የአሜሪካ እሴቶች በአፍሪካ ውስጥ ምን ፋይዳ አላቸው?


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

“እኛ ትክክለኛ እና ጠቃሚ የሆኑ በርካታ ነገሮችን አከናውነናል፣ ሆኖም ግን ከዚህ በተለዬ መልኩም ህዝብን አሰቃይተናል፣ ከእሴቶቻችን ጋር ተጻጻሪ የሆኑ ነገሮችን ፈጽመናል፡፡ ከፍ ወዳሉ የምርመራ ስልቶች ስንገባ ማለትም ማሰቃየትን ጨምሮ ማንም ሚዛናዊ የሆነ አስተሳሰብ ያለው ሰው እንደሚያስበው እና እንደሚያምነው የምናደርገው ድርጊት ማሰቃየት ሆኖ ሲገኝ መስመሩን አለፍን ማለት ነው፡፡ እናም ይህ ጉዳይ ግንዛቤ ሊወሰድበት እና ተቀባይነትንም ማግኘት አለበት“ በማለት ፕሬዚዳንት ኦባማ ከጥቂት ቀናት በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ገልጸዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ የሲአይኤ ስለላ ክፍል ዘገባ በትክክል ያልቀረበ መሆኑን በመግለጽ የአንድ ዋና መርማሪን ዘገባ ካዳመጡ በኋላ የኮንግረሱን ትችት ለማደብዘዝ ሲባል በዚያ ድርጅት የቀረበውን የምርመራ ስልት ህገወጥ በሆነ መልኩ የሴኔቱን ኮምፒውተር በመሰለል ትክክል አለመሆኑን ያላቸውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ ለአሜሪካውያን/ት እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል፣ “የአሜሪካ ህዝብ ላለፉት በርካታ ዓመታት ባከናወናቸው አበይት ተግባራት በመኩራራት የሞራል የበላይነትን ከማንገስ ስሜት እንዲቆጠብ“ በማለት አሳስበዋል፡፡ እንደዚሁም በተመሳሳይ መልኩ ፕሬዚዳንት ኦባማ እንዲህ የሚል ትዕዛዝ ሰጥተዋል፣ “የሀገራችን ልዩ መለያ የሆነው ባህሪ ነገሮች ቀላል በሚሆኑበት ጊዜ ብቻ በከፊልም ቢሆን መለካት የለበትም፣ ሆኖም ግን ይህ ጉዳይ መገምገም እና መለካት ያለበት ነገሮች ከባድ በሆኑበት እና መፈናፈኛ በጠፋበት ጊዜ ጭምር መሆን ይኖርበታል፡፡“

በፕሬዚዳንት ኦባማ የተወገዘው የሲ አይ አኤ ማሰቃየት ድርጊት ቀደም ሲል በሽብርተኝነት ላይ ለተከፈተው ጦርነት ዋና መሀንዲስ በነበሩት በአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት በዲክ ቸኒ ወደ ላቀ የምርመራ ደረጃ በማሸጋገር የማሰቃየት የምርመራ ዘዴን እንደጀመሩት ይታወሳል፡፡ የቡሽ አስተዳደር የማሰቃየት የምርመራ ዘዴውን ከፍ ወዳለ ደረጃ ማለትም በውኃ ውስጥ መዝፈቅ፣ እንቅልፍ እንዳይተኙ መከልከል፣ ድምጽ እና ብርሀን በመልቀቅ የስሜት ህዋሳት እዲረበሹ ማድረግ፣ ለተራዘመ ጊዜ ብቻን አድርጎ ማቆየት እና የጾታ ትንኮሳን ማካሄድ ከብዙዎቹ የማሰቃያ ዘዴዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በቅርቡ ዲክ ቸኒ እንዲህ ብለው ነበር፣ “ሁሉንም ነገር ማድረግ ካሰብኩ ላደርገው እችላለሁ፡፡“

የማሰቃየት የምርምራ ዘዴን አስመልክቶ ፕሬዚዳንቱ ለዩኤስ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ያደረጉት ንግግር ስለማሰቃየት ድርጊት በአንክሮ እንዳስብ አድርጎኛል፡፡ እ.ኤ.አ ከኦገስት 5 – 6/2014 ለሚካሄደው ጉባኤ ፕሬዚዳንት ኦባማ የማሰቃየት ልምድ ያካበቱትን፣ የሙስና ጠበብቶችን እና የሰብአዊ መብት ረገጣ የወንጀል ጌቶችን ከአፍሪካ ስለንግድ እና ስለአሜሪካ ኢንቨስትመንት ፍሰት ጉዳይ (ስለሰብአዊ መብት ወይም ደግሞ አሜሪካ እየተከተለቻቸው ስላሏት እሴቶች ሳይሆን) ለመነጋገር በኋይት ሀውስ ተሳትፎ እዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈው ነበር፡፡ በበርካታ የሰብአዊ መብት ረገጣ የወንጀል ክሶች ጉዳያቸው በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በመታየት ላይ ካለው ከኬንያው ምክትል ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጭምር በጉባኤው ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የተሳታፊዎች ስም ዝርዝር በሰብአዊ መብት ረገጣ ዕኩይ ተግባራት ጣራ የነኩትን እና ለዚህ እኩይ ምግባራቸው ሰርቲፊኬት ያገኙትን ማለትም የካሜሮኑን ፓውል ቢያንን፣ የቡርኪና ፋሶውን ብላይስ ኮምፓውሬንን፣ የሩዋንዳውን ፓውል ካጋሜንን፣ የኡጋንዳውን ዮሪ ሙሴቬንን፣ የኢኳቶሪያል ጊኒውን ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ንጉማ ባሶጎንን፣ የአንጎላውን ኤዱዋርዶ ዶሳንቶስን፣ የቻዱን ኢድሪስ ዴቢንን፣ እና የጋምቢያውን ያህያ ጃመህን ያካተተ ነው፡፡ እነዚህ በሰብአዊ መብት ረገጣ ወንጀል የተዘፈቁ የአፍሪካ አምባገነን መሪዎች የሲአይኤን የወንጀል ምርመራ ዘዴዎች በፓርክ ውስጥ እንደመሄድ ያህል የቀለለ እንዲሆን አድርገውታል፡፡

ለማመን በሚያስቸግር መልኩ ፕሬዚዳንት ኦባማ እነዚህን የሰብአዊ መብት ህግን ደፍጣጮች እና ሸፍጠኛ አምባገነኖች የአሜሪካ “አጋሮች” እያሉ ይጠሯቸዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ “የሀገራችን ልዩ መለያ የሆነው ባህሪ ነገሮች ቀላል በሚሆኑበት ጊዜ ብቻ በከፊልም ቢሆን መለካት የለበትም፣ ሆኖም ግን ይህ ጉዳይ መገምገም እና መለካት ያለበት ነገሮች ከባድ በሆኑበት እና መፈናፈኛ በጠፋበት ጊዜ ጭምር መሆን ይኖርበታል“ በማለት የይስሙላ ጩኸት ያሰማሉ፡፡ ሆኖም ግን የፕሬዚዳንታችንን ባህሪ እንዴት መለካት እንችላለን? ፕሬዚዳንቱ በሚናገሯቸው ማራኪ ቃላት እና በተዋቡ ሀረጎች ወይም በድርጊት አልባ ተሞክሯቸው መቸ ነው “ነገሮች ሁሉ ከባድ የሚሆኑት”? የቀድሞ አባባል እንደሚያሳየን “አንድ ሰው ያለው ቁምነገር በሚያራምደው የጓደኝነት ጥራት ላይ የሚመሰረት ከሆነ አንድ ሰውም ባሉት እና በሚያራምዱት የአጋርነት ባህሪ የሚመዘን ሲሆን ፕሬዚዳንት ኦባማ ከአፍሪካ የሰብአዊ መብት ደፍጣጭ ወንጀለኞች ጋር አጋርነትን ሲመሰርቱ በሞራል ልዕልና የበላይነት እና በእምነተ ቢስነት እና በሙሰኝነት መካከል ያለውን መስመር አላለፉም ነበርን? ማሰቃየትን አስመልክቶ በአሜሪካ ባሉ እሴቶች እና በአፍሪካ በሚተገበሩ የአሜሪካ እሴቶች መካከል ባሉ እሴቶች ላይ ልዩነት ለመኖሩ ግንዛቤ ጠፍቶ እና ተቀባይነት አጥቶ ነውን?

በአፍሪካ የአሜሪካ የንግድ መዋዕለንዋዮች ከሞራል ስግብግብነት ውጭ በተመሰረቱ መርሆዎች ላይ ሳይሆን በስቃይ እና በዘረፋ ላይ የተመሰረቱ እንደሆኑ አምናለሁ፡፡ በሰብአዊ መብት መከበር ላይ ያልተመሰረተ አንድ በአፍሪካ ላይ የሚተገበር የአሜሪካ ኢኮኖሚያዊ መዋዕለ ንዋይ ፖሊሲ በአፍሪካ አህጉር ላይ የተንሰራፋውን ሙስና ከማፋጠን እና የአፍሪካውያንን/ትን ስቃይ እና ተስፋ ከማደብዘዝ ውጭ የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ በአፍሪካ ባንኮች፣ ግድቦች፣ የማዕድን ቦታዎች፣ የባቡር ሀዲዶች፣ ሆቴሎች እና ህንጻዎች ላይ የሚተገብሯቸው ስራዎች ከሞራል መሰረት ውጭ ፋይዳ የሌላቸው እና በቂ አለመሆናቸውን መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህም በላይ አሜሪካ ቻይና አይደለችም፡፡ የአሜሪካ እሴቶች የቻይና እሴቶች አይደሉም፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ እንዲህ ብለው ነበር፣ “አሜሪካኖች እንደ እንግሊዞች፣  እንደዚሁም እንደ ግሪኮች የተለየ ልዩ ባህሪ አላቸው…“ ያ ልዩነት በአሜሪካ የነጻነት እሴቶች፣ እኩልነት፣ ግለሰባዊነት፣ ሬፐብሊካዊነት፣ ብዝሀነት እና በነጻ የኢኮኖሚ የንግድ መርሆዎች  ላይ የተመሰረተ ነው፡፡

የካፒታሊዝም አባት የሆነው አዳም ስሚዝ እንኳ የሞራል መሰረትን በመገንዘብ ትክክለኛ፣ ፍትሀዊ እና ፍቅር የነገሰበት ማህበረሰብን በነጻ የኢኮኖሚያዊ ስርዓት የመመስረትን አስፈላጊነት በመገንዘብ አጽንኦ በመስጠት ተከታታይነት ያለው ትምህርት መስጠት እንደሚያስፈልግ አስተምሯል፡፡ ይህንንም “የጋራ አስተሳሰብ” ብሎ የሰየመው ሲሆን ከዚህ አስተሳሰብ ውጭ የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት አካሄድ የሞራል ኪሳራን እና ዝቅጠትን እንደሚያስከትል ተናግሯል፡፡ ይህ የጋራ አስተሳሰብ ባለብቶች እና ኃይለኞች በሀብታቸው እና በጉልበታቸው በመመካት ደካሞችን እና አቅመቢሶችን እዳያጠቀቋቸው ለማድረግ የሚያስችሉ ጠቃሚ ነገሮች ናቸው በማለት አስፈላጊነታቸውን ግልጽ አድርጓል፡፡ በአፍሪካ በሚከናወኑ የአሜሪካ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት የጋራ አስተሳሰብ መሰረቶች ላይ የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ እና ወደፊትም ይኸው መርህ ብቻ መሆን ይኖርበታል፡፡ አሁንም ላሰምርበት የምፈልገው እውነታ አፍሪካ የሰው ልጆች መገኛ የመሆኗን ያህል በአሁኑ ጊዜ የሰብአዊ መብቶች መቀበሪያም ሆናለች፡፡

ፕሬዚዳንት  ኦባማ በእርግጠኝነት በአሜሪካ እሴቶች ላይ እምነት አላቸውን? ፕሬዚዳንት ኦባማ ከአፍሪካ አምባገነኖች ጋር አጋርነትን በመመስረት የትኞቹን የአሜሪካ እሴቶች ነው  የደፈጠጧቸው? 

ሴናተር ኦባማ “የተስፋ መለምለም፡ አሜሪካንን ህልም የመመለስ ሀሳብ” በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፍ ላይ እንዲህ የሚል ጽሑፍ አስፍረዋል፣

በጊዜ ሂደት የተፐወዙ እና የደበዘዙ ቢመስሉም እንኳ በእሴቶቻችን ላይ ተጣብቀን እንቀጥላለን፡፡ እንደ ሀገር እና እንደ የግል ህይወታችን ማየት የሚገባን ቢሆንም እንኳ አብዛኛውን ጊዜ ከምናስታውሳቸው በላይ ስንተገብራቸው አንታይም፡፡ ታዲያ እኛ ልንመራባቸው የሚገቡ ሌሎች መርሆዎች እና እሴቶች ምን ሊሆኑ ይችላሉ? እነዚያ እሴቶች የወረስናቸው ውርሶች ናቸው፣ እናም እኛን እንደ ህዝብ ያደረገን ምንድን ነው? እኛ እንደ ህዝብ እሴቶቻችን ለበርካታ ችግሮች የተጋለጡ እንደሆኑ የምናምን ቢሆንም ምሁራን እና ሌሎች የባህል ትችት አቅራቢዎች ጣት የሚቀስሩባቸው እና ትችት የሚሰነዝሩባቸው ቢሆኑም ለበርካታ ጊዚያት በመደቦች እና ጎሳዎች አንዲሁም እምነቶች እና ትውልዶች መካከል፣ በስራ ላይ ሲውሉ ቆይተዋል፡፡ የእኛ እሴቶች በእውነታ እና በልምድ የተፈተኑ መሆናቸውን ለማረጋገጥ  እነርሱን በመወከል በተግባር የሚገለጹ እንጅ በቃላት ብቻ የሚነበነቡ አለመሆናቸውን ልንጠይቅ እንችላለን…፡፡ ለእሴቶቻችን ዋጋ ለመክፈል ዝግጁዎች እስካልሆን ድረስ፣ እነዚህን እሴቶች ለመተግበር መስዋዕትነት ለመክፈል ዝጉጁዎች ካልሆንን በእርግጠኝነት በእነዚህ እምነቶች ላይ ሙሉ እምነት ያለን እና የሌለን ለመሆናችን እራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡

ፕሬዚዳንት ኦባማ “የአሜሪካን እሴቶች” ወይም ደግሞ “የእኛ እሴቶች” እያሉ ሲናገሩ ምን ለማለት ፈልገው እንደሆነ በእርግጠኝነት ለማወቅ አልቻልኩም፡፡ በእርግጠኝነት እነዚህን እሴቶች ሲተገብሯቸው በፍጹም አልታዩም፡፡ በየትኞቹ እሴቶች ላይ መጣበቅ እንዳለባቸው ለማወቅ አስቸጋሪ ጉዳይ ነው፡፡ የትኞቹን እሴቶች ነው የወረስናቸው ወይም ደግሞ ያልተገበርናቸው? የአሜሪካንን እሴቶች ያልተገበራቸው እና የከዳቸው በእርግጠኝነት ማን ነው? ጣታቸውን የሚቀስሩት ምሁራን እና ባህላዊ ትችት አቅራቢዎች ናቸው ወይስ ደግሞ እነዚህ እሴቶች ወደ ተግባር እንዳይሸጋገሩ መስዋዕትነትን ለመክፈል ዝግጁ ያልሆኑ የአሜሪካ መሪዎች? በየትኞቹ የአሜሪካ እሴቶች ላይ ነው አሜሪካውያን/ት እምነት ያላቸው?

ማሰቃየት የአሜሪካ እሴት ነውን?

አንድ ጊዜ እ.ኤ.አ በፌብሯሪ 2012 ለተባበሩት የአውቶሞቲቭ ሰራተኞች ንግግር ባደረጉበት ጊዜ ፕሬዚዳንት ኦባማ የአሜሪካንን እሴቶች ግንዛቤ እንዲህ በማለት አጭር ጨረፍታ ሰጥተው ነበር፡፡ “ከልብ ልነግራችሁ እፈልጋለሁ፣ ሁልጊዜ ከህዝቡ ስለእነዚህ ተመሳሳይ እሴቶች አፈታሪክ ሲነገር እሰማለሁ፣ ስለእሴቶቻችን ለመናገር ትፈልጋላችሁን? ጠንካራ ሰራተኝነት…ይህ ትልቅ እሴት ነው (ጭብጨባው ቀለጠ)፣ እርስ በእርስ መተሳሰብ… ይህ ታላቅ እሴት ነው፡፡ ሁላችንም ነበርንበት የሚለው ሀሳብ እና እኔ የእኔ ወንድም እና እህት ጠባቂ ነኝ የሚለው…ይህ እሴታችን ነው፡፡“ 

በእርግጠኝነት የማምንባቸው የአሜሪካ እሴቶች፣

አሜሪካውያን/ት ከልብ የሚያምኑባቸው ታላላቅ ባህላዊ እሴቶች አሏቸው፣ ከእነዚህም ውስጥ ጠንካራ የስራ ዲሲፕሊን፣ ለሌሎች አሳቢ መሆን፣ እራስ ወዳድ አለመሆን እና ሁሉም ሰው መከሰስ እንደሚችል ማመን የሚሉት የአሜሪካ እሴቶች በእርግጠኝነት ፊርማቸው የማይናወጡ የአሜሪካ እሴቶች ናቸው፡፡ ፕሬዚዳንቱ ከተናገሯው ውጭ የረሷቸው ሌሎች ታላላቅ የአሜሪካ እሴቶች እንዳሉ አስባለሁ፡፡ አሜሪካውያን/ት ለግል መብቶች ነጻነት እና ግለሰብአዊነት ታላቅ ቦታ የሚሰጡ እና ይህም ማለት ግለሰብ በተለየ መልኩ ልዩ እና በጣም ጠቃሚ የሆነ ነገር እንደሆነ እምነት አለኝ፡፡ የግለሰቦችን ተነሳሽነት፣ ግለሰቦች ሀሳባቸውን የመግለጽ ሙሉ መብት እንዳላቸው እና የግለኝነት ሙሉ መብት እንዳላቸው በከፍተኛ ሁኔታ ዋጋ ይሰጣሉ፡፡ በእኩልነት እና ግልጽ ማህበረሰብን በመገንባት ረገድ ትልቅ ዋጋ ይሰጣሉ፡፡ ለሳይንስ እና ለቴክኖሎጂ መዳበር እና ስርጸት ከፍተኛ ዋጋ ይሰጣሉ፡፡ በውድድር መርህ ላይ ሙሉ እምነት ይሰጣሉ (ዩኤስኤ ሁልጊዜ አንደኛ ) የሚል አስተሳሰብ አላቸው፡፡ ለበጎ ፈቃደኝነት እና ግብረገባዊ እርዳታ መስጠት ተግባራት ታላቅ ዋጋ ይሰጣሉ፡፡ ለእልህ አስጨራሽ ጥረት እና ለስኬት-አዘል እንቅስቃሴዎች ልዩ ዋጋ ይሰጣሉ፡፡ አሜሪካውያን/ት ኃቀኞች፣ ግልጾች፣ እና ለሚያደርጓቸው ነገሮች ሁሉ ቀጥተኞች ናቸው፡፡ በእርግጠኝነት እኔም በእነዚህ እሴቶች ላይ ሙሉ እምነት አለኝ፡፡

ሆኖም ግን ለተግባራዊነታቸው መስዋዕትነት ሊከፈልባቸው የሚገቡ ሌሎች የበለጡ የአሜሪካ እሴቶች አሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ትልቁ እሴት የህግ የበላይነት መጠበቅ ነው፡፡ ይህ ማለት ህግ አገርን ማስተዳደር አለበት እንጂ ፖለቲከኞችን ማስተዳደር የለበትም፡፡ የፕሬዚዳንት ድዊት ዲ. ኢሰንሀወር አባባልን በመዋስ፣ “ለአሜሪካ የህግ የበላይነት ምን ማለት እንደሆነ ለማሳየት    በአሁኑ ጊዜ የህግ የበላይነት ባልተጠበቀበት በአፍሪካ የቀን ተቀን የህዝብ ህይወት ላይ የሚፈጸሙትን በደሎች ማስታወስ ብቻ ነው፡፡“ እኔ የህገመንግሰታዊ ስርዓት ግንባታ የህግ ባለሙያ የሆንኩበት ዋናው ምክንት በህግ የበላይነት ላይ የማይናወጥ እምነት እና አቋም ስላለኝ ብቻ ነው፡፡

የአሜሪካንን የመናገር፣ የፕሬስ ነጻነት፣ በሰላማዊ መልክ ለመሰብሰብ እና ቅሬታን በሰላማዊ መንገድ ለመንግስት ለመግለጽ፣ ከህግ አግባብ ውጨ በሆነ መልኩ ከሚደረግ ምርመራ እና መያዝ፣ የህግ የምክር አገልግሎት የማግኘት እና ጥላሸት ከመቀባት የውንጀላ ድርጊት ለመከላከል ሲባል የተጣሉት የአሜሪካ እሴቶች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲደረጉ እንዲሁም እንዲጠበቁ እና ክብካቤ እንዲደረግላቸው…ወዘተ “የተወሰኑ መስዋዕትነቶችን ለመክፈል ሙሉ ፈቃደኝነት አለኝ፡፡ “መንግስት የሰውን ህይወት ከማጥፋቱ በፊት ትክክለኛውን የህግ ሂደት መርሆ መከተል እንዳለበት፣ የነጻነት ወይም የንብረት ዋስትና መርሆዎችን የመከተል፣ ከአድልኦ በጸዳ መልኩ የፍትህ ሂደቱ መካሄድ እንዳለበት እና በዋና ዋናዎቹ የአሜሪካ ፊትሐዊ እሴቶች ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት ሙሉ እምነት አለኝ፡፡ አንድ በጥርጣሬ ተወንጅሎ የተያዘ ተጠርጣሪ ጥፋተኝነቱ በፍርድ ቤት እስካልተረጋገጠ ድረስ ጥፋተኛ ሊባል እንደማይገባ እና ነጻ እንደሆነ መንግስት ከጥርጣሬ በላይ ማረጋገጫ ሊሰጥ ይገባል፡፡ መንግስት አንድን በጥርጣሬ የተያዘ ሰው ከፍላጎቱ ውጭ መብቱን በመጣስ ለምርመራ ተብሎ በግዳጅ ቃል እንዲሰጥ መጠየቅ እንደሌለበት እና ዝም የማለት እና ያለመናገር መብቱ ሊጠበቅለት እንደሚገባ የማክበር እና የመሳሰሉትን የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡

እንደዚሁም ደግሞ የአሜሪካን የውክልና መንግስት፣ የአካባቢ እና የፌዴራል መንግስት እሴቶች እንዲጠበቁ “የተወሰኑ መስዋዕትነቶችን ለመክፈል ሙሉ ፈቃደኝነት አለኝ፡፡” ልዩ የጥድፊያ ፍላጎትን ሊያስወግድ የሚችል ሌላ የጥድፊያ ፍላጎትን የሚተገብር መንግስት ስርዓት መኖር እንዳለበት እምነት አለኝ፡፡ ስልጣን በአንድ ግለሰብ ወይም በሌሎች ቡድኖች እና በአካባቢ መንግስታት መዳፍ ስር እንዳይከማች እና አደገኛ የሆነ ችግር እንዳይፈጠር ለማድረግ ህገመንግስታዊ የስልጣን ክፍፍል መኖር እንዳለበት አምናለሁ፡፡

የተጠያቂነት እና የቁጥጥር ስርዓት ያለው መንግስታዊ ስርዓት ነጻ ከሆነ የፍትህ አካላት ጋር መኖር የአንድ ስርዓት የጀርባ አጥንት እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ስልጣንን ለክልል እና ለፌዴራል መንግስት አግባብ በሆነ መልኩ በማከፋፈል የተዋቀረ ፌዴራላዊ የመንግስት አወቃቀር መኖር እንዳለበት አምናለሁ፡፡ በአጭሩ በነጻነት፣ እኩልነት፣ እና በሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ላይ እንዲመሰረት “የተወሰኑ መስዋዕትነቶችን ለመክፈል ሙሉ ፈቃደኝነት አለኝ፡፡”

አንድ በአሜሪካ እሴቶች ላይ ሙሉ እምነት ያለው ሰው እንዴት ከአፍሪካ አምባገነኖች ጋር አጋርነት  ሊመሰርት ይችላል?

ባለፉት ስድስት ዓመታት ከፕሬዚዳንት ኦባማ እና ከአስተዳዳራቸው ስለአሜሪካ እሴቶች እና ስለአፍሪካ የሰብአዊ መብቶች መከበር በርካታ ቃልኪዳኖችን የያዙ ብዙ ንግግሮች ሲደረጉ ሰምተናል፡፡ እንዲህ የሚሉትንም አዳምጠናል፣ “ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ለመመስረት እና ግልጽ የፖለቲካ ውይይት እና ምክክር በማድረግ ለኢትዮጵያ ተጨባጭነት ያለው ለውጥ ለማምጣት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቅርበት እንሰራለን… በእስር ቤት ውስጥ የሚገኙ ምሁራን፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና የተቃዋሚ የፖለቲካ መሪዎች እንዲፈቱ አበርትተን እንሰራለን…ሁሉም የሰው ልጅ ዘሮች የሚያምኑበትን ነገር ያለምንም መሸማቀቅ መግለጽ እንዲችሉ፣ መሪዎቻቸውን ያለማንም ጣልቃገብነት መምረጥ እንዲችሉ እና በክብር እና በመፈቃቀር ላይ በተመሰረተ ስርዓት መኖር እንዲችሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሴቶች እና ከወንዶች ጎን እንሰለፋለን…፡፡የአፍሪካን ወጣቶች እናጠናክራለን… አፍሪካ ጠንካራ ሰዎች አያስፈልጓትም፣ ይልቁንም ጠንካራ ተቋማት ናቸው የሚያስፈልጓት፡፡ ጠንካራ እና ቀጣይነት ያላቸው መንግስታትን እንደግፋለን… አሜሪካ እጆቿን ለመዘርጋት ከመቸውም ጊዜ በላይ ተዘጋጅታለች፡፡ እርዳታ በእራሱ ግብ አይደለም… አምባገነንነት በእራሱ ዴሞክራሲ አይደለም፣ ይልቁንም የጭቆና አገዛዝ ነው፣ እናም ከዓለም ዳብዛው እንዲጠፋ ለማድረግ ጊዜው አሁን ነው… አሜሪካ እየተመለከተች ነው…“እስከ አሁን ድረስ የሰማናቸው እና እየሰማናቸው ያሉት ሁሉም ባዶ ቃል ኪዳኖች እና እርካሽ ንግግሮች ናቸው፡፡

ኤድመንድ ቡርኬ የተባሉት የእንግሊዝ ቃል አቀባይ እና ፈላስፋ እንዲህ ብለው ነበር፣ “የሞራል ዝቅጠት ከሚገባው ቃልኪዳን በላይ ዘልቆ የማይሄድ ምንም ዋጋ የሌለው ነገር ነው፡፡“ የአሜሪካንን እሴቶች ከሚገባው በላይ እያጋነኑ ዲስኩርን መደርደር ንግግሩን ለሚያደርጉት ምንም ዓይነት ዋጋ የሌለው እና ንግግራቸውን በተግባር የማይተገብሩ ባዶ የተስፋ ልፍለፋ ነው፡፡ ሆኖም ግን የአሜሪካንን እሴቶች ከመጠን ባለፈ መልኩ እያጋነኑ የሚያወሩ በሚሰሟቸው ህዝቦች ላይ ባዶ ተስፋን እያወሩ በአሜሪካ ላይ እያወሩ በአፍሪካ ላይ የማይተገብሩ በአንድ ወቅት ዋጋ የሚያስከፍላቸው መሆኑን ሊገነዘቡት ይገባል፡፡

በሽብርተኝነት ላይ በተከፈተው ዓለም አቀፍ ጦርነት አሜሪካ ከመንግስታዊ አሸባሪዎች ጋር አጋርነትን መመስረቷ አስፈላጊዊ ሊሆን ይችላል፡፡ በአሸባሪዎች እና በመንግስታዊ አሸባሪዎች መካከል ባለው መስተጋብር መንግስታዊ አሸባሪነት ለፕሬዚዳንት ኦባማ አስተዳደር ከሁለቱ ሰይጣኖች ያነሰ ሆኖ ሊታየው ይችላል፡፡ የጸረ ሽብር ፖለቲካ ለዩኤስ አሜሪካ እና ለአፍሪካ መሪዎች እንግዳ አጋርነት ነው፡፡ ይህንን ካልኩ በኋላ የአሜሪካ ህዝብ የሚያዋጣው የዶላር ግብር የአሜሪካንን እሴቶች በአፍሪካ አህጉር ለመተግበር በድጋፍነት እየዋለ ነው በማለት ህዝቡ እንዲታለል የሚያደርጉት ጥረት የሚያበሳጨኝ ነገር ነው፡፡ የአሜሪካ ህዝብ የሚያዋጣው የዶላር ግብር በአፍሪካ አጭበርባሪ አምባገነን መሪዎች ኪስ ሲታጨቅ እና ለግል የቅንጦት መጠቀሚያ ፍላጎታቸው በቀጥታ በውጭ በሚገኙ ባንኮች ሲከማች ስመለከት በጣም ያበሳጨኛል፡፡ ሆኖም ግን እነዚህን መቅኖቢስ የአፍሪካን ለማኝ መሪዎች በቀጥታ ወደ ኋይት ሀውስ በመዝለቅ በንጉሳውያን ኃያላን ፊት ተገኝተው የእጆቻቸውን መዳፎች እያሻሹ እና ለከታቸውን እስከጆሯቸው ድረስ እየገለፈጡ የሚሰጣቸውን የውጭ እርዳታ የደህንነት ቸክ በጥቂት ቀናት ውስጥ ለመረከብ ሲተራመሱ ስመለከት በጣሙን እበሳጫለሁ!!!

ለእሴቶቻችን ዋጋ ለመክፈል ፈቃደኛ ካልሆንን እና ለተግባራዊነታቸው የተወሰኑ መስዋዕትነቶችን ካልከፈልን በእርግጠኝነት በእነዚህ እሴቶቻችን ላይ እምነት ያለን ለመሆናችን እራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል ሴናተርባራክኦባማ 

ዩናይትድ ስቴትስ ሰብአዊ መብቶች በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር እንዲከበሩ ለማድረግ ጠንክራ ትሰራለችሁሉም የሰው ልጅ ዘሮች የሚያምኑበትን ነገር ያለምንም መሸማቀቅ መግለጽ እንዲችሉ፣ መሪዎቻቸውን ያለማንም ጣልቃገብነት መምረጥ እንዲችሉ እና በክብር እና በመፈቃቀር ላይ በተመሰረተ ስርዓት መኖር እንዲችሉ ለማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሴቶች እና ከወንዶች ጎን እንሰለፋለን፡፡ የአፍሪካን ወጣቶች እናጠናክራለን አፍሪካ ጠንካራ ሰዎች አያስፈልጓትም፣ ይልቁንም ጠንካራ ተቋማት ናቸው የሚያስፈልጓት፡፡ ጠንካራ እና ቀጣይነት ያላቸው መንግስታትን እንደግፋለን አሜሪካ እጆቿን ለመዘርጋት ከመቸውም ጊዜ በላይ ተዘጋጅታለች፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ደህንነታችንን እና ሰላማችንን እናጠናክራለን፣ ምክንያቱም የሰብአዊ መብቶች መደፍጠጥ በዓለም ላይ የሚያጋጥሙንን አደጋዎች የበለጠ ተመጋጋቢ በማድረግ ወታደራዊ ግጭት እና ሰብአዊ ቀውሶችን በማስከተል በሙስና፣ በጥላቻ እና በኃይል የተሞላ ርዕዮተ ዓለም እንዲስፋፋ መንገድ ይከፍታል፡፡ ፕሬዚዳንትባራክ ኦባማ 

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ነሐሴ 18 ቀን 2006 .