ዛሬም እየተገደልን ነው… ሲደብር! (አቤ ቶኪቻው)


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ሰሞኑን ከተሰሙ አስደንጋጭ ዜናዎች ውስጥ የሚከተለው ይገኛል…

“በዛሬዉ እለት በአርሲ አሳሳ ከተማ የጁምአ ሰላት ከተሰገደ በኋላ ሼህ ሱዑድ በአንድ መስጂድ ዳዕዎ አድርገዉ ሲወጡ በፓሊስ በመያዛቸዉ፤ የአካባቢዉ ሙስሊም ህብረተሰብ “ሼሁ ለምን ይታሰራሉ ምንም ጥፋት አልፈፀሙም” በሚል ለማስለቀቅ ሲሞክሩ ከፓሊሶች ጋር በተፈጠረዉ አለመግባባት ፓሊስ በከፈተዉ ተኩስ እስካሁን ባለዉ መረጃ መሠረት አምስት(5) ሰዎች መገደላቸዉና ብዙ ሰዎች መቁሰላቸዉን የአካባቢዉ ምንጮች ገለፁ:: ከተገደሉት ሰዎች መካከል ሼህ ኸድር የሚባሉ ታላቅ አሊም እንደሚገኙበትም ምንጮች ጨምረዉ ገልፀዎል:: እንደሚታወሰዉ ሼህ ሱዑድ ሻሸመኔ በተካሄደዉ ስብሰባ ላይ “ኢህአዴግን ለሀያ አመታት ስንደግፈዉ ኖረን አሁን እንዴት አሸባሪ አክራሪ ብሎ ይወነጅለናል” በማለት የተሰማቸዉን ቅሬታ በስብሰባዉ ላይ ገልፀዉ እንደነበር የሚታወስ ነዉ::

ይህንን ያገኘሁት ከአንድ የፌስ ቡክ ወዳጃችን ግድግዳ ላይ ነው። ዜናውን ሚዛናዊ ለማድረግ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ደግሞ ቀጥሎ እጠቅሳለሁ።

“በአርሲ ዞን አሳሳ ከተማ በሙስሊም አክራሪነት ሰዎችን ሲያደራጅ እና በመንግስት እና በህዝብ ላይ ጀሀድ ሲያውጅ የነበረ የነበረ አንድ ግለሰብ በቁጥጠር ስር ዋለ። ግለሰቡ በቁጥጥር ስር የዋለው በህብረተሰቡ ተሳትፎ መሆኑን ኢኒስፔክተር (ስማቸው ጠፍቶብኛል) ብቻ አንድ የፖሊስ አባል ኃላፊ ተናግረዋል። ሰውየው አያይዘው እንደተናገሩት በወቅቱ ግለሰቡ ያደራጃቸው አንዳንድ አክራሪዎች እና የተለየ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ግብረ አበሮቹ ባነሱት ግርግር የአሳሳ ከተማ ፖሊስ ጣብያ ወድሞ አራት ሰዎች ሲሞቱ አስር ፖሊሶች ቆስለዋል።”

ቀጥሎ የኔ አስተያየት ይከተላል።

እንግዲህ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ስንሰማ ትርጉም አዋቂ እንደሚያስፈልግ የታወቀ ነው። “በመንግስት እና በህዝብ ላይ ጀሀድ ሲያውጅ የነበረ አንድ ግለሰብ” ማለት ምን ማለት ነው? ያልን እንደሆነ መዝገበ ቃላታችን “የመንግስትን በሀይማኖት ጣልቃ ገብነት የተቃወመ” በሚል ይፈታልናል።

ያው እንደሚተወቀው ሙስሊም ወንድሞቻችን፤ “መንግስት የራሱን አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሃይማኖት ይንከባከብ የኛን ሃይማኖት ለኛው ይተውልን!” ብለው ድምፃቸውን ማሰማት ከጀመሩ ቆይተዋል። ኢቲቪ እና መንግስት ብዙ ሀሳብ ስላለባቸው ይህንን ዜና ስንከታተል እንደቆየን ረስተውታል መሰል፤ “በመንግስት እና በህዝብ ላይ ጀሀድ ሲያውጅ የነበረ ግለሰብ” ይለናል። ለመሆኑ ይህ ትርጉም ይሰጣልን!? መንግስትንም ህዝብንም ላጥፋ የሚል ጀሀድ ታይቶ ይታወቃልን?  እኒህ ማንንም ያልገደሉ የሀይማኖት አባት ጀሀድ አወጁ ከተባሉስ በከተማው  አምስት ሰዎችን የገደለው መንግስት ምን አወጀ ሊባል ነው…?

ወዳጄ ባለፈው ግዜ ያስታውሱ እንደሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማቸው ቀርበው በአርሲ የአልቃኢዳ ሴል ተገኝቷል! ብለው ያለምንም “ሼ” ሲናገሩ ይህንን መጠርጠር ተገቢ ነበር። የምር ግን፤ ጠቅላይ ሚኒስትራችን አምርረውብናል። አንዳንዶች እንደሚሏቸው ከሆነ፤ “እኒህ ሰውዬ መጀመሪያ ኑሯችንን ዘቀዘቁ ዝም አልን፤ በመቀጠል ባንዲራችንን ዘቀዘቁ አሁንም ተሳስተው ይሆናል ብለን ዝም አልን፤ ቀጥሎ ደግሞ እያንዳንዳችንን ሊዘቀዝቁን ቆርጠው ተነስተዋል!” ይሏቸዋል። እኔ እንኳ እስከዛ መድረሳቸውን እጠራጠራለሁ። ነገር ግን በእውነቱ ጥምድ አድርገው የያዙን ይመስለኛል። ምን እንዳስቀየምናቸው እንጃ… እንዴ አስቡት እስቲ “አልቃይዳ” ከማለት ውጪ ምን ሊሉን ይችላሉ። በዚህ አይነት እኮ ሰውዬው የአሜሪካ ጦር ራሱ አካባቢውን ገብቶ እንዲደበድብ ሊጠይቁ ይቻላሉ ማለት ነው…!

የሆነ ሆኖ ዛሬም ተቃውሞ እና አመፅ ስለተነሳ ሰዎች ይገደላሉ… ሲደብር። አረ መንግስታችን በናትህ የጉርምስና መንፈስህን ገስፀው!