የደቡብ ሱዳን መንግሥት ለመንግሥቱ ኃይለማርያም መኖርያ ቤት ሠራ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በኃይሌ ሙሉ | ሪፖርተር

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ነፃነቱን ያወጀው የደቡብ ሱዳን መንግሥት ለቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ቤት ሠርቶ ያጠናቀቀ መሆኑን የደቡብ ሱዳን ምንጮቻችን ገለጹ፡፡ ከምንጮቻችን ለመረዳት እንደቻልነው፣ የደቡብ ሱዳን መንግሥት ለኮሎኔል መንግሥቱና ቤተሰቦቻቸው መኖርያ የሚሆን ዘመናዊ ቤት እንዲሠራ ያደረገው፣ የቀድሞው ፕሬዚዳንት በነፃነት ትግሉ ወቅት ለደቡብ ሱዳን የሰጡትን ድጋፍ በማስታወስ ነው፡፡

‹‹ኮሎኔል መንግሥቱና መንግሥታቸው በነፃነት ትግሉ ወቅት ለደቡብ ሱዳን ሕዝብ የሰጡት ድጋፍ መቼም የሚረሳ አይደለም፤›› ያሉት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ቢሮ አንድ የሥራ ኃላፊ፣ መንግሥታቸው ኮሎኔል መንግሥቱ የዋሉትን ውለታ ትኩረት ውስጥ በማስገባት ዘመናዊ መኖርያ ቤት ሠርቶ ያጠናቀቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከፍተኛ ገንዘብ ወጥቶበት የተሠራው ይኼው የኮሎኔል መንግሥቱ ቤት በፀጥታ ሰዎች ጥብቅ ጥበቃ የሚደረግለት መሆኑን የገለጹት ምንጮቻችን፣ ኮሎኔል መንግሥቱ የደቡብ ሱዳን መንግሥትን ግብዣ ተቀብለው በቅርቡ ወደ ጁባ ያመራሉ የሚል እምነት እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዘመነ ደርግ ለደቡብ ሱዳን ነፃ አውጪ ግንባር ሠራዊት ሙሉ ድጋፍ መስጠቷና ለመሪው ዶክተር ጆን ጋራንግ በመዲናዋ አዲስ አበባ መኖርያ ማዘጋጀቷ ይታወሳል፡፡