እ.ኤ.አ በ1984 የተከሰተው የኢትዮጵያ ታላቁ ረኃብ ሲታወስ፣


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

.. 2014 በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያ ረኃብ አለ፣ ሆኖም ግን የሌለ ለማስመሰል ስሙ የሚጠራው በሌሎች የመቀባቢያ፣ የመሸፋፈኛ፣ የማስመሰያ እና የማደናገሪያ ተቀጽላ ስሞች አማካይነት ነው፡፡ 

በኢትዮጵያ ረኃብ የሚያስደነግጠኝ ርዕሰ ጉዳይ ነው፡፡ እራሱን ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ እያለ የሚጠራው የማፊያ ቡድን እና አሁን በህይወት የሌለው መሪው መለስ ዜናዊ እ.ኤ.አ በ1991 ስልጣንን ከተቆናጠጡ ጀምሮ ላለፉት በርካታ ዓመታት በተደጋጋሚ በረኃብ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሊደበቁ የማይችሉትን ያፈጠጡ እና ያገጠጡ እውነታዎችን ፈልፍዬ በማውጣት የሸፍጥ እኩይ ምግባር አራማጆቹ ረኃብ እዳልተከሰተ በማስመሰል ለመደበቅ ሲሉ የተለያዩ ቅጥፈቶችን በመፈብረክ እና ለረኃቡ የተለያዩ የማደናገሪያ ስሞችን በመስጠት ሊያስተባብሉ ሲሞክሩ በተጨባጭ መረጃ ላይ በመመስረት እያጋለጥኩ በጣም ረዥም የሆኑ የትንታኔ ትችቶችን እያዘጋጀሁ ለዓለም አቀፉ እና በአገር ውስጥ ላለው ማህበረሰብ ሳቀርብ ቆይቻለሁ፡፡ በእርግጥ እ.ኤ.አ ከ1991 ጀምሮ በኢትዮጵያ ረኃብ በየዓመቱ ሲከሰት ቆይቷል፡፡ እነዚህ በስልጣን እርካብ ላይ ተፈናጥጠው የሚገኙት በቅጥፈት የተሞሉት አስመሳዮች ግን ረኃቡን አፋቸውን ሞልተው ረኃብ ብለው ደፍረው የመጥራት ወኔው የላቸውም፡፡ ይልቁን ለዚህ የማቅለያ እና የማለሳለሻ ማደናገሪያ ስም በመስጠት የዓለምን እና የሀገር ውስጥ ማህበረሰብ የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየስ እና ረኃብ በአገሪቱ ውስጥ ያልተከሰተ እና ፍጹም የሌለ አስመስለው ለማቅረብ ይሞክራሉ፡፡ ይህንንም የሸፍጥ ዓላማቸውን ለማሳካት ሲሉ ረኃብ የምትለዋን ቃል ከአንደበታቸው ፍቀው በማውጣት ከፍተኛ የምግብ ንጥረ ነገር እጥረት/extreme malnutrition፣ አስደንጋጭ የምግብ እጥረት/severe under-nutrition፣ አሳሳቢ የምግብ እጥረት/extreme food shortage፣ የምግብ እጥረት ቀውስ/catastrophic food shortages እና ሌላ ሌላም የአፈጮሌነት የማደናገሪያ ስሞችን በመስጠት የህዝብን የትኩረት አቅጣጫ ማስቀየስ አንዱ እና ዋናው ስልታቸው ሆኖ ቆይቷል፡፡ ረኃብ ግን ያው ረኃብ ሆኖ በኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ላይ በማናጠር ላይ ይገኛል፡፡ ሆኖም ግን ረኃብ የትኛውንም ዓይነት የማስመሰያ እና የማደናገሪያ ቀለም ቢቀባም ያው ረኃብ ሆኖ ዘልቋል! 

ምግብ  ለሰው እጅግ በጣም አስፈላጊው እና መሰረታዊ መብቱ ነው፡፡ ሁሉም የሰው ልጆች ከአምላክ የተሰጣቸው ምግብ የማግኘት መብት አላቸው፡፡ ከምግብ እና ውኃ ውጭ ህይወት የለም፣ እናም ምግብን እና ውኃን የሚቆጣጠር ማንኛውም አካል ቢሆን ህይወትን እራሱን ተቆጣጠረ ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከአንድ ተኩል ምዕተ ዓመት ጀምሮ ያለው ትልቁ ችግር በስልጣን ላይ የነበሩት እና ያሉት መንግስታት እና ገዥዎች የረኃብ ጉዳይ በተነሳ ቁጥር በጽናት ላይ የተመሰረተ፣ የማይለወጥ እና የማይናወጥ አንድ ዓይነት የድንቁርና ምክንያት ይሰጣሉ፡፡ ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ እ.ኤ.አ ከ1973 – 1974 በሰሜን ኢትዮጵያ ተከስቶ ስለነበረው ረኃብ ሽምጥጥ አድርገው በመካድ የማውቀው ነገር የለም፣ ረኃብ በአገሪቱ ውስጥ የለም የሚል ምላሽ ሰጥተው ነበር፡፡ እ.ኤ.አ ከ1984 – 1985 በኢትዮጵያ ተከስቶ ስለነበረው ረኃብ የወታደራዊው መንግስት ቁንጮ የነበሩት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ያንኑ የንጉሱን አባባል በተመሳሳይ ሁኔታ እንዳለ ደገሙት:: መለስ ዜናዊም ያንኑ ነገር እንደውዳሴ ማርያም ደገሙት…እንዲህ ነበር ያሉት፣ “በደቡብ ኢትዮጵያ ሰውነታቸው የቀጨጨ እና የተጎዳ ህጻናት ብቅ ማለታቸውን እስከአየን ድረስ ረኃብ ስለመኖሩ ያወቅነው ነገር አልነበረም፡፡“ ወይ ጉድ!  ጎበዝ ይገርማል እኮ! ኢትዮጵያ ስለረኃብ ያወቅነው ነገር የለም የሚሉ እና ረኃብን ለማስወገድ ምንም ነገር የማያደርጉ መንግስታት እና ገዥዎች የሚፈራረቁባት ምስኪን አገር!

እ.ኤ.አ በ2005 በኢትዮጵያ ተካሄደ በተባለው የይስሙላ አገር አቀፍ ምርጫ መለስ ዜናዊ በመቶዎች በሚቆጠሩ ባልታጠቁ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ትዕዛዝ በመስጠት እልቂት እንዲፈጸም ካደረገበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ትግል ውስጥ በመግባት ትግሉን እስከጀመርኩበት ድረስ ብዕሬን እና የኮምፒውተሬን የመክፈቻ ቁልፎች እጠቀም የነበረው መለስ ዜናዊ እና የእርሱ የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) ደቀመዝሙሮች ቢያንስ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ቀርበው ተጠያቂ እንዲሆኑ ካልሆነ ደግሞ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የህሊና ዳኝነት እንዲዳኙ ባልተቋረጠ መልኩ በተደጋገሚ በመጻፍ ግንዛቤ ለመስጠት ጥረት ማድረግ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ዓመት እስከ ዓመት ለረኃብ ሰለባ እየተጋለጠ ባለበት ሁኔታ እና እነርሱ ግን ለዚህ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ለመጣው እና ለማህበራዊ ውርደት የሚዳርግ ረኃብ የሚባል ክፋ መናጢ ነገር ትኩረት ባለመስጠት ቸል ማለት ቀጣይነት ላለው እና ለዚህ ታላቅ በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸም ወንጀል ጠንካራ ማረጋገጫ ነው፡፡

ስልጣንን በጠብመንጃ ኃይል የተቆናጠጡት መለስ እና ጓደኞቹ አዲስ አበባ እንደገቡ መለስ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የስኬታችን ዋናው ማረጋገጫ እና መለኪያው የኢትዮጵያ ህዝቦች በቀን ሶስት ጊዜ ምግብ መብላት መቻላቸው ነው ብሎ ነበር (ከዚህ ጋ ጫን በማድረግ ቪዲዮውን ይመልከቱ) ፡፡ ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ በ2011 መለስ እራስን ከፍ ከፍ በሚያደርግ እና የምጸት ስብዕናን በተላበሰ መልኩ እንዲህ ነበር ያለው፣ “እ.ኤ.አ እስከ  2015 ድረስ ምንም ዓይነት የውጭ እርዳታ ድጋፍ ሳንጠይቅ ትርፍ ምርት በማምረት እራሳችንን መመገብ የሚያስችለንን የአሰራር ዘዴ ቀይሰናል፡፡“

በ2014ቷ ኢትዮጵያ ለአብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን/ት በቀን ሶስት ጊዜ መብላት ላም አለኝ በሰማይ ወተቷን የማላይ ወይም ደግሞ እኔን ካገኘሽኝ አፍንጫሽን ላሽው ሆኖባቸዋል፡፡ ከአሁን በኋላ ሁለት ወራት ብቻ በቀሩት የፈረንጆች ዓመት 2015 ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የምግብ እርዳታ ካልተደረገላት በስተቀር እራሷን የመመገብ ዕድል የላትም፡፡ በእርግጥ  በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ አስከፊ የምግብ እጥረት ችግር ካለባቸው 125 አገሮች መካከል ኢትዮጵያ በ123ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ እ.ኤ.አ በ2014 ኦክስፋም የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት ያወጣው ዘገባ  እንዲህ ይላል፣ “በዓለም ላይ እጅግ የተትረፈረፈ፣ የተሟላ የምግብ ንጥረ ነገር ያለው፣ ጤናማ የሆነ እና ተመጣጣኝ ዋጋ ያለው ምግብ ካላቸው የዓለም አገሮች ውስጥ ኔዘርላንድ በአንደኛ ደረጃ ተራ ቁጥር ላይ የምትገኝ ስትሆን ቻድ ከኢትዮጵያ እና ከአንጎላ በኋላ የ125ኛ ደረጃን በመያዝ የመጨረሻ በመሆን ተቃራኒውን እና ሌላኛውን ጫፍ ይዛለች፡፡“

የወያኔ መሪዎች በድርቅ ምክንያት የሚከሰተውን የምግብ እጥረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማስወገድ ለበርካታ ዓመታት ቃል ሲገቡልን ኖረዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2009 የአደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት ሲሞን መቻሌ እንዲህ በማለት በእውነታ ላይ ያልተመሰረተ በኩራት የታጀበ ግግር አሰምተው ነበር፣ “ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ የእራሷን የምግብ ዋስትና ታረጋግጣለች፡፡“ የመለስ “ትርፍ ምርት የማምረት ዕቅድ” በዋናነት ዓላማ አድርጎ የተነሳው ለም የሆኑትን በሚሊዮን ሄክታር የሚቆጠሩ የእርሻ መሬቶችን ከአርሶ አደሩ በመንጠቅ የግብርና ምርቶችን በወሰዷቸው መሬቶች ላይ በማምረት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ትርፍ የማግበስበስ ዓላማን ያነገቡ ዓለም አቀፍ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ወይም መሬት ተቀራማቾች (land grabbers) እየተባሉ ለሚጠሩት የውጭ ኩባንያዎች እና ግለሰቦች በኪራይ/lease በመስጠት ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የእራሷ ዜጎች በረኃብ አለንጋ እየተገረፉ እና እየተሰቃዩ የሌሎች አገሮችን ዜጎች ትመግባለች፡፡ ሁሉም የመስኩ ባለሙያዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ መንግስታዊ ጠቅላይነትን በማስወገድ የመሬት በግል ይዞታ ስር መዋል ብቸኛው መንገድ መሆኑን እየመሰከሩ ባሉበት ሁኔታ ላይ በተቃራኒው ደግሞ መለስ እና ሌሎች የወያኔ ወሮበላዎች መሬት በግል መያዝ እንደማይኖርበት እና የግል የባለቤትነት መብት እንዳይኖር የማይለወጥ እና ግትር ሀሳብ ይዘው ሌት ከቀን ሲሰብኩ እና ሲከራከሩ ኖረዋል፡፡ እንዲያውም ግትርነታቸው እና እብሪተኝነታቸው ህልቆ መሳፍርት የሌለው መሆኑን በተጨባጭ ለማሳየት የመሬት የግል ባለቤትነት ፖሊሲ በመቃብሬ ላይ እስከማለት ደርሰዋል፡፡ እርግጥ ነው ጸሎታቸውን በሚሰማው አምላክ ፈቃድ እና በኢትዮጵያ ህዝብ ተጋድሎ በእነርሱ ከርሰ መቃብር ላይ የኢትዮጵያውያንን/ትን ሁሉ የምግብ ዋስትና የሚያረጋግጠው እና በነጻ ገበያ መርህ ላይ የተመሰረተው የመሬት የግል ባለቤትነት ፖሊሲ ያለምንም ጥርጥር የሚያብብ እና የሚፈካ ይሆናል፡፡ በዚህ የደናቁርት የተሳሳተ ፖሊሲ ምክንያት እ.ኤ.አ በ2010 የምግብ የዋጋ ግሽበት በአገሪቱ 47.4 በመቶ ላይ በመድረስ ተሰቅሎ ቀርቷል፡፡

ወያኔ እና ዓለም አቀፍ የድህነት ወትዋቾች እና አቃጣሪዎች የወያኔ ገዥ አካል ባለሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበ መሆኑን፣ ግዙፍ የሆነ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን እና በሽብርተኝነት ላይ እያራመደ ያለው አቋም እና እየሰጠው ያለው አመራር ከፍተኛ መሆኑን እያራገቡ እና እያጋነኑ በማቅረብ ኢትዮጵያ በስኬታማ የእድገት ጎዳና ላይ እየተጓዘች እንደሆነ የዓለም ህዝብ እምነት እንዲያድርበት ለማድረግ አቀነባብረው በማዘጋጀት የሚያነቡት ባዶ የልብወለድ ትረካ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብ ለበርካታ አስርት ዓመታት እስከ አሁንም ድረስ በማሰቃየት ላይ ስለሚገኘው ረኃብ ፍጹም ትንፍሽ ብለው አያውቁም፡፡ እነዚህ የምግብ ወትዋቾች እና አቃጣሪዎች አካፋን አካፋ ማለት ስለማይወዱ እንደዚሁም ሁሉ እየተከሰተ ያለውን አስከፊ ረኃብ የተለያዩ ቃላት እና ሀረጎችን በመፈብረክ እየለጠፉ የማታለል ስራ በመስራት የተካኑ መሰሪዎች ስለሆኑ ረኃብ በማለት ስሙን ለመጥራት አይፈልጉም፡፡ ረኃብ የምትለዋ ቃል ከሚያቀርቧቸው ዘገባዎች ውስጥ በፍጹም እንድትገባ አይደረግም፣ ፍጹም ክልክል ነው፡፡ አይነኬ! ይልቁንም አስከፊ የምግብ ንጥረ ነገር እጥረት፣ የምግብ እጥረት፣ አስከፊ የምግብ ዋስትና እጦት፣ አስከፊ የምግብ መመገብ ክፍተቶች እና በርካታ ሌሎች የማታለያ እና የማደናገሪያ ስያሜዎችን በሚይዙ ቃላት እና ሀረጎች ይተካሉ፡፡

እ.ኤ.አ ኦገስት 15/2014 የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት/United States Agency for International Development (USAID) ባወጣው ዘገባ እንደ ዳክዬ የሚጓዘውን፣ እንደ ዳክዬ የሚጮኸውን እና እንደ ዳክዬ የሚዋኘውን ትክክለኛ ወፍ የለም ዳክዬ አይደለም የሚል እምነት እንዲኖረን ይፈልጋል፡፡ ዩኤስ ኤአይዲ/USAID እንዲህ የሚል እርስ በእርሱ የሚጣረስ ዘገባ አቅርቧል፣ “ኢትዮጵያ ፈጣን የሆነ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ያለች ሀገር ብትሆንም…ከፍተኛ እና አስከፊ በሆነ የምግብ ዋስትና እጦት ችግር በተለይም በገጠሩ ህዝብ እና አነስተኛ ይዞታ ባላቸው አርሶ አደሮች ዘንድ ሲንጸባረቅ ይታያል፡፡ በግምት 44 በመቶ የሚሆኑ እድሚያቸው ከ5 ዓመት በታች ያሉ በኢትዮጵያ የሚገኙ ህጻናት ከፍተኛ በሆነ የምግብ ንጥረ ነገር እጥረት ወስጥ የሚገኙ ወይም ደግሞ የቀጨጩ ናቸው፡፡ እንደተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ድርጅት ዘገባ ከሆነ ይህ ከፍተኛ የሆነ የምግብ ንጥረ ነገር እጥረት እና የህጻናት መቀጨጭ በሀገሪቱ ላይ የረዥም ጊዜ አሉታዊ ተጽዕኖ በማስከተል በኢትዮጵያ መንግስት ላይ በግምት 16.5 በመቶ የሚሆነውን የሀገሪቱን ጠቅላላ ዓመታዊ ምርት/GDP እንዲያጣ ያስገድደዋል“ ይላል፡፡

ይኸ ቅጥአንባሩ የጠፋበት የቢሮክራሲ ውጣውረድ በእርግጠኝነት ምን ማለት ነው የፈለገው? በአብዛኛው በገጠሩ አካባቢ የሚኖረው ህዝብ ረኃብ መሰል ነገር ገጥሞታል ማለቱ ይሆን? ህጻናት፣ ከፍ ከፍ ያሉት እና ትናንሽ ልጆች እየተራቡ ነው ማለታቸው ይሆን? እኔ እንደዚህ ያለውን ዥዋዥዌ ጨዋታ ማየትም ሆነ መስማት ሆዴን ያመኛል! ዩኤስኤአይዲ/USAID እና ሌሎች ዓለም አቀፋዊ የድህነት ወትዋቾች እና የአቃጣሪዎች መረብ አባላት በኢትዮጵያ ስላለው ረኃብ ዘገባ የሸፍጥ አካሄድ እና የእነርሱን የድድብና ቃላት እና ሀረጎች ፍብረካ ጭዋታ የማናውቅ እና የማንገነዘብ ደደቦች እና ደንቆሮዎች እንደሆንን አድርገው ይቆጥራሉ፡፡ የማንገነዘብ ደንቆሮዎች እንዳልሆንን እና ምንም ዓይነት የድድብና ስብዕናዎች ወይም ምልክቶች የሌሉብን መሆናችንን ሊገነዘቡ ይገባል! (ነን እንዴ!?!? የሚገርም ነገር እኮ ነው ጎበዝ!)፡፡ እነርሱ የፈለገውን ዝባዝንኪ ይዘባርቁ እንጅ ይህ በፍጹም የእውነተኛ ኢትዮጵያውያን/ት መለያ ባህሪ አይደለም! “ጽጌረዳ እያልን የምንጠራውን ተክል የፈለገውን ዓይነት ስም ብንሰጠውም ያው ጽጌረዳ ጽጌረዳ መሽተቱን እና መሆኑን አይቀይረውም፡፡“ ሆኖም ግን ዩኤስኤአይዲ እና ሌሎቹ ዓለም አቀፍ የድህነት ወትዋቾች እና አቃጣሪዎች በኢትዮጵያ ያለውን ያፈጠጠ እና ያገጠጠ ረኃብ በማቃለል እና በመቀባባት እያለሳለሱ የተለያዩ ስሞች በመስጠት ከፍተኛ የሆነ የስነምግብ ንጥረ ነገር እጥረት፣ የምግብ ቀውስ፣ ጅኒ ቁልቋል… እያሉ ማንንም ያሞኘን መስሏቸው ቢቀባጥሩ ያታለሉ እና ያሞኙ እራሳቸውን እንጅ ማንንም እንዳልሆነ ሊገነዘቡ ይገባል፡፡

1984 ታላቁ የኢትዮጵያ ረሃብ፣ 

በአሁኑ ወቅት ለእኔ ተመራጩ እና ለህሊናዬ የማይኮሰኩሰው ትክክለኛው መንገድ እ.ኤ.አ በ1984 በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረውን ታላቁን ረኃብ ለማስታወስ 2014 በኢትዮጵያ በድብቅ ተይዞ ወገኖቻችንን እንደሰደድ እሳት በመለብለብ ላይ ያለውን ረኃብ ጭምር ማንሳት እና ማስታወስ እንዲሁም ማጋለጥ ነው፡፡ እ.ኤ.አ ኦክቶበር 1984 ቢቢሲ የተባለው ዓለም አቀፍ የዜና አውታር “ዓለምን ያስደመመው የኢትዮጵያ ረኃብ” በሚል ርዕስ እንዲህ የሚል ዘገባ አውጥቶ ነበር፡፡ “ያንን ረኃብ “አስደንጋጭ” ብቻ ብሎ ማለፍ እውነታውን ሙሉ ለሙሉ አሳንሶ የማየት እና የመካድ ዓይነት አካሄድ ነው፡፡ ይልቁንም ያ ረኃብ አስቀያሚ እና የሞራል ተቀባይነት የሌለው፣ እጅግ በጣም መጥፎ፣ በጣም አስደንጋጭ እና የሚያሸማቅቅ፣ አደገኛ እና ፋታ የማይሰጥ በሽታ፣ የሞራል ልዕልና የሌለው፣ በህዝብ ላይ የተጫነ ውርደት እና ለመናገር የሚዘገንን አስቸጋሪ ሁኔታ ነበር፡፡ የቢቢሲ ዘጋቢ ሚካኤል ቡርክ ረኃቡን “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸ ረኃብ” በማለት ገልጾታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የእርሱ የዘገባ ስራ በሀያኛው ክፍለ ዘመን የመጨረሻዎቹ ዓመታት አካባቢ ከቀረቡ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ዘገባዎች አንዱ ሆኖ ይቆጠራል፡፡“ ከ30 ዓመታት በፊት ተከስቶ አያሌ ህዝብ የጨረሰውን የዚያን የረኃብ የቪዲዮ ዘገባ በአሁኑ ጊዜ መመልከት ስብዕናን የሚፈታተን አደገኛ ሁኔታ ነው፡፡

እ.ኤ.አ በ1984 በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ደርሶ በነበረው የረሀብ አደጋ ምክንያት ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ወገኖቻችን አልቀዋል፡፡ ወደ 600 ሺ የሚሆኑ ወገኖቻችን ደግሞ ከፍላጎታቸው ውጭ በግዳጅ በወታደር ማጓጓዣ ትላልቅ መኪኖች እየተጫኑ ከነበሩበት ቀዬ እና የእርሻ ቦታዎች በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል ውስጥ ወደሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች እንዲጓጓዙ እና እንዲሰፍሩ ተደርገዋል፡፡ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች በማጓጓዝ ሂደቱ ወቅት እና በሰፈሩባቸው የተለያዩ የሰፈራ ቦታዎች ላይ ሞተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ወታደራዊው የደርግ ገዥ አካል የመንደር ምስረታ የሚል ፕሮግራም በመንደፍ ለአማጺ ኃይሎች ድጋፍ ይሰጣሉ ብሎ የሚጠረጥራቸውን መንደሮች እና አካባቢዎች የመንደር ምስረታ ፕሮግራሙን እንደጥሩ አጋጣሚ በመቁጠር ከቀያቸው በማፈናቀል ሰው አልባ ባዶ ቦታዎች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ ለዚያ ረኃብ የደርግ መንግስት የሰጠው ምላሽ ውጤቱ ሲገመገም እና ሲታይ ሊቋቋመው ያልቻለው እልቂትን አስከትሎ አልፏል፡፡

እ.ኤ.አ በ1987 ታይም የተባለው መጽሔት በዚያው ዓመት በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረውን  ረኃብ በማስመልከት በእርግጠኝነት በኢትዮጵያ ምን እየተካሄደ እንዳለ ጥያቄ በማቅረብ እንዲህ በማለት ጽሁፍ አስፍሮ ነበር፣ “ከሶስት ዓመታት በፊት [1984] በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረው ረኃብ በኢትዮጵያ ታላቅ የሆነ ታምራዊ የምጽዓት ዕልቂትን አምጥቶ አልፏል፡፡ ምዕራባውያን በቴሌቪዥን መስኮቶቻቸው ሞልተው የሚቀርቡላቸውን የሰዎች እሬሳዎች፣ በዝንብ የተወረሩ ሬሳዎችን ክምር፣ ያለወላጅ የቀሩ ያፈጠጡ እና ያገጠጡ የህጻናት የጣዕረ ሞት አጥንቶችን እና በአሰቃቂው ረኃብ ምክንያት የሚሰቀጥጡ የህጻናት ጩኸቶችን…በታላቅ ድንጋጤ ይሰሙ እና ይመለከቷቸው ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ በሌላ ድርቅ መካከል ቆማለች… በዓለም ባንክ ዘገባ መሰረት በዓለም ካሉ የመጨረሻዎቹ ደኃ አገሮች መካከል በመሆን አስቀያሚውን ቦታ በመያዝ እንደገና ለዳግም የረኃብ እልቂት ተዳርጋ በቋፍ ላይ ትገኛለች፡፡ 46 ሚሊዮን ከሚሆኑ ለረኃብ አደጋ ከተጋለጡት ዜጎች መካከል ቢያንስ 6 ሚሊዮን የሚሆኑት ዜጎች የረኃብ ሰለባ ሆነዋል፣ እናም ከሶስት ዓመታት በፊት የተጀመረውን እርዳታ የማቅረብ ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ ብቻ ህይወታቸውን መታደግ ይቻላል…ምግብ እና ገንዘብ ለማግኘት የሚደረገው የእርዳታ ጩኸት አንዴ ከተሰማ በኋላ አስመሳዮች እንደገና ለሚከሰተው ነገር ሁሉ ተጠያቂ እና ተወንጃይ እንደማይሆኑ አድርገው ይቆጥራሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ያለው ረኃብ በግልጽ ሙሉ በሙሉ በተፈጥሮ እርግማን ብቻ የመጣ ነው ወይስ ደግሞ ይህንን እየመጣ ያለውን የረኃብ እልቂት እያባባሰው እና እንዲመጣ እያደረገው ያለው ሰው-ሰራሽ ችግር ነው?“

እንደ መለስ ዜናዊ እና ወያኔ ደቀመዝሙሮቹ ባዶ ዲስኩር የረኃብ ፍጻሜ በኢትዮጵያ፣

ለበርካታ ዓመታት መለስ እና የወያኔ ደቀመዝሙሮቹ የምግብ ለስራ ፕሮግራም/Productive Safety Net Program (የበጀት ድጋፍ በሚል የውጭ እርዳታ ላይ የተንጠለጠለ) ረኃብን ለማስወገድ ታምራዊ መፍትሄ ነው ብለው ሲያስቡ ቆይተዋል፡፡ ያ ፕሮግራም ”በቤተሰብ ደረጃ የሀብት ውድመትን ይከላከላል፣ እናም በህብረተሰብ ደረጃ ለስራ የሚውሉ ምርታማ ሀብቶችን በመፍጠር ምግብን አስመልክቶ በውጭ እርዳታ እና ምጽዕዋት ላይ የሚኖርን የእርዳታ የጥገኝነት አዙሪት ፍጻሜ በማፋጠን ያስወግዳል” የሚል ግምት አለ፡፡

እ.ኤ.አ ኦክቶበር 2011 መለስ ለእርሱ ፓርቲ የእራስ መተማመን መንፈስን በተላበሰ ሁኔታ እንዲህ በማለት ተናገረ፣ “እ.ኤ.አ እስከ በ2015 ድረስ ምንም ዓይነት የውጭ እርዳታ ድጋፍ ሳንጠይቅ ትርፍ ምርት በማምረት እራሳችንን መመገብ የሚያስችለንን የአሰራር ዘዴ ቀይሰናል፡፡“ የመለስ “ትርፍ ምርት የማምረት ዕቅድ” በዋናነት ዓላማ ያደረገው ለም የሆኑትን በሚሊዮን ሄክታር የሚቆጠሩ የእርሻ መሬቶችን ከአርሶ አደሮች በመንጠቅ የግብርና ምርቶችን በወሰዷቸው መሬቶች ላይ በማምረት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ትርፍ የማግበስበስ ዓላማን ያነገቡ ዓለም አቀፍ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ወይም መሬት ተቀራማቾች (land grabbers) እየተባሉ ለሚጠሩት የውጭ ኩባንያዎች እና ግለሰቦች በኪራይ/lease በመስጠት ምርቶችን በማምረት የህንድ እና የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ዜጎችን ለመመገብ ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ ነበር፡፡ የወያኔ “የምግብ እርዳታ የጥገኝነት አዙሪት ፍጻሜ” ይፋ የሆነ የተጋነነ ድንፋታ እንግዲህ ይህንን ይመስላል፡፡

እውነታዎች በእራሳቸው ይናገራሉ፡፡ እርኃብን ለማጥፋት እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተባበሩት መንግስታት እና የዓለም ትልቁ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ድርጅት የሆነው እንደ የዓለም የምግብ ፕሮግም ድርጅት/World Food Program (WFP) ዘገባ እ.ኤ.አ በ2014 በትክክል 207 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን/ት የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ድርጅቱ በመግለጽ እና 6.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን/ት ማለትም ተማሪዎች፣ አርሶ አደሮች፣ ከኤች አይቪ ኤድስ ጋር የሚኖሩ ሰዎች፣ እናቶች እና ህጻናት፣ ስደተኞች እና ሌሎችም ለምግብ እና ለልዩ የምግብ ንጥረ ነገር እጥረት ተጋላጮች እንደሆኑ ግልጽ አድርጓል፡፡ እ.ኤ.አ በ2012 እንደዚሁ 3.76 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ፈላጊዎች እንደነበሩ፣ እ.ኤ.አ በ2011 ደግሞ ቁጥሩ 4.5 ሚሊዮን እንደነበር፣ እ.ኤ.አ በ2010 እና በ2009 ቁጥሩ 5 ሚሊዮን እንደነበር እና በ2008 ደግሞ 6 ሚሊዮን እንደነበር ይፋ ተደርጓል፡፡ እ.ኤ.አ በ2013 የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና የግብርና ድርጅት/Food and Agricultural Organization (FAO) ባወጣው ዘገባ መሰረት “34 ሚሊዮን ኢትዮያውያን/ት…40 በመቶ የሚሆነውን የህዝብ ድርሻ የያዙት በአስከፊ የረኃብ ቀውስ ውስጥ እንዳሉ ይቆጠራሉ“ ብሎ ነበር፡፡ “በአስከፊ ሁኔታ መራብ” ማለት ለረዥም ጊዜ ምግብ ሳይበሉ መቆየት ማለት ነው፡፡ ይኸ ማለት እ.ኤ.አ በ1984 ረኃብ እና ቸነፈር እያልን ስንጠራው የነበረው አልነበረምን?

አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት በረኃብ ያለቁ ወገኖቻችንን ማሰብ እና መዘከር፣

እ.ኤ.አ በ1984 በኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው ታላቁ የረኃብ አደጋ እና ከዚያም ወዲህ አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት ያለቁትን ወገኖች ለማስታወስ እና ለመዘከር በምግብ እጥረት፣ በረኃብ እና በቸነፈር ላይ ለበርካታ ዓመታት የጻፍኳቸውን ጥቂት ትችቶች በክለሳ መልክ አቀርባለሁ፡፡ ይህንን የማደርገው የህዝቡን ግንዛቤ ከፍ በማድረጉ እረገድ ላከናወንኳቸው በጣም ጥቂት ጥረቶች እራሴን ለማሞካሸት ወይም ደግሞ እውቅና ለመስጠት በማሰብ አይደለም፡፡ ይልቁንም ይህንን የማደርገው የሰብአዊ መብት ጥበቃ ጩኸቴን እንደማደርገው ሁሉ ለዚህም ተመሳሳይ ምክንያት ነው፡ ይህም ማለት በስልጣን ላይ ተፈናጥጠው ለሚገኙ እና ስልጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጭ ለሚጠቀሙ እውነት እውነቱን እስከ አፍንጫው ድረስ ለመንገር ነው፡፡

ለበርካታ ዓመታት አሁን በህይወት የሌለውን መለስ ዜናዊን እና የወያኔ ገዥ አካል ረኃብ እና ቸነፈርን አስመልክቶ በሚነሱ ጉዳዮች ላይ ለምን ዝምታን እንደሚመርጡ እና አስቸኳይ መፍትሄ እንደማይወስዱ ባለማቋረጥ ትችቶችን ስሰነዝር ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ2008 የመካድ (መዋሸት) ስልት በሚል ርዕስ ትችት አቅርቤ ነበር፡፡ በዚያ ትችቴ ላይ መለስ እና የወያኔ ደቀመዛሙርት ቡድን እንደ አንድ ወንጀል ፈጽመው በቁጥጥር ስር ውለው ሲያዙ እና ለህግ ሲቀርቡ ሙልጭ አድርገው ክህደት የሚፈጽሙ ወንጀለኞች እንደሚያሳዩት ሁሉ እነርሱም በዚያ መልኩ ሽምጥጥ አድርገው መካድን እንደ በጎ ነገር ይቆጥራሉ በማለት የመሞገቻ ጭብጤን አቅርቤ ነበር፡፡ መለስ በኢትዮጵያ ላይ በተከሰተው ረኃብ እውነታነት በተጋፈጠ ጊዜ ይሰጥ የነበረው መልስ እንዲህ የሚል ነበር፣ “የምን ረኃብ?“ እ.ኤ.አ ኦግስት 7/2008 ታይም ከተባለው መጽሔት ጋር ቃለመጠይቅ በተደረገለት ጊዜ መለስ ሙልጭ አድርጎ በመካድ በኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ዓይነት ረኃብ እንደሌለ አድርጎ እንዲህ የሚል ምላሽ ሰጥቶ ነበር፣ “ረኃብ በኢትዮጵያ በአስከፊ ሁኔታ ለብዙ ጊዜ ሲከሰት ቆይቷል፣ እንደዚህ ያሉ አደጋን የሚያስከትሉ ነገሮች አይከሰቱም የሚል አስተሳሰብ ካለ ያ የለየት ድድብና ነው፡፡ በእኛ እይታ እና ሁኔታ ግን ረኃብ የሚባል ነገር አልተከሰተም…የአስቸኳይ ጊዜ ብቻ ነው… ረኃብ በፍጹም የለም፡፡“ (በአንድ ዓይነት ስም በፊልም ላይ ገጸባህሪ ሆኖ ሲሰራ የነበረው ፎረስት ጉምፕ የተባለ የፊልም ተዋንያን እንዲህ ብሎ ተናግሮ ነበር፣ “ደደብነት ደደብ እንደሚሰራው ነው፡፡“)

የመለስ ምክትል የነበረው አዲሱ ለገሰ እንዲህ የሚል ተደጋጋሚ የመከላከያ ስሞታ ያቀርብ ነበር፣ “በኢትዮጵያ ውስጥ የምግብ እጥረት እንዳለ አድርገው እያጋነኑ የሚያቀርቡ እና የሚቀርቡት አሀዛችም የተጋነኑ ናቸው እያሉ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት በማብጠልጠል ለማሳነስ የሚጥሩት ሁሉ የእራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት የሚቋምጡ ሰዎች ናቸው፡፡“ በአንድ ወቅት ምትኩ ካሳ የተባለው የመለስ ዜናዊ “የግብርና እና የገጠር ልማት ሚኒስትር” የነበረው ተመሳሳይ የሆነ ዓላማን ያነገበ አስተሳሰብን በማራመድ እንዲህ ብሎ ነበር፣ “በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ረኃብ እና ቸነፈር የሚባል ነገር የለም…ረኃብ አለ የሚለው አሰተሳሰብ መሰረተቢስ ነው፣ በአገሪቱ በመሬት ላይ ካለው ተጨባጫ እውነታ ጋር ፍጹም በሆነ መልኩ የሚጻረር ነው፡፡ ውንጀላው በመረጃ የተደገፈ አይደለም“ በማለት ነበር የሸመጠጠው፡፡

እ.ኤ.አ ኦገስት 22/2012 መለስ፣ ፔተር ጊል ከሚባል ጋዜጠኛ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ በደቡብ ኢትዮጵያ ረኃብ ተንሰራፍቷል የሚለው አባባል መሰረተቢስ ነው በማለት እንዲህ ብሎ ተናግሮ ነበር፣ “ያ በእኛ በኩል ውድቀት ነበር፣ በእጃችን ላይ አስቸኳይ ነገር ያለ መሆኑን ለመገንዘብ ዘግይተን ነበር፡፡ በአንዳንድ የተወሰኑ አካባቢዎች የህጻናት አካላት ገርጥተው እና አጥንቶቻቸው ገጥጠው እስከሚወጡ ድረስ በአካባቢው የረኃብ ቀውስ እየተስፋፋ ለመሆኑ አናውቅም ነበር፡፡“ ለመለስ የረኃብ መከሰት ማረጋገጫው “አካላቸው የገረጣ እና አጥንቶቻቸው ያገጠጡ ህጻናትን ማየት ነውን፡፡ ማንኛውም በአስከፊ ሁኔታ ላይ ያለ ሁሉ “የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ” ነው፡፡ ሁሉም ስለረኃብ የሚደረግ ዲስኩር ሁሉ የውጭ ሜዲያዎች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በእራሳቸው ምናብ እየፈጠሩ በሀሰት የሚያቀርቧቸው ዘገባዎች ናቸው፡፡

እ.ኤ.አ ኖቬምበር 2009 ረኃብ እና አደገኛው አውሬ በኢትዮጵያ“ በሚል ርዕስ ትችት ጽፌ አቅርቤ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ባለፉት ግማሽ ምዕተ ዓመታት በተከታታይ በስልጣን ላይ የቆዩት መንግስታት እና ገዥዎች በኢትዮጵያ ላይ በተለያዩ ጊዚያት ሲከሰት የቆየው ረኃብ በእራሳቸው በገዥዎች የአስተዳደር ብልሹነት እና ጎደሎ ፖሊሲዎች አማካይነት መሆኑ ቀርቶ ረኃብ መነሻው መለኮታዊ ኃይል እና “የእግዚያአብሄር ቁጣ” ነው እያሉ በውጫዊ ኃይል ለምን ያሳብቡ እንደነበረ እና አሁንም በማሳበብ ላይ እንደሚገኙ የሚገርመኝ እና የሚያሳዝነኝ እስከ አሁንም ድረስ እንቆቅልሽ ሆኖ የቀጠለ ጉዳይ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በስልጣን ላይ ያለው የወያኔው ገዥ አካልም እንደቀድሞዎቹ ገዥዎች ሁሉ ደካማ እና ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ፣ የድርቅ ሁኔታዎች፣ የደን ውድመት እና የአፈር መሸርሸር፣ የግጦሽ መሬቶች ከመጠን በላይ መጋጥ እና በሌሎች ተፈጥሯዊ ምክንያቶች የሚመጡ “አስከፊ የምግብ ንጥረ ነገር እጥረት”፣ እና የከፋ “የምግብ እጥረት” እያለ የእራሱን የተበላሹ፣ ሊቀየሩ እና ሊሻሻሉ ባልቻሉ የበከቱ ፖሎሲዎቹ እና ስትራቴጅዎች ምክንያት መሆኑ ቀርቶ በውጫዊ ኃይል በማላከክ የባጥ የቆጡን በመዘባረቅ ላይ ይገኛል፡፡ በኩራት ትከሻቸውን እየነፉ “የችግሩ መንስዔ እኛ አይደለንም፡፡ ይኸ የእግዚአብሄር ስራ ነው! እግዚአብሄር ዝናብ ማዝነቡን እረስቶታል“ በማለት ይሳለቃሉ፡፡

እ.ኤ.አ ኤፕሪል 2010 በኢትዮጵያ ኮሽታ ሳያሰማ እየተሳበ የመጣው ረኃብ በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችቴ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚከሰቱትን ረኃቦች እና የብዙሀን ዜጎች የምግብ እህል እጥረቶችን አስከፊ እውነታ በመደበቅ እና የተለያዩ ስያሜዎችን በመስጠት ታማኝነታቸውን ባጎደሉት የዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ቢሮክራቶች እና ባለስልጣኖች ላይ ጠንካራ የሆነ ትችት አቅርቤ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ እና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ያሉ ህዝቦች ምንም ዓይነት ምግብ ባለማግኘታቸው ወይም ደግሞ በጣም ጥቂት ብቻ ምግብ በማግኘት እንዲሞቱ መደረጋቸው እነዚህ ልብየለሽ የዓለም አቀፍ ድህነት ወትዋቾች እና አቃጣሪዎች የረኃቡን እውነታ ከህዝብ ለመደበቅ በሚፈርኳቸው እንቶ ፈንቶ ቃላት እና ሀረጎች አማካይነት ነው፡፡ ዓለም አቀፍ የድህነት ወትዋቾች እና አቃጣሪዎች ስለምግብ ዋስትና እጦት፣ የምግብ እጥረት፣ በምግብ እራስን አለመቻል፣ የምግብ መከልከል፣ አስከፊ የምግብ እጥረት፣ የከፋ የምግብ ንጥረ ነገር እጥረት፣ ቋሚ የምግብ ንጥረ ነገር እጥረት እና የመሳሰሉትን ቃላት እና ሀረጎች በመፈብረክ ረኃብ የምትለዋን ቃል ለመደበቅ ያለ የሌለ ፍሬከርስኪ ነገሮችን የሚቀባጥሩትን ከስሻቸዋለሁ፡፡ አካፋን አካፋ ብለው መጥራት ይጠበቅባቸዋል!

የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት/USAID የፈጠረው የርኃብ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት ኔትዎርክ/Famine Early Warning Systems Network (FEWSNET) እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች በረኃብ የሚጠቁትን ሰዎች ለመግለጽ የተለያዩ አሰልቺ የሆኑ ስያሜዎችን ይፈበርካሉ፡፡ እንደ FEWSNET አቀራረብ ምግብን በሚመለከት ብዙ ሰዎች የሚገለጹባቸው ስያሜዎች አሉ፣ እነርሱም የምግብ ዋስትና የተረጋገጠላቸው፣ በከፊል የምግብ ዋስትና ያልተረጋገጠላቸው፣ ከፍተኛ የሆነ የምግብ ዋስት እጦት፣ የከፋ የምግብ ዋስትና እጦት፣ እና የረኃብ ሰለባ የሆኑ በሚል የተለያዩ ስያሜዎች ይሰጡ ነበር፡፡ እነዚህ ቃላት እና ሀረጎች ወደ ተራ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ሲተረጎሙ እና እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ተግባራዊ ሲደረጉ እነዚህ ትርጉመቢስ የአመዳደብ ክፍሎች በቀን አንድ ጊዜ ብቻ የሚበላውን በአጠቃላይ የምግብ ዋስትና ያለው ብለው ሲመድቡት በየሁለት ቀኑ የሚበላውን ደግሞ በከፊል የምግብ ዋስትና ያለው በማለት ይመድበዋል፡፡

በሶስት ቀናት ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ የሚበላውን ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የምግብ ዋስትና እጦት ውስጥ ያለ በማለት ይመድበዋል፡፡ በጣም አስከፊ የምግብ ዋስትና እጦት ደግሞ በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ የሚበላ ነው፡፡ ሆኖም ግን ምንም ዓይነት ምግብ የማያገኙት የርኃብ ሰለባ በመሆን የሞት ሰለባ ይሆናሉ፡፡ የ“ሳይንስ” የስራ ውጤት በማስመሰል ለማታለያነት የተቀነባበረ የለየለት እብደት!

እ.ኤ.አ ማርች 2011 የዩኤስ የአፍሪካ ፖሊሲ የሞራል ልዕልና ዝቅጠት በሚል ርዕስ አቅርቤው በነበረው ትችት የወያኔ ገዥ አካል በምግብ ለስራ ከውጭ በሚሰጠው እርዳታ፣  ከብዙ ሀገሮች በገፍ በሚገኝ በድር ላይ እና እራሱ በሚፈልገው መልኩ እንዲጠቀምበት የሚተውለት (ሆኖም ግን የወያኔው አገዛዝ እርዳታውን በማታለል ኃላፊነት ባለው መልኩ የሚጠቀምበት በማስመሰል) በማያቋርጥ ሁኔታ በሚገኘው የሰብአዊ እርዳታ ላይ በከፍተኛ ደረጃ ጥገኛ እንደሆነ መሰረታዊ የሆነ የሙግት ጭብጤን አቅርቤ ነበር፡፡ ለምንድን ነው ለጋሽ እና አበዳሪ ድርጅቶች የወያኔውን ገዥ አካል ያለምንም የቁጥጥር ሰንሰለት ኢኮኖሚውን እንደፈለገው እንዲመዘብረው እና አውዳሚ የሆነ የሙስና ቅሌት እየሰራ ዝም ብለው የሚመለከቱት? እውነታው በተጨባጭ ሲታይ ግን ላለፉት ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የወያኔ ገዥ አካል የመለመኛ አኩፋዳውን ይዞ ያለምንም ተጠያቂነት ከለጋሽ እና አበዳሪ ድርጅቶች የምግብ እርዳታ በመለመን በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን/ት ይመግብ ስለነበር ነው፡፡ ስለሆነም ገዥው አካል ስለህዝቡ ዕጣ ፈንታ ፍጹም ደንታ አልነበረውም፡፡

እ.ኤ.አ ጁላይ 2011 የምጽአት ቀን አሁን ወይስ 40 ዓመታት በኋላ? በሚል ርዕስ ትችት አቅቤ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ2050 ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር እንደ ሀገር መኖር አለመኖሯን ከጥያቄ ምልክት ውስጥ በማስገባት ቀደም ሲል የነበረኝን እና አሁንም ድረስ ያለኝን ስጋት አቅርቤ ነበር፡፡ የክርክር ጭብጤን በማጠናከር ኢትዮጵያ እራሷን የቻለች ሀገር ሆና እ.ኤ.አ በ2050 ከጦርነት፣ ከበሽታ፣ ከተላላፊ ወረርሽኝ በሽታ እና ከረኃብ ነጻ ሆና ስለመኖር እና አለመኖሯ እንዲሁም በምዕናባዊ የውሸት ባለሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት ስሌት ወይም ተራ ማጭበርበር ሳይኖር በምርጫ 99.6 በመቶ የድምጽ ውጤት አግኝቸ ድል ተጎናጸፍኩ ሳይባል የሚኖርባት መሆን አለመሆኗን የሚዳስስ የክርክር ጭብጥ አቅርቤ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የእድገት ሁኔታ የሚወሰነው ትንሽ ከፍ ብሎ የሚታየውን በሶስት በመቶ እያደገ ያለውን ችግር ከመፍታት ላይ ነው፡፡ በሌላ አባባል በአሁኑ ጊዜ እና በቀጣዮቹ ዓመታት ከፍተኛ የህዝብ ብዛት በኢትዮጵያ አንዱ እና ዋነኛው ብቸኛ አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኖ ቀርቧል፡፡

እ.ኤ.አ በ2011 የዩኤስ የህዝብ ቆጠራ ቢሮ የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር እ.ኤ.አ በ2050 ከሶስት ጊዜ በላይ እጥፍ በመሆን 278 ሚሊዮን ይሆናል በማለት አስደንጋጭ የሆነ ትንበያ አስቀምጧል፡፡ የአትዮጵያ የምግብ ዋስትና እጦት ከከፍተኛው ደረጃ ላይ በመድረስ አስከፊ ገጽታን በመላበስ አስደንጋጩን የማልተስ የህዝብ ብዛት እልቂት ህልዮት (በሽታ፣ ረኃብ፣ ጦርነት፣ ወዘተ የህዝቡን ብዛት በአገሪቱ ከሚቀርበው የምግብ መጠን ጋር የማስተካከል) እንዲታሰብ ያደርገዋል፡፡ የወያኔ አገዛዝ እንደ እነዚህ ያሉ አሰቃቂ እልቂቶችን ለመከላከል የሚያስችል ብሄራዊ የቤተሰብ ምጣኔ ዕቅድ ፕሮግራም ፖሊሲ በማውጣት በትክክል ወደ ተግባር መለወጥ ተስኖታል፡፡ ሊደበቅ የማይችለው እውነታ ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት በየዓመቱ በ3 በመቶ እድገት በማስመዝገብ ላይ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ከ90 ሚሊዮን በላይ የሚሆነውን ህዝብ በበቂ ሁኔታ መመገብ፣ ማልበስ እና መጠለያ ማቅረብ ካልቻለች በ35 ዓመታት ሂደት ውስጥ ማለትም እ.ኤ.አ በ2050 ኢትዮጵያ በአምላክ ታምር አረንጓዴ መሬት አግኝታ 278 ሚሊዮን የሚሆነውን ህዝቧን መመገብ ትችል ይሆን? እጅግ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ እኮ ነው ጎበዝ! ምን ፍቱን መፍትሄ አለ?!

እ.ኤ.አ ኦገስት 8/2011 መለስ ዜናዊ እና ረኃብን በመሳሪያነት መጠቀም“ በሚል ርዕስ መለስ እና የወያኔ ወሮበላ አመራሮች በስልጣን ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው ለመቆየት በሚል እኩይ እሳቤ እርዳታን የፖለቲካ እና ለወታደራዊ መሳሪያ ግዥ እያዋሉት እንደሆነ ተጨባጭ የሆነ የክርክር ጭብጤን አቅርቤ ነበር፡፡ የክርክር ጭብጤን በመቀጠል ረኃብ ያገጠጡ የህጻናት አጥንቶችን እና የመጨረሻ እስትንፋሻቸውን ለማድረግ በጣዕረሞት አፋፍ ላይ ያሉትን ህጻናት እና በዚያ በሚያቃጥል የበረሀ ሙቀት ምንም ማድረግ ሳይችሉ ግን በጣዕረሞት ላይ ያሉትን ህጻናት በተስፋ መቁረጥ ሁኔታ አፍጥጠው የሚያዩ እናቶች ብቻ ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም ረኃብ የወታደራዊ እና የፖለቲካ መሳሪያም ነው፡፡ መለስ እና ህወሀት በደቡብ እና በደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍሎች “የአማጺያን አካባቢዎች” ያሏቸውን አካባዎች መንግስቱ በጊዜው በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የአማጺያን ቦታዎች ብሎ በዚያ አካባቢ ያሉ ህዝቦች የምግብ እርዳታ እንዳያገኙ አድርገዋል፡፡ ይኸ እንግዲህ መለስ ከመንግስቱ የተማረው ስትራቴጂያዊ ትምህርት ነው፡፡ ረኃብ አንድን ተቃዋሚ ቡድን ለማጥቃት እንደ ስልት እና ስትራቴጅ ሆኖ በመሳሪያነት ያገለግላል፡፡

እ.ኤ.አ ኦገስት 15/2011 ተቃዋሚዎችን ማስራብ ሰላማዊ ሰዎችን መመገብ በሚል ርዕስ ባወጣሁት ትችቴ ለተግባራዊ ምላሽ ጥሪ አቅርቤ ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን/ት ምዕራባውያን ለጋሽ እና አበዳሪ ድርጅቶች ለወንጀለኛው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ እና ህወሀት በቀጣይነት እየሰጡት ያለውን እርዳታ በማቆም “የህወሀት ጨካኝ አውሬዎችን ማስራብ የኢትዮጵያን ህዝብ መመገብ” በሚል መፈክር ስር ተሰባስበው ተቃውሟቸውን እንዲያሰሙ የሚያውጅ ነበር፡፡ ጣቶቹን በተራቡ ህጻናት የጎድን አጥንቶች ላይ እየፋቀ እና እየቆፈረ በስልጣን እርካብ ላይ ተፈናጥጦ ለመቆየት ለሚጣጣር አምባገነን ገዥ አካል ከእንግዲህ ወዲያ እርዳታ መስጠት ይቁም፡፡ ህዝቦችን ለሚያሰቃዩ እና የሰብአዊ መብቶችን ለሚደፈጥጡ አምባገነኖች ከዚህ በኋላ እርዳታ መስጠት ይቁም፡፡ ለምርጫ ድምጽ ዘራፊዎች የሚሰጠው እርዳታ ይቁም፡፡ ደጋፊዎቻቸውን ለመመገብ እጆቻቸውን ለሚያነሱ እና ተቃዋሚዎቻቸውን ለማስራብ እጆቻቸውን በመመለስ ለመበቀል እና ወገኖቻችንን በረኃብ ለመግደል ለሚተጉ አምባገነኖች የሚሰጠው እርዳታ ይቁም፡፡ ስለሆነም በተባበረ ድምጽ በመሰባሰብ በአንድነት በመቆም ምዕራባውያንን – አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ የአውሮፓ ህብረት፣ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት፣ የዓለም ባንክ እና ሌሎችም ላልተጠቀሱት እርዳታ እና አበዳሪ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ስርዓት ላይ አብጠው የሚገኙትን የወያኔ ጨካኝ አውሬዎች በማስራብ የተራበውን የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲመግቡ ድምጻችንን ከፍ አድርገን እንጩህ የሚል ነው፡፡

እ.ኤ.አ ኦገስት 22/2011 ኢትዮጵያውያን/ ለምንድን ነው 2011 ለዳግም ረኃብ የሚዳረጉት? በሚል ርዕስ ትችት አቅርቤ ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን/ት በ2011 (እና በ2014ም እንደዚሁ) ለምን እየተራቡ እንዳሉ 10 ምክንያቶችን ዘርዝሬ አቅርቤ ነበር፡፡ ምክንያቶቹም፡ 1ኛ) በኢትዮጵያ ረኃብ የሰብአዊ እልቂት ብቻ አይደለም፣ ይልቁንም በኢትዮጵያ ረኃብ ጠንካራ የሆነ የፖለቲካ እና ወታደራዊ መሳሪያ ነው፡፡ 2ኛ) ረኃብ በኢትዮጵያ ተደጋግሞ የሚከሰት እውነታ ነው፣ ምክንያቱም ያች ሀገር ማቋረጫ ለሌላቸው ለበርካታ አምባገነናዊ ዘመናት አዙሪት ውሰጥ ገብታ በመዳከር ላይ የምትገኝ ስለሆነ ነው፡፡ 3ኛ) ረኃብ በኢትዮጵያ ዓመታዊ ቀውስ እየሆነ ነው፣ ምክንያቱም የህወሀት አምባገነኖች የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ በአንድ ወይም በሚሊዮኖች እንዳለ ቢረግፍ እና ቢያልቅ ደንታቸው አይደለም፡፡ 4ኛ) ረኃብ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ችግር አንዱ አካል ነው፣ ምክንያቱም መንግስት ሁሉንም መሬት እራሱ ጠቅልሎ ይዟል፡፡ 5ኛ) ረኃብ አሁንም ቢሆን በኢትዮጵያ ይቀጥላል፣ ምክንያቱም በአገሪቱ ውስጥ ግዙፍ የሆነ የሰብአዊ መብት ረገጣ ተንሰራፍቶ ይገኛልና፡፡ 6ኛ)ረኃብ አሁንም ቢሆን በኢትዮጵያ ይቀጥላል፣ ምክንያቱም የመለስ ዜናዊ የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያ የሚከሰተው ረኃብ ድብቅ ሆኖ በድብቅ በሚስጥር በመያዝ ስኬታማ ሆኗልና፡፡ 7ኛ) ረኃብ አሁንም ቢሆን በኢትዮጵያ ይቀጥላል፣ መክንያቱም “የዝምታ ዱለታ” ተንሰራፍቷል፣ ወይም ደግሞ በምዕራቡ ዓለም እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች፣ በወኔቢስ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ደንታቢስ ዓለም አቀፍ የፕሬስ ድርጅቶች “የአላየሁም አልሰማሁም ዓይነት ዱለታ” ተንሰራፍቶ ይገኛልና፡፡ 8ኛ) ረኃብ አሁንም ቢሆን በኢትዮጵያ ይቀጥላል፣ ምክንያቱም ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ያህል በስልጣን እርካብ ላይ ተፈናጥጦ የሚገኘው ገዥ አካል ውጤታማ የሆነ የቤተሰብ ዕቅድ ፖሊሲ ነድፎ ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያዎችን አዘጋጅቶ በስራ ላይ ማዋል ስለተሳነው ነው፡፡ 9ኛ) በኢትዮጵያ የሚከሰት ረኃብ ለወያኔ ጥሩ የቢዝነስ ማስገኛ ዘዴ ነው፡፡ 10ኛ) “የተራበ ወንድ/ሴት የተበሳጨ ወንድ/ሴት” የመሆኑ እውነታነት ቅቡል መሆኑ ነው፡፡

እ.ኤ.አ ኦገስት 29/2011 የተራቡ ኢትዮያውያንን/ትን ለመታደግ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ምን ማድረግ ይጠበቅበታል? በሚል ርዕስ ትችት አቅርቤ ነበር፡፡ የተራቡ ኢትዮጵያውያንን/ትን ለመታደግ 10 የመፍትሄ ምክንያታዊ የሆኑ ሀሳቦችን ሰንዝሬ ነበር፡፡ እነርሱም፣ 1ኛ) ለምዕራቡ ዓለም የእርዳታ ጥገኛ ባለመሆን በኢትዮጵያ ላይ ዘቅጦ የሚገኘውን የምዕራቡን ዓለም የሞራል ልዕልና ከኢትዮጵያ ከባቢ አየር ላይ እንዲነሳ ማድረግ፣ 2ኛ) ምዕራቡ ዓለም ለኢትዮጵያ  ከሚሰጠው እርዳታ ጋር የሰብአዊነት እና የሰብአዊ መብት ጥበቃ ጉዳዮች እንዲካተቱበት ማድረግ፣ 3ኛ) ለኢትዮጵያ ህዝብ የተረጋጋ እና ጤናማ ህይወት መጎልበት እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ጥረት ማድረግ የሚጠበቅባቸው ሲሆን የኃይል ጡንቻ ባለቤቶችን እና አምባገነኖችን የሚያግዝ እርዳታ መስጠት ማቆም ይኖርባቸዋል፣ 4ኛ) ከምዕራቡ ዓለም ግብር ከፋይ የተሰበሰበውን ገንዘብ ለአምባገነኖች በመስጠት ለሌለ ለግል ጥቅማቸው እና ህዝቡን ለመጨቆኛ እኩይ ምግባር እንዳያውሉት ማድረግ፣ 5ኛ) እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ትብብራቸውን ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር እንጅ ከመለስ ዜናዊ የህወሀት አምባገነናዊ ቡድን ጋር መሆን የለበትም፣ 6ኛ) በአገር ውስጥ ያሉ ገንዘብ ከፋዮች ከውጭ በእርዳታ ስም የመጣውን ገንዘብ ለተረጅው ወገን በሚያከፋፍሉበት ጊዜ ተጠያቂነት እንዲኖርባቸው ማድረግ፣ 7ኛ) የውጭ እርዳታ ለኢትዮጵያ ሲቀርብ በኢትዮጵያ አጠቃላይ የሆነ የቤተሰብ ዕቅድ ፕሮግራምን እና አፈጻጸምን እንደ ቅድመ ሁኔታ በማካተት እንዲሰጥ ማድረግ፣ 8ኛ) የተራቡ የኢትዮጵያ ህዝቦችን ለመርዳት የኢትዮጵያ ሴቶችን ማገዝ አስፈላጊ ነው፣ 9ኛ) የተራቡ የኢትዮጵያ ህዝቦችን ለመርዳት የኢትዮጵያ ወጣቶችን ማገዝ አስፈላጊ ነው (70 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ እድሜው ከ35 ዓመት በታች ነው)፣ 10ኛ) የህወሀትን አረመኔ አውሬዎች በማስራብ የኢትዮጵያን የተራበ ህዝብ በመመገብ፡፡

እ.ኤ.አ ኦክቶበር 2012 ኢትዮጵያ፡ 2013 ረኃብ ቅድመ ማስጠንቀቂያ በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችቴ ላይ የማስጠንቀቂያ ደወል ደውዬ ነበር፡፡ ጥንቃቄ በተመላበት መልኩ መረጃዎችን በመልቀም፣ በመተንተንና ግኝቶችን ከተለያዩ ምንጮች ማለትም የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት መረብ/Famine Early Warning Systems Network (FEWSNET)፣ ኦክስፋም፣ የተባበሩት መንግስታት የምግብ ፕሮግራም ድርጅት፣ የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና የግብርና ድርጅት እና የተለያዩ ዘገባዎችን ከተለያዩ ድርጅቶች ማለትም የአዲሲቷ እንግሊዝ ውስብስብ ስርዓቶች ተቋም/New England Complex Systems Institute [NECSI]፣ (ከሀርቫርድ እና ኤም አይ ቲ ከተባሉት እውቅ የአካዳሚክ ተቋማት በአካባቢ ላይ የሚከሰቱ ለውጦች እንዴት አድርገው የፖለቲካ አለመረጋጋትን እና አመጽን እንደሚያስከትሉ የሚያጠኑ የባለሙያዎች ስብስብ) በማሰባሰብ የእራሴን ትንታኔ እና ማጠቃለይ ሰጥቻለሁ፡፡

እ.ኤ.አ 2013 ረኃብ ወይም “አሰቃቂ የምግብ ቀውስ” መከሰት የሚጀምርበት የመነሻ ዓመት ሊሆን እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ሰጥች ነበር፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ዓለም አቀፍ የድህነት ወትዋቾች እና አቃጣሪዎች እና የእነርሱ የቅጥፈት ሳይንሳዊ የምግብ እጦት ደረጃዎች አመዳደብን ለምሳሌም ያህል አስከፊ የምግብ ዋስትና እጦት፣ የተገደበ ሁኔታ፣ ቀውስ፣ ወዘተ  በማስመልከት የሚያቀርቡትን መሰረተቢስ አመዳደብ አጣጥዬ ክርክር አቅርቤበት ነበር፡፡

እ.ኤ.አ ሜይ 2012 የአፍሪካ የረኃብ ጨዋታ በካምፕ ዳቪድ” በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ሞጋች ትችት የምግብ እርዳታ በኢትዮጵያ ገዥ አካል የፖለቲካ መጠቀሚያ መሳሪያ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል ብዬ ነበር፡፡ ረኃብ ለህወሀት ገዥ አካል ደጋፊዎቹን የበለጠ ድጋፍ ለማስገኛ እና የፖለቲካ ተቀናቃኞቹን ደግሞ ለማዳከም እና ለመደቆስ ሌላ የማጥቂያ ምርጫ ሆኖ ቀርቦለታል የሚል የመከራከሪያ ጭብጥ አቅርቤ ነበር፡፡ መለስ እና ህወሀት የህዝቦችን ሆድ ባዶ በማድረግ ልቦቻቸውን በመስበር፣ አዕምሯቸውን እና ህሊናቸውን በመስለብ ለዕኩይ ዓላማቸው ስኬታማነት አጠንክረው በመስራት ውጤታማ ሆነዋል፡፡ ህወሀትን የሚቃወሙ ሁሉ የሰብአዊ፣ የምግብ እና ሌሎች እርዳታዎችን ብቻ አይደለም የሚከለከሉት ሆኖም ግን ከቦታቸው እና ከእርሻ ይዞታቸው በማፈናቀል፣ መሬት ባለመስጠት እና ያላቸውንም በመንጠቅ ወይም ደግሞ ያላቸውን መሬት መጠን በመቀነስ፣ የብድር ተጠቃሚ እንዳይሆኑ በመከልከል፣ ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር ወዘተ እንዳያገኙ በማድረግ የድንቁርና የበቀል እርምጃቸውን ይወስዳሉ፡፡ በምዕራብ ኢትዮጵያ የጋምቤላ ጉዳይ ሲነሳ ሁሉም ማህበረሰብ የነበረበትን ይዞታ እንዲለቅ በማድረግ እና በማፈናቀል ህዝቦች በቋሚነት ሰፍረው ከኖሩበት ቦታ በኃይል ሊነሱ አይችሉም የሚለውን ዓለም አቀፋዊ ስምምነት በመጣስ እና መብታቸውን በመደፍጠጥ ለም መሬታቸውን እና ይዞታቸውን ለህንድ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሽ ባለሀብት ነጋዴዎች ተሰጥቷል፡፡

እ.ኤ.አ ፌብሯሪ 21014 በኢትዮጵያ እየዳኸ በመምጣት ላይ የሚገኘውን ረኃብ በጨረፍታ” በሚል ርዕስ ትችት አቅርቤ ነበር፡፡ በዚያው ወር ኤን ቢሲ/NBC በምርመራ ዘገባው ኢትዮጵያ የዓለም የምግብ ቀውስ መገለጫ ፊት ናት ብሎ ነበር፡፡ በደቡብ ኢትዮጵያ ባለ በአንድ መንደር ውስጥ እናቶች ለምግብ እርዳታ በምግብ ንጥረ ነገር ከተጎዱ ህጻናት ጋር አብረው ተሰልፈዋል፡፡ ህጻኖቻቸውን ለመመገብ አቅም እንሷቸዋል እናም የዓለም አቀፍ የእርዳታ ሰጭ ድርጅቶችም እንደዚሁ፡፡ ሁለት ደካማ የመኸር ሰብል ስብሰባ ወቅቶች ካለፉ በኋላ የረኃብ ምልክት የሆነው የበርካታ ህጻናት ሆድ በመነፋት ህጻናቱ በመሰቃየት ላይ ናቸው፡፡ እንደዚሁም በእየለቱ በርካታ አዳዲስ ህጻናት እየታመሙ ነው…ከ10 ቀናት በፊት የምግብ ራሽን ሸቀጥ ተሰጥቷቸው ነበር… የመንግስት ክምችት ከብዙ ጊዜ በፊት አልቋል፣ እናም አሁን ደግሞ የተባበሩት መንግስታት የምግብ ክምችትም በመመናመን ላይ ይገኛል፡፡ (እ.ኤ.አ በ2008 መለስ ዜናዊ በደቡብ ኢትዮጵያ ስለተከሰተው ረኃብ ምንም የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ተናግሮ ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን በፌብሯሪ 2014 ረኃብ ስለመኖሩ የሚያውቁት ነገር የላቸውም፡፡ አጥንታቸው ያገጠጡ እና ፊታቸው የገረጣ እና የጠወለገ ህጻናት በየአውራ መንገዶች እና በገጠሮች ሲንከላወሱ ሲመለከቱ ብቻ ነው እነርሱ ረኃብ መኖሩን የሚያምኑት፡፡) ምንም የሚያውቀው ምንም የሚያደርገው ነገር የሌለው ገዥ አካል!

በቅርቡ ፕሬዚዳንት ኦባማ ሴፕቴምበር 23 የወያኔውን የልዑካን ቡድን አባላት በዋሽንግተን ዲ.ሲ በማግኘት የሰጧቸው መግለጫዎች የለየላቸው ውሸቶች መሆናቸውን በማስመልከት ጠንካራ የማስተባበያ ነጥቦችን አቅርቢያለሁ፡፡ ዓላማቸውን ለማሳካት ሲሉ ያደረጓቸው የሸፍጥ ንግግሮች እንደሚከተለው ቀርበዋል፣ “እንደ ኢትዮጵያ ባለች በአንድ ወቅት ዜጎቿን መመገብ ያልቻለች አገር በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሆነ እድገት እየተመለከትን ነው፡፡ አገሪቱ በአሁኑ ጊዜ የግብርና ምርት ውጤቶችን በገፍ በማምረት በአፍሪካ አህጉር የመሪነቱን ደረጃ መያዝ ብቻ ሳይሆን በቅርቡ የግብርና ምርት ውጤቶችን ወደ ውጭ አገር ወጭ በማድረግ በዓለም ገበያ ላይ መሰለፍ ብቻ ሳይሆን እንዲያውም በቅርቡ ኃይልንም በማምረት ለውጭ ገበያ ልታቀርብ ትችላለች ምክንያቱም የተሻለ የልማት እንቅስቃሴ እያደረገች ስለሆነ ነው“ ብለዋል ፕሬዚዳንት ኦባማ፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ ፍጹም የሆነ የሀሰት መረጃ የተሰጣቸው እና በዚያ ላይ መሰረት አድርገው የተሳሳተ መግለጫ የሰጡ እንደሆነ እምነት አለኝ፣ ምክንያቱም የዩናይት ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት/USAID እ.ኤ.አ ኦግስት 15/2014 ካወጣው ዘገባ ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጣረስ እና የሚቃረን በመሆኑ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅቱ ዩኤስኤአይዲ ባዘጋጀው ዘገባው ውሰጥ የሚከተለውን አስፍሮ ይገኛል፣ “ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ብትሆንም ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ከሚገኙ የመጨረሻ ደኃ አገሮች መካከል አንዷ ናት፡፡ በከፍተኛ ደረጃ ያሉ አስከፊ እና በጣም አስከፊ የምግብ ዋስትና እጦት በተለይም በገጠሩ አካባቢ እና ዝቅተኛ የመሬት ይዞታ ባላቸው አርሶ አደሮች ላይ ጎልቶ ይታያል፡፡“

የኢትዮጵያ ረኃብ ህወሀትሰራሽ ነው፣ 

እ.ኤ.አ 2011 ዎልፍጋንግ ፌንግለር የተባሉት የዓለም ባንክ ዋና የምጣኔ ሀብት ባለሙያ በአንድ የተረጋጋ ስሜት በነበረበት ወቅት ለአንድ ዓለም አቀፍ የባንክ ባለቤት እንዲህ የሚል ንግግር አሰምተው ነበር፣ “በአፍሪካ ቀንድ ለተከሰተው ረኃብ መነሻው በምግብ ላይ በዘፈቀደ እየናረ የመጣው የምግብ ዋጋ ግሽበት እና በተፈጥሮ እና በአካባቢያዊ ምክንያቶች በሚፈጠሩ ግጭቶች ነው፡፡ ይህ ቀውስ ሰው ሰራሽ ነው፡፡ ድርቆች ከብዙ ጊዜ ጀምሮ እና አሁንም እየተከሰቱ ነው፣ ሆኖም ግን ለዚያ ምክንያቱ አምባገነን መንግስታት ወደ ረኃብ የሚያመሩ መጥፎ ፖሊሲዎችን ማውጣታቸው ነው፡፡“

በሌላ አባባል በኢትዮጵያ ስለሚከሰተው የረኃብ ችግር መነሻው ድርቅ ወይም ሌላ አካባቢያዊ ምክንያቶች ሳይሆኑ መጥፎ እና ደካማ አስተዳደራዊ ችግሮች ናቸው፡፡ ላለፉት 23 ዓመታት ህወሀት አገሪቱን በተሳሳተ መንገድ አስተዳድሯል፣ መርቷል እናም የኢትዮጵያን ህዝብ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ የማደግ እድሎች አዛብቷል፣ አምክኗል፡፡ የኦክስፋም ዓለም አቀፍ ዳይሬክተር የሆኑት ፔኒ ላውረንስ እ.ኤ.አ ሜይ 2012 ኢትዮጵያን ከጎበኙ በኋላ የሚከተለውን ምልከታ አስፍረው ነበር፣ “ድርቅ በእራሱ ረኃብን እና አስከፊ ድህነትን ያስከትላል ማለት አይደለም፡፡ ማህበረሰቦች የመስኖ ስራን ተጠቅመው የምግብ እህል ማምረት ከቻሉ፣ የእህል ማከማቻ መጋዘኖች ካሉ እና የዝናብ ውኃን በማጠራቀም በጉድጓድ ውስጥ በማከማቸት ለግብርና ስራ መጠቀም ከተቻለ ህዝቦች ድርቅን መቋቋም ይችላሉ የፈለገውን ያህል ነገሮች ከውጭ ቢወረወሩባቸውም፡፡” የቢቢሲ ዓለም አቀፍ የዜና አገልግሎት ወኪል አርታኢ የሆኑት ማርቲን ፕላውት በተመሳሳይ መልኩ እንዲህ የሚል ገለጻ አድርገው ነበር፣ “የአሁኑ [2012 የኢትዮጵያ ምግብ] ቀውስ ዋና መንስኤው አርሶ አደሮችን የመንግስት ይዞታ በሆነው መሬት ላይ ታስረው እንዲኖሩ መሬት እንዳይሸጥ እና እንዳይለወጥ የሚያስገድደው የተበላሸ እና ቀያጅ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው፡፡“ በአጠቃላይ በኢትዮጵያውያን/ት ላይ ለተንሰራፋው ረኃብ ተጠያቂው (የፈለገውን ያህል ረኃብ የምትለዋን ቃል የተለያዩ የውሸት እና የማስመሰያ ቃላት እና ሀረጎች በመፈብረክ ለመደበቅ የሚሞክሩ ቢሆንም) የህወሀት መሪዎች እና መሪዎች ብቻ ናቸው፡፡ ስለሆነም በግልጽ ሊነሱ የሚችሉት ጥያቄዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡

ሶሻሊዝምን አሽቀንጥሮ የጣለ እና የነጻ ኢኮኖሚ ገበያ ፖሊሲን ለማራመድ ቃል የገባ ገዥ አካል ለምንድን ነው መሬትን ጠቅልሎ የሚይዘው?

ለምግብ አገልግሎት የሚውሉ ሰብሎችን ለማምረት የሚያስችል በቂ የሆነ የመስኖ ስራ ስርዓት፣ የእህል ማከማቻ መጋዘኖች እና የዝናብ ውኃን በማጠራቀም ወደ ጉድጓዶች በማስገባት ጠብቀው የሚያቆዩ ነገሮችን በጠቅላላ በአገሪቱ ውስጥ ማደራጀት ያልተቻለው ለምንድን ነው?

ለሀገሪቱ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችል የህወሀት አመራሮች ያዘጋዙት ዕቅድ የት አለ?

በሚሊዮኖች ሄክታሮች የሚቆጠሩ ለም መሬቶችን ኢንቨስተሮች/መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች እየተባሉ ለሚጠሩት እና ለንግድ የሚውሉ የግብርና ምርት ውጤቶችን በማምረት ወደ  ውጭ አገሮች በማውጣት እየሸጡ እና የእራሳቸውን ትርፍ እያጋበሱ ባሉበት ሁኔታ እውነት በእርግጠኝነት የህወሀት መሪዎች ድህነትን መከላከል ወይም ደግሞ የምግብ ዋስትናን በኢትዮጵያ እንዴት ማረጋገጥ ይችላሉ?

ለወያኔ አገዛዝ የምግብ እርዳታ በመስጠት እና ወያኔው እራሱ ደግሞ እርዳታውን የፖለቲካ እና ወታደራዊ ጠቀሜታ በማዋል የእራሱን ስልጣን ለማራዘም እና በስልጣን ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ ለመቆየት የሚያውለው ከሆነ ዓለም አቀፍ የድህነት ወትዋቾች እና አቃጣሪዎች ኢትዮጵያ በምግብ እራሷን ትችላለች ብለው ያስባሉን?

ዓለም አቀፍ የድህነት ወትዋቾች እና አቃጣሪዎች ኢትዮጵያውያን/ት በአስከፊ የምግብ ንጥረ ነገር እጥረት ይሰቃያሉ በማለት ደጋግመው በመስበክ እና ለዚህ ብቻ ማረጋገጫ ዋስትና በመስጠት ረኃብ እየሞረሞረው ያለውን የኢትዮጵያውያንን/ትን ባዶ ሆድ መሙላት ይችላሉን?

ድህረጽሁፍ፣

ባለፉት በርካታ አስርት ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ህዝብ በአሰቃቂ የረኃብ አደጋ ውስጥ ሆኖ ሲያልቅ እና ሲሰቃይ የኖረበትን አሰቃቂ ክስተት ለማስታወስ ግንባር ቀደም ተነሳሽነቱን ወስደው እንዲታወስ ለማድረግ የሚጥሩ ጥቂት ሰዎችን ብቻ በመመልከቴ ደስተኛ አይደለሁም፡፡ ቢቢሲ በዛሬው ዕለት የሜዲያ አመራር የበላይነቱን ወስዶ እ.ኤ.አ በ1984 በኢትዮጵያ ላይ ተከስቶ የነበረውን ታላቁን ረኃብ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ እንዲታወስ በማድረጉ በጣም ላመሰግነው እወዳለሁ፡፡ የምዕራቡ ዓለም ታላላቅ  የረኃብ እልቂቶችን በመከላከል እና ወገኖቻችንን በየጊዜው ከሞት ሲታደጉ በቆዩት የምዕራበውያን ተቋማት እና ሰዎች ላይ አፍራለሁ (ሆኖም ግን ዘላለማዊ ምስጋና ለምዕራባውያን ጓደኞቻችን)፡፡ የእኛ ሰብአዊ መብቶች በሚደፈጠጡበት ጊዜ እኛን የሚያግዙን እና የሚጮሁልን ተቋማት ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ፍሪደም ሀውስ፣ ጀኖሳይድ ዎች እና ሌሎችም እደዚሁ ናቸው፡፡ የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች ሲታሰሩ እና ሀገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ሲደረጉ በማውገዝ እና በመከላከል የመጀመሪያው ረድፍ ላይ የምናገኘው ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተከላካይ  ኮሚቴን/Committee to Protect Journalists የተባለው ድርጅት ነው፡፡ ወንዞቻችን እና ወገኖቻችን በቋሚነት ከኖሩበት ቀዬ ሰብአዊ መብታቸው ተጥሶ በግድ እንዲፈናቀሉ ሲደረግ ለእኛ መከላከል እና ድርጊቱን ለማውገዝ በግንባር ቀደምትነት የሚቆሙልን ዓለም አቀፍ ወንዞች እና ኦክላንድ ተቋም/International Rivers and the Oakland Institute የተባሉት ድርጅቶች ናቸው፡፡ የበለጠ በእጥፍ የሚያሳፍረው ነገር ደግሞ እንደዚህ እያደረጉ ለእኛ እና ለወገኖቻችን መብት መጠበቅ እና ክብር እየታገሉ ላሉት ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች አባላት በጣም ጥቂት የሆንን ዜጎች ብቻ ነን እርዳታ የምናደርግላቸው (እውነታው ይጎዳናል፣ አይደለምን?!)

ምናልባትም ጥቂት አንባቢዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ላይስማሙ ይችላሉ፣ ሆኖም ግን ጥቂት የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች የሰብአዊ መብትን ወይም የፕሬስ መብትን በኢትዮጵያ ለማስከበር ጥረት ሲያደርጉ አያለሁ፡፡ በጋምቤላ፣ በኦጋዴን እና በሌሎች በርካታ የአገሪቱ ቦታዎች የሚፈፈጸሙ የዘር ማጥፋት ወንጀሎችን ለመከላከል ጥረት የሚያደርጉ ጥቂት የሲቪክ ድርጅቶችን አያለሁ፡፡ ለወጣቶች እድገት ወይም ለሴቶች መብቶች መከበር እና መጠናከር ጉዳዮችን የሚከታተሉ እራሳቸውን በማጠናከር ላይ የሚገኙ ጥቂት የሲቪክ ድርጅቶችን እያየሁ ነው፡፡ የተለየ የስራ ውጤት የሚያስመዘግቡ ኢትዮጵያውያንን/ትን የሚያስታውስ አንድ ብቻ የሲቪክ ድርጅት ያለ መሆኑን ተገንዝቢያለሁ፡፡ ለእራሳችን የማንቆመው ለምንድን ነው? የምዕራብ ጓደኞቻችን የሚያገኙት እኛ ግን የማናገኘው ምንድን ነው? ገንዘብ ነውን? እውቀት ነውን? ተነሳሽነት ነውን…? ምንድን? ለምንድን ነው ከወሮበሎች እና ከዘራፊዎች የእራሳችንን መብት ለማስጠብቅ በጽና የማንቆመው?

እ.ኤ.አ 2014 ላይ ሆነን በ1984 የተከሰተውን ታላቁን የኢትዮጵያ ረኃብ ስናስታውስ አንባቢዎቼ እንዲገነዘቡልኝ የምፈልገው ነገር ዛሬም በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ረኃብ እየተስፋፋ እና ወገኖቻችንን እያሰቃዬ ያለ መሆኑን ነው፡፡ ቢቢሲ ወይም ደግሞ ሌሎች ጥቂት የምርመራ የዜና ወኪሎች አልዘገቡትም ተብሎ ረኃብ የለም ማለት አይቻልም፡፡ በአሁኑ ጊዜ የህወሀት አገዛዝ በነጻው ፕሬስ ላይ የከፈተው ዘመቻ እና የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞችን በየእስር ቤቱ የሚያጉራቸው፣ በይስሙላው የዝንጀሮ ፍርድ ቤት እያስቀረበ ፍዳቸውን የሚያሳያቸው እና እናት አገራቸውን እየለቀቁ እንዲሰደዱ ካደረገባቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ይህንን በአስከፊነቱ እየተስፋፋ የመጣውን ረኃብ እንዳይዘግቡ ለማድረግ እና የዓለም

አቀፉ ማህበረሰብ ዘገባውን እንዳያገኝ በታሰበ እኩይ ምግባር ነው፡፡ እየተቃረበ የመጣው የምርጫው ጉዳይም ሌላው ነገር ሆኖ፡፡

በኢትዮጵያ በየዓመቱ በቢሊዮን ብር የሚቆጠር የምግብ እርዳታ እያሰባስቡ ተጠያቂነት ለሌለበት የህወሀት አገዛዝ የሚያስረክቡት ዓለም አቀፍ የድህነት ወትዋቾች እና አቃጣሪዎችም “ረኃብ” የምትለዋን ቃል ትንፍሽ ላለማለት የሸረቡት የዝምታ ሴራ እና ዱለታ መሆኑን አንባቢዎች እንዲገነዘቡልኝ እፈልጋለሁ፡፡ በኢትዮጵያ በጣም በሚያስፈራ ሁኔታ አፍጥጦ እና አግጥጦ የመጣውን ረኃብ ለመሸፋፈን እና እነርሱ በየጊዜው ለዚህ ዕኩይ ተግባራቸው አገልግሎት ሲባል እየፈለፈሉ በሚያወጧቸው ቢሮክራሲያዊ በሆኑ ቃላት እና ሀረጎች እየቀያየሩ በማቅረብ ረኃብ እንደሌለ አድርገው በማቅረብ የኢትዮጵያን ህዝብ እና የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማደናገር የታሰበ የሸፍጥ አካሄድ ነው፡፡

በእኔ የግል ምልከታዬ በዓለም ላይ ስለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን/ት ጉዳይ ድምጻቸውን ማሰማት የሚችሉ በርካታ የበቁ እና የመጠቁ ኢትዮጵያውያን/ት ልሂቃን እና ምሁራን፣ ሴቶች እና ወንዶች ስንት ማስተማር የሚችሉ በየሀገሩ ተሰራጭተው እያሉ ከሳምንት ሳምንት፣ ከዓመት ዓመት ለበርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያውያን/ት ላይ ተጽእኖ ሊፈጥሩ በሚችሉ በተለያዩ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የአንድ ሰው ድምጽ ብቻ ሲሰማ መቆየቱ በጣም አስደንጋጭ እና የሚያሳስበኝ ሁኔታ ነው፡፡ አንድም ሳምንት ሳላቋርጥ በየሳምንቱ ለበርካታ ዓመታት በበርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ረዣዥም ትችቶችን በመጻፍ የእራሴን ሀሳብ እና አለመካከት በይፋ በመገልጽ ስጽፍ በመቆየቴ ብዙ ሰዎች ይደነቃሉ፡፡ እኔ ያንን አድናቆት ምንም ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ይልቁንም እኔን በጣም በሚያስደነግጥ ሁኔታ የሚገርመኝ እና የሚያስደንቀኝ  በርካታ የበቁ፣ የተማሩ እና የተመራመሩ ኢትዮጵያውያን/ት በእያንዳንዷ ሳምንት አንድም ሳምንት ሳያቋርጡ፣ ዓመት አስከ ዓመት ለበርካታ ዓመታት ሃሳባቸውን እና አመለካታቸውን በመብረቃዊ ዝምታ ማሳለፋቸውን የመምረጣቸው እውነታ ነው፡፡

ተነሳሽነት እና ፍቅር ለአንድ ክስተት እውን መሆን የእያንዳንዱ ግለሰብ ልዩ ባህሪ ነው፣ ሆኖም ግን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ/ት በተለይም ከፍተኛ ትምህርትን ለመቅሰም ዕድሉን የተጎናጸፋችሁ ምሁራን በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ እና በሌሎችም ክፍለ ዓለሞች ለሰብአዊ መብት መጠበቅ እና መከበር፣ ልታስተምር እና ልታስተምሪ የሞራል ግዴታ አለብህ/ሽ፡፡ የወደፊቱ የኢትዮጵያ ትውልድ የአሁኑን ትውልድ ወደኋላ መለስ ብለው በማየት በአንድ ላይ ቆመው ሁሉንም የጋራ አመልካች ጣቶቻችንን በእኛ ላይ ቀስረው ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ይጮሀሉ፣ “ከሰናችኋል!” በማለት፡፡ በትወልድ ታሪክ ከመከሰስ ያድነን፣ አሜን!

(ትግሉ ይቀጥላል!)

በኢትዮጵያ ያለው ረኃብ የፈለገውን ያህል በማስመሰያ እና በማደናገሪያ ቃላት እና ሀረጎች ተሸፋፍኖ እና ታጅቦ ቢቀርብም ያው አሁንም ቢሆን ረኃብ ነው!

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ጥቅምት 18 ቀን 2007 ዓ.ም