የትላንት በያይነቱ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ትላንት ፀሎተ ሀሙስ ነበር። ቀኑን የጀመርኩት ግን በፀሎት አይደለም በሀዘን ነው። ይሄኔ ምን ሆነክ ይላል ብልህ ሰው፤ አዎ እንደርሱ ነው የሚባለው።

በፌስ ቡክ መልዕክት ሳጥኔ ፤ “አንድ ኢትዮጵያዊ ኩዌት ውስጥ በድንገት ሞቶ ተገኘ ልጁ ወደ ኩዌት ከመጣ ገና ሶስት ወር እንኳ አልሞላውም” ሲል ከወዳጆቼ አንዱ መርዶ አስቀምጦልኛል። መልዕክቱን አንብቤ እንደጨርስኩ ድብርት እና ሀዘን በላዬ ላይ ተከመረ። አጠገቤ የነበረውን ጓደኛዬን ጠየቅሁት፤ እስከ መቼ ነው በተሰደድንበት ሁሉ እንዲህ አይነት ስቃይ እና አበሳ የምናየው? አልኩት። እርሱም “ምርጫ ቢኖረው ኖሮ  “መ” እልህ ነበር” አለኝ። “መ” መልሱ የለም ነው። ወይ ጣጣችን!

ከጥቂት ቁዘማ በኋላ እንደ ምንም ድብርቴን ለማራገፍ ድጋሚ ወደ ፌስ ቡክ መንደር ጠልቄ ገባሁ። በርከታ ወዳጆቼ የአመትባሉ ገበያ አሳስቧቸዋል። አንዳንዶች “በግ እናከረያለን ዶሮ ቅርጫ እናቃርጣለን…” የሚሉ ሹፈቶችን ለጥፈዋል። በርካቶችም ዘና ዘና የሚያደርጉ አስተያየቶችን ሰጥተውበታል።

የአውራምባ ታይምሱ ዳዊት ከበደ፤ “በዚህ አመት በዓል ኢትዮጵያ ውስጥ ዶሮ 250 ብር እየተሸጠ እንደሆነ ሰማሁ፡፡ ኢትዮጵያ ያላቸሁ የፌስ ቡክ ጓደኞቼ እውነት መሆኑን ታረጋግጡልኛላችሁ? ወይ ስምንተኛው ሺ!”  የሚል ፅሁፍ ከጥሩ እንስት ዶሮ ጋር ለጥፎ አገኘሁት። ግማሹ “አይ ሁለት ከሃምሳ… ተጋኗል ሁለት መቶ ብር ታገኛለህ” ብሎ ሲያፅናና ሌላው ደግሞ “በሁለት መቶ ሃምሳ ዶሮ የት እንደሚገኝ ለነገረኝ ውለታ እከፍላለሁ” ብሎ  እየፃፈ ተስፋ ያስቆርጣል።  እኔም የተሰጡትን አስተያየቶች ከኮመኮምኩ በኋላ ለማንኛውም ብዬ የዶሮዋን ስዕል “ሴቭ” አድርጌ  ጉዞዬን ቀጠልኩ።

ኢዮብ ብሃነ አንድ ግጥም ለጥፏል፤

እህል ተወደደ፣

ቅቤም ተወደደ፣

ስጋም ተወደደ፣

ፍቅር ከሀገር ጠፋ ዋጋው ተወደደ፣

ምሁር ከሀገር`ራቀ እየተሰደደ፣

ከሀገሬ ገበያ ቁጥሩም የጨመረ

ዋጋው የቀነሰ፣

የካድሬ ብቻ ነው ህዝብ እያስለቀሰ።

እንዴት ማለፊያ ግጥም ናት ብዬ መውደዴን ለመግለፅ “ላይክ” የሚለው ላይ ጠቅ አድርጌ አለፍኩ።

መሰረት ሊ የተባለች ወዳጃችን ደግሞ እንዲህ የሚል ለጥፋለች፤

“በቅርቡ በአሰሪዎችዋ ድብደባ ደርሶባት፥ ህይወትዋ በአሳዛኝ ሁኔታ በሊባኖስ ላለፈው ወ/ሮ ዓለም ደቻሳ መታሰቢያና ልጆችዋን መርጃ እንዲሆን በማሰብ ሀሙስ ሚያዝያ 11/2004 ዓ/ም ከቀኑ 11:30 ጀምሮ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል አዳራሽ ታላቅ የገቢ ማሰባሰቢያ እና የኪነ-ጥበብ ፕሮግራም ተዘጋጅቷል። በፕሮግራሙ ላይ ወጣት ገጣሚያን እንዲሁም ታዋቂ የኪነ ጥበብ ሰዎች ይገኛሉ። እርስዎም በፕሮግራሙ ላይ ታድመው እየተዝናኑ ለወ/ሮ ዓለም ደቻሳ ቤተሰብ ስተዋፅኦ ያደርጉ ዘንድ በታላቅ አክብሮት ተጋብዘዋል።”

እነዚህን ልጆች ያኑርልን! ስል በልቤ ምርቃት አወረድኩ። መሰረትን ጨምሮ የማህሌት፣ የጆማኔክስ፣ የዮሃንስ እና የታምራት ታም “መለያ ስዕሎች” ለአለም ደቻሳ ገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም የተዘጋጀ ፎቶግራፏን ያካተተ የጥሪ ካርድ ሆኖ አገኘሁት። በዛም ውስጥ ተቆርቋሪነታቸው እና ለወገን አለሁ ባይነታቸው ታየኝ። በዕውነት እናንተ ልባሞች ናችሁ እና የእናንተ አይነት ልብ የት እንደሚገኝ ለመሪዎቻችን ጠቁሙልን እስቲ ልላቸው ወደድኩ።

አሁንም የፌስቡኬን መንገድ ይዤ ቁልቁለቱን ወረድኩት…. ሌላ አሳዘኝ ወሬ።

“ኢትዮጵያውያን እህቶቻችን በስደት እና በእብደት ላይ” በሚል ርዕስ በሪያድ የሚገኙ እህቶቻችንን ስቃይ የሚያሳይ ቪዲዮ…! በጣም አሳዛኝ ነው። በአንድ ቤት ውስጥ ለመቁጠር እንደሞከርኩት ወደ አራት የሚጠጉ እህቶቻችን በአዕምሮ መቃወስ ሲሰቃዩ ተመለከትኩ። በእውነቱ ሀዘኔ በረታ “ሙዴም ተከነተ” ፌስ ቡኬም አስጠላኝ ኮምፒውተሬም “ደበረኝ” እስከመቼ ነው በየሰዉ አገር የምንሰቃየው። መቼ ነው ኢትዮጵያ ለሁላችንም የምትበቃ አገር የምትሆነው? እስከ መቼ ድረስ መልሱ “መ” ሆኖ ይቀጥላል? ብዬ ከኮምፒውተሬ ገለል አልኩኝ።

ከተወሰኑ የቁዘማ ሰዓታት በኋለ ኮምፒውተሬን ከፈትኩ፤ ኢንተርኔቴን አገናኘሁ። ወደ ፌስ ቡክ መንደርም  ድጋሚ ጎራ አልኩ።

“እምዬ ኢትዮጵያ የጀግኖች እናት እስቲ ፈልጊልኝ የሚከራይ ቤት” የሚል ፅሁፍ ተለጥፎ አየሁ። ይህንን ፅሁፍ ከዚህ በፊትም አይቼዋለሁ። እውነትም የሚከራይ ቤት እንኳ ኢትዮጵያችን ብታገኝልን ቢያንስ በየ አረብ ሀገራቱ እህቶቻችን አየሰቃዩም ነበር። ብዬ እያሰብኩ…  ወረድ አልኩ። አሁን አሪፍ ዜና አየሁ።

እስክንድር ነጋ ታላቅ አለም አቀፋዊ ሽልማት አገኘ!

ታዋቂው እና ተወዳጁ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ “ፔን ኢንተርናሽናል” ከተባለ ድርጅት PEN/Barbara Goldsmith Freedom to Write Award. የተባለውን ሽልማት አገኝቷል።

እንደሚታወቀው እስክንድር ነጋ በአሁኑ ግዜ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ይገኛል። እንደማይታወቀውም እስክንድርን ከባለቤቱ ከልጁ እና ከጥቂት የተመዘገቡ ሰዎች ውጪ በቃሊቲ ማንኛውም ሰው ሄዶ ሊጠይቀው እንደማይችል ሰምተናል።

እስኬው ይህንን ሽልማት ማግኘቱ ሲያንሰው ነው። በሸላሚዎቹ መግለጫ ላይ እንደተገለፀው እና እኛም ስናየው እንደኖርነው እስክንድር እያንዳንዷን ቃላት ሲፅፍ ሰዎቻችን ደግሞ እስከ ሞት የሚያደርስ ጉንጉን እንደሚሸርቡለት ያውቃል። ይህንን ተጋፍጦ ነበር የሚፅፈው። በነገራችን ላይ እስክንድር ስለ ፃፈ ብቻ ከሰባት ግዜ በላይ እስራት ደርሶበታል። እርሱ ግን ወይ ፍንክች! አሁንም ያው ነው!

አንበሳ … ቀነኒሳ ሳይሆን እስክንድር ነው። ብንልስ… (ቴዲ ቢሰማ አስተካክሎ ይዘፍናት ይሆን…?)

አሁን መሸ

ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ጠራሁት “…እንኳንስ ጠርተውኝ…” ብሎ ብቅ አለ። የዜና ሰዓት ደርሷል። የዛሬው ዜና አቅራቢ ያ አሽሟጣጩ ነው። እርሱ ሰውዬ ይገርመኛል እንደምን አመሻችሁ… ሲል ጠረቤዛውን በግንባሩ ገጭቶ ነው። ከዚህ በፊት “የመተጣጠፍ ብቃትህን እናደንቃለን ቢሆንም ግን ማጎብደዱ ሲበዛ ሽሙጥ ይመስላልና በቅጡ አድርገው” ብለን ለማስመከር ሞክረን አልተሳካልንም።

ዜናው ቀጠለ “በዛሬው እለት ፀሎተ ሀሙስን አስመልክቶ የትህትና ምሳሌ የሆነው የእግር ማጠብ ስነ ስርዓት ተካሄደ። ብፁህ አቡነ ጳውሎስ የካህናትን እግር አጥበዋል” ብሎ የአቡኑን ትህትና ሊያሳየን ሞከረ።

እኔም በሀሳቤ የአቡኑ በርካታ ትህትናዎች መጡብኝ…

ትህትና አንድ

የዛሬ ስንት አመት እንደሆነ እንጃ በመስቀል አደባባይ የደመራ ስነ ስርዓት ይከናወን ነበር። ታድያ አባታችን ፀሎት እንዲመሩ መነጋገሪያ “ማይክራፎን” ተሰጣቸው። እሳቸውም የዛኔ በምን ተበሳጭተው እንደነበር እንጃ “እስቲ ዞር በሉልኝ ምድረ ጭቃ!” ሲሉ በቀጥታ ቴሌቪዥን ተላለፉ። እኔም ለርሳቸው “ትህትና” አምስት ሳንቲም እስከማክል ድረስ ተሸማቀኩላቸው።

ትህትና ሁለት

እኔ የምለው ቦሌ መድሃኒያለም ልንሳለም ስንሄድ ዛሬም መጀመሪያ የምንሳለመው የብፁህ አባታችንን ሀውልት ነው አይደል? ከትህትናቸው ብዛት የገዛ ሀውልታቸውን መርቀው የከፈቱ ብቸኛ ሰው “አባታችን” መሆናቸው ነው። (በነገራችን ላይ አቡነ ጳውሎስን ዋና ዋና የኢህአዴግ ሰዎች “ብፁህ አባላችን” ነው የሚሏቸው ሲባል ሰማሁ። እውነት ነው እንዴ እስቲ አጣሩልኝ! (ይቺ እንደ ለከፋ ትቆጠርልኝ))

በመጨረሻም

ስለ ስቅለት

ስለ ስቅለት ትንሽ ለማለት ሳስብ ስብሀት ገብረእግዚአብሄር ትዝ አለኝ አንድ ወቅት ይህንን አውግቶ ነበር እስቲ እናስታውስ፤

ኢየሱስ መስቀሉን ተሸክሞ ወደ ጎልጎታ ተራራ እየሄደ ነበር። መንገድ ላይ አንድ የዛፍ ጥላ ያለበት ቦታ አገኘ። ይሄኔ ትንሽ ፋታ ባገኝ ብሎ ርምጃውን ቀስ አደረገ። ታድያ ዛፉ ጥላ ስር አንድ ባለ ሱቅ ነበር እና በግርግሩ ገበያው እንዳይቀዘቅዝ አስቦ “ባክህ ሂድ አትንቀራፈፍብኝ” ብሎ ጌታን አመናጨቀው። ኢየሱስም ቀና ብሎ አየውና “እኔስ እሄዳለሁ አንተ ግን እስክመለስ እዚሁ ትጠብቀኛለህ!” ብሎት ሄደ። ስብሀት እንዳለን ከሆነ ያ ሰውዬ አሁንም ጭምር ሀገር እየቀያየረ ይኖራል።