የአሜሪካንን የህዝብ ጠባቂ ፖሊስ የሚጠብቀው ፖሊስ ማን ነው?


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም 

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

“የእኛ መንግስት…እራሱን አርዓያ በማድረግ ለሁሉም ህዝብ ትምህርት ያስተምራል፡፡ መንግስት እራሱ ህግን የማያከብር እና የሚጥስ ከሆነ ለህግ ያለውን ንቀት ይፈልፍላል፣ እያንዳንዱ ሰው ለእራሱ ህግ እንዲሆን ይጋብዛል፣ ስርዓተ አልበኝነትን ይጋብዛል” የዩኤስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ለዊስ ዲ. ብራንዲስ

የጉዳዩ ዋና ፍሬ ነገር፡ ያልተነጣጠሉ ጉዳዮች፣

እ.ኤ.አ ጁላይ 17/2014 ኤሪክ ጋርነር የተባለ የ43 ዓመት እድሜ የአፍሪካ አሜሪካዊ ጎልማሳ ከመሸጫ ሱቅ ውጭ ታክስ ያልተከፈለበት ሲጋራ በመሸጥ ህገወጥ ንግድ አካሂደሀል በሚል ጥርጣሬ ቢያንስ በአራት የኒዮርክ ከተማ ፖሊስ መምሪያ (ኒከፖመ) ኃላፊዎች ጥያቄ ቀረበለት፡፡ በዚያ ጥያቄ በቀረበበት ወቅት በተንቀሳቃሽ ስልክ ሲናገር በቪዲዮ ይታይ እንደነበረው ጋርነር ምንም ዓይነት ጥፋት እንዳላጠፋ እና ምንም ዓይነት ስህተት ያልሰራ መሆኑን በመግለጽ ቀጣይነት ባለው ሁኔታ በፖሊስ እየተሰቃዬ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ለፖሊስ ኃላፊው እንዲህ የሚል ተቃውሞውን አሰምቷል፡

ሁልጊዜ ባየኸኝ ቁጥር እኔን በቁጥጥር ስር ለማዋል ትፈልጋለህ፡፡ እኔ ይኸ ጉዳይ በጣም አሰልችቶኛል፡፡ ዛሬ ይህ ድርጊት መቆም አለበት፡፡ ምንም ማድረግ አልቻልኩም፡፡ ሁሉጊዜ ባየኸኝ ቁጥር ልታስፈራራኝ ትፈልጋለህ፡፡ እኔን ልታቆመኝ ትፈልጋለህ፡፡ ሲጋራ ሸጠሃል ብለህ በምክንያት በቁጥጥር ስር ልታውለኝ ትፈልጋለህ፡፡ እኔ  የራሴን ጉዳይ ነው የማረገው ፡፡ ሌላ ላይ አልደርስም፡፡ ከዚህ ቀደም ለመጨረሻ ጊዜ ነግሬህ ነበር፣ እባክህ ተወኝ…አትንካኝ… አታዋክበኝ

ፖሊሱ ግን ጋርነርን ሊተወው አልቻለም አልፈለገም ፡፡ ግማሽ ደርዘን የሚሆኑ የፖሊስ ኃላፊዎች ወዲያውኑ ጋርነርን ማጥቃት ጀመሩ፡፡ ከፖሊሶቹ መካከል አንደኛው የጋርነርን አንገት አንቆ እንዳይተነፍስ አድርጎ በመያዝ ህገወጥ ድርጊት ይሰራበት ጀመር፡፡ የቪዲዮ ምስሉን በተመለከትሁ ጊዜ ከአዕምሮ ጓዳዬ ውስጥ ወዲያውኑ ብልጭ ያለልኝ የጋርነር ጉዳይ በኒዮርክ ከተማ በልዩ ልዩ የእግር መንገዶች እና በህንጻዎች መካከል በተከበበ ጫካ ውስጥ በህገወጥ ፖሊሶች ተይዞ የሚሰቃይ ሰብአዊ ፍጡር ከመሆኑ በስተቀር በአፍሪካ ሜዳማ ምድር ውስጥ በሚያሽካኩ የጅብ መንጋዎች መካከል ተከብቦ አሳር ፍዳውን የሚቀበል ጎሽን ይመስል ነበር፡፡

ፖሊሱ ጋርነርን በኃይል በመምታት ከመሬት ቀላቀለው፡፡ የጋርነር እጆች በእጅ የሽቦ ሰንሰለት  የፊጥኝ ታስረው በስተጀርባው በኩል ተንከርፍፈው ይታዩ ነበር፡፡ ጋርነር መላ አካላቱ በመሪቱ ላይ ተዘርሮ ሲታይ የፖሊስ ኃላፊዎች እግሮች ከጋርነር ጀርባ እና ፊት ላይ ረግጠው ቆመው ይታዩ ነበር፡፡ “መተንፈስ አልቻልኩም” በማለት 11 ጊዜ ደጋግሞ ሲጮህ ይሰማ ነበር፡፡ ቀጣይነት ባለው እና ጭካኔ በተሞላበት መልኩ ድብደባውን የሚያካሂዱት የፖሊስ ኃላፊዎች ጋርነርን እንደ ቁጫጭ ከብበው በአፍሪካ እንደሚታዩት አዳኞች ህይወት አልባ የሆነውን በድን አካላቱን ህይወት ያለው ወይም የሌለው መሆኑን ይፈትሹ ነበር፡፡ ጋርነር ይተነፍስ ወይም አይተነፍስ እንደሆነ ወይም ደግሞ በህይወት ይኑር አይኑር ለማወቅ እንዲችሉ መላ አካላቱን ይዳስሳሉ፡፡ የደም ቅዳ የዝውውር ኡደቱን ለመመለስ እና ስራውን እንዲሰራ በማድረግ ወይም ደግሞ ሌላ ማናቸውም የህይወት እስትንፋስ ለመስጠት የሚያስችል አጋዥ መሳርያ መጠቀም አልቻሉም፡፡ አንድ ፖሊስ ጋርነርን “መተንፈስ አይችልም” ይላል፡፡

አስቸኳይ የነብስ አድን የጤና ባለሙያዎች በቦታው ተገኙ፡፡ የጤና ባለሙያዎ የጋርነርን አንገት በመዳሰስ የደም ስርጭት መኖር አለመኖሩን ታረጋግጣለች፡፡ በድን ከሆነው ጋርነር ጋር ለመገናኘት ሙከራ ታደርጋለች፡፡ እንዲህ በማለትም ትናገራለች፣ “እኛ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ሰጭ ሰዎች ነን፡፡ አንተን ለመርዳት ነው እዚህ ያለነው፡፡ በዚህ በድንገተኛ ተጎጅ ሰው መያዣ አልጋ ላይ እናደርግሀለን፡፡ እሺ?“ እንደ ጋርነር የተጎዱትን እና በሽተኞችን በተለመደው የአሰራር ሂደት መሰረት እርዳታ በመስጠት እንዲተነፍሱ በማድረግ ወደ ቀድሞው ቦታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ በማድረግ የህይወት አድን ስራ አልሰራችም፡፡ የአስቸኳይ የነብስ አድን የጤና ባለሙያዋ ዝም ብላ ሄደች፡፡ ጋርነር በድንገተኛ ተጎጂ ሰው አልጋዋ ላይ ተዘርሯል፡፡ ጋርነር ሆስፒታል በደረሰ ጊዜ ህይወቱ አልፋ ነበር፡፡

የተንቀሳቃሽ ስልክ ቪዲዮው ጋርነር በፖሊሶች ኃላፊዎች ላይ ወይም ደግሞ በሌላ ከሸቀጦች መሸጫ ሱቅ ውጭ ባለ በማንኛውም ሰው ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እና ማስፈራራት ያላደረገ መሆኑን ያሳያል፡፡ በካናቴራ እና በቁምጣ ሱሪ ሆኖ ፖሊሶች የሚያደርጉበትን ማስፈራራት ትክክል ያለመሆን በመናገር ቆሞ ቅሬታውን ያሰማ ነበር፡፡ ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ አልያዘም ነበር፡፡ ማንንም የፖሊስ ኃላፊ አልገፋም ወይም ደግሞ በአካላቸው ላይ ጉዳት አላደረሰም፣ ወይም ደግሞ የፖሊስ ኃላፊዎቹ እርሱን በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ በየትኛውም ቦታ እና ጊዜ ምንም ዓይነት ማስፈራራት አላደረገም ነበር፡፡ በመጨረሻም ግማሽ ደርዘን የሚሆኑ የፖሊስ ኃላፊዎች ግብር ያልተከፈለበት ሲጋራ በመሸጥ ወንጀል ጥርጣሬ አንገቱን አንቀው እና ትንፋሽ እንዲያጣ አድርገው አፍነው እንዲሞት አደረጉ፡፡ ጋርነር ከህግ አግባብ ውጭ በዘፈቀደ በኒዮርክ ከተማ ፖሊስ መምሪያ (ኒከፖመ) ኃላፊዎች የተገደለ የሞት ሰለባ ነውን?

የኒዮርክ መርማሪ ግራንድ ጁርይ የጋርነርን ሞት ለዘጠኝ ሳምንታት ያህል ካጠና በኋላ የጋርነርን ጉሮሮ አንቆ ህይወቱ እንድታልፍ ባደረገው ዳንኤል ፓንታሎ በተባለው የፖሊስ ኃላፊ ላይ ክስ መመስረትን በመቃወም አንዳይከሰስ ተደረገ ። እናም ጋርነርን ህገወጥ በሆነ መልኩ አንገቱን አንቆ አየር በማሳጣት እንዲሞት ያደረገው የፖሊስ ኃላፊ በህግ ፊት ቀርቦ መጠየቅ የለበትም ብሏል፡፡   በሌላ አገላለጽ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የጋርነር ሞት መንስዔ ወይም ደግሞ መነሻ ምክንያቶች ከኒዮርክ ከተማ ፖሊስ መምሪያ (ኒከፖመ) ኃላፊዎች ጋር የተያያዙ ድርጊቶች ሳይሆኑ ከዚህ ጋር ምንም ዓይነት ዝምድና በሌለው እራስን በእራስ የማጥፋት ድርጊት ነው ብሏል፡፡

ከህግ አግባብ ውጭ በዘፈቀደ በአንድ ፖሊስ የተገደለውን የጋርነር ሞት በቪዲዮ ምስል ለተመለከቱት የጋርነር ቤተሰቦች እና በዓለም ላይ ለሚገኙ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ህዝቦች በሙሉ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እንዲህ የሚል ቀላል መልዕክት ያስተላልፋል፣ “ጉዳዩን ለዘጠኝ ሳምንታት ስንመረምረው እና ስናየው የቆየነውን እኛን ልታምኑን ትችላላችሁ ወይስ ደግሞ በቪዲዮ ምስል ያያችሁትን የተንሸዋረረ የዓይን እይታ ውጤት የሆኑትን ውሸቶች እና የሌብነት አካሄዶችን?“  ባዓይን ያያችህሁትን  አትመኑ አይነት ነገር ነው።

ሊታመን የማይችለው ፖሊሱ እውነታ ሲታይ በቪዲዮው የጋርነርን አንገት አንቆ አየር አሳጥቶ ይታይ የነበረው የፖሊስ ኃላፊ የሆነው ፓንታሊዮ ያለምንም ጥርጥር ለጋርነር ሁለተኛ ደረጃ የነብስ ግድያ ወንጀል መንስዔ ቀዳሚ ተጠርጣሪ ሊሆን እንደሚችል እና ለእዚህ ደጋፊ የሚሆኑ በርካታ ማስረጃዎች እንደነበሩ ያመላክታል፡፡ የኒዮርክ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀጽ 125.15 እንዲህ በማለት በግልጽ ያስቀምጠዋል፣ “አንድ ሰው የሚያስከትለውን አደጋ በውል ሳያገናዝብ የሰው ህይወት በማጥፋት ተወንጅሎ ሲገኝ፡ 1. ሆን ብሎ ሳያስብበት እና የሚያስከትለውን አደጋ ሳያገናዝብ የግድያ ወንጀል የፈጸመ ተብሎ ሊጠየቅ ይችላል…“

የኒዮርክ ህግ በግልጽ እና በማያሻማ መልኩ የተቀመጠ ስለሆነ ጥቂት ትርጉምን ብቻ የሚጠይቅ ነው፣ አንድ ሰው ሆን ብሎ ሳያስብበት እና የሚያስከትለውን አደጋ ሳያገናዝብ በሰው ላይ የሞት አደጋ ቢያስከትል ያ ሰው በሁለተኛ ደረጃ የነብስ ማጥፋት ወንጀል ጥፋተኝነት ተጠያቂ ይሆናል፡፡ የሚያስከትለውን አደጋ ሳያገናዝብ ማለት የአንድን ሰው ድርጊት ወይም ደግሞ በሌሎች ሰዎች ላይ ተጨባጭነት ባለው እና በሌለው ሁኔታ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ወይም ጉዳት በውል ሳያጤኑ የሚደረግ የግድያ ወንጀል ተጠያቂነት ማለት ነው፡፡

እንደዚሁም ደግሞ በኒዮርክ ከተማ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ በአንቀጽ 125.15 በተሰጠው ትርጉም መሰረት የፖሊስ ኃላፊ የሆነው ፓንታሊዮ አደጋ ሊያስከትል የሚችል መሆኑን በውል ሳያጤኑ የሞት አደጋን የሚያስከትል የግድያ ወንጀል ቢፈጸም በሁለተኛ ደረጃ የነብስ ማጥፋት ወንጀል ተጠያቂ ያደርጋል በማለት በማያሻማ መልኩ በግልጽ ያስቀመጠው ስለሆነ ፓንታሊዮ ከህግ ስርዓት ውጭ በዘፈቀደ ህግን በመተላለፍ በሟች ጋርነር ላይ የሚያስከትለውን አደጋ እና ጉዳት በውል ሳያጤን በቁጥጥር ስር ያዋለ እና እንዲሞትም ያደረገ በመሆኑ በሁለተኛ ደረጃ የግድያ ወንጀል ተጠያቂ ሆኖ ክስ ሊመሰረትበት የሚያስችል በቂ መረጃ እንዳለ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሊያስብ ይገባል፡፡

የኒዮርክ ፖሊስ መምሪያ የጥበቃ መመሪያ መሰረት ማነቅ በጥብቅ ተከለከለ መሆኑን የሚከተለውን ዋቢ ማድረግ ይቻላል፡

ከገጽ 203 – 11 ኃይልን መጠቀም፡ በስራ ላይ የሚውልበት፡ .. 01/01/2000 ጀምሮ፣ የኒዮርክ ፖሊስ መምሪያ አባላት አንገት ማነቅን በስራ ላያ አያውልም፡፡ አንገት ማነቅ የሚከተሉትን ሆኖም ግን እነዚህ ብቻ ያልሆኑትን ያካትታል፡ በጉሮሮ ወይም በአየር ማስገቢያ ቧንቧ ላይ አየር እንዳይተላለፍ ወይም ደግሞ ወደ ውስጥ የሚገባውን የአየር መጠን በመቀነስ በቂ አየር እንዳይገኝ የሚደረግ ማንኛውም ጫና ማለት ነው፡፡  አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ኃይልን መጠቀም ወይም ደግሞ በእስር ቤት ውስጥ ኃይል ለመጠቀም እና  ተቃውሞን ለማሸነፍ የፖሊስ ኃላፊዎች አስፈላጊ የሆኑ ስልቶችን በተቀነባበረ ሁኔታ ይጠቀማሉ…

የፖሊስ ኃላፊ ፓንታሊዮ ሰዎችን ከህግ አግባብ ውጭ በቁጥጥር ስር የማዋል መጥፎ ታሪክ አለው፡፡ ፖሊስ ፓንታሊዮ በጋርነር ህይወት ላይ ካደረሰው አደጋ በፊት ቢያንስ ሶስት ጊዜ ያህል ለህግ ቀርቧል፡፡ እንደ “ዩኤስኤ በአሁኑ ጊዜ” ዘገባ ከሆነ “እ.ኤ.አ ማርች 2012 ፓንታሊዮ እና ሌሎች ቢያንስ አራት የፖሊስ ኃላፊዎች ከህግ አግባብ ውጭ ሰዎችን በማዋረድ እና በአደባባይ ልብስን አስወልቆ በመፈተሽ እና በስታተን ደሴት ሰዎችን አስረው በቁጥጥር ስር በማዋል ወንጀል ምክንያት ተከስሰው ጉዳዩን እ.ኤ.አ በ2013 የፌዴራል ፍርድ ቤት ሲከታተለው ቆይቶ ኒዮርክ ከተማ ከከሳሾች ጋር ያለውን ይህንን ጉዳይ እልባት ሰጥቶታል፡፡

እ.ኤ.አ ኦገስት 9/2014 የፖሊስ ኃላፊ ዳረን ዊልሰን በፈርግሰን ከተማ በሚሶሪ፣ በሴንት ሌዊስ ከከተማ ወጣ ባለ አካባቢ በስም ሚካኤል ብራውን እየተባለ የሚጠራውን የ18 ዓመት እድሜ ያለውን አፍሪካ-አሜሪካዊ ወጣት በጥይት ተኩሶ ገድሎታል፡፡ ከግድያው ጋር በተያያዘ መልኩ የማያከራክሩ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ገዳዩ ፖሊስ ዊልሰን ብራውንን እና ጓደኛውን በጎረቤት እግር መንገድ መካከሉን ይዘው በመጓዝ ላይ እንዳሉ ጠርቶ ጠይቋቸዋል፡፡ ፖሊስ ዊሊሰን እነብራውን የመንገዱን ዳርቻ በመያዝ እንዲሄዱ ይነግራቸዋል፡፡ በዚህን ጊዜ በብራውን እና በዊልሰን መካከል የቃላት ልውውጦች ይደረጋሉ፡፡ ከዚያም ነገሮች እየተጋጋሉ ጠብ ይነሳል፣ ቁጣን ያዘለ አካላዊ እንቅስቃሴም ይጀምራል፡፡ በማስከተልም ፖሊስ ዊልሰን በጥይት ተኩሶ ብራውንን መታው፡፡ ብራውን እና ጓደኛው ከቦታው ተነስተው ሮጡ፡፡ ፖሊስ ዊልሰን ብራውንን እያሳደደ በእርሱ ላይ መተኮሱን ቀጠለ፡፡ ዊልሰን 12 ጊዜ ተኮሰ፡፡ ብራውን 7 ወይም 8 ጊዜ በተተኮሱት ጥይቶች ተመታ፡፡ ፖሊስ ዊልሰን እና ሌሎች ፖሊሶች የብራውንን ሬሳ በመንገድ ላይ ተዘርሮ ለአራት ሰዓት ያህል እንዲቆይ በማድረግ ጥለውት ሄደዋል!!!

ፖሊስ ዊልሰንን ለህግ ለማቅረብ እና ክስ እንዲመሰረትበት ለማድረግ ስልጣን ያለው የአካባቢው አቃቤ ህግ ጉዳዩን ለጠቅላፍ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ መረጠ፡፡ ከዓመታት በፊት የአቃቤ ህጉ አባት የፖሊስ ኃላፊ የነበሩ ሲሆን በአንድ አፍሪካ-አሜሪካዊ ተጠርጣሪ አደጋ ደርሶባቸው ህይወታቸው አልፏል፡፡ በርካታዎቹ የአቃቤ ህጉ የቤተሰብ አባላት እናታቸውን፣ ወንድማቸውን፣ አጎታቸውን እና የአጎታቸውን እና የአክስታቸውን ልጆች ጨምሮ በሴንት ሌዊስ ፖሊስ መምሪያ ሰርተዋል፡፡ አቃቤ ህጉ በ23 ዓመታት ጊዜ ውስጥ አምስት ጊዜ ብቻ የወንጀል ጉዳዮችን ለጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅርበዋል፡፡ በሌሎች የወንጀል ጉዳዮች የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሳይመረምራቸው አቃቤ ህጉ በጠረጠሯቸው ወንጀለኞች የቢሮ ፋይሎች ተሞልተዋል፡፡

አቃቤ ህጉ ይህ የግድያ ወንጀል ለመፈጸሙ እና ይህም ወንጀል በተከላካዩ ለመፈጸሙ የሚያመላክቱ ጭብጦች ስለመኖራቸው መወሰን እንዲችል የፖሊስ ዊልሰንን ጉዳይ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አቀረቡ፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በዊልሰን ላይ ክስ መመስረት እንደሌለበት ወይም መከሰስ እንደሌለበት ተቃወመ፡፡ አቃቤ ህጉ በ23 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከተደረጉ የግድያ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ መልኩ የዊልሰንን ጉዳይ በማስረጃ አስደግፈው እያቀረቡ በግድያ ወንጀል የተከሰሰው የፖሊስ ኃላፊው በየጊዜው እየተኮሰ መሆኑን አሳሰቡ፡፡ አቃቤ ህጉ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ካቀረቧቸው ጉዳዮች አንዳቸውም ቢሆኑ ወንጀል የተፈጸሙባቸው ናቸው ተብለው ውሳኔ የተሰጠባቸው የሉም፡፡

እ.ኤ.አ በ2009 አዲስ ዓመት ኦስካር ግራንት III የተባለ የ22 ዓመት እድሜ ያለው አፍሪካ-አሜሪካዊ ወጣት በኦክላንድ ካሊፎርኒያ ውስጥ የቤይ አካባቢ የባቡር ፖሊስ (ቤአፈደፖ)/Bay Area Rapid Transit Police (BART) ኃላፊ በነበረው ጆሀንስ መህሰርሌ በተባለው ሰው በጀርባው ላይ በጥይት ተመትቶ ተገድሏል፡፡ መህሰርሌ እና ሌሎች የቤአፈደፖ ኃላፊዎች በመሬት ውስጥ ለውስጥ ከሚያስሄደው መንገድ ጣቢያ ችግር ተፈጥሮ ስለጉዳዩ መፍትሄ እንዲሰጡ የስልክ ጥሪ ደረሳቸው፡፡ መህሰርሌ እና ሌላው የፖሊስ ጓደኛው ግራንትን ከመሬት ላይ በመጣል ያዘው፡፡ ገራንት የጦር መሳሪያ የታጠቀ ሰው አልነበረም፡፡ መህሰርሌ ቆመ እና ለኃላፊው ጓደኛው እንዲህ ብሎ ነገረው፣ “ተመለስ፣ እኔ እመረምረዋለሁ“፡፡ መህሰርሌ ሽጉጡን አወጣ እና ገራንትን ከጀርባው ላይ አንድ ጊዜ ተኩሶ መታው፡፡ በማግስቱ ግራንት ሞተ፡፡ መህሰርሌ በነብስ ማጥፋት ወንጀል ክስ ተመሰረተበት ሆኖም ግን ዳኛው ሆን ተብሎ ያልተፈጸመ ግድያ ወንጀል (በአጋጣሚ፣ ያልታሰበበት ግድያ) ነው በማለት ከዋና ገዳይነት ወንጀል ለማዳን ተሞክሯል፡፡ በዚህም መህሰርሌ የሁለት ዓመታት እስራት ብቻ ተወሰነበት፡፡ ይህንንም ቅጣት በወረዳ እስር ቤት ፈጽሞ ወጣ!

እ.ኤ.አ ኖቬምበር 25/2006 የሲቪል ልብስ የለበሱ እና ተመሳስለው ከስብሰባ ውስጥ በመግባት ሚስጥር የሚሰበስቡ የኒዮርክ ከተማ ፖሊስ መምሪያ (ኒከፖመ) ኃላፊዎች በጠቅላላው 11 ዙር ጥይት በመተኮስ የ23 ዓመት እድሜ ያለውን እና ሲያን ቤል በመባል የሚጠራውን አፍሪካ-አሜሪካዊ ወጣት በመግደል ሌሎች ጓደኞቹን አቁስለዋል፡፡ የፖሊስ ኃላፊዎቹ ህገወጥ በሆነ መልክ ገንዘብ ከሚገኝበት ክለብ በመገኘት ህገወጡን ድርጊት ለማጣራት ባሉበት አካባቢ ቤል እና ጓደኞቹ በአንድ የወንድ ሙሽራ ቤት ውስጥ ነበሩ፡፡ ቤል እና ጓደኞቹ ከክለቡ በመውጣት በመኪናቸው ውስጥ ገቡ፡፡ መሳሪያ አልታጠቁም ነበር፡፡ የዓይን እማኞች እንዳረጋገጡት የፖሊስ ኃላፊዎቹ ያለምንም ማስጠንቀቂያ ቤል እና ጓደኞቹ ወዳሉበት መኪና የእሩምታ ተኩስ በመክፈት መተኮስ ጀመሩ፡፡ ሶስት የፖሊስ ኃላፊዎች ሁለተኛ ደረጃ ግድያን ጨምሮ በርካታ ክሶች ተመሰረቱባቸው፡፡ ሆኖም ግን ነጻ ተብለው ተለቀቁ!!!

እ.ኤ.አ ፌብሯሪ 4/1999 አራት የሲቪል ልብስ የለበሱ የኒዮርክ ፖሊሶች  ከአፓርትማው ውጭ ቆሞ የነበረ አንድ አማዱ ዲያሎ የሚባል የ23 ዓመት እድሜ አፍካዊ ስደተኛን በመተኮስ ገድለውታል፡፡ የፖሊስ ኃይሎቹ በአጠቃላይ 41 ጥይቶችን የተኮሱ ሲሆን ከእነዚህ ጥይቶች ውስጥ 19ኙ ዲያሎን ደብድበዋል፡፡ አራት የፖሊስ ኃላፊዎች በሁለተኛ ደረጃ የነብስ ማጥፋት ወንጀል ተከስሰው ነበር ሆኖም ግን ሁሉም ነጻ ተብለው ተለቀዋል!

እ.ኤ.አ ጁላይ 2014 የተንቀሳቃሽ ስልክ ቪዲዮ የካሊፎርኒያ አውራ መንገድ የጥበቃ ፖሊስ አንዲትን የአፍሪካ-አሜሪካዊ ቤት የለሽ ሴት በቁጥጥር ስር በማዋል ለማሰር ሲሞክር አሳይቷል፡፡ ከእርሱ መንጭቃ ልታመልጥ ስትንቀሳቀስ ታይታለች፡፡ ሆኖም ግን የፖሊስ ኃላፊው ሴትዮዋን ገፍትሮ በመጣል ከመሬት ቀላቀላት፡፡ በፖሊስ ኃላፊው የሚደረጉ ነገሮች ሲታዩ በጣም ኋላቀር እና የሚያሳዝኑ ሲሆን ንዴት በተቀላቀለበት ሁኔታ 11 ጊዜ ፊቷን በቦክስ ሲመታት ታይቷል፡፡ ከዚያ በኋላ ከካሊፎርኒያ አውራ ጎዳና የጥበቃ አባልነት በእራሱ ፈቃድ ስራውን ለቅቋል፡፡

የፖሊስ ከህግ አግባብ ውጭ ስልጣኑን የመጠቀም እና ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል መጠቀም ትናንሾቹን እና ትላልቆቹን የፖሊስ መምሪያዎች እየጎዳ ያለ ሀገር አቀፍ ችግር ነው፡፡ እ.ኤ.አ ዴሴምበር 4/2014 የዩናይትድ ስቴትስ ፍትህ መምሪያ “የክሌቨላንድ ከተማን የፖሊስ መምሪያ ምርመራ ውጤት” አወጀ፡፡ ዘገባው በማጠቃለያው ላይ የክሌቨላንድ ከተማ የፖሊስ መምሪያ የአሜሪካንን አራተኛውን ተሻሽሎ የወጣውን ህገመንግስት በተጻረረ መልኩ ከመጠን ያለፈ ኃይልን እንደሚጠቀም የፍትህ መምሪያው አመክኗዊ እምነት እንዲኖረው አድርጓል፡፡ ፍትህ መምሪያው እንዲህ በማለት የችግሩን ጭብጥ ለማመላከል ሞክሯል፣ “በቂ ያልሆነ ተጠያቂነት፣ በቂ ያልሆነ ስልጠና፣ ውጤታማ ያልሆኑ ፖሊሲዎች እና በቂ ያልሆነ የማህበረሰብ አሳታፊነትን ጨምሮ መዋቅራዊ፣ ስልታዊ ጉድለቶች እና ልምዶች ምክንያታዊ ያልሆነ ያልተመጣጠነ ኃይል ለመጠቀም አስተዋጽኦ እንዳላቸው አረጋግጠናል…”

እ.ኤ.አ ኦክቶበር 2014 በአሜሪካ ሲቪል ነጻነቶች ህብረት/American Civil Liberties Union የተለቀቀው ጥናት እንዳረጋገጠው የቦስተን ፖሊስ ኃላፊዎች ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ ምልከታዎችን ያደርጋሉ፣ ትክክለኛ ያልሆነ ጥያቄ ያቀርባሉ ወይም ደግሞ ጥቁር ኗሪዎችን ከ2007 እስከ 2010 ድረስ ትክክል ያልሆነ ምርመራ ያካሂዳሉ፡፡ እንደ ጥናት ውጤቱ ከሆነ የቦስተን ፖሊሶች 63.3 በመቶ የሚሆኑትን ችግሮች የፈጠሯቸው ብዛታቸው ከሩብ በታች የሆኑት በቦስተን ከተማ የሚኖሩት ጥቁሮች ናቸው የሚል ዓላማን ይዟል፡፡ ጥናቱ በመጨረሻ እንዲህ በማለት አጠቃልሏል፣ “ይህ የዘር መድልኦ በቦስተን ፖሊስ መምሪያ የዒላማ ጥረት ብቻ ሊወገድ አይችልም“፡፡

እ.ኤ.አ በ2008 በሎስ አንጀለስ ፖሊስ መምሪያ ላይ በዘር በተለያዩ ህዝቦች ላይ የተደረገ ጥናት ውጤት እንዳመለከተው አፍሪካ-አሜሪካውያን/ት እና የእስፓኒሽ የዘር ሀረግ ባላቸው ሰዎች ላይ ሁልጊዜ የማስቆም፣ የበለጠ ቶሎ ቶሎ የመፈተሽ፣ ብዙውን ጊዜ የመመርመር እና አብዛኛውን ጊዜ በቁጥጥር ስር የመዋል ድርጊቶች እየተፈጸሙባቸው እንዳሉ ዘገባው ይፋ አድርጓል፡፡ በተወሰኑ የሎስ አንጀለስ ወረዳዎች ያለውን ተመጣጣኝ ኃይል መጠቀም እና የንብረት ዘረፋ ወንጀሎችን በቁጥጥር ስር ከተደረጉ በኋላ ሌሎችን ተለዋዋጮች በመተው በተደረገው ጥናት መሰረት የጥናት ውጤቱ እንደሚያሳየው “ከ10,000 ኗሪዎች ውስጥ ጥቁሮችን የማስቆም መጠኑ ከነጩቹ የማስቆም መጠን በ3,400 የበለጠ ሲሆን የእስፓኒሾች ደግሞ ከጥቁሮችም በላይ በ360 (3,400+360= 3,760 ማለት ነው) በልጦ ተገኝቷል”፡፡

ወጣት አፍሪካአሜሪካውያን/ ወጣቶች ብቻ አይደሉም እምነት በማይጣልባቸው የፖሊስ ኃላፊዎች የጥቃት ሰለባ የሚሆኑት፣

አብዛኛውን ጊዜ በእምነትየለሽ የፖሊስ ኃላፊዎች የስቃይ፣ ማስፈራራት፣ እና ከህግ አግባብ ውጭ ለዘፈቀደ ግድያ ዒላማ የሚዳረጉት ወጣት አፍሪካ-አሜሪካውያን/ት ወጣቶች ብቻ እንዳልሆኑ ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ ታዋቂ የሆኑ የአፍሪካ-አሜሪካውያን/ት ተዋንያኖች፣ አትሌቶች፣ ዶክተሮች፣ የህግ ባለሙያዎች እና ሌሎች ባለሙያዎችም በእምነትየለሾቹ የፖሊስ ኃላፊዎች ማሰቃየት እና ስልጣንን ከህግ አግባብ ውጭ መፈጸሚያ ዒላማ ይደረጋሉ፡፡

እ.ኤ.አ ዴሴምበር 5/2014 በተለቀቀ የድረ ገጽ የግንኙነት መስመር የኬይሰር ዋና ኃላፊ/Chief Executive Officer የሆኑት ቤርናርድ ታይሰን እራሳቸውን ከኤሪክ ጋርነር እና ከሚካኤል ብራውን ጋር አመሳስለዋል፡፡ ታይሰን እንዲህ በማለት ጽፈዋል፣ “የእኔን ልምድ ከግንዛቤ በማስገባት እንደ ቁንጮ ባለስልጣን ኃላፊነት ያለኝ ሊመስላችሁ ይችላል – (መሰረቱን የምመራው ኩባንያ ኬይሰር 55 ቢሊዮን ዶላር ያለው አትራፊ የሆነ ድርጅት) – በችርቻሮ ንግድ ወይም ደግሞ በምግብ አገልግሎት ስራ ላይ ተሰማርቶ ቤተሰቡን በማገዝ ላይ ካለ ሰራተኛ ጋር ከሚሰራ ጥቁር ሰው የሚለይ ሊመስላችሁ ይችላል፡፡ ሆኖም ግን እርሱ እና እኔ ሁለታችንም የቱንም ያህል የኢኮኖሚ ደረጃ ወይም የኃላፊነት መጠሪያ ርዕስ ቢለይም በፖሊስ አይን ግን አንድ ነን፣ ልዩነት የለውም፡፡“

እ.ኤ.አ ፌብሯሪ 2014 የሎስ አንጀለስ ግዛት ከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኛ እና የድሮው ፖሊስ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት የነበሩት ዳቪድ ከኒንግሀም III  በሎስ አንጀለስ ፖሊስ መምሪያ ይሰሩ የነበሩ ሁለት የፖሊስ ኃላፊዎች እርሳቸውን በዘረኝነት ፈርጀው ትክክለኛ ያልሆነ ከመጠን ያለፈ ኃይል በመጠቀም “ዳኛው ከነበሩበት መኪና ገፍትረው በማውጣት እጆቻቸውን በሰንሰለት እንዲታሰሩ አድርገው ከፖሊስ መኪናቸው ከላንድክሩይሰሩ በስተኋላ በኩል ካለው መቀመጫ ላይ በመጣል ወንጀል በመስራታቸው የ10 ሚሊዮን ዶላር የህግ ክርክር ዶሴ ከፈቱ”፡፡

እ.ኤ.አ ጁላይ 2009 በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያላቸው የሀርቫርድ ፕሮፌሰር አፍሪካ-አሜሪካዊ ምሁር (እንዲሁም የፕሬዚዳንት ኦባማ ቅርብ ጓደኛ) የሆኑት ሄንሪ ስኪፕ ጌትስ በቁጥጥር ስር ውለዋል! አንድ የነጭ ጎረቤት የዓይን እማኝ ምስክርነቷን ለፖሊስ እንደሰጠችው ከሆነ ሁለት ጥቁር ወንዶች ከመግቢያ በር ላይ ጣራ ያለው መጠለያ ላይ ሆነው በጀርባቸው ሻንጣ መሳይ ነገር በመያዝ አንደኛው በኃይል በሩን ሰብሮ ለመግባት በትከሻው ሲገፋ ይታይ ነበር፡፡ ፖሊሶቹ በደረሱ ጊዜ ፕሮፌሰር ጌትስ በእራሳቸው ቤት ውስጥ ነበሩ፡፡ ፕሮፌሰሩ የእራሳቸውን የመኪና መንጃ ፈቃድ እና የሀርቫርድ ዩኒቨርስቲን መታወቂያ ካርድ ለፖሊሶቹ በመስጠት ፖሊሶቹ ስማቸውን እንዲነግሯቸው እና የባጅ ቁጥራቸውን እንዲነግሯቸው ጠየቋቸው፡፡ መረጃ ለመስጠት ተቃወሙ፡፡ ፕሮፌሰር ጌትስ ከፊት ለፊት ካለው የመውጫ በራቸው ሲረግጡ ከመቅጽበት ተይዘው እጆቻቸው በሰንሰለት ታስረው በጥበቃ ፖሊሶች መኪና ውስጥ እንዲቀመጡ ተደረጉ፡፡ ፕሮፌሰር ጌትስ “በጣም ከፍተኛ ድምጽ በማሰማት እና የሁከት እና ጫጫታ ባህሪ በማሳየታቸው” በሚል የውንጀላ ክስ ተመስርቶባቸው በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡ ያ ሁኔታ ፕሮፌሰር ጌትስ ወደ ኋይት ሀውስ ሄደው ከፕሬዚዳንት ኦባማ ጋር ተገናኝተው የውይይት ርዕሰ ጉዳይ በሆነ ጊዜ ወደ “ቢራ ጉባኤነት” ተቀየረ፡፡

አሜሪካ የእግር ኳስ ጀግኖችም እንኳ ከእነዚህ እምነትየለሽ ስሜታዊ ፖሊሶች ከለላ ሊያገኙ አይችሉም፡፡ እንደ 2013 “የአሜሪካ ዛሬ” ዘገባ 66 በመቶ የሚሆኑት ተጫዋቾች ጥቁሮች እና 31 በመቶ የሚሆኑት ተጫዋቾች ደግሞ ነጮች በሆኑበት ሁኔታ ጥቁር ተጫዋቾች ከነጮቹ ተጫዋቾች 10 ጊዜ በላይ በቁጥጥር ስር ይውላሉ (260 ለ28) ማለት ነው፡፡ እንደዚሁም በትራፊክ ማስቆም ጥቁሮቹ 88 በመቶ ያህሉን ይይዛሉ፡፡ ይህ ጥናት እ.ኤ.አ ከ2000 እስከ 2013 የተካሄደ ነው፡፡

እኔ በግሌ የዘር መድልኦ ፍረጃ ጥቃት ተደርጎብኛል፡፡ ይህም እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ነው፡፡ የዘር ፍረጃውም ያነጣጠረው እንዴት ጥቁር ዝርያ ሆኖ እንደዚህ ያለ ውድ መኪና ይይዛል የሚል ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ አንዳንዶቹ በጣም ውድ የሆነ የስፖርት መኪና የሚሉትን በሎስ አንጀለስ ከተማ በዋና የህዝብ መንገድ እነዳ ነበር፡፡ ከዚያም በአንድ የሎስ አንጀለስ የነጭ ዝርያ የሆነ የፖሊስ ኃላፊ እንድቆም ተጠየቅሁ፡፡ በቀጣይነትም የመንጃ ፈቃዴን እና የምዝገባ ቁጥሬን እንዳሳየው ጠየቀኝ፡፡ የተጠየቅሁትን ነገር ሁሉ አደረግሁ፡፡ ሁሉንም አይቶ ካረጋገጠ በኋላ የተመዘገብኩ የመኪናው ባለቤት መሆኔን ተገነዘበ፡፡ አንድን ሰው በቁጥጥር ስር ለማዋል በቂ መረጃ ስለመኖር አስፈላጊነት ትህትና በተቀላቀለበት ሁኔታ የውይይ መንፈስ በመክፈት ተሳታፊ እንዲሆን ለማድረግ ሞከርኩ፡፡ እርሱ ግን ፍላጎት አልነበረውም፡፡ እኔ ስህተት ሰርቸ እንደሆን እንዲነግረኝ ጠየቅሁት፡፡ ምንም ዓይነት ምላሽ አልሰጠም፡፡ በሎስ አንጀለስ ስላለው የመኪና ስርቆት በለሆሳስ ድምጽ ማጉተምተም ጀመረ፡፡ ነገሩን ማብራራት ግን አልፈለገም፡፡ ከዚያም የመንጃ ፈቃዴን እና የምዝገባ ቁጥሬን መለሰልኝ፡፡ እኔን እንዳደረገኝ ሁሉ የፖሊሱን ባጅ ቁጥር እና የጥበቃ መኪናውን የሰሌዳ ቁጥር መዝግቤ መያዝ አለብኝ የሚል ሀሳብ አሰብኩ፡፡ ፖሊሱ በጥበቃ መኪናው ውስጥ ገባ፡፡ እኔም መኪናዬን ነዳሁ፡፡ እስከተወሰነ ርቀት ድረስ ሲከተለኝ እንደነበረ በኋላ መስተዋት እመለከተው ነበር፡፡ በሁሉም ጉዳዮች ላይ ደስተኛ አልነበርኩም፡፡ የፖሊስ ኃላፊው እኔን አስቁሞ እኔ የመኪናው ህጋዊ ባለቤት ስለመሆን አለመሆኔ የመጠየቅ ህጋዊ መብት አልነበረውም፡፡ ከዘጠኝ ወራት በኋላ ጉዳዩን ከሎስ አንጀለስ ፖሊስ መምሪያ ጋር አጥጋቢ በሆነ ሁኔታ ፈታነው፡፡ በ1990ዎቹ ሌላ ከዚህ አነስ ያለ ጉዳይ ገጥሞኝ ከሎስ አንጀለስ ፖሊስ መምሪያ ጋር በመፍታት ይህንኑ ጉዳይ ለሎስ አንጀለስ መጽሔት አካፍየዋለሁ፡፡

ይህ ጉዳይ በሰዎች ላይ ደባ በመስራት የመደሰት ጉዳይ ነው፣ የእምነትየለሽ የፖሊስ ኃላፊዎች ሁለተኛ ደረጃ የጾታ ባህሪያት ግፊት ነው፣

ሁሉንም ነጭ ዝርያ ያላቸውን ዜጎች ሁሉ ዘረኛ ናቸው ብሎ በጥቅሉ መፈረጅ ፍትሀዊ እና አመክንዮአዊ አይደለም፡፡ የፖሊስ ስልጣንን ከህግ አግባብ ውጭ መጠቀም የማንኛውም የአንድ ዘር ጥቅል መብት አይደለም፡፡ እንደዚሁም ሁሉ በአሜሪካ በእያንዳንዱ የፖሊስ መምሪያ በሰዎች ላይ የተንኮል ደባ በመስራት የሚደሰቱ እና የሁለተኛ ደረጃ የጾታ ባህሪያትን የሚተገብሩ እምነትየለሽ ፖሊሶች በመሆን ህዝቡን ማገልገል እና መጠበቅ የሚለውን ዓለም አቀፋዊ የፖሊስ መፈክር ወደ አንድ ዓይነት ዝርያ በማዞር በተለይም በቆዳ ቀለም እየተመሩ የሚሰሩ የእኩይ ምግባር አራማጆች እንዳሉ የሚካድ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሁሉንም የፖሊስ ኃላፊዎች ጥላሸት መቀባት ኢሞራላዊ ነው፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ሁሉንም ወጣት ጥቁር ወንዶች ጥላሸት መቀባት ኢሞራላዊ ነው፡፡ ስለፖሊስ ኃይል አይደለም ጉዳዩ፣ ሆኖም ግን ስለህገመንግስታዊ መብት ጉዳይ ነው፡፡

የፖሊስ ኃላፊዎች ሰላምን ለማስከበር ጠንካራ እና አደገኛ የስራ ድርሻ እንዳላቸው ጥርጥር የለውም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ፖሊሶች ስራዎቻቸውን በሚሰሩበት ጊዜ እና ህጋዊ በሆነ መልክ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር በሚያውሉበት ጊዜ እንዲሁም የትራፊክ ጉዳዮችን በሚፈጽሙበት ጊዜ በሰዎች ዘንድ ይጠላሉ፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አደጋ በሚኖርበት ጊዜ ፖሊሶች የመጀመሪያ ደረጃ ተከላካይ እንዲሆኑ ይጠራሉ፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ፖሊሶች ሰላምን በሚያስከብሩበት ጊዜ የሚያገለግሉትን ማህበረሰብ በመነጠል እንደ ጦርነት ቀጣና  መቁጠር እየለዩ ወንጀለኞችን በእያንዳንዷ ቋጥኝ በመደበቅ እና ከወንጀለኞች ጋር ህብረትን በመፍጠር ንጹሀን ዜጎችን የሚያጠቁበት እና የሚገድሉበት ሁኔታ መፈጠር እንደሌለበት ከጥርጣሬ ውስጥ መግባት የለበትም፡፡ የፖሊስ ኃላፊዎቹ እራሳቸውን እንደታጣቂ አዳኝ መንገዶችን የሚጠብቁ ወይም ደግሞ እንደ አንድ በጦር መሳሪያ ኃይል አንድን አካባቢ እንደተቆጣጠረ ወራሪ ኃይል በመሆን ህዝቡን እያንገላቱ እና በዘር እየለዩ ጥቃት እየሰነዘሩ ህዝቡን እንጠብቃለን የሚለው አባባል ለፖሊስ መምሪያዎች የሚያስሄድ ዓላማ ሊሆን አይችልም፡፡

ህብረተሰቡ አመልካች ጣቱን ወደ ፖሊሶች በሚቀስርበት ጊዜ እና ፖሊሶች ዓመቱን ሙሉ ክፍት የሆነ የአደን ወቅት እንዳላቸው እና ህዝብን እያተራመሱ መሆናቸውን ካወጀ ቆም ብሎ ማሰብ እና ፈጣን የሆነ የመፍትሄ እርምጃ መውሰድ ተገቢ ነው፡፡ ፖሊሶች፣ ዳኞች እና ዓቃብያነ ህጎች  በህብረተሰቡ ላይ የቆዳ ቀለምን ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን ግንዛቤ ከወሰደ ህገመንግስቱን በመጥቀስ እና በመያዝ የተጠያቂነት ጉዳይን ማንሳት ነው፡፡ የሰላም ፖሊስ ጦርነትን በማወጅ ደባ እየሰራ በመደሰት ሰላምን በምንም ዓይነት መንገድ ሊያመጣ አይችልም፡፡

ለምንድን ነው ሁሉም በሚባል መልኩ በፖሊስ የተፈጸሙ ግድያዎች “ምክንያታዊ ግድያዎች” የሚባሉት ? ፖሊስ ዜጎችን ለመግደል ፈቃድ ተሰጥቶታልን?

ሁልጊዜ መርማሪ ግራንድ ጁሪ የፖሊስ ክስ መመስረትን ይቃወማል፣ (የክስ መጥሪያ እንዳይወጣ ይቃወማል) ወይም ደግሞ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ፍርድ ቤቶች ፖሊሶች በግድያ ወንጀል በደረሰባቸው ዜጎች ወገኖች ተከስሰው ወደ ፍርድ ቤት በሚቀርቡበት ጊዜ ምክንያታዊ ግድያዎች በማለት ታዕማኒነት የሌለው ምክንያት በመስጠት በነጻ ያሰናብቷቸዋል፡፡ ምክንያት የሚሰጣቸውምክንያታዊ ግድያዎች ብዙ ትርጉም ይኖራቸዋል፡ የፖሊስ ኃላፊው ሆን ብሎ አስቦ የፈጸመው ግድያ አይደለም ወይም ደግሞ ግድያው የተፈጸመው በድንገተኛ ሁኔታ ነው፣ የፖሊስ ኃላፊው ግድያውን የፈጸመው እራሱን ለመከላከል በወሰደው እርምጃ ነው ወይም ደግሞ ፖሊስ እንደ ፖሊስ ግድያውን የፈጸመው የስራ ኃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት በትክክለኛው የህግ ማዕቀፍ ስር የሚሰጥ ምክንያትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ነው የሚሉት ናቸው፡፡ ሆኖም ግን የጉዳዩ አስቸጋሪነት እውነታ በአጠቃላይ መልኩ ሲታይ በአብዛኛው የግድያ ወንጀል ጉዳዮች ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ እራስን የማጥፋት ወንጀል ነው በማለት ፖሊሶች ዜጎችን እየገደሉ ይቅርታ ይደረግላቸዋል፣ ወይም ደግሞ የግድያ ወንጀሎች በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ላሉ ፍርድ ቤቶች ሲቀርቡ ጉዳዩ ከታየ በኋላ በተመሳሳይ መልኩ እራስን ማጥፋት ወይም ሌላ ፖሊሶችን ነጻ ሊያደርጉ የሚችሉ ምክንያቶችን በመስጠት ፍትህን ይነፍጋሉ፡፡ ይሄ እንዴት ሊሆን ይችላል?

በቅርቡ የፌዴራል ቢሮ የምርመራ መረጃን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ፣ በፖሊስ ኃላፊዎች የተደረጉ ግድያዎችን ውስጣዊ ምዝገባ ለመመርመር እና በሀገሪቱ ውስጥ ከሚገኙት 110 ታላላቅ የፖሊስ መምሪያዎች ላይ የተያዙትን መረጃዎች ለማወቅ በዎል ስትሬት ጆርናል በተደረገ ጥናት መሰረት የሚከተለው ውጤት ታይቷል፡፡ በዎል ስትሬት የጥናት ውጤት ትንተና መሰረት እ.ኤ.አ ከ2007 እስከ 2012 በ105 የፖሊስ መምሪያዎች ቢያንስ 1,800 ዜጎች እንደተገደሉ እና ከእነዚህም ግድያዎች ውስጥ ወደ 45 በመቶ ወይም ደግሞ 1,242 የሚሆኑት እራስን ማጥፋት የሚል ምክንያት በእነዚህ ፖሊስ መምሪያዎች እንደሚገኝ ያመለክታል፡፡ ሁሉም በፖሊስ የሚፈጸሙ ግድያዎች ማለት ይቻላል በፖሊስ መምሪያዎች ወይም ደግሞ በሌሎች ስልጣን ባላቸው ተቋማት ፖሊስን ነጻ በሚያደርግ መልኩ ምክንያት ተፈብርኮ ይዘጋጅላቸዋል፡፡ እዚህ ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተፈጸሙት ግድያዎች የሚቀርበው ሁሉንም ያላካተተ ዝቅተኛ ብዛት በዚህ ስሌት ውስጥ እንደማይካተት ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ በዎል ስትሬት መጽሔት ከላይ በተጠቀሰው ጊዜ በተደረገው ትንታኔ መሰረት 753 የፖሊስ ተቋማት 2,400 በፖሊስ የተፈጸሙ ግድያዎችን ዘገባ አቅርበዋል፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ወደ 18,000 የሚሆኑ የመንግስት የህግ አስፈጸሚ አካላት ምንም ዓይነት ዘገባ አላቀረቡም፡፡

የእምነትየለሽ ፖሊስ ጸያፍ ባህሪ መጠንን ያለፈ ኃይል በመጠቀም እና እራስን በማጥፋት ተብሎ በሚሰጥ ሰበብ ብቻ የተወሰነ አይደለም፣

የእምነትየለሽ ፖሊስ ጸያፍ ባህሪ መጠንን ያለፈ ኃይል በመጠቀም ወይም ደግሞ ኃይል፣ ማሰቃየት፣ ማስፈራራት፣ በዘር መፈረጅ እና ሌሎች ዓይነት ስልጣንን ከህግ አግባብ ውጭ በመጠቀም ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ የእምነትየለሽ የፖሊስ ስልጣንን ከህግ አግባብ ውጭ መጠቀም እና ጸያፍ ባህሪ ማንጸባረቅ ሁሉንም ነገሮች ማለትም በሀሰት በቁጥጥር ስር ማዋልን፣ መደብደብ እና ተጠርጣሪዎችን ማሰቃየት፣ በፍርድ ቤት ቀርቦ በሀሰት መመስከርን፣ የተቀነባበረ ወይም የተፈበረከ የሀሰት ውንጀላ ክስ መመስረትን፣ የሀሰት የፖሊስ የምርመራ ውጤት ዘገባን ፋይል አድርጎ መያዝን፣ ተጠርጣሪዎችን ከሰሩት ስራ ውጭ ሌላ ስም በመስጠት መፈረጅ፣ ማስፈራራት፣ ከህግ አግባብ ውጭ ቃላት መጠቀም፣ በተጠርጣሪዎች ላይ በዘፈቀደ የነርቭ ስሜትን የሚረብሹ ሆርሞኖችን እና ኬሚካሎችን መጨመር፣ ህገወጥ ፍተሻ ማካሄድ፣ ከህግ አግባብ ውጭ ምርመራ ማካሄድ፣ ነጥሎ የህግ ተፈጻሚነትን መተግበርን እና ሌሎችንም ያካትታል፡፡

በ1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በካሊፎርኒያ ግዛት በወንጀል በሚጠረጠሩ ዜጎች ላይ ፖሊሶች ሲያካሂዷቸው በነበሩ አግባብነት የሌላቸው ጥያቄዎች ላይ ከፍተኛ የህግ ጥረት በማድረግ በተጠርጣሪዎች ላይ ሲፈጽሟቸው የነበሩትን የተንሰራፉ የፖሊስ ባህሪያት ፈር እንዲይዙ በማድረጌ ኩራት ይሰማኛል፡፡ እ.ኤ.አ በ1967 የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዩኤስ አሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን እና በጣም ታዋቂ የሆነውን የወንጀል ጉዳይ ቃለመጠይቅ በሚደረግበት ጊዜ ዝም የማለት መብትን በአሪዞና ምራንዳ በሚል ጉዳይ ላይ ወሰነ፡፡ በዚያ ጉዳይ ላይ ፍርድ ቤቱ ዝም የማለት መብት ህግ/Miranda rule የሚለውን ህግ አወጀ፡፡ ያ ህግ የፖሊስ ኃላፊዎች በቁጥጥር ስር ያዋሏቸውን ተጠርጣሪዎች የማማከር ወይም ደግሞ በእስር ቤት በቁጥጥር ስር ያሉ የህግ ታራሚዎች ለሚጠየቁት ጥያቄ መልስ ባለመስጠት ዝም የማለት ህገመንግስታዊ መብት እንዳላቸው (በፖሊስ ኃላፊው የሚጠየቁትን ማናቸውንም ዓይነት ጥያቄዎች ያለመመለስ ይችላሉ) እና በማንኛውም ቃለ መጠይቅ በሚደረግላቸው ጊዜ ፍርድ ቤቱ የመረጠላቸው የህግ ባለሙያ ሊመድብላቸው እንደሚገባ በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ ዝም የማለት መብትን በመከልክል ከተጠርጣሪው የተገኘ ማንኛውም ዓይነት እምነት በህግ አግባብ በፍርድ ቤት ተቀባይነት የለውም፡፡

እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ እና ከዚያ ቀደም ብሎም ቢሆን በካሊፎርኒያ የተወሰኑ የፖሊስ መምሪያዎች እና የዓቃቤ ህግ ቢሮዎች ለፖሊስ ኃላፊዎቻቸው ዝም ከማለት ውጭ የሚደረጉ ጥያቄዎችን/outside Miranda interrogation እየተባሉ ይጠሩ የነበሩትን ነገሮች የመተግበር ስራ ላይ እንዲሳተፉ ያበረታቱ ነበር፡፡ ያ ተሞክሮ በመሰረቱ በወንጀል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የዋለን ተጠርጣሪ በመጠየቅ ሂደት ዝም የማለት እና ያለመመለስ መብቱን ከተጠቀመ በኋላ በፖሊስ ለሚጠየቀው ጥያቄም ተጠርጣሪው የህግ ባለሙያ የመጠየቅ መብቱን በመጠቀም የሚደረግ የህግ አግባብ ሂደት ነው፡፡ ህገወጥ የጥያቄ ማቅረብ ሂደት የወንጀል ስርመሰረቱን መርምሮ ለማግኘት፣ ለግንዛቤ እና ቅጣት ለመጣል ያግዛል ተብሎ ይታመን ነበር፡፡ ዓቃብያነ ህጎች እና የፖሊስ መምሪያዎች በተጠርጣሪዎች ላይ ጥያቄዎችን በማቅረብ መጠየቅ እና የወንጀል ተጠርጣሪዎች ሊያምኑ እንደሚችሉ በመንገር መጠየቅን እንዲቀጥሉ ነግረዋቸዋል፡፡ ይህንንም ለማድረግ እንደ ምክንያት የሚያቀርቧቸው ነገሮች የሚከተሉት ናቸው፡ የዜጎችን ደህነነት የሚጻረሩ አደጋዎችን አስቀድሞ ለማምከን፣ የጦር መሳሪያዎችን እና መረጃዎችን ለማመላከት፣ ምስክሮችን ለመለየት፣ ስህተት እንዲሰራ የሚደግፉትን ጥላሸት ለመቀባት እና ለምርመራ የሚያግዙ መረጃዎችን ለማግኘት እንዲሁም ዋስትና ለመስጠት ይረዳሉ ብለው ያምናሉ፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ዝም ለማለት እና ጥያቄ ላለመመለስ እንዲሁም የህግ ባለሙያ እንዲመደብላቸው የሚፈልጉትን ተጠርጣሪዎች ፖሊሶች መጠየቅ እንዳለባቸው ተነግሯቸዋል፡፡ ምክንያቱም ይህ በመደረጉ በፍርድ ሂደቱ ጊዜ መካድ (በህግ ሂደቱ ወቅት ተካላካዩ አላደረግሁም ወይም አልፈጸምኩም ብሎ ቢክድ የፖሊስ ኃላፊው ይህንን ጉዳይ ለችሎቱ ለማስረዳት በማሰብ ተጠርጣሪው ቀደም ሲል በቁጥጥር ስር በዋለበት ጊዜ የተናገረው አሁን እዚህ ከችሎቱ ከተናገረው አንጻር ተጻራሪ ነው) ሊል ይችላል፡፡

አንድ የፈጣን ምግብ ቤት ስራ አስኪያጅ የሆነውን ሰው ፒቪ የሚባል ተጠርጣሪ ሁለተኛ ደረጃ የንብረት ዘረፋ ወንጀል በሚል ተከስሶ እኔ ለፒቪ ጠበቃ ሆኘ ነበር፡፡ በችሎት ሂደቱ ወቅት በቁጥጥር ስር ያዋለው ፖሊስ ተጠርጣሪው ፒቪ ዝም የማለት መብቱን እንዲጠቀም መክሮት እንደነበር ተናግሮ ፒቪ ግን (እኔ ከምናገር ይልቅ ጠበቃዬ እዚህ ይምጣለኝ አለ) በማለት መናገር እንዳልፈለገ ግልጽ ማድረጉን ለችሎቱ ግልጽ አድርጓል፡፡ የፖሊስ ኃላፊው ደንታው አይደለም፡፡ የፖሊስ ኃላፊው ስለሰራው ስህተት ከፒቪ ጋር በመወያየት ጥያቄዉን ቀጠለ፡፡ ስለወንጀሉ ፕቪ ጀመረ። የፖሊስ ኃላፊው ቀደም ሲል ከተሰጠው ስልጠና አኳያ ጥያቄ እያቀረበ ፒቪን መጠየቁን እንደሚያምነበት እና ፒቪ ክህደት በሚፈጽምባቸው ጉዳዮች ላይ መረጃ ለማግኘት ሲል የፒቪን ያለመናገር መብት መጣሱን እንደሚያውቅ ተናገረ፡፡ በዚህም መሰረት ተከላካዩ ቆሞ ይህንን ድርጊት እንዳልፈጸመ ለተሰየመው ችሎት አስረዳ፡፡ የተሰየመው ችሎት ፒቪ እራሱን ችሎ ተናግሯል ስለሆነም ፖሊሱ ፒቪ ላቀረበው ማስተባበያ መረጃ እንዲያቀርብ ተጠየቀ፡፡ ከዚህ በኋላ ፒቪ የሁለት ዓመታት እስራት ተበየነበት፡፡

በካሊፎርኒያ ከፍተኛው ፍርድ ቤት አቤቱታ ለማቅረብ ዋናው ጉዳይ በፖሊስ የተገኘ እምነት ሆን ተብሎ ወይም ደግሞ ታስቦበት ዝም የማለት መብትን በመጣስ የተገኘ ስለመሆኑ እና ወይም ደግሞ ተከላካዩን ስህተት እንደሰራ ለማስመሰል የተደረገ ነገር መሆኑን ከመገንዘብ ላይ ነው፡፡ (የካሊፎኒያን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስተያየት ሙሉ ቃሉን እዚህ ጋ በመጫን ማንበብ ይችላሉ)፡፡ ፍርድ ቤቱ በዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ዋና ዋና የህግ ጉዳዮች ላይ መሰረት በማድረግ፡ የሀሪስ ህግ (እ.ኤ.አ በ1971 የኒዮርክ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሀሪስ ቪ. በሚል ያጸደቀው ህግ) ምንም እንኳ ፖሊስ ተጠርጣሪዎች ያለመናገር ወይም ዝም የማለት መብት ቢኖራቸውም የተጠርጣሪውን ዝም የማለት እና የህግ አማካሪ ባለሙያ እንዲመደብለት የተሰጠውን መብት በመጣስ የፒቪን አቤቱታ ውድቅ አደረገው፡፡

ለሎስአንጀለስ ታይምስ ጋዜጣ በሰጠሁት ቃለምልልስ ላይ የተሰማኝን ጥልቅ ቅሬታ ገልጨ ነበር፡፡ በአጠቃላይ ፖሊስ በተጠርጣሪዎች ላይ ከህግ አግባብ ውጭ የሚያንጸባርቃቸውን መጥፎ ባህሪያት ከማረም ይልቅ እንዲሁ እየቀጠሉ እንዲሄዱ የመተው ሁኔታ ነው እየተስተዋለ ያለው፡፡ ይህ አካሄድ ፖሊሶች በስራ መስካቸው ተሰማርተው በሚሰሩበት ጊዜ በሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች ተጠርጣሪው ዝም የማለት መብቱን እንዳይጠቀም እና በማያምንበት ሁኔታ እምነት በመስጠት እንዲወነጅል ለማድረግ ፖሊሶች ሆን ብለው ያለመናገር መብትን እዲጥሱ የሚጋብዝ አካሄድ ነው፡፡ ይህንን ድርጊት ለማስቀረት በዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ  አስገብቻለሁ፡፡ የካሊፎርኒያ ዋና አቃቤ ህግ ለእኛ አቤቱታ ምላሽ እንዲሰጡ ከታዘዙ በኋላ ፍርድ ቤቱ የፍርድ ሂደቱን የማያሳዩ ሰነዶችን (ከፒቪ ጉዳይ ጋር የተያያዙ ሰነዶችን) ፒፕል ፒቪ፣ 17 ካል. 4ኛ 1184፣ ሰርት 525 ዩኤስ . 1042 (1968) መስጠት ከለከለ፡፡ ሆኖም ግን የአሜሪካ ህገመንግስታዊ መብት ከግላዊ ወንጃዮች እና አማካሪዎች የጥቃት ሰለባ እንዲድን ለማድረግ እራሳቸውን ባዘጋጁ ጥቂት የህግ ባለሙያ ቡድን አባላት አማካይነት የካሊፎርኒያ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ በመንገድ ላይ ያለ ትነሽ አንቀፋት ነበር፡፡ የእኛን የጦርነት አውድማ ተጠርጣሪዎች ከፖሊስ ሆን ተብሎ ወይም ደግሞ ታስቦበት ጥያቄ በሚቀርብላቸው ጊዜ ዝም የማለት መብት እንዳላቸው እንዲሁም አማካሪ የህግ ባለሙያ ሊመደብላቸው እንደሚገባ ወደሚሉት እና የፖሊስ ማንአለብኝነት ድርጊት እንዲያበቃ ወደሚለው እንዲዞር ለካሊፎርኒያ ግዛት ህግ አውጭ እና ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች እንዲቀርብ አደረግነው፡፡ ሌሎቹም በተመሳሳይ መልኩ በዩኤስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ትግላቸውን ቀጠሉ፡፡

የመጀመሪያው ተጠያቂዎች በሚጠየቁበት ጊዜ ዝም የማለት መብት እንዳላቸው ድል የተጎናጸፉት እ.ኤ.አ በ2000 በዲከርሰን ቪ. በዩናይትድ ስቴትስ፣ 530 ዩኤስ 428 ነው፡፡ በዲከርሰን በፖሊስ ጥያቄ ወቅት ዝም የማለት መብት ላይ ኮንግረሱ የተፋጨበት ክርክር ተደርጓል፡፡ በዲከርሰን ላይ የተደረገው ክርክር የፒቪን ጉዳይ መሰረት ያደረገ ነበር፡፡ በፖሊስ ጥያቄ ወቅት ዝም የማለት ዓላማ መሰረቱ የዩኤስ ህገመንግስት ዝም የማለት መብት ማስጠንቀቂያ ባለመሆኑ ነው፣ ሆኖም ግን ዝም ብሎ በደፈናው በህጉ ፖሊሲ ላይ ተቀምጧል፡፡ በሌላ አባባል በፖሊስ ጥያቄ ወቅት ዝም የማለት መብት ህገመንግስታዊ መብት ነው ወይስ ዳኛ የፈጠረው ድነጋጌ ነው?

ዋና የፍትህ ኃላፊ የሆኑት ዊሊያም ሬንኩይስት በፖሊስ ጥያቄ ወቅት ዝም የማለት መብት ህግ የዳኛ ህግ ነው የሚለውን ሀሳብ በትችት ሸንቁጠውታል፡፡ ሬንኩይስት ዉሳነአቸው ላይ ሀሳባቸውን ሲያጠናክሩም እንዲህ ብለዋል፣ “በፖሊስ ጥያቄ ሲቀርብ ዝም የማለት መብት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ህገመንግስታዊ ውሳኔ ነው፣ እናም እንደዚህ ያለ ውሳኔ በኮንግረስ በሚተላለፍ ውሳኔ ሊሻር አይችልም“፡፡ የክርክር ጭብጣቸውን በመቀጠል እንዲህ ብለዋል፣ “ግልጽ ሆነው የተቀመጡትን መርሆዎች እንደገና ከመሻር በላይ ዋጋን ያስከፍላሉ…“ በፖሊስ ጥያቄ ጊዜ ዝም የማለት መብት በፖሊስ የዕለት ከዕለት ተግባራት ውስጥ በመታቀፍ የእነርሱ ማስጠንቀቂያዎች የብሄራዊ ባህላችን አንዱ ገጽታ ሆኗል በማለት ጠቁመዋል፡፡ በዲከርሰን የተፈጠረው በፖሊስ ጥያቄ ሲቀርብ ዝም የማለት መብት ህገመንግስታዊ ህግ ነው!

እ.ኤ.አ በ2000 የካሊፎርኒያ የወንጀል ፍትህ ዓቃብያነ ህጎች፣ 9ኛው ሰርኩይት የዩኤስ ፍርድ ቤቶች ይግባኝ ሰሚ ችሎት ከፖሊስ ጥያቄ በሚነሳበት ጊዜ ዝም የማለት መብትን በሚጥሱ ፖሊሶች እና ተጠርጣሪዎችን አስገድደው እምነትን እንዲሰጡ የሚያደርጉ ፖሊሶች ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ዝም የማለት መብትን በመጣስ የሚደረግ ጥያቄ ሁሉ ተክክለኛ እና ህጉን አክብሮ ሲሰራ የቆዬን ዳኛ ህገወጥ ነው እንደማለት ይቆጠራል፡፡ ፍርድ ቤቱ እንዲህ በማለት አውጇል፣ “የፖሊስ ኃላፊዎች በፖሊስ ጥያቄ ወቅት ሆን ብለው ዝም የማለት መብትን በመጣስ የሚቀጥሉበት ከሆነ ከህዝብ የሚነሳባቸውን ተቃውሞ መከላከል መቻል አለባቸው“ በሌላ አባባል የፖሊስ ኃላፊዎች ህዝብን በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ ሁሉ እንደ ሲቪል ሰው በመሆን የእራሳቸውን አቅም ባገናዘበ መልኩ ማገልገል እንጅ በሲቪል ጉዳዮች ላይ እንደ ፖሊስ ኃላፊነት የስልጣን ቦታ ሆነው ህዝብን በመጉዳት የጥቃት ሰለባ ቢፈጽሙ በግል ሊከሰሱ ይችላሉ፡፡

እ.ኤ.አ ማርች 2001 የካሊፎርኒያ ስቴት ሴናተር የሆኑት ግሎሪያ ሮሜሮ  “የሰላም ኃላፊዎች የሀሪስ ቪ. የኒዮርክ (1971) 401 ዩኤስ. 222 እና ፒፕል ቨ. ፒቪ (1998) 17 ካል. 4ኛ 1184 መሰረት ስልጠና ማግኘት አለባቸው፣ በእስር ቤት የሚገኙ ተጠርጣሪ አንድ ጊዜ ዝም የማለት መብት እንዳለው ጥያቄ ካቀረበ ወይም ደግሞ አማካሪ ሊሆነው የሚችል የህግ ባለሙያ እንዲመደብለት ከጠየቀ በኋላ ይህንን ጉዳይ ከምንም ባለመቁጠር ፖሊስ ጥያቄ እያቀረበ ምርመራውን መቀጠል የለበትም…“ የሚለውን የሴኔት ቢል 1211 የሆነውን አቅርበዋል፡፡

እ.ኤ.አ በ2003 በፒፕል ቪ. ኒያል የካሊፎርኒያ ግዛት ከፍተኛው ፍርድ ቤት በፒቪ ላይ ይዘነው የነበረውን ዋነኛ የመከራከሪያ ጭብጥ አጸደቀው፡፡ ፍርድ ቤቱ እንዲህ የሚል ውሳኔ አስፍሮ ነበር፣ “…እነዚያ እምነቶች በፒፕልስ ጉዳይ የሚፈቀዱላቸው አልነበሩም ብለን ብቻ ድምዳሜ አንሰጥም ምክንያቱም የኤድዋርድን ህግ በመጣስ የተገኙ ስለሆኑ ብቻ አይደለም ሆኖም ግን ለማንኛውም ነገር መፈቀድ የሌለባቸው ተግባራት ስለሆኑ ነው፣ ምክንያቱም መብትን በጣሰ መልኩ አስገዳጅ ስለሆኑ ብቻ ነው፡፡ የፖሊስ ኃላፊው መጥፎ ባህሪ ውጤት ማለትም በችሎት ሂደቱ ወቅት ፍጹም የሆነውን እና የማያስገድደውን የእምነት መቀበል ስራ መስራት ያለመቻል እና ሌሎች ፖሊሶች ለወደፊቱ ከዚህ ዓይነት ድርጊት እንዲታቀቡ ማድረግ ያለመቻል“ ናቸው፡፡

ከዚህ በኋላ ወዴት ነው የምንሄደውየግልጽነት እና የህግ ተጠያቂነት አስፈላጊነት ለእምነትየለሽ የፖሊስ ኃላፊዎች፣

ስለፖሊሲ አድልኦዎች፣ ስለዘር ፍረጃ፣ ከመጠን ያለፈ ኃይልን ስለመጠቀም እና ስለመሳሰሉት በርካታ የኑ የፖሊሲ ጥናቶች አሉ፡፡ በፖሊስ መምሪያዎች እና በህብረተሰቡ መካከል የተንሰራፋውን የዘረኝነት ውጥረት፣ አመጾችን  እና የንብረት ውድመትን  ለመከላከል፣ የፖሊስ ኃላፊዎችን ደህንነት ለማሻሻል፣ በአሁኑ ጊዜ ህዝቡ በፖሊሶች ላይ ስላለው አጠቃላይ ግንዛቤ እና የህዝቡን ግንኙነት ለማሻሻል ባለው ሁኔታ ላይ የባለሙያዎች የሀሳብ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ብዙ ባለሙያዎች የህብረሰብ ፖሊስ መኖርን እንደጥሩ መፍትሄ አድርገው ሀሳብ ይሰጣሉ (በህግ  አስፈጻሚው አካላት እና በማህበረሰብ መሪዎች እንዲሁም በድርጅቶች መካከል ትብብራዊ አጋርነት እንዲኖር ማድረግ ውጤታማ መፍትሄን በማምጣት በፖሊስ ላይ ታማኝነትን ይጨምራል) እንዲሁም ስልጠና በተለይም ለፖሊስ ኃላፊዎች በጣም ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ስልጠናዎችን በመስጠት ለማሻሻል ይቻላል፡፡ አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት ፖሊስ የሰላም ጠበቃ እንጅ ወታደራዊ ኃይል መሆን የለበትም፡፡ ወታደራዊ ትጥቅን መፍታት አለባቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ ሰዎች እንደሚያቀርቡት ሀሳብ ከሆነ ፖሊሶች ከሰውነታቸው ጋር የተያያዘ ካሜራ ተገጥሞ ሊንቀሳቀሱ ይገባል የሚል ሀሳብ አላቸው ምክንያቱም ካሜራው ካለ በየአጋጣሚው የሚያደርጉትን ከህግ አግባብ ውጭ የሚሰሩ ስራዎችን በማጋለጥ በማስረጃነት ስለሚያገለግል ነው፡፡ እነዚህ ሀሳቦች በሙሉ እና ሌሎች ሀሳቦችም ሊያሰሩ የሚችሉ፣ ምክንያታዊ እና ጠቃሚ የሆኑ ለውጦችን በማምጣት ከህግ አግባብ ውጭ የሚፈጸሙትን የፖሊስ ስልጣንን  በመቀነስ ጠቃሚ ሚናን ይጫወታሉ፡፡

የእኔ ግላዊ እይታ ፖሊስ ከህግ አግባብ ውጭ ስልጣኑን የመጠቀም እና መጥፎ ባህሪያትን እያንጸባረቀ የመሆኑ ጉዳይ መዋቅራዊ ችግር እንደሆነ እና በእምነትየለሽ ፖሊሶች እየከፋ እንደመጣ እገነዘባለሁ፡፡ በሌላ አገላለጽ የፖሊስ መምሪያዎች እና የአካባቢ መንግስት አመራሮች ግልጽ ባልሆነ መልኩ የህግ አስፈጻሚ በተለይም በቆዳ ቀለም ላይ ትኩረት አድርጎ በመስራት ረገድ የሚታየውን መጥፎ ሁኔታ ዝም ብሎ በመመልከት ታጋሽነታቸውን አብዝተዋል፡፡ ከህግ አግባብ ውጭ የሚደረጉ የፖሊስ ስራዎች ከፖሊስ ጸጥ የማለት ባህል ጋር ተዳምረው በፖሊስ እና በአካባቢው የፖለቲካ አመራሮች ቀጥተኛ የሆነ እና ወሳኝ የሆኑ ድርጊቶች ካልተከናወኑ በስተቀር በህብረተሰቡ እና በፖሊስ የቆዳ ቀለም ማጣራት ስራ ግንኙነት ላይ ችግር በመፍጠር እውነተኛ ለውጥ ይመጣል የሚል እምነት የለም፡፡

ይህንን ጉዳይ በማስመልከት የእኔ አዲስ ሀሳቦች ለየት ያሉ እና ሶስት ናቸው፡፡ የ9ኛው ዙር የካሊፎርኒያ የወንጀለኛ ፍትህ ጠበቆች እንዲህ የሚል የህግ ወይም ደግሞ የዳኝነት ተግባር ሊኖር ይገባል፣ “የፖሊስ ኃላፊዎች ሆን ብለው አስበውበት የዕለት ከዕለት ተግባራቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ የህዝቦችን መብት ሲደፈጥጡት ለዚህ ወንጀላቸው በግል ሊከሰሱ ይቻላል ብለዋል”።  በሌላ አባባል የህዝቦችን መብት ሆን ብለው እና አስበውበት በሚደፈጥጡ ፖሊሶች ላይ ባላቸው በእራሳቸው አቅም ብቻ እንጅ እንደ ፖሊስ ባልደረባነት አይጠየቁም፡፡ ለዚህም ለሰሩት ወንጀል እና ላወደሙት ንብረት ከእራሳቸው ኪስ እንዲከፍሉ ቢደረግ የተሻለ ነው!

አንደኛ ወንጀለኛ የፖሊስ ኃላፊዎችን ጥፋት ለምን ግብር ከፋዩ ህዝብ ሊከፍልላቸው እንደሚችል አሳማኝ ምክንያት የለም፡፡ ፖሊስ ከህግ አግባብ ውጭ ለሚያደርሰው ጥፋት በግብር ከፋዩ የሚከፈለው ክፍያ እጅግ በጣም ግዙፍ ነው፡፡ ባለፉት አስርት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከጭካኔነት ጋር የተዛመዱ የህግ ሂደቶች ለችጋጎ ግብር ከፋዮች 521 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፈል አድርጓል፡፡ እ.ኤ.አ በ2013 ብቻ የችጋጎ ከተማ 84.6 ሚሊዮን ዶላር ለዕርቅ፣ ለዳኝነት፣ ለህግ አገልግሎት እና ለሌሎች ወጭዎች በማስወጣት ለዚህ ጉዳይ ተይዞ ከነበረው በጀት ሶስት ጊዜ እጥፍ ክፍያ ተፈጽሟል፡፡ እ.ኤ.አ በ2011 ኒውዮርክ አስደንጋጭ የሆነ 735 ሚሊዮን ዶላር ከህግ አግባብ ውጭ ፖሊስ ላደረሰው ጥፋት እና ለሌሎች ወጭ ሆኖ ተከፍሏል፡፡ ባለፉት አስርት ዓመታት በሌሎች ከተሞች ማለትም ባልቲሞርን፣ ኒውዮርክን፣ ዳህላስን፣ ዴንቨርን፣ ክሊቬላንድን እና ሌሎችን ጨምሮ ፖሊስ ከህግ አግባብ ውጭ በሚያደርጋቸው ጥፋቶች ምክንያት በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እንዲከፍል አድርጓል፡፡

ሁለተኛ የመንግስት ህጎች ጭካኔን በተሞላበት መልኩ በህዝቦች ላይ በደል የሚያደርሱትን  ፖሊሶች እና የሚያሳዩትን ባህሪ በመገንዘብ ከህዝቡ በኩል እርምጃ ለመውሰድ እና የተመዘገበ ፋይል በፖሊሶች ላይ ለመያዝ እንዲያስችል ግልጽ የሚያደርግ ህግ ለሲቪሉ ማህበረሰብ ማቅረብ አስፈላጊ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህልም በካሊፎርኒያ የመከላከል የህግ ባለሙያዎች አብዛኛውን ጊዜ “የፒቼስ ሕግ ማዘጅያ/Pitchess motion” (የካሊፎርኒያ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ጉዳይ በፒቼስ እና በሱፔሪየር ፍርድ ቤት መካከል ባለው (1974)) በመባል የሚጠራው ይታወቃል፡፡ እነዚህ የህግ ባለሙያዎች ከመጠን ያለፈ ኃይል መጠቀምን፣ በዘር መፈረጅን፣ በግዳጅ እምነት መቀበልን እና በፖሊስ ዘገባ ላይ እምነት ያለመኖር እና የመሳሰሉትን ጨምሮ ፖሊስ  ከህግ እግባብ ውጭ ወይም መጥፎ የፖሊስ ምግባር ምክንያት ደንበኛቸው የጥቃት ሰለባ ሆኗል ብለው ካሰቡ እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋሉ፡፡ ሆኖም ግን ፍርድ ቤቶች እና የፖሊስ መምሪያዎች የፒቼስን እንቅስቃሴ ከፖሊሱ የግል ማህደር በጣም ጥቂት ጠቀሜታ ያላቸው መረጃዎች ብቻ እንዲቀመጡ እና ለጥቃት ሰለባው እንዲገለጹ በመፍቀድ አሰራሩን እንዲጠብ አድርጎታል፡፡ የፖሊስ መምሪያዎች አብዛኛውን ጊዜ የፖሊሶችን መጥፎ ባህሪያት የሚገልጹትን የተመዘገቡ መረጃዎች ከ5 ዓመታት በኋላ ያስወግዷቸዋል፡፡

ሶስተኛ የፖሊስ መምሪያዎች ውስጣዊ የስነስርዓት አካሄዶች ማጥበቅ እና ከፍተኛ የሆኑ የሙያ እና የስምግባር መስፈርቶችን የሚያሟሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ከፍተኛ የሆነ የስነምግባር ጥሰት የፈጸሙ የፖሊስ ኃላፊዎች ማዕቀብ ሊደረግባቸው እና እንዲያውም ክስ ቢመሰረትባቸውም ባይመሰረትባቸውም ከስራ ሊባረሩ ይገባል፡፡ ሁሉም ሙያዎች አባሎቻቸውን የወንጀል ተግባራት ያልሆኑትን ማለትም ታማኝ ያለመሆን፣ ከስነምግባር ውጭ መሆንን ወይም ደግም ሙያዊ ያልሆኑ የማታለል፣ የማጭበርበር ወይም በህዝቡ ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ተግባራትን ሲፈጽሙ ሊታቀቡ እና ከአባልነትም ሊወገዱ የሚችሉበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት፡፡ እንደዚሁም ሁሉ የፖሊስ ኃላፊዎች ተመሳሳይ የስነምግባር እና የሞራል መስፈርት ሊኖራቸው ይገባል፡፡

ለመተንፈስ አልችልምለመተንፈስ አንችልም…” 

በዚህ ትችት ላይ በተደጋጋሚ እንደገለጽኩት ሁሉም የነጭ ዝርያ ያላቸው ፖሊሶች ዘረኛ ናቸው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አፍሪካ አሜሪካዊ፣ የእስፓኒሽ  እና የኢስያ ዝርያ ያላቸው በፖሊስ ሙያ ላይ የተሰማሩ የፖሊስ ኃላፊዎች የተበላሸ የፖሊስ ባህሪ ያለቸው ወይም ደግሞ ስልጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጭ ይጠቀማሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሁሉም ሙያዎች የእራሳቸው መጥፎ ተጽዕኖዎች አሏቸው፡፡ መጥፎ የህግ ባለሙያዎች፣ ዶክተሮች፣ ኢንጂነሮች፣ ወዘተ አሉ፡፡ የፖሊስ መምሪያዎች የአሜሪካንን ግዙፍ ህዝብ የሚወክሉ ትንሽ ተቋማት ናቸው፡፡ የግዙፍን ህዝብ ችግሮች እና ድክመቶች የሚያንጸባርቁ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን በአሜሪካ የህግ ማስፈጸም ሂደት ላይ እውነተኛ የሆኑ የዘረኝነት ጉዳዮች ይታያሉ፡፡ 

ባለፈው ሳምንት የኒዮርክ ታይምስ አምደኛ የሆኑው ኒክ ክሪስቶፍ እንዲህ የሚል ምልከታን አድርጓል፣ “ነጭ አሜሪካውያን/ት የእኛ የዘር መድልኦ እንደ ደቡብ አፍሪካ አይደለም በማለት ሊቃወሙ ይችላሉ፡፡ አይደለም፣ ሆኖም ግን ዩናይትድ ስቴትስ በመጠን ከደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ የበለጠ እስረኞችን አስራ ትገኛለች፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካ ውስጥ የጥቁር-ነጭ ኃብት ልዩነት እ.ኤ.አ በ1970 በደቡብ አፍሪካ ከነበረው አፓርታይድ የበለጠ ሆኗል፡፡ “

ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የወንጀል መከላከል የህግ ተሞክሮ ውስጥ የፖሊስ ኃላፊ መሆን ያልነበረባቸው ጥቂት ሰዎች ወይም ደግሞ ምንም ዓይነት የህግ ማስፈጸም ተግባራትን ከሚያከናውኑ ተቋማት ጋር መቀላቀል ያልነበረባቸው ሰዎች እንዳሉ ግንዛቤ ወስጃለሁ፡፡ በዩኤስ አሜሪካ የፖሊስ ኃይል ውስጥ ባጅ የለበሱ ብቻ ሳይሆን በትከሻቸው ላይ ዱላ የሚይዙ ሰዎችም አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች የተባሳጩ እና  በጥላቻ የተሞሉ ግለሰቦች እና በዓለም ላይ የሚንገላወዱ እብዶች ናቸው፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ፖሊስ ለመሆን መልካም ባህሪ፣ ብስለት እና የዓዕምሮ መረጋጋት ይጎድላቸዋል፡፡ በፖሊስ መምሪያው ያላቸው የእነርሱ አባልነት እይታ የሰላም አስከባሪ ፖሊስ መሆን አይደለም ሆኖም ግን ማንኛውንም የሚፈልጉትን ሰው ለመደብደብ፣ በማንም ላይ ለመተኮስ እና ለመግደል ፈቃድ ያለው ህጋዊ ወሮበላ ማለት ነው፡፡ በደረታቸው ላይ የለጠፉትን ባጅ ያለምንም ተጠያቂነት ዜጎችን ለመግደል እና ከህግ አግባብ ውጭ መብታቸውን ለመርገጥ የሚያስችል ፈቃድ አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ ከህንጻው ጀርባ በድብቅ ተቀምጠው ወንጀሎችን ይሰራሉ፡፡ ለማንም ተጠያቂ እንደማይሆኑ እምነት እያሳደሩ መጥተዋል፡፡ ወንጀል ቢሰሩ በጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደማይከሰሱ ወይም ደግሞ በህግ ተይዘው የችሎት ሂደት እንደማይጎበኛቸው ያውቃሉ፡፡ ምንም ዓይነት ወንጀል ቢሰሩ ከፖሊስ ቦርድ ፊት ቀርበው የስነስርዓት ጉድለት እርምጃ እንደማይወሰድባቸው ያውቃሉ፡፡ በእርግጥ እነርሱ በህጉ መሰረት ህዝቡን ማገልገል ሳይሆን እራሳቸውን ከህጉ በላይ ያስቀመጡ እብሪተኞች ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ማሰቃየት፣ ማስፈራራት፣ አድልኦ መፈጸም፣ በሀሰት ዜጎችን በቁጥጥር ስር የማዋል፣ ስልጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጭ መጠቀም ያለምንም ፍርኃት እና እቀባ እንዲሁም ሌላ ቅጣት መፈጸም እንደሚችሉ እምነት አዳብረዋል፡፡ የእምነትየለሽ ፖሊስ ኃላፊዎች ሆነዋል፡፡

እምነትየለሽ የፖሊስ ኃላፊዎች ቁስ አካል እና መንፈስ በሚል ለያይቶ በሚያየው ባህል እና አስተሳሰብ ውስጥ ሲዘፈቁ ጥሩ ሰዎች፣ መጥፎ ሰዎች እያሉ ሲለያዩ ነገሮች ሁሉ ወደ መጥፎው የዜጎች የቀለም ምርጫ መግባት ይመጣል፡፡ እምነትየለሽ የፖሊስ ኃላፊዎች  እራሳቸውን እንደ ህዝብ እና እንደያንዳንዱ ሰው በተለይም የቆዳ ቀለም ጠባቂ መልዓክ አድርገው ይቆጥራሉ፡፡ የእነርሱ ትንሹ ዓለም የጥሩ እና የጭራቃዊነት የጦርነት አውድማ ይሆናል፡፡ የቱንም ያህል መስዋዕትነት ያስከፍል አንድ ላይ መሆን አለባቸው፡፡ በእራሳቸው እና በእያንዳንዳቸው ብቻ ላይ ነው እምነት ያላቸው፡፡ ስህተት ከሰሩ እንዳልሰሩ ሆኖ ይሸፈንላቸዋል፡፡ በጸጥታ ድባብ ውስጥ አንዲያልፍ ሆኖ ነጻ ይሆናሉ፡፡

የፖሊስ መንግስትየፖሊስ ከተማ?

የአሜሪካ ዜጋ መሆን ትልቁ ክብር ህይወት ባላቸው እና በሚተነፍሱ የሰብአዊ መብት ጥበቃ የደህንነት ዋስትና ማግኘት ነው፡፡ የእምነትየለሽ ፖሊሶች ስልጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጭ በመጠቀማቸው እና ዜጎችን በመጥፎ ሁኔታ እያስተናገዱ በመሆናቸው ምክንያት የብዙ አፍሪካ አሜሪካውያን ዜጎች መብቶች መጣሳቸውን በቀላሉ ማየት ይቻላል፡፡ ይህንን እኩይ ምግባር ለማጥፋት እና መብቱን ከእምነትየለሽ ፖሊሶች መጠበቅ የእያንዳንዱ ሰው ኃላፊነት እና በጣም ታላቅ ድል ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1837 የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት አንድሪው ጃክሰን ከስልጣን መንበራቸው በተሰናበቱበት ዕለት የሚከተለውን የስንብት ንግግር አድርገው ነበር፣ “… በህዝቡ የሚደረግ ዘላለማዊ ጥበቃ የነጻነት ዋጋ ነው፣ ስለሆነም በረከቱን ለማግኘት የምትፈልጉ ከሆነ ዋጋውን መክፈል አለባችሁ“፡፡ እንደ አሜሪካዊ ዜግነታችን በህገመንግስቱ መግቢያ ላይ በግልጽ እንደተመለከተው በየቀኑ ለነጻነታችን ማንኛውንም መስዋዕትነት የሚጠይቅ ትግል በማድረግ የሚፈለገውን ዋጋ ለእራሳችን እና ለመጭው ትውልድ መክፈል አለብን፡፡

ፍሬደሪክ ዳጉላስ በአሜሪካ የመጀመሪያው ባሪያ እና በኋላም የጸረ ባሪያ አቋም አራማጅ የነበሩት እንዲህ የሚል ተመሳሳይ ጩኸትን አሰምተው ነበር፣ “የጨቋኞች የመጨቆን ደረጃ የሚወሰነው በሚጨቁኗቸው ህዝቦች የመጨቆን ጽናት ነው… ምንም ዓይነት ትግል ከሌለ ምንም ዓይነት እድገት አይኖርም፡፡ ነጻነትን ለመጎናጸፍ የሚመኙ እና ሆኖም ግን ነጻነት የሚያስገኘውን የቅስቀሳ ስራ የማይሰሩ ሰዎች መሬቱን ሳይርሱ እህል ማፈስን እንደሚልጉ ገበሬዎች ማለት ነው፡፡ መብረቅ እና ፍልቅታ ሳይኖር ዝናብ ማግኘትን ይፈልጋሉ፣ የብዙ ውሀዎችን አስፈሪ ድንፋታ እና ጩኸት ሳይሰሙ ውቅያኖስ ማግኘትን ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ትግል የሞራል ሊሆን ይችላል ወይም ደግሞ የአካል ትግል ሊሆን ይችላል፣ አለዚያም ደግሞ የሁለቱም የሞራል እና የአካል ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ትግል መሆን አለበት፡፡ ስልጣን ያለ ጥያቄ ምንም ነገር አይሰጥም፡፡ ሆኖም አያውቅም፣ ወደፊትም ሊሆን አይችልም“፡፡

ሁሉም አሜሪካውያን/ ጭራቀዊነትን ለመግደል እጅ ለእጅ መያያዝ አለባቸው፣

ፖሊስ ዳረን ዊልሰን በጠቅላይ ፍርድ ቤት ተገኝቶ በሰጠው የምስክርነት ቃል የወጣቱን ሚካኤል ብራውንን ፊት በተመለከተው ጊዜ “ጭራቅ መስሎ እንደታየው” አስረድቷ፡፡ ከጥበቃ መኪናው በሚወጣበት ጊዜ እና በደርዘን የሚቆጠሩ ጥይቶችን በተኮሰበት ጊዜ ክቡር በሆነው በሰው ልጅ ህይወት ላይ ሳይሆን በጥቁር ጭራቅ ላይ እንደተኮሰ ማመን አለበት፡፡ የፖሊስ ኃላፊ ዊልሰን የሚካኤል ብራውንን ፊት ሲመለከት ጭራቅ መስሎ እንደታየው ሁሉ ሌላም ጭራቅ መመልከት አለበት፣ “ነጭ ጭራቅ”::

አሳዛኙ ድርጊት ግን በፖሊስ ዊልሰን እና በሚካኤል ብራውን መካከል እውነተኛ ሆኖም ግን የማይታይ የቆመ ጭራቅ አለ፡፡ ምንም ዓይነት ቀለም፣ ፊት እና ዘር የሌለው ጭራቅ ነው፡፡ የዘርኝነት፣ የጥላቻ፣ ስልጣንን ከህግ አግባብ ውጭ የመጠቀም እና ጨካኝነትን የሚታገስ የፖሊስ ባህል ጭራቅ ነበር፡፡ ያ ጭራቅ የአሜሪካንን ነጻነት የሚያስፈራራ ጭራቅ ነው፡፡ ለዚህም ነው ሁሉም አሜሪካውያን/ት እጆቻቸውን ተጨባብጠው ይህንን እርኩስ ጭራቅ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ ያለባቸው፡፡

ኃይል ፍትህን ወይም ደግሞ ሰላምን አያመጣም፡፡ ኃይል ሌላ ኃይልን ይወልዳል፡፡ ጥቂት እምነትየለሽ የፖሊስ ኃላፊዎች የፖሊስ ስልጣን ከጠብመንጃ አፈሙዝ የተገኘ ይመስላቸዋል፡፡ የጠብመንጃ የበላይነት ህግ በህግ የበላይነት መተካት አለበት፡፡ በአንድ በተበሳጨ፣ ተስፋ በቆረጠ እና ደህንነት በማይሰማው የፖሊስ ኃላፊ እጅ ያለ ጠብመንጃ በማንኛውም ጊዜ ሊፈነዳ የሚችል የጊዜ ቦንብ ነው፡፡

ፖሊስ ዳረን ዊልሰን እ.ኤ.አ ኦገስት 9/2014 ጧት ከመኝታው ሲነሳ ሚካኤል ብራውንን እገለዋለሁ የሚል ዕቅድ ነበረው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሆኖም ግን ዳረን ዊልሰን እርሱን ለመግደል ለዓመታት የታመቀ የአዕምሮ ዝግጀት ሲያደርግ እንደቆየ እምነት አለኝ፡፡ ፖሊስ ዊልሰን በነጮች ኃላፊዎች እና በጥቁር ኗሪዎች መካከል በዘረኝነት ጥላቻ ከታወረች እና የከተማው ማዘጋጃ ቤት ሁሉንም ኃይል አስወግዶ አዲስ በገነባው ጀኒንግስ ሞ. ከሚባለው አካባቢ ከትንሽ የፖሊስ መምሪያ የመጣ ሰው ነው፡፡ ፖሊስ ዊልሰን የዚህን ጉዳይ ወደ ፈርግሰን ሚሶሪ ይዞት መጣ፡፡ 

የፖሊስ ኃይል፣ የፖሊስ ስልጣን፣ የሰላም ፖሊሶች፣ ሰላም ጠባቂዎች፣

አብዛኞቹ ፖሊስ ለመሆን የሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ሰዎችን ሁሉ ለማሰቃየት እና በዜጎች ላይ ስልጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጭ ይጠቀማሉ ብሎ ማመን የተሳሳተ አመለካከት ነው፡፡ አንዳንዶቹ ወደ ፖሊስ የስራ መስክ የሚሰማሩት ባለው ስልጣን ቋምጠው እና ለስራው ካለው የስራ ደረጃ አንጻር ነው፡፡ አደጋ ካንዣበበት እና ውጥረትን ከሚስብ የፖሊስ ሙያ አብዛኞቹ የፖሊስ አባላት ለህዝቡ ደህንነት እና ሰላም ሲሉ ህዝቡን ለማገዝ በጥሩ መንፈስ ይሰራሉ፡፡

እንደአጋጣሚ ሆኖ የፖሊስ ስልጣን እንደ ሌሎች በሰዎች እንደሚዘወሩ ስልጣኖች ሁሉ በጣም በጠበቀ መልኩ ከሙስና ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ማንም የፖሊስ ኃላፊ ለማንም ተጠያቂነት እንደሌለው የሚያምን ከሆነ እራሱን ኃይለኛ እና የማይበገር አድርጎ በመቁጠር በቀጣይነት ወደተሳሳተ አቅጣጫ በመመራት ባልተሰጠው ስልጣን ላይ በመመካት ሰዎችን ከህግ አግባብ ውጭ ማዋል ሊጀምር ይችላል፡፡ መለዮ በመልበሱ እና የሚያብለጨልጭ ባጅ በደረቱ ላይ በመለጠፉ ምክንያት የህዝብ ከበሬታ እና ታማኝነትን ያገኘ መስሎ ስለሚታየው ሰዎችን ማዘዝ እና ከተሰጠው ስልጣን ውጭ በቁጥጥር ስር ማዋል ይጀምራል፡፡

ጠባቂውን ፖሊስ የሚጠብቀው ፖሊስ ማን ነው? ህገመንግስቱ በሚፈልገው መሰረት እያንዳንዱ/ዷ ፖሊስ እራሱን/ሷን መጠበቅ አለበት/ባት የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡ እያንዳንዱ ፖሊስ ታማኝነት እና የስነምግባር መስፈርቱን በመጠበቀ መልኩ በንጹህ ህሊና እና ሙያዊ ስነምግባር የእራሱን የስራ ኃላፊነት መወጣት አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ ሆኖም ግን እኔ ከምጠብቃቸው አንጻር ሆነው ለመገኘት የዋህ ልሆን እችላለሁ፡፡ ለዚህም ነው ከዚህ በላይ 3 የፖሊሲ ትዕዛዞችን ለመሰንዘር የፈለግሁት፡፡

ስለዘር ብዙ ንግግሮች እና ውይይቶች ሲደረጉ እሰማለሁ፡፡ ይሄ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ስለ ኤሪክ ጋርነር፣ ሚካኤል ብራውን እና የሌሎች ቀኖናዊ አይደለም ወይም ደግሞ ሁሌ የሚቀነቀኑ ጉዳዮች አይደሉም፡፡ ስለሰው ልጆች ክብር ጉዳይ ነው፡፡ ይሄ ነገር በህጉ ስላለው ስለአሜሪካ ፍትህ ጉዳይ ነው፡፡ ሁላችንም ልንወያይበት ይገባል፡፡

በዘር ላይ የሚደረግ ውይይት አንደኛውን ወይም ሌላኛውን ወገን ጥላሸት በመቀባት የሚጠናቀቅ ጉዳይ አይደለም፣ ሆኖም ግን ሁሉንም ሰብአዊ ፍጡር ሁሉንም ወገን የሚያብጠለጥል እና የሚጎዳ ነገር ነው፡፡ በሀገር አቀፍ የዘር ውይይት ጊዜ አንደኛውን ጭራቃዊ በማድረግ ሌላኛውን ደግሞ መልዓክ አድርገን ማቅረብ የለብንም ብዬ ተስፋ አደርጋሁ፡፡ አንደኛውን በመሳሪያ ሌላኛውን በዘረኝነት ማጠናከር የለብንም፡፡

በዶ/ር ማርቲን ሉተር ትምህርቶች ላይ ጽኑ እምነት ያለኝ ሰው ነኝ፡፡ ማርቲን ሉተር እንዲህ ብለው ነበር፣ “በመጨረሻም ፍቅር ዝም ብለን በዘፈቀደ የምንነጋገርለት ስሜታዊ ነገር አይደለም፡፡ ዝም ብሎ በስሜት የተጀቦነ እና የተሞላ አይደልም፡፡ ፍቅር ፈጠራ የተሞላበት፣ ለሁሉም ሰዎች ለመልካም ነገር መግባባት የሰፈነበት ነገር ነው፡፡ ሁሉንም ነገር ማሸነፊያው መንገድ ነው፡፡ ፍቅርን እያዳበርክ፣ ቆንጆ እና ኃይል ያለው መሆኑን እየተገነዘብክ  በምትመጣበት ጊዜ ጭራቃዊ ብቻ የሆነውን ስርዓት ለማሸነፍ ትፈልጋለህ፡፡ በዚያ ስርዓት ውስጥ ያሉትን ግለሰቦች ትወዳቸዋለህ ሆኖም ግን ስርዓቱን ለማሸነፍ ትፍለጋለህ፡፡“ ሁሉም አሜሪካውያን/ት መነሳት አለባችሁ እናም ኢሰብአዊነትን የሚያራምደውን፣ የሰዎችን በህይወት የመኖር፣ ነጻነትን የመጎናጸፍን እና ደስታ የማግኘት መብትን የሚጻረረውን ስርዓት ማሸነፍ አለባቸው ፡፡

የአሜሪካን የሲቪል መብቶች መከበር ታላቅ ክብር እና ሞገስ ይሰጠኛል፡፡ ከማገኘው ጥቅም እና ደስታ በላይ የትም ሆነ የት ኃይልን በመዋጋት የማገኘው እርካታ የላቀ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ የፒቪ ውሳኔ የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤትን ጨምሮ በዩናይትድ ስቴትስ ከመቶ ጊዜ በላይ የሚጠቀስ በመሆኑ ኩራት ይሰማኛል፡፡ የፒቪ ጉዳይ በአሁኑ ጊዜ የህግ ስልጣን ከፍተኛ የወንጀል ጉዳይ በመሆን በአሜሪካ የወንጀል ህግ እንደ በጥያቄ ጊዜ ዝም የማለት መብት፣ ኤድዋርድስ እና ሁሪስ የመሳሰሉትን አጥብቆ የሚይዝ ስለሆነ ኩራት ይሰማኛል፡፡

በካሊፎርኒያ እና በሌሎች አካባቢዎች ቀስ በቀስ እያደገ የመጣውን እና አደገኛ የሆነውን የፖሊስ ባህሪያት መበላሸትን ለማስቆም ባደረግሁት እልህ አስጨራሽ ትግል ኩራት ይሰማኛል፡፡

እስከ አሁን ድረስ በአሜሪካ ባለው የሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ ብዙም ትችት አላቀረብኩም፡፡ ባለፉት ስምንት ዓመታት የእኔ የሰብአዊ መብት ተቀዳሚ ይዞታዬ የሆነው በአፍሪካ እና በኢትዮጵያ ያለው የሰብአዊ መብት አያያዝ ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም ግን በአሜሪካ የሲቪል ነጻነቶች ጥበቃ ላይ ያለኝ ከፍተኛ ፍላጎት በኢትዮጵያ እና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ላይ ካለኝ የሰብአዊ መብት ጥበቃ የማያንስ እንደሆነ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት የነጻነት ጠላቶች ዘር አይኖራቸውም፣ ጎሳ አይኖራቸውም፣ ጾታ አይኖራቸውም፣ ህሊና አይኖራቸውም፣ ሞራል አይኖራቸውም፣ ሀገር እና ዜግነት አይኖራቸውም::

የነጻነት ዋጋ ዘላለማዊ ጥበቃ ከሆነ በህግ ማዕቀፍ ጥበቃ ውስጥ ለዘላለም በደስታ እቆያለሁ፡፡  

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ታህሳስ 1 ቀን 2007 .