በክፍሉ ሁሴን
እንደመንደርደሪያ አንዳንድ ትውስታ
ጊዜው 1967 ዓ.ም ክረምት።ክረምት መሆኑን የማስታውሰው ት/ቤታችን በተለመደው ዋና የዝናም ወራት ተዘግቶ ሰፈር በጭቃ ተራግጠን ውለን ስንገባ ተሸክመን ይዘን በምንገባው ጭቃ ምን ያህል ቤተሰቦቻችንን እንደምናስመርርም ትዝ ስለሚለኝ ነው።በተለይ ግን የስድሳ ሰባቱ ክረምት ከሁሉም በላይ ትክዝ የሚለኝ አንድ ምሽት አንዳፍታ የሚያሸብረን ሁኔታ በመከሰቱ ነው።የአስር አመት ከዘጠኝ ወይም ከአስር ወር ልጅ ስሆን በዚያን ጊዜ ህጻናት ከነበሩት ሶስቱ ወንድሞቼ በቀር ታናሽ ወንድሜና እናቴ በተከሰተው ሁኔታ እጅግ ተረብሸን ነበር።ራስ አሉላ በቀለ የሚባሉ ደርግ ያሰራቸው ወይም የገደላቸው ሰው በጅምር ሳይጨርሱት የተውትን ቪላ የተወረሱ የባለሃብት ቤቶችን እንዲያስተዳድር የተቋቋመው የኪራይ ቤቶች ጅምሩን ጨርሶ ለሩዋንዳ መንግስት ኤምባሲ ጽ/ቤትነት እስኪያከራየው ድረስ ሰፈራችን ይጠራ የነበረው “ቦሌ ድልድይ”ተብሎ ነበር።በተለይ የእኛ ቤት የቡልቡላ ወንዝ ባይኖር ኖሮ ወሎ ሰፈር ተብሎ ከሚታወቀው የጎረቤት መንደር እንዳንዱ ሊሆን በቻለ ነበር።ከወሎ ሰፈር ከወንዙ ወዲህ ማዶ ወደቦሌ በኩል በመሆናችንም የከፍተኛ 17 ቀበሌ 20 በኋላም ሩዋንዳ ኤምባሲ ነዋሪዎች ለመባል መብቃት ብቻ ሳይሆን ወሎ ሰፈርን ጨምሮ በሌሎች አጎራባች ቀበሌ ያሉ ልጆች በብዛት በቀይ ሽብር ሲቀጠፉ የተረፉትም ሰቆቃ ሲፈጸምባቸው አስተዋይና ደግ በነበረው የወቅቱ የቀበሌ ሊቀመንበራችን አቶ ተፈራ እንዳለ ምክንያት አገር አቀፍ ከነበረው ግፍ የእኛ ሰፈር ልጆች በአቶ ተፈራ ደግነት ልንተርፍ ችለናል።
የአሁኑ ዘመንም አሸባሪው የወያኔ አገዛዝ ራሱ ኢትዮጲያውያኖችን አሸብሮ ሌሎችን በአሸባሪነት እየፈረጀ እንደመሆኑ በዚያን ጊዜ በተለይ የእኛን ቤተሰብ ወዳሸበረን ጉዳይ ልመለስ።ከምሽቱ ወደ ሁለት ተኩል አካባቢ ስልካችን ተንጫረረች።እንደተለመደው ማንም ሳይቀድመኝ ተቅለብልቤ አነሳሁ።ፒ 11 ተብሎ ከሚታወቀው የአየር ሃይል የቅጥር ዘመን ጀምሮ ኢትዮጲያ አየርመንገድ በተመሳሳይ ወቅት አብረው እስከተዛወሩበት የአብዮቱ ዘመን መባቻ ድረስ የረጅም ጊዜ የአባቴ ጓደኛ የሆነው ነፍሱን ይማረውና አብራሪ ሻለቃ ጌታቸው ከበደ ነበር የደወለው።ሁሌ እንደሚያደርገው በዚያን ምሽት አባቴን ባወጣለት ቅጽል ስም አልጠራውም።በቀጥታ “አባትህ አለ?”ነበር ያለኝ። “በሯል” ለሚለው መልሴ በመጣደፍ እናቴን እንዳቀርብለት ጠየቀኝ።ጌታቸው በመስመር በራሪነት ተመድቦ በዚያን ጊዜ ሲ 47 ወይም ዳኮታ የሚባለው አውሮፕላን ላይ የሚሰራ ስለነበር የበረራ ተረኛ ካልሆነ በስተቀር እንደሌሎች ሰራተኞች በመደበኛ የስራ ሰአት መ/ቤት መገኘት አይጠበቅበትም ነበር።በተቃራኒው አባቴ በበረራ ማስልጠኛ ት/ቤት በበረራ አስተማሪነት ተመድቦ ይሰራ የነበር ከመሆኑም ባሻገር አልፎ አልፎ ፓይፐር ከብ ተብላ በምትታወቀው አነስተኛ አውሮፕላን በአብዮቱ ዋዜማ በሜካናይዝድ እርሻ ላይ ተሰማርተው ለነበሩ የውጪ አገርና የአገሩ ውስጥ ባለሃብት የቻርተር አገልግሎት በመስጠት እያበረረ ከአዲስ አበባ ውጪ እንደመስመር ፓይለቶች ያድር ነበር።/ባለሃብቶቹ ንብረታቸው ቢወረስም የተወሰኑቱ ፈረንጆች ከውርሱ ጋር በተያያዘ ጭፍጫፊ ምክንያቶች ወደ ቀድሞ ሃብታቸው ከአብዮቱ መባቻም በኋላ በቻርተር አገልግሎት ምልልስ አድርገዋል።/በተረፈ እንደማንኛውም ሌላ የአየርመንገዱ ሰራተኛ በመደበኛ የስራ ሰአት ተማሪዎቹን አስተምሮ ቤቱ ይመለሳል።በዚያን እለት የደንብ ልብሱን ለብሶ እንደወጣ ስላልተመለሰ በደመናና ሌሎችም ምክንያቶች ደጅ ከሚያሳድሩት የቻርተር በረራዎች አንዱ አድርጌ ስለቆጠርኩት መልሴ “በሯል”ሆነ።ለማንኛውም እናቴ ስትቀርብ ተመሳሳይ ጥያቄ ከጠየቃት በኋላ ፍጹም በተረጋጋ ሁናቴ ስለመለሰችለት ተገርሞ “ለመሆኑ ምንም ተኩስ አልሰማሽም ወይም ዜና በቴሌቪዥን?”መልሷ “የምን ተኩስ እነዚህ እየተንጫጩ ምን መስማት ይቻላል፤ቴሌቪዥኑም እንጨት እንጨት ስለሚል ትቼዋለሁ።”እሱም “የቴሌቭዥኑ ይሁን ካልሞታቹህ በቀር የትናየት የሚሰማውን ተኩስ አየርመንገዱ ስር ተቀምጠሽ እንዴት አትሰሚም?”ሲል ያልጠበቅነውን ዱብእዳ ጣለብን።ያኔ ባይገባኝም ከአመታት በኋላ እንደተረዳሁት የአየርመንገዱ ሰራተኛ ለካ “የወዛደር ደመወዝ ሰላሳ ሸመታው ስድሳ”በሚል መሪ መፈክር አድሞ የደመወዝ ጭማሪና ሌሎች ማሻሻያዎች በመጠየቁ “ለሰፊው ህዝብ የመጣው አብዮታዊው መንግስት”ዙሪያውን ከቦ በጥይትና በሰደፍ ሰራተኛውን እንካ ይቀመስልህ ይለው ኖሯል።
በኢትዮጲያ ሰራተኞች ንቅናቄ ታሪክ ውስጥ ስማቸው ዝንተአለም ገናና የሆኑትን አቶ አበራ ገሙ አይነቱን አርበኞች እንዳፈራው የምድር ባቡር ድርጅትና የአቃቂ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ባይሆንም የኢትዮጲያ አየርመንገድ ሰራተኛም በደጉ ዘመን ለመብቱ ወደኋላ የማይል እንደነበር ታሪክ ያወሳል።እኔ በሚገባ እስከማውቀው ድረስ ያ እንቅስቃሴ በአየርመንገዱ ለመጨረሻ ጊዜ የተካሄደ የጋራ የመብት ትግል ነው።እንደአብዛኛው የኢትዮጲያ ህዝብ በግል ከማልጎምጎምና በየመሸታ ቤቱ ሳያስተጓጉል በደል የሚያደርስበትን አገዛዝ ድምጹን ቀብሮ ከማማት በቀር ተደራጅቶ እምቢ ለመብቴ ማለት ከዚያ የደርግ እመቃ በኋላ የፋራ ታሪክ ሆኖ ቀርቷል።በአዲስ የቃላት ሽንገላ የኢትዮጲያን ሰራተኛ “ላብአደር”እያለ የሚጠራው አዲሱ የወያኔ አገዛዝ ደግሞ ጭራሹኑ የኢትዮጲያ አየርመንገድ ሰራተኛ ምን ግፍ ቢውልበት የስራ ማቆም አድማ እንደማይፈቀድለት በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መንፈስ አውጆ ሲያበቃ የላብአደሩ መብት ያላንዳች እንከን መረጋገጡን አበሰረ።/በወያኔ ጊዜ በሥራ ላይ ያለውን የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ይመልከቱ/።ለነገሩ የየትኛውም ድርጅት ሰራተኛ እንኳን ሊያድም ቀርቶ ከአገዛዙ የተለየ ሃሳብ እንዳለው ከተጠረጠረ በቁም ከነቤተሰቦቹ ፍዳውን የሚቀበልበትን ልዩ የወኔ መስለቢያ ስልት ወያኔ ከቀየሰ መቆየቱን ገና በማለዳ በኢትዮጲያ ንግድ ባንክ ሰራተኞችና እንዲሁም ነጻ የሰራተኛ ማህበር ፈጽሞ እንዳይኖር የወሰደው የፈላጭ ቆራጭ ብቻ ሳይሆን የለየለት የወሮበላ ተግባር የሚዘነጋ አይደለም።በዚህ ጉዳይ ላይ መመላለሴ ስለማይቀር የጀመርኩሎትን የቤተሰቤን የዚያን እለት ምሽት ልቋጭልዎ። አባቴ ለበረራ ከተሰማራበት ቦታ ተመልሶ ካረፈ በኋላ አየርመንገዱ በጦርሰራዊት ከመከበቡ ጥቂት ደቂቃዎች በፊት የደንብ ልብሱን ጃኬት በሻንጣው ይዞት በነበረው የሹራብ ጃኬት ለውጦ የእስልምና ሃይማኖት ጥብቅ ተከታይ ለነበሩት እናቱ የገዛዛውን/የእስላም ጾም መግቢያ ወይም መፍቻ ዋዜማ ነበር መሰለኝ/እቃ ለማድረስና ወዲያውም በምንድህስና ሙያ የተመረቀ የቀድሞ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ጓደኛው ባደረገለት ግብዣ/እንደ አባቴ ሳይሆን ጓደኛውም የእስልምና ሃይማኖቱን አጥብቆ የያዘ ነበር/በቀጠሮ ለመገኘት ወደሱ ቤት ገሰገሰ።እዚያ በቴሌቪዥን የአየርመንገዱን ረብሻ ከሰማ በኋላ ደውሎልን ተረጋጋን።በዚህ ጽሁፌ ዝቅ ብዬ ላነሳው ካሰብኩት ጉዳይ ጋር ስለሚያያዝ ተጨማሪ አንድ ሁለት ትውስታዎቼን ላክልና ይህን ሁሉ እንድዘበዝብ ወዳረገኝ ዋና ነጥብ ልዝለቅ።
ሻለቃ ጌታቸው ከፓይለቶች ማህበር ክበብ እንዳጣራው አብዛኞቹ የበረራ ማስልጠኛ ት/ቤት ባልደረቦች ወደቤታቸው አለመመለሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውም እንደተረበሹ ለእናቴ ስለነገራት አባቴ ደውሎልን እፎይ እስክንል ድረስ ሌላው የአባቴ ጓደኛና በአንጋፋ የበረራ አስተማሪነቱ ወደሚታወቀው ካፕቴን ወይም በአየር ሃይል ማእረጉ ሌተ/ኮሎኔል ቶላ ቢነጋ ቤት መደወል አስፈላጊነቱ ለእናቴ አልታያትም።ይልቁን በዚያ በደጉ ዘመን ባለቤቱ የእናቴ ጓደኛ የሆነች ልጆቹ ደግሞ የእኛ ጓደኛ የሆኑ ጎረቤታችን የሆነና በዚያን ጊዜ በአየርመንገዱ የጄት ሞተር ጥገና ክፍል በመካኒክነት በሌሊት ፈረቃ የሚሰራ ሰው ቤት ሄዳ ለማጣራት ስለወሰነች አብሬያት ሄድኩ።እንደተፈራው መካኒኩ ጎረቤታችን በረብሻው ምክንያት ለሌሊት ፈረቃ ስራው እንዳልሄደና ሁኔታውም ጥሩ እንዳልሆነ ከገለጸልን በኋላ ሲነጋ ማጣራት እንደሚሻል መክሮን ተመለስን።ይህ ሰው ከመጀመሪያውም የአየርመንገዱ ቅጥር ሲሆን ከተራ መካኒክነት ተነስቶ በአየርመንገዱ የአቪዬሽንና ጥገና ት/ቤት በአሰልጣኝነት ከማደግ ጀምሮ ችሎታው እስከፈቀደ ድረስ በደርጉ ስርዐት የጄት ሞተር ጥገና ክፍል ስራ አስኪያጅነት ያላንዳች መድልዎ ተሹሞ ሲያገለግል ቆይቶ በጡረታ ተገልሎ እስከዛሬ በህይወት አለ። “ፈሪ ተራራ ነው ዘላለም ይኖራል፤ጀግና ብርሌ ነው ወድቆ ይሰበራል”የሚለውን አባባል በሚያስታውሰኝ መልኩ የቀድሞው መካኒክ እድሜው አለቅጥ ተንዘላዝሎበት ነው መሰለኝ ወያኔ ካመጣው የጎሳ ፖሊቲካ ጥምቀት ወስዶ በሰብቅ ተግባር በመሰማራት የቀድሞ ባልንጀሮቹን በወያኔ እስከማስወጋት ድረስ ሄዷል።በተለይም ራሱ በአባቷ ከኤርትራ የምትወለድ ሴት አግብቶ ዘጠኝ ልጆች አዲስ አበባ ላይ ወልዶ እንዳልከበረ የወያኔና የሻዕቢያ ከንቱ ደም አፋሳሽ ጦርነት ሲመጣ ቀድሞ በመሰሪ ባህሪውና በደካማ ሰብእናው ይሸነቁጡጥ የነበሩትን አንዳንድ እንደሚስቱ በግማሽ የኤርትራ ውልደት ያላቸውን በኢትዮጲያዊነታቸው እንከን የማይወጣለቸው ብቻ ሳይሆን ለአገራቸው ያበረከቱት አስተዋጽዖ በክብር መዝገብ ላይ የተጻፈላቸውን ሰዎች ሁሉ ከአገር እንዲባረሩ ለማድረግ ፋትሯል።ምን ያህል እንደተሳካለት ባላውቅም ባንድ ኢትዮጲያዊ ላይ ያደረገው ሙከራ ግን በራሱ በወያኔ ካድሬዎች እንዳሰደበው መረጃዎች አሉኝ።ሙሉጌታ ሉሌ እንደሚሉት ድሮ በመሃይማን ካድሬዎችና ሶስተኛ ደረጃ ጮሂዎች ጥቆማ ብዙ ንጹሃን ኢትዮጲያውያን በመደብ ትግል ስም እንዳልተጋዙና እንዳልተቀጠፉ ዛሬ ደግሞ በጎሳው ፖሊቲካ ላይ አምባገነንት ተጨምሮበት ዜጎች የዜግነት መብታቸውንም ጭምር ፍጹም የኢትዮጲያ ጠላት በሆኑ ሰዎች ሰብቅ ያጣሉ።
አሳዛኙ ነገር ግን የዘሬን ብተው ያንዘርዝረኝ በሚመስል መልኩ ልጆቹ ቢያንስ ከልጆቹ አንዱ በለየለት ጎሰኝነት የተለከፈ መምሰሉና ከሃያ አምስት አመት በላይ በነጻነት ማሰብ ማስተዋል መጠየቅና መማር የሚቻልበት አሜሪካ ቢኖርም ሰማይ ጠቀስ ህንጻ እንዲሁም የቀለበት መንገድ በአዲስ አበባና መቀሌ በብዛት ስለተቆለለና ስለተነጠፈ መወድስ ቅኔ ለመለስ ዜናዊ ልታቀርብለት ይገባል ሲል በፌስ ቡክ በኩል ባልንጀራው ካደረገኝ በኋላ እስከዛሬ ይህንኑ ጅል ሃሳብ ሊሸጥልኝ እንደታገለ አለ።የአራተኛ ታናሽ ወንድሜ እኩያ ለሆነውና በዳላስ ቴክሳስ ኗሪ ለሆነው የቀድሞ የሰፈሬ ልጅ ብሩክ አረጋይ ዮሃንስ ኮንፊውሸስ የተባለ የቻይና ፈላስማ “መልካም አስተዳደር ባለበት አገር መናጢ ድሃ መሆን የሚያሳፍር፤ ብልሹ አስተዳደር ባለበት ደግሞ የናጠጠ ሃብታም መሆን እንደሚያሳፍር”የተናገረውን በማንሳት በወያኔ ጋጠወጥ አገዛዝም የሚገነባውና በጥቂት ምርጦች እጅ የሚግበሰበሰው ሃብት ሁሉ የእኛው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም እንዳሉት
“ቂልነት ነው፤ትዕቢት?
ወይስ ደደብነት?
ነገ የሚፈርሰው ዛሬ የሚካብበት?”ብዬ ላስረዳው ከጀመርኩ በኋላ አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት አይሰማም አይነት ነገር መሆኑ ስለገባኝ ካልተትረፈረፈኝ በቀር ከብሩክ አይነቱ ሰው ጋር ብዙም ጊዜ ላላጠፋ ወሰንኩ።ይሁንና ይህን የግል ተሞክሮዬንና ትውስታዬን አደባባይ እንዳወጣው የሚያስገደድ አንጋብጋቢ አገራዊ ጉዳይ አጋጠመኝ።
በኢት/አየርመንገድና ተዛማች ጉዳዮች የኤልያስ ክፍሌ ሃሳብ
በራሳችን ስንፍና ራስ ወዳድነትና አርቆ አለማሰብ ከጣሪያ በላይ የሄደው የወያኔ ዘረኛና ግፈኛ አገዛዝ እነበቀለ ገርባንና እነደበበ እሸቱን በድጋሚ ያፈነበትን ምክንያት በማድረግ ኤልያስ ክፍሌ ከወትሮው በተለየ ወያኔን በሚያሽመደምድ ተግባር እንድንሰማራ ሃሳብ አቀረበ።ሃሳቡ በሁለት ተከፍሎ ውጪ አገር ለምንኖርና በአገር ውስጥ ላሉ አገር ወዳድ ኢትዮጲያውኖች የቀረበ ሲሆን እነአንዷአለም የሚከፍሉትን መስዋትነት እንጋራ በሚል መሪ መፈክር ሰባት ነጥቦችን ይዟል።ከነጥቦቹ አንዱ ታዲያ የምመካበትና የአገሬን ሰንደቅአላማ እያውለበለበ በመብረር አገሬን በበጎ በማስጠራቱ ብቻ ሳይሆን እኔንም ያሳደገ በነጻ ቲኬት የተንፈላሰስኩበት አየርመንገድ ላይ ያነጣጠረና ማእቀብ እንድንጥልበት የሚጠይቅ በመሆኑ ላንዳፍታ እንድደነግጥ አደረገኝ።ወደቀልቤ ስመለስ ግን የኤልያስ ሃሳብ በጎና በአስቸኳይ ተወያይተንበት ልናዳብረው የሚገባ መስሎ ስለተሰማኝ ለመጀመሪያ ደረጃ ውይይት በፌስ ቡክ ላይ ሰቀልኩት።ውጤቱ “በጎ ሃሳብ ያላቸው በቸልተኝነት ወይ በፍርሃት ዝም ስለሚሉ ክፉ ሃሳብ ያላቸው ይገናሉ” በሚለው የቆየ ይትባሃል መሰረት ከፌስ ቡክ ባልንጀሮቼ ሁሉ የመለስ ዜናዊ አፍቃሪ የሆነው ሳተናው የቴክሳሱ ነዋሪ ብቻ ብቅ ብሎ “አባትህና አባቴ የሰሩበትን አሁን ደግሞ ወንድምህና ለኔ ደግሞ ‘አብሮ አደግ ጓደኛዬ’የሚሰራበት ‘የቤተሰባችን’ አየርመንገድ ላይ የምታደርገውን አሉታዊ ዘመቻ አቁም!ወንድምህ ስራ አጥ እንዲሆን ትፈልጋለህ ወይ?”ሲል ሁልጊዜም የምጠረጥረውና ወያኔም እንደታላቅ ወንድሙ ሻዕቢያ ተሰደን የምንኖረውን ሲቻል በአፍቅሮ ነዋይ መሸበብ፤ ሳይቻል አገር ቤት ባሉ ቤተሰቦች ህልውና ከሲያትል እስከሜልቦርን ተሰደው የሚኖሩት አብዛኞቹ ኤርትራውያን ስደተኞች ጸጥ በተደረጉበት ዘዴ እኛንም ጸጥ የማድረግ እቅድ እንዳለ ጠቆመኝ።ከንቱ ልፋት! አንደኛ አራተኛ ታንሽ ወንድሜ የአባቱን ኮስታራ ሃሞት ባይወርስ በወጣትነቱ የትልቅ ጄት አውሮፕላን ዋና አብራሪ/pilot in command/አይሆንም ብዬ ስለማምንና ይኸው ሃሞት ለማናቸውም ፈታኝ ሁኔታ አዘጋጅቶታል ብዬ ስለማስብ ነው።በዘመናችን አንዳንድ ፓይለቶችና ሌሎች ባለሙያዎች ላይ እንደሚታየው ተዘናግቶ ተልፈስፍሶና ተስገብግቦ ከአላሙዲን ጋር ባለሟልነት ከቆስጠንጢኖስ ጋር ደግሞ ባልንጀርነት ገብቶ ከሆነ እኔ ለራሴ ኑሮ ሃላፊነቱን እንደወሰድኩት ሁሉ ሃላፊነቱን ይወስዳል።ሁለተኛ በዚህ ረገድ ለሚመጣብኝ ግልጽና ረቂቅ ዛቻ/subtle blackmail/ አንዳርጋቸው ጽጌን በአርዓያነት ስለወሰድኩ ወያኔ ከነጀሌዎቹ ከሚደክም በቀር ይኽ ግድም ማፈግፈግ አይኖርም፤በስደት አብረውን እንደሚኖሩት የቀድሞ ኢትዮጲያውኖች/ኤርትራውያኖቹን ማለቴ ነው/ በነጻነት አገር እየኖሩም በፍርሃት ቆፈን መቀፍደድም የለም።በመሆኑም አሁን በኢትዮጲያ አየርመንገድ አውሮፕላኖች ላይ ባለመሳፈር ማእቀብ የመጣሉን ጉዳይ አግባብነት ወደ መፈተሹ እሄዳለሁ።
ስለኢት/አየርመንገድ ብሄራዊ እሴትነትና የወያኔ የገቢ ምንጭነት
በግሌ እንደማምነው ኢትዮጲያችንና ኢትዮጲያኖች በብዙ ረገድ በተዋረድንበት ዘመን ከለየለት የከፋ ገጽታ የሚታደገን አየርመንገዳችን ሲሆን አትሌቲክስም በቅርብ ከደረሰበት ስብራት በቀር ሌላው መልካም ገጽታችን ነው።በረሃብተኝነት በስደተኝነት በአረብ አገር ግርድና በኤድስ በህገወጥ የሰዎች ሽግግር የሚነሳውን ክፉ ስማችንን ሁልጊዜም በበጎ ሚዛን እንዲደፋ የሚያደርገው አየርመንገዳችን መሆኑ ጥርጥር የለውም።ምንም እንኳን ዛሬ አዛዥ ናዛዥ የሆነበት ወያኔ ቢሆንም የውጪ ምንዛሪ ከማስገባትም በላይ በሚያስገኝልን መልካም ስም የተነሳ ብሄራዊ እሴታችንም አድርጌ እመለከተዋለሁ።ከምር በብሄራዊ እሴትነቱ ወይም ጥሪትነቱ እንዲቀጥል ለማድረግ ግን የአየርመንገዱ ሰራተኞችም ሆኑ ሌሎች ኢትዮጲያኖች ነጻ መሆን አለባቸው።በአፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ከኢትዮጲያ አየርመንገድ ያነሰ ትርፍና ስኬት ያላቸው አየርመንገዶች ለሰራተኞቻቸው የተሻለ ክፍያ እንዲሁም በነጻ መደራጀትና ይህንኑ የማስከበር መብታቸውን ያከብሩላቸዋል።ኢትዮጲያ አየርመንገድ ከተመሰረተ ከብዙ አመታት በኋላ የተመሰረተው የጎረቤት ኬንያ አየርመንገድ ዛሬ በተወዳዳሪነት እስከመገዳደር የደረሰው ሰራተኞቹን በተለጣፊ የካድሬ ሰራተኛ ማህበር እየለጎመ በአለማቀፍ ደረጃ የታወቀ እስከ ስራ ማቆም ድረስ የሚያቀዳጅ መብታቸውን እየገፈፈ አይደለም።የኬንያ ኤርዌይስ ሰራተኞች በተለያየ ጊዜ ባደረጉት የስራ ማቆም አድማ የስንግ መንግስታቸውን ይዘው መብታቸውን አስከብረዋል።ኬንያ የራሷን ዜጎች በማሰልጠንና በጥሩ ክፍያ የፓይለቶቿን ቁጥር ስታሳድግ በወያኔ ስርዓት ደግሞ ልምምጥ አከል በሆነ አቤቱታ መልክ ደመወዝ እንዲስተካከልላቸው የጠየቁ ፓይለቶች “መንገዱን ጨርቅ ያድርግላቹህ”አይነት ስለተባሉ በአንድ ወቅት በብዛት ወደመካከለኛው ምስራቅ አገራት አየርመንገድ ፈልሰዋል።ይህ የተፈጸመው ዛሬ ከአምባገነኑ የዘረኛ አገዛዝ ጎራ ወጥቶ የህዝቡን ጎራ በተቀላቀለው ስዬ አብርሃ የቦርድ ሊቀመንበርነት ጊዜ ሲሆን ከዚህም የከፋ ነገር በአየርመንገዱ ተፈጽሞ እንደነበር ይታወቃል።ባጭሩ ግን ድምር ውጤቱ አየርመንገዱን ለከፍተኛ የፓይለት እጥረት ሲያጋልጠው ከስሮ ከተዘጋ እንደጋና አየርመንገድ ከመሳሰሉና መብረር ያቆሙ ፓይለቶችን እስከመቅጠር የሚያደርስ ደረጃ ላይ ተደረሰ።አስገራሚው ነገር ጋናውያኑ ፓይለቶች በእኛው ፓይለቶች የክለሳ ስልጠና ተሰጥቷቸው የሚከፈላቸው ደመወዝ ከእኛ ፓይለቶች የሚበልጥ መሆኑ ነው።እስከዛሬ ድረስ ወያኔ ለኢትዮጲያውን ፓይለቶች ተገቢውን ደመወዝ ላለመክፈል ፈቃደኛ ባለመሆን በብዛት የውጪ አገር ዜጎችን የቀጠረ ሲሆን ምን ያህል እንደሚከፈላቸውም በውል አይታወቅም።ከዚህም ባሻገር አየርመንገዱን ያቆሙት ፓይለቶች ብቻ ይመስል ለሌሎቹ ሰራተኞች የሚከፈለው ደመወዝ ዝቅተኛ በመሆኑ በአብራሪዎችና በሌላው ሰራተኛ መካከል ክፍፍልን የፈጠረ ሁኔታ እንዲኖር አድርጓል።
ወያኔ አየርመንገዱን ሲረከበውም ሆነ ዛሬም ድረስ አንዳችም ብሄራዊ ስሜት ስለሌለው አየርመንገዱን በዘላቂ እድገት ላይ ለማቆም ሳይሆን ለአገዛዙ ከሚሰጠው ትርፍ አኳያና በንግስናቸው ማግስትም ወዲያዉኑ እንደተረዱት በራስ አገር አየርመንገድ መብረር ለሚስገበገቡላት ከይሲ ነፍሳቸውም አስፈላጊ በመሆኑ ነው።በተቀር የአየርመንገዱ መሰረት የሆነውን የኢትዮጲያ አየር ሃይል እንዳልነበር አድርገው በየሳምንቱ ገበያና የእርሻ ማሳዎች ላይ በብዙ ሚሊዮን ዶላር የተገዙ ተዋጊ ጄት አውሮፕላኖችን ወደሚከሰክስ ተቋም ደረጃ በማውረድ ለአገሪቷ ተጨማሪ እዳ እንዳመጡት ሁሉ አየርመንገዱንም ለዚህ ከመዳረግ አይመለሱም ነበር።ይህ ጽሁፍ አለቅጥ ስለረዘመ ነው እንጂ አሁንም ቢሆን አየርመንገዱ ከዚህ አደጋ ሙሉ ለሙሉ አለመላቀቁንና እንዲያውም በጊዜ ብዛት ሊከሰት ስለሚችል የደህንነት ስጋትና የኪሳራ ምልክቶች ብዙ ማለት ይቻል ነበር።ባጭሩ ግን ሁልጊዜም የአየርመንገዱ መሰረት የነበረው አየር ሃይላችን በወያኔ እጅ እንዳልነበር መሆን አየርመንገዱን የጀማሪ አውሮፕላን አብራሪዎች አስተማሪ እጥረት በአንገብጋቢ ሁኔታ እንዲፈጠርበት እያደረገ ሲሆን የዚህ ውጤት በአየርመንገዱ ታሪክ ተሰምቶ በማያውቅ ሁኔታ በስልጠና ላይ የነበረና ለአገር አቋራጭ በረራ ለብቻው/cross country solo/እንዲሄድ የተደረገ ተማሪ ፓይለት ከአንድ ከሁለት አመት በፊት ተከስክሶ መሞቱ ነው።ከዚህ ጋር የተያያዘ ራሱን የቻለ ታሪክ ስላለ እንደስፈላጊነቱ በሌላ ጊዜ የምመለስበት ሲሆን አሁን የማእቀቡን ነገር ልቋጭ።
ሲሆን ሲሆን የኢትዮጲያ አየርመንገድም ሆነ የሌሎች ድርጅት ሰራተኞች የራሳቸውንም ሆነ አገራዊ መብት ለማስከበር በራሳቸው ተነሳሽነት የስራ ማቆምና ሌሎችም ተዛማጅ እርምጃዎችን ሊዎስዱ በተገባ ነበር።እውነታው ይህን የማይፈቅድ ስለሆነ ኤልያስ እንዳቀረበው ሃሳብ የኢትዮጲያውያንና በአጠቃላይ የሰብአዊ መብት መደፈር የሚያንገበግበው በውጪ አገር ነዋሪነቱን ያደረገ ሁሉ የኢትዮጲያ አየርመንገድ ለወያኔ ገቢ ማስገኘት ብቻ ሳይሆን የጥጋብ ምንጭ መሆኑን ተገንዝቦ ራሱን ወያኔን ከሚያደልብ ተግባር የኢትዮጲያ አየርመንገድን ቲኬት ባለመግዛትና ባለመሳፈር ጭምር መግለጽ ይጀምር።ልብ በሉ!ወያኔ የኢትዮጲያ አየርመንገድን በመጥለፍና ከነንጹሃን መንገደኞቹ ጋር ሊያጋዩ የቃጡ እንደማርታ መብራቱና ዋለልኝ አይነት ሽብር ፈጣሪዎችን እንደ ነጻነት አርበኛ የሚያይ ወሮበላና ዘረኛ ቡድን ነው።በኢትዮጲያ ህዝብ ላይ የሚደረገውን ግፍ በህዝባዊ እምቢተኝነት/civil disobedience/በመገዳደር ማእቀብ በኢትዮጲያ አየርመንገድም ሆነ በሌሎች የዘረፋ ተቋማቱ ላይ የሚጠይቁትን ግን ልማታችንን ለማደናቀፍ የተነሱ ሽብርተኞች ናቸው እንደሚልዎት ጥርጥር አይግባዎት።የወያኔን የአብዬን እከክ ለእምዬ እነተወውና በበኩሌ በግሌ የማውቃቸውን የሌላ አገር ዜጎችንም ወያኔ የሰብአዊ መብት አያያዙን በተጨባጭ እስኪያሻሽል ድረስ በኢትዮጲያ አየርመንገድ አትሳፈሩ እያልኩ ከመቀስቀስ ባሻገር በፈረንጅኛም “Proud of Ethiopian Airlines, yet I urge you to boycott it”በሚል ርእስ መጣጥፍ መልቀቄ አይቀርም።ይህ በእንዲህ እንዳለ በሽብርተኝነት ፈርጆ ወያኔ ካገታቸው ኢትዮጲያውያን አርበኞች መካከል ስለአንዱ ብዙም የማይታወቅ ነገር አንስቼ ልሰናበትዎ።
አንጋፋው ተዋናይ ደበበ እሸቱ አውሮፕላን ስለማብረሩ
የኤልያስን ሃሳብ ለማዳበር ስዳክር ብዙ ኢትዮጲያኖች በተለይም ወጣቶች ስለደበበ እሸቱ ያልሰሙት የሚመስለኝን ነገር ልነግራቸው ወደድኩ።ወዲያውም ጉዳያችን ከአቪዬሽን ጋር የተያያዘ በመሆኑ ጥሩ አጋጣሚ መስሎ ተሰማኝ።ደበበ እሸቱ ወደጥበብ ጥሪ በማዘንበል ወደ ትወና ከመግባቱ በፊት በኢትዮጲያ አየር ሃይል በእጩ መኮንነት ተመዝግቦ የአውሮፕላን አብራሪነት ስልጠና ለመውሰድ ገብቶ ነበር።ታዲያ አብራሪነቱ አቅቶት እንዳይመስሎት የወጣው።በተቃራኒው ብዙዎች የማይወጡትን የመጀመሪያ ደረጃ ስልጠና አጠናቆ አውሮፕላን ለብቻው ያበረረ ከመሆኑም ባሻገር እንኳን በኢትዮጲያ ደረጃ ቀርቶ እንደአሜሪካን አገር ባሉ ሃብታም አገሮች ሳይቀር በጉጉት የሚጠበቀውንና የሚቀናበትን ክንፍ/the coveted wing/የሚባለውን ለመውሰድ የጥቂት ሰአታት በረራ ሲቀረው ከአየር ሃይል ግቢ በተደጋጋሚ እያመለጠ ስላስቸገረ ተባረረ።ለመንገደኞች በሚሰጥና በደርግ ጊዜ በታተመ የአየርመንገዱ ሰላምታ መጽሄት ላይ ደበበ እንደገለጸው የወጣበት ምክንያት “ከብረት የጠነከረ የውትድርና ዲሲፕሊን”ስላልተስማማው ከአየር ሃይሉ በተደጋጋሚ እያመለጠ በማስቸገሩ መባረሩን ገልጿል።በመጽሄቱ ላይ አንብቤ ይሁን ባንድ አጋጣሚ ከአባቴ ጋር ቢራ ላይ የመተዋወቅ እድል ባጋጠማቸው ጊዜ የነገረውን ይዤ ይሁን ተዘነጋኝ እንጂ ሳብ ሳፊር በተባለችው አውሮፕላን ወደ 117 ሰአት ገደማ የበረረ ከመሆኑም በላይ የእነሜጀር ጄኔራል አምሃ ደስታ ኮርሰ እንደነበር ገልጿል።ዛሬ ታዲያ ከዚህ ታሪክ እኔን የሚገርመኝ ደበበ ሰው ሁሉ በዚያን ጊዜ ይሻማበት የነበረውን ግን በቀላሉ የማያገኘውን እድል ካገኘ በኋላ የአየር ሃይል ፓይለት መሆን የሚያስገኘው ዝና/glory/ሳያስጎመዠው ጥሎት በመውጣት እግረመንገዱን ከሃይልና ደም ከማፍሰስ ጋር ለተያያዘ ዝና ደንታ እንደሌለው ማስመስከሩ ነው።በህገአራዊት በሚመራው ፍርደገምድሉ ወያኔ ዘንዳ ይህ ትርጉም ስለሌለው አንጋፋው የጥበብ ሰው ዛሬ ከሌሎች አርበኛ ኢትዮጲያውያኖች ጋር አሸባሪ ተብሏል።ከፍጹም ንቀት ጋር የተያያዘውን እንዲህ ያለውን የለየለት ግፍ ለማስቆም መፍትሄው በተጨባጭ የሚታይ ተግባራዊ እርምጃ ብቻ ነው።አንዳንዶቻችን ኤልያስ ክፍሌን በአወዛጋቢነት በመውሰድ ምናልባት ሃሳቡን ከቁምነገር ባንወስደው እንኳን በመሰሪ ተግባር የተካነው ወያኔ ግን ኤልያስ ዝም ብሎ በድህረ ገጽ ብቻ የሚራቀቅና ጸጉር በመሰንጠቅ ጊዜውን የሚያባክን ሰው እንዳልሆነ ያውቃል።በመሆኑም ወያኔ በውጪ አገር ከሚኖሩ ኢትዮጲያውያን አርበኞች መካከል በግምባር ቀደም የሚፈራው የተግባር ሰዎችን ስለሆነ በየወቅቱ በሚፈበረኩ የፈጠራ ክሶች የኤልያስ አይነቱ ስም በማጣፈጫነት ይጠራል።ባጭሩ በወሬ መራቀቅ ቀርቶ ለወያኔ ማናቸውንም ትብብር የሚነፍግ ተግባር መታየት መጀመር አለበት።ከወያኔ ጋር በመሞዳሞድ ንግድ ማኪያሄድን እንደኑሮ መላ የያዙ ወገኖቻችንም የተሰማሩበት ተግባር ንግድ ሳይሆን ዘረፋ መሆኑን ተገንዝበው ከዚህ ተግባር በአስቸኳይ ሊታቀቡ ይገባል።በዚህ መንገድ የተግበሰበሰ ሃብት ሁሉ በድቡሽት ላይ እንደተገነባ ቤት መሆኑን ከቱኒዚያ ግብጽ ሊቢያና ሌሎችም እንዲያጤኑ እየመከርኩ ያልተማረው ገበሬ አጎቴ “ከፈረጃ ጋር የጠጣ ራሱ ፈረጃ ነው”በማለት የተረተልኝንም እንዲያሰላስሉት እተውላቸዋለሁ።
ሊመይሉልኝ ቢሹ kiflukam@yahoo.com
