Author Archive
Friday, July 13th, 2012
ከአቤ ቶኪቻው
ዛሬ አዲሳባ ፍትህ ጋዜጣ ላይ የምትወጣ ስለ አቶ መለስ መጥፋት አበክራ የምትጠይቅ እና የምትጨነቅ አንድ ጨዋታ አለችኝ። ለዝች ብሎግ አንባቢዎች ነገ ትለጠፋለች። እስከዛ ይቺን መቆያ እንኩማ፤
ያው ሁላችንም እንደሰማነው አቶ መለስ ተይዘዋል። ስንቱን ሲይዙ የነበሩት ሰውዬ አሁን ግን ራሳቸው በእግዜሩ በሽታ ተይዘዋል። በህመማቸው ሳቢያም ፓርላማው እንኳ ይኸው የ2005 ዓ.ም በጀቱን እስካሁን አላፀደቀም።
እኔ የምለው ግን በቃ አቶ መለስ ከሌሉ ሁሉም ነገር አለቀለት ማለት ነው? የምር ይሄ ነገር በጣም ያሳስባል።
ልክ እንደ አቶ መለስ ሆኖ የሚጫወት “ካስት” እንዴት አይኖርም!? እሳቸው ስለታመሙ እከሌ ወይም እከሊት እንደ አቶ መለስ ሆነው ይጫወቱልናል! መባል የለበትም እንዴ!? የቡድን ስራ ምናምን የሚባል ነገር የለም ማለት ነው…? አይበልባቸውና የሆነ ነገር ቢሆኑ ታድያ ምን ሊውጠን ነው!
ለማንኛውም ይቺን ያኽል ከተንደረደርን ወደ ፉገራችን እንግባ፤
እንግዲህ ይህ ዘገባ የሚተላለፍላችሁ በእግዜር ቁጥጥር ስር በሚገኘው ቴሌቪዥን ነው አሉ። በእግዜር ቁጥጥር ስር የሚገኝ ቴሌቪዥን የቱ ነው? ካሉኝ ህልም መሆኑን እገልፃለሁ። የምር ግን እግዜር ህልምን ያህል ቴሌቪዥን በእያንዳንዳችን ላይ ገጥሞ ሳለ ለገዛ ፕሮፖጋንዳው መጠቀም ሲችል በነፃነት የፈለገንን እንድናይ ማድርጉ ምን ያህል ዲሞክራት ቢሆን ነው ብለው አይደነቁም! በእውነቱ እንደ እግዜር አይነት ነፃነት የሚሰጠንን መንግስት ያምጣልን! እንደርሱ እንኳ የትም አይገኝም ግን ቢያንስ የሚቀራረብ…
ለማንኛውም እግዜር ኢህአዴግ አይደለም እንጂ ቢሆን ኖሮ የአቶ መለስን መያዝ አስመልክቶ በቴሌቪዥኑ እንዲህ ይል ነበር፤ ብለን ብንገምት ምን ይለናል!? በነገራችን ላይ ይህ ዜና ቃል በቃል ከዚህ በፊት እነ እስክንድር ነጋ፣ እነ አንዳለም አራጌ፣ እነ ውብሸት እና ርዮት የተያዙ ጊዜ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ያነበበልን ነው። ልዩነቱ እነ አስክንድርን የያዛቸው ፖሊስ ነው አቶ መለስን ደግሞ በሽታ ነው፤
አባቴ በህመም አይቀለድም ይለኝ ነበር። ነገር ግን በላዬ ላይ ያደረው በል ብሎኛልና እንደሚከተለው እጀምራለሁ፤ አባቴ ይቅርታ አድርግልኝ። እርስዎም ሲጀምሩ እግዜሩ ይቅር ይበልህ ብለው ከጀምሩልኝ ችግር የለውም!
ገመትን፤
አቶ መለስ ዜናዊ ራሱን ኢህአዴግ ብሎ ከሚጠራ አሸባሪ ድርጅት ጋር የህዝብን መሰረተ አንድነት እና የሀይማኖት አውታሮችን ለማፈራረስ ሲንቀሳቀሱ በህብረተሰቡ ጥቆማ እና በፌደራል በሽታ እና ፀረ ሽብር ወቅስፈት ግብረ አይል በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ግለሰቡ በውጪ ሀገር የሚንቀሳቀሰው ቻይና ኮሚኒስት የተባለ አፋኝ ድርጅት የሀገር ውስጥ አደራጅ፣ ቀስቃሽ እና አንቀሳቃሽ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ስልጣንን ሽፋን በማድረግ አብዮታዊ ዴሞክራሲ አክራሪነት እንዲስፋፋ፣ አንድ ለአምስት የሚል ህዋስ በመፍጠር በመላው ሃገሪቱ መረብ ዘርግተው ሀገሪቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ የሽብር ጥፋት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ታውቋል።
ተጠርጣሪው ግለሰብ በልማት ስም ሰላማዊ የሀይማኖት ሰዎችን ከፀሎት ስፍራቸው በማፈናቀል እንዲሁም ህገ መንግስቱን ሽፋን በማድረግ በርካታ ሙስሊሞችን ኢላማ ያደረገ ጥቃት ሲፈፅሙ እንደነበር ፌደራል በሽታ እና ፀረ ሽብር ወቅስፈት ቡድን አረጋግጧል።
ተከሳሹ በቁጥጥር ስር ሲውሉ ህመሞቹ የመያዣ ፈቃድ እንዳሳዩዋቸው እና በአሁኑ ሰዓት በተኙበት ቦታ የተለያዩ በሽታዎች በጥበቃ ስር ያሉ ሰዎች ማግኘት ያለባቸውን ተገቢ እንክብካቤ እያደረጉለት መሆኑን ተጠርጣሪው ራሳቸው አረጋግጠዋል!
አቶ መለስ ዜናዊ በአሁኑ ሰዓት የተያዙ ሰዎች መብት እንዲያገኙ መደረጉን ለማረጋገጥ የተለያዩ ጎብኚዎች እንዲመለከቷቸው ተፈቀዷል። ጎብኚዎቹም ተጠርጣሪው እንደፈለጉ ማቃሰት እና የሚያስፈልጋቸውን ነገርም ያለ አንዳች ገደብ ሲጠይቁ መመልከታቸውን ተናግረዋል።
የተጠርጣሪው ግለሰብ ፍርድ ነፃ እና ገለልተኛ በሆነው መንግስተ ሰማያት መታየት የተጀመረ ሲሆን ጥፋታቸውን አምነው እና ተፀፅተው ይቅርታ ከጠየቁ ምህረት ሊደረግላቸው እንደሚችል ተያይዞ የደረሰን ዜና ያመለክታል።
በድጋሚ ይቅር ይበለን ዜናው አበቃ!
Filed under: Uncategorized

Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 7 Comments »
Wednesday, July 11th, 2012
በ1998 ዓ.ም አካባቢ ከጓደኞቼ ጋር ሆኜ፤ ለአንድ ስታስቲክሳዊ ስራ ወደ ወደ አርማጭሆ አካባቢ ሄጄ ነበር። በወሬ ደረጃ ስንሰማው የነበረ “አርበኞች ግንባር” በመባል የሚታወቅ የታጠቀ ቡድን እዚህ አካባቢ “በህይወት” መኖሩን ሰማሁ። ለስታስቲክሳዊ ስራው የገጠሩን መንደር መንገድ እንዲመሩን የተመደቡልን የመንግስት ታጣቂዎች ነበሩ። እኔ እና ሌሎች ከአዲሳባ ለስራ ወደ እዚህ የመጣን ልጆች ስለ አርበኞች ግንባር በደንብ ለማወቅ ጉጉት አድሮብናል። ነገር ግን የመንግስት ታጣቂን ስለ ተቃዋሚ ለዛውም ስለ ሸማቂ ሃይል መጠየቅ እየፈራን እየተባን በአካባቢው ስለሚኖሩ ሽፍቶች በመጠየቅ እናሟሙቅ ጀመር።
“እዚህ አካባቢ ሽፍታ አለ ይባላል እውነት ነው?” አልነው አጃቢያችንን፤
“እንዴ ጋሼ ሽፍታማ ሃገሩ ነው!” አለን በኩራት። (በነገራችን ላይ አርማጭሆ ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያ ያሉ ክፍለ ሀገሮች ቢሄዱ በእድሜ የሚበልጥዎም ሰው እንኳ “ጋሼ” ብሎ በአክብሮት ነው የሚጠራዎት። እናውቃለን ባክህ… ካሉኝ “እኮ…” ብዬ ቀጥላለሁ!)
ጥያቄያችን ቀጥሏል።
“ሰዉ ምን ሆኖ ነው የሚሸፍተው…?” አልነው።
“ሰበቡማ ብዙ ነው ምሰሌ፤ በመንደር ግጭት የተጠቃ እንደሆነ፤ አኩርፎ ጥቃቱን ለመወጣት ይሸፍትና በዛው ሽፍታ ሆኖ የሚቀር አለ…” ልክ ይህንን ምላሽ እንደሰማሁ፤ መቼም ያን ጊዜ ቀልጣፋ ነበርኩ፤ ለማወቅ ወደፈለግነው ዋና ነጥብ ቀልጠፍ ብዬ ገባሁ፤
“በመንግስት ላይ አኩርፎ የሚሸፍትስ የለም?” ብዬ ጠየቅሁ…!
ይሄኔ መንገድ መሪያችን የመንግስት ታጣቂ ያነገታትን አሮጌ ክላሽ ከፍ ከፍ እያደረገ፤
“እሱማ ምን ይጠፋል!?” ብሎ በጥርጣሬ እያየን ዋናው ጨዋታችንን በአጭሩ ሊቀጨው ፈለገ። ስለ አርበኞች የማወቅ ጉጉት የሁላችንም ነበርና አንዱ ወዳጃችን፤
“አርበኞች የሸፈቱት በመንግስት ላይ አኩርፈው አይደል እንዴ!?” ብሎ ሌላ ጠቋሚ ጥያቄ አመጣ። በሆዳችን ጎ…በዝ ብለን ወዳጃቸንን አደነቅን!
ይሄን ጊዜ የገጠሩን መንገድ ሲመራን የነበረው የመንግስት ታጣቂ ቆም አለና፤ ትክ ብሎ አየን፣ ከዛም በሆዱ “የመጣው ይምጣ!” ያለ በሚመስል መልኩ፤
“ጋሼ አትሳሳት አርበኛማ ሽፍታ አይደለም። አርበኛ የአላማ ሰው ነው!” ብሎ መንግድ መምራቱን ቀጠለ።
በእውነት በጣም ነበር የተደነኩት። በወቅቱ የሄድነው ለመንግስት ስራ ነበር። መንገድ የሚመራን የመንግስት ታጣቂ ነው። ይህ የመንግስት ታጣቂ ስለ ሸማቂው የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባር በአድናቆት ሲናገር መስማት በእውነቱ ያስገርማል። ግንባሩ እውነትም በህዝብ ልብ ውስጥ የገባ ስለመሆኑ ማስረጃ ነው።
ከዛ በኋላ በይፋ ድጋሚ ስለ አርበኞች ግንባር የሰማሁት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ነበር። “ሀገር ጫታ ሆነ!” በሚል ርዕስ በ2001 ዓ.ም አካባቢ (ነው መሰለኝ) መንግስታችን ከዛ በፊት አንድም እንኳ፤ በዛ አካባቢ ስለነበረው እንቅስቃሴ ያልነገረን ለግንባሩ እውቅና ላለመስጠት ነበር ለካ!
“ሀገር ጫታ ሆነ” በሚለው እና ስለ አርበኞች ግንባር የሚዳስሰው የኢቲቪ ፕሮግራም ስለ አርበኞች ግንባር ተጨማሪ ማወቅ ቻልን…! “ለካስ እነዚህ ሰዎች በዚህ ደረጃ መንግስታችንን አስጨንቀውታል!?” እኛኮ መንግስታችን ዝም ሲል ግንባሩን ከቁብም አልቆጠረውም ብለን ነበር። ለካስ የሆዱን በሆዱ ችሎ ነው ፀጥ ያለው…? ምስኪን መንግስታችን! ብለን አዘንን።
ከዛ በኋላ ለረጅም ጊዜ ስለዚህ ግንባር በቅጡ ሰምቼ አላውቅም ነበር። አሁን በቅርቡ ደግሞ ሌላ ወሬ ሰማሁ።
በዋልድባ ገደም ህልውና ላይ እየተገነባ ያለው የስኳር ፋብሪካ ግንባታ ባለፉት ሰሞናት ብዙ ሲያነጋግር ቆይቷል። ኢቲቪም ትንሽ “ፎገር ፎገር” አድርጎ ነገሩን አንደተረሳ አድርጎታል። የአካባቢው ህዝብ መነኮሳቱ እና ምዕመኑ ግን ዝም አላሉም ለፈጣሪም ለህዝቡም አቤት እያሉ ነበር። ቢሆንም ግን መንግስት አካባቢውን በጦር ከቦ ቁፋሮውን ተያይዞታል። እሰይ የኔ አንበሳ! ብለን አድንቀን ሳንጨርስ ታድያ ሌላ ነገር ሰማን፤ ምን…? አዲስ መስመር ላይ አለልዎት
አርበኞች ግንባር፤ “በአካባቢው የህዝቡን ተቃውሞ ችላ ብለው በቁፋሮ የተሰማሩ መሳሪያዎችን አወደሜያለሁ” የሚል መግለጫ አወጣ።
ከላይ እንዳልነው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር። ልክ እንደ ኢህአዴግ ብሶት የወለደው፤ በኢህአዴግ አመራር ተማሮ ጫካ የገባ የታጠቀ ሃይል ነው።
ባለፈው ጊዜ ደጀ ሰላም የተሰኘ ድረ ገፅ በዋልድባ ገዳም መነኮሳት መታሰራቸውን እና ለተቃጠለው ዶዘር እና ለተሰነዘረው ጥቃት ሃላፊነቱን ትወስዳላችሁ። መባላቸውን ዘግቦልን ነበር። እስከ አሁንም መነኮሳቱ በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ አልሰማንም። ልብ አድርጉ ሸማቂዎች ላደረሱት ጉዳት ተጠያቂው ከዋሻ ወጥተው የማያውቁ መነኮሳት ተደርገዋል።
አሁን እንግዲህ አንድ ጥያቄ ልጠይቅ ነው። ጥያቄው የኢህአዴግ አባላትን ደጋፊዎችን እና ተደጋፊዎችን ይመከታል። ማሳሰቢያ መልሱን በትግሉ ወቅት የተሳተፉ አንዲመልሱ ይበረታታል። ከድህነት ጋር የምትታገሉትን አላልኩም።
እኔ የምለው ኢህአዴግ በትግል ላይ እያለች የደርግ አድናቂ ነበረች ማለት ነው…? ከመቼው ገብተን ከመቼው እንደ ደርግ በሆነን! ብላ አብዝታ ታስብ ነበር ማለት ነው? የታጠቀ ሃይል ሃላፊነቱን እወስዳለሁ ባለበት ጥቃት የአካባቢው ሰው እና የሀይማኖት አባቶችን ማሰር አግባብ ነው!? ወይስ መነኮሳቱ በዋሻ ውስጥ ሲገኙ ምሽግ ውስጥ ያሉ ታጋዮች መስዋቸው ነው!?
በመጨረሻም
እመክራለሁ
ጎበዝ ይሄ ነገር ብሶትን ማቀጣጠል በመባል ይታወቃል። ደርግም ጉድ የሆነው እንዲሁ ለታጋዮች ጥቃት በአፀፋው ህዝቡን ሲያንገላታ ነው! እንደ እውነቱ ከሆነ፤ ይሄንን እናንተው በትግል ላይ ያሳለፋችሁት እንጂ፤ እኔ ከኑሮ ጋር የምታገለው ግለሰብ ልነግራችሁ አይገባም ነበር። ግን ተናግሪአለሁ ባለስልጣኖቻችን ሆይ የብሶት ማርገብገቢያ አትሁኑ!
Filed under: Uncategorized

Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 1 Comment »
Tuesday, July 10th, 2012
ትላንት ሐምሌ 2/ 2004 ዓ.ም ታዋቂው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ኬኒያ በሚገኘው ኤርትራ ኤንባሲ መታየቱን ናይሮቢ የሚገኙ ኤርትራዊ ወዳጆቼ ነገሩኝ። ኃይሌ ገብረስላሴ ኤርትራ ኤንባሲ ምን ይሰራል!?
በነገራችን ላይ እንዲህ አይነት የጭምጭምታ ወሬዎችን መናቅ አይገባም። ከዚህ በፊት ራሱ ኃይሌ ገብረስላሴን ጨምሮ ሌሎችም ራሳቸውን “ሽማግሌ” ብለው የሚጠሩ ግለሰቦች ተሰባስበው በቃሊቲው እስር ቤት ሲመላለሱ ነበር። የሚል ጭምጭምታ በሰማን በማግስቱ ነው ነገሩ ሽምግልና መሆኑ የተሰማው። ማን ያውቃል አሁንም ኃይሌ ኤርትራ ኤንባሲ በታየ በነጋታው አቶ ኢሳያስ እና አቶ መለስ ሊሸማገሉ ነው የሚል ዜና እንሰማ ይሆናል።
እንግዲህ ዝርዝሩን ወደፊት የምንሰማው ቢሆንም፤ ለጊዜው ግን እኔ ነገር መደበቅ አይሆንልኝምና እንሆ ሹክ ብያችኋለሁ። ኃይሌ ገብረስላሴ በኤርትራ ኤንባሲ ትላንት ታይቶ ነበር። መቼም “የኢትዮጵያ ኤምባሲ መስሎኝ ነው” አይለንም። ታድያ እንዴት እዛ ሊገኝ ቻለ?
ይቺን ያህል እኔ ወሬ ካቀበልኩ፤ እንዴት? ለምን? ከየት? ወዴት? የሚሉትን ጠለቅ ያሉትን ግምቶች ለፕሮፌሽናል ገማቾች እንተዋለን!
ኃይሌ ገብረስላሴስ የተመለከቱት ወዳጆቼ ጠርተው ሰላምታ ሰጥተውት እሱም “ታድያስ ሰላም ናችሁ” ብሎ አፀፋውን የሰጣቸው ሲሆን ከሁለት አማርኛ ተናጋሪ ሰዎች ጋ እንደነበረም ሹክ ብለውኛል!
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 7 Comments »
Tuesday, July 3rd, 2012
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 7 Comments »
Tuesday, June 26th, 2012
አቤ ቶኪቻው
ድሮ ድሮ አሉ የሰው ልጆች ቋንቋ ሁሉ አንድ ነበር። ታድያ ከእለታት በአንዱ ቀን ትልቅ ግንብ ገንብተው ፈጣሪያቸው ያለበት ሰባተኛው ሰማይ ላይ ደርሰው ምን እያደረገ እንደሆን ሊሰልሉት አሴሩ።
የሀሳባቸውን ለመሙላትም፤ አንድም የሰው ልጅ ሳይቀር ተሰባስበው በዚህ እኩይ ስራ ላይ ተጠመዱ። እግዜርም ይህ የማይሆን የቂል ሀሳባቸው እንደማይሳካ ያውቃልና፤ በሌሎች መልካም ስራዎች ላይ ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ፣ እንዲሁም በዚህ የተነሳ የሚደርስባቸውን አደጋ ለመታደግ ብሎ ይህንን ስራ ሊያቋርጥባቸው ፈለገ። ከዛም ቋንቋቸውን ደበላለቀው። ከዛስ…? ከዛማ አንዱ ብሎኬት አምጣ ሲል ውሃ ሲያቀብለው፣ ሙገር ሲሚንቶን አቀብለኝ ሲል የቀበና አሸዋ ሲያመጣ ግንቡ በየት በኩል ይግባቡ በየት በኩልስ ይገንቡ!? ሀሳባቸው ከንቱ ሆኖ ቀረ።
ይህ ታሪክ አፈታሪክ ይሁን ሀይማኖታዊ ታሪክ እንጃ፤ ግና ከድሮም ጀምሮ ስንሰማው ኖረናል። ንግግራችን እና ቋንቋችን ለመልካም ካልሆነ ቢደበላለቅ በስንት ጣዕሙ! የሚል አንኳር ሃሳብም ይዟል። እውነትም አለው።
በዛ ሰሞን “ስካይፕ እና የመሳሰሉት የኢንተርኔት ቴክኖሎጂዎች በኢትዮጵያ ምድር መጠቀም ሊያስቀጣ ነው።” ተብለን፤ “አይይይ… እንግዲህማ ምን ቀረ…? ከዚህ ቀጥሎ ህልማችንንም ቁዘማችንንም ፀሎታችንንም በአዋጅ የምንቀማበት ጊዜ ደረሰ አይደለምን!?” ብለን እጅግ አድርገን ስናማርር ድንገት ከመንግስት ባለስልጣናት አንዱ ቤቴሌቪዥናችን ብቅ ብለው “ስካይፕም ሆነ ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን በአዋጅ ሊከለክሉ ነው የተባለው በሬ ወለደ ወሬ ነው” ብለው ተስፋ ሰጥተውን ነበር።
በነጋታው ደግሞ ሌላው ባለስልጣን ተነስተው፤ “ስካይፕም ሆነ ሌሎች የቴሌን ገቢ የሚቀንሱ እና በደህንነት ስጋት የእኛን ኪሎ የሚቀንሱ የኢንተርኔት አገልግሎቶችን ጥርቅም አድርገን እንዘጋለን ምን ታመጣላችሁ!?” አይነት ንግግር መናገራቸውን ሰማን!
እኔ የምለው አቶ ሽመልስ፤ የመንግስት ቃል አቃባይ ሆነው ሳለ ለምን ቃላባይ ሲያደርጉዎት ዝም ይላሉ!? እርሶ ያቀበሉት ቃል በነጋታው “ውሸቱን ነው አትስሙት!” ሲባሉ ጎረቤትዎስ፣ ለቤተሰብዎስ፣ ለባንኮኒ ጓደኞችዎስ ምን ስም ያሰትዎታል? እንዴ ምንም ቢሆን ሁለት ፀጉር አብቀለዋልኮ… የማንም ማላገጫ ሲሆኑማ ዝም አይበሉ!? እውነቴን ነው የምልዎ እኔ ለርሶ በመቆርቆር ነው የምናገረው…! ከዚህ በኋላ፤ “ይህንን ቃል አቀብል” ሲባሉ “መጀመሪያ እውነት መሆኑን ማሉልኝና” በሉዋቸው እንጂ ዝም ብለውማ አይመኑ! እንዴነችና ስልጣኑ ባፍንጫዎ ይውጣ እንጂ የማንም መጫወቻማ አይሆኑም…!
እኔ የምለው አቶ በረከት፤ እኛማ እኮ እርሳቸውን አምነን ለስንት ወዳጆቻችን “ስካይፕ አልተከለከለም!” ብለን ነገርን መሰልዎ…!? ለወደፊቱም ቢሆን አቶ ሽመልስ የሚናገሩትን ለማረጋገጥ እርስዎ ጋር እንድንደውል ስልክዎን ቢሰጡን ደስ ይለኛል።
እዝችው ጋ ግን አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎትማ… አቶ ሽመልስ ባለፈው ጊዜ “ስካይፕ አይከለከልም” ብለው የዋሹን እለት አያይዘውም ስለ አቶ መለስ ጤና ነግረውን ነበር። “እኛ በአደባባይ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ክስት ግርጥት ብለው ተመልክተናቸው እግዜር ይማራቸው እያልን እየፀለይን ነው አሁንስ ሻል አላቸው ወይ?” ብለን ብንጠይቃቸው፤ እርሳቸው ሆዬ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሙሉ ጤንነት ላይ ናቸው!” ብለው ነግረውናል። አሁን ሳስበው ግን ስካይፕ አይከለከልም ብለው እንደዋሹን ሁሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩንም ጤና አስመልክቶ የነገሩንን ለማመን ተቸግረናል። እና እርስዎ ቢነግሩን ደስ ይለናል! አለበለዛ ግን ህዝቡ፤ የአቶ ሽመልስን ንግግር ተቃራኒ ትርጉም በመውስድ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጣር ተይዘዋል በቅርቡም ቀብር ሊሆን ይችላል!” ብሎ ቢያስብ እኔ የለሁበትም።
እኔ የምለው ወዳጄ፤ ባለስልጣኖቻችን እንደምን ያለ ተንኮል አስበው ይሆን ቋንቋቸው እንዲህ የተደበላለቀባቸው!?
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 3 Comments »
Monday, June 25th, 2012
አቤ ቶኪቻው
እኔ የምለው ወዳጄ ቅድም ስለ በእውቀቱ ስዩም ጉዞ ሳወራ አብሬው አነሳዋለሁ ብዬ ስደተኛ እንደመሆኔ መጠን ቀልብ አጥቼ የራሳሁት አንድ ጉዳይ አለ… ምን መሰልዎ…!?
ታዋቂዋ ተዋናይ መሰረት መብራቴ ከሀገር ወጥታ አሜሪካ ጥገኝነት ጠየቀች የተባለው እውነት ነው እንዴ!? መቼም ምን ሆና!? ብሎ መጠየቅ አግባበብ አይደለም። ምክንያቱም “ጉዳችንን” መቼ አጣነውና!
መሰረት መብራቴ በቀጥታ ከፖለቲካው ጋር የሚያገናኛት ነገር ባይኖርም ሁሉን ሰብስበው መያዝ የሚፈልጉ ዋና “የሴራ” ሂደት ባለቤቶች መሰረትንም፤ “የኢህአዴግ ንብረት ነሽ አለበለዛ ወዮልሽ!” አይሏትም ለማለት አያስደፍርም።
እውነቱን ለመናገር በአቶ በረከት ስምዖን የመፅሐፍ ምረቃ ላይ ተገኝቶ፤ “ከመፅሀፉ የተመረጠ አንድ ክፍል አንብብ” መባል እንኳንስ መሰደድ ጫካ መግባትም ያሰኛል። ሰውየው የኢህአዴግ ባለስልጣን ስለሆኑ አይደለም እንዲህ የምለው… “እህ” ይበሉኝማ፤ ባለፈው ጊዜ በጣም የምናከብረው ፍቃዱ ተክለማሪያምን ጨምሮ ሌሎችም “አርቲቶች” የሁለት ሀውልት ወጎች መፅሐፍ ምረቃ ላይ ከመፅሀፉ የተወሰነ ክፍል በዕለቱ ለነበረው ታዳሚ እንዲያነቡ ታዘው ነበር። “ትዕዛዝ አይደለም” የሚለኝ ካለ፤ “የጌቶች ልመና ከትዕዛዝ እኩል ነው” የሚለውን የአበው ንግግር አስታውሳለሁ።
ታድያ በዛ ምረቃ ዕለት አንጋፋው ፍቃዱ ተክለማርያም እያነበበ ሳለ አንድ እንኳ በቅጡ የሚሰማው ሰው አልነበረም። ራሳቸው የአቶ በረከት ስምዖን ሳይቀሩ ውስኪያቸውን እየጨለጡ ወሪያቸውን ሲያቀልጡት ነበር። (ካላመኑኝ “ዩቲዩብ” ይመስክር!) ምስኪን ፍቃዱ ተክለማርያም ግን በሞቅታ ውስጥ ላሉት ባለስልጣኖች ንባቡን ቀጥሏል። በእውነቱ እኔ ፍቃዱን ብሆን ኖሮ የአፄ ቴውድሮስን ሽጉጥ የምመኘው ይሄኔ ነበር! ለአንድ ተዋናይ መድረክ ላይ ስራ አቅርብ ተብሎ አለመሰማትን ያህል ውርደት የትም የለም። በእርግጥ ሰዎቻችንም ቢሆኑ አርቲስቶቹን እጃቸውን እየጠመዘዙ አብራችሁን ኳስ ተራገጡ አብራችሁን መሸታ ጠጡ የሚሉት ወደዋቸው እንዳልሆነ ይታወቃል…! እናስ? የተባለ እንደሆነ አርቲሰቶቹ ያላቸውን የተቃባይነት በረከት ለመቋደስ እንደሆነ ግልፅ ነው።
እናም መሰረት መብራቴም እንዲህ አይነት ተደጋጋሚ እጅ መጠምዘዞች አይደርሱባትም ብሎ ማሰብ ይከብዳል። ፍሬንዶቼ ሰዎቹ እኮ አምርረዋል። በዚሁ ሰሞኑን ተመስገን ደሳለኝ ላይ የደረሰውን ማንሳት እንችላለን!
እኔ የምለው ትላንት ፍትህ ጋዜጣን በኢንተርኔት ተመልክቻት ነበር። “ፍትህ እና አልሸባብ ምን አገናኛቸው!” በሚል ርዕስ ተመስገን የፃፈውን ተመልክቼ በጣም ነው የተደነቅሁት። እኔ የምለው ሰዎቻችን ይሄንን ያህል ወርደዋል!? ተዋርደዋል እንዴ…!? አረ ሼ…!
አንዴ… ቆይኝማ ደብዳቤውን ላላያችሁት ወዳጆች እዚሁ ላይ ላምጣምውና እንየው ድጋሚ እስቲ…
“To Ato Temesgen Desalegne
Chief Editor of Fitih magazine
Ethiopia
It has to be remembered that AlShebab has assigned me secretly to make propagation activities in Ethiopia, Somaliland, Kenya and Uganda. To accomplish the task we have agreed with you through your representative Ato Mamush Sentie in Eritrea to publish propaganda articles against the Ethiopian government, against the interest of the Ethiopian people and the American government. It has to be remembered that we have paid US dollar 24,000 for 30 consecutive editions. Now alshebab has made strategic change to accomplish its tasks. Therefore we need the 14 edition charges US dollar 11,200 dollar to alshebab. We believe that you will return back the money to our organization. If this is not fulfilled on time you will bear a cost on your representative Ato Mamush Sentie and your life according to the rule of the organization.
Alshebab wins
Ahmedin Nasir”
ተመስገን በፅሁፉ ላይ እንደነገረን፤ እኔም በበኩሌ የዚህን ደብዳቤ የእጅ አጣጣል በፍፁም የአልሸባብ ነው ብሎ ማመን ይከብደኛል። ይህ ኢሜል ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ነው የተላከው ብዬ ደፍሬ ለመናገር ባልችልም፤ ከኢትዮጵያን ሄራልድ መሆኑ እንደማይቀር ግን 99.6 % እርግጠኛ ሆኜ እናገራለሁ!
እስቲ አስቡት ተመስገን ደሳለኝ የኢትዮጵያን መንግስት፤ የኢትዮጵያ ህዝብ እና የአሜሪካንን መንግስት ጥቅም የሚፃረር ፕሮፖጋንዳ ለአልሸባብ ለማተም ሲስማማ…! ምናለበት “የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም የሚጎዳ” የሚለውን እንኳ ቢያወጡት! ይሄ ግፍ ምናምን የሚባለው ነገር ቀረ እንዴ…!?
ሌላው ይህ “የአልሸባብ” ተወካይ እንደሚለው ከሆነ ተሜ 30 እትሞች ላይ እኛን መንግስታችንን እና አሜሪካንን የሚጎዳ ፕሮፖጋንዳ ሊያወጣ 24 ሺህ ዶላር ተቀብሏል። አንግዲህ አሁን መልስልን የተባለው 11200 ዶላር ነው። ያም ማለት ከግማሽ በላይ ፕሮፖጋንዳውን ተግባራዊ አድርጓል ማለት ነው። እስቲ የትኛው የፍትህ ጋዜጣ ፅሁፍ ነው “አልሸባብዬ የኔ ጌታ አይዞህ በርታ በርታ…!” የሚል ይዘት ያለው!? በበኩሌ ከሀጥያቴ የተነሳም እንደሆነ እንጃ እንዲህ አይነት ፅሁፍ ፍትህ ጋዜጣ ላይ አይቼ አላውቅም! እናንት በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ብፁህ የሆናችሁ ትመሩኝ ዘንድ እለምናለሁ!
እርግጥ ነው ፍትህ ጋዜጣ የመንግስትን እንከን ፈልገው ከሚተቹት ጋዜጦች ወገን ናት። እንደውም አውራ ናት ማለት ይቻላል። ይህም የኢትዮጵዩያ ህዝብ ፍላጎት ለመሆኑ ሁላችንም “ቀፈፈኝ” ብለን ስንወጣ፤ እርሱ የመጣው ይምጣ ብሎ በፃፈ ቁጥር የአንባቢው ምላሽ እንዴት እንደሆነ ራሱ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኤጀንሲን ጠይቆ መረዳት ይቻላል።
ለማንኛውም ባለፈው ጊዜ የሰማናት ጭምጭምታ እውን ልትሆን ይመስላል። ከዛም በተጨማሪ ሰዎቻችን ከበድ ያሉ ጥቃቶችንም ሰንዝረውብን “አልሸባብ አደረገው!” ሊሉን ይችሉም ይሆናል። በእውነቱ ይሄ ምንም ባልታጠቀ ህዝብ ላይ ጣንያን የተጠቀመው የአውሮፕላን ድብደባ ጋር ይመሳሰላል ብል ምንም ማጋነን አይሆንም… ከሆነም ይሁን…(ደሞ ለማጋነን! ይህው መንግስታችን ስንት ነገር ያደርግ የለም እንዴ!?) እና በፀሎቱም በጥንቃቄውም መትጋት ያስፈልጋል። የሰማሃት ጭምጭምታ ምንድናት? ብሎ የጠየቀ መልሱን በአዲስ መስመር ያገኘዋል።
መንግስት ተጨማሪ ሰዎችን በአሸባሪነት ክስ ሊጠረንፍ አስቧል አሉ። እዚህ ውስጥ ፍትህ ጋዜጣ ነፃነት ጋዜጣ እና አገር ቤት ያሉ ጦማሪያን ሊኖሩበት እንደሚችሉ ጠርጣሮቹ ጠርጥረዋል። ስለዚህ ነቃ ብሎ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል ያለ ሁሉ አረማመዱ ጥንቃቄ የተሞላበት እንዲሆን አደራ ማለት ይገባል። ለቸሩ መድሃኒያለምም አደራ እንላለን!
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 2 Comments »
Saturday, June 23rd, 2012
ትላንት ሰኔ 15 2004 ዓ.ም የጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ ይግባኝ ታይቶ ነበር።
በይግባኟም “ከግንቦት ሰባት ጋር ወይም ከኤርትራ መንግስት ጋር አሲራለች ለሚለው ክስ ማስረጃ አልቀረበብኝም።” ብላ የተከራከረች ሲሆን ከኢትዮጵያ ሪቪው ድረ ገፅ ጋር ያላት ግንኙነት የጋዜጠኝነት ግንኙነት መሆኑን ለዚህም ክፍያ እንደተከፈላት እና ከውጪ ሀይሎች የገንዘብ ድጋፍ አግኝታለች የተባለው ይሄው የሰራችበት ክፍያ መሆኑን አስረድታለች። ያገኘችው ክፍያም አንድ ጊዜ 1500 ብር እና ሌላ ጊዜ ደግሞ 2100 የኢትዮጵያ ብር መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ተናግራለች።
አቃቤ ህግ በበኩሉ ሌሎች አብረዋት የተከሰሱ ይቅርታ መጠየቃቸውን አውስቶ ርዮት አለሙ አዲሳባን ለመበጥበጥ ከውጪ ሀይሎች የገንዘብ ድጋፍ ማግኘቷን ደግሞ ለመናገር ሞክሯል።
አሽሟጣጮችም በበኩላቸው ርዮት አለሙ በድምሩ 3600 ብር አግኝታ አዲሳባን የምትበጠብጠው እንዴት ነው? ሲሉ የጠየቁ ሲሆን ልጅቷ ጠጪ እንኳ ብትሆን “አንድ ምሽት በገንዘቡ ጠጥታበት በሞቅታ ከተማዋን ልትበጠብጥ ስትል በቁጥጥር ስር አውለናታል!” ለማለት ይመች ነበር። ከዚህ በላይ ግን የዘንድሮ ሶስት ሺህ ብር አይደለም ሀገር እና በሶ እንኳን መበጥበጥ ያስችላልን!? ሲሉ አሽሟጠዋል።
ለማንኛውም ቀጣዩ ቀጠሮ ለሀምሌ 10 2004 ዓ. ም ሆኗል።
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 3 Comments »
Tuesday, June 19th, 2012
ትላንትና ከስንት ጊዜ በኋላ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትርዬን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አየኋቸው። ያኔ አበበ ገላው በዋሽንግተን ዲሲ ቆሌያቸውን ከገፈፋቸው በኋላ በቴሌቪዥን መስኮት ስናያቸው ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው። (በቅንፍ፤ እንደ ድሮ ጎረቤት ብንሆን ኖሮ በቴሌቪዥን መስኮት ሲጠፉብን በሳሎናቸው መስኮት ለማየት ሙከራ እናደርግ ነበር። ዛሬ ግን ሩቅ ሆንና ናፍቆታቸው ሲያስቸግረን ሰነበተ! ብዬ ሀሳቢነቴን ለመግለፅ እወዳለሁ።)
አረ እዝች ጋ ሳይረሳ ባለፈው ጊዜ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ሰዎች “አበበ ገላው ዋሽንግተን ዲሲ ያልሄደው በርካታ የኢህአዴግ ደጋፊዎች ስላሉ እነርሱን ፈርቶ ነው!” ብላችሁን ነበረ። ረስቼላችሁ፤ ሰውየው እኮ አንገታቸውን የደፉት በዋሽንግተን ዲሲ ነው።
ታድያ የዛን ጊዜ ያ ሁሉ የአንገት እና የቅስም ስብራት ያጋጠማቸው የጋዜጠኛ አበበ ገላው ንግግር ብቻ መስሏችሁ ከሆነ ተሸወዳችሁ።
ከውጪ የነበሩት የአካባቢው ኢትዮጵያውያን የተቃውሞ ጩኸትም “ምነው እግሬን በሰበረው!” አስብሏቸው ነበር። ውስጥ ደግሞ አበበ ትንታግ ሲጨመርበት…! እና ታድያ አዲስ አድማሶች ይሄ ሁሉ ነገር በዋሽንግተን ዲሲ ሲከናወን ደጋፊዎቻቸው የት ሄደው ይመስላችኋል? “በልማታዊ ስራ ተወጥረው ነበር!” ብላችሁ ሳቄን እስቲ አብዙልኝ! “ምን አይነት አዲስ አድማስ መጣ ደሞ ባካችሁ!?”
በነገራችን ላይ አሁንም እርሳቸው እርም የላቸውም የቡድን ሃያ አገራት ስብሰባ ላይ ደግሞ ሊገኙ ሲሄዱ ነው ያየኋቸው። እንደኔ እንደኔ ይሄ ቡድን ምናምን የሚባል ነገር ቢቀርባቸው ይሻላል። በርግጥ ስብሰባ ሊናፍቃቸው አንደሚችል ጠረጥራለሁ። ምን ችግር አለው ታድየ በፈለጉ ጊዜ የሚሰበስቡት በፈለጉ ጊዜ የሚበትኑት ፓርላማ አላቸው አይደል እንዴ…!? እዛው እንደሚሆኑ ቢሆኑ ይሻላቸዋል እንጂ፤ ገና ለገና የፈረንጆቹ “ቡድን” አያልቅም እና እርሳቸው “በድን” እየሆኑ የሚመጡበት ምክንያት ምንድነው!?
የሆነ ሆኖ “ታንክ ተደግፈው መፅሀፍ የሚያነቡት ጀግናው ጠቅላይ ሚኒስትራችን” በአበበ ገላው ንግግር የተነሳ ለአንድ ወር ያህል ተሸማቀው እና ተሸምቀው ሲያበቁ ትላንት በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለዋል።
ታድያልዎ፤ ትላንት ሳያቸው ክስት ብለዋል። ምን ሆኑ!? እንዴ ጠንከር ይበሉ እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትርዬ! ቀጣዩ ጩኸት እኮ እየባሰ ነው የሚመጣው! ታድያ ጠንከር ጠንከር ማለት አይሻልም ይላሉ? ቁጣ እና ጩኸት ይህንን ያህል የሚረብሽዎት ከሆነ ግን ዘዴውን ልንገርዎት…!? እሺ አይሉኝም እንጂ ዛሬውኑ ስልጣንዎን ልቅቅ አድርገው አዲስ አገራዊ መግባባት፣ አዲስ አገራዊ ምርጫ ማከናወን! አቤት ያኔ ጤናዎ ላይ ራሱ ምን አይነት መሻሻል አንደሚመጣ ያዩት ነበር።
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 20 Comments »
Tuesday, June 12th, 2012
አቤ ቶኪቻው
የዛሬ ሳምንት ከደቡብ አፍሪካ ባፋና ባፋናዎች ጋር በሳላዲን ሰይድ ጎል አቻ ተለያይቶ መነጋገሪያ የነበረው ብሄራዊ ቡድናችን ትላንት ደግሞ አሁንም በማይጨበጠው አጥቂ ሳላዲን ሰይድ ሁለት ጎሎች አስቆጥሮ፤ ሁለት ለምንም በሆነ ውጤት መካከለኛው አፍሪካን አሸንፏል። በስታድየም፣ በቴሌቪዥን እና በኢንተርኔት ስንከታተል የነበርን በርካቶችም ፈንድቀናል።
ሳላዲን ሰይድም ከስታድየሙ ታዳሚ “ጥቁር ሰው” የሚል ማዕረግ ተሰጥቶታል። እንደውም አንድ የፌስ ቡክ ወዳጃችን እንዲህ ብሎ ለጥፏል።
“ብራዚል ሊሄድ ሳላዲን ኑ ካለ
አረ አይቀርም በኢትዮጵያ ስለማለ
ታድያ ልጁስ ሲጠራው ምናለ….
ወ….ይ…
ወይ ባለለው ያኔ
አዝናብኝ ነበር ሀገሬ”
እንግዲህ ሀገሩን የሚያኮራ የጀግና ስራ የሚሰራ ሁሉ በአሁኑ ግዜ “ጥቁር ሰው” የሚል ማዕረግ የሚያገኝበት ሁኔታ ነው ያለው! (እንዲህ ነው እንጂ የኔ ኢቲቪ አይሉኝም!)
እዝች ጋ ውድ ቴዲ መለኪያ ሰጥተከናል እና እግዜር ይስጥህ! ብለን ማመስገን ይገባናል። እውነቱን ለመናገር ራስህም “ጥቁር ሰው” ነህ ብዬ ደፍሬ ለመናገር እወዳለሁ። እንዴት…? የሚል ካለ ምንም እንኳ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ሚኒሊክ ሲባል ደማቸው ቢንተከተክም የመጣው ይምጣ ብሎ “ጥቁሩን ሰው” አሞካሽቷልና… እደግመዋለሁ ቴዲም “ጥቁር ሰው” ነው!
በነገራችን ላይ ከላይ በርዕሴ ያልጠቀስኳቸው በርካታ “ጥቁር ሰዎች” እንዳሉን ለማስታወስ እወዳለሁ።
ባለፈው ጊዜ እንዳየነው አበበ ገላው ቆሌ ገፋፊውን ጠቅላይ ሚኒስተር ቆሌያቸውን የገፈፈ ጊዜ በበርካቶች ዘንድ “ጥቁር ሰው” የሚል ማዕረግ ተሰጥቶት እንደነበር እናስታውሳለን። አረ እዚህ ጋ ሳይጠቀስ የሚያልፍ ነገር አለ። ትላንት አዲስ አድማስ ጋዜጣን በኢንተርኔት መስኮት ጎብኘት አድርጌው ነበር። “አበበ ገላው በድጋፍ እና ተቃውሞ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል” የሚል አንድ ዘገባ ወጥቶ አየሁ። ፅሁፉን ልብ ብዬ ስመለከት ጠቅላይ ሚኒስትራችንን እና እጅግ ወዳጆቻቸው የሆኑ ግለሰቦችን ከደረሰባቸው የቅስም ስብራት ለማከም የተፃፈ ይመስላል።
አረ እንደውም፤ “አበበ ገለው ዋሽንግተን ዲሲ ያልሄደው የኢህአዴግ ደጋፊዎችን ፈርቶ ነው!” የሚል ነገርም አይቻለሁ። እሰይ አድማሶች እንዲህ ነው እንጂ… ለዚህ አኩሪ ተግባር “ጥቁር ሰው” ባልላችሁም ለጊዜው “አስር አለቃ” ልበላችሁ ይሆን…!? ግን ለምን ይዋሻል…? በአዲስ መስመር እወቅሳችኋለሁ፡
እኔ የምለው ለምን ድርጅታችንን ታሳስቷታላችሁ? በእውነቱ ኢህአዴግ እንኳንስ ከፍቶት በተሰደደው የዋሽንግተን ዲሲ ነዋሪ ይቅርና በአገርቤቱ ደሴ እንኳ እናንተ እንደምትሉት አይነት ደጋፊ አለውን…? (ዲሲ እና ደሴ ለማመሳሰል ብዬ ደሴን ጠቀኩ እንጂ በመላው ኢትዮጵያ… የኢህአዴግ ደጋፊ ማነው…?) በእውነቱ በመላዋ ኢትዮጵያ ኢህአዴግ ብዙዎችን ራሱ በአበል እየደገፈ ነው እንጂ ህብረተሰቡ ኢህአዴግን ለመደገፈ አቅም አለውን!? በእውነቱ በዲሲ በርካታ ደጋፊዎች ቢኖሩት ኖሮ ባለፈው ጊዜ ባለስልጣኖቻችንን ለአባይ ገንዘብ ስብሰባ በሄዱ ወቅት በተቃውሞ ብዛት ንግግር እንኳ ማደረግ ተስኗቸው ይመለሱ ነበር? ለማንኛውም አድማሶች ድርጅታችን አታሳስቷት…! በተለይ ውጪ ሀገር ከኤንባሲው የጥበቃ ሰራተኞች ውጪ ይሄ ነው የሚባል ደጋፊ እንደሌለን እኛም እናውቀዋለን!
ወደ ዋናው መስመር ስንመለስ… ሀገራችን በተለያየ ቦታ የተለያዩ “ጥቁር ሰዎች” እያፈራች ትገኛለች። ልብ አድርጉልኝ እነዚህ ጥቁር ሰዎች ባንዲራዋን ከፍ አድርገው የሚያውለበልቡ ናቸው እንጂ ባንዲራዋን የሚዘቀዝቁ አይደሉም። በድፍረት የሚናገሩ ናቸው እንጂ በአፍረት አንገት የሚደፉ አይደሉም። ሀቅን የሚለብሱ ናቸው እንጂ ውሸት የሚቀዱ አይደሉም።
ሳላዲን ሰይድ ኢትዮጵያ ለአለም ዋንጫ ለማለፍ ባደረገችው ማጣሪያ እስከ አሁን ያስቆጠረቻቸውን አምስት ጎሎች በሙሉ አስቆጥሯል! በዚህም ባንዲራችን ከፍ ብሎ ተውለብልቧል እኛም ሳላዲንን ብለነዋል “ጥቁር ሰው” ይህንን ማዕረግ መላው የብሄራዊ ቡድኑ አባላትም ይጋራሉ!
አበበ ገላው እና እስክንድር ነጋ ሁለቱም የሚወክሏቸው ህዝቦች አሏቸው አበበ በውጪ ሆነው ደከመኝ ሳይሉ ለሀገራቸው መልካም እንዲመጣ አበሳቸውን የሚያዩ ሰዎችን፣ እስክንድር ደግሞ “ሀሰት ለመናገር አትሻም ምላሴ ለእውነት እሞታለሁ አልሳሳም ለነብሴ” ብለው በየ እስር ቤቱ መከራቸውን የሚያዩ የኢትዮጵያ ልጆችን ይወክላሉ። ወክለውም የ “ጥቁር ሰው” ማዕረግን ያገኛሉ።
“ጥቁር ሰው! ያብዛልን እኛንም “ጥቁር ሰው” ያድርገን አሜን በሉ!
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | No Comments »
Tuesday, June 5th, 2012
ይህንን ጨዋታ ትላት ላካፍላችሁ ነበር ያሰብኩት በቴክኒክ ምክንያት ሳይሳካልኝ ቀረና ይኸው ለዛሬ ሆነ!
በአለም ዙሪያ ያላችሁ የዝች ብሎግ አንባቢዎች እንዴት አላችሁልኝ…? ሰንበቶቹ እንዴት አለፉ!? ባመዛኙ አሸወይና እንደነበሩ እገምታለሁ! ከፊል ደመናማ የሆኑ እንደሚኖሩም እጠረጥራለሁ። ስለዚህ በጥቅሉ ደመናው እንዲጠራ፤ አሸወይናው እንዲጠናከር እየተመኘሁ እንደሚከተለው ይቺን ቀደዳ ይዤ ቀርቤያለሁ።
የቃላት መፍቻ
አሸወይና… ማለት አስደሳች፣ ማራኪ እና “ጣመኝ ድገሙኝ” የሚሉት ጊዜ ሲሆን፣
ቀደዳ … ማለት ደግሞ ወሬ፣ ወግ፣ ጨዋታ በማለት የአራዳ ልጆች ይፈቱታል። (እዝችው ጋ አራዳ ማለት ብዬ ደግሞ ልቀጥል እንዴ…? አራዳ ማለት ምን ማለት አንደሆነ የጋሽ ፍቅሩ ኪዳነን የፒያሳ ልጅ መፃፍ ሲያነቡ ወለል ብሎ ይገለጥልዎታል።…
ቀደዳችን ተጀመረ፤
በአለም ዋንጫ ማጣሪያ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ተጫውቶ የነበረው ብሄራዊ ቡድናችን ሳላዲን ሰይድ በሃያ ሰባተኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ድንቅ ግብ እስከ ሰባ ሰድስተኛው ደቂቃ ድረስ ሲመራ ቆይቶ፤ በሰባ ሰባተኛው ደቂቃ ላይ ደቡብ አፍሪካዎች ባስቆጠሩት ግብ አንድ እኩል በሆነ ውጤት ጨዋታው ሊጠናቀቅ ችሏል። (ድሮም ይሄ ሰባ ሰባት አይመቸንም… ብለን እንመፀትና እንቀጥላለን፤)
ይሄ ውጤት ቡድናችን ላይ ተስፋ የምንጥልበት እንደሆነ አሳይቶናል። እስከዛሬ ድረስ በኒያላዎቹ ተስፋ ቆርጦ የነበረው የእግር ኳስ ደጋፊ ብሔራዊ ቡድኑን “ቡድን” ከሚለው ውስጥ “ቡ” በመግደፍ እና “በ” በማድረግ፤ “ብሄራዊ በድናችን” እያለ እሰከመጥራት ደርሶ የነበረ ሲሆን፤ የትላንቱ ውጤት ይህንን ስም ለማደስ እነ ሳላዲን ቆርጠው መነሳታቸውን አላህም ሊረዳቸው ተነሳሽነት እንዳሳየ የሚያመላክት ነው።
በነገረችን ላይ ሰሞኑን በስፖርቱ አዳዲስ ውጤታ ውጤቶችን እያስመዘገብን ነው። ሉሲዎቹ የሴቶች እግር ኳስ ብሄራዊ ብድን አንድ በሉልኝ፤ ከእንደገና ደግሞ በጣሊያን ሮም ላይ በአጭር እርቀት ሩጫ በሺህ አምስት መቶ እና በስምንት መቶ ሜትሮች አሪፍ ውጤት አግኝተናል። እሰይ እሰይ እንትፍ እንትፍ እያልን ብለን እንመርቃለን።
የኢትዮጵያ ሴት እግር ኳስ ቡድን አባላት ታንዛኒያን ካሸነፉ በኋላ ላስመዘገቡት ውጤት ከ አንድ ሺህ እስከ ሁለት ሺህ ድረስ ቦንድ ተገዝቶላቸዋል። ይሄም “ለቀጣይ ስራ የሚያበረታታ” እንደሆነ የሴቶቹ ተወካይ ገልፃለች። የተወካይዋን ንግግር ከመመህራን ማህበር ኃላፊዎች ጋር ያመሳሰሉት ወዳጆች ነበሩ። ምናለበት ግን የምር ማበረታቻ ቢሸልሟቸው…!? ብለን አስተያየት ብንሰጥ “ከዚህ የበለጠማ የምር ሽልማት የለም” ሊሉን እንደሚችሉ እንገምታለን…
እዝችጋ አንድ ሃሳብ አለኝ…! እንደዚህ አይነት ሽልማት የሚያቀርቡ ባለስልጣናትን እኔም አንድ ሽልማት ልሸልማቸው አስቤያለሁ። ምን መሰላችሁ…? እዛው አባይ ወንዝ ላይ ወርደው ለአንድ ወር ድንጋይ እንዲያቀብሉ ቁፋሮ እንዲቆፍሩ…! (አዎና ከልማት የበለጠ ሽልማት ከየት ይመጣል? በርግጠኝነት ሽልማቴ ባለስልጣኖቹን ለወደፊት ስራ የሚያበረታታቸው እንደሆነ አምናለሁ።)
አረ በደቡብ አፍሪካው ጨዋታ ላይ የሆነውን ከ “ከረንት አፌርስ” ድረ ገፅ የኮረጅኩትን ትንሽ ልንገራችሁ እንጂ…!
በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በብዛት በስታድየሙ ታድመው ነበር። በቅርቡ አክቲቪስት እና አርቲስት ታማኝ በየነን በጀግና አቀባበል ተቀብለውት የነበሩት ኢትዮጵያውያን፣ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እዝች ሀገር ድርሽ እንዳይሉ ብለው ያስከለከሉ ኢትዮጵያውያን፤ ትላልቅ እና ኮከብ ሳይኖርባቸው እንዲሁ በሚያበሩ በርካታ የኢትዮጵያ ባንዲራዎችን የደቡብ አፍሪካን ስታድየም አድምቀውት ነበር። “ኢትዮጵያ የኛ መመኪያ” የሚለው መዝሙር “የዜግነት ክብር” የሚለውን ብሄራዊ መዝሙር ተክቶ ነበር። (እኔ የምለው ግን መንግስታችን በዮቦታው እንዲህ ተጠምዶ እና አይንህ ላፈር ተብሎ እስከመቼ ይኖራል…!?)

ለማንኛውም የፊታችን ቅዳሜ ሉሲዎች በዳሬሰላም፤ እንዲሁም ኒያላዎቹ እሁድ በአዲስ አበባ ስታድየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። እናስ… እናማ ሆ ብለን ሄደን ድጋፋችንን እንሰጣለና!
ወይኔ አዲሳባ ስታድየም እንዴት እንደናፈቀኝ አትጠይቁኝ…! በዙሪያው ካለው ድራፍት ጀምሮ ውስጥ እስከሚገኘው ሽንብራ ደቤ፤ ከተጨዋቹ ጨዋታ እስከ ደጋፊው ሆታ…! የምር ናፍቆኛል። እሁድ ከች ልበል ይሆን…!?
ዘግይቶ የደረሰኝ ኩምክና…
እግር ኳስ ፌዴሬሽን “በደቡብ አፍሪካ የተካሄደውን ጨዋታ የሚያሳይ ቪዲዮ የለኝም” አለ በማለት ሰይድ ኪያር አሁን በኢቲቪ ሲናገር ሰማሁት… እንዴ ፌዴሬሽንዬ ትንሽ ሼም የለም እንዴ…? እንዴት አንድ እንኳ ጋዜጠኛ መላክ ያቅታችኋል!? ሌላው እንኳ ቢቀር በሞባይላችሁም ቢሆን መቅረፅ ነበረባችሁ እነጂ ይህንን የመሰለ ታሪካዊ ጨዋታ ቪዲዮ የለኝም ማለት በእውነቱ ትልቅ ኩምክና ነው። “የት ሄጄ ልፈንዳ…!?” ያለችው ማን ነበረች!?
እስቲ ሰላም ይግጠመን ወዳጄ!
ከፌስ ቡክ ግድግዳችሁ ላይ ፎቶ የወሰድኩባችሁ ወዳጆች ሳላስፈቅዳችሁ በመውሰዴ ይቅርታ ጠይቄ እግዜር ይስጥልኝ! ብዬ ልመርቃችሁ!
Filed under: Uncategorized

Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 8 Comments »
Friday, June 1st, 2012
ኢናሳ የተባለው የኢትዮጵያ ቆላፊ እና ጠላፊ መስሪያ ቤት የግለሰቦችን ፌስ ቡክ ሳይቀር በመቆለፍ ስራ ተጠምዷል። በትላንትናው ዕለት በርካታ ብሎጎች ድጋሚ እንደተዘጉ ሰምተናል። መንግስቴ ፈርቷል… በእውኑ እንዲህ ያለው ፍርሃት “ተራሮችን ካንቀጠቀጠ ትውልድ” አይጠበቅም…
እኔን ጨምሮ ሌሎችም “ባለ ብሎጎች” አንዱ ቢዘጋ በሌላ መስኮት ወደ አገራቸን መግባታችን እና ከወዳጆቻችን ጋር መጨዋወታችን እንደሚቀጥል እርግጠኛ ነኝ። ስለዚህ የተዘጋው በር ሁሌም መንኳኳቱ አይቀርም ማለት ነው። ታድያ በተንኳኳ ቁጥር መንግስት እየተነሳ ሲዘጋ መንግስቴን ስትራፖ እንዳይዘው ሰጋሁለት…!
የዛሬ ሃሳቤን በግጥም ብገልፅ በደንብ ይወጣልኝ ነበር። ነገር ግን ብንደፋደፍ ብንደፋደፍ ጠብ ሊልኝ አልቻለም። ታድያ ከወዳጆቼ ጋር ለምን አናዋጣም ብዬ እንደዚህ ጀመርኩ፤
በአንኳኪ ብዛት ሰላም ከምታጣ
በርህን ክፈተው ያሻው ይግባ ይውጣ…
ይበሉ ወዳጄ አንድ አንድ ስንኝ ያዋጡ… ከዛ ዜማ አበጅተን እንዘፍናት ይሆናል።
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 96 Comments »
Friday, June 1st, 2012
ሰፈሬ ሽሮሜዳ እንጦጦ ኪዳነ ምህረት አቅራቢያ እንደመሆኑ መጠን በርካታ ግዜ በአጋንንት የተለከፉ ፀበልተኛ ወገኖች “ትለቃለህ አትለቅም” በሚለው አስገምጋሚ የአስጠማቂው ቁጣ ሁልግዜም መልሳቸው ከተረበሸ ድምፅ የሚፈልቅ “እለቃለሁ!” የሚል ሲቃ እንደነበር አይቻለሁ። ችግሩ ግን ብዙ ግዜ “እለቃለሁ” ካሉ በኋላም በነጋታው “አብሬያት አድጌ፣ አብሬው ከርሜ” ለማን ትቼው እለቃለሁ” ብለው ድጋሚ ያገረሻሉ። አሁንም አስጠማቂው “አንተ ክፉ መናጢ ትለቃለህ አትለቅም…!?” ሙግታቸውን ይጀምራሉ። መስቀል እና ፀበል ለአጋንቱ ፀር ናቸውና “እለቃለሁ እለቃለሁ…” እያለ ይለፈልፋል። ምሱን ተናግሮ ቀምሶ ጨርሶ እስኪለቅ ድረስ ግን “እለቃለሁ” ስላለ ብቻ አይታመንም!
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዘንድሮም “እለቃለሁ!” እያሉ ነው። በእርሳቸው ፍቅር የተለከፍን እኛ፤ “ያለ እርስዎ በሳል አመራር ችግር እና ጉስቁልና ያበስለናልና እባክዎ ይሄንን አሳብ ወደ አዕምሮዎ አያምጡት!” ብለን ብንመክርም፤ ሌሎች ደግሞ በተቃራኒው “ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አያስጎምጁን!” እያሏቸው ይገኛሉ።
በተደጋጋሚ እንዳየነው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አስለፍላፊያቸው ብዙ ነው። ከዚህ በፊት በፓርላማ ውስጥ፤ ከዛም በተለያዩ የውጪ ሃገር ጋዜጠኞች “ትለቃለህ አትለቅም!” የሚሉ አስለፍላፊዎች አጋጥመዋቸዋል። ያው የተከበሩ ጠቅላይ ሚንስትራችንም ደንብ ነውና፣ ስርአቱ ነውና “እለቃለሁ!” እያሉ በተደጋጋሚ ለፍልፈዋል። ነገር ግን አለቀቁም።
እኔ የምለው ግን ክቡርነታቸው በርካታ ግዜ “ለቃለሁ” እያሉ ሲተዉት፣ “ለቃለሁ” ሲሉ ሲተዉት ሰዉ ንግግራቸውን አጓጉል ከእርኩስ መንፈስ ጋር እያዛመደባቸው እኮ ነው…!
በነገራችን ላይ ከላይ ያለውን የኪዳነምህረት ፀበል ትዝታዬን ያመጣሁት እንደው ነገር ለማሳመር ብቻ ብዬ አይደለም። በቅርቡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን አንድ የውጪ ሀገር ጋዜጠኛ “ትለቃለህ አትለቅም?” ብሎ ሲጠይቃቸው “እለቃለሁ!” ብለው በመናገራቸው (“እለቃለሁ” ብለው ሲለፈልፉ…” ልላቸው ነበር! ይቅርታ ከላይም “ለፈለፉ” የሚል ቃል ካለ ከፀበልተኞቹ ጋር ተምታተውብኝ ነውና በጅምላው ይቅርታ ጠይቄ እቀጥላለሁ)
እና ታድያ ጋዜጠኛው በጠየቃቸው ጊዜ “እለቃለሁ!” ብለው ሲመልሱ አንዱ ወዳጄ “አፈር ስሆን ‘ምስህ’ ምንድነው? በለህ ጠይቃቸው እና ያሉትን አቅርበን ቀምሰው በደንብ ይልቀቁን ሁሌ “ለቀኩ እያሉ አያስጎምጁን!” ብሎ የተናገረውን አስታውሼ ነው።
እኔ የምለው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስልጣን መልቀቅ ከአጋንንት መልቀቅ ጋር ማመሳሰል ፍትሃዊ ንፅፅር ነው ትላላችሁ…!?
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 16 Comments »
Friday, June 1st, 2012
አናንት በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የተባረካችሁ ክቡራን እና ክቡራት ሰላም እላችኋለሁ! ያው እንደምታውቁት ድርጅታችን መልካም ነገር ሲያጋጥመው የምንወዳደሰውን ያህል ችግር ባጋጠመን ግዜም ደግሞ እንዲህ በራችንን ዘግተን መገማገም እና ድርጅታችንን “ከመበስበስ” አደጋ መታደግ የዘወትር ተግባራችን እንደሆነ ይታወቃል።
ለዛሬ በአንድ ግለሰብ ላይ በዝግ ብሎግ እንድናወራ አነሆ ልጀምር ነው። (በነገራችን ላይ ዝግ ብሎግ ያልኩት እንደወትሮው ብሎጌ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ስለመታገዱ ላወራ አይይደለም። (በሌላ ቅንፍ ለድርጅታችን ከጠቀመ ልሳናችንም ቢዘጋ ቅር የማይለን ቁርጠኞች መሆናችንን በዚህ አጋጣሚ ለማረጋገጥ እወዳለሁ!) ይልቅስ በርዕሱ “ለኢህአዴግ አባላቶች ብቻ” ብዬ በማለቴ ሌሎች፤ ፅንፈኞች፣ አክራሪዎች፣ ነፍጠኞች፣ ነውጠኞች፣ ሽብርተኞች፣ ኒዬ ሊበራሎች፣ የሻቢያ ተላላኪዎች (ዉዉዉ ይሄንን ሁሉ ስም አውጥተንላቸዋል እንዴ ለካ…? ለነገሩ ከዚህም እጥፍ እጥፍ ስም አውጥተንላቸዋል። ለካስ ከኢኮኖሚ እድገቱ እኩል ተቃራኒዎቻችንን በመሞለጭም ታላቅ እምርታ አስመዝግበናልና! በእውኑ በድርጅቴ ኮራሁ! የሆነው ሆኖ፤ ባጠቃላይ እነዚህ ወዘተዎች ስለማያነቡት እና ጨዋታው የቤተሰብ ጨዋታ በመሆኑ ነው በዝግ ብሎግ ማለቴ!)))

እንደሚከተለው እጀምራለሁ…!
እኔ የምለው ባለፈው ግዜ ሰለ ጓድ ሰለሞን ተካ አንዳንድ ነገሮችን አንስቼ ተናግሬ ነበር። በርግጥ ግለሰቡ የተናገርኩትን ቢሰማም ቅሉ ሂሱን አልዋጠም። ሰሞኑን እንዳሰማሁት ደግሞ እንኳን ሂሱን እና መድሃኒቱንም በአግባቡ መዋጥ እንዳቆመ ያመላከተኝ ነገር አስተውያለሁ።
ተጠቃሹ ግለሰብ በግል ስሜቱ በመነሳሳት ፅናት በተባለ ራዲዮ ጣቢያው ላይ ድርጅታችንን ለዝቅጠት የሚዳርግ አንዳች ንግግር ተናግሯል። ሰሞኑን ጋዜጠኛ አበበ ገላው ስመ ገናናውን ጠቅላይ ሚኒስትራችን አምባገነን ብሎ በተናገረበት ንግግሩ ላይ ጓድ ሰለሞን ተካ ምላሽ ለመስጠት ሞክሮ ነበር። በእውነቱ ሙከራውን ሳላንደንቅ አናልፈም።
ነገር ግን፤
1ኛ ጉድ ሰለሞን ተካ (ይቅርታ ጓድ በሚል ይስተካከል) በራዲዮ ጣቢያው ላይ በንባቡ አንድ ታዋቂ ጋዜጠኛን ለማስመሰል በግልፅ ጥረት ሲያደርግ ተስተውሏል። በተጨማሪም ተደጋጋሚ የንባብ ችግር ይታይበት ነበር። እንደውም ይህንን የሰማ አንድ ለድርጅታችን ቅርብ የሆነ ግለሰብ ይህ ሰው ራዲዮ ጣቢያ ሳይሆን ፖሊስ ጣቢያ ነበር የሚገባው” ብሎ አስተያየት ሰጥቷል። (ፖሊስ ጣቢያ ይገባዋል ያለው እንዲታሰር ፈልጎ መሆኑ የገባኝ በስተ መጨረሻ ነው።) በማስመሰል ጥረቱ እና በንባብ ድንቅፋቱ የራዲዬ ጣቢያውን ሚኒ ሚዲያ አስመስሎታል።
2ኛ አባሉ በአሁኑ ሰዓት በራዲዮ ጣቢያው እያስተላለፈ ያለው አበል የተቀበለበትን የድርጅት ስራ ሳይሆን የተጣሉትን ግለሰቦች ለማብሸቀያ እንደሆነ ፍንጭ አግኝቻለሁ። በዚህም የተነሳ ድርጅታችን ላይ ተደጋጋሚ ነጥብ ሲያስቆጥርባት ይስተዋላል።
3ኛ ጓድ ሰለሞን ራሱም ሳያውቀው “በህቡዕ” ለሌላ ድርጅት እየሰራ እንደሆነ ለማየት ችያለሁ። እንዲህ የምለው ከመሬት ተነስቼ አይደለም። ነገር ግን የሚናገራቸው እጅግ ርካሽ የሆኑ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ስድባ ስድቦች ድርጅታችንን የሚያዋርዱ ከመሆናቸውም በላይ በተቃራኒው ደግሞ ለተቃዋሚዎች ትልቅ ግብአት እንደሚሆኑ በተግባር በመመልከቴ ነው።
4ኛ የዚህ አባል ጉዳይ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። የራዲዮ ፕሮግራሙ እንደማንኛውም ስልጠና እንደወሰደ ግለሰብ ተቃዋሚዎችን “የደርግ ርዝራዦች፣ ነፍጠኞች ሽብርተኞች…” ሲል መሳደቡ ጥሩ ሆኖ ሳለ በፕሮግራሙ መጨረሻ ላይ ግን “ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ቆራጥ አመራር ጋር ወደፊት!” በማለት የቀድሞ የደርግ አባላት ለኮሎኔር መንግስቱ የሚያሙትን ፉከራ ስም ብቻ ቀይሮ አሰምቷል። በእውኑ ይሄ በድርጅታችን ላይ ታላቅ የመበስበስ አደጋ አይደለምን…?
100ኛ ባጠቃላይ ግለሰቡ ከላይ አንድ ወዳጄ ብሎኛል እንዳልኩት ራዲዮ ጣቢያ ሳይሆን ፖሊስ ጣቢያ የሚገባው ቢሆንም ድርጅታችን የምትታገስ ናትና ለጊዜው በትዕግስ እንድታለፈው አስተያየቴን ስሰጥ ቀጥሎ የሚገኘው የውሳኔ ሃሳብ ተግባራዊ እንዲሆንበት አበክሬ እጠይቃለሁ።
የውሳኔ ሃሳብ
ይህ ግለሰብ ለኢህአዴግ እየሰራለት ነው ብዬ አላምንም። ከሆነም ደግሞ “ቆይ ባልሰራላችሁ!” በሚል ጥላቻ እና ቂም በቀል ኢህአዴግን ሊያጠፋ ቆርጦ የተነሳ ነው። (እርግጥ ነው ለተቃዋሚዎችም እየሰራ እንዳለሆነ ግልፅ ነው እናስ…? የተባለ እንደሆነ በግሉ ከወዲያ ማዶ ላለበት ብሽሽቅ ኢህአዴግን መጠቀሚያ ያደረገ ግለሰብ ነው። ይህም ግልፅ የሆነ ኪራይ ሰብሰቢነት እንደሆነ በተደጋጋሚ በተሰጡ ድርጅታዊ ስልጠናዎች ላይ ተረድተናል።) ስለሆነም በእውኑ ድርጅታችንን ከተጋረጡባት ሰርጎ ገቦች እና ጥቅመኞች የማዳን ጊዜው አሁን ነው። ከልባችሁ ለእናት ድርጅታችን ፍቅር ያላችሁ አባላት ዛሬውኑ ሰለሞን ተካ በኢህአዴግ ጉዳይ ላይ ትንፍሽ እንዳይል ድርጅታዊ ውሳኔ ይተላለፍ ዘንድ በተሰዉ ሰማህታት ስም እጠይቃለሁ። የግድ በአባልነት መቀጠል ካለበት ሰላማዊ ሰልፎች በሚኖሩ ግዜ መፈክሮችን ከተሸከመልን ይበቃል።
ከልማታዊ ሰላምታ ጋር!
Filed under: Uncategorized

Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 17 Comments »
Tuesday, May 29th, 2012
በስላቃዊ ጨዋታዎቹ የሚታወቀው ዘላለም ማልኮም ክበረት በፌስ ቡክ ግድግዳው ላይ ይህንን አስቀምጧል።
What a heartbreaking news?:
<<በአቧሬ አድዋ አደባባይ ፊት ለፊት ተሰቅሎ የነበረው እና ከ35,000 ብር በላይ የወጣበት የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ 4 ሜትር በ7 ሜትር እና ‘በዘመነ ትውልድ ያልተደፈረውን አባይ የደፈረ ጀግና’ የሚል ፅሁፍ ያለበት ግዙፍ ምስል ባልታወቁ ሰዎች ተሰረቀ>>
እንኳን የዙፋኑን ወንበር አልሰረቁት እንጅ ይሄንስ ከደመወዛችንም ቢሆን ቆርጠን ወይም ቦንድ ገዝተንም ቢሆን እንተካዋለን፡፡ ካጠፋው ልታረም አለ ሰካራም፣ አይደለም እንዴ Abe ?
የሚያሳዝነው ደግሞ የሊቀ ሊቃውንት ምስል ከተሰቀለ ገና 5 ቀን እነኳን አልሆነውም እኮ፡፡ “ጠርጥር ከገንፎ ውስጥ አለ ስንጥር” ነውና ነገሩ የሽብር ሃይላትን እጅግ ጠረጠረኩ ለአቧሬና አካባቢው ህዝብ እንዲሁም ለመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ መፅናናትን እማኛለሁ፡፡
Zelalem
በርግጥ እኔ በበኩሌ ይህንን የሚያክል የጠቅላይ ሚኒስትራችን ፎቶግራፍ ገና አምስት ቀን ባልሞላ ግዜ ውስጥ መወሰዱ ጥልቅ ሀዘን ቢሆንብኝም ምናልት “ለጤንነታቸው አመቺ የሆነ ቦታ” ተወስደው ሊሆን እንደሚችልም ጠርጥሬያለሁ። አሁንም ደግሜ እመኛለሁ። ፎቶግራፋቸው ብቻ ሳይሆን እርሳቸውንም “በቂ እንክብካቤ” ወደሚያገኙበት ቦታ ብናደርሳቸው አይከፋም…!
የምር ግን ይሄ ምን ያመለክታል…?
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 7 Comments »
Monday, May 28th, 2012
በመጀመሪያም ጋሽ ግርማን አየኋቸውኮ!
በዛን ሰሞን “ሞቱ” ተብሎ ጥልቅ ሀዘን ውስጥ ከተውን የነበሩት መቶ አለቃ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ድንገት ተከስተው “እንኳን ለግንቦት ሃያ አደረሳችሁ” ብለው ፡”ሰርፕራይዝ” አድርገውናል። ትንሽ ሸንቀጥ ቢሉም እየተነፈሱ እንደሆነ በማየታችን እኛም ከመቀመጫችን ብድግ ብለን “እንኳን አብሮ አደረሰን!” ብለናቸዋል።
ኢህአዴግ አዲሳባን ከተቆጣጠረ 21 ዓመት ሞላው። ይህንንም ለማረጋገጥ ዛሬ ጠዋት አዲሳባ 21 ጊዜ መድፍ ተተኩሶላታል። ለገና እና ለመውሊድ 9 ጊዜ ብቻ እንጂተኮስ የተወሰነው መድፍ ለኢህአዴግ ልደት ሃያ አንድ ግዜ መተኮሱ መንግስት “ከሁሉ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው” ሊለን ፈልጎ እንደሆነ ግልፅ ነው።
እንግዲህ ኢህአዴግ አሁን በደንብ ጎረመሰ ማለት ነው። ይህ ወቅት ጡንቻ የሚፈረጥምበት ጢም የሚቀመቀምበት ከመሆኑም በላይ እግዜር ላልባረከው፤ ልብ የሚነፋበት ጆሮ የሚደፈንበት አስቸጋሪ ወቅት ነው። በዚህ ዕድሜ ላይ ያለ ያልተባረከ ጎረምሳ ኮረዳዎች “ሳመኝ” ሲሉት እንጂ አዋቂዎች “ስማኝ” ሲሉት ጥሪ አይቀበልም። ከላይ ከላይ መናገር እና ከኔ በላይ ላሳር ማለት ልዩ ባህሪያቱ ናቸው። (አይ ጉርምስና!) እናም ኢህሃዴግ አሁን ዋናው የአፍላ ጉርምስና ወቅቱ ላይ ይገኛል። በአራዶች ቋንቋ “ፍንዳታ” ሆነ የሚባለው ማለት ነው። ወደ ጨዋታችን ዘልቀን ከመግባታችን በፊት “ኢህአዴግዬ ጉርምስናውን በቅጡ ያድርግልህ” ብለን እንመርቀዋለን!
“ጀግናው የኢህአዴግ ሰራዊት ደርግ ሲጠቀምበት የነበረውን የሬድዬ ጣቢያ ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ተቆጣጥሮታል ግንቦት 20 ሺ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ሶስት አመተ ምህረት!” የተባለ ጊዜ አብዮታዊ ዴሞክራሲ እምነትን እና አባታችን ኢህአዴግን እንደ ግል አዳኙ አድርጎ የተቀበለው ቴሌቪዥናችን በአሁኑ ግዜ ዋና የኢህአዴግ ፓስር ሆኖ ስብከቱን ሲያሰማ ውሎ ያድራል። በተለይ ሰሞኑን ኢህአዴግ ጉርምስናውን ሲያከበር ኢቲቪ ውዳሴ እና ዝማሬ በማዝነብ የሚስተካከለው አልተገኘም። እኛም በተለይ ከህዝቡ ዘንድ የተደበቀውን ጥጋብ ለመየት የታደለው ኢቲቪ ይህንን ይመለከት ዘንድ የተቻለው “እንደምን ያለ አብዮታዊ ዴሞክራሲ መንፈስ ቢሰርፅበት ነው!?” ስንል አድንቀናል።
አፈር ስሆን ትንሽ ቆየት ባለ ጨዋታችን ላይ ያወጋነውን የአንድ የኢቲቪ ጋዜጠኛ ገጠመኝ እዝች ጋ እናምጣት፤
ጋዜጠኛው በልማታዊ ዘገባ የሚታወቅ ነው። ፐርሰንትን ማውራት ለጥጋብ የሚዳርግ ቢሆን ኖሮ ከሁሉም በላይ ይህ ጋዜጠኛ ለመንደሩ ሰው ሁሉ ጥጋብን የሚያከፋፍል በሆነ ነበር። የሆነ ግዜ ቤቱ እንግዳ መጣበት። ከዛም በአባወራ ደንብ ሳሎን ቁጭ ብሎ “እስቲ ምሳ አቀራርቢ” ብሎ ለሚስቲቱ ትዕዛዝ አስተላለፈ። ከእንግዳ ጋር ይመጣል ብላ ያልገመተች ሚስትም “ምናባቴ ይሻለኛል ባዶቤት እንግዳ ይዞብኝ መጣ…!” ብላ እየተጨነቀች ለእርሱ የተዘጋጀውን እንደነገሩ የሆነ ምሳ አቀረበች። አባወራ ሆዬ እንገዳውን፤ “ብላ እንጂ አልጠፈጠህም እንዴ?” ብሎ አየጋበዘ አንገቱን ወደ ጓዳው ቀለስ አድርጎ “ትንሽ ቅቤ ጣል አድርገሽ ወጥ ጨምሪልን እስቲ…” ሲል አዘዘ። ሚስት ክው ብላ እየደነገጠች እንግዳ ፊት “ከየት አምጥቼ…” አይባልም እና፤ “እሺ” በማለት እዛው ጓደ ቁጭ አለች።
ባልም ትንሽ ከእንግዳው ጋር ከተጨዋወተ በኋላ “የት ጠፋሽ አረ እንጀራም ጨምሪልን እንጂ…” አለ እና “ይሄውልህ ያ አለቃችን ደግሞ…” እያለ መውጋቱን ቀጠለ። ሚስት “እሺ መጣሁ” ብላ አሁንም ጓዳዋ ቁጭ ማለትን መረጠች… ቢጠብቋት… ቢጠብቋት አትመጣም፤ ከዛ ባል ሆዬ “የት ሄድሽ ቡናስ አታፈይልንም እንዴ…?” ብሎ ተጨማሪ ትዕዛዝ ቢያዛት ከቡናው ቀድሞ ደሟ ፈልቶ እየተብከነከነች፤ ጓዳዋ ኩርምት ብላ ቁጭ! በዚህ ግዜ ባል እንግዳውን ሳሎን ጥሎ “ቀረሽ እኮ!” እያለ ወደ ጓዳው ሲገባ ከተቀመጠችበት ብድግ ብላ “ስማ እንጂ ይሄ እኮ በኢቲቪ የምታሳየው የልማት ፕሮግራምህ ሳይሆን መኖሪያ ቤትህ ነው… ቅቤ ጣል አድርጊ፣ እንጀራ ጨምሪ፣ ቡና አፍዬ… ትለኛለህ ቤቱ ባዶ እንደሆነ አታውቅም…!?” በማለት ስቅስቅ ብላ አለቀሰች።
የኢቲቪ ጋዜጠኞች በቤታቸው የሌለውን ምቾት በሀሪቱ ሞልቶ ተትረፍርፏል ብለው ሲሰብኩን ትንሽም ድንቅፍ አይላቸውም። ይሄ በእውነቱ ከፍ ያለ “ምንፍስናን” የሚጠይቅ የፃድቅ ሰው ስራ ነው።
የሆነ ሆኖ ሰሞኑን ከመቼውም ግዜ በበለጠ ቴሌቪዥኔ ዋና ካድሬ ሆኖብኝ ከርሟል። ላለፉት ስምንት አመታት ተከታታይ እደገት ማሳየታችንን፣ አራት ዴሞክራሲያዊ ምርጫዎችን ማከናወናችንን፣ የትምህርት ጥራትን ማረጋገጣችንን፣ በምግብ ምርት ራሳችንን መቻላችንን፣ ከአገር አልፈን የአፍሪካ መኩሪያ መሆናችንን አስረግጦ ነግሮኛል። (“ይሄ ሁሉ ሲሆን እኔ የት ነበርኩ!?” ብለው እንዳይጠይቁኝ ብቻ)
እኔ የምለው ግን ኢህዴግ ይህንን የጉርምስና ግዜውን በሚያከብርበት ወቅት አዲስ ስድብ ማስመዘገቡን ልብ ብላችሁልኝ ይሆን? “ሟርተኛ” የሚለውን ስድብ በቴሌቪዥኔ ስንት ግዜ እንደሰማሁት ለመቁጠር ፈልጌ ደክሞኝ ነው ያቆምኩት። ይህንን ስድብ ከኢህአዴግ አደረጃጀት ሃላፊው አቶ ሬድዋን ጀምሮ ሁሉም ሃላፊዎች እና ጋዜጠኞች እንደየ ሃላፊነታቸው መጠን በተደጋጋሚ ሲጠቀሙበት ሰምቼ አንድ ስድብ ላይ ከሚሻሙ ለምን፤ “መተተኛ” “አስማተኛ” “ድግምተኛ” “ሰላቢ” እና የመሳሰሉትን ተመሳሳይ ስድቦች እየቀላቀሉ አይጠቀሙም? ስል ተጨንቄላቸዋለሁ። ለነገሩ ለቀጣዮቹ ግዚያት እንቆጥብ ብለው እንጂ ከእኔ ያነሰ የስድብ ዕውቀት አላቸው ብዬ አላስብም። እውነትም ደግሞ ቁጠባን ባህል ማደረግ ጥሩ ነው።
ለማንኛውም ዛሬ የኢህአዴግ ልደት ነው። ልደቱን አስመልክቶ ምን ያህል ጥጋብ እና ተድላ ላይ መሆናችንን መንግስታችን ነግሮናል። አልጠገብንም ብሎ መከራከር አይቻልም። በአገሪቱ የመፃፍ እና የመናገር ነፃነት ያለ ምንም ገደብ እንደተፈቀደም ተነግሮናል። የለም እየታፈንን ነውኮ! ብሎ መጨቃጨቅ አይቻልም። ምንያቱም ይሄ ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው። ጠግባችኋል ተብለናል። አዎ ጠግበናል። ዴሞክራሲ ሰፍኖላችኋል ተብለናል አዎ ሰፍኗል። እግዜር ይስጥልና! (ይቺ እግዜር ይስጥልና እንዴት ያለች ምርቃት መሰለቻችሁ…!?)
ከሁሉ የሚያስገርመኝ 1
ህገ መንግስቱ
ኢህአዴግ እጅግ በጣም ከሚመካባቸው ትህምክቶቹ መካከል “ህዝብ ተወያይቶበት” ያፀደቀው ህገ መንግስት ባለቤት አደረኳችሁ” የሚለው ይገኝበታል። ነገር ግን በዚህ ወቅት በርካታ ተንታኞች ኢህአዴግ ራሱ ህገ መንግስቱን እያከበረ እንዳልሆነ ይናገራሉ። (እንደው ለትህትና ተንታኞች አልኩ እንጂ እኔ ራሴ አረ ብዙ ታዝቤያለሁ)
ህገ መንግስቱ “ከዚህ ህገ መንግስት ጋር የሚቃረኑ ማነኛቸውም አዎጆች ደንቦች እና መመሪያዎች ተቀባይነት የላቸውም” ይላል። ግን ማን ይሰማዋል…? መንግስታችን የሚያወጣቸው የተለያዩ አዋጆች እና መመሪያዎች ህገ መንግስቱ ከሚለው በተቃራኒ እየታወጁ እና ተግባራዊ እየተደረጉ ተመልክተናል። በትሹ የመሰብሰብ እና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነት በተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎች “ተከልክሏል” ለማለት ያስደፍራል። የቅርብ ግዜ ምሳሌ ብናመጣ እንኳ ዳኛ ብርቱካን ሚዴቅሳ ዳግም የታሰረች ግዜ ደጋፊዎቿ ሰልፍ ሊወጡ ሲሉ “ከ250 በላይ ሰው ማሰለፍ አይቻልም” ተብለዋል። በአዲሳባ “መድረክ” የመሰብሰቢያ አዳራሽ አጥቶ ሁልግዜ ኡኡታውን የሚያሰማው ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረን መመሪያ ሰለባ በመሆኑ ነው። በነገራችን ላይ ለዚህ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውጪ ሀገር ተቃውሞ ሰልፍ እና የህዝብ ቁጣ ሲያጋጥማቸው “ክው” የሚሉት። ሀገር ውስጥ ቢፈቅዱልን ይለምዱት ነበር። (የሚሉ ወገኖች አሉ ብለው ይጨምሩልኝ)
በደንብ እናጥና ካልን ሌሎችም መመሪያዎች እና አዋጆች ህገ መንግስቱን ሲረመርሙት ማየት ብርቅ አይደለም። በቅርቡ ብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት እንኳ ከአቅሟ የማትመው “ፅሁፋችሁን መጀመሪያ መርምሬ ነው” ብላናለች! አረ ህገ መንግስቱ ቅድመ ምርመራ (ሳንሱርን) ይከለክላል ብለው ዋይ ዋይ ቢሉ “ይሄ የማተሚያ ቤቱ መመሪያ ነው” ይባላሉ!።
ከሁሉ የሚገርመኝ 2
ኢህአዴግ ልደቱን ባከበረ ቁጥር የጦር ገድሉን አንስቶ አይጠግብም። በገድሉም ይህንን ትግል ለማድረግ ያነሳሳውን ምሬት እና ብሶት ደጋግሞ ያነሳል። ቀጥሎም ከዚህ ምን እንማራለን? ብሎ ይጠይቃል? በርግጥ መልሱ “አሁንም ብሶት ከበዛ ቆርጦ መታገል ነው” የሚል ነው። (በቅንፍ የትግሉን አይነት የሚመርጠው ታጋዩ እንደሆነ አስታውሳለሁ።) ግን ይህንን ጥያቄ መጠየቅ በዚህ ወቅት ተገቢነውን?
ከሁሉ ያሳቀኝ
አሁን የግንቦት 20 ልደት እያከበረ ያለው ኢቲቪ አንድ ነገር ሲናገር ሰማሁት “ከዚህ ቀጥሎ ምርጫ ከድምፅ ካርድ እንጂ ከጠመንጃ አፈ ሙዝ አይገኝም” የሚል ንግግር። እኔ የምለው “ተኳሾቹ” በምርጫ 97 የነበረውን ሰው በሙሉ ገድለን ጨርሰናል። ብለው ነው እንዴ ሪፖርት ያደረጉት… (አረ ፍሬንድ ወቅቱን የታዘቡ ብዙ አሉ!) “ከጠመንጃ አፈ ሙዙ ስልጣን አይገኝም…” የምሬን ነው የሳኩት… አሃ ምናልባት የአጋዚዎች ተኩስ የጠመንጃ አፈሙዝ አይባልም ይሆን…? ይቺ የጦር እውቀት ማጣት እኮ የምታስጠቃው ይሄኔ ነው!
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 1 Comment »
Thursday, May 24th, 2012
ወዳጄ ኢዮብ ብርሃነ፤ “አንዲት ኢትዮጵያዊት ሞት ተፈረደባት” የሚል መረጃ አድርሶኝ ነበር። ከዚሁም ጋር “ካላመንከኝ እህቷን ደውለህ ማናገር ትችላለህ!” ብሎ የስልክ ቁጥሯንም አስቀምጦልኛል። እኔም የፈጀውን ይፍጅ ብዬ ደወልኩላት…
እርሷም ይህንን አረጋገጠችልኝ…!
ሰናይት ትባለለች። በዱባይ “አባደና” ሰፈር በቤት ሰራተኝነት ተቀጥራ ትሰራ ነበር። በምትሰራበትም ቤት አሰሪዋ የምታደርስባትን ጥቃት ለመከላከል ስትል በወሰደችው ርምጃ ርጉዝ አስሪዋን ትገድላታለች። ከዛም ደም የነካ ልብሷን ስታቃጥል በቤት ውስጥ የነበረው የ2 ዓመት ህፃን በጭስ ታፍኖ ይሞታል።
ወድያውም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውላ ፍርድ ቤት የቀረበችው ሰናይት ፍርዷን ለሁለት አመታት ስትከታተል ቆይታ የሞት ፍርድ ተፈረደባት። ሰናይት በጠበቃዋ አመካኝነት “የሞት ፍርዱ ተገቢ አይደለም” ብላ ይግባኝ የጠየቀች ሲሆን ይግባኙም ድጋሚ ታይቶ በድጋሚም የሞት ፍርዱ ተበይኖባታል።
እህቷ እንደነገረችኝ ከሆነ “ከዚህ በኋላ ይግባኝ መጠየቅ አትችይም!” ተብላለች።
ወይ ጣጣችን…! ምን ማድረግ ይቻለን ይሆን? የእህቶቻችን ሰቆቃ ማብቂያው የት የሆን…!? በእውነቱ ይህንን ዜና ስፅፍ እየተሰማኝ ያለው ሀዘን ማቆሚያው መቼ ነው…? መቼ ነው ሀገራችን ለሁላችንም የምትበቃን…? መቼ ነው መሰደዳችን የሚቆመው? መቼ ነው…?
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 10 Comments »
Wednesday, May 16th, 2012
ሰላም ወዳጄ… በቀጠሯችን መሰረት መጥቻለሁ።
ትላንት ግንቦት ሰባት ነበር። ይቺ ቀን ለኛ የተለየች ቀን ነች። የዲሞክራሲ መብራት ብልጭ ብላ የጠፋችበት በርሱ ጦስም በርካታ አቅም እና ችሎታ ያላቸው ትራንስፎረመሮች ተቃጥለው፤ በምትካቸው ትራንስፎርሜሽን የተባለ ቃል መተካት የጀመረባት ታሪካዊ ቀን። እስቲ ያቺን ሰዓት ትንሽ እንዘክራት…
አንድ
እኔ በምርጫ ዘጠና ሰባት ጎጃም አካባቢ ነበርኩ። የአቤ ጎበኛው የትውልድ ቦታ የሆነችው አቸፈር፣ ዱር ቤቴ፤ እንዲሁም አዴት እና መራዊ ከዛም አልፎ ሶስት እና አራት ሰዓት በእግር የሚያስገቡ ገጠራ ገጠሮችን በስራዬ ሰበብ ሳስሳቸው ነበር። ከዛ አካባቢ በአንዱ ገጠር የሚከተለውን አንዱ አጫወተኝ።
“ይገርምሃል ጋሼ ሪም ቀበሌ ህዝብ ተጨንቋል።”
“ምን አጋጠመው?”
“የቀበሌው ሰው ሁሉ ካርዱን ለቅንጅት ሊሰጥ ተስማመቶ ነበር።”
“ታድያስ?”
“ኋላ ላይ ሲቆጠር አንድ ካርድ ለንቢቱ ገብታ ተገኘች።”
“ይገርማል። ታድያ ጭንቀቱ ከምን መጣ የሚፈልጉትን መርጠው የለ?”
“እሱማ ልባቸው የፈቀደውን መርጠዋል። ግና ይሄ ንቢቱን የመረጠው አንድ ሰው ማነው ከቀዬው ትዕዛዝ እና ስምምነት እንዴት ሊወጣ ቻለ ብሎ ነው ሰዉ ጭንቅ የገባው።” አለኝ።
አንድ ነጥብ ሁለት
በዚሁ ቀበሌ የመረጡትን መርጠው ካበቁ በኋላ ኢህአዴግ “ተጭበርበሪያለሁ” ብሎ ምርጫው ካልተደገመ ሞቼ እገኛለሁ አለ። (አሉ… ይቺ እንኳ “አሉ” ናት) ታድያ ሰዉ በሙሉ በምን ተስማማ መሰላችሁ… “እኛ ዳግሞሽ ምርጫ አንገባም። ከፈለጋችሁ ገበያ ለይ እንሰብሰብና ንቢቷን የሚል ካለ አለሁ ብሎ ይቆጠር እንጂ አንድግዜ የመረጥነውን መርጠናል።” አሉ (አሉ።)
ሁለት
አዴት አካባቢ በሆነው ቀበሌ ደግሞ ምርጫው ተጠናቆ ማታ ላይ ድንገት መብራት እልም ብሎ ጠፋ። ይሄኔ “ካርድ ሳይቆጠር አንሄድም” ብሎ የነበረው የአካባቢው ህዝብ ባትሪ ፍለጋ መተራመስ ያዘ። ባትሪው ተገኘ። ሲበራ ከታዛቢዎች መካከል አንዱ የኢህአዴግ ቀንደኛ ተከራካሪ የነበረው ሰውዬ ጠፍቷል። የት ገባ? ቢጠሩት ቢፈለጉት የት ይገኝ!? መብራቱ ከመጥፋቱ በፊት አጠገባቸው ነበረ። ታድያ የት ገባ?
ትንሽ ቆይቶ መብራት መጣ ይሄን ግዜ አንድ ሰውዬ በአካባቢው ሰዎች ማጅራቱ ተጨምድዶ አንዳች ነገር ታቅፎ፤ “ይሄ ሌባ” እየተባለ ወደ ምርጫ ጣቢያው ገባ። ሰውየው “የት ጠፋ?” ብለው ሲጨነቁለት የነበረው አፍቃሪ ኢህአዴግ ነበር። ምን አድርጎ ነው? ተብሎ ሲጠየቅ ለካስ መብራት እንደ ጠፋች ኮሮጆ ይዞ ነበር የተሰወረው። ድንገት የአካባቢው ሰዎች እጅ ከፍንጅ ይዘው ማጅራቱን ጨምድደው አመጡት እንጂ!
ሶስት
ምርጫው አለቀ እና እነዛ ቀውጢ ቀናት መጡ። ፖሊሶች ማንኛውንም ጎረምሳ እየወሰዱ በየእስር ቤቱ ይከቱት ጀመር። በአንዱ የክፍለሀገር ከተማ የሚከተለው ሆነ፤
ወጣት ልጃቸው የታሰረባቸው አባት ወደ ፖሊሶቹ አዛዥ ሄደው “እባክህ የኔ ጌታ የኔ ልጅ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም ለራሱ ህመምተኛ ነው ልቀቁልኝ” ብለው ይጠይቃሉ። ፖሊሱም ትኩር ብሎ እያያቸው “የእርስዎ ልጅ ምንም ውስጥ እንደሌለበት ለማወቅ ትንሽ ግዜ ያስፈልገናል። አሁን ገና እየተረጋገጠ ነው” ብሎ ይመልስላቸዋል። አባትም በአዕምሯቸው “እየተረጋገጠ ነው…” የምትለው ቃል አቃጨለችባቸው። ከዛ ደግመው ጠየቁት፤ “ካልተረጋገጠ አይለቀቀም…?” “አዎ መጀመሪያ መረጋገጥ አለበት” አላቸው ፖሊስ ኮስተር ብሎ “አይ አበሳዬ በሉ እንግዲያስ አደራ እጁ በሽተኛ ነው ስትረጋግጡት ተጠንቀቁልኝ… በስንት ወጌሻ ነው የተሻለው” በማለት የነሱ ማረጋገጥ መረጋገጥ መሆኑን ነግረዋቸው እያዘገሙ ሄዱ።
አራት
በዘጠና ሰባቱ ምርጫ ጦስ ስለመጡ አስቂኝ ነገሮች ወዳጃችን በኋይሉ ገብረ እግዚአብሄር “ኑሮ እና ፖለቲካ” በተባለው መፅሀፉ ውስጥ ካጫወተን ደግሞ ትንሽ እንቀላውጥ፤
በግርግሩ ሳብያ ፖሊሶች ማታ ማታ በእያንዳንዱ ሰው ቤት እየገቡ ድምፁ ጎርነን ያለ ጎረምሳ ሁሉ እያፈሱ ይወስዱ ነበር። ታድያ በአንዱ ማታ በአንዱ ቤት ፖሊሶቹ ሲገቡ፤ ጀርመን አገር ያሉት የልጆቹ አባት በቴሌቪዥን የሚያዩት ነገር ረብሿቸው ስልክ ሲደውሉ እኩል ሆነ። ይሄን ግዜ በፖሊሶቹ ዘው ብሎ መግባት የተደናገጡት ልጆች ስልኩ ሲያምባርቅ በፍርሃት ያዩት ጀመር። ይሄኔ አንዱ ቆፍጣና ፖሊስ አንዱን የቤቱን ጎረምሳ “ስልኩን አንሳ” ብሎ አዘዘውና የሚያወራውን ለመስማት ጠጋ ብሎ።
“ሃሎ”
“ሃሎ”
“የምን ጦርነት ነው የምሰማው ልጆቼ ተረፋችሁ?”
ልጅ የሚመልሰው ጠፋበት ትንሽ እንደማሰብ አለና፤ “አባዬ ምንም ችግር የለም። ሁላችንም ደህና ነን። ፖሊሶች እቤታችን ድረስ መጥተው እየተንከባከቡን ስለሆነ አታስብ!” በማለት መለሰ አፉ በፍርሃት እየተሳሰረ።
አምስት
በአመቱ ሰሜን ወሎ ፍላቂት ላይ ትንሽ ቆይታ አድርጌ ወደ ጎንደር አርማጭሆ ዘልቄ ነበር።
አምስት ነጥብ አንድ
ፍላቂት
የፍላቂት ህዝብም እንደመላው የሀገሪቱ ህዝብ ሁሉ የመረጠው ቅንጅትን ነበር። ታድያ በዛው አመት የአካባቢው ገበሬ ሁለት አይነት ወከባ ነበረበት። አንዱ ማዳበሪያ እና የመሳሰሉትን አገልግሎቶች ሲጠይቅ የየቀበሌው ካድሬዎች “ቅንጅት ይስጣችሁ” እያሉ የሚያጉሏሏቸው ሲሆን ሌላው ደግሞ “ምን አድርገን ነው እኛን ያልመረጣችሁን?” የሚል ስብሰባ ነበር። ታድያ ለምን አልመረጣችሁንም? በሚለው ላይ የሰማናት ቀልድ በጣም ታዋቂ ሆናለች። እዚህ ላይ እርሷን ሳያነሱ ማለፍ አግባብ አይደለም።
ካድሬው፤ “እኛ እስከዛሬ ትምህርት ቤት ሰርተንላችሁ… ጤና ጣቢያ ገንብተንላችሁ… መንገድ ጠርገንላችሁ… ለምንድነው ያልመረጣችሁን?”
ገበሬዎቹ፤ “እግዜር ይስጣችሁ ደህና አድርጋችሁ ሰርታችሁልናል! አሁን ግን ይበቃችኋል እናንተም ይደክማችኋል አረፍ በሉ እኛም ትንሽ አረፍ እንበል!”
አምስት ነጥብ ሁለት
ጎንደር
ጎንደር አርማጭሆ ስንደርስ ስለ አርበኛ ግንባር ዝና ሰማን። የአካባቢው ሰው የመንግስት ታጣቂው ሳይቀር አርበኞችን የሚያነሳቸው በመልካም ነው። ተኳሽነታቸውን እና ስነምግባራቸውን አውርተው አይጠግቡም። አንዱ የመንግስት ታጣቂ ስለ ግንቦት ሰባቱ ምርጫ እንዲህ አወጋኝ፤
“እኛ ገና ከጀምሩ ምርጫ ምርጫ መባሉ ደስ አላለንም ነበር። በስብሰባ ላይ ከወረዳ ለመጡትም ነገረናል። ‘ሰዉ ያሻውን ይምረጥ ካላችሁ አይሆንም፤ ኋላ መዋረድ ይመጣል። ሰዉ ሆድ ስለባሰው አንድ እንኳ የሚመርጣችሁ አይገኝም። ስለዚህ ዝም ብለን እንደቀደመው ግዜ እዚች ላይ አጥቁሩ እያልን እኛው እንምራቸው እና ንቢቱን እናስመርጥ።’ ብለን ብንላቸው “የለም ዲሞክራሲ ነው።” አሉን ከዛስ ምን ሆነ አትለኝም…? ሁሉም ሆ ብሎ ቅንጅቱን መረጠ። ከዛልህ “እኛን በአግባቡ ስላልቀሰቀሳችሁ ነው” ብለው ብዙ ጓዶቻችንን እስር ዶሏቸው። ኋላ ያልታሰርነው ሆ ብለን ወጣናታ… እንግዲህ ለአርበኛ መግባታችን ነው። “በዛሬው እለት የታሰሩ ጓዶቻችን ካልተለቀቁ ነገ ከጫካ ነን።” ብንላቸው ማምሻውን በኦራል መኪና አምጥተው አስረከቡን!
እኔ የምለው ቀጣዩ ምርጫ መቼ ነው…?
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 3 Comments »
Monday, May 14th, 2012
ሰሞኑን ሰለሞን ተካ “ፅናት” በተባለ የሬድዮ ጣቢያው ላይ ጮክ ብሎ ሙስሊም ወንድሞቻችንን በሚመለከት አንድ መግለጫ ሰጥቷል። ሰለሞን የቱ…? ብሎ የጠየቀ ካለ ሰለሞን ዜሮ ዞሮው በሚል አብራራለሁ። መጨመር ካስፈለገም ምን ነካው? የማይባለው ሰለሞን ተካ! ብንለውም ይሆናል።
የሚገርመኝ ነገር 1
ይሄ “ፅናት” የተባለው ራዲዮ ጣቢያ አዘጋጁ ራሱ ሰለሞን ተካ ነው። ስጠረጥር ባለቤቱም እርሱ ይመስለኛል። ታድያ እዚህ ላይ ግርም ያለኝ ነገር፤ ሰለሞን እንዴት ይሄንን ስም ተሸክሞ ቆሞ መሄድ እንደቻለ ነው። በእውነቱ ይሄ ተዓምር ነው። ሰለሞን ተካ ዜሮ ዜሮ፤ ፅናት የሚል ስም በላዩ ላይ ተጭኖት በአደባባይ ሲንከላወስ ማየት አይጥ አንበሳ አዝላ ስትዞር ከማየት ጋር እኩል ያስደንቃል።
የሚገርመኝ ነገር 2
እኔ የምለው ሰለሞን ተካ እንዴት ነው ነገሩ አነጋገረህ እኮ እንደ መንግስት ነው። መቼ ነው የነገስከው የኔ ጌታ። አለግባኝም “ጨለፍ” አደረግህ እንዴ? እውነቴን ነው የምለው ከቤተሰብ እና ዘመድ ጋር ተቆራርጠሃል ማለት ነው? እንጂማ በአደባባይ እንደዚህ ስትናገር በቀጥታ የአዕምሮ ህክምና ቦታ ወይም ደግሞ ፀበል… ወይም ዱዓ ለሚያደርግ ቃልቻ ወስዶ መስጠት ይገባ ነበር።
የሚገርመኝ ነገር 3
የኢህአዴግ ሰዎች እንዴት ዝም አሉ? የምሬን ነው። በዚህ አነጋገሩ እና በዚህ ለዛው ስለሞን ተካን ኢህአዴግን የሚወክል ጋዜጠኛ ማድረግ የሚያመለክተው ትልቅ የሆነ የሰው ሃይል ችግር መኖሩን ነው። እውነቴን ነው የምላችሁ ውድ የኢህአዴግ ዋና የስራ ሂደት ባለቤቶች ሆይ ሰለሞን ተካ እንኳንስ በጋዜጠኝነት እና በዘፈኑም ቢሆን ለሚያደርገው “አስተዋፅኦ” ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል። ባለፈው ግዜ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንን “ቅንድቡ ያማረው” ብሎ ዘፍኖላቸው ስንቱ ነው በሌላ የጠረጠራቸው? እሱ የራሱ ጉዳይ እርሳቸው ግን በምን እዳቸው እንዲህ አይነት ጥርጣሬ ውስጥ ይወድቃሉ። ምንም ቢሆን ባለትዳር ናቸውኮ!
እውነቱን ለመናገር ሰለሞን ተካ ለኢህአዴግ በጋዜጠኝነት እሰራለሁ ማለቱን ማንኛውም ለድርጅቱ አሳቢ የሆነ ግለሰብ ሊያስቆመው ይገባል። የምሬን ነው የምለው ድርጅቱ ስንት የሚተችበት ጉዳዮች እያሉት በማንም ሰርጎ ገብ የሚብጠለጠልበት ምክንያት አለ ብዬ አላስብም።
ቀጥሎ ያለው አንቀፅ ለኢህአዴግ ከልብ በመቆርቆር የተሰነዘረ ነው።
እንደኔ እምነት ሰለሞን ተካ በቅፅል ስሙ “ብሪቱ” እልም ካለው የተቃውሞ ጎራ ወደ ኢህአዴግ ደጃፍ መምጣቱ ለኢህአዴግ ጥሩ ነው። ነገር ግን “ደርሶ ከኔ በላይ ኢህአዴግ ላሳር” ማለቱ እና በየአደባባዩ ድርጅቱን የሚወክል ወሬ ማውራቱ ለኢህአዴግም መልካም ገፅታ አይበጅም። አረ በድንብ ስሙት ጎበዝ ሰውየው እኮ እሳት ይቀረዋል። ስለ እውነት እላችኋለሁ አልበሰለም። ታድያ በሳል ሰው ከየት እናምጣ? ካላችሁ ድርጅቱ ራሱ ተሀድሶ ያስፈልገዋል ማለት ነው። አለበለዛ ግን “ሃይ” ባይ ሰው ያስፈልጋል። ልክ ተቃዋሚዎች “መለስ በቃ” እንደሚሉት አይነት የኢህአዴግ ሰዎች ይበልጡኑም ለድርጅቱ አሳቢ የሆኑቱ “ሰለሞን በቃ” ብለው ሊያስቆሙት ይገባል። ከልቤ ነው የምላችሁ። (ከፈለጋችሁ ንግግሬ ላብራቶሪ “ቼክ” ይደረግ)
ለማንኛውም ሰለሞን ተካ ሰሞኑን ራሱን መንግስት አድርጎ መግለጫ ሰጥቷል። በመግለጫውም “መጅሊስ ይውረድ መንግስት በእምነታችን ጣልቃ አይግባ” ሲሉ ፍፁም ሰላማዊ የሆነ ተቃውሞ እያሰሙ ያሉ ሙስሊም ወዳጆቻችንን “የአልቃኢዳ ቅጥረኞች” ብሏቸዋል። ሰለሞን ይህንን ነገር ከየት አመጣው ያልን እንደሆነ ባለፈው ግዜ ጠቅላይ ሚንስትራችን “በአርሲ እና ጅማ አካባቢ የአልቃይዳ ሴል ተገኝቷል” በማለት የተናገሩትን ለመኮረጅ ሞክሮ ነው። ሰሌ በእብደቱ ተዓምር በየ ጁምዓው ተቃውሞ የሚያሰሙ ሙስሊሞችን በሙሉ “የአልቃይዳ ቅጥረኛ” ብሏቸዋል። አላህ ምህረቱን ያውርድልህ እንጂ ይሄ የጤና አይደለም። “ፍሬንዴ” የአልቃይዳ ቅጥረኛ ቢሆኑማ በአንድ ቦንብ “እምጷ” ያደርጉህ ነበር።
በመጨረሻም
አንድ ጥያቄ
እኔ የምልህ ሰለሞን ተካ ባለፈው ግዜ እኮ “ከዚህ ቀጥሎ ቤተሰቤን ይዤ መጥቼ አዲሳባ መኖር እጀምራለሁ” ብለህ የአዲሳባ ህዝብ በጉጉት እየጠበቀህ ነው። እኔ የምልህ ያንግዜ ካዛንቺስ አካባቢ የጎሻሸሙህ ነገር አናትህን ነክቶት ይሆን እንዴ!? ያልከውንም አስረሱህ የምትናገረውንም አቀዣበሩብህ እኮ!
ሌላ ደግሞ ራስህን “አርቲስት” እያልክ ስተጠራ ሰምቼ ለዚህ ጨዋታ የሚሆን ፎቶ ፍለጋ “ጎግል ኢሜጅ” ውስጥ ገባሁልህና “አርቲስት ሰለሞን ተካን” አፋልገኝ ብለው ብሰራው አንዴ አበበ ተካን ሲያመጣልኝ፤ አንዴ ሰለሞን ቦጋለን ሲያመጣልኝ ስሰማ ተሳስቼ ይሆናል ብዬ ደመደምኩ። ይቅርታ ትደግምልኛለህ… ምን “…ቲስት” ነኝ ያልከው?
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 15 Comments »
Thursday, May 10th, 2012
ይቺ ጨዋታ ዛሬ ቀን ላይ ለኢትዮጵያ ተዘጋጅቶ የነበረው ብሎጋችን ላይ ለጥፈናት ነበር። በዋናው ቤትስ ለምን ይቅርባት ተብላ እነሆ እዚህም መጣች!
ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ሁልግዜም እከታተለዋለሁ። ወደኔ የሚመጣውን ካላቋረጡት በቀር… ወደፊትም በትጋት ማየቴን እቀጥላለሁ። ታድያ ሁልግዜም እንዳስደነቀኝ ሁልግዜም እንዳስገረመኝ ነው። እንደውም አሁን አሁን “ከሪሞት” ላይ ወደ ኢቲቪ የሚወስደውን ቁጥር ስጫን በለሆሳስ “ታምረ ኢቲቪን ልከታተል” እያልኩ ነው።
እኔ የምለው ዜና አንባቢዎቻችን በተለይ መሰለ እና ተመስገን አለቅጥ ሽቅርቅር ያሉበትን ምክንያት ሊነግረኝ የሚችል አለ? እንዴ ሞዴሎች እኮ ነው የመሰሉት። አንዳንዴማ የፍትሁ ወዳጃችን ተመስገን ደሳለኝ ባለፈው ግዜ “መለስ ሆይ ባልተመቸው ህዝብ ላይ የተመቸው መሪ መሆን አስከመቼ…?” ብሎ የፃፈውን እያስታወስኩ እናንት ዜና አነብናቢዎች ሆይ በጎስቋላው ህዝብ ላይ እንዲህ መሽቀርቀር እስከመቼ? ብዬ ልጠይቃቸው ይቃጣኛል።
ስለ ኢቲቪ በደንብ ቁጭ ብለን በሰፊው የምንነጋገርበት የሆነ ቀን ይመጣል። አሁን ግን በተለይ ለኢትዮጵያ ወዳጆቼ ብሎጓም ሳትዘጋ ገብስ ገብሱን እንጨዋወት ገብስ ገብሱን ተብሎ የተገለፀው የኢቲቪ ማስታወቂያዎች ናቸው፤
ገብስ ገብሱን 1
እኔ የምለው በኢቲቪ አንድ ማስታወቂያ አይታችሁልኛል? ማስታወቂያው የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማስታወቂያ ነው። ልማታዊቷ ሙሉአለም ሆዬ ብቅ ብላ “የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሊሸልማችሁ ነው በኤስ አም ኤስ የሆነ ነገር ብላችሁ ላኩልንና በሽልማት እናንበሻብሻችኋለን” ትለናለች። ለምንድነው የምትሸልሙን? ብለን ብንጠይቅ መልስ የለውም። ዝም ብሎ ያለምንም ምክንያት ምን በወጣቸው ነው የሚሸልሙን? ወይስ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አትሌቶችን ብቻ ሳይሆን እድላችንንም እንዲያሯሩጥ መብት አለው? ፌዴሬሽኑ ነጋዴ ቢሆን “ለማስታወቂያ ግብአት ነው” አንላለን። ወይም ደግሞ እንደሰዉ በጨዋ ደንብ “ተቸግሬ ነው የማስቸግራችሁ ለገቢ ማሰባሰቢያ ተባበሩን እግረ መንገዳችሁንም ዕድላችሁን ሞክሩ” ማለትም የአባት ነው። አለበለዛ እኮ ነገ የጠቅላይ ሚኒስትሩም ቢሮ ተነስቶ “በኤስ ኤም ኤስ ሽልማት በሽልማት ልናደርግዎ ቆርጠን ተነስተናል!” ሊለን ነው። (ውይ እኔ ደግሞ ዘልዬ እርሳቸው ቢሮ ላይ ይቅርታ…) የምር ግን ካለ አንዳች ምክንያት “ልሸልማችሁ እጣ ቁረጡ” ብሎ ማለት ከቁማር ተለይቶ ይታያል? ቁማር ለማጫወት ደግሞ ለአስቆማሪ ድርጅት እንጂ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መብት ያለው አይመስለኝም ስራውም አይደለም። ኢቲቪም ይህንን ማስታወቂያ ከመስራቱ በፊት ፈተሽ ማድረግ አለበት ብዬ አምናለሁ። ለማንኛውም እርስዎ ሁለት ብርዎን ከመቅለጥዎ በፊት ለምን ብለው ፈተሽ ያድርጉ?
ገብስ ገብሱን 2
ይሄኛው ማስታወቂያ ደግሞ የኮንደም ማስታወቂያ ነው… ልጁ በአንድ የግንባታ ስራ ላይ የተሰማራ ነው። በስራ ላይ እያለ አንዲት ምስኪን ኮረዳ የሚሸጥ በቆሎ እሸት ቅቅል (መሰለኝ) በእቃ ታቅፋ ስታልፍ ያያታል። ከዛም ተንደርድሮ ወደ ልጅት ይሄዳል። በቴሌቪዥን ስናየው የበቆሎ ቅቅሉን ዋጋ እያስቀነሰ ነው የሚመስለን። ታድያ አንዲት ሴት በመኪና በአጠገባቸው ስታልፍ ምን ሲያደርግ እንዳየችው እንጃ መኪናዋን ቀጥ አድርጋ አቁማ እየተጣደፈች ኮንደሟን መዥረጥ አድርጋ ታሳየዋለች። ከዛም የስራ ባልደረባው ሽማግሌ ከኪሳቸው ኮንደማቸውን አውጥተው ያሳዩታል፤ እያለ እያለ በአካባቢው ያለ ሁሉም ሰው ኮንደሙን እያወጣ ለጎረምሳው ሲያሳየው እርሱም ከኋላ ኪሱ ብቅ ያደርገዋል። ምን ማለት ነው…? በቆሎ ቅቅል እና ወሲብን ምን አገናኘው? ኢቲቪ ምንድነው የሚመክረን….? “ጎረምሶች ሆይ ማንንም ሴት እንዳታልፉ የስጋ ፈቃዳችሁን አላፊ አግዳሚው ላይ መፈፀም ትቻላላችሁ ማለቱ ነው?” ወይስ ምንድነው? ግራ ያጋባኝ ማስታወቂያ ነው።
ገብስ ገብሱን 3
ይቺን እንኳ ከዚህ በፊትም ብያታለሁ። ግን ከጓደኞቿ ጋር ትደገም ብዬ ነው። “መግብ ልጅን መግቡ በእድሉ ያድጋል እንዳትሉ” የምትል ህፃናትን ተመጣጣኝ ምግብ መመገብ እንዳለብን የምታስገነዝብ ማስታወቂያ ነች። እዝች ላይ ሁሌ ግራ የሚገባኝ ነገር አለ። ልጆቻችንን የማንመግበው እና “በእድሉ ያድጋል” የምንለውኮ እጅ አጥሮን ነው እንጂ ቢኖረንማ… “ጎሽ ለ ጇ ስትል…” ብለን የተረትነው እኛም አልነበርን? የኛ ሰፈር መዋል ህፃናት ተማሪዎች ያሉትን በሀይሉ አልነገራችሁም እንዴ? “ልጆች ከኮልስትሮል ነፃ የሆነ ቅቤ ብሉ እሺ” ብላ መምህሯ ትመክራለች። ተማሪዎቹስ ምን አለ…? “ከየት አምጥተን ቲቸር!?”
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 2 Comments »
Thursday, May 10th, 2012
እኔ ዘወትር ስለመንግስቴ የምጨነቀው፤ እኔ ሁሌም የፀሐዩ መንግስቴ ነገር የሚያቃጥለኝ፣ እኔ ከታማሚ ካድሬዎች ይልቅ ለድርጅታችን ታማኝ የሆንኩት… ሰሞኑን ስለመንግስቴ አብዝቼ ስጨነቅ እና ስጠበብ ቆይቻለሁ።
ባለፈው ግዜ በመርካቶው አንዋር መስጂድ ውስጥ ሁለት የመካከለኛው ምስራቅ ወጣቶች “በቁጥጥር ስር” ውለው በኢቲቪ ዜና አይተናቸዋል። ወጣቶቹ “ከኤርፖርት በቀጥታ መርካቶ ሄደው ወረቀት ሲበትኑ እንደነበር” ተነግሮናል። እዚች ላይ አንዳንድ አስተያየቶችን ሰጥቼ ዘወር ልበል። እኔ የምለው ምናባታቸው ቆርጧቸው ነው ወረቀት የሚበትኑት? የሚለው ብስጭት ውስጤ እንዳለ ሆኖ ሲበትኑ የነበረውን ወረቀት ግን ብናየው እንዴት ደስ ይለኝ ነበር። አዎና ለብዙዎች ትምህርት ይሆን ነበር። በርግጥ እኔ እንደምጠረጥረው ከሆነ ዘንድሮ ሁሉ ሰው የተነሳው በርሳቸው ላይ ነውና ፈረንጆቹ ሲበትኑ የነበረው ወረቀት “መለስ በቃ” የሚል እንደነበር እጠረጥራለሁ። ይቅርታ እዝች ጋ ትዝ ያለኝን በአዲስ መስመር ላይ እናውጋት፤
በነ ኤልያስ ክፍሌ መዝገብ ተብሎ እነ ውብሸት ታዬ ፍርድ ቤት ሲመላለሱ በነበረበት ወቅት ያጋጠመኝን ነው የማወጋዎ… (ክቡር ፍርድ ቤት ይሄ ጉዳይ እልባት ስላገኘ እንዳሻን መቧለት እንችላለን አይደል…?) ‘ቴንኪው’ ክቡር ፍርድ ቤት እቀጥላለሁ፤ እናልዎ ያስታውሱ እንደሆነ ውብሸት ታዬ መታሰሩን ስንሰማ “የኤሌክትሪክ እና መብራት ሃይሎችን ለማውደም ሲሉ በህብረተሰቡ ጥቆማ በቁጥጥር ስር ዋሉ!” ተብሎ ነበር የተዘገበልን።
እኛም ታድያ አምርረን “እነዚህ እርኩሶች…” ብለን ጥርሳችንን ነክሰንባቸው ስናበቃ እንዴት እንዴት ብለው የስልክ እና የኤሌክትሪክ ተቋምን ሊያፈርሱ እንደነበር መስማት አለብን በማለት በየቀጠሮው ሁሉ ከፍርድ ቤት አንቀርም ነበር። ላካስ አቃቤ ህጉ ዋናውን ክስ ረስቶት ኖሮ፤ ክሱ “በቃ” የሚል ፅሁፍ አደባባይ ላይ አስፅፋችኋል ፎቶግራፍ አንስታችኋል በኢሜልና ፌስ ቡክ መልዕክት ተለዋውጣችኋል” በሚል ተለውጦ ተገኘ።
በዚሁ የተበሳጩ አንዳንድ ተቆርቋሪዎች “በቃ” የሚለውን የለጠፋችሁት ቴሌ ዋናው መስሪያ ቤት በር ላይ እና ግልገል ግቤ ሃይል ማመንጫ ላይ ነው! ቢባል እንኳ መጀመሪያ የሰማነውን ክስ ይመስል ነበር። ሲሉ አጉረምርመው እንደነበር ይታወሳል። የሆኖ ሆኖ ፍርድ ቤቱ ምን ሲደረግ “በቃ” ትላላችሁ ብሎ በርካታ አመታት ሲደመር ደጎስ ያለ ብር ፈርዶባቸዋል። ይኸው ከዛ በኋላ እንኳንስ ሌላ ቀርቶ ማህበረሰቡ የሚበላውን ምግብ ሆነ የሚጠጣውን ውሃ ሲበቃው፤ “በቃኝ” ማለት ፈርቶ እጅ በማውለብለብ ወይም አንገት በመነቅነቅ ብቻ ሆኗል ሀሳቡን የሚገልፀው። አስተማሪ የሆነ ርምጃ ማለት ይሄ ነው። ይሄማ ርምጃ አይደለም ሩጫ ነው… ካሉኝም ይሆናል።
ውይ ወዳጄ እልም ብዬ ሌላ ወግ ውስጥ ገባሁ አይደል? አሁን ወደ ዋናው መስመር ተመልሻለሁ። ከወዳጆቼ ጋር ስናወጋ እነዚህ ከመካከለኛው ምስራቅ መጥተው መስጂድ ውስጥ የተገኙት ልባቸው የተደፈነ ጎረምረሶች ሲበትኑ የነበረው ወረቀት ምንነት ብናውቀው እና እነርሱም ላይ አስተማማኝ ርምጃ ቢወሰድ ለሁሉም ትምህርት ይሆን ነበር። የሚል አስተያየት ሰንዝሪያለሁ።
ይህንን አስተያየት ስሰጥ የሰማኝ አንድ ወዳጄ፤ “ርምጃው በአስተማሪነቱ እንኳ እንከን አይወጣለትም” አለኝ። ቀጠለናም፤ “አነዚህ ፈረንጆች ከሌላ ሀገር የመጡ ስለሆኑ በ24 ሰዓት ውስጥ ወደ ሀገራችሁ ተመለሱ ከተባሉ፤ እኛ ሀገራችን እዚሁ የሆነው፤ በተመሳሳይ መልኩ ወረቀት ስንበትን የተገኘን እንደሆነ መንግስታችን በ24 ሰዓት ውስጥ ወደ መጣንበት ሊመልሰን ነው ማለት ነው። ከዚህ የበለጠ አስተማሪ እርምጃ ከየት ይምጣልህ?” አለኝ። እኔም እኛ የመጣንበት የት ነው? ብለው በጣቱ ወደ ሰማይ እየተኮሰ “ከአላህ ዘንድ ነዋ!” አይለኝ መሰልዎ…
እንደዚህ ወዳጄ ንግግር መንግስታችን ባለፈው ግዜ አርሲ አሳሳ ውስጥ ወደ ሰባት የሚጠጉ ወጣቶች ላይ የወሰደባቸው ርምጃ ለዚህ ማሳያ ነው።
የምር ግን መንግስት በሆነ ባልሆነው እግዜሩ የሰጠን ቪዛ ሳያልቅ “ወደመጣችሁበት ተመለሱ” እያለ የሚያሰናብተን ከሆነ ከእግዜሩ ጋር ያለው ዲፕሎማሲ አይሻክርበትም ትላላችሁ? በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አፈ ቀላጤ አቶ ዲና ሙፍቲንን ብንጋብዝ “በአሁኑ ሰዓት ከተለያዩ ሀገሮች ጋር መልካም ግንኙነት አለን በተለይም ከቻይና… ስለዚህ ከእግዜሩ ጋር ያለን ግንኑነት አያሳስበንም!” ሊሉን እንደሚችሉ እንጠርጥር ወይስ አንጠርጥር…?
የኔ ነገር… አረ ወደ ዋናው ርዕሰ ጉዳይ መልሱኝ ወዳጄ… እኔ የምለው እነዛ በመስጊድ የተገኙ የመካከለኛው ምስራቅ ጎረምሶች ግን ወደ ሃገራቸው መመለሳቸውን እንደ አንድ የመንግስት ታማኝ አልደገፍኩትም ብዬ ጀምሪልዎ አይደል። ለምን በሉኝ…? ለምን ማለት ጥሩ ጥያቄ ነው…! ነገ ደግሞ “ዋልድባ ገዳም ወረቀት ሲበትኑ ተገኙ” ብለን ዜና ለመስራት ገና ሌላ ሰው ልናስመጣ ነው? እንደኔ አስተያየት ከሆነ በ ”ቢፒአር” ም እንተሰለጠንነው አንድን ስራ በጥቂት ሰዎች ማሰራት ውጤቱ አመርቂ ነው። በዛ ላይ ደግሞ ገና ሌላ ሰው ማሰልጠን እና መለማመጡም መካራ ነው። እናም እላለሁ መስጂድ የተገኙት እስካሁን ካልወጡ ለዋልድባ ገዳም ደግሞ ይቀመጡ!
ሰላም ነዎት ግን ወዳጄ ትላንት እኮ አልተገናኘንም… ሰላም ይግጠመን እስቲ!
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | No Comments »
Tuesday, May 8th, 2012
ባለፈው ግዜ ቼልሲ ከባርሴሎና ጋር ሲጫወት በሩን ጥርቅም አድርጎ በፓስዋርድ ነበር የዘጋው። ለምን ዘጋ ያልን እንደሆነ በርካታ ምክንያቶችን መደርደር እንችላለን። ከእኛ ይልቅ ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ኤርሚያስ የሆነ ነገር ብሎ እንደሆነ እንፈልግ እና እንመልከት። ምንም ካላለም ከቀጣዩ የዋንጫ ጨዋታ ጋር አያይዞ ዘርዘር ያለ አጥጋቢ ምክንያቶች እንደሚነግረን ተስፋ እናድርግ።
ትላንት አንድ ፈረንጅ ወዳጃችን፤ “ብሎጌ በተደጋጋሚ ተዘጋ ብዬ ዋይ ዋይ” ማለቴን ወሬ ሰምቶ ደውሎልኝ ነበር። እኔም ስለሁኔታው አስረዳሁት። “ብታምነም ባታምንም አስራ አንድ ግዜ ብሎጌ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ተዘግቷል፤ ከዛም አልፎ ተርፎ አንዳንድ አክቲቭ የሆኑ ልጆች ፌስ ቡክ አካውንት ሁሉ እየተዘጋባቸው ድጋሚ እየከፈቱ ነው።” ብዬ ማቃጠር፤ ከዛልዎ ፈረንጁ ወዳጃችን በእንግሊዘኛ ተገርሞ ተገርሞ ተገርሞ ሲያበቃ ለመሆኑ “መንግስት ለምንድነው በዚህ ግዜ እንዲህ የሚያደርገው? ምርጫ እንኳ ቢኖር ድምፅ እንዳያሳጡኝ ብሎ ነው ይባላል? አሁን ግን ምን ሆኖ ነው…?” አለኝ። ለዚህ መልስ የለኝም። ስለዚህ እኔ ራሴ ይህንን ጥያቄ ልጠይቅ… መንግስት እንደ ቼልሲ ዘግቶ መጫወት ለምን ፈለገ?
ወሬዬን ልቀጥል ነበር ሳስበው ሁልግዜ እኔ ብቻ ሳወራ “ያንተ ወሬ ብቻ አላልቅ አለ!” እንዳይሉኝ ሰጋሁና ለምን መድረኩን ለአንባቢ ወዳጆቻችን አልተወውም አልኩ “እርስዎም ይሞክሩት” ብንለውም ይሆናል። እንደሚያውቁት ወይም ደግሞ ማወቅ እንደሚገባዎ መንግስታችን የተለያዩ ዌብ ሳይቶችን ጥርቅም አድርጎ ዘግቷል። ለምን…? እባክዎን ወዳጄ ይሳተፉ… መንግስት ዘግቶ መጫወትን ለምን መረጠ…? እንደ “ሙዳችን” ፈቃድ መልስዎን ከፌስቡኩም ከብሎጉም ሰብሰብ አድርጌ ሌላ ጨዋታ ይወጣው ይሆናል።
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 6 Comments »
Monday, May 7th, 2012
ባለፈው ግዜ መንግስት ቅድመ ምርመራ ወይም የሳንሱርን ትንሳኤ ሊያመጣው እንደሆነ ፍንጭ አግኝተናል ብለን አንዳንድ ጩኸቶችን ጮኸን ነበር። በጩኸታችን ማግስት የአለም የፕሬስ ነፃነት ቀን በመላው አለም ተከበረ። ከመላው አለም አክባሪዎች ውስጥ “ወጉ ለምን ይቀራል” ብላ ኢትዮጵያም አንዷ ሆና ነበር።
በክብረ በዓሉ ላይ አቶ ሽመልስ ከማል ካልታሰሩ ጋዜጠኞች ጋር አንድ መድረክ ላይ ተገናኝተው ነበር አሉ። ታድያ አንድ ጥያቄ ተወነጨፈባቸው። “መንግስት ቅድመ ምርመራ ወይም ሳንሱርን ድጋሚ እያመጣው ነው፤ ይኸው “ብርሃንና ሰላም የምታሳትሙትን አይቼ ቀልቤ ካልወደደው እንቢ የማለት መብት አለኝ” የሚል ውል እያስፈረመን ይገኛል።” ብለው ነግረዋቸው ነበር። ታድያ አቶ ሽመልስ ምን አሉ?
“ይሄ የብርሃንና ሰላም ድርጅት ያወጣው ህገ ደንብ ነው እኛ በዚህ ላይ የለንበትም!” ብለው እርፍ! እኛስ ምን እንላቸዋለን…
አቶ ሽመልስ በመጀመሪያ እንኩ ሰላምታ፤ የት ጠፍተው ከረሙ…? እኔ የምልዎ… ከዚህ በፊትም እንዲህ የማይሆን ንግግር ሲናገሩ የሰሙ ወገኖች እና ወገኞች “አቶ ሼም የለሽ” ብለው ስም አውጥተውልዎ ነበር። ስሙ እንደተጠበቀ ይቆይ ካሉ ጥሩ፤ አለበለዛ ግን ይሄ ትልቅ የሆነ ህገ መንግስትን የመናድ ተግባር ነው። ታድያ እንዴት አፍዎን ሞልተው በዚህ ጉዳይ እኛ የለንበትም ይላሉ። በህገመንግሰቱ ጉዳይ ከሌላችሁበት በምን ጉዳይ ላይ ነው የምትኖሩት? የምሬን ነው የምልዎ ተሸወዱ! እኔ እርስዎን ብሆን ምን እንደማደርግ ያውቃሉ…? እርግጠኛ ነኝ አያውቁም። ስለዚህ እራሴው እነግርዎታለሁ።
መጀመሪያ ብርሃንና ሰላም አዘጋጀ ስለተባለው ውል ከጋዜጠኞቹ ስሰማ ምንም እንኳ ቀድሜ የሰማሁት ቢሆንም፤ አውቄ ድንግጥ እላለሁ። ድንግጥ ቢሉዎት ደግሞ ዝም ብሎ ድንግጥ ብቻ አይደለም። ክው! ከዛ ንግግሬን እቀጥላለሁ “ይሄ ስህተት ነው! ድርጅቱ ህገመንግስቱን እየናደ ስለሆነ አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰንበት ጉዳዩን ወደ ህግ እንወስደዋለን!” እላለሁ።
እውነቴን ነው የምልዎ አቶ ሽመልስ፤ እንኳንስ ሌላ ቀርቶ እነ እስክንድር ነጋን እና ስንቱን ምስኪን ሰው… “ህገ መንግስቱን ሊንዱ ሲሉ በህብረተሰቡ ትብብር ተያዙ!” ብለውን የለ እንዴ!? (በምን አቅማቸው ሊንዱት እንደሞከሩ ባይታወቅም) ታድያ ስለ ብርሃንና ሰላም ላይ ይህንን የመሰለ ጥቆማ ሲደርስዎ ከዚህ የበለጠ የህብረተሰብ ትብብር ከየት ይመጣል!? አረ “ሼ” ይኑር “ሼም” …ነውር እንወቅ… ስማችንንም እናድስ! እስከ መቼ ሼም የለሽ እንባላለን!?
ምናልባት ህገ መንግስቱን ረስተውት ከሆነ እንደሚከትለው አስታውሶታለሁ፤
“ሕገ መንግስቱ አንቀፅ 9 ላይ እንዲህ ይላል፤ “ሕገ መንግስቱ የሀገሪቱ የበላይ ህግ ነው። ማንኛውም ህግ፤ ልማዳዊ አሰራር፤ እንዲሁም የመንግስት አካል ወይም ባለስልጣን ውሳኔ ከዚህ ህገመንግስት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት አይኖረውም።” ይላል። ይህ ደግሞ ብርሃንና ሰላምንም ጨምሮ ነው። አረ ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ይጨምራል። ሄደው ሄደው ሄደው አንቀፅ 29 ላይ ሲደርሱ ደግሞ ስለ ፕሬስ ነፃነት ያወራ እና “ሀ” ላይ ገና በመጀመሪያው ማለት ነው “የቅድመ ምርመራ በማነኛውም መልኩ የተከለከለ መሆኑን…” ይደነግጋል።
ታድያ ብርሃንና ሰላም “የሚታተመውን ፅሁፍ አይቼ ውቃቤዬ ካልወደደው አላትምም” የሚለው በምን ህግ ነው? ይህ ህገ መንግስቱን መናድ አይደለምን?
አቶ ሽመልስ ከሰሙኝም ካልሰሙኝም እንኩ ሰላምታ… ! (በምን ልምታህ እንዳይሉኝ ብቻ!) እንኩ ወቀሳም! ወቀሳው ግን ከመብዛቱ የተነሳ ለልጅ ልጅ ሁሉ የሚያወርሱት ሆኖሎታል አሉ! (አሉ ነው)
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 3 Comments »
Sunday, May 6th, 2012
ውድ የፍትህ ጋዜጣ አንባቢ ወዳጆቼ እንዴት አላችሁልኝ? “እኔስ አለሁ አለሁ አለሁ እንደምንም እግዜር ያመጣውን ሰው አልችል አይልም” የሚል ዘፈን የሚዘፍንልን ሁነኛ ሞዛቂ አጣን አይደል…? ለማንኛወም አንተ እንዴት ነህ ብለው የጠየቁኝ እንደሆነ እኔው ራሴ አዜማታለሁ!
ይህ ደብዳቤ ለቀዳማዊት አዜብ መስፍን በታላቅ ትህትና እና አክብሮት የተፃፈ ነው። ከሁሉም በላይ ግን ለቤተመንስግስቱ ቤተሰቦች ያነኝን የላቀ ፍቅር እና አክብሮት እንዲሁም ታማኝነት የሚያሳብቅ በመሆኑ ይህንን ሀሳብ የምትቃወሙ ወዳጆችን ከወዲሁ ይቅርታ መጠየቅ ተገቢ ነው።
ጀመርኩ፤
ክብርት ወ/ሮ አዜብ መስፍን እንዴት ሰነባበቱልኝ? ባለፈው ግዜ ይድረስዎ አይድረስዎ እንጃ አንድ መልዕክት ሰድጄልዎ ነበር። እርግጥ ነው ደብዳቤዬን በዌብ ሳይቶች ላይ እንዲታተም አደረግሁ እንጂ በአድራሻዎ አላኩልዎም። ታድያ እነዚህ ድረ ገፆች ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ ክልከላ የተደረገባቸው በመሆናቸው፤ ምናልባት ለገበያ፣ ወይም ቤተሰብ ጥየቃ፣ ወይም ደግሞ አንዱን ቅዳሜና እሁድ ንፋስ ለመቀበል ዱባይ ወይ ቻይና ወይም እንግሊዝና አሜሪካ ብቅ ካላሉ በስተቀር አራት ኪሎ ቁጭ ብለው በድረ ገፅ የታተመ ደብዳቤዬ ላይደርሶት ይችል ይሆናል ብዬ እሰጋለሁ።
አሁን አሁንማ ያው እንደሚያውቁት “ኢንሳ” የተባለው ዌብሳይቶችን በመዝጋት የሚተዳደረው ዘጊ መስሪያቤት እንኳንስ የተጠናከሩ ዌብ ሳይቶችን ይቅርና እንደኔ ያለን ምስኪኖች ወግ ይድረሰን እና ወግ እናወጋ ብለን የከፈትናቸውን ሚጢጢ ብሎጎች ሁሉ እየዘጋ ከምንወደውና ከሚወደን መንግስታችንም ሆነ ህዝባችን የማለያየት ስራ እየተሰራብን ይገኛል።
የምሬን ነው የምልዎ ይሄ ክፋት ነው። ለምን ከመንግስታቸው ጋር ተግባቡ… ለምን ደብዳቤ ተላላኩ ለምን ተስማሙ የሚል ምቀኝነት። እኔ በበኩሌ ዘወትር እርስዎን እና ጠቅላይ ሚኒስትሬን ጨምሮ መላው የኢህአዴግ አባላት በስራ የዛለ አዕምሯችሁን ዘና ለማድረግ እንደተጋሁ ነው። (እዝች ጋ ታይፕ አልገደፍኩም አይደል…? እባክዎ ይቺ የታይፕ ግድፈት ከብዙ ሰው አያቀያየመችኝ ነው። በተለይ ስራ እኔ ሴራ እየተመሳሰሉብኝ ስቸገር ባዩኝ…! የኛ ሰው ደግሞ ቶሎ ነው የሚከፋው። …አይ አሁን ግን ልክ ነኝ። ሴራ አላልኩም ስራ ነው ያልኩት።) እናልዎ በስራ የዛለ አዕምሯችሁን ትንሽ ዘና እንዲል የማላደርገው ጥረት የለም።
ታድያ ይገርምዎታል የእኔ ብሎግ እንኳ ሳይቀር ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገበ ተከልክልዎሎታል። እኔማ የለም ተሳስተው ነው የእኔ ባይመስላቸው ነው… ብዬ ድጋሚ ስከፍት፤ አሁንም ሲዘጉት፣ አሁንም ስሞክር፤ አሁንም ሲዘጉት ቢያምኑኝም ባያምኑኝም አስራ አንድ ግዜ ተዘግቶብኛል። ከዚህ በላይ ከሄድኩኝ ከሀገሪቱ የእድገት ቁጥር ጋር መፎካከር ነው ብዬ ለግዜው ብሎግ ከፈታውን ተወት አድርጌዋለሁ።
እሜትዬ እኛ ኢቲቪ የፈለገውን ሲያቀርብ “ብሎክ” ማድረጊያ ሪሞቱ አጠገባችን እያለ ይሁን ለኛው ብሎ ነው በሚል ቅን አመለካከት ያሻውን ቢናገር ያሻውን ቢያወራ ዝም ብለን እንሰማለን እንጂ አንዘጋውም። በርግጥ ብዙ ግዜ የቴሌቪዥናችን ፕሮግራሞች እርሾ ይበዛባቸዋል መሰለኝ ሆድ ይነፋሉ። ቢሆንም ግን ተመልክተን ከጨረስን በኋላ ቀንዶ ወይም እናትና ልጅ አረቄ ጠጥተን እንበትነዋለን እንጂ ፕሮግራሙን “ብሎክ” አድርገን ወይም አቋርጠነው አናውቅም።
ውይ ኢቲቪን ሳነሳ ምን ትዝ አለኝ መሰልዎ አንዱ ፀሀፊ በቅርቡ በእናንተ ላይ የፃፈውን አይቼ እንዴት እንዴት ስበሳጭ እንደነበር ቢመለከቱኝ፤ ምን ያህል ተቆርቋሪዎ እና ወዳጅዎ እንደሆንኩ ይረዱልኝ ነበር። በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ገበና እና ሰው ለሰው ድራማ መቼም ሳይከታተሉት አይቀሩም…! እናልዎ በዛ ላይ ያሉ እኩይ ገፀ ባህሪ ሆነው፤ ነገር ግን ሁሌ ሲሳካላቸው የሚታዩ ሰዎች አሉ። የሰው ለሰዉ አስናቀ እና የገመናዋ ለምለም። ታድያ ይህ ያበሳጨኝ ክፉ ፀሀፊ አቶ አስናቀን ከአቶ መለስ ጋር ወ/ሮ ለምለምን ደግሞ ከእርስዎ ጋር አመሳስሎ አላየሁትም መሰልዎ…!? በእውነቱ በብስጭት ደሜ ከዋጋ ግሽበቱ በላይ ነው የጨመረው።
ታድያ ከላይ እንዳልክዎ በየ ድረገፁ የምንለጥፈው ፅሁፍ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ሲከለከል ለእርስዎ እና ለጠቅላይ ሚኒስትሬም የምልከው መልዕክት ሳይደርስ ይቀራል ብዬ እሰጋለሁ። ወይስ ቤተ መንግስቱ ከኢትዮጵያ ውጪ ነው የሚገኘው…? አንዳንድ አሽሟጣጮች እንደሚሉት ከሆነ አገሪቷ ላይ የሚመጣ ችግር አንድም ግዜ ጎብኝቶት ስለማያውቅ ቤተመንግስቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ለማለት አያስደፍርም ይላሉ።
ለምስሌ “የገበያ ዋጋ መናር ለቤተመንስግስት ሰዎች ምናቸውም አይደለም ምክንያቱም ገበያቸው ዱባይ እና ቻይና ነው” እያለ ሰዉ ያልተጠየቀውን ሲያወራ ቢሰሙት ይደነቃሉ። ይቺ ይቺ እርስዎን ለመንካት ነው። እኔ ግን እከራከርልዎታለሁ። ለራስዎ “በአለም ላይ ደሃ ከሚባሉ መሪዎች መካከል አይደሉ እንዴ?” አረ ይልቁንስ ሰሞኑን የሰማሁትን ሳልነግርዎ… እኚያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደቡብ አፍሪካ የሄዱ ግዜልዎ… ወደ አስር ሺህ ዶላር አውጥተው ጌጣጌጥ ሲገዙ ነበር አሉ። ይሄ ነገር ግን ለድርጅታችን ስም ጥሩ ነው ይላሉ? ለአባይ መዋጮ ሰዉን በምናስጨንቅበት በዚህ ግዜ ባለስልጣኖቻችን ይህንን ያህል ወጪ ሲያወጡ መልካም ነው…? በእውነቱ ጥሩ አይመስለኝም። በርግጥ እኔ በበኩሌ ይሄንን የሰማሁ ግዜ ድሮ ድሮ በእንዲህ ያለው ነገር የሚጠረጠሩት እርስዎ ስለነበሩ ጎሽ ትንሽ ከሳቸው ራስ ላይ ገለል ይላሉ ብዬ ውስጥ ውስጡን ደስ ብሎኝ ነበር።
ምን ዋጋ አለው በነጋታው ሌላ ወሬ መጥቶ የእርስዎን ስምም አደባባይ አገኘሁት። በርግጥ እንደተለመደው ስምዎ ሲነሳ የሰማሁት ከቅንጦት ገበያ ጋር ተያይዞ ባለመሆኑ ተደስቻለሁ ቢሆንም ግን… በአደባባይ ስምዎ ሲነሳ ቅር ይለኛል። ምን መሰልዎ…? ያ ጎረምሳ ልጅዎ፤ ነፍሱን ይማረውና ከቀድሞው የደህንነት ሹም አቶ ክንፈ የሚወለደው… እ! እሱልዎ በየ ጋዜጣውና መፅሔቱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ይዝታል አሉ። አረ እንደው ሌላ ሰው አይስማን እንጂ እንደርሱ አባባልማ ለአባቱ ሞት ሁሉ ተጠያቂ የሚያደርገው ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ነው። እኔማ በየድረ ገፁ ላይ ይህንን ባየሁ ግዜ በእውነቱ ይሄ ጉርምስና ነው…! ብዬ ወቀስኩት። በምን አነሳሁት እቴ…
የኔ ነገር አንድ ግዜ ጨዋታ ከጀመርኩ እና እህ… ብለው ከሰሙኝ መቼም ማብቂያም የለኝ፤ ወደ ዋናው ቁም ነገሬ ስመጣ ያንን ነገር እንዴት አደረጉልኝ ወ/ሮ አዜብ? ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንዲመክሩልን ጠይቄዎት ነበር። ባለፈው ግዜ እንዳልኩዎ በእርስዎ ያምራል። እኛ ያሻንን ያህል ብንለፋ እርስዎ በሚስት ብልሀት የሚመክሩትን ያህል አይሆንልንምና ባለቤትዎን በዘዴ በዘዴ ይምከሩልን! ብዬዎት ነበር።
እውነቴን ነው የምልዎ ወ/ሮዬ እኛ ከአንጀታችን በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍቅር የወደቅነውን ያህል ብዙ ሰዎች ደግሞ ከልባቸው እየተቀየሟቸው ነው። ይህንን በስንትና ስንት ስለላ ያገኘሁት መረጃ መሰልዎ…! ባለፈው እንዳልኩዎ የሰዉም ሁናቴ የሳቸውም ምላሽ በዚሁ ከቀጠለ ወደፊት እንኳንስ ህዝቡ እና የገዛ ጉርሻቸው እሺ ብሎ አልጠቀለል የሚላቸው ግዜ ሊመጣ ይችላልና ከአሁኑ ተመካክረን አንዳች ዘዴ እንዘይድ በሚል ነው ይህንን ደብዳቤ መፃፌ!
ይኸውልዎ ወይዘሮ አዜብ ህዝብ ሲከፋው፤ ህዝብ ሲበሳጭ ምን ሊያደረግ እንደሚችል ጠቅላይ ሚኒስትራችንም ጠንቅቀው ያውቁታል። እና ሳስበው ከእርስዎ ብዙ የሚጠበቅብዎ አይመስለኝም። እርሱን ብቻ ያስታውሷቸው እርሳቸው አንድም ስራ ስለሚበዛባቸው አንድም በሌላ ሌላ ምክንያት ሊረሱት ይችላሉ።
ቀዳማዊት እመቤት ሆይ መፅሐፍ ቅዱስ ላይ መፅሐፈ አስቴር በሚለው ምዕራፍ ውስጥ የአስቴርን ታሪክ አንብበውታል? “ምን ይሄ የቤተመንግስት ጣጣ እኮ ለእንዲህ ያለ መንፈሳዊ ምንባብ ግዜ አይሰጥም” ብለው እንደሚያጉረመርሙ በጠረጠርኩ። አይዞት እኔ እያለሁ ሀሳብ አይግባዎት ትንሽ ቀንጭቤ ከታሪኩ እንደሚከተለው እነግርዎታለሁ፤
በዛን ወቅት አርጤኬስ የሚባል ንጉስ በአስቴር ፍቅር ወደቀና ንግስት አደረጋት። እሷም በዛ እየኖረች ሳለ አሳዳጊዋ መርደኪዮስም ሆነ አጠቃላይ ህዝቧ እና ወገኗ ለታላቅ መከራ ተዳረጉ። ሐማ በተባለ የንጉሱ ሰው (ልክ በአሁኑ ግዜ እኛ ስራ አስፈፃሚ አካላት እንደምንላቸው ሹማምንት መሆኑ ነው) ህዝቡን ክፉኛ ስጋት ላይ ጣለው። እንደ እቅዱና አሳቡ አባቷን መርደኪዮስን ጨምሮ ህዝቡን በሙሉ ማጥፋት ነበር። በዚህ ግዜም ህዝቡ “አስቴር ወገናችን አንቺ በቤተመንግስቱ ውስጥ ነሽና እባክሽ ለምኝልን! ሊያጠፉን ቆርጠው ተነስተዋል…!” ሲሉ ወተወቷት። አባቷ መርደኪዮስም የሚመጣባቸውን መከራ በማሰብ የተነሳ ማቅ ለብሶ ሰነበተ።
የዛኔ አስቴር በንጉሱ ዘንድ ያላት አቅም እርስዎ ዛሬ በአቶ መለስ ላይ ያልዎትን አያክልም ነበር። እንደ ልቧም ገባ ወጣ እያለች “ያንን ነገር እንዴት አደረግኸው?” ብላ መጠየቅ አትችልም። በዚህም የተነሳ ለንጉሱ “በህዝቤ ላይ የተጫነውን መከራ አንሳልኝ” ብላ ጥያቄ ከማቅረቧ በፊት ለድፍረቱም ለስኬቱም እንዲሆን ህዝቡ ሶስት ቀን ሶስት ለሌት እንዲፆም አዘዘች። እርሷም ፆም እና ፀሎት አደረገች። ከዛም ለንጉሱ እራት ግብዣ ካደረገችለት በኋላ፤ “ወገኖቼ በአንተ ትዕዛዝና በአስፈፃሚህ ሐማ የተነሳ ሊያልቁ ነው እባክህን ይህንን አታድርግ አለችው።” ይገርምዎታል ወድያውኑ ልመናዋን ሰማት።
ወ/ሮ አዜብ ህዝብዎ ላይ መከራ ተጭኗል። አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ በታላቅ አበሳ ውስጥ ነው። ከዛም ወረድ ብለን ይበልጥ ወደ እርስዎ ህዝብ ጠጋ እንበል ካልን የወልቃይት ጠገዴ ሰው መከራውን እያየ ነው። የመላው ትግራይ ህዝብ አበሳውን እየቆጠረ ነው። አማራው ጉራጌው ኦሮሞው ከንባታው ሃድያው እውነት እውነት እልዎታለሁ አንድም የደላው ሰው የለም። ድሎቱም ምቾቱም ያለው እዛችው አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ውስጥ ብቻ ነው።
በኑሮ ውድነት የሚጠበሰው አንሶ ለተለያዩ ልማታዊ መዋጮዎች በየቀኑ ገንዘብ አምጣ እየተባለ ነው። መሬቱ እየተወሰደ፣ እምነቱ እየተሸረሸረ፣ ቤተ አምልኮው እየፈረሰ ያለው ህዝብ የእርሶው ህዝብ ነው። እናም እንደ አስቴር ከንጉሱ ዘንድ የተጫነብን እንዲነሳልን ለምኑልን ብለን አብዝተን እንጮሀለን። አይዞት ሶስት ቀን ሶስት ሌት ፁሙ ማለት አይጠበቅብዎትም እኛ ቀድሞውንም እየፆምን ነውና ሃሳብ አይግባዎ…!
ባለፈውም ግዜም ያልኩዎት ይህንኑ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዝቡ ሰላማዊ ሰልፍ በላይ ከህዝቡ ኡኡታ በላይ የእርስዎን ምክር እና ልመና ተግባራዊ እንደሚያደርጉ አምናለሁ። እናም እባክዎ ለእርስዎ ጠቅላይ ባለቤት ለእኛ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት አቶ መለስ በህዝቡ ላይ የጫኑትን መከራ ያነሱ ዘንድ ይምከሩልን ይለምኑልን!
ከዚህ ሁሉ ጭቅጭቅ ብላችሁ ሁለታችሁም ዘወር ብትሉልንማ የመከራዎች ሁሉ መከራ ቀለለ ማለት ነበር።
ብቻ ቀዳማዊ እመቤት ይምከሩ እና እንደሚሆን ያድርጉ እባክዎን ጉዳዬን ችላ አይበሉብኝ። ኋላ ጥሩ ላይመጣ ይችላል።
አክባሪዎ…!
ወዳጄ እስቲ ቸር ያሰማን!
አማን ያሰንብተን!
Filed under: Uncategorized

Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 2 Comments »
Friday, May 4th, 2012
በፍትህ ጋዜጣ አምደኛ ሆና በምትሰራበት ወቅት “አሸበርሽ” ተብላ የታሰረችው ርዮት አለሙ “ኢንተርናሽናል ውመን ሚዲያ ፋውንዴሽን” የተባለ ድርጅት የሚዲያ ጀግና ሲል ለሽልማት መረጣት።
ሽልማቱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ራስን ለአደጋ አጋልጦ በጋዜጠኝነታቸው ለተጉ ሴቶች የሚሰጥ ሲሆን፤ ከርዮት አለሙ ጋር አንዲት የፓልስቲን እና አንዲት የአዠርባዣን ጋዜጠኞች ለሽልማቱ ተመርጠዋል።
እንደሚታወቀው ርዮት አለሙ በአሁኑ ግዜ የገንዘብና የእስር ቅጣት ተወስኖባት በቃሊቲ እስር ቤት የምትገኝ ሲሆን “አሸባሪ” ተብላ በተከሰሰች ግዜ ለማስረጃነት ከቀረቡባት መካከል የፎቶ ካሜራ እና በፍትህ ጋዜጣ ላይ ያሳተመቻቸው ፅሁፎች እና በፌስ ቡክ በኩል ሰዎች “ታግ” ያደረጓት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የሚያላግጡ ምስሎች ይገኙበታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስክንድር ነጋን ሽልማት ባለቤቱ ሰርካለም ፋሲል አሜሪካ ሄዳ መቀበሏ ተሰምቷል። (እየተከታተላችሁ ያላችሁት… ልላችሁ እኮ ምንም አልቀረኝም…!)
ጥርጣሬ
መንግስታችን “አሸባሪ” ያላቸውን በሙሉ በተለይ በአሜሪካ የሚገኙ አለም አቀፍ ድርጅቶች ጀግና እያሉ እየሸለሙ ይገኛሉ። አሁን አንዳች ነገር ጠረጠርኩ። በዚህ ብስጭት መንግስት አሜሪካ አሸባሪ ብላ የገደለችውን ቢላደንን እዛው ያለበት ድረስ ሄጄ የጀግና ሽልማት ልስጠው እንዳይል እየሰጋሁ ነው። እልህ ጩቤ ያስውጣል አይደል የሚባለው!
በመጨረሻም
ርዮት አለሙ እና ወዳጅ ዘመዶቿ እንዲሁም የሙያ አጋሮቿን በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ!
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 1 Comment »
Thursday, May 3rd, 2012
ከዚህ በፊት ሳይገባኝ “ሪፖርተር” የሚል ማዕረግ ሰጥታኝ የነበረ አንድ ጋዜጣ ነበረች። “ሆመር” ትባላለች። እንዴት በፍቅር ምንወዳት ጋዜጣ ነበረች መሰላችሁ። በአሁኑ ወቅት እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ጋዜጣ ወግ ደርሷት “ነብስ ይማር” ለመባል በቅታለች። በዚሁ አጋጣሚ ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ የፕሬስ ቀን እየተከበረ ነው አሉ ስላቅ በየፈርጁ ማለት ይሄኔ ነው! ግን እንኳን አደረሰን ማለት ይገባል።
በዛች ጋዜጣ ላይ የሚወጣ “ዶሮዋ መንገዱን አቋረጠች” የሚል አንድ አምድ ነበረን። በነገራችን ላይ በዚህ “ዶሮዋ መንገዱን አቋረጠች” ጨዋታ ከባለቤቷ ሆመር ጋዜጣ ይልቅ የነ ብርሃኔ ንጉሴ ኢንፎኢቴመንት ታዋቂ ሆናበታለች።
የሆነው ሆኖ በተለይ ዶሮዋ መንገዱን ስታቋርጥ የተለያዩ መሪዎቻችን የተናገሩትእውቅና ያገኘ ጨዋታ ነበር።
አሁን በቅርቡ በዋልድባ ገዳም የሚገነባው ስኳር ፋብሪካ ሂደቱን ክፉ እንዳያጋጥመው መንግስት ከመደባቸው ፌደራል ፖሊሶች ውስጥ አራቱን ጅብ በልቷቸው ነበር። ይህ አስደንጋጭ ዜና ነው። ልብ ላለው መንግስት ጥሩ ትምህርት የሚሰጥም ነው። አፍሮ ሬድዬ በሚል የፌስቡክ አድራሻ አንድ ወዳጃችን ኢቲቪ ይህንን ዘገባ እንዴት ሊያቀርበው እንደሚችል አስነብቦናል። ታድያ እኔም ከሆመር ጋዜጣ ትዝታ እና ከአፍሮ ራድዮ ጨዋታ በመነሳት ለዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ሁኔታ በተለያየ ግዜ እንዴት እንደሚያወጉን እንደሚከተለው እገምታለሁ… (ጨዋታ ነው እሺ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር)
ከድርቅ ጋር ተያይዞ
እ… የተከበሩት የህዝብ ተወካይ ልብ ያላሉት አንድ ነገር ያለ ይመስለኛል። በጣት የሚቆጠሩ ጥቂት ጅቦች የሚበላ ነገር አጣን በሚል የሀገሪቱን መልካም ገፅታ ለማጠልሸት፤ ፖሊሶችን መብላታቸው በአካባቢው የምግብ እጥረት ያለ ለማስመሰል እንጂ፤ ከዚህ የዘለለ አላማ አለው ብዬ አላምንም። ይህንን የተከበሩ የፓርላማ አባሉም ሳያውቁት አይቀርም ። አበዛኛዎቹን ጅቦች ሀገሩ ተርቧል ድርቅ ገብቷል ብሎ ለማጯጯህ ሲሉ የመድረክ አመራር አባላት በርቱ እና ምግብ ትታችሁ የፖሊስ አባላትን ተመገቡ እንደሚባሏቸው፣ እንዲሁም የውጪ ሀገር ጋዜጠኛ እቦታው ድረስ እየወሰዱ ይኸው ጅቡ የሚመገበው አጥቶ ፖሊስ እየበላ ነው እያሉ እንደሚያለቃቅሱ እናውቃለን!
ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ተያይዞ
የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገትን አስመልክቶ እያደግን ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ጥያቄው አሁን የቁጥር ጉዳይ ነው። አሁን ግን አንድ ጅብ አራት ፖሊሶችን ተመግቧል። ዕቅዳችንን ስናቅድ አንድ ጅብ ቢያንስ ሶስት ፖሊስ ከበላ ይበቃናል ብለን ነበር። አሁን ግን አ…ራ…ት ፖሊስ ተመግቧል። ይሄ ከዕቅዳችን አንፃር ስናየው ከበቂ በላይ ነው።
ስለዚህ ሁሉም፤ ተቃዋሚውም ጭምር የኢኮኖሚ እድገቱ አልዋጥ ቢላቸውም ለመቀበል እየተገደዱ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው። ይሄ በየትኛውም ሀገር ታይቶ የማይታወቅ የእድገት ማሳያ ነው። ቻይና በአሁኑ ግዜ ለምዕራባዊያኑ ሁሉ ስጋት እስክትሆን ድረስ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች እንደሆነ ይታወቃል። በቻይና አንድ ጅብ አንድ ፖሊስ እንኳ በልቶ አያውቅም። በህንድም ተመሳሳይ ነው። የእኛ ጅቦች ግን በአንድ ጀምበር አራት ፖሊሶችን መብላት እንደሚቻል አሳይተዋል። ከዚህ የበለጠ የእድገት ማስረጃ ከየት እንደምናመጣ አይገባኝም።
ከሙስና ጋር በተያያዘ
በአሁኑ ሰዓት በአገሪቱ ትልቁ ችግር የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ነው። በዋልድባ ጫካ ብትሄዱ ጅቦቹ እንደ እንዝርት እየሾሩ… ይሄ እናቶቻችን የሚፈትሉበት እንዝርት ልክ እንደሱ…እየሾሩ በተለያየ ስልት እና ፊሊክሴብሊቲ በሆነ መልኩ አራት ፖሊሶችን በልተዋል። እሺ ፖሊሶቹ ይበሉ። ነገር ግን እነዚህ ጅቦች ለመንግስት ታክስ ከፍለዋል ወይ? ብለን የጠየቅን እንደሆነ መንግስት ካዝና የገባ አንድም ፖሊስ የለም። ይሄ ነው አሁን የቸገረን ነገር። ይሄ ከመሰረቱ ልናጠፋው የሚገባ የሙስና ችግር ነው። አሁን ያለን ምርጫ አንድ እና አንድ ነው። ወይ ጅቦቹ ፖሊሳቸውን እንደፈለጉ እየበሉ ይኖራሉ፤ ወይም ደግሞ አንድ ፖሊስ በበሉ ቁጥር ሌላ ፖሊስ መንግስት ካዝና የሚያስገቡበት ስርዓት ይዘረጋል። አራት ነጥብ!
ከአሸባሪነት ጋር በተያያዘ
በዋልድባ ገዳም አካባቢ ጅቦች የፈፀሙት ተግባር ሰሞኑን ተከታትለናል። ይሄ የአሸባሪነት ህጋችን በግልፅ አስቀምጦታል። እልም ያለ የሽብር ተግባር ስለመሆኑ ምንም አያከራክርም። ጥያቄው ከእነዚህ ጅቦች ጀርባ ማን አለ? የሚለው ጥያቄ ነው። ይህንን በተመለከት የቀለም አብዮት ማካሄድ የሚፈልጉ ሀይሎች፣ አክራሪ የሀይማኖት ሰዎች፣ ግንቦት ሰባቱ፣ ኦነጉ፣ ኦብነጉ፣ ሻቢያው እና የውስጥ አርበኛው ሁሉ ድጋፍ እና አይዞህ ባይነት እንዳለበት እናውቃለን።
በየሰዓቱ ለጅቦቹ ከተለያየ አገራት ስልክ እየተደወለ፤ “አስከ አሁን አራት ፖሊስ ብቻ ነው እንዴ የበላችሁት በርቱ እነጂ በቀደመው ግዜ የነበሩ ጅቦች እኮ ይሄን ስንት ፖሊስ በልተው ነበር…” እያሉ እንደሚወተውቷቸው እናውቃለን። በዚህ አጋጣሚ ለመድረክ አመራር አካላት ማሳወቅ የምፈልገው ነገር ከጅቦቹ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ባይኖራችሁም ውስጥ ውስጡን እንደምትገናኙ እናውቃለን። በሽብርተኝነት አዋጁ ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው ከጅቦቹ ጋር ወዳጅነት የመሰረተ ከአንድ ቀን በላይ ሻይ ቡና ያለ ሁሉ እንደሽብርተኛ እንደሚቆጠር ትረዱታላችሁ የሚል ግምት አለን። እንደውም በዚሁ ፓርላማ ውስጥ ከአጠገባችን ቁጭ ብለው ከጅቦቹ ጋር ግንኙነት ያለው እንዳለም እናውቃለን። ነገር ግን ማስረጃ የለንም!
የጨዋታው አሳብ አመንጪ አፍሮ ሬድዮን እና እናት ሆመር ጋዜጣን አመሰግናለሁ!
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 3 Comments »
Wednesday, May 2nd, 2012
ይህንን ጨዋታ ስፅፍ ፋሲል ደሞዜ የተባለ አቀንቃኝ “አለ ነገር…” እያለ የሚያንጎራጉረውን ሙዚቃ እየሰማሁ ነው! ልብ አድርጉልኝ ይህ ስጋት ነው እንጂ ቅስቀሳ አይደለም! ምክር ነው እንጂ ቁጣም አይደለም! አክብራቹሁ ብሎጋችንን የምትዘጉ ሰዎች ምክራችንንም ስሙ…!
አስቲ ሰሞኑን የሰማኋቸውን አጫጭር ዜናዎች ልንገራችሁ።
አንድ
በአርሲ ዞን አሳሳ ከተማ “መንግስት በሀይማኖታችን ጣልቃ አይግባብን” ያሉ ሙስሊሞች ከመንግስት ታጣቂ ሃይሎች በተከፈተባቸው ተኩስ አምስት ሰዎች ተገደለው በርካቶች ቆስለዋል። መንግስትም “አስር ፖሊሶቼ ተጎድተውብኛል ብሏል።” ይህ እንግዲህ የመርካቶው አንዋር መስጊድ እንቅስቃሴ አካል ነው። ይህንን መንግስት በሰላም እንዲፈታ ሁላችንም መክረናል ለምነናል ሰሚ ግን አላገኘንም እናም፤ መርካቶ አለ ነገር አትሉልኝም!
ሁለት
ጋምቤላ ከመሬታቸው የተፈናቀሉ የህብረተሰቡ አካላት በሼኩ እና በፓኪስታኖቹ የሩዝ አምራቾች ላይ እያሰሙ ያሉት ተቃውሞ ከእለት እለት እየተባባሰ፤ ወደ ተቀናጀ ጥቃት ተለውጦ አሁን በቅርቡ በሩዝ እርሻው ላይ ሲሰሩ የነበሩ የውጪ ዜጎች እና ኢትዮጵያውያን ላይ እስከ ሞት የደረሰ ጉዳት አድርሰውባቸዋል። ይህንንም አቤት እያሉ ሲጮሁ የነበሩ ብዙ ናቸው ግን ማን ይስማ…? በዚህም የተነሳ ጋምቤላ አለ ነገር! ያስብላል።
ሶስት
የዋልድባ ገዳምን ህልውና በሚፈታተን መልኩ የስኳር ምርት ሊያመርት መንግስት ደፋ ቀና እያለ ነው። የገዳሙ ሰዎችም “ተዉ ስለ እግዚአብሄር ብላችሁ አትንኩን” ብለው ቢለምኑ ቢማፀኑ የሚሰማ አላገኙም። መንግስት ነብሴ በቴሌቪዥኑ “ዋልድባ ሳይነኩት ጮኸ” አይነት ይዘት ያለው ዘገባ አሰራ! ቄሱም ዲያቆኑም መከረ ዘከረ “መንግስት ሆይ እባክህን ነገርህን በልኩ አድርገው!” አሉ። ነገር ግን አልሰማም። ልክ በአሁኑ ሰዓት የጎንደር ህዝብ ነብስ ወከፍ መሳሪያውን ይዞ በአስፈሪ ሁኔታ ወደ ዋልድባ ገዳም እየተመመ እንደሆነ ሰማን… ጎንደር አለ ነገር ማለት ይሄኔ ነው!
“ሶስት በአንድ” ይሄ እነ “ማዘር ቤት” የመሳሰሉ ምግብ ቤቶች ገብተን ምግብ የምናዝበት ቋንቋ ነው። ብዙ ግዜ እንደዚህ የምናዘው ለአራት ሆነን ነበር። አሁን ግን መንግስታችን ብቻውን ሆኖ ሶስት በአንድ አዟል። ደሞ ሌሎች ተከታዮችም አያጣም…!
ታድያልዎ ምን አስጨነቀኝ መሰልዎ… መንግስት ምን ያህል ቢርበው ነው ሶስት በአንድ ያዘዘው? የሚለው ጥያቄ ያሳስበኛል። በአዲስ መስመር እንደተለመደው መንግስቴን እመክራለሁ…
አረ ተዉ ግድ የላችሁም…! አንድ ግዜ ሰዉ ምን እያለ እንደሆነ ቆም ብላችሁ አዳምጡ! እየተጠየቁ ያለሉት እጅግ በጣም ቀላል ቀላል ጥያቄዎች ናቸው። ነገር ግን እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ከከበደን የምንከፍለው ዋጋ ይወደድብናል! እባካችሁ!!! ሶስት ለአንድ አያልቅም ትዕዛዝም ልክ አለው! ተዉ…!

Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 12 Comments »
Wednesday, May 2nd, 2012
እኔ የምለው ወዳጄ ሳሱር ነብሴ ድጋሚ መጣች አይደል እንዴ!? እሰይ! እልል በሉ እንጂ። ድግስ አትደግሱም እንዴ!? ጠላው ይጠመቅ፣ ድፎው ይደፋ፣ ቡናውም ይፈላ፣ ፈንዲሻው ይፈንደሽ፣ እጣን ሰንደሉ ተጫጭሶ ቄጤማውም ይጎዝጎዝ። በዓሉ የትንሳኤ በዓል ነውና ሁሉም ሰው ይደሰት።
አዎ አሁን ወቅቱ የትንሳኤ ነው። ሞቱ ተቀበሩ ያልናቸው ችግሮቻችን በሙሉ በስንተኛው ቀን እየተነሱ ዳግም ህያው እየሆኑ ነው። ይህ እንዲሆን ያደረገው እርሱ ኢህአዴግ ተዓምረኛ ነው። ያደረገውም ተዘርዘሮ አያልቅም።
መቼም ትዝ ይልዎታል… የዛሬ ሃያ አመት ኢህአዴግ አዲሳባን ሲቆጣጥር መጀመሪያ ይፋ ያደረገው ነገር፤ እናንት ነፃ ህዝቦች ሆይ ከእንግዲህ ያለ አንዳች ገደብ እንዳሻችሁ መናገር፣ እንደፈቀዳቸሁ መፃፍ፣ ደስ እንዳላችሁ መሞዘቅ ትችላላችሁ። ብሎ ነበር።
እኛም የዛኔ በልጅነት ጀብደኝነት ተነሳስተን “እውነት ዴሞክራሲ አለ?” የሚለውን ለመፈተን ወደ ትምህርት ቤት ስንሄድ እና ስንመጣ በየመንገዱ፤ እንዲሁም በትምህርት ቤታችን ቅጥር ግቢ ድምፃችንን ዘለግ እያደረግን፤
“በመለስ መላጣ ቅማል ትሄጂና
እንዳትሰበሪ ያዳልጥሽና፣
መለስን ለመሳል በጣም ቀላል ነው
ፍየሊቷን ስሎ ቀንዷን መተው ነው”
እያልን የግጥም ችሎታችንንም የዴሞክራሲ መብታችንንም እንፈትን ነበር። አዎ እውነትም ማንም የሚናገረን ሰው አልነበረም። እውነትም ዴሞክራሲ ተከብሯል ስንል የግንቦት ሃየ ሰልፎች ላይ “…ግንቦት ሃያ ለዘላለም ኑሪ” የሚለውን መዝሙር እየዘመርን በደስታ እንሰለፍ ነበር። እያደግንም ስንመጣም ጠቅላይ ሚኒስትሩ “መለስ መላጣ ብሎ መሳደብ ይቻላላ መላጣዬን መንካት ግን አይቻልም” ብለው ጭራሽ አስደሰቱን። (በቅንፍ በዚህ ንግግር የደነገጠ አንድ ግለሰብ ቢኖር የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፀጉር አስተካካይ ብቻ ነበር አሉ። መላጣቸውን ሳይነካ እንደምን ቀሪ ፀጉራቸውን መከርከም ይችለዋል…? ብለን እንቀልዳለን! ቅንፍ ለዘላለም ትኑር!)
ቀልዱ ቀልድ ነው የምር ግን በግንቦት ሃያ ማግስት ሀገሪቷን ያጥለቀለቋትን የህትመት ውጤቶች ስናስታውስ ለካስ ህዝቤ ታፍኖ ኖሯል፤ ያስብላል። እዝችጋ ተወዳጁን እስክንድር ነጋን ሳይጠቅሱ ማለፍ ነውር ነው። አዲስ መስመርም ይገባዋል፤
አስክንድር ነጋ ሲኖርበት ከነበረው ፈረንጅ አገር ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የሳንሱር መቅረት እና የነፃው ፕሬስ መፈቀድን ተከትሎ ነበር። እንደመጣም “ኢትዮጵስ” የተባለች በሃምሳ ሳንቲም የምትሸጥ ጋዜጣ ጋዜጣ ማሳተም ጀመረ። ከትንሽ ቆይታ በኋላ ግን ለተሰጠው የፕሬስ መብት ዱላ እና እስር ያስከፍል ጀመር። በዚህም አስክንድር ብቻ ሰባት ግዜ ታስሮ ብዙ ሰባት ግዜ ተደብድቧል። ይህንን ስናይ አዋጁ ወጥመድ ነበር እንዴ…? ብለን ጠርጥረናል።
“ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሯ መሄድ ትጀምራለች” (ይቺ አባባል የት ጠፍታ ከርማ ነበር ባካችሁ?) ብቻ ቀስ በቀስ የፕሬስ ህግ ሲወጣ ቀስ በቀስ የአሸባሬነት ህግ ሲወጣ ህገ መንግስታችን የፈቀደልን ያለ “ሳንሱር” ቅድመ ምርመራ የመፃፍ መብት ራስን በራስ ወደመመርመር ተሸጋገረ። እኛ “ፀሀፊ” በሆንበት ዘመን ራሳችንን ሳንሱር እያደረግን መፃፍ ጀመርን። ከዛም አልፎ በግልፁ መፃፍ የሚያመጣውን ጦስ እየፈራን ያለ አመላችን አሽሟጣጭ ሆነን ቁጭ አለን (እዝች ጋ ሳይስቁብኝ አይቀሩም… ግን የምሬን ነው!) አሁንም እያደር ሽሙጡም ቢሆን እሳቸውን እና ቤተሰባቸውን የማያስቀይም እንዲሆን መከራችንን ማየት ጀመርን። (ቤተሰባቸው ተብሎ የተገለፀው የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችን ነው) እሱም አልተሳካም!
ወዳጄ ለማንኛውም አሁን በይፋ ሳንሱር ተጀምሯል። ከዚህ ቀጥሎ ማተሚያ ቤቶች የሚያሳትሙትን ማነኛውም የህትመት ውጤት ላይ ምርመራ እንዲያከናውኑ ተወስኗል። አንጋፋው ብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት ስራውን መጀመሩን ሰምተናል። ሌሎቹም ይቀጥላሉ… ባለፈው ሳምንት ውስጥ ማህሌት የተባለች የልብ ወዳጃችን ፌስ ቡክ ግድግዳዋ ላይ ይህንን ለጥፋ ነበር።
“የብርሃና ሰላም አዲስ ህትመት ስራ ውል አንቀጽ አንቀጽ 10 የሚከተለውን ይላል፡፡ ምን ማለት ይሆን?!
አንቀፅ 10
ሕግን የተላለፈ ይዘትን አለማተም
10.1 አታሚው በአሳታሚው እንዲታተም የቀረበለት የፅሁፍ ስክሪፕት ህግን የሚተላለፍ ስለመሆኑ በቂ ምክንያት ካለው አላትምም የማለት መብት አለው፡፡
10.2 አታሚው አሳታሚው የሕግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል የህትመት ይዘት የማውጣት ዝንባሌ ያለው መሆኑን ለማመን በቂ ምክንያት ካለው በማናቸውም ጊዜ ውሉን ለማቋረጥ ወይም ለመሰረዝ ይችላል፡፡”
ወዳጃችን ማህሌት፤ ምን ማለት ነው? ነው ያልሽው…? ምን ማለት መሰለሽ ፅሁፍሽ ከመታተሙ በፊት በብርሃን እና ሰላም የምርመራ ዋና ስራ ስራ ሂደት ባለቤት ይመረመራል። ሳንሱር ይደረጋል ማለት ነው።
እነሆ መንግስታችን ተዓምረኛ ነው! በህገ መንግስቱ ሞተ ያልነውን ሳንሱር አስነስቷል እና ደስ ይበላችሁ!!!
ይህንን በሂሳብ እናስላው ካልን ህገ መንግስቱ ሲባዛ በዜሮ ይሆናል ዜሮ! ይሆናል ማለት ነው። ታድያ ማሽኑ የመንግስት ነው!

Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 2 Comments »
Monday, April 30th, 2012
የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተመሰገን ደሳለኝ ከዚህ በፊት በምታወጣቸው ፅሁፎች በፍርድ ሂደቱ ላይ ጣልቃ ገብተሃል ተብሎ ተከሶ እንደነበር ይታወሳል።
ተመስገን “የተከሰሱኩት አለ አግባበብ ነው ነው” በሚል ተከራክሮ ፅሁፉ ተከሳሾች የሰጡት መሆኑን አስረድቶ ነበር። ይህንንም ለማረጋገጥ አቃቤ ህግ አበበ ቀስቶ (ክንፈሚካኤል ደበበን) ለምስክርነት ጠርቶት የነበረ ሲሆን መስካሪውም “በፅሁፉ መጠየቅ ካለብኝ የምጠየቀው እኔ ነኝ። ሃሳቤን በፍርድ ቤት ለመግለፅ ባለመቻሌ ጋዜጣ ላይ እንዲወጣ አድርጌያለሁ!” ብሎ ምስክርነቱን ሰጥቶ ነበር።
በዚህም ዛሬ ሚያዝያ 22/2004 ዓ.ም ድጋሚ ቀጠሮ ይዞ የነበረው ፍርድ ቤት በተመስገን ደሳለኝ ላይ አራት ወር እስር ወይም ሁለት ሺህ ብር እንዲሁም በአበበ ቀስቶ ላይ ወደፊት ከሚፈረድበት ላይ የሚጨመር ስምንት ወር እስራት ተፈርዶባቸዋል።
በአሁኑ ሰዓት ተመስገን በፖሊስ ቁጥጥር ስር የሚገኝ ሲሆን ከባንክ የሁለት ሺህ ብር ሲፒዮ ጓደኞቹ አሰርተው እስኪመጡለት ድረስ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል። ተመስገን ሲፒኦው ለዛሬ ካልደረሰለት ነገ የስራ ቀን ባለመሆኑ ዛሬ እና ነገን እስር ቤት ለማደር ሳይገደድ አይቀርም ሲሉ ወሬውን ያቀበሉኝ ወዳጆቼ ስጋታቸውን ገልፀውልኛል!
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 1 Comment »
Monday, April 30th, 2012
በአንድ ቤተሰብ ውጥ የሚኖሩ ሰዎች ነበሩ። የቤተሰቡ ሃላፊ የሆኑት አባወራ ሲያገኙ በድፍረት ሲያጡም በሌላ ድፍረት ጠጥተው ሞቅ ብሏቸው ነው የሚገቡት። ስጠረጥር የዘንድሮ ኑሮ እንደምንም ብለው ሞቅታ ውስጥ ካልተደበቁ በስተቀር እንደማይቻል ገብቷቸዋል።
አሁንም ስጠረጥር አባወራው በዱቤም ይሁን፣ በብድርም ይሁን፣ በቅልውጥ መጠጥ ቤት ካላመሹ በቀር በጊዜ ቤታቸው ቢገቡ የቤተሰቡ አባላት የሚጠይቋቸውን ጥያቄ መመለስ እንደማይችሉ ስለሚረዱትም ይመስለኛል።
ታድያልዎ ከእለተታ አንድ ቀን አንዱ ልጃቸው “ዛሬስ አባዬ ሲመጣ ጠብቄ የማናግረው አለኝ” ብሎ ሲጠብቅ፣ ሲጠብቅ፣ ሲጠብቅ ተስፋ ሊቆርጥ ትንሽ ሲቀረው መጡ…ማ…? አባወራው! ልጅም ገና እንደመጡ የተበጫጨቀ የትምህርት ቤት ዩኒፎርሙን እያሳያቸው “አባዬ… ይኸውልህ ትምህርት ቤት የምለብሰው ዩኒፎርም ይሄ ነው… ጓደኞቼ እብዱ እብዱ… እያሉ ያበሽቁኛል። ደሞ ደብተሬም አልቋል። ሌላ ደግሞ …” እያለ ጥያቄ ቢያከታትልባቸው ግዜ በሞቅታ እና በመልስ እጦት ውስጥ ያሉት አባት ምን አሉት መሰልዎ… “አንተ ልጅ ዘወር በል ፖለቲካ አታውራብኝ!”
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ቀልዱ አላስቆትም!? እንግዲያስ ከቀልብዎ አይደሉም ማለት ነውና ደግመው ያንብቡት። ዘንድሮ እንደሁ ባለስልጣኑ ቀልብ ነዋሪው ደግሞ ቀለብ በፅኑ የተቸገረበት ሁኔታ ነው ያለው (አሁን እኔው ሳቄ መጣ!)
ይህንን ቀልድ ለምን አወራሁልዎ እንደው እስቲ ዘና ላድርጋቸው ብዬ ነውን? በፍፁም አይደለም አንበሳዬ… እህስ ይበሉና ይከተሉኝ ይምጡ አዲስ መስመር ላይ፤
አቶ መለስ የምሬን ነው የምልዎ ግራ መጋባት ይታይብዎታል። ትንሽ ይረጋጉ እንጂ… (አክብሬዎት እንጂ ሞቅታ ውስጥ ነው ያሉት!) ብዬ ልናገር ነበር። ነገር ግን ጠቅላይ ሚንስትሬ ነዎትና እንዲህ እንደዞህ አልልዎትም። ነገረ ስራዎ ግን ከላይ ካነሳውልዎ ሞቅ ያለው አባት ጋር ይመሳሰላል።
ከየትኛው ልጀምርልዎ…
የዋልድባ ገዳም መነኮሳት ገዳማችን አይታረስ የአባቶቻችን አፅም አይፈንቀል… ብለው አቤት ቢሉ “ድብቅ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው መነኩሴዎች አሏቸው” ይቅር ይበልዎ…! (አንድ ይበሉልኝ)
መምህራን ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ያቀረበብን ዘገባ ትክክል አይደለም “ህይወታቸውን የሚቀይር ገንዘብ ተጨመረላቸው ብሎ ዘግቦ ህይወታችንን አዘበራረቀው በይፋ የተናገረው ስህተት መሆኑን ይናገርልን” ብለው አቤት ቢሉ “ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው መምህራን!” አሉዋቸው። (ሁለት)
ከደቡብ ክልል አማራዎች መፈናቀላቸው አግባብ አይደለም በሚል እኔ ሳልቀር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ያደረጉት ነገር ለመንግስትዎም ጥሩ ስም አያሰጠውምና አንድ ይበሉዋቸው ብለን ብንጠይቅዎ፤ “በኢትዮጵያዊነት እንታወቅ የሚሉ ልዩ የፖለቲካ ጥቅም ፈላጊዎች…” ሲሉ ሃሳቡን አጣጣሉት (እየቆጠሩ ነው…? ሶስት ይበሉልኝ)
“እስልምና ሃይማኖታችን ላይ ጣልቃ አይግቡ አህባሽን ከወደዱት ራስዎ ሊያምኑ ይችላሉ እኛ ላይ ግን አይጫኑብን እኛ ሙስሊሞች አላህን እንዴት እንድምናምን መንግስት ሊያስተምረን አይገባም መንግስት ሌላ ሀይማኖት ሌላ!” የሚል ተቃውሞ ሲነሳብዎ “ይሄ አክራሪነት ነው የተለየ የፖለቲካ አጀንዳ ያነገቡ እንደ ቱኒዚያ፣ እንደ ግብፅ፣ እንደ ሊቢያ፣ እንደ የመን እና እንደ ሴሪያ መሆን የፈለጉ ሰዎች የሚያነሱት አጀንዳ ነው…!” ብለው በራሰዎ ላይ አሟርተው እርፍ አሉ።
እንደው የቅርብ የቅርቡን ልንገርዎት ብዬ እንጂ ሌላም ብጨምር ማለቂያ የለውም… የተጠየቁት ጥያቄ በሙሉ ፖለቲካ እየመሰልዎ ግራ ገብትዎ ግራ አጋብተውናል።
ነገረ ስራዎን እስቲ ልብ ብለው ይመልከቱት ሁኔታዎ “አባዬ ዳቦ ራበኝ” ለሚል ልጅ “ዘወር በል ድብቅ ፖለቲካ አታራምድብኝ” ብሎ የሚመልስ ሞቅታ ከተጠናወተው አባት ጋር ይመሳሰላል።
ክቡርነትዎ ሞቅ ካልዎ ቀዝቀዝ ያለ ሽሮ ፍትፍት ይውሰዱበት እና ጥያቄዎቹን በሙሉ ድጋሚ ይስሟቸው። እውነት እውነት እልዎታለሁ እስከ አሁን የሰማናቸው ጥያቄዎች በሙሉ አንድም ፖለቲካ የላቸውም። ይልቅስ እንዲህ ሲያደፋፍኑ የፖለቲካ ጥያቄው እንዳይመጣብዎ ይፍሩ! “ለምን እፈራለሁ ሙሉ ትጥቅ እያለኝ!” ካሉ አሁንም ሞቅታ ውስጥ ነዎት ማለት ነውና ሲነጋ እንነጋገራለን!
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 3 Comments »
Monday, April 30th, 2012
ሰሞኑን ከተሰሙ አስደንጋጭ ዜናዎች ውስጥ የሚከተለው ይገኛል…
“በዛሬዉ እለት በአርሲ አሳሳ ከተማ የጁምአ ሰላት ከተሰገደ በኋላ ሼህ ሱዑድ በአንድ መስጂድ ዳዕዎ አድርገዉ ሲወጡ በፓሊስ በመያዛቸዉ፤ የአካባቢዉ ሙስሊም ህብረተሰብ “ሼሁ ለምን ይታሰራሉ ምንም ጥፋት አልፈፀሙም” በሚል ለማስለቀቅ ሲሞክሩ ከፓሊሶች ጋር በተፈጠረዉ አለመግባባት ፓሊስ በከፈተዉ ተኩስ እስካሁን ባለዉ መረጃ መሠረት አምስት(5) ሰዎች መገደላቸዉና ብዙ ሰዎች መቁሰላቸዉን የአካባቢዉ ምንጮች ገለፁ:: ከተገደሉት ሰዎች መካከል ሼህ ኸድር የሚባሉ ታላቅ አሊም እንደሚገኙበትም ምንጮች ጨምረዉ ገልፀዎል:: እንደሚታወሰዉ ሼህ ሱዑድ ሻሸመኔ በተካሄደዉ ስብሰባ ላይ “ኢህአዴግን ለሀያ አመታት ስንደግፈዉ ኖረን አሁን እንዴት አሸባሪ አክራሪ ብሎ ይወነጅለናል” በማለት የተሰማቸዉን ቅሬታ በስብሰባዉ ላይ ገልፀዉ እንደነበር የሚታወስ ነዉ::
ይህንን ያገኘሁት ከአንድ የፌስ ቡክ ወዳጃችን ግድግዳ ላይ ነው። ዜናውን ሚዛናዊ ለማድረግ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ደግሞ ቀጥሎ እጠቅሳለሁ።
“በአርሲ ዞን አሳሳ ከተማ በሙስሊም አክራሪነት ሰዎችን ሲያደራጅ እና በመንግስት እና በህዝብ ላይ ጀሀድ ሲያውጅ የነበረ የነበረ አንድ ግለሰብ በቁጥጠር ስር ዋለ። ግለሰቡ በቁጥጥር ስር የዋለው በህብረተሰቡ ተሳትፎ መሆኑን ኢኒስፔክተር (ስማቸው ጠፍቶብኛል) ብቻ አንድ የፖሊስ አባል ኃላፊ ተናግረዋል። ሰውየው አያይዘው እንደተናገሩት በወቅቱ ግለሰቡ ያደራጃቸው አንዳንድ አክራሪዎች እና የተለየ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ግብረ አበሮቹ ባነሱት ግርግር የአሳሳ ከተማ ፖሊስ ጣብያ ወድሞ አራት ሰዎች ሲሞቱ አስር ፖሊሶች ቆስለዋል።”
ቀጥሎ የኔ አስተያየት ይከተላል።
እንግዲህ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ስንሰማ ትርጉም አዋቂ እንደሚያስፈልግ የታወቀ ነው። “በመንግስት እና በህዝብ ላይ ጀሀድ ሲያውጅ የነበረ አንድ ግለሰብ” ማለት ምን ማለት ነው? ያልን እንደሆነ መዝገበ ቃላታችን “የመንግስትን በሀይማኖት ጣልቃ ገብነት የተቃወመ” በሚል ይፈታልናል።
ያው እንደሚተወቀው ሙስሊም ወንድሞቻችን፤ “መንግስት የራሱን አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሃይማኖት ይንከባከብ የኛን ሃይማኖት ለኛው ይተውልን!” ብለው ድምፃቸውን ማሰማት ከጀመሩ ቆይተዋል። ኢቲቪ እና መንግስት ብዙ ሀሳብ ስላለባቸው ይህንን ዜና ስንከታተል እንደቆየን ረስተውታል መሰል፤ “በመንግስት እና በህዝብ ላይ ጀሀድ ሲያውጅ የነበረ ግለሰብ” ይለናል። ለመሆኑ ይህ ትርጉም ይሰጣልን!? መንግስትንም ህዝብንም ላጥፋ የሚል ጀሀድ ታይቶ ይታወቃልን? እኒህ ማንንም ያልገደሉ የሀይማኖት አባት ጀሀድ አወጁ ከተባሉስ በከተማው አምስት ሰዎችን የገደለው መንግስት ምን አወጀ ሊባል ነው…?
ወዳጄ ባለፈው ግዜ ያስታውሱ እንደሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማቸው ቀርበው በአርሲ የአልቃኢዳ ሴል ተገኝቷል! ብለው ያለምንም “ሼ” ሲናገሩ ይህንን መጠርጠር ተገቢ ነበር። የምር ግን፤ ጠቅላይ ሚኒስትራችን አምርረውብናል። አንዳንዶች እንደሚሏቸው ከሆነ፤ “እኒህ ሰውዬ መጀመሪያ ኑሯችንን ዘቀዘቁ ዝም አልን፤ በመቀጠል ባንዲራችንን ዘቀዘቁ አሁንም ተሳስተው ይሆናል ብለን ዝም አልን፤ ቀጥሎ ደግሞ እያንዳንዳችንን ሊዘቀዝቁን ቆርጠው ተነስተዋል!” ይሏቸዋል። እኔ እንኳ እስከዛ መድረሳቸውን እጠራጠራለሁ። ነገር ግን በእውነቱ ጥምድ አድርገው የያዙን ይመስለኛል። ምን እንዳስቀየምናቸው እንጃ… እንዴ አስቡት እስቲ “አልቃይዳ” ከማለት ውጪ ምን ሊሉን ይችላሉ። በዚህ አይነት እኮ ሰውዬው የአሜሪካ ጦር ራሱ አካባቢውን ገብቶ እንዲደበድብ ሊጠይቁ ይቻላሉ ማለት ነው…!
የሆነ ሆኖ ዛሬም ተቃውሞ እና አመፅ ስለተነሳ ሰዎች ይገደላሉ… ሲደብር። አረ መንግስታችን በናትህ የጉርምስና መንፈስህን ገስፀው!

Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 5 Comments »
Saturday, April 28th, 2012
አንጋፋው ደራሲ ስብሐት ገብረ እግዚአብሄር ነብሱን ይማረው እያልን ማውራት ከጀመርን ሰማንያ ቀን እንደሚሞላው በቅርቡ አንድ ወዳጃችን በለጠፈው ማስታወሻ አስታውሰናል። እንደውም ዛሬ ሳይሆን አይቀርም… የሆነ ሆኖ ከዚህ ቀጥሎ ጋሽ ስብሀት ፅፎት በሳቅ ፍርስ ካደረገኝ ጨዋታ መካከል የሚከተለውን እንድናወጋ ወደድኩ… እንደሚከተለው አስታውሳለሁ!
በቀድሞ ግዜ ከነበሩ “ዋና ሰዎች” መካከል አሉ የሚባሉ አንድ ባለስልጠን ቀኟዝማች ይሁኑ ግራ አዝማች ወይም ፊታውራሪ ረስቼዋለሁ… ዘመቻ ሄደው ሲመጡ ታሪኩ ይጀምራል።
ዘመቻው ሁለት አመት የፈጀ ነበር። እናም ባለታሪካችን ከሁለት አመት ቆይታ በኋላ ነው ማለት ነው የሚመለሱት። መጀመሪያ የተቀበላቸው ታድያ ማነው…? ገብሬ። ገብሬ ማነው…? ገብሬማ የባለታሪካችን ዋና አገልጋይ ነው። መንገድ ገብሬ እቃቸውን ተሸክሞ ከፊት ከፊት እየሄደ፤ ጨዋታ ተጀመረ…
“እሺ ገብሬ ሀገሩ ሰላም ነው…?”
“ሰላም ነው ጌታዬ… ሁሉ ሰላም ነው… ብቻ…” አለ ገብሬ የጌታውን እቃ ተሸክሞ ከፊት ከፊት ኩስ ኩስ እያለ።
“ብቻ ምን…? አንተ የተፈጠረ ችግር አለ እንዴ?”
“የለም ጋሼ ብዙ አይደንግጡ… ብቻ ጉራች መሞቱን ልነግረዎ ነው” አላቸው። ጉራች ማነው…? ያላችሁ እንደሁ ጉራች ባለታሪካችን አብዝተው የሚወዱት በሬ ነበር።
“ውይ አፈር ስሆን… ጉራች ሞተ…!?”
“አዎ ጌታዬ…! ሞተ…! ምፅ…” ኩስኩስታውን ገብሬ ቀጥሏል።
“ምን ሆኖ ሞተ በል…?” አሉ ባለታሪካችን፤ እንኳንም ሌላ መርዶ አልነገርከኝ በሚል ዜማ!
“እሱማ… ለእሜቴ ተስካር ታርዶ ነው ጌታዬ…!” አለ። እሜቴ እኮ ባለቤታቸው ናቸው!
ክው አሉ ባለታሪካችን! ጠላትዎ ክው ይበልና! ይሄኔ ገብሬም ኩስ ኩስ ማለቱን ትንሽ ገታ አደረገ።
“አንተ ምንድነው የምታወራው…? እሜቴ ሞተች ነው የምትለኝ…?”
“ምፅ… አዎ ጌታዬ እሜቴ ሞቱ እኮ!”
“የጉድ ሀገር…! ምን ሆና ሞተች መሆኑን?”
“አይ ጌታዬ… በወሊድ ነው!” (ልብ አድርጉልን ባለታሪካችን ከሁለት አመት በኋላ ወደ ቀያቸው መምጣታቸው ነው…)
“እንዴ… አንተ ሰውዬ ዛሬ ታመሃል እንዴ…? ከማን አረገዘችው…? እስቲ ንገረኝ…?” አሉ በቁጣ ተገስለው።
ይሄኔ ገብሬ ጣጣ አለው እንዴ…! ቀልጠፍ ብሎ መለሰ።
“እንጃ ጌታዬ ሰዉ ከገብሬ ነው ይላል እኔ ደግሞ ከኔ አይደለም እላለሁ!” ብሏቸው እርፍ።
በአግባቡ ተርኬው ይሆን? ብቻ ጋሽ ስብሀት ለመዘከር ያህል ነውና ልክ አንብው ሲጨርሱ “ጋሽ ስብሀት ነፍስህን ይማረው!” በማለት ተባበሩኝ! አመሰግናለሁ።
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 7 Comments »
Friday, April 27th, 2012
ጋዜጠኛ እና መምህርት ርዮት አለሙ “አሸብረሽናል” ተብላ አስራ አራት አመት እስር እና ሰላሳ አምስት ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባት (መቼም የዛሬ ፈራጅ ከየት ይመጣል ብሎ አያስብም…) ብቻ በአሁኑ ሰዓት በቃሊት እስር ቤት ትገኛለች።
ርዕዮት ከፍርዱ በፊት “ኤልያስ ክፍሌ አሸባሪ ነው” ስትይ መስክሪ እና ትፈቻለሽ ተብላ፤ በማስፈራራትም በማባበልም ብትጠየቅ አሻፈረኝ “እኔ የማውቀው ኤልያስ ጋዜጠኛ እንደሆነ ነው። በማላውቀው ጉዳይ ላይ አልመሰክርም።” ብላ በአቋሟ በመፅናቷ አሳሪዎቿ፤ “እንዲህ ጠንካራ አቋም ካለሽ ለምን ጫካ አትገቢም” ብለው ሲዘባበቱባት እንደነበር በዛ ሰሞን ስንሰማ ሰንብተናል።
ታድያ ይቺ መምህር እና ጋዜጠኛ ርዮት አለሙ በጡቷ አካባቢ ያጋጠማትን ተደጋጋሚ ህመም ለእስር ቤቱ ኃላፊዎች ስታመለክት የቆየች ሲሆን አንድ ግዜ “ፓራሲታሞል ዋጪበት” ስትባል። ሌላ ግዜ ደግሞ “አንቺን ሃኪም ቤት የሚወስድ ሴት ፖሊስ የለም” እየተባለች በህመም ስትሰቃይ ቆይታለች።
ማክሰኞ ሚያዝያ 16/2004 ዓ.ም ግን ፓራሲታሞሉም ከቃሊቲ አለቀ፣ ሴት ፖሊስም ተቀጠረ መሰለኝ (ይሄ የኔ ጥርጣሬ ነው) ፖሊስ ሆስፒታል ተወስዳ ነበር። ርዕዮት በሆስፒታሉ ኦፕሬሽን አድርጋ በዛው ቀን ወደ ቃሊት እስር ቤት ተመልሳለች። አረ ግፍ ነው… ትንሽ እንኳ አረፍ ሳትል? ቢሉ የሚመልስልዎ መንግስት የለም።
በአሁኑ ግዜ መመህርት እና ጋዜጠኛይቱ “አሸባሪ” ሻል እያላት መሆኑንም ሰምቻለሁ!
በመጨረሻም
ኦፕሬሽን ስል ምን ትዝ አለኝ መሰልዎ…
ርዕዮት በታሰረችበት የነ ኤልያስ ክፍሌ የክስ መዝገብ ከታሰሩት መካከል የአውራምባው ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ በፍርድ ቤት ማስረጃ ሆኖ ከቀረበበት የስልክ ለውውጥ ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፤
ውቤ ወንድሙ ከውጪ ሃገር ይደውልለታል። የሚጠይቀው ስለ አባታቸው ህመም ነበር። ታድያ ወንድምየው… “እሺ አሁን አባባ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?” ይለዋል። ውብሸትም “ኦፕሬሽኑ ተከናውኗል። ስለዚህ ገንዘብ ብትልክልኝ ደስ ይለኛል” ብሎ ይመልስለታል።
እናልዎ ጠላፊው ከመጀመሪያው ጀመሮ ስልኩን በትጋት አልጠለፈም መሰለኝ… “ኦፕሬሽኑ ተከናውኗል ገንዘብ ብትልክልኝ ደስ ይለኛል” ያለውን ብቻ ቀድቶልዎ… “ኦፕሬሽንን” ያልከው የሽብር ኦፕሬሽን ነው። በሚል ማስረጃ ሆኖ ቀረበልዎታ…
አረ ይሳቁ ወዳጄ ከት ብለው ይሳቁ እንጂ…!
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 5 Comments »
Friday, April 27th, 2012
የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ በእነ አንዷለም አራጌ የክስ መዝገብ የተከሰሱ ሰዎችን ቃል በጋዜጣህ ላይ አትመሃል ይህም በፍርድ ሂደቱ ጣልቃ መግባት ነው ተብሎ ተከሶ እንደነበር ይታወቃል። (ካልታወቀም አሁን ይታወቅ… ልል ነበር በዜና ላይ አይቀለድም ለካ…)
ተሜ የተከሰሰበት ጣልቃ መግባት ክስ የአንዷለም አራጌን፣ የእስክንድር ነጋ፣ የናትናኤልን እና የአበበ ቀስቶን ፅሁፍ በጋዜጣህ ላይ በማተምህ የሚል ሲሆን፤ ተመስገንም “ተጠቃሾቹ የሰጡኝን ፅሁፍ የማተም መብት አለኝ” ሲል ተከራክሮ ነበር።
በዚህም ምክንያት “እውነትም ተጠርጣሪዎቹ ፅሁፉን ሰጥተውት ነበር ወይ?” የሚለውን ለማጣራት ለእማኝነት የተጠራው አበበ ቀስቶ… “ፅሁፉ የኔ ነው በወጣው ነገር መጠየቅ ካለብኝ የምጠየቀው እኔ ነኝ እንጂ ተመስገን አይደለም። በጋዜጣው ላይ የታተመው በፍርድ ቤት ላቀርበው እፈልግ የነበረ ሃሳብ ነው። ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ግዜ ሊሰጠኝ ስላልቻለ እንዲታተም ሰጥቼዋለሁ…” ብሎ ሲናገር ዳኛው “ንግግርህን አሳጥር ይህንን የጠየቀህ የለም” በማለት አቋርጠውታል።
በዛሬው የተመስገን ደሳለኝ ችሎት ካለፉት ግዚያት የበለጠ በርካታ ሰው ተገኝቶ እንደነበር ከስፍራው የደረሰኝ ወሬ ያስረዳል።
ፍርድ ቤቱ የምስክሩን ክንፈ ሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) ቃል ከሰማ በኋላ ለሚያዝያ 22 ቀጠሮ ሰጥቶ ተበትኗል።
በነገራችን ላይ ሚያዝያ 24 ኢቲቪም በአኪልዳማ የተነሳ ፍርድ ቤት እንደሚቆም ባለፈው ተጨዋውተናል አይደል። እስቲ የሚባለውን እንጠብቃለን!
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | No Comments »
Wednesday, April 25th, 2012
ሰንደቅ ጋዜጣ በዛሬ እትሟ “አዲስ ራዕይ” የተሰኘውን የኢህአዴግ “ቅዱስ” መፅሀፍ ጠቅሳ እንደዘገበችው ከሆነ፤ ገዢው ፓርቲ ምንም እንኳ ላለፉት ሃያ አመታት ሲገዛ እና ሲሸጠን የቆየ ቢሆንም የተሳካለት ግን ግማሹን ያኸል ብቻ መሆኑን እንዳመነ አውስታለች።
ይህንን የሰሙ ሽሙጠኞችም ኢህአዴግ አስሩን አመቱ በኪሳራ ሲገዛን፤ እንዲሁም ሌላውን አስር አመት በትርፍ ሲሸጠን ከርሟል ማለት ነው ሲሉ በሪፖርቱ ተሳልቀዋል።
የምር ግን ኢህአዴግ እኮ ደስ የሚለኝ ለዚህ ነው። በኢቲቪ ቢዋሽ በአዲስ ራዕይ አይፎግርነም። ኢቲቪ ሃያውንም አመት እድገት በእድገት እንደነበርን፣ ሃያውንም አመት ከኢህአዴግ ጋር ያለፈው ግዜ ብሩህ እንደነበር፤ ግንቦት ሃያ እና የካቲት አስራ አንድ በመጡ ቁጥር ሲነግረን ከርሟል። አዲስ ራዕይ ደግሞ እንዲህ እውነቱን ታፍረጠርጠዋለች። ይሄ ጥሩ ነው። ምናልባትም እንደ ንስሀም ይቆጠር ይሆናል። (ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች እየተናገሩ ነው። የሚለውን ጨምሩልኝማ…!)
አንድ ወዳጃችን “አስር አመት ሙሉ በብላሽ ነበር የመራናችሁ” የሚለውን ባነበበ ግዜ ወድያውኑ ያደረገው ነገር ምን እንደሆነ ያውቃሉ? የሂሳብ ማሽን ከኪሱ አወጣ ቀጠለናም፤ አስር የኪሳራ አመታትን ከእያንዳንዳችን መወሰዱን አሰመረበት ከዛስ…? ከዛማ የሰማንያ ሚሊዮኖች አስር አመት ስንት እንደሚመጣ መታው… 80ሚሊዮን ሲባዛ በ10 እኩል ይሆናል… 800 ሚሊዮን አመታት መጣ። “ስለዚህ መንገስታችን ይህንን ደሁሉ ጊዜ ስቀልድባችሁ ነበር እያለን ነው ማለት ነው።” ሲል ብስጭቱን ገልፆልናል።
የምር ግን ወዳጄ ሃያ አመት ሙሉ በስልጣን ላይ የነበረ ገዢ አፉን ሞልቶ “ግማሹን ብቻ ነው የተሳካልኝ!” ማለቱ ምን ማለት ነው? አልሆን ሲለው በቃኝ ብሎ አለመልቀቁ አያስጠይቅም ትላላችሁ? ቢያንስ ቢያንስ በእግዜሩ ዘንድ ማስጠየቁ አይቀርም ካላችሁ እናንተ የተባረካችሁ ናችሁ!
ቀጥሎ የሚገኘው የመካሪዎች ድምፅ ነው…
ኢህአዴጎች ሆይ ግማሽ ቀልድ ግማሽ ስራ ከኮሜዲያን እንጂ ከመንግስት የሚጠበቅ አይደለም እና የባከኑትን አስር አመታት ኪሳራ ከእግዜር እናገኘዋለን እናንተ ግን ሌላ አስር አመታት ደግሞ ሳታባክኑ ቢያንስ ቢያንስ አረፍ በሉ! … አይዟችሁ ቀጥሎ ደግሞ ተመልሳችሁ ወይ ታባክናላችሁ ወይ ትሰራላችሁ! ጎሽ እሺ በሉና ዛሬውኑ እረፍት አድረጉ ጎሽ…
መስታወሻ
የዝች አጭር ጨዋታ ሀሳብ ባለቤት የፌስቡክ ወዳጄ “ጆሞ” መሆኑን ለመጥቀስ እወዳለሁ።
Filed under: Uncategorized

Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | No Comments »
Tuesday, April 24th, 2012
በወዳጃችን ዳንኤል ተፈራ የተሰናዳው “ዳንዲ የነጋሶ መንገድ” የተሰኘው መፅሀፍ ላይ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በአንድ ስብሰባ ላይ አቶ መለስ ዜናዊ እነ ስዬን አጓጉል ሲዘልፏቸው ይሰማሉ። (ምን እያሉ…? ይበሉ እንጂ…) ምን የማይሉት አለ ብዬ እቀጥላለሁ፤ “አፈንጋጮቹን ጃኬታቸውን አስወልቀን ሸኝተናቸዋል።” በማለት ይናገሩ ነበር። ይሄኔ ዶክተር ነጋሶ ሆዬ መንጌ በአንድ ወቅት ጀነራሎቹን “ማዕረጋቸውን አስወልቀን ቂጣቸውን በሳንጃ ወግተናቸዋል” ያለው ትዝ አላቸው… ትዝ ብሏቸውም ዝም አላሉም አቶ መለስን ትኩር ብለው እያዩ “አሁንስ መንግስቱን መንግስቱን መሰልከኝ!” ብለው እርፍ።
እዝች ጋ ከሁሉ ያሳቀኝ ምን እንደሆነ ያውቃሉ የወ/ሮ ገነት ዘውዴ ነገር፤ “እንዴት መለስን ከመንግስቱ ጋር ታመሳስለዋለህ” ብለው እዛው ስብሰባ መሃል ስቅስቅ ብለው አላለቀሱም መሰልዎ…? ያኔ ወ/ሮ አዜብ በስብሰባው ላይ መኖራቸውን እንጃ፤ ቢኖሩ ግን ወ/ሮ ገነትን ዝም የሚሏቸው አይመስለኝም።
ሳስበው ወደ ዶክተር ነጋሶ ዞር ብለው “እርስዎ ቆይ እንነጋገራለን… አንቺ ግን ምን ቤት ነሽ እንዲህ የምትነፋረቂብኝ…” ካሉ በኋላ፤ ወደ አቶ መለስ ደግሞ ዞረው፤ “ስማ እንጂ አንተ የጀመራችሁት ነገር አለ እንዴ…? እዛች ቤት እንገናኛታለን!” ብለው ሲያመናጭቋቸው አሁንም ያው ወ/ሮ ገነት መቼም አያስችላቸውም እንባ ሳይተናነቃቸው አይቀርም። ይሄኔ… “አላበዛሽውም እንዴ…!?” እየተባባሉ በስሊፐር ሲጠፋጠፉ ይታየኝ ነበር።
እኔ የምለው ወ/ሮ ገነት ዘውዴ ግን የት ጠፉ? በነገራችን ላይ ከባለቤታቸው ጋር እንዴት እንደተፋቱ ሰምተዋል…? ቆይ ልንገርዎትማ…
ባለቤታቸው ከኢህአዴግ አመራር አባላት መካከል ነበሩ። ታድያ ሲያስቡት ሲያስቡት የኢህአዴግ ነገረ ስራው ምንም አልጥም አላቸው። እናም “በቃኝ ከእንግዲህ አባልነቱ ይቅርብኝ እና በባልነቱ እንቀጥላለን” ብለው አማከሯቸው። ታድያ ወ/ሮ ገነት ሆዬ ምን አሉ መሰልዎ… “ከኢህዴግ ጋር ተፋቶ ከእኔ ጋር መኖር አይቻልም ልጅነቴን የሰጠሁት ባሌ ድርጅቴ ነው። ከድርጅቱ ከወጣህ ከቤቴም ትወጣልኛለህ… መንገዱንጨርቅ ያድርግልህ” ብለው አሰናበቷቸው። (እውነትም ወ/ሮ አዜብ መጠራጠር አለባቸው… ብለው ግፍ እንዳይናገሩ ወዳጄ…!)
እናልዎ አንዳንድ ተናግሮ አናገሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ዛሬ ዶክተር ነጋሶ አቶ መለስን “አሁንስ መንግስቱን መንግስቱን መሰልከኝ” ብለው ቢናገሩ እንደዛን ግዜ ወ/ሮ ገነት ዘውዴ ብቻ ሳይሆኑ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ስቅስቅ ብሎ ያለቅስ ነበር ይሎታል። እንዴት ያላችሁ እንደሆነ “መንጌ ምን በደለን እና ከመለስ ጋር ያመሳስሉታል?” ብለው ይመልሳሉ።
ለነገሩ ይሄም ተጋኗል። እኔ ይቅርታ አድርጉልኝና መለስ ከመንግስቱ የበለጡ እርኩስ ናቸው ብዬ አላምንም።
ይልቅስ መቼለታ አየር ሃይል ሰልጣኞቹን ሲያስመርቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር አድርገው ነበር። ታድያ ወደመድረክ የጋበዛቸው ሰውዬ ምን ብሎ እንደጠራቸው ያውቃሉ…? “የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ አቶመለስ ዜናዊ…” በእውነት ክው ነው ያልኩት ቁርጥ መንግስቱን መሰሉኝ። ለነገሩ ባለፈው ግዜ ተመስገን ደሳለኝ እንደዘረዘረልን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የያዙት ስልጣን መንጌ ይዘውት ከነበረው ይበልጥ እንደሁ እንጂ አይተናነስም።
ከሁሉ ከሁሉ ግን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን አሁን በተለይ ኮሎኔር መንግስቱን ስናብጠለጥልባቸው የነበሩ ነገሮችን በሙሉ እያሟሉ ይገኛሉ። እንደ እግዜር ፈቃድ በቅርቡ ሚኒማውን በሙሉ አሟልተው ቁርጥ መንግስቱን የሚሆኑ ይመስለኛል። በየእስር ቤቱ ያለውን ገረፋ እና ስቃይ አናነሳም… ገብስ ገብሱን ለማንሳት ያህል፤ ለምሳሌ ነፃ ፕሬሱ ላይ የተጋረጠው ነገር፣ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ላይ እደረሰ ያለው፣ የሙያ ማኅበራት እየሆኑ ያሉትን በሙሉ ስናይ “አሁንስ መንግስቱን መንግስቱን መሰልከኝ” የሚባሉበት ትክክለኛው ግዜ ላይ እየደረሱ ይመስላሉ። ቀለል ያለ ቋንቋ መጣችልኝ… እንደውም ከአይን ያውጣቸው እንጂ አቶ መለስ ዜናዊ ለአቅመ መንግስቱ ኃይለ ማርያም ደርሰዋል! ብንል የተሻለ ሳይሆን አይቀርም።
የምር ግን ወዳጄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ አሁን አሁን ጥያቄ ሲጠየቁ ቆጣ ቆጣ ማለታቸውን ስታዩ “ይሄንን ቁጣ የት ነበር የማውቀው?” ብላችሁ ድንገት መንጌ ትውስ አይሏችሁም። የምሬን እኮ ነው… እውነቱን ለመናገር አቶ መለስ ከመንጌ የሚለዩት “ኢትዮጵያ የኛ መመኪያ” ሲባል ልባቸው ድንድጥ አለማለቱ፣ ባንዲራ ገልብጠው በየ ሰዉ አገር መታየታቸው እና የአክሱም ሀውልት ለደቡብ ምኑ ነው በሚለው ፍልስፍናቸው ካልሆነ በስተቀር ከመንጌ ምንም አይተናነሱም። እሰይ የኔ አንበሳ! አይሏቸውም እንዴ!?
ምስጋና
ለፌስ ቡክ ወዳጄ ቤዚ ቢል ይህንን ፎቶ “ታግ” አድርገህ ለዚህች ጨዋታ አነሰሳስተኸኛልና! ምስጋና ይገባሃል።
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 8 Comments »
Friday, April 20th, 2012
ይህ ፅሑፍ “አርብ አርብ ይሸበራል ኢየሩሳሌም” በተባለበት በዕለተ ጁምአ ለምትታተመው ፍትህ ጋዜጣ የተሰናዳ ነው። ከጋዜጣዋ ርቃችሁ ለምትገኙ ወዳጆች ደግም እነሆ በዚህ መልኩ…
የፍቅር ደብዳቤውን ያሰናዳው ታታሪ ካድሬ ከዚህ በፊት ቁጥር አንዱን በአውራምባ መፅሔት፣ እንዲሁም ቁጥር ሁለቱን ደግሞ በአውራምባ ጋዜጣ ላይ ታትመውለታል። የዛሬውም የነዛ ተከታይ መሆኑ ነው። እሱም ይበርታ ይበርታ እና ይፃፍ ፤ እርስዎም ይበርቱና ያንብቡለት!
ይድረስ እንደ ሰማህታት ሀውልት በልቤ ውስጥ ለተተከልሽ፣ እንደ መደበኛ ግምገማ ሁሌ ለምታስጨንቂኝ፣ እንደ ድርጅታችን አርማ ዘወትር ለምትታይኝ፣ እንደ ውሎ አበል ለምትናፍቂኝ ውድ ፍቅሬ፤ ለጤናሽ እንደምን አለሽ? መቼም የተዘረጋው የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም እያለ እንከን ያጋጥምሻል ብዬ አላስብም!
የኔ እመቤት እኔ ከድርጅታዊ ስራዬ ጎን ለጎን፤ ዘወትር አንቺን ማሰብ እና ስለ አንቺ መጨነቅ ኦቨር ታይም የማልጠይቅበት በራስ ተነሳሽነት የማከናውነው የየዕለት ተግባሬ ሆኗል።
የኔ ውድ ይሄን ሰሞን ደግሞ ለምን እንደሁ እንጃልኝ ከእጄ የምታመልጪኝ እየመሰለኝ ስጨነቅ እና ስጠበብ ከርሜልሻለሁ።
ያስያዝሽኝ ፍቅር ህዝባዊ መሰረት እንዳለው ፓርቲያችን የጠነከረ ነው። ቢሆንም ከአንቺ ዘንድ ያለውን ቁርጠኝነት እስከ አሁን ባለማወቄ የተነሳ እሰጋለሁ። ከአሁን አሁን የኪራይ ሰብሳቢነት ባህርይ የተጠናወታቸው ግለሰቦች ወስደው ለግላቸው ያደርጓት ይሆን? ብዬ እጨነቃለሁ።
ያው አንቺም እንደምታውቂው በአሁኑ ግዜ የሁላችንም ዋነኛ ችግር ሙሰኝነት፣ ግለኝነት እና ኪራይ ሰብሳቢነት ነው። ለሰዎች ያለማሰብ ለህብረተሰቡ ያለመጨነቅ የዘቀጠ አሰራር በየቦታው ተንሰራፍቷል። ታድያ ምድረ ኪራይ ሰብሳቢ እንደ መሬት ወረራ ሊቀራመትሽ የሞት ሽረት ትግል ሲያደርግ እየታየኝ ከአሁን አሁን አጣት ይሆን ብዬ እጨነቃለሁ።
የኔ እመቤት ነጋ ጠባ በስስት ነው የምመለከትሽ። በሀገሪቱ ላይ የሚነሳ ማነኛውም ጉምጉምታ አንቺን የሚያሳጣኝ እየመሰለኝ ስጨነቅ ብትመለከቺኝ ታዝኚልኝ ነበር። ጋዜጠኞች የሚያስቡት፣ ፖለቲከኞች የሚናገሩት፣ መምህራን የሚጠይቁት ሁላ እኔ እና አንቺን ለማለያየት ታስቦ ነው ስል እጨነቃለሁ። የኔ ቆንጆ የአወሊያው ሰላት፣ የዋልድባው ሱባኤ ሳይቀር እኔን ከአንቺ ለመነጠል ሆን ተብሎ የሚጠነሰስ ሴራ እየመሰለኝ ስጋቴ እንደ ዋጋ ግሽበቱ ከእለት እለት እየጨመረብኝ ነው።
እውነቱን ለመናገር አንዳንድ ግዜ ሰዉን በሙሉ በአሸባሪነት ክስ ዘብጥያ አውርጄ ብቻችንን የምንኖርባት ምድር ለመፍጠር እመኛለሁ።
አበዛኸው አትበይኝና ማንም እንዲጠጋሽ አልፈልግም። እንኳንስ ሌላ ቀርቶ ጥቃቅን እና አነስተኛ ማህበራት፣ የወጣቶች እና ሴቶች ሊግ፣ እንኳን አንቺን በነፃነት እንዲያቅፉብኝ አልሻም። እኔው ማህበር ልሁንሽ የኔ ቆንጆ፣ እኔው ላደራጅሽ የኔ እመቤት፤ እኔው ልቀፍሽ የኔ ሸጋ። እመኚኝ እሺ ካልሽኝ፤ በአጭር ግዜ መካከለኛ ፍቅር ካላቸው ግለሰቦች ተርታ እንሰለፋለን።
እሳሳልሻለሁ።
ለዚህም ነው፤ ተሳክቶልኝ ከአንቺ ጋር ግንባር ፈጥረን አብረን መኖር እስክንጀምር ድረስ ማንም እንዳያይብኝ፣ ማንም እንዳይረብሽብኝ፤ ብድር እና ቁጠባ ተቋም ውስጥ ላስቀምጣት ይሆን…? ብዬ የማስበው።
እውነቴ ነው የኔ ቆንጆ እንደምታውቂው፤ ከለበስኳት ሱፍ እና ከጥቂት መፅሀፎቼ ውጪ የሚቆጠብ ገንዘብ የለኝም። ሀብቴ አንቺ ነሽ። አንቺኑ ልንከባከብ፤ አንቺኑ ለዘላለም እንድትቆይ ክፉም እንዳይነካሽ፤ በቁጠባ ባንክ ላስቀምጥሽ። እናም ከጫጫታውም ከግርግሩም የፀዳሽ ሁኚልኝ።
አረ የኔስ ስስት ለጉድ ነው፤ ሰሞኑን ያ ቴውድሮስ ካሳሁን ያወጣው አዲስ ዘፈን ተለቆ፤ ከተማዋን የግሉ ጭፈራ ቤት አስመስሎት የለ? እናልሽ ፍቅሬን በሙዚቃ ሊበጠብጡብኝ ነው እንዴ? ብዬ ለመላው የከተማ ነዋሪ ሙዚቃውን እንዲቀንሱ መመሪያ መስጠት ሲያሰኘኝ ሰንብቶልሻል። እውነቴን ነው የኔ ቆንጆ አንቺ ካልሽኝ አደርገዋለሁ። አንቺን ለመጠበቅ እንኳንስ ሙዚቃ ወንዛ ወንዙን ሁሉ እገድባለሁ።
አረ ሳልነግርሽ በቅርቡ ጓደኞቼ የዳቦ ስም አውጣላት ብለው አበሳዬን ሲያሳዩኝ ነበር። እንደ አቅጣጫ፤ ሳንጋባ የዳቦ ስም ሊኖር እንደማይችል ግንዛቤው አለኝ። ነገር ግን እውነትም ከወዲሁ ቅደመ ዝግጅት ባደርግ አይከፋም ብዬ አንዳንድ ስሞችን መርጨልሻለሁ።
ሚሊኒየም አበባ
ልክ አንቺን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር እንዳዋልኩ ያኔ ለእኔ አዲስ ጊዜ፤ አዲስ ዘመን እንደመጣልኝ እቆጥረዋለሁ። ያ ግዜ ግን መቼ ይሆን…? በአስተማማኝ ሁኔታ እጄ ላይ ሆነሽ ለሚቀጥሉት አርባ እና ሃምሳ… አረ ያንሳል መቶ አመታት አብረን እንድንኖር እፈልጋለሁ።
ቦንድ አለሜ
ይህንን ስም የመረጥኩልሽ ልማት ላይ ያለሽን ቁርጠኝነት አሳምሬ ስለማውቅ ነው። “እኔ ለአባይ በገንዘቤም በጉለበቴም ዘራፍ እላለሁ!” ያልሽ የልማት አርበኛ መሆንሽን መቼ አጣሁት? ከዛም በላይ ግን አንቺ ማለት ዛሬ በቁጠባ ባንኬ ያስቀመጥኩሽ እና ነገ የምመነዝርሽ ሀብቴ መሆንሽን ለማመላከት “ቦንድ አለም” ብዬሻለሁ።
ህዳሴ ወርቅ
አንቺ ለእኔ አዲስ ህይወት ነሽ። ባለፉት ጨቋኝ ሴቶች ከፍቅር ልማት ርቆ የቆየው ልቤ በአንቺ እንደሚያገግም አዲስ ራዕይ ይታየኛል። እንግዲህ መቶ ፐርሰንት የእኔ ከሆንሽ ከዚህ በላይ ህዳሴ ከየት ይመጣል?
የኔ እመቤት ይሄ ብቻ አይምሰልሽ በርካታ ስሞችን አዘጋጅቼልሻለሁ። “ግድብ ነሽ፤ ሽብር ይራቅ፣ ልማቴ፣ ሊዝ አዋጄ…” ምን ያላልኩሽ አለ! የአንቺን ይሁንታ ብቻ ላግኝ እንጂ ያዘጋጀኋቸውን ስሞች በሙሉ ከነ ምክንያቶቼ ዘርዝሬ እነግርሽ እና አሳታፊ በሆነ መልኩ ተወያይተንበት አንዱን እናፀድቃለን። በአካሄዴ እንደምትደሰቺ ባለ ሙሉ ተስፋ ነኝ።
እመቤቴ፤
በየ አቅጣጫው የተነሱ ፀረ ፍቅር ሃይሎች በተቀነባባረ መልኩ ሊያለያዩን እንደሚያሴሩ አውቃለሁ። አንቺም ይህንን ግንዛቤ ልትወስጂ ይገባል። ማንም ወደዳጅ መሳይ መጥቶ ጥገኛ እንዳይሆንብሽ ጥንቃቄ አድርጊ። ዘንድሮ ማንም የማይታመንበት ሁኔታ ነው ያለው።
ውዴ
እንደምንም ብዬ አውራ ፓርቲሽ ሆኜ ለዘለቄታው አብሬሽ መኖር እስክንጀምር ድረስ ራስሽን ከኒዮ ሊበራል ሀይሎች ጠብቀሽ እና በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ሀይማኖትሽ ፀንተሽ እንደምትጠብቂኝ ዘጠና ዘጠኝ ነጥብ ስድስት በመቶ እርግጠኛ ነኝ!
ከሰላምታ ጋር!
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 3 Comments »
Thursday, April 19th, 2012
የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የሆነው ተመስገን ደሳለኝ “በአንዷለም አራጌ፣ እስክንድር ነጋ እና ናትናኤል መኮንን ላይ ያቀረብከው ፅሁፍ በፍርድ ሂደቱ ጣልቃ መግባት ነው” ሲል አቃቤ ህግ በከሰሰው መሰረት ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረበ።
ልደታ በሚገኘው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሶስተኛ ምድብ ችሎት ዛሬ ጠዋት የተከሰሰበትን እንዲያስረዳ ቀርቦ የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን በችሎቱ በተገኘበት ወቅት ከተጠበቀው በላይ ሰው በመምጣቱ ችሎቱ ሰፋ ወዳለ አዳራሽ እንዲቀየር ተደርጓል።፡
ተመስገን መከላከያውን በኮምፒውተር ታይፕ አድርጎ ቢያቀርብም “ጥቅጥቅ ያለ ፅሑፍ በመሆኑ አይነበብም እና አስተካክለህ ተመለስ” ተብሎ ለከሰዓት በኋላ ተቀጥሯል። እንደ ምንጬ ገለፃ ከሆነ ተመስገን ፅሑፉ አይነበብም ባሉት ግዜ “እኔ ይነበብልኛል ላንብብላችሁ” ብሎ ፍርድ ቤቱን በትህትና ጠይቆ ነበር። ነገር ግን የተመስገን “ላግዛችሁ” ጥያቄ ውድቅ ሆኗል።
በፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ላይ የቀረበበት ክስ እንደሚለው ከሆነ በፍርድ ቤት የተያዘ ነገር ላይ ጣልቃ ገብቶ ዘገባ ማቅረብ “ነውር” መሆኑን፤ የሚያስጠይቅም እንደሆነ ያትታል።
በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይህንኑ በፍርድ ቤት የተያዘ የእነ አቶ አንዷለም አራጌ ጉዳይ ላይ “አኬልዳማ” የሚል ፊልም ሰርቶ “አሸባሪ” እያለ ሲፈርጃቸው እንደነበር ይታወቃል። እርሱ ብቻም አይደለም፤ አቶ አንዷለም አራጌ፤ “ይህ ጉዳይ በህግ አግባብ ትክክል ባለመሆኑ የፍርድ ሂደቱ ሳያልቅ እንደ ወንጀለኛ የቆጠረን ኢቲቪ ይጠየቅልን” ብለው አመልክተው እንደነበረም ይታወቃል። አሁንም ይህ ብቻ አይደለም፤ ኢቲቪን ማንም ፍርድ ቤት እንዳላቀረበውም ይታወቃል። (የማይታወቅ ከሆነም አሁን ይታወቅ)
በመጨረሻም 1
የፍትህ ሳምንት ክብረ በዓል ከዛሬ ጀመሮ ለአንድ ሳምንት እንደሚከበር ትላንት ነግሬያችኋለሁ። እንዳልኳችሁ በኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓቱ በጣም ተሻሽሏል።
በመጨረሻም 2
ትላንት ተመስገን በፌስ ቡክ ገፁ ላይ እንዳወጋን ፍትህ ለህትመት በምትገባበት ቀን ዘወትር ሀሙስ መብራት ይጠፋል። እንደ ተሜ ገለፃ “መብራቱን ማን እንደሚያጠፋው ከፈጣሪ በስተቀር የሚያው የለም።” እንደኔ ጥርጣሬ ደግሞ ባልቦላውን የሚመልሰው የኤልፓ ሰራተኛ እና አለቃውም እንደሚያውቁ እገምታለሁ።
እዝችው ላይ ይህንኑ አጋጣሚ አውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ላይ በምጫጭርበት ወቅትም አስታውሳለሁ። ብዙውን ግዜ አውራምቦች አርብ አርብ “መብራት ተረኛ ነበሩ” ይሄ ነገር ቢሮ በቀያየሩ ቁጥር ሲከተላቸው እንደነበረም ትዝ ይለኛል። ያኔ በየዋህ ልቦና ነገሩ “የቤት ጣጣ” ይመስለኝ ነበር!
አሁን በአዲሳባ ገበያ ላይ “አርብ አርብ ይሸበራል ኢየሩሳሌም” ብላ በዕለተ ጁምአ ብቅ የምትለው ፍትህ ጋዜጣም በየ ሀሙሱ መብራት እየጠፋባት ተቸግራለች። ባለፈው ሳምንት መብራቱን ያጠፋው ሰውዬ የህንፃውን በሙሉ ማጥፋት ሲገባው የፍትህን ለይቼ አጠፋለሁ ሲል ከፍትህ ዋና ቢሮ ጋር የማይገናኘውን የመፀዳጃ ቤቱን መብራት ስቶታል። በዚህም ምክንያት ፍትህ መፀዳጃ ቤት በር ላይ ታይታለች።
ይሄንን የቤት ጣጣ ማለት ከባድ ነው… “የመንግስት ጣጣ!” ሳይሆን አይቀርም!
አሽሙረኞችም ብለዋል “እነሆ ፍትህን ከመፀዳጃ ቤት ደጃፍ የጣላችሁ እናንተ የፍትህ ሳምንትን ማክበር ይቻላችኋልን?”
Filed under: Uncategorized

Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | No Comments »
Wednesday, April 18th, 2012
ያው እንደሚታወቀው ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ፍቅር ከወደቅሁኝ ቆይቻለሁ። ስለዚህ ነጋ ጠባ ኢቲቪን ብጠቅስብዎ አየሰልቹ።
ዛሬም “ቸር ያሳደርከኝ ቸር አውለኝ፣ ከተናግሮ አናጋሪ አገናኘኝ” ብዬ ፀሎት ካደረስኩ በኋላ መጀመሪያ ያገኘሁትት የኢቲቪ ዜና አንባቢን ነበር። ባትሰማኝም “ደህና አደርሽ እግዚአብሄር ይመስገን” ብዬ ተቀበልኳት። እርሷም ዜናዋን ቀጠለች።
“የፍትህ ሳምንት በኢትዮጵያ ሊከበር መሆኑ ተገለጠ…” አለችኝ። እውነትሽን ነው? ፍትህ …ፍትህ… ፍትህ የቱ…? ብላት ግዜ “አቶ ወርቅነህ ገበየሁ እንደገለጡት ከሆነ የፍትህ ስርአቱ በሀገራችን እየተሻሻለ መጥቷል።” ስትል ጨመረችልኝ። እሰይ ከተናግሮ አናጋሪ አገናኘኝ ብዬው አይደል እንዲህ ነው እንጂ ጌታዬ ተመስገን ብዬ የፍትህ ስርዓቱን በረከቶች እንዳመጣልኝ መቁጠር ጀመርኩ።
አንድ
የጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ልጅ “ፍትህ ውብሸት” ይባላል። አራት አመት ቢሞላው ነው። አባቱ “አሸባርከን” ተብሎ ታስሯል። ውብሸት በታሰረበት ወቅት አቶ ዘላለም፣ ሂሩት ክፍሌ እና ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙም አብረው ታስረዋል።
እናም በተሻሻለው የፍትህ ስርዓት መሰረት አስራ ምናምን አመት እስር እንዲሁም፤ የቦንድ መግዣ ከሰላሳ አምስት እስከ ሃምሳ ሺህ ብር ቅጣት ተጥሎባቸዋል። ታድያ በቅርቡ ምን ሰማሁ መሰላችሁ። ለነዚህ ወዳጆቻችን መፅሀፍ ወደ ቃሊቲ ብትልኩላቸው፤ ከመግባቱ በፊት ለዚሁ ስራ የተመደበ ሰው “ሙልጭ አድርጎ” ያነበዋል። ከዛም በውስጡ ምንም ክፉ ቃል አለመኖሩን ካረጋገጠ በኋላ ያሳልፍላቸዋል። እንዲህ ነው እንጂ የፍትህ ስርዓት መሻሻል ብለው ይከተሉኝ። (እዚህ ላይ ርዮት አለሙ ጡቷ አካባቢ እየተሰማት ላለው ህመም ህክምና ጠይቃ “ፓራሲታሞል ይበቃሻል” ተብላ በህመም ስትሰቃይ “አረ የፍትህ ያለ” እያለች እንደነበር ማንሳት እችል ነበር ግን ገና በቁጥር አንድ እንዲህ ያለ ሀዘን አላሰማዎትም ብዬ ነው)
ሁለት
ወጣቱ ፖለቲከኛ ናትናኤል “አሸባሪ” ተብሎ ከታሰረ በኋላ በምርመራ ላይ የደረሰበትን ለፍርድ ቤቱ አቅርቦ ነበር።
ርቃኑን በማድረግ እጁን ወደላይ አስረው ቀዝቃዛ ውሃ በላዩ ላይ እየተቸለሰበት ለሶስት ቀናት ምግብ ተከልክሎ መከራውን ሲያይ እንደከረመ። ለፍርድ ቤቱ ሲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ምን አለው… “እንደው ከጀመርክ እናስጨርስህ ብለን እንጂ እኛ ይሄንን ልንሰማ አልተሰየምንም” ብሎት እርፍ። ፍክንያቱም የፍትህ ስርዓቱ ተሻሽሏላ።
ሶስት
አቶ አንዷለም አራጌ በቃሊቲ መታሰሪያ ቤት ታስሮ የከሳሾቹን ፍርድ እየተጠባበቀ ይገኛል። በኢትዮጵያ ህግ መሰረት ፍረደኛ ሰው ፍርዱን ከሚጠባበቅ ሰው ጋር አይቀላቀልም።
ለእነ አንዷለም አራጌ ሲሆን ግን የፍትህ ስርዓቱ ይሻሻላል። በዚህም መሰረት በአደገኛ ወንጀል አደገኛ ፍርድ የተፈረደበት አደገኛ ሰው እነ አንዷለምን ተቀላቀላቸው። ከተቀላቀለም በኋላ አደገኛ በሆነ መልኩ አቶ አንዷለምን ደበደው። የፍርድ ቤቱ ምላሽ ምን እንደሆነ አልሰማንም! “የፍትህ ስርዓቱ መሻሻል ውጤት ነው” መባሉ ግን አይቀርም።
አራት
ዜና አንባቢቱ እንደነገረችኝ ከሆነ የፍትህ ስርዓቱ ተሻሽሏል። ብለው የተናገሩት የፌደራል ፖሊሱ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ ናቸው። እኒህን ሰው በምን መሰላችሁ የማስታውሳቸው…? ያኔ ገና መንግስት፤ “ሽብርተኝነት ሽብርተኝነት” መጫወት ከመጀመሩ በፊት እስክንድር ነጋን ቢሯቸው ድረስ በፖሊሶች አሳግተው ወሰደውት ነበር። ልብ አድርጉልኝ ፖሊሶቹ መጥሪያ ወረቀት እንኳ አልያዙም። እንኳንስ ወረቀት ለመጥሪያ የሚሆን ፉጨትም አላፏጩለትም። እስክንድር ሀገር ሰላም ብሎ ቁጭ ካለበት ኢንተርኔት ካፌ መጡ አንጠልጥለው ሜክሲኮ አደባባይ ከሚገኘው አቶ ወርቅነህ ቢሮ ወሰዱት። ታድያ እርሳቸው ምን ቢሉት ጥሩ ነው…?
“በዘጠና ሰባቱ ምርጫ የደሀ ልጅ ተገድሏል። አሁን ግን የደሀ ልጅ አይገደልም። አንድ ነገር ኮሽ ቢል መጀመሪያ ርምጃ የሚወሰደው አንተ ላይ ነው። እርምጃው እስር እንዳይመስልህ እንደፋሀለን” አላሉትም መሰላችሁ! አይገረሙ ይሄ የፍትህ ስርአቱ መሻሻል መገለጫ ነው።
እንግዲህ ሰሞኑ የፍትህ ሳምንት በኢትዮጵያ የሚከበርበት ሰሞን ነው። ልብ አድርጉ የሚቀበርበት አይደለም ቀብሩ ትንሽ ቆይቷል። እናም መልካም የፍትህ ሳምንት ልመኝልዎት። እንዲህ ነው እንጂ ስላቅ አይሉኝም!
በመጨረሻም
ትላንት ጠቅላይ ሚኒስተሩ ስለ ኑሮ ውድነቱ በአንዲት ወይዘሮ የፓርላማ አባል የተጠየቁ ግዜ “የዋጋ ግሽበቱን ከሚያባባብሱት ነገሮች መካከል የአለም ነዳጅ ዋጋ መጨመር እንደ ምሳሌ ጠቅሰዋል። ከዚህ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአንድ የተቀናቃኝ ፓርቲ አባል “የነዳጅ ድጎማ ለምን ቀረ?” ተብለው ሲጠየቁ “እኔ እስከማውቀው ድረስ ሰማንያ አምስት በመቶ የሚሆነው ህዝብ በእግሩ ነው የሚሄደው። ነዳጅ የሚጠቀሙት ሀብታሞች ናቸው ስለዚህ የነዳጅ ዋጋ በገበያው ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል ብዬ አላምንም። ስለማላምንም አልደጉምም” በማለት ተናግረው ነበር።
እኔ የምለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ የስራ ማስታወቂያ ማውጣት ያለባቸው አይመስላችሁም? ምን አይነት በሉኝማ… የስራ መደቡ መጠሪያ “አምና የተናገሩትን ዘንድሮ አስታዋሽ።” ልዩ ችሎታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲናገሩ አቤት ውሸት ብሎ የማይሳቀቅ!
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 5 Comments »
Tuesday, April 17th, 2012
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ዛሬ ማብራሪያ ሰጥተው ነበር።
ብቸኛው የተቀናቃኝ ፓርቲ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በርካታ ጥያቄዎችን አንስተውላቸው ነበር።
ከጥያቄዎቹ መካከልም ስለ ፖለቲካ ምህዳሩ፤
ፓርቲያቸው በይፋ ስብሰባ ባደረገበት ወቅት ኢቲቪ የቀረፀውን ዋቢ በማድረግ “በህቡዕ በማሴር” ተብለው አባላቶቻችን እና ደጋፊዎቻችን ተከሰውበት እስር ቤት ይገኛሉ፣
ስብሰባ ለማድረግ አዳራሽ አከራዮች “ለሰርግ ካልሆነ በስተቀረ አታከራዩ ተብለናል” ብለው ከልክለውናል።
በዚህ ላይ ማብራሪያ ይሰጠኝ ያሉ ሲሆን በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ደግሞ፤
ከደቡብ ክልል ስለተፈናቀሉ ዜጎች የክልሉ ፕረዘዳንት “አንድም ሰው አልተፈናቀለም” ብለው ተናግረዋል በአይናችን ያየናቸው እርስዎ ፅ/ቤት አቤት ለማለት መጥተው ፀሀይ ተንቃቅተው በኋላም በመኪና ተጭነው የተወሰዱ ዜጎች “አንድም ሰው” አይደሉም ወይ?
ከደምወዝ ጋር በተያያዘ መምህራን ተቃውሞ ሲያሰሙ ገሚሱ ከስራ ተግዷል ገሚሱ ማስፈራሪያ ደርሶበታል። እንደዚህ አይነት “ሆድ የባሰው” መምህር ይዘን ስለ ትምህርት ጥራት ማውራት እንችላለን ወይ?
የሚሉ ጥያቄዎችን ጠይቀዋለው።፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩም አብዛኛዎቹን የአቶ ግርማ ሰይፉን ጥያቄዎች በመላ በመላ አልፈዋቸዋል። (የእድሜ እና የስልጣን እኩያዬ ቢሆኑ ኖሮ አጭበርብረው አልፈዋቸዋል እል ነበር)
መምህራኑን በሚመለከት በሰጡት ምላሽ ግን “የማስተማር ስራው በተቋረጠ ወቅት ከወላጆች እና ከተማሪዎች ጋር ውይይት አድርገን ነበር። “በዛን ግዜም መምህራኑ ቀድሞውንም እንዲባረሩልን አቤት ስንል ነበር” የሚል አስተያየት ከወላጆች እና ተማሪዎች አግኝተናል።” ብለዋል። በዚሀም አላበቁም “እነዚህ ከአምስት መቶ እስከ አንድ ሺህ የሚደርሱት መምህራን በመምህርነት አልሳካ ሲላቸው ሌላ አማራጭ ለመሞከር ያሰቡ ናቸው” ሲሉ አብጠልጥለዋቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ግርማ ሰይፉን እንዲሁም መመህራኑን “ጭማሪው የደሞዝ ጭማሪ ሳይሆን የእርከን ማሻሻያ መሆኑ ስላልገባችሁ ነው” ሲሉም ተችተዋል።
በዚህም አንዳንድ አስተያየታቸውን የሰጡ መምህራን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ጠብቀን ማረሪያ አግኝተናል ብለዋል።
በነገራችን ላይ (አዲስ ነገር ጋዜጣ ናፈቀችኝ መስፍኔ በሚፅፋቸው ፅሁፎች ጣልቃ አነስ ያለች በነገራችን ላይ የምትል የጨዋታ “ቦነስ” ነበረችው። ሰላም መስፍኔ! ሰላም አዲስ ነገሮች)
ስቀጥልም በነገራችን ላይ
የመምህራኑ ጥያቄ ባለፉት ግዚያት በተደጋጋሚ እንደገፁልን የኢቲቪ የተጋነነ ዘገባ እንጂ የደሞዝ ማሻሻያው አነሰ አላነሰ አይደለም። ኢቲቪ ሆዬ “መምህራኑ ህይወታቸውን የሚቀይር ገንዘብ ተጨመረላቸው” ብሎ በዘገበ በነጋታው አካራዮች አከርካሪ የሚሰብር ጭማሪ አደረጉብን እናም ዘገባው ይስተካከል ነው ያሉት። ካላመናችሁኝ ድጋሚ አንዱን የአዲሳባ ወይም የአማራ ክልል መምህር ጠይቁት።
በመጨረሻም 1
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው የፓርላማ ስብሰባቸው በማሳቁ በኩል ብዙም አልተሳካላቸውም። በዚህም ሳቅ ጨዋታ ጠብቀው የሄዱ የፓርላማ አባላት እጅጉን ተከፍተዋል አሉ። እንደውም አንዳንዶች “ካላሳቁ ይልቀቁ” ሲሉ አጉረምርመዋል ሲል ታማኝ ያልሆነ ምንጭ ሹክ ብሎኛል። እዝችው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ሶማሊያ ሲናገሩ “እኛ ሶማሊያ እንደገባን የሶማሊያ ህዝብ ጫት መቃም ጀምሯል።” በማለት በኩራት ሲናገሩ የሰማ አንድ ወዳጃችን “እንዴት ነው ነገሩ ለማቃቃም ነበር እንዴ የሄዳችሁት?” ሲል የማይመለስ ጥያቄ ጠይቋል።
በመጨረሻም 2
“የግድብ ስራው ተቋረጠ” በሚል አጭር መረጃ አድርሻችሁ ነበር። እኔማ “እስቲ አንዳንዴ እንኳ ጥሩ ወሬ አውራ መንግስታችንን አመስግንልን” ለሚሉ ወዳጆች ጥሩ አጋጣሚ አገኘሁ ብዬ ተደስቼ ነበር። ምን ዋጋ አለው ዌብ ሳይቶቹ ለሶስት ቀናት ተከፍተው የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት ደግመው ተከርችመዋል። አሉ! በቀደመው ጨዋታዬ ላይ
“…ስለ ኢትዮጵያ የሚያወሩ ድረ ገፆች እንደ ምንጬ አባባል “ፏ” ብለው ይታዩ ነበር። እንዴት ነው ነገሩ መንግስት ተቀየረ… ወይስ ዌብሳይቶችን ሲገድብ የነበረው ሰውዬ ደህና አይደለም? እነዚህን ጥያቄዎች እርሱ ባለቤቱ ይመልሳቸው።” ብዬ ነበር?
አዎ መልሱን እርሱ ባለቤቱ መልሶልናል። ለሶስት ቀናት ድረ ገፆቹ “ፏ” ብለው የመታየታቸው ምስጢር ገዳቢው ከአመት በዓል ጋር በተያያዘ ጥቂት ጉዳት ደርሶበት ስራውን በአግባቡ ባለመስራቱ ነበር። (ጉዳት የሚለውን ሞቅታ ብሎ መተርጎም አግባብ አይደለም) እናም እንደምንጠረጥረው ልክ በአሁኑ ሰዓት በ”ኢንሳ” መስሪያቤት “የዌብሳይት ግደባ እና ቁለፋ ዋና የስራ ሂደት ባለቤት” የሆነው ግለሰብ በግምገማ ቁም ስቅሉን እያየ እንደሚሆን ይገመታል።
እኔ የምለው ግን ምናለ ምስጋናችን እንኳ ጠፈፍ እስኪል ጠብቃችሁ ብትቆልፉት!?
Filed under: Uncategorized

Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 2 Comments »
Tuesday, April 17th, 2012
ከአቤ ቶኪቻው
ቆይ ቆይ አይደናገጡ! መጀመሪያ የቱ ግድብ? ብለው ይጠይቁ እንጂ፤ “ወይኔ ቦንዴ? ወይኔ ደሞዜ” ብለው ሀዘን አይግባዎ!
መንግስታችን አባይን ለመገደብ ከማሰቡም በፊት በትጋት ሲገድብ የነበረው ድረ ገፆችን፣ ቴሌቪዥን እና ራዲዮ ጣቢያዎችን እንደነበረ የታወቀ ነው። እንደውም አንዳንድ አሽሟጠጮች እንደሚሉት ከሆነ መንግስት ያለ ምንም ዕቅድ አባይን ልገድብ ብሎ የተነሳው፤ ድረ ገፅ እና ራዲዮ ጣቢያ በመገደብ ያዳበረውን ልምድ በመተማመን ነው ይሉታል።
ትላንት ዘላለም የተባለ የልብ ወዳጃችን በፌስ ቡክ ግድግዳው ላይ “ስጋትን ስለመግለፅ” ብሎ እንደለጠፈልን ከስቅለተ አርብ ጀምሮ ከዚህ በፊት ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ ተገድበው የነበሩ ድረ ገፆች በሙሉ ተከፍተዋል። እኔም ይህንኑ ዜና እንዲያረጋግጥልኝ በጠየቅሁት ግዜ በመሃላ አረጋግጦልኛል።
አሁን በቅርቡ ይቺን የኔዋን ምስኪን ብሎግ ጨምሮ ሎሎችም ብሎጎች ለሳምንት ያህል ወደ ወደ አገር ቤት እንዳይገቡ ታግተው ሰንብተው ነበር። የዛኔም መንግስት የግድብ ስራውን እያጧጧፈ እንደሆነ ግንዛቤ ወስደናል። (“ግንዛቤ ወስደናል” አሪፍ የካድሬ ንግግር ናት ብዙ ግዜ በገንዘብ ከሚደረጉ ስብሰባዎች በኋላ የስብሰባው ተሳታፊዎች “ገንዘብ አግኝተናል” አይሉም ግንዛቤ አግኝተናል ነው የሚሉት።)
እውነትም ታድያ ከብሎጎቹ ቀጥሎ አብዝተው ዴሞክራሲን የሚሰብኩ የፌስ ቡክ ታጋዮችም ጭምር የግድቡ ሰለባ ሆነው ነበር። እኛም በያለንበት “ጨምሯል ግድብ ጨምሯል” እያልን ስናንጎራጉር ሰንብተናል።
አሁን ግን ይኸው ከስቅለተ አርብ ያነሳ ቢያንስ እስከ ሰኞ አመሻሹ ድረስ ከዚህ በፊት ታግደው የነበሩ ስለ ኢትዮጵያ የሚያወሩ ድረ ገፆች እንደ ምንጬ አባባል “ፏ” ብለው ይታዩ ነበር። እንዴት ነው ነገሩ መንግስት ተቀየረ ወይስ ዌብሳይቶችን ሲገድብ የነበረው ሰውዬ ደህና አይደለም? ወይስ መንግስት ተፀፀተ? እነዚህን ጥያቄዎች እርሱ ባለቤቱ ይመልሳቸው።
ነገሩ ግን በዚሁ ካዘለቀው በጣም ጥሩ ጅምር ነው። እግረ መንግድ ታድያ እነ እስክንድር ነጋ ውብሸት ታዬ እና ርዮት አለሙን የመሳሰሉ ጋዜጠኞች የተገደቡበት የቃሊቲ ግድብም ቢፈርስ፤ እንዲሁም ብቸኛዋን ፍትህ ጋዜጣ እየደረሰባት ያለው “ሰፋጣ” ቢቆምላት መንግስትን “የዴሞክራሲ አርበኛ” ብለን እንሸልመው ነበር!
ከዚህ በፊት ያልኩትን አሁንም እደግመዋለሁ። የመናገር እና የመፃፍ መብት መገደብ የኤሌክትሪክ ሀይል አያመነጭም እናም በጅምሩ “መንግስቴ በርታ በርታ…” ብዬ ላዜምለት እወዳለሁ።
ወዳጄ እንግዲህ አሁን ጎግልዎ ላይ ያሻዎን ድረ ገፅ ታይፕ አድርገው ያሻዎን መረጃ ማግኘት ይችላሉ ማለት ነው። ታድያ ዛሬም ሊገደብ ስለሚችል ቀልጠፍ ቀልጠፍ ይበሉና በኢቲቪ የሚመጡ ህመሞችን ያስታግሱ!
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 2 Comments »
Saturday, April 14th, 2012
ቴዲ አፍሮ ሰሞኑን “ጥቁር ሰው” የሚል የሙዚቃ አልበም ይለቃል ተብሎ በጉጉት እየተጠበቀ ነበር። እንደሚታወቀው የቴዲ አፈሮ ሙዚቃ መልቀቅ ከኢህአዴግ ስልጣን መልቀቅ እኩል በጉጉት የሚጠብቁት ብዙዎች ናቸው። እኔም… አንዱ ሳልሆን አልቀርም።
ታድያ ቴዲ ሙዚቃውን ከመልቀቁ ከጥቂት ቀናት አስቀድሞ በርካቶች በራሱ በቴዲ ላይ ነጠላ ዜና ሲለቁ ሰምተናል። (በዚህ አረፍተ ነገር አግባብ “ዜና” ማለት ወሬ ማለት ነው። ለነገሩ በሌላ አረፈተ ነገር አግባብም ዜና ወሬ ነው ለካ!)) እናም ከነጠላ ዜናዎቹ ውስጥ አንዱ “ከኔ በላይ መንፈሳዊነት ላሳር” ያለ ግለሰብ፤ “ሙዚቃ ሀጥያት ነው!” በሚል መፈክር ከመፅሀፍ ቅዱስ ሁሉ ጠቅሶ፤ የቴዲ አፍሮን አልበም እንዳንገዛ አስጠንቅቆናል። እንደዚህ “ሀይማኖተኛ” ማሳሰቢያ ቢሆን ኖሮ” እንኳንስ የሙዚቃ አልበሙን እና ቤቱ እንኳ ስንሄድ የፎቶ አልበሙን አናይም ነበር።
ከ “አማኙ” የወዮላችሁ አዋጅ ስር በርካታ አስቂኝ አስተያየቶች ተለጥፈዋል። ከነዚህ ውስጥ አንዱ፤ “እሺ ሙዚቃ ሀጥያት ነው ካላችሁ ለምን ከፍቅረ አዲስ ወይም ከሰሜ ባላገሩ ጀምራችሁ አታውጁም ነበር?” ብሎ ጠይቋል።
እኔም በሆዴ ፍቅር አዲስስ እሺ ለባለ አወሊያ ትዘፍን ነበር፤ ሰማህኝ ደሞ ምን አደረገ? ብዬ ጠይቄ መልሱን አላገኘሁትም። እኔ የምለው ሰሜ ባላገሩ ግን “በተቀነባበረ መልኩ ሰው ገድሏል” ተብሎ ከታሰረ በኋላ የተለቀቀው ለአባይ በመዝፈኑ ነው” የሚለውን “ቡጨቃ” እንዴት ታዩታላችሁ? እንጃ… እኔ በበኩሌ አላምንም…!
ሌላው በቴዲ አፍሮ ላይ የተመለከትኩት “ነጠላ ዜና” ጥርጣሬ ወለድ ነው። አንዳንድ ጠርጣራሮች ቴዲ ከዚህ በፊት በደረሰበት እስር የተነሳ የፍርሃት ቆፈን ይዞታል። ከሚል መነሻ፤ “የቦብ ማርሊን ስዕል ደረቱ ላይ ለጥፎ ስለፍቅር ብቻ መዝፈን ጀምሯል… ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ጆሮ ዳባ እያለ ነው። በአዲሱ አልበሙም ከፍቅር ዜማ ውጪ የሚኖረው አይመስለኝም እንደዛ ከሆነ ግን…” እያለ በነጠብጣብ የሚቀጥል ማብጠልጠል ሲያብጠለጥሉት ሰሙነዋል።
ለጠርጣራም ጠርጣራ አለውና የእነዚህን ወዳጆቻችንን ንግግር “ኢህአዴግ አመሳስሎ የሰራው ነው” ሲሉ የጠረጠሩት ብዙዎች ናቸው።
በነገራችን ላይ እናት ድርጅታችን ኢህአዴግ ከምትታማባቸው ነገሮች ውስጥ ከአቅሟ በላይ ልጆች በመሰብሰብ ነው። በተለይ ደግሞ እንደ ቴዲ ያሉ ያደጉ እና የበለጠጉ ልጆችን ከእናታቸው ጉያ ነጥቃ በእንጀራ ልጅነት እንደመጠቅለል የሚያስደስታት የለም… ይባላል። (እንግዲህ ይባላል ነው ያልኩት አታኩርፉኛ…) እውነቴን እኮ ነው። እንደሰማሁት ከሆነማ፤ ለምሳሌ ቴዲ አፍሮ የህዝብ ልጅ ነው። ታድያ እናት ኢህአዴግ ምን ታደርጋለች አሉ፤ እንደምንም ብላ ከእናቱ ህዝብ አጣልታም ቢሆን ማለያየት ከዛስ…? ከዛማ ትንሽ ትንከባከብ እና ሳያስበው ኋላ ኪሷ አስገብታ ቁጭ ትልበታለች አሉ።
የዚህ የኋላ ኪስ ሰለባ ከሆኑት መካከል ሰለሞን ተካልኝ እና … እና ማን ነበር ስሙ አፌ ላይ እኮ አለ… ንዋይ ደበበ ይጠቀሳሉ ሲባል ሰምቻለሁ። (መቼም እኔ ወሬ መደበቅ አይሆንልኝ!)
እና ታድያ አሁንም ቴዲን ከእናቱ ከህዝብ የሚለይ መግለጫ በየቦታው ተለጥፎ ነበር። “ቴዲ የህዝብ እና የሀገርን ነገር ትቷል ከዚህ በኋላ የኛ መሆኑን እንጃ…” የሚል ይዘት ያለው ልጥፍ በየፌስ ቡኩ ተለጥፎ ነበር።
በዚህም ላይ ግማሹ “ቴዲ አፍሮን ድሮውንም ለአገረ ገዢነት አልመረጥነውም እናም ያሻውን ሙዚቃ ቢያቀነቅን መብቱ ነው፤ ከጣመን እንሰማለን ካልጣመን ራሳችን እናንጎራጉራለን” ብሎ ሲሟገትለት ገሚሱም ደግሞ “ሰውን ማመን ቀብሮ ብላለች ቀበሮ ብዬ ገጠምኩልህ ስማኝ ቴዲ አፍሮ” እያለ በስንኝ ቀጠሮ በተቀደደለት የፀብ ቦይ ሲፈስ ታይቷል።
ይህ በሆነ በነጋታው ነው መሰለኝ ጠቅላይ ሚኒስትራችን የቴዲን ጥቁር ሰው አልበም ከፍ አድርገው ይዘው የሚያሳይ ፎቶግራፍ በየ ኮምፒውተራችን ደጃፍ ቆሞ አገኘን። ይህም “ቴዲ በእጃችን ገባ እነሆ ከኛ ዘንድ ነው…” የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ዋና የፌስ ቡክ ስራ ሂደት ባለቤቶች የለጠፉት ሳይሆን እንደማይቀር ይገመታል።
እነሆ የቴዲ አልበም ሳይለለቅ በፊት በርሱ ላይ የሚለቀቁ ነጠላ ዜናዎች በረከቱ። እንደ ነገ ፋሲካ ሊሆን እንደ ዛሬ ግን ተናፋቂው ሙዚቃ ሲጋልብ መጣ!
ለእምዬ ምንሊክ የተዘፈነው ጥቁር ሰው!
ኢህአዴግ ይበልጡንም ደግሞ ህውሃት ሚኒሊክን እንዴት አድርገው እንደጠመዷቸው ልብ ስል አደዋ ላይ ሚኒሊክ ድል የነሱት ጣልያንን ሳይሆን ህውሃትን ነበር እንዴ? ብዬ እጠይቃለሁ። ባለፈው ግዜ እምዬ ምኒሊክን ክፉኛ የሚያንጓጥጥ መፅሐፍ ከህውሃት ወዳጆች አንዱ የሆኑ ሰው አሳትመው ነበር። በዛ ላይም እንዳየነው ከኢህአዴግ ወላጅ አባቶች አንዱ የሆኑት አቦይ ስብሀት ፀሐፊውን “እጅህ ይለምልም!” ብለው ከሞካሹ በኋላ በሚኒሊክ ላይ ዘመቻው እንደሚቀጥል ተናግረው ነበር። እኔማ ጭንቅ ቢለኝ እነዚህ ሰዎች እርሳቸውን እናሳድዳለን ሲሉ የተቀበሩበት ጉድጓድ ውስጥ እንዳይገቡ ስል እፈራላቸዋለሁ። አዎና ወዳጄ “እልህ ሳንጃ ያስነክሳል” ያሉት እኮ የኛ ሰዎች ናቸው!
የሆነ ሆኖ “ጥቁር ሰው” ሙዚቃ አፄ ሚኒሊክን ድጋሚ ያነገሰ ቢባል ይገባዋል። ሙዚቃው ሲጀምር በደቡቤዎች ዜማ ይጀምርና ሚኒሊክ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆኑ የመላው ጥቁር ንጉስ መሆናቸውን በይፋ አውጆ በአማርኛ እና በኦሮምኛ ቋንቋዎች እየተላቆጠ ይንቆረቆራል። በዚህም በርካታ የአራዳ ልጆች “ጀዲካ” እያሉ ረገዳ ጨፍረዋል። ከእልልታ ጋርም እስክስታውን አቅልጠውታል።
አሁን እንግዲህ ሰሞነ ቴዲ አፍሮ ገብቷል።
“ጥቁር ሰው” ሙዚቃ ብቻ አይደለም። ህብረት ነው። አንድነትም ነው። ነፃነትም ነው።
ውይ አፈር ስሆን ይሄ የሙዚቃ ሲዲ “አቦይ ስብሀት እና ባልደረቦቻቸው የማይደርሱበት ቦታ ይቀመጥ!” የሚል ካልተፃፈበት አደጋ አለው! እንዴት ማለት ጥሩ ጥያቄ ነው።
ባለፈው ግዜ በኮምፒውተሮቻችን እንዳየነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደዋዛ ያያዙት የቴዲ ሙዚቃ በውስጡ ሚኒልክን የሚያከብር መሆኑን ቢያውቁ በሀዘን ክልትው ይሉብናል። ቀልዴን አይደለም። “ህውሃት ከማይደርሱበት ቦታ ይቀመጥ” ተብሎ ይፃፍበት። እኔ ተናግሪያለሁ!
በመጨረሻም
የቴዲ አፍሮን ጥቁር ሰው ሙዚቃ የሰማሁት አልበሙን ገዝቼ ሳይሆን ኢንተርኔት ላይ ተለቆ አግኝቼው ነው። ሙዚቃው በርሱ ፈቃድ ይለቀቅ አይለቀቅ እንጃ። ያለ ባለቤቱ መልካም ፈቃድ የተለጠፈ ከሆነ ግን አግባብ አለመሆኑን አምኜ ንስሀ እገባለሁ። ሌሎችንም እመክራለሁ እባካችሁ ኦሪጅናል እንግዛ!
መልካም ፋሲካ ብያለሁ እንዴ… አሁን ልበላ! (አረ ባለቅኔው አትሉኝም?)
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 1 Comment »
Friday, April 13th, 2012
ትላንት ፀሎተ ሀሙስ ነበር። ቀኑን የጀመርኩት ግን በፀሎት አይደለም በሀዘን ነው። ይሄኔ ምን ሆነክ ይላል ብልህ ሰው፤ አዎ እንደርሱ ነው የሚባለው።
በፌስ ቡክ መልዕክት ሳጥኔ ፤ “አንድ ኢትዮጵያዊ ኩዌት ውስጥ በድንገት ሞቶ ተገኘ ልጁ ወደ ኩዌት ከመጣ ገና ሶስት ወር እንኳ አልሞላውም” ሲል ከወዳጆቼ አንዱ መርዶ አስቀምጦልኛል። መልዕክቱን አንብቤ እንደጨርስኩ ድብርት እና ሀዘን በላዬ ላይ ተከመረ። አጠገቤ የነበረውን ጓደኛዬን ጠየቅሁት፤ እስከ መቼ ነው በተሰደድንበት ሁሉ እንዲህ አይነት ስቃይ እና አበሳ የምናየው? አልኩት። እርሱም “ምርጫ ቢኖረው ኖሮ “መ” እልህ ነበር” አለኝ። “መ” መልሱ የለም ነው። ወይ ጣጣችን!
ከጥቂት ቁዘማ በኋላ እንደ ምንም ድብርቴን ለማራገፍ ድጋሚ ወደ ፌስ ቡክ መንደር ጠልቄ ገባሁ። በርከታ ወዳጆቼ የአመትባሉ ገበያ አሳስቧቸዋል። አንዳንዶች “በግ እናከረያለን ዶሮ ቅርጫ እናቃርጣለን…” የሚሉ ሹፈቶችን ለጥፈዋል። በርካቶችም ዘና ዘና የሚያደርጉ አስተያየቶችን ሰጥተውበታል።
የአውራምባ ታይምሱ ዳዊት ከበደ፤ “በዚህ አመት በዓል ኢትዮጵያ ውስጥ ዶሮ 250 ብር እየተሸጠ እንደሆነ ሰማሁ፡፡ ኢትዮጵያ ያላቸሁ የፌስ ቡክ ጓደኞቼ እውነት መሆኑን ታረጋግጡልኛላችሁ? ወይ ስምንተኛው ሺ!” የሚል ፅሁፍ ከጥሩ እንስት ዶሮ ጋር ለጥፎ አገኘሁት። ግማሹ “አይ ሁለት ከሃምሳ… ተጋኗል ሁለት መቶ ብር ታገኛለህ” ብሎ ሲያፅናና ሌላው ደግሞ “በሁለት መቶ ሃምሳ ዶሮ የት እንደሚገኝ ለነገረኝ ውለታ እከፍላለሁ” ብሎ እየፃፈ ተስፋ ያስቆርጣል። እኔም የተሰጡትን አስተያየቶች ከኮመኮምኩ በኋላ ለማንኛውም ብዬ የዶሮዋን ስዕል “ሴቭ” አድርጌ ጉዞዬን ቀጠልኩ።
ኢዮብ ብሃነ አንድ ግጥም ለጥፏል፤
እህል ተወደደ፣
ቅቤም ተወደደ፣
ስጋም ተወደደ፣
ፍቅር ከሀገር ጠፋ ዋጋው ተወደደ፣
ምሁር ከሀገር`ራቀ እየተሰደደ፣
ከሀገሬ ገበያ ቁጥሩም የጨመረ
ዋጋው የቀነሰ፣
የካድሬ ብቻ ነው ህዝብ እያስለቀሰ።
እንዴት ማለፊያ ግጥም ናት ብዬ መውደዴን ለመግለፅ “ላይክ” የሚለው ላይ ጠቅ አድርጌ አለፍኩ።
መሰረት ሊ የተባለች ወዳጃችን ደግሞ እንዲህ የሚል ለጥፋለች፤
“በቅርቡ በአሰሪዎችዋ ድብደባ ደርሶባት፥ ህይወትዋ በአሳዛኝ ሁኔታ በሊባኖስ ላለፈው ወ/ሮ ዓለም ደቻሳ መታሰቢያና ልጆችዋን መርጃ እንዲሆን በማሰብ ሀሙስ ሚያዝያ 11/2004 ዓ/ም ከቀኑ 11:30 ጀምሮ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል አዳራሽ ታላቅ የገቢ ማሰባሰቢያ እና የኪነ-ጥበብ ፕሮግራም ተዘጋጅቷል። በፕሮግራሙ ላይ ወጣት ገጣሚያን እንዲሁም ታዋቂ የኪነ ጥበብ ሰዎች ይገኛሉ። እርስዎም በፕሮግራሙ ላይ ታድመው እየተዝናኑ ለወ/ሮ ዓለም ደቻሳ ቤተሰብ ስተዋፅኦ ያደርጉ ዘንድ በታላቅ አክብሮት ተጋብዘዋል።”
እነዚህን ልጆች ያኑርልን! ስል በልቤ ምርቃት አወረድኩ። መሰረትን ጨምሮ የማህሌት፣ የጆማኔክስ፣ የዮሃንስ እና የታምራት ታም “መለያ ስዕሎች” ለአለም ደቻሳ ገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም የተዘጋጀ ፎቶግራፏን ያካተተ የጥሪ ካርድ ሆኖ አገኘሁት። በዛም ውስጥ ተቆርቋሪነታቸው እና ለወገን አለሁ ባይነታቸው ታየኝ። በዕውነት እናንተ ልባሞች ናችሁ እና የእናንተ አይነት ልብ የት እንደሚገኝ ለመሪዎቻችን ጠቁሙልን እስቲ ልላቸው ወደድኩ።
አሁንም የፌስቡኬን መንገድ ይዤ ቁልቁለቱን ወረድኩት…. ሌላ አሳዘኝ ወሬ።
“ኢትዮጵያውያን እህቶቻችን በስደት እና በእብደት ላይ” በሚል ርዕስ በሪያድ የሚገኙ እህቶቻችንን ስቃይ የሚያሳይ ቪዲዮ…! በጣም አሳዛኝ ነው። በአንድ ቤት ውስጥ ለመቁጠር እንደሞከርኩት ወደ አራት የሚጠጉ እህቶቻችን በአዕምሮ መቃወስ ሲሰቃዩ ተመለከትኩ። በእውነቱ ሀዘኔ በረታ “ሙዴም ተከነተ” ፌስ ቡኬም አስጠላኝ ኮምፒውተሬም “ደበረኝ” እስከመቼ ነው በየሰዉ አገር የምንሰቃየው። መቼ ነው ኢትዮጵያ ለሁላችንም የምትበቃ አገር የምትሆነው? እስከ መቼ ድረስ መልሱ “መ” ሆኖ ይቀጥላል? ብዬ ከኮምፒውተሬ ገለል አልኩኝ።
ከተወሰኑ የቁዘማ ሰዓታት በኋለ ኮምፒውተሬን ከፈትኩ፤ ኢንተርኔቴን አገናኘሁ። ወደ ፌስ ቡክ መንደርም ድጋሚ ጎራ አልኩ።
“እምዬ ኢትዮጵያ የጀግኖች እናት እስቲ ፈልጊልኝ የሚከራይ ቤት” የሚል ፅሁፍ ተለጥፎ አየሁ። ይህንን ፅሁፍ ከዚህ በፊትም አይቼዋለሁ። እውነትም የሚከራይ ቤት እንኳ ኢትዮጵያችን ብታገኝልን ቢያንስ በየ አረብ ሀገራቱ እህቶቻችን አየሰቃዩም ነበር። ብዬ እያሰብኩ… ወረድ አልኩ። አሁን አሪፍ ዜና አየሁ።
እስክንድር ነጋ ታላቅ አለም አቀፋዊ ሽልማት አገኘ!
ታዋቂው እና ተወዳጁ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ “ፔን ኢንተርናሽናል” ከተባለ ድርጅት PEN/Barbara Goldsmith Freedom to Write Award. የተባለውን ሽልማት አገኝቷል።
እንደሚታወቀው እስክንድር ነጋ በአሁኑ ግዜ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ይገኛል። እንደማይታወቀውም እስክንድርን ከባለቤቱ ከልጁ እና ከጥቂት የተመዘገቡ ሰዎች ውጪ በቃሊቲ ማንኛውም ሰው ሄዶ ሊጠይቀው እንደማይችል ሰምተናል።
እስኬው ይህንን ሽልማት ማግኘቱ ሲያንሰው ነው። በሸላሚዎቹ መግለጫ ላይ እንደተገለፀው እና እኛም ስናየው እንደኖርነው እስክንድር እያንዳንዷን ቃላት ሲፅፍ ሰዎቻችን ደግሞ እስከ ሞት የሚያደርስ ጉንጉን እንደሚሸርቡለት ያውቃል። ይህንን ተጋፍጦ ነበር የሚፅፈው። በነገራችን ላይ እስክንድር ስለ ፃፈ ብቻ ከሰባት ግዜ በላይ እስራት ደርሶበታል። እርሱ ግን ወይ ፍንክች! አሁንም ያው ነው!
አንበሳ … ቀነኒሳ ሳይሆን እስክንድር ነው። ብንልስ… (ቴዲ ቢሰማ አስተካክሎ ይዘፍናት ይሆን…?)
አሁን መሸ
ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ጠራሁት “…እንኳንስ ጠርተውኝ…” ብሎ ብቅ አለ። የዜና ሰዓት ደርሷል። የዛሬው ዜና አቅራቢ ያ አሽሟጣጩ ነው። እርሱ ሰውዬ ይገርመኛል እንደምን አመሻችሁ… ሲል ጠረቤዛውን በግንባሩ ገጭቶ ነው። ከዚህ በፊት “የመተጣጠፍ ብቃትህን እናደንቃለን ቢሆንም ግን ማጎብደዱ ሲበዛ ሽሙጥ ይመስላልና በቅጡ አድርገው” ብለን ለማስመከር ሞክረን አልተሳካልንም።
ዜናው ቀጠለ “በዛሬው እለት ፀሎተ ሀሙስን አስመልክቶ የትህትና ምሳሌ የሆነው የእግር ማጠብ ስነ ስርዓት ተካሄደ። ብፁህ አቡነ ጳውሎስ የካህናትን እግር አጥበዋል” ብሎ የአቡኑን ትህትና ሊያሳየን ሞከረ።
እኔም በሀሳቤ የአቡኑ በርካታ ትህትናዎች መጡብኝ…
ትህትና አንድ
የዛሬ ስንት አመት እንደሆነ እንጃ በመስቀል አደባባይ የደመራ ስነ ስርዓት ይከናወን ነበር። ታድያ አባታችን ፀሎት እንዲመሩ መነጋገሪያ “ማይክራፎን” ተሰጣቸው። እሳቸውም የዛኔ በምን ተበሳጭተው እንደነበር እንጃ “እስቲ ዞር በሉልኝ ምድረ ጭቃ!” ሲሉ በቀጥታ ቴሌቪዥን ተላለፉ። እኔም ለርሳቸው “ትህትና” አምስት ሳንቲም እስከማክል ድረስ ተሸማቀኩላቸው።
ትህትና ሁለት
እኔ የምለው ቦሌ መድሃኒያለም ልንሳለም ስንሄድ ዛሬም መጀመሪያ የምንሳለመው የብፁህ አባታችንን ሀውልት ነው አይደል? ከትህትናቸው ብዛት የገዛ ሀውልታቸውን መርቀው የከፈቱ ብቸኛ ሰው “አባታችን” መሆናቸው ነው። (በነገራችን ላይ አቡነ ጳውሎስን ዋና ዋና የኢህአዴግ ሰዎች “ብፁህ አባላችን” ነው የሚሏቸው ሲባል ሰማሁ። እውነት ነው እንዴ እስቲ አጣሩልኝ! (ይቺ እንደ ለከፋ ትቆጠርልኝ))
በመጨረሻም
ስለ ስቅለት
ስለ ስቅለት ትንሽ ለማለት ሳስብ ስብሀት ገብረእግዚአብሄር ትዝ አለኝ አንድ ወቅት ይህንን አውግቶ ነበር እስቲ እናስታውስ፤
ኢየሱስ መስቀሉን ተሸክሞ ወደ ጎልጎታ ተራራ እየሄደ ነበር። መንገድ ላይ አንድ የዛፍ ጥላ ያለበት ቦታ አገኘ። ይሄኔ ትንሽ ፋታ ባገኝ ብሎ ርምጃውን ቀስ አደረገ። ታድያ ዛፉ ጥላ ስር አንድ ባለ ሱቅ ነበር እና በግርግሩ ገበያው እንዳይቀዘቅዝ አስቦ “ባክህ ሂድ አትንቀራፈፍብኝ” ብሎ ጌታን አመናጨቀው። ኢየሱስም ቀና ብሎ አየውና “እኔስ እሄዳለሁ አንተ ግን እስክመለስ እዚሁ ትጠብቀኛለህ!” ብሎት ሄደ። ስብሀት እንዳለን ከሆነ ያ ሰውዬ አሁንም ጭምር ሀገር እየቀያየረ ይኖራል።
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | No Comments »
Friday, April 13th, 2012
በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የትንሳኤ በዓል ሊመጣ ሳምንት የማይሞላ ግዜ ቀርቶታል። እስቲ በሰላም ያምጣውና ሌላው ቢቀር እንኳን አደረሳችሁ ለመባባል ያብቃን።
አሁን ህማማት ላይ እንገኛለን። በሀይማኖቱ የበቁ ወዳጆቻችን እንደሚነግሩን በዚህ ሰሞነ ህማማት ውስጥ ያሉ እያንዳንዱ ቀናት ክርስቶስ ስለ ሰው ልጅ የደረሰበት ስቃይ የሚታሰብባቸው ናቸው። በተለይም ኢየሱስ በአደባባይ ቆሞ ባስተማረ እና በተናገረ ግዜ የደረሰበት ስቃይ፤ ከአጓጉል ውንጀላ አንስቶ ግርፋት፣ እስራት፣ በመጨረሻም ስቅላትን ያካተተ ነበር።
ነገር ግን ከዚህ ሁሉ በኋላ እሁድ ትንሳኤ ይሆናል። ደስታም ይበዛል።
ከመንፈሳዊው ጉዳይ ፊታችንን ዘወር ስናደርግ የሚከተለውን እናገኛለን፤
ኢህአዴግ አዲሳባን እና መላውን አገሪቷን “ለሰፊው ህዝብ ጥቅም” ብሎ ከተቆጣጠረ ስንት አመት ሆነው? ግንቦት ሲመጣ ሃያ አንድ አመት ይሞላዋል። (ደህና ጎርምሶ የለም እንዴ!?) አሁንማ ሚስት አምጡ ብሏል! አይሉኝም?
ከደርግ ጋር ሲነፃፀር የኢህአዴግ በትረ ስልጣኑን መያዝ እንደ አዲስ ኪዳን የቆጠሩት ብዙዎች ነበሩ። በተለይ ለዲሞክራሲ ናፋቂዎች ትልቅ ተስፋ ፈንጥቆ ነበር። “የመናገር እና የመፃፍ ነፃነት ተከብሯል።” ተብሎ ታወጀ። እሰየው ተባለ። “ተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋም ይቻላል ተብሎ ተነገረ።” እንዲህ ነው እንጂ ብለን አደነቅን! “የነፃ ገበያ ስርዓት ተግባራዊ ይሆናል” ተባለ። እልልል… ይህንን ሁሉ አለም የሚያሳዩን እነዚህ እነማን ናቸው? የሚል ውዳሴ ጎረፈ። ህዝቤም በየ መስኩ ተሳትፎውን አሳየ።
ቀን ቀንን እየወለደ ሄደና ዛሬ ሀያ አንድ አመት ሞላን አዲስ ኪዳን ስንል ያሞካሸነውም ዘመነ ኢህአዴግም በመግቢያው ያበሰራቸውን በሙሉ ረሳቸው። ችግር ረሀብ እና እርዛትም በዙ። ነፃ ገበያም ሆነ ነፃ ንግግር ተግባር ላይ ጠፉ። ይልቁንም በአደባባይ ቆሞ መናገር ያስወነጅል ጀመር። እስራት እንግልት ምርመራውም በረከተ። በሁሉም ዘንድ ስቃዩ በዛ! በርካቶችም አሉ፤ “ህማማቱ ገባ”
እውነትም ወዳጄ ኢህአዴግ አዲሳባ ሲገባ አዲስ ኪዳን ሆኗል ካልን አሁን ያለነው በርግጠኝነት ህማማቱ ላይ ነው። ከህማማቱ ቀጥሎ ምን የሚከሰት ይመስላችኋል? እኔ ግን እላለሁ ትንሳኤ እየመጣ ነው! እናም በህማማቱ ላይ ያላችሁ በሙሉ አይዟችሁ!
ለማንኛውም ለመላው የክርስትና እምነት ተከታይ ወዳጆቼ መልካም ሰሙነ ህማማት ይሁንላችሁ! ተግታችሁ “አቤት” በሉ!
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | No Comments »
Tuesday, April 10th, 2012
አቤ ቶኪቻው
መጀመሪያ ቆይ ርዕሱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን አንቱ ያላልኩት በትህትና ጉድለት ሳይሆን ርዕሴ ቤት እንዲመታልኝ ፈልጌ ነው።
ዛሬ እና ትላንት ከደቡብ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎችን አስመልክቶ ሀሳቤን ላካፍላችሁ ሙከራ አድርጌያለሁ። እውነቱን ለመናገር እየተፈጠረ ያለው ነገር በጣም የሚያስጨንቅ ነው። ለዚህም ነው ደጋግሜ ነገሩን ማንሳቴ ወደፊትም ደግሜ አነሳዋለሁ።
ታድያ በእናት ድርጅታችን ኢህአዴግ ውስጥ “የብሎግ እና ፌስ ቡክ ጨዋታዎች አደናቃፊ ዋና የስራ ሂደት ባለቤቶች” በሰጡት አስተያየት ተነስቼ ትንሽ ጭማሪ ይዤ መጥቻለሁ። በርግጥ በርካታ ወዳጆቼ መልስ ሰጥተዋቸዋል እኔም ብጨምርላቸው ግን ክፋት የለውም።
በተለይ ዮሴፍ የተባለ ወዳጃችን ይህንን ነገር በተደጋጋሚ መጠየቄ አልተዋጠለትም መሰለኝ በፃፈልኝ አስተያየት፤
“…የሆነ የትግርኛ ምስሌያዊ አነጋገር አስታወስከኝ ”ዐሻስ’ያ ሐደ ደርፉ”ልተርጉምልህ አይደል የሞኝ ዘፈን ሁሉ ግዜ አንድ አይነት ነው እንደ ማለት ነው ነገሮችን እየደጋገምክ ስትጽፍ እንደፊትህ ( ይቅርታ የሞኝ የሚመስል ፊት ስላለህ ነው) አንተም ሞኝ እየመሰለከኝ መጣህ!”
በማለት ወርፎኛል። ይህ ወዳጄ የኢህአዴግ ቀንደኛ ደጋፊ መሆኑን በተለያዩ ሰላማዊ ሰልፎች እና ሰላም ባላቸው አበሎች ያረጋገጠ ይመስለኛል። ጎበዝ እንዲህ ነው እንጂ “እየበሉ እየጠጡ ዝም የጋን ወንድም” ከመባል ድነሃል። እናም ወዳጄ ዮሴፍ ለሚከፈለው አበል ጥሩ አገልግሎት እየሰጠ ስለሆነ ለትጋቱ ላመሰግነው እወዳለሁ።
ምን መሰለህ ዮሴፍ እንግዲህ ሞኝ ከመሰልኩህ አይቀር አሁንም ልጠይቅህ ነው። ቀጥሎም ነገሩ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ እኔም ሌሎች ደጋግመን መጠየቃችንን እንቀጥላለን! በሌላ አባባል መነዛነዛችን አይቀርም። በቅንፍ (የግድቡን ዜና እና ዜማ ያኽል ግን ሰዉ “ኤጭ አሁንስ…” እስኪለን ድረስ አይደለም)
በነገራችን ላይ የደቡቡ ፕረዘዳንት አቶ ሽፈረው ሽጉጤ የወሰዱት ርምጃ ምን ማለት እንደሆነ ገብቶሃል? ከገባህስ ትክክል ናቸው ብለህ ታስባለህ? እውነቱን ለመናገር ወዳጄ ርምጃው ገብቶህ ቢሆን፤ ቢያንስ ቢያንስ ለአቶ መለስ ህልውና ስትል ነገሩን ትቃወመው ነበር።
ከአማራ ክልል የመጡ ዜጎችን “ወደ ሀገራችሁ ሂዱ!” ብሎ ማባረር ትክክል ነው ብለህ ካሰብክ እደነቃለሁ። (አንቅሃለሁ አላልኩም። ማነቅ ከኛ ወገን አይደለችም)
“ብሄር ብሄረሰብ እጅ ለእጅ ተያይዞ አባይን ይገነባል ህዳሴን ያበስራል ወዘተ ይወዝታል…” የሚባለው ታድያ እንዴት ነው? አንዱ ብሄር አንዱ ዘንድ ሄዶ መኖር ካለቻለ እጅ ለእጅ የሚያያዙት “በብሉቱዝ” ነው? እረ እርሱም ቢሆን ተቀራርቦ መቀመጥን ይጠይቃል!
እንደኔ እምነት አቶ መለስ ዜናዊም ቢሆኑ በአቶ ሽፈራው ሽጉጤ ውሳኔ ይስማማሉ ብዬ አላምንም። ነገር ግን ተስማምተው፤ እሳቸውም “በደቡብ ክልል የሚኖሩ የሌላ ክልል ተወላጆች ወደ ሀገራቸው መዛወራቸው አግባብ ነው!” ብለው ውሳኔውን በይፋ ካደነቁ፤ ያኔ በሰፊው እፅፋለሁ። ምን ብለህ አትለኝም? አቶ መለስም ወደ እናት ሀገራቸው ኤርትራ ይሂዱ! እኔም ወደ እናት ሀገሬ አዲሳባ እመጣለሁ!
ዮሴፍ ለምን ግን ክፉ ታናግረኛለህ?
ለማንኛውም በብሎጋችን ቆይታህ ይቀጥል!
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 6 Comments »
Tuesday, April 10th, 2012
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 2 Comments »
Wednesday, April 4th, 2012
ሰሞኑን መነጋገሪያ ከነበሩት ጉዳዮች መካከል አቶ ሽፈራው ሽጉጤ የተባሉ የኢህአዴግ ባለሰይጣን (ታይፕ አልገደፍኩም ዝም ብለው ይከተሉኝ ወዳጄ) ባለስይጣኑ በሚያስተዳድሩት ክልል ሲኖሩ የነበሩ ከሰባ ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎችን “ወደ ሀገራችሁ ሂዱ” ብለው አባረዋቸዋል።
ይህንን አስመልክቶ ዛሬ በኢሜል የደረሰኝ የአንድነት ፓርቲ ልሳን የሆነው የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ በርዕሰ አንቀፁ ባስቀመጠው ካርቱን ስዕል፤ ሰውየው አቶ ሽፈራው ሽጉጤ መሆናቸው ነው… “ወደ ሀገራችሁ ሂዱ” እያሉ ዜጎቹን በመጥረጊያ ሲጠርጓቸው ያሳያል። በእናቱ ጀርባ ላይ ያለ ህፃን ደግሞ “እማዬ ሀገራችን የት ነው?” ብሎ እናቱን ይጠይቃል። ልብ አድርጉልኝ የታዘለ ልጅ ከ”ትልቁ ሰውዬ” ሲበልጣቸው። በነገራችን ላይ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በቁመት ከሁሉም የኢህአዴግ ባለስልጣናት ትልቁ ናቸው ።
የምር ግን ነገሩ በጣም አሳፋሪ ነው። “ህገ መንግስቱ ማንም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም አካባቢ ተዘዋውሮ መኖር፤ መኖር ብቻም አይደል ንብረት ማፍራት እንደሚችል” ይገልፃል። እየሆነ ያለው ግን፤ በአንድ ወቅት ፕሮፌሰር መስፍን እንዳሉት “መንግስታችን በህገ መንግስቱ ሳይሆን በህገ አራዊት ነው የሚመራው።” የሚለውን የሚያጋልጥ ነው! “እኔን የማትመስሉ በሙሉ ወግዱ” ማለት ከሰዎች አይጠበቅም።
አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በፃፉት “የውጡልኝ ከዚህ ቤት” ደብዳቤ ዜጎቹን በህገ ወጥ መንገድ መሬት ይዘዋል፣ በህገ ወጥ መንገድ መሬት ይሸጣሉ… ሲሉ ወንጅለዋቸዋል። ታድያ ይሄ ጉዳይ በህግ ሊዳኝ አይችልም እንዴ? ብለው ቢጠይቁ ባለስልጣኑ ይቀየሙዎታል።
አንድ ወዳጄ እንዳለኝ “እውነቱን ለመናገር እኒህን ባለስልጣን ባለስልጣን ብለን ብንጠራ እግዜሩም ቅር ይለዋል። እናም አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ባለስጣን ሳይሆኑ ባለሰይጣን ናቸው!” ብሎኛል። “ውጡልኝ” ብለው ያፈናቀሏቸው ዜጎች ጎረቤቶቻቸው የነበሩ የደቡብ ተወላጅ ወዳጆቻቸው ዘንድ ንብረት እንኳ እንዳያስቀምጡ ከልክለው አራስ እና ርጉዝ ሳይቀር በአንድ ጀንበር ማባረር በእውነቱ ባለስልጣን አያሰኝም።
ይህንን የተመለከቱ አንዳንድ ወገኖች፤ “ልዩነታችን ውበታችን” መሆኑን የሚያሳዩ በርካታ ልማታዊ ዜማዎች አሉን። ልዩነታችን ውበታችን መሆኑን የሚያሳዩ መሪዎች ግን የሉንም።” እያሉ እየወቀሱ ነው።
እኔ የምለው ግን በዚህ የእብደት ውሳኔ ላይ “ዋናው” መንግሰት የሆነ ነገር ማለት ያለበት አይመስላችሁም? አለበለዛ ምንም እንኳ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአባይ ዙሪያ ሲያወሩ “ኢትዮጵያ ውስጥ ያበደ መንግስት እንደማይኖር የሚያረጋግጥ ሞያተኛ የለም” በማለት ቢናገሩም የአቶ ሽፈራው ሽጉጤን ጉዳይ በቸልታ ሲመለከቱት ግን ያለ ምንም ባለሞያ እኛ ራሳችን መንግስታችን እብድ መሆኑን እናረጋግጥለታለን ማለት ነው። (ይሄኔ እርስዎ በሆድዎ “እኔ ካረጋገጥኩ ቆየሁ!” ሊሉ እንደሚችሉ እጠረጥራለሁ)
አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በሰባ ሺህ ዜጎች ላይ፤ “የሌላ ክልል ሰዎች ናችሁ” በሚል ምክንያት ሽጉጣቸውን ተኩሰውባቸው ሲያበቁ ከዚህ ቀጥሎ እርሳቸው፤ ለስብሰባ ወይም ለመዝናናት ወይም ዕቃ ለመግዛት ወደ ሌላ ክልል የመሄድ ሞራል አላቸው?
ወዳጄ ግድየሎትም እንፀልይ፤ “በቸርቻሮ የሚሸጡንን ወዲያ አድርጎ፤ አንድ አድሮጎ የሚገዛንን ያምጣልን!”
ለማብቂያ በአንድ ወቅት ታማኝ በየነ በአዲሳባ ስታድየም ያነበባትን ግጥም ቀንጨብ እናድርጋት
“…በሶማሊያ ችግር
አብረን ስንጨነቅ
በዩጎዝላቪያ ቆመን ስንሳለቅ
በእንጀራ አባታችን በሩሲያ ስንስቅ
ከነሱ ሳንማር ካለፍነው በዋዛ
አርባ መንግስት ሆነን
ክልል ስናበዛ
እንዳንጠያየቅ ፓስፖርት እና ቪዛ” ታማኝን እድሜ ይስጥልን!
ለካርቱን ስዕሉ ፍኖተ ነፃነትን ማመስገን ይገባል!
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 8 Comments »
Saturday, March 31st, 2012

ይሄ ወግ ትላንት አርብ አዲሳባ ፍትህ ጋዜጣ ላይ የወጣ ነው። ታድያ ለዲያስፖራ አንባቢዎቼ አዲሳባ በተዘጋችው በዝችኛዋ ብሎግ አቅርቤያለሁ። ኢትዮጵያ አላችሁ ወዳጆቼ ፍትህ ላይ ታነቡታላችሁ በሚል እሳቤ ነው በዛችኛዋ መስኮት ያለጠፍኩላችሁ።
ወዳጄ እንዴት አሉልኝ? እኔ ከእርሰዎ ሃሳብ እና ከፒያሳ ናፍቆት በሰተቀረ በጣም ደህና ነኝ። በዝች በምንወዳት እና በምትወደን፤ ፍትህ ጋዜጣ ላይ ባለፈው ሳምንት እከሰታለሁ ብዬ አስቤ ነበር። ግና እንዲሁ ስንደፋደፍ ሳይሳካልኝ ቀረ። ይህው እርሱ ባለው ቀን ተገናኘና!
እኔ የምልዎ ወዳጄ ሰሞኑን አባይ አንድኛ አመት ልደቱን ያከብራል ተብሎ ሽር ጉዱ ደርቶ የለ? እሰይ ይድራ እንጂ፤ ዋናው ነገር ሽር ጉድን ማድራት ነው። ሌላው ነገር ቀስ ብሎ ይመጣል። ካልመጣም ችግር የለም “እነሱ ተፍጨርጭረዋል!” የሚለው ስም ራሱ ግድቡ ከሚያመነጨው በላይ ሀይል ያመነጫል። እናም ሽር ጉድን የመሰለ ነገር የለም።
አንድ ወዳጄ ሰሞኑን በቴሌቪዥኑ “የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከተጀመረ እነሆ አመት ሊሞላው ነው!” ሲባል ሰምቶ ጠላትዎ ድንግጥ ይበልና “ክው” ብሎ ሲደነግጥ አየሁት። ምን አስደነገጠህ? ብዬ ብጠይቀው “አባይ ገና አንድ አመቱ ነው እንዴ?” በማለት አናቱን ይዞ ጠየቀኝ። ምነው ያለ እድሜው አረጀብህ…? አልኩት ጥያቄው ቢያስገርመኝ። እሱም በንግግሬ በስጨት እያለ፤ “አይ እዳዬ እኔን አስረጀኝ እንጂ እርሱማ ምን አለበት?” አለኝ።
ይህ ወዳጄ እንደሚለው አባይ ገና አንድ አመቱ ከሆነ (በመንግስት ስሌት እንኳ) ለቀጣይ ስድስት አመት መዋጮ ማዋጣት ይጠበቅብናል ማለት ነው። እኛ ደግሞ ከወዲሁ ተዳክመናል። እናም አባይ ገና ድክ ድክ ሲል እኛን ብርክርክ እያደረገን ነው። እናም መጨረሻችንን እንዲያሳምረው መፀለይ አለብን ብሎኛል።
ለማንኛውም ጠቅላይ ሚኒስትራችን “አባይን የደፈረ መሪ!” ተብለው ከባንዲራችን እኩል ወደ ላይ ከተሰቀሉ… (ውይ የምን መሰቀል አመጣሁባቸው…? ከተውለበለቡ… ልበል ይሆን…? የባሰውን አመጣሁት… እኔ ልውልብለብልዎ። አግዙኝ እንጂ ጎበዝ፤ በቃላት እጦት አኮ ጠቅላይ ሚኒስትሬን አጎሳቆልኳቸው ባንዲራ ከፍ ካለ በኋላ ምንድነው የሚሆነው…? አዎ… ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከባንዲራው እኩል ከፍ ብለው ከደመቁልን… አንድ አመት ሞልቷቸዋል። ብዬ ልገላገል)
በነገራችን ላይ፤ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሰሞኑን ኬኒያ ውስጥ የላሙ ወደብ ግንባታ መጀመርን አስመልክቶ በተገኙበት ወቅት ባንዲራቸውን ዘቅዝቀው ይዘው የተነሱት ፎቶግራፍ በጣም አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል። አንድ ወዳጄ፤ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባንዲራችንን እንዴት ይገለብጣሉ…? ለዛውም ባለ ኮከቡን እኮ ነው። እኛ ብንሆን እንዲህ ያደረግነው “ባንዲራን የገለበጠ ይገለበጣል” የሚል አዋጅ ጠቅሰው ይገለብጡን ነበር። እሳቸው ባንዲራችንን ሲገለብጡ ማን ይገልብጣቸው…?” እያለ ያለቅጥ ሲያማርር ሰማሁት። ዝም ብለው ግዜም፤ እስከ ዛሬ የነበሩን መሪዎቻችን ለባንዲራቸው እንዴት ቀናኢ እንደነበሩ እያወሳ ወቀሳውን በጣም አበዛው።
በዚህ ግዜ እሳቸው ሲነኩብኝ የምታመመው እኔ፤ ተው እስቲ እሳቸው በስንት ስራ የተጠመዱ ሰው ናቸው። እና ልብ ላይይሉት ይችላሉ። አንዲት ባንዲራ ዘቀዘቁ ብሎ እንዲህ ማማረር ተገቢ አይደለም። ምንም ቢሆን አባይን የደፈሩ ባለውለታ ናቸው። ብዬ የወዳጅነቴን ላስረዳ ሞከርኩኝ። ይሄን ግዜ ወዳጄ የባሰውን ቱግ ብሎ “ይቅርታ አድርግልኝና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በፊት ባንዲራ ጨርቅ ነው አሉ ሲባል አላመንም ብዬ ነበር። አሁን ግን በአይኔ በብረቱ ባንዲራችንን ዘቅዝቀው ሳያቸው፤ ሰውየው አባይን ሳይሆን የደፈሩት ኢትዮጵያን ነው። ብያለሁ!” አለኝ። እኔም በሆዴ ሌላ ተጨማሪ ምክንያት ቢኖረው ነው ብዬ የመማረር ነፃነቱን ሰጠሁት።
እኔ የምለው ወዳጄ ሰሞኑን ታድያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአባይ ግድብ ዙሪያ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ ሊሰጡ እንደሆነ ሰምተናል። አብዛኛዎቹ ጥያቄዎች ግን ገና ግድቡ ሲጀመር በየ ጓዳው፣ በየ አደባባዩ ሲጠየቁ የነበሩ ናቸው ታድያ እነዚህን ግርታዎች ለማጥራት የተከበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር፤ አንድ አመት ሙሉ ተጨነቅው የሚሰጡን መልስ አላጓጓችሁም?
ለማንኛውም አባይ መገደብ ከጀመረ አንድ አመት ሞላው። በዚች አንድ አመት ግዜ ውስጥ ስንቱን አሳለፈው? እስቲ የተወሰኑትን እንቁጠር
አንድ ፤
አባይ ላይ ሊገደብ የታቀደው ግድብ (ውይ ይቅርታ የታቀደው አልኩ እንዴ…? የምን ዕቅድ አመጣሁኝ… ዕቅድ ምናምን ለሚል ዝባዝንኬ የምናባክነው ግዜ የለንም ለካ…) ዝም ብለን አባይ ላይ የሚሰራው ግድብ… ብለን እንቀጥል። ስያሜው መጀመሪያ “ታላቁ የሚሊኒየም ግድብ ነበር” ከዛ በምን ምክንያት እንደሆን እንጃ ስሙ ተቀየረ።
ስለ ስም ቅያሬ እኔ የማውቀው አንድ ጨዋታ አለ። እንቃመሰው…
በሀገሬ በርካታ ገጠረማ አካባቢዎች የመዞር እድሉ ገጥሞኛል። ታድያ ከዙረት ብዛት አንዳንድ ሁነቶችን የት እንዳየዋቸው እዘነጋለሁ። ብቻ ከዞርኩባቸው አካባቢዎች በአንዱ፤ ገበሪዎች ስማቸውን ቶሎ ቶሎ ነበር የሚቀያይሩት። አምና እርገጣቸው የተባለ ሰው ዘንድሮ ታገሳቸው ሊባል ይችላል። የዚህ የስም መቃያየር ነገር ምስጢሩን በጠየቅሁበት ግዜ ምን ሆኖ ተገኘ መሰልዎ… “አዋቂ እያዘዘን ነው” አሉኝ። የምን አዋቂ…? አይባልም። የምድር አዋቂ ነው።
“ምርትህ እንዲሰምር ከብቶችህ ጤና እንዲያገኙ አትሻም?”
“አረ ጌታዬ ታድያ መባተሌ ለምን ሆነ…?”
“ስምህን ማን ነበር ያልከኝ…?”
“እልሁ… እሰኛልው ጌታዬ”
“እልሁ… እልሁ… ባዶ እልህ ምን ያደርጋል ማሸነፍ ያስፈልጋል… እልህ ብቻውን እህል አይሆንም… ትሰማኛለህ…?”
“አዎ ጌታዬ”
“እልሁ የሚለው ስም አይሆንህም። ጠላት ያበዛብሃል… ምርትህን ይቀንስብሃል… ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ አሸናፊ ብዬሀለሁ። አይዞህ ታሸንፋለህ…!”
ብለው ፈርደው የደንቡን ተቀብለው ይሸኙታል። እልሁም ዘንድሮ ስሙን አሸናፊ ብሎ ያማረ ምርት እንደሚገጥመው ተስፋ አድርጎ ይጠብቃል።
ትላንት አብዛኛውን ከገበሬው ማህበረሰብ የተውጣጡት ጀግና የኢህአዴግ ሰራዊት ታጋዮች፤ የዛሬ ባለስልጣኖች መጀመሪያ ሚሊኒየም ተብሎ ሲጠራ የነበረውን ግድብ “ህዳሴ ግድብ” ብለውታል። አዋቂ የሚለውን መስማት ጥሩ ነው። ብለን እኛም አልተጨቃጨቅንም እሺ ብለናል።
ሁለት፤
አባይ ግድብ ሲጀመር በአምስት አመት ግዜ ውስጥ ያልቃል ተብሎ ነበር። እያደር እያደር “በአምስት አመት ያልቃል የተባለው ለቀልድ ነው መቀለድ አይቻልም እንዴ?” ተባለና ወደ ስድስት አመት ተኩል ነው ወደ ሰባት አመት አደገ። ከዚህ ጋርም የተያያዘ ጨዋታ አናጣም፤
ነብሱን ይማረውና ይህንን ጨዋታ ስብሀት ገብረ እግዚአብሄር ነበር የሆነ ቦታ የከተባት። ይችትልዎ፤
በአንድ ወቅት አንድ ሰውዬ ይኖር ነበር። ብቻውን ሳይሆን ከሚስቱ ጋር ነበር የሚኖሩት። እነዲሁ ቁጭ ብለው ሳይሆን ደግሞ አንሶላ እየተጋፈፉም ነበር። ሲኖሩ፣ ሲኖሩ፣ ሲጋፈፉ፣ ሲጋፈፉ በአንዱ ቀን ሚስት ፀነሰች። ባልም “አባት ደስ ይለዋል ልጅ ሲወለድለት” የሚለውን ሙዚቀ እያንጎራጎረ፤ ለልጁ አልጋ ሊያሰራ አንድ እውቅ አናጢ ቤት ሄደ። “ሚስቴ አርግዛልኝ ደስ ብሎኛል እስክትወልድ ድረስ ቀስ ብለህ በጥሩ ሁኔታ አንድ የህፃን አልጋ ታዘጋጅልኛለህ?” ብሎ ቢጠይቀው፤ አናጢውም “ሁሉ ሰው እንዳተ ብልብ ቢሆን ምንኛ መልካም ነበር? እንዲህ ቀደም ብለው ማዘዛቸውን ትተው ደረሰ አልደረሰ ብለው ይጨቃጨቃሉ!” ብሎ ቀድሞ ማዘዙን አመሰገነ።
ከወራት በዋላ ልጁ ሲወለድ አባት ሚስቱን “ሰርፕራይዝ” ሊያደርጋት አናጢው ዘንድ ሄደ። አልጋው አልደረሰም። “ትንሽ ቀናት ብትጨምርልኝ ይደርሳል” አለው። አባወራው እያጉተመተመ ተመለሰ። ከተጨማሪው ትንሽ ቀናት በኋላም ድጋሚ ሄዶ ጠየቀ አሁንም አናጢ ጢሙን እያሻሸ “ይቅርታ ጌታዬ ትንሽ ቀን ብንጨምርበት ጥሩ አልጋ አደርስልሃለሁ” አለው።
እያለ እያለ አልጋው ሳይደርስ የተወለደው ልጅ አደገ። ምን ማደግ ብቻ እርሱም አግብቶ አስረገዘ። ሚስቱ ማረገዟን ላባቱ ቢነግረው ግዜ አባቱም “ጎሽ እንዲህ ነው እንጂ…!” ብለው አስረጋዥነቱን ካደነቁት በኋላ፤ “አንተ ልትወለድ ስትል አንድ አናጢ ዘንድ አልጋ አዝዤ ነበር ሂድና አመጣው ለልጅህ ይሆንሃል ሌላ አልጋ እንዳትገዛ” አሉት። ልጅም “ጎሽ ከወጪ ተገላገልኩ” እያለ በደስታ ሄደ።
አናጢውም የልጁን የወራሽነት መብት በተለያየ ማውጣጫ ካረጋገጡ በኋላ፤ ችግር የለም በጥሩ ሁኔታ ይደርስልሃል ብቻ ትንሽ ግዜ ስጠኝ አሉት ጢማቸውን እያሹ። ልጅም አንድም በአናጢው ሁኔታ፤ አንድም ይሄ ካልደረሰ የሚጠብቀውን ወጪ በማሰብ ብስጭቱ መጣ እና፤ “አባቴ እኔ ስወለድ ያዘዘው አልጋ እንዴት ለልጄ እንኳ አይደርስም? የምን ተጨማሪ ግዜ ነው የሚጠይቁኝ…?” ብሎ በቁጣ ተናገራቸው። አናጢ ሆዬ “ካፈርኩ አይመልሰኝ” ነውና፤ “አይ እንግዲህ… እኔ በስራዬ ላይ ሲያጣድፉኝ አልወድም” አሉት። ብሎ ስብሐት ነግሮናል። የጋሽ ስብሐትን ነብስ ጥሩ ቦታ ያስቀምጥልን!
በአምስት አመት ያልቃል የተባለው አባይ ግድብ እዛው አይናችን እያየ ወደ ሰባት አመት አደገ። “እንዴ ገና ሰባት አመት ሙሉ ደሞዛችን ሊቆረጥ” ብሎ ማጉረምረም አይገባም መልሱ “ይቅርታ ሲያጣድፉን አንወድም ነው!”
ሶስት
የመዋጮው ነገር፤ “አባይን በራሳችን አቅም እንገድባለን!” ብለን ከህፃን እስከ አዋቂ ሁላችንም ፎክረናል። አንዳንዶቻችንም “ፎግረናል” በነገራችን ላይ በቴሌቪዥን እና በመስሪያ ቤታቸው ስብሰባዎች ላይ፤ “እኔ ለአባይ ዘራፍ እላለሁ!” ብለው ፊታቸውን አስመትተው በአለቆቻቸው ዘንድ ሞገስ ያገኙ በርካቶች እንደሆኑ ባለፉት ግዚያት አይተናል። እነዚህ ወዳጆቻችን በመስሪያ ቤታቸው ሰዎች ዘንድ “አስተኳሽ” የሚል የማዕረገት ስምም ተሰጥቷቸዋል።
እኔ የምለው ወዳጄ አንዳንዶች የሚሰጡትን አስተያየት ልብ ብላችሁልኛል? “አባይን በራሳችን አቅም ገድበን ከአምስት አመት በኋላ ድህነትን ማጥፋት እና ካደጉት ሀገሮች ተርታ መቀላቀል አለብን!” እያሉ ነው።
ቆይ ቆይ እዝች ጋ ትንሽ ፍሬን ያዝ እናድርግ…
አባይ በራሳችን አቅም በእኛው መዋጮ ለማለቅ ስንት አመት እንደሚፈጅበት እናስላ፤ ባለፈው አመት ሰባት ቢሊዮን ብር ተገኝቷል። በመነሻው ሞራል እንቀጥላለን፤ “ምናባቱ የመጣው ይምጣ!” ብንል እንኳ፤ ሰማኒያ ቢሊዮን ለማግኘት… (ሰማኒያን ለሰባት ማካፈል ነው።) አስራ አንድ አመት ይፈጃል።
ታድያ “በአምስት እና በስድስት አመት ያልቃል” የሚሉን ወዳጆቻችን የሚያውቁት ሌላ ምስጢር ካለ ቢነግሩን ጥሩ ነው። የሚሉ ወገኖች በርካታ ናቸው። የምር ግን መንግስታችን ራሱ በሰባት አመትም ይሁን በስድስት አመት የሚያልቀው በምን ስሌት እንደሆነ፤ ድህነትንስ ሙልጭ አድርጎ የሚያጠፋው በምን መልኩ እንደሆነ የማስረዳት ኃላፊነት ያለበት አይመስልዎትም…?
አንድ ወዳጃችን አባይን ገድበን ድህነትን እናጠፋለን ተብሎ በቴሌቪዥን ሲነገር ሰምቶ ምን አለ መሰልዎ “እነዚህ ሰዎች ድህነት በኤሌክትሪክ ተንጨርጭሮ የሚጠፋ መሰላቸው እንዴ…?” ብሎ ጠየቀን። በዙሪያው ያለን ሰዎችም “ፖለቲካ አናወራም” ብለን ዝም ብንለው፤ “የኔ ጌታ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ድህነት ፕላስቲክ ለበስ ነው። ኤሌክትሪክ አይዘውም!” አለና ከት ብሎ መሳቅ፣ ከዛም ስቅስቅ ብሎ ማልቀስ ጀመረ።
የሆነ ሆኖ እያለቀስንም ሆነ እየሳቅን እናዋጣለን። “አናዋጣም” ብለን ከሚመጣው ጣጣ አዋጥተን የሚመጣውን ችጋር መቻል ይሻለናል።
አረስቼው ዋናው ከዚህ ከመዋጮ ጋር ተይዞ ልነገግርዎ የፈለግሁት፤ ልብ ብለው እንደሆነ መዋጮው መጀመሪያ በስጦታ ተብሎ ነበር ከዛ ደግሞ ወደ ቦንድ ግዢ ተለውጦላችኋል አታስቡ መንግስት ሰርቶ ይከፍላችኋል ትብሏል። በርግጥ ለርሱም እስካሁን ማረጋገጫ ያገኘ የለም። (ካለ እጁን ያውጣ!)
እንግዲህ አባይ ይገደባል በተባለ አመት ባልሞላ ግዜ ውስጥ በርካታ ነገሮችን አይቷል። ጠዋት የተነገረለት ከሰአት ከበርጫ ሰዓት መልስ ይቀየራል። እስከ አሁን እንኳ ሶስት ዋና ዋና ለውጦቹን አየን? በአዲስ መስመር አንድ እንጨምር፤
አራት
አባይ ግድብ ሊጀመር ጠዋት አካባቢ አምስት ሺህ ሁለት መቶ ሃምሳ ሜጋ ዋት ኋይል ያመነጫል ተብሎ ነበር። ትንሽ ረፈድ ሲል በቃሚዎች ቋንቋ፤ “ኢጃባና” ከተቃመ በኋላ አባይ ስድስት ሺህ ሜጋ ዋት አመነጫለሁ ብሏል ተባለ።
ይሄ ነገር የደህናውን ግዜ የጉሊት ገበያ ያስታውሰኛል። በተለይ ክረምት አካባቢ የስሙኒ ተብሎ የሚታሰረው ጎመን በደንብ ከተከራከሩ ሌላ እሱኑ የሚያክል ይመረቅ ነበር። (በጥጋቡ ግዜ ነው) ታድያ አሁንም አባይ ጥሩ የጉሊት ነጋዴ ነው የመሰለኝ። አምስት ሺህ ነው የማመነጨው ብሎ ሲያበቃ “አረ ባክህ አወጥተን እኮ ነው ገንዘብ እንኳ የለንም እባክህን መርቅልን!” ብለው አስተዛዝነው ነግረውት ነው መሰለኝ፤ መረቅረቅ አድርጎ ስድስት ሺህ ገብቶልናል።
እኔ የምለው ግን “የሚያመነጨው ሃይል ስለጨመረልን “ቲፕ” እናድርገው” ተብሎ መዋጮው ላይ እንዳይጨመርብን አይሰጉም?
እናልዎ ወዳጄ አባይ ግድብ ከተጀመረ አንድ አመት ሞልቶታል። በአንድ አመት ውስጥ እኛም እርሱም ብዙ ነገር አሳልፈናል። እርሱም ከላይ እስከ አራት የገለፅናቸውን ለውጦች እና ከስር እስከ አርባ አራት ያልገለፅናቸው ድንገተኛ ለውጦች ተከናውነውበታል። (እንደውም በቅንፍ፤ ለውጪ ሃይሎች እና የሀገሪቱን መልካም ለማይሹ ሰዎች አይናገሩ እንጂ… ለሙያው ቅርበት ያላቸው ወዳጆቻችን እንደሚሉት ከሆነ፤ “አባይ ከስያሜው ጀምሮ ይሄን ሁሉ ለውጥ ያስተናገደበት ምክንያት ያለ ዕቅድ መሰራቱ ነው።”) ከቅንፍ ውጪ እኛን በእቅድ ኑሩ እያለ የሚመክረን መንግስት ራሱ ያለ ዕቅድ የሚሰራው የሚከተለውን ጦስ አያውቅምን? ብዬ እጠይቃለሁ።
የሆነው ሆኖ አባይ አንድ አመት ሞልቶታል። ልጅ ቢሆን ኖሮ ይሄኔ ድክ ድክ የሚልበት ግዜው ነበር። እርሱም ድክድክ እያለ እንደሆነ በቴሌቪዥን አይተናል! እኛም ለአባይ እናዋጣለን ብለን “በሞራል” ከተንቀሳቀስን አመት ሞላን። እኛም በዝች አንድ አመት ውስጥ ብዙ አሳልፈናል። ድጋሚ ኑሮ ውድነቱ ከፍቶ የዋጋ ተመኑም ቀርቶ መኖር ይሉት ጣጣ ብርክርክ አድርጎናል። እንዲህም ሆኖ ለቀጣይ ስንት አመት ለአባይ እናዋጣ ይሆን…? እስቲ እንበርታ… ባንበረታስ…? ብንበረታም እንበርታ!
በመጨረሻም
አማን ያሰንብተን!
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | 6 Comments »
Friday, March 16th, 2012
አቤ ቶኪቻው
ባለፈው ሳምንት ውስጥ ተዓምረኛው ኢቲቪ ለማርች ስምንት የሴቶች ቀን መታሰቢያ አንድ ዶክመንተሪ ፊልም አሳይቶናል። ቐሽ ገብሩ ስለተባለች የህውሃት ህፃን ታጋይ የሚዘክር ዘጋቢ ፊልም። (ፊልሙ ልብ ብለው ሲከታተሉት ዘጋቢ ብቻ ሳይሆን አወዛጋቢም ነው… እንዴት…? የሚለውን የታገሰ ያነባል (ሳቅ))
በመጀመሪያ አበሻ እንደመሆኔ መጠን ጭቆናን “እምቢ” ብለው ፋኖን ለዘመሩ ታጋዮች ትልቅ አክብሮት እንዳለኝ ያለ ሽሙጥ እገልፃለሁ።
ተስፋዬ ገብረ አብ ከተረካቸው ትረካዎች በሙሉ “የቁንድዶ ፈረስ” ትረካ በጣም የመሰጠችኝ ናት። እስቲ ለማስታወስ ልሞክር…
ሐረር አካባቢ፤ የጋሪ ፈረሶች የሚደርስባቸው የስራ ጫና እጅግ በጣም ከባድ ነበር። ከስራ ጫናው እኩል ደግሞ ዱላም አለው። ልክ አሁን አሁን ደሞዛችን አነሰ ብለን “ኡኡ” ስንል “ለአባይ እና ለሌሎች ልማቶች ደግሞ መዋጮ አዋጡ” ተብለን መከራችንን እንደምናየው ማለት ነው። በዚህ ላይ እነዚህ የጋሪ ፈረሶች ስራውና ዱላ የሚደራረብባቸው አንሶ ጌታቸው (አባ ፈርዳው) ቀለባቸውንም በአግባቡ አይሰፍርላቸውም ነበርና ከሰውነት ጎዳና ወጥተው ክስት ጉስቁል አሉ።
ይሄን ግዜ “እምቢኝ” አሉና “ቁንድዶ” ወደተባለ ጫካ ገቡ። ከዛም ባህሪያቸው ተለውጦ እንደፈረስ ሳይሆን እንደ እንደ አውሬ ሆኑ። ማን ወንድ መጥቶ ዳግም ወደዛ የጋሪ ባርነት ይመልሳቸው? ማንም።
ታድያ ፈረሶቹ እዛው ጫካ ውስጥ መሽገው እንዳሻቸው እየበሉ እንዳሻቸው እየቦረቁ አማረባቸው። ወዘናቸውም “ጢም” አለ።
“በአሁኑ ግዜ የሀረር አካባቢ ነዋሪዎች የኦህዴድ አባላትን እስከ መቼ የጋሪ ፈረስ ትሆናላችሁ? አንዳንዴ እንኳን የቁንድዶ ፈረስ ሁኑ እንጂ…! እያሉ ያሽሟጥጧቸዋል።” ብሎናል ተስፋዬ። (ልክ ነኝ አይደል ተስፋዬ…? “ይሄንን እኔ አላልኩም” ካልክ እኔ ለማለት እገደዳለሁ…!(ፈገግታ))
እናም እኔ በበኩሌ የቁንድዶ ፈረስነትን አደንቃለሁ። አላማው ልክ ነው አይደለም የሚለው ጥያቄ በይደር ይቆይ። ነገር ግን በደል ሲበዛ “እምቢ” ማለት ከአባት የወረስነው ነው። ዛሬ የሽብረተኝነት አዋጅ ወጥቶ ሳይከለከል አይቀርም እንጂ አንድ ዘፈን ትዝ ይለኛል…
“ደብቆታል መሰል ዞማ በረሃው
“እምቢ” ያለው ጎበዝ የታል ሽፈራው” የሚል ዘፈን።
በአሁኑ ወቅት፤ ይህንን ዘፈን በይፋ መዝፈን የሚቻል አይመስለኝም። ምክንያቱም በሽብርተኝነት አዋጁ አንድ ግለሰብ፤ በዘፈን በፅሁፍ እና በተለያዩ መንገዶች “ሽብርተኛን” እንኳንስ ሲያበረታታ ተገኝቶ ይቅርና፤ “አበረታቷል” ተብሎ ሲታሰብም “ጉዱ ይፈላል” ይላል። በተጨባጭ እንደምናየው ደግሞ እንኳንስ እምቢ ብለው ዞማ ጫካ ገብተው ይቅርና በከተማው ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎች ራሳቸው “አሸባሪ” ስለመሆናቸው መረጃው አለ። ማስረጃው ጠፍቶ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩም እኛም የጨነቀን…! ስለዚህ “ደብቆታል መሰል ዞማ በረሃው እምቢ ያለው ጎበዝ የታል ሽፈራው…” ብሎ ማዜም አይቻልም ማለት ነው።
ለማንኛውም፤ ዘፈኑ ግን “እምቢ” ባይነትን እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙሃን የሀገሬ ሰው እንደሚያደንቅ ያስረዳልኛል። አዎ አንዳንዴም እምቢ ማለት ጥሩ ነው። “እምቢ… እምቢ ለሀገሬ! እምቢ… እምቢ ለክብሪ! እምቢ… ታታታታ” ፉከራው ራሱ ማማሩ።
ስለዚህ ቐሽ ገብሩ፤ አሞራውና ሌሎችም “እምቢ” ባይ ታጋዮች “እምቢ” በማለታቸው አደንቃቸዋለሁ። እንኳንም እምቢ አላችሁ!
ወደ ቐሽ ገብሩ ስንመጣ የዶክመንተሪው አዘጋጆች ልብ ያላሉት ወይም ደግሞ “ምን ታመጣላችሁ” ብለው ችላ ያሉት አንድ ስህተት የፌስ ቡክ ወዳጆቼ አግኝተው ለጥፈውት ነበር። ወድያው የፕሬዘዳንቱ ወሬ መጥቶ ሸፈነው እንጂ ትልቅ መወያያ አጀንዳ ሳይሆን አይቀርም ነበር። ልብ በሉልኝ ህውሃት ሆዬ ቐሽ ገብሩን መትረየስ ሲያሸክማት ገና የአስራ ሶስት አመት ልጅ ነበረች። ከፈለጋችሁ አስሉት በአስራ ዘጠኝ ስድሳ አንድ ተወለደች። በአስራ ዘጠኝ ሰባ አራት ወደ ትግል ገባች። ማነው ሂሳብ የሚችል…? በሉ እስቲ አስሉልኝ። ሰባ አራት ሲቀነስ ስድሳ አንድ እኩል ይሆናል፤ አስራ ሶስት። ዘጋቢው ፊልም ሲቀጥልም “…ትግሉን በተቀላቀለች በጥቂት ወራት ውስጥ እጇን ተመታች። እንደዛም ሆና መትረየስ ትሸከም ነበር።” ይላል። ጉድ በል ህውሃት…! አይሉኝም?
ሰሞኑን አለም ሲነጋገርበት ከሰነበተባቸው ነገሮች ውስጥ በኡጋንዳ የሚገኘው የሎርድ ሬዚስታንት አርሚ መሪ፤ ጆሴፍ ኮኒ ህፃናትን ጦርነት ውስጥ እየማገደ ነው በሚል ታድኖ ይከሰስ ዘንድ የተጀመረው “ኮኒ ሁለት ሺህ አስራ ሁለት” የሚል እንቅስቃሴ ነው። በአለም አቀፍ ህግ፣ አረ በኢትዮጵያ ህገ መንግስትም ቢሆን ህፃናትን ለጦርነት ማሳተፍ የለየለት ወንጀል ነው። በእግዜሩ ዘንድም ያስጠይቃል።
እና ህውሃት የአስራ ሶስት አመቷን ህፃን ሙሉ “ቐሽ ገብሩ” ን በጦርነት ማሳተፉ ሳያንስ የግፉ ግፍ ደግሞ ለማርች ስምንት የሴቶች መብት ክብረ በዓል ላይ ታሪኳን እንደ ጥሩ ነገር ዘገበልን። እውነቱን ለመናገር ይሄ ትልቅ የወንጀል መረጃ ነው። እንደኔ እምነት ይህንን መረጃ ያጠናከሩ ሰዎች የውስጥ አርበኝነት ስራ እየሰሩ ነው። ይሄ የደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ ገና በርካታ መረጃዎችን ያወጣል። እዝችው ላይ ሙሉ ወይም ቐሽ ገብሩ ገና አስራ ስምንት አመት እንኳ ሳይሞላት አንድ ጎረምሳ በፍቅር ስም አስረግዞ እስከማስወረድ እንድትደርስ እንዳደረጋትም ዶክመንተሪው ይዘግባል። ሰውየው ከሷ ጋር ያሳለፈውን ፍቅርም ሲናገርም በኩራት ነው። እንዴት ነው ነገሩ… እኛ መሀሙድ አህመድ በአንድ ዘፈኑ ላይ “ሸግየዋ ጉብሊቷ… የአስራ አምስት አመቷ እንዴት ነሽ በሉልኝ የምታውቁ ቤቷን” ብሎ ስለዘፈነ አይደል እንዴ ከህፃናት መብት አንፃር ወንጀል ነውና ይቅርታ መጠየቅ አለበት እያልን የምንሟገተው? እንዲህ የባሰውን ነውር በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አየነው። ለዚህ ነው አይናችን የተርገበገው…?
ወዳጄ እንዴት ሰነበቱ አይገርምዎትም ይሄ ሁሉ መንደርርደሪያ መሆኑ… ይበሉ ወደ ዋናው ጉዳይ ተያይዘን እናምራ
እናልዎ… ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተለያየ ግዜ የተለያየ ዘጋቢም አወዛጋቢም ፊልሞችን ያቀርብልናል።
በዛ ሳምትን ያየነውም የቐሽ ገብሩ ዶክመንተሪም የዚሁ አካል ነው። እንግዲህ ከላይ ያነሳነውን በቐሽ ገብሩ የተጋለጠውን ህፃናትን ወደ ጦርነት የማሰማራት እና ለአቅመ ህይዋን ያልደረሱ ሴቶችን የማማገጥ ወንጀል እንዲህ ያለውን ጉዳይ ለሚከታተሉ አካሎች እንተወው እና የፈረደባትን ይቺን ህፃን “እምቢ” እንዳለች ጀግና እንቁጠራት። ቆጠርናት…!
ኢህአዴግ ደርግን ብዙ ግዜ ደርግ በጦርነት የማረካቸውን ታጋዮቼን የማያምኑበትን እንዲናገሩ ያሰቃያቸው ነበር፤ ከዛም እምቢ ሲሉት ያስራቸዋል፤ ይገድላቸዋል። ብሎ ይወቅሳል። ይቀጥልናም ቢሆንም ግን፤ “እንደ አሞራው ሁኑ እንደ ቐሽ ገብሩ ሁኑ ብሎ ይመክረናል። እኛም ምክር የምንሰማ ልባሞች ነንና እሺ ብለን እንደ አሞራው፤ እንደ ቐሽ ገብሩም ለመሆን እንታትራለን ከዛ ውጤቱ ምን ይሆናል አይሉኝም…? ለምን እጠይቅሀለው እያወቅሁት…? አሉኝ እንዴ!?
ሰሞኑን አቶ አንዷለም አራጌ ላይ የሆነውን ነገር ሰምተዋል። አንዷለም አራጌ እንደ አሞራው ሁኑ ከመባሉ በፊትም እንደ አሞራው “እምቢ” ባይ ነበር። ለዛውም ጫካ ሳይገባ ፊት ለፊት እምቢ ብሎ የተጋፈጠ ደፋር የተቃማዊ ፓርቲ አመራር ነው። ምን ዋጋ አለው አንዷለም እንደ አሞራው “እምቢ” ቢልም ኢህአዴግ ደግሞ እንደ ደርግ “እምቢ” ማለት አይቻልም ብሎ አሰረው። ማሰር ብቻ ቢሆን በስንት ጣዕሙ ጎረምሳ አስገብቶ አስደበደበው እንጂ!
ማርች ስምንት የአለም ሴቶች ቀን ነው። በአለም ላይ ያሉ ሴቶች ቀደም ሲል ሲደርስባቸው የነበረ ጭቆና ይብቃ የተባለበት ቀን። ይህ ቀን፤ የህውሃት ሴቶች ቀንም የአንድነት ሴቶች ቀንም፤ የጋዜጠኛ ሴቶች ቀንም፣ የሁሉም ሴቶች ቀን ነው።
ርዕዮት አለሙ አሳሪዎቿ የጠላነውን አብረሽን ከጠላሽ ትለቀቂያለሽ ብለዋት ነበር። ቃል በቃል ሲነገር “ኤልያስ ክፍሌ የተባለው ጋዜጠኛን አሸባሪ ነው መሰስክሪበት እና ትለቀቂያለሽ” ተባለች። እርሷም እኔ “በወንጀለኝነት አላውቀውም” ብላ ድርቅ አለች። እንግዲያስ ብሎ ኢህአዴግም አስራ አራት አመት ፈረደባት። ቐሽ ገብሩን ደርግ የያዛት ግዜ “የህውሃት ሰዎችን ወንጀለኛ ናቸው ብለሽ መስክሪባቸው” አላት እምቢኝ ብላ ድርቅ አለች ሞት ፈረደባት። እንግዲህ ቐሽ ገብሩ እና ርዮት አለሙ አንድ ናቸው “እምቢኝ” ብለዋልና። ደርግ እና ኢህአዴግስ…? የመጣው ይምጣ ደፍሬ ልናገር ነው..! አዎ ደርግ እና ኢህአዴግም አንድ ናቸው። እምቢ ያላቸው ላይ ሁሉ ይፈርዳሉና። በነገራችን ላይ የደርግ ፕሮፖጋንዳ ሰራተኞች ቐሽ ገብሩን ለማናገር መከራቸውን ሲያዩ የነበረውን ያህል የኢህአዴግ ጋዜጠኞችም በተደበቀ ካሜራ ሳይቀር ርዮትን ለማናገር አበሳቸውን ሲያዩ ነበር። ነገር ግን ቐሽ ገብሩም ርዮትም አለሙም ፍንክች የአባ ቢላው ልጅ ብለዋል። ወይ መገጣጠም…! አይሉልኝም?
እና ታድያ የሴቶች ቀን ክብረ በዓል ሲዘከር መንግስት ርዕዮትን አስሮ ስለ ቐሽ ገብሩ ሲተርክ የአራዳ ልጆች ሰሙ። ሰምተውም ጠየቁ “ሼም የለም እንዴ በአገሩ!?” አሉ ዝርዝር ያለው የስራ ሂደት ካለ መልስ ያምጣ…!
በጥቅሉ መንግስት እነ ርዕዮትን፣ እነ እስክንድርን፣ እነ ውብሸትን፣ እነ ሂሩትን፣ እነ አንዷለምን እነ ናትናኤልን፤ ስንቱን ጠርቼ እዘልቀዋለሁ? በጅምላው እምቢ ያሉትን ሁሉ እያሰረ እና እየገረፈ “ደርግ ታጋዮቼን አሰረ፣ ገረፈ፣ ገደለ” ብሎ ዋይ ዋይ ማለት ውሃ የማያነሳ ወቀሳ ነው። መፅሐፉም ይላል “የሌሎችን ጉድፍ ከማየትህ በፊት በአንተ አይን ውስጥ ያለውን ቆሻሻ ተመልከት…”
በመጨረሻም
ያወጋነውን ለፍሬ ይበልልን
አማን ያሰንብተን!
Tags: addis ababa, Ethiopia, health, import/export, politics
Posted in Amharic | 23 Comments »
Friday, March 16th, 2012
ባለፈው ሳምንት ውስጥ ተዓምረኛው ኢቲቪ ለማርች ስምንት የሴቶች ቀን መታሰቢያ አንድ ዶክመንተሪ ፊልም አሳይቶናል። ቐሽ ገብሩ ስለተባለች የህውሃት ህፃን ታጋይ የሚዘክር ዘጋቢ ፊልም። (ፊልሙ ልብ ብለው ሲከታተሉት ዘጋቢ ብቻ ሳይሆን አወዛጋቢም ነው… እንዴት…? የሚለውን የታገሰ ያነባል (ሳቅ))
በመጀመሪያ አበሻ እንደመሆኔ መጠን ጭቆናን “እምቢ” ብለው ፋኖን ለዘመሩ ታጋዮች ትልቅ አክብሮት እንዳለኝ ያለ ሽሙጥ እገልፃለሁ።
ተስፋዬ ገብረ አብ ከተረካቸው ትረካዎች በሙሉ “የቁንድዶ ፈረስ” ትረካ በጣም የመሰጠችኝ ናት። እስቲ ለማስታወስ ልሞክር…
ሐረር አካባቢ፤ የጋሪ ፈረሶች የሚደርስባቸው የስራ ጫና እጅግ በጣም ከባድ ነበር። ከስራ ጫናው እኩል ደግሞ ዱላም አለው። ልክ አሁን አሁን ደሞዛችን አነሰ ብለን “ኡኡ” ስንል “ለአባይ እና ለሌሎች ልማቶች ደግሞ መዋጮ አዋጡ” ተብለን መከራችንን እንደምናየው ማለት ነው። በዚህ ላይ እነዚህ የጋሪ ፈረሶች ስራውና ዱላ የሚደራረብባቸው አንሶ ጌታቸው (አባ ፈርዳው) ቀለባቸውንም በአግባቡ አይሰፍርላቸውም ነበርና ከሰውነት ጎዳና ወጥተው ክስት ጉስቁል አሉ።
ይሄን ግዜ “እምቢኝ” አሉና “ቁንድዶ” ወደተባለ ጫካ ገቡ። ከዛም ባህሪያቸው ተለውጦ እንደፈረስ ሳይሆን እንደ እንደ አውሬ ሆኑ። ማን ወንድ መጥቶ ዳግም ወደዛ የጋሪ ባርነት ይመልሳቸው? ማንም።
ታድያ ፈረሶቹ እዛው ጫካ ውስጥ መሽገው እንዳሻቸው እየበሉ እንዳሻቸው እየቦረቁ አማረባቸው። ወዘናቸውም “ጢም” አለ።
“በአሁኑ ግዜ የሀረር አካባቢ ነዋሪዎች የኦህዴድ አባላትን እስከ መቼ የጋሪ ፈረስ ትሆናላችሁ? አንዳንዴ እንኳን የቁንድዶ ፈረስ ሁኑ እንጂ…! እያሉ ያሽሟጥጧቸዋል።” ብሎናል ተስፋዬ። (ልክ ነኝ አይደል ተስፋዬ…? “ይሄንን እኔ አላልኩም” ካልክ እኔ ለማለት እገደዳለሁ…!(ፈገግታ))
እናም እኔ በበኩሌ የቁንድዶ ፈረስነትን አደንቃለሁ። አላማው ልክ ነው አይደለም የሚለው ጥያቄ በይደር ይቆይ። ነገር ግን በደል ሲበዛ “እምቢ” ማለት ከአባት የወረስነው ነው። ዛሬ የሽብረተኝነት አዋጅ ወጥቶ ሳይከለከል አይቀርም እንጂ አንድ ዘፈን ትዝ ይለኛል…
“ደብቆታል መሰል ዞማ በረሃው
“እምቢ” ያለው ጎበዝ የታል ሽፈራው” የሚል ዘፈን።
በአሁኑ ወቅት፤ ይህንን ዘፈን በይፋ መዝፈን የሚቻል አይመስለኝም። ምክንያቱም በሽብርተኝነት አዋጁ አንድ ግለሰብ፤ በዘፈን በፅሁፍ እና በተለያዩ መንገዶች “ሽብርተኛን” እንኳንስ ሲያበረታታ ተገኝቶ ይቅርና፤ “አበረታቷል” ተብሎ ሲታሰብም “ጉዱ ይፈላል” ይላል። በተጨባጭ እንደምናየው ደግሞ እንኳንስ እምቢ ብለው ዞማ ጫካ ገብተው ይቅርና በከተማው ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎች ራሳቸው “አሸባሪ” ስለመሆናቸው መረጃው አለ። ማስረጃው ጠፍቶ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩም እኛም የጨነቀን…! ስለዚህ “ደብቆታል መሰል ዞማ በረሃው እምቢ ያለው ጎበዝ የታል ሽፈራው…” ብሎ ማዜም አይቻልም ማለት ነው።
ለማንኛውም፤ ዘፈኑ ግን “እምቢ” ባይነትን እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙሃን የሀገሬ ሰው እንደሚያደንቅ ያስረዳልኛል። አዎ አንዳንዴም እምቢ ማለት ጥሩ ነው። “እምቢ… እምቢ ለሀገሬ! እምቢ… እምቢ ለክብሪ! እምቢ… ታታታታ” ፉከራው ራሱ ማማሩ።
ስለዚህ ቐሽ ገብሩ፤ አሞራውና ሌሎችም “እምቢ” ባይ ታጋዮች “እምቢ” በማለታቸው አደንቃቸዋለሁ። እንኳንም እምቢ አላችሁ!
ወደ ቐሽ ገብሩ ስንመጣ የዶክመንተሪው አዘጋጆች ልብ ያላሉት ወይም ደግሞ “ምን ታመጣላችሁ” ብለው ችላ ያሉት አንድ ስህተት የፌስ ቡክ ወዳጆቼ አግኝተው ለጥፈውት ነበር። ወድያው የፕሬዘዳንቱ ወሬ መጥቶ ሸፈነው እንጂ ትልቅ መወያያ አጀንዳ ሳይሆን አይቀርም ነበር። ልብ በሉልኝ ህውሃት ሆዬ ቐሽ ገብሩን መትረየስ ሲያሸክማት ገና የአስራ ሶስት አመት ልጅ ነበረች። ከፈለጋችሁ አስሉት በአስራ ዘጠኝ ስድሳ አንድ ተወለደች። በአስራ ዘጠኝ ሰባ አራት ወደ ትግል ገባች። ማነው ሂሳብ የሚችል…? በሉ እስቲ አስሉልኝ። ሰባ አራት ሲቀነስ ስድሳ አንድ እኩል ይሆናል፤ አስራ ሶስት። ዘጋቢው ፊልም ሲቀጥልም “…ትግሉን በተቀላቀለች በጥቂት ወራት ውስጥ እጇን ተመታች። እንደዛም ሆና መትረየስ ትሸከም ነበር።” ይላል። ጉድ በል ህውሃት…! አይሉኝም?
ሰሞኑን አለም ሲነጋገርበት ከሰነበተባቸው ነገሮች ውስጥ በኡጋንዳ የሚገኘው የሎርድ ሬዚስታንት አርሚ መሪ፤ ጆሴፍ ኮኒ ህፃናትን ጦርነት ውስጥ እየማገደ ነው በሚል ታድኖ ይከሰስ ዘንድ የተጀመረው “ኮኒ ሁለት ሺህ አስራ ሁለት” የሚል እንቅስቃሴ ነው። በአለም አቀፍ ህግ፣ አረ በኢትዮጵያ ህገ መንግስትም ቢሆን ህፃናትን ለጦርነት ማሳተፍ የለየለት ወንጀል ነው። በእግዜሩ ዘንድም ያስጠይቃል።
እና ህውሃት የአስራ ሶስት አመቷን ህፃን ሙሉ “ቐሽ ገብሩ” ን በጦርነት ማሳተፉ ሳያንስ የግፉ ግፍ ደግሞ ለማርች ስምንት የሴቶች መብት ክብረ በዓል ላይ ታሪኳን እንደ ጥሩ ነገር ዘገበልን። እውነቱን ለመናገር ይሄ ትልቅ የወንጀል መረጃ ነው። እንደኔ እምነት ይህንን መረጃ ያጠናከሩ ሰዎች የውስጥ አርበኝነት ስራ እየሰሩ ነው። ይሄ የደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ ገና በርካታ መረጃዎችን ያወጣል። እዝችው ላይ ሙሉ ወይም ቐሽ ገብሩ ገና አስራ ስምንት አመት እንኳ ሳይሞላት አንድ ጎረምሳ በፍቅር ስም አስረግዞ እስከማስወረድ እንድትደርስ እንዳደረጋትም ዶክመንተሪው ይዘግባል። ሰውየው ከሷ ጋር ያሳለፈውን ፍቅርም ሲናገርም በኩራት ነው። እንዴት ነው ነገሩ… እኛ መሀሙድ አህመድ በአንድ ዘፈኑ ላይ “ሸግየዋ ጉብሊቷ… የአስራ አምስት አመቷ እንዴት ነሽ በሉልኝ የምታውቁ ቤቷን” ብሎ ስለዘፈነ አይደል እንዴ ከህፃናት መብት አንፃር ወንጀል ነውና ይቅርታ መጠየቅ አለበት እያልን የምንሟገተው? እንዲህ የባሰውን ነውር በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አየነው። ለዚህ ነው አይናችን የተርገበገው…?
ወዳጄ እንዴት ሰነበቱ አይገርምዎትም ይሄ ሁሉ መንደርርደሪያ መሆኑ… ይበሉ ወደ ዋናው ጉዳይ ተያይዘን እናምራ
እናልዎ… ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተለያየ ግዜ የተለያየ ዘጋቢም አወዛጋቢም ፊልሞችን ያቀርብልናል።
በዛ ሳምትን ያየነውም የቐሽ ገብሩ ዶክመንተሪም የዚሁ አካል ነው። እንግዲህ ከላይ ያነሳነውን በቐሽ ገብሩ የተጋለጠውን ህፃናትን ወደ ጦርነት የማሰማራት እና ለአቅመ ህይዋን ያልደረሱ ሴቶችን የማማገጥ ወንጀል እንዲህ ያለውን ጉዳይ ለሚከታተሉ አካሎች እንተወው እና የፈረደባትን ይቺን ህፃን “እምቢ” እንዳለች ጀግና እንቁጠራት። ቆጠርናት…!
ኢህአዴግ ደርግን ብዙ ግዜ ደርግ በጦርነት የማረካቸውን ታጋዮቼን የማያምኑበትን እንዲናገሩ ያሰቃያቸው ነበር፤ ከዛም እምቢ ሲሉት ያስራቸዋል፤ ይገድላቸዋል። ብሎ ይወቅሳል። ይቀጥልናም ቢሆንም ግን፤ “እንደ አሞራው ሁኑ እንደ ቐሽ ገብሩ ሁኑ ብሎ ይመክረናል። እኛም ምክር የምንሰማ ልባሞች ነንና እሺ ብለን እንደ አሞራው፤ እንደ ቐሽ ገብሩም ለመሆን እንታትራለን ከዛ ውጤቱ ምን ይሆናል አይሉኝም…? ለምን እጠይቅሀለው እያወቅሁት…? አሉኝ እንዴ!?
ሰሞኑን አቶ አንዷለም አራጌ ላይ የሆነውን ነገር ሰምተዋል። አንዷለም አራጌ እንደ አሞራው ሁኑ ከመባሉ በፊትም እንደ አሞራው “እምቢ” ባይ ነበር። ለዛውም ጫካ ሳይገባ ፊት ለፊት እምቢ ብሎ የተጋፈጠ ደፋር የተቃማዊ ፓርቲ አመራር ነው። ምን ዋጋ አለው አንዷለም እንደ አሞራው “እምቢ” ቢልም ኢህአዴግ ደግሞ እንደ ደርግ “እምቢ” ማለት አይቻልም ብሎ አሰረው። ማሰር ብቻ ቢሆን በስንት ጣዕሙ ጎረምሳ አስገብቶ አስደበደበው እንጂ!
ማርች ስምንት የአለም ሴቶች ቀን ነው። በአለም ላይ ያሉ ሴቶች ቀደም ሲል ሲደርስባቸው የነበረ ጭቆና ይብቃ የተባለበት ቀን። ይህ ቀን፤ የህውሃት ሴቶች ቀንም የአንድነት ሴቶች ቀንም፤ የጋዜጠኛ ሴቶች ቀንም፣ የሁሉም ሴቶች ቀን ነው።
ርዕዮት አለሙ አሳሪዎቿ የጠላነውን አብረሽን ከጠላሽ ትለቀቂያለሽ ብለዋት ነበር። ቃል በቃል ሲነገር “ኤልያስ ክፍሌ የተባለው ጋዜጠኛን አሸባሪ ነው መሰስክሪበት እና ትለቀቂያለሽ” ተባለች። እርሷም እኔ “በወንጀለኝነት አላውቀውም” ብላ ድርቅ አለች። እንግዲያስ ብሎ ኢህአዴግም አስራ አራት አመት ፈረደባት። ቐሽ ገብሩን ደርግ የያዛት ግዜ “የህውሃት ሰዎችን ወንጀለኛ ናቸው ብለሽ መስክሪባቸው” አላት እምቢኝ ብላ ድርቅ አለች ሞት ፈረደባት። እንግዲህ ቐሽ ገብሩ እና ርዮት አለሙ አንድ ናቸው “እምቢኝ” ብለዋልና። ደርግ እና ኢህአዴግስ…? የመጣው ይምጣ ደፍሬ ልናገር ነው..! አዎ ደርግ እና ኢህአዴግም አንድ ናቸው። እምቢ ያላቸው ላይ ሁሉ ይፈርዳሉና። በነገራችን ላይ የደርግ ፕሮፖጋንዳ ሰራተኞች ቐሽ ገብሩን ለማናገር መከራቸውን ሲያዩ የነበረውን ያህል የኢህአዴግ ጋዜጠኞችም በተደበቀ ካሜራ ሳይቀር ርዮትን ለማናገር አበሳቸውን ሲያዩ ነበር። ነገር ግን ቐሽ ገብሩም ርዮትም አለሙም ፍንክች የአባ ቢላው ልጅ ብለዋል። ወይ መገጣጠም…! አይሉልኝም?
እና ታድያ የሴቶች ቀን ክብረ በዓል ሲዘከር መንግስት ርዕዮትን አስሮ ስለ ቐሽ ገብሩ ሲተርክ የአራዳ ልጆች ሰሙ። ሰምተውም ጠየቁ “ሼም የለም እንዴ በአገሩ!?” አሉ ዝርዝር ያለው የስራ ሂደት ካለ መልስ ያምጣ…!
በጥቅሉ መንግስት እነ ርዕዮትን፣ እነ እስክንድርን፣ እነ ውብሸትን፣ እነ ሂሩትን፣ እነ አንዷለምን እነ ናትናኤልን፤ ስንቱን ጠርቼ እዘልቀዋለሁ? በጅምላው እምቢ ያሉትን ሁሉ እያሰረ እና እየገረፈ “ደርግ ታጋዮቼን አሰረ፣ ገረፈ፣ ገደለ” ብሎ ዋይ ዋይ ማለት ውሃ የማያነሳ ወቀሳ ነው። መፅሐፉም ይላል “የሌሎችን ጉድፍ ከማየትህ በፊት በአንተ አይን ውስጥ ያለውን ቆሻሻ ተመልከት…”
በመጨረሻም
ያወጋነውን ለፍሬ ይበልልን
አማን ያሰንብተን!
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | No Comments »
Friday, March 9th, 2012
ዛሬ ለቀዳማዊት እመቤት አዜብ መስፍን አንድ መልዕክት ለመስደድ አስቤያለሁ። እስከ ዛሬ ድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትራችን የተለያዩ መልዕክቶችን ስንልክላቸው ነበር። እርሳቸው ግን አይተው እንዳላየ፣ ሰምተው እንዳልሰማ ዝም ብለውናል። በርግጥ መልዕክቶቻችንን እንደሚያነቡ ባለፈው ግዜ ጠቁመውናል። “እያንዳንዳችሁ በየጋዜጣው የምትፅፉትን እናያለን የጋዜጠኝነት ሀሁ ያልገባችሁ ጋጥ ወጦች ናችሁ” ብለው እስከ ዶቃ ማሰሪያችን በተናገሩበት “ዲስኩር” ቢያንስ መልዕክቶቻችንን እያዩ እንደሆነ ተረድተናል። እኛም “ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚያነቡን ባወቅን ግዜ ደስ አለን” ብለን ጮቤ ረግጠናል።
ቢሆንም ግን አንድም ቀን እንኳ “እንዲህ ይባላል፤ “እንዲህ አድርገን እናሻሽላለን። እንዲህም ተብለናል፤ እንግዲህ ካልፈለጋችሁ ምን እናደርጋለን … እንለቃለና…” ብለው ምላሽ ለመስጠት አልሞከሩም። (እኛ እንደሳቸው “አህያ ትልቅ ጆሮ አላት ግን በቅጡ አትሰማም ትላልቅ አይንም አላት ግን ያለመነፅር ማየት ይቸግራታል…” ብለን ሰውን ያህል ክቡር ፍጡር ከእንስሳ ጋር አናዛምድም። እናስ… እናማ… በቃ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዙ ነገር እየጠየቅናቸው “ጆሮ ዳባ” አሉን። ብለን እናልፈዋለን…
ታድያ ምን ይጠበስ…? ያሉኝ እንደሆነ፤ ምን ይጠበስ መሰልዎ… ጉዳያችንን ይዘን ሄደን ለባለቤታቸው እንነግራለን። እናም ውጤቱን እንከታተላለን። ይሄ እስከ አሁን ያልተሞከረ ጥሩ መላ አይመስልዎትም?
ከዛ በፊት ከዚህ ጋር የተያያዘ አንድ ጨዋታ አለኝ እንደሚከተለው ይቀርባል…
ባል እና ሚስት ከተጋቡ በኋላ የባል እናት ቤት አብረው ይኖሩ ነበር አሉ። ሲኖሩ ሲኖሩ ከዕለታት አንድ ቀን ሚስት እና የባል እናት ይጣላሉ። ጭቅጭቃቸውም በበረታ ግዜ እናት ሆዬ “እኔ ከአንቺ ጋር ምን አነዛነዘኝ… አንቺንም እኔንም የሚያስተዳድረን ልጄ ነው። እርሱ ሲመጣ ሁሉንም ዘክዝኬ እነግረዋለሁ…!” በማለት “ሀርድ ይሰጣሉ። ታድያ ሚስት ምን አለች መሰልዎ… “ንገሪው… አንቺ አጠገብሽ ቁጭ አድርገሽ ከምትነግሪው እና እኔ አንገቱ ስር ገብቼ ከምነግረው የማንን እንደሚሰማ እናያለን?” አለች አሉ።
እንግዲህ ይህ ህዝብ እናት የሆነ ህዝብ ነው። ግና አጠገብ ቁጭ አድርጎ ቢመክርም የሚሰማው አላገኘም። ስለዚህ በተሻለ ሁኔታ የሚመክር ካገኘን እንሞክር…
እባክዎ ወይዘሮ አዜብ ባለቤትዎን ይምከሯቸው… እንበል።
ወዳጄ… እንዴት ሰንብተውልኛል? ሰላምም ሳልልዎ ቀጥታ ወሬዬን ጀመርኩ አይደል? ይቅርታ ይደረግልኝ ለመሆኑ ጤና እንዴት ይዝዎታል…? አይዞት በርታ ይበሉ። “ዋናው ነገር ጤና” እንዳለው ዘፋኝ ጤና እና እድሜ ካለ ሌላው ትርፍ ነውና ጤናውን ከእድሜ ጋር እንዲያጎናፅፍዎ ምኞቴን እገልፃለሁ።
እኔ የምለው “የአዲሳባ ኑሮ አሁንም አልተቻለም!” የሚል ወሬ ሰማሁ። ለምሳሌ “ባለ ብሩ ዳቦ” ሙዚየም ውስጥ ካልሆነ የመገኘት እድሉ የመነመነ ሆኗል (አሉ) አሁን አሁን አዲሳባ ላይ “ባለ አንድ ብሩን ዳቦ ስጠኝ” ብለው ቢጠይቁ ዳቦ ቤቱ ውስጥ ያለው ነጋዴ ብቻ ሳይሆን አንድ ብርዎት ላይ የተሳለው ልጅ ራሱ “አልሰሜን ግባ በሎ” ብሎ ከወትሮው በተለየ መልኩ ይስቅብዎታል እየተባለ ነው። ታድያ አሉ ነው። ምን ይደረግ ከሀገር ርቄ የአሉ ወሬ ሰለባ ሆኜ የለ? (“እሱ እንኳን ተው ድሮም አሉ ትወዳለህ…” ብሎ ማሽሟጠጥ የተከለከለ ነው።)
ይልቅስ ከላይ ሙዚየም ስል ያቺ ሉሲ ትዝ አለችኝ። እሷ ሴትዬ በቃ እንደወጣች ቀረች እንዴ…? የከተማው ሰው “ዲቪ ደርሷት ነው” እያለ ሲቧልት ሰምተን ነበር። በርግጥ የመንግስት ሰዎች “ለጉብኝት ነው ትመለሳለች” ብለው ለማስተባበል ሞክረዋል። ይህው እርሷ ግን በዛው ጥገኝነት ጠይቃ ይሁን፣ ድሮውን አካሄዷ ለዘለቄታው ይሁን? ባልተለየ ሁኔታ እስከ ዛሬ ከአሜሪካ አልተመለሰችም። አረ ጎበዝ “ሼም” ነው።
ነገ ይህንን ልብ ያለ አንድ ጋዜጠኛ “ሀገሪቱ ህያው ብቻ ሳይሆን ሙታንም የሚሰደዱባት ሀገር ሆነች!” የሚል ዘገባ ቢሰራብን እንደተለመደው “መልካም ገፅታችንን ለማጥፋት ላይ ታች የሚሉ አካላት…” ብለን ለመልስ ምት መከራችንን ከምናይ ከአሁኑ መላ ቢበጅላት መልካም አይደለም? የምሬን ነው፤ የሉሲ ነገርማ በጣም አሳሳቢ ነው። ወይ ደግሞ ሰዎቹ “እሟ ቀሊጦ” ብለውን ከሆነም የአክሱምን ሀውልትን ለማስመለስ የተቋቋመው ኮሚቴ አይነት ለእርሷም ይቋቋም። እንጂ በውነቱ ይሄ ነገር ለሰሚም መልካም አይደለም።
ውይ ይቅርታ ቀዳማዊ እመቤት አቆምኩዎ አይደል…? አሁን ወደ እርስዎ ተመልሻለሁ። እባክዎ ባለቤትዎን ይምከሯቸው ብዬ ጀምሬም አልነበር…? እንቀጥል
ችግሩ ምን መሰልዎ… “ያው እንደሚያውቁት…” ብዬ ልልዎት ነበር ለካስ እርስዎ ምን ችግር እንዳለብን ምን አበሳ በላያችን ላይ እንደተጫነ አያውቁምና…
ይህውልዎ ወይዘሮ አዜብ ባለቤትዎ ዜጎቻቸውን እያማረሩ ይገኛሉ። እንዲገጥም እያባረሩ የሚልም እንጨምርበት። እውነቴን ነው የምልዎ… እኔ የእርስዎም፤ የባለቤትዎም፣ የእናት ድርጅትዎም ወዳጅ ነኝ… ማንም ያላወቀልኝ ወዳጅ። ነገር ግን ሀገሬው የሚያወራውን እሰማለሁ ሰምቼም እናገራለሁ። ስለዚህ ንግግሬን ከክፋት አይዩብኝ ለራሳችን ብዬ ነው…
ባለቤትዎ በትዳርዎ ላይ ያላቸው አስተዳደር የተሳካ ሊሆን እንደሚችል አስባለሁ። በሀገር ማሰተዳደር ላይ ግን “ከማስተዳደር ይልቅ ማደናገር ነው የያዙት” እያለ የማያማቸው ኢትዮጵያዊ የለም። በሀገር ውስጥ ያለው ህዝብ በየ ቡና ረከቦቱ እና በየመጠጥ ባንኮኒው፤ በውጪ ያለው ደግሞ በየ አደባባዩ እና በየ ኢንተርኔት መስኮቱ… ባጠቃላይ ባለቤትዎን ሁሉም ያብጠለጥላቸዋል። እኔማ ይሄንን ሳይ ውይ… ወደዛ “በቃኝ” ባሉ እና በተገላገሉ እያልኩ ሁሌ ነው የምመኘው።
አንድ ግዜ እርስዎ በአንድ ቴሌቪዥን ጣብያ ባደረጉት ቃለ ምልልስ “እኔ ገንዘብ ብፈልግ መለስን ከዛ ስራ ነው የማስለቅቀው…” ሲሉ ተናግረዋል። ታድያልዎ ይንን ንግግርዎን በቅርቡ ድጋሚ አዳምጬው ነበር። እና በሀሳቤ ቀዳማዊት እመቤታችን ገንዘብ በፈለጉ… ስል አጥብቄ ተመኝቻለሁ። ለምን እንደሆነ መቼም ይገባዎታል…
እኔ የምልዎት ግን በዛ ቴሌቪዥን ላይ “በአለም የመጨረሻዎቹ ደሀ መሪዎች እኛ ነን” ሲሉ የሰማሁት ነገር ጆሮዬ ነው… ወይስ እውነት እንደዛ ብለው ተናግረዋል? ምን ነካዎ… ቢያንስ ቢያንስ ለመልካም ገፅታችን ሲሉ እንኳ እነ ኢፈርትን፣ እነ ጉናን፣ እነ መስፍን ኢንጂነሪንግን፣ እነ መሰቦን፣ እነ ወጋገንን፣ እነ ወዘተን ጠቅሰው “መካከለኛ ገቢ ካላቸው መሪዎች መካከል ነን” ቢሉ ምን ነበረበት? ለምን ህዝቡስ ሰጥቶ እንዳልሰጠ ይቆጠራል? እኛ በዚህ በኩል መልካም ገፅታን ለመገንባት መከራችንን ስናይ እርስዎ ደግሞ በዚህ በኩል ሲያፈርሱ ጥሩ ነው…? (ለነገሩ ይሄ እርስዎን ሳስመክርዎ ለመካሪዎ የምነግረው ይሆናል)
ለአሁኑ ግን እባክዎን ወይዘሮ አዜብ ባለቤትዎን ይምከሩዋቸው…
ዋና የጨነቀኝ ነገር ምን መሰልዎ… ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየደረሰባቸው ያለው ተቃውሞ በየግዜው እየበረታ፤ እየበረታ የመምጣቱ ነገር ነው። እንደኔ ግምት ከዚህ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንኳንስ ህዝቡ እና የገበታ እንጀራቸው ራሱ በፈቃደኝነት የሚጠቀለልላቸው አይመስለኝም።
ለዚህ ምክንያቱ ብዙ ነው፤ ከብዙዎቹ መካከል የኑሮ ውድነቱ ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ እየጨመረ ቁርስ እና ምሳ ለመብላት እንኳ ድርጅቶች ስፖንሰር ካላደረጉ የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱ ነው። ለዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልስ “የዕድገት መገለጫ ነው” የሚል ነው። ይታይዎት ርሃብ የዕድገት መገለጫ ሲሆን… ህዝቡ በዚህ ጉዳይ በየጓዳው እያጉረመረመ ለመሆኑ መረጃ አለኝ። በርግጥ ማስረጃ የለኝም… (በቅንፍ የመረጃ እና የማስረጃን ልዩነትና አንድነት ለመረዳት ባለቤትዎን ይጠይቁ)
እንግዲህ እርስዎም ያስቡት ይህ ማጉረምረም እየጠነከረ ሲሄድ ሊፈጠር የሚችለውን ይገምቱ…
ቀዳማዊት ሆይ፤ እውነቱን ልንገርዎ… እኔ እያቃዠኝ ነው…! ህዝቡ ብሶት በማቆር ላይ ነው። ብሶት ምን እንደሚያደርግ ለርስዎም ለርሳቸውም ለመንገር አይቃጣኝም። ስለዚህ እባክዎን ይምከሯቸው።
“ህዝቡ ይወደኛል” ብሎ መዘናጋት ለጋዳፊም አልበጀም። ለማንኛውም ተዘገጃጅቶ መጠባበቅ ይሻላል። ውይ ምን ነካኝ የምን መጠባበቅ አመጣሁኝ? መጠባበቅ ቅርቃር ውስጥ ገብቶ ለመጣበቅ ይዳርጋል እንጂ ዋጋ የለውም። ግድየልዎትም ዝም ብለው “በቃኝ” እንዲሉ ቢያደርጉ ነው የሚሻለው። ምን አስጨነቅዎ “የመለስ ጭንቅላት ለልጆቼ ትምህርት፣ ለቤት መግዣ፣ ከዛም በላይ በሚሆን ገቢ ያመጣል ብለው የለ…? ይህንኑ ለርሳቸውም ይንገሩዋቸው። መንገር ከፈሩም “YouTube” ላይ ያገኙታል ይክፈቱላቸው።
ለነገሩ እንደሰማነው ከሆነ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በምድር ላይ የሚፈሩት ብቸኛ ሰው እርስዎ ነዎት። አንድ ግዜ አንድ ወዳጃችን በፃፈልን መጣጥፍ፤ ያኔ በበረሃ ዋሻ እያላችሁ እንኳ እንዴት እንዴት ያሽቆጥቁጡዋቸው እንደነበር ነግሮን አድንቀንዎታል። እንዲህ ነው እንጂ! እኔም ዛሬ ይሄንን ብቃትዎን ተማምኜ ነው ይምከሯቸው ማለቴ።
እኒያ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና “የሚበላውን ያጣ ህዝብ መሪውን ይበላል!” ብለው ተናግረዋል። እኔም ያስጨነቀኝ ይህው ነው። ጠቅላይ ሚንስትርዬን እወዳቸዋለሁ እርስዎንም እወድታለሁ እናት ድርጅታችንም ደስ ትለኛለች። ታድያ የሚበላውን ያጣ ህዝብ “ሆ” ብሎ እንዲበላችሁ አልመኝም። ስለዚህ ልክ ይሄ መልዕክት እንደደረስዎ ከባለቤትዎ ጋር ይማከሩ እና “በቃን” ይበሉ። እውነቴን ነው በቃችሁ! ምንም ባይፈጠር እንኳ ይሄን ሁሉ አመት እናተ ብቻችሁን እዳ አለባችሁ እንዴ? ስለዚህ “ይብቃችሁ”
ውድ ቀዳማዊ እመቤታችን፤ እንግዲህ ባለቤትዎ እኛ አጠገባቸው ሆነን ብንናገር ሊሰሙን አልቻሉም። እስቲ እርስዎ ደግሞ በሚስት ዘዴ ይምከሯቸው። አልመክርም ካሉ ለርስዎ ደግሞ ሌላ ዘዴ እናፈላልጋለን! እስከዛው ሰላም ይሁኑ!
በመጨረሻም
ማርች 8
ትላንት የሴቶች ቀን ሴቶች በሚገኙበት ሁሉ ተከብሮ ውሏል። እኔም ቀዳማዊት እመቤትን ጨምሮ ሴቶቻችንን በሙሉ እናኳን አደረሳችሁ እላለሁ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ይህንን ክብረ በዓል በዋናነት እንዲያሰናዳ ሃላፊነት የተሰጠው አንድ የሚኒስቴር መስሪያ ቤት አለ። ማን መሰላችሁ…? “የሴቶች የህፃናትና የወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር” መስሪያ ቤት ነበር። ይሄ ሚንስቴር መስሪያ ቤት ሁሌ እንዳስገረመኝ ነው። እንዴት ማለት ጥሩ ጥያቄ ነውና እንዴት…? ይበሉኝ
መስሪያ ቤቱ ሴቶችን ይዟል፣ ህፃናትን ይዟል እንዲሁም ወጣቶችን ይዟል። እዚህ ውስጥ የቀሩት ሽማግሌዎች ብቻ ናቸው። ታድያ እነርሱንም አካቶ ለምን “የሰዎች ጉዳይ ሚንስቴር” አይባልም? እያልኩ ሁሌ እገረማለሁ።
የሳምንት ሰው ይበለን!
አማን ያሰንብተን!
Tags: addis ababa, Amharic, Ethiopia, Ethiopians, export, health, immigration, import/export, market, money transfer, politics, scholarship
Posted in Amharic | No Comments »