The Reporter
ከፍሬው አበበ እና በኃይሌ ሙሉ
የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እንደገና መታሰር በአገሪቱ እየታየ ያለውን የሕግ ጥሰት አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑን አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ትናንት ለሪፖርተር ጋዜጣ በላከው መግለጫ አስታወቀ፡፡
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ "ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመለወጥ ሙከራ አድርገዋል" በሚል በተከሰሱበት ጉዳይ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ሐምሌ 13 ቀን 1999 ዓ.ም የተፃፈ ደብዳቤ ሙሉ ይቅርታ የተሰጣቸው መሆኑን ያረጋግጣል ያለው የፓርቲው መግለጫ ወ/ት ብርቱካን ለወደፊቱ ከእንደዚህ አይነት ተግባር እስካልተሳተፉ፣ ሕገመንግስቱን የማክበርና የማስከበር ዜግነታዊ ግዴታቸውን በአግባቡ እስከተወጡና በሕገ መንግሥቱ የተደራጁ የመንግሥት ተቋማትን ሥልጣንና ተግባር ተቀብለውና አክብረው እስከቀጠሉ ድረስ ጸንቶ እንደሚቆይ ፕሬዚዳንቱ የሰጡት የይቅርታ ሰርተፊኬት እንደሚያረጋግጥ አስታውሷል፡፡ ወ/ት ብርቱካን የገቡትን ቅደም ግዴታ በምንም መልኩ ያልጣሱ በመሆኑና በዚህ ረገድ በመንግሥት በኩል የቀረበ ክስ ባለመኖሩ የእርሳቸው መታሰር የሕግ ጥሰትን አጉልቶ እንደሚያሳይ አመልክቷል፡፡
ለወ/ት ብርቱካን ተሰጥቶ የነበረው ይቅርታ የተነሳው በአንድ መድረክ ላይ "ይቅርታ አልጠየቅኩም" ብለዋል በሚል ምክንያት መሆኑንና ይህ ደግሞ በምንም መልኩ ይቅርታን ሊያሰርዝ የሚችል ድርጊት ነው ሊባል እንደማይቻል የገለጸው አንድነት ፓርቲ ይህም ሆኖ ለወ/ት ብርቱካን ተሰጥቶ የነበረው ይቅርታ ሲሰረዝ መሟላት የነበረባቸው ሕጉ የሚደነግጋቸው ሥነ ሥርዓቶች ሙሉ በመሉ ተጥሰዋል ብሏል፡፡
በፓርቲው መግለጫ ላይ እንደተመለከተው አዋጅ ቁጥር 395/1996 አንቀጽ 17 በሚደነግገው መሰረት ይቅርታ ለማሰረዝ የሚያበቃ በቂ ምክንያት ሲገኝ ምክንያቱ በግልጽ በጽሁፍ ተዘጋጅቶ ለይቅር ተባይ እንዲደርሰው መደረግ ያለበት ቢሆንም ወ/ት ብርቱካን ግን ይቅርታው የተሰረዘባቸው ሕጉ በሚያዘው መሰረት በጽሁፍ ሳይደርሳቸውና መልስ ለመስጠት የሃያ ቀናት ጊዜ የመሰጠት መብታቸው ሳይከበር ነው፡፡
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ታህሳስ 20 ቀን 2001 ዓ.ም ከቀኑ በ8፡00 ሰዓት ላይ ማንነታቸውን ባላሳወቁና ሕጋዊ መጥሪያ ባላሳዩ ግለሰቦች እንግልትና ወከባ የደረሰባቸው መሆኑንና በወቅቱም አብረዋቸው የነበሩት ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያምና የወ/ት ብርቱካን ሾፌር በሆኑት አቶ አብዱራህማን አህመድ ላይ የድብደባ ደርጊት እንደተፈፀመባቸው የጠቀሰው ይኸው መግለጫ "ከላይ የተጠቀሱት ድርጊቶች ሕገወጥ ብቻ ሳይሆን የዜጎችን ሰብዓዊነት ሕገ መንግሥታዊ መብቶቻቸው መረገጣቸውን ያሳየ ድርጊት ነው" ብሏል፡፡ አያይዞም ወ/ት ብርቱካን ይቅርታ ሲሰጣቸው የገቡትን ግዴታ ያልጣሱ በመሆኑ የተሰጣቸው ይቅርታም የተሰረዘው ሕጉ የሚደነግገውን ሥርዓት በመጣስ መልኩ በመሆኑ እና ይቅርታው ተሰርዞ ወደ ወህኒ በወረዱበት ወቅት የደረሰባቸው እንግልት በሕገ መንግሥቱ የተከበረላቸው ሰብዓዊ መብቶችን የሚጥስ በመሆኑ፣ የተሰረዘው ይቅርታ ውድቅ ሆኖ ቀደም ሲል የተሰጣቸው ይቅርታ እንዲፀና ጠይቋል፡፡
ወ/ት ብርቱካን በታሰሩበት እለት ከቀኑ 8፡00 አካበቢ ከኦሎምፒያ ወደ መስቀል ፍላወር በሚወስደው መንገድ አካባቢ በሚገኘው ፕሪዝን ፌሎ ሽፕ ድርጅት በር ላይ ከእርሳቸው ጋር አብረው የነበሩት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ዩኒፎርም በለበሰ አንድ ወታደር ፊኛቸውን በሰደፍ መመታታቸውን ለሪፖርተር ጋዜጣ ገልጸዋል፡፡
ቁጥራቸው 10 የሚጠጉ ወታደሮች ወ/ሪት ብርቱካንን ከብበው መያዝና መገፋፋት ሲጀምሩ "አንድ ሰው ለማሰር ይህ ሁሉ ሰው እና ጠበንጃ ለምን ያስፈልጋል?" የሚል ጥያቄ ማንሳታቸውን የገለጹት ፕሮፌሰር መስፍን የእርሳቸውን ጥያቄ ተከትሎም አንድ ወታደር በሰደፍ ፊኛቸውን እንደመታቸው፣ ወታደሩ ሲመታቸውም የህመም ስሜት የተሰማቸው የተመቱበት ቦታ ላይ ሳይሆን ባታቸውና ቋንጃቸው ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከድበደባው በኋላ ብሩክ ክሊኒክ በመሄድ አልትራሳውንድ መነሳታቸውንና በፊኛቸው ላይ ምንም ጉዳት እንደሌለ ሀኪሞች የነገሯቸው መሆኑን ፕሮፌሰሩ የገለፁት አሁንም ድረስ ግን ባታቸውንና ቋንጃቸውን እንደሸመቀቃቸው ጠቁመዋል፡፡
"የወ/ት ብርቱካን መታሰር በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ ምንድነው?" በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ፕሮፌሰሩ ሲመልሱ "ፖለቲካ የሚባል ነገር አብቅቷል፡፡ አርፈን እንድንቀመጥ ብቻ ነው የተፈለገው" ብለዋል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን ያነጋገርናቸው የኢዴኅህ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በእሁዱ ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ወ/ት ብርቱካን ይቅርታ መጠየቃቸውን እንዳልካዱ የሚገልፅ ዜና እንደተመለከቱና ያ ቃል ከወ/ሪት ብርቱካን እስከወጣ ድረስ መንግሥት የፈለገውን ምላሽ ያገኘ መሆኑን ጠቁመው መንግሥት በጉዳዩ ገፍቶ በመሄድ የአንድን ሰው ሕይወት የሚቀይር እርምጃ መውሰዱ "ቀድሞውንም ይቅርታ መባሉ ከልብ አልነበረም ማለት ነው" ብለዋል፡፡ አያይዘውም እርምጃው የአገሪቱን የተረጋጋ ፖለቲካ ሁኔታ የሚበክል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
"መንግሥት እልህ ውስጥ መግባት የለበትም" ያሉት ፕሮፌሰር በየነ አገራዊ ኅላፊነት የሚሰማው ወገን ይህንን እርምጃ መውሰድ ለአገርም ሆነ ለሕዝቦቿ የሚጠቅም አለመሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የኦሮሞ ህዝቦች ኮንግረስ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና በበኩላቸው የቀድሞ የቅንጅት አመራሮች ከእስር የተፈቱት በድርድር ነው ብለው ያምኑ እንደነበርና በኢትዮጵያ ባህል መሰረት የድርድር ሚና ተጫውተዋል የተባሉ የአገር ሽማግሌዎች ለማደራደር ጥረት ሲያደርጉም ብዙ ሲነገር የሚሰማ መሆኑን ገልፀው አሁን በተፈጸመው እርምጃ ግን የኢትዮጵያ ባህል የተባለውን ሽምግልና በማይሆን መንገድ የተጣሰ ያስመስለዋል ብለዋል፡፡ አሁን የተፈጠረው ችግር የፖለቲካ ባህሉን የበለጠ እንዳያበላሽና እንዳያጨልም፣ የሽማግሌዎቹን ዋጋም እንዳያሳጣ ሽማግሌዎቹን በአደባባይ ወጥተው የቀድሞ ቅንጅት አመራሮች ከእስር የወጡበትን መንገድ ለሕዝብ ማሳወቅ እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡
"መንግሥት የድመትና የአይጥ ጨዋታ ውስጥ ገብቶ የትም የሚደርስ አይመስለኝም" ያሉት ዶ/ር መረራ የወ/ት ብርቱካን መታሰር የአገሪቱን ፖለቲካ ችግር ውስጥ የሚከት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አያይዘውም "በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ መጨመር አለበት እየተባለ በተደጋጋሚ በሚነገርበት በአሁኑ ሰዓት አንዲት ሴት ፈረንጅ አገር ሄዳ የሆነ ንግግር አድርጋለች በሚል መንግሥት የእድሜ ልክ እስራት እርምጃ መውሰዱ አኢሕአዴግን ምን ያህል እንደሚጠቅመው አላውቅም" ብለዋል፡፡
የኦፌዴን ሊቀመንበር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በበኩላቸው የወ/ት ብርቱካንን መታሰር "ማንም የኢትዮጵያ ዜጋ ሊያወግዘው የሚገባው ተግባር ነው" ሲሉ ተችተዋል፡፡ እንደ አቶ ቡልቻ ገለፃ በአንድ ቅጣት አንድ ሰው ሁለት ጊዜ ሊታሰር የማይችል በመሆኑ የወ/ት ብርቱካን ድጋሚ መታሰር አግባብ አይደለም፡፡ "ውሸት ተናገርሽ ብሎ ማሰር ሕጋዊም ሰብዓዊም እርምጃ አይመስለኝም" ብለዋል፡፡
የወ/ት ብርቱካን ይቅርታ መነሳት ከሕግ አንጻር
የአንድነት ለዴሞክሲና ለፍትሕ ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ሰኞ ታህሳስ 20 ነቀን 2001 በድንገት ከመንገድ ላይ በፖሊስ ከታሰሩ በኋላ ማምሻውን የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን የፍትሕ ሚኒስቴር ሰጠው የተባለው መግለጫ ወ/ት ብርቱካን የታሠሩትና የተሰጣቸው ይቅርታ የተሠረዘባቸው "ይቅርታ አልጠየቀኩም" በሚል በውጪ ሚዲያዎች መግለጫ በመስጠታቸው መሆኑን ይገልፃል፡፡ ይህን እንዲያስተባብሉ በተደጋጋሚ ተነግሯቸው ይቅርታ አልጠየኩም በሚለው አሉታዊ መግለጫቸው በመፅናታቸው የተደረገላቸው ይቅርታ በገዛ ፈቃዳቸው የማንሳት ድርጊት በመሆኑ የይቅርታውን ሁኔታ ጥሰዋል፡፡ በዚህም በይቅርታ ሥነ ሥርዓት አዋጅ አንቀፅ 16 ንዑስ አንቀፅ 4 መሰረት የሕግ ሒደቱን ተከትሎ የተደረገላቸው ይቅርታ በመነሳቱ ከይቅርታው በፊት በጥፋታቸው ፍ/ቤት የወሰነባቸው የዕድሜ ልክ ጽኑ እሥራት እንዲፈፅሙ ለማድረግ በቁጥጥር ስር ውለው ወደማረሚያ ቤት እንዲገቡ መደረጉን ዘግበዋል፡፡
አንድ ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ የሕግ ባለሙያ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደተናገሩት ፍትሕ ሚኒስቴር ስለወ/ት ብርቱካን የይቅርታ አነሳስ ሰጠው የተባለውና በመንግሥት መገናኛ ብዙሃን የተላለፈው መግለጫ ይቅርታው በማንና እንዴት እንደተነሳ አይገልጽም፡፡ በይቅርታ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 395/1996 መሰረት ፍትሕ ሚኒስቴር ስላለው ሥልጣንና ተግባር በግልፅ የተቀመጠና የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ምናልባት የይቅርታ ቦርዱ በፍትህ ሚኒስቴር ስር ስላለ፣ የቦርዱ ሰብሳቢም የፍትሕ ሚኒስትሩ ስለሆኑ ሁለቱ ተቋማት አንድ ናቸው በሚል አስተሳሰብ ተወስዶ ከሆነ ይህም ግልፅ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
በአዋጁ አንቀፅ 4 ንዑስ አንቀፅ 3 ላይ በግልጽ እንደተደነገገው ይቅርታ የተደረገላቸው ሰዎች ቅድመ ሁኔታ አላሟሉም ወይም ጥሰዋል የሚል ክስ ሲቀርብባቸው ጉዳዩን መርምሮ ለፕሬዚዳንቱ የውሳኔ ኃሳብ የሚያቀርበው የይቅርታ ቦርድ ነው፡፡ በአዋጅ አንቀጽ 10 ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት ከቦርዱ የቀረበውን የውሳኔ ኃሳብ መሰረት በማድረግ ይቅርታውን የመሰረዝ ሥልጣን ያላቸው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ፍትህ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ እነዚህን ሁኔታዎች ስለመሟላታቸው ምንም ያለው ነገር ባለመኖሩ ሕግ አስከባሪው ሕግ አከብራለሁ ሲል ራሱን ሕግ አለመጣሱን የማረጋገጥ ኃላፊነቱን አለመወጣቱን የሚያሳይ ይመስላል ብለዋል፡፡
የሕግ ባለሙያው አያይዘው በአዋጁ አንቀፅ 17 መሠረት ይቅርታ ሲሰረዝ ምክንያቱ ለባለ ጉዳዩ በግልጽ ቋንቋ በፅሁፍ ሊደርሰውና ባለጉዳዩም በ20 ቀናት ውስጥ ምላሽ የመስጠት መብት አለው፡፡ ይህ በይቅርታ ቦርዱ በኩል ተሟልቷል ወይ? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡
የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ወ/ት ብርቱካን ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ለመጀመሪያ ጊዜ ታህሳስ 1 ቀን 2001 ዓ.ም በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጥሪ እንደደረሳቸው፣ የአጠራሩ ሁኔታ ግን ሕግን ያልተከተለ ወይም የፖሊስ መጥሪያ ያልደረሳቸው መሆኑን በወቅቱ ባወጣው መግለጫ መግለፁ ይታወሳል፡፡
በቀጣይም ወ/ት ብርቱካን ታህሳስ 13 ቀን ቀን 2001 ዓ.ም ከቀኑ በ11፡30 ሰዓት እስከ 12፡00 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ሁለት የደንብ ልብስ የለበሱ ፖሊሶች ወ/ት ብርቱካን መኖሪያ ቤት ቢሄዱም ወ/ት ብርቱካን በሰዓቱ ባለመኖራቸው ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጽ/ቤት እንደሚፈለጉ የቃል መልዕክት ትተው መሄዳቸውን ያስታውሳል፡፡ በማግስቱ ታህሳስ 14 ቀን 2001 ከጠዋቱ በ12፡00 ሰዓት የደንብ ልብሰ የለበሱ ፖሊሶችና አንድ ሲቪል የለበሰ ግለሰብ ወደመኖሪያ ቤታቸው በመሄድና ከተኙበት በመቀስቀስ ከቀኑ በ5፡00 ሰዓት ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ፅ/ቤት እንዲቀርቡ በቃል መልዕክት ነገሩ፡፡ ለምን ጉዳይ ነው?" ተብለው ሲጠየቁ የተላኩት ሰዎች ስለጉዳዩ እንደማያውቁ ተናገሩ፡፡
ሆኖም ወ/ት ብርቱካን የደረሳቸው የቃል ጥሪ በመሆኑና የፍ/ቤት ወይም የፖሊስ መጥሪያ ያልደረሳቸው በመሆኑ በተጠሩበት ሰዓት አለመሄዳቸውን ገል"ል፡፡ በዚሁ እለት ከቀኑ 8፡30 ሰዓት ገደማ ሁለት የሲቪል ልብስ የለበሱ ሰዎች አንድነት ጽ/ቤት ድረስ መጥተው የመጥሪያ ወረቀት በማቅረብ ወ/ት ብርቱካንን ይዘዋቸው ሄደዋል፡፡ ፖሊስ ካነጋገራቸውም በኋላ የተሰጣቸውን መጥሪያ እንዲመልሱ ተጠይቀው ለመጠራታቸው ሕጋዊ ማስረጃ ስለሆነ አልመልስም ብለዋል፡፡ ሆኖም ወደቢሯቸው እንዲመልሷቸው የታዘዙት ፖሊሶች ወደታዘዙበት በመውሰድ ፈንታ ወደማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ አስገድዶ በመውሰድ የጥሪ ወረቀቱን እንዲመልሱ ቢያስገድዱም ወ/ሪት ብርቱካን በአቋማቸው በመፅናታቸው የጥሪ ወረቀቱን ይዘው መመለሳቸውን አንድነት ፓርቲ ታህሳስ 14 ቀን 2001 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ምርጫ 97ን ተከትሎ በተፈጠረው ሁከት እጃቸው አለበት በሚል በእነ አቶ ኃይሉ ሻውል መዝገብ ከቀረቡ 131 ተከሳሾች መካከል ወ/ት ብርቱካንን ጨምሮ ከ30 በላይ ተከሳሾች ሐምሌ 8 ቀን 1999 ዓ.ም በዕድሜ ልክ ጽኑ የመምረጥና መመረጥ ሰብዓዊ መብቶቻቸው እንዲሻር የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት መወሰኑ አይዘነጋም፡፡ በኋላም በአገር ሽማግሌዎች ጥረት በይቅርታ ሕጉ መሰረት ሐምሌ 13 ቀን በሙሉ ይቅርታ ከእስር ተለቀዋል፡፡
በወቅቱ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ለቅንጅት የቀድሞ የቅንጅት አመራሮች የተደረገውን ይቅርታ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ላይ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የሰጡት ይቅርታ በተሟላ መልኩ የተሰጠ ሆኖ በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ አያይዘውም የገቡትን ቃል ጠብቀው እስከተጓዙ ድረስ ይቅርታው ይቀጥላል፤ ቃላቸውን ጠብቀው ካልቀጠሉ ግን የይቅርታ ቦርዱ ጉዳዩን እንደገና የማየትና ቅጣቱ እንዲፈፀም የማድረግ መብት ይኖረዋል ማለታቸውንም አይዘነጋም፡፡