ከጋሽ ስብሐት ጨዋታዎች… አቤ ቶኪቻው


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


አንጋፋው ደራሲ ስብሐት ገብረ እግዚአብሄር ነብሱን ይማረው እያልን ማውራት ከጀመርን ሰማንያ ቀን እንደሚሞላው በቅርቡ አንድ ወዳጃችን በለጠፈው ማስታወሻ አስታውሰናል። እንደውም ዛሬ ሳይሆን አይቀርም… የሆነ ሆኖ ከዚህ ቀጥሎ ጋሽ ስብሀት ፅፎት በሳቅ ፍርስ ካደረገኝ ጨዋታ መካከል የሚከተለውን እንድናወጋ ወደድኩ…  እንደሚከተለው አስታውሳለሁ!

በቀድሞ ግዜ ከነበሩ “ዋና ሰዎች” መካከል አሉ የሚባሉ አንድ ባለስልጠን ቀኟዝማች ይሁኑ ግራ አዝማች ወይም ፊታውራሪ ረስቼዋለሁ… ዘመቻ ሄደው ሲመጡ ታሪኩ ይጀምራል።

ዘመቻው ሁለት አመት የፈጀ ነበር። እናም ባለታሪካችን ከሁለት አመት ቆይታ በኋላ ነው ማለት ነው የሚመለሱት። መጀመሪያ የተቀበላቸው ታድያ ማነው…? ገብሬ። ገብሬ ማነው…? ገብሬማ የባለታሪካችን ዋና አገልጋይ ነው። መንገድ ገብሬ እቃቸውን ተሸክሞ ከፊት ከፊት እየሄደ፤ ጨዋታ ተጀመረ…

“እሺ ገብሬ ሀገሩ ሰላም ነው…?”

“ሰላም ነው ጌታዬ… ሁሉ ሰላም ነው… ብቻ…” አለ ገብሬ የጌታውን እቃ ተሸክሞ ከፊት ከፊት ኩስ ኩስ እያለ።

“ብቻ ምን…? አንተ የተፈጠረ ችግር አለ እንዴ?”

“የለም ጋሼ ብዙ አይደንግጡ… ብቻ ጉራች መሞቱን ልነግረዎ ነው” አላቸው። ጉራች ማነው…? ያላችሁ እንደሁ ጉራች ባለታሪካችን አብዝተው የሚወዱት በሬ ነበር።

“ውይ አፈር ስሆን… ጉራች ሞተ…!?”

“አዎ ጌታዬ…! ሞተ…! ምፅ…” ኩስኩስታውን ገብሬ ቀጥሏል።

“ምን ሆኖ ሞተ በል…?” አሉ ባለታሪካችን፤ እንኳንም ሌላ መርዶ አልነገርከኝ በሚል ዜማ!

“እሱማ… ለእሜቴ ተስካር ታርዶ ነው ጌታዬ…!” አለ። እሜቴ እኮ ባለቤታቸው ናቸው!

ክው አሉ ባለታሪካችን! ጠላትዎ ክው ይበልና! ይሄኔ ገብሬም ኩስ ኩስ ማለቱን ትንሽ ገታ አደረገ።

“አንተ ምንድነው የምታወራው…? እሜቴ ሞተች ነው የምትለኝ…?”

“ምፅ… አዎ ጌታዬ እሜቴ ሞቱ እኮ!”

“የጉድ ሀገር…! ምን ሆና ሞተች መሆኑን?”

“አይ ጌታዬ… በወሊድ ነው!” (ልብ አድርጉልን ባለታሪካችን ከሁለት አመት በኋላ ወደ ቀያቸው መምጣታቸው ነው…)

“እንዴ… አንተ ሰውዬ ዛሬ ታመሃል እንዴ…? ከማን አረገዘችው…? እስቲ ንገረኝ…?” አሉ በቁጣ ተገስለው።

ይሄኔ ገብሬ ጣጣ አለው እንዴ…! ቀልጠፍ ብሎ መለሰ።

“እንጃ ጌታዬ ሰዉ ከገብሬ ነው ይላል እኔ ደግሞ ከኔ አይደለም እላለሁ!” ብሏቸው እርፍ።

በአግባቡ ተርኬው ይሆን? ብቻ ጋሽ ስብሀት ለመዘከር ያህል ነውና ልክ አንብው ሲጨርሱ “ጋሽ ስብሀት ነፍስህን ይማረው!” በማለት ተባበሩኝ! አመሰግናለሁ።