Ethiopian Review

HOME | CONTACT | FORUM | ALBUM

ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲን እነ ማን ናቸው ያፈረሱት?

EthiopianReview.com | December 22nd, 2009 at 4:58 pm | | Print This Post

በያዕቆብ ኃይለማርያም)

ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንደተናገርኩት ወጣቶች በፓርቲዎች አመራር ውስጥ ገብተው አዛውንቶቹን ይተኩ በማለት ሳራምደውና ስገፋው የነበረው ሃሳብ በራሴ በኩል ተግባራዊ ለማድረግ፣

ከአንድነት ለዴሞክራሲና የፍትሕ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርነት መሰናበቴን ያሳወቅሁበት በሪፖርተር ጋዜጣ ኅዳር 6 ቀን 2002 ዓ.ም. ላይ የወጣው ቃለ ምልልስ በአገርም በውጭም ብዙ ውይይት ቀስቅሷል፡፡ ለውይይት ከበቁት ርዕሶች መካከል በአገር ውስጥም ሆነ ውጪ አገር በሚኖሩ አስተያየት ሰጪዎች ያስነቀፈኝ በተለይ የተከበሩ አቶ ልደቱ አያሌውን አስመልክቶ የሰጠሁት አስተያየት ነው፡፡ ነቀፌታው ተገቢና በአክብሮትም የምቀበለው ነው፡፡ ቃለ ምልልሱ ውይይት መፍጠሩ የሚደገፍ ሲሆን፣ በውይይቱ ላይ የተነሳው ወጣቶች የፓርቲዎችን አመራር መረከብ አለባቸው የሚለው ወቅታዊ ሃሳብ መሆኑን ይጠቁማልና ውይይቱ ቢቀጥል ጠቃሚ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

በመጀመሪያ ግልጽ ላደርገው የምፈልገው ከአቶ ልደቱ ጋር ግላዊም ሆነ ፖለቲካዊ ግንኙነት የሌለኝና ፓርቲአቸውንም ለመቀላቀል ፍላጎቱ እንደሌለኝ፣ አሁንም የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ አባል መሆኔን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ የሆነውንና እውነቱን ለሕዝብ ከማሳወቅ ውጭ ሌላ ፍላጎትም የለኝም፡፡

አቶ ልደቱን አስመልክቶ በሰጠሁት አስተያት ከቅንጅት መቋቋም በፊት ማለት ከ1997 ዓ.ም. ቀደም ብሎ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኢዴፓ) መሪ ሆነው የፓርቲአቸውን ፕሮግራም ለማስፈፀም ባደረጉት እንቅስቃሴ ምክንያት በደረሱባቸው የተለያዩ እንግልቶችና እስርም ጭምር ከግንዛቤ በማግባት ነበር፣ ብዙ መስዋዕትነት የከፈሉ ሰው ናቸው ያልኩት፡፡ በጊዜውም ቢሆን ከብዙ ፖለቲከኞች በበለጠ የህዝብን ቀልብ የሳቡ የፓርቲ መሪ እንደነበሩ አሌ ሊባል አይቻልም፡፡ ሚያዚያ 30 ቀን 1997 ዓ.ም. በተደረገው ታሪካዊ ሕዝባዊ ሰልፍ ሰዎች አቶ ልደቱን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ደርበውላቸው “ማንዴላ፣ ማንዴላ” እያሉ ሲያወድሳቸው እንደነበር የትናንት እውነታ ነው፡፡

በቃለ ምልልሱ ወቅት አቶ ልደቱ ቀደም ሲል የሰሯቸውን በጎ፣በጎ ሥራዎቻቸውን ብቻ በማውሳት ጥፋቶቹን ወደ ጎን በመተው በቅንጅት መፍረስ የነበራቸውን ሚና ለመተው ፈልጌ ነበር፡፡ ሆኖም “አጥብቆ ጠያቂ የእናቱን ሞት ይረዳል” እንዲሉ፣ አቶ ልደቱ በተደጋጋሚ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ቅንጅትን ለማፍረስ የተጫወቱት ሚና እንዳልነበረ እንዲያውም በጮሌ አነጋገር “ያዕቆብ ፓርቲውን ያፈረስነው እኛ ነን ብሎ መስክሮልኛል” በማለት ዓይናችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁ ስላሉ፣ ሁኔታውን እንዳብራራና አሉባልታ ሳይሆን እውነቱን ለሕዝብ እንዳቀርብ አቶ ልደቱ እራሳቸው አስገድደውኛል፡፡

በቃለ ምልልሱ ወቅት “በቅንጅት መፈራረስ እኛ አመራሮቹ ይብዛም ይነስም ሁላችንም አስተዋጽኦ አድርገናል” ስል፣ ኢሕአዴግና አቶ ልደቱ (አንድም ሁለትም ናቸው ይባላል) ሌሎችም ከፋፋይ ኃይሎች የሰነዘሩብንን የጥቃት ዱላ በገንዘቡና በጉልበቱ ብቻ ሳይሆን፣ በውድ ሕይወቱ ጭምር የደገፈንን ሕዝባችንን ከጎናችን ቆሞ እየታገለልን እያለ ይህንን ጥቃት ተቋቁመንና የማፍረሱን እንቅስቃሴ አክሽፈን፣ የፓርቲውን ሕልውና አስጠብቀን ፓርቲው እንዲቀጥል ማድረግ ባለመቻላችን በተሰማኝ ጥልቅ ሐዘንና ቁጭት ምክንያት ነበር፡፡ በቅንጅት አፍራሽነት ሁሉም የየድርሻውን ያንሳ ቢባል ከገዢው ፓርቲ ወይም ከአቶ ልደቱ የአንበሳውን ድርሻ የሚያነሳው የትኛው ይሁን ለማለት ያዳግታል፡፡

የገዢው ፓርቲ የቅንጅት አመራሮችና ደጋፊዎቻቸውን ማሰር በአንድ በኩል፤ የአቶ ልደቱ አራቱም ፓርቲዎች የተስማሙበት የውህደት ሰነድ ላይ የፓርቲአቸውን ማህተም አላሳርፍም በማለታቸው የምርጫ ቦርድ ቅንጅትን አልመዘግብ ብሎ ስሙን ለሌላ መስጠቱ በሌላ በኩል፣ ሁለቱ ሚዛን ውስጥ ቢገቡ ሚዛኑን የሚደፋው የቱ እንደሚሆን ሕዝብ ይፍረድ፡፡ የቅንጅት አመራሮች ታስረውም ቅንጅት በፓርቲነት ቢቀጥል ኖሮ በታሰሩት መሪዎች ምክት ሌሎች ተተክተው የፓርቲውን ዓላማ ማስፈጸም በቻሉ ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያንም በረጅም ታሪካቸው አጣጥመው የማያውቁትን ዴሞክራሲ፣ ፍትሕ፣ ነፃነት፣ ወንድማማችነትና እህትማማችነት በራፋቸው ደርሶ ባልተመለሰ ነበር፡፡

አራቱ ፓርቲዎች ማለትም የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲ ፓርቲ፣ ቀስተ ደመናና የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ሊግ ስለ ውህደቱ መነጋገር ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ሕዝቡ ..ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ.. እያለ ለውህደቱ ከፍተኛ ግፊት በሚያደርግበት ወቅት እንኳን፣ አቶ ልደቱ በሂደቱ ላይ ችግር ስለፈጠሩ ከሌሎች መሪዎች ጋር ሰልፋቸውን እንዲያሳምሩ በፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም በተደጋጋሚ ቢመከሩም ፈቃደኛ ሳይሆኑ እስከ መጨረሻው ቀጠሉበት፡፡ በሌላም ወቅት በዶክተር አለማየሁ አረዳ በሚመራ ኮሚቴ አማካይነት መግባባት እንዲፈጠር ቢሞከርም አሁንም አልተሳካም፡፡ በወቅቱ የውህደቱ ኮሚቴ ሊቀ መንበር ስለነበርኩ ለውህደቱ ስኬት የእያንዳንዱ ፓርቲ መሪ ያደረገው አስተዋጽኦ ጠንቅቄ እንደማወቄ መጠን፣ አንዳንድ የፓርቲ መሪዎች ለውህደቱ ስኬትና የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎት ለማክበር ሲሉ የፓርቲዎቻቸውን አንዳንድ ጥቅሞች መስዋዕት ያደርጉ እንደነበር ሳልጠቅስ አላልፍም፡፡ አቶ ልደቱ ግን ከእነዚህ መሪዎች ተርታ እንዳልነበሩ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡

በቃለ ምልልሱ ውስጥ ሌላው አወያይ የሆነው የወጣቶች በፓርቲ አመራርነት የመውጣት ጉዳይ ነው፡፡ አንዳንድ ሃያሲዎች የፓርቲዎች አመራር በወጣቶችም በአዛውንቶችም መዋቀር አለበት ብለዋል፡፡ ዛሬ የአገራችንም ይሁን የዓለም ሁኔታ በ60ዎቹና በ70ዎቹ ከነበረው በእጅጉ ተለውጧል፡፡ ዛሬ የፖለቲካውም ሆነ የኢኮኖሚው ሥርዓት ቀድሞ ከነበረው ጋር በፍፁም የተለየና የማይጣጣም ነው፡፡ አገራችንም የምትታወቀው በአብዛኛው የወጣት አገር እንደሆነች ነው፡፡ ስለሆነም ቀደም ሲል የነበረው የኢኮኖሚም ሆነ የፖለቲካ ሥርዓት የማይጫናቸው ወጣቶች የፓርቲዎቹን አመራር ይረከቡ ነው ያልኩት፡፡ ከቃሊቲ “ቆይታችን” በኋላ የቅንጅት አመራሮች በአውሮፓ የሚገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን እኛንና ሌሎችንም ከእስር ለማስፈታት ላደረጉት ትግልና ለከፈሉት መስዋዕትነት ለማመስገንና ለዴሞክራሲ የሚደረገውን ትግል በበለጠ እንዲያጠናክሩ ለማበረታታት ዘጠኝ አገሮችን በጎበኘንበት ወቅት፣ ይቀበሉን የነበሩ የአውሮፓ የተለያዩ አገሮች የፓርቲ መሪዎች በሰላሳዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ነበሩ፡፡

ሁኔታው እንዴት እንደዚህ ሊሆን እንደቻለ ስንጠይቃቸው ፓርቲ የወደፊት መሪዎች የሚሰለጥኑበት ትምህርት ቤት ስለሆነ መሆኑን ያስረዱን ነበር፡፡ ወጣቶች አመራሩን መረከብ አለባቸው ስል በፓርቲ አመራር፣ በሌላም ዕውቀት የዳበሩ አዛውንቶች እጃቸውን አጣጥፈው ቤታቸው ቁጭ ብለው እሳት ይሙቁ አለማለቴ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ፡፡ አዛውንቱ ከዕድሜ መሰንበት፣ ከሥራና ከሕይወት ተሞክሮ ብዙ ያካበቱት ዕውቀት እንደሚኖራቸው አያጠራጥርም፡፡ ይህን ዕውቀታቸውን ለወጣት መሪዎች ምክር በመለገስ፣ ፓርቲዎቹ የሚከተሏቸውን የዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚ፣ የፖሊሲ ወዘተ ዶኩሜንቶችን በማዘጋጀት፣ በእነዚህና በመሳሰሉት ላይ ለፓርቲው አባላትና አመራሩ ትምህርት በመስጠት ጉልህ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡ የፓርቲ አመራር በአሁኑ ጊዜ በወጣት እጅ መግባት ይገባዋል ስል የደረደርኳቸውን ምክንያቶች በዲሴምበር 13 ቀን 2009 ዓ.ም. በወጣው “ካፒታል” ጋዜጣ የተብራራ ስለሆነ መመልከት ይቻላል፡፡

አንፀባራቂ የትግል ታሪክ ቀርጸው እንዳለፉት እንደ ቀድሞዎቹ ወጣት ኢትዮጵያውያን የዛሬዎቹም ለአመራር ብቁ ለመሆናቸው የሁሉንም ጠባይ በመቻልና አሰባስባ የመምራት ልዩ ችሎታ ያላት፣ የተሰጣት ይቅርታ በሕገ ወጥ መንገድ ተሰርዞ ወህኒ ቤት ከምትማቅቀዋ ከወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የተሻለ ዋቢ አይገኝም፡፡ ሌሎችም በየፓርቲዎቹ ውስጥ ስለመገኘታቸው አልጠራጠርም፡፡ እንደ ቀድሞዎቹ የ60ዎቹና የ70ዎቹ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው የግል ጥቅም ሳይሹ በሙሉ መስዋዕትነት ኢትዮጵያ የድሃ ድሃ አገር ነች፣ ሕዝቡ ዴሞክራሲ፣ ፍትሕና እኩልነት አጣጥሞ አያውቅም የሚለውን መሳለቂያ ለመለወጥ ቆርጠው በመነሳት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተደርጎ የየፓርቲዎቻቸውን መሪነት መረከብ አለባቸው፡፡

አገር ተረክበው ሊመሩ የሚችሉትም ሲሆን በአንድ በተጠናከረ ፓርቲ ተሰባስበው፣ ካልሆነም በየፓርቲዎቻቸው ውስጥ ተደራጅተው አገርን የመምራት ትምህርት ከአሁኑ መቅሰም ይኖርባቸዋል፡፡ ይህንንም ዕድል አዛውንቶቹ ለወጣቱ የመስጠት ግዴታ አለባቸው፡፡ አልፎ አልፎ ስህተት ቢሰሩም ከስህተታቸው የመማር ዕድልም ሊነፈጋቸው አይገባም፡፡ የአመራር ችሎታም ይሁን እውቀት ከእናቱ ማህጸን ይዞ የወጣ የለምና ይህ የፓርቲ አመራርን በወጣት የመተካቱ ሃሳብ በዘላቂነት እንዲተገበር የተሰነዘረ ሲሆን፣ በ2002 ዓ.ም. ምርጫ ኢሕአዴግን የማሸነፍ ጉዳይ የወቅቱ አንገብታቢና ዋናው አጀንዳ ነው፡፡

ማስታወሻ፡- ይህ ጽሑፍ ቅንጅትን ማነው ያፈረሰው ለሚለው ጥያቄ ሙሉ መልስ አይሰጥም፡፡ ይህ ጥያቄ ወደፊት በሚደረጉ ውይይቶች ምላሽ ያገኛል፡፡

Write a Comment

Please answer the following question:

what is 5 plus 3?



No related posts.