የአቶ ሽፈራው ሽጉጤ ሽጉጥ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ሰሞኑን መነጋገሪያ ከነበሩት ጉዳዮች መካከል አቶ ሽፈራው ሽጉጤ የተባሉ የኢህአዴግ ባለሰይጣን (ታይፕ አልገደፍኩም ዝም ብለው ይከተሉኝ ወዳጄ) ባለስይጣኑ በሚያስተዳድሩት ክልል ሲኖሩ የነበሩ ከሰባ ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎችን “ወደ ሀገራችሁ ሂዱ” ብለው አባረዋቸዋል።

ይህንን አስመልክቶ ዛሬ በኢሜል የደረሰኝ የአንድነት ፓርቲ ልሳን የሆነው የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ በርዕሰ አንቀፁ ባስቀመጠው ካርቱን ስዕል፤ ሰውየው አቶ ሽፈራው ሽጉጤ መሆናቸው ነው… “ወደ ሀገራችሁ ሂዱ” እያሉ ዜጎቹን በመጥረጊያ ሲጠርጓቸው ያሳያል። በእናቱ ጀርባ ላይ ያለ ህፃን ደግሞ “እማዬ ሀገራችን የት ነው?” ብሎ እናቱን ይጠይቃል። ልብ አድርጉልኝ የታዘለ ልጅ ከ”ትልቁ ሰውዬ” ሲበልጣቸው። በነገራችን ላይ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በቁመት ከሁሉም የኢህአዴግ ባለስልጣናት ትልቁ ናቸው ።

የምር ግን ነገሩ በጣም አሳፋሪ ነው። “ህገ መንግስቱ ማንም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም አካባቢ ተዘዋውሮ መኖር፤ መኖር ብቻም አይደል ንብረት ማፍራት እንደሚችል” ይገልፃል። እየሆነ ያለው ግን፤ በአንድ ወቅት ፕሮፌሰር መስፍን እንዳሉት “መንግስታችን በህገ መንግስቱ ሳይሆን በህገ አራዊት ነው የሚመራው።” የሚለውን የሚያጋልጥ ነው! “እኔን የማትመስሉ በሙሉ ወግዱ” ማለት ከሰዎች አይጠበቅም።

አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በፃፉት “የውጡልኝ ከዚህ ቤት” ደብዳቤ ዜጎቹን በህገ ወጥ መንገድ መሬት ይዘዋል፣ በህገ ወጥ መንገድ መሬት ይሸጣሉ… ሲሉ ወንጅለዋቸዋል። ታድያ ይሄ ጉዳይ በህግ ሊዳኝ አይችልም እንዴ? ብለው ቢጠይቁ ባለስልጣኑ ይቀየሙዎታል።

አንድ ወዳጄ እንዳለኝ “እውነቱን ለመናገር እኒህን ባለስልጣን ባለስልጣን ብለን ብንጠራ እግዜሩም ቅር ይለዋል። እናም አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ባለስጣን ሳይሆኑ ባለሰይጣን ናቸው!” ብሎኛል። “ውጡልኝ” ብለው ያፈናቀሏቸው ዜጎች ጎረቤቶቻቸው የነበሩ የደቡብ ተወላጅ ወዳጆቻቸው ዘንድ ንብረት እንኳ እንዳያስቀምጡ ከልክለው አራስ እና ርጉዝ ሳይቀር በአንድ ጀንበር ማባረር በእውነቱ ባለስልጣን አያሰኝም።

ይህንን የተመለከቱ አንዳንድ ወገኖች፤ “ልዩነታችን ውበታችን” መሆኑን የሚያሳዩ በርካታ ልማታዊ ዜማዎች አሉን። ልዩነታችን ውበታችን መሆኑን የሚያሳዩ መሪዎች ግን የሉንም።” እያሉ እየወቀሱ ነው።

እኔ የምለው ግን በዚህ የእብደት ውሳኔ ላይ “ዋናው” መንግሰት የሆነ ነገር ማለት ያለበት አይመስላችሁም? አለበለዛ ምንም እንኳ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአባይ ዙሪያ ሲያወሩ “ኢትዮጵያ ውስጥ ያበደ መንግስት እንደማይኖር የሚያረጋግጥ ሞያተኛ የለም” በማለት ቢናገሩም የአቶ ሽፈራው ሽጉጤን ጉዳይ በቸልታ ሲመለከቱት ግን ያለ ምንም ባለሞያ እኛ ራሳችን መንግስታችን እብድ መሆኑን እናረጋግጥለታለን ማለት ነው። (ይሄኔ እርስዎ በሆድዎ “እኔ ካረጋገጥኩ ቆየሁ!” ሊሉ እንደሚችሉ እጠረጥራለሁ)

አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በሰባ ሺህ ዜጎች ላይ፤ “የሌላ ክልል ሰዎች ናችሁ” በሚል ምክንያት ሽጉጣቸውን ተኩሰውባቸው ሲያበቁ ከዚህ ቀጥሎ እርሳቸው፤ ለስብሰባ ወይም ለመዝናናት ወይም ዕቃ ለመግዛት ወደ ሌላ ክልል የመሄድ ሞራል አላቸው?

ወዳጄ ግድየሎትም እንፀልይ፤ “በቸርቻሮ የሚሸጡንን ወዲያ አድርጎ፤ አንድ አድሮጎ የሚገዛንን ያምጣልን!”

ለማብቂያ በአንድ ወቅት ታማኝ በየነ በአዲሳባ ስታድየም ያነበባትን ግጥም ቀንጨብ እናድርጋት

“…በሶማሊያ ችግር

አብረን ስንጨነቅ

በዩጎዝላቪያ ቆመን ስንሳለቅ

በእንጀራ አባታችን በሩሲያ ስንስቅ

ከነሱ ሳንማር ካለፍነው በዋዛ

አርባ መንግስት ሆነን

ክልል ስናበዛ

እንዳንጠያየቅ ፓስፖርት እና ቪዛ” ታማኝን እድሜ ይስጥልን!

ለካርቱን ስዕሉ ፍኖተ ነፃነትን ማመስገን ይገባል!