እነሆ የሳንሱር ትንሳኤም መጣ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


እኔ የምለው ወዳጄ ሳሱር ነብሴ ድጋሚ መጣች አይደል እንዴ!? እሰይ! እልል በሉ እንጂ። ድግስ አትደግሱም እንዴ!? ጠላው ይጠመቅ፣ ድፎው ይደፋ፣ ቡናውም ይፈላ፣ ፈንዲሻው ይፈንደሽ፣ እጣን ሰንደሉ ተጫጭሶ ቄጤማውም ይጎዝጎዝ። በዓሉ የትንሳኤ በዓል ነውና ሁሉም ሰው ይደሰት።

አዎ አሁን ወቅቱ የትንሳኤ ነው። ሞቱ ተቀበሩ ያልናቸው ችግሮቻችን በሙሉ በስንተኛው ቀን እየተነሱ ዳግም ህያው እየሆኑ ነው። ይህ እንዲሆን ያደረገው እርሱ ኢህአዴግ ተዓምረኛ ነው። ያደረገውም ተዘርዘሮ አያልቅም።

መቼም ትዝ ይልዎታል… የዛሬ ሃያ አመት ኢህአዴግ አዲሳባን ሲቆጣጥር መጀመሪያ ይፋ ያደረገው ነገር፤ እናንት ነፃ ህዝቦች ሆይ ከእንግዲህ ያለ አንዳች ገደብ እንዳሻችሁ መናገር፣ እንደፈቀዳቸሁ መፃፍ፣ ደስ እንዳላችሁ መሞዘቅ ትችላላችሁ። ብሎ ነበር።

እኛም የዛኔ በልጅነት ጀብደኝነት ተነሳስተን “እውነት ዴሞክራሲ አለ?” የሚለውን ለመፈተን ወደ ትምህርት ቤት ስንሄድ እና ስንመጣ በየመንገዱ፤ እንዲሁም በትምህርት ቤታችን ቅጥር ግቢ ድምፃችንን ዘለግ እያደረግን፤

“በመለስ መላጣ ቅማል ትሄጂና

እንዳትሰበሪ ያዳልጥሽና፣

መለስን ለመሳል በጣም ቀላል ነው

ፍየሊቷን ስሎ ቀንዷን መተው ነው”

እያልን የግጥም ችሎታችንንም የዴሞክራሲ መብታችንንም እንፈትን ነበር። አዎ እውነትም ማንም የሚናገረን ሰው አልነበረም። እውነትም ዴሞክራሲ ተከብሯል ስንል የግንቦት ሃየ ሰልፎች ላይ “…ግንቦት ሃያ ለዘላለም ኑሪ” የሚለውን መዝሙር እየዘመርን በደስታ እንሰለፍ ነበር። እያደግንም ስንመጣም ጠቅላይ ሚኒስትሩ “መለስ መላጣ ብሎ መሳደብ ይቻላላ  መላጣዬን መንካት ግን አይቻልም” ብለው ጭራሽ አስደሰቱን። (በቅንፍ በዚህ ንግግር የደነገጠ አንድ ግለሰብ ቢኖር የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፀጉር አስተካካይ ብቻ ነበር አሉ። መላጣቸውን ሳይነካ እንደምን ቀሪ ፀጉራቸውን መከርከም ይችለዋል…? ብለን እንቀልዳለን! ቅንፍ ለዘላለም ትኑር!)

ቀልዱ ቀልድ ነው የምር ግን በግንቦት ሃያ ማግስት ሀገሪቷን ያጥለቀለቋትን የህትመት ውጤቶች ስናስታውስ ለካስ ህዝቤ ታፍኖ ኖሯል፤ ያስብላል። እዝችጋ ተወዳጁን እስክንድር ነጋን ሳይጠቅሱ ማለፍ ነውር ነው። አዲስ መስመርም ይገባዋል፤

አስክንድር ነጋ ሲኖርበት ከነበረው ፈረንጅ አገር ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የሳንሱር መቅረት እና የነፃው ፕሬስ መፈቀድን ተከትሎ ነበር። እንደመጣም “ኢትዮጵስ” የተባለች በሃምሳ ሳንቲም የምትሸጥ ጋዜጣ ጋዜጣ ማሳተም ጀመረ። ከትንሽ ቆይታ በኋላ ግን ለተሰጠው የፕሬስ መብት ዱላ እና እስር ያስከፍል ጀመር። በዚህም አስክንድር ብቻ ሰባት ግዜ ታስሮ ብዙ ሰባት ግዜ ተደብድቧል። ይህንን ስናይ አዋጁ ወጥመድ ነበር እንዴ…? ብለን ጠርጥረናል።

“ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሯ መሄድ ትጀምራለች” (ይቺ አባባል የት ጠፍታ ከርማ ነበር ባካችሁ?)  ብቻ ቀስ በቀስ የፕሬስ ህግ ሲወጣ ቀስ በቀስ የአሸባሬነት ህግ ሲወጣ ህገ መንግስታችን የፈቀደልን ያለ “ሳንሱር” ቅድመ ምርመራ የመፃፍ መብት ራስን በራስ ወደመመርመር ተሸጋገረ። እኛ “ፀሀፊ” በሆንበት ዘመን ራሳችንን ሳንሱር እያደረግን መፃፍ ጀመርን። ከዛም አልፎ በግልፁ መፃፍ የሚያመጣውን ጦስ እየፈራን ያለ አመላችን አሽሟጣጭ ሆነን ቁጭ አለን (እዝች ጋ ሳይስቁብኝ አይቀሩም… ግን የምሬን ነው!) አሁንም እያደር ሽሙጡም ቢሆን እሳቸውን እና ቤተሰባቸውን የማያስቀይም እንዲሆን መከራችንን ማየት ጀመርን። (ቤተሰባቸው ተብሎ የተገለፀው የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችን ነው) እሱም አልተሳካም!

ወዳጄ ለማንኛውም አሁን በይፋ ሳንሱር ተጀምሯል። ከዚህ ቀጥሎ ማተሚያ ቤቶች የሚያሳትሙትን ማነኛውም የህትመት ውጤት ላይ ምርመራ እንዲያከናውኑ ተወስኗል። አንጋፋው ብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት ስራውን መጀመሩን ሰምተናል። ሌሎቹም ይቀጥላሉ… ባለፈው ሳምንት ውስጥ ማህሌት የተባለች የልብ ወዳጃችን ፌስ ቡክ ግድግዳዋ ላይ ይህንን ለጥፋ ነበር።

“የብርሃና ሰላም አዲስ ህትመት ስራ ውል አንቀጽ አንቀጽ 10 የሚከተለውን ይላል፡፡ ምን ማለት ይሆን?!

አንቀፅ 10
ሕግን የተላለፈ ይዘትን አለማተም
10.1 አታሚው በአሳታሚው እንዲታተም የቀረበለት የፅሁፍ ስክሪፕት ህግን የሚተላለፍ ስለመሆኑ በቂ  ምክንያት ካለው አላትምም የማለት መብት አለው፡፡

10.2 አታሚው አሳታሚው የሕግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል የህትመት ይዘት የማውጣት ዝንባሌ ያለው መሆኑን ለማመን በቂ ምክንያት ካለው በማናቸውም ጊዜ ውሉን ለማቋረጥ ወይም ለመሰረዝ ይችላል፡፡”

ወዳጃችን ማህሌት፤ ምን ማለት ነው? ነው ያልሽው…? ምን ማለት መሰለሽ ፅሁፍሽ ከመታተሙ በፊት በብርሃን እና ሰላም የምርመራ ዋና ስራ ስራ ሂደት ባለቤት ይመረመራል። ሳንሱር ይደረጋል ማለት ነው።

እነሆ መንግስታችን ተዓምረኛ ነው! በህገ መንግስቱ ሞተ ያልነውን ሳንሱር አስነስቷል እና ደስ ይበላችሁ!!!

ይህንን በሂሳብ እናስላው ካልን ህገ መንግስቱ ሲባዛ በዜሮ ይሆናል ዜሮ! ይሆናል ማለት ነው። ታድያ ማሽኑ የመንግስት ነው!