BY: Dawit Fanta
ህወሃት – በሞተ አባቱ በሬ ዝና የሚኖር ጥጃ !!!
ላለፉት ሃያ አንድ አመታት የወያኔ ቁንጮ የነበረው መለስ ዜናዊ ሞት በመንግስት ደረጃ ይፋ ከተደረገ እነሆ ቀናት ተቆጥረዋል።ይሁንና በአንድ ሰው አምባገነንነት ላይ የተመሰረተው የወያኔ መንግስት ከወዲሁ ግራ መጋባቱን የሚያሳብቁ ሁኔታዎች ከመከሰታቸውም ባሻገር ይህንን የዕውር ድንብር ግራ መጋባት ለመሸፈንና ብሎም በቀጣይ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት /Legitimacy/ ለማግኘት ወያኔ እየወሰደ ያለውንና ሊወስድ እየተዘጋጀባቸው ስላሉ እርምጃዎች እና የእርምጃዎቹን የአጭር እና የረጅም ጊዜ አንድምታ መፈተሽ የዚህ ፅሑፍ ዋና አላማ ይሆናል።
ሀ. መለስን የህዝብ ልጅ ለማስመሰል የተደረገው ሩጫ
ወያኔ/ኢህአዴግ የመለስ አስከሬን አዲስ አበባ ከገባ ጀምሮ ያለመታከት እየታተረበት የሚገኘው አንዱ ክስተት መለስ ዜናዊን የህዝብ ልጅ ለማስመሰል የሚያደርገው ከንቱ ሩጫ ነው።ለዚህም፦
1. ቅጥረኛ ካድሬዎች እና የሥርዐቱ ተጠቃሚዎች በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ወጥተው እንዲያለቅሱ በማድረግ እና የለቅሶ ፕሮግራሙን በቀጥታ የቴሌቪዥን ሽፋን በመስጠት መለስ በህዝብ የሚወደድ ማስመሰል፤እንዲሁም እነዚህን ቅጥረኞችንና ጥቅመኞችን በቴሌቪዥን ቃለ ምልልስ እንዲያደርጉ በማድረግ “መለስ ቢለየንም ግቡን ወደፊት እናስቀጥላለን” በማለት የህወሃትን የግፍ አገዛዝ ቀጣይነት በዘወርዋራው ለቀሪው ህዝብ መልዕክት ማስተላለፍ፤
2. ባልተለመደ ሁኔታ ቤተ መንግስቱን ለተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ክፍት በማድረግ በኢትዮጵያውያን ወግ መሠረት በሟች ቤት እርም እንዲያወጡ በማድረግ ነገር ግን በመለስ ጓዳ መንግስት እና ህዝብን ያቀራርባል ብለው ያሰቡትን የህዝብ ግንኙነት ሥራ መስራት፤
3. በቀጣይነትም ወያኔ ያቋቋማቸው ሊጎች፧ፎረሞች እንዲሁም ማህበራት እያደረጓቸው ያሉ እና ያደርጓቸዋል ተብለው የሚጠበቁ “ጫጫታዎችን” /Noises/ በተለመደው የወያኔ የፕሮፖጋንዳ ማሽን ህዝባዊ መሰረት ያለው አስመስሎ ማቅረብን ያካትታል።
ነገር ግን የወያኔ ቀሪ አውራዎችም ሆኑ አድር ባይ ጥቅመኞች ሊዘነጉት የማይገባው ጥሬ ሃቅ ቢኖር በሙት ሬሳ ላይ የሚደረግ የፖለቲካ ንግድን ህዝባችን እንዲሁ የሚቀበለው ሳይሆን ሟች በህይወት ዘመኑ ከህዝብ ጋር የነበረውን ግንኙነት በውክልና ከሚደረገው የሬሳ ፖለቲካ ጋር እያነፃፀረ የሚጠቅመውን የሚመርጥ ሲሆን ለማሳያ ያህልም፦
1. መለስ በስልጣን በቆየባቸው ዘመናት ሁሉ “ህዝባችን” እና “ህዝቡ” በሚል አንዱን ልጅ ሌላውን የእንጀራ ልጅ የማድረግ ድርጅታዊና ግላዊ አመለካከት የነበረው ሲሆን ህዝባችን እያለ የሚጠራውን የህብረተሰብ ክፍልም በአደባባይ “ወርቅ” እያለ ከማንቆለጳጰሱም ባሻገር ሌላውን “ጨርቅ” አስመስሎ ለማቅረብ ያደረገውን ጥረት ከሆድ አደር ጥቅመኞች ውጭ ለቀሪዎቻችን የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
2. መለስ “ህዝቡ” እና “ህዝባችን” እያለ ይከተለው የነበረው አካሄድ እንዲሁ በድንገት የተነገረ /ድኃፄ አንደበት/ ሳይሆን በድርጅት ደረጃ እንደመርህ የተያዘ እና በዚህ ረገድም ብዙ የተሄደበት ለመሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው።
3. መለስም ሆነ ህወሃት “ህዝቡ” እያሉ የሚጠሩትን ማህበረሰብ ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ እንደአስፈላጊነቱ እንደሚጠቀሙበት ለዚህም የብዙሃንን ልብ ማግኘት ስለማይችሉ ውስን ቅጥረኛ ሆድ አደሮችን በማሰማራት እጅ ተወርች በመጠርነፍ የወረራ እና የዘረፋ ተግባራቸውን ሲከውኑ ኖረዋል::
4. በተመሳሳይ መለስም ሆነ ህወሃት “ህዝባችን” እያሉ የሚጠሩትን የህብረተሰብ ክፍል እንደ ቀንድ አውጣ ጠጠር /Shell/ ለክፉ ቀን መሸሸጊያነት ብቻ ሲጠቀሙበት አይተናል።
በመሆኑም ይይዝ ይጨብጠውን ያጣው የወያኔ ቡድን በሬሳ ፖለቲካ እና መለስን ህዝባዊ መሰረት ያለው በማስመሰል ሊያገኝ ያሰበው የወደፊት ተቀባይነት ጥረት “ለዕብድ አሞራ ሲላ ደንገጡራ” እንድንል ያስገድደናል።
ለ. “ለውሻ ጆሮውን ቆርጠው ቢሰጡት ሥጋ ነው ብሎ ይበላዋል”
ከላይ እንደርዕስ የተጠቀምኩበትን አባባል በአንድ ወቅት የአፄ ኃ/ሥላሴ ልጅ ልዕልት ተናኘወርቅ በአንድ ታሪካዊ ወቅት እንደተናገረችው የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ።ይኸውም በንጉሱ የአገዛዝ ዘመን ማብቂያ ወታደሩ የደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ በማንሳቱ የንጉሱ አማካሪዎች አይሆንም በማለት ሲከራከሩ ልዕልቲቱ “በቀጥታ እምቢ ከማለት እሺ ብለን ጥያቄያቸውን እንመልስ ነገር ግን በወታደሩ ላይ የታክስ ጭማሪ እናድርግ መቼስ ለውሻ ጆሮውን ቆርጠው ቢሰጡት ሥጋ ነው ብሎ ይበላዋል” በማለት ነበር የተናገረችው።በእርግጥ የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ ከኢትዮጵያ ህዝብ አብራክ የተገኘው የጦር ሰራዊት “የጆሮውን ቁራጭ ሥጋ ነው ብሎ የሚበላ ውሻ” አለመሆኑን በወቅቱ አስመስክሯል::
እናም ከ39 ዓመታት በኋላ የህወሃት ሰዎችም ከዚህ አባባል ጋር በተግባር የሚዛመድ ሁኔታን ለመከወን በውጤቱም የህወሃትን ልዕልና ለማስጠበቅ ደፋ ቀና ማለት ጀምረዋል:: በተጨባጭም የህዝብን ልብ ያሸንፍልናል የሚሉትን እርምጃዎች ለመውሰድ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ጥገናዊ ለውጥ ለማድረግ ተዘጋጅተዋል።
1. በይቅርታ ስም የታሰሩ የፖለቲካ እና የኅሊና እስረኞችን መፍታት፦በመሠረቱ የወያኔ አስተዳደር ፓርቲውን ይቃወማሉ የሚላቸውን ሁሉ ለመቀጥቀጥ የፍትህ ስርዐቱን እንደ መውጊያ ዘንግ ሲጠቀምበት ኖሯል።በመሆኑም በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞች በወያኔ የማጎሪያ ካምፖች /Concentration Camps/ በግፍ በሽብርተኝነት ታስረው ይገኛሉ።ይሁን እንጂ በዚህ አጣብቂኝ ወቅት ወያኔ/ኢህአዴግ ራሱን “ለቁጣ የዘገየ፧ምህረቱም የበዛ ይቅር ባይ” በማስመሰል እነ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅን በተለመደ “የሽምግልና” ካባ በፊት አውራሪነት በማሰለፍ “በይቅርታ” የተወሰኑትን በተለይም በአለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑትን ሊፈታ ይችላል /የመለስ ሞት በይፋ ከተገለፀ በኋላ የታሰረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ይሁን አይሁን ለመተንበይ ያስቸግራል/። በዚህም በሌሎች ዘንድ የሞራል ገዢ መሬቶችን /Morale High Grounds/ በመያዝ በለውጥ ጎዳና ላይ ያለ ለማስመሰል ሊጥር እንደሚችል ይገመታል።ነገር ግን ይህ ዓይነት የወያኔ አካሄድ ለኢትዮጵያ ህዝብ እንግዳ ባለመሆኑ ይልቁንም ወያኔ አጣብቂኝ ውስጥ ሲገባ እና የታፈነ የህዝብ ቁጣ በድንገት እንዳይፈነዳ ስጋት ሲይዘው የፖለቲካ እና የኅሊና እስረኞችን በይቅርታ ሽፋን ከእስር መፍታትን እንደ የማስተንፈሻ መስኮት /Relief Valve/ የሚጠቀምበት ታክቲክ መሆኑን ከወዲሁ መገንዘብ ያስፈልጋል።ለምሳሌ ምርጫ-97ን ተከትሎ የቅንጅት አመራሮችን እና ደጋፊዎችን ማሰሩ በውጭ መንግስታት በኩል ጠንካራ ተቃውሞ እና ግፊት ሲያይል እንዲሁም በሃገር ቤት በህዝብ ውስጥ የተዳፈነ ግን ጊዜ ጠብቆ ሊፈነዳ የሚችል ተቃውሞ በመኖሩ የቅንጅትን አመራሮችንም ሆነ ደጋፊዎችን መፍታት ችሎ ነበር::ይሁን እንጂ ያ የውጥረት ጊዜ ሲያልፍ “ድመት መንኩሳ …………..” እንደሚባለው የህግ ሽፋን በመስጠት የእስሩን ሁኔታ ከቀደመው ይልቅ በሰፊው ቀጥሎበታል። በመሆኑም ምናልባትም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ሊያደርገው የሚችለውን የእስረኞችን የመፍታት ሁኔታ እንደለውጥ መቁጠር ለወያኔ የባርነት ቀንበር ተጨማሪ ጊዜ እና ዕድል መስጠት መሆኑን ከወዲሁ ልብ ልንለው የሚገባ ጉዳይ ነው።
2. የማይሳኩ የተናጠል ድርድሮችን ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር ማድረግ፦ ወያኔ በፖለቲካ ምህዳሩ ውስጥ ጉልህ ሚና እያበረከተ ጠንካራ ሃይል ሆኖ በመውጣት ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በእውነተኛ መድብለ ፓርቲ ሥርዐት ለመኖር ህልም የሌለው ይልቁንም በተናካሽ እና የአጥቂነት ባህርይው ለድርድር የማይመች፤ጊዜው ከሚጠይቃቸው ሁኔታዎች ጋር የማይተጣጠፍ እና በሃገራችን ዘላቂ ሰላም እና ብሄራዊ መግባባት እንዳይመጣ የድርድር አጋጣሚዎችን በሙሉ በአታላይነት ባህርይው ሲያጨነግፍ የኖረ ድርጅት ነው።ይልቁንም የ “እንደራደር” ጥያቄዎችን ወደ ጠረጴዛ ይዞ የሚመጣው የተቃውሞ ግፊት ሲበረታበት የተቃዋሚውን ሃይል ለመከፋፈል አልያም የተቃውሞውን ጎራ እያታለለ ወደ መግደያ መሬት ለማስገባት እና በዚያው ለመድፈቅ ነው።ለምሳሌ በሽግግር መንግስቱ ወቅት ከኦነግ ጋር በኋላም በምርጫ-97 ወቅት የአፍሪካ የመሪዎች ስብሰባ በሰላም እንዲያልፍ ስለፈለገ ብቻ ከህብረት እና ከቅንጅት ጋር ያደረጋቸው የሚጠቀሱ ሲሆን ሌሎችም መሰል ፍሬ አልባ “ድርድሮች” በወያኔ ማህደር ውስጥ በሰፊው ይገኛሉ።
በመሆኑም አሁን ባለንበት ወቅት ወያኔ በተለይ ብረት ካነሱ የተቃዋሚ ሃይሎች ጋር በዋናነት ከኦብነግ እና ኦነግ ጋር የተለመደ “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደራደር” የሚል የማደናገሪያ ሃሳቡን ይዞ እንደሚመጣ የሚጠበቅ ሲሆን በተለይ በኦሮሚያ እና በኦጋዴን አካባቢ የህዝብን ተቃውሞ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ለማርገብ ሲል ድርድርን ከፍ አድርጎ ሊያስጮኸው እንደሚችል በሰፊው ይታመናል።
ነገር ግን ጥሪ ሊደረግላቸው የሚችሉ የተቃዋሚ ድርጅቶችም ሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ የወያኔን የተሙለጭላጭነት ባህርይ ከግንዛቤ በማስገባት ወደ ወያኔ የመግደያ መሬት ተታሎ ላለመግባት እና ለወያኔ የመተንፈሻ ጊዜ በመስጠት መጠቀሚያ ላለመሆን ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።
3. ወያኔ የሚወቀስባቸውን አፋኝ ህጎች ለጊዜው ማሻሻል በሂደት ግን ወደ ነበሩበት መመለስ፦ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወያኔ በስፋት ከሚተችባቸው አበይት ጉዳዮች መካከል “የፀረ-ሽብር ህግ” በመባል የሚታወቀው አዋጅ ቁጥር 652/2009 ሲሆን በትርጉምም ይሁን በትንተና ግልፅነት የጎደለው አሻሚ /Subjective/ ከመሆኑ ባሻገር የአዋጁ መፅደቅ በእርግጥም የሽብርን ተግባር ለመቆጣጠር ሳይሆን በተግባር እንደታየው በህግ ሽፋን ጭል ጭል የሚለውን የነፃ ፕሬስ እንቅስቃሴ በእንጭጩ ለመቅጨት፧የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን በማሰር አባሎቻቸውን ለማሸማቀቅ እና እንቅስቃሴያቸውንም ለማሽመድመድ ብሎም የሲቪክ ማህበራትን ሚና ለመገደብ ሲባል በፖለቲካ መንፈስ የተቃኘ በወረቀት ላይ የሰፈረ እግረ ሙቅ ነው።ይህ አንቀፅ እየተጠቀሰባቸው ወደ ወያኔ እስር ቤቶች በግፍ የተወረወሩ ጋዜጠኞች፧የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች እና ደጋፊዎች እንዲሁም አክቲቪስቶች በርካቶች ሲሆኑ ይህንንም ተከትሎ በተለያየ ጊዜ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ቡድን /CPJ/፧የሰብዐዊ መብት ተሟጋች ቡድን /Human Rights Watch/ እንዲሁም ሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት የወያኔን አስተዳደር የሚያወግዙ ሲሆን ይህም በወያኔ አለም አቀፍ ገፅታና ፖለቲካዊ ተክለ ስብዕና ላይ ጥቁር ጥላውን እንዳጠላበት ይገኛል።ይሁን እንጂ እስካሁን ባለው ውጫዊ ግፊት የወያኔ መንግስት ህጉን ለማሻሻልም ሆነ ለመቀየር አዝማሚያ ያላሳየ ቢሆንም በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ በገባበት ወቅት ግን ቢያንስ ውጫዊ ተቀባይነትን /External Legitmacy/ ለጊዜውም ቢሆን ለማግኘት ሲል በህጉ ላይ መጠነኛ ለውጥ ሊያደርግ ይችላል።
ለዚህ እንደማሳያ የሚሆነን የአረቡ ዓለም አብዮት በሰሜን አፍሪካ እየተቀጣጠለ በነበረበት ወቅት የአብዮቱ ማዕበልም ወደ ኢትዮጵያ ይመጣል የሚል ስጋት በወያኔ ላይ በመፈጠሩ እከተለዋለሁ ከሚለው ገበያ መር ኢኮኖሚ ባፈነገጠ እና ባልተለመደ መልኩ የዕዝ ኢኮኖሚ አሰራርን በመከተል በዕቃዎች ዋጋ ላይ የመሸጫ የዋጋ ጣራ በማውጣት ለህዝብ ተቆርቋሪ መስሎ ለመታየት ጥረት ቢያደርግም በሂደት ስጋቱ /ከአምስት ወራት በኋላ/ ሲቀንስ በሃይል በነጋዴው ላይ የጫነውን የዋጋ ተመን ሲያነሳ የዕቃዎች ዋጋም በፊት ከነበረው በባሰ ሁኔታ ሊጨምሩ ችለዋል። ከዚህ የተሞክሮ ጭብጥ መረዳት የሚቻለው ወያኔ የፖለቲካ ትርፍ እስካስገኘለት ድረስ ማንኛውንም ነገር ከማድረግ የማይመለስ በመሆኑ የአዋጅ ቁጥር 652/2009 ማሻሻልን ሌላው የጊዜ መግዣ የወያኔ የቁማር ካርድ ሊያደርገው እንደሚችል ከወዲሁ በመገንዘብ በዚህ ዙሪያ የሚደረግ ማሻሻያም ሆነ ለውጥ ዘለቄታ የሌለው ይልቁንም በሂደት ወደ ነበረበት የሚመለስ የማደናገሪያ እርምጃ መሆኑን ከተደጋጋሚ የወያኔ ተሞክሮ በመነሳት ልብ ልንለው ይገባል።
4. የኢትዮጵያን አንድነት ከወያኔ/ኢህአዴግ ህልውና ጋር አቆራኝቶና አግዝፎ ማሳየት፦ ወያኔ ራሱን በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን እንደ ዩጎዝላቭያ እና ሶቭየት ህብረት ከመበታተን የታደገ መሲህ በማስመሰል የሌባ ዓይነ-ደረቅ ክርክሩን ሲያስደምጠን በተለያዩ መድረኮች ሰምተናል።ይሁን እንጂ ይህን “የመበታተን አደጋ” በድጋሚ እንዳይመጣ ዋስትናችን ወያኔ ብቻ እንደሆነ በተለይም አጣብቂኝ ውስጥ ሲገባ የአንድነታችን መድህን እሱ ብቻ እንደሆነ እንድናስብ በፍርሃት /Appeal to fear/ ውስጥ ሊያሳየን ይሞክራል።ለምሳሌ በድኅረ ምርጫ-97 ወቅት ወያኔ “አጋር ድርጅቶች” እያለ የሚጠራቸው ተለጣፊ ድርጅቶች ህዝቡ የወያኔ/ኢህአዴግን የምርጫ ድል ካልተቀበለ አንቀፅ 39 ተግባራዊ እንዲደረግልን በክልላችን እንንቀሳቀሳለን እስከማለት የደረሱበት አጋጣሚ ሲኖር የወያኔው መስራች አቶ ስብሐት ነጋ /አቦይ ስብሐት/ ለቪኦኤ በሰጡት መግለጫ “……………..አለበለዚያ ሁላችንም በየመንደሮቻችን እንመሽጋለን ኢትዮጵያ የምትባልም ሃገር አትኖርም” በማለት የህወሃት የመንግስትነት ህልውና ለኢትዮጵያ እንደ አንድ ሉአላዊት ሃገር መቀጠል መሠረቱ መሆኑን ሊያሳዩን ሞክረዋል።ይህ በተግባር በአንድነታችን ላይ ሲቆምር የኖረ ነገር ግን እንደ አስፈላጊነቱ የአንድነታችን መሰረት እሱ መሆኑን በፍርሃት ውስጥ ሊያሳየን እንደሚሞክር እና ይህም የወያኔ አካሄድ በዚህ ወሳኝ ወቅት ከሚመዘዙ ካርዶች ውስጥ በሰፊው የሚጠበቀው ይሆናል።
5. የሃውዜን ሞዴል ዘመቻዎችን /False Flag Operation/ ማዘጋጀት እና የተወሰኑ የህ/ሰብ ክፍሎችን ህልውና ከወያኔ ህልውና ጋር አቆራኝቶና አግዝፎ ማሳየት፦ ወያኔ በኢትዮጵያ መራኄ መንግስት ከሆነበት 1983 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያየ ወቅት ለተለያየ አላማ የሃውዜን ሞዴል ዘመቻዎችን /False Flag Operation/ ያካሄደ ሲሆን ከነዚህም መካከል፦
1. ኦነግን ከህዝብ የመነጠል ዘመቻ፦በ1984/85ዓ.ም. አካባቢ ኦነግን ከኢትዮጵያ ህዝብ ለመነጠል በሚል በአሰቦት፧በበደኖ እና በአርባጉጉ በሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ጥቃት በመፈፀም ኦነግ ያደረገው አስመስሎ ማቅረቡ ያደባባይ ምስጢር ሲሆን በዚህም የተወሰኑ ከክልላቸው ውጭ የሚኖሩ ዜጎችን ህልውና የሚታደግ መድህን እሱ ብቻ እንደሆነ ለማሳየት ሞክሯል፤
2. የአኬልዳማው ተረት ተረት፦በቅርቡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርቦ በኋላ ላይ በነታማኝ በየነ ብርቱ ጥረት በኢሳት ቴሎቪዥን የተጋለጠው “አኬልዳማ” የተሰኘው የወያኔ የፈጠራ ድራማ የስርዓቱን የሞራል መላሸቅ /Moral Deprivation/ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ሲሆን አላማውም ተቃዋሚዎችን በህዝብ ዘንድ አሰይጥኖ /Demonize/ ለማሳየት ነበር።
3. “ትግሬ ወደመቀሌ ንብረቱ ወደቀበሌ”፦ይህች ሐረግ /Phrase/ በደህንነቱ መ/ቤት በሚገኙ የጌታቸው አሰፋ ቡችሎች በምርጫ-97 ወቅት ተፈብርካ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የትግራይ ተወላጆችን ነጥለው ለማጥቃት የተጠቀሙበት አባባል በማስመሰል የተናፈሰ እና ወያኔ የትግራይ ተወላጆችን የተለየ ድጋፍ ለማግኘት የተጠቀመበት ስልት ነው።
ከላይ በሶስት ምሳሌ ለማሳየት እንደሞከርኩት የሃውዜን ሞዴል ዘመቻዎችን /False Flag Operations/ ወያኔ በስፋት የሚጠቀምበት ሲሆን አሁንም በተለይ የትግራይ ተወላጆችን አደጋ ውስጥ እንዳሉ የሚያስመስሉ ድርጊቶችን እና ግርግሮችን በማድረግ የተለየ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የማይመለስ መሆኑን ከወዲሁ ልንገነዘብ ይገባል።በዚህ አጋጣሚ ግን የትግራይ ህዝብ ከቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ በባሰ ሁኔታ የዚህ ስርዓት ሰለባ የሆነ ሲሆን ዛሬም ቢሆን በአስከፊ ድህነት የሚኖር፧ፍትህን የተጠማ፧የመናገር እና የመቃወም መብቱን በአደባባይ የተቀማ፧በወያኔ የስለላ መረብ መፈናፈኛ ያጣ በጥንታዊትም ይሁን በዘመናዊት ኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ የማይደራደር ታላቅ ህዝብ ሲሆን ቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ የትግራይን ህዝብ በወያኔነት ይፈርጃል የሚል አመለካከት ሁሉ ፍፁም የተሳሳተ አተያይ መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል።በመሰረቱ ወያኔ ማለት ከኦሮሚያ የወጡ፧ከአማራ የወጡ፧ከደቡብ ኢትዮጵያ የወጡ ስብስቦችም ጭምር መሆናቸውን ማንም ኢትዮጵያዊ የሚያውቀው ሃቅ ነው።
ማጠቃለያ
የመለስ ዜናዊ ሞት በኢትዮጵያም ሆነ በአካባቢው ሃገሮች ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩ አሌ የማይባል ሃቅ ነው።ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ ጉዳይን በዳር ቆመን ከማየት በዘለለ የእያንዳንዳችንን ገንቢ አስተዋፅኦ ማበርከት ከሁላችንም የሚጠበቅ የዜግነት ሃላፊነት ሲሆን ለዘመናት የተዘጋው የፖለቲካ ምህዳር ተከፍቶ፧የሃገራችን ጉዳይ ያገባናል የሚሉ አካላት በሙሉ ተሳታፊ የሚሆኑበት የሽግግር መድረክ ተዘጋጅቶ፧ብሄራዊ መግባባት ተፈጥሮ፧በእውነተኛ መሰረት ላይ የተገነባ እና ሁላችንንም ሊያስታርቅ የሚችል ነገር ግን እንደአስፈላጊነቱ በየጊዜው የሚሻሻል ህገ-መንግስት ጸድቆ፧ህዝብም በግልጽ በተቀመጠ የጊዜ ገደብ ውስጥ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚያስተዳድረውን መንግስት ያለ ተፅዕኖ የሚመርጥበት ዕድል እንዲመቻችለት እንዲሁም የኢትዮጵያ የመከላከያ ሃይል እና የደህንነት ተቋማት ተጠሪነታቸውም ሆነ ተአማኒነታቸው ለህዝብ የሚሆንበት ስርዓት ተገንብቶ እንድናይ ሁላችንም በዚህ ወሳኝ ወቅት በጋራ እንነሳ!!!!
Dawit Fanta
August 26, 2012
You can leave a comment below.
