣ ራስን ለሌላ ሲሉ ከመሠዋት በላይስ ፍቅር የታለ? የፍቅር ዋጋውስ ይህ ነውን? ራሱ ፈጣሪስ ፍቅር አይደለምን? ታድያ ለዚህ ፍቅሩ ዋጋው ሞት መሆን አለበትን?
እነሆ ከሰማይ ድምፅ መጣ፡፡
«ሕይወት የምትሰጥ እናት ሕይወት እየሰጠች በወሊድ መሞት የለባትም፤ ለሕይወት ሞት፤ ለደግነትም ክፋት፣ ለጣፋጭም መራራ ሊከፈል አይገባም» አለ፡፡
ይህን ጊዜ ሞት የሁላገርሽን ነፍስ ወደ መሬት ለቀቃት፡፡ መላእክትም እልል አሉ፡፡ የመላእክትን ድምፅ ሰምተውም ለልቅሶ ተዘጋጅተው የነበሩ የመንደሯ ሴቶች አብረው እልል አሉ፡፡
«እናት ሕይወት ስትሰጥ ሕይወቷን እንድታጣ ያደረገ ባል፣ መንደርተኛ፣ ሐኪም፣ ሾፌር፣ መድኃኒት ሻጭ፣ ርዳታ ሰጭ፣ አዋላጅ፣ እስከ ሰባት ትውልድ ነፍሱ አትማርም» የሚል አዋጅም ታወጀ፡፡
ይህን ጊዜ በቤቱ የሕፃን ልቅሶ ተሰማ፤ የመንደሩም ልቅሶ በሁለት እልልታ ታጀበ፡፡ በሁላገርሽ ትንሣኤ እና በሕፃኑ መወለድ፡፡
