የካድሬው የፍቅር ደብዳቤ 3


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ይህ ፅሑፍ “አርብ አርብ ይሸበራል ኢየሩሳሌም” በተባለበት በዕለተ ጁምአ ለምትታተመው ፍትህ ጋዜጣ የተሰናዳ  ነው። ከጋዜጣዋ ርቃችሁ ለምትገኙ ወዳጆች ደግም እነሆ በዚህ መልኩ…

የፍቅር ደብዳቤውን ያሰናዳው ታታሪ ካድሬ ከዚህ በፊት ቁጥር አንዱን በአውራምባ መፅሔት፣ እንዲሁም ቁጥር ሁለቱን ደግሞ በአውራምባ ጋዜጣ ላይ ታትመውለታል። የዛሬውም የነዛ ተከታይ መሆኑ ነው። እሱም ይበርታ ይበርታ እና ይፃፍ ፤ እርስዎም ይበርቱና ያንብቡለት!

ይድረስ እንደ ሰማህታት ሀውልት በልቤ ውስጥ ለተተከልሽ፣ እንደ መደበኛ ግምገማ ሁሌ ለምታስጨንቂኝ፣ እንደ ድርጅታችን አርማ ዘወትር ለምትታይኝ፣ እንደ ውሎ አበል ለምትናፍቂኝ ውድ ፍቅሬ፤ ለጤናሽ እንደምን አለሽ? መቼም የተዘረጋው የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም እያለ እንከን ያጋጥምሻል ብዬ አላስብም!

የኔ እመቤት እኔ ከድርጅታዊ ስራዬ ጎን ለጎን፤ ዘወትር አንቺን ማሰብ እና ስለ አንቺ መጨነቅ ኦቨር ታይም የማልጠይቅበት በራስ ተነሳሽነት የማከናውነው የየዕለት ተግባሬ ሆኗል።

የኔ ውድ ይሄን  ሰሞን  ደግሞ ለምን እንደሁ እንጃልኝ ከእጄ የምታመልጪኝ እየመሰለኝ ስጨነቅ እና ስጠበብ ከርሜልሻለሁ።

ያስያዝሽኝ ፍቅር ህዝባዊ መሰረት እንዳለው ፓርቲያችን የጠነከረ ነው። ቢሆንም ከአንቺ ዘንድ ያለውን ቁርጠኝነት እስከ አሁን ባለማወቄ የተነሳ እሰጋለሁ። ከአሁን አሁን የኪራይ ሰብሳቢነት ባህርይ የተጠናወታቸው ግለሰቦች ወስደው ለግላቸው ያደርጓት ይሆን? ብዬ እጨነቃለሁ።

ያው አንቺም እንደምታውቂው በአሁኑ ግዜ የሁላችንም ዋነኛ ችግር ሙሰኝነት፣ ግለኝነት እና ኪራይ ሰብሳቢነት ነው። ለሰዎች ያለማሰብ ለህብረተሰቡ ያለመጨነቅ የዘቀጠ አሰራር በየቦታው ተንሰራፍቷል። ታድያ ምድረ ኪራይ ሰብሳቢ እንደ መሬት ወረራ ሊቀራመትሽ የሞት ሽረት ትግል ሲያደርግ እየታየኝ ከአሁን አሁን አጣት ይሆን ብዬ እጨነቃለሁ።

የኔ እመቤት ነጋ ጠባ በስስት ነው የምመለከትሽ። በሀገሪቱ ላይ የሚነሳ ማነኛውም ጉምጉምታ አንቺን የሚያሳጣኝ እየመሰለኝ ስጨነቅ ብትመለከቺኝ ታዝኚልኝ ነበር። ጋዜጠኞች የሚያስቡት፣ ፖለቲከኞች የሚናገሩት፣ መምህራን የሚጠይቁት ሁላ እኔ እና አንቺን ለማለያየት ታስቦ ነው ስል እጨነቃለሁ። የኔ ቆንጆ የአወሊያው ሰላት፣ የዋልድባው ሱባኤ ሳይቀር እኔን ከአንቺ ለመነጠል ሆን ተብሎ የሚጠነሰስ ሴራ እየመሰለኝ ስጋቴ እንደ ዋጋ ግሽበቱ ከእለት እለት እየጨመረብኝ ነው።

እውነቱን ለመናገር አንዳንድ ግዜ ሰዉን በሙሉ በአሸባሪነት ክስ ዘብጥያ አውርጄ ብቻችንን የምንኖርባት ምድር ለመፍጠር እመኛለሁ።

አበዛኸው አትበይኝና ማንም እንዲጠጋሽ አልፈልግም። እንኳንስ ሌላ ቀርቶ ጥቃቅን እና አነስተኛ ማህበራት፣ የወጣቶች እና ሴቶች ሊግ፣ እንኳን አንቺን በነፃነት እንዲያቅፉብኝ አልሻም። እኔው ማህበር ልሁንሽ የኔ ቆንጆ፣ እኔው ላደራጅሽ የኔ እመቤት፤ እኔው ልቀፍሽ የኔ ሸጋ። እመኚኝ እሺ ካልሽኝ፤ በአጭር ግዜ መካከለኛ ፍቅር ካላቸው ግለሰቦች ተርታ እንሰለፋለን።

እሳሳልሻለሁ።

ለዚህም ነው፤ ተሳክቶልኝ ከአንቺ ጋር ግንባር ፈጥረን አብረን መኖር እስክንጀምር ድረስ ማንም እንዳያይብኝ፣ ማንም እንዳይረብሽብኝ፤ ብድር እና ቁጠባ ተቋም ውስጥ ላስቀምጣት ይሆን…? ብዬ የማስበው።

እውነቴ ነው የኔ ቆንጆ እንደምታውቂው፤ ከለበስኳት ሱፍ እና ከጥቂት መፅሀፎቼ ውጪ የሚቆጠብ ገንዘብ የለኝም። ሀብቴ አንቺ ነሽ። አንቺኑ ልንከባከብ፤ አንቺኑ ለዘላለም እንድትቆይ ክፉም እንዳይነካሽ፤ በቁጠባ ባንክ ላስቀምጥሽ። እናም ከጫጫታውም ከግርግሩም የፀዳሽ ሁኚልኝ።

አረ የኔስ ስስት ለጉድ ነው፤ ሰሞኑን ያ ቴውድሮስ ካሳሁን ያወጣው አዲስ ዘፈን ተለቆ፤ ከተማዋን የግሉ ጭፈራ ቤት አስመስሎት የለ? እናልሽ ፍቅሬን በሙዚቃ ሊበጠብጡብኝ ነው እንዴ? ብዬ ለመላው የከተማ ነዋሪ ሙዚቃውን እንዲቀንሱ መመሪያ መስጠት ሲያሰኘኝ ሰንብቶልሻል። እውነቴን ነው የኔ ቆንጆ አንቺ ካልሽኝ አደርገዋለሁ። አንቺን  ለመጠበቅ እንኳንስ ሙዚቃ ወንዛ ወንዙን ሁሉ እገድባለሁ።

አረ ሳልነግርሽ በቅርቡ ጓደኞቼ የዳቦ ስም አውጣላት ብለው አበሳዬን ሲያሳዩኝ ነበር። እንደ አቅጣጫ፤  ሳንጋባ የዳቦ ስም ሊኖር እንደማይችል ግንዛቤው አለኝ። ነገር ግን እውነትም ከወዲሁ ቅደመ ዝግጅት ባደርግ አይከፋም ብዬ አንዳንድ ስሞችን መርጨልሻለሁ።

ሚሊኒየም አበባ

ልክ አንቺን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር እንዳዋልኩ ያኔ ለእኔ አዲስ ጊዜ፤ አዲስ ዘመን እንደመጣልኝ እቆጥረዋለሁ። ያ ግዜ ግን መቼ ይሆን…? በአስተማማኝ ሁኔታ እጄ ላይ ሆነሽ ለሚቀጥሉት አርባ እና ሃምሳ… አረ ያንሳል መቶ አመታት አብረን እንድንኖር እፈልጋለሁ።

ቦንድ አለሜ

ይህንን ስም የመረጥኩልሽ ልማት ላይ ያለሽን ቁርጠኝነት አሳምሬ ስለማውቅ ነው። “እኔ ለአባይ በገንዘቤም በጉለበቴም ዘራፍ እላለሁ!” ያልሽ የልማት አርበኛ መሆንሽን መቼ አጣሁት? ከዛም በላይ ግን አንቺ ማለት ዛሬ በቁጠባ ባንኬ ያስቀመጥኩሽ እና ነገ የምመነዝርሽ ሀብቴ መሆንሽን ለማመላከት “ቦንድ አለም” ብዬሻለሁ።

ህዳሴ ወርቅ

አንቺ ለእኔ አዲስ ህይወት ነሽ። ባለፉት ጨቋኝ ሴቶች ከፍቅር ልማት ርቆ የቆየው ልቤ በአንቺ  እንደሚያገግም አዲስ ራዕይ ይታየኛል። እንግዲህ መቶ ፐርሰንት የእኔ ከሆንሽ ከዚህ በላይ ህዳሴ ከየት ይመጣል?

የኔ እመቤት ይሄ ብቻ አይምሰልሽ በርካታ ስሞችን አዘጋጅቼልሻለሁ። “ግድብ ነሽ፤ ሽብር ይራቅ፣ ልማቴ፣ ሊዝ አዋጄ…” ምን ያላልኩሽ አለ! የአንቺን ይሁንታ ብቻ ላግኝ እንጂ ያዘጋጀኋቸውን ስሞች በሙሉ ከነ ምክንያቶቼ ዘርዝሬ እነግርሽ እና አሳታፊ በሆነ መልኩ ተወያይተንበት አንዱን እናፀድቃለን። በአካሄዴ እንደምትደሰቺ ባለ ሙሉ ተስፋ ነኝ።

እመቤቴ፤

በየ አቅጣጫው የተነሱ ፀረ ፍቅር ሃይሎች በተቀነባባረ መልኩ ሊያለያዩን እንደሚያሴሩ አውቃለሁ። አንቺም ይህንን ግንዛቤ ልትወስጂ ይገባል። ማንም ወደዳጅ መሳይ መጥቶ ጥገኛ እንዳይሆንብሽ ጥንቃቄ አድርጊ። ዘንድሮ ማንም የማይታመንበት ሁኔታ ነው ያለው።

ውዴ

እንደምንም ብዬ አውራ ፓርቲሽ ሆኜ ለዘለቄታው አብሬሽ መኖር እስክንጀምር ድረስ ራስሽን ከኒዮ ሊበራል ሀይሎች ጠብቀሽ እና በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ሀይማኖትሽ ፀንተሽ እንደምትጠብቂኝ ዘጠና ዘጠኝ ነጥብ ስድስት በመቶ እርግጠኛ ነኝ!

ከሰላምታ ጋር!