የከሳሽና ፈራጅን ካባ ደርቦ: ህዳሴን ማብሰር!
ከዳዊት ከበደ
ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባለፈው አርብ ለአገር ውስጥ ሚዲያዎች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የአዲስ ነገር ጋዜጠኞች ከአገር መውጣትን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ጋዜጠኞቹ ስለ ዲሞክራሲ ሲሰብኩ እንዳልነበር ሂስ ሲቀርብባቸው ግን ሽሽትን እንደመረጡ ነበር የገለፁት፡፡ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በበተከታይ ‹ከሽብርተኞች ጋር የወገኑ፣ ሰይጣናዊ ተልእኮ ያነገቡ፣ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የሚያጋጩ፣ ደም በማፋሰስ መዋዕለ ንዋይ ለማካበት የቋመጡ› እየተባለ ለኢትዮጵያዊ ጨዋነት ባፈነገጠና ቅጥ ባጣ መልኩ ሲቀርብ የነበረውን ዘመቻ በጠ/ሚኒስትሩ ቀለል ባለ አገላለጽ ‹ሂስ› ብቻ ነው ተብሎ ሲገለጽ ማመዛዘን ለሚችል ለማንም ሰብአዊ ፍጡር አሳማኝ አይመስለኝም፡፡
‹ሂስ› ማለት የህግ ተጠያቂነትን ግምት ውስጥ ያስገባ ገንቢ ትችት ነው፡፡ የሂስ አላማ ማስተማር እንጂ ስለ ሽብርና ስለ ደም መፋሰስ እያወሩ መወንጀል አይደለም፡፡ ዘመቻው ከሂስ ያለፈ መልዕክት እንዳለው ግለጽ ነው፡፡ አቶ መለስ ምናልባት አዲስ ዘመንን እንደማያነቡ ስለነገሩን፤ የጽሁፉን ይዘት ላያውቁት ይችሉ ይሆናል፡፡ ከጋዜጣው አላማና ኤዲቶሪያል ፖሊሲ አንጻር ግን ፕሬሱ በምን ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት ለጋዜጣው ‹አቅጣጫ ሲወርድ› የወረደውን አቅጣጫ ከግብ ለማድረግ የተመደበው ‹ልማታዊ› ጸሐፊ ታማኝነቱን ለማሳየት ጠቃሚ ነው ያለውን አሸማቃቂ ሀረግ ሲጠቀም ቢያንስ ጸሐፊው በህግ ባይጠየቅ እንኳን ከኢትዮጵያዊነት የሞራል ሚዛን አንጻር ትንሽ እንዲያገናዝብ መካሪ አለቃ ያስፈልገው ነበር፡፡ ይህ ግን በኢህአዴግ ባህሪይ አይታሰብምና ሊሆን አልቻለም፡፡ ስለዚህ ‹መንግስትን አያስወቅስም› ብሎ መከራከር ስነ አመክንዮአዊ አይደለም፡፡
የዛሬው ጽሁፌ በአቶ መለስ ምላሽ ላይ አያተኩርም፡፡ ስለ አዲስ ዘመን ዘመቻም አይደለም፡፡ ይለቁንስ ‹ልማታዊ ጋዜጠኞች› ስለመሆናቸው አውርተው በማይጠግቡ ትጉኃን ተከሽኖ ‹አላማችን ሕዳሴን ማብሰር ነው› ብለው በቆረቡ ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ሰፊ ሽፋን ተሰጥቶት በተለይ ከተዘጉ አስር አመትና ከዚያ በላይ የሆናቸው ጋዜጦች ያወጧቸውን ዘገባዎች እየመዘዙ ማደንቆር ልማታዊ ግቡ ምን እንደሆነ ምላሽ የሌለው ጥያቄ ለመጠየቅ ነው፡፡ በተለያየ ወቅት የነበሩ አገዛዞች ካሳደሩብን ተጽእኖ አንጻር ዜጐች አንድ ለየት ያለ ዝግጅት በመንግስት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ተደጋግሞ ሲስተጋባ ሲመለከቱ ‹ደግሞ መንግስት ምን ሊያደርግ አስቦ ነው› የሚል ስጋት አዘል ጥያቄ ይጠይቃሉ፡፡ በቴሌቪዥን መስኮት መሰል ፕሮግራሞች ከቀረቡ በኋላ በቀጣይ ጊዜያት ሲወሰዱ የነበሩ እርምጃዎች ምን እንደሆኑ በስፋት ይታወቃሉና፡፡ እኔም የጥያቄዎቹን መንፈስ የምጋራባቸው ምክንያቶች አሉኝ፡፡
አዎ! በፕሮግራሙ ላይ የቀረቡ ፕሬሶች (በተለይ አንዳንዶቹ ህትመታቸው ከተቋረጠ ደርግ በስልጣን ላይ የቆየበትን ያህል ዕድሜን አስቆጥረዋል) ከብዙ ዓመታት በኋላ አሁን ላለው ነባራዊ ሁኔታ አስረጂ ሆነው ሊቀርቡ የቻሉበት ምክንያት ግራ ያጋባል፡፡ ‹በዚህ ደረጃ ‹ነፃነት› የነበራቸው ፕሬሶች ነበሩ› ለማለት ተፈልጎ ከሆነም ያ ነፃነት ዛሬ እስከሌለ ድረስ ለፖለቲካዊ ፕሮፖጋንዳ አይጠቅምም፡፡ ‹ጥፋት ተፈጽሞአል› እየተባለ ከሆነም በወቅቱ በእስርና በወከባ አገር ጥለው እንዲሰደዱ ካደረግናቸው በኋላ (ኮብልለው እንደወጡ በዚሁ ፕሮግራም እማኝነት እየሰጠን) ያኔ መንግስት አልባ የነበርን ይመስል ዛሬ የሚታተሙ ፕሬሶች ለመወንጀል የሰነድ ‹ማስረጃ› አድረገን ስናቀርባቸው አስቂኝ ነው፡፡
የእነዚህ ጋዜጣ ባለቤቶች አንዳንዶቹ ለህልውናቸው ሰግተው ሸሽተው የወጡ፣ ሌሎቹ የአሳታሚነት መብታቸው ተገፎ መስራት እንደማይችሉ አስተዳደራዊና ህጋዊ እገዳ ተደርጎባቸው ለበርካታ አመታት (ስራውን እርግፍ አድርገው ትተው) በሌላ የስራ መስክ ላይ የተሰማሩ፤ ቀሪዎቹ ደግሞ በአቋራጭ ንሰሀ ገብተው አምነው ተጠምቀዋልና ‹ተንጋደው በበቀሉ› ፕሬሶች ውሰጥ ያኔ የፊታውራሪነት ሚና እንዳልነበራቸው፤ በዚህ ፕሮግራም ላይ ቀርበው ያለምንም ይሉኝታ የራሳቸውን የስራ ውጤት ሲያወግዙ ከመታየታቸው ባሻገር ከሊቀመንበሩ በስተቀር አባል እንኳን በሌለው ማህበር ውስጥ መሽገው የአልቃሽ ሙሾ አውራጅ ሰበካ ሲያሰሙ – ያስተዛዝባል፡፡
በመሠረቱ ደርግ አምባገነንና ጨቋኝ እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ ስርዓቱ አምባገነን ነበርና በሆነ አጋጣሚ በስርዓቱ ውስጥ ያገለገሉ ዜጎች ህገ-መንግስታዊ መብት እንደሌላቸው አድርጎ መደምደም ተገቢ አይደለም፡፡ በስርዓቱ ውስጥ ካገለገሉ ቱባ ባለስልጣናት መካከል ዛሬም በኢህአዴግ መንግስት ውስጥ በወሳኝ የስልጣን እርከን ላይ የሚገኙ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ አንድ ዜጋ ቀደም ብሎ በነበረው ስርዓት ውስጥ የነበረውን ስልጣን መከታ በማድረግ በህግ የሚያስጠይቅ ወንጀል ፈጽሞ ከሆነ፤ ህግ ፊት የማቅረብ ሞራል ባለው መንግስት በእውነተኛ የፍትህ አካል ሊዳኝ ግድ ነው፡፡ ነገር ግን አንድን ዜጋ በደፈናው ‹በቀድሞው ስርዓት ውስጥ ምንትስ የሚባል ወታደራዊ ማዕረግ ስለነበረህ መስራት አትችልም› የሚል አስተሳሰብ ማራመድ ትልቅ የመብት ጥሰት ነው፡፡ ህግ አውጪ፣ ህግ ተርጓሚና አስፈጻሚ አካላት ‹በገለልተኝነት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው› ብለን በምንደሰኩርባት አገር ‹ነጻ ነው› ባልነው ፍርድ ቤት አማካኝነት በ‹ነጻ› ያሰናበታቸውን ዜጎች አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ አቃቤ ህግና ዳኛ ሆኖ የአንድን ንጹህ ዜጋ ስም እየጠቀሰ ከአውቶብስ ቃጠሎ ጋር አቀነባብሮ ፈራጅ ሲሆን መመልከት እንኳን ለመንግስት፤ ስለ ህግ የበላይነት ግንዛቤ ያለውን ዜጋ አንገት የሚያስደፋ ነው፡፡
ህግ አለ በሚባልበት አገር አንድ ዜጋ ያለፍላጎቱ ‹ማንነቱና ኋላ ታሪኩ ምን ይመስላል?› እየተባለ ሚሉዮኖች በሚከታተሉት የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲብጠለጠል ተጠያቂ የሚሆን አካል ሊኖር ይገባል፡፡ እዚህ ጋር አቶ ሽመልስ ከማል በዚሁ ፕሮግራም ላይ ቀርበው ሪፖርተር ጋዜጣ በሚድሮክ ላይ የከፈተው ዘመቻ አግባብ እንዳልሆነ አስተያየት ሲሰጡ የተጠቀሙበትን አባባል ልዋስና፡- ‹አንደኛ ከሞራል አንጻር ነውር ነው፤ ሁለተኛ (ተጠያቂ የሚሆን ካለ) በህግ የሚያስጠይቅ ነው፤ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ከሚዲያው ስነ ምግባር እጅግ ያፈነገጠ ነው፡፡›
የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ጋዜጣ አሳታሚዎቹ ከደርግ ጋር የጠበቀ ቁርኝት እንደነበራቸው፤ በአስር አለቃነት እና በመቶ አለቃነት ደረጃ ላይ ማገልገላቸው እንደ ጸያፍ የኋላ ታሪክ አድርጎ አቅርቦልናል፡፡ ነገር ግን ይኸው ፕሮግራም በአስረጅነት ያቀረባቸው አንዳንዶቹ ‹ሙሾ አውራጆች› በደርግ ውስጥ የነበራቸው ወታደራዊ ማዕረግ ከተወንጃዮቹ አሳታሚዎች በብዙ እጥፍ ከፍ ያለ ከመሆኑ ባሻገር ለከፍተኛ የፖለቲካ ስልጠና ኩባ እና ሩሲያ ድረስ የተላኩ ታማኞች እንደነበሩና ለስርዓቱ የነበራቸው ታማኝነት (የዛሬን አያድርገውና) ለመግለጽም በፕሬሶቻቸው የፊት ገጽ ላይ ‹መንግስቱ ኬንያ የሚገኝ ጦራቸውን ጎበኙ› በማለት ያለ ይሉኝታ የዘገቡ የደርግ ታማኝ ቃል አቀባዮች እንደነበሩ የሚጠራጠር ዜጋ ካለ ብዙ ምርምር ሳያስፈልገው ወመዘክር ቤተመፃህፍት ጎራ ብሎ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ የነበሩ ስራዎቻቸውን መመልከት በቂ ይመስለኛል፡፡
ከፍ ብዬ እንደገለጽኩት ዜጎች በአንድ ስርዓት ውስጥ ተሳትፎ ማድረጋቸው ብቻውን ሊያስወነጅላቸው አይገባም፡፡ በተለይ በውዴታና በግዴታ ዜጎችን እያፈሰ ውትድርና ውስጥ ይማግድ በነበረው የደርግ ስረዓት ውስጥ ‹አገልጋይ ነበራችሁ ብሎ ማብጠልጠል› ያልበሰለ ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡
እንኳንና (በአስር አለቃነት ደረጃ ላይ የነበሩ) አሳታሚዎች ይቅርና ኩባና ሩስያ ድረስ ተልከው የሰለጠኑ ‹ሙሾ አውራጆች›ም ቢሆኑ ‹እኔ ከደሙ ንጹህ ነኝ› ብለው በሌላው ላይ ስለዘመቱ እንተቻቸዋለን እንጂ ደርግን ስላገለገሉ ሊኮነኑ አይገባም፡፡
ከሁሉ እጅግ ያስገረመኝ ‹ፕሮፌሰር ተብዬው› የተናገሩት ነገር ነው፡፡ በጋዜጠኝነት ሙያ እስከ ፕሮፌሰርንት ማዕረግ የደረሱ ሰው ‹ጋዜጠኛ ለሚሰራው ለእያንዳንዱ ዘገባ የመረጃ ምንጩን ለአንባቢ ማሳወቅ አለበት› የሚል አዲስ ግኝት ይዘው ብቅ ሲሉ ይህ አባባል አንቱ የተባሉ የምዕራባዊያን ሚዲያዎችንም ጭምር ሊያስገርም ስለሚችል አዲስ ግኝት ብየዋለሁ፡፡ በአውሮፓና በአሜሪካ ፕሬስ እጅግ የተከበረ ተቋም ነው፡፡ ሰፊ ተቀባይነት ባገኙ ሚዲያዎች ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያዎችም ከተለያዬ አቅጣጫ መረጃ ለማሰባሰብ አፍሪካ ውስጥ ያለው አይነት ፈተና አይገጥማቸውም፡፡ ሴናተሮች፣ ህግ አውጪዎች፣ የመንግስታት አማካሪዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ የውጭ ጉዳይ ኃላፊዎችና ፖሊሲ አውጪዎች ጋር የቀረበ ወዳጅነትን መስርተው ያሻቸውን መረጃ ያገኛሉ፡፡ እነኚህ ኃላፊዎች ታዲያ መረጃውን ሲሰጡ ሁሌም በኦፊሴላዊ መንገድ አይደለም፡፡ ለምሳሌ የፕሬዚዳንት ኦባማ አማካሪ ዜጎች ሊያውቁት የሚባና በሚዲያ እንዲሰራጭ የሚፈለግ መረጃ ሲኖር በተለያዬ አጋጣሚ ለሚቀርባቸው የጋዜጣ ኤዲተር ሻይ ቡና እያሉም ሆነ ቢራ ጨብጠው ሹክ ሊሉት ይችላል፡፡ ሚዲያውም በስምምነታቸው መሰረት anonymous, unidentified ብሎ መረጃውን ለአንባቢ ያቀርባሉ፡፡ የመረጃ ምንጭ በተለያየ ምክንያት በምስጢር ሊያዝ ይችላል፡፡ ዘጋቢው የመረጃ ምንጩ ማንነት ለሚዲያው ኤዲቶሪያል ኮሚቴ ማሳወቅ ቢጠበቅበትም ለተደራሹ የማይገልጽበት ሙያዊ ከለላዎች አንደሉት ግን ይታወቃል፡፡ የመረጃ ምንጭን ያለማሳወቅ መብት አገራችንን ጨምሮ በበርካታ አገራት ህገ-መንግስት ከለላ የተሰጠው ነው፡፡ ነገር ግን ይህ የ‹ልማታዊው ፕሮፌሰር› አገላለጽ ምንም አይነት ሙያዊ ድጋፍ የሌለው ብቻ ሳይሆን ህገ መንግስታዊ ድጋፍም የሌለው ነው፡፡ ምናልባት ድርጊቱን የተአማኒነት ካባ ለማላበስ በዘርፉ የገዘፈ ማዕረጋቸውን ተተግኖ የተፈለገውን መልዕክት በማናገር የሙያውን ህግ መጣስና የተዛባ መረጃ ማስተላለፍ ይሆናል፡፡
ቀደም ባሉ ጊዜያት በዩኒቨርስቲ አካባቢ የነበሩ ምሁራን በምርምርና በስነ አመክንዮ የተመሰረተ ክርክር ያቀርቡ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን ከአሁኖቹ የህዳሴው ምሁራን የሚሰማው ትንታኔ ግን ከስነ-አመክንዮ ይልቅ በዳበሳ ላይ የተመሰረተ፤ ከምሁራዊ ክርክር ይልቅ የቡና ላይ ወግ የመሰለበት ሁኔታ ተንጸባርቋል፡፡ ለዚህ ማስረጃ የሚሆነው ‹አሁን ያሉ የፖለቲካ ጋዜጦች እያንዳንዳቸው ከጀርባቸው ሃይ! የሚላቸው አካል አለ› የሚለው ለቡና ወግ አይነቱ ድምዳሜ አይነተኛ ማስረጃ ነው፡፡ ለመሆኑ ‹ሃይ› ባዩ ማነው? በምን የህግ አግባብ? ይህ ፍጹም የተሳሳተ ድምዳሜ ብቻ ሳይሆን ፈውስ የሌለው ድንቁርናም ነው፡፡ በእኔ እምነት ‹ሃይ› የመባል አግባብ ቢኖር እንኳን ሃይ ባዩ የአገሪቱ የህግ ስርዓት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለአንዳንድ ሆድ አምላኪ ምሁራን የጨበጣ ምሁራን ማስታወስ ተገቢ ብልህነት ይመስለኛል፡፡
(ዳዊት ከበደ የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር ነው)
|
|
Write a Comment
No related posts.