
በረከት ስምኦን የተናገረው አይረሳኝም፣
- “በዚህ ዘመን መሬት ይሸጥ ይለወጥ ብንል ያልተነካ ሰፊ ድንግል መሬት ያለው በደቡብና በኦሮሚያ ነው። የመሬት ሽያጭ ከፈቀድን መሬት ሊገዛ የሚችለው ገንዘብ ያለው ባለሃብት ነው። በዚህ ዘመን ገንዘብ ያለው ማን እንደሆነ ደግሞ ይታወቃል። በዚህ ወቅት መሬት እንዲሸጥ ከፈቀድን ቀደም ሲል ነፍጠኛው በጠመንጃ ይዞት የነበረውን መሬት አሁን ደግሞ መልሶ በገንዘቡ እንዲቆጣጠረው መፍቀድ ማለት ነው…”
ኢህአዴግ ስልጣኑን ከለቀቀ የመሬት ፖሊሲው እንደሚቀየር ያውቀዋል። ስለዚህ ዋጋ ያለውን መሬት ሁሉ ከወዲሁ ሸጦ መጨረስ ይፈልጋል። ዛሬ መሬቱ ለውጭ ዜጎች ተሸጦ ካለቀ ወደፊት መሬት የመግዛት አቅም ያለው ኢትዮጵያዊ ቁራሽ መሬት ሊያገኝ አይችልም። ቢያገኝ እንኳ ውድ ይሆንበታል። ለ50 አመት ውል የተፈረመለትን ህንዳዊ ማባረርም ቀላል አይሆንም። ምክንያቱም ብዙ ችግር ያስከትላል።
ሙሴቪኒ ስልጣን ይዞ ምእራባውያንን እርዳታ ሲጠይቅ፣ በቅድሚያ ኤዲአሚን ዳዳ ያባረራቸውን ህንዶች መሬትና ንብረት እንዲመልስ ነበር ያዘዙት። ሳይወድ አፍንጫውን ተይዞ መለሰ። የአማራ ባለሃብቶችን ማዳከም፣ የኦሮሞ ባለሃብት እንዳይፈጠር ማገድ የወያኔ ግንባር ቀደም መርህ መሆኑ ግልፅ ነው። መሬት በችኮላ እንዲህ የሚቸበችቡበት ምክንያት ከዚሁ ጋር የተያያዘ ይመስላል።
በርግጥ “ኢትዮጵያዊው ባለሃብት ቡና ቤት ከመገንባት አያልፍም” እያሉ የሚያላግጡ አሉ። መቼ ተሞከረና? እንኳን በዚህ ዘመን፣ በ60ዎቹ መጀመሪያ ላይ ወጣቶች ቦሎቄ እያመረቱ ወደ ውጭ መላክ ጀምረው ነበር። ወያኔ የሃገሪቱን መሬት ለውጭ ሰዎች ሸጦ የማጠናቀቅ ተልእኮ እንደያዘ ብዙ አስረጅ ማቅረብ ይቻላል።
ለአብነት ከአዲሳባ ናዝሬት በግማሽ ሰአት ውስጥ መግባት የሚያስችል ዘመናዊ መንገድ ተሰርቶ በመጠናቀቅ ላይ ነው። የዚህ መንገድ መገንባት አላማ፣ “ወደ ናዝሬት በፍጥነት ለመድረስ ነው” ብሎ የሚያስብ የዋህ የሚኖር አይመስለኝም። ወያኔ ከአዲሳባ ናዝሬት በፍጥነት ስለመግባት ሊያሳስበው አይችልም። የመንገዱ መገንባት ሁለተኛ አንጓ፣ ከአዲሳባ ናዝሬት በሚዘረጋው አዲስ መንገድ ግራና ቀኝ ያለውን መሬት ለቻይናና ለቱርክ ለመሸጥ ያለመ ነው። ምክንያቱም በደብረዘይት በኩል ያለውን መሬት ሸጠው ጨርሰውታል። ይህን ማድረግ ለሃገርና ለህዝብ እንደሚጠቅም የሚያሳምን ማብራሪያ እስካሁን አላነበብኩም። መለስ እራሱ ለውጭ ባለሃብቶች መሬት መሸጥ ጉዳት መሆኑን ሲናገር ተደምጦአል። ዚምቧቡዌ በተመሳሳይ መሬቷ እንዲህ ተበዝብዞ ነበር። ሙጋቤ መሬት ለማስመለስ በተነሳበት ወቅት ሃገሪቱ የገጠማት መከራ ግን መቼ እንደሚያቆም እንኳ አልታወቀም። ኢትዮጵያዊው ዜጋ የገዛ መሬቱን መጠቀም እንዳይችል በአዋጅና በፖሊሲ አግደህ፣ ለውጭ ባለሃብት በርካሽ ዋጋ መቸብቸብ ልማታዊ አላማ ይኖረዋል?






