በሁሉም ክልሎች መሬት ለኢትዮጵያ ባለሀብቶች እንዳይሰጥ ታገደ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በውድነህ ዘነበ | The Reporter

የመሬት ዝርፊያ እየተባባሰ በመምጣቱና ይህንን ለመቆጣጠር ወጥ የሆነ አሠራር ባለመኖሩ፣ የፌዴራል መንግሥት አዲስ አበባንና ድሬዳዋን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች መሬት ለባለሀብቶች እንዳይሰጥ ወሰነ፡፡ መንግሥት ይህንን የወሰነው መሬት ዋነኛው ‹‹የኪራይ ሰብሳቢነት›› መከማቻ በመሆኑ ይህንን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍታት ያስፈልጋል በሚል ነው፡፡

ወጥ የሆነ የመሬት አሰጣጥ አሠራርን ተግባራዊ ለማድረግ እየተጠበቀ ያለው የአዲስ አበባ ከተማ ልምድ ሲሆን፣ የከተማው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መኩሪያ ኃይሌ ባሳለፍነው ሳምንት መጀመሪያ ከእናት ፓርቲያቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) አባላት የመሬት አቅርቦት የቆመበትን ምክንያት ተጠይቀው ሲመልሱ፣ ‹‹የመሬት አሰጣጥ ሥርዓት ዘረጋን ብለን ወደፊት ስንሄድ የችግሩ ስፋት እንደገና ወደኋላ ይመልሰናል፡፡ በድርድር ቦታ መስጠት ጀምረን ነበር ስላልቻልን አቋረጥን፤›› በማለት የችግሩን ውስብስብነት አስረድተዋል፡፡

ይህንን ችግር ለመፍታት የከተማው አስተዳደር ዘመናዊና ዲጂታል በሆነ መንገድ የመሬት ሥርዓት ለመዘርጋት ለአንድ የጀርመን ኩባንያ በ50 ሚሊዮን ብር በመጀመሪያ ዙር እንዲሠራለት ተዋውሏል፡፡

ይህ ሥራ የአዲስ አበባ ከተማ ይዞታ የሆነውን 54 ሺሕ ሔክታር መሬት መረጃ ካዲስተር በሚባል ፕሮግራም ከመያዙም በተጨማሪ፣ እያንዳንዱ ግንባታ በምን ያህል ቦታ ላይ እንደተካሄደ፣ ባለፉት ጊዜያት የተነሱትን የኖርቴክና የጂአይኤስ ካርታዎች በመጠቀም የቱ ግንባታ መቼ እንደተካሄደ ማሳወቅ ያስችለዋል፡፡

ይህ ዘመናዊ አሠራር አስተዳደሩ ለሁሉም ቤቶች አዲስ የቤት ቁጥር እንዲሰጥና ሁሉም የከተማው ነዋሪ በቀበሌ (በአሁኑ ወረዳ) ፋይል በኮምፒዩተር እንዲያዝ የማድረግ ዕቅድ አለው፡፡ ይህ አሠራር ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ ሁሉንም ወረዳዎች በኔትወርክ ከማዕከል፣ ከፖሊስና ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ጋር እንዲገናኙ ያደርጋል፡፡ ይህም የሰዎችን የኋላ ታሪክ በቀላሉ ለማወቅና በአገሪቱ የሚገኙ ባንኮች የክሬዲት ካርድ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ ያስችላል ተብሏል፡፡

ይሁንና የአዲስ አበባ ከተማ ልምድ በማጠናቀቅ ለሌሎች ክልሎች ማስተማርያ የሚሆነው ይህ ፕሮጀክት ሥራ ሲጠናቀቅ በመሆኑ፣ ይህንን ፕሮጀክት ደግሞ ለማጠናቀቅ ከሦስት ዓምት በላይ ሊፈጅ ይችላል፡፡ ክልሎች ተግባራዊ ሲያደርጉት ከአንድ ዓመት በላይ ሊወስድባቸው እንደሚችል ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

ይህም ዋነኛ የመንግሥት የገቢ ምንጭ የሆነውን የመሬት አቅርቦትን የሚገታው በመሆኑ፣ በመንግሥት ገቢ ላይ ችግር ከመፍጠሩም በተጨማሪ ባለሀብቶች ኢንቨስት የሚያደርጉበት መሬት እጥረት ይፈጠራል፣ የመኖሪያ ቤትና የመሳሰሉ ግብዓቶችን ዋጋ ይንራል ሲሉ እነዚህ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

ከመስከረም 5 እስከ መስከረም 7 ቀን 2003 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ በተካሄደው የኢሕአዴግ 8ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ የቀረበው ሪፖርት እንደሚጠቁመው፣ የመሬት አስተዳደር በገጠርም በከተማም የኪራይ ሰብሳቢነትና የሙስና ምንጭ ሆኗል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት የመሬት አስተዳደር ግልጽ፣ ፍትሐዊና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን ይደረጋል ሲል የኢሕአዴግ ሪፖርት ያስረዳል፡፡

ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ በአዲስ አበባ ከጀርመኑ ኩባንያ ጋር የሚካሄደው ሥራ እንዳለ ሆኖ፣ በተለይ ከመሬት አስተዳደር ጋር የተያያዘ የትምህርት ካሪኩለም እንዲያዘጋጅና ማስተማር እንዲጀመር የሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ኃላፊነት እንደተሰጠው ለማወቅ ተችሏል፡፡

‹‹በዘርፉ ያለውን የሰው ኃይል እጥረት መቅረፍ አስፈላጊ በመሆኑ ነው ይህ የተደረገው፤›› በማለት አቶ መኩሪያ ለፓርቲያቸው አባላት በተጨማሪ አስረድተዋል፡፡