ተመስገን ደሳለኝ ፍርድ ቤት ቀረበ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የሆነው ተመስገን ደሳለኝ “በአንዷለም አራጌ፣ እስክንድር ነጋ እና ናትናኤል መኮንን ላይ ያቀረብከው ፅሁፍ በፍርድ ሂደቱ ጣልቃ መግባት ነው” ሲል አቃቤ ህግ በከሰሰው መሰረት ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረበ።

ልደታ በሚገኘው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሶስተኛ ምድብ ችሎት ዛሬ ጠዋት የተከሰሰበትን እንዲያስረዳ ቀርቦ የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን በችሎቱ በተገኘበት ወቅት ከተጠበቀው በላይ ሰው በመምጣቱ ችሎቱ ሰፋ ወዳለ አዳራሽ እንዲቀየር ተደርጓል።፡

ተመስገን መከላከያውን በኮምፒውተር ታይፕ አድርጎ ቢያቀርብም “ጥቅጥቅ ያለ ፅሑፍ በመሆኑ አይነበብም እና አስተካክለህ ተመለስ” ተብሎ ለከሰዓት በኋላ ተቀጥሯል። እንደ ምንጬ ገለፃ ከሆነ ተመስገን ፅሑፉ አይነበብም ባሉት ግዜ “እኔ ይነበብልኛል ላንብብላችሁ” ብሎ ፍርድ ቤቱን በትህትና ጠይቆ ነበር። ነገር ግን የተመስገን “ላግዛችሁ” ጥያቄ ውድቅ ሆኗል።

በፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ላይ የቀረበበት ክስ እንደሚለው ከሆነ  በፍርድ ቤት የተያዘ ነገር ላይ ጣልቃ ገብቶ ዘገባ ማቅረብ “ነውር” መሆኑን፤ የሚያስጠይቅም እንደሆነ ያትታል።

በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይህንኑ በፍርድ ቤት የተያዘ የእነ አቶ አንዷለም አራጌ ጉዳይ ላይ “አኬልዳማ” የሚል ፊልም ሰርቶ “አሸባሪ” እያለ ሲፈርጃቸው እንደነበር ይታወቃል። እርሱ ብቻም አይደለም፤ አቶ አንዷለም አራጌ፤ “ይህ ጉዳይ በህግ አግባብ ትክክል ባለመሆኑ የፍርድ ሂደቱ ሳያልቅ እንደ ወንጀለኛ የቆጠረን ኢቲቪ ይጠየቅልን” ብለው አመልክተው እንደነበረም ይታወቃል። አሁንም ይህ ብቻ አይደለም፤ ኢቲቪን ማንም ፍርድ ቤት እንዳላቀረበውም ይታወቃል። (የማይታወቅ ከሆነም አሁን ይታወቅ)

በመጨረሻም 1

የፍትህ ሳምንት ክብረ በዓል ከዛሬ ጀመሮ ለአንድ ሳምንት እንደሚከበር ትላንት ነግሬያችኋለሁ። እንዳልኳችሁ በኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓቱ በጣም ተሻሽሏል።

በመጨረሻም 2

ትላንት ተመስገን በፌስ ቡክ ገፁ ላይ እንዳወጋን ፍትህ ለህትመት በምትገባበት ቀን ዘወትር ሀሙስ መብራት ይጠፋል። እንደ ተሜ ገለፃ “መብራቱን ማን እንደሚያጠፋው ከፈጣሪ በስተቀር የሚያው የለም።” እንደኔ ጥርጣሬ ደግሞ ባልቦላውን የሚመልሰው የኤልፓ ሰራተኛ እና አለቃውም እንደሚያውቁ እገምታለሁ።

እዝችው ላይ ይህንኑ አጋጣሚ አውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ላይ በምጫጭርበት ወቅትም አስታውሳለሁ። ብዙውን ግዜ አውራምቦች አርብ አርብ “መብራት ተረኛ ነበሩ” ይሄ ነገር ቢሮ በቀያየሩ ቁጥር ሲከተላቸው እንደነበረም ትዝ ይለኛል። ያኔ በየዋህ ልቦና ነገሩ “የቤት ጣጣ” ይመስለኝ ነበር!

አሁን በአዲሳባ ገበያ ላይ “አርብ አርብ ይሸበራል ኢየሩሳሌም” ብላ በዕለተ ጁምአ ብቅ የምትለው ፍትህ ጋዜጣም በየ ሀሙሱ መብራት እየጠፋባት ተቸግራለች።  ባለፈው ሳምንት መብራቱን ያጠፋው ሰውዬ የህንፃውን በሙሉ ማጥፋት ሲገባው የፍትህን ለይቼ አጠፋለሁ ሲል ከፍትህ ዋና ቢሮ ጋር የማይገናኘውን የመፀዳጃ ቤቱን መብራት ስቶታል። በዚህም ምክንያት ፍትህ መፀዳጃ ቤት በር ላይ ታይታለች።

ይሄንን የቤት ጣጣ ማለት ከባድ ነው… “የመንግስት ጣጣ!” ሳይሆን አይቀርም!

አሽሙረኞችም ብለዋል “እነሆ ፍትህን ከመፀዳጃ  ቤት ደጃፍ የጣላችሁ እናንተ የፍትህ ሳምንትን ማክበር ይቻላችኋልን?”

Filed under: Uncategorized