አባ ገብረመድህን የሰላሳ ሚሊዮን ብር ቦንድ ሊገዙ ነው


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


የኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ቀኖና በጣሰ አካሄድ የፓትሪያርክነት ሹመት አግኝተዋል ተብለው ለአመታት ሲወቀሱና ከምዕመኑም ተገቢውን ክብር ሳያገኙ እስካሁን የቆዩት አባ ገብረመድህን (የቀድሞው አቡነ ጳውሎስ) በያዝነው ሳምንት የ30 ሚሊዮን ብር ቦንድ እንደሚገዙ አስታውቀዋል፡፡

አባ ገብረመድህን እገዛለሁ ያሉት ኢህአዴግ ከህዝቡ እየመጣ ያለውን የተቃውሞ ወላፈን ለመከላከል ከተገበራቸው በርካታ የማስቀየሻ ስልቶች አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት የአባይ ግድብ እውን እንዲሆን በሚል ለገንዘብ መሰብሰቢያ እየተሸጠ ያለውን ቦንድ ነው፡፡ ለቦንዱ ግዢ የሚውለውን ገንዘብ የሚያዋጡት ደግሞ በአዲስ አበባ የሚገኙ ቤተ ክርስቲያናት ሲሆኑ ወደ 200 ለሚጠጉ ቤተ ክርስቲያናት ከተጻፈው ደብዳቤ ለመረዳት እንደተቻለው እያንዳንዳቸው ሁለት መቶ ሺኅ ብር እንዲያዋጡ ታዘዋል፡፡

ለአባ ገብረመድህን ቀጭን ትዕዛዝ አፋጣኝ ምላሽ የሰጡት ዘመዶቻቸው የሆኑ ጥቂት የቤተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች ብቻ ሲሆኑ አብዛኞቹ ግን ከምዕመናኑና ከሰበካጉባኤ አባላቱ ጋር መክረው መልስ እንደሚሰጡ መግለጻቸውን ውስጥ አዋቂ ምንጮቻችን አረጋግጠዋል፡፡ የሁን እንጂ አንዳንድ አፍቃሬ ኢህአዴግ የሆኑ ሚዲያዎች የቤተ ክርስቲያናቱ ምላሽ ሳይታወቅ ቤተ ክርስቲያኗ የ30 ሚሊዮን ብር ቦንድ ገዛች ሲሉ ዘግበዋል፡፡

ይህን ጉዳይ አስመልክቶ አስተያየታቸውን የሰጡን አንድ የቅድስት ስላሴ ካቴድራል አገልጋይ የሆኑ አባት “ቤተ ክርስቲያናችን በፖለቲካ እየተበረዘች የመጣችው አሁን አይደለም፡፡ በቅዱስ ሲኖዶሱ ጉባኤ ሳይቀር እነ አቶ አባይ ጸሀዬ እየተገኙ መመሪያ ለአባቶች ሲያስተላልፉ ቆይተዋል፡፡ ሀገር ማልማት የተቀደሰ ተግባር ቢሆንም የአሁኑም የቦንድ ግዢ የፖለቲካ ስሜት የተጫነው ነው፡፡ በየደጀ ሰላሙ ስንት ነዳያን ተዘርግተው የሚልሱትና የሚቀምሱት የሚያቀብላቸው ጠፍቶ በሞት እየረገፉ ለፖለቲካ ድጋፍ ተብሎ የሚወጣውን 30 ሚሊዮን ብር አልደግፈውም፡፡” በማለት ተቃውሟቸውን ገልጸዋል፡፡