Ethiopian Review

HOME | CONTACT | FORUM | ALBUM

የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይስ የመለስ ዜናዊ ምክር ቤት

EthiopianReview.com | November 14th, 2009 at 10:21 pm | | Print This Post

ከምስክረ ዘኅዳር

በቅርቡ ታሪካዊ እየተባለ የተወደሰው በተቃዋሚ ፓርቲ ነን ባዮች እና በመለስ መካከል የተፈረመው የማጭበርበሪያ ሰነድ የመለስን አገዛዝ እንደገና የሚያረጋግጥ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በአድርባዮች፡ በህልመኞች፡ በከሃዲዎችና ግራ በተጋቡ እልከኞች እየተፈጸመ ያለ ከባደ ስህተትና ወንጀል ነው። ሰነዱ ላይ የተዘረዘሩት አብዛኛው መብቶች በመለስ ሕገ-መንግስት ውስጥ የተካተቱ እና በአለም አቀፍ የሰብዓዊና የዲሞክራሲ መብቶች የተደነገጉ ሲሆን፡ እነዚህን መብቶች በተመለከተ ላለፉት 18 ዓመታት የመለስ አገዛዝ ወቅት ለኢትዮጵያ ህዝብ ሙሉ በሙሉ ተረጋግጠዋል እየተባለ ሲለፈፍ የነበረ ነገር ግን ላለፉት 18 ዓመታት ለ24 ሰዓትም እንኳን ተግባራዊ ሆነው የማያውቁ መብቶች ሲሆን፡ አሁን ታሪካዊ የሚያደርጋቸው ተለጣፊው አየለ ጫሚሶ፡ ከሀዲው ልደቱ አያሌው፡ ግራ የተጋባው ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል እና ጨካኙና ራስ ወዳዱ መለስ ዜናዊ ስለፈረሙት ነውን?

ይህ ተቋቋመ የተባለው የፓርቲዎች (የመለስ ዜናዊ) ምክር ቤት አወቃቀሩ አሁን ካለው የመለስ ፓርላማ ብዙም የማይለይ ሲሆን ይባስ ብሎ ግን እነዚ ተፈራራሚ አራት ፓርቲዎች ሌሎች አባል ባልሆኑ ፓርቲዎች ላይ ምርጫን በተመለከተ ውሳኔ የማስተላለፍ መብት ተሰጥቷቸዋል። ይህ እንግዲህ የፀረ-ዲሞክራሲያዊነት የመጀመሪያው መገለጫ ነው። ከእነዚ አራት መስራች ተብዬ ፓርቲዎች ውስጥ እስካ አሁን ድረስ ከኢንጅነር ኃይሉ ፓርቲ በሰተቀር የተለጣፊው አየለ ጫሚሶ እና የከሃዲው ልደቱ ፓርቲዎች ሁልጊዜ ከመለሰ ፓርቲ ጋር የወገኑና ከመለስ ጋር አብረው የሚሰሩ ናቸው። ከአሁን በኃላም እነዚ ተለጣፊዎች እና ህዝብ ከሃዲዎች ከመለስ ጋር ከመስራት ዉጪ ሌላ አማራጭ የላቸዉም፡ ባሁኑ ወቅትም እየመሰከሩ እና እየሰሩ ያሉት ይህንኑ ነው ። እነዚህ ሁለት ቡድኖች የታማኝ ተቃዋሚን መስፈርት እንኳን የማያሟሉ ነገር ግን ለገዢው ፓርቲ ትርፍራፊና ለግል ጥቅማቸው የቆሙ ተለጣፊዎች ናቸው።

ታዲያ የኢንጅነር ኃይሉ ፓርቲ እነዚ ቡድኖችና መለስ በበላየነት በሚቆጣጠሩትና በሚወስኑበት ምክር ቤት አብሮ መሆን ጠቀሜታው ለኢትዮጵያ ህዝብ የዲሞክራሲ ትግል እድገት ወይስ ለመለስ ወይም ለሌላ መበርከክ ነው? ወይስ ከኢትዮጵያ ህዝብ ተደብቆ ለኢንጅነር ኃይሉ ሌላ ቃል የተገባላቸው ነገር አለ? ወይስ እዚህ ምክር ቤት ዉስጥ ምን የረባ የነፃ ምርጫና የዲሞክራሲ ውሳኔ ይወሰናል ብለዉ ነው የሚጠብቁት። አወቃቀሩ በግልፅ ለመለስ የሚጠቅም ሆኖ በተዋቀረ ምክር ቤት መሳተፍ ለመለስ ቀጣይ አምስት ዓመታት የግፍ አገዛዝ ተባባሪ ከመሆን ባሻገር ለኢትዮጵያ ህዝብ የዲሞክራሲ ትግል ምን ፋይዳ ያለው ነገር ሊፈይድ ነው?

የፓርቲዎቹን ምክር ቤት አወቃቀር እና ኃላፊነት ስንመለከት፡ አባላቱ የሚወከሉት ከመስራች ተፈራራሚ አራት ፓርቲዎች (3ቱ የመለስ ታማኞች የሆኑ) ከሚመድቧቸው ከ3-5 በሚደርሱ አባላትና እነሱ ፈቅደውና ተስማምተው አባል ሊወክሉ ይችላሉ በሚሏቸው አዲስ ተቀላቃይ ፓርቲዎች ይሆናል። እንግዲህ መስራች ፓርቲዎቹ እያንዳንዳቸው 5ት አባላት ቢመድቡ ጠቅላላ መስራች የምክር ቤቱ አባላት 20 ሲሆኑ ከዚህ ውስጥ የመለስ ታማኞች 15 ማለትም 75 ፐርሰንት ይሆናሉ ማለት ነው። የመድረክ ፓርቲ ምክር ቤቱን ቢቀላቀል እንኳን የመለስ ታማኞች ድርሻ ወደ 60 ፐርሰንት ሆኖ ምክር ቤት ውስጥ የአብላጫ ወገን ሆኖ ይቀጥላል ማለት ነው። እንግዲህ ይህ ”ታሪካዊ” ነዉ እየተባለ ኃላፊነት በጎደለው አንደበት የሚወደሰው ማንን ለማሞኘት ነው። የኢትዮጵያ ህዘብ በዚህ ርካሽ ቲያትር በሚመስል የማጭበርበሪያ ተውኔት አይታለልም። ይህ ምክር ቤት መለስ እንደልቡ ከሚፈነጭባቸውና ጥቅሙን ከሚያስጠብቁለት ከፓርላማው፡ ከፍርድ ቤቶችና ከምርጫ ቦርድ ምንም የሚለየው ነገር የለም። እንደው ተቃዋሚዋችም አሉበት ብሎ ፈረንጆችን ለማታለል የተወጠነ ርካሽ ቲያትር ነው። ታዲያ ከወዲሁ እንዴት እንደሚሰራ በግልፅ በታወቀና ህፃን ልጅ እንኳን ሊስተው በማይችል ሁኔታ ውስጥ ኢንጅነር ኃይሉ እና ፓርቲው ምን ይሠራሉ? ወይስ እነሱም የመለስ ታማኝ ሆነው አረፉት እንዴ?

ለምክር ቤቱ የተሠጡትን ቁልፍ የሥራ ኃላፊነቶች ስንመለከት፡ ምክር ቤቱ የስነ ምግባር ደንቡ በሁሉም ፓርቲዎች ተፈፃሚ መሆኑን ይከታተላል፡ ያረጋግጣል፡ የምርጫ ስነ ምግባር መጣስ ይመረምራል፡ የአጣሪ ኮሚቴ ያቋቁማል፡ ይመክራል፡ ይቆጣጠራል፡ የተደረሱ ስምምነቶችን ይተገብራል፡ ችግሮችን ይፈታል፡ ወዘተ እንግዲህ ይህ ሁሉ ኃላፊነት የተሰጠው መለስና ታማኞቹ የበላይ በሆኑበት ምክር ቤት ውስጥ ነው፡ ታዲያ የኢንጅነር ኃይሉ ፓርቲም ሆነ፡ ሌላ ሊገባ ይችል ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀውና የሚገፋው ፓርቲ ለኢትዮጵያ ህዝብ ምን ሊፈይዱ ነው፡ መለስና ታማኞቹ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ለሚያደርጉት ርካሽ ቲያትር አሽብራቂና አደግዳጊ ተባባሪ ከመሆን ባሻገር።

የዚህ ምክር ቤትን የውሣኔ አሰጣጥ ደንብ ስንመለከት፡ በምክር ቤቱ ውሣኔ የሚተላለፈው በጋራ መግባባትና በመተባበር ነው ይላል፡ ይህ እንግዲህ የተለመደው የመለስ ተራ የማጭበርበርያ ዘዴ ነው፡ በየትኛው አገር ነው ለሥልጣን ተፎካካሪ ፓርቲዎች በዚህ ዓይነት ውሣኔ የሚያስተላልፉት፡ በምእራባዊያኑም ሆነ በሌሎች ዲሞክራቲክ አገሮች ፓርቲዎች ሥልጣን ለመያዝ አጥብቀውና ጠንክረው ይፎካከራሉ ከዛም በገለልተኛ አካል የፀደቀውን የምርጫ ውጤት ይቀበላሉ እንጂ የገዢው ፓርቲ ታማኝና ተባባሪ ሆነው የገዢውን ፓርቲ ጥቅም ለሚያስጠብቅ የምርጫ ሂደት ተገዢ ነን ብለው እራሳቸውንና ደጋፊዎቻቸውን ከወዲሁ አኮላሽተው ወደ ምርጫ አይገቡም። የምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ባልሆነበት፡ የፍትህ አካለት፡ የፀጥታ ኃይሎች፡ የመንግሥትና ሕዝባዊ ድርጅቶች በመለስ አገዛዝ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር ባሉበት ሁኔታ፡ ለኢንጅነር ኃይሉ ፓርቲ በትክክል የሚፈርዱት ተለጣፊው አየለ ጫሚሶና ከሀዲው ልደቱ አየለ ሊሆኑ ነውን? እንግዲህ የኢንጅነር ኃይሉ ፓርቲ ዕድል የሚወሰነው ትላንት የቅንጅት ዛሬ ደግሞ የቅንጅት አባል የነበሩ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ቀንደኛ ጠላት በሆኑት በአየለ ጫሚሶና በልደቱ አያሌው ሊሆን ነው ማለት ነው። ውጤቱ እንግዲህ በግልፅ የታወቀ ነው። ይህ እንግዲ መለስ ዜናዊ የተለመው አዲሱ ስልት ነው፡ ተቃዋሚዋች እርስ በራስ የሚናቆሩበት አጀንዳ መስጠትና እሱ ደግሞ ከለጋሽ ምእራባዊያን አገሮች የመጪውን ምርጫ አስመልክቶ እየተደረገ ያለበትን ጫና በሽወዳ ማለፍ ማለት ነው። ይህ ለመለስ ዜናዊ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንደሚባለው ነው።

ታዲያ እንዴት በዚህ ሁኔታ ለመለስ ዜናዊ ጊዜያዊ ጥቅም አስጠባቂና ተባባሪ እንሆናለን፡ እንዴት መለስ ዜናዊ እኛ ተቃዋሚዋች ላይ ትያትር እየሰራብንና እርስ በራስ እያራገጠን የግፍ አገዛዙን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጭኖ ይቀጥላል። በጣም የሚገርመው ደግሞ በሪፓርተር ድኅረ ገፅ እንደተዘገበው፡ የፓለቲካ ትግሉ ታላቅ አባት የሁኑት ፕ/ሮ መስፍን ወ/ማርያም አሉ የተባለው፡ ”የመለስ እና የኃይሉ ሻውል መጨባበጥ የጥላቻ ዝንባሌ ለመሰበሩ ምልክት የሚሆን ነዉ፡ ”ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቀየሩ ይመስለኛል” ወዘተ ምን ማለት ነው? በሺዎች የሚቆጠሩ የፓለቲካ እስረኞች በግፍ በሚማቅቁበት ስርዓት፡ የመለስ አገዛዝ አስተዳደሩን ኢኮኖሚውን፡ ፓሊሱን፡ የፍርድ አካላትን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ የህዝብ መጨቆኛ መሣሪያ ሆነው እያገለገሉ ባለበት ሁኔታ የቱ ላይ ነው ለውጥ ያለው። የአባት ፕ/ሮ መስፍን ወ/ማርያምን የእድሜ ሁኔታን በማገናዘብ እና ለኢትዮጵያ ህዝብ ያበረከቱትን ትልቅ የሥራ ድርሻ በማስታወስ ሁልጊዜም አክብሮታችንን ሳንቀንስባቸዉ፡ ቀጣዩ ትውልድ የትግሉን ኃላፊነት በበላይነት ሊመራው ይገባዋል።

መለስ ዜናዊ ጥቅሙን ለማስጠበቅ ከኃይሉ ሻዉል ጋር ብቻ አይደለም ከሌላም ጋር ሊጨባበጥ ይችላል፡ በአንድ ወቅት መለስ እራሱ በግልፅ ሲናገር፡ ”ዓላማዬን ለማሳካት ከሰይጣን ጋርም ቢሆን እሠራለሁ” ብሏል፡ ታዲያ የመለስ ከኃይሉ ሻውል ጋር መጨባበጥ የመለስ የመለወጥ ምልክት ሳይሆን፡ መለስ ጥቅሙን ለማስከበርና በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ በቀላሉ ለመግደል የሚያስችለው ርካሽ ትወና ነው።

(አስተያየቶን በሚከተለዉ የኢሜል አድራሻ ይላኩልን፡ miskirhidar@yahoo.com)

Write a Comment

Please answer the following question:

what is 2 in addition to 4?



Related posts:

  1. ጥያቄ ለኃይሉ ሻውል እና ለመኢአድ አባላቶች
  2. የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፓለቲካ – ከዶክተር ነጋሶ ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ