ቱኒዚያውያን ተገላገሉ፤ ግብፆችም …እኛስ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ከሲሣይ አጌና

ቬጋስን ጎብኝቶ፣ ውብ ህንፃዎቿን አይቶ፣ በማራኪ ትዕይንቷ ውስጥ አልፎ ስለዚያ ለመጻፍ አለመቻል አለመታደል ነው፤እንደኛ ላለው ሀገሩ በጣዕር ላይ ላለችበት ከቬጋስ ሕንፃዎች በላይ ክፋታቸው የተከመረ ገዢዎች አሉብንንና በሲዘር ፓላስ፣ በፕላኔት ሆሊዎድ፣ በኤም.ጂ.ኤም ግራንድ፣ በቢላጆ… ወዘተ ካዚኖ ሆቴሎች ስለሚታየው ትንግርት እና ትዕይንት መች የምናወራበት ግዜ ሆነ፤ …ይህችው በአሜሪካ ሀገር በኒቫዳ ግዛት የምትገኘውና “የሓጢያት ከተማ” የሚል ቅፅል የለጠፉላት ላስቬጋስ በሓጢያት የከበሩትና 20 ዓመታት ደማችንን እየጠጡ የሚገኘት ገዢዎቻችንም ከባለፀጎቹ ሰፈር የሚሊዮን ዶላሮች ቤት መገንባታቸውንም ስሰማ እውነትም የሀጢያት ከተማ ብዬ ሳልጨርስ የቬጋስ የሃጢያት ከተማነት ሌላ መሆኑ ስውል ሳድር ተከሰተልኝ፤ በነገራች ላይ የቬጋሱ ቤት ለንደን ሰሩት ከተባለው በተጨማሪ መሆኑ ነው፤ …መቼም እብደት ነው፤ ይህንነ ሁሉ ወንጀል ተሸክሞ አሜሪካና አውሮፓ ለመሸሽ ማሰብ በነሳሞራ ጭንቅላት እንጂ በእነ አቶ መለስ ብልጠት የማይጠበቅ ነበር፤እርግጥ ነው ወደ ሩቅ ምስራቅ ብዙ እንዳሸሹ መጠርጠር ቢቻልም፣ሰልሞ ወደ ሳውዲ እንደመሸሽ ለአምባገነኖች ምቹ ስፍራ የለም፤የእስር ዋራንት እስኪቆረጥላቸው ማለቴ ነው፤ማምሻም ዕድሜ ነው ይባል የለ።

የፈረንጆቹ 2011 ፍትህ፣ ዴሞክራሲና ነፃነት ለተራቡ ወገኖች የምስራችን ይዞ ብቅ ያለ ይመስላል፤ በዓላማችን በስልጣን ላይ ረጅም ዓመታት ካስቆጠሩ በመጀመሪያው ረድፍ ከሚገኙ 15 መሪዎች የቱኒዚያው ቢን አሊ ተዋርደው ስንብት አድርገዋል፤ የግብጹ ሙባረክም በመንገድ ላይ ይገኛሉ፤የሱዳኑ አልበሽር እና የየመኑ አሊ አብዱላ ሳላህ ሰልፍ ይዘዋል፤ የቱኒዚያው ቢን አሊ እስከ ተባረሩበት ዕለት ድረስ ከኣለም የሀገራት መሪዎች ረጅም አመት ሥልጣን ሙጭጭ በማለት ቀደሚ ከሆኑት 15 የሀገር መሪዎች አቶ መለስን ጨምሮ 13ቱ በአፍሪካ ሲገኙ፣ሁለቱ ከእስያ አህጉር የመንና ባህሬን ናቸው፤ በሌላ መንገድ ከተመለከትነው ደግሞ 8ቱ ከጥቁሩ የአፍሪካ ክፍል፣7ቱ ከዓረቡ ዓለም ናቸው፤ ቀዳሚውን ስፍራ የያዙት የሊቢያው ሙዓመር አል ጋዳፊ በስልጣን ላይ 42 ኛ ዓመታቸውን ይዘዋል። የቱኒዚያው አብዮት ቢን አሊን ሲጠርግ፣አቶ መለስ ደረጃቸውን አሻሽለው ወደ 14ኛ ደረጃ ከፍ ብለዋል፤ ሙባረክ ሲሄዱ ወደ 13ኛነት ደረጃ ይሻገራሉ፤ …እኛስ ጋዳፊ ጋ እስኪደርሱ የሰው ገድል እያወራን ስንቆዝም እንኖራለን ወይንስ በአንድ መክረን፣ በጋራ ተነስተን በቃ እንላለን? ምንስ መደረግ አለበት?

በቱኒዚያ ተነስቶ ፕሬዚዳንቱን ቢን አሊን ወደ ስደት ሸኝቶ በዘረፋ የከበረውን ቤተሰብ ወደእስር ቤት ከቶ ወደ ግብጽ የተሸጋገረው ተቃውሞ የሙባረክን መንግስት ማራድ ከጀመረ ሰነበተ፤ የዚህ እንድምታ በሌላው የአፍሪካ ክፍል ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ምንድን ነው የሚል ውይይትም ቀስቅሱዋል፤ በኢትዮጵያችንም ይህ ነገር የማይቀር ስለመሆኑ አንብበናል፤በምን መንገድ ሊከወን ይችላል በሚለው ላይም አስተያየቶች ተሰንዝረዋል፤ እኔም እንደዜጋ ከአንዳንዶች ጋር የምጋራቸው ከሌሎች ጋር በማልስማማባቸው ጉዳዮች ላይ ጥቂት ልበል፤

በአሁኑ ወቅት በቱኒዚያ ፍጻሜ ያገኘውና ወደ ግብፅ የተሸጋገረው ተቃውሞ በኢትዮጵያም ሊደገም እንደሚችል ቢታመንም፣በቱኒዝያና በካይሮ የነበሩትና ያሉት መንግስታት የቱኒዚያና የግብፅ መንግስታት መሆናቸው ላይ ጥያቄ የማይነሳ ሲሆን፣በአዲስ አበባ ያለውን መንግስት ግን የኢትዮጵያ መንግስት እንደሆነ አምነው የሚቀበሉት ኢትዮጵያውያን ያልሆኑና ኢትዮጵያዊ የሆኑ ከህሊናቸው ጋር የተጣሉ የጥቅም ህመምተኞች ብቻ ናቸው፤በዘረኝነት የሚደግፉት በኢትዮጵያዊነቱ ሳይሆን፣ በዘረኝነቱ ስለሆነ እነርሱም የሚመለከቱት እንደኢትዮጵያዊ ሳይሆን እንደትግራይ ወኪልነቱ መሆኑም ሊሰመርበት ይገባል።

ቱኒዚያ እና ግብፅ ውስጥ ያሉትና የነበሩት መንግስታት ከሀገራቸው እና ሕዝባቸው ይልቅ ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው የቆሙ መሆናቸው እርግጥ ቢሆንም፣ቱኒዚያውያንንና ግብፃውያንንን በጠላትነት የሚመለከቱ ወይንም ሀገራቱን እንደሀገር ከእነርሱ ጋር አብረው እንዲያከትሙ የሚሰሩ አልነበሩም፤ አይደሉምም፤ አቶ መለስ ኢትዮጵያዊ ስሜት እንደሌላቸው እርሳቸውም ደጋፊዎቻቸውም በዚህ ረገድ ክርክር እንደማያነሱ የታመነ ቢሆንም፣ ምናልባት በደጋፊዎቻቸው ወገን ሊባል የሚችል ማስተዛዘኛ ቢኖር ኢትዮጵያን አይውደዱ እንጂ አይጠሉዋትም የሚል ሊሆን ይችላል፤ ህሊናቸውን በወለዳግድ አስይዘው ለሆዳቸው የሚኖሩት የሚነግርኑን ሳይሆን እውነቱን ስንመረምረው አቶ መለስ ኢትዮጵያንን አለመውደድ ብቻ ሣይሆን ኢትዮጵያን አምርረው የሚጠሉ መሆናቸውን የ20 ዓመታት አገዛዘቸው ህያው ምስክር ነው፤ ለተጨማሪ ዘረፋ እና ቀጣይ ክብር በስልጣን ለመቆየት የሚንፈራገጡ የቱኒዚያና ግብፅ መሪዎችን ሀገርን ጭምር ለማውደም ከሚሰሩት እና የዚያችን እንስሳ ፍልስፍና ከሚከተሉት አቶ መለስ ጋር ማወዳደር ሕሊናዊ አይደለም።

በሁለተኛ ደረጃ የቱኒዚያ እና የግብፅ ወታደሮች የቱኒዚያና የግብፅ ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያ ግን የራስዋ ወታደር አላት ለማለት ፈጽሞ አይቻልም፤የሀገሪቱ የመከላከያ ሃይል አዛዦች ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ከአንድ ብሄረሰብ የወጡ ብቻ ሳይሆኑ፣በህወሃት የጥላቻ ፖለቲካ የተጠመቁ 20 ዓመት የኢትዮጵያ ጦር አዛዦች ሆነው፣ አዲስ አበባ ቁጭ ብለው በአመለካከት የትግራይን ድንበር መሻገር ያቃታቸው እንደሆኑ የሚጠራጠር ቢኖር ለአብነቱ በአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ውስጥ የተፈፀመውን ለምን አላስታውሳችሁም፤አንበሳ ባንክ በኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ላይ ከሚገኙ የግል ባንኮች አንዱ ሲሆን፣እንደ ዘመኑ ፖለቲካ እና አንዳንድ የቀደሙ ባንኮች በቀደዱት ቦይ በዘር ተደራጅቶ በመፍሰስ ላይ የሚገኝ ባንክ ነው፤ አብዛኛዎቹ ባለአክስዮኖች የትግራይ ተወላጆች ናቸው፤ ጥቂትም ቢሆኑ የሌላ ብሄረሰብ ተወላጆች ባለድርሻ ሆነዋል፤ የኢትዮጵያ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማጆር ሹም ጄኔራል ሳሞራ የኑስም የዚህ ባንክ ባለአክስዮን ናቸው፤

በባንኩ የቦርድ አባላት ምርጫ በተፈጠረ አለመግባባት ብሄራዊ ባንክ ጣልቃ ይገባና ነሀሴ 15/2002 ከቀትር በፊት በባንኩ የስብሰባ አዳራሽ ስብሰባ ይጠራል፤በዚህ ስበሰባ ላይ ጄኔራል ሳሞራም በባለድርሻነታቸው ይገኛሉ፤ስብሰባው ከመጀመሩ ሳሞራ እጀቸውን ያነሳሉ፤ሲፈቀድላቸውም ቀጠሉ “ባለፈው የተመረጡት የት ሔደው ነው ሌላ ምርጫ የሚደረገው?ይህንን ባንክ ያቐቐምነው በታጋዮች የህይወት መስዋትነት እና አካላቸውን ባጡት የትግራይ ልጆች ደም ነው፤ቀደም ሲል ተካሄደው ምርጫ ውድቅ የሆነበት ቃለጉባኤ እንዲሰጠኝ ፈልጋለሁ፤ደርግን ከፍተኛ መስዋትነት ከፍለን ከስልጣን አውርደነዋል፤ አማራንም ዳግም እንዳይንሰራራ አድርገን አጥፍተነዋል” ሳሞራ ይህንን ሲናገሩ አዳራሹ በጭብጨባ ደመቀ፤ ሌሎች ደንግጠውና ፈዘው ይመለከቱ ነበር፤ ከባለ አክስዮኖቹ አንዱ የሆኑትና ይህንን አሳፋሪ ትዕይንት የተከታተሉት አቶ ሙሉጌታ በሪሁን ይህንን ድርጊት ፅናት በተሰኘው የአንድነት ፓርቲ ልሳን ላይ በስማቸው ጻፉ፤ አቶ ሙሉጌታን ከጽሁፉ በኋላ በአካል አግኝቼ አነጋግሬያቸው ነበር፤እንዴት በዘር የተሰባሰበ ባንክ ውስጥ ባለድርሻ እንደሆኑ ስጠይቃቸው የሰጡኝ ምላሽ “በዘር እንደተሰባሰቡ መች አወቅኩ፤እኔ አንበሳን አይቼ የአንድነት ምልክት አድርጌ ነው የገባሁት”የሚል ነበር፤

አቶ ሙሉጌታ በጄኔራል ሳሞራ ንግግር ተበሳጭተው አስተያየት ሊሰጡ ሲሉ ያስቆሙዋቸው ከጎነቸው የነበሩትና በሳሞራ ንግግር የተበሳጩ የትግራይ ተወላጅ ናቸው፤ “ለርሱ መልስ መስጠት እነደርሱ መቅለል ነው”እንዳሉዋቸው አቶ ሙሉጌታ ያስታውሳሉ፤ አቶሙሉጌታ በሪሁን የፕሮፌሰር አስራት ጠበቃ የነበሩ የህግ ባለሙያ ናቸው። ቀደም ሲል የተመረጡትም ሆነ የተቃወሙት ባለአክስዮኖች የትግራይ ተወላጆች በሆኑበት ሳሞራ በሌላ ብሄረሰብ ላይ የሚፎክሩበት ምክንያት ከጥላቻቻው ባሻገር የግንዛቤ ችግር እንዳለባቸው የሚያሳይ ነው፤በአደባባይ ሕዝብ በተሰበሰበበት ማንም ሳይነካቸው በዚህ መጠን ጥላቻ የሚያሳዩ ወገኖች በእርስ በርስ ግኑኝነትና ውስጣዊ ስብሰባቸው ላይ ምን ድረስ ሊሄዱ እንደሚችሉ መገመት አያስቸግርም፤ ልጆቻቸው መስዋዕት የሆኑ የትግራይ ወላጆችን በ5 ሺህ ብር ሸኝተው፣ አካላቸውን ያጡትንም በአልባሌ ገቢ አስቀምጠው አነርሱ በዘረፋ ለሚወጡበት የሀብት ጋራ እነዚያኑ ዛሬም በሽፋንነት እየተጠቀሙባቸው ነው። …ወደ ዋናው ጉዳያችን ስንመለስ የኢትዮጵያ ጦር ኃይል ጠቅላይ ኤታማጆር ሹም ጄኔራል ሳሞራ የኑስ መጠሪያቸው እንጂ የሰፋው ርሳቸው አሁንም እዚያው ናቸው 1968 ላይ ቆመዋል፤ እነ አቶ መለስ ከሰፉላቸው የአስተሳሰብ ጥብቆ ውስጥ ሊወጡ አልቻሉም።

የኢትዮጵያ የጦር አዛዦች የሚባሉት የኢትዮጵያን የጋራ ሲሳይ ብቻቸውን እየዘረፉም በሌላው ኢትዮጵያዊ ላይ ያላቸው ጥላቻ ያልረከሰ፣ይህም ከደማቸው አልፎ አጥንታቸው ላይ የተለወሰ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ለተቃውሞ አደባባይ ሲወጡ የሚፋለማቸው ይሕ ቡድን የሚመራው ጦር መሆኑም ሊሰመርበት ይገባል፤ይህ ቡድን አጥንቱ ድረስ በዘለቀ ጥላቻው እና በዘረፋ ለገነባው ሃብት ንብረት ሲል ክላሽንኮቭ ተኩስ ቢባል በታንክ እና በጄት ጭምር ለመጨፍጨፍ የማያመነታ ዘረኛ ቡድን መሆኑም ግምት ውሥጥ መግባት አለበት፤

ኢትዮጵያውያን ያለብን ስቃይና መከራ በአመታዊ ነፍስ ወከፍ ገቢያቸው ከ10 ሺህ እና 6 ሺህ ዶላር በላይ ከሚያገኙት ቱኒዚያና ግብፅ ጋር ፈፅሞ ሊወዳደር አይችልም፤ በተግባር ሰው ኪስ በማይታየው በወረቀት ላይ ብቻ የሚያድገውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እውነት ነው ብለን ብንቀበል እንኳን የኢትዮጵያ ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ 1ሺ ዶላር ገደማ ነው፤ ከቱኒዚያ 10 ዕጥፍ በታች ከግብፅ 6 ዕጥፍ ያነሰ፤ስሌቱ በህዝቡ ቁጥር ይካፈል እንጂ ባለድርሻዎቹ ጥቂቶች እንደሆኑ ግልጽ ነው፤ የቱኒዚያው ፕሬዚዳንት ቤን አሊ ከስልጣን መባረራቸውን ተከትሎ የወጡ መረጃዎች የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከ30 እስከ 40 ከመቶ በርሳቸውና በቤተሰባቸው መያዙን ያረጋግጣሉ፤በኢትዮጵያም በተለይ ከምርጫ 97 ወዲህ የህወሓት ኩባንያዎችና የህወሃት ሰዎች ሀገሪቱን እየጋጡዋት ይገኛሉ፤ አቶ ስዩም መስፍን የቦርድ ሊቀመንበር የሆኑበት ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ለህወሃት ሰዎች በሚፃፍላቸው የትብብር ደብዳቤ በርካታ ሺ ኩንታል ሲሚንቶ በፋብሪካ ዋጋ እያወጡ፣በመከላካያ መኪና እያስጫኑ በገበያ ዋጋ በመሸጥ በአንድ ጀምበር ወደሚሊየነርነት ሲተኮሱ፤ያለምንም መያዣ ከህዝብ ባንክ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እየወሰዱ ባለህንፃ ሲሆኑ እያየን፤ሕንጻዎቹንም የመንግስት ተቋማት ሲከራዩዋቸው እየታዘብን ነው፤

አንዳንድ ሚኒስቴር መስርያ ቤቶች የመንግስት ሕንጻዎችን እየተዉ፣ግለሰቦችን ለመጥቀም ወደግል ሕንጻ እየተሸጋገሩ ይገኛሉ፤የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን በአመት ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ እየከፈለ ሶማሌ ተራ አካባቢ የሚገኝ ሕንጻ ውስጥ ከገባ አመት አልፎታል፤የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሄራልድ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል 22 ማዞሪያ አክሱም ሆቴል አካባቢ የሚገኝ ህንፃ ውስጥ ከትሟል፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተወሰነ ክፍሉን ካዛንቺስ አካባቢ ወደሚገኘው አንድ ታወር አዛውሯል፤ በዚህ መልክ ህንጻዎች ተከራይ እንዳያጡ እና የመንግስት ሃላፊዎችም በኮሚሽን የሚከብሩት ሁኔታ ተመቻችቷል፤በዚህን መሰል ሁኔታዎች የሀገሪቱ ሃብት ወደ ጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች በህገወጥነት እየሄደ አብዛኛው ዜጋ እነርሱን ለመጥቀም በሚበተን የመንግስት ገንዘብ ግሽበት እየተመታ ከዛሬው ይልቅ የነገውን ጭለማ እየፈራ ይገኛል፤ በእንዲህ ያለ መከራ ውስጥ የሚኖር እና በዘረኝነት የተንገፈገፈ ሕዝብ በቀላሉ ለለውጥ መንቀሳቀሱ የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ትግሉ የማይቀለበስበት መሰረት እስካልተጣለ ድረስ በቀላሉ ሊጨፈለቅ ከመቻሉ ባሻገር በወሳኝ ወቅት የሚደረጉ ጥሪዎችን በጥርጣሬ እንዲገፋው ሊያደርጉት ይችሉ ይሆናል።

በዘረፋ የተጠመዱ ገዢዎቻችንም አለማስተዋላቸው እንጂ በዚህ መልክ በዘረፋ የተገነባ ሃብት ነገ የህዝብ መሆኑ እንደማይቀር የቅርቡ የቱኒዚያ ሁኔታ አስተምሮናል፤ቤን አሊ በህዝብ ተገፍተው ከሀገር ሲወጡ እንዳይንቀሳቀስ የታገደው በሀገር ውስጥ ያለው ሃብታቸው ብቻ ሳይሆን፣ በፈረንሳይ ፣በስዊዘርላንድ እና በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ጭምር ያለው ንብረት ነው፤ይህም ብቻ ሳይሆን ምንም መንግስታዊ ሓላፊነት የሌላቸው የዘረፋው ተባባሪ የሆኑ 33 ያህል የቅርብ ሰዎቻቸው ወዲያውኑ በቁጥጥር ስር ውለዋል፤እነ አቶ መለስ ልጆቻቸው 18 ዓመት እስኪሞላቸው ጠብቀው የሃብት ማስመዝገብ አዋጅ በማውጣት ንብረት አካለ መጠን በደረሰ ልጅ ስም ለማሸሽ ያደረጉት ሁሉ የልጆች ጨዋታ እንደሆነ ከቱኒዚያው ትምህርት እንደቀሰሙ ተስፋ ይደረጋል።

ሕዝባዊ ትግሉም እነ ሳሞራ ታንክ ስለሚተኩሱ፣ አውሮፕላን ስለሚያስነሱ ተብሎ የሚቆም አይሆንም፤ ጉዳቱን መቀነስ፣እንዳይቀለበስ መንቀሳቀስ እና ውጤታማ ማድረግ እንዴት ይቻላል በሚለው ላይ መምከር እንጂ በውርደት፣በባርነትና በርሃብ መኖርን ማንም አይፈቅድም፤ የኢትዮጵያውያን ስቃይ ከቱኒዚያ እና ከግብፅ የከፋ ብቻ ሣይሆን ጨርሶ የማይነፃፀር የእኩልነት እና የነጻነት ጥያቄ ጭምር ነው፤ …አንድ ለጋዜጣችን “ኢትኦጵ” መረጃ የሚያቀብል የነበረ የብአዴን ታጋይ ሁልግዜ ደጋግሞ የሚያነሳት ቁጭት ኢትዮጵያ ውሥጥ ያለው ኢፍትሃዊነት አብረው በታገሉ የሌላ ብሄረሰብ አባላት ላይ ጭምር ተፈጻሚ መሆኑን ነው፤ የብአዴኑ ታጋይ እንዲህ ነበር የሚለው “ለዲሞክራሲ ታግለን፣ የእኩልነት መብታችንንም ጭምር አስወስደን ቁጭ አልን።”

ይህ የሚያሳየው ከህወሃት ታጋዮች ጋር ያሉት የሌላ ብሄረሰብ ተወላጆች የጭቆናው ሰለባ መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን፣ከጭቆና ለመውጣት ከሌላው ጋር ለመሰለፍ ያለቸውንም እልህ ጭምር ነው፤በመሆኑም በሰራዊቱ ውስጥ ያሉ የሌላ ብሄረሰብ ተወላጆችና የጥቅም ተጋሪ ያልሆኑና በዘረኝነት ያልሰከሩ የትግራይ ተወላጆች ከህዝብ ጎን እንዲሰለፉ እንዴት መድረስ ይቻላል;ትግሉ ሳይቀለበስ ወደ ፍሬ እንዲያመራ እና ሠራዊቱ የታጠቀውን መሳሪያ በህዝብ ላይ እንዳይጠቀም ምንማድረግ ይገባል? ሰራዊቱ (ጠመንጃውን የተሸከመው ማለቴ ነው) ከጥርጣሬ ውጭ ሆኖ በእርግጥኛነት ትግሉ እንደማይቀለበስ አምኖ እንዲሰለፍ ምን ዋስትና ያስፈልገዋል? ሀገር ቤት ያለው ህዝብ ተባብሮ እንዲወጣ ከመጠየቅ በፊት የሚያስር፣የሚገድል በሌለበት መተባበር ያልቻሉት ሰዎች ተባብረው ማሳየት የለባቸውምን?

በቱኒዚያም ሆነ በግብፅ ሀገራቱን የሚመስል መንግስታዊ መዋቅር ስለነበር የርክክብና የሽግግር ሂደቱ ቀላል በሚባል ደረጃ የተከናወነና የሚከናወን ቢሆንም በኢትዮጵያ ግን እርስ በርሱ የተቆራኘ ኢትዮጵያዊ ስዕል የሌለው አንድን አካባቢ መሰረት ያደረገ ቡድን ነው፤ይህ ቡድን መናጋቱ ሰራዊቱንና የደህንነት መዋቅሩን ጭምር ስለሚነካ እና አንድ ላይ ስለሚበተን ስልጣኑን ለመረከብ የተዘጋጀ የሚታመንበት ብቻ ሳይሆን አቅም (ጉልበት) ያለው ሃይል አያስፈልግምን?

…ከዚህ ውጭ ስላጣን ላይ ካሉት የህወሐት መሪዎች እና የጦር አዛዦች ከሕዝብ ጎን የሚሰለፍ ይኖር ይሆናል ብለው ተስፋ ለሚያደርጉ ቢሆን ምኞቴ ቢሆንም፤ በበኩሌ በፍፁም ተስፋ አላደርግም፤ 20 ዓመት ኢትዮጵያን ገዝተው ኢትዮጵያዊ መሆን ያቃታቸው ሰዎች በ21ኛ ዓመታቸው ኢትዮጵያዊነት አይከሰትላቸውም በሚል ብቻ ሣይሆን፣ ከ10 ዓመት በፊት ከሕወሃት የተለየው ቡድን አንዳንድ አባላት ከህዝብ ጋር ተቀላቅለውም ኢትዮጵያዊ ለመሆን ሲቸገሩ በማየቴ ጭምር ነው፤

በየካቲት 1993 ህወሐት ለሁለት መሰንጠቁን ተከትሎ ከአየር ሃይል አዛዥነታቸው የተነሱት ሜጀር ጄኔራል አበበ ተ/ሃይማኖት በምርጫ 97 ወቅት የትግራይን ህዝብ ለመታደግ ሲሉ ተደራጅተው እንደነበር “ደሃይ” ለተባለ የትግርኛ መጽኄት ተናግረው ነበር፤በነሀሴ 2000 የወጣው “ደሃይ” የትግርኛ መፅሄት በምርጫው ግዜ የትግራይ ሕዝብ አደጋ ላይ በነበረበት ወቅት አልደረሳችሁለትም ተብለው ሲጠየቁ “አዝማሚያውን አይተን መሰባሰብ ጀምረን ነበር፤ሁኔታዎች ሲረጋጉ ግን ተበተንን ነበር “ያሉት፤ ለጄኔራል አበበ የሁኔታዎች መረጋጋት ማለት የ200 ንጹሀን መገደል፣የቅንጅት መሪዎችን ጨምሮ በ30 ሺ የሚቆጠር ዜጋ ወደ ወህኒ መነዳት እና የሕወሐት በስልጣን ላይ መቆየት ነበር፤እንግዲህ የተማሩት ከስርዓቱ ከተለዩ 10 ዓመታት ያስቆጠሩት አበበ ተ/ሃይማኖት ከ10 ዓመታት በኋላም እንደህወሃት እያሰቡ ያልተማሩትና ዛሬም የስርዓቱ ተጠቃሚ የሆኑት የህወሐት የጦር አዛዦች ከሌላው ጋር ይሰለፋሉ ብሎ ማመን አስቸጋሪ ነው፡፡

አበበ ተ/ሃይማኖት ከርሳቸው ጋር ተቧድነው በኋላ ስለተበተኑት ሰዎች ባይናገሩም ዛሬ የቢራ ፋብሪካ ለማቐቐም ደፋ ቀና የሚሉት ሌፍትናንት ጄኔራል ፃድቃን ገብረተንሳይ አንዱ እነደነበሩ ይታመናል፤ ለነርሱ መረጋጋት የህወሀት የበላይነት መቀጠል በመሆኑ የህዝብ ብሶትና በደል ደንታ ሳይሰጣቸው ጥቅም በማሳደድ ላይ ናቸው፤ የሕወሐት የበለይነትን የሚቀናቀን እንቅስቃሴ ሲጀመር አነርሱም ከሕወሀት ጎን እንደሚሰለፉ ከወዲሁ ታሳቢ ማድረጉ አይከፋም፤

አለማቸው ምንም ይሁን ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር አብረው ተሰልፈው በትግሉ ውሥጥ ለቀጠሉት አቶ ስየ አብርሃ ፣አቶ ገብሩ አስራት ፣አቶ አውአሎም ወልዱ፣ ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ አክብሮት አለኝ፤ እነዚህም ሰዎች የሕወሐት የበላይነት እንዲቀጥል እየሰሩ ነው ለሚሉት ወገኖች ይህ አክብሮት የማረጋገጫም፣የማስተባባያም ሳይሆን እንደዚያ በጥላቻ የታወሩ ሰዎች ካሉበት ቡድን ውሥጥ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገናቸው ጋር በአንድ ማዕድ በእኩልነት ለመታደም በመዘጋጀታቸው ብቻ ነው፤ በሕወሀት ላይ ሥር ነቀል ለውጥ ሊያመጣ የሚችል እንቅስቃሴ ሲፈጠር ሰልፋቸው የት ይሆናል የሚለው አጠያያቂ ቢሆንም፤ ከህወሃት ጋር በመሰለፍ በዘላቂው የትግራይን ሕዝብ መታደግ እንደማይቻል ግን በደማቁ ሊሰመርበት ይገባል፤

… ሃሳቤን ላጠቃልል፤ለማለት የፈለኩት የሚደረገው ትግል የኢትዮጵዊነት መነሻ ከሆነው ሥፍራ በቅለው በሌላው ኢትዮጵያዊ ላይ ሥር የሰደደ እና ወደ በሽታነት በተለወጠ ጥላቻ ከተቧደኑ ሰዎች ጋር ነው፣ይህ ኃይል ደግሞ አጠቃላይ የሀገሪቱን ወታደራዊና የፖለቲካ ሥልጣን ስለተቆጣጠረ፣ የደህንነት መወቅሩን ሙሉ ለሙሉ ስለያዘ ይህንን ሁሉ ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት ያስፈልጋል፤ አደነቁረው ሊገዙን በተነሱ ጨካኞች እጅ በመሆናችንም በ0.4% ኢነተርኔት ተመልካች፣ በ0.28 የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ባለባት ኢትዮጵያ የግንኙነት መስመሩም መፈተሸ ይገባዋል፤በሕዝቡ ላይ ዕምነት ለማሳደር የተቃዋሚዎች ትብብር እና የትብበር ጥሪ እንዲሁም በባህርማዶ ያሉ ኢትዮጵያውያን አጋርነት የግድ ይላል፤የዘረኞቹ ምሽግ ሲናድ በክፍተቱ እንደገና ራሳቸው አፈር ልሰው እንዳይነሱ ቦታውን የሚተካ የተደራጀ ኃይል ያስፈልጋል፤ …በግሌ ከነዚህ ጥንቃቄዎችና ዝግጅቶች በፊት የሚደረጉ ሙከራዎች በአሁኑ ብቻ ሳይሆን በቀጣይ እንቅስቃሴም ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል የሚል ስጋት አለኝ፤መንገዱ እኮ የግድ ይህ ብቻም ላይሆን ይችላል ፡፡

እነሆ አድራሻዬ፣ [email protected]