Ethiopian Review

Ethiopian News and Opinion Journal

አቶ ኃይሉ ሻውል በብርቱካን ጉዳይ ላይ ምን ያደርጉ ይሁን?

ethiopianreview.com | November 15th, 2009 at 2:11 pm |


ግርማ ካሳ (ቺካጎ)

«ብርቱካን በቃሊቲ – አቶ ኃይሉና አቶ መለስ ተጨባበጡ» በሚል አርዕስት ጥቅምት ሃያ አንድ ቀን 2002 ዓ.ም የሚከተለዉን ጽፌ ነበር:

«ይህ የአቶ ኃይሉ ሻውልና የአቶ መለስ ዜናዊ መቀራራብና ተፈረመ የተባለዉም ሰነድ፣ በአሁኑ ወቅት ትልቅ ቦታ ባንሰጠዉም፣ ከአሁን በኋላ ባለዉ ጉዞ ለሁላችንም በሚበጅ መልኩ፣ ከተቃና ትልቅ ጥቅም ሊያመጣ ይችላል ባይ ነኝ። አቶ ኃይሉ ሻዉል፣ ይህ ከነአቶ መለስ ዜናዊ ጋር ያደረጉትን ስምምነት ሕዝብ እንዲቀበለዉና ለሕዝብ መሸጥ ከፈለጉ፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ እንድትፈታ አቶ መለስ ዜናዊን በግልጽ እንዲያነጋገሩና እንዲያሳምኑ ያስፈልጋል። (አሁን ጓደኛሞች ስለሆኑ) አቶ መለስ ዜናዊም ቢሆኑ በሼራተን እንደተናገሩት፣ በአገራችን የሚደረገዉ የ2002 ምርጫ ነጻ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ከፈለጉ፣ በርግጥ ድርጅታቸዉ ለዚህ ቁርጠኝነት ካለዉ በሥራ በተግባር ያሳዩን ዘንድ ይገባል። ከአቶ ኃይሉ ሻውልና ከሌሎች ጋር የተደረገዉ ስምምነት የበለጠ ዳብሮ ጠቃሚ ሊሆን የሚችል ስምምነት እንዲሆንና በሕዝብ የበለጠ ተቀባይነት አግኝቶም ዉጤት እንዲያመጣ፣ ተጨባጭ ሥራዎች በኢሕአዴግ መሰራት አለባቸዉ። ኢሕአዴግንም ተቃዋሚዎችንም ሁሉ የሚጠቅም ስምምነት እንዳይኖር ጋሬጣ የሆነዉን ነገር መግፈፍ ያስፈልጋል። ወ/ት ብርቱካን ሚድቅሳ በአስቸኳይ መፈታት አለባት።»

በቅርቡ አቶ ኃይሉ ሻውል ከኢትዮጵያዉያን ለቀረበላቸዉ በርካታ ጥያቄዎች፣ በአሜሪካን ድምጽ ሬዲዮ ምላሽ ሰጥተዋል። ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል የፖለቲካ እሥረኞችን በተመለከተ ተጠይቀዉ በመለሱት መልስ ላይ ትንሽ ሃሳቤን መስጠት እፈልጋለሁ።

«የርስዎ ድርጅት አባላት ሁሉ ሳይቀር በየጊዜዉ እሥር ቤት እንዳሉ ይዘገባል። እና እሥረኞችን ስለማስፈታት፣ የፓርቲ አባላት እንዳይታሰሩ፣ እንዳይዋከቡ የተሰጣቹህ ዋስትና ምንድን ነዉ ? የተስማማችሁበት ምንድን ነዉ?» የሚል ጥያቄ አቶ ኃይሉ ሻውል ቀረበላቸዉ። ሲመልሱም «በስምምነቱ ዉስጥ የተካተቱ ናቸዉ። … እንዴት እንደሚፈቱ (እሥረኞቹ) ሞዳሊቱዉን ምናምን ተስማምተናል።…… ለፓርቲዎች ምክር ቤት ይቀርቡና የቀረበዉ ጄንዊን(እዉነተኛ) ሆኖ ከተገኘ ይፈታሉ።» የሚል ምላሽ ነበር የሰጡት።

«ይፈታሉ የሚባሉት፣ ከእሥር ቤት፣ በዚህ በሚቋቋመዉ ምክር ቤት የሌሉ ፓርቲዎች ደጋፊዎችንም ነዉ ? ወይስ ይህን ስምምነት የተፈራረማችሁት ደጋፊዎች ብቻ ነዉ ? ምክንያቱም የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ጉዳይ አለ» የሚል ጥያቄ ቀረበ። አቶ ኃይሉ ሻውል ሲመልሱ «ይሄ የሁሉም ተቃዋሚ ፖርቲዎች ፣ ዘጠና አንድ ነዉ ፣ ዘጠና ሁለት አሉ ። እነርሱ ሁሉ የሚያቀርቡት (የፖለቲካ እሥረኛ ማለታቸዉ ነዉ) ትክክለኛ ሆኖ ከተገኘ ይፈታሉ። » የሚል መልስ ሰጡ። በስም «ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ» ለማለት ፍቃደኛ ባይሆኑም አቶ ኃይሉ ሻውል የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ጉዳይም በፓርቲዎች ምክር ቤት፣ ባልሳሳት፣ እንደሚቀርብ ለማስረዳት የሞከሩ ይመስለኛል።

ሐሙስ ግንቦት ሃይ ቀን 2001 ዓ.ም ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በግፍና በጭካኔ የታሰረችበትን አምስተኛ ወር ለማስታወስ በአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ጽ/ቤት በተደረገዉ የቃሌ ምሽት ፕሮግራም ላይ፣ አቶ ኃያሉ ሻውልን ጨምሮ በርካታ የመኢአድ አመራር አባላት መገኘታቸዉ ይታወሳል። በዚያ ቀን የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት አቶ ኃይሉ ሻውል የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ መታሰር ሕገ ወጥ መሆኑን በመግለጽ በአስቸኳይ መፈታት እንዳለባት አሳስበዉም ነበር።

በቅርቡ የብሉምበርጉ ጄሰን ማክሉር እንደዘገበዉ የኢሕአዴግ ባለሥልጣን የሆኑት አቶ ሴኩቱሬ ጌታቸዉ የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ጉዳይ የፖለቲካ ጉዳይ እንዳልሆነና በሚደረገዉ ድርድር ኢሕአዴግ በብርቱካን ሚደቅሳ መፈታታ ላይ እንደማይነጋግር ገልጸዋል። እንደ አቶ ሴኩቱሬ ጌታቸዉ አባባል ኢሕአዴግ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን በግፍና በጭካኔ አስሮ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ እንደሚሆንለት እያሰበ ያለ ይመስላል።

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የታሰረችበት ምክንያትም አቶ ኃይሉ ሻውልም ከዚህ በፊት በተከሰሱበት «ወንጀል» ነዉ። ኢሕአዴግ አቶ ሴኩቱሬ እንዳሉት «ወ/ት ብርቱካን ሚድቅሳ የፖለቲካ እሥረኛ አይደለችም። የወ/ት ብርቱካን ጉዳይ የፖለቲካ ጉዳይ አይደለም» የሚል መከራከሪያ ካቀረበ፣ አቶ ኃይሉ ሻዉል ከዚህ በፊት የታሰሩት በፖለቲካ እምነታቸዉ ምክንያት አልነበረም ማለት ነዉ። እንግዲህ አንዱ ጥያቄ «ይህንን አቶ ኃይሉ ሻዉል እንዴት ያዩት ይሆን ?» የሚል ነዉ። የፓርቲዎች ምክር ቤት የሚሉት ላይ የወ/ት ብርቱካን ሚድቅሳ ጉዳይ ሲነሳ፣ ኢሕአዴግ ብርቱካን «የፖለቲካ እሥረኛ አይደለችም» ብሎ የብርቱካን ጉዳይ እንዳይነሳ ቢያደርግ የአቶ ኃይሉ ሻውል መኢአድ መልሱ ምን ሊሆን ይችላል የሚለዉ ደግሞ ሁለተኛ ጥያቄ ነዉ።

መኢአድ ብርቱካንና ሌሎች የፖለቲክ እሥረኞችን በድርድሩ ያስፈታል – Best Case Scenario ( ከሁሉም የሚሻለዉ ውጤት)

ከአቶ ኃይሉ ሻዉል ጋር የተደረገዉን ስምምነት ወያኔ/ኢሕአዴግና ካድሬዎቹ ከመጠን ባለፈ እያራገቡት እንዳለ እያየን ነዉ። ከአቶ ኃይሉ ሻውል ጋር አቶ መለስ ዜናዊ በመጨባበጣቸዉ ኢሕአዴግ በማይካድ ሁኔታ እጅግ በጣም ትልቅ ጊዜያዊ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ድልን ተጎናጽፏል። የዚያኑ ያህል ደግሞ አቶ ኃይሉ ሻውል ከድርድሩ ቢወጡ ኢሕአዴግ የተጠቀመዉን ያህል ተመልሶ የሚጎዳበት ሁኔታ አለ። በመሆኑም አቶ ኃይሉ ሻውል በኢሕአዴግ ላይ በተዘዋዋሪ መንገድ ትልቅ ተጽእኖ ሊያመጡ የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጠሯል ማለት ነዉ።

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እንዳትፈታ እንቅፋት የሆኑት በኢሕአዴግ ዉስጥ ያሉ ጭፍን አክራሪ ኃይላት እንደመሆናቸዉ፣ አቶ ኃይሉ ሻውል የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳንና ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች መፈታት እንዳለባቸዉ አጥብቀዉ ከተከራከሩ፣ ኢሕአዴግ ዉስጥ ያሉ ልቦናና አይምሮ ያላቸዉ አመራር አባላት በቀላሉ አክራሪዎችን መጫን ይችላሉ። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳም በሳምንታት ዉስጥ ከቃሊቲ የምትወጣበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል።

ይህ ከሆነ በርግጥ በአገራችን ኢትዮጵያ ሁላችንም የምንመኘዉ ሰላማዊ የስልጣን ፉክክር የምናይበት ሁኔታ ይፈጠራል ማለት ነዉ። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የአንድነት ፓርቲዋን ይዛ በሰላም ትንቀሳቀሳለች። አቶ ኃይሉ ሻውልም ወ/ት ብርቱካን ሚድቅሳ የፖለቲካ እሥረኞችን ለማስፈታት ባደረጉት ጥረት በሕዝቡ ዘንድ አድናቆትን ያተርፋሉ። ተወዳጅነታቸዉም ሊጨምር የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠራል። ምናልባትም የወ/ት ብርቱካንና የአቶ ኃይሉ ሻውል ድርጅቶች የበለጠ ግንባር ሊፈጥሩም ይችላሉ። የሼራተኑ መጨባበጥ ዉጤት እንዳመጣ ቆጥረን አብዛኞቻችንም ልንደግፈዉ እንችላለን።

በዚህ ሁሉ ሂደት ኢሕአዴግም በእጅጉ ተጠቃሚ ይሆናል። በአገራችን ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ለማድረግ ወኔ ያለዉ እርምጃ በመወሰዱ በታሪክ ይመዘገባል። ደርግን ለመጣል ደማቸዉን ያፈሰሱ ሰምዓታት መስዓእትነት በከንቱ እንዳልቀረ ያስመስክራል። በኢትዮጵያም የጥላቻ የበቀል ፖለቲካ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያከትማል። በመያያዝና በአንድነት የጋራ ጠላቶቻችን የሆኑትን ረሃብ፣ በሽታ፣ መሃይምነትና ድህነት ላይ መዝመት እንጀምራለን። የተከበረች፣ የበለጸገች አንዲት ዲሞክራሲያዎት ኢትዮጵያንም ለልጆቻን እናወርሳለን። መኢአድም፣ ኢሕአዴግም፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የምትመራዉ የአንድነት ፓርቲም አሸናፊዎች ይሆናሉ።

መኢአድ ችግር ያጋጥመዋል – አቶ ኃይሉ ሻዉል የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት ይሆናሉ – Worst Case Scenario ( በጣም የማይፈለገዉ ዉጤት)

በአቶ ኃይሉ ሻዉል ላይ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ከፍተኛ የሆነ ተቃዉሞ እየደረሰባቸዉ ነዉ። አንዳንዶች «በሚስጥር ከኢሕአዴግ ጋር ወደፊት የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት እንደሚሆኑ ቃል ተገብቶላቸዋል» ይላሉ። ሌሎች ደግሞ በአዲስ አበባ ትልቅ ኢንቨስትመንት ስላላቸዉ ነዉ፣ ጥቅማቸዉ እንዳይነካ፣ የሕዝብን ጥቅም በመሸጥ ከገዢዉ ፓርቲ ጋር የተዋዋሉትና እነ መለስን ለማስቀየም ያልፈለጉት የሚሉም አሉ።

ይህ እዉነት ከሆነ የኢሕአዴግን ማሸነፍ አቶ ኃይሉ ሊፈልጉ ይችላሉ ማለት ነዉ። የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ መፈታትንም በጥቅማቸዉ ላይ እንደመጣ አድርገዉ በማሰብ ለወይዘሪቷ መፈታት አንዳች ጥረት ላያደርጉ ይችላሉ። «ከድርድሩ ዉጭ የሆነዉ ፓርቲዋ እራሱ የርሷን ጉዳይ ያንሳዉ» ብለዉ ብርቱካን እንድትፈታ ከመከራከር ይቆጠቡ ይሆናል። የኢሕአዴግ አክራሪዎች እንደፈለጉትም ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በቃሊቲ ልትቆይ ትችላለች።

የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በእሥር ቤት መቆየት ደግሞ በማያጠራጥር ሁኔታ ምርጫዉ በሕዝብ ተቀባይነት እንዲያጣ የሚያደርግ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ በአገራችን ያለዉን የፖለቲክ ቀዉስ በእጅጉ የሚያባብስ ይሆናል። የመኢአድ አባላት አመራር አባላቶቻቸዉን ሊያስወግዱ ይችላሉ። ካልቻሉም ደግሞ መኢአድን ይደግፉ የነበሩ ሁሉ ፓርቲዉን ልቀዉ ይሄዳሉ። መኢአድ ይፈርሳል ወይንም የግልሰሰቦች ስብሰብ ሆኖ የሚቀርበት ሁኔታ ይፈጠራል። ኢትዮጵያዉያን በሰላማዊ መንገድ የሥልጣን ሽግግር ሊኖር አይችልም ወደሚል መደምደሚያ ይደርሳሉ። ኢሕአዴግም ሕዝብ ሳይመርጠዉ ሕዝብ መረጠኝ ብሎ ለብቻዉ በብረት በትር ከመግዛት ሙከራ ያደርጋል። የከፋዉ ኢትዮጵያዊም ለመብቱና ለነጻነቱ ብረት ያነሳል። ጠመንጃ አንስተዉ የሚንቀሳቀሱ ኃይላት ብቸኛ አማራጭ ይሆናሉ። አገራችንም የእርስ በርስ ጦርነትና ደም መፋሰስ ሰለባ ትሆናለች።

መኢአድ ከድርድሩ ይወጣል፣ ከመድረክ ጋር ግንባር ይፈጥራል (ሁለተኛዉ የተሻለ ዉጤት)

የህዝብ ጥያቄ ነዉና አቶ ኃይሉ ሻውልና ድርጅታቸዉ መኢአድ አጠንክረዉ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እንድትፈታ ሊጠይቁ ይችላሉ። ገዢዉ ፓርቲ ዉስጥ ያሉ አክራሪ ኃይላት ግን ዝንፍ አንልም ብለዉ፣ አቶ ሴኮቱሬ እንዳሉት፣ በምንም አይነት መልኩ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ለመፍታታ ፍቃደኛ ሳይሆኑ ይቀራሉ። ይህ የኢሕአዴግ ግትርነት አቶ ኃይሉ ሻውልንና ሌሎች የመኢአድ አመራር አባላትን ሊያበሳጭ ይችላል።

ነገሩ አልጥም ሲላቸዉና ኢሕአዴግ እየተጠቀመባቸዉ እንደሆነ ሲገባቸዉ መኢአዶች ከስምምነቱ እራሳቸዉን ያገላሉ። ከኢሕአዴግ ጋር መሥራቱ ጥቅም አለዉ እንዳሉት ሁሉ «ለሰላም ስንል ከኢሕአዴግ ጋር ለመሥራት ሞክረን ገዢዉ ፓርቲ ግን ግትር ፖለቲካዉን እያሳየን ነዉ» በሚል ገዢዉን ፓርቲ ያጋልጡታል። ያበረከቱለትን አለም አቀፍ ድጋፍ እንደገና የሚገፉበት ሁኔታ ይፈጠራል።

መኢአድ ከመድረክ ጋር በመተባበር የተቃዋሚዉ ካምፕ የበለጠ እንዲጠናከር ሊያደርግም ይችላል። መድረክና መኢአድ የተደራጀና የተጧጧፈ የእምቢተኝነት ዘመቻ ይጀምራሉ። በምርጫ ዘጠና ሰባት እንደተደረገዉ «ትግሬን ሊያጠፉ ነዉ» የሚል የዘረኝነትን ካርድ በመጠቀም ኢሕአዴግ የጦር ኃይሉንና የትግራይን ሕዝብ ወደእርሱ የመሰብሰብ አቅም ያጣል። መድረክና መኢአድ የሚፈጠሩት ትብብር በትግራይ፣ በጎንደር፣ በወሎ፣ በጎጃም፣ በወለጋ፣ በሸዋ፣ በሲዳሞ፣ በኢሊባቡር በመላዉ አገሪቷ፣ በገጠርና በከተማ ከፍተኛና ሥር ነቀል ሕዝባዊ እንቅስቃሴን ይፈጥራል። በሕዝብ ትግል የሥርዓቱ ለዉጥ የማታ ማታ ይመጣል።

ማጠቃለያ ሃሳብ

እንግዲህ ወደየትኛዉ መንገድ እንደምንሄድ በቅርብ ጊዜ የምናየዉ ይሆናል። የፖለቲካ መሪዎቻችን፣ የኢሕአዴግ አመራር አባላት በሚያደርጉት ድርድርና በሚወስዱት ውሳኔዎች ለሁላችንም የሚበጀዉንና ሁላችንም አሸናፊ የሚያደርገንን አማራጭ እንዲወስዱ ጸሎቴ ነዉ።

በዚህ አጋጣሚ አቶ ኃይሉ ሻውልና መኢአድ ላይ አንዳንዶቻችን እያቀረብነዉ ያለዉን ጠንካራ ትችት ለጊዜዉ ቀነስ ብናደርገዉ ደስ ይለኛል። መኢአድ በሼራተን ያደረገዉን ስምምነት በርግጥ ቅንነት ያለዉ ከሆነ፣ የሚጠቅምና መልካም ጅማሬ ሊሆን ይችላል። እስት ትንሽ እንታገስ። በሕዝብ ሊያስጠላቸዉ የሚችልን እርምጃ ወስደዉ ከኢሕአዴጎች ጋር ተደራድረዉና አሳምነዉ የመኢአድ መሪዎች ተጨባጭ ዉጤት ካመጡ፣ ዛሬ በተናገርነዉ ነገር ነገ ልናፍር እንችላለን።





Related Posts

  1. በነጄነራል ተፈራ ማሞ ላይ የተወሰነዉ የፍርድ ቤት ዉሳኔ በተመለከተ
  2. አቶ መለስና ወ/ት ብርቱካን ሲነጻጸሩ
  3. የሥነ ምግባር ደንብ ውዝግብ በፓርላማ
  4. የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፓለቲካ – ከዶክተር ነጋሶ ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ

Leave a Reply