ጠቅላይ ሚኒስትርዬ ከሱብኝ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ትላንትና ከስንት ጊዜ በኋላ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትርዬን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አየኋቸው። ያኔ አበበ ገላው በዋሽንግተን ዲሲ ቆሌያቸውን ከገፈፋቸው በኋላ በቴሌቪዥን መስኮት ስናያቸው ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው። (በቅንፍ፤ እንደ ድሮ ጎረቤት ብንሆን ኖሮ በቴሌቪዥን መስኮት ሲጠፉብን በሳሎናቸው መስኮት ለማየት ሙከራ እናደርግ ነበር። ዛሬ ግን ሩቅ ሆንና ናፍቆታቸው ሲያስቸግረን ሰነበተ! ብዬ ሀሳቢነቴን ለመግለፅ እወዳለሁ።)

አረ እዝች ጋ ሳይረሳ ባለፈው ጊዜ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ሰዎች “አበበ ገላው ዋሽንግተን ዲሲ ያልሄደው በርካታ የኢህአዴግ ደጋፊዎች ስላሉ እነርሱን ፈርቶ ነው!” ብላችሁን ነበረ። ረስቼላችሁ፤ ሰውየው እኮ አንገታቸውን የደፉት በዋሽንግተን ዲሲ ነው።

ታድያ የዛን ጊዜ ያ ሁሉ የአንገት እና የቅስም ስብራት ያጋጠማቸው የጋዜጠኛ አበበ ገላው ንግግር ብቻ መስሏችሁ ከሆነ ተሸወዳችሁ።

ከውጪ የነበሩት የአካባቢው ኢትዮጵያውያን የተቃውሞ ጩኸትም “ምነው እግሬን በሰበረው!” አስብሏቸው ነበር። ውስጥ ደግሞ አበበ ትንታግ ሲጨመርበት…!  እና ታድያ አዲስ አድማሶች ይሄ ሁሉ ነገር በዋሽንግተን ዲሲ ሲከናወን ደጋፊዎቻቸው የት ሄደው ይመስላችኋል? “በልማታዊ ስራ ተወጥረው ነበር!” ብላችሁ ሳቄን እስቲ አብዙልኝ! “ምን አይነት አዲስ አድማስ መጣ ደሞ ባካችሁ!?”

በነገራችን ላይ አሁንም እርሳቸው እርም የላቸውም የቡድን ሃያ አገራት ስብሰባ ላይ ደግሞ ሊገኙ ሲሄዱ ነው ያየኋቸው። እንደኔ እንደኔ ይሄ ቡድን ምናምን የሚባል ነገር ቢቀርባቸው ይሻላል። በርግጥ ስብሰባ ሊናፍቃቸው አንደሚችል ጠረጥራለሁ።  ምን ችግር አለው ታድየ በፈለጉ ጊዜ የሚሰበስቡት በፈለጉ ጊዜ የሚበትኑት ፓርላማ አላቸው አይደል እንዴ…!?  እዛው እንደሚሆኑ ቢሆኑ ይሻላቸዋል እንጂ፤ ገና ለገና የፈረንጆቹ “ቡድን” አያልቅም እና እርሳቸው “በድን” እየሆኑ የሚመጡበት ምክንያት ምንድነው!?

የሆነ ሆኖ “ታንክ ተደግፈው መፅሀፍ የሚያነቡት ጀግናው ጠቅላይ ሚኒስትራችን” በአበበ ገላው ንግግር የተነሳ ለአንድ ወር ያህል ተሸማቀው እና ተሸምቀው ሲያበቁ ትላንት በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለዋል።

ታድያልዎ፤ ትላንት ሳያቸው ክስት ብለዋል። ምን ሆኑ!? እንዴ ጠንከር ይበሉ እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትርዬ! ቀጣዩ ጩኸት እኮ እየባሰ ነው የሚመጣው! ታድያ ጠንከር ጠንከር ማለት አይሻልም ይላሉ? ቁጣ እና ጩኸት ይህንን ያህል የሚረብሽዎት ከሆነ ግን ዘዴውን ልንገርዎት…!? እሺ አይሉኝም እንጂ ዛሬውኑ ስልጣንዎን ልቅቅ አድርገው አዲስ አገራዊ መግባባት፣ አዲስ አገራዊ ምርጫ ማከናወን! አቤት ያኔ ጤናዎ ላይ ራሱ ምን አይነት መሻሻል አንደሚመጣ ያዩት ነበር።