የሥነ ምግባር ደንብ ውዝግብ በፓርላማ
በኃይሌ ሙሉ | The Reporter
አራቱ ፓርቲዎች የተስማሙበትን የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሥነምግባር ለመደንገግ የተዘጋጀው አዋጅ ሐሙስ ዕለት ለተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት የተካሄደበት ከተለመደው አሰራር ለየት ባለ መልኩ ነበር፡፡
የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት የአማካሪ ምክር ቤት አባላት “የምርጫ ሥነምግባሩ ደንብ አዋጅ ሆኖ እንዲፀድቅ ወደ ምክር ቤቱ ይመራ ወይስ አይመራ?” በሚለው ጉዳይ ላይ ባለመስማማታቸው ሐሙስ ዕለት ጉዳዩ ለምክር ቤቱ ቀርቦ ውሳኔ እንዲሰጥበት ተደርጓል፡፡
በአማካሪ ምክር ቤት ውስጥ አብዛኛውን መቀመጫ የያዘው ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ቢሆንም አንድ ጉዳይ አጀንዳ ሆኖ እንዲቀርብ ውሳኔ የሚተላለፈው በስምምነት እንጂ በአብላጫ ድምጽ ባለመሆኑ ረቂቅ አዋጁ ወደ ምክር ቤት እንዲመራ ግድ ብሏል፡፡
የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሥነምግባር ለመደንገግ በወጣው አዋጅ አጀንዳ ሆኖ መቅረቡን የተቃወሙና የደገፉ የአማካሪ ምክር ቤት አባላት መኖራቸውን ጠቁመው ሁለቱም ወገኖች መከራከሪያ ነጥባቸውን እንዲያቀርቡ እድል ሰጥተዋል፡፡
ሥነምግባር ደንቡ አጀንዳ ሆኖ መቅረብ የለበትም በማለት በመጀመሪያ የመከራከሪያ ሀሳብ ያቀረቡት የኢዴኃህ ተወካይ አቶ ገብሩ ገብረማርያም ናቸው፡፡
ሥነምግባር ደንቡ በህገ መንግሥቱ ለምርጫ ቦርድ የተሰጠውን ስልጣን የሚጥስና የምርጫ ቦርድን ህልውና የሚሸረሽር መሆኑን የገለጹት አቶ ገብሩ አጀንዳው ለምክር ቤት መቅረብ የለበትም ሲሉ ተቃውሟቸውን ሰንዝረዋል፡፡
አቶ ብሩ በርመጅን በበኩላቸው ከህብረተሰብ እድገት ጋር ህጐች እንደሚሻሻሉ ነገር ግን አዋጅ በአዋጅ ላይ እንደማይወጣ ገልጸው በአራቱ ፓርቲዎች የተፈራረሙት የሥነምግባር ደንብ ህግ ሆኖ እንዲወጣ ማድረግ የምርጫ ቦርድ ስልጣንን እንደሚጥስ ተናግረዋል፡፡
የሥነምግባር ደንቡ ህግ ሆኖ እንዲጸድቅ ለማድረግ አጀንዳ ሆኖ ለምክር ቤቱ መቅረብ አለበት በማለት የተከራከሩት አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው ፖለቲካ ፓርቲዎች ይቅሩና አንድ ግለሰብ ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ የማቅረብ መብት እንዳለው ጠቁመው አራቱ ፓርቲዎች የተፈራረሙትና ሥነምግባር ደንብ ህግ ሆኖ እንዲጸድቅ ማድረግ ምንም ዓይነት ህግ እንደማይጥስ በማስረዳት ጉዳዩ በአጀንዳነት እንዲቀርብ ጠይቀዋል፡፡
በፓርላማ የመንግሥት ተጠሪ አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝም በተቃዋሚዎቹ የቀረበው መከራከሪያ ሀሳብ ብዙም ውሀ የማይቋጥር መሆኑን፣ የምርጫ ሥነምግባሩ ደንብ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጐትና ጥቅም በማየት እንደተዘጋጀ ጠቁመው ሥነምግባር ደንቡ ብጥብጥ እንዳይፈጠር የሚያደርግ በመሆኑ አጀንዳ ሆኖ መቅረብ አለበት ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አቶ ኃይለማርያም እንዳሉት በዓለም ደረጃ ባለው አሰራር የምርጫ ስነምግባር ደንብ በሦስት ዓይነት መልኩ ይዘጋጃል፡፡ አንደኛው ፓለቲካ ፓርቲዎች ተደራድረው በራሳቸው ፍላጐት የሚተገበር (በፈቃደኝነት የሚመሰረት የስነምግባር ደንብ) ሁለተኛው የምርጫ አስፈፃሚው (ምርጫ ቦርድ) አዘጋጅቶ የሚያቀርበውና ፓርቲዎች አስተያየት ሰጥተውበት ራሱ የሚያስፈጸምበት ሲሆን ሦስተኛው የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጭ ብለው ከተደራደሩ በኋላ አስገዳጅነት እንዲኖረው ፓርላማ ቀርቦ እንዲጸድቅ የሚደረግ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የፖለቲካ ባህል ፓርቲዎች ሠጥቶ የመቀበል ባህል ስለሌላቸው ከአንደኛውና ከሁለተኛው አማራጭ ይልቅ ሦስተኛው አማራጭ ሁሉንም ፓርቲዎች ግዴታ ውስጥ የሚያስገባ በመሆኑ ተመራጭ ሆኖ እንደተገኘ ያመለከቱት አቶ ኃይለማርያም በድርድሩ ሂደት የጥላቻና የመራራቅ ፖለቲካ ቀርቶ በመቀራረብ የሚሰሩበት ሁኔታ እንዳለ መታየቱን አስረድተዋል፡፡
ሁለቱም ወገኖች የመከራከሪያ ሀሳብ ካቀረቡ በኋላ ጉዳዩ በአጀንዳነት ይቅርብ ወይስ አይቅረብ በሚለው ላይ ድምጽ ተሰጥቶ በ255 ድጋፍ በ58 ተቃውሞና በ4 ድምጽ ተአቅቦ በአጀንዳነት ተይዟል፡፡
ሥነምግባር ደንቡ በአማካሪ ምክር ቤት ስምምነት ስላልተደረሰበት ለውይይት የሚሆን ሰዓት እንዳልተመደበለት የገለጹት አፈጉባኤ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ለውይይቱ 1፡30 መመደቡን ይህንንም የመንግሥት ተጠሪውና እርሳቸው እንደደገፉት ተናገሩ፡፡ ከዚህ በኋላ ነው የሥነስርዓት ጥያቄ የተጀመረው፡፡ አንድ የፓርላማ አባል በተደጋጋሚ ሥነስርዓት እያሉ ጥያቄ ቢያነሱም አፈ ጉባኤው ሥነስርዓት የሚያስጠይቅ ነገር እንዳልተፈጠረ በመግለጽ የፓርላማ አባሉን ጥያቄ ሳይቀበሉት ቀርተዋል፡፡ ከዚያ በኋላ በቀጥታ የተሄደው ወደ ውይይቱ ነው፡፡
የሥነምግባር ደንቡ አዋጅ ሆኖ መጽደቅ የለበትም ብለው የተከራከሩት አቶ ብሩ በርመጅን “የሥነምግባር ደንቡ የተለየ ነገር ይዞ ይመጣ ይሆናል” የሚል እምነት የነበራቸው ቢሆንም ቀደም ሲል ከነበረው የማስፈጸሚያ መመሪያ የተለየ ነገር እንዳላገኙበት ይልቁንም በአዋጅ ላይ አዋጅ ይዞ እንደመጣ ተናግረዋል፡፡ “እንኳን ዘንቦብሽ እንደውም ጤዛ ነሽ” ሲሉ የተረቱት አቶ ብሩ ሥነምግባር ደንቡ ብዥታ የሚፈጥር መሆኑን ገዋጸዋል፡፡
ገዥው ፓርቲና መንግሥት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ በሆኑበት አገር ሥነምግባር ደንቡ በመንግሥት ሥራ አስፈፃሚ አካላት ላይ ምንም ጫና እንደማይፈጥር የገለጹት አቶ ብሩ ሥነምግባር ደንቡ በአብዛኛው ያተኮረው በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጽዕኖ እንደሚፈጥሩ ተደርጐ መቅረቡም እንቆቅልሽ እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡
በህገ መንግሥቱ ምርጫ ቦርድ ተጨማሪ የሥነ ምግባር ደንብን ከሌሎች ጋር በመመካከር ያወጣል ተብሎ የተጠቀሰውን ህግ በመጣስ የሥነ ምግባር ደንቡ በመዘጋጀቱ ምርጫ ቦርድ በአቋራጭ ሥልጣኑን እንደተነጠቀ የተናገሩት አቶ ብሩ አጀንዳው ተመልሶ ወደ ምርጫ ቦርድ እንዲመራ ጠይቀዋል፡፡
ጉዳዩ አጀንዳ ሆኖ መቅረብ የለበትም በማለት የተከራከሩት የፓርላማ አባላት ህግ ሆኖ እንዲጸድቅ ወደ ምክር ቤት የቀረበው የምርጫ ሥነምግባር ደንብ የተዘጋጀው ትልልቅ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ባላካተተ መልኩ በመሆኑ ተቀባይነት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡
አቶ ብሩ አስተያየታቸውን ከሰጡ በኋላ አፈ ጉባኤው ለቅንጅቱ ሊቀመንበር አቶ ለገሰ ቢራቱ እድል ሰጡ፡፡ ይሁን እንጂ “ሥነስርዓት” የሚል ድምጽ ከአንድ የፓርላማ አባል ተነሳ፡፡ የሥነስርዓት ጥያቄውን ያነሱት አቶ ገብሩ ገብረማርያም ነበሩ፡፡ እድሉ ተሰጣቸው፡፡ አቶ ገብሩም “የተከበሩ አቶ ለገሰ ፓርላማ ውስጥ ያሉት ኢድሊን ወክለው እንጂ በቅንጅት ስም አይደለም፤ በኢድሊ ስም ፈርመው ፓርላማ የገቡበት ሰነድ አለኝ” በማለት ለአቶ ለገሰ በቅንጅት ስም እድል እንዳይሰጣቸው ጠየቁ፡፡ ነገር ግን አፈ ጉባኤ አምባሳደር ተሾመ “እኔ የማውቀው ቅንጅት ከምርጫ በኋላ የተፈጠረውን ቅንጅት ነው” በማለት የሥነስርዓቱን ጥያቄ ሳይቀበሉት ቀሩ፡፡ አቶ ለገሰም ንግግራቸው ቀጠሉ፡፡
በዴሞክራሲ ስርዓት ውስጥ በአብላጫ ድምጽ የተወሰነውን መቀበል እንደሚያስፈልግ የጠቆመት አቶ ለገሰ 65ቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተስማሙበት ሥነምግባር ደንብ እንደ ህግ መቅረቡ ትልቅ እመርታ መሆኑን ገልጸው “ቀጣዩ ምርጫም በህዝብ ተቀባይነት ያለውና ወደፊት የሚገነባው ሥርዓት በጡንቻና በመሳሪያ ሳይሆን በሕዝብ ድምጽ የሚያምን ነው ብለን እናምናለን” ብለዋል፡፡
ቀጥሎ አስተያት የመስጠት እድል የፓርላማ ቡድን አባል የሆኑት መቶ አለቃ ጉአ ነበሩ፡፡
መቶ አለቃ ጉአ የሥነምግባሩን ደንብ በመደገፍ ንግግር እያደረጉ ባሉበት ወቅት ሌላ የሥነ ስርዓት ጥያቄ ተነሳ፡፡ ጠያቂው እድል ሲሰጣቸው የፓርላማ አባል መቶ አለቃ ጉአ አስተያየት እያቀረቡ ያሉት እያነበቡ በመሆኑና አስተያየታቸውን በጽሑፍ እንደሚያቀርቡ አስቀድመው ባለማሳወቃቸው ጽሑፉን ማንበብ እንዲከለከሉ የሥነስርዓት ጥያቄ ያነሱት የፓርላማ አባል ጠየቁ፡፡ አፈ ጉባኤ ተሾመ ቶጋ ግን “ሁሉም ሰው እስከአሁን ሲናገር የነበረው በማስታወሻው እያነበበ ስለሆነ መቶ አለቃ ጉአ ከማስታወሻቸው እያነበቡ አስተያየት መስጠት ይችላሉ” በማለት የሥነስርዓት ጥያቄውን በድጋሜ ውድቅ አደረጉት፡፡ እያነበቡ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ የተፈቀደላቸው የቅንጅቱ ተመራጭ መቶ አለቃ ጉአም “በሥነምግባር ደንቡ ህይወት ያላቸው 65 የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳተፉበት በመሆኑ ይህ ደንብ ወደ ቋሚ ኮሚቴ ሳይመራ በሁለተኛ ንባብ እንዲያልፍ” በማለት ሲጠይቁ አፈ ጉባኤ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ “ምንም እንኳን የፓርላማ ቡድን ዛሬ እንዲያልፍ ቢፈቅድም እኛ ደንቡን ተከትለን እንሄዳለን” የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡
የኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው የሥነምግባር ደንብ ህገመንግሥቱን ይጥሳል በማለት የተከራከሩ ወገኖች አንድም አንቀጽ አውጥተው ሲተቹ አለመታየታቸውን ጠቁመው “ይህም ሰነዱ የተዋጣለት መሆኑን ያሳያል” ብለዋል፡፡
ትልልቅ ፓርቲዎች ከድርድሩ ተገፍተዋል በሚል ከአንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት የቀረበውን ትችት በተመለከተ አስተያየታቸውን ሲሰጡም “ትልቅነት የሚለካው በዕድሜ ይሁን በቁመት አላውቅም” ብለዋል፡፡
አቶ ልደቱ ይህንን ሲናገሩ አቶ በቀለ የተባሉ የፓርላማ አባል የሥነስርዓት ጥያቄ አቀረቡ፡፡ አፈ ጉባኤው ግን ጥያቄውን አልተቀበሏቸውም፡፡ አቶ በቀለ የሥነስርዓት ጥያቄ የማቅረብ መብት አለኝ በማለት ቢከራከሩም አፈ ጉባኤ ተሾመ የሥነስርዓት መብትን ያለ አግባብ መጠየቅ በደንቡ መሠረት የተከለከለ መሆኑን በመግለጽ እድል አልሰጧቸውም፡፡ እናም አቶ ልደቱ ንግግራቸውን ቀጠሉ፡፡ አንድ ሰው በሌሎች ላይ አስተያየት ሲሰጥ ምላሹ ምን ሊሆን እንደሚችል መጠበቅ እንዳለበት ያስገነዘቡት አቶ ልደቱ ሌሎች ምላሽ በሚሰጡበት ሰዓት አስተያየታቸውን በጩኸት ለማፈን መሞከር ተገቢ አለመሆኑን ገለጹ፡፡
አንድም ተቃዋሚ ፓርቲ በሰነዱ ላይ ትችት ያቀረበበት ሁኔታ አለመኖሩ ሰነዱን ብቁ መሆኑን እንደሚያሳይ የገለጹት አቶ ልደቱ ምርጫው እየተቃረበ በመሆኑ ቋሚ ኮሚቴው በአስቸኳይ አይቶ ሥነምግባር ደንቡ ህግ ሆኖ እንዲጸድቅ ጠይቀዋል፡፡
አቶ ልደቱ አስተያየታቸውን ሲጨርሱ የማስተካከያ ጥያቄ አንስተው እድል የተሰጣቸው አቶ ገብሩ “ኢዴኃህ ዋነኛ ተቃዋሚ የሆነው 53 መቀመጫ ይዞ ነው” በማለት አቶ ልደቱ “ትልቅነት የሚለካው በእድሜ ይሁን በቁመት አላውቅም” በማለት ለተናገሩት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የመንግሥት ተጠሪ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው በምክር ቤቱ ውስጥ የመደማመጥ የመመካከር ባህል ቢኖር የተሻለ መሆኑን ምክራቸውን ለግሰው በጀመሩት አስተያየት በአገሪቱ ነፃና ዴሞከራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ ለማድረግ የሥነ ምግባሩ ደንብ ህግ ሆኖ መጽደቅ ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አቶ ኃይለማርያም “በድርድር የማያምን አካል በዚምባቡዌና በኬንያ እንደታየው በብጥብጥና ስልጣን ለመያዝ የሚፈልግ ነው” ሲሉ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና የሥነስርዓት ጥያቄ ስለአነሱ እድሉ ተሰጣቸው፡፡ እርሳቸውም በኬንያና በዚምባቡዌ እንደታየው በብጥብጥ ስልጣን ለመያዝ እንደሚፈልግ የገለጸ አካል እንደሌለ ገልጸው “ቅኔው ቢቀር ጥሩ ነው” በማለት አቶ ኃይለማርያም ንግግራቸውን እንዲያስተካክሉ ጠየቁ፡፡ ይሁን እንጂ አፈ ጉባኤው “የተከበሩ አቶ ኃይለማርያም የማንንም ስም ጠርተው አልከሰሱም እርስዎም ምንም አልተናገሩም” በማለት ስለተናገሩ አቶ ኃይለማርያም ንግግራቸውን ቀጠሉ፡፡ አቶ ኃይለማርያም “ከሸራተኑ ግብዣ መሞጋገስና ከቤተ መንግሥት ግብዣ መራቅ በእርግጥ ሊያስቆጭ ይችላል” ሲሉ አሁንም ሌላ የሥነስርዓት ጥያቄ ተነሳ አሁን ግን ለሥነስርዓት ጠያቂው እድል አልተሰጠም፡፡ አቶ ኃይለማርያም መልስ እየሰጡ ያሉት ቀደም ሲል ከተቃዋሚዎች ለተነሱ ጥያቄዎች መሆኑን የጠቀሱት አፈጉባኤው የሥነስርዓቱን ጥያቄ እንደማይቀበሉ ገለጹ፡፡
“መድረክ እየረገጡ መውጣትና መድረክ መበጥበጥ ልምድ እየሆነ መጥቷል” ያሉት አቶ ኃይለማርያም ይህ አካሄድ አግባብ አለመሆኑንና በስነምግባሩ ደንብ ገዥው ፓርቲ ለምርጫው የተደላደለ ሜዳ እንዲፈጥር የሚያስገድደው በመሆኑ ተቃዋሚዎችም በሰላማዊ መንገድ ለመወዳደር የተስማሙ በመሆናቸው ህግ ሆኖ መጽደቁ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
ሥነምግባር ደንቡን ደግፈው ያቀረቡና የተቃወሙ የፓርላማ አባላት በተሰጣቸው 1፡30 የመከራከሪያ ሰዓት ሀሳባቸውን አቅርበው ከተከራከሩ በኋላ በተሰጠው ድምጽ አሰጣጥ ደንቡ በአብላጫ ድምጽ ለህግና አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ እንዲመራ ተወስኗል፡፡ በእለቱ የታየው የሥነምግባር ጥያቄ ድራማም በዚያው ተጠናቅቋል፡፡
|
|
Write a Comment
Related posts:
- ጥያቄ ለኃይሉ ሻውል እና ለመኢአድ አባላቶች
- የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይስ የመለስ ዜናዊ ምክር ቤት
- ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲን እነ ማን ናቸው ያፈረሱት?
- የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፓለቲካ – ከዶክተር ነጋሶ ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ