Ethiopian Review

HOME | CONTACT | FORUM | ALBUM

ጥያቄ ለኃይሉ ሻውል እና ለመኢአድ አባላቶች

EthiopianReview.com | November 18th, 2009 at 1:39 pm | | Print This Post

ከምስክረ ዘኅዳር

በቅርቡ ከመለስ ጋር ያደረጉትን ስምምነት አስመልክተው ለተለያዩ የዜና ማሠራጫዎች እንደገለፁት የተመሠረተው የፓርቲዎች ምክር ቤት አሠራር እና የውሳኔ አሰጣጥ ደንብ በአብላጫ ድምፅ ሳይሆን በስምምነት በመሆኑ ለእርሶም ሆነ ለፓርቲዎ ትልቅ ድል መሆኑን አብሥረዋል። ይህ እንግዲህ አንዱ እና ትልቁ ስህተት ነው። ይህ ትልቅ ድል የመለስ ፓርቲ እንጂ ለሌሎች ሀቀኛ ፓርቲዎ በፍፁም ሊሆን አይችልም። ይህንን ቀላል የመለስ የማጭበርበር ዘዴ እንዴት መገንዘብ ተሳኖት? ይህ ተቋቋመ የተባለውን የፓርቲዎች ምክር ቤት ዋናው ትልቁ የሥራ ኃላፊነቱ ከምርጫው ጋር የተያያዙ ሥነ ምግባር ጉድለቶችን፡ ማጭበርበሮችን፡ በደሎችን እና ስህተቶችን በመመርመር አስፈላጊውን ውሣኔ ማስተላለፍ ነው። በምክር ቤቱ ውስጥ ውሣኔ የሚተላለፈው በአብላጫ ድምፅ ሳይሆን በስምምነት በመሆኑ እንግዲህ በምክር ቤቱ ውስጥ ውሣኔ ሊወሰን የሚችለው ሥነ ምግባር አጉዳዩ ፓርቲ ትክክል ነው ሥነ ምግባር አጉድያለሁ ብሎ ሲስማማ፡ ያጭበረበረውም አጭበርብሬያለሁ ብሎ ሲስማማ፡ በደል ፈፃሚውም በደል አድርሻለሁ ብሎ ሲስማማ ብቻ ይሆናል ማለት ነው። በዚህ ዓይነቱ የአሠራር ዘዴ ስለ አንድ በደል ወይንም የማጭበርበር ድርጊት ውሣኔ ለማስተላለፍ የሚቻለውም በደል ፈፃሚው ወይም አጭበርባሪው ድርጊቱን ፈፅሚያለው እና የሚወሰንብኝን ውሳኔ አብረን እናስተላልፍ ብሎ ሲስማማ እንጂ ከዚህ ውጭ ምንም ውሣኔ ማስተላለፍ አይቻልም ማለት ነው።

እንደዚህ ዓይነት የዋህነት በፓለቲካው ዓለም ቀርቶ በሃየይማኖት ተቋሞች ውስጥም መኖሩ ብዙም የማይታሰብ ነው። ይህ ዓይነት ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ከሣሽም፡ ተከሣሽም፡ ዳኛም ሆነው ሁሉም ተስማምተው ውሣኔ የሚያስተላልፉበት የምርጫ አፈፃፃም ትወና በዲሞክራሲ በተራቀቁትም ሆነ በጀማሪ አገሮች ሲሰራበት ታይቶ አይታወቅም። ይህ የሕፃን የልጅ ልጅ ጨዋታ ነው። በዲሞክራሲ ጀማሪ አገሮች ውስጥ ያሉት የዲሞክራሲያዊ ምርጫ አስፈፃሚ ተቋማት ጠንካራ ባለመሆናቸው፡ በአብዛኛው የምርጫ ሂደት እና አፈፃፃም ውሣኔ የሚወሰነው ተወዳዳሪ ፓርቲዋች በስምምነት በሚያቋቁሙት ገለልተኛ የሆነ የምርጫ አስፈፃሚ አካል ይሆናል እንጂ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች እራሳቸውን በአንድ ጊዜ ዳኛም፡ ከሣሽም፡ ተከሣሽም በሚሆኑበት ዓይነት አካሄድ አይሆንም።

ይህ ዓይነት አሠራር ወጣም ወረደ ትልቁ ጠቀሜታው ለመለስ ፓርቲ ነው። ያለፉት ተመክሮዎችም ሆነ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈፀመ ያለው ሁኔታ በግልፅ እንደሚያስገነዝበው ምርጫን የሚያጭበረብር፡ የምርጫ ሥርዓት የሚጥስ፡ በደል የሚፈፅም ገዢው የመለስ ፓርቲ ነው፡ እንግዲህ ምክር ቤቱ ይህን ማጭበርበርና በደል በመመርመር ውሣኔ ሊያስተላልፍ የሚችለው የመለስ ፓርቲ ሲስማማ ብቻ ነው፡ ምክንያቱም በምክር ቤቱ የአሠራር ደንብ መሠረት ምክር ቤቱ ውሳኔ ማስተላለፍ የሚችለው በሁሉም አባላቱ ስምምነት ብቻ ስለሆነ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ገዢዉ የመለስ ፓርቲ እንደማይስማማ አንድ መቶ አንድ ፐርሰንት ከአሁኑ ማስገንዘብ ይቻላል፡፡ ኢንጅነር ኃይሉ ሻውልም ይህንን ይስቱታል ተብሎ አይታመንም። እንግዲህ ምክር ቤቱ ይህንን መወሰን ካልቻለ፡ ጉዳዩ ከምክር ቤቱ ውጪ በመለስ ሕገ-መንግስት ወይም ሌላ ሕግ ሥልጣን በተሠጠው እና በመለስ ሙሉ በሙሉ ቁጥጥር ስር በሆነ አካል ይወሰናል ማለት ነው። በመመሥረቻው ሰነድ ላይም በግልፅ እንደተቀመጠው ለምርጫ ቦርድ በሕግ የተሰጠው ሥልጣን እንደተጠበቀ ነው ይላል። እንግዲህ ዞሮ ዞሮ መግቢያው ጭራሮ ማለት ይህ ነው።

መለስም ይህንን ሰነድ ሲፈርም የመጨረሻ ውጤቱ የሱን ጥቅም የማይፃረር መሆኑን በሚገባ ተረድቶ፡ በቅድሚያ የቤት ሥራውን በሚገባ አከናውኖ፡ ከባድ የቼዝ ጨዋታም ተጫውቶ የቀረበ ሲሆን በተቃራኒው ኢንጅነር ኃይሉ ሻውል ግን ጉዳዩን በጥልቀት የመረመሩት በፍፁም አይመስልም። ምክር ቤቱ በስምምነት ብቻ ውሣኔ እንዲያስተላልፍ ያቀረብነው ሀሣብ ተቀባይነት በማግኘቱ ትልቅ ድል አግኝተናል ብሎ መፎከር የሃሳቡን እንደምታ ካለማውቅ ሊሆን ይችላል። ይህ እንግዲህ፡ ”…ገደሉን ሳታይ ዓይነት” ማለት ነው። በመኢአድ የቀረበ ነው የተባለው በስምምነት ብቻ ውሣኔ የማስተላለፈ ሀሳብ መልሶ መኢአድን የሚጎዳ እና መለስን በጣም የሚጠቅም ነው። ይህን ሀሣብ መለስ ዜናዊ በብልጥነት መኢአድን መተብተብያ ነው ያደረገው፡፡ ይህ እንግዲህ ለመኢአድ አመራሮችም ሆነ አባላቶች ባቀረባችሁት ገመድ እራሳችሁ መታሰራችሁን የሚያሳይ የመለስን የፓለቲካ ብልጠት የሚያሳይ ሲሆን የእናንተን የፓለቲካ ኪሣራ የሚያሣይ ነው። ከዚህ በፊት መለስ ዜናዊ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ሲሳለቅ ”በረጅም ገመድ የታሠረ ተፈትቶ የተለቀቀ ይመስለዎል” ብሎ ነበር። አሁን ደግም ”እራሱ ባመጣው ገመድ እራሱን አሰርኩት” ብሎ እንደሚሳለቅ ምንም ጥርጥር የለውም። የሆነውም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው።

ሁለተኛው ኢንጅነር ኃይሉን ለመጠየቅ የምፈልገው ምርጫው ዲሞክራሲያዊ እንደሚሆን መለስ ዜናዊ ቃል ገብቶልኛል ብለው የገለፁትን እና የተማመኑበት የሚመስለውን ጉዳይ ነው። በመጀመሪያ ይህንን ቃል መግባት መለስ ዜናዊ ማድረግ ያለበት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ ለእርሶ ብቻ አለመሆኑን አበክረው ቢገልፁለት ለእርሶም የሚበጅ ይሆን ነበር። ሌላው ዋናው ቁም ነገር ግን መለስ ዜናዊ ማን መሆኑን እንዴት ረሱት፡ መለስ ዜናዊ እድሜ ልኩን ሲክድ፡ ሲያጭበረብር ሲዋሽ የኖረ አረመኔ ሰው ነው። መለስ ዜናዊ ለግሉ ሥልጣንና ጥቅም ሲል በጣም ቅርቡ የሆኑ የትግል ጓደኞችን የከዳ ለአገር በሀቅ እና በታማኝነት የሚያገለግሉ ሰዎችን ሥልጣኔን እና ጥቅሜን ይፃረራሉ ብሎ በማሰብ ብቻ በየእስር ቤቱ የሚያጉር፡ የሚያሰቃይ እንዲሁም በአሰቃቂ ሁኔታ የሚያስገድል ሰው መሆኑን አገር ያወቀው ሀቅ ሲሆን፡ ይህ ዛሬ እንዴት ለእርሶ ሊዘነጋዎ ወይንም ላይገባዎ ቻለ?

ስለምርጫው ዋናው ጉዳይ መለስ ዜናዊ ነገ የሚክደውን ወይንም የሚያጭበረብረውን ቃል ሳይሆን፡ ምርጫውን ነፃና ዲሞክራሲያዊ የሚያደርጉ ሁኔታዎችንና አካላትን አሁኑኑ መፍጠር ነው። ሁሉም ፓርቲዎች የሚስማሙበት ገለልተኛ የሆነ የምርጫ ቦርድ መመስረት፡ ገለልተኛ የምርጫ አስፈፃሚ አካላት ማደራጀት፡ ገለልተኛ የምርጫ ታዛቢዎችን በሁሉም የምርጫ ጣቢያ መመደብ፡ ሕዝቡ ማንንም ሳይፈራ እንዲመርጥ ያለፈው ምርጫ ዓይነት በእስር የመገላታትና በጭካኔ የመገደል ሁኔታ እንደማይኖር ማረጋገጥ እና ሌሎች ለነፃ እና ለዲሞክራሲያዊ ምርጫ አስፈላጊ የሆኑ ሁኔታዎችን መፍጠር እንጂ አትዮጵያን በግፍ በጭካኔ እና በማጭበርበር በመግዛት ላይ ያለው መለስ ዜናዊ ሥልጣኔ እንድትነጥቁኝ የሚያስፈልገውን አደርጋለሁ ብሎ ለኢንጅነር ኃይሉ ሻውል ተረት ተረት በሚመስል ቃል መግባት ከቶም ሊሆን አይችልም። ቃል የተገባው ነገር ማጭበርበሪያ ብቻ መሆኑን በቀላሉ የሚያረጋግጠው ደግሞ ቃል የተገባውን ነገር ተግባሪያዊ ሊያደርግ የሚችል ምንም ነገር ባለመኖሩ ነው። ይህ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያውቀው እና የተለመደው የመለስ ዜናዊ የማጭበርበርያ መንገድ ሲሆን፡ የሚያስገርመው ግን ለፓለቲካ አዲስ ጀማሪ የሆነ ሰው እንኳን ሊስተው የማይችለውን እንዴት በፓለቲካ ውስጥ ለብዙ ዓመታት ተሣትፎ ያላቸው ኢንጅነር ኃይሉ እና የመኢአድ አባላቶች ሊስቱት ቻሉ።

በመጨረሻም ኢንጅነር ኃይሉ ይህ ጉዳይ የሕዝብ ስለሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መልስ እንዲሚሰጡበት በመተማማን የምጠይቃቸው ሁለት ጥያቄዎች የሚከተሉት ናቸው፡

1. በአንድ በጣም ከባድ የምርጫ ጉዳይ ላይ የተመሠረተው የፓርቲዎች ምክር ቤት ውሣኔ በስምምነት ለማስተላለፍ ካልተቻለው ጉዳዩ በየትኛው አካል ሊወሰን ነው?

2. የገዢው ፓርቲ መሪ መለስ ዜናዊ ምርጫው ነፃ እና ዲሞክራሲያዊ ይሆናል ብሎ ቃል ገብቶልኛል ያሉትን በማመን ብቻ ነው ወደ ምርጫ የሚገቡት ወይንስ ይህ ቃል ተግባራዊ እንዲሆን ተገቢው ሁኔታዎች ካሁኑ እንዲደረጉ ያስደርጋሉን? ይህንንም ለሕዝብ ያሳውቃሉን?

(በሚከተለው የኢሜል አድራሻ ለፀሀፊው አስተያየት መላክ ይቻላል፡ miskirhidar@yahoo.com)

Write a Comment

Please answer the following question:

what is 5 in addition to 5?



Related posts:

  1. የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይስ የመለስ ዜናዊ ምክር ቤት
  2. የሥነ ምግባር ደንብ ውዝግብ በፓርላማ