የ2014 የዩኤስ – አፍሪካ የመሪዎች ፍሬከርስኪ ጉባኤ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

የአፍሪካ የሰርከስ (አሻንጉሊቶች አንበለው) ተውኔት ጉባኤ እውን ለመሆን እየተቃረበ ነው፡፡ ይህ የጉባኤ ተውኔት በይፋ “የዩኤስ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ“ በመባል ይጠራል፡፡ ይህ ጉባኤ እ.ኤ.አ ከኦገስት 5-6/2014 በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ በይፋ ይካሄዳል፡፡ የጉባኤው ርዕስ “በሚቀጥለው ትውልድ ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ“ የሚል ነው፡፡

እንደ ቅድመ ጉባኤው ይፋዊ መግለጫ ከሆነ በዚህ የመጀመሪያ እና ልዩ በሆነው የዩኤስ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ የአፍሪካ መሪዎች ከፕሬዚዳንት ኦባማ፣ ከእርሳቸው የካቢኔ አባላት እና ከሌሎች ቁልፍ ቦታ ከያዙት አመራሮች ማለትም ከዩኤስ እና የአፍሪካ የንግድ ሰዎች፣ ከኮንግረስ (የአሜሪካ መክር በት) አባላት እና ከሲቪል ማህበረሰብ አባላት ጋር የመገናኘት እድል ይኖራቸዋል፡፡ ጉባኤው “ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት፣ ወጣት የአፍሪካ መሪዎችን ማሳተፍ፣ ዘላቂነት ያለው ልማትን ማስፋፋት፣ ሰላም እና ደህንነትን የማጠናከር ህብረት መፍጠር እና ለአፍሪካ ቀጣይ ትውልድ የተሻለ ህይወት ማስገኘት“ በሚሉ ባለ5 ቀለበት የሰርከስ ተውኔት ደረጃዎች ላይ የተመሰረተ ነው፡፡

ሰብአዊ መብት በዚህ ጉባኤ ላይ በእርግጠኝነት በአጀንዳ ምርጫ ዝርዝሮች ላይ ምንም ዓይነት ቦታ አልተሰጠውም፡፡ በመሆኑም ይህንን ጉዳይ በማስመልከት መናገር አለብኝ! ቶማስ ጃፈርሰን ቀደም ሲል እንደተናገሩት ለአቅም የለሾች ምንም ዓይነት ደንታ ለሌላቸው ሆኖም ግን አሁን በስልጣን ላይ ላሉት፣ ስልጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጭ ለሚጠቀሙት እና ለፍትህ መስፈን ጆሯቸውን ለደፈኑት እና በደም ለተሳሰሩት ገዥዎች እውነታውን እስከ አፍንጫቸው የመናገር የሞራል ግዴታ አለብኝ፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ በኋይት ሀውስ ድረ ገጽ እንዲህ በማለት አውጀዋል፣ “የአፍሪካን አገሮች እና ህዝቦች ከዓለም ህዝብ ነጥዬ አላያቸውም፡፡ ይልቁንም አፍሪካን በጽኑ ቁርኝት ከተሳሰረው ዓለም ጋር ያላትን ግንኙነት በማጠናከር ለወደፊት ልጆቻችን የምናልመውን አብይ ጉዳይ ለማሳካት የአሜሪካ ጠንካራ አጋር እንደሆነች እገነዘባለሁ…“ ይህ ዓይነት አነጋገር የህግ ሰዎች የሁለትዮሽ ምላስ ንግግር እያሉ የሚጠሩት ነውን? ፕሬዚዳንቱ በተለይም “የአፍሪካ ህዝቦች እና አገሮች“ በማለት ገልጸው ነበር፡፡ “የአፍሪካ መሪዎች ለምን አላሉም?“ የአፍሪካ መሪዎች “ከዓለም የተለዩ ናቸውን“? ወይስ ደግሞ “የአሜሪካ አጋር የሆኑ እና ከተለየ ዓለም የመጡ ናቸው?“

በእርግጥ “የአፍሪካ አገሮች እና ህዝቦች“ ወደ ዋሺንግተን ዲሲ አልመጡም፡፡ የመጡት “የአፍሪካ መሪዎች ናቸው“፡፡ ከዚህ ነጥብ ላይም ነው እኔ እና ፕሬዚዳንት ኦባማ የምንለያየው፡፡ በእርግጥም ላይሆን ይችላል፡፡ በአፍሪካ “መሪዎች” ላይ “የአጋርነት እና የመሪነት ባህሪ አላየሁም፡፡“ ያየሁት ከፕሬዚዳንት ኦባማ የተረት ዘመቻ በመዋስ የአሳማ ቆንጆ ልፕስቲክ (የከንፈር ቀለም) መቀባት አይነት አነጋገር ነው፡፡ “ታውቃላችሁ፣ አሳማን ሊፒስቲክ መቀባት ይቻላል፣ ሆኖም ግን ያው አሳማነቷን አይለቅም፡፡ “አንድን የጠነባ ዓሳ በወረቀት በመጠቅለል “ለውጥ” ማለት ይቻላል፣ ሆኖም ግን የተጠቀለለው ዓሳ እስከ “አሁንም ድረስ መጠንባቱን አይለቅም” በማለት ዕጩ ፕሬዚዳንት ኦባማ የምርጫ ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ወቅት ተናግረው ነበር፡፡

የአፍሪካን የሰብአዊ መብት ደፍጣጭ ወንጀለኞች፣ ዘር አጥፊዎች፣ አሰቃዮች እና የብዙሀን ገዳዮችን በኋይት ሀውስ የስብሰባ አዳራሽ በማጎር “መሪዎች” ማለት ይቻላል፣ ሆኖም ግን ከቀኑ መጨረሻ ሊፒስቲኩ እየደበዘዘ ሲያልቅ በሚታዩበት ጊዜ እውነተኛ ማንነታቸው ቁልጭ ብሎ ይታያል፡፡ የአፍሪካን አረመኔ አምባገነኖች እና ወሮበላዎች በአንድ ላይ በማሰለፍ “አጋሮች” ማለት ይቻላል፣ ነገር ግን ለበርካታ አስርት ዓመታት በስልጣን ላይ ከበሰበሱ በኋላ መጠንባታቸው አይቀርም፡፡

በአፍሪካ መሪዎች የሰርከስ ተውኔት እይታ ላይ ትኩረት ለማድረግ አልፈልግም፣ “እነዚህን መሪዎች በትችት በኃይል መምታት እና በእነርሱ ላይ መቀለድ“ የሚለውን ትችት ሁልጊዜ የማዳምጠው ነው፡፡ እነርሱን የሚከፋፍል ነገር አይደለም፡፡ በእኔ የክርክር ጭብጥ “ለአምባገነን አንድም የእፎይታ ጊዜ መስጠት አያስፈልግም“ የሚለውን አባባል ከደብልዩ.ሲ ፊልድስ  በመዋስ በአንድ ላይ ቀምሪያለሁ፡፡ ዋናው ነጥብ እንዳየሁት እና እንዳረጋገጥኩት እውነታውን ወዲያውኑ መናገር አለብኝ፡፡ በኋይት ሀውስ የተሰበሰቡት የአፍሪካ መሪዎች እየተባሉ የሚጠሩት ስብስቦች በእኔ ግንዛቤ በሰብአዊ መብት ላይ የሚቀልዱ እና በመንግስት ስህተቶች ላይ የአስመሳይነት ሚና የሚጫወቱ ከልዩ ዓለም የመጡ ዝርያዎች ናቸው፡፡

ወደ ኋይት ሀውስ ለእራት ግብዣ የተጠሩትአጋሮች” (ሰባዊ መብት ወንጀለኞች) በስም ዝርዝር፤

ወደ እራት ግብዣው የሚመጡት የአፍሪክ “መሪዎች” እና አጋሮች ስም ዝርዝር የ21ኛውን ክፍለ ዘመን የሰብአዊ መብት ደፍጣጭ መጥፎ ወንጀለኞች፣ ነፍሰ ገዳዮች፣ አሰቃዮች፣ አጭበርባሪዎች፣ አስመሳይ እምነተቢሶች ናቸው፡፡ ከእነዚህ መሪ ተብዮ የስም ዝርዝር ውስጥ በጥቂቱ እነሆ፣

የኬንያው ኡሁሩ ኬንያታ፣ እ.ኤ.አ ከ2013 ጀምሮ በስልጣን ላይ ያለ፡፡ ኬንያታ የኬንያ ድህረ ምርጫን ተከትሎ በተከሰተው ውዝግብ ሳቢያ ከሰብአዊ መብት ረገጣ ጋር በተያያዘ መልኩ እ.ኤ.አ በ2008 በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በተለያዩ ወንጀሎች ምክንያት ክስ ተመስርቶበት ጉዳዩ በመታየት ላይ ይገኛል፡፡ በተባበሩት መንግስታት ግምት መሰረት ወደ 1,200 ንጹኃን ዜጎች የተገደሉ ሲሆን በዴሴምበር 2007 እና በፌብሯሪ 2008 መካከል ከ600,000 በላይ የሚሆኑ ዜጎች ከሚኖሩበት ቦታ በኃይል እንዲፈናቀሉ ተደርገዋል፡፡ በኬንያታ ላይ የተያዘው የክስ ጉዳይ በቀሪዎቹ ወራት ተጨማሪ ማስረጃ ካልተሰባሰበለት በስተቀር በመጭው ኦክቶበር ጉዳዩ ውድቅ ሊደረግ እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ (የአፍሪካን አምባገነን መሪዎች ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት መከላከል በሚል ርዕስ ቀደም ሲል ያቀረብኩትን ትችት ይመለከቷል)

የካሜሮኑ ፓውል ቢያ፣ ከ1982 ጀምሮ በስልጣን ላይ ያለ ሲሆን ይህ የ80 ዓመት አዛውንት የሆነው ቢያ እ.ኤ.አ ከ1960 የነጻነት ጊዜ ጀምሮ የካሜሮን 2ኛ ፕሬዚዳንት በመሆን በስልጣን ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ ይገኛል፡፡ ቢያ ረዥም የሆነ የሰብአዊ መብት ረገጣ መዝገብ ያለው ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ማሰቃየት፣ ከህግ አግባብ ውጭ በዘፈቀደ ግድያ መፈጸም እና በነጻ ጋዜጠኞች፣ ደራሲያን እና ተቃውሞ በሚያሰሙ ተማሪዎች ላይ የኃይል እርምጃ መውሰድ ከብዙዎቹ ጥቂቶች ናቸው፡፡

የቡርኪና ፋሶው ብለይስ ኮምፓሬ፣ እ.ኤ.አ በ1987 ደም አፋሳሽ በሆነ መፈንቅለ መንግስት ስልጣንን የተቆጣጠረ ሲሆን ኮምፓሬ ቡርኪና ፋሶን ለእራሱ እና ለግብረ አበሮቹ የግል ንብረት አድርጎ ሲመዘብር ቆይቷል፡፡ የሰብአዊ መብት ረገጣ መዝገቡ እንደሚያስረዳው በሰላማዊ ህዝቦች እና በእስር ቤቶች በቁጥጥር ስር ባሉት ታራሚዎች ላይ ከመጠን ያለፈ የኃይል እርምጃ መውሰድ፣ ለጤና አደገኛ እና አስቀያሚ የሆኑ የእስር ቤት አያያዝ ሁኔታዎችን ማስፋፋት እና መጠነ ሰፊ በሆነ ሙስና መዘፈቅ የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

የሩዋንዳው  ፓውል ካጋሜ፣ እ.ኤ.አ ከ1994 (መጀመሪያ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የመከላከያ ሚኒስትር) ጀምሮ በስልጣን ወንበር ላይ ተፈናጥጦ የሚገኝ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት በቅርቡ ካጋሜ የሩዋንዳን ጠረፍ በማቋረጥ የምስራቅ ኮንጎን አማጺያን በመደገፍ ለ30,000 ህዝብ መፈናቀል እና በእስር ቤት መጋዝ እና በርካታ የፖለቲካ ተቀናቃኞቹን እና ተፎካካሪዎቹን በመግደል ከስሶታል፡፡ በአሜሪካ የካጋሜ የቀድሞው አምባሳደር የነበሩት ቲኦጅን  ሩዳሲንግዋ እንዳቀረቡት ዘገባ ከሆነ ካጋሜ እ.ኤ.አ በ1994 የወቅቱ የአገሪቱ መሪ የነበሩትን ፕሬዚዳንት ጁቬናል ሐቢያሪማናን የያዘውን አውሮፕላን ለማስመታት ተኩስ እንዲከፈት ትዕዛዝ መስጠቱን እና ዛቻ ሲያሰማ እንደሰሙ በግልጽ ተናግረዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2007 ካጋሜ ለቢቢሲ የፊት ለፊት ንግግር ሲያደርግ በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ምንም ደንታ እንዳልነበረው እንዲህ በማለት ተናግግሮ ነበር፣ “ለሐቢያሪማና ሞት እኔ ተጠያቂ አይደለሁም፣ እናም ደንታ የለኝም፣ ስለእርሱ ደህንነት ተጠያቂ አልነበርኩም፣ እንደዚሁም ደግሞ ስለእኔ ደህንነት እርሱም ተጠያቂ አልነበረም፡፡ እኔ ብሞት ኖሮ እርሱ ተጠያቂ አይሆንም ነበር፣ እናም በእርሱ ላያ ስለደረሰው ነገር ጉዳየ አይደለም” በማለት አቅጩን ተናግሮ ነበር፡፡

የዩጋንዳው ዮሪ ሙሴቬኒ፣ እ.ኤ.አ ከ 1986 ጀምሮ በስልጣን ላይ የሚገኝ ሲሆን ሙሴቬኒ ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ረገጣ ሪከርድ አለው፡፡ እ.ኤ.አ ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ባቀረበው ዘገባ መሰረት “የፕሬዚዳንት ሙሴቬኒ መንግስት የመገናኛ ብዙሀንን፣ የሲቪል ማህበረሰቡን፣ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን እና ማንኛውንም የእርሱን አስተዳደራዊ ዘይቤ የሚተቸውን ሁሉ ጉሮሮ አንቆ ይዟል“ የሚል ዘገባ አውጥቶ ነበር፡፡ በደርዘን የሚቆጠሩ የህዝብ ተወካዮች አባላት የፖሊስ ጥያቄ እንዲቀርብባቸው የተደረገ ሲሆን የመንግስት ፖሊሲዎችን በመንቀፍ በሚደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ ንግግሮችን አድርጋችኋል በማለት የወንጀለኝነት ክሶች እንዲመሰረቱባቸው አድርጓል፡፡

የኢኳቶሪያል ጊኒው ቶዶሮ ኦቢያንግ ምባሶጎ፣ እ.ኤ.አ በ1979 ደም አፋሳሽ በሆነ መፈንቅለ መንግስት ስልጣንን ከተቆጣጠረ በኋላ ኦቢያንግ በስልጣን ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ ለመቆየት ማንኛውንም ምርጫ በማጭበርበር 95 በመቶ የሚሆነውን ድምጽ በመቀማት በስልጣን ላይ ቆይቷል፡፡ የኦቢያንግ ልጅ እና “የዘውድ ወራሽ” የሆነው ቴዎዶሪን ኦቢያንግ እምነት በማጉደል የሲቪል ማህበረሰቡን ሀብት በመዝረፍ ወደ ውጭ ያሸሸ መሆኑን በካሊፎርኒያ የዩናይትድ ስቴትስ የፍትሕ መምሪያ እና የኮሎምቢያ ግዛት 46 ገጽ የያዘ ዘገባ አቅርበዋል፡፡ ውንጀላው የሀብት ዘረፋ፣ የገንዘብ ማጭበርበር እና ማባከን፣ የህዝብን ሀብት በመስረቅ ወይም ሙስና በመስራት የሀገሪቱን አንጡራ ሀብት ለውጭ ሀገር ባለስልጣኖች ጥቅም እንዲውል አድርጓል የሚል ነው፣ (በአሜሪካ ተደብቀው የሚገኙትን ታላላቅ ሌቦች መያዝ! በሚል ርዕስ ቀደም ሲል ያዘጋጀሁትን ትችት ያጤኗል፡፡)

የአንጎላው ጆሴ ኤዲዋርዶ ዶሳንቱስ፣ እ.ኤ.አ ከ1979 ጀምሮ በስልጣን ላይ የቆዬ ሲሆን ዶሳንቱስ መንግስቱን እንደ እራሱ የግል የቤተሰብ ንግድ በመቁጠር ሲመራ ቆይቷል፡፡ ኢሳቤል ዶሳንቱስ የተባለችው የእርሱ ሴት ልጅ በአፍሪካ በጣም ኃብታም የተባለች ሴት ናት፣ (አሁን በህይወት ከሌሉት መለስ ዜናዊ ሚስት የበለጠ ኃብታም ናት አየተባለም ተነግሯል፡፡) እናም እንደ ፎርበስ መጽሔት ዘገባ ከሆነ ከአፍሪካ የሴት ቢሊየነሮች መካከል ብቸኛዋ ሴት ባለሀብት እርሷ እንደሆነች ተረጋግጧል፡፡ ወደ 70 በመቶ የሚጠጋው የአንጎላ ህዝብ በቀን 1.7 ዶላር በማግኘት ከድህነት ወለል በታች በመኖር ላይ የሚገኝ ሲሆን 28 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በቀን 30 ሳንቲም ብቻ በማግኘት ኑሮውን የሚገፋ ነው፡፡ ዶሳንቱስ 750 ባለ ስምንት ፎቅ ያላቸው የአፓርታማ ህንጻዎች፣ በደርዘን የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች እና ከ100 በላይ የሚሆኑ የችርቻሮ መደብሮች ለማስገንባት ወደ 4 ቢሊዮን የሚጠጋ ዶላር ለቻይና ኩባንያዎች ክፍያ ፈጽመዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኖቫ ሲዳድ ዲ ክላምባ እየተባለ የሚጠራው ከተማ ባዶ ሰው አልባ ከተማ ሆኗል!

የቻዱ ኢድሪስ ዴቢ፣ እ.ኤ.አ ከ1990 ጀምሮ በስልጣን እርካብ ላይ ተቆናጥጦ የሚገኝ ሲሆን ዴቢ የተንሰራፋ ሰብአዊ መብት ረገጣ ሪከርድ አለበት፡፡ እንደ 2013 ዩኤስ  የመንግስት መምሪያ የሰብአዊ መብት  ዘገባ ከሆነ “በቻድ ትልቁ የሰብአዊ መብት ረገጣ ችግር በደህንነት ኃይሎች የሚካሄደው የሰብአዊ መብት ረገጣ ማለትም ማሰቃየት፣ ንጹሀን ዜጎችን በዘፈቀደ ከህግ አግባብ ውጭ በቁጥጥር ስር ማዋል፣ የተራዘመ የጊዜ ቀጠሮ በመስጠት ጉዳያቸው በህግ የተያዘ ዜጎችን ማጉላላት፣ አስቀያሚ የእስር ቤት አያያዝ፣ ፍትህን መካድ፣ ባለስልጣኖች ከህግ አግባብ ውጭ ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ በፍትህ ሂደቱ ላይ ጣልቃ መግባት እና የንብረት ባለቤትነት መብትን መንጠቅ የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡“

የዴሞክራቲክ  ኮንጎ ሬፐብሊኩ ጆሴፍ ካቢላ፣ እ.ኤ.አ. በ2001 በ30 ዓመቱ ስልጣንን ከአባቱ የወረሰው ካቢላ በጁላይ 2012 እና በጁላይ 2013 መካከል ባሉት ዓመታት ብቻ በሚያስገርም ሁኔታ የ75 ሚሊዮን ዶላር በጣም ከፍተኝ ተከፋይ የፖለቲካ ሰው መሆኑ ሲታወቅ በክፍያ ከእርሱ ተወዳዳሪ ከሆነው ሁለተኛው ሰው ከ40 ሚሊዮን በላይ በሚሆን ዶላር እንደሚበልጥ ተረጋግጧል፡፡ እ.ኤ.አ በ2013 አጠቃላይ የያዘው የተጣራ ገንዘብ 215 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡

የደቡብ አፍሪካው ጃኮብ ዙማ፣  እ.ኤ.አ በ2014 በድጋሜ ለሁለተኛ ዙር የፕሬዚዳንትነት ዘመን የተመረጠ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በሙስና ተጠርጥሮ በምርመራ ላይ ይገኛል፡፡ የደቡብ አፍሪካው አቃቤ ህግ ጃኮብ ዙማንን ወደ 7 ሚሊዮን የሚጠጋ ዶላር “ያልታሰበበት የዘፈቀደ፣ ከልክ ያለፈ እና የህዝብ ገንዘብ በማባከን“ የሚል ስያሜ በመስጠት የግል መኖሪያ ቤቱን ለማሻሻል ያላግባብ ወጭ አድርጓል በማለት ክስ መስርቶበታል፡፡ ይህ አካሄድ በደቡብ አፍሪካ ሙስና ላይ መጠነኛ ለውጥ ያሳያል፡፡ ሆኖም ግን ደቡብ አፍሪካ በሙስና ላይ እያደረገችው ያለውን ጥረት ያመላክታል፡፡

የናይጀሪያው ጉድላክ ጆናታን፣ ቦኮ ሃራም በተባለው ጽንፈኛ አክራሪ ኃይል ተጠልፈው ከነበሩ ልጃገረዶች ዳብዛ መጥፋት ጋር በተያያዘ መልኩ ከሙሉ 100 ቀናት በኋላ ጆናታን በመጨረሻ የልጃገረዶችን ወላጆች አግኝቷል፡፡ ቦኮ ሀራም የተባለው አሸባሪ ቡድን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ የናይጀሪያ ዜጎች ላይ በየዓመቱ ግድያውን፣ ጉዳት ማድረሱን እና ጠለፋ ማካሄዱን በተጠናከረ መልክ ቀጥሎበታል፡፡ ጆናታን ይህንን አሸባሪ ቡድን በኃይል ለማጥፋት፣ ጉቦ በመስጠት ወይም ደግሞ ይቅርታ በመጠየቅ የተጠለፉትን ልጃገረዶች ለማስመለስ የሚያደርገው ጥረት በውል አይታወቅም፡፡ እንደ ዩኤስ የሰብአዊ መብት ዘገባ ከሆነ “የተንሰራፋ፣ የተስፋፋ እና በተደጋጋሚ የሚከሰት ሙስና በናይጀሪያ ሁሉንም የመንግስት እርከኖች እና የደህንነት ኃይሎች በማጥቃት ላይ ይገኛል“

የጋምቢያው ያህያ ጃመህ፣ እ.ኤ.አ ከ1994 የ24 ዓመት ወጣት ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ የወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ግልበጣ ተከትሎ ስልጣንን ተቆጣጠረ፡፡ እ.ኤ.አ በ2007 የጋምቢያው መሪ ከተፈጥሮ ዕጽዋት የኤች አይቪ ኤድስ በሽታን የሚፈውስ መድኃኒት አግኝቻለሁ እና በአሁኑ ወቅት ከዚህ ቀደም የነበረውን መድኃኒት የምትጠቀሙ የበሽታው ሰለባዎች መድኃኒት መውሰዳችሁን በመተው የእኔን መድኃኒት ውሰዱ በማለት ዓለምን ያስደነቀ እና ያሳዘነ ድርጊት ፈጽሟል፡፡ እ.ኤ.አ በ2014 አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው ዘገባ መሰረት “የጃመህ መንግስት ምንም ዓይነት ትዕግስት የሌለው እና በሰላማዊ መንገድ ሀሳባቸውን በገለጹ አመጸኞች ላይ አስቀያሚ የሆነ የሰብአዊ መብት ረገጣ ፈጽሟል፡፡ በመንግስት ፖሊሲዎች ላይ ትችት በሚያቀርቡት የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ተቀናቃኞች እና ሌሎች ጋምቢያውያን/ት በመንግስት ታጣቂ እና የደህንነት ኃይሎች ማስፈራሪያ፣ የማበሳጨት፣ የዘፈቀደ እስራት፣ በእስር ቤት መታጎር፣ መጥፎ የእስር ቤት አያያዝ፣ የግድያ ዛቻ እና ደብዛ የማጥፋት ድርጊቶች ይፈጸሙባቸዋል” በማለት ይፋ አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያው ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የኢትዮጵያው የይስሙላ ጠቅላይ ሚኒስትር የእርሱ አሻንጉሊት ጌቶች ከጀርባ በስውር ተቀምጠው ከሌሎች የአፍሪካ መሪዎች ጋር ለይስሙላ እንዲቀመጥ አድርገው የይስሙላ ተሳታፊ በማድረግ ሁሉን ሂደት በአንክሮ ይቆጣጠራሉ፡፡

ወደ እራት ግብዣው የማይጠሩ ጥቂት የአፍሪካ “መሪዎች” አሉ፡፡ የዙምባብዌው አዛውንቱ ሮበርት ሙጋቤ እና በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ተጠርጥሮ የእስር ትዕዛዝ የወጣበት ኦማር አልባሽር ከእዚህ የእራት ግብዣ እንዲገኙ ጥሪ አይደረግላቸውም፡፡ ለኤርትራ፣ ለጊኒ ቢሳው እና ለመካከለኛው የአፍሪካ ሬፐብሊክ መሪዎች የግብዣ ጥሪ ከተላለፈ በኋላ በሂደት ከፖሰታ ቤቱ የጥሪ ወረቀቱ የጠፋ ይመስላል፡፡

እውነት ለመናገር ከእነዚህ ወንጀለኞች እና አጭበርባሪ መሪ ተብየዎች ጋር በአንድ ቦታ በአንድ ከተማ አብሬ መገኘት በጣም አስቀያሚ የሆነ ስድብ እንደተሰደብኩ ያህል ይሰማኛል፡፡

የአፍሪካ ለማኞች ወደ ኋይት ሀውስ የሚያስገባ ቀጥተኛ መንገድ መፍጠር ይችላሉን?

ፕሬዚዳንት ኦባማ እነዚህ የአፍሪካ “መሪዎች” ለወደፊት ልጆቻችን ፍላጎት ሲባል ከአሜሪካ ጋር አጋርነት መፍጠር ይችላሉ የሚል ብሩህ ተስፋ አላቸው፡፡ እኔ በበኩሌ በዚህ ዓይነት መልክ አልመለከተውም፡፡ ይልቁንም ለወደፊቶቹ የአፍሪካ ልጆች የልመና መጥፎ ተምሳሌትነትን በማስተማር የስርዓት ቀውስን የሚፈጥሩ የአሜሪካ ለማኞች አድርጌ እቆጥራቸዋለሁ፡፡

በአፍሪካ መሪዎች ዘንድ ያለው የልመና ባህል እኔ ያገኘሁት አዲስ ግኝት አይደለም፡፡ ከብዙ አስርት አመታት ገደማ ጀምሮ በታዋቂው ናይጀሪያዊ ብሄረተኛ፣ ደራሲ እና ቃል አቀባይ በአለቃ ኦባፌሚ አወሎዎ ሲነገር የቆየ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1967 አለቃ ኦባፌሚ አወሎዎ በ4ኛው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጉባኤ ላይ በመገኘት እንዲህ በማለት ንግግር አድርገው ነበር፣ “በአሁኑ ጊዜ አፍሪካ የተፎካካሪ ለማኝ አገሮች አህጉር ናት፡፡ ከድሮዎቹ የእጅ አዙር ቅኝ ገዥ አለቆቻችን እውቅና ለማግኘት እርስ በእርሳችን ውድድር እንገባለን፣ እናም በእኛ የኢኮኖሚ ዕጣ ፈንታ ላይ እንዲወስኑ አንዱ በአንዱ ላይ እተነባበርን ወደ ግዛታችን እንዲመጡልን ልመናችንን እናቀርባለን፡፡“

የአፍሪካ መሪዎች በሚሊዮኖች እና በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ዘርፈው እና በውጭ ባንኮች አጭቀው የሚገኙ ቢሆንም የአፍሪካ ሀብት እነርሱ በሚያስቡት እና በሚያደርጉት ድርጊት መሰረት የለማኞች ኢኮኖሚ ነው፡፡ ለመዝረፍ፣ ለማጭበርበር፣ እና ለመስረቅ የአፍሪካ አምባገነን መሪዎች ጠብመንጃዎቻቸውን እና የማረጃ ካራዎቻቸውን ወደሚዘርፉት ህዝብ በማያዞሩበት ጊዜ ደግሞ የመለመኛ አኩፋዳቸውን ወደ ዓለም አቀፍ መጽዋች ማህበረሰብ ያዞራሉ፡፡ ዋናው ዓላማቸው “አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ ቻይና… ለአፍሪካ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ጠይቅ የሚል ነው… ሁልጊዜ፡፡“ እነርሱ ከአሜሪካ፣ አውሮፓ ወይም ቻይና ምጽዋት፣ ዕርዳታ፣ እና ልመና ውጭ ለአፍሪካ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ምንም ዓይነት ጥያቄ አያቀርቡም፡፡

እ.ኤ.አ በ2012 በአዲስ አበባ ከተማ ለተመረቀው ለአዲሱ የአፍሪካ ህብረት ጽ/ቤት ህንጻ ግንባታ ከአፍሪካ ማን ገንዘብ የከፈለ አለ? ያ ህንጻ “የቻይና ለአፍሪካ የቀረበ ገጸበረከት” ነው፡፡ ቻይና ጠቅላላ የግንባታውን ወጭ የሚሸፍነውን 200 ሚሊዮን ዶላር ያወጣች ሲሆን ለህንጻው መገጣጠሚያ እና ለቢሮ ቁሳቁሶች ጭምር ወጭ አድርጋለች፡፡ የቻይና መንግስት የኮንስትራክሽን  ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ የቻይናን ሰራተኞች በመጠቀም የህንጻውን የግንባታ ስራ አጠናቅቋል፡፡ “የቻይና ለአፍሪካ የቀረበ ገጸበረከት” በአፍሪካ የቻይና ማባበያ ፈረስ ሊሆን ይችላልን?

በአሁኑ ወቅት በህይወት የሌለው መለስ ዜናዊ የተጠናቀቀውን ህንጻ መርቆ ሲከፍት እንዲህ የሚል የጉራ ንግግር አድርጎ ነበር፣ የዚህ ህንጻ ግንባታ በቻይና እና በአፍሪካ ህዝቦች መካከል “ቀጣይነት ያለው የብልጽግና አጋርነት ይፈጥራል፡፡“ መለስ የአፍሪካ የለማኞች አለቃ ነበር፡፡ የሁሉም ጉዳዮች አስፈጻሚ አቅራቢ እንዲሁም የጂ-ምናምን እና የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ተጠሪ ሰው ነበር፡፡ የአፍሪካን ንብረት እና ሀብቶች እንዲሁም የአፍሪካን መሪዎች በጋራ ለአህጉሩ ጉልህ የሚሆን ለውጥ ለማምጣት የሚለው ባዶ መፈክራቸው ሲወድቅ ሳይ በሀፍረት እራሴን እነቀንቃለሁ፡፡ መለመንም ነበረባቸው!!! (የአፍሪካ የለማኞች አዳራሽ በሚል ርዕስ ያዘጋጀሁትን ትችት መመልከት ይቻላል)

አፍሪካ ለምጽዋት እና ለልመና ለበርካታ ጊዚያት የቆዬ የመለመኛ አቁማዳ አላት፡፡ ዳምቢሳ ሞዮ እንዲህ የሚል የመከራከሪያ ጭብጥ አቅርባ ነበር፣ “ባለፉት 50 ዓመታት አንድ ትሪሊዮን ዶላር ልማት ነክ ለሆኑ እርዳታዎች ከኃብታም አገሮች ወደ አፍሪካ ተሰጥቷል፡፡“ ይህ እርዳታ የአፍሪካውያንን/ትን ህይወት ለውጧልን? በፍጹም፡፡ በእርግጥ በአህጉሩ ውስጥ በዚህ እርዳታ ምክንያት አፍሪካውያን/ት ህይወታቸው አልተሻሻለም፣ ሆኖም ግን መጥፎ እና እጅግ በጣም መጥፎ እየሆነ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2013 የሁለትዮሽ እርዳታ (ከአንድ እርዳታ ሰጭ ነጠላ ሀገር ለአንድ እርዳታ ተቀባይ ነጠላ ሀገር) ለሰብ ሰሀራ አፍሪካ የተሰጠው እርዳታ 26.2 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ በጠቅላላ በዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት/በዩኤስ ኤይድ እና በአሜሪካ የመንግስት መምሪያ በዩኤስ አሜሪካ እ.ኤ.አ በ2012 የተሰጠው እርዳታ ከ7.08 ቢሊዮን ዶላር በላይ ነበር፡፡

በአፍሪካ የውኃ ተርቡ የጭልፊቷን ምሳ ሊበላ ይችላልን? 

በመጨረሻም አሜሪካ በአፍሪካ የመሪነቱን ቦታ እየያዙ የመጡትን ቻይናን፣ የአውሮፓ ህብረትን እና ጃፓንን ለመያዝ እየሞከረች ነውን?

በአሁኑ ጊዜ ቻይና የአፍሪካ ትልቋ የሁለትዮሽ የንግድ ሸሪክ መሆኗ አጠያያቂ ጉዳይ አይደለም፡፡ በመጨረሻው ሰዓት አሜሪካ የቻይናን ምሳ ልትበላ ትችላለችን? (በአፍሪካ የውኃ ተርቡ የጭልፊቷን ምሳ ሊበላ ይችላልን? በሚል ርዕስ ከዚህ ቀደም አዘጋጅቸ ያቀረብኩትን የሚለውን ትችት መመልከት ይቻላል፡፡)

የኦባማ አስተዳደር በኢንቨስትመንት፣ በንግድ፣ በመሰረተ ልማት እና በሌሎች መሰል ተግባራት ላይ ላለፉት ጥቂት ዓመታት ሲናገሩ ቆይተዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ፕሬዚዳንት ኦባማ የአሜሪካንን የኃይል ማመንጫ ኩባንያዎች የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ስራዎችን ለማሳለጥ በሚል እሳቤ “አፍሪካን በኃይል ተነሳሽነት ማጠናከር” በሚል ርዕስ የ7 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ ፓኬጅ መዘጋጀቱ የሚታወስ ነው፡፡ እኔ እንደምመለከተው በአሁኑ ጊዜ ብቸኛው የአፍሪካ ኃይል የአፍሪካ መሪዎች ስልጣንን ከህግ አግባብ ውጭ መጠቀም እና ሙስና ናቸው፡፡ (አፍሪካን በኃይል ማሳደግ? አፍሪካን ማጎልበት! የሚለውን ቀደም ሲል ያዘጋጀሁትን ትችት ይመልከቱ)

እ.ኤ.አ በ2012 ፕሬዚዳንት ኦባማ በርካታ የአፍሪካ መሪዎችን ለምግብ ጉባኤ የጥሪ ግብዣ ካደረጉ በኋላ እንዲህ በማለት አወጁ፣ “ለምግብ ዋስትና ኑትሪሽን አዲስ አጋርነት ቀጣይነት እና አካታች የግብርና እድገት ለሚቀጥሉት 10 ዓመታት ከአፍሪካ አመራር ጋር በማቀናጀት 50 ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ ከድህነት ለማውጣት እና ዉጤታማ የአገር እቅድ እና ፖሊሲዎችን ለማሳካት ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ የጋራ እርብርብ የማድረግ ዓላማ አለው፡፡“ አዲሱን አጋርነት ለመተግበር እና አረንጓዴውን የግብርና አብዮት በአፍሪካ ለማቀጣጠል በደርዘን የሚቆጠሩ ዓለም አቀፍ የምግብ ኩባንያዎች ማለትም ታላላቆቹ ህብረብሄራዊ ድርጅቶች ካርጊል፣ ዱፖንት፣ ሞንሳንቶ፣ ክራፍት፣ ዩኒሌቨር፣ ሲንጌንታ ኤጂ “የአፍሪካን ግብርና ልማት ለመደገፍ የግል ዘርፍ አዋጅ“ ስምምነት ተፈርሟል፡፡ የአፍሪካ ህዝቦች ከ20 ወይም 30 ዓመታት በፊት ከነበሩበት በአሁኑ ጊዜ የምግብ ዋስትና አግኝተዋልን? (ምግብ ለረሀብ እና ለማሰብ! በሚል ርዕስ ያዘጋጀሁትን ትችት ይመልከቱ)

ፕሬዚዳንት ኦባማ የአፍሪካን ወጣት አመራሮች ተነሳሽነት ለማጎልበት መጭዎቹን የአፍሪካ ወጣት አመራሮች ለመደገፍ እ.ኤ.አ በ2010 ፊርማ በማስቀመጥ እንዲጀመር አደረጉ፡፡ የዴሞክራሲያዊ አስተዳደርን ለማጎልበት እና ሰላም እና ደህንነትን በአህጉሩ ለማስፋፋት እንዲቻል ስንት ወጣት አፍሪካውያን/ት በዩኤስ አሜሪካ ስልጠና ወሰዱ? በጣም ብቁ የሆኑ ወጣት አፍሪካውያን/ት በአፍሪካ ዴሞክራሲን ያጠናክራሉ ተብለው የሚታሰቡት ማለትም ወጣት ጋዜጠኞች፣ ጦማርያን፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት አመራሮች፣ እና ሰላማዊ አመጸኞች በፍርድ ቤት እየተያዙ እየተንገላቱ ነው፣ እየተሰቃዩ እና በገፍ ወደ እስር ቤት እየተጋዙ ነው፡፡ በአሜሪካ የተሻለ ህይወት መኖር ከጀመሩ በኋላ ስንቶቹ ወጣት የአፍሪካ አመራሮች ወደ አፍሪካ እንደሚመለሱ ማወቅ የሚያስደንቀኝ ነገር ነው! (“ዩኤስ አሜሪካ ከጀግኖች አፍሪካውያን/ት ጎን ልትሰለፍ ትችላለችን?” በሚል ርዕስ ያቀረብኩትን ትችት ይመልከቱ)

የአወሎዎ ተቃርኖየልመና ባህልን እንዴት ማስወገድ እንደሚቻል እና የልመና አፍቅሮትን እንዴት ማጥፋት እንደሚቻል፣

የአፍሪካ “መሪዎች” አፍሪካን እና እራሳቸውን ለማዳን ከፈለጉ የአለቃ አዎሎዎን ነቢያዊ እና ተቃርኖያዊ ቃላትን በምክርነት መከተል አለባቸው፡፡ በ1967 ባደረገው ንግግር አለቃ አዎሎዎ የአፍሪካን መሪዎች በሚከተለው መልክ አስጠንቅቋል፡

“ወደፊት እንቀጥላለን፣ እናም ለመቀጠላችን ኃይል ለመጠቀም እና ሉዓላዊነት የሰጠንን እምነት በመጠቀም ተጽእኖ ለመፍጠር ትክክለኞች ነን፡፡ እንደዚሁም ደግሞ የሚደረጉት ስልቶች እና ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲዎች ህጋዊነት ያላበሱትን ከገንዘብ ለጋሾች ብዙ ምጽዋቶችን ለመሰብሰብ ውይይት ተደርጓል፡፡ ሆኖም ግን ቋሚው ሰይጣን እንዳለ ነው፣ እናም ከእኛ ጋር ይቆያል ከማንም ጋር ሳይሆን፡፡ ለማኝ ፊቱን ካላዞረ እና በማይመለስ መልኩ ጀርባውን ካልሰጠ በስተቀር እድሜ ልኩን ለማኝ እንደሆነ ይቀራል፡፡ ብዙ በለመነ ቁጥር የለማኝነት ባህሪን የበለጠ እያዳበረ ይሄዳል፣ የተነሳሽነት እጥረት፣ ድፍረት፣ ቁርጠኝነት እና በእራስ የመተማመን ወኔ እየራቀ ይሄዳል፡፡”

የአፍሪካ መሪዎች ሀብታም ለማኞች እንደሆኑ አምናለሁ፡፡ በመስታወት ውስጥ እራሳቸውን ሲመለከቱ ሚሊየነሮችን፣ ቢሊየነሮችን እና በሀብት እና በተፈጥሮ ሀብት የተሞላች አህጉር፣ መመልከት አይችሉም፡፡ ይልቁንም የእራሳቸውን ምስል እና በድህነት ውቅያኖስ ላይ የምትዋኘውን እና ግልጽ ባልሆነ መልኩ በሙስና እና በሰብአዊ መብት ረገጣ በመስመጥ ላይ የምትገኝ አህጉርን ይመለከታሉ፡፡ ድህነት አካላዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ብቻ የሚያረጋግጥ ጉዳይ አለመሆኑን ሆኖም ግን የህሊና ጉዳይ ጭምርም እንደሆነ የሚያመላክት ነው፡፡ የሞራል ዝቅጠት የደረሰባቸው በመሆኑ ምክንያት ሁልጊዜ መለመን አለባቸው እናም በማያቋርጥ ሁኔታ እራሳቸውን ከምጽዋት፣ ከልመና እና ልግስና ጋር በማዋሀድ የአዘቅት ህይወትን እየመሩ ይገኛሉ፡፡ የልመናው ባህል እና የምጽዋት አፍቅሮ በደም ስራቸው ውስጥ ዘልቆ ገብቷል፡፡ ብቸኛው ጥያቄ ግን እነዚህ የምጽዋት ቀበኞች አለቃ አዎ ከብዙ ጊዜ በፊት እንደተገረመው  ለዘላለም ለማኞች እንደሆኑ ይቀራሉ ወይ የሚለው ነው፡፡

እንደ ሰብአዊ መብት ተሟግችነቴ ፕሬዚዳንት ኦባማ እ.ኤ.አ በ2009 አክራ ጋናን በጎበኙበት ወቅት የተናገሯቸውን ቃላት እንዲያከብሩ ብቻ ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ “… አንዳትሳሳቱ ተገንዘቡ፣ ታሪክ ከእነዚህ ጀግና አፍሪካውያን/ት ጎን ነው፣ እናም ታሪክ መፈንቅለ መንግስት ከሚያደርጉ ወይም ደግሞ በስልጣን ላይ ለመቆየት እንዲያስችላቸው ህገመንግሰቱን ከሚቀይሩ ሰዎች ጋር አይደለም፡፡ አፍሪካ ጠንካራ ሰዎችን አትፈልግም፣ አፍሪካ የምትፈልገው ጠንካራ ተቋማትን ነው…“ፕሬዚዳንት ኦባማ ከጠንካራ የአፍሪካ ሰዎች ጎን በመቆም ታላቅ ስህተት ሰርተዋል የሚል አምነት አለኝ ::

ለፕሬዚዳንት ኦባማ የማቀርበው ብቸኛ ጥያቄ የሚከተለው ነው፣ የአፍሪካ መሪዎች የአሁኑን ትውልድ በመቀማት እና በማባከን ላይ እያሉ በምን ዓይነት ሁኔታ ነው በሚቀጥለው ትውልድ ላይ ሀብትን በማፍሰስ ለውጥ ለማምጣት የሚታሰበው?

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ነሐሴ 17 ቀን 2006 .