Author Archive

የአባይ ግድብና የኢትዮጵያ ህዝብ – “ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ”

Tuesday, May 17th, 2011

ከደምስ በለጠ

በውጪ ያለው ኢትዮጵያዊ በሃገሩ ልማት ላይ ለመሳተፍ ያለው ፍላጎት ከፍተኛ ቢሆነም በ ወያኔ ስርአት የተፈተነ ተለምዶው የተነሳ ተቃውሞውን ሲያሰማ ቆይቶአል:: ወያኔዎቹ እንደሚሉት ዳያስፖራው በጋጠወጥነት አደባባይ እየወጣ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በጎደለው መንገድ የሚቃወምም አይደለም :: ሰሞነኛው የአብይ ግድብ ኡኡታ በተለይ በአገዛዙ በኩል እየታየ ያለው የሚዲያ ያዙኝ ልቀቁኝ እጅግ አስገራሚ ሆኖአል:: ህዝቡ እጅ እጅ እስከሚለው ድረስ ነው ሚዲያዎቹ እያሰላቹት ያሉት:: ዳያስፖራው የሚለው ፍትህና ርትእ ይቅደም ዜጎች በመጀመሪያ መብታቸው ይከበር: መድልዖ ይቁም:ከቁሳዊ ልማት በፊት ሁሉንም ያማከለ መሰረታዊ ነጻነት ይቅደም ነው:: በሃገሪቱ ወስጥ የዜጎች እኩልነት እስካልተረጋገጠ ድረስ የልማት ስራዎች የሚባሉት ሁሉ ለሙስናና ለንቅዘት የተጋለጡ ናቸው:: ዳያስፖራው በሚኖርባቸው አገራት ከነዚህ ሁኔታዎች የፀዳ አገልግሎት ያገኛል አገሩም ላይ እንዲሁ እንዲሆን ይመኛል:: ይህን መጠየቁ ደግሞ ፀረ ልማት ሊያሰኘው አይችልም።

ዛሬ በሃገራችን ለአባይ ግድብ መዋጮ ርብርቦሽ እየተደረገ ነው:: ህዝባዊው ተሳትፎ ሁለት አይነት ባህርያት ይስተውለውበታል:: አንደኛው ህዝቡ በፍላጎቱ የሚያደርገው መዋጮ ሲሆን ይህም አገራዊ ስሜቱ ላይ ተመርኩዞ ያለ አንዳች ተፅእኖ የሚያደርገው ነው:: ሁለተኛው ደግሞ ያቶ መለሰን ሰሞነኛ ቃለ-መጠይቅ አባባል ልዋስና “ቁርስ የማይበላው ህብረተሰብ” በየመስሪያ ቤቱ የደሞዙን አንድ አስራሁለተኛ በወር የሚለቅበት ሲሆን :ይህም ለቤት ኪራይ ለመብራት ለውሃ እና ለትራንስፖርት ወጪ እንዲሁም ሌሎች ጥቃቅን ወጪዎች ተደማምረውበት የዛሬው ኑሮ ወደነት ተጨምሮ እሱም ሆነ ቤተሰቡ ምሳቸው ወይ ራታቸው ተቀነሰ ማለት ይሆናል:: በኔ አስተያየት ልጆቹንና ራሱን አስርቦ ኑሮውን ደፋፍቶ አንድ አስራሁለተኛ ደሞዙን የሚለቅበት ምክንያት ምንድነው ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ ይሆናል:: በየመስሪያ ቤቶቹ የተሰገሰጉት የወያነ አባላት ፍጥጫና ግልምጫ አንዱ ምክንያት ሲሆን ቤቴን ደፍቼ አላዋጣም ቢል የመንግስትን ትራንስፎርማሽን ፖሊሲ ተቅውመሃል ተብሎ ጠቅላላ ስራውንም ሊያጣ ይችላል:: ሌላው በየገጠር ከተማው ስራ እየቆመ የሚደረገው ሰልፍ አስደንቆኛል:: ከአንድ አስራ ሁለተኛ ደመወዝ ለቀቃ ቀጥሎ በከፍተኛ ደረጃ የአባይ ግድብ ድጋፍ ሰልፍ በየትናንሿ ከተማ ወስጥ እየተደረገ ነው:: በፍላጎቱም ሆነ ያለፍላጎቱ እያዋጣ ያለው ህብረተሰብ ተማሪው ከስራ ቀርቶ ሰራተኛው ስራውን ትቶ ነጋዴው ሱቁን ዘግቶ ሰልፍ ውጣ ይባላል :: ይህ ለምን አስፈለገ ብየ ስጠይቅ ያገኘሁት መልስ የአምባ-ገነን መሪዎች ምስ መሆኑን ነው በሹመኞቻቸው አማካይነት ህዝቡ ብቁጥጥራቸው ስር መሆኑን ይገመግሙበታል:: በነገራችን ላይ አቶ መለስ ከሁለት ቀናት በፊት በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በሰጡት ቃለመለለስ ላይ የታዘብኩተን ላካፍላችሁ:: አቶ መለስ በተደላደለ ቢጫማ ሶፋ ላይ ተደላድለው ተቀምጠዋል:: ጋዜጠኛው ወይም ጠያቂው በሌላ የተለቭዥን ዝግጅቶች ላይ አወያይ እየተባለ ሲቀርብ አይቸዋለሁ ከአቶ መለስ ትይዩ አንዲት ነጠላ ወንበር ላይ እግሮቹን ከታች በኩል አጠላልፎ ከወንበሩ ስር ቀብሮአቸዋል:: ቃለ መጠይቁን ሲያቀርብ እስከአጋማሹ ድረስ እጆቹ ይንቀጠቀጡ ነበር:: ይህ ፍርሐት በውስጡ የተፈጠረበት ምክንያት ምን ይሆን? ብየ ራሴን ጠይቄአለሁ::የተረዳሁት ነገር ቢኖር ከተሌቭዥን ድርጅቱ ለቃለመጠይቅ ሲላክም ሆነ ቤተመንግስት ሲገባ የተሰጡት ማስጠንቀቂያዎች ሳይረብሹት አልቀሩም:: የህም አምባ-ገነን መሪዎች በሚፈጥሩትና በሚታወቀው ጨካኝ ባህሪያቸው የተነሳ ሌሎች ሰዎችን የስነ-ልቡና ሽብር ወስጥ ይከቱአቸዋል:: በጠያቂውም ላይ የታየው መንቀጥቀጥ ከዚህ የተነሳ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል::
ሌላው ጠያቂው ያነሳቸው በተለይ ህዝቡና አገዛዙ መካከል ተፈጠረ የሚላቸውን መቀራረቦች በተለይ ህዝቡ እያሳየ ያለውን መነሳሳት አስመልክቶ ላቀረበው ጥያቄ አቶ መለስ የሰጡአቸው መልሶች ሁለት ባህርያት ተስተውለውባቸዋል:: አንደኛው ሀዝቡን እያደረገ ላለው ርብርቦሽ ምስጋና መስጠት ተገቢ የነበረ ሲሆን ይህም ህዝብን አክብሮ ራሰን ማስከበር ሲቻል ሳያደርጉት ሁለትና ሶስት ጊዘ እድሉ አልፎአቸዋል:: ባለማወቅ የተደረገ ነው እንዳይባል መለስ የዝንብ:ይቅርታ የንብ ልጃገርድ ከሩቅ የሚያውቁ መሆናቸውን የማያውቅ የለም:: የሚገርመው ባህሪያቸው ህዝብ ላይ ተቀምጠው ሁለት ነገሮች ካፋቸው ማውጣት ይቸግሯቸዋል:: ይኅውም ህዝብ ላደረገው ተሳትፎና ቀና ቀረቤታ ምስጋና ማቅረብ የምጥ ያህል ታስቸግራቸዋል የህም ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በሗልም ታይቶአል ዛሬም ላይ ተደገመ:: ሌላው ከአቶ መለስ አፍ የማትሰሙት ቃል የኢትዮጵያ አንድነት የሚለውን ነው: የአገሪቱ አንድነት ጥያቄ ሲነሳ ሁልጊዜ ሉአላዊነት በሚል ማደናገሪያ ቃል አውሸልሽለው ያልፉታል::የኢትዮጵያ አንድነት ግን በአባይ ግድብ ግንባታ ዙሪያ በዛሬው ቀንና ሰአት እየተገለጸ ነው:: ኢትዮጵያዊው ከዳር እስከዳር የተነሳሳው እየተረባረበም ያለው ናፍቆት የነበረውን አንድነቱን የሚገልፅበት ብቸኛ መንገድ በማግኘቱ ነው:: አማራ ትግሬ ጉራጌ ኦሮሞ ከንባታ ሃድያ ጋምቤላ ሶማሌ ሳይል ባንድነት መነሳሳቱ::

እንዲያውም እንደ አቶ መለስ የቃለ መጠይቅ መልስ ይህ ህዝባዊ መነሳሳት ህዝቡ በፍላጎቱ ያመጣው ሳይሆን እሳቸውና መንግስታቸው ባደረጉት ቆራጥ አመራር የተነሳ የተገኘ ውጤት ነው::
ሌላው ቃለ መጠይቁ ላይ የተነሳውና በሌሎችም ሁነታዎች እየተገለጸ የሚገኘው ኢትዮጵያ ማንንም የማትጎዳ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ የአባይ ፍጆታዋን ለመጠቀም የምትፈልግ አገር ናት የሚለው ሲሆን መሰረተ ሃሳቡ መልካም ሆኖ ሳለ የተወስኑ የግብፅ ላኡካን አዲስ አበባ መጥተው ራትና ምሳ እየተጋበዙ ስለገለፈጡ ለግብፅም ሆነ ለለሎች ሃገራት የውሃ ተመራማሪዎች ግንባታችንን መጥተው እንዲመረምሩ እንፈቅዳለን ማለት ምንድነው? የወያኔ መንግስት በ1993 ከግፅብጽ ጋር አድርጎት የነበረው ስምምነት አንቀፅ 4 ላይ ኢትዮጵያ ግዛቷ ውስጥ በሚገኙ በአባይና በአባይ ተፋሰስ ወንዞቿ ላይ የምትገነባውን ማንኛውንም ፕሮጀክት በግብፅ ባለሙያውች ታስመረምራለች ከሚለው ስምምነትስ በምን ይለያል:: ሳይጠይቁንስ የለሎች አገራት የውሃ ጠበብትን መጋበዝ ምን አመጣው? በዚህ የግብጾቹ ልኡካን ቡድን የዲፕሎማሲ የበላይነቱን ተቀዳጅቶ ሄዷል:: ምን ማሌቴ ነው አሁን ግብፅ የተረጋጋ መንግስት ስለሌላት ፋታ ስጡንና የተረጋጋ መንግስት ከመሰረትን በኋላ እንነጋራለን ማለት ነው:: መንግስታቸው በእግሩ ሲቆም ምን አይነት አቋም ሊይዙ እንደሚችሉ ገና መናገር አንችልም:: አብሮ ራት በተበላ ቁጥር ይህን እናረግላችኋለን ያን እንፈፅምላችኋለን እያሉ ቃል መግባትስ ምን አመጣው? ግብፅ ደግሞ የምትናቅ አገር አይደለችም ጠንካራ እኮኖሚና ጠንካራ ወታደራዊ ሃይል ያላት አገር ነች አባይ ደሞ ትንፋሿ ነው::

የለሎች አገራትስ የውሃ ተመራማሪውች ምን አገባቸው “እባብ ያየ በልጥ ይደነግጣል”እንዲሉ ራሱ በመረጣቸውና ደሞዛቸውን ይከፍላቸው በነበሩ ዳኞች በአልጀርሱ ስምምነት ስንት ደም የተከፈለበትን ሃገር እንድናጣ የተፈረደብን ሰዎች ሳይጠይቁን ጋብዘን ወደፊት ግብፅ ንትርክ ብታመጣ መሰክሮች ለማቅረብ ምቹ እንዲሆንላት ማዘጋጀትስ አይሆንም ወይ? ይህ የዲፕሎማሲ አልብቃት ነገ ግብጽ አሻፈረኝ ብትል ለሚነሱ ፖለቲካዊም ሆነ ወታደራዊ ጥቃቶች በቀላሉ አገራችንን አያጋልጣትም ወይ?

ሌላው ግድቡ ሲገነባ የምንደርስበት ይሆናል::በተለያየ ጊዜአት የልማት እቅዶች እየተባሉ የተሰጡ መመሪያዎች ህዝባችንን በየደረጃው የተለያየ ዋጋ አስከፍለውታል ለምሳሌ በፊት የማኔጅመንት ስትራቴጂክ ዕቅድ (SPM)፣ በኋላ መሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ (BPR) ቆይቶ ደግሞ ውጤት ምዘና (BSC)፣ አሁን ደግሞ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ (GTP) እየተባለ ቁም ስቅሉን አይቷል ግማሹ ከስራ ተባሯል ሌላው ቤቱ ተበትኗል ልጆቹ የጎዳና ተዳዳሪ ሆነዋል:: በነዚህ ምክንያቶች በተለያየ ደረጃ ዋጋ ከፍሏል አሁን ደግሞ የትራንስፎርሜሽን እቅድ አካል የሆነው የአባይ ግድብ ካለው የኑሮ ውድነት ጋር ተደምሮ ድሮም ከጠፋው ቁርሱ ጋር ምሳው ወይ ራቱ በአንድ አስራሁለተኛም መዋጮ ምክንያት ከጠረጴዛው ላይ ተወስዶበታል:: ይህን ስል ታዲያ ሰርቶ የሚገባውን ብቻ ነው ያን ባጋጣሚ ጉሮሮውን ዘግቶ የሚቀጥለው ምግብ መቼ እንደሚገኝ የሚያልመውን ወገኔን አይጨምርም::

በዚህ የአባይ ግድብ ዙሪያ እነአቶ መለስ የአመራር ብቃታቸው ህዝባዊ ርብርቦሹን አመጣው ብለው ሲሞካሹ እኛ ደግሞ ለንከስትላቸው የሚገባ አንድ ኅቅ አለ ይኅውም ሕዝባችን የአባይ ግድብ ስራ ርብርቦሽን የታፈነው የአንድነት ድምፁ መገለጫ እንዲሆነው አድርጎታል:: የምትፈሩት አንድነትም እንዲህ እየተገለጸ ነው: ስለዚህ ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ ሆኖባችኋል::

ከደምስ በለጠ

ሰሞነኛ ወጋ-ወግ – ከደምስ በለጠ

Saturday, August 7th, 2010

ዘረኝነት ጥፋት ነው! ዘረኝነት በሽታ ነው! የቅርቡን የአለማችንን ታሪክ እንኳ ብንመለከት በዘረኝነት መሰረት ላይ የሐገራቸውን ስርኣት የገነቡ አገሮች ውድቅት: ታላቅ ከነበረችው ሶቭዬት ህብረት ይጀምራል። ዛሬ ሩሲያ ተብሎ በሚጠራው የቀድሞዋ ሶቭዬት ትልቁ አካል ውስጥ ተደብቆ የነበረው ዘረኝነት ቸችኒያና ታታርስታን ወስጥ መንግስቱንም ሆነ ህዝቡን ቁም ስቅሉን እያሳየው ይገኛል።

ተከባብሮና ተፋቅሮ እየኖረ ነው ይባል የነበረው የሶቭዬቱ ታላቅ ህዝብ ዛሬ እንደውሻ ሲናከስ ይስተዋላል። ጆርጂያ ወስጥ አብሐዚያ በሚባለው አጋማሽ ግዛት ውስጥ ከመፈረካከሱ ወዲህ የራሱን መንግስት መስርቶ ኤኮኖሚውን ከሩሲያ ጋር አስተሳስሮ የራሱን ጦር አቋቁሞ ዘራፍ እያለ ይገኛል::ቼኮዝሎቫኪያ ይባል የነበርው አገር ለሁለት ተሰንጥቆ ከታላቅ የኢንዱስትሪ ባለቤትነት ወደሁለት ራሱን እንኳ መመገብ ያቃተው ጥቃቅን አውሮፓዊ መንግስትነት ተለውጧል: ሌሎች ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል: ታዲያ ይህ ሁሉ   ስር የሰደደ ድብቅ ዘረኝነት በየአገሮቹ ህዝቦች ላይ የየራሱን አሻራ ጥሎ እስከመበታተንና ህዝቻቸውን ለረሃብ አለንጋ እስከማጋለጥ አድርሶታል።

በሐገራችንም ወያኔያዊው ስርኣት በመንግስታዊ ፖሊሲ ቀርጾ ካስቀመጠው የዘረኝነት ፖሊሲው ውጪ:የአንድነት ሃይል ተብየው ውስጥ ጎጥኝነትን ያማከለ ፖለቲካ ለማራመድ ግንባር ቀደም የሆነ ሚና የሚጫወቱ እየተስተዋሉ ነው:: በተለያየ መንገድ ላለፉት ሃያ አመታት ቅርፅና ይዘቱ ይለዋወጥ እንጂ ዘረኝነት እንደ ኢንፍሉዌንዛ ካንዱ ወዳንዱ ሲተላለፍ ቆይቷል።

ዘረኝነት በትግሬነት:ዘረኝነት በኦሮሞነት:ዘረኝነት በጉራጌነት ወይም በአማራነት ከመጣ ቋንቋውንና ቦታውን ይለዋውጥ እንጂ ያው ዘረኝነት ነው:: ያንድነት ሃይል ሁሉ ሊዋጋው ይገባል።

በጓዳ ከመንደር ልጅ ጋር ተሰብስቦና ዶልቶ ሌላውን ኢትዮጵያዊ ገፍቶ በኢትዮጵያ ስም መማል ወያኔዎቹ የተጠቀሙበት ያለፈ ስልት ነው::ብርቱካን ሚደቅሳ በአባቷ ኦሮሞ ደሟ ፖለቲካዊ እይታዋን የምንለካ ከሆነና: ብርሃኑ ነጋን በጉራጌው አባቱ ደም ፖለቲካዊ ፓርቲውን የምንመዝን ወይም አኙዋኩን ኦባንግ ሜቶን ኢትዮጵያዊነቱን በዘር ሃረጉ መትረን ልንወስንለት የምናስብ ከሆነ በአንድነቱ ጎራ ቦታ የሚኖር አይመስለኝም:: ላፍታም ቢሆን ይህ አስተሳሰብ ያላችሁ ጊዜው ሳያልፍ ለይቶላችሁ ከዘረኛው ጎራ መቀላቀሉ ለአንድነቱም ጎራ ሆነ ለራሳችሁ እርፍት ይሆንላችኋልና ቢያስቡበት እንመክራለን።

“እዚህ ላይ አንድ ወግ ላውጋችሁ:- እንዼት እንደተፈጠረ እንኳ የማያውቅ ተፈጥሮ ኩሬ ያወረሰችው አንድ አይና እንቁራሪት (ጓጉንቸር) ነበር:: ከኩሬው ጫፍ ላይ አንድ ቋጥኝ አለና እዚያ ቋጥኝ ላይ ደሞ ጠዋት ጠዋት ከእንቅልፉ ሲነቃ ተጎልቶ ፅሃይ ይሞቅበታል: ይህቺ ኩሬው በአለም ላይ ያለች ብቸኛ ውሃም መስላ ትታየዋለች በዚህም ከፍተኛ ደስታ እየተሰማው ይኖራል:: አንድ ጊዜ የውቅያኖስ ማአበል ተነስቶ አንዲት የውቅያኖስ ዔሊን ተራራ አሻግሮ ከኩሬው አጠገብ ይወረወራታል: ታዲያ ያች ዔሊ ውሃ ሸቷት ወደ ኩሬው ስትቀርብ ባለበቱ አንድ አይናው ጓጉንቸር ጠጋ ይላትና አንቺ ለመሆኑ ማነሽ እንዲህ አይነት አፈጣጠር ያለሽ: ከወዴትስ መጣሽ ወደ ኩሬዬ?-ሲል በጥያቄ ያፋጥጣታል:: ረጋ ባለመንፈስ ዔሊዋም እንዲህ ስትል መለሰች “ወዳጄ ሆይ እኔ የውቅያኖስ ዔሊ ነኝ የምኖረውም እንዳንተው ውሃ ውስጥ ነው እናም ማእበል ተነስቶ ከውቅያኖስ አስፈንጥሮ አውጥቶ ወደዚህ ወደ አንተ ኩሬ ጥግ ጣለኝ ስለዚህ ነፍሴን ለማቆየትና ጊዜው ደርሶ ወደውቅያኖሴ እስክመለስ ድረስ ወሃ ያስፈልገኛል ለዚህ ነው ውሃ ሸቶኝ ወደዚህ ኩሬ የተጠጋሁት ትለዋለች:: ለሌላው ፍጡር ጥገኝነት ለመስጠት የተዘጋጀውና እጅግ ልቡ በኩራት ጢም ያለው አንድ አይና:ከቀኝ ወደ ግራ አንገቱን አጠማዞ ያችን ኩሬ ከቃኘ በኋላ ለራሱ እንዲህ ሲል ተመፅደቀ:: እኔ የዚህ ሁሉ ጌታ ነኝ ይህ ኩሬዬ እሷ ከምትለው ውቅያኖስ በብዙ እጅ እንደሚበልጥ ጥርጥር የለውም ያም ሆነ ይህ እስቲ ልጋብዛትና የውቅያኖስዋን ስፋትና መጠን ታሳየኝ ሲል እምቡር ብሎ ዘሎ ከኩሬው ገባና ዔሊዋም እንድትገባ ጋበዛት:: የኩሬውን ሲሶ እንደዋኙ ዔሊ ሆይ የመጣሽበት ውቅያኖስ ይህን ያሕላል?- ሲል ጠየቃት ወዳጄ ሆይ ወቅያኖስ በጣም ትልቅ ነው ስትል መለሰች። ቆይ እስቲ ጨመር አድርጌ ላሳያትና ምን ማለቴ እንደሆነ ትረዳ ሲል ሁለተኛውን ሲሶ ካሳያት በኋላ ይህንንስ ያህላል? ሲል ጠየቃት ደንቁርናው የገባት ዔሊ ምን መሰለህ ወዳጄ እውነቱን ለመናገር ውቅያኖስ እጅግ በጣም በጣም ትልቅና ሰፊ ነው ፅሃይ ሲመታው አድሮ ሲመታው ቢውልና ቢከርም ጥቂት እንኳን አይቀንስም :ያንተ ኩሬ ግን በሰአታት ጊዜ ውስጥ ደርቆ ያንተንም ሆነ ሌሎች ጥገኞችም ካሉህ ሕይወታችሁ አደጋ ላይ ሊወድቅ ስለሚችል አማራጭ ያስፈልግሃል ስትል ትመልስለታለች።

ያ አንድ አይና ጓጉንቸር ወዲያውኑ ደሙ ተንተከትከ ያቺው ያለቺው አንድ አይኑ ጉሽርጥ መሰለች: ከሰማው መማር ያልቻለው ጓጉንቸር ኩሬዋን ቀውጢ አረጋት አምቦጫርቃት “ስሚ አንቺ:-እንዳንቺ አይነት ዋሾ በዚህ ዓለም ላይ ተፈጥሮ አይውቅም  ለመሆኑ ውቅያኖስ የሚባል በዓለማችንስ አለ: ማእበል ምናምን እያልሽ የቀባጠርሽውንስ ማን ሊያምን ይችላል? እኔ ከተወለድኩ ከጥንት:(በዘመን ላስላልሽና)ከዛሬ ሁለት ወር ጀምሮ ኩሬዬ ደርቆ አያውቅም!! ከዬት አምጥተሽ ነው እንዲህ ያለ ነጭ ወሬ የምታወሪው?  በይ በይ በይ ውጪልኝ ከኩረዬ ሲል በቁጣ ዔሊዋን አባረራት።

ወደ ተነሳንበት ጉዳይ ልመለስና አንድ ሌላ ምሳሌ ልስጣችሁ:-ወያኔ ያን ሰሞን ከኢትዮጵያ ምእራባዊ ግዛት ድንበር ለመስጠት ከሱዳን ጋር ሲደራደር ኤሊባቦረው ተነስቶ የኤሊባቦር መሬት ተወሰደ! ክፌው ተነስቶ የከፋ መሬት ተወሰደ! ወለጌው ተነስቶ የወለጋ መሬት ተወሰደ! ጎጃሜው ተነስቶ የጎጃም መሬት ተወሰደ! ጎንደሬውም ተነስቶ የጎንደር መሬት ተወሰደ! ብሎ የሚጮህ ከሆነ ካንድ አይናው ጓጉንችር በምን ተሻለ?  ሌላው ኢትዮጵያዊስ ጉራጌው ሶማሌው አፋሩ ትግሬው ወሎየው ሸዌው ሃረሬው አያገባውም መባሉ ይሆን የሚል ጥያቄስ አይስነሳም? ይህስ ቅርጹን ይለውጥ እንጂ ዘረኝነት አይደለም?

የዘመነ ፊውዳል ታሪክ ተጠቅሶ ለዛሬው ትውልድ የፖለቲካ ማእድ ማጣበቂያ ማድረግስ የምንመኛትን ታላቂቷን ኢትዮጵያስ ሊያቆያት ይችላልን? ሸዋ በኅይለ-ስላሴ ትግሬን ወርሮ ይህን አድርጎ ነበር ጎንደር በቴዎድሮስ ጎጃምን ወርሮ ይህን ፈፅሞ ወጣ:ትግሬ በዮሐንስ ጎጃምን አቃጥሎ ተበቀለ : ወሎ በእያሱ ትግሬና ጎንደር ላይ አባቱን ንጉስ አድርጎ ሾመ እየተባለ አንዱን ባንዱ የአንድነት ሃይል ላይ ላይ ማነሳሳት ዛሬ ላይ ሆኖ ሲታይ ኋላ-ቀርነት ብሎም ያለፈውና የዛሬው ዘመኑ የትቀላቀለበት ከጆሮ ጠገብነት ባላለፈ የሃገሩን ታሪክ የማይውቅ መሃይም ዜጋ ያሰኛል:: በሌላ መልኩም ዘረኝነት ነው; ከዚያ ከላይ ከተጠቀሰውስ አንድ አይና ጓጉንቸር በምን ይለያል? ይህንን መሰል አስተሳሰብ የአንድነቱ ጎራ ሊፋለመው ይገባል እላለሁ።

ትላንት ታልፏል ዛሬ ደግሞ እየተኖረ ነው መጭው ነገንም መተለም ያስፈልጋል።  የትላንትናዋ ኢትዮጵያ መልካም ዝና ያተረፉ ነገስታት እንደነበሯት ሁሉ የተዋረደ ታሪክ የነበራቸው ነገስታትም ነበሯት:: አገር:-ቅን የሚያስቡ ዜጎች እንዳላት ሁሉ ወራዳ አዕምሮ ያላቸው ዜጎችም አሏት::እድፍ አስተሳሰባቸው የሚለካበት:-ነገ አገር ብትፈርስ ለሚፈጠሩት ጥቃቅን  መንግስታት ሚኒስቴርና አምባሳደር ለመሆን ጭምር ከወዲሁ ዝግጅት ላይ ያሉ መሆናቸው ነው።

ለአገሪቱ አንድነትና ዲሞክራሲያዊ ትግል ቅንጣት ታክል አስተዋፅአኦ የሌላቸው መፍርሷን ጠብቀው  ጦር አሰብቀው(ራሳቸው ሳይዋጉ ማለት ነው) በመንደርተኝነት ተጠራርተው ካቢኔ ማቋቋም ደረጃ ላይ ያሰፈሰፉ ጎጠኞች እየተመለከትን ነው እነዚህ ታዲያ ያንድነቱን ጎራ በስወር ደባ እየቦረቦሩት ይገኛሉ መሰረታቸውም ዝረረኝነትን የተመረኮዘ ነው። ቋንቋቸውን ቋንቋችን መሐላቸውን መሐላችን አድርገው ጊዜዋ እስክትደርስ የሚጠብቁትን እድፋጭ መንደርተኞች ከአንድ አይናው ጓጉንቸር በምን እንለያቸዋለን።

አንዱ የአንድነት ቡድን ያቀደው ተግባር ፍሬ ማሳየት ሲጀምር በመንደር ልጅነት ተጠራርቶና ተመሳሳይ እቅድ አውጥቶ በጎን እጅ መንሻ አሞሌ እየሸጎጡ መሰናክል መሆን ጎራ ለይተው በዘር ከተደራጁት ተለይቶ የሚታይ አይደለም።

ዛሬ ላይ ሆነን ያለፈውን ታሪካችንን ስናጤን ከዛሬ መቶ አመት በፊት ከነበሩ አባቶቻችን በምን እንለያለን? ለያንዳንዳችን ይህን ጥያቄ ልተውና: አዲስ አበባ ውስጥ ጃን ሜዳ ላይ ግንቦት 10 ቀን 1901 ዓመተ ምህረት ንጉሰ-ነገስት ምኒሊክ ያሳወጁትን አዋጅ:ታሪክ ዘጋቢያቸው አፈወርቅ ገብረ-እየሱስ ለታሪክ ባቆዩልን  ቃል ልሰናበታችሁ፤

ያገሬ የኢትዮጵያ ሰዎች፣ ልጆች፣ ወዳጆች፣ እግዚአብሔር የገለጸልኝን ምክር ልምከራችሁ፡፡ ምክሬንም እግዚአብሔር በልባችሁ እንዲአሳድርባችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

አፄ ቴዎድሮስ የሞቱ ጊዜ ከሳቸው ጋር የነበረው ሰው ሁሉ ያንዱን አገር አንዱ እደርባለሁ አንዱን ገድዬ እኔ ጌታ እሆናለሁ እያለ ሁሉም ላይረባ ተላልቆ ቀረ፡፡

ከዚህም በኋላ የአፄ ዮሐንስ ሰው የኾነውን የምታውቁት ነው፤ ባገር በሽታ ሳይገባበት ሌላ የባዕድ ጦር ሳይነሳበት በምቀኝነት እርስ በርሱ እንደተላለቀ አይታችሁታል፡፡

አሁንም ልጆቼ ወዳጆቼ አንዱ ባንዱ ምቀኝነት ይቅር ያንድን አገር አንዱ እኔ እንደርባለሁ እንዳትባባሉ፡፡ እኔ እስካሁን በፍቅር እንዳኖርኋችሁ እናንተም ተስማምታችሁ በፍቅር እንድትኖሩ እለምናችኋለሁ፡፡

እናንተ አንድ ልብ ከሆናችሁ በምቀኝነት እርስ በርሳችሁ ተዋግታችሁ ካላለቃችሁ በቀር አገራችንን ኢትዮጵያን ለሌላ ለባዕድ አትሰጧትም ክፉም ነገር አገራችንን አያገኛትም፡፡ ነፋስ እንዳይገባባችሁ አገራችሁን በያላችሁበት በርትታችሁ ጠብቁ፡፡ ወንድሜ፣ ወንድሜ እየተባባላችሁ ተደጋገፉ የኢትዮጵያን ጠላት ተጋግዛችሁ ተድንበር መልሱ፡፡» – ዳግማዊ አጼ ምኒሊክ