ትዝታ ወ ግንቦት ሰባት! (አቤ ቶኪቻው)


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ሰላም ወዳጄ… በቀጠሯችን መሰረት መጥቻለሁ።

ትላንት ግንቦት ሰባት ነበር። ይቺ ቀን ለኛ የተለየች ቀን ነች። የዲሞክራሲ መብራት ብልጭ ብላ የጠፋችበት በርሱ ጦስም በርካታ አቅም እና ችሎታ ያላቸው ትራንስፎረመሮች ተቃጥለው፤ በምትካቸው ትራንስፎርሜሽን የተባለ ቃል መተካት የጀመረባት ታሪካዊ ቀን። እስቲ ያቺን ሰዓት ትንሽ እንዘክራት…

አንድ

እኔ በምርጫ ዘጠና ሰባት ጎጃም አካባቢ ነበርኩ። የአቤ ጎበኛው የትውልድ ቦታ የሆነችው አቸፈር፣ ዱር ቤቴ፤ እንዲሁም አዴት እና መራዊ ከዛም አልፎ ሶስት እና አራት ሰዓት በእግር የሚያስገቡ ገጠራ ገጠሮችን በስራዬ ሰበብ ሳስሳቸው ነበር። ከዛ አካባቢ በአንዱ ገጠር የሚከተለውን አንዱ አጫወተኝ።

“ይገርምሃል ጋሼ ሪም ቀበሌ ህዝብ ተጨንቋል።”

“ምን አጋጠመው?”

“የቀበሌው ሰው ሁሉ ካርዱን ለቅንጅት ሊሰጥ ተስማመቶ ነበር።”

“ታድያስ?”

“ኋላ ላይ ሲቆጠር አንድ ካርድ ለንቢቱ ገብታ ተገኘች።”

“ይገርማል። ታድያ ጭንቀቱ ከምን መጣ የሚፈልጉትን መርጠው የለ?”

“እሱማ ልባቸው የፈቀደውን መርጠዋል። ግና ይሄ ንቢቱን የመረጠው አንድ ሰው ማነው ከቀዬው ትዕዛዝ እና ስምምነት እንዴት ሊወጣ ቻለ ብሎ ነው ሰዉ ጭንቅ የገባው።” አለኝ።

አንድ ነጥብ ሁለት

በዚሁ ቀበሌ የመረጡትን መርጠው ካበቁ በኋላ ኢህአዴግ “ተጭበርበሪያለሁ” ብሎ ምርጫው ካልተደገመ ሞቼ እገኛለሁ አለ። (አሉ… ይቺ እንኳ “አሉ” ናት) ታድያ ሰዉ በሙሉ በምን ተስማማ መሰላችሁ… “እኛ ዳግሞሽ ምርጫ አንገባም። ከፈለጋችሁ ገበያ ለይ እንሰብሰብና ንቢቷን የሚል ካለ አለሁ ብሎ ይቆጠር እንጂ አንድግዜ የመረጥነውን መርጠናል።” አሉ (አሉ።)

ሁለት

አዴት አካባቢ በሆነው ቀበሌ ደግሞ ምርጫው ተጠናቆ ማታ ላይ ድንገት መብራት እልም ብሎ ጠፋ። ይሄኔ “ካርድ ሳይቆጠር አንሄድም” ብሎ የነበረው የአካባቢው ህዝብ ባትሪ ፍለጋ መተራመስ ያዘ። ባትሪው ተገኘ። ሲበራ ከታዛቢዎች መካከል አንዱ የኢህአዴግ ቀንደኛ ተከራካሪ የነበረው ሰውዬ ጠፍቷል። የት ገባ? ቢጠሩት ቢፈለጉት የት ይገኝ!? መብራቱ ከመጥፋቱ በፊት አጠገባቸው ነበረ። ታድያ የት ገባ?

ትንሽ ቆይቶ መብራት መጣ ይሄን ግዜ አንድ ሰውዬ በአካባቢው ሰዎች ማጅራቱ ተጨምድዶ አንዳች ነገር ታቅፎ፤ “ይሄ ሌባ” እየተባለ ወደ ምርጫ ጣቢያው ገባ። ሰውየው “የት ጠፋ?” ብለው ሲጨነቁለት የነበረው አፍቃሪ ኢህአዴግ ነበር። ምን አድርጎ ነው? ተብሎ ሲጠየቅ ለካስ መብራት እንደ ጠፋች ኮሮጆ ይዞ ነበር የተሰወረው። ድንገት የአካባቢው ሰዎች እጅ ከፍንጅ ይዘው ማጅራቱን ጨምድደው አመጡት እንጂ!

ሶስት

ምርጫው አለቀ እና እነዛ ቀውጢ ቀናት መጡ። ፖሊሶች ማንኛውንም ጎረምሳ እየወሰዱ በየእስር ቤቱ ይከቱት ጀመር። በአንዱ የክፍለሀገር ከተማ የሚከተለው ሆነ፤

ወጣት ልጃቸው የታሰረባቸው አባት ወደ ፖሊሶቹ አዛዥ ሄደው “እባክህ የኔ ጌታ የኔ ልጅ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም ለራሱ ህመምተኛ ነው ልቀቁልኝ” ብለው ይጠይቃሉ። ፖሊሱም ትኩር ብሎ እያያቸው “የእርስዎ ልጅ ምንም ውስጥ እንደሌለበት ለማወቅ ትንሽ ግዜ ያስፈልገናል። አሁን ገና እየተረጋገጠ ነው” ብሎ ይመልስላቸዋል። አባትም በአዕምሯቸው “እየተረጋገጠ ነው…” የምትለው ቃል አቃጨለችባቸው። ከዛ ደግመው ጠየቁት፤ “ካልተረጋገጠ አይለቀቀም…?” “አዎ መጀመሪያ መረጋገጥ አለበት” አላቸው ፖሊስ ኮስተር ብሎ “አይ አበሳዬ በሉ እንግዲያስ አደራ እጁ በሽተኛ ነው ስትረጋግጡት ተጠንቀቁልኝ… በስንት ወጌሻ ነው የተሻለው” በማለት የነሱ ማረጋገጥ መረጋገጥ መሆኑን ነግረዋቸው እያዘገሙ ሄዱ።

አራት

በዘጠና ሰባቱ ምርጫ ጦስ ስለመጡ አስቂኝ ነገሮች ወዳጃችን በኋይሉ ገብረ እግዚአብሄር “ኑሮ እና ፖለቲካ” በተባለው መፅሀፉ ውስጥ ካጫወተን ደግሞ ትንሽ እንቀላውጥ፤

በግርግሩ ሳብያ ፖሊሶች ማታ ማታ በእያንዳንዱ ሰው ቤት እየገቡ ድምፁ ጎርነን ያለ ጎረምሳ ሁሉ እያፈሱ ይወስዱ ነበር። ታድያ በአንዱ ማታ በአንዱ ቤት ፖሊሶቹ ሲገቡ፤ ጀርመን አገር ያሉት የልጆቹ አባት በቴሌቪዥን የሚያዩት ነገር ረብሿቸው ስልክ ሲደውሉ እኩል ሆነ። ይሄን ግዜ በፖሊሶቹ ዘው ብሎ መግባት የተደናገጡት ልጆች ስልኩ ሲያምባርቅ በፍርሃት ያዩት ጀመር። ይሄኔ አንዱ ቆፍጣና ፖሊስ አንዱን የቤቱን ጎረምሳ “ስልኩን አንሳ” ብሎ አዘዘውና የሚያወራውን ለመስማት ጠጋ ብሎ።

“ሃሎ”

“ሃሎ”

“የምን ጦርነት ነው የምሰማው ልጆቼ ተረፋችሁ?”

ልጅ የሚመልሰው ጠፋበት ትንሽ እንደማሰብ አለና፤ “አባዬ ምንም ችግር የለም። ሁላችንም ደህና ነን። ፖሊሶች እቤታችን ድረስ መጥተው እየተንከባከቡን ስለሆነ አታስብ!” በማለት መለሰ አፉ በፍርሃት እየተሳሰረ።

አምስት

በአመቱ ሰሜን ወሎ ፍላቂት ላይ ትንሽ ቆይታ አድርጌ ወደ ጎንደር አርማጭሆ ዘልቄ ነበር።

አምስት ነጥብ አንድ

ፍላቂት

የፍላቂት ህዝብም እንደመላው የሀገሪቱ ህዝብ ሁሉ የመረጠው ቅንጅትን ነበር። ታድያ በዛው አመት የአካባቢው ገበሬ ሁለት አይነት ወከባ ነበረበት። አንዱ ማዳበሪያ እና የመሳሰሉትን አገልግሎቶች ሲጠይቅ የየቀበሌው ካድሬዎች “ቅንጅት ይስጣችሁ” እያሉ የሚያጉሏሏቸው ሲሆን ሌላው ደግሞ “ምን አድርገን ነው እኛን ያልመረጣችሁን?” የሚል ስብሰባ ነበር። ታድያ ለምን አልመረጣችሁንም? በሚለው ላይ የሰማናት ቀልድ በጣም ታዋቂ ሆናለች። እዚህ ላይ እርሷን ሳያነሱ ማለፍ አግባብ አይደለም።

ካድሬው፤ “እኛ እስከዛሬ ትምህርት ቤት ሰርተንላችሁ… ጤና ጣቢያ ገንብተንላችሁ… መንገድ ጠርገንላችሁ… ለምንድነው ያልመረጣችሁን?”

ገበሬዎቹ፤ “እግዜር ይስጣችሁ ደህና አድርጋችሁ ሰርታችሁልናል! አሁን ግን ይበቃችኋል እናንተም ይደክማችኋል አረፍ በሉ እኛም ትንሽ አረፍ እንበል!”

አምስት ነጥብ ሁለት

ጎንደር

ጎንደር አርማጭሆ ስንደርስ ስለ አርበኛ ግንባር ዝና ሰማን። የአካባቢው ሰው የመንግስት ታጣቂው ሳይቀር አርበኞችን የሚያነሳቸው በመልካም ነው። ተኳሽነታቸውን እና ስነምግባራቸውን አውርተው አይጠግቡም። አንዱ የመንግስት ታጣቂ ስለ ግንቦት ሰባቱ ምርጫ እንዲህ አወጋኝ፤

“እኛ ገና ከጀምሩ ምርጫ ምርጫ መባሉ ደስ አላለንም ነበር። በስብሰባ ላይ ከወረዳ ለመጡትም ነገረናል። ‘ሰዉ ያሻውን ይምረጥ ካላችሁ አይሆንም፤ ኋላ መዋረድ ይመጣል። ሰዉ ሆድ ስለባሰው አንድ እንኳ የሚመርጣችሁ አይገኝም። ስለዚህ ዝም ብለን እንደቀደመው ግዜ እዚች ላይ አጥቁሩ እያልን እኛው እንምራቸው እና ንቢቱን እናስመርጥ።’ ብለን ብንላቸው “የለም ዲሞክራሲ ነው።” አሉን ከዛስ ምን ሆነ አትለኝም…? ሁሉም ሆ ብሎ ቅንጅቱን መረጠ። ከዛልህ “እኛን በአግባቡ ስላልቀሰቀሳችሁ ነው” ብለው ብዙ ጓዶቻችንን እስር ዶሏቸው። ኋላ ያልታሰርነው ሆ ብለን ወጣናታ… እንግዲህ ለአርበኛ መግባታችን ነው። “በዛሬው እለት የታሰሩ ጓዶቻችን ካልተለቀቁ ነገ ከጫካ ነን።” ብንላቸው ማምሻውን በኦራል መኪና አምጥተው አስረከቡን!

እኔ የምለው ቀጣዩ ምርጫ መቼ ነው…?