አበበ ቀስቶ ተመስገን ነፃ ነው ሲል መሰከረ!


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ በእነ አንዷለም አራጌ የክስ መዝገብ የተከሰሱ ሰዎችን ቃል በጋዜጣህ ላይ አትመሃል ይህም በፍርድ ሂደቱ ጣልቃ መግባት ነው ተብሎ ተከሶ እንደነበር ይታወቃል። (ካልታወቀም አሁን ይታወቅ… ልል ነበር በዜና ላይ አይቀለድም ለካ…)

ተሜ የተከሰሰበት ጣልቃ መግባት ክስ የአንዷለም አራጌን፣ የእስክንድር ነጋ፣ የናትናኤልን እና የአበበ ቀስቶን ፅሁፍ በጋዜጣህ ላይ በማተምህ የሚል ሲሆን፤ ተመስገንም “ተጠቃሾቹ የሰጡኝን ፅሁፍ የማተም መብት አለኝ” ሲል ተከራክሮ ነበር።

በዚህም ምክንያት “እውነትም ተጠርጣሪዎቹ ፅሁፉን ሰጥተውት ነበር ወይ?” የሚለውን ለማጣራት ለእማኝነት የተጠራው አበበ ቀስቶ… “ፅሁፉ የኔ ነው በወጣው ነገር መጠየቅ ካለብኝ የምጠየቀው እኔ ነኝ እንጂ ተመስገን አይደለም። በጋዜጣው ላይ የታተመው በፍርድ ቤት ላቀርበው እፈልግ የነበረ ሃሳብ ነው። ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ግዜ ሊሰጠኝ ስላልቻለ እንዲታተም ሰጥቼዋለሁ…” ብሎ ሲናገር ዳኛው “ንግግርህን አሳጥር ይህንን የጠየቀህ የለም” በማለት አቋርጠውታል።

በዛሬው የተመስገን ደሳለኝ ችሎት ካለፉት ግዚያት የበለጠ በርካታ ሰው ተገኝቶ እንደነበር ከስፍራው የደረሰኝ ወሬ ያስረዳል።

ፍርድ ቤቱ የምስክሩን ክንፈ ሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) ቃል ከሰማ በኋላ ለሚያዝያ 22 ቀጠሮ ሰጥቶ ተበትኗል።

በነገራችን ላይ ሚያዝያ 24 ኢቲቪም በአኪልዳማ የተነሳ ፍርድ ቤት እንደሚቆም ባለፈው ተጨዋውተናል አይደል። እስቲ የሚባለውን እንጠብቃለን!