Ethiopian Review

HOME | CONTACT | FORUM | ALBUM

በነጄነራል ተፈራ ማሞ ላይ የተወሰነዉ የፍርድ ቤት ዉሳኔ በተመለከተ

EthiopianReview.com | January 11th, 2010 at 1:04 am | | Print This Post

ከግርማ ካሳ

«የከሸፈዉ የጨለማ ጉዞ» በሚል አርዕስት ሥር ኢሕአዴግ የሚቆጣጠረዉ ቴሌቭዥን ያሰራጨዉን ቅንብር፣ አፍቃሪ ኢሕአዴግ ድህረ ገጾች ላይ ወጥቶ አየሁት። በዚህ ቅንብር፣ የሞት ፍርድ ከተፈረደባቸዉ አምስት ግለሰቦች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ መላኩ ተፈራና የእድሜ ልክ እሥራት የተፈረደባቸዉ እነ ጄኔራል አሳምነዉ ጽጌ፣ ጄኔራል ተፈራ ማሞ ሌሎች የሰጡት «ምስክርነቶችም» ይገኙበታል። (ምስክርነቶች የሚለዉን ቃል በቅንፍ ያደረኩት በምን ሁኔታ እንደሰጡ እርግጠኛ ስላልሆንኩ ምስክርነት ነዉ ብዬ ለመናገር ስለከበደኝ ነዉ)

ይህ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ዘገባ፣ ኦሳማ ቢንላድንን እያሳየ እሥረኞቹ የአገሪቷን ሕገ መንግስት ለመናድ እንደሞከሩና የሽብር ሥራ ላይ እንደተሰማሩ ነበር ለማሳየት የሞከረዉ።

ይህ ብቻ አይደለም፣ በጣም እስክስቅ ድረስ ያስገረመኝ ነገር ቢኖር የዝግጅቱ አንባቢ ወደ ማጠቃለያዉ ላይ የተናገራቸዉ አርፍተ ነገሮች ነበር። «ምንም እንኳን እነ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ የአገሪቷን ሕገ መንግስት በኃይል ሊንዱ ቢንቀሳቀሱም ሕገ መንግስቱ ግን እንደ ዜጋ ሊያገኙት የሚገባቸዉን የዜግነት መብት አልነፈጋቸዉም። የሽብር ቡድኑ በቁጥጥር ሥር በዋለበት ወቅትም ሆነ የፍርድ ሂደቱ ሲከናወን እንደዜጋ ያልተሸራረፈ መብቶቻቸዉ ተጠብቆላቸዋል። እነርሱ የካዱትና ሊያወድሙት የፈለጉት ሕገ መንገስት የነርሱ ሕጋዊ መብታቸዉ እንዲጠበቅ የሕግ ከለላ ሆኗቸዋል» ነበር ያለዉ።

እሥረኞቹ በፖሊስ የተያዙት ሚያዚያ 18 ቀን 2001 ዓ.ም ነበር። የመጀመሪያዉ ደረጃ ፍርድ ቤት – አራዳ ችሎት ለመጀመሪያ ጊዜ ግንቦት አራት ቀን ቀረቡ። ፖሊስ የምርመራ ጊዜ ይኖረዉ ዘንድ አሥራ አራት ቀናት ጠየቀ። ፍርድ ቤቱም ፈቀደ። ሰኔ አንድ ቀን የፌደራል ከፍተኛ አቃቤ ሕግ ክስ መሰረተ። በዚያን ቀን የሪፖርተር ጋዜጣ እንደዘገበዉ «ተከሳሾቹ ተራ በተራ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት ማመልከቻ፣ ከተጠረጠሩበት ጉዳይ ጋር ግንኙነት የሌለው ንብረት እንደተወሰደባቸው፣ ሕመምተኛ እንደሆኑና በሦስትና በስድስት ወራት የማይቋረጥ ሕክምና የሚከታተሉ እንዳሉ፣ ተሳትፋችኋል የተባሉበት ጉዳይም በክስ ቻርጁ ላይ አለመኖሩንና ግልፅ እንዳልሆነላቸው፣ ከታሰሩ ጀምሮ ዘመዶቻቸውን አግኝተው እንደማያውቁና መቀየሪያ ልብስ እንኳን ማግኘት እንዳልቻሉ ለፍ/ቤቱ አስረድተዋል፡፡»

እስረኞቹ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ሚያዚያ 18 ቀን ነዉ ብለናል። ፍርድ ቤት የቀረቡት ግንቦት ሶስት ነዉ። በመሃከሉ አሥራ አምስት ቀናቶች አልፈዋል። ያን ሁሉ ቀናት እሥረኞቹ የት እንደነበሩና ምን ሲደረጉ እንደነበረ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ዘገባ ምንም ያለዉ ነገር የለም። ይህም በመጀመሪያ ደረጃ ሕገ መንግስቱን እራሱ እየናደ «ሕገ መንግስት ንደዋል» እያለ ሰዎችን በግፍና በጭካኔ የሚያስረዉ እራሱ ወያኔ/ኢሕአዴግ እንደሆነ በግልጽ የሚያሳይ ነዉ።

በሁለተኛ ደረጃ ማየት የምፈልገዉ የኑዛዜዉን ሁኔታ ነዉ። ብዙ ጊዜ ጥፋታቸዉን አምነዉ እሥረኞች የሚናዘዙት እንደሚፈቱ ወይንም የእሥር ዘመናቸዉ እንደሚቀነስ ከአቃቢ ሕግ ጋር ስምምነት ሲደርሱ ነዉ። ፈረንጆች “plea bargain” የሚሉት ማለት ነዉ።

ነገር ግን እነጄኔራል ተፈራ በዚህ አይነት ሁኔታ አይደለም የተናዘዙት። አቶ ተፈራ መላኩ የሞት ፍርድ፣ ጄነራል ተፈራና ጄነራል አስምነዉ የእድሜ ልክ እሥራት ተፈርዶባቸዋል። በመሆኑም ምንም አይነት ስምምነት ከአቃቢ ሕግ ጋር እንዳልተደረገ የሚያሳይ ነዉ። ስምምነት ቢደረግ ኖሮ ያህን ያህል አይፈረድባቸዉም ነበርና።

የቅንጅት መሪዎች እሥር ቤት ታስረዉ በነበረ ጊዜ ፈረሙ የተባለዉን የይቅርታ ሰነድ የፈረሙት፣ አቶ መለስ ዜናዊ ያላቸዉን ሥልጣን ተጠቅመው የፍርድ ሂደቱን እንደሚያቋርጡት በሽማግሌዎች በኩል ቃል በመግባታቸዉ እንደነበረ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ቃሌ በተሰኘዉ ዝነኛ ጽሁፏ መግለጿ ይታወሳል። አቶ መለስ ግን የነብርቱካን ሚደቅሳን ፊርማ ካገኙ በኋላ የገቡትን ቃል አጥፈዉና ክደዉ፣ የቅንጅት እሥረኞች የእድሜ ልክ እሥራት እንዲፈረድባቸዉ አደረጉ።

ስለዚህ በተመሳሳይ ሁኔታ ከነጄኔራል ተፈራ ጋር ስምምነት ተደረጎ ፣ ነገር ግን ኢሕአዴግ የተሰማማዉን ቃል እንደለመደዉ በመጣስ፣ ካናዘዘ በኋላ፣ የሞት ፍርድና የእድሜ ልክ እሥራት ሊበይንባቸዉ እንደሚችል ማሰቡ በአንድ በኩል ሊያስኬድ ይችላል።

ነገር ግን ከነብርቱካን ሚደቅሳ ጋር ታስረዉ የነበሩና የይቅርታዉን ሰነድ የፈረሙ ሰዎች መካከል አሁን የሞት ፍርድ የተፈረደባቸዉ አቶ መለኩ ተፈራ ይገኙበታል። አቶ መላኩ ተፈራም ሆነ ሌሎች ከኢሕአዴግ ጋር የሰሩና ኢሕአዴግን ጠንቅቀዉ የሚያወቁ እሥረኞች፣ የኢሕአዴግ መሪዎች ቃል በገለልተኛ አካል ፊት በጽሁፍ እስካልቀረበ ድረስ፣ ሊቀያየር እንደሚችል የሚያወቁ ናቸዉ። ስለሆነም እንዲሁ በየዋህነት ኢሕአዴግ የሚገባላቸዉን ቃል አምነዉና ተቀብለዉ ለኢሕአዴግ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ መሳሪያ ይሆናሉ ብዬ አላስብም።

ስለዚህ ወደ አንድ መደምደሚያ ነዉ ልንደርስ የምንችለዉ። እርሱም እሥረኞቹ ተናገሩ ተብሎ በቴሌቭዥን ለሕዝብ የቀረበዉ ኑዛዜ በድብደባና በቶርቸር የተገኘ፣ ተራ ርካሽ የአገዛዙ ፕሮፖጋንዳ እንደሆነ ነዉ። ይህም የአገሪቷን ሕግ ብቻ ሳይሆን የአለም አቀፍ ሕግንም የረገጠ ሊወገዝ የሚገባዉ ድርጊት ነዉ።

ከታሳሪዎቹ አንዱ የሆኑት ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ማሞ ከአሥራ ስምንት አመታቸዉ ጀመሮ ደርግን ሲታገሉ እንደነበረ፣ ኢትዮጵያ በባድመ ጦርነት ከኤርትራ ጋር ባደረግችዉ ጦርነት ትልቅ ሚና እንደተጫወቱ፣ ለአገራቸዉ ሲዋጉ በጥይት እንደቆሰሉና የመታቸዉም ጥይት እስከ አሁን ድረስ ሰዉነታቸዉ ዉስጥ እንዳለ፣ ለሃያ ስድስት አመታት ለአገራቸዉ ላበረከቱት አስተዋጾም የክብር ሜዳሊያ እንደተሸለሙ፣ መግለጻቸዉን የዘገበዉ ዘካፒታል ኢትዮጵያ ጋዜጣ፣ ጄነራሉ «በማረሚያ ቤት እየተደበደብኩኝ ነዉ» ማለታቸዉንም ዘግቧል። እንደ ጄነራል ተፈራ ማሞም፣ ጄነራል አሳምነዉ ጽጌም ፊታቸዉ እስኪያብጥ ድረስ የተደበደቡ ሲሆን እስረኞቹ በአጠቃላይ ከፍተኛ የሆነ ቶርቸር እንደደረሰባቸዉ ጉዳዩን በቅርበት የተከታተሉ ይናገራሉ።

ቶርቸር የሚደረግ ሰዉ ቶርቸር አድራጊዎቹ እንዲናገር የሚፈልጉትን ነዉ ብዙ ጊዜ የሚናገረዉ። ስለሆነም «እነጄኔራል ተፈራ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የተናገሩት ለኢትዮጵያ ሕዝብ መናገር የሚፈልጉትን ሳይሆን ገዢዉ ፓርቲ ጽፎ የሰጣቸዉን ነዉ» የሚለዉ አስተያየት በጣም የሚያስኬድ አስተያየት ነዉ።

«ገዢዉ ፓርቲ ለምን ይህንን አይነት ድራማ በቴለቭዥን ማሰራጨት ፈለገ ?» ብለን ብንጠይቅ ደግሞ መልሱ ቀላል ነዉ የሚሆነዉ። ከደርግ ለመማር ባለማቻሉ !

ደርግ ከስልጣን ከመወገዱ በፊት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ አድርገዋል ያላቸዉን እነ ጄኔራል አለማየሁ ደስታን የይስሙላ የጦር ፍርድ ቤት ወስዶ እንዲረሸኑ ማድረጉ ይታወሳል። በየጊዜዉ «የወያኔ/የሻቢያ እሥረኞች፣ ተገንጣዮች፣ አሸባሪዎች …» እያለም ሲያናዝዝ እንደነበረም ሁላችንም የምናወቀዉ ነዉ።

እንግዲህ የአቶ መለስ አገዛዝም ተመሳሳይ ሥራ እየሰራ እንደሆነ ነዉ እያየን ያለነዉ። ለሃያና አሥር አመታት በውስጡ ሲያገለግሉት የነበሩትን ሁሉ በጭክኔ ማሰርና መፍጀት መጀመሩ አገዛዙ ከዉስጡ እየበሰበሰ እንደሆነ የሚያሳይ ትልቅ ምልክት ነዉ።

አንድ ታኒካ «ነካ» ሲደረግ ትልቅ ጩኸት የሚያሰማዉ ውስጡ ባዶ ሲሆን ነዉ። ይህ በቴሌቭዥኝ የምናየዉ የኢሕአዴግ ጩከት፣ የአቶ መለስ ዜናዊ በየሳምንቱ እየቀረቡ የሚሰጡት ብርቱካን ሚደቅሳ አትፈታም እያሉ የሚደነፉበት ቃለ መጠይቅ፣ የሚያመልክተዉ፣ ኢሕአዴግ ባዶና ቀፎ ከመሆኑ የተነሳ ጩከት እያበዛ እንደሆነ ነው።

ይህ አይነቱ ርካሽ፣ ሕዝብን በማስፈራራት፣ በማሰር፣ በመግደል በሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚደረገዉ ሙከራ ለደርግም፣ ለነ ቻዎቼስኮም አልሰራም። አሁንም በኢትዮጵያ አይሰራም። የቀድሞ ጄነራሎችንና የኢሕአዴግ መሪ የነበሩትን በማሰርና በመግደል ሌሎች አሁን ያሉ የጦሩ መኮንኖችን እንዲሁም ልቦና ያላቸዉን የኢሕአዴግ አመራር አባላት እንዲፈሩና እንዲንቀጠቀጡ ማድረግ ብዙም ርቀት አያስኬድም።

እንስሶችን በጅራፍ እየገረፉ መግዛት ይቻላል። የሰዉን ልጅ ግን በሰላምና በፍቅር ነዉ እንጂ ማሸነፍ የሚቻለዉ በጉልበት ማሸነፍ አይቻለም። የአንድነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ አቶ ስዬ አብርሃ እንዳሉት ለአገራችን መፍትሄዉ ዜጎችን ማሰርና መግደል ሳይሆን በምህረት፣ በእርቅና በይቅርታ ብሄራዊ መግባባትና ወንድማማችነት እንዲኖር ማስፈን ብቻ ነዉ።

በመሆኑም እነአቶ መለስ በአስቸኳይ በነጄኔራል ተፈራ ላይ የተወሰደዉ እርምጃ ሽረዉ፣ እሥረኞቹ በርግጥ የተከሰሱበት ክስ መሰረት ካለዉ፣ ነጻ፣ ገለልተኛና ለሕዝብ ግልጽ በሆነ ችሎት ጉዳያቸዉ እንደገና እንዲታይ እጠይቃለሁ።

(muziky68@yahoo.com)

Write a Comment

Please answer the following question:

what is 9 plus 4?



No related posts.