ሰሞነ ቴዲ አፍሮ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ቴዲ አፍሮ ሰሞኑን “ጥቁር ሰው” የሚል የሙዚቃ አልበም ይለቃል ተብሎ በጉጉት እየተጠበቀ ነበር። እንደሚታወቀው የቴዲ አፈሮ ሙዚቃ መልቀቅ ከኢህአዴግ ስልጣን መልቀቅ እኩል በጉጉት የሚጠብቁት ብዙዎች ናቸው። እኔም… አንዱ ሳልሆን አልቀርም።

ታድያ ቴዲ ሙዚቃውን ከመልቀቁ ከጥቂት ቀናት አስቀድሞ በርካቶች በራሱ በቴዲ ላይ ነጠላ ዜና ሲለቁ ሰምተናል። (በዚህ አረፍተ ነገር አግባብ “ዜና” ማለት ወሬ ማለት ነው። ለነገሩ በሌላ አረፈተ ነገር አግባብም ዜና ወሬ ነው ለካ!)) እናም ከነጠላ ዜናዎቹ ውስጥ አንዱ “ከኔ በላይ መንፈሳዊነት ላሳር” ያለ ግለሰብ፤ “ሙዚቃ ሀጥያት ነው!” በሚል መፈክር ከመፅሀፍ ቅዱስ ሁሉ ጠቅሶ፤ የቴዲ አፍሮን አልበም እንዳንገዛ አስጠንቅቆናል። እንደዚህ “ሀይማኖተኛ” ማሳሰቢያ ቢሆን ኖሮ” እንኳንስ የሙዚቃ አልበሙን እና ቤቱ እንኳ ስንሄድ የፎቶ አልበሙን አናይም ነበር።

ከ “አማኙ” የወዮላችሁ አዋጅ ስር በርካታ አስቂኝ አስተያየቶች ተለጥፈዋል። ከነዚህ ውስጥ አንዱ፤ “እሺ ሙዚቃ ሀጥያት ነው ካላችሁ ለምን ከፍቅረ አዲስ ወይም ከሰሜ ባላገሩ ጀምራችሁ አታውጁም ነበር?” ብሎ ጠይቋል።

እኔም በሆዴ ፍቅር አዲስስ እሺ ለባለ አወሊያ ትዘፍን ነበር፤ ሰማህኝ ደሞ ምን አደረገ? ብዬ ጠይቄ መልሱን አላገኘሁትም። እኔ የምለው ሰሜ ባላገሩ ግን “በተቀነባበረ መልኩ ሰው ገድሏል” ተብሎ ከታሰረ በኋላ የተለቀቀው ለአባይ በመዝፈኑ ነው” የሚለውን “ቡጨቃ”  እንዴት ታዩታላችሁ? እንጃ… እኔ በበኩሌ አላምንም…!

ሌላው በቴዲ አፍሮ ላይ የተመለከትኩት “ነጠላ ዜና” ጥርጣሬ ወለድ ነው። አንዳንድ ጠርጣራሮች ቴዲ ከዚህ በፊት በደረሰበት እስር የተነሳ የፍርሃት ቆፈን ይዞታል። ከሚል መነሻ፤ “የቦብ ማርሊን ስዕል ደረቱ ላይ ለጥፎ ስለፍቅር ብቻ መዝፈን ጀምሯል… ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ጆሮ ዳባ እያለ ነው። በአዲሱ አልበሙም ከፍቅር ዜማ ውጪ የሚኖረው አይመስለኝም እንደዛ ከሆነ ግን…” እያለ በነጠብጣብ የሚቀጥል ማብጠልጠል ሲያብጠለጥሉት ሰሙነዋል።

ለጠርጣራም ጠርጣራ አለውና የእነዚህን ወዳጆቻችንን ንግግር “ኢህአዴግ አመሳስሎ የሰራው ነው” ሲሉ የጠረጠሩት ብዙዎች ናቸው።

በነገራችን ላይ እናት ድርጅታችን ኢህአዴግ ከምትታማባቸው ነገሮች ውስጥ ከአቅሟ በላይ ልጆች በመሰብሰብ ነው። በተለይ ደግሞ እንደ ቴዲ ያሉ ያደጉ እና የበለጠጉ ልጆችን ከእናታቸው ጉያ ነጥቃ በእንጀራ ልጅነት እንደመጠቅለል የሚያስደስታት የለም… ይባላል። (እንግዲህ ይባላል ነው ያልኩት አታኩርፉኛ…) እውነቴን እኮ ነው። እንደሰማሁት ከሆነማ፤ ለምሳሌ ቴዲ አፍሮ የህዝብ ልጅ ነው። ታድያ እናት ኢህአዴግ ምን ታደርጋለች አሉ፤ እንደምንም ብላ ከእናቱ ህዝብ አጣልታም ቢሆን ማለያየት ከዛስ…? ከዛማ ትንሽ ትንከባከብ እና ሳያስበው ኋላ ኪሷ አስገብታ ቁጭ ትልበታለች አሉ።

የዚህ የኋላ ኪስ ሰለባ ከሆኑት መካከል ሰለሞን ተካልኝ እና … እና ማን ነበር ስሙ አፌ ላይ እኮ አለ… ንዋይ ደበበ ይጠቀሳሉ ሲባል ሰምቻለሁ። (መቼም እኔ ወሬ መደበቅ አይሆንልኝ!)

እና ታድያ አሁንም ቴዲን ከእናቱ ከህዝብ የሚለይ መግለጫ በየቦታው ተለጥፎ ነበር። “ቴዲ የህዝብ እና የሀገርን ነገር ትቷል ከዚህ በኋላ የኛ መሆኑን እንጃ…” የሚል ይዘት ያለው ልጥፍ በየፌስ ቡኩ ተለጥፎ ነበር።

በዚህም ላይ ግማሹ “ቴዲ አፍሮን ድሮውንም ለአገረ ገዢነት አልመረጥነውም እናም ያሻውን ሙዚቃ ቢያቀነቅን መብቱ ነው፤ ከጣመን እንሰማለን ካልጣመን ራሳችን እናንጎራጉራለን” ብሎ ሲሟገትለት ገሚሱም ደግሞ “ሰውን ማመን ቀብሮ ብላለች ቀበሮ ብዬ ገጠምኩልህ ስማኝ ቴዲ አፍሮ” እያለ በስንኝ ቀጠሮ በተቀደደለት የፀብ ቦይ ሲፈስ ታይቷል።

ይህ በሆነ በነጋታው ነው መሰለኝ ጠቅላይ ሚኒስትራችን የቴዲን ጥቁር ሰው አልበም ከፍ አድርገው ይዘው የሚያሳይ ፎቶግራፍ በየ ኮምፒውተራችን ደጃፍ ቆሞ አገኘን። ይህም “ቴዲ በእጃችን ገባ እነሆ ከኛ ዘንድ ነው…” የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ዋና የፌስ ቡክ ስራ ሂደት ባለቤቶች የለጠፉት ሳይሆን እንደማይቀር ይገመታል።

እነሆ የቴዲ አልበም ሳይለለቅ በፊት በርሱ ላይ የሚለቀቁ ነጠላ ዜናዎች በረከቱ። እንደ ነገ ፋሲካ ሊሆን እንደ ዛሬ ግን ተናፋቂው ሙዚቃ ሲጋልብ መጣ!

ለእምዬ ምንሊክ የተዘፈነው ጥቁር ሰው!

ኢህአዴግ ይበልጡንም ደግሞ ህውሃት ሚኒሊክን እንዴት አድርገው እንደጠመዷቸው ልብ ስል አደዋ ላይ ሚኒሊክ ድል የነሱት ጣልያንን ሳይሆን ህውሃትን ነበር እንዴ? ብዬ እጠይቃለሁ። ባለፈው ግዜ እምዬ ምኒሊክን ክፉኛ የሚያንጓጥጥ መፅሐፍ ከህውሃት ወዳጆች አንዱ የሆኑ ሰው አሳትመው ነበር። በዛ ላይም እንዳየነው ከኢህአዴግ ወላጅ አባቶች አንዱ የሆኑት አቦይ ስብሀት ፀሐፊውን “እጅህ ይለምልም!” ብለው ከሞካሹ በኋላ በሚኒሊክ ላይ ዘመቻው እንደሚቀጥል ተናግረው ነበር። እኔማ ጭንቅ ቢለኝ እነዚህ ሰዎች እርሳቸውን እናሳድዳለን ሲሉ የተቀበሩበት ጉድጓድ ውስጥ እንዳይገቡ ስል እፈራላቸዋለሁ። አዎና ወዳጄ “እልህ ሳንጃ ያስነክሳል” ያሉት እኮ የኛ ሰዎች ናቸው!

የሆነ ሆኖ  “ጥቁር ሰው” ሙዚቃ አፄ ሚኒሊክን ድጋሚ ያነገሰ ቢባል ይገባዋል። ሙዚቃው ሲጀምር በደቡቤዎች ዜማ ይጀምርና ሚኒሊክ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆኑ የመላው ጥቁር ንጉስ መሆናቸውን በይፋ አውጆ በአማርኛ እና በኦሮምኛ ቋንቋዎች እየተላቆጠ ይንቆረቆራል። በዚህም በርካታ የአራዳ ልጆች “ጀዲካ” እያሉ ረገዳ ጨፍረዋል። ከእልልታ ጋርም  እስክስታውን አቅልጠውታል።

አሁን እንግዲህ ሰሞነ ቴዲ አፍሮ ገብቷል።

“ጥቁር ሰው” ሙዚቃ ብቻ አይደለም። ህብረት ነው። አንድነትም ነው። ነፃነትም ነው።

ውይ አፈር ስሆን ይሄ የሙዚቃ ሲዲ “አቦይ ስብሀት እና ባልደረቦቻቸው የማይደርሱበት ቦታ ይቀመጥ!” የሚል ካልተፃፈበት አደጋ አለው! እንዴት ማለት ጥሩ ጥያቄ ነው።

ባለፈው ግዜ በኮምፒውተሮቻችን እንዳየነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደዋዛ ያያዙት የቴዲ ሙዚቃ በውስጡ ሚኒልክን የሚያከብር መሆኑን ቢያውቁ በሀዘን ክልትው ይሉብናል። ቀልዴን አይደለም። “ህውሃት ከማይደርሱበት ቦታ ይቀመጥ” ተብሎ ይፃፍበት። እኔ ተናግሪያለሁ!

በመጨረሻም

የቴዲ አፍሮን ጥቁር ሰው ሙዚቃ የሰማሁት አልበሙን ገዝቼ ሳይሆን ኢንተርኔት ላይ ተለቆ አግኝቼው ነው። ሙዚቃው በርሱ ፈቃድ ይለቀቅ አይለቀቅ እንጃ። ያለ ባለቤቱ መልካም ፈቃድ የተለጠፈ  ከሆነ ግን  አግባብ አለመሆኑን  አምኜ  ንስሀ እገባለሁ። ሌሎችንም እመክራለሁ  እባካችሁ ኦሪጅናል እንግዛ!

መልካም ፋሲካ ብያለሁ እንዴ… አሁን ልበላ! (አረ ባለቅኔው አትሉኝም?)