አዲስ አማራጭ ማቅረብ የፖለቲካ እድገት ያሳያል


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


አክሎግ ቢራራ (ዶ/ር)

መግቢያ፤

የኢትዮጵያ ሕዝብ ተከታታይ ችግር፤ የስልጣኑ ባለቤት አለመሆኑ ነው። ይህ ሕዝብ፤ ለመብቱ ስኬታማነት፤ ለሃገሩ ክብርና ግዛታዊ አንድነት ያደረገው ትግል፤ የከፈለው ዋጋ፤ ሁላችንም የሚያኮራ ነው። ለስኬታማነቱ ማነቆ የሆነው ሕዝቡ ሳይሆን፤ ለሕዝቡ ቁመናል የምንለው ድሃው ህብረተሰብ ያስተማረን እኛው ነን። ድክመታችንና ጥንካሪያችን ረጋ ብለን መመርመርም ያለብን እኛው ነን። ኋላ ቀር የሆነ ያፖለቲካ ባህል ይዘን ዲሞክራሳዊ ስርአት ለመገንባት አንችልም። ለውጥ የሚያስፈልገን መሆኑን፤ በሃቅ፤ በጥበብ መመርመርና ብሩህ አማራጭና አቅጣጫ ማቀርብ ያለብን እኛው ነን። በእኛ እድሜ፤ ሶስት የመንግስት ለውጦች አይተናል፤ የአጼ ሃይለስላሴ ንጉሳዊ፤ ፌውዳላዊ፤ የመንስቱ ሃይለማሪም ወታደራዊ አምባገነን ሶሻሊዝም፤ መለስ ዜናዊ ይመሩት የነበረውን፤ የጠባብ ብሄርተኛ የአንድ ፓርቲ የበላይነት። አንጻራቸው ይለያይ እንጅ፤ እነዚህ መንግስታት፤ የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚ፤ የማህበረሰብ፤ የስራ እድል፤ የትምህርት፤ የሃይማኖት አድሎና የጥቅም የበላይነት አሳይተዋል። የሃይሉ ሚዛን፤ የጥቅሙ ክብደት ተመሳሳይ ባይሆንም፤ ተከታታይ መንግስታት፤ በሃገራችንና በተራው ህዝብ ላይ ያስከተሉት በደል ክብደት ያለው ነው ለማለት ይቻላል። የተራውን ህብረተሰብ ችግር ሊፈቱት አልቻሉም። የመንግስታቱ የበላዮች፤ የገዥውን ክፍል ያገለግሉ ስለነበር፤ የልዩ፤ ልዩ፤ ህብረተሰብ ክፍሎችን ችግር በጥበብና በዘላቂነት ሊያስወግዱት አልቻሉም። ከህዝብ ድምጽና ስልጣን አንጻር ሲታይ፤ ተከታታይ መንግስታት ጥለውልን ያለፉት ችግር እንጅ መፍትሄ አይደለም።

አሁን፤ ይህ አዙሪኝ የሆነ (Vicious Cycle) ጊዜ ያለፈበት የፖለቲካ ባህል እንዲለወጥ ትንሽ ቀዳዳ ተከፍቷል። ዋናው ጥያቄ፤ ይህን እድል ለመጠቀም ምን ያህል ተለውጠናል፤ ተዘጋጅተናል፤ ምን ያህል ፈቃደኛ ነን፤ ምን ያህል ጥበበኛ ነን? ምን ያህል የሃገርና የሕዝብን ጥቅም ከድርጅትና ከግለሰብ ጥቅም በላይ አስቀድመናል? የሚለው ነው። በእኔ እምነት፤ የአሁኑ እድል ካመለጠን፤ ማንንም ለመውቀስ አንችልም፤ መውቀስ ያለብን እኛኑ ነው።

አንድ የምንጋራው አበይት ጉዳይ ቢኖር፤ የህወሓትን/ኢህአዴግን መንግስት ከሁለቱ የሚለየው ዋና ራእይ፤ “በማይታረቅ፤ የብሄር ልዩነት” የታነጸ መሆኑ ነው። በህገ መንግስቱ አንቀጽ ሰላሳ ዘጠኝ የመገንጠል መብትን የተቀበለ የገዥ ፓርቲ የሚለው፤ ከተመቸን አብረን እንኖራለን፤ ካልተመቸን እንገነጥላለን ማለት የኢትዮጵያ ህልውና የተረጋገጠ ሳይሆን፤ የገዥው ፓርቲ እንደፈለገ የሚወስነው ሆኗል ማለት ነው። ማን መብት ሰጠው? የገዥው ፓርቲ፤ ይህን በብሄር ላይ የተመሰረተ ቅርጽ፤ በጦር ሃይል በተረዳ መንገድ ተጠቅሞበታል። አሁንም እንዳለ ነው። የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ፤ አምባገነንነትን እንደ ተፍጥሮ ህግ፤ እንደ ሕዝባዊ አገልግሎት አድርገው አለምን ያሳመኑበትን ምክንያት እዚህ አልተችም። አልፏል። መጥቀስ የምፈልገው፤ የማይታረቅ የብሄር ልዩነት፤ የአምባገነን ስርአት ልጅ ነው፤ አደጋው ከፍ ያለ የሚሆነውም ለዚህ ነው። የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት የታላላቅ፤ በተለይ፤ የምእራባዊያንን፤ በቅርቡ ደግሞ፤ የቻይናን አመኔታና ድጋፍ በማግኘቱ፤ አገራችን ያልታየ እድገት (Growth) አስመዝግባለች እየተባለ ይነገራል። በሃይል ማመንጫ ግድብ፤ በመንገድ ስራ፣ በትምህርት ስርጭት፤ በጤና ጣቢያወች ስፋት፤ በህንጻ፤ በከተሞች ስፋት፤ ወዘተ ያሳየው ለውጥ ሊናቅ አይችልም፤ የሚታይ ነው።

ሆኖም፤ እድገቱ አያስደንቅም።የማያስደንቅበት ዋና ምክንያት፤ ከአጼ ሃይለስላሴና ከደርግ መንግስታት ጋር ሲንጻጸር፤ የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ከልዩ ልዩ ለጋስ መንግስታት፤ ድርጅቶችና የግል ተቋሞች ቢያንስ US$40 billion አግኝቷል። በስደት ላይ የሚገኘው አሁን ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚገመተው ስደተኛ፤ የእድገቱ ተካፋይ ሁኗል። ቢያንስ፤ በአመት ሶስት ቢሊየን፤ ሰቫት መቶ ሚሊዮን ዶላር ይልካል። ተሳትፎው ጎልቶ የሚታየው በተለይ በፍጆት ስራ፤ በቤት ባለቤትነት፤ በግል ህንጻ፤ በምግብ ተቋሞች፤ በሆቴሎች፤ ወዘተ፤ በቤተሰብ፤ ዘመድና ጓደኛ በመደጎም መስክ ላይ ነው። ይህ በፍጆት ላይ የተመሰረተ እድገት፤ መዋቅራዊ ለውጥ አላመጣም፤ ኢትዮጵያ የባሰውን ጥገኛ ሁናለች። ሕዝቡ፤ በተፈጥሮ ሃብቱ ለማዘዝ ከማይችልበት ደረጀ ላይ ደርሷል። የውጭ አገር እንቬስተሮች፤ ሸክ አላሙዲ፤ ወዘተ፤ በሃገራችን አዛዦች ሁነዋል። ተራው ኢትዮጵያዊ በሃገሩ ድምጽ፤ መብት የለውም።

አለም ባንክ እንደሚገምተው፤ ቢያንስ አምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን የሚደገፉት ስደተኛው በሚልከው ገንዘብ ነው። ሌሎች በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን አሁንም፤ የእለት ምግብ የሚያገኙት ለጋስ የሆኑ መንግስታትና ድርጅቶች በሚሰጡት ገንዘብ/ርዳታ ነው። ከሁለቱ መንግስታት ጋር ሲወዳደር፤ የሃይለ ስላሴ መንግስት የእርዳታ ማስረጃ መሰብሰብ (Aid flow data) ከጀመረበት አንስቶ ያገኘው US$150 million፤ ይገመታል። ሳይሰረቅ ከስራ ላይ ዉሏል። የወታደራዊ መንግስት፤ በተለይ ከሶቬት ህብረት ለመሳሪያ መግዣ ያገኘውን ጨምሮ፤ 1974-1991 ከUS$3.4 billion ይገመታል። የህወሓት/ኢህአዴ አንድ አስረኛ መሆኑ ነው። አብዛኛው ለመሳሪያ፤ አገር ለመከላከል የዋለ። ደርግ፤ ከአሜርካ፤ ከእንግሊዝ፤ ከአለም ባንክ ለእድገት የሚሆን ርዳታ አያገኝም ነበር። ከህወሓት/ኢህአዴግ በፊት የነበሩት፤ ሁለቱ የኢትዮጵያ መንግስታት ከእርዳታ የተገኘ ገንዘብ በማሸሺ (Massive Illicit Transfer) አልተከሰሱም። ለመስረቅ፤ ብዙም መፈናፈኛ አልነበራቸውም።

በአንጻሩ፤ የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት በሙስና፤ በአድሎና ፤ከህግ ውጭ ገንዘብ በማሸሺ በሃገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያውን ቦታ ይዟል። በአመት፣ ቢያንስ፤ US$ 3 billion ከህግ ውጭ ከሃገር ይወጣል፤ ይሰረቃል። ሙስናና ከህግ ውጭ የገንዘብ ሽሽት ባይኖር፤ ስርአቱ ተሳትፏዊና ፍትሃዊ ቢሆን፤ የኢትዮጵያ የእድገት ደረጃ ከፍ ባለ ነበር። ቢያንስ፤ ሕዝቡ፤ አስተማማኝ የምግብ ዋስትና ያገኝ ነበር። የስራ እድል በብዛት ይከፈት ነበር። የዋጋ ግሽፈት ሊገታ ይችል ነበር፤ ወዘተ። የተገኘው እድገት ዘላቂነትና ፍትሃዊ ሊሆን አልቻለም የምለው ለዚህ ነው። የእድገት ዋና መለኪያው የጥቂት ግለሰቦች ገቢና ኑሮ ተአምራዊ በሆነ ገጽታ ማደግ ሳይሆን፤ የአብዛኛው ህዝብ ኑሮ መሻሻል ሲያሳይ ነው። “የእድገታዊ መንግስት” አመራርና ፖሊሲ ለፍትህ የታሰበ አይደለም። የነፍስ ወከፍ ገቢ ፍጹም ድሃ ከተባሉት እንደ ናይጀር፤ እንደ ዝምባብዌ ካሉት ሊለይ ያልቻለው ለዚህ ነው። ዋናው መለኪያ፤ የአፍሪካ አማካኝ የነፍስ ወከፍ ገቢ US$1,070 ሲሆን፤ የኢትዮጵያ አሁንም US$365 (በአመት) መሆኑ ነው።

“አስደናቂ እድገት ተጎናጽፋለች” በምትባለው ኢትዮጵያ የገቢ ልዩነት እየሰፋ መሄዱ፤ በድሃና በሃብታም መካከል ያለው የኑሮ ልዩነት አደገኛ ደረጃ ላይ መድረሱ፤ ሊገታ የማይችል የዋጋ ግሸፈት የሰውን ኑሮ መጉዳቱ፤ የወጣቱ እድል ተምሮ መሰደድ ተደጋጋሚ መሆኑ፤ ወዘተ፤ ፖሊሲውና መዋቅሩ የፈጠራቸው፤ ያለለውጥ፤ ህወሓት/ኢህአዴግ ብቻውን ሊፈታቸው የማይችል መሆኑን የሚያሳዩ መለኪያወች ናቸው። “እድገታዊ መንግስት” የተባለው የገዥውን ፓርቲ ባለስልጣኖችና የጥቂት ቤተሰቦችን የኢኮኖሚ የበላይነቱን አስተጋባ እንጅ ዘላቂነትና ፍትሃዊ የሆነ፤ ህይወት ለዋጭ የሆነ እድገትን አልገነባም። ለዚህ የተዛባ የኑሮ ሁኔታ ቀጣይነት አስተዋጾ የሚያደርገው ግልጽነት፤ በህግ የሚተዳደር ውድድር አለመኖሩ ነው። የገበያ ውድድር፤ ያለነጻነት፤ ያለህዝብ ድምጽና ቀጥተኛ ተሳትፎ ሊኖር አይችልም። የሰው ሃይል፤ የተፈጥሮ ሃብት፤ የውጭ እርዳታ፤ የሃገር ውስጥ ገቢ የሚባክነውም ለዚህ ነው። ስርአቱ ለፍትህ፤ ለሰላም፤ ለእርጋታ፤ አብሮና ተቻችሎ ለመኖር ጫና ማድረጉ፤ ድህነትንና ኋላ ቀርነትን ለማጥፋት፤ የሚደረግውን ጥረት ይገታዋል። ለዚህ መፍትሄ የሚሆነው መላውን የህብረተሰብ ክፍሎች በሃገራቸው ሙሉ ተሳታፊ ማድረግ ብቻ ነው። የገዥው ፓርቲ፤ እነዚህን ችግሮች በከፊልም ቢሆን፤ ቀንሷል ቢባል፤ ህወሓት/ኢህአዴግ ሃገራችን ከኋላ ቀርነት፤ ከርሃብ፤ ከስደት፤ ከጥገኝነት፤ ከተስፋ መቁረጥ ነጻ ለማድረግ አልቻለም። የፖለቲካ፤ የህብረተሰብ፤ የኢኮኖሚ ምህደሩ (Political, Social and Economic Space) መስፋት ያለበት ለዚህ ነው። የጋራ ችግሮችን በጋራ ለማሰወገድ የሚቻለው፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ መብቱ ተጠብቆ በሃገሩ ሰርቶ፤ ተከብሮ፤ ተንቀሳቅሶ፤ ኑሮውን ለማሻሻል ሲችል ብቻ ነው።

ሁሉም አለም አቀፍ ዘገባወች የሚያሳዩት፤ ገዡው ፓርቲ የፈጠራቸው የፖሊሲ ችግሮች ለሃገርና ሕዝብ ማነቆ መሆናቸውን ነው። World Economic Forum (2012-2013) ፤ ተቋሞችን፤ አስተዳደርን፤ ህግን፤ ነጻነትን፤ ሙስናና አድሎን፤ የሃብት ሽሽትንና ሌሎች መለኪያወችን ተጠቅሞ ያወጣው ዘገባ ባሳየው መሰረት፤ ኢትዮጵያ ከመቶ አርባ አራት አገሮች መቶ አስራ ስምንተኛ (118th out of 144 countries) ናት። በተለይ በጤና አገልግሎት፤ በትምህርት ጥራት፤ በገብያ ውድድርና ቅልጥፍና፤ በባንክ አገልግሎት፤ በሙስና፤ የሚታየው ዘገባ አሳፋሪ ነው። ዘላቂነትና ፍትሃዊ እድገት ካለ፤ እነዚህ መለኪያወች ከአመት ወደ አመት እየተሻሻሉ በፍጥነት ከሚያድጉ አገሮች ጋር ተወዳዳሪ መሆን ነበረባቸው፤ አይደሉም።
Freedom House ያወጣው Freedom in the World 2012 Index በተለይ፤ የሰብአዊና የፖለቲካ መብቶች ዘገባ፤ የኢትዮጵያን ኋላ ቀርነት በግልጽ ያሳያል።

የአፈና “ወረርሽኝ” ተቋማዊ ሲሆን፤

ይህ ዘገባ፤ ነጻነት ያላቸውንና የሌላቸውን አገሮች በማወዳደር፤ “ነጻ የሆኑ ህብረተሰቦች ማለት ምንድን ነው” ብሎ ይጠይቃል። ትርጉሙ፤ in societies that are free, “There is open political competition, a climate of respect for civil liberties (and human dignity), significant independent civic life and independent media.” ይህ ሁኔታ ኢትዮጵያ በፍጹም የለም። የከለከለው ገዥው ፓርቲ ነው። እንዲያውም፤ ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገች ነው በተባሉበት ባለፉት አስር አመታት አፈናው እየባሰ እንጅ እየተሻሻለ አልሄደም። ዘገባው ያቀረበውን እንይ። “Five of the ten countries that registered the most significant declines in the Freedom of the World Report over the two-year period (2010-2011) were in Africa: Ethiopia, Gambia, Burundi, Rwanda and Djibouti….Ethiopia continued a decade-long trend of authoritarianism with the government of Prime Minister Meles Zenawi making increased use of anti-terrorism laws against the political opposition and journalists.”

የህወሓት/ኢህአዴግ አምባገነን መንግስት በተለይ፤ በተቃዋሚ ፓርቲወችና በጋዜጠኞች ላይ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ጫና፤ አፈና የሚያደርግበት ለምን ነው? ስልጣኑና የኢኮኖሚ ጥቅሙ እንዳይዛባ ነው። የፖለቲካ ውድድር ካለ፤ ተቃዋሚው አማራጮችን ለሕዝብ ያቀርባል፤ ካቀረበ፤ የመመረጥ እድሉ ከፍ ይላል፤ ምርጫ ዘጠና ሰባት ያሳየው ይህን ነው። የገዥው ፓርቲ የበላዮች ከሁሉም የሚፈሩት ነጻ የሆኑ ጋዜጠኞች እውነቱን ለሕዝብ ያለገደብ ማቅረባቸውን ነው። የሚድያ ቁጥጥር የሚጠቅመው ሕዝቡ እውነቱን በቀጥታ ለማግኘት እንዳይችል በመደረጉ ነው። ከጠበንጃ፤ ከመትረየስ የበለጠ መሳሪያ እውቀትና ያልተበረዘ ዜና ሕዝብ ማግኘቱ ነው። ለዲሞክራሲ ቁልፍ መሳሪያ ነጻ መዲያ መሆኑን የገዥው ፓርቲ የበላዮች ጠንቅቀው ያውቃሉ። የሚገቱት ለዚህ ነው።

ሌላ ቀርቶ፤ የኢትዮጵያን እድገት አድናቂ የሆኑ መንግስታትና አበዳሪ ድርጅቶች ያለውን ጫናና አፈና ያውቁታል፤ በውስጥ ይነጋገሩበታል፤ ያምኑበታል። ጠለቅ ብሎ ያየ ታዛቢ፤ አገር ወዳድ፤ የገዥው ፓርቲ ተራ አባል፤ የጦር ሃይሎች አባል፤ የውጭ ተመልካች፤ ህወሓት/ ኢህአዴግ እነዚህንና ሌሎችን አገራዊ ችግሮች ብቻውን ሊፈታቸው እንደማይችል ይገነዘባል። ችግሮቹ ካልተፈቱ፤ ዘላቂነትና ፍትሃዊ እድገት እንደማይኖርም ያምናሉ። በሁሉም ኢትዮጵያዊያን በኩል የአመለካከት ለውጥ አስፈላጊ የሚሆነው፤ አብሮ ተባብሮ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት አስፈላጊ ስለሆነ ነው። ሁሉን አቀፍ የሆነ የመንግስት ስርአት መፈጠር ያለበት ለዚህ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ የማይፈልገው፤ እስካሁን እንደነበረው አመራር “በጠላትነት እየተያዩ፤ ሆድና ጀርባ ሁኖ” መኖርን ነው። ለምን? እንኳን በሃገር ደረጃ፤ በቤተሰብ ደረጃም ቢሆን፤ በጠላትንትና በጥላቻ ባህል የጋራ ችግሮችን ለመፍታት አይቻልም። የሌሎች አገሮች ምሳሌ እንደሚያሳየው፤ ፍትሃዊ፤ ሁሉን አቀፍ፤ ለሁሉም አገልጋይ በሆነ የመንግስት ስርአትና አመራር ፓርቲወች በጠላትነት አይተያዩም፤ ጠላትነት የሚመነጨው ዲሞክራሳዊ ስርአትን ከመፍራት ነው። ልዩነትን እንደ ጠላትነት ከመመልከት ልምድ ነው። አድሏዊ መንግስት ለፍትህ የቆመ ተቃዋሚ ሁሉ፤ ጠላት አድርጎ የሚያሳድደው፤ የሚገድለው፤ የሚያስረው፤ ከሰላም፤ከነጻነት፤ ከዲሞክራሲ ይልቅ መረጋጋትን (Permanent Instability and Suspence) ስለሚመርጥ ነው።

አዲስ የለውጥ ምእራፍ፤ አዲስ አቅጣጫ፤ ዛሬ፤

የዚህ አቅርቮት ዋና አላማ፤ የሃገራችን ሁለ ዘርፍ የሆኑ ችግሮች በጋራ ሊፈቱ ይችላሉ የሚል ነው። አገራዊ ችግሮችን በጋራ ለማሰወገድ ከተፈለገ፤ የአንድ ፓርቲ የበላይነት አገዛዝ በአስቸኳ መለወጥ አለበት። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የስልጣኑ ባለቤት መሆን አለበት። መንግስትና መሪወች የሕዝብ ተገዥ፤ የሕዝብ አገልጋይ፤ የህዝብ ድምጽ አዳማጭ መሆን አለባቸው። አዲስ የለውጥ ምእራፍ ማለት እንደዚህ ነው። ለእውነተኛ የዲሞክራሳዊ መንግስት መቋቋም እውቅትና ብልሃት ያለው ሽግግር ማድረግ አሰፈላጊ ነው የሚለውን መሰረተ ሃሳብ ህወሓት/ኢህአዴግና ተቃዋሚ ሃይሎች ከተጋሩ፤ (መጋራት አለባቸው ብየ አምናለሁ)፤ ወደዚህ የሚያደርሱ ቅድመ ሁኔታወችን (Favorable Conditions) መፍጠርና ማመቻቸት የሁሉም፤ በተለይ የገዡ ፓርቲ መሪወች ታሪካዊ ሃላፊነት ነው።ማሰብ ያለባቸው፤ አምባገነናዊ አገዛዝ ከአሁን በኋላ ለገዥውም ፓርቲ የበላዮች አያዋጣም። ሰላም፤ እርጋታ፤ አይኖርም። አንዱ በይ፤ አንዱ ጦም አዳሪ፤ አንዱ በስር ቤት ነዋሪ፤ አንዱ በቤተመግስት ወይንም ቪላ ኗሪ፤ ሆኖ ሰላምና እርጋታ ይኖራል ማለት ዘበት ነው። ለኢትዮጵያ አገራዊ አንድነት፤ ለመላው ሕዝቧ ሰላም፣ ለፍትህ፤ ለብልጽግና፤ ለእኩልነት፤ ለነጻነት፤ ለከብር፤ ከርሃብ አለንጋ፤ ከጥገኝነትና ከስደት፤ ነጻ ለመሆን፤ ቁመናል የሚሉ መንግስታት፤ ተቋሞችና ግለሰቦች ሊረዱን የሚገባቸው የገንዘብ ወይንም የምግ እርዳታ በመስጠት አይደለም። ፍትህ ካለ የኢትዮጵያ ሕዝብ እራሱን ይችላል፤ አገሩን ዘመናዊ ያደርጋል። ሊረዱን የሚችሉት፤ ህወሓት/ኢህአዴግና ተቃዋሚ ሃይሎች በሙሉ በአስቸኳይ ሁሉን አቀፍ የሆነ፤ ለሰላም፤ ለእርቅ፤ ለፍትህ፤ ለዲሞክራሳዊ ስርአት ሽግግር፤ አገራዊ ስብሰባ እንዲያደርጉ አስተዋጾ በማድረግ ነው። አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ይህን አዲስም እራፍ ከፋች ሊሆኑ ይችላሉ። ለታሪክ ትተውት የሚያልፉት አስተዋጾ ይህ ነው። ካለፉት ጠቅላይ ሚንስትር የሚለያቸውም ይህ ነው። የእኮኖሚ ተሃድሶ ሊመጣ የሚችለው የፖለቲካና የመንፈው ተሃድሶ ሲኖር ብቻ ነው። አለበለዚያ፤ የዛሬ አምስት አመት፤ አለም አቀፍ ዘገባወች የሚያሳዩት ተመሳሳይ ውጤትን ነው።

በመጀመሪያ ደረጃ፤ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ፤ የሃገራችን ችግሮች እኛው ተመካከረን፤ እኛው ተደራድረን፤ እኛው ተሰብሰበን፤ እኛው መፍትሄ ለመስጠት እንችላለን የሚል የአስተሳሰብ ውሳኔ ማድረግ አለብን። ይህን ለማድረግ ኢትዮጵያንና መላውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ማእከል ማድረግ አለብን (Place Ethiopia’s National Inerest and the Interests of all of the Ethiopian People on the Radar Screen and subordinate individual and partisan interest)፤ የቀረው ይከተላል። ይህን ካደረግን በአምስት አመታታ ውስጥ፤ ዛሬ ጋና ነጻ ከተባሉ የአፍሪካ አገሮች ከደረሰችበት ለመድረስ እንችላለን። ጠቅላይ ሚንስትር ሃይለማሪያም ወደዚህ አላማ ለመጓዝ ጥረት ማድረግ አለባቸው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብሯቸው እንደሚቆም አልጠራጠርም።

ሽግግር ሲባል ምን ማለት ነው?

ሁሉን አቀፍ አገራዊ ውይይት አካሂዶ፤ የእርቅ/የዲሞክራሳዊ ስርአት ግንባት ድልድይ የሆነ ጊዜአዊ መንግስት መመስረት ማለት ነው። ይህ በውይይት እንጅ በዛቻ፤ በፉከራ፤ በመለፍለፍ የሚገኝ አይደለም። ለዚህ ለተቀደሰ፤ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሚመኘው አላማ፤ መንፈሳዊ አባቶች፤ የሃገር ሽማግሌወች፤ የታወቁ ምሁራን፤ ወዘተ ድልድይ ሁነው “ተሰብሰቡ፤ ተነጋገሩ፤ አገራችንና ጉራማይሌ ሕዝቧን አስቀድሙ፤ መወነጃጀልን አቁሙ፤ “ታሪክ ያላችሁና ጥበበኛ መሆናችሁን ለአለም ህብረተሰብ አስመስክሩ” ሊሉና የመተማመን ቅድመ ሁኔታን ሊያጠናክሩ ይችላሉ። የድርድር ምርኩዞች፤ አገራዊ አንድነት፤ ሰላም፤ እርቅ፤ ይቅር ባይነት፤ እኩልነት፤ የህግ የበላይነት፤ ነጻ ምርጫ፤ የፖለቲካ ውድድር፤ ዲሞክራሳዊ ስርአት፤ ሰብአዊ መብቶች፤ ሊሆኑ ይችላሉ። ሌሎችን የኢትዮጵያ ሕዝብ በውይይት፤ በምርጫ ሊወስናቸው ይችላል።

ይህን ስል፤ ህወሓት/ኢህአዴግ ጥቅሙን ወደ ጎን ትቶ፤ ለሰላምና፤ ለእርቅ፤ ለድርድርና ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ግንባታ በሩን በቀላሉ ይከፍታል የሚል “ቅዠት” ውስጥ አልገባም። ጉዞው ቀላል አይሆንም። በመጀመሪያ፤ በሃገር ውስጥና ከሃገር ውጭ ያሉ ተቃዋሚ ድርጅቶች፤ ግለሰቦች፤ ስብስቦች ሁሉ፤ መሰብሰብ፤ መደጋገፍ፤ በአንድ ድምጽ፤ ለአንድ አገራዊና ሕዝባዊ አላማ መቆም አለባቸው። አገር ውስጥ፤ አገር ውጭ የሚባለው ልዩነት መጥፋት አለበት። ይህን ካደረጉ፤ የአለምን ህብረተሰብ፤ በተለይ፤ የደጋፊ መንግስታትን አቋም ሊለውጡ ይችላሉ። ገዥውን ፓርቲ፤ ለድርድር ከሚያስገድዱበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ያለው እድል ከፍ ይላል። ሕዝቡ እንዲደፋፈር ያደርጋል፤ ወጣቱ ትውልድ በብዛት ወደዲሞክራሳዊ ግንባታው፤ ወደ ሰላማዊ አመጹ (Popular, peaceful resistance) እንዲገባ ያበረታታል። የፍርሃትን ባህል ይቀንሳል፤ ወዘተ። ይቻላል ብለን ማሰብ ይረዳል። የገዠውን ፓርቲ ለማሳፈር/ለማጋለጥ ለሚደረገው ትግል አስተዋጾ ያደርጋል። ከውጭ ያለነው አገር ቤት ከሚታገሉ ሃይሎች ጋር የጠነከረ ግንኙነት መፍጠር አለብን፤ የገንዘብ እርዳታ በዘላቂነት መስጠት አለብን።

ያልተሞከረው መሞከር አለበት የምለው ለዚዝ ጭምር ነው። ሆኖም፤ የሰላማዊ አገራዊ ሁሉን አቀፍ ስብሰባና ድርድር ጥሪ፤ ቀላል ይሆናል የሚል ግምት የለኝም። ምኞትና ህልም ሁኖ ሊቀር ይችላል፤ መሞከር አለበት የሚል እምነቴ ግን ጠንካራ ነው። ለዚህ ስኬታማነት ቅድመ ሁኔታወችን ተጠቅሞ፤ የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ሊያደርግ የሚገባውን ጥያዌወች ለአለም ሕዝብና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያለመሰልቸት፤ ማቅረብ፤ ማስረዳት የተቃዋሚወችና የእያንዳዳችን ሁሉ ሃላፊነት ነው።

ከጦርነት ባህል፤ ወደ እርቅና ድርድር ባህል መራመድ ለሃገራችን ዘላቂነት፤ ለመላው ሕዝቧ፤ ፍትሃዊ/ተሳታፊያዊ እድገት ይጠቅማል። ዘመናዊ የፖለቲካ ባህል ማለትም ይህ ነው። ቂም በቀልነት፤ እብሪተኝነት፤ “እኔ ብቻ ነኝ አዋቂው” ባይነት ካልቆመ የትም አንደርስም።

ቅድመ ሁኔታ ምን ማለት ነው? ምን ያካትታል?

“የምርጫ ዘጠና ሰባት የፖለቲካ መንፈስ” አለ ለማለት የሚያስደፍሩ ምልእክቶች አሉ። ዋናው መለኪያ፤ ሕዝቡ ለዲሞክራሳዊ ለውጥ ያለው ጉጉት ነው። አሁንም አልጠፋም። ለዚህ የቆሙለት በእስር ቤት የሚሰቃዩ፤ በድብቅ የሚሰሩ፤ በውጭ የሚታገሉ፤ ህወሓት/ኢህአዴግ በነጻነት እንዲሰሩ ከባድ ጫና ቢያደርግም፤ አገር ቤት ሁነው ቀንና ሌሊት የሚታገሉ የሰላማዊ ለውጥ ደጋፊወች፤ ጠበቃወች፤ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ጋዜጠኞች አሉ። በተለይ ወጣቶች። ቅድመ ሁኔታወች ይመቻቹ ስል፤ መግለጫ የማደርገው ከዚህ በፊት ቅንጅት/ህብረት ያቀረባቸውን ስምንት አንኳር ጥያቄወች ነው። ጥቅማቸው፤ ተገቢነታቸው አልተለወጠም። እነዚህም፤

i) ህወሓት/ኢህአዴግ ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠረው የምርጫ ቦርድ በአዲስ መልክ ይዋቀር፤ ከገዥው ፓርቲ ቁጥጥር ነጻ ሆኖ የኢትዮጵያን ሕዝብ ያለ አድሎ ያገልግል፤
ii) ሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲወች፤ የማህረሰብ ድርጅቶች፤ ግለሰቦች መገናኛ ብዙሃን የመጠቀም መብታቸው ይጠበቅ:: የፕሬስ ነጻነት ከስራ ላይ ይዋል፤ የፕሬስ ነጻነት ገደብ የሆነው፤ የሽብርተኝነት ህግ ተብሎ ንጹህ ኢትዮጵያዊያን የሚታሰሩበት ህግ ይወገድ፤
iii) የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ፤ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ ይፈቱ፤
iv) የጦር ሃይሎች በሙሉ፤ በፖለቲካ ውድድር ውስጥ ጣልቃ መግባታቸውን ያቁሙ፤ ከገዥው ፓርቲ ቁጥጥር ነጻ ሁነው፤ አገራቸውንና መላውን ሕዝብ ያገልግሉ፤
v) የህግ ተቋሞች፤ ፍርድ ቤቶች በሙሉ ከማንም ፓርቲ ቁጥጥር ነጻ ሁነው፤ ህብረተሰቡን ያገልግሉ፤
vi) ከገዥው ፓርቲ ቁጥጥር ነጻ የሆነ ኮሚሽን ተቋቁሞ ሁሉንም ግድያወች ይመርምር፤
vii) የፓርላማ አስተዳደር/አሰራር ዲሞክራሳዊና ግልጽነት ባለው መንገድ ይስራ፤
viii) ከላይ ያሉትን ሁሉ የሚያስተናግድ/ የሚዳኝ ከገዥው ፓርቲ ቁጥጥር ነጻ የሆነ ኮሚሽን ይቋቋም የሚሉ ናቸው።

እነዚህን ጥያቄወች ከስራ ላይ ለማዋል እስካሁን በአምባገነኑ መንግስት ያልተደረገ የፖለቲካ ባህል ለውጥ፤ ሂደትና አቀራረጽ አስፈላጊ ነው። በመጀመሪያ፤ ፈቃደኛነት ማሳየት ያለበት ገዥው ፓርቲ ነው። የኢህአዴ መንግስት፤ ኢትዮጵያንና መላውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ማእከልና ተቀዳሚ አድርጎ ፤ ለነገዋ ኢትዮጵያ፤ ለሰላም፤ ለሕዝብ ስልጣን የበላይነት፤ ለእውነተኛ እኩልነት፤ለእርቅ፤ ለመግባባት፤ በውይይት ልዩነቶችን ለመዳኘት መሞከር ታሪካዊ ጥሪ እንደሆን ካየው፤ እንዚህን ቅድመ ሁኔታወች በስራ ይተረጉማል የሚል ግምት አለኝ። አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ይህን ለማድረግ ትምህርቱም፤ የስራ ልምዱም፤ ቅንነቱም፤ የአቀራረብ ችሎታውም አላቸው። ፈቃደኛ መሆናቸውን የምናየው ወደፊት ቢሆንም፤ ማበረታታ እንጅ ማነቆ መሆን የለብንም።
ሆኖም፤ ተቃዋሚ ሃይሎች በሙሉ ተባብረው ድምጽ ካላሰሙ፤ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመሩት መንግስት ወዶ አያደርገውም የሚሉ ብዙ ናቸው። የሃገራችንና የሕዝቧን ታላቅነት የሚያሳይ ይህ መንገድ መሆኑን መቀበለ ግዴታ መሆኑን ለአለም ሕዝብ ማሳሰብ ጠቃሚ የሚሆነው ለዚህ ነው። ውጭ ያለው ተቃዋሚ በቅንነት፤ ባንድነት ከሰራ፤ የአለምን ሕዝብ አስተሳሰብ ለመለወጥ ይችላል። ሰላም፤ እርቅ፤ ይቅር ባይነት፤ ለወደፊቱ ትውልድ ማሰብ፤ የአገርን፤ የህዝብን ችግሮች በጋራ ለማስወገድ መሞከር ያለመድነው ባህል መስሎ ይታያል፡፡ ራስን፤ ጥቅምን ካላስቀደምን በስተቀር፤ ባህሉ አለን። ኢትዮጵያ ለብዙ ሽህ አመታት ክብሯን፤ ነጻነቷን ይዛ የቆየችው ልዩኑነቶችን በማቻቻል፤ አብሮ መኖርን በማጠናከር፤ በጋራ ቁሞ፤ የውጭ ጠላትን በመከላከል ነው። ህወሓት/ኢህአዴግ ከተከለብን መርዝ አንዱ፤ በዘር መለያየቱ ነው። ወደኋል ዞር ብሎ የመቻቻል ባህልን አድሶ መጠቀም፤ የሃገራችን ሕዝብ ታላቅነት የሚያሳይ እንጅ የድክመት ምልክት አለመሆኑን በተግባር ማሳየት ያለብን እኛው ነን። በዘር ልዩኑት የተበከለ መርዝ ለእኛ ድክመት፤ ለሃገራችን ጥገኝነት፤ ኋላ ቀርነትና ድህነት መሳሪያ መሆኑን ሌላው ሳይቀር አገራችን አንጡራ ሃብቷን፤ የባህር በሯን አሰብን ማጣታችን ብቻ ይመሰክራል። ሁሉን አቀፍ ለውጥ የሚጠቅመው ያለፈውን ስህተት አንዳንደግም፤ ብሩህ የሆነ በር እንድንከፍት ስለሚረዳ ጭምር ነው። አብሮ ተባብሮ የሃግርን ችግሮች ማስወገድ፤ ታላቅ የሆነች፤ በፍጥነት የምታድግ ኢትዮጵያን ይፈጥራል፤ መላውን ሕዝቧን ከድህነት፤ ከስደት ነጻ ያወጣል።

አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር፤ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ለዚህ አዲስ ምእራፍ አስተዋጾ እንዲያደርጉ ማበረታታት የሚያስፈልግው ለዚህ ጭምር ነው። በርሳቸው የሚመራው የኢህአዴግ መንግስት ለድርድር ክፍት መሆን የድክመት ምልክት አይደለም፤ ለሃገር፤ ለመላው ሕዝብ የመቆም ምልክት ነው። ለእውነተኛ ዲሞክራሲ፤ ለጭቁን ብሄር/ብሄረሰብ ፍትህ፤ ለነጻነት፤ የመቆም ምልከት ማለት ይህ ነው። በአንጻሩ፤ ለሰላማዊ ድርድር፤ ለእውነተኛ የህዝብ ስልጣን የሚያሸጋግር መንገድ፤ ለፍትህ አለመዘጋጀት የአንድ ፓርቲ አምባገነን አገዛዝ አሁንም ይቀጥል እንደማለት ነው። ይህን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲረዱት፤ ተቃዋሚ ሃይሎች ሁሉ በጋራ፤ ሃየለማሪያም ደሳለኝ፤ ለፍትህ፤ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ እስከቆሙ ድረስ፤ አብሯቸው እነደሚቆም ማሰማት ያለበት አሁን ነው።

የመከላከያ ተቋሞች አገራዊ ይሁኑ፤

የኢትዮጵያ የደህንነትና የመከላከያ ሰራዊት የአምባገነን መንግሥት ስርአት ጠባቂና ተከላካይ ሆኖ በ”ጥቁር ቀለም” ታሪክ እንዲፈረጅ መፍቀድ የለበትም። ቃል በገባው የህዝብ አደራ መሰረት፤ የአንድ ፓርቲ የበላይነት ማገልገል ሳይሆን፤ የወገኑን ብሶት በማየት፤ “የጉራማይሌ (Diverse/Mosaic)” ሕዝቡን አለኝታነትና ክብር፤ የኢትዮጵያን ግዛታዊ አንድነት ብቻ እንዲያስቀድም፤ መመሪያው እንዲያደርግ ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግ የሚያስፈልገው ለዚህ ነው። ዘጠና በመቶ የሚሆነውን ተራ አባል፤ መካከለኛ እዝ፤ ከአንድ ብሄር የተወጣጣው የበላይ እዝ ሊወክለው አይችልም፤ አይገባም፤ ብለን አደራውን እንዲወጣ፤ ሃይሉ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጫና እንዳያደርግ፤ ወገኑን እንዳይገድል፤ መቀስቀስ አለብን። ለዚህ፤ የቅርብ ምሳሌ አለ።
ውጣ ውረድ ቢያሳይም፤ የግብጽን የጦር ሃይልና የስለላ ድርጅት ከሶሪያው የሚለየው፤ የህዝብ አመጽ ሲነሳ፤ ታንክ፤ የጦር አውሮፕላን፤ መትረየስ፤ የጠበንጃ አፈሙዝ ወደ ሰላማዊው የግብጽ ህዝብ አላዞረም። ባለማዞሩም፤ የእርስ በእርስ እልቂት ዝቅተኛ ነው፤ የጦር ሃይሉ ከህብረተሰቡ ጎን ቁሟል። አገራዊ እንጅ የገዡ ፓርቲ አገልጋይ አለመሆኑን አስመስክሯል። የኢትዮጵያ የጦር ሃይል የሚያኮራ ታሪክ ሊሰራ ይችላል ብየ የምገምተው፤ የራሱ የሚያኮራ ታሪክ ስላለው፤ አገር ወዳድ ስለሆነ፤ አብዛኛው ከህብረተሰቡ ጋር ያለው ግንኙነት ጠንካራ ስለሆነ፤ ጭምር ነው። የሰላም፤ የእርቅ፤ የነጻነት፤ የፍትህ፤ የዲሞክራሳዊ ስርአት ግንባት፤ የመወያየት፤ አብሮ ችግሮችን የመፍታት ጥሪን እንደሚደግፍ ተስፋ የማደርገው ለዚህ ነው። ጠንካራ ኢትዮጵያ ልትኖር የምትችለው ጠንካራና በነጻነት የሚኖር፤ ያለ አድልወ የሚሰራ፤ ሕዝብ ሲኖር ብቻ፤ ነው የሚለውን እሴት ሊቀበል እንደሚችል መገመት አለብን። ጠንካራ ሕዝብ ያለ ፍትህ፤ ያለ መብት፤ ያለ ክብር፤ ያለ ነጻነት፤ ያለ እኩልነት፤ ሊኖር አይችልም ብለን ለመላው አለም ማስረዳት ያለብን እኛው ነን። ይህን የኢትዮጵያ ጦር ሃይል ያውቃል። ጥሪው ሃይሉን የሚመለከተው ለዚህ ጭምር ነው።

ከለቅሶው ባሻገር እንይ፤

የኢትዮጵያ ሕዝብ አገር አቀፍ በሆነ ሁኔታ፤ ተገዶም ሆነ ፈቅዶ ለመለስ ማልቀሱ በአብዛኛው ሕዝብ ላይ ያለውን ብሶትና ጭንቀት፤ በወጣቱ ላይ የደረሰውን አሳፋሪ የስደት እጣ፤ በፍትህ ላይ ያለውን ተደጋጋሚ (Recurring) ጭነትና አፈና፤ በሃገራችን ላይ የሚታየውንና የሚያንዣበበውን ግልጽ አደጋ ሊበርዘው ወይንም ሊሽፍነው አይችልም።
የመለስን እንደማንኛውም ህያው ከዚህ አለም ማለፍ በሰብእነታቸው አስቦ ማዘን/መቀበል የሰው ፍጥሩ ሁሉ ባህርይ ነው። ሆድ የባሰውም ያለቅሳል። እያዘኑ ያለፈውንና የሚመጣውን ማሰብ አስተዋይነት ነው። ከሚያጠያይቁት ነገሮች አንዱ፤ ህወሓት/ኢህአዴግ የመለስን “አስከሬን ለምን” ትእይንት አስመሰለው፤ አቀረቡት፤ ሌሎች እንደሚሉት፤ ለምን “አስከሬኑን መነገጃ አስመሰሉት? ለአሁኑና ለተከታታይ ትውልድ ምን መልእክት ለማስተላለፍ ተብሎ ነው? ህወሓት/ኢህአዴግ የቀናት አገር አቀፍ ለቅሶ “ሲያውጅ” የሚያስተላልፈው የአገዛዝ መልክት ስላለው ነውን? ይህ ከሆነ፤ መልእክቱ ምንድን ነው? ለነዚህም ከማውጣት ከማውረድ በላይ መልስ የለኝም። አልፏል። ሆኖም፤ ስብሰቡ፤ “ትእይንቱ” አያስገርምም ብለን ልናልፍ እንችላለን። አንዳዶች እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ሰሜን ኮሪያን ሁናለች ብለን እንለፈው። ለመለስ ማለፍ ለምን የዚህን ያህል ለቅሶ አስፈለገ ብለን እንለፈው። በደርግም ጊዜ ሰው ተገዶ ተሰልፏል። ንግግሩ፤ ውይይቱ፤ የውጭ መንግስታት ፕሬዝደንቶችና ተወካዮች ለልቅሶው ለምን መጡ፤ መለስን ለምን አሞገሱ፤ በብዙ ሽህ የሚቆጠሩ፤ ኢትዮጵያዊያን በዘር፤ በሃይማኖት፤ በጾታ፤ በእድሜ፤ በገቢ፤ በኑሮ ሳይገቱ ለምን አለቀሱ፤ በልቅሶው ወቅት ለምን ሕዝቡ የእምቢተኛነት ስሜት አላሰማም፤ የሚለው አይደለም። የዚህ አይነት አስተያየት የትም አያደርሰንም።

በግል ሳየው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጨዋነቱን ደጋግሞ አስምሮበታል፤ እንኳን ለሃያ አመታት አምባገነን ሁኖ የገዛ፤ ለተራ ሰው ያለቅሳል፤ ያዝናል። አንዱም መለያችን ይህ ነው። አብረን ለማልቀስ ከቻልን፤ አብረን የሃገራችን ተጠቃሚወች መሆን መብታችን ነው። ሕዝቡ፤ ኢትዮጵያዊነቱን፤ ሰብእነቱን፤ አስመስክሯል። ሁኔታው ቢፈቅድለት ኖሮ፤ አጼ ሃይለስላሴ ሲያርፉ፤ አገር አቀፍና አለም አቀፍ በሆነ መልኩ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ባለቀሰ ነበር። የሚያሳፍረው፤ የደርግ መንግስት፤ በጊዜአቸው የሚያኮራ ስራ የሰሩትን፤ በአፍሪካና በአለም ከመለስ ዜናዊ በላይ ለሃገራችን እውቅና ከፍ ያለ አስተዋጾ ያደረጉትን መሪ፤ በድብቅ እንዲቀበሩ አደረገ፤ ክብራቸውን በመግፈፍ የኢትዮጵያን ሕዝብ ክብር ገፈፈ። በዚያ ጊዜ የነበሩ እንደሚያስታውሱት፤ በብዙ ሽህ የሚቆጥሩ ኢትዮጵያዊያን በእየቤታቸው አልቅሰዋል። ከዚያ ወዲህ፤ ሁኔታወች አስደናቂ በሆነ መልክ ተለውጠዋል። ከግማሽ በላይ (More than 50 percent of the Ethiopian population of 94 million today) የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያውቀው አንድ መሪ ነው፤ መለስ ዜናዊን።

ከንግስት ዘውዲቱ በኋላ፤ (መቶ አመት ሊጠጋ ነው)፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጤና ምክንያት ከዚህ አለም ያለፈ መሪ ሲቀብር የመጀመሪያው መለስ ናቸው። ከሃዘኑ ባሻገር ልብ ብለን ማየት ያለብን፤ መለስ የተለቀሰላቸውና የተቀበሩት እንደ አንድ ብሄር ተወካይ ወይንም እንደ እንደ ትግራይ ተወላጅ ሳይሆን፤ “እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ መሪ፤ እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ” ሆነው ነው። ይህን ስል፤ለሃያ አመታት የሰሩትን በደል፤ እንርሳ፤ ማለቴ አይደልም፤ ቢያንስ በአራት መጽሃፎች ላይ እርሳቸው የመሩት መግንስት በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያደረሰውን በደል በማስረጃ አቅርቤዋለሁ፤ ሁለቱን መጽሃፎቸን እራሳቸው እንዳነበቡና “እንደተቹብኝ” ተነግሮኛል። ከደጋፊወቻቸው ጋር በይፋ ተከራክሪያለሁ።

ከጠባብ ብሄርተኛነት ወደ ኢትዮጵያዊነት፤

ለተመልካቾች እንቆቅልሽ የሆነው፤ የመለስ ኢትዮጵያዊነት እውቅና ያገኘው ከዚህ አለም ሲሞቱ መሆኑ፤ ነው። አንዱ የምንማረው ትምህርት፤ መለስ በኢትዪጵያዊነታቸው ከኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ፤ ከኢትዮጵያ ዋና መታወቂያ ቤተክርስቲያን ከተቀበሩ (ማለትም፤ በአዲስ አበባ)፤ በናቁትና፤ “ጨርቅ ነው” ባሉት ሰንደቅ አላማ” ከተሸፈኑ፤ ህወሓት የተባለው በጠባብ ብሄርተኝነት የተመሰረተው የፖለቲካ ራእይም አብሮ ተቀበረ ማለት ነው። ጠባብ ዘረኝነት ከተቀበረ እልል ብለን መቀበል አለብን። ሌላም አይነት ዘረኝነት እንዳይደገም መከላከል አለብን። ትግራይ፤ አድዋ ቢቀበሩ ኖሮ፤ የአለምና የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ፤ ይደንቀውና ይበሳጭ ነበር የሚል ትርጉም ይሰጥ ነበር። ከዱሮውም እንቃወም የነበረው፤ በብሄር፤ ክልል በተባለ አስተዳደር መደራጀትን ነበር። ለአንድ ብሄር አድልወ ማድረግን ነበር፤ የራስን ብሄር ቡድን ማበልጸግን ነበር። ኢትዮጵያዊነት እስከሞት ድረስ የሚቆይ ሳይሆን፤ ከልጅነት እሰከሞት አብሮ የሚታይ መግለጫ ነው። ከአሁን በኋላ በብሄር መጠራት፤ በብሄር መደራጀት፤ ለብሄር ማሰብ፤ በብሄር መበልጸግ፤ የማይጠቅመው፤ ትርጉም የማይኖረው ለዚህ ነው። በዘር ልዩነት መነገድ በወገንና በሃገር ላይ በደል ሰርቶ እንደማለፍ ነው። መለስ፤ በህይወት በነበሩበት ወቅት፤ “እኔ በብሄሬ ሳይሆን፤ የምኮራው በኢትዮጱያዊነቴ ነው ቢሉ ኖሮ” ታሪካዊ ስራ ሰሩ ለማለት እችል ነበር። አላደረጉም። ሆኖም፤ የቀብራቸው ስነስርአት የለውጥ/የተሃድሶ ምልክት ነው። ወደፊት የምንፈልጋት ኢትዮጵያ፤ ለሁሉም እድል የምትሰጥ፤ ሁሉም የሚኮራባት፤ ሁሉም በፈቃዱ ችሎታ ያላቸውን መሪወቹን የሚመርጥባት፤ አልቅሶ የሚቀብርባት አንድ፤ ፍትሃዊ ሃገር መሆን ይኖርባታል። ከሆነ፤ ሆይ “ብለን እንመርጣለን፤ ወይ አምላክ ብለን” እንቀብራለን ማለት ነው።ነጻነት ማለት ይህ ነው።

ታዛቢወች ለቅሶውን “በአስከሬን መነገድ፤ ምን ትርጉም አለው” የሚሉት ያለፈውና ያሁኑ ምንም ግንኙነት ስለሌለው ነው። መለስ ለኢትዮጵያ ታሪክ፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ንቀት ነበራቸው፤ ለኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ንቀት ነበራቸው፤ ለተቃዋሚው ንቀት ነበራቸው፤ ለጋዜጠኞት ንቀት ነበራቸው፤ ለአስተማሪወች ንቀት ነበራቸው። ለራሳቸው ነገድ አድናቆት ነበራቸው። ሰድበው ለሰዳቬ አስተላልፈውናል፤ ሱዛን ራይስ ስትሰደበን፤ ከመለስ የተማረችውን መነሻ አድርጋ ነው፤ ፈጥራ አይደለም። በተለይ፤ ለተቃዋሚው ክፍል ያላትን ንቀት ነው ያቀረበችው። ከመለስ ባገኘችው ግንዛቬና ድምደማ መሰረት ነው የሚሉ ብዙ ታዛቢወች አሉ። እኔ የማሳስበው፤ ታዝበን ከወቀሳ፤ ወደ ኢትዮጵያዊ ለውጥ ማተኮር አለብን የሚል ነው። አለበለዚያ፤ ሙተውም መለስ እንደተፈለገው ከመቃብራቸው የእኛን አስተሳሰብ ይዳኙታል፤ ይገዙናል። እንደዚህ ከሆነ፤ ሁኔታው የሚያመልክተው የእኛን ደካማነት ነው። ማተኮር ያለብን ለወደፊቷ ኢትዮጵያ፤ ለወደፊቱ ትውልድ ነው። ኢትዮጵያዊያን የሚፈልጉት በኢትዮጵያዊነቱ ኮርቶ፤ ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን አገልጋይ የሆነ መንግስትና መሪ ነው። መጓዝም ያለብን በዚህ በኢትዮጵያዊነት መንገድ፤ ለመላው ኢትዮጵያዊያን አገልጋይ የሆነ ፍትሃዊ ስርአትን ለመገንባት ነው። ቀላል መንገድ አይደለም። የህወሓት/ኢህአዴግ ብዙ ዘርፍ ያለው አገዛዝ መለስ በማለፋቸው አልተለወጠም። በተለይ፤ የቁጥጥር ተቋማት። ቅድመ ሁኔታወች ተስተካክለው፤ ሁሉን የሚያካትት መንገድ ካልተቀየሰ፤ የአምባገነኑ ስርአት እንዳለ ይቆያል፤ አደጋው በዚያው ልክ ያይላል። አደጋው፤ ለህወሓት/ኢህአዴግም ጭምር ነው። ሰላምን የነሳ በሰላም ለመኖር አይችልም። አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ይህን ይረዱታል ብየ እገምታለሁ።

ለዚህ ነው፤ የጠቅላይ ሚንስትሩ አድናቂወች፤ ለኢትዮጵያ እርጋታ፤ ለመላው ሕዝቧ ሰላም፤ ከርሃብ አለንጋ፤ ከስደት፤ ከበሽታ፤ ከጠለላ ማጣት ወዘተ ነጻ መሆን ካሰቡ፤ የስርአቱን ደካማ ጎን ጭምር ማሳየት ይኖርባቸው የነበረው። ለማሳየትም የዲፕሎማቲክ ፕሮቶኮል ካልፈቀደ፣ አድናቆቱን ለዛ፤ ሚዛናዊና እውነተኛነት በተሞላበት፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ “አላዋቂ” በማያደርግበት መልክ ማቅረብ የነበረባቸው።

ተከታታዩ (ክፍል አስራ ሁለት) የአለም ጋዜጠኞች፤ የመንግስታት መሪወች፤ በተለይ፤ የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ውስጥ በተከታታይ የተካሄደውንና አሁንም የሚካሄደውን ጫና፤ ግፍና አፈና ለምን አላዩትም፤ ተቃዋሚው ክፍልስ ለዚህ ምን ስትራተጅ አውጥቷል የሚለውን ይዳስሳል።