የአላሙዲ ሸራተን ሆቴል ከ10 ቀናት በኋላ እንደሚዘጋ የሆቴሉ ማኔጅመንት አስታወቀ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በዘካሪያስ ስንታየሁ | ሪፖርተር

ሸራተን አዲስ ሆቴል ከአሥር ቀናት በኋላ እንደሚዘጋ የሆቴሉ ማኔጅመንት ለክፍል ኃላፊዎች ጥር 26 ቀን 2003 ዓ.ም. አስታወቀ፡፡

የሆቴሉ ሥራ አስኪያጅ ዦን ፒር ማኒጐፍ ከሰው ኃይል አስተዳዳሪው አቶ ዳንኤል መዝገቡ ጋር የክፍል ኃላፊዎችን ሰብስበው የሠራተኛ ማኅበሩ ከማኔጅመንቱ ጋር ያለውን ውዝግብ ካላቆመ፣ ሆቴሉ በአሥር ቀን ውስጥ እንደሚዘጋ ማስጠንቀቃቸውን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የሆቴሉ የክፍል ኃላፊዎችም ከማኔጅመንቱ የተላለፈላቸውን ትዕዛዝ ጥር 27 ቀን 2003 ዓ.ም. ለሁሉም ሠራተኞች የተናገሩ ሲሆን፣ ሆቴሉም አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ከ13 ዓመት በኋላ ሥራውን እንደሚያቆም አስረድተዋቸዋል፡፡

ሪፖርተርም በስፍራው በመገኘት ሆቴሉ ከየካቲት 8 ቀን 2003 ዓ.ም. ጀምሮ የሪዘርቬሽን አገልግሎት እንደማይሰጥ መረዳት ችሏል፡፡ ባለፈው ሐሙስ በላሊበላ አዳራሽ በተካሄደው ስብሰባ ቁጥራቸው 53 አካባቢ የሚደርሱ ኃላፊዎች መሰብሰባቸውም ታውቋል፡፡

በዚያኑ ቀን የሆቴሉ ሠራተኛ ማኅበር ከሆቴሎች፣ ቱሪዝምና አገልግሎቶች ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን ጋር ከማኔጅመንቱ ጋር ያለበትን አለመግባባት ለመፍታት ተሰብስቦ ነበር፡፡ የሆቴሉ ማኔጅመንት ጥር 27 ቀን 2003 ዓ.ም. ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ላይ በዳሸን አዳራሽ የሠራተኛ ማኅበሩን ሰብስቦ በጉዳዩ ላይ የተወያዩ ቢሆንም፣ የሠራተኛ ማኅበሩ የሆቴሉ መዘጋት እርሱን የሚመለከተው ጉዳይ ባለመሆኑ፣ በጉዳዩ ላይ መወያየት አስፈላጊ አለመሆኑን ለማኔጅመንቱ ገልጿል፡፡ ሆቴሉ የከሰረ ከሆነም ሊዘጋ እንደሚችል የሠራተኛው ማኅበር በውይይቱ ላይ ተናግሯል፡፡

የሠራተኛ ማኅበሩም ማኔጅመንቱ ሆቴሉን እዘጋዋለሁ እያለ ማኅበሩ የሚያነሳው ጥያቄ እንዲታፈን ለምን እንደሚያደርግ ማኒጐፍን ጠይቋል፡፡ ሆኖም ማኒጐፍ ማኔጅመንቱ ሠራተኞችን ለማስፈራራት ሳይሆን ከሆቴሉ ባለቤት ሼክ መሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ጋር የሆቴሉን ማስፋፊያ ፕሮጀክት ለማካሄድ በመስማማቱ ሆቴሉ እንደሚዘጋ መናገራቸውን ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡

ምንጮቹ እንደሚሉት፣ ሆቴሉ ሙሉ በሙሉ አልጋዎችን ከቀየረ አንድ ወር አካባቢ ይሆነዋል፡፡ የሆቴሉ ምንጣፍም በሙሉ ተቀይሮ ያለቀው የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ከመጀመሩ ከአንድ ሳምንት በፊት ነው፡፡ ይህ ሁሉ ነገር እየተካሄደ ሆቴሉን ከአሥር ቀናት በኋላ እዘጋዋለሁ ማለት ቀልድ ነው ብለዋል፡፡ ማኒጐፍ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት ሚድሮክ ኮንስትራክሽን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለተበደረው 170 ሚሊዮን ብር ማስያዣ ያደረገው ሸራተን አዲስ ለጨረታ ከመውጣቱ በፊት መንግሥት ጣልቃ እንዲገባና ችግሩን እንዲፈታው ባንኩ መጠየቁን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ሌግዠሪ ኮሌክሽን የሚባለው ምድብ ውስጥ በመግባት ከአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው ሸራተን አዲስ ሆቴል ባለቤት ሼክ መሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ናቸው፡፡ ሆቴሉ ከተከፈተ 13 ዓመት ሲሆነው፣ እስካሁንም የተለያዩ ታላላቅ ስብሰባዎችን አስተናግዷል፡፡