ቃሌ የመወያያ ክፍል 5 የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጁላይ 28 ቀን ለውይይት ጋበዘ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


(ዘ-ሐበሻ) በፓልቶክ ውስጥ ካሉት በርከት ያሉት የመወያያ ክፍሎች መካከል አንዱና ግንባር ቀደሙ የሆነው ቃሌ የመወያያ ክፍል 5 የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በጁላይ 28 ቀን 2012 በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለማወያየት መጋበዙን ለዘ-ሐበሻ በላኩት ጥሪ አስታወቁ። የጥሪውን ሙሉ ቃል እንደሚከተለው አቅርበናል።

July 21, 2012

ለተከበራችሁ፡

የጥምረት ለነጻነት ለእኩልነትና ለፍትህ በኢትዮጵያ

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ

የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት

መሪዎችና አባሎች፤

ጉዳዩ፤ ቃሌ (የብርቱካን መዴቅሳ) የፖለቲካ መወያያ ክፍል ዉስጥ በጁላይ 28 ቀን 2012. ኤም ኢስተርን ታይም ወይንም በ20 ሴንትራል ዩሮፒያን ታይም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዳይ ላይ አስተያየታችሁን እንድትሰጡ በክብር ተጋብዛችሗል።

የቃሌ ታዳሚዎች ስለ ኢትዮጲያ ፖሌቲካ ዉይይት የጋበዟችሁ ለጁላይ 28 ቀን 2012 ቢሆንም፣ ሌሎች እህት ክፍሎች፤ ከረንት አፌይርስ፣ አበራሽ በርታ፣ አሉላ አባነጋና ለሌሎቹም ዉይይቱን መከታተል ለሚፈልጉ ለማሰማት ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ እንዲቻል የሚመጡትን የተወካዮቻችሁን ስም የሚገልጽ የኢሜል መልስ ይህ ኢሜል ወደመጣበት አድራሻ ከጁላይ 26 ቀን 2012 በፊት በመላክ እንድትተባበሩን እየጠየቅን፣ ተወካይ ለመላክ የማትችሉ ከሆነ ደግሞ ከጁላይ 26 ቀን 2012 በፊት በኢሜል እንድትገልጹልን በአክብሮት እንጠይቃለን።

በመጀመሪያ ቃሌ (የብርቱካን መዴቅሳ)፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ መወያያ ክፍል ዓላማ ጸረ-ወያኔ አቋም ያለን ኢትየጵያዉያን እንዴት ፍትሕ፣ የግለሰብ ነጻነትና ዲሞክራሲ የሰፈነባት ኢትዮጵያን ማምጣት በሚቻልበት ጉዳዮች ላይ እንድንወያይ ማድረግ ነዉ። ለዚህም የክፍሉ አድሚኖች በዚሁ ዓለማ የሚያምኑና የተለያየ የፖለቲካ ድርጅት ደጋፊዎችና እንዲሁም ደግሞ የምንም ድርጅት መስመር ተከታዮች ያልሆኑም ይገኙበታል።

ለክፍሉ ታዳሚዎች፣ የወያኔን ፖለቲካ ማራመድ ከሚጥሩት በስተቀር፣ ዉይይቱ ላይ ሃሳባቸዉን በነጻ እንዲገልጹ መድረኩ ክፍት ነዉ። ቃሌ እንደዉይይት መድረክ የማንም የፖለቲካ ድርጅት ፕሮፓጋንዳ አይካሄድበትም። በተቃዋሚና በጸረ-ወያኔ ፖለቲካ የሚታወቅ የፖለቲካ ድርጅትም ሆነ ግለሰብ ወይንም የድርጅት መሪ አይዘለፍበትም።

በኢትዮጵያ ዉስጥ ስላለዉ ፖለቲካ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ኢትዮጵያዉያን ለዉይይት በሚቀርቡት የዉይይት ርእሶች ላይ የግራም ሆነ የቀኝ አመለካከት ይኑራቸዉ፣ ወይንም ደግሞ ይሄንን ድርጅት አልደግፍም በማለታቸዉ ከዉይይት አይታቀቡም። ከዉይይት የሚታቀቡት በዘለፋ፣ በስም ማጥፋት እንዲሁም ከተያዘዉ የዉይይት ርእስ እየወጡ ሲያስቸግሩ ብቻ ነዉ። የመሳተፍ መብታቸዉ ለአጭር ጊዜ ብቻ ይወሰድባቸዋል። የቃሌ አድሚኖችና ታዳሚዎች በአማካይ ቀን ለዉይይት እሰከ 110 ሲደርሱ፣ ለየት ባሉ ቀናት ደግሞ ከ250 በላይም በመሆን ሁለተኛ ክፍል እሰከመክፈትም የሚደረስበት ጊዜ አለ። እንደ ጁላይ 28 ቀን 2012 ባለዉ ሰፊ ዝግጅት ወቅት ደግሞ አህት ክፍሎች ከረንት አፌርስ፣ አበራሽ በርታ፣ አሉላ አባነጋና ሌሎቹም ዉይይቱን እንዲያሰተላልፉ ሲደረግ የታዳሚዉ ብዛት ከ800 በላይ ይሆናል ብለን እንገምታለን። ይህ እንግዲህ ቃሌን በሩቁ ለምታዉቁ ባጭሩ ግልጽ እንዲሆንላችሁ ለማድረግ ነዉ።

በዚህ ባሳለፍናቸዉ ጥቂት ወራት ኢትዮጵያዉያን ባገር ዉስጥና ከኢትዮጵያ ዉጭ በዲሞክራሲና በፍትሕ ዙሪያ በሚከተሉት ተግባራዊና ፖሌቲካዊ ሂደት ዉስጥ በከፍተኛ ፍጥነት እየተጓዙ ይገኛሉ፤

• በጋምቤላ፣ በአፋር፣ በኦጋዴንና በበጌምድር ሕዝቡ ለነጻነቱ በተለያየ መንገድ እየተናነቀና እይተዋደቀ ነዉ።

• ሙሰሊም ዜጎቻችን ለእምነት ነጻነታቸዉ በየሳምንቱ ድምጻቸዉን በማሰማት እየታሰሩና እየተገደሉ ይገኛሉ።

• መምሕራን፣ ጋዜጠኞች፣ እንዲሁም ሰላማዊ ታጋዮች የነጻነት ያለህ በማለታቸዉ ከስራ በመባረርና በሽብርተኛነት እስከእድሜልክ እስራት እየተበየነባቸዉ ናቸዉ።

• አቶ መለስ ዜናዊ አንዴ ታመዋል፣ አንዴ እረፍት ሄደዋል በሚል ሊተኳቸዉ የሚችሉትንም የሕወአት/ኢሕአዴግ መሪዎች ስም በተለያየ መንገድ በማስወራት ሕወአት በአንድ በኩል የአቶ መለሰን መገለል በሌላ በኩል ሌሎች የሚተኳቸዉ መሆኑን ቀስ በቀስ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲቀበለዉ በማለማመድ ላይ ይገኛል።

• በኢትዮጵያ ዉስጥ ያሉ የሰላማዊ ትግል የሚያካሂዱ የፖሌቲካ ድርጅት መሪዎች ደግሞ ጊዜዉ የሚጠይቀዉ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ የአገር ማዳን ስብስብ ማድረግ አለባቸዉ እያሉ ነዉ።

• በዉጭ አገር ያሉ የኢትዮጵያ ፖሌቲካ ድርጅቶችና ኢትዮጵያዉያን፣ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ በወያኔ ላይ በሚወሰደዉ ፖለቲካዊ እርምጃ ሁሉ ትብብር እያሳዩ ነዉ። የፖሌቲካ ድርጅቶች የጋራ ግንባሮች ተፈጥረዋል፣ የሽግግር ምክር ቤትም ተመስርቷል። የኢትዮጵያ ዲያስፖራም የፖሌቲካ ድርጅቶች ተሰባስበዉ ስለኢትየጵያ መነገጋር ያለባቸዉ ጊዜዉ አሁን በሚል በየመድረኩ ሲነጋገር ይሰማል።

ከየድርጅቶቻችሁ በጁላይ 28 ቀን 2012 ቃሌ የመወያያ ክፍል የምትልኳቸዉ ተወካዮች ከዚህ በታች በተዘረዘሩት ሶሰት አበይት ጉዳዮች ላይ የድርጅቶቻችሁን እምነትና አስተያየት እንዲያካፍሉን በከፍተኛ ጉጉት እንጠብቃለን፤

1. የሃገሪቱ ወቅታዊ ፖለቲካ አየር ምን ይመስላል? ሕወአት/ኢሕአዴግ ከመለስ በዃላ እመርታዊ ተሃድሶ ሊያመጣ ይችል ይሆን?

2. በተቃዋሚ ጎራ ያሉ የፖሌቲካ ቡድኖች መሰባሰብና ስለወደፊቷ ኢትዮጵያ መነጋገር አያስፈልግም? ተሰባስቦ ስለሀገር መወያየት አያስፈልግም ከተባለ ደግሞ ምክንያቱ ምን ይሆን? ተሰባስቦ መነጋገር ካሰፈለገ ደግሞ የዚህ ተሰባስቦ መወያየት ጥቅሙ ምንድን ነዉ?

3. የመለስን መገለል ተከትሎ፣ የምእራብ አገሮች በፖለቲካ ስልጣን ዙሪያ እናደራድራችሁ ቢሉ፣ ሊሆን የሚችለዉ ምንድን ነዉ? የፖለቲካ ቡድኖች ወይንም ግንባሮች በተናጠል የሚደራደሩበት ሁኔታ ሊኖር ይችል ይሆን? በተናጠል የሚደራደሩ ከሆነ ደግሞ ከሕዝቡ የነጻነትና የፍትሕ ጥያቄ ጋር እንዴት ሊያያዝ ይችላል?

ዉይይቱ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ያለበት ሆኖም መጠየቅ ያለባቸዉ ጥያቄዎች ከታዳሚዉ በአክብሮት ስለሚጠየቁ ተወካዮቻችሁ ተገቢዉን መልስ ባለመሰልቸት እንደሚሰጡ እንተማመናለን።

ከአክብሮት ጋር

ቃሌ የኢትዮጵያ ፖለቲካ መወያያ ክፍል አድሚኖችና ታዳሚዎች