አቶ ሽመልስ ከማል እንኩ ሰላምታ! (አቤ ቶኪቻው)


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ባለፈው ግዜ መንግስት ቅድመ ምርመራ ወይም የሳንሱርን ትንሳኤ ሊያመጣው እንደሆነ ፍንጭ አግኝተናል ብለን አንዳንድ ጩኸቶችን ጮኸን ነበር። በጩኸታችን ማግስት የአለም የፕሬስ ነፃነት ቀን በመላው አለም ተከበረ። ከመላው አለም አክባሪዎች ውስጥ “ወጉ ለምን ይቀራል” ብላ ኢትዮጵያም አንዷ ሆና ነበር።

በክብረ በዓሉ ላይ አቶ ሽመልስ ከማል ካልታሰሩ ጋዜጠኞች ጋር አንድ መድረክ ላይ ተገናኝተው ነበር አሉ። ታድያ አንድ ጥያቄ ተወነጨፈባቸው። “መንግስት ቅድመ ምርመራ ወይም ሳንሱርን ድጋሚ እያመጣው ነው፤ ይኸው “ብርሃንና ሰላም የምታሳትሙትን አይቼ ቀልቤ ካልወደደው እንቢ የማለት መብት አለኝ” የሚል ውል እያስፈረመን ይገኛል።” ብለው ነግረዋቸው ነበር። ታድያ አቶ ሽመልስ ምን አሉ?

“ይሄ የብርሃንና ሰላም ድርጅት ያወጣው ህገ ደንብ ነው እኛ በዚህ ላይ የለንበትም!” ብለው እርፍ! እኛስ ምን እንላቸዋለን…

አቶ ሽመልስ በመጀመሪያ እንኩ ሰላምታ፤ የት ጠፍተው ከረሙ…? እኔ የምልዎ… ከዚህ በፊትም እንዲህ የማይሆን ንግግር ሲናገሩ የሰሙ ወገኖች እና ወገኞች “አቶ ሼም የለሽ” ብለው ስም አውጥተውልዎ ነበር። ስሙ እንደተጠበቀ ይቆይ ካሉ ጥሩ፤ አለበለዛ ግን ይሄ ትልቅ የሆነ ህገ መንግስትን የመናድ ተግባር ነው። ታድያ እንዴት አፍዎን ሞልተው በዚህ ጉዳይ እኛ የለንበትም ይላሉ። በህገመንግሰቱ ጉዳይ ከሌላችሁበት በምን ጉዳይ ላይ ነው የምትኖሩት? የምሬን ነው የምልዎ ተሸወዱ! እኔ እርስዎን ብሆን ምን እንደማደርግ ያውቃሉ…? እርግጠኛ ነኝ አያውቁም። ስለዚህ እራሴው እነግርዎታለሁ።

መጀመሪያ ብርሃንና ሰላም አዘጋጀ ስለተባለው ውል ከጋዜጠኞቹ ስሰማ ምንም እንኳ ቀድሜ የሰማሁት ቢሆንም፤ አውቄ ድንግጥ እላለሁ። ድንግጥ ቢሉዎት ደግሞ ዝም ብሎ ድንግጥ ብቻ አይደለም። ክው! ከዛ ንግግሬን እቀጥላለሁ “ይሄ ስህተት ነው! ድርጅቱ ህገመንግስቱን እየናደ ስለሆነ አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰንበት ጉዳዩን ወደ ህግ እንወስደዋለን!” እላለሁ።

እውነቴን ነው የምልዎ አቶ ሽመልስ፤ እንኳንስ ሌላ ቀርቶ እነ እስክንድር ነጋን እና ስንቱን ምስኪን ሰው… “ህገ መንግስቱን ሊንዱ ሲሉ  በህብረተሰቡ ትብብር ተያዙ!” ብለውን የለ እንዴ!? (በምን አቅማቸው ሊንዱት እንደሞከሩ ባይታወቅም)  ታድያ ስለ ብርሃንና ሰላም ላይ ይህንን የመሰለ ጥቆማ ሲደርስዎ ከዚህ የበለጠ የህብረተሰብ ትብብር ከየት ይመጣል!? አረ “ሼ” ይኑር “ሼም” …ነውር እንወቅ… ስማችንንም እናድስ! እስከ መቼ ሼም የለሽ እንባላለን!?

ምናልባት ህገ መንግስቱን ረስተውት ከሆነ እንደሚከትለው አስታውሶታለሁ፤

“ሕገ መንግስቱ አንቀፅ 9 ላይ እንዲህ ይላል፤ “ሕገ መንግስቱ የሀገሪቱ የበላይ ህግ ነው። ማንኛውም ህግ፤ ልማዳዊ አሰራር፤ እንዲሁም የመንግስት አካል ወይም ባለስልጣን ውሳኔ ከዚህ ህገመንግስት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት አይኖረውም።” ይላል። ይህ ደግሞ ብርሃንና ሰላምንም ጨምሮ ነው። አረ ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ይጨምራል። ሄደው ሄደው ሄደው አንቀፅ 29 ላይ ሲደርሱ ደግሞ ስለ ፕሬስ ነፃነት ያወራ እና “ሀ” ላይ ገና በመጀመሪያው ማለት ነው “የቅድመ ምርመራ በማነኛውም መልኩ የተከለከለ መሆኑን…” ይደነግጋል።

ታድያ ብርሃንና ሰላም “የሚታተመውን ፅሁፍ አይቼ  ውቃቤዬ ካልወደደው አላትምም” የሚለው በምን ህግ ነው? ይህ ህገ መንግስቱን መናድ አይደለምን?

አቶ ሽመልስ ከሰሙኝም  ካልሰሙኝም እንኩ ሰላምታ… ! (በምን ልምታህ እንዳይሉኝ ብቻ!) እንኩ ወቀሳም! ወቀሳው ግን ከመብዛቱ የተነሳ ለልጅ ልጅ ሁሉ የሚያወርሱት ሆኖሎታል አሉ! (አሉ ነው)