ርዕዮት አለሙ ኦፕሬሽን አደረገች (አቤ ቶኪቻው)


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ጋዜጠኛ እና መምህርት ርዮት አለሙ “አሸብረሽናል” ተብላ አስራ አራት አመት እስር እና ሰላሳ አምስት ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባት (መቼም የዛሬ ፈራጅ ከየት ይመጣል ብሎ አያስብም…) ብቻ በአሁኑ ሰዓት በቃሊት እስር ቤት ትገኛለች።

ርዕዮት ከፍርዱ በፊት “ኤልያስ ክፍሌ አሸባሪ ነው” ስትይ መስክሪ እና ትፈቻለሽ ተብላ፤ በማስፈራራትም በማባበልም ብትጠየቅ አሻፈረኝ “እኔ የማውቀው ኤልያስ ጋዜጠኛ እንደሆነ ነው። በማላውቀው ጉዳይ ላይ አልመሰክርም።” ብላ በአቋሟ በመፅናቷ አሳሪዎቿ፤ “እንዲህ ጠንካራ አቋም ካለሽ ለምን ጫካ አትገቢም”  ብለው ሲዘባበቱባት እንደነበር በዛ ሰሞን ስንሰማ ሰንብተናል።

ታድያ ይቺ መምህር እና ጋዜጠኛ ርዮት አለሙ በጡቷ አካባቢ ያጋጠማትን ተደጋጋሚ ህመም ለእስር ቤቱ ኃላፊዎች ስታመለክት የቆየች ሲሆን አንድ ግዜ “ፓራሲታሞል ዋጪበት” ስትባል። ሌላ ግዜ ደግሞ “አንቺን ሃኪም ቤት የሚወስድ ሴት ፖሊስ የለም” እየተባለች በህመም ስትሰቃይ ቆይታለች።

ማክሰኞ ሚያዝያ 16/2004 ዓ.ም ግን ፓራሲታሞሉም ከቃሊቲ አለቀ፣ ሴት ፖሊስም ተቀጠረ መሰለኝ (ይሄ የኔ ጥርጣሬ ነው) ፖሊስ ሆስፒታል ተወስዳ ነበር። ርዕዮት በሆስፒታሉ ኦፕሬሽን አድርጋ በዛው ቀን ወደ ቃሊት እስር ቤት ተመልሳለች። አረ ግፍ ነው… ትንሽ እንኳ አረፍ ሳትል? ቢሉ የሚመልስልዎ መንግስት የለም።

በአሁኑ ግዜ መመህርት እና ጋዜጠኛይቱ “አሸባሪ” ሻል እያላት መሆኑንም ሰምቻለሁ!

በመጨረሻም

ኦፕሬሽን ስል ምን ትዝ አለኝ መሰልዎ…

ርዕዮት በታሰረችበት የነ ኤልያስ ክፍሌ የክስ መዝገብ ከታሰሩት መካከል የአውራምባው ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ በፍርድ ቤት ማስረጃ ሆኖ ከቀረበበት የስልክ ለውውጥ ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፤

ውቤ ወንድሙ ከውጪ ሃገር ይደውልለታል። የሚጠይቀው ስለ አባታቸው ህመም ነበር። ታድያ ወንድምየው… “እሺ አሁን አባባ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?” ይለዋል። ውብሸትም “ኦፕሬሽኑ ተከናውኗል። ስለዚህ ገንዘብ ብትልክልኝ ደስ ይለኛል” ብሎ ይመልስለታል።

እናልዎ ጠላፊው ከመጀመሪያው ጀመሮ ስልኩን በትጋት አልጠለፈም መሰለኝ… “ኦፕሬሽኑ ተከናውኗል ገንዘብ ብትልክልኝ ደስ ይለኛል” ያለውን ብቻ ቀድቶልዎ…   “ኦፕሬሽንን” ያልከው የሽብር ኦፕሬሽን ነው። በሚል ማስረጃ ሆኖ ቀረበልዎታ…

አረ ይሳቁ ወዳጄ ከት ብለው ይሳቁ እንጂ…!