ዘመን ባንክ አዲስ የቦርድ ሊቀመንበር ሊመርጥ አልቻለም


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


የዘመን ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ኤርምያስ አመልጋ ከቦታቸው እንዲነሱ መደረጋቸውን ተከትሎ በምትካቸው ሌላ ሰው ለማስመረጥ የተደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀረ፡፡

የብሔራዊ ባንክ ተወካዮች በመሩትና ያለፈው ቅዳሜ በሚሊኒየም አዳራሽ በተደረገው ስብሰባ ወቅት የዘመን ባንክ ጠቅላላ ጉባኤ አባላት ሌላ ሰው ከመምረጣቸው አስቀድሞ ለምን አቶ ኤርሚያስ እንደተባረሩ ማወቅ እንደሚፈልጉ ጠይቀዋል፡፡ ለጥያቄዎቹ የተሰጠው ምላሽ ግን “ይሄን መናገር አንችልም” የሚል ነበር፡፡

የጠቅላላ ጉባኤው አባላት በመልሱ ያለመርካታቸውን የሚያሳዩ በርካታ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን በማከታተል ያቀረቡ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ አንድ ከጀርመን ለዚሁ ስብሰባ ብለው የመጡ የጠቅላላ ጉባኤ አባል አስተያየት ይገኝበታል፡፡

ተሰብሳቢው ዘመን ባንክ አሁን ለደረሰበት ስኬት የበቃው በአቶ ኤርሚያስ አመልጋ ታታሪነት መሆኑን ገልፀው “ስትፈልጉ ባንኩን ልትወስዱት ትችላላችሁ እንጂ ሌላ ሰው አንጠቁምም እናንተስ ብትሆኑ ዛሬ በአቶ ኤርሚያስ የደረሰው ነገ በእያንዳንዳችሁ እንደሚመጣ ማሰብ ሲገባችሁ እንዴት እንደዚህ አይነት ተልዕኮ ተቀብላችሁ ትመጣላችሁ?” በማለት ለባንኩ ተወካዮች ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡

ከሳቸው በመቀጠል አስተያየታቸውን የሰጡ አንዲት የጠቅላላ ጉባኤ አባል በአቶ ኤርሚያስ ላይ የተፈፀመው በደል እዚህ ሀገር ላይ ከአሁን በኋላ ምንም ነገር ላለመስራት እንድወስን አድርጐኛል” ሲሉ አቶ ታምሩ የተባሉ ጠበቃና የጠቅላላ ጉባኤ አባል ደግሞ “እሱ እዚህ ሀገር ምን ያህል የተቡካካ አሰራር እንዳለ ሳያውቅ ነው እዚህ ማጥ ውስጥ የገባው” በማለት ለአቶ ኤርሚያስ ያላቸውን ተቆርቋሪነት ገልፀዋል፡፡

በተሰብሳቢዎቹ አስተያየቶች የተበሳጩት የብሔራዊ ባንክ ተወካይ “ከላይ እሳት ከታች እሳት እኛ ምን እንሁን? በአቶ ኤርሚያስ ላይ የተጀመረው ምርመራ በሁለት ወር ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡ ያኔ ለምን ተባረሩ ለሚለው ጥያቄያችሁ መልስ ልታገኙ ትችላላችሁ፡፡ እስከዚያ ግን በእሳቸው ምትከ ምርጫ አካሂደን እንለያይ” ቢሉም ተሰብሳቢው “የአቶ ኤርሚያስን መጨረሻ ካወቅን በኋላ ምርጫ ማድረግ ካስፈለገ እናደርጋለን በቦታው ላይ እናንተ የፈለጋችሁበትን አስቀምጡበት” በማለት ከቀኑ 10፡00 ላይ ስብሰባውን ረግጦ በመውጣቱ ስብሰባው እንደተቋረጠ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በስብሰባው ላይ ጋዜጠኞች እንዳይገቡ ተከልክለው እንደነበር ታውቋል፡፡