አቶ መለስና ወ/ት ብርቱካን ሲነጻጸሩ
ከግርማ ካሳ
(pdf)
ሁለቱም በኢትዮጵያ እየተፋፈመ በመጣዉ የፖለቲካ ሂደት ዉስጥ ትልቅ ስፋራ አላቸዉ። ሁለቱም አባል የሆኑበት ድርጅት ሊቀመንበር ናቸው። ሁለቱም በደጋፊዎቻቸዉ ይደነቃሉ። ሁለቱም የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ የነበሩ ጊዜ ጎበዝ ተማሪዎች ነበሩ። ሁለቱም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሆነዋል። ሁለቱም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን ያጠናቀቁት በአዲስ አበባ ነው። ሁለቱም ወላጆች እንደመሆናቸው የልጅን ፍቅር ያውቃሉ። ሁለቱም ኢትዮጵያዉያን ናቸው።
የመጀመሪው አቶ መለስ ዜናዊ ይባላሉ። የአምሳ አራት አመት አዛዉንት ናቸው። እናታቸው የአዲቋላ (ኤርትራ ተወላጅ) ሲሆኑ አባታቸው ደግሞ የአድዋ ትግራይ ሰው ነበሩ። ሌላኛዋ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ናት። አባቷ የወለጋ ሰው ሲሆኑ እናትዋ ደግሞ የሸዋ ሰው ናቸው።
በነዚህ ሁለት የፖለቲካ ሰዎች ዉስጥ ትግራይ፣ ኤርትራ፣ ወለጋንና ሸዋን እናያለን። (ከቀድሞ የኢትዮጵያ አሥራ አራቱ ክፍለ ሃገራት አራቱ ማለት ነው)
አቶ መለስ ወላጆቻቸው ያወጡላቸዉ ስም ለገሰ የሚል ነበር። «ዜናዊ» ማለት ዜና አብሳሪ ማለት ይመስለኛል። ወላጆቻቸዉ ለገሰ ዜናዊ ሲሏቸዉ «የሚያበስር ተሰጠን፣ ተወለደልን፣ ተለገሰልን» ብለው ሳይሆን አይቀርም ያንን ስም የሰጧቸዉ። መቼም ወላጆቻቸው ያኔ የተመኙት አቶ መለስ(ለገሰ) መልካም ብሥራት፣ መልካም ወሬ አብሳሪ እንዲሆኑላቸው ነበር የሚል ግምት አለኝ።
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ስሟ እንደሚገልጸዉ፣ ወላጆችዋ «ያማረች፣ የጣፈጠች፣ በሰዉ የተወደደች ትሁን» ብለው ይመስላል «ብርቱካን» ያሏት። «ሚደቅሳ»ም ተመሳሳይ ትርጉም አለዉ። «ሚደቅሳ» በኦሮምኛ ማሳመር፣ ማስዋብ ማለት ነዉ።
የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳም ሆነ የአቶ መለስ ዜናዊ ቤተሰቦች ሁለቱም ልጆቻቸዉ ትልቅ ደረጃ ደርሰዉ፣ መልካም ነገር አድርገዉ፣ በመልካም ስም ታዉቀዉ እንዲያልፉ ፍላጎት እንደነበራቸዉ ነው የምናየዉ።
የነዚህ ሰዎች መመሳሰል ግን እዚህ ላይ ያበቃል። አሁን ባለንበት ሁኔታ አቶ መለስ ዜናዊ ትልቅ ጭካኔ የተሞላበት ኢሰብአዊ ሥራ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ጨምሮ በሰላማዊ ዜጎች ላይ እስኪሰሩ ድረስ፣ በጥላቻና በክፋት የተሞሉ፣ እልኸኛ ሰው እንደሆኑ እያሳዩን ያለበት ወቅት ነው።
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ «ቅንጅት የሰው ጠላት የለውም። ወያኔ ጠላት አይደለም። ለአገራችን መፍትሄ ፍቅር ነዉ። ያሰሩኝን ይቅር ብያለሁ» እስከማለት ድረስ በፍቅርና በደግነት የተሞላች፣ የበደሏትንና ወደ ሁለት አመት ገደማ በግፍ ያሰሯትን ሰዎች ፣ አቶ መለስን ጨምሮ ፣ይቅር ያለች ታላቅ የፍቅር ሴት ናት። አንድ በሉ።
አቶ መለስ ዜናዊ በሚቆጣጠሩት የደህንነት ጽ/ቤት፣ የፌደራል ፖሊስና የአጋዚ ጦር ይመካሉ። እነዚህን ሕሊና የለሽ ሰዎችን በመላክ በመቶ የሚቆጠሩ ዜጎችን በጠራራ ጸሃይ አስገድለዋል። በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን በግፍ አሳስረዋል። ሰላማዊ መንደሮችን እንዲቃጠሉ አስደርገዋል።
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የታጠቀ ሰራዊት የላትም። በቤቷ መሳሪያ አልተገኘም። በእጆችዋ የወደቀዉን አነሳች እንጂ የቆመዉን ተኩሳ አልጣለችም። የምትተማመነዉ በሕዝብ ጉልበት እንጂ በጠመንጃ ጉልበት አይደለም። ሁለት በሉ።
አቶ መለስ ዜናዊ በተደጋጋሚ እርሳቸዉንና ደጋፊዎቻቸዉን ትዝብት ዉስጥ እስኪከቱ ድረስ የሚዋሹ ቀጣፊ ሰዉ ናቸዉ። ለምሳሌ የቅንጅት መሪዎች ከሁለት አመታት በፊት በተፈቱ ጊዜ፣ አቶ መለስ « ከአሁን በኋላ ወደ ፊት እንጂ ወደ ኋላ መመለስ የለብንም። ሕግን እስካልጣሱ ድረስ (የተፈቱት እሥረኞች) ሙሉ የፖለቲካ መብታቸዉ ተጠብቆ መንቀሳቀስ ይችላሉ» ነበር ያሉት። ነገር ግን ቃላቸዉን ለውጠዉ፣ ቀድሞ ከተፈቱት እሥረኞች መካከል ወ/ት ብርትካን ሚደቅሳን በግፍ እንድትታሰር አድርገዋል።
አቶ መለስ፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከታህሳስ 2001 እስከ ሐምሌ 2001 ድረስ በጨለማ ቤት ዉስጥ በግፍና በጭካኔ እንድትቀመጥና ሕገ መንግስትና ፍርድ ቤት የፈቀደላትን በዘመድ፣ በሃኪም፣ በመንፈሳዊ አባት፣ በጠበቃ .. የመጎብኘት መብቷ እንዲረገጥ አስደርገዋል። በማንም ነፈሰ ገዳይ ላይ እንኳን ያልደረሰ ጭካኔ እንዲደርስባት ፈቅደዋል። በአንድ በኩል ይህን ሁሉ እያደረጉ በሌላ በኩል ግን ወ/ት ብርቱካን ሰብዓዊ እንክብካቤ እየተደረገላት እንደሆነ በአደባባይ ይናገራሉ። ይህም በዉሸት መለኪያ በዓለም ከቀዳሚዎች መካከል የሚሰለፉ ሰዉ መሆናቸዉን በግልጽ የሚያሳይ ነዉ።
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ያላደረገችዉን «አድርጊያለሁ» እንድትል፣ እንድትዋሽ፣ ግፊትና ዛቻ ቢደረግባትም «እምቢ» ብላ ለእዉነት የቆመች ናት። ለእዉነትም በመቆሟ ትልቅ ዋጋ በአሁኑ ወቅት በመክፈል ላይ ትገኛለች። ሶስት በሉ።
አቶ መለስ ዜናዊ ከቀድሞ የ66ቱ አብዮት ዘመን ከነበረዉ፣ እርስ በርስ በደም ከተቃባዉ ፣ እምነተ ቢስ ፍልስፍናን ለኢትዮጵያ ህዝብ ካስተዋወቀዉ፣ እግዚአብሄርን ከካደዉ፣ አገራችንን ወደ ጨለማ ከወሰደዉ ትዉልድ ናቸዉ። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በጥላቻና በቂም በቀል ካልተሞላዉ ከአዲሱ ትዉልድ ናት። አራት በሉ !
የአቶ መለስ ዜናዊ ሴት ልጅ (ገንዘቡ ከየት እንደተገኘ እግዜር ይወቀዉ) በአለም ዝነኛ የሆነዉ የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ እየተማረች ናት። ለኑሮ፣ ለትምህርት ቤት ክፍያና ለተለያዩ ወጭዎች በአመት ሃያ አምስት ሺህ ፓዉንድ ወይንም ሰላሳ ስምንት ሺህ ዶላር አካባቢ ( ከአራት መቶ ሺህ ብር በላይ ) አቶ መለስ ለልጃቸዉ ይከፍላሉ። የአቶ መለስ ዜናዊ ልጅ እንደ አባቷ ጎበዝ ተማሪ ከሆነችና በአራት አመት ዉስጥ የባችለር ዲግሪ የምትይዝ ከሆነ፣ የአራቱን አመት ሂሳብ ብናሰላዉ፣ ከአንድ ሚሊዮን ስድስት መቶ ብር በላይ ገንዘብ ያወጣል።
የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ልጅ ሕጻን ሃሌ፣ እናቷ በጭካኔ ተወስዳባት፣ በሳምንት አንድ ቀን ፣ ከፈረንሳይ ለጋሲዮን ቃሊቲ ድረስ፣ ከአሮጊት አያቷ ጋር በመሄድ፣ ለአሥራ አምስት ደቂቃ ብቻ ነዉ የምታያት። በቃሊቲ እሥር ቤትም ያሉ ሰራተኞች፣ ከአራት ኪሎ በሚደርሳቸዉ ጥብቅ መመሪያ ፣ በእናቷ እንኳን መታቀፍ እናቷንም መሳም ያልቻለች ምስኪን ልጅ ናት። አምስት በሉ !
አቶ መለስ ሕግን እንደ በትር በመጠቀም፣ እንዳሻቸዉ በመተርጎምና በመለጠጥ በሕግ ስም በዜጎች ላይ የግፍ ቀንበር የሚጭኑ ሰዉ ናቸዉ። በአፋቸዉ «ሕግ ሕግ» ይላሉ በተግባራቸዉ ግን ሕግ የሚያስፈራቸዉና ከሕግ ጋር የተጣሉ፣ ሕግንም የሚረግጡ ግለሰብ ናቸዉ።
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከአመታት በፊት በሕግ ፊት ለቀረቡት አቶ ስዬ የዋስትና መብት በሰጠችበት ጊዜ እንዳስመሰከረችዉ፣ ከአራት ኪሎ በአቶ ስዬ ላይ ኢፍትሃዊ ዉሳኔ እንድትወስን ተጽኖ ቢደረግባትም፣ ሕግ ከማንም በላይ መሆኑን ያሳየች የፍትህ ሴት ናት።
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ለሕግ የበላይነት ያላትን ቁርጠኝነት በወሬ ብቻ ሳይሆን በተግባር ያሳየች ታላቅ ኢትዮጵያዊት ናት። ለዚህም ነዉ የአቶ መለስ የልጅነት ጓደኛ የሆኑት አቶ ስዬ አብርሃ «ጀግንነት በጦር ሜዳ ብቻ አይደለም። በጦርነት ከሚታይ ጀግንነት ያልተናነሳ ጀግንነት ያሳያች ፣ ጀግና ሴት» ሲሉ ለብርቱካን ሚደቅሳ ያላቸዉን ክብር የገለጹት። ስድስት በሉ!
ምንም ቢሆን ክፉ የሰራ ሰዉ በመንፈሱ ሰላም ስለማያገኝ ፣ አቶ መለስ ዜናዊ የጭንቀትና የመንፈስ መረበሽና የፍርሃት እሥረኛ ሆነዉ እየተሰቃዩ ናቸዉ። እራሳቸውን ይፈራሉ። አብረዋቸዉ ያሉትን የፖሊት ቢሮ አባላት ይፈራሉ። ህዝቡን ይፈራሉ። (ምናልባት የማይፈሩት ጎርደን ብራዉንና ሲልቪዮ ቤሎስኮኒን ብቻ ሳይሆን አይቀርም።) ሌሊት፣ በቤተ መንግስት በላጠጠ መኝታ ላይ እየተኙም እንቅልፍ የላቸዉም። እንደምንሰማዉም ከፍተኛ የራስ ምታት ስላለባቸዉ ለሕክምና ወደ ዉጭ አገር ብዙ ጊዜ ይሄዳሉ። አላወቁትም እንጂ የታሰሩትስ አቶ መለስ ዜናዊ እራሳቸዉ ናቸዉ ። በክፋትና በጭካኔ ፣ በክፉ መንፈስ !
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በመንፈሷ ነጻ የሆነች ሴት ናት። በሥጋ በማይመች ቦታ ታስራለች። ግን በዚያ በማይመች ቦታ ሆና የጣፈጠ እንቅልፍ ትተኛለች። ዉስጧ በፍርሃት የተሞላ አይደለም። በራሷ ትተማመናለች። ከማንም ጋር መኖር ትችላለች። በየትም ቦታ ብትሄድ ማንም አይነካትም። ሁልጊዜ እራሷን ቀና የምታደርጋት ናት። ሰባት በሉ!
አቶ መለስ ዜናዊ በ1991 ስልጣን እንደጨበጡ የኢትዮጵያ ባንዲራ ጨርቅ ነዉ በማለት አገራችንን በዘር የከፋፈሉ ጸረ-ኢትዮጵያ የኋላ ቀር ፖለቲካን ያራመዱ ሰዉ ናቸዉ። ኦሮሞዉ ከአማራዉ ጋር እንዲጋጭ፣ አማራዉ ኦሮሞዉን እንዲሸሽ፣ ትግሬዉ አማራዉንና ኦሮሞዉን እንዲፈራ፣ በአሥር ሚሊዮን የሚቆጠር ከተለያየ ዘር የተወለደዉና የተደባለቀዉ ኢትዮጵያዊ መብቱን እንዲረገጥ ያደረጉ፣ከፋፋይ መሪ ናቸዉ። እርሳቸዉ የዘረጉት ፖለቲካ፣ የዘር ድርጅቶች እንደ አሸን እንዲፈሉ ያደረገ ፖለቲካ ነዉ።
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የኢትዮጵያ አንድነትንና ሉዓላዊነትን መሰረት ያደረገ ድርጅትን የምትመራ ሴት ናት። የኢትዮጵያዊነትን ትልቅነት በማጉላትና በማሳያት በተለያዩ አቅጣጫዎች ተሰልፈዉ የነበሩትን ያሰባሰበች፣ መድረክ የሚባለዉን በአሁኑ የ2002 ምርጫ ጠንካራ አማራጭ ሆኖ የኢትዮጵያ ህዝብን ለመብቱና ለአንድነቱ እያደራጀ ያለዉ አካል፣ እንዲመሰረት መሰረቱን የጣለች ሴት ናት። በርሷ መሪነት የጎሳና የብሄር ድርጅቶች የኢትዮጵያ አንድነትን እያነገቡ በሕብረ ብሄራዊነትና በኢትዮጵያዊነት ሥር ተሰባስበዉ እየታገሉ ናቸዉ።
አቶ መለስ ከኢትዮጵያዊነት ወደ ዘረኝነት የሚወስድ ፖለቲካ ሲያራምዱ፣ ወ/ት ብርቱካን ከዘረኝነት ወደ ኢትዮጵያዊነት የሚያመጣ፣ የአንድነት፣ የፍቅርን የወንድማማችነትን ፖለቲካ የምታራምድ ናት። ስምንት በሉ !
ሰዉ የቅርቡንና የላይ ላዩን ያያል። እግዚዚብሄር ግን የሩቁንና የልብን ይመለከታል። እምቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም የመጥምቁ ዮሐንስ እናት ኤልሳቤትን ለመጎብኘትና ለማገልገል በሄደች ጊዜ የተናገረችዉ አንድ ትልቅ አባባል ነበር። «እግዚአብሄር ለትሑታን ጸጋን ይሰጣል። ትእቢተኞች ግን ያዋርዳል» ነበር ያለችዉ።
ዛሬ አቶ መለስ ጠዋትና ማታ በኢትዮጵያ ቴለቭዥን ስማቸዉ ሲጠራ፣ ዛሬ አፍሪካን ወክያለሁ ብለዉ በአለም አቀፉ መድረክ ከነኦባማና ጎርደን ብራዉን ጋር ፎቶ ሲነሱ፣ ከኒኮላይ ሳርኩሲ ጋር ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ፣ ዛሬ አይጋ ፎረምና የመሳሰሉ «መለስ የኢትዮጵያ አንበሳ » እያሉ ሲያወድሷቸዉ፣ የጸኑ፣ የበረቱ፣ የማይወድቁ ሊመስላቸዉ ይችላል።
ነገር ግን በትዕቢት ሰንሰለት ታስረዋልና መሰበራቸዉ አይቅርም። ንስሀ ካልገቡ ወደ እግዚአብሄር ካልተመለሱ፣ ክፉ ከመሥራት ካልተቆጠቡ፣ የቀናዉን መንገድ ካልያዙ በርግጥ አሰባበራቸዉና አወዳደቃቸዉ እጅግ ታላቅ ነዉ የሚሆነው።
ብዙዎች አቶ መለስን እንደ ጠላት ነዉ የሚያዩት። ብዙዎች የአቶ መለስ ዜናዊ ፎቶ ላይ ቀንድ እያደረጉ እንደ ጭራቅ ይመስሏቸዋል። (ይሄ ሁሉ ከሚሰሩት ግፍ የተነሳ ነዉ። ስራቸዉ ነዉ እንዲጠሉ ያደረጋቸዉ)
ነገር ግን አቶ መለስ አሁንም የሚታገስና የሚችል አንድ ወዳጅ አላቸዉ። እርሱም የሐጢያተኞች ወዳጅ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየስስ ክርስቶስ ነዉ። ወደዚህ ወደ ቸሩ መድሃኔዓለም ከመጡ፣ ልባቸዉን በፊት ካዋረዱ፣ ከታዘዙት ይባረካቸዋል። እርሱም ሐጢያታቸዉን ይቅር ይላል። በፍርሃትና በጭንቀት የተሞላዉን ሕይወታቸዉን ይለዉጠዋል። ከራሳቸዉ አልፈዉ ለአገር እርግማን ሳይሆን በረከት ያደርጋቸዋል። ከዚህ በፊት ያበላሹትን የሚክስ ሥራ የሚሰሩ ይሆናሉ።
«እሺ ብትሉ፣ ብትታዘዙ የምድረን በረከት ትበላላቹህ፤ እምቢ ብትሉ ግን፣ ብታምጹ ሰይፍ ይበላቹህል» ተብሎ በትንቢተ ኢሳይስ ምእራፍ አንድ ላይ እንደተጻፈዉ፣ እምቢ ካሉ፣ ልባቸዉን ካደነደኑ፣ ለድሆችና ለተጎዱት የምትፈርደዋ የታላቁ እግዚአብሄር እጅ በተዘረጋች ጊዜ፣ ያኔ አያዝልቅ ነዉ!!! እግዚአብሄር ከዚህ ይሰዉረን! አቶ መለስንም ከመንፈሳዊ እሥራት ወ/ት ብርቱካን ሚድቅሳ ደግሞ ከሥጋ እሥራት ይፍታቸው ! አገራችን ኢትዮጵያንም ይጎብኛት!
|
|
1 comment
Write a Comment
Related posts:
- ፓስተሩ ግን እግዚአብሄርን ነዉ መለስን ነዉ የሚያገለግለው?
- አቶ ኃይሉ ሻውል በብርቱካን ጉዳይ ላይ ምን ያደርጉ ይሁን?
- የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፓለቲካ – ከዶክተር ነጋሶ ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ
- በነጄነራል ተፈራ ማሞ ላይ የተወሰነዉ የፍርድ ቤት ዉሳኔ በተመለከተ
- የኢትዮጵያው አውሮፕላን አደጋ መንስኤ እስካሁን አልታወቀም
sileshi girmaw
7 May 10 at 3:43 pm
you have forced me to read more .
thank you