ሁሉም ወደ “ሀገሩ” ከተባለ እኔም ልምጣ፤ አቶ መለስም ይውጣ (ብልስ?)


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


አቤ ቶኪቻው

መጀመሪያ ቆይ ርዕሱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን አንቱ ያላልኩት በትህትና ጉድለት ሳይሆን ርዕሴ ቤት እንዲመታልኝ ፈልጌ ነው።

ዛሬ እና ትላንት ከደቡብ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎችን አስመልክቶ ሀሳቤን ላካፍላችሁ ሙከራ አድርጌያለሁ። እውነቱን ለመናገር እየተፈጠረ ያለው ነገር በጣም የሚያስጨንቅ ነው። ለዚህም ነው ደጋግሜ ነገሩን ማንሳቴ ወደፊትም ደግሜ አነሳዋለሁ።

ታድያ በእናት ድርጅታችን ኢህአዴግ ውስጥ “የብሎግ እና ፌስ ቡክ ጨዋታዎች አደናቃፊ ዋና የስራ ሂደት ባለቤቶች” በሰጡት አስተያየት ተነስቼ ትንሽ ጭማሪ ይዤ መጥቻለሁ። በርግጥ በርካታ ወዳጆቼ መልስ ሰጥተዋቸዋል እኔም ብጨምርላቸው ግን ክፋት የለውም።

በተለይ ዮሴፍ የተባለ ወዳጃችን ይህንን ነገር በተደጋጋሚ መጠየቄ አልተዋጠለትም መሰለኝ በፃፈልኝ አስተያየት፤

“…የሆነ የትግርኛ ምስሌያዊ አነጋገር አስታወስከኝ ”ዐሻስ’ያ ሐደ ደርፉ”ልተርጉምልህ አይደል የሞኝ ዘፈን ሁሉ ግዜ አንድ አይነት ነው እንደ ማለት ነው ነገሮችን እየደጋገምክ ስትጽፍ እንደፊትህ ( ይቅርታ የሞኝ የሚመስል ፊት ስላለህ ነው) አንተም ሞኝ እየመሰለከኝ መጣህ!”

በማለት ወርፎኛል። ይህ ወዳጄ የኢህአዴግ ቀንደኛ ደጋፊ መሆኑን በተለያዩ ሰላማዊ ሰልፎች እና ሰላም ባላቸው አበሎች ያረጋገጠ ይመስለኛል። ጎበዝ እንዲህ ነው እንጂ “እየበሉ እየጠጡ ዝም የጋን ወንድም” ከመባል ድነሃል። እናም ወዳጄ ዮሴፍ ለሚከፈለው አበል ጥሩ አገልግሎት እየሰጠ ስለሆነ ለትጋቱ ላመሰግነው እወዳለሁ።

ምን መሰለህ ዮሴፍ እንግዲህ ሞኝ ከመሰልኩህ አይቀር አሁንም ልጠይቅህ ነው። ቀጥሎም ነገሩ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ እኔም ሌሎች ደጋግመን መጠየቃችንን እንቀጥላለን! በሌላ አባባል መነዛነዛችን አይቀርም። በቅንፍ (የግድቡን ዜና እና ዜማ ያኽል ግን ሰዉ “ኤጭ አሁንስ…” እስኪለን ድረስ አይደለም)

በነገራችን ላይ የደቡቡ ፕረዘዳንት አቶ ሽፈረው ሽጉጤ የወሰዱት ርምጃ ምን ማለት እንደሆነ ገብቶሃል? ከገባህስ ትክክል ናቸው ብለህ ታስባለህ? እውነቱን ለመናገር ወዳጄ ርምጃው ገብቶህ ቢሆን፤ ቢያንስ ቢያንስ ለአቶ መለስ ህልውና ስትል ነገሩን ትቃወመው ነበር።

ከአማራ ክልል የመጡ ዜጎችን “ወደ ሀገራችሁ ሂዱ!” ብሎ ማባረር ትክክል ነው ብለህ ካሰብክ እደነቃለሁ። (አንቅሃለሁ አላልኩም። ማነቅ ከኛ ወገን አይደለችም)

“ብሄር ብሄረሰብ እጅ ለእጅ ተያይዞ አባይን ይገነባል ህዳሴን ያበስራል ወዘተ ይወዝታል…” የሚባለው ታድያ እንዴት ነው? አንዱ ብሄር አንዱ ዘንድ ሄዶ መኖር ካለቻለ እጅ ለእጅ የሚያያዙት “በብሉቱዝ” ነው? እረ እርሱም ቢሆን ተቀራርቦ መቀመጥን ይጠይቃል!

እንደኔ እምነት አቶ መለስ ዜናዊም ቢሆኑ በአቶ ሽፈራው ሽጉጤ ውሳኔ ይስማማሉ ብዬ አላምንም። ነገር ግን ተስማምተው፤ እሳቸውም “በደቡብ ክልል የሚኖሩ የሌላ ክልል ተወላጆች ወደ ሀገራቸው መዛወራቸው አግባብ ነው!” ብለው ውሳኔውን በይፋ ካደነቁ፤ ያኔ በሰፊው እፅፋለሁ። ምን ብለህ አትለኝም? አቶ መለስም ወደ እናት ሀገራቸው ኤርትራ ይሂዱ! እኔም ወደ እናት ሀገሬ አዲሳባ እመጣለሁ!

ዮሴፍ ለምን ግን ክፉ ታናግረኛለህ?

ለማንኛውም በብሎጋችን ቆይታህ ይቀጥል!