“ላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ” የግንቦት ሰባት የትጥቅ ትግል


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ከእምቢበል ወገኔ

ሰሞኑን በተለያዩ በውጭ በሚገኙ የኢትዮጵያውያን የዜና ማሰራጫዎች፣ ድረገጾች፣ ብሎጎች፣ ፓልቶኮች፣ የማሕበራዊ መረብ መገናኛዎችና ሌሎችም  ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ የቆየው ጉዳይ ኤርትራ ውስጥ ይገኛሉ በተባሉ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች ላይ ሻቢያ ስለሚፈጽማቸው ወንጀሎችና አሻጥሮች እንዲሁም ግንቦት 7 ያለተደረገውን ተደረገ፤ ያልተፈጸመውን ተፈጸመ በማለት በኢትዮጵያዊያን ተስፋና ህልውና ላይ ሲያሾፍና ሲያላግጥ ለብዙ ዓመታት መኖሩ በተጨባጭ መጋለጡ ነው። በዚህም መሠረት አቶ ኤልያስ ክፍሌ ለበርካታ ዓመታት ባካበቱት  ዜናዎችን በከፍተኛ ስልት የማጣራትና ጥብቅ ሚስጥሮችን ጎልጉሎ የማውጣት ክህሎታቸው በመጠቀም በቅርቡ ከየመን ወደ ኢትዮጵያ ታፍነው የተወሰዱት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በሻቢያ ለወያኔ ተላልፈው የተሰጡ መሆናቸውን የሚያሳይ ልዩ ዘገባ አቅርበዋል። የዚህ በጥንቃቄ የተከናወነ ዘገባ መውጣት ግንቦት ሰባት ቆሞበት የነበረው መሬት እንዲከዳውና ሲከምረው የነበረው የውሸት ኩይሳ እንዲፈርስበት አድርጎበታል።

በመሠረቱ ሻቢያ ኢትዮጵያ ውስጥ ወያኔን ሊተካ የሚችል ጠንካራ ኢትዮጵያዊ ብሔረተኛ የሆነ ኃይል እንዳይቋምና እንዳያቆጠቁጥ አበክሮ እንደሚሰራ በተለያየ ጊዜ በአገር ወዳድ ወገኖችና ውስጥ አወቆች ሲገለጽ የነበረ ጉዳይ እንደሆነ ማንም የአገራችንን ሁኔታ የሚከታተል ዜጋ ይዘነጋዋል ተብሎ የሚገመት ጉዳይ አይደለም። ሻቢያ ከአደንቋሪ ልፍለፋ ባለፈ ሁኔታ ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ነገር ለመስራት ቢፈልግም አንኳ ባህርዩና ብሔራዊ ጥቅሙ አይፈቅድለትም። ሻቢያ ከወያኔ የተሻለ የኢትዮጵያዊያንን አንድነት የማያሰለስልና የሚያጠፋ ኃይል ከየት ሊያመጣ ይችላል? በተለይም ሻቢያ የኢትዮጵያዊያን የግዛት አንድነትና ወደቦቿን ጭምር የሚያስከብርና ሉዓላዊነቷን የሚያረጋግጥ ማንኛውም ኃይል ኢትዮጵያ ውስጥ ሥልጣን ላይ እንዳይወጣ ከወያኔ ባልተናነሰ መልኩ ተግቶ ለሊትና ቀን ይሰራል። ለምን ብሎ ዶሮውን በቆቅ ይለውጣል? ወያኔን የመሰለ ተባይ ኢትዮጵያ ውስጥ ስልጣን ላይ ሆኖ ቢቀጥልለት እንጅ ሌላ ኢትዮጵያዊ ብሔረተኛ ኃይል እንዲመጣ አይኑ እያየ አይፈቅድም።

ይህንን አገር ያወቀውንና ጸፀይ የሞቀውን ጉዳይ ግንቦት ሰባት በማደናገርና በማምታታት ሀቁ እንዳይታወቅ ለብዙ ዓመቶች ሸፍኖ በማቆየት የሕልም እንጀራ ሲቀልበን የቆየ ቢሆንም ሳይጋለጥ ተሸፍኖ የሚቆይ ነገር ባለመኖሩ በተለይ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ታፍነው ለወያኔ እንዲሰጡ ከተደረጉ ወዲህ “የሻቢያ ለኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ድጋፍ ይሰጣል” የሚባለው ቅጥፈት መሆኑ በማያሻማ ሁኔታ እንዲረጋገጥ አድርጓል።

አቶ ኤሊያስ ክፍሌ ኤርትራ ውስጥ የመስክ ጉብኝት አድርገው የነበረ መሆኑ የሚታወስና በርካታ መረጃ የሚያገኙበት መረብ እንዳላቸው ስለሚታወቅ ያቀረቡልን ልዩ ዘገባ ተአማኒነት ያለው መሆኑ አያጠራጥርም። ግንቦት 7 ለብዙ ዓመታት የትጥቅ ትግል አካሂዳለሁ እያለ አንዲት ቀበሌ ከወያኔ ነጻ ያላወጣ የአፍ ነጻ አውጭ መሆኑ ተግባሩና ምላሱ የሰማይና የምድር ያልህ የተራራቁ መሆናቸውን ለማሳየት የሚያስቸግር ነገር አይደለም። ስለሆነም ግንቦት ሰባት በሻቢያ ድጋፍና እርዳታ ወያኔን እጥላለሁ የሚለው ቅጥፈት እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል እንደሚባለው ተጋልጧል። በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ከወያኔ አፋኝ አገዝዝ ለመውጣት የሽቢያ እርዳታ ሳይስፈልጋቸው በራሳቸው መንገድ በመንቀሳቀስ ድል እንደሚቀዳጁ ሳይታለም የተፈታ ነው።